የኢትዮጵያ ፈዴራል ሕገ መንግስት አንቀጽ 46 «ክልሎች የሚዋቀሩት በሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ የማንነት እና ፈቃድ ላይ በመመስረት ነዉ» ይላል። አንቀጽ 47 ደግሞ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሩፑብሊክ አባላት የሆኑቱን ክልሎች ይዘረዝራቸዋል። እነርሱም የትግራይ፣ የአፋር ፣ የአማራ፣ የሱማሌ፣ የቤኔሻንጉል/ጉሙዝ፣ የደቡብ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ፣ የጋምቤላ ሕዝቦች እና የሃረሪ ሕዝብ ክልሎች ናቸው።
የዚህን የፌደራል ክልልን በተመለከተ በክልሎች እየታዩ ያሉትን አንዳንድ ሁኔታዎች ለማሳየት እንሞክራለን። ከትልቁ ክልል ኦሮሚያ እንጀምር።
ኦሮምኛ የማይናገሩትን የማግለል ዘረኛ አሰራር
ኦሮሚያ ክልል ዉስጥ ሃያ ዞኖች አሉ። ሶስቱ «ልዩ ዞኖች» ይባላሉ። ናዝሬት/አዳማን ያካተተ፣ የአዳም ልዩ ዞን፣ ጂማን ያካተተው፣ የጂማ ልዩ ዞን እና የቡራዮ ልዩ ዞን ናቸው። በነዚህ ዞኖች የመጀመሪያ ቋንቋቸው አፋን ኦሮሞ የሆኑቱ ቁጥራቸው ከ45 በመቶ በታች ነዉ። በአዳማ 26%፣ በጂማ 39% እና በቡራዮ 44% ናቸው።
በአሥራ ሶስቱ ሌሎች የኦሮሚያ ዞኖች አፋን ኦሮሞ የመጀመሪያ ቋንቋቸው የሆኑ ከ90 % በታች ናቸው። እነዚህም ምስራቅ ሸዋ ( 69%)፣ ጉጂ (77%) ፣ አርሲ ( 81%)፣ ሰሜን ሸዋ ( 82%)፣ ደቡብ ምስራቅ ሸዋ (84%)፣ ሆሮ ጉድሩ ወለጋ (85%) ፣ ምእራብ አርሲ (87%)፣ ምስራቅ ወለጋ ( 88%) ፣ ምእራብ ሃረርጌ (89 %)፣ ኢሊባቡር (90%) ፣ ጂማ – የጅማ ከተማ አካባቢ ( 90%)፣ ባሌ (90%)፣ ቦረና (90%) ናቸው። እንግዲህ ከሃያ የኦሮሚያ ዞኖች፣ በአሥራ ስድስቱ፣ ምን ያህል አፋን ኦሮሞ የመጀመሪያ ቋንቋቸው ያልሆኑ ኢትዮጵያዉያን በስፋት እንዳሉ እያየን ነዉ። በአራት የኦሮሚያ ዞኖች፣ በአፋን ኦሮሞ አፋቸዉን የፈቱ፣ ከዘጣና ሶስት በመቶ በላይ ናቸው። እነርሱም ምእራብ ወለጋ (97%) ፣ ምእራብ ሸዋ (93%)፣ ምስራቅ ሃረርጌ፣ (94%)፣ ቀለም ወለጋ ( 94%) ናቸው።
አሁን በሥራ ላይ እየተተገበረ ያለው የኦሮሚያ ክልል ሕገ መንግስት አንቀጽ 33 «በክልሉ ዉስጥ ነዋሪ የሆኑና የክልሉን የሥራ ቋንቋ የሚያውቅ ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ በማንኛዉም የክልሉ መንግስታዊ ወይም ሕዝባዊ ሥራ ተመርጦ ወይም ተቀጥሮ የመስራት መብት አለዉ።» ይላል። አንቀጽ 5 ደግሞ « ኦሮምኛ የክልሉ መንግስት የሥራ ቋንቋ ይሆናል። የሚጻፈዉም በላቲን ፊደል ነው» ይላል።
74% የአዳማ፣ 61% የጂማ ከተማ ፣ 56% የቡራዩ ዞን፣ 31% የምስራቅ ሸዋ ዞን፣ 23% የጉጂ ዞን ፣ 25% የሆሮ ጉድሮ ወለጋ ዞን፣ 23% የምእራብ አርሲ ዞን … ነዋሪዎች የመጀመሪያ ቋንቋቸው አፋን ኦሮሞ ባላመሆኑ፣ አፋን ኦሮሞ ካልተማሩ በቀር፣ የመመረጥ፣ በኦሮሚያ ክልል የመስራት መብት የላቸውም። ይህም አማርኛና ሌሎች ቋንቋዎች የሚናገሩ፣ በኦሮምያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንን እንደ ሁለተኛና ሶስተኛ ዜጋ እንዲቆጠሩ የሚያደርግ ነዉ። በብሄረሰብ መብት ስም የግልሰበ መብት እየተረገጠ ነዉ።
«ኦሮሚያ ፈርስት» የሚል እንቅስቃሴን የሚመራው ጃዋር ሞሃመድ፣ አንድ ወቅት «Ethiopians Out from Oromia» የሚል መፈክር ያሰማበትን ቪዲዮ ተመልክቻለሁ። ጃዋር በአጭሩ አነጋገር፣ ኦሮሚያ የኦሮሞዎች ብቻ እንደሆነችና ሌሎች «ኦሮሞ» ያልሆኑ፣ በኦሮሚያ ዉስጥ እንግዶች፣ ኦሮሞዎች ሲፈቅዱላቸው ብቻ ሊኖሩ የሚችሉ እንደሆኑ ነው የነገረን። ይህ የጃዋር አባባል፣ ብዙዎችን እንዳስገረመ ተመልክቻለሁ። ነገር ግን አንድ የዘነጋነው ነገር ቢኖር፣ ይህ የጃዋር አባባል ፣ ጃዋር የፈጠረዉ ሳይሆን በኦሮሚያ በአሁኑ ሕግ መንግስት፣ በሰነድ የተቀመጠ እንደሆነ ነዉ።ይህ አይነቱን ዘረኛ የጃዋር አባባል፣ የኦሮሚያ ክልል «ሕግ» ይደግፈዋል። ስለዚህ ትኩረታችንን ከጃዋር አዙረን ወደ ኦሕደድ/ኢሕአዴግ እንዲሁም ኦነግ ማዞር አለብን።
የኦሮሚያ ክልል ሕገ መንግስት አንቀጽ ስምንት «የኦሮሞ ሕዝብ የክልሉ የበላይ ስልጣን ባለቤት ሲሆን ..» ሲል የኦሮሚያ ባለቤት «ኦሮሞው» ብቻ እንደሆነ ነው ያስቀመጠው።
ኦሮምኛ ተናጋሪው በኢኮኖሚ እንዲጎዳ ያደረገ ጎጂ ፖለቲካ
የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ፖሊሲን ካየን ደግሞ፣ አዲስ አበባ አካባቢ ያሉ እንደ አዳማ/ናዝሬት ያሉ ቦታዎች ሕዝቡ ተቃዉሞ ስላስነሳ፣ በዚያ ተማሪዎች አማርኛም ከአፋን አፋን ኦሮሞ ጎን ለጎን እንዲማሩ ከመደረጉ በስተቀር፣ በኦሮሚያ የሚኖሩ ተማሪዎች አማርኛ እንዲማሩ አይደረግም። አማርኛ ማንበብና መጻፍ አይችሉም።
አንድ የግል ባለሃብት ከአዲስ አበባ ሄዶ አንድ ኩባንያ በአንድ የኦሮሚያ ከተማ ይመሰርታል። ሰራተኞች ቀጥሮ ያሰራል። ሰራተኞቹ ስራቸዉን በተመለከተ፣ ሪፖርት ማቅርብ ሲጠበቅባቸው ሪፖርት ሳያቀርቡ ይቀራሉ። አለቃቸው ያስጠራቸዉና ይጠይቃቸዋል። ሪፖርታቸውን በቃል ያቀርቡለታል። «እሺ በፋይል እንዲቀመጥ በጽሁፍ አምጡልኝ» ሲላቸው፣ ማንገራገር ጀመሩ። «ጌታዬ እኛ አማርኛ መጻፍ አንችልም። በቁቤ እንጻፈዉና ከፈለጉ ያስተርጉሙት፤ ወይም እኛ አስተርጉመን እንመጣለን» ይሉታል። ሰዎዬዉ ባንድ በኩል ቢናደድም፣ በሌላ በኩል አዘነ። ቢዝነስ ነዉና፣ ለስራው ብቃት ከሌላቸው ሰራተኞቹ ማባረር ግድ ሆነበት።
አማርኛን የመጥላት የኦህደድ እና ኦነግ ፖለቲካ ፣ ዜጎች አፋን ኦሮሞን ያዉም በቁቤ ብቻ እንዲማሩ በማድረግ፣ ትልቅ የኢኮኖሚ ጉዳት በ«ኦሮሞዎች» ላይ አድርሷል። እዚህ ላይ «ብቻ» የሚለውን ቃል እናስምርበት። በትግራይ ከአንደኛ ክፍል ጀመሮ ከትግሪኛ ጎን አማርኛ እንዲማሩ ይደረጋል። የኦሕደድ ባለስልጣናት እነ አባ ዱላ ገመዳ፣ ኩማ ደመቅሳ የመሳሰሉት ልጆቻቸዉን የሚያስተምሩት በአዲስ አበባ ሃሪፍ ትምህርት ቤቶች ነዉ። ሃብታም የሆኑና አቅሙ ያላቸው ልጆቻቸውን ወደ አዲስ አበባ እየላኩ ያስተምራሉ። ለምን ቁቤ ብቻ ተምረው ልጆቻቸው የትም እንደማይደርሱ ስለሚያወቁ።
የግል ኢንቨስተሮች የሥራ ቋንቋቸው በኦሮሚያም ሳይቀር በብዛት አማርኛ ነዉ። በናዝሬት፣ በጂማ በመሳሰሉት ቦታዎች ሂዱ፣ የንግድ ተቋማት፣ የግል መስሪያ ቤቶች .. የሚጠቀሙት አማርኛን ነዉ። ከክልል መንግስት ጋር አንዳንድ ደብዳቤዎች መላላክ ካስፈለገ ፣ የክልሉን የአፋን ኦሮሞ ብቻ ፖሊስ ሕግን ለማክበር ፣ ተርጓሚ ይቀጥራሉ።
በኢትዮጵያ ካሉ 9 ክልሎች በአራቱ (አማራዉ፣ ደቡብ፣ ጋምቤላና ቤኔሻንጉል ጉሙዝ) ክልሎች፣ እንዲሁም በአገሪቷ መዲና አዲስ አበባ፣ በድሬደዋ የሥራ ቋንቋ አማርኛ ነው። የፌደራልም ቋንቋ አማርኛ ነዉ።
በመሆኑም ኦሮሚያ ያለው የቁቤ ትዉልድ፣ በፌደራል መንግስት ዉስጥ ተቀጥሮ የመስራት አቅሙ ዜሮ ነዉ። እንደ ባህር ዳር፣ አዋሳ፣ ድሬደዋ፣ አዲስ አበባ በመሳሰሉ ታላላቅ ከተሞች ለመኖርና ለመስራት፣ ለመቀጠር በጣም ይቸገራል። በአጭሩ፣ ይህ የኦሮሚያ ክልል አሰራር፣ የኦሮሚያ ተማሪዎች፣ በኢኮኖሚ እንያድጉና እንዳይሻሻሉ ትልቅ ማነቆ ነው እየሆነባቸው ያለዉ። በሌሎቹ ክልል ካሉ ጋር ሲወዳደሩ ወደኋላ ቀርተዋል። ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የኦነግ መሪዎች ልጆቻቸው በበርሊን፣ ሚኒሶታ …በመሳሰሉ ቦታዎች እያስተማሩ ነዉ። አማርኛም ባያወቁ፣ እንግሊዘኛ እስካወቁ ድረስ ችግር አያጋጥማቸዉም። የኦህደድ መሪዎች ልጆቻቸውን ሃሪፍ ትምህርት ቤቶች ነዉ በአዲስ አበባ የሚያተምሩት። ድሃዉና ምስኪኑ የኦርሚያ ተማሪ ግን፣ አጥር ታጥሮበት፣ በአጉል የኦሮሞ ብሄረተኘንት ስም እንዲተበተብ ተደርጎ ጉዳት እየደረሰበት ነዉ።
ይህ በኦሮሚያ የሚኖሩት ወገናችን በኢኮኖሚ፣ በትምህርት ፖሊሲ ረገድ እየደረሰባቸው ካለው ግፍ በተጨማሪም፣ ኦነግ እየተባሉ በሺሆች የሚቆጠሩ እየታሰሩና እየተሰቃዩ ናቸው። ሕወሃት/ኢሃዴግ በአንድ በኩል እነሌንጮን፣ ቀንደኛ ኦነጎችን፣ እያባበለና እያቀፈ፣ በሌላ በኩል የነሌንጮ ደጋፊ ናችሁ እያለ ሰላማዊ ዜጎችን ያስራል።
ታዲያ መፍትሄዊ ምንድን ነዉ ? አራት ነጥቦች ላስቀምጥ፡
1. ኢትዮጵያዉያን አፋቸዉን በየትኛው ቋንቋ ነዉ የፈቱት የሚለዉን ጥያቄ ብንጠይቅ ፣ በአንደኝነት የሚቀመጠዉ ኦሮምኛ ነዉ። በበርካታ ዞኖች ከዘጠና በመቶ በላይ ኦሮምኛ የሚነገርባቸው ቦታዎች አሉ። 33.8 % የሚሆነው ሕዝባችን አንደኛ ቋንቋዉ አፋን ኦሮሞ ነዉ። 29.36% የሚሆነው ህዝብ አማርኛ አንደኛ ቋንቋዉ እንደመሆኑ፣ አማርኛን ወይንም ኦሮምኛን እንደ አንደኛ ቋንቋ የሚናገሩ 63.2% ይደርሳሉ። በመሆኑም ኦሮሞኛ ከአማርኛ ጎን የፌደራል ቋንቋ ቢሆን ትልቅ ጥቅም ይኖረዋል። ቢያንስ አማርኛ ፊደል የማያነበው፣ የጠፋው አንዱ የቁቤ ትዉልድ በፌደራል መሥሪያ ቤቶች የመስራት እድል ያጋጥመዋል።
2. በሁሉም ክልሎችና ወረዳዎች፣ በአካባቢዉ ከሚነገረው ቋንቋ ጎን ለጎን፣ ተማሪዎች አማርኛ እንዲማሩ መደረግ አለበት። አማርኛ እንደ አንደኛ ቋንቋ 29.3% የሚሆነው ሕዝብ ይናገረዋል። እንደ ሁለተኛ ቋንቋ ደግሞ፣ ከ30፣ 40 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝብ ሊናገረው ይችላል ብዬ አስባለሁ።በመሆኑም አማርኛ ማወቅ ጥቅም አለው። ቋንቋ በአጠቃላይ ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም። አማርኛን መማር ኦሮሞኛን አይጎዳም። የኦሮሞ መሪ ነን የሚሉ ፖለቲከኞች፣ ለራሳቸው ልጆች እንዳሰቡት፣ ለተቀረዉም የኦሮሞ ልጅ ሊያስቡ ይገባል ባይ ነኝ።
እነርሱ አቀላጥፈው አማርኛ መናገር፣ ማንበብ መጻፍ እንደሚችሉትም ሌላዉን እነርሱ ታገኙትን እድል ማሳጣት የለባቸውም። እስቲ አስቡት አሁን አባ ዱላ አማርኛ መጻፍና ማንበብ ባይችል ኖሮ የፓርላማ አፈጉባኤ ይሆን ነበር ? ዶር ነጋሶ ፕሬዘዳነት መሆን ይችሉ ነበር ? እያልን ያለነዉ እኮ የኦሮሞ ወጣት፣ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ፣ አቶ ኩማ ደመቅሳ፣ ዶር ዲማ ነግዎ፣ ጀነራል ከማል ገልቹ ፣ ዶር መራራ ጉዲና ያገኙት እድል ያግኙ ነዉ። አፋን ኦሮሞም ይማሩ፤ አማርኛም ይማሩ።
3. የኦሮሚያ ክልል መንግስት አማርኛን ከኦሮሞኛ ጎን የሥራ ቋንቋ ማድረግ አለበት። ኦሮሞኛ የማይናገር በክልሉ አስተዳደር ዉስጥ የመስራት መብቱ ሊጠበቅለት ይገባል። በኦሮሚያ 95% ነዋሪዉ ኦሮሞኛ የሚናገር ቢሆን፣ እሺ አንድ ነገር ነዉ። ግን ከ 15% በመቶ በላይ ሕዝብ አንደኛ ቋንቋም ኦሮሞኛ ባልሆነበት፣ «አፋን ኦሮሞ ብቻ ወይንም ሞት» ማለት ትልቅ ስህተት ነዉ። ዘረኝነትም ነዉ። በክልሉ ዋና ከተማ አዳማ/ናዝሬት እንኳን ፣ አንድ አራተኛ ሕዝብ ብቻ ነው ኦሮሞኛ የሚናገረው።
4. ናዝሬት/አዳም እና ጂማ የመሳሰሉ እንደ አዲስ አበባና ድሬደዋ፣ ለጊዜዉ ቻርተር ከተማ ቢሆኑ መልካም ነዉ። (ለዘለኬታዉ፣ ለሁሉም በሚበጅ፣ የተለያዩ ሁኔታዎችን ከግምት ባስገባና በተጠና መልኩ ፣ፌደራል አወቃቀሩ እንደገና በአዲስ የሚዋቀርበትን ሁኔታ በመፈለግ ለብዙ ችግሮች መፍቴሄ ማግኘት ይቻላል)
ከላይ የዘረዘርኳቸዉ አሃዞች በኦፊሴል ከተመዘገበዉ የኢትይጵፕያ ሕዝብ ቆጠራ ሪፖርት ነዉ። በሚቀጥለው ጊዜ የቤኔሻንጉል ጉምዝ እና ሃረሪ ክልሎችን እንመለከታለን።