አቶ አለማየሁ ለፌቦ የተባሉ በሲዳማ ጭሬ የአንድነት ፓርቲ አባል ከፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ማግስት ወደ ክልሉ ሲመለሱ አርሲ ሚጣ ነሴቦ ወረዳ ወርቃ ከተማ ታህሳስ 26 ቀን 2006 ዓ.ም እንደተያዙ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ከታሰሩበት ወረዳ ያንተ ጉዳይ የፖለቲካ ጉዳይ ስለሆነ እዚህ አይታይም በማለት ጥር 9 ቀን ወደ ሻሸመኔ ዞን ፖሊስ ተወስደው ታሰሩ፡፡
ፍኖት –የአንድነት ፓርቲ አባል ከጠቅላላ ጉባኤ ምግስት ጀምሮ በእስር እየተንገላቱ ነዉ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዜና አቀራረብ ጋዜጠኞችን ብቻ ሳይሆን አንባቢን ያሳፍራል –ታደሰ ብሩ
የኢዜአ ማደናገሪያ ዜና – አንድ ተጨባጭ ምሳሌ
January 20, 2014
ታደሰ ብሩ
በቅድሚያ የሚከተለውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን (ኢዜአ) ዜና አጣጥሙልኝ።
…
ጎባ ጥር 10/2006
በባሌ ዞን ከእርሻ ስራ በተጓዳኝ በንብ ማነብ ፓኬጅ የተሳተፉ አርሶ አደሮች ከ53 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ማግኘታቸውን የዞኑ የእንስሳት ሀብት ልማትና ጤና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በጽህፈት ቤቱ የእቅድና ግምገማ በለሙያ አቶ ታዬ ኣጋ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ባለፉት ስድስት ወራት የማር ምርቱን ለአካባቢው ገበያ ያቀረቡት ከ89ሺ 200 የሚበልጡ አርሶ አደሮች ናቸው ።
የማር ምርቱን ለአካባቢያቸውና ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ከሆኑት አርሶ አደሮች መካከል ከ21 ሺህ 699 የሚበልጡት ሴቶች መሆናቸውንም አብራርተዋል ።
በዞኑ ዘጠኝ ደጋማ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ አርሶ አደሮች የማር ምርቱን የሰበሰቡት ከ100ሺ ከሚበልጡ ባህላዊ፣ የሽግግርና ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች በመጠቀም እንደሆነ አብራርተዋል ።
በዞኑ ባለፉት ስድስት ወራት ለገበያ የቀረበው የማር ምርት ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ1ሺህ ኪሎ ግራም ብልጫ ያለው እንደሆነም አስታውቀዋል ።
ጽህፈት ቤቱም የዞኑን አርሶ አደሮች የማር ምርትና ምርታማነት በሁለት እጥፍ ለማሳደግ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎችን ለአርሶ አደሮቹ በማሰራጨት ላይ እንደሆነም ጠቁመዋል ።
…
ይህንን ዜና እዚህ ያገኙታል።
ዜናውን በጥንቃቄ ያላነበበ ሰው የተለመደ ልማታዊ ዜና በመሆኑ ምንም የሚያስደንቅ ነገር አያገኝበትም። ሆኖም ትንሽ ስሌት ብጤ እንጨምርበት።
ሀ. ከሽያጭ የተገኘው ገንዘብ 53.7 ሚሊዮን: ብር 53, 700, 000
ለ. የአምራቾቹ ብዛት: 89, 200 ገበሬዎች
ሐ. የፈጀባቸው ጊዜ: 6 ወር
ከዚህ በመነሳት የሚከተለውን ማስላት ይቻላል።
የአንድ አምራች አማካይ የሽያጭ ገቢ: 53, 700, 000 ÷ 89, 200 = ብር 602.02
የአንድ አምራች አማካይ ወርሃዊ የሽያጭ ገቢ: 602.02/ 6 = ብር 100.34
በዚህ “ድንቅ ስኬታማ ፓኬጅ” አንድ ገበሬ በወር በአማካይ የሚያገኘው የሽያጭ ገቢ ብር 100.34 ነው። በአማካይ ማለት ደግሞ ከዚህም በታች የሚያገኙ ብዙ አሉ ማለት ነው። በተለይ አንድ ብርቱ “ልማታዊ” ገበሬ ካለ የሌሎቹ ሰብስቦ ነው የሚወስደው። ለማንኛውም ግን የገበሬዎች ምርታነት እኩል ነው ብለን እናስብና ስሌታችንን በአማካይ እንቀጥል።
አንባቢ እንደሚያውቀው የሽያጭ ገቢ የተጣራ ገቢ (ወይም ትርፍ) አይደለም። ገበሬዎች ከዚህ ፓኬጅ ምን ያህል እንደተጠቀሙ ለማስላት ወጪያቸው መሰላትአለበት። ከዜናው በመነሳት በአዕምሮዓችን የሚመጡ ወጪዎች የሚከተሉት ናቸው።
እያንዳንዱ ገበሬ በአማካይ በወር ምን ያህል ሰዓታት በዚህ ሥራ ላይ አዋለ?
