Quantcast
Channel: Abugida Ethiopian American Amharic Web Page
Viewing all 1809 articles
Browse latest View live

ሚስ ዌንዲ ሸርማን በቅርቡ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሁኔታ ላይ የስጡት አስተያየት የተሳሳተና ጎጂ ነው ሸንጎ

$
0
0

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ ከብዙ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ሕዝብ፣እንዲሁም ነጻ ከሆኑት የሰብአዊ መብት ድርጅቶች፣ ከፍሪደም ሃውስ፣ከሂውማን ራይትስ ዋች፣ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ከኢንተርናሽናል ሪቨርስና ከሌሎቹ ጋር በማበር የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ የፖለቲካ ቢሮ ም/ሃላፊ የሆኑት ዊንዲ ሸርማን በቅርቡ ባደረጉት የአዲስ አበባ ኦፊሴላዊ ጉብኝት ወቅት በ16-04-2015 የሰጡት አስተያየት እውነትን የማያንቀባርቅ በመሆኑ ከማዘናችንም በላይ የአሜሪካንንም ሆነ የኢትዮጵያን መሰረታዊ ጥቅም ሊያሰከብር የሚችል እንዳልሆነ መግለጽ ይወዳል፡፡

ካሁን በፊት የአሜሪካ መንግስት በተደጋጋሚ ባወጣው መግለጫ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣እስራት፣ማሳደድ፣የሃይማኖትና የፖለቲካ አፈና፣በግዳጅ መሰወር፣የአካል ጉዳትና ስቃይ ማድረስና ሕዝቡን ለባርነት አሳልፎ መስጠት አሁን በስልጣን ላይ ባለው መንግስት የሚፈጸም እለታዊ ተግባር እንደሆነ አረጋግጧል።ይህንኑም ግፍና በደል ያሜሪካን ባለስልጣናት ራሳቸው በአካል በማየት መንግስት ከዚህ አይነቱ ተግባር እንዲታቀብና ጋዜጠኞችና ጦማርያንም እንዲፈቱ ጠይቀዋል ጨቋኝ ህግጋትም እንዲለወጡ አሳሰበው ነበር።

ይህ አይነቱ ግፍና ወንጀል የሚፈጽም መንግስት ባለበት አገር፣ሚስ ሸርማን “ኢትዮጵያ ውስጥ የሰፈነው ዲሞክራሲ በየቀኑም እየጎለበተ ነው፣የሚመጣውም አገር አቀፍ ምርጫ ሁሉን አቀፍ በሚያደርግ መንገድ እየተዘጋጀ ነው”ብለው ማለታቸው ከብዙሃኑ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ከአሜሪካ መንግስት በጽሁፍ ካሰፈራቸው መረጃወችና መግለጫወች ጋር የሚቃረን ነው ብለን እናምናለን።

የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በሕገወጥ መንገድ በገዥው ፓርቲ ቀጥተኛ ጥቃት እንዲፈራርሱ በሚደረግበትና የፖለቲካ ምህዳሩ በተዘጋበት ሁኔታ ፣በየጊዜው በሚደረገው የግብር ይውጣ ምርጫ እድገትና መሻሻል እየታዬ መጥቷል ብሎ መመስከር መሰረተቢስ ከመሆኑም በላይ የኢትዮጵያን ሕዝብ አመለካከት በመናቅና በማኳሰስ ብቻ ሳይገታ አሜሪካም በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ውስጥ የሚኖራትን ቋሚ የጥቅምና ጤነኛ ግንኙነት የሚበክል ነው።

የዛሬው የኢትዮጵያ ሁኔታ ከአምስት ዓመት በፊት ከነበረው ሁኔታ የሚብስ እንጂ የተሻለ አይደለም።እራሳቸው ሚስ ሸርማን የሚወክሉት ተቋም በ29-01-2015 ዓ.ም.እ.አ.አ.(ከሶስት ወር በፊት)”የኢትዮጵያ መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን በማጥበብ፣ተቃዋሚዎቹን እያሳደደና እያሸበረ፣የሲቪል ማህበረሰቡን በመቆጣጠር፣የነጻ ሚዲያ ዘርፎችን በማፈን ሁሉንም እንዳይንቀሳቀሱ አድርጓቸዋል”ሲል መግለጫ ማውጣቱ የሚታወስ ነው።ባለስልጣኗ ለኢትዮጵያ መንግስት በይፋ ድጋፋቸውን ሲሰጡ ያላገናዘቡት ነገር ቢኖር የከሰሱትና የሚያወግዙት የወንጀለኛውን መንግስት ተቃዋሚዎች ብቻ ሳይሆን የራሳቸውንም መንግስትና ተቋም ጭምር መሆኑን ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ሌላ ሆኖ ሳለ፣ሚስ ሸርማን የአንድ ነጠላ ፓርቲ የበላይነት በሰፈነበት ስርዓት፣ሃሳብ መግለጽን፣የመሰብሰብና ሰላማዊ ተቃውሞን ወንጀል አድርጎ የሚቀጣ ጨቋኝ መንግስት ለዴሞክራሲ የቆመ ነው ብሎ እውቅና መስጠታቸው እጅግ ጊጂ ሆኖ አግኝተነዋል።

ኢትዮጵያ ዛሬ ነጻ ጋዜጠኞችን በማሰር፣ በመላው አለም ቁንጮ ከሚባሉት ሀገሮች ውስጥ አንዷ ነች፡ከተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና ደጋፊዎች በእስር ቤት እንደሚሰቃዩ ፣ እንደሚሰደዱና ታፍነው የት እንደደረሱ የማይታወቅበት ሀገር እንደሆነች ብዙ ነጻ አለምአቀፍ ድርጅቶች የመዘገቡት እውነታ ነው። በሺወች የሚቆጠሩ ዜጎችም በፖለቲካ አመለካከታቸው የተነሳ በየእስር ቤቱ ይሰቃያሉ፡ሌሎችም ይሰደዳሉ፡፡

ላለፉት 23 ዓመታት በጉልበት በስልጣን ላይ የተቀመጠው ነጠላው የጎሳ ድርጅት የምርጫ ቡርዱን በመቆጣጠሩ ሕብረ ብሔርም ሆኑ የአካባቢ ፖለቲካ ድርጅቶች በነጻ እንዳይንቀሳቀሱ አግዷቸዋል ። አስመራጭ ተብየው የመንግስት አካል የሆነው የምርጫ ቦርድ፣ፖሊስና የፍትህ ተቋምም የተቃዋሚ ማፈኛ መሳሪያዎች ሆነዋል።ሆኖም ግን ተቃዋሚው ክፍል በሚችለው መንገድ እነዚህን ግንቦች በሰላማዊ ትግል ለማለፍ ጥረት ከማድረግ አልተቆጠበም።

እንደሚታወቀው “የትግራይ ነጻ አውጭ ግንባር”ኢሕአዴግ የተባለ የጎሳ ስብስብ በመፍጠርና በመቆጣጠር ብዙ መስሎ ቀርቦ በማምታታት ላይ ነው።ይህ በብዙ ስም የሚነግድ ነጠላ ፓርቲ ሌሎቹን የተቃዋሚ ፓርቲዎች ያላካተተ “ምርጫ” ቢያካሂድ የሚወዳደረው ከራሱ ጋር ስለሆነ አሸነፍኩ ብሎ የሚወጣውም እራሱን እንደሆነ መታወቅ አለበት።

እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ የባለስልጣኗ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ሰፍኗል ብሎ ተገቢ ያልሆነ ለአምባ ገነን ስርዓት እውቅና መስጠት የአሜሪካንን መንግስት ከትዝብት ውስጥ የሚከት ብቻ ሳይሆን 100 ሚሊዮን የሚሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚጎዳና በዝቅተኛ ደረጃ የሚያስቀምጥ ነው፡፤ይህን የተዛባ አቋም የአሁኑ ትውልድ ለሚመጣው ትውልድ በታሪክ መጽሃፉ አስፍሮ ያወርሰዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ የአሜሪካ መንግስት ለአጭርና ውስን ለሆነ “ለጸረ ሽብር አጋርነት”ሲል ከአሸባሪና የሕዝብ ድጋፍ ከሌለው አምባገነን ቡድን ጋር ያለውን ትስስርና የሚሰጠውን ድጋፍ እንዲመረምረውና እንዲያስተካክለው ይጠይቃል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ አሸባሪነትን አጥብቆ የሚያወግዝ እንደሆነ እየገለጸ በሀገራችን ውስጥ በየጊዜው ለሚታየው የፖለቲካ አክራሪነት በዋናነት አመች ሁኔታ የሚፈጥረው አግላይ እና ግፈኛ የሆነው የገዥው የህወሀት/ኢህአዴግ ፖሊሲና ተግባር እንደሆነ ሊያሰምርበት ይሻል።

በሀገራችን ውሰጥም ሆነ ባካባቢያችን የሚታየውን አደጋ ለማሰወገድ ሽንጎው በዋናነት ሁሉንም አሳታፊ የሆነ፣ የህዝብ መብትና የህግ የበላይነት የተረጋገጠበት ፖለቲካዊ ስርአትን እውን ማድረግ አስፈላጊ ነው ብሎ ያምናል። ይህንንም እውን ለማድረግ በተደጋጋሚ እንዳሳሰብነው ሁሉንም ባለድርሻወች ያሳተፈ ብሄራዊ መግባባትና እርቅ ሊተገበር ይገባል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ


እርም በላ ከንቱ ፍጡር ነኝ ከበላይነህ አባተ

ወያኔና ISIS ጽንፈኛና ፤ ዘረኛ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች!

የሃዘኑ ድባብ በዱላ ታጅቦ…ክንፉ አሰፋ

$
0
0

የሃዘኑ ድባብ ከመብራቱ መቆራረጥ ጋር ተዳምሮ ጨለማውን አብሶታል። የአሁኑ መብራት መቋረጥ ግን ከወትሮ ፈረቃ ለየት ያለ ነው። ሆን ተብሎ የተደረገ ይመስላል። ከጥቂት ስፍራ በስተቀር ሁሉም ቦታ በአንዴ እንዲጠፋ ነው የተደረገው። ከሬድዋን ሁሴን እና ከሃይለማርያም የቴሌቭሽን ዲስኩር በኋላ ሃገሩ ሁሉ ጨለማ እንዲሆን አደረጉ። ይህንን ለማድረግም በቂ ምክንያት ነበራቸው። ሃዘን ያልወጣለት ህዝብ አደባባይ ወጥቶ በአረመኔ ወታደሮች ሲቀጠቀት በማህበራዊ ድረ-ገጽ እንዲታይ አልተፈለገም። ህዝቡ እርስበርስ መረጃ እንዲለዋወጥ መፍቀዱም አደጋ አለው። ስልኩም ጠፋ!

ለጥቂት ጉልበተኞች ግን ይህ መብራት ከቶውንም አይጠፋም። ግዜው እስኪደርስ፣ የሚመኩበት ጉልበታቸው እስኪፈታ ድረስ ይበራል። እስከዚያው ብዙሃኑ በጨለማ ይኖራሉ።

የአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ንግግር ግን ከቴድሮስ አድሃኖም ጋር ትንሽ የሚጣረዝ ይመስላል። ድህነታችን ለስደት እንደዳረገን ነበር ሃይለማርያም በአደባባይ ይናገሩ የነበረው። ተሳስተው ነው? ወይንስ በጥድፍያው ምክንያት አልተናበቡ ይሆን? ልማታዊ መንግስት ድህነት የምትለዋን አይጠቀምም። ቴዎድሮስ አድሃኖም ግን በፌስ ቡክ ገጻቸው “ሁላችንም ወያኔ ነን” አዎ አሁንም ሁላችንም ወያኔን ነን። ወያኔነት ልማት፣ ኩራትና ዴሞክራሲ ነው።..ይህን ችግር የሚፈታውም ወያኔነት ነው!” ብለውናል። በመስቀል አደባባይ ወታደራቸውን አሰልፈው የሰላማዊውን ህዝብ ሃዘን በወያኔነት ሲመልሱትም አሳዩን። በሊቢያ፣ በየመን እና በደቡብ አፍሪካ በሰቆቃ ያሉ ወገኖች የሚሉትንም እየሰማን ነው። “የኛ የምንለው መንግስት የለንም! … ጨለማ ውስጥ ሆነን እየጸለይን ነው።” ይህ ነው የወያኔነት ወጤት።

አቶ ሃይለማርያም ተሳስተው አንድ እውነት ተናገሩ። አንድ ነገር ቢጨምሩበት ጥሩ ነበር። ለስደቱ መንስኤ የፍትሃዊ ስርዓት እና ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል መጥፋቱ መሆኑን። ለማንኘውም በውስጥ ግምገማ ላይ ይህችን ለምን እንደተናገሩ ያስረዱ ይሆናል።

ለሃዘን የወጣ ህዝብ በአረመኔ ወታደሮች ሲቀጠቀት ሮይተርስ ከአዲስ አበባ አሳይቶናል። ዜጎች ሲቀጠቀጡ የሚያሳዩ የቪድዮ ምስሎች በማህበራዊ ድረ-ገሶች በስፋት ተበትነዋልል። ሬድዋን ሁሴን ግን ወታደሮቹ አንድም ሰው እንዳልነኩ ነገሩን። ታድያ ዥጉርጉሩን የፌዴራል ልብስ ያጠለቀ አይሲስ ነበር እንዴ በመስቀል አደባባይ ህዝቡን ሲያሸብር የነበረው? ሃፍረት ያልፈጠረባቸው፤ የሰብአዊ ፍጡር ህሊና የሌላቸው ውሸታሞች ናቸውና ይህን ማለታቸው አይደንቅም። ኢውሮ ኒውስ ከአዲስ አበባ በቀጥታ ያሳይ የነበረው ትእይንት ዘግናኝ ነበር። አይሲስ በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸመውን የማይተናነስ ጭካኔ አሳዩን። ህጻን፤ ሴትና አዛውንት እንኳን ሳይለዩ ሁሉንም በጭካኔ ቀጠቀጡ። የህዝብ ወገን ቢሆኑ በወገን፤ ለዚያውም በሃዘን ላይ ያለ ህዝብ ላይ እንዲህ አይጨክኑም። በእውነቱ ባእዳንም እንዲህ ባዘነ ህዝብ ላይ አይጨክኑም። የ97ቱን ሰቆቃ አስታወሱን።

የታፈነው ህዝብ በአንድ ላይ ሆኖ ብሶቱን ሲገልጽ ሰማን። ሬድዋን ሁሴን እንደሚሉት ከዚህ ረብሽ ጀርባ ሰማያዊ ፓርቲ አለበት። ከጨርቆስ እስከ ፈረንሳይ ለጋሲዮን፣ ከቦሌ እስከ ኮልፌ፤ ከዘነበወርቅ እስከ ሽሮ ሜዳ … ያለ ህዝብ ሁሉ ሰማያዊ ፓርቲ ከሆነ ህዝብ ከናንተ ጋር አይደለምና ስልጣኑን ለሰማያዊ ፓርቲ ማስረከብ ነው ያለባቸው። አይገባቸው ይሆናል እንጂ በተዘዋዋሪ እየነገሩን ያሉት ህዝብ በሙሉ እንደጠላቸው ነው። ጥቂት ያሉትንም የህዝብ ቁጥር በምስል አየነው።

ይህ የህዝብ መልእክት ትምህርት ካልሆናቸው አምሯቸው የታወረ ነው። ክስተቱ እንደፈርዖን በባርነት የያዙት ህዝብ ምን ያህል እንደተከፋ ያሳየናል። 23 አመታት በጫንቃው ላይ የተቀመጠው ስርዓት ምን ያህል እንዳንገፈገፈው የሚያሳይ ባሮ ሜትር ነው።

ለመሆኑ እነዚያ ባለስልጣናት ሲሞት ደረት የሚመቱት ልማታዊ አርቲስቶች የት ጠፉ? “ታላቁ መሪ” ባረፉ ግዜ ማቅ ለብሰው እዩኝ-እዩኝ ይሉ የነበሩ አርቲስቶች ነብስ እየመረጡ ነው የሚያለቅሱት? በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ የተሰውት ወገኖች የሰብአዊ ፍጡራን አይደሉም እንዴ? ወይንስ ሃዘንም በትእዛዝ ሆነ? መቼም በዚህ ሰቆቃ ለማዘን የግድ ኢትዮጵያዊ መሆን አያስፈልግም። ለማዘን ሰው መሆን ብቻ ይበቃል። በዚህ የጨለማ ወቅት ከህዝብ ወገን ያልሆነ ሁሉ ለህሊናው ሳይሆን ለሆዱ የሚገዛ እንስሳ ብቻ ነው። መቼም የማያልፍ ነገር የለም ይህም ያልፍና ሁላችንንም ያስተዛዝበናል።

ባለቤት ያጣ ትውልድ እንደ በግ ሲታረድ የዓረና ትግራይ ድጋፍ ከሚቴ

በቦስተን እና አካባቢዋ ለምትኖሩ ኢትዮጵያውያኖች በሙሉ!! ታላቅ የወገን እና የእናት አገር ጥሪ!!

$
0
0

እማማ ኢትዮጵያ የሐዘን ማቅ ለብሳ በዋይታና በልቅሶ ተጨንቃ ልጆቿን የድረሱልኝ ጥሪ እያሰማች ትገኛለች!!

አንገታችንን የሚያስደፋና በሐፍረት የሚያሸማቅቅ፣ ጆሮን ጭው የሚደርግ፣ የወላድ እናቶችን አንጀት የሚያላውስና በእንባ ጎርፍ
እንዲታጠቡ የሚያደርግ ሌላ የሞት፣ ሌላ የውርደት፣ ማብቂያ የሌለው የሚመስል መሪር የሆነ የመርዶ፣ ሰቅጣጭና ክፉ ዜና ለእናት
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ምድር፣ ከሊቢያ፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከሀገረ የመን ተሰምቷል፡፡

ስለሆነም በቦስተን እና አካባቢዋ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ለወገን ደራሽ ወገን ነው፤ ሰለሆነም ይህንን የወገኖቻችንን እና
የእማማ ኢትዮጵያን የድረሱልኝን ጥሪ ምላሽ ለመስጠት፤ ቁጭታችንን ለመግለጽ እና የወገን አጋርነታችንን ለማሳየት በመጪው ቅዳሜ
ሁላችንንም ኢትዮጵያውያኖች በዘር፤ በሃይማኖት፤ በፖለቲካ ያለንን ልዩነት ወደጎን በመተው በጋራ የምንሰባሰብበት መድረክ
ተዘጋጅቷል።

ቀን፤……………………………… ቅዳሜ ኤፕሪል 25 2015
ሰዓት፤…………………………… ከቀኑ 2፡00 PM ሰአት ጀምሮ
የስብስባ አድራሻ፤ ………… 85 Bishop Allen Dr, Cambridge, MA 02139
Central square behined former Harvest supermarket.

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!
ለወገን ደራሽ ወገን ነው!!

ይህንን መልዕክት ለቤተስብዎ፤ ለጓደኝዎት በስልክ፤ በኢሜይል እንዲደርስ በማድረግ የድርሻዎን ይወጡ!!

በቦስተን ኢትዮጵያውያን የወገን ጥሪ ምላሽ አስተባባሪ ኮሚቴ- ቦስተን
ለበለጠ መረጃ 617 669 154215580_963560867011816_859833479060526288_n

ከጩኸት ወደ ተግባር የሚነገድበት የስደት ማእበል ትውልድ ከየት መጣ? ለማቆም እንረባረብ። አክሎግ ቢራራ (ዶር)

“ልጄ! እንካንተ እኔም ባልተወልድኩ”


ሰማያዊ ፓርቲን መወንጀል በዜጎች ደም እንደመቀለድ ይቆጠራል::ከፋፈልነው ያሉትን ሕዝብ አንድነት አዩት!! –ምንሊክ ሳልሳዊ

$
0
0

የ24 አመታት ሂደቶች .. ዜጎች በሃገራቸው ሰርተው እንዳይኖሩ የሆነበት…ለአንድ ወገን ያደላ እና በፓርቲ አባልነት ላይ የተመሰረተ አድልኦ የተንሰራፋበት … ጥቂት የፖለቲካ ቱጃሮች ብዙሃን ደሆች የፈሉባት … አምባገነንነት የነገሰባት ….ሃገራችን ኢትዮጵያ ልጆቿን አቅፋ እንዳታኖር የተደረገበት እና ወደ ስደት የተበተኑበት … ይህንን ሁሉ ተሸክመን ከትከሻችን ለማውረድ የምንታገልበት ወቅት … ከትግሉ ፍሬዎች አንዱ ሰማያዊ ፓርቲ ነው::ሰማያዊ ፓርቲ ሰላማዊነቱን ይዞ በሚቀሳቀስበት ቦታ ላይ እንደ አሸባሪ አድርጎ መፈረጅ የማያዛልቅ ጸሎት ለቅጽበት መሆኑን ማወቅ ግድ ይላል::ስርአቱ የገፋቸው በሃገራቸው ሰርተው እንዳይኖሩ ያደረጋቸው ወጣት ወገኖቻችን በስደት በረሃ መሰዋታቸው ለለውጥ የሚደረገው አብዮታዊ ትግል አንዱ አካል መሆኑን ይመሰክራል::

አለም እየመሰከረ ወያኔ በሊብያ የሟቾችን ዜግነት አጣራለሁ ማለቱ ሲገርምን ሳማያዊ ፓርቲ መወንጀል የፖለቲካ ኪሳራን በግልጽ ያሳያል::በሊቢያ የታረዱትን ወገኖቻችንን ሃዘን ተከትሎ የወያኔው ስርአት መወንጀል የሚገባውን አሸባሪው አይሲስ እያለ ሰማያዊ ፓርቲን መወንጀል እና ሃዘኑን ለመግለጽ የወጣውን ሕዝብ ደም ያፋሰሰው ሰማያዊ ፓርቲ ነው በማለት መፈክር አሲይዞ አደባባይ ላይ ማሰማራት የስርአቱን ዋልጌነት እና በዜጎች ደም መቀለድ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል::ከዜጎች መታረድ ጀርባም ሌላ ምስጢር ያዘለ ነገር እንዳለ ጠቋሚ ነገሮች እንዲታሰቡ እድሉን አስፍቷል::ሰማያዊ ፓርቲን እንደ ደም አፋአሳሽ እና አፍሳሽ አድርጎ ፕሮፓጋንዳ ማቀነባበር በአሸባሪው አይሲስ የታረዱ ዜጎችን ሃዘን የሚገልጸው ሕዝብ ላይ እንደማሾፍ ይቆጠራል::ያለው ስርአት ምን ያህል እንደወረደ በተደጋጋሚ ከማመልከቱም ባላይ ያሁኑ ግን ብሶ እና አግጥጦ መውጣቱ ለሕዝብ ያለውን ንቀት በተግባር እያሳየ ነው::

የህዝቡ አንድነት ያስደነገጠው ወያኔ ከፋፈለነዋል ብለው እፎይ ብለው ፕሮፓጋንዳ ሲረጩ ድንገት ተቆጥቶ የተመመው ህዝብ አንድነቱን ከማሳየቱም በላይ ኢትዮጵያዊነት የማይበረዝ የማይከለስ መሆኑን ሲያሳይ የቀድሞው ወታደራዊ መሪን ማረን እስከማለት መድረሱ ሕዝቡ ለአንድነቱ እና ለኢትዮጵያዊነቱ ምን ያህል ቀናኢ እንደሆነ አሳይቷል:: የወያኔ የጎሳ ፖለቲካ እንዳልሰመረ በተግባር የታየበት የህዝብ ድምጽ የተሰማበት ሕዝብ ብሶቱን የተነፈሰበት ትእይንት ግርምትን ከመፍጠሩም በላይ የወያኔ ሴራዎች ምንም እንዳልሰሩ እና የ24 አመታት የስርአቱን ክሽፈት በተግባር አሳይተዋል::ከሕዝብ ያልወጣ አስተዳደር እና መንግስት ለዜጎቹ እንደማይበጅ መንግስት የለም የሚል ድምጽ በማሰማት አሳይቷል::ከፋፈልነው ያሉትን ሕዝብ አንድነቱን አዩት::ይህንን እኩይ ስርአት ለማስወገድ በጋራ ልንቀሳቀስ ይገባል::

መሰረዝ ያለበት አስደንጋጭ እቅድ –ግርማ ካሳ

$
0
0

“መንግስት በሊቢያ በዜጎቻችን ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ድርጊት ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ ሰፋፊ ሰራዎችን ለመስራት በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ቴድሮስ በቤንጋዚ ያሉ ኢትዮጵያውያን በግብጽ መንግሰት በኩል፣ ትሪፖሊ ያሉትን ደግሞ ከሱዳን መንግሰት ጋር በመተባበር ከሊቢያ ለማውጣት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።” የሚል በዶር ቴድሮስ አዳኖም ፌስ ቡክ ገጽ ላይ አነበብኩ። የዝግጅቱን ዝርዝር ባላውቅም ዝግጅቶች እየተደረጉ ሊሆኑ እንደሚሉ ማንበቤ ትንሽም ቢሆን ደስታ ሰጥቶኛል።

በሊቢያ ከአሥራ አምስት በላይ የሚሆኑ ኃይላት አሉ። እነዚህ ኃይላት እርስ በርስ እየተቀናጁ በዋናነት ሦስት ቡድኖች ተፈጥረዋል። እነርሱም፡
መቀመጫዉን ቱብሩክ (ወደ ግብጽ ድንብር የተጠጋች ከተማ) ያደረገው በጀነራል ካሊፋ ሃፍተር የሚመራው ስብስብ ነው። ይህ ስብስብ ደርና ከምትባለዋና አይሰስ ከሚቆጣጠራት ከተማ በስተቀር፣ አብዛኛዉ ቤንጋዚ ጨምሮ፣ እስከ ግብጽ ድንበር ድረስ ያሉትን ግዛቶች ይቆጣጠራል። ይህ ስብስብ በአለም አቀፍ ማህበረሰብ እንደ ሕጋዊ የሊቢያ መንግስት የሚቆጠር ሲሆን ከግብጽ መንግስት ጋር የቀረበ ግንኙነት አለው።

መቀመጫው ሚስራታ የሆነውና ትሪፖሊን የሚቆጣጠረው፣ Libyan Dawn (የሊቢያ ጎህ) የሚባለው ስብስብ ነው። ይህ ስብስብ በዋናነት አይሰስን ሳይጨመር፣ ከሙስሊም ብራዘር ሁድ ጋር ግንኙነት ያላቸውን በርካታ እስላማዊ የሆኑ ድርጅቶችን ያሰባሰበ ነው። እንድ ቱርክ፣ ካታር ያሉ አገሮች በዚህ ስብስብ ላይ ተጽእኖ ማሳደር እንደሚችሉ ይነገራል:
ሶስተኛው አሸባሪው የአይሰስ ቡድን ነው። በሚስራታና በቤንጋዚ መካከል የምትገኘው የሲርት ከተማን እና አካባቢዉ ይቆጣጠራል። በቤንጋዚ እና በቱብሩክ መካከልም ያለቿን የደርና ከተማ ዉስጥም አለ። በዚሁ በደርና ከተማም ነው የግብጽ ክርስቲያኖችችን አይሰስ አንገታቸውን ያቀላው። በተጨማሪ በደቡብ ሊቢያም በቻድና በኒጄር ድንበር አካባቢም እንደሚንቀሳቀስ ይነገራል።
በሊቢያ ያለው የኃይል አሰላለፍ ይህ ሆን እንዳለ፣ ኢትዮጵያዉያንን ለማስወጣት የግደታ ከጀነራል ካሊፋ ሃፍተር ቡድን እንዲሁም ከሊቢያ ዶዉን ባለስልጣናት ጋር መነጋገር ያስፈልጋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ዝግጅት፣ ትሪፖሊ ያሉትንን በሱዳን በኩል፣ ቤንጋዝዚ ያሉትን ደግሞ በግብጽ በኩል በማስወጣት ላይ ያጠነጠነ ሳይሆን እንዳልቀረ አስባለሁ። በዚህ ጉዳይ ላይ ትልቅ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባ በጣም አንገብጋቢ ጉዳዮችን እንዳነሣ ይፈቀድልኝ።

ኢትዮጵያዉያን በቤንጋዚ፣ በሚስራታና በትሪፖሊ በብዛት አሉ። በመሆኑምም ከጀነራል ካሊፋ ሃፍተር እንዲሁም ከሊቢያ ዶውን ባለስልጣናት ጋር በተናጥል በመነጋገር፣ ከቻያና፣ ወይም ግርሪክ፣ አሊያም ጣሊያን ትላልቅ ቻርተር መርከቦችን በመከራየት ከሶስቱ ወደቦች በመሰብሰብ ወደ ግብጽ እንዲገቡ ማድረጉ በጣም የተሻለ አማራጭ ነው።

በባስ ጭኖ ለማስወጣት ከታሰበ ደግሞ፣ ቤንጋዚ ያሉትን ወደ ግብጽ ለማምጣት የታሰበው መልካም ሐሳብ ነው። ሆኖም መጠነኛም ቢሆን፣ ደርና አካባቢ አይሰሶች ሊኖሩ ስለሚችሉ፣ በደርና በኩል ሳይሆን በአጅዳቢያ በኩል መሆን ይኖርበታል።

ከትሪፖሊ ወደ ሱዳን ወገኖቻችንን ለማስወጣት የታስበው ፈጽሞ ሊሆን የሚገባው አይደለም። ይህ ከግምት ዉስጥ መግባቱ ራሱ አስደንጋጭ ነው። አንደኛ ከትሪፖሊ ሱዳን ድንበር ቢያንስ 1920 ኪሎሜትር ረቅት ነው ያለው። ሁለተኛ እልም ያለ በረሃ ነው። ሶስተኛ ቢያንስ 4 እስከ 5 ቀን ይፈጃል። ሕጻናትት አሉ። ሴቶችን፣ ነፍሰ ጡሮች አሉ። አራተኛና ትልቁ ነጥብ ደግሞ አይሰስ በዚያ መንገድ ላይ የመንቀሳቀሱ እድል በጣም ከፍ ያለ መሆኑ ነው። በቅርቡ የተገደሉት ወገኖቻችን ከሱዳን ወደ ትሪፖሊ ሲሄዱ አይሰስ ይዟቸው ነው።

በሱዳን በኩል ወገኖቻችችንን ለማስወጣት ማቀድ፣ እንደገና ወገኖቻችን ለአደጋ ማጋለጥ ነው። ይሄንን እቅድ የኢትዮጵያ መንግስትት መሠረዝ አለበት የሚል አቋም ነው ያለኝ። የመሠረዝ ፍላጎት ከሌለው፣ ኢትዮጵያዉን በአገር ዉስጥና ከአለም ዙሪያ ሁሉ ጠንካራ ተቃዋሞ ማሰማት ይኖርብናል። እንደገና ወገኖቻችን አይሰስ ሊንቀሳቀስባቸው ወደ ሚችልባቸው ቦታዎች መወሰድ የለባቸውም።
የሚሻለው፣ የኢትዮጵያ መንግስት ከሱዳን ጋር ሳይሆን ከቱኒዚያ መንግስት ጋር በመነጋገር፣ ከሚስራታና ትሪፖሊ ያሉ ወገኖቻችን በቀጥታ ሳብራታና ዙዋራ በሚባሉ ከተሞች አልፎ፣ መዲኒን ወደ ተባለችዋ የቱኒዚያ ከተማ እንዲሄዱ ማድረግ ነው። ርቀቱ 800 ኪሎሜተር ብቻ ሲሆን በ3 ሰዓት ዉስጥ ይገባል፡11156316_10206341228440328_1740631521258789980_n

መንግስት በሰማያዊ ፖርቲ ላይ የከፈተውን የስም ማጥፋት ዘመቻ በአስቸኳይ ያቁም!!! –ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

$
0
0

ሰማያዊ ፓርቲ በየመን፣ ደቡብ አፍሪካና በሊቢያ ውስጥ በኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ያለውን በደል እየተከታተለ መንግስት ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ ሲያሳስብ ቆይቷል፡፡ በእነዚህ ሀገራት ችግር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰውን በደል በማውገዝና መንግስትም መፍትሄ እንዲሰጥ መግለጫ ከማውጣት ባለፈ የደቡብ አፍሪካ መንግስት በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰውን በደል እንዲያስቆም አዲስ አበባ ለሚገኘው የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ደብዳቤ በመጻፍ ፓርቲያችን የቻለውን ሁሉ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በተመሳሳይ መንግስት አይ ኤስ አይ ኤስ በኢትዮጵያውያን ላይ የፈፀመውን ዘግናኝ እርምጃ ለመቃወም የጠራውን ሰልፍም በመደገፍ ሰማያዊ ፓርቲ የመጀመሪያው ተቃዋሚ ፓርቲ ነው፡፡

ይሁንና የዜጎችን ስቃይ ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል የፈለገው ሕወሀት ኢህአዴግ ሰማያዊ ፓርቲ በወገኖቻችን ላይ ለሚደርሰው በደል መፍትሄ እንዲሰጥ መወትወቱ፣ የፖለቲካ ልዩነታችን ወደ ጎን አድርገን በሰልፉ ላይ መገኘታችን እንዳላስደሰተው ከሰልፉ ቀን ጀምሮ በፓርቲያችን ላይ የተከፈተው ዘመቻ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡ መንግስት ሊቢያ ውስጥ በወገኖቻችን ላይ ለተፈፀመው ጭካኔ ምንም አይነት ትኩረት ባለመስጠቱ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ተቃውሞ በማሰማታቸው ያላሰበውን ሰልፍ ጠርቷል፡፡ በጠራው ሰልፍ ላይም መንግስት ለወገኖቻችን ያሳየው ንቀት ያበሳጫቸው ኢትዮጵያውያን ተቃውሟቸውን ገልጸዋል፡፡ በተቃውሞው ወቅት ከፍተኛ ድብደባ የፈፀመው ፖሊስ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኢህአዴግ አባላትን ጭምር ማሰሩ ይታወቃል፡፡ ይህ በሆነበት ወቅት ኢህአዴግ ለተነሳበት ቅሬታና ተቃውሞ ጣቱን ሰማያዊ ፓርቲ ላይ በመቀሰር ከፍተኛ ውንጀላና ዛቻ እያደረገ ይገኛል፡፡

ከሰልፉ ማብቃት ጀምሮም ጉዳዩን ገና ፖሊስ ሳይመረምረው የመንግስት ኮሚኒኬሽን ፅ/ቤት ሚኒስትር ሬድዋን ሁሴን ሰማያዊ ፓርቲ ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት እየጣረ ነው የሚል ውንጀላ አሰምቷል፡፡ ከዚህ ዕለት ጀምሮ የስርዓቱ አፍ በሆኑት ሚዲያዎች ሁሉ ቀን ከሌሊት ሰማያዊ ፓርቲ ሁከትና ብጥብጥ ሊያስነሳ ነው እያለ እያላዘነ ይገኛል፡፡ አይ ኤስ አይ ኤስን ለመቃወም ተብለው በተጠሩ ሰልፎችም ሁሉ ከአራጁ ቡድን ይልቅ ሰማያዊ ፓርቲ ለመቃወም እየተጠቀመባቸው ይገኛል፡፡

በሰልፉ ዕለት አባላቶቻችን ገና ሰልፉ ሳይጀመርና መስቀል አደባባይ ሳይደርሱ፣ ሁከትና ብጥብጥ ልታስነሱ ነው ተብለው የታሰሩ ሲሆን ሕወሀት ኢህአዲግ እንደሚለው በሰልፉ ላይ ያልነበሩት አባላቶቻችንም እንዲሁም ሰልፉ ካበቃ በኋላ እየታደኑ ተይዘው ታስረዋል፡፡ ይህን ያደረገው የራሱን አባላት ከቀበሌ ደብዳቤ እያስመጣ በፈታበት ወቅት ሲሆን በቦታው ያልነበሩትን አባላቶቻችንን በማሰር የፈጠራ ክስ በመክሰስ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም በፌደራል ፖሊስ አማካኝነት ተደጋጋሚ የስም ማጥፋት ዘመቻ በፓርቲያችን ላይ እያደረሰ ይገኛል፡፡

ትናንት ሚያዝያ 18/ 2007 ዓም ምሽት 2 ሰዓት ዜና ላይ የፌደራል ፖሊስ 7 የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችን እና ከ20 በላይ አባላትን ማሰሩን በማስመልከት ፈፅሞ ከእውነት የራቀ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በእስር ላይ የሚገኙ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ቁጥር 6 ብቻ ሲሆን እነዚህ በእስር ላይ የሚገኙ የፓርቲው አባላት እንደማንኛውም ዜጋ ሀዘናቸውን ለመግለፅ ወደ መስቀል አደባባይ በማቅናት በነበሩበት ወቅት ሰልፉ የሚካሄድበት ቦታ እንኳን ሳይደርሱ በደህንነቶች አባላት ታፍነው የታሰሩ ናቸው፡፡ ሰልፉ ከመጀመሩ ከሰዓታት በፊት የታሰሩ የሰማያዊ አባላትን በሰልፉ ላይ ለተፈጠሩት ማንኛውም ድርጊቶች ተጠያቂ ማድረግም በእጅጉ መሰረተቢስ ነው፡፡

ይህ በህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት አማካኝነት እየቀረበ ያለው ክስ እና የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ህወሓት/ኢህአዴግ ለዜጎች ህይወት የማይጨነቅ እና በዜጎች ሞት የራሱን የፖለቲካ ትርፍ ለማጋበስ እና ጠንካራ ተቃዋሚ የሆነውን ሰማያዊ ፓርቲን ለማጥቃት እየተጠቀመበት መሆኑን በተጨባጭ የሚያሳይ ነው፡፡ በፍርድ ቤት ውሳኔ ያልተሰጠበትን ጉዳይ ተጠርጣሪ ከማለት ይልቅ ወንጀለኞች ናቸው በማለት በህገወጥ ስራ ላይ ተሰማርቶም ይገኛል፡፡
ይህ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ በዋነኝነት ያነጣጠረው
1- ሰማያዊ ፓርቲን ከምርጫ ለማስወጣት እና ምርጫ 2007ን ያለምንም ተቀናቃኝ እና ስጋት ለማለፍ
2- ያለይሉኝታ እና ያለ ሀፍረት የፓርቲ እና የመንግስት ስልጣንን አቀላቅሎ የያዘው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ የምርጫ ስነ-ምግባር አዋጁ 662/2002ን በሚቃረን መልኩ ያሉትን የመገናኛ ብዙሀንን በሙሉ ተቀናቃኞቹን እና ተፎካካሪዎቹን ለማጥቂያነት እየተጠቀመባቸው መሆኑን ለማድበስበስ
3- ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት ህወሓት/ኢህአዴግ እንዳደረገው ሁሉ አሁንም የሰማያዊ አመራሮችን እና አባላትን በማሰር ትግሉን ለማዳከም የተወጠነ ሴራ መሆኑን፡፡
4- በተለይም በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ ሚዲያዎች በሊቢያ እና በየመን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ህይወት አደጋ ውስጥ እንዳለ እየተገለፀ በሚገኝበት ወቅት እና የኢትዮጵያ ህዝብም በአንድ ድምፅ መንግስት የዜጎችን ደህንነት እንዲያስጠብቅ እና በአይ ኤስ አይ ኤስ ላይ የአፀፋ እርምጃ እንዲወስድ እየወተወተ ባለበት ወቅት የህዝብን መሰረታዊ ጥያቄ ለማስረሳት እና ለማዘናጋት የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት በኢትዮጵያውን ላይ የጭካኔ ድርጊት የፈፀመውን አይ ኤስ አይ ኤስን ወደጎን በመተው ሰማያዊ ፓርቲን የጥቃቱ ዋና አላማ አድርጎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡
ስለዚህ ሰማያዊ ፓርቲ መንግስት እና የመንግስት መገናኛ ብዙሀን ከዚህ አኩይ ተግባራቸው የማይታቀቡ ከሆነ ፣የሰማያዊን ስም በሀሰት በማጠልሸት ስራ ላይ የተሰማሩ የመንግስት ተቋማትን እና ግለሰቦችን በህግ ፊት ለማቆም ዝግጅቱን ያጠናቀቀ መሆኑን እየገለፀ ሌሎች ተከታታይነት ያላቸውን እርምጃዎችም ለመውሰድ የሚገደድ መሆኑን እያስታወቀ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሰማያዊ ፓርቲ ለሚያደርጋቸው ህዝባዊ ጥሪዎች በንቃት ተዘጋጅቶ እንዲጠብቅ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ሚያዝያ 19/2007 ዓም
አዲስ አበባ988529_1584502611820936_8721941900200532873_n

11169883_1584502648487599_4615036497156649806_n

ክርክር 6፡ ኢህአዴግ እና 1997 ስብርባሪዎች!!!! ግርማ ሠይፉ ማሩ

$
0
0

በዛሬው ሰድስተኛ ዙር የምርጫ ተብዬ ክርክር ጉዳዩ በመሰረተ ልማት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ኢህአዴግ ጎምቱ ያላቸውን ሹሞቹን ለክርክር ይዞ የቀረበበት ቢሆንም ለእኔ ግን ትኩረቴን የሳበው የተከራከሩበት ርዕስ ሳይሆን ተከራካሪዎቹ ሰዎች እና ፓርቲዎች ናቸው፡፡ ማለት የፈለኩት የመሰረተ ልማት በሚል ርዕስ ክርክር ስመለከት የተገነዘብኩት ጉዳይ ቢኖር ኢህአዴግ ክርክር እያደረገ ያለው የዛሬ አስር ዓመት ለሚዲያ ክርክር ድመቅት ይሰጥ ከነበረው ከቅንጅት ስብርባሪ ጋር አንደሆነ ተረዳሁኝ፡፡ ህብረትም ቢሆን አሁን በመድረክ በኩል በድሮ ግርማ ሞገሱ አይታይም፡፡ እውነቱን ለመናገር አሁን በክርክሩ ላይ የሚገኙት ሰዎች ኢህአዴግ በልኩ የሰራቸው፤ በእግራቸው ገመድ የተበጀላቸው ጭምር ናቸው፡፡ ምንም ቢሉ ማንም ምንም የማይሰማቸው፡፡

ኢዴፓ በ1997 ከተቀናቃኙ መኢህአድ ጋር ያለውን የውስጥ ግብ ግብ ቅንጅት የሚባል ፓርቲ እውን እንዳይሆን በማድረግ፣ አንድ አንዶቹን በግል ታሪካዊ የፖለቲካ ዋጋ አስከፍሎ አሁን ባለበት ደረጃ ይገኛል፡፡ ይህ የኢዴፓ አመራር ውሳኔ ኢትዮጵያ ሀገራችንም በመድበለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ዋጋ እየከፈለች እንድትገኝ አድርጓል፡፡ በሁለት ሺ ሰባት ምርጫ ኢዴፓ እንደ ፓርቲ መንግሰት እንደማይሆን ቢታወቅም ወደፊት ፓርቲስ ይሆናል ወይ? የሚል ጥያቄ ሁሉ ማንሳት የግድ የሚል ነው፡፡ ይህ በፍፁም ሟርት አይያደለም በምድር የሚታይ ሀቅ ነው፡፡ ለማነኛውም ኢዴፓ የዛሬ አሰር ዓመት በ1997 ክርክር የቅንጅት ፈርጥ ሆኖ ክርክሩን ያደመቀ ቢሆንም ዛሬ ይህን ሊያደርግ አልተቻለውም፡፡ ኢህአዴጎች በጥርስና ጥፍራቸው ቅንጅትን ሲያፈርሱ ያተረፉት ሽራፊ ኢዴፓ አሰር ዓመት አፈር ልሶ መነሳት ሳይችል ቀርቷል፡፡ አሁንም በምድር ላይ እየዳከረ ይገኛል፡፡

ኢዴፓ ማህተም አላደርግም በማለት ያፈረሰውን ቅንጅት ቢያንስ በፍረስራሽ በቅጡ እንዳይሰራ ያደረገው ደግሞ አቶ አየለ ጫሚሶ ነው፡፡ መቼም ይህን ሰም የማያውቅ ያለ አይመስለኝም፡፡ “ቅንጅት” በአቶ አየለ ጫሚሶ ተወክሎ ቅንጅት ቢመረጥ እንዲህ ያደርጋል ይህን ይፈጥራል ሲሉን እኛ የምናወቀው የ1997 ቅንጅት የሌለ መሆኑን፤ የፈለግነው ቅንጅት እንዳይኖር የተሰራው “ቅንጅት” እንኳን ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠቅም አጀንዳ አይደለም እንደ ድርጅትም ቁመናውን አስተካክሎ የሚሄድ እነዳልሆን እናውቃለን፡፡ እውነቱን ለመናገር እነርሱም በሚዲያ ቀርበው አይተናቸዋል፡፡ ለማነኛውም ይሉሹን በሰማሽ ገበያ ባልወጣሽ የሚባለው የዚህ ዓይነቱ ድርጊት ነው፡፡ የቅንጅት ምልክት የነበረው ሁለት ጣት አሁንም “ቅንጅት” ለሚባው ድርጅት ቢሰጥም በተግባር ግን በስራ ላይ እንደሌለ ይታወቃል፡፡ ትዝ ይላችሁ እንደሆን “ጣት እንቆርጣለን” እስክንባል ድርስ ይህች አስማተኛ ምልክት የዛሬ አስር ዓመት የሰራቸው ስራ በእውነት ግሩም ድንቅ ነበር፡፡ የእኛን ቅንጅት ነብስ ይማር ብለናል፡፡

መድረክ አሁን ባለው ቁመና የ1997 ህብረት ሰዎች በተወሰነ ደረጃ ቢይዝም ህብረትን የሚያክል አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ ከምርጫ በኋላ ቅንጅት የሚባል እንዳይኖር የአሁኖቹ መድረኮች ያላቸው ጥላቻ ቀላል አይደለም፡፡ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ አሁንም ቢሆን ከቅንጅት መንፈስ ጋር ግብ ግብ ላይ እንዳለ ማወቅ የፈለገ የ1997 ጫወታ አንስቶ መሞከር ነው፡፡ በሌሎቹም የህብረት አባል ድርጅቶች እሰከ ፓርላማ የደረሰ ደባ በቅንጅት ላይ እንደሚሰራበት የሚታወቅ ነው፡፡ የዚህ ደባ ባለቤቶች አሁንም የመድረክ አባሎችና አመራሮች ናቸው፡፡ መድረክ አንድነትን ከሚጠላበት አንዱ ምክንያት በአንድነት ውስጥ የሚታየው የቅንጅት መንፈስ ጭምር ነው፡፡ የአሁኖቹ አመራሮች ከአንድነት ጋር ሲነነጋገሩ የሚሰማቸው ሰሜት በ1997 ህብረት ሆነው ከቅንጅት ጋር የሚያደርጉት ውይይት/ክርክር ነው፡፡ በክርክሩ ውስጥ ሁሌም ጠልፉ መጣል አለ!! የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ልዬ ችሎታ፡፡
አሁን ደግሞብ በብረት ሰንሰለት ተይዞ የሚገኘው ሰማያዊ ፓርቲ ነው፡፡ ሰማያዊ የት ድረስ ይጓዛል? አላውቅም፡፡ ሰማያዊ ፓርቲም ቢሆን የቅንጅት አብዛኛውን አመራርና አባል ይዞ የተመሰረተው አንድነት ፓርቲ ስባሪ ነው፡፡ ስለዚህ የቅንጅት አካል እንደነበር ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ በሁለት ሺ ሁለት ምርጫ አንድነትን ምርጫው ላይ ውጤታማ እንዳይሆን ከኢህአዴግ ባልተናነሰ ገትረው የያዙት ልጆች ሳይዘገዩ በአምስተኛ ዓመቱ የምርጫ ፈተና ከኢህአዴግ ጋር እንዴት እንደሆነ እየቀመሱት ነው፡፡ በሆነ ባልሆነው ሰማያዊ የሚለው መንግሰትም ከሰማያዊ አልላቀቅ ብሎ ምን ሊያደርግ እንደሚችል እየተጠበቀ ነው፡፡ የኢህአዴግ ትልቅ ግብ በዚህ ምርጫ መንግሰት መመስረት የሚመስለው ካለ ተሳስቷል፡፡ ሰማያዊን ለማዋረድ ነው የሚሰራው፡፡ በኢቲቪ በሰማያዊ ላይ የተያዘው ዘመቻ የአንድ አንድ የህግ ባለሞያዎች ተብዬ አስተያየት ጥፍራችን ውስጥ እንድንደበቅ የሚያደርግ ነው፡፡ እረ በህግ መባል ያለባቸው ናቸው፡፡

ሌሎች ተሳታፊ ፓርቲዎችን ትተን ከላይ የዘረዘርናቸው ፓርቲዎችን ስንመለከት ኢህአዴግ የዛሬ አስር ዓመት ሰንገው ይዘውት ከነበሩ አሁን ግን ምንም ማድረግ ከማይችሉ ደካማ ስብርባሪ ፓርቲዎች ጋር ተራ ገብቶ እየተጫወተ ነው፡፡ ሁሌም እንደምለው ኢህአዴግ ብጤዎቹን በትክክል መርጦዋል፡፡ ከዚህ ከፍ ያለ ጫወታ አይችልም፡፡ ከዚህ ከፍ ካለ ኢህአዴግ ቀልድ አያውቅም ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ሲል ታንክም ባንክም ለመጠቀም ወደኋላ የሚል አይደለም፡፡ አሁን ለጊዜው በቁጥጥር ስር ያሉ ሚዲያዎች እና ሆዳሞች ይበቁታል፡፡ ታንክ አያስፈልግም ማለቴ ነው፡፡ ሚዲያና ሆዳሙን ለመጥቀም ያህል ባንክ ይጠቀም ይሆናል፡፡
ቸር ይግጠመን!!!!!

Article 0

“ሞት የዘመኑ ዕለት እንጅ የመነኑ ዕለት አይደለም”በበልጂግ አሊ

$
0
0

“ከመሸ ተነሳሁ ከተፈታ በሬ፣
እደርስ አይመስለኝም ከእንግዲህ ሃገሬ።“

አገኘሁ እንግዳ

ጀርመን ፍራንክፈርት በሚገኘው የመድኃኒዓለም ቤተክርስትያን ውስጥ በሊቢያ ለተሰው ዜጎቻችን ጸሎተ-ፍትሃትና ከዛም ሰላማዊ ሰልፍ ሲደረግ ተገኝቼ ነበር። በደቡብ አፍሪካም ይሁን በሊቢያ በደረሰው ችግር ሁላችንም ሃዘን ገብቶናል። በዚህ ግፍ እንባ ያነባንም አለን። ከልባችንም ያዘንን ብዙ ነን። ቄሱ ትምህርት ሲሰጡ እነዚህ ለሃይማኖታቸው ሲሉ በወጣትነት የሞትን ጽዋ የተቀበሉ ሰማዕታት ትልቅ በረከት አግኝተውበታል ነው ያሉት። አዎ ለእምነት መሞት ትልቅ በረከት ነው። ጥንትም ለአመኑበት መሞት ታሪክ መስራት ነው፤ ሕይወትን በሌላ ፈርጅ መቀጠል ነው፤ ዳግም ትንሳዔ፣ ዳግም ልደት ነው። አሁንም ቢሆን የተቀየረ ነገር የለም።

ቤተክርስትያን ውስጥ ሆኜ ጸሎተ-ፍትሃቱን በመከታተል ላይ እያለሁ ለማነው የምናለቀሰው? ለምንስ ነው የምንላቀሰው? የሚለው ጥያቄ አዕምሮዬን አጣበበው። በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ችግሩ ባለ ብዙ ፈርጅ ነውና እያንዳንዳችን የችግሩን ምንጭ ማሰባችን አይቀርም። የስደቱ ምንጭ ሃገራችን ውስጥ ያለው ቅጥ ያጣ የዘረኝነት ሥርዓት መሆኑ ግልጽ ነው። ምንም እንኳን የምናለቅስው አሁን በወገኖቻቸን ላይ በደረሰው ችግር ቢሆንም የችግሩ መንስዔ ግን ሃገራችን ውስጥ ያለው አገዛዝ መሆኑን ልንዘነጋው አይገባም። ለዚህ አስከፊ ሥርዓት መቀጠል የእኛም አስተዋፅዖ ትንሽ አይደለም። እንዲውም ከፍተኛው ቦታ ሊይዝ ይችላል።

ሁኔታውን ልብ ብለን ስናጤነው ለዚህ ሁሉ መንስዔ የሆነውን ወያኔ እንዳይወድቅ በተለያየ ምክንያት አቅፈን ደግፈን የያዝነው እኛው ነን ማለት ይቻላል ። የሕዝብ ሰቆቃና ስቃይ ያራዘምነው እኛው፤ የስደት አዙሪት ያባዛነው እኛው ነን። ውል የለሾች፣ ማተባችንን የበጠስነው እኛው መሆናችንን ሳስበው ከተለቀሰ መለቀስ ያለበትማ ለእኛ ነው እንጂ ለተሰውት መሆን የለበትም የሚል ድምዳሜ ላይ ደረስኩ። እነርሱማ ለእምነታቸው ውድ ሕይወታቸውን ከፍለዋል።

እውነትም መለቀስ ያለበት ለእኛ ነው። የግፍን ዓይነት ለምንመርጠው፣ ሰው በወገንተኝነት እየለየን ለአንዱ ለምናለቅስ፣ ለሌላው ጆሮ ዳባ ለምንለው፤ ለባለጊዜ ጉልበተኛ ለምንሰግደው፤ በዘር፣ በሃይማኖት ለምንከፋፈለው፤ ራሳችን ያቋቋምነውን (ቤተክርስትያን፣ ማህበር፣ የፖለቲካ ድርጅት፣ የሲቪክ ድርጅት . . . ወዘተ) ራሳችን ለምናፈርሰው፤ አቋማችንን በየወቅቱ ለምንለዋውጠው፤ የሃዘናችን ዳርቻ ከፌስ ቡክ ዋይታ ለማይዘለው፤ የሃይማኖታችን ብጽእና ሻማ ከማብራት አልፎ ወደ ላይ ለማያርገው፤ የምንኩስና ቆባችንን በፖለቲካ እራፊ ለምንጥፈው፣ ሽምግልናችን የእንጨት ሽበት ለሆነብን፤ መክረን ለማንመልሰው፣ ዘክረን ለማንቀልሰው፣ ላለው እምናሸረግድ፣ ለሌለው ፊት እምንነሳ፤ ሞልቶ ለተረፈው የምንሰጥ፤ ድሃውን ለምናሽጓጥጠው፤ የደሃን መጠለያ ጎጆ እያፈረስን መሬት ለምንመራው፤ ማልቀስማ ለእኛ ነው፣ አለን እያልን ለጠፋነው፣ በቁማችን ለሞትነው፤ በእኩይ ምግባራችን ገልሙተን ባህሪያችን ለሸተተው፣ ቀባሪ ዕድር አጥተን እንጂ ከሞትንማ’ ለቆየነው፣ ማልቀስ ለኛ ነው።

የለም! የለም! ዛሬ ለእኛ ነው መለቀስ ያለበት። ሃዘናችን ከቫይበር ስዕል ፣ ከፌስ ቡክ RIP ያለፈ ቁም ነገር ለማይፈይደው፤ ምን አልባትም ለአንድ ቀን “እኔም እነርሱን ነኝ“ ከሚል መፈክር በላይ ለማንሄድ፤ ነገን ለኛ ለምናልም ጉድጓዳችን የተማሰ አዛውንቶች፤ በድሃው አናት ላይ ግራውንድ ፕላስ . . . ቤት ለመስራት ለምንስገበገብው። በሰጥቶ መቀበል ቀመር በደራው የወያኔ ገበያ በዜጎች ሕይወት በዜጎች መብት ለምንነግድ፤ ለምናተርፍ ለእኛ ነው መለቀስ ያለበት።

ጎበዝ! ይለቀስ እንጂ ለእኛ በዘር፣ በድርጅት ተከፋፍለን መነጋገር ላቆምነው፤ የድርጅት መሪ ሆነን በሥልጣን ጥም ጠኔ ለምናጣጥረው፤ ከሕዝብ የተዋጣ ገንዘብ ለምንመዘብረው፤ ትላንት ተቃዋሚ ዛሬ የወያኔ ጋሻ ጃግሬ፤ ትላንት ዓለም አቀፋዊ ዛሬ ጎጠኛ ለሆነው፤ ትላንት ኮምኒስት ነን ብለን ካፒታሊዝምን ያብጠለጠልን ፣ ዛሬ ካፒታሊዝምን ወደን ሶሻሊዝምን የምንረግም፣ ትላንት የተቃዋሚ ሊጋባ ዛሬ የወያኔ አልባሽ አጉራሽ ለሆነው። መለቀስ ያለበትማ ለእኛው፤ ለገበያ ኢኮኖሚ ልማታዊ ባለሃብቶች፣ ፔንዱለሞች፤ አንዴ እዚህ አንዴ እዚያ ለምንዋትት፣ የሁለት ዜጋ ሰዎች፣ በሁለት ካራ በላዎች፣ ማተብ የለሽ ክርስትያኖች፣ ሶላት ለማንሰግድ ሼኮች። ደረት ይመታልን ለእኛ።

ለእኛ ይለቀስ እንጂ! ትላንት አማራዎች ከየቦታው ሲፈናቀሉ አይተን እንዳላየን ለሆነው፤ ስንት የፖለቲካ እስረኞች ቤተሰቦች ሲበተኑ ሰምተን ላለመስማት ለጣርነው፤ በ97 ምርጫ የተገደሉትን ወጣቶች ለረሳነው፤ ወያኔና ሻብዕያ ወጣቱን በጅምላ ለማይረባ ጦርነት ሲማግዱ ለደገፍነው፤ ከክልላችን ይውጡ እያልን ያዙን ልቀቁን ለምንለው፤ ማልቀስ ለኛ ነው በቁማችን ለሞትነው። እንጂማ በሃይማኖቱ ጠንቶ! በዜግነቱ ኮርቶ! ታሪክ ሰርቶ፣ ስም ተክቶ፣ ለሞተው ጀግና ወገንማ ምን ብለን እናለቅሳለን። ለዚህ መሰሉ የሃገር ክብር መግለጫ፣ ለዜግነት ኩራት ለተከፈለ መስዋዕትነት ለማውራትም ይሁን ለማልቀስ ከቶ ስንቶቻችን የሞራል ብቃት ይኖረን ይሆን?

“ሞት የዘመኑ ዕለት እንጅ የመነኑ ዕለት አይደለም“።

ከውጭ ለቃቅመንና ተበድረን በሄድነው ገንዘብ ሃገርቤት ሄደን አሽሼ ገዳሜ ለምንለው፤ በአስረሽ ምችው ዋልጌነት መጥፎ ባሕልን ለምናስፋፋው፤ በማስመሰል ስብእና የድሆችን ቀልብ እያማለልን ስደትን ለምናስፋፋው፤ ጸረ ዘረኝነት ትግልን ለምናጥላላው፤ በየመሸታ ቤቱ በጨበጥነው የድራፍት ብርጭቆ ስፍር የሀገር ልማትን ለምንለካ፣ አዳዲስ የተገነቡትን ሕንጻዎች እንጅ በህንጻው ስር የወደቁትን አዳዲስ ድሃዎች ለማናስተውል፤ የተሰራውን ቀለበት መንገድ ስናደንቅ ጫማ የሌለውን ምስኪን ረግጠን ላለፍነው፤ በተቀዳደዱ እራፊ ጨርቆች ውስጥ ሾልኮ የሚታየውን አቧራ ጸሐይና ቁር የጠገበን ያገር ልጅ ገላ ያላሳሰበን፤ የውስኪውን ጣዕም እንጅ ጥሪኝ ውሃ የሌለውን ወገን ያላስተዋልን፤ የክትፎውን ጣዕም፣ የጥሬውን ስጋ ጮማነት እንጅ . . . እኛ ጠግበን ከጣልነው የእጅ ማበሻ ሶፍት ውስጥ ፈልቅቆ ከትራፊያችን አጥንት ጋር የሚታገለውን ታዳጊ ወጣት የረሳን፤ በሚቀያየር የቀለም መብራት ደንሰን ሻማ መግዥያ የሌለውን ያልተመለከትን፤ አንድ የዕለት ጉርሻ ለመግዛት ገንዘብ ያጣውን ለረሳነው፤ የሃገርን እድገት በሃብታሞች የብር ጥራዝ ለለወጥነው፣ የሆቴሎቹን ማማር፣ የኮረዳዎችን ውበት፣ የሪዞርቶችን ምቾት በየመንገዱ ለምንቆጥረው። ለቅሶ የሚገባው ለእኛ ነው ልማታዊ ቱሪስቶች ለሆነው።

አሁንማ ተራው የእኛ ይሁን እንጂ! ለእኛ ይለቀስ እንጂ፣ የቁም ተዝካራችንን እናውጣ እንጂ፣ የምራዕብውያንን የራስ ጥቅም አሳዳጅነት እያወቅን በየኤምባሲው፣ በስቴት ዲፓርትመንት፣ ነጻነታቸንን ይቸሩናል ብለን 23 ዓመታት ሙሉ ለሰገድነው፤ በሃገራቸን ሕዝብ እምነታችንን ላጣነው፤ ሳንታገል ሳንሰዋ ድል እንደ ኬክ በሳህን ከምዕራብውያን እንዲታደለን ለምንቋምጠው፣ በጣት የሚቆጠሩ ደጋፊዎች አስከትለን በአንድ መሪ አምላኪነት በድርጅት ስም መግለጫ እያወጣን በብዙሃን ትግል ለምንነግደው፤ ሃገርንና ሕዝብን ለስልጣን ጥም በጥቅም ለቀየርነው። መለቀስስ ያለበት ለኛ ነው። በቁም መሞት ከዚህ በላይ ምን አለና!?

ኧረ ሙሾ ደርድሩልን ለእኛ! ከሕዝብ የተዋጣን ገንዘብ ለምንበላው፤ ለጥቅም ስንል ስንት አባላት የተሰውበትን ትግልና ድርጅት እያመከንን ላለነው፤ የውሸትን ፕሮፖጋንዳ እየደሰኮርን ለደጋፊዎቻችን መደለያ ለምናደርገው፤ በድርጅትና በትግል ስም ገንዘብ ለምነን ለግል ጥቅም ለምናውለው፤ ማልቀስ ለኛ ነው ጥሩ እድር አጥተን ላልተቀበርነው ።

ወገን አልቅሱ ለእኛ የስምንተኛው ሺህ የጥፋት ምልክቶች ለሆነው፣ እንደ ቄስ መስፍን (የሙኒኩ) ከህዝብ የተዋጣ 150 ሽህ ዩሮ በላይ የደብሩን ገንዘብ አጥፍቶ “ቀድሼ እከፍላለሁ“ እንዳለዉ በእግዚአብሔርም በዜጋም ለምንቀልድ፣ እንደ(ፕሮቴስታንቱ) ፓስተር ተከስተ የእንስትን ራቁት ፎቶ በስልክ እየበተን ለምንዝናና፣ እንደ አባ ግርማ (የለንደኑ) በሕዝብ ገንዘብ የተገዛን ቤተ-እግዚአብሔር ለግል ጥቅምና ለሹመት ስንል ለዓመታት ለዘጋን፣ ማልቀስ ለኛ ነው እንጅ የስምንተኛው ሺህ ምልክቶች ለሆን፣ ቀብራችን ለተማሰ ግብዓተ መሬታችንን ለምንጠብቅ።

እናልቅስ ከተባለ ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ እናልቅስ! ካልሆነ ግን ለራሳችን እናልቅስ!

ሰሞኑን አዲስ አበባ ለተደበደቡት እናልቅስ፤ የወያኔ ቅልብ ለወንድሞቻቸው ሐዘን የወጡትን ሲደበድቡ እኛም እንቢ እንበል፤ በደቡብ አፍርካ የተደረገውን ግፍ እንዳወገዝን የሃገራችንን አፓርታይድ የክልል አገዛዝንን እናፍርስ፤ ዛሬም ለእነ እስክንድር ቤተሰቦች እናልቅስ ፣ ለነተመስገንም ቤተሰቦች እናልቅስ ፣ ከአንዳርጋቸው ጽጌ ልጆች ጋር አብረን እንነሳ . . . ወዘተ ፣ ለሁሉም የፖለቲካ እስረኞች እንታገል። ለፍትህ እንቁም፣ ለዜጎች መብት እንጋደል፣ ለዲሞክራሲ እንትጋ፣ ለአንድነት በአንድነት እንቁም። በሉ ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ አብረን እናልቅስ።

መታገላችን ካልቀረ፣ ማልቀሳችን ካልቀረ የግፍ ሁሉ ግፍ፣ የስደት ሁሉ ስደት ምክንያት የሆነውን ወያኔን ለማስወገድ፣ ዘረኝነትን፣ ኢ-ፍትሃዊ የሆነውን የሃብት ክምችት፣ ጎጠኝነትን፣ የስርዓት ንቅዘትን፣ ፅንፈኝነትን፣ ብሄራዊ ውርደትን፣ የሉዓላዊነት መደፈርን፣ የአንድነታችን መሸርሸርን ከምንጩ ለማንጠፍ እንታገል። የስርዓቱን ሰለባዎችን ለመታደግ፣ የወገንን ውርደት እንዲያከትም፣ እንነሳ። ሳንከፋፈል ስር የሰደደውን ቀንደኛ የሃገር የሕዝብ ጠላት ወያኔን ለማስወገድ አብረን እንታገል፣ አብረን ተግተን ከልብ እናልቅስ፤ ያኔ ስደትም ይቆማል ሰቆቃችንም ያከትማል፣ እኛም ማልቀሳችንን እናቆማለን ።

ስለ ሰማዕታቱ የሚያስቡ ሁሉ በሰላም ይክረሙ።

beljig.ali@gmail.com

ፍራንክፈርት

30.04.2015

ለእኛ ግን የበቀል ሰይፋችን ፍቅር ነው!፡- ኢትዮጵያዊነት ፍቅርና ይቅር ባይነት የገነነበት ማንነት ነው!! በዲ/ን ተረፈ ወርቁ

$
0
0

‹‹ሰይፍህን አንሣ፣ ክተት ሠራዊት፣
ዝመት ለፍቅር፣ ሰልጥን ለምሕረት፡፡›› (አርቲስት ዘሪቱ ከበደ)

ከሰሞኑን በደቡብ አፍሪካ በቆንጨራ ለተጨፈጨፉ፣ በሚያሰቅቅና በሚዘገንን ኹናቴ እሳት በቁማቸው ለተለቀቀባቸው፣ ሀብት ንብረታቸው ለተዘረፈባቸውና ለጋየባቸው፣ የጦርነትና የእልቂት አውድማ በሆነችው በአገረ የመን ለሞቱና በጭንቅ ውስጥ ለሚገኙ ወገኖቻችንና በተለይም ደግሞ በሊቢያ በአይ ኤስ የአክራሪና ጽንፈኛ ቡድን የተሠዉትን ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን አስመልክቶ በጥቂቱም ቢሆን የጥበብ ባለ ሙያዎቻችን በሥራዎቻቸው ሕመማችንን እየታመሙ፣ ጭንቀታችንን እየተጨነቁ፣ ብሶታችንን፣ ሰቆቃችንንና ዋይታችንን አብረውን እየጮኹ፣ እየተካፈሉ ነው፡፡

የጥበብ ባለ ሙያዎቻችን በሥራቸው የተገኙበትን የሕዝባቸውን ወይም የሀገራቸውን ታሪክ፣ ባህል፣ ቅርስ፣ ትውፊት፣ ማንነት እያስተዋወቁ ነውን?!፤ በሀገራችን ያሉ የጥበብ ባለሙያዎችስ ላለንበትና ለሚያጋጥሙን ማኀበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተግዳሮቶቻችንና ፈተናዎች መፍትሔ በማመላከት፣ ስለ ፍቅር፣ ሰላም፣ ነፃነትና ፍትሕ በመጮኽ፣ ለሕዝባቸው አንደበት፣ ዓይንና ጆሮ በመሆን ሙያዊ ግዴታቸውን እየተወጡ ነው ወይ?! ልክ እንደ ሰሞኑንም አገር የኀዘን ማቅ ስትከናነብ፣ በለቅሶና በዋይታ ስትናጥ፣ ሕዝብ ይዘው ይጨብጠው ሲጠፋ የጥበብ ሰዎቻችን አድራሻቸው ወዴት ነው?!፣ ስለ ምድራችን ግፉአንና ምስኪኖች ድምፃቸውስ ከፍ ብሎ ይሰማል ወይ?! ወዘተ … የሚሉ ጥያቄዎችን ብናነሣ ምላሹ ብዙም የሚያረካ እንዳልሆነ እርግጠኛ ነኝ፡፡

በነጋ ጠባ ጥበብና የጥበብ ሰዎቻችን ወዴት አቅጣጫ እየሔዱ ነው?!፣ የሕዝብ አንደበትና ጆሮ የመሆን ሙያዊ ግዴታቸውስ ወዴት ነው?! የሚል ሮሮ በገነነበትና የቁጭት ደመና ባጠላበት ሁኔታ፣ በአገራችን የጥበብ እንዱስትሪ ውስጥ እንደ መስቀል ወፍ ብቅ በማለት በአገራችን ሙዚቃ ታሪክ እንደ አጥቢያ ኮከብ ደምቀው ያበሩና እያበሩ ያሉ ባለሙያዎችን ግን ፈጣሪ አላሳጣንምና ተመስገን ነው፡፡

መቼም ሥነ ጥበብ በአንድ አገር ሕዝቦች ታሪክ፣ ቅርስና ማንነት እንዲሁም በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችና በሰው ልጆች የዕለት ተዕለት ማኅበራዊ ግንኙነቶች ላይ ያለው ጉልህ አስተዋፅኦና ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ/የምጣኔ ሀብት ምሁር፣ ሐያሲና የሥነ ጽሑፍ ሰው ጋሽ አስፋው ዳምጤ ‹‹ፎረም ፎር ሶሻል ስቴዲስ›› ለሁለት ዓመታት በተከታታይ ባደረገው ‹‹ልማትና ባህል በኢትዮጵያ›› በሚለው የውይይት መድረክ ላይ ‹‹ሥነ ጥበብና ልማት›› በሚል ባቀረቡት የጥናት ጽሑፋቸው የጥበብን ሁለተናዊ ፋይዳ አስመልክተው እንዲህ ብለው ነበር፡-

‹‹… ሰው በተፈጥሮው ከአራዊት ወይም ከእንሰሳት የሚዛመድባቸውን ባሕርያት መሞረድ፣ ማለዘብ፣ እና የሰብአዊነት ባሕርያቱን ማጎልበት፣ ብሎም የማኅበራዊ ሕይወት ንቃቱን ከፍ በማድረግ፣ በጎና ሁለተናዊ ለሆኑ የልማት የጋራ ግቦች ለመነሳሳት ምቹ የሚያደርገው የአስተሳሰብ ዝንባሌ እና አመለካከት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የጥበብ ዘርፎች ሁሉ ዓላማና ግብ ነው፡፡›› በማለት ሥነ ጥበብ በሰው ልጆች ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ያለውን ሁለተናዊ ፋይዳ አብራርተዋል፡፡

በሥነ ጥበብ ዘርፍ ውስጥ ከሚካተቱትና ከፍጥረት ወይም ከሰው ልጆች ታሪክ ጅማሬ ዘመን ጋር አቻ ሊባል በሚችል በጥንታዊነቱ ወይም በዕድሜ ጠገብነቱ የሚነሳው አንጋፋው ሙዚቃ፣ በሰው ልጆች ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሕይወትና መስተጋብር ውስጥ ትልቅ ድርሻና ግዙፍ አሻራ እንዳለው ብዙዎች የዘርፉ ምሁራን ይስማሙበታል፡፡

በዛሬው አጭር መጣጥፌ የቀድሞዋ ዘፋኝ አሁን ግን ወደ ሃይማኖት ፈቷን በማዞር ወደ ዝማሬ ያዘነበለችው አርቲስት ዘሪቱ ከበደ በሊቢያ በአይ ኤስ ጽንፈኛ ቡድን ሰማዕት ለኾኑ ወገኖቿ ‹‹ሰይፍህን አንሳ!›› በሚል ርእስ ከሰሞኑን አንድ ነጠላ መዝሙር አስደምጣናለች፡፡ የዚህ ዝማሬ መልእክቱ እጅግ ጥልቅ የኾነ ፍቅርን፣ ምሕረትንና ይቅርታን የሚሰብክና ከመንፈሳዊነቱ ባሻገርም ኢትዮጵያዊነት ከፈጣሪ የተቸረ በፍቅርና በውበት ጥበብ ተሸምኖ የደመቀ፣ ፍቅርና ይቅር ባይነት የተሞላ ሕያው ማንነት መሆኑን የገለጸችበትን ዝማሬዋን ከማኅበራዊ ድረ ገጾች አደመጥኩኝ፡፡ እናም አርቲስቷ በዚህ በሰማዕትነት ለተሠዉ ወገኖቻችን በሠራችው ሙዚቃዋ ዙርያ ጥቂት ነገሮችን ለማለት ወደድኹ፡፡

በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በሊቢያ በግፍ ለታረዱ ልጆቿ የሰማዕትነትን ማዕረግ መስጠቷ ይታወቃል፡፡ ባሳለፍነው ሳምንትም ለሰባት ቀን ያህል ቤተ ክርስቲያኒቱ እነዚህ ሰማዕታት የኾኑ ልጆቿን በጸሎተ ፍታትና በምሕላም ስታስባቸው ሰንብታለች፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ መሪና የመንጋው እረኛ የሆኑት ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስም እነዚህ ወገኖቻችንን በግፍ የሠዉትን የጽንፈኛው ቡድንን ከፈጣሪ ዘንድ ምሕረትንና ይቅርታን ያገኙ ዘንድ የንስሓ ጥሪ መልእክታቸውን በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም ማስተላለፋቸውንም ተከታትለናል፣ አድምጠናል፡፡

ይህ ፓትርያርኩ ያስተላለፉት መልእክት ቤተ ክርስቲያኒቱ ያላት ብቸኛው የበቀል ሰይፏ ፍቅር፣ ምሕረትና ይቅርታ መኾኑን ያረጋገጠና ያስረገጠ ነው፡፡ ይህ ታላቅ የሆነ መልእክትም በክርስትና ሃይማኖት ታሪክ፣ በዘመነ ሰማዕታት ለክፉ አውሬ ለአንበሳና ለነብር እየተሰጡ፣ በሰም የተነከረ ሸማ ለብሰው በእሳት እየተቃጠሉና እየጋዩ፣ በሰይፍ እየታረዱና እንደ ጎመን እየተቀረደዱ፣ በስለት እንደ ሸንኩርት እየተከተፉ፣ በድንጋይ እየተወገሩ ያለፉ የወንጌልና የኢየሱስ ክርስቶስ ሕያው ምስክሮቹ የሆነ ሰማዕታት ሞትን ላወጁባቸው ኹሉ ምሕረትንና ይቅርታን ከፈጣሪያቸው ዘንድ ያገኙ ዘንድ ነው ሲማጸኑ የነበሩት፡፡

ይህ ከወዳጅ አልፎ ለጠላቶችም የሚተርፍና የሚተረፈረፍ ፍቅር፣ ምሕረትና ይቅርታ የክርስትና ሃይማኖት መሠረትና ጉልላት፣ ዋልታና ማገር ነው፡፡ የክርስትናው ዓለም ወርቃማ ሕግም፡- ‹‹ባልንጀራህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ፤ ጠላትህንም ደግሞ ውደድ፡፡›› የሚል ነው፡፡ ከዚህ የክርስትናው ዓለም እውነታና አስተምህሮ ጋር አያይዤም አርቲስት ዘሪቱ ከበደ ‹‹ሰይፍህን አንሣ›› በሚል በሰማዕትነት ለተሠዉ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን መታሰቢያነት ባቀረበችው ዝማሬዋ ውስጥ ያነሣቻቸውን ልብ የሚነኩና ጥልቅ የኾነ መንፈሳዊ መልእክቶቿን በጥቂቱ ለመፈተሽ እሞክራለኹ፡፡

አርቲስት ዘሪቱ ይህን ከልቧ የፈለቀውን ዝማሬዋን የጀመረችው ወገኗን እንደ እግር እሳት እየለበለበ መቆሚያ መቀመጫ ያሳጣውና ከምድሩ ያሳደደው ድኅነት፣ ችግር፣ ሰቆቃና መከራው፣ ተስፋን፣ ሕይወትንና የተሻለን ነገ አልሞና ሽቶ በተሰደደበት፣ በዚያ እዋዩ እንደ ሰደድ እሳት በሚንቀለቀልበትና የአሸዋው ግለት እንደ ወላፈን በሚጋረፍበት የሊቢያ በረኻ በወገኖቿ አንገት ላይ በጨካኞቹና በሞት አበጋዞቹ በአይ ኤስ ቡድን የተጋደመባቸውን ሰይፍ እያሰበችና በዓይነ ሕሊናዋ እየሣለች፡-

‹‹አመመሕ፣ ተቃጠልክ፣ ተቆጨኽ …›› በማለት ነው የወገኖቿን የዘመናት ብሶትና ምሬታቸውን፣ ሰቆቃና ዋይታቸውን በመካፈል ነው ልብን በሚሰረስር ዜማ ዝማሬዋን የምትጀምረው፡፡ ዘሪቱ በሙዚቃው ዓለም በነበረችበት ጊዜ እጅጉን በምትታወቅበትና ተወዳጅነትን ባተረፈችበት በተለየ ቅላጼዋና በሚስረቀረቅ ድምፅዋ፣ ፍቅርን፣ ምሕረትንና ይቅርታ በሰበከችበት የሙዚቃ ሥራዋ እንዲህ ስትልም ኢትዮጵያውያን ወገኖቿንና የሰው ልጆችን ኹሉ በፍቅርና በምሕረት ከፍ ባለ ድምፅ ትጣራለች፡-
‹‹ሰይፍህን አንሣ፣ ክተት ሠራዊት፣
ዝመት ለፍቅር፣ ሰልጥን ለምሕረት፡፡››

ዘሪቱ የሰው ልጆች ኹሉ እንዲያነሡት እያወጀችው ያለው ሰይፍ ስውር፣ ባለ ድልና ኹሉን የሚረታ ሕይወትን፣ ፍቅርን፣ ሰላምን የሚያውጅ መኾኑን እንዲህ ታበስረናለች፡፡ ይህን ሰይፍ አንስቶ፣ ይህ ሰይፍ ታጥቆ የሚተመው፣ የሚከተው ሠራዊትም ሰማያዊ፣ መለያውና በሩቅ ደምቆ የሚታየው ሰንደቀ ዓላማውም ፍቅር እንደሆነ እየነገረችን፣ እያወጀችልን ነው፡፡ አርቲስቷ በዚህ ጥልቅ መልእክትን ባዘለው ዝማሬዋ ይህ ሰይፍ የጨካኞችን ልብ በፍቅር የሚማርክ፣ ሞትን ሣይቀር የሚያሸንፍ፣ የሚረታና ይህ የበቀል ሰይፍ በሕይወትና በፍቅር ላይ የሚነግሥ ባለ ታላቅ ድል መኾኑንም እንዲህ ትነግረናለች፡-
‹‹ሰይፍህን አንሣ ተጋደልበት፣
ቀላል አይደለም ይኼ ጦርነት፡፡
ሰይፍህን አንሣ ማን ይችለዋል፣
ሞትን ራሱን ያሸንፈዋል!!››

የዘሪቱ የዝማሬዋ ጥልቅ መልእክት ሌላም እውነታን ይነግረናል፡፡ የዝማሬዋ ስንኞች መልእክታቸው ከመንፈሳዊነታቸው ባሻገርም የአገራችንና የሕዝባችንን ግዙፍ ታሪክና ገናና ሥልጣኔ የሚዳስስና የሚተርክ ነው፡፡ በአርእስቴ ላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ዘሪቱ በዚህ ዝማሬዋ ፍቅርና ይቅር ባይነት የሰለጠነበትንና የገነነበትን ያን ታላቅ የሆነ፣ በዘመን ተፈትኖ ያለፈ ክቡር የሆነ የኢትዮጵያዊነትን ረቂቅ መንፈስ ወይም ታላቅ ማንነትን እያነሳች፣ እያስታወሰችን ጭምር ነው፡፡

እንደሚታወቀው አገራችን ኢትዮጵያ በረጅም ዘመን ታሪኳና በገናና ሥልጣኔዋ በርካቶችና ጠላቶቿም ጭምር ሣይቀር እንደመሰከሩላት የሰው ልጆች ኹሉ የፍቅር እጇን ዘርግታ የምትቀበል፣ እንግዳ ተቀባይ፣ ግዞት፣ ስደትና ሞት የታወጃበቸውን ኹሉ የምትታደግ ለፍቅር፣ ለእውነትና ለፍትሕ የቆመች አገር መኾኗንም እንድናስታውስ የሚያተጋን፣ የሚቀሰቅሰን ነው፡፡

ለአብነትም የነቢዩ መሐመድ ተከታዮች በዐረቢያ ምድር ሞት በታወጀባቸው ጊዜ ነቢዩ ፍትሕና ፍቅር ወደነገሠባት የሐበሾች ምድር ይሰደዱ ዘንድ ነበር ለተከታዮቻቸው ያስታወቋቸው፡፡ በእውነትም ክርስቲያኖቹ አክሱማውያን እነዚህ ሰዎች በክብር ተቀብለውና አስተናግደው ነበር በሰላም ወደ አገራቸው የሸኟቸው፡፡ በሰውነታቸው አልቃና አክብራ፣ በሃይማኖት አስተምህሮዋ እግራቸውን አጥባና ፍቅርን አስተምራ ያስተናገደች፣ ሰላምና ፍቅርም የኢትዮጵያዊነት መለያና ሰንደቅ ዓላማ ነበር፣ ነውም!!

በሌላ የታሪካችን ገጽም ድንበር ጥሶና ውል አፍርሶ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብን ንቆና ተገዳድሮ ማን ወንድ ነው ከፊቴ የሚቆመው በሚል ትእቢት ከሮማ ምድር ወደ ሐበሻ መሬት ገሥግሦ የመጣውን የቀኝ ገዢውን የኢጣሊያን ኃይል አባቶቻችን ውርደትና ሽንፈትን ካከናነቡት በኋላ ለአውሮፓ አገራት ነገሥታትና የሃይማኖት መሪዎች በጻፉት ደብዳቤያቸው ፍቅርንና ይቅርታን ነበር ያወጁት፡፡

ዐፄ ምኒልክ ከድሉ በኋላ ለፈረንሳይና ለሩሲያ ነገሥታትና ለሮማው ፖፕ በጻፉት ደብዳቤያቸውና ባስተላለፉት መልእክታቸውም፡- ‹‹በድንቁርናቸው ብዛት የእነዛ ሁሉ ክርስቲያኖች ደም በከንቱ በመፍሰሱን እያየኹ ድል አደርኩ ብዬ ደስ አይለኝም፡፡›› ነበር ያሉት፡፡ ንጉሡ እንደውም ኢጣሊያውያኑ ምርኮኞችንም በበቤተ መንግሥታቸው አቅራቢያ አስፍረው ራሳቸውና ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ ነበር ሲንከባከቧቸው የነበረው፡፡ እንደእነ በርክሌይ ያሉት አውሮፓውያን ጸሐፊዎችና የታሪክ ተመራማሪዎች ሣይቀሩ ይህን በምሕረት የሰለጠነ የኢትዮጵያ ሠራዊት በልዩ ክብር አድንቀው ነው የጻፉለት፡፡

ይህ ታሪክ በወርቀ ቀለም የከተበው የኢትዮጵያዊነት እውነተኛ ማንነት ከቂም በል የጸዳ፣ ለእውነትና ለፍትሕ የሚቆምና የሚከራከር፣ ፍቅርና ይቅር ባይነት የገነነበት ማንነት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነትም ከፈጣሪ የተቸረ ነጻነት ያበበበት የቃል ኪዳን ምድር ነው፡፡ ይህ ነጻነትም በአባቶቻችን አኩሪ ተጋድሎ በደም የጸና ግዙፍ ታሪክም ነጻነታቸውን የሚያፈቅሩ፣ ሰብአዊነትን የተላበሱ፣ የመንፈስ ልእልና ላይ የደረሱ የሰው ልጆች ሁሉ የሚጋሩት፣ የሚኮሩበት ከአድማስ አድማስ የናኘ የነጻነት ክቡር መንፈስ እንደሆነ ከግሪክ ጠቢባንና ፈላስፎች እስከ ጥንቶቹ ታላላቅ የታሪክ ጸሐፍትና ምሁራን፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ እስከ ቅዱስ ቁርአን በአንድነት የመሰከሩለት ነው፡፡

ኹላችንም ልንኖርባት በተሰጠን በዚህች ምድር ላይ በልባችን ውስጥ ባለ በመለኮታዊው ብርሃን ጨለማውን እያሸነፍን፣ ጽልመትን የምንገፍ የብርሃን ልጆች፣ የክፋትን ኃያላትንና ክፉዎችን በመለኮታዊ ፍቅር ድል የምንነሳ፣ አርበኞች የመኾን ክብር ከፈጣሪ ዘንድ ተችሮናል፡፡ ምንም እንኳን በወገኖቻችን ላይ የደረሰውን አሰቃቂ የኾነ ግፍ ኀዘናችን ጥልቅና መሪር ቢሆንም ትናንትና፣ ዛሬም ወደፊትም የበቀል ሰይፋችን ግን ፍቅር ነው!! የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም በዚህ የአምላኳ አስተምህሮ መሠረት ለነፍሰ ገዳዮቹ የአይ ኤስ ቡድን በትሕትና የፍቅርንና የንስሓ ጥሪን አስተላልፋለች፡፡

እኛም ክርስቲያኖች በደማቸው ፍቅርን ሠርተውና ኑረው ሕያዋን ምስክር ሆነው እንዳለፉት የሃይማኖት አርበኞችና ሰማዕታት፣ በዘመናችንም ለትውልድ ምስክር እንደሆኑት እንደእነ ማንዴላ፣ ማርቲን ሉተርና ማኅተመ ጋንዲ ሁሉ የጠላቶቻችን ልብ የሚያቀልጠውን፣ የሚያርደውንና ከፊቱ ችለው መቆም የማይቻላቸውን የፍቅርን የበቀል ሰይፍ እናነሳለን፡፡

‹‹ሰይፍህን አንሣ የአባቶችህን፣
እግዚአብሔር ይመስገን ባይ ሕዝብ ያደረገኽን፡፡
ሰይፍህን አንሣ፣ በል ጊዜ የለም፣
በክፋት ካራ እንዳትቀደም፡፡
የዘላለም ትጥቅ የዛሬው መከታ፣
የፍቅር ካራ ነው እርሱን ይዘህ ውጣ፡፡
ሰይፍህን አንሣ ክተት ሠራዊት፣
ዝመት ለፍቅር ሰልጥን ለምሕረት፡፡›› (ዘሪቱ ከበደ)

ሰላም! ሻሎም!


አሜሪካ አይሲስን ለምን ፈጠረችው? ክንፉ አሰፋ

$
0
0

ግብጽ የሃያ አንድ ክርስቲያን ዜጎችዋን በአይሲስ መታረድ ዜና እንደሰማች ዝም ብላ አልተቀመጠችም ነበር። ብሄራዊ የሃዘን ቀንም አላወጀችም። እንዲህ ነበር የሆነው። ከመቅጽበት ተዋጊ አውሮፕላኖችዋን አስነስታ ወደ ሊቢያ ላከቻቸው። የአይሲስ አራጆች የተከማቹበትን ደርና የተሰኘ ስፍራ እያከታተለች በቦምብ ቀጠቀጠችው። ብዙ አራጆች በድብደባው አለቁ። እንደ ግብጽ አጀማመር ቢሆን የሊብያው አይሲስ ክንፍ ድሮ-ድሮ ከምድረ-ገጽ ይጠፋ ነበር። ግና አልሆነም። አሜሪካ ጣልቃ ገባች። ግብጽ የአሜሪካን “ጸረ-ሽብር” ዘመቻ በማገዝዋ ምስጋና ማግኘት ሲገባት በተቃራኒው ተወገዘች። ከጥቂት ድብደባ በኋላ ፔንታጎን ግብጽን አስጠነቀቀ[0]። የኦባማ አተዳደርም ደብደባው በአፋጣኝ እንዲቆም ቀጭን መልእክት ላከ። ይህ ድርጊት ከዚህ ቀደም ስለ አይሲስ አፈጣጠር ኤድዋርድ ስኖደን[1] የለቀቀው ምስጢራዊ መረጃ ጋር ተዳምሮ በአሜሪካ ላይ የነበረውን ጥርጣሬው አጠናከረው።
ነገሩን ለማመን ያዳግት ይሆናል። በግልጽ የሚታዩ መረጃ እና ማስረጃዎች ግን ተአማኒነታቸው ጥርጥር ውስጥ የሚገባ አይደለም። “በአይሲስ እየታረዱ ያሉት ዜጎች የፊልም ቅንበር እንጂ እውነት አይደለም![2]” የሚሉ ባለሞያዎችም የትንተናቸው መነሻ ከዚህ ጉዳይ ጋር ይያያዛል።

ይህ አሸባሪ ድርጅት ስራውን ከጀመረ አንድ አመት ባልሞላ ግዜ ውስጥ ከመቶ ሺ በላይ ዜጎችን በአሰቃቂ ሁኔታ እንደገደለ ይናገራል። ቦምብ እንደዝናብ የሚወርድባቸው ሃገሮች፤ ሶማልያ፣ የመን፣ ኢራቅ፣ ሶርያ፣ አፍጋኒስታን፣ፓኪስታን… ተደምረው አይሲስ ከሚነግረን ግድያ ሩብ ያህሉንም አላደረጉም። የሃያላን ሃገሮች ምላሽ ግን በአፍ ከማውገዝ ያለፈ አለመሆኑ በአይሲስ አሰራር ላይ ተጨማሪ ጥርጣሬ ይፈጥራል።

አይሲስ የእስራኤል፣ የኢንግሊዝ እና አሜሪካ የጋራ ፕሮጀክት መሆንን ያጋለጠውን፤ የኤድዋርድ ስኖደን መረጃ እንደገና እንድንመረምረው ይገፋናል። በአይሲስ ዙርያ የሚተነትኑ አንዳንድ ጸሃፊዎች እጃቸውን በአሜሪካ ላይ መቀሰር ከጀመሩ ሰነበትበት ብለዋል። አሸባሪ ሃይልን መፍጠር ለአሜሪካ የመጀመርያ አይደለም። አላማው ይለያይ እንጂ ኦሳማ ቢን ላደንም የአሜሪካ ስሪት መሆኑ በይፋ ተገልጿል። የአሜሪካ ቁጥር አንድ ጠላት የነበረው ኦሳማ ቢን ላደን በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት በአሜሪካው የስለላ ተቋም፤ በሲ.አይ.ኤ እንደተፈጠረ በግልጽ ተቀምጧል። እ.ኤ.አ. በ1979 ሶቭየት ህብረት አፍጋኒስታንን በወረረች ግዜ ኦሳማ ቢን ላደን አማጺውን የሙጃህዲን ሃይል በመቀላቀል ወደ አፍጋኒስታን አመራ። በወቅቱ አሜሪካ ሙጃህዲንን ለማሰልጠን እና ለማስታጠቅ ሶስት ቢሊየን ዶላር እንዳፈሰሰች የብሪታንያው ዜና አገልግሎት ቢ.ቢ.ሲ. ዘግቧል። እንደ ቢ.ቢ.ሲ. ዘገባ ሲ.አይ.ኤ. ለኦሳማ ቢን ላደን በግል ደረጃውን የጠበቀ የኢንተልጀንስ ስልጠናም አድርጎለታል። ቀዝቃዛው ጦርነት ሲያበቃ እና ሶቭየት ህብረት አፍጋኒስታንን ለቅቃ ስትወጣ ነው ቢን ላደን አሜሪካ ላይ የዞረው።

የዘመናችን ዘግናኝ የሽብር ድርጅት የሆነው አይሲስንም የፈጠረችው አሜሪካ ናት የሚሉ ጸሃፍት ጥቂት አይደሉም። የእነዚህ ተንታኞች መረጃ በከፊል የሚንተራሰው ከአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት ኤጀንሲ ሰነድ የጠለፈው ኤድዋርድ ስኖደንን ነው። የአሜሪካ ስለላ ድርጅት NSA ውስጥ ይሰራ የነበረው ይህ ሰው የአሜሪካን ብሄራዊ ምስጢሮች ካጋለጠ በኋላ ሩስያ ውስጥ ተደብቋል። እርግጥ ነው። ኤድዋርድ ስኖደን የለቀቀው ሰነድ የአይሲስን አፈጣጠር ምስጢር በጥቁርና – ነጭ አስቀምጦታል። ሾልኮ የወጣው ይህ ሰነድ የአይሲሱ መሪ አቡባክር አል ባግዳዲ የአሜሪካ ደህንነት ግብአት እንደሆነ ይገልጻል። እንደ ምስጢራዊው የኬብል መረጃ ከሆነ ለአይሲስ መመስረት ሃላፊነቱን የሚወስዱት እስራኤል፣ ታላቋ ብሪታንያ እና አሜሪካ ናቸው። “ምክንያቱም” ይላሉ ዶክመንቱን የሚተነትኑ አምደኞች፣”ምክንያቱም እስላማዊ ጦረኞች የሚሏቸው ሃይሎች ሁሉ ከአለም ዙርያ እየሄዱ ሶርያ ላይ እንዲሰባሰቡ ነው።” ይህ ስትራቴጂ እውን ሲሆን፤ በአንድ በኩል በእነሱ የሚመራ ህይል ለማስቀመጥ እና በሌላ በኩል ደግሞ እስራኤል በቅርብ አደጋ ላይ መውደቋን ለማስመሰል የተወጠነ ታክቲክ ነው። መካከለኛው ምስራቅ ሽብር ያለ ማስመሰሉ አካባቢውን ዘልቆ ለመቆጣጠር ይረዳቸዋል። ይህን ለማድረግ አይሲስን እንደ ምክንያት ይጠቀሙበታል።”

የኤድዋርድ ስኖደን ምስጢራዊ መረጃ በጥሬው ተቀብለን፣ ስነዱን እንደማስረጃ ወስደን ለድምዳሜ መቸኮል የለብንም። ጉዳዩ ትንሽ ከበድ ያለ ነውና ሌሎች ተጓዳኝ ነገሮችን መመርመርም ተገቢ ይሆናል።
የእስላማዊ ዲሞክራቲክ ጂሃድ ፓርቲ መስራች እና ቀደም ሲል ከፍተኛ የአልቃይዳ ኮማንደር የነበረው ናቢል ናኢም ለሜዲያ የተናገረው መረጃ የኤድዋርድ ስኖደንን ማስረጃ ያጠናክረዋል። ናቢል ናኢም ለቤይርቱ ፓን አረብ ቴሌቭዥን በሰጠው ቃል፤ “አይሲስን ጨምሮ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያላቸው ደርጅቶች ሁሉ፤ በአሁን ሰዓት እየሰሩ ያሉት ለአሜሪካው የስለላ ተቋም ለሲ.አይ.ኤ. ነው።” ሲል በዚህ ወር መግቢያ ላይ ተናግሯል[3]።
ናቢል ናኢም በቴሌቭዥን የሰጠው አስደንጋጭ ምስጢር በዚህ አላበቃም፤ ሌላም ለማመን የሚከብድ ነገር አክሎበታል። አይሲስ በደንብ የሰለጠነ እና በደንብ የታጠቀ የሽብር ድርጅት ነው። መጠነ ስፊ የሆኑ የኢራቅን እና የሶርያን ክልሎች ተቆጣጥሯል።

የባህሬኑ “ዘ ገልፍ ዴይሊ ኒውስ” ጋዜጣም ባለፈው አመት አጋማሽ ላይ በዋና ገጹ የአይ.ሲስ መሪ አቡ ባክር አል ባግዳዲን የእስራኤሉ የስለላ ድርጅት ሞሳድ በጦር፣ በመንፈሳዊ ትምህርት እና በንግግር ክህሎት እንዳሰለጠነው ጽፏል[4]።
የዮርዳኖስ ባለስልጣናትን ጠቅሶ “ወርልድ ኔት ዴይሊ” የተሰኘው ጋዜጣ የአሜሪካ ወታደሮች በዮርዳኖስ ግዛት ውስጥ የአይሲስ አባላትን እንዳሰለጠኑ ዘግቧል[5]።
እነዚህን መረጃዎች በአንድ ወገን እንያዛቸው እና ወደ ሌሎች ምልከታዎች ደግሞ እንሂድ። ታላላቅ የአሜሪካ ጋዜጠኞችም የአይሲስ መጠናከር እና የአለም ዝምታ እንቆቅልሽ ነው የሆነባቸው። የፎክስ ኒውስ አምደኛ የሆነችው ግሬታ ቫን ሱስተረን እንግዳ የሆነባትን አስደንጋጭ የአይሲስ ግድያ እና የምእራባውያን ዝምታ እጅግ በመደነቅ ታነሳለች። አይሲስ በሺዎች የሚጠጉ ክርስቲያኖችን እያረደ፤ የተባበሩት መንግስታት፣ አሜሪካም ሆነ የአውሮፓ ህብረት ጉዳዩን ከምንም አልቆጠረውም ብላለች። ጋዜጠኛ ግሬታ ንግግርዋን ቀጠለች። “ያለነው በሂትለር ዘመን አይደለም። ዘመኑ የመረጃ ነው። እልቂቱን የሚያሳዩ መረጃዎች በግልጽ ይታያሉ። አሰቃቂ መረጃዎችን እየተመለከተ አለም ግን ዝም ነው ያለው። ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ሊጋባን በማይችል ምክንያት ጉዳዩን ችላ ብሎታል። …” ትላለች።
ሌላው ሉ ዶብስ የተባለ በአሜሪካ ታዋቂ የቴሌቭዥን አቅራቢና ጸሃፊ፤ ህዝብ እየታረደ አለም ግን በአይሲስ ላይ ችላ ማለቱ እንዳስገረመው ይናገራል። ጋዜጠኛ ሉ ዶብስ ሜሪካዊውን ደራሲ ጆኒ ሞር በጉዳዩ ማብራርያ እንዲሰጥም አድሮታል። ጆኒ ሞር “Defying ISIS” “ውጉዝ መአሪዮስ አይሲስ” የሚል መጽሃፉ አይሲስን ከናዚዎች ጋር እያመሳሰለ ነው ያስቀመጠው። ጆኒ ሞር በፎክስ ኒውስ ላይ ቀርቦ የተናገረው ያስደምማል። “የ አይሲስ አራጆችን የጫኑ አርባ መኪናዎች በአንዲት የሶሪያ መንደር በነጻነት እየተዘዋወሩ 3000 ክርስቲያኖችን አፍሰው ወሰዱ። … ቦስንያ ላይ በቀን 140 ቦምብ ሲጥሉ የነበሩ የኔቶ ተዋጊ አውሮፕላኖች፣ በኢራቅ እና ሶርያ ላይ በቀን ከ 7 – 12 ቦምብ ሲጣል አይሲስ ግን ችላ ነው የተባለው።”

ጆን ዊልገር የተሰኘ የፖለቲካ ተንታኝ ደግሞ በአንድ ጥናታዊ ጽሁፉ፤ “አይሲስ የአሜሪካ ፍጡር ነው” ከማለት አልፎ፣ አይሲስን ከካምቦዲያው ካመሩዥ ጋር ያመሳስለዋል። በ 1969 እ.ኤ.አ. ፕሬዝዳንት ኒክሰን ካምቦዲያን በቦንብ አስደብድበው ሲያበቁ አንባገነኑ ፖል ፖትን አበቀሉ። የፖልፖት ካመሩዥ ከአይሲስ ጋር የሚያመሳስላቸው ነገር አለ። “ሁለቱም የአሜሪካ ውጤቶች፣ ሁለቱም የጨለማው ዘመን ጨካኞች ናቸው” ሲል ጽፏል።

ይህን ክስተት ስከታተል “ሲ. አይ. ኤ – ዘ ከልት ኦፍ ኢንተሊጀንስ” የተሰኘው መጽሃፍ ታወሰኝ። ቪክቶር ማርቼቲ የተባለ የቀድሞ ሲ.አይ.ኤ አባል የጻፈው “ዘ ከልት ኦፍ ኢንተሊጀንስ” መጽሃፍ አሚሪካኖች ብሄራዊ ጥቅማቸውን ለማስከበር የማያደርጉት ነገር እንደሌለ ይነግረናል። ሲ. አይ.ኤ. የአሜሪካን ብሄራዊ ጥቅም ሲያስከብር ለሞራል እሴቶች፣ ለሰዎች ስብዕና እና ለፍትህ ቦታ እንደማይሰጥ ደራሲው ቪክቶር ማርቼቲ ይነግረናል። መጽሃፉ በከፊል በአሜሪካ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሳንሱር ተደርጎ የወጣ ነው። እንደዚህም ሆኖ ሲ.አይ.ኤ. ከረቀቀ ቴክኖሎጂ እስከ ረቀቀ ወንጀል እንደሚሰራ ይተነትናል። አሜሪካኖች ጉዳያቸውን ለማስፈጸም ዝናብ ማዘነብ ካለባቸው እንኳን፤ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ያንን ሊያደርጉ እንደሚችሉ መጽሃፉ ያሳየናል።

የአይሲስ አራጆች የሚናገሩት እንግሊዝኛ በአሜሪካ ቅላጼ (አክሰንት) ነው። አሜሪካ ተወልደው ያደጉ ሽብርተኞች ሊሆኑ ይችላሉ ብለን እንውሰድ። አይሲስ የሚለቅቃቸውን የቪድዮ ምስሎች የሚጠራጠሩ ባለሙያዎች፤ ጉዳዩን ከፖለቲካ ብቻ ሳይሆን ከሙያ አንጻርም ይመለከቱታል። የጃፓን ዜጎች ሲታረዱ የሚያሳየውን ቪድዮ ፍሬም፣ በፍሬም እያሳዩ የአይሲስ ግድያ ውሸት መሆኑን ለመግለጽ የሚሞክሩ የፊልም ባለሞያዎች የሚናገሩት ሙሉ በሙሉ ባያሳምንም ተመልካቹን ማደናገሩ አልቀረም[6]። እየወጡ ያሉት የግድያ ፊልሞች በአረንጓዴ ጨርቅ green screen በስቱዲዮ ውስጥ የሚሰሩ የትራይካስተር ቴክኒኮች ናቸው ብለው ነው እርግጠኝነት የሚናገሩት። ግሎባል ሪሰርች የተባለ አንድ የካናዳ የምርምር ተቋም፤ ISIS Video ‘Execution’ of Ethiopians in Libya Appears Fake [2] ሲል በሊቢያ የተሰዉት የኢትዮጵያ ሰማእታት ጉዳይ፤ የቪድዮ ቅንብር እንጂ እውነት አይደለም ሲል የምስሉን ፍሬም እየከፋፈለ በስሎው ሞሽን አቅርቦታል። ትንተናው አሳማኝ ላይሆን ይችላል። አይቶ መፍረዱ ግን ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም። ምኞታቸውም ከሆነ ይህ እውነት ይሆን ዘንድ ጸሎታችን ነው።

ያልተፈታ እንቆቅልሽ!
ለመሆኑ እስራኤል፣ የኢንግሊዝ እና አሜሪካ በጋራ ሆነው የአይሲስን ፕሮጀክት ለምን ፈጠሩ? የሚለው ጥያቄ ምላሽ ካገነ እንቆቅልሹን ይፈታው ይሆናል። ተንታኞች እና ተቺዎች ለዚህ በርካታ ምክንያቶችን ይደረድራሉ። አንደኛው ምክንያት እስራኤል በመሃከለኛው ምስራቅ ውስጥ ሁከት በመፍጠር የሁከቱ ተጠቃሚ ለመሆን እንድትችል ነው ይላሉ። ይህ ከሆነ እስራኤል በክልሉ ሃያልነቷን ሙሉ ለሙሉ ለማስከበር ይረዳታል ይላሉ። አይሁዶች ክርስትና እና እስልምና ጠላት ባይሆኑም በሁለቱም እምነቶች ላይ ችግር አለባቸው። ይሁንና አላማቸው የአይሁድን እምነት ለማስፋፋት ሳይሆን የእስራኤልን በሄራዊ ጥቅም ማስጠበቁ ላይ ነው። የእስራኤል አላማ የሁለቱ ሃይማኖት ተከታዮችን እርስ-በእርስ ማፋጀትና ማዳከም ነው ብለው የሚጽፉም አሉ። በእርግጥ አረቦች በሙሉ ጸረ-አይሁድ ናቸው። አረቦች በሙሉ ደግሞ ሙስሊሞች አይደሉም። እንደፍልስጤም፣ ኢራቅ፣ ዮርዳኖስ፤ ሊባኖስ እና ሶርያ ባሉ አረብ አገሮች ክርስቲያኖችም አሉ።

አሜሪካ እና እንግሊዝም ከዚህ ሽብር ጀርባ የሃገራቸውን ብሄራዊ ጥቅም ያስከብራሉ። አለምን በአሜሪካ አምሳል መፍጠር ከሚለው የአሜሪካ የውጭ ፖሊሲን በሌላው ከመጫን ባሻገር ከመካከለኛው ምስራቅ በኢኮኖሚ ዘርፍ የሚያገኙት ጥቅምም ቀላል የሚባል አይደለም። አንደኛው “ሽብርን መዋጋት” በሚል ምክንያት የጦር መሳሪያ ሽያጭ ነው። ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በመሳርያ ሽያች በአመት ከአራት ትሪልዮን ዶላር በላይ ገቢ ያገኙበታል። መካከለኛው ምስራቅ ሃገር ያሉ ዋና ዋና የነዳጅ ክምችቶችን ለመቆጣጠርም የእነሱ የሆነን ሃይል በሽብር ሰበብ በስፍራው ማስቀመጥ ግድ ነው።

አሜሪካ ለሃገሯ ብሄራዊ ጥቅም ስትል በሌሎች ላይ ቁማር መጫወት አይገዳትም። በዚያን በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት አሜሪካኖች ከምስራቁ ጎራ ጋር የቃላት ጦርነት ነበር ያካሂዱ የነበረው። ያ ወቅት ለእኛ ግን ቀዝቃዛ አልነበረም። ለሁለቱ ሃያላን ሃገሮች የጦር ቀጠና ነበርን። አይሲስ የአሜሪካ ፍጡር ይሁንም አይሁን ገፈቱን የምንቀምሰው እኛው ሆነናል። በሰማዕታቱ እልቂት ምክንያት ከገባንበት ብሄራዊ ሃዘን ገና አልተላቀቅንም። ሁኔታው ሰቅጣጭ፣ ድርጊቱ ቅስም ሰባሪ ነውና የሃዘኑ ሸክም በቀላሉ የሚወርድ አይመስልም። ከዚህ ሁሉ ሃዘን በኋላም በአልጃዚራ ቴሌቭዥን ላይ የቀረቡ ወጣቶች ከአገር ቤቱ ኑሮ ወደውጭ መውጣቱን እንደሚመርጡ ተናግረዋል። አሁን ያለውን መረጃ ብቻ ይዞ አይሲስን የፈጠረችው አሜሪካ ናት ብሎ መደምደም ባይቻልም፤ ጥቅሟን ካስጠበቀላት ይህንን ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማትል ያለፉ ተመክሮዎች ይጠቁሙናል። የሌላው ማለቅ፣ መረበሽና መተራመስ ለአሜሪካ ደንታ አይሰጣትም።

[0]http://www.americanthinker.com/blog/2015/02/obama_administration_egypt_bad_iran_good_israel.html
[1]http://www.hangthebankers.com/?s=snowden
[2]http://www.globalresearch.ca/stagecraft-isis-video-execution-of-ethiopians-in-libya-appears-fake/5444466
[3]http://www.infowars.com/former-al-qaeda-commander-isis-works-for-the-cia
[4]http://www.gulf-daily-news.com/NewsDetails.aspx?storyid=381153
[5]http://www.infowars.com/blowback-u-s-trained-isis-at-secret-jordan-base/
[6]https://www.youtube.com/watch?v=QrdDavSw_Fg

ሞት እንካንስ አለ በበላይነህ አባተ

የኢትዮጵያውያኑ በግፍ የፈሰሰ ደም ከወደ እስራኤል ይጣራል፣ ይጮኻል …!! በፍቅር

$
0
0

የምድራችን ግፉአንና ምስኪኖች እንባና ጩኸት፣ ዋይታና ሰቆቃ ምድሪቱን ክፉኛ እየናጣትና እያናወጣት፣ እያስጨነቃት ነው፡፡ በዚህች ክፋት በሰለጠነባት፣ ዓመፃ በነገሠባት ዓለማችን ጆሮን ጭው የሚያደርግ፣ እግዚኦ የአንተ ያለህ! የሚያሰኝ ሌላ ክፉ ወሬን እያየን፣ እየሰማን ነው፡፡ ገና አንዱን ኀዘናችንን በቅጡ ሳንወጣው፣ እንባችን ‹‹የፍትሕ ያለ!›› በሚል በጉንጫን ላይ እየፈሰሰ ባለበት እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ጻድቁ ኢዮብ የኀዘን መርዶን በላይ በላዩ እየሰማን፣ እየተደረበብን ነው፡፡

በምስኪን ሕዝባችን ላይ በደቡብ አፍሪካ፣ በየመን፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በሊቢያ በኾነውና እየኾነ፣ እየደረሰ ባለው ግፍ፣ መከራና ሰቆቃ ተጽናንተን ሳናበቃ፣ እንባችን ገና በጉንጫችን ላይ እያለ ይኸው ከምድረ እስራኤል ደግሞ ወገኖቻችን ደማቸው እንደ ውሻ ደም በቴላቪቭ፣ በአደባባይ እየፈሰሰ መኾኑን ከመገናኛ ብዙኃን እያየን፣ እየሰማን ነው፡፡ ምን ጉድ ነው ይኼ ወገኔ?!

በእርግጥ በዛች የተስፋ ምድር የቤተ-እስራኤላውያኑ አትዮጵያውያን ወገኖቻችን እየደረሰባቸው ያለው ግፍና መከራ ትናንትና የጀመረ አይደለም፡፡ እነዚህ ሰዎች ያችን የተስፋ ምድር ከረገጡ ጊዜ ጀምሮ እምብዛም አልደላቸውም፡፡ ማንነታቸውንና ታሪካቸውን፣ ባህላቸውንና ትውፊታቸውን በተመለከተ የገጠማቸውን ቀውስና ፈታኝ ጉዞ በድል ለመወጣት ዛሬም ብርቱ ትግል፣ ተጋድሎ ላይ ናቸው፡፡

የዘር፣ የታሪክ፣ የሃይማኖት፣ የባህል፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚው ጥያቄ በየፈርጁ እየተነሡና እየተጣሉ እረፍትና ሰላም በናፈቃት በዛች ምድር በየጊዜው የሚታየውና የሚሰማው ኹሉ የምድሪቱን እስትንፋስ የሚገዛ ከመሆን ካለፈም ሰነባብቷል፡፡ ከአይሁዳውያኑ ምድር የሚሰማ ዜና ኹሉ የምድሪቱን ልብ ምት ቀጥ የሚያደርግ እስኪመስል ድረስ ዜናው ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ፣ ከአውሮፓ እስከ ኤዥያ፣ ከቻይና እስከ ሕንድ፣ ከጃፓን እስከ አውስትራሊያ የሚናኝበት ፍጥነቱ አስገራሚም፣ ደናቂም ነው፡፡

የምድር ኹሉ ዓይን ማረፊያና የዓለማችን ፖለቲካዊ ትኩሳት ማዕከል በኾነችው እስራኤል ከሰሞኑን ደግሞ በሌላ መልክና ገጽታ ኢትዮጵያውያኑ ቤተ-እስራኤላውያን ኢሰብአዊ የኾነ ግፍና መድሎ እየደረሰባቸው ነው፡፡ በቴላቪቭ ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ኢትዮጵያውያን ከእስራኤል ፖሊሶች ጋር በመጋጨታቸው የተነሣ ደማቸው እንደ ውሻ ደም በእስራኤል ምድር እንዲፈስ ኾኗል፡፡

እነዚህ ወገኖች ጥቁር በመሆናቸው የተነሣ የዘር መድሎ ሲደረግባቸው፣ ለሕክምና በሚል ሰበብ የተቀዳ ደማቸውን ተጸይፈውት በመሬት ላይ ተደፍቶ ከአፈር ሲቀላቀልና ሲላቁጥ፣ በቅርቡም ቤተ እስራኤላውያኑ ሴቶች እንዳይወልዱ ዘራቸው እንዲመክን የተደረገበትን ሴራ፣ ኢሰብአዊና ጸያፍ የኾነውን አሰቃቂ ዜና ከዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ሲቀባበሉት እየተሳቀቅንና እያዘንን ሰምተናል፡፡

ግና የእኛ የኢትዮጵያውያን መከራችን፣ ዋይታችን፣ ሰቆቃችን ማባሪያ፣ ማቆሚያ የሌለው የመሰለው ለምን ይኾን?! እንዲህ በሔድንበት ምድር ኹሉ ክብር የሌለን፣ የተዋረድን፣ ያየን ኹሉ ፊቱን የሚያጠቁርብን፣ ግንባሩን የሚከሰክስብን፣ በረገጥናት ምድር ኹሉ እንደ ቃየል የጨካኞች የበቀል ሰይፍ የሚከተለን፣ የሚያሳደድደን፣ ጦርና ጎራዴ የሚመዘዝብን የኾነበት ምክንያቱ ምን ይኾን?! እንዲህ በላያችን ላይ ሰማይ ናስ፣ ምድሪቱም ብረት የኾነችብን ምክንያቱ ምንድን ነው፣ እኛ ምን ሕዝቦች ነን?!

ይህን ጥያቄ፣ ይህን ለዘመናት እንቆቅልሽ የሆነ በኢትዮጵያችን ላይ የተጣበቀብንን መከራ፣ ውርደትና ግፍ በተመለከተ ሃይማኖተኛውም፣ ፖለቲከኛውም፣ የተማረውም ያልተማረውም ኹላችንም በአንድነት ይህን ጥያቄ መጠየቅ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ግፋችን እንዲህ የበዛው፣ ተንከራታችና መፃተኛ የኾነው፣ እንባችን ማቆሚያ ያጣው፣ ተነሣን ስንል የምንወድቅበት፣ አሁንስ ነጋልን ስንል የሚጨልምበት፣ ተስፋችንና ብሩህ ነጋችን እንዲህ የራቀበትን ምክንያቱን ለማወቅ ራሳችንን መጠየቅ፣ አሁንም መጠየቅ!!

በምድረ እስራኤል በወገኖቻችን ላይ ወደደረሰባቸው ግፍ ጉዳይ ስንመለስም ከኹለቱ አገራትና ሕዝቦች ከታሪክና ከሃይማኖት አንጻር አንዳንድ እውነታዎችን ማነሳት ግድ ይለናል፡፡ በአንድ ወቅት አሁን በሕይወት የሌሉት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚ/ር የነበሩትና በቅጽል ስማቸው ‹‹ሻሮን ዘቡል ዶዘር›› በሚል የሚታወቁት ኤለን ሻሮን፣ አገራቸውን ሲጎበኙ ለነበሩት ለቀድሞው ጠቅላይ ሚ/ር ለአቶ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያውያንና እስራኤላውያንን በተመለከተ እንዲህ ብለዋቸው ነበር፡፡ ‹‹የኹለቱ አገራትና ሕዝቦች ሺ ዘመናትን ያስቆጠረው ግንኙነታቸው ጥልቅ የኾነ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ መሠረት ያለው ነው፡፡››

በእርግጥ በሃይማኖትና በታሪክ፣ በባህልና በትውፊት የተሳሰረ፣ ዘመናትን የተሻገረ በጋራ የሚጋሩት ማንነትና ታሪክ ባላቸው በኢትዮጵያና በእስራኤላውያን መካከል ይህ መኾኑ አሳፋሪም፣ እጅግም አሳዛኝ ነው፡፡ እስራኤላውያን ለነጻነታቸው ብርቱ የኾነ መሥዋዕትነትን ከከፈለው፣ የፈርኦን የልጅ ልጅ ከመባልና ከግብጽ ቤተ መንግሥት ድሎትና ደስታ ይልቅ ግፉአንን ምስኪን ከኾኑ ሕዝቦቹ ጋር መከራን መቀበል ከመረጠው ከነጻ አውጪያቸው ከትሑቱ ነቢያቸው፣ ከሙሴ ጀምሮ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የታሪካቸው፣ የማንነታቸው ማዕከልና ማጠንጠኛ ነበር፣ ነውም ብል እምብዛም ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡

አይሁዳውያኑ ለነጻነታቸው ባደረጉት ለአርባ ዓመት በዘለቀው የበረኻ ጉዞአቸው ኢትዮጵያዊቱን ያገባው ነጻ አውጪው ሙሴ፣ በሚስቱ አማካኝነት የኢትዮጵያዊነት ክቡር ማንነትን ተካፍሏል፡፡ ከፈጣሪ ዘንድ የተቸረውን የኢትዮጵያዊነት የነጻነት ክቡር መንፈስ፣ ግዙፍ ታሪክ፣ ገናና ሥልጣኔና ሕያው ቅርስ ሙሴን ልቡን በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ማንነት ውስጥ እንዲሸፍት እንዳደረገውም ጥርጥር የለውም፡፡

እናም የአይሁዳዊው ሙሴና የኢትዮጵያዊቱ ጋብቻ መሠረቱ የወረት ፍቅርና ዘርን የመተካት ዓላማን ብቻ ያነገበ አልነበረም፡፡ ጋብቻው ከሥጋዊነት ባለፈ ጥልቅ የኾነ መንፈሳዊ መሠረትና ትርጓሜ ያለው ነበር ማለትም ይቻላል፡፡ ይህን አሁን ለመተንተን የምሞክረው አይሆንም፡፡ ግና በወቅቱ ይህ የሙሴ ጋብቻ ብርቱ የኾነ ቁጣን አስነሥቶ ነበር፡፡ ከእኛ ዘርና ሃይማኖት ውጭ ጋብቻ ምን ሲባል ይታሰባል በሚሉት በወንድሙ አሮንና በእህቱ ማርያም በኩል ሙሴ የበረታ ተግሣጽና ቁጣ ነበር የገጠመው፡፡

ከወገናችን ውጭ የተደረገ ጋብቻ ነው በሚል ተነሣውን ግብዞቹን የዘር፣ የማንነት ጥያቄ መሠረት አልባ፣ እርባና ቢስና ውድቅ ያደረገ ምላሽ ከሰማይ አምላክ ዘንድ ተሰጣቸው፡፡ በእነዚህ በሙሴ ተቃዋሚዎች ላይ ከአምላካቸው ያሕዌ ዘንድ የመጣው ቁጣ በለምጽ እንዲነዱ አደረጋቸው፡፡ ይህን አይሁዳውያኑን ግብዝነት ከንቱ ያደረገ ሌላም እውነታ በታሪካቸው ኾኗል፡፡ እስቲ በአጭሩ እንየው፡፡

ከአሕዛብ ወገን የኾነችው ሞዓባዊቷ ሩት አይሁዳዊት ምራቷን ኦርፋን ሕዝብሽ ሕዝቤ፣ አምላካችሁ አምላኬ ይኾናል፡፡ እኔና አንቺን ሞት እንኳን ቢሆን አይለየንም በሚል የበረታ እምነት፣ ጽኑ ፍቅርና ተስፋ በኢየሱስ ክርስቶስ ዘር ግንድ ውስጥ የገባች ብቸኛዋ ሴት ለመኾን በቅታለች፡፡ እናም እውነታው ሲከፈት፣ ሐቁ ሲገለጽ ጥያቄው አይሁዳዊ የመኾን፣ የዘር ወይም የማንነት ጉዳይ አልነበርም፡፡ ይልቁንም ሞት እንኳን የማይረታው ፍቅር፣ የጸና እምነት፣ ብርቱ ትዕግሥት፣ ዘላለማዊና ሰማያዊ ተስፋ እንጂ!! ሙሉ ታሪኩ በመጽሐፈ ሩት ውስጥ በዝርዝር ተጽፎ ይገኛል፡፡

በሙሴና በልጆቹ ደም ውስጥ የሠረጸው የኢትዮጵያዊነት ነጻነት፣ ውበትና ጥበብ እዛ ጋር ብቻ አልቆመም፡፡ በዝና በሰማችው ጥበቡና ማስተዋሉ በጥበብ ፍቅር የወደቀችው ኢትዮጵያዊቷ ንግሥተ ሳባ ጥበብን ፍለጋ አገሯንና ሕዝቦቿን ጥላ ተሰዳ ነበር፡፡ ይህን በጆሮ የሰማችውን የንጉሥ ሰለሞንን ጥበብ በዓይኗ አይታ ለማረጋገጥ ከብዙ ጓዝና ስጦታ ገር ወደ እስራኤል ምድር የተጓዘችው ሳባ ‹‹ባየችውና በሰማችው ነገር ነፈስ አልቀረላትም፡፡›› ነበር ይለናል ቅዱስ መጽሐፍ፡፡

ይህች የጥበብ ምርኮኛ፣ በጥበብ ፍቅር የተነደፈች ኢትዮጵያዊት ንግሥት በዛ በሰለሞን ጥበብና ማስተዋል ውስጥ አሻግራ ያየቸው፣ በሩቅ የተሳለመችው፣ ሐዋርያው ቅዱስ ጳወሎስ ለቆላስያስ ክርስቲያኖች በጻፈው መልእከቱ አስረግጦ እንደተናገረው፣

‹‹የእግዚአብሔርን ምሥጢር፣ የተሰወረ የጥበብና የእውቀት መዝገብ የኾነውን››፡- የዳዊትን ልጅ፣ የቅድስት ድንግል ማርያምን ልጅ፣ የሕያው እግዚአብሔርን ልጅ፣ የሰው ልጅ ተብሎ የተጠራውን ኢየሰሱ ክርስቶስ ነበር፡፡ በመዋዕለ ሥጋዌውም ኢየሱስ እንዲህ ሲል ተናገረ፡፡ ‹‹… ንግሥተ ዓዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰለሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፤ እነሆም ከሰለሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ፡፡ (ማቴ. ፲፪፣፵፪)

በንግሥተ ሳባ ውስጥ በሩቅ ቆመን፣ በሩቅ ኾነን የተሳለምነውን፣ የናፈቅነውና ተስፋ ያደረግነውን የእግዚአብሔርን ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን በኋለኛው ዘመን ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ በወንጌላዊው ፊሊጶስ አማካኝነት በጥምቀት ተቀበልነው፡፡ ያች በጥበብ ፍቅር የወደቀች ኢትዮጵያና ሕዝቧም በኢየሩሳሌም ሊሰግድና መሥዋዕት ሊያቀረብ በኼደው በጃንደረባው፣ የዘላለም ኪዳን ተስፋ በኾነው በኢየሱስ ክርስቶስ ናፍቆቷ ፍጻሜውን አገኘ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሀ ሀበ እግዚአብሔር!›› እንዲል፡፡ ንጉሥ ዳዊት፡፡

ከዚህ እውነታ ጋር መታረቅ፣ ዛሬም ከዚህ እውነታ ጋር መቆም ያቃታቸው ‹‹የእፉኝት ልጆች›› ግን ዛሬም ዘር መዘው፣ አጥንት ቆጥረው፣ የቆዳ ቀለም ለይተው ደም እያፈሰሱ ነው፡፡ የአብርሃም ልጆች ነን ይላሉ፤ ግና የአብርሃምን ሥራ ለመሥራት ፈጽመው አይወዱም፣ አይፈቅዱምም፡፡ እናም ዛሬም አባቶቻቸው እንዳደረጉት ኹሉ ደምን በግፍ ያፈሳሉ፡፡ ‹‹በምድርህ ላይ በሚኖሩ ስደተኞችና መፃተኞች ግፍን አታድርግ፣ አንተም በአሕዛብ ምድር መፃተኛና ስደተኛ የኾንከብትን ጊዜ አስብ፡፤›› የሚለውን የአምላካቸውን ማስጠንቀቂያና ማሳሰቢያ ረስተውታል፣ ዘንግተውታል፡፡

እነዚህ አይሁዳውያን ሕዝቦች ለዘመናት እንደ ጨው ዘር በተበተኑበት ዓለም ኹሉ መጠጊያና መድረሻ የተነፈጋቸው፣ በምድር ዙርያ ኹሉ ተበትነው፣ ፍዳቸውን ሲያዩ የነበሩ፣ መከራና ግፍ የጸናባቸው ሕዝቦች፣ በቁማቸው ቆዳቸው እየተገፈፈ፣ ሰውነታቸው ስብ እየቀለጠ ለሳሙና መስሪያነት የዋለ፣ በሂትለር ትእዛዝ ስድስት ሚሊዮን ሕዝባቸው በግፍ ያለቁባት እስራኤል ዛሬ ያን የትናንትና ታሪካቸውን ዘንግተው በምድራቸው መፃተኛ በኾኑ ሕዝቦች ላይ እንዲህ ዓይነቱን ግፍ መፈጸማቸው ወዮው ያሰኛል፡፡

እስቲ መቼም ሰሚ አገኝንም አላገኘንም አንድ ነገር እናድርግ፡፡ በአገራችንም ኾነ በዓለም ዙርያ ኹሉ በሕዝባችን ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍና በደል ይቆም ዘንድ ድምፃችንን ከፍ አድርገን እናሰማ፡፡ የአንድ ነጭ ሞት ዜና ከጫፍ እስከ ጫፍ በሚናኝነበትና ቁጣ በሚቀሰቅስባት፣ ፍትሕ በጎደላት በዚህች በምንኖርባት ዓለም አፍሪካዊ፣ ኢትዮጵያዊ ወይም ጥቁር በገፍ በሚታረድባት ዓለም፣ የጥቁር ዘር ነፍስን ባለቤትና ጠያቂ የሌላት አድርጎ መቁጠር የግፍ ግፍ፣ ኢሰብአዊነትና ወደር አልባ የኾነ ጭካኔ ነውና ኹላችንም ድምፃችንን እናሰማ፡፡

መቼም በነጩም ኾነ በጥቁር ወንድሞቻችን ደም ስር ውስጥ የሚፈሰው ደም ያው ቀይ መኾኑን ይዘነጉታል ብልን አናስብም፡፡ በዘረኝነት ክፉ መርዝ ፈጽሞ የነተበ፣ ብኩን የኾነ ግብዝ ማንነታቸው ወደ ፍቅር፣ ወደ እውነት፣ ወደ ፍትሕ መንገድ ይመለስ ዘንድ ለእነዚህ ወገኖች እንጸልይላቸኋለን፣ እንመኝላችኋለንም፡፡ እስከዛው ግን ፍቅርን፣ ሰላምን፣ እውነትንና ፍትሕን በተጠማች ምድር የወገኖቻችን፣ የግፉአንና የምስኪኖች እንባና ደም እስኪታበስ ድረስ ለፍቅር፣ ለሰላም፣ ለእውነትና ለፍትሕ እንባችን ምድሪቱን አልፎ ሰማዩን እስኪያናውጥ ድረስ መጮኻችንን አናቋርጥም፡፡
ሰላም! ሻሎም!

የተቀዳደደዉ የዜጐች ነጻነት በኢትዮዽያ በመሃመድ አሊ

አውነቱ ይውጣ! –መስፍን ወልደ ማርያም

$
0
0

ሴቶችን በወንዶች ፊት፣ ወንዶችን በሴቶች ፊት ልብስ እያስወለቁ የአካላቸውን ክፍሎች ሁሉ ለማየት የሚያስችል አንቅስቃሴ አንዲሠሩ ማስገደድ በሽተኞችን ያስደስታል፤ የምርመራ ዘዴ ግን አይደለም፤ ውርደት እንዲሰማቸው ከሆነ በወራዶች ሰዎች ፊት የምን መዋረድ አለ? ወራዶች እነሱ ደረጃ ላይ ከእነሱ ጋር ያስተካክላሉ አንጂ አያዋርዱም፤ በሌላ አነጋገር ወራዶች አያዋርዱም፤ ወራዶቹ ደንቆሮዎችም ሆነው ነው እንጂ ልብስ የሚያስወልቁ እነሱ ብቻ አይደሉም፤ ሀኪሞችም ልብስ አስወልቀው፣ አጋድመው በጣታቸውም ሆነ በመሣሪያ የፈለጉትን የአካል ክፍል አንደፈለጉ ያደርጉታል፤ ወራዶቹና ደንቆሮዎቹ ከሚያደርጉት የሀኪሞቹ የሚለየው ሀኪሞቹ ሰዎችን ለማዳን ሲሉ ነው፤ ወራዶቹና ደንቆሮዎቹ ግን የራሳቸውን ሱስ ለማርካት፣ የራሳቸውን ህመም ለማስታገስ ነው፤ ወራዶቹንና ደንቆሮዎቹን ከመለዮአቸው አራቁቻቸዋለሁ!

ከነውር በቃላት ወደነውር በተግባር፣ ያውም በመሥሪያ ቤት! ዱሮ ዱሮ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቲያትር ፊት ለፊት የአንድ ኢጣልያዊ ቡና ቤት ነበር፤ እዚያ ውጭ ተቀምጠን ቡና ስንጠጣ አንዲት ውብ ሴት ወደጸጉር መሥሪያው ቤት ስትመጣ የሁላችንም ዓይኖች እየዘለሉ እስዋ ላይ ዐረፉ፤ ከሦስታችን አንዱ ስለሴትዮዋ የወሲብ ችሎታ በዝርዝር መናገር ሲጀምር ሁለታችን ተያየንና አፈርን፤ ጨዋታው የጣመለት መስሎት ሲቀጥል የሕግ ባለሙያ የሆነ ጓደኛዬ አቋረጠውና ‹‹ስማ! ይህን ጊዜ እናትህ በአንድ ቦታ ስታልፍ አንዱ እንዳንተ ያለ ስለስዋ ችሎታ ያወራ ይሆናል!›› አለው፤ ሊጠጣ ወደአፉ ያስጠጋውን ስኒ ቁጭ አደረገና ተነሥቶ ሄደ፡፡

ሥልጣን ተሰጥቷቸው ሴቶችን ልብስ እያስወለቁ ምርመራ ነው የሚሉ በእናቶቻቸውና በእኅቶቻቸው ላይ ሊደርስ እንደሚችል አይገነዘቡም ይሆናል፤ ደንቆሮ የሚያደርጋቸውም ይኸው ነው፤ የአንዱ እናት አንድ ቦታ ላይ ራቁትዋን ቆማ በሽተኞች ተሰብስበው ሲስቁባት፣ በሌላ ቦታ ደግሞ ጓደኛው የእሱን እናት ወይም እኅት ያንኑ እያደረገ ያስቅባት ይሆናል፤ አንተ በእኔ እናትና በእኔ አኅት አስቅባቸው፤ እኔ ደግሞ በአንተ እናትና በአንተ እኅት አስቅባቸዋለሁ፤ ይህንን እየሠራን ኑሮአችንን እናቃናለን፤ እቤታቸው ሲገቡና ከእናቶቻቸውና ከእኅቶቻቸው ጋር ሲቀመጡና ሲበሉ (?!) ሰው ይመስላሉ፤ እነዚያም ግፉ የተፈጸመባቸው እናቶችና እኅቶች ‹ነውራቸውን› ምሥጢር አድርገው ለሰው ስለማይናገሩ ግፈኞችና የግፍ ሰለባዎች አብረው ይበላሉ!
አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ አንዳንድ ሴቶች የደረሰባቸውን ተናገሩ፤ አሁን ያፍራሉ የተባሉት እውነቱን ራቁቱን አወጡትና ከእፍረት ነጻ ወጡ! እውነቱ ሲወጣ የሚያፍረው ማን ነው? ደካማዎቹና የግፍ ሰለባ የነበሩት በጭራሽ አያፍሩም፤ የሚያፍሩት ግፈኞቹ ናቸው፤ የሚያፍሩት የሕዝብን አደራ በማቆሸሻቸው፣ በሥልጣን በመባለጋቸው፣ የሕዝብንና የአገርን ክብር በማዋረዳቸው ያፍራሉ፤ ኅሊናቸው በየቀኑ ነፍሳቸውን አርባ ሲገርፋት እየሳሳች እንቅልፍ ትነሳቸዋለች፡፡
ለመሆኑ በአገሩ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ጳጳሳት፣ መነኮሳት፣ ቀሳውስት — ሼሆች፣ ሽማግሌዎች በአገሩ የለንም?
መስፍን ወልደ ማርያም

Viewing all 1809 articles
Browse latest View live


<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>