“ከ100ሺ ከሚበልጡ ባህላዊ፣ የሽግግርና ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች” በሥራ ላይ ውለዋል። የእነዚህ ቀፎዎች የእልቀት ዋጋ (depreciation) በወር ምን ያህል ነው?
(በነገራችን ላይ ይኼ ራሱ ሌላ ዜና የሚወጣው ነገር ነው። በአገሪቱ ትልቁ የዜና አገልግሎት በትላልቅ ፎንት ዜና የሠራለት “ፓኬጅ” ለአንድ ገበሬ በአማካይ ሁለት ቀፎ እንኳን ሳያቀርብ ነው። ለ 89,200 ሰው 100, 000 ማለትም በአማካይ ለአንድ ገበሬ 1.12 ቀፎ ነው!)
ማሩ በምን ታሸገ? (ስልቻም ከሆነ የስልቻው ዋጋ)
ማሩ በምን ተጓጉዞ ገበያ ደረሰ?
የገበሬን ድካም ለሚያውቅ ወጪዎቹ እነዚህ ብቻ እንደማይሆኑ ይረዳል፤ ግን ይብቃኝ።
ይህንን ሁሉ ስናስብ ነው ዜናው እጅግ አስገራሚ የሚሆነው። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዜና አቀራረብ ጋዜጠኞችን ብቻ ሳይሆን አንባቢን ያሳፍራል። ይህንን ዜና ሳነብ የተሰማን ስሜት እፍረት ነው። ይህ ነው የኢዜአ ልማታዊ ጋዜጠኝነት!!!
የኢዜአ ስኬትን የማጋነን ፍላጎት፤ ማለትም የተገኘው ገንዘብ እና በፓኬጁ የተሳተፉ ገበሬዎችን ብዙ አድርጎ የማቅረብ ፍላጎት፣ ብዙ ሲካፈል ብዙ ትንሽ የሚሆን መሆኑ ያስረሳው ይመስለኛል።
አቡጊዳ –ሰማያዊ ጥር 25 ቀን በጎንደር ሰልፍ ጠራ
«አባቶቻችን በደምና በጥንታቸው ገትረው ያቆዩልንን መሬት ስንዝር አናሳልፍም» በሚል መርህ የሰማያዊ ፓርቲ በጎንደ ከተማ ታላቅ የተቃዉሞ ሰልፍ ጠርቷል።
ሰልፉ የሚደረገዉ እሁድ ጥር 25 ቀን ሲሆን፣ ቦታውም በጎንደር መስቀል አደባባይ እንደሚሆን የሰማያዊ መግለጫ ይጠቁማል።
ሰማያዊ ሌሎች የሲቪክ ማህበራት እና የፖለቲካ ድርጅቶ እንዲተባበሩ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ የአደባባይ ጥሪ ከማስተልለፍ ባሻገር፣ ምን ያህል ግን ሰልፉን በጋራ ለማቀናጀት ከሌሎች ጋር ንግግር እያደረገ እንደሆነ የሚታወቅ ነገር የልም።
አቡጊዳ –የአንድነት ፓርቲ የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይን በተመለከተ እንቅስቃሴዎች እያደረገ ነዉ
የአንድነት ፓርቲ በሱዳን ድንበር ጉዳይ፣ ተደረጉ እየተባለ ያሉ ስምምነቶች ዙሪያ ለአማራዉ ክልል አስተዳዳሪ እንዲሁም ለጠቅላ ሚኒስተር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ማብራሪይ መጠይቁ ይታወሳል። እንኳን አንድ በአገሪቱ ያለ አብይ የፖለቲክ መሪ ቀርቶ፣ማንም ዜጋ በአገር ጉዳይ ላይ ጠያቄ ጠይቆ፣ ለጠያቄው ማብራሪይ የመቀብል መብት እንዳለዉ ቢታወቅም፣ የክልሉም ሆነ የፌደራል አስተዳዳሪዎች የሕዝብንም ሆነ የአንድነት ፓርቲን ጥያቄ ጆሮ ዳባ ልበስ ብልዉታል።
የሱዳን ድንበር ጉዳይን በተመለከተ የሱዳን ጋዜጥኞች የተደረጉ ስምምነቶችን እንደ ድል እየዘገቡ ባለበት ወቅት፣ የኢትዮጵያ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ሆነ የምነግስት ባለስልጣናት ትንፍሽ አለማለታቸውና ጉዳዩን ከሕዝብ መደበቃቸው፣ በጣም እንዳሳሰበው የሚገልጸው የአንድነት መግለጫ፣ የስልጣን የበላይ አካል ለሆነዉ ለፓርላማዉ በድንበር ጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ጠይቋል።
የመንግስት አባላት ምላሽ ማራሪይ እንዲሰጡ በደብዳቤ ግፊት እማድረግ በተጨማሪ፣ ፓርቲዉ የጉዳዩ ባለቤት ከሆነ ሕዝብ ጋር ለመወያያት ጥር 18 ቀን 2006 ዓ.ም ስብሰባ ጠርቷል።
ሌላዉ አገር ቤት የሚንቀሳቀሰ፣ የሰማያዊ ፓርቲ በዚሁ በኢትዮ ሱዳን ድንበር ዙሪያ በጎንደር ከተማ ጥር 25 ቀን 2006 ሰላማዊ ሰልፍ መጥራቱ ይታወሳል። ፓርቲዉ ሌሎች ሲቪክ ማህበራትና የፖለቲክ ድርጅቶ እንዲተባበሩት ጥሪ ያቀረበ ቢሆንም፣ በተግባር ግን ምን ያህል በመግለጫ ጥሪ ከማቅረብ ባለፈ፣ ከሌሎች ፓርቲ አመራሮች ግር ለመነጋገርና ሰልፉን ለማቀናጀት እየሰራ እንደሆን ብዙም አይታወቁም።
የአንድነት ሕዝባዊ ስብሰብ ጥሪን በተመለተ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ
የአንድነት ፓርቶ ለፓርላማው የላከዉን ደብዳቤ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ !
አቡጊዳ –በኢትዮ- ሱዳን ድንበር ዙሪያ ፕ/ሮ መስፍን ማብራሪይ ይሰጣሉ
የሰማያዊ ፓርቲ በፌስ ቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ መሰረት፣ ቅዳሜ ጥር 17 ቀን በፓርቲዉ ጽ/ቤት በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ዙሪያ የዉይይት መድረክ አዘጋጅቷል። « ድንበራችንን ጉዳይ በተመለከተ በተጨባጭ መረጃ በህብረተሰቡ ውስጥ ግንዛቤ ይፈጠር ዘንድ ትምህርታዊ ውይይት መድረክ ያዘጋጀ ሲሆን በዝግጅቱ ላይም በዘርፉ ለረጅም አመታት በመስራት የሚታወቁት የረጅም ጊዜ የጆግራፊ ባለሞያ የሆኑት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ድንበሩን በተመለከተ ሰፋ ያለ ትምህርት ይሰጣሉ» ሲል የገለጸው የሰማያዊ መግለጫ፣ ኢትዮጵያዉያን በስፍራዉ ተገኝተዉ በጉዳዩ ላይ ሙሉ ግንዛቤ እንዲያገኙ ጥሩ አቅርቧል።
የሰማያዊ ፓርቲ ፣ እንዲሁም የአንድነት ፓርቲ ለተለያዩ የመንግስት አካላት በጉዳዩ ላይ ግልጽ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን እስከአሁን ጉዳዩን በድብቅ ለመያዝ ከፈለጉ የመንግስት አካላት እስከአሁን ማብራሪያ ሊገኝ አልተቻለም።
የወያኔ ነፍስ በበረከት ስምዖን በኩል ስትቃዥ ነፃነት ዘለቀ
አንደኛው መስከረም ጠብቶ ሌላኛው መስከረም እስኪጠባ ድረስ ባሉት የ365.25 ቀናት ውስጥ ስንት ጉድ መስማት እንዳለብን የሚጠቁም አሃዛዊ መረጃ ሊኖር እንደማይችል መቼም ግልጥ ነው፤ ነገር ግን የዘመናችን ኢትዮጵያ የታሪክ ጎርፍ ያመጣብን ከወያኔና መሰሎቹ በስተቀር ሌሎቻችን ያልጠበቅነው ዱብዕዳ ክስተት ምሥጋና ይንሳውና በዬቀኑ የማንሰማውና የማናየው ዕንቆቅልሽ እንዳይኖረን ሆነናል፡፡ በዚህ መልክ በተለይ ባለፉት 22.8 ዓመታት ውስጥ የታዘብነው የታሪክ ምፀትና ወኔያዊ የውሸት ስንክሳር በረጂሙ ታሪካችን ታይቶም ሆነ ተሰምቶ እንደማያውቅ ማንም ጤናማ ኅሊና ያለው ዜጋ የሚመሰክረው ይመስለኛል፡፡ ለዛሬ አንዱን የወያኔ ነጭ ውሸት እንመለከታለን፡፡
በነገራችን ላይ ወያኔና እውነት ዐይንና ናጫ መሆናቸውን የማይረዳ ወገን እንደማይኖር እገምታለሁ፡፡ የወያኔን ተፈጥሮ ወያኔ ራሱን ጨምሮ ሁሉም ያውቃል፤ የወያኔ እውነት፣ የእውነት ግልባጭ የሆነችው ሀሰት ናት፡፡ ለወያኔ ውሸት ማለት እውነት ናት፡፡ ለወያኔ እንደእውነት የሚመርና የሚያቅር ነገር የለም፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ለወያኔ እንደሀሰት የሚጣፍጥ ምንም ነገር የለም፡፡ ወያኔና እውነት በሂሳባዊ አገላለጽ ‘asymptote’ ናቸው – መቼም ሊገናኙ የማይችሉ ተጻራሪ ኑባሬያት በመሆናቸው፡፡ ወያኔ የሀሰት የህግ ባል ነው፤ የሚለያዩት ወይም የሚፋቱት ከሁለት አንድኛቸው ወይም ሁለቱም ሲሞቱ ብቻ ነው፡፡ ሀሰት ግን እስከዓለም ፍጻሜ ስለምትኖር ወያኔ ካልጠፋ ከውሸታምነቱና ከሀገር አጥፊነቱ ተፈጥሯዊ ባሕርይው ሊፋታ አይቻለውም፡፡ ታሪክ ግን ሥራውን የማይረሣ ቆፍጣና ገበሬ በመሆኑ ጊዜውን ጠብቆ እነዚህን ጉግማንጉጎች ወደማይቀረው መቃብራቸው እንደሚሰዳቸው የታመነ ነውና መፍረስ የጀመረው የበሰበሰ ሥርዓታቸው ከነሰንኮፉ ተገርስሶ ሀገራችን በቅርቡ ነጻ እንደምትወጣ በሙሉ ልብ አምናለሁ፡፡ በዚህች መንደርደሪያ ወደሰሞነኛው የበረከት ስምዖን ውሽከታ እንለፍ፡፡
“የኢትዮጵያ አርሶ አደር እስካሁን በተደረገለት ሥራ በሚገባ የረካ ስለሆነ ‹መንግሥት ሰልፍ ውጣ ቢለው ይወጣል፤ መንግሥት ተኛ ቢለው ይተኛል፤ ግፍ ብንፈጽም እንኳን አርሶ አደሩ ይህንን መንግሥት ይሸከመዋል እንጂ ምንም አይለውም፡፡”
ይህን የብፃይ በረከት ንግግር በዓይነቱ ልዩ የሚያደርገው የተባበሩት መንግሥታት ሰሞኑን ባወጣው አንድ ጥናታዊ ዘገባ ላይ በአፍሪካ ፈጣን ዕድገት ከሚያሳዩ አሥር ሀገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ አለመካተቷና በተጓዳኝም ይህቺው ኢትዮጵያ – ይህቺው ወያኔን በጫንቃዋ እንደምትሸከም በረከት አፉን ሞልቶ የመሰከረላት ጉደኛዋ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጠኔ ጓዙን ጠቅልሎ ከመሸገባቸው አምስት የመጨረሻ ድሃ ሀገራት ውስጥ መመደቧ ነው – (በረከት ይህን ሪፖርት ሳያነብ መሆን አለበት ያን በህልሙ የደረሰውን ጅሎችን የማሞኛ ተምኔታዊ(utopian) ቧልታይና ድንቃይ ድርሰቱን የደሰኮረው!)፡፡ በነገራችን ላይ በአምባገነንነትና በድህነት በወያኔ መንግሥት ሳይቀር የምትታማዋ ኤርትራ በነዚህ ዘገባዎች አልተካተተችም(እንዲያውም ዘገባው ኢትዮጵያን ይግረማት ብሎ ከአሥሩ በፍጥነት እያደጉ ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ አንዷ ኤርትራ እንደሆነች የገለጠ መሰለኝ)፡፡ ኢትዮጵያ ቻድን ብቻ በልጣ በአፍሪካ በርሀብተኝነት ሁለተኛ ስትወጣ ኤርትራ ከአምስቱ የባሰባቸው ሀገራት ውስጥ አልገባችም፡፡ የርሷ መግባት አለመግባት የኔ ራስ ምታት አይደለም፡፡ ነገር ግን ይህች በማዕቀብና በልዩ ልዩ የማሰቃያ መንገዶች የተወጠረች የቀድሞ የኢትዮጵያ ግዛት ከኢትዮጵያ የተሻለች መሆንዋን በመረጃ በተደገፈ ዘገባ የሚረዳ ጤናማ ሰው የወያኔን ሚዲያ አስችሎት እንዴት ሊከታተል እንደሚችል ይታያችሁ፡፡ ክርስቶስ ‹አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ› አለ፡፡ ወያኔም ይህችን የክርስቶስ አባባል ቀምቶ በማንሻፈፍ ‹አፌን በሀሰትና ዕብለት እከፍታለሁ› አለና ነጋ ጠባ የማያቅመን የሀሰት ወሬ የማይነጥፍበት አስገራሚ ፍጡር ሆነ፡፡
መዋሸት የማይሰለቸው ‹ልማታዊው መንግሥታችን› በሚዲያው የሚያሳየን ኢትዮጵያና እኛ በግልጥ የምናያት ኢትዮጵያ ተለያይተውብን ተቸግረናል፡፡ እነሱ ‹ኢትዮጵያ በልማት ጎዳና እየተመመች ናት፤ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ራዕይ ለማሳካት በየፈርጁ የምናካሂደው የልማት ግስጋሴ ግቡን እየመታ ነው፤ የኢትዮጵያ ልማት ማንም በማይወዳደረው ሁኔታ ወደፊት እየተምዘገዘገ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችንን በማይነቃነቅ ዓለት ላይ ገምብተናል፤ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት ሳይሸራረፍ የተከበረባትና በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ አንድነት እውን የሆነባት አዲሲቷ ኢትዮጵያ ተፈጥራለች፡፡ አሁን ዋናው ጠላታችን ድህነት ነው፡፡ እሱንም እየተዋጋነው ነው…›እያሉ በቲቪያቸው እያላገጡብን ነው – ድህነትን ለመዋጋትና ለማሸነፍ ደግሞ ስንት አሥር ዓመቶች እንደሚያስፈልጉን እነሱው ናቸው የሚያውቁት፤ ለመልካም አስተዳደር እኮ አንድ የመኸር ወቅትም ትልቅ ጊዜ ነው – እንኳንስ 23 ዓመታት፡፡ ወያኔዎች ግን በድህነት ላይ እንደዛቱና ወደታሪክነት እንለውጠዋለን እንዳሉ ሦስት ዐሠርት ዓመታትን ሊደፍኑ ነው፤ አያፍሩም፡፡ በማከያው ግን ዕድሜ ለወያኔው ጉጅሌ በምግብ “ሞልቶ መትረፍረፍ” ከአፍሪካ አንዲት ሀገር ብቻ በልጠን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻችን የተንጣለሉ የአስፋልት መንገዶችንና በአብዛኛው የትግራይ ተወላጆች የሆኑ ኢንቬስተሮች የገነቧቸውን ሕንፃዎች “እየተመገቡና እየጠገቡ” መሆናቸው እየተነገረን ነው፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ያጡ የነጡ ዜጎቻችንም ከዬቆሻሻ ገንዳዎች የሀብታም ፍርፋሪና የሙዝ ልጣጭ ለመሻማት ቀን ከሌሊት ሲራኮቱ ይታያሉ፡፡ የወያኔ ዕድገት ይህ ነው፡፡ የወያኔ ‹ልማታዊ ጋዜጠኞች›ም በበኩላቸው የሕዝቡን ሰቆቃ እንዳይመለከቱና እንዳይዘግቡ እንደአቃቂ ፈረስ ዐይኖቻቸውን በወያኔ ተከልለው በብድርና በዕርዳታ በተገነቡ መንገዶችና ድልድዮች ላይ ካሜራዎቻቸውን በመደቀን ሌት ከቀን በተመሳሳይ ዜናዎችና ሀተታዎች ማደንቆራቸውን ተያይዘውታል፡፡ እኛን እሚያሳክከን ሆዳችን ላይ እነሱ እሚያኩልን እግራችንን፡፡ የሚገርሙ ጋዜጠኞችና የሚገርም የማፊያዎች መንግሥት፡፡
ወደበረከት ንግግር እንመለስ፡፡ እንደእውነቱ በረከት ከፍ ሲል የተናገረውን ነገር ለምን እንደተናገረው አልገባኝም፡፡ ምን ማለት እንደፈለገ ለመረዳት አስተርጓሚ ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ አማርኛ ቋንቋን አውቃለሁ ብዬ ደረቴን ነፍቼ እናገራለሁ፡፡ ነገር ግን ይህንን የበረከትን ንግግር እንደመሰለኝ ተርጉሜ እንዲገባኝ ጥረት አደረግሁ እንጂ በቅጡ ልረዳው አልተቻለኝም፤ እርሱም ቢሆን ጎንደር ውስጥ ብዙ ዓመታትን ስለኖረ አማርኛን ከአፍ መፍቻው ባልተናነሰ ያውቃል ብዬ እገምታለሁና ‹ምን ማለት እንደፈለገ ሳይገባው እንዲህ ያለ የተወነዣበረ ንግግር በአደባባይ ተናግሮ የሰው መሣቂያ ለመሆን አይደፍርም› ብዬ ለማመንም በጣም ተቸገርኩ፡፡
ይህን ንግግር በብዙ መልኩ መገንዘብ እንደሚቻል አምናለሁ፤ በአማርኛው “የጊዮርጊስን ግብር የበላ ሳይነኩት ይለፈልፋል” ወይም በሌላ ፈሊጣዊ አገላለጽ “የምላስ ወለምታ” የምንላቸው ምሥል ከሳች አባባሎች አሉ፡፡ በፈረንጅኛው “Fruedian slip” የሚባል በሥነ ልቦና የትምህርት ዘርፍ የሚጠቀስ ሐረግ አለ፡፡ ይህ ሰው የተናገረውን ከነዚህ ጽንሰ ሃሳባዊ ዕይታዎች አንጻር ብንመለከተው ወያኔ ከመጃጀቱና በወንጀል ድርጊቶች ከመጨመላለቁ የተነሣ ነፍሱ እየቃዠች መሆኗን መረዳት አያዳግተንም፡፡ አለበለዚያ ግፍ በመሥራት ላይ የቆመ የወሮበሎች መንግሥት “ገበሬው ግፍ ብንፈጽምበትም ይሸከመናል” ብሎ መናገሩ ምን ትርጉም ይኖረዋል? አንድ ጤነኛ ሰው ከመሬት ተነስቶ “በጥፊ ባጮልህና ዐይንህን በጉጠት ባወጣውም እንደማትቀየመኝ አውቃለሁ! ከኔ በበለጠ ሊያሰቃይህ የሚችል ወገን እንደሌለ ስለማውቅ ለስቃይ ለስቃይ እኔው እሻልሃለሁና ምርጫህ እኔው ብቻ ልሆን ይገባኛል” ብሎ እንዴት ሊናገር ይችላል? እንዲህ ብሎ የሚናገር ሰው ካለ ደግሞ እንደበረከት የለዬለት በሽተኛ እንጂ ጤናማ ሰው ሊሆን አይችልም፡፡ ከወፈፌና በሽተኞች ንግግር ይሠውረን፡፡ “ዱባ ካላበደ ቅል አይጥልም” አሉ? የሚገርም በረከት ነው የሆነብኝ እባካችሁን፡፡
ይህን ንግግር በቁሙ መረዳት እንደሚቻለው በረከት ማለት ቅል ራስና እሚናገረውን እንኳን የማያውቅ ገልቱ ሰው ነው፡፡ ለመደዴ የቃላት አጠቃቀሜ ይቅርታ ይደረግልኝና እንደዚህ ያለ ድፍን ቅልና ባልጩት ራስ የኢትዮጵያ አንዱ ባለሥልጣን እንደነበረ በነገው የታሪክ መዝገባችን ሠፍሮ ሲታይ በቀጣይ ትውልዶቻችን ዘንድ በእጅጉ ከምናፍርባቸው የታሪክ ስብራቶቻችን መካከል አንዱና ትልቁ ነው፡፡ ሰው ምን ቢጃጃል እንደዚህ አይናገርም ወይም አይጽፍም፤ አለበለዚያም አብዷል ማለት ነው፡፡ “አፍ ሲከፈት ጭንቅላት ይታያል” የሚባለው እኮ እንደዚህ ያለ በደናቁርት አስተሳሰብ የተለወሰ የአነጋገር ጭቅቅት ሲያጋጥም ነው፡፡ ተመልከቱልኝ፡-
“መንግሥት ሠልፍ ውጣ ቢለው ይወጣል፤ ተኛ ቢለው ይተኛል፡፡”
ምን ማለት ነው? ገበሬውን በማስገደድም ይሁን በማታለል ሠልፍ ማስወጣት ይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን እንዴት ነው እንደሕጻን ልጅ ገበሬውን በትዕዛዝ አባብሎ ማስተኛት የሚቻለው? ምን ዓይነት ዕብሪትና ትምክህት ነው? ምን ዓይነት የድንቁርና አነጋገር ነው? ለነገሩ ወያኔዎች ከአለቃቸው ከመለስ ጀምሮ ለአነጋገራቸው ደንታ የላቸውም፤ የሚያስቡት እንደጤናማ ሰው በጭንቅላት ሣይሆን እንደ አውሬ በጡንቻ ሣይሆን አይቀርም – አውሬ በጡንቻው ካሰበ፡፡ ሀገር፣ ታሪክና ወገን አለን ብለው ራሳቸው ስለራሳቸው የሚያምኑ አይደሉም፤ ባህል የላቸውም፤ ሞራል ወይም ‘ethical values’ ብሎ ነገር አያውቁም፤ ምናልባት ከሴቴኒዝም በስተቀር ሁነኛ ሃይማኖትም ያላቸው አይመስሉም (ለዚህም ይመስላል ወንጀለኝነት የሚያዝናናቸውና በሰዎች ስቃይ የሚደሰቱት)፤ በትውፊትና በወግ ልማድ አያምኑም፤ ባጭሩ ወፍዘራሽ የመርገምት ውጤቶች ናቸው፡፡ ከሁሉም ነገር የወጡና ከዜሮ መጀመር የሚወዱ በፈረንጅኛው አገላለጽ nihilists ናቸው – hedonist የሚል ምርቃትም ማከል ይቻላል፡፡ ታሪክን ማጥፋትና ነባር ባህልን ማውደም ያረካቸዋልና፡፡
ወያኔዎች ማለት ባጭሩ ማሊ በምትባለዋ አፍሪካዊት ሀገር ‹አዛዋድ› በሚል ራሳቸው በፈጠሩት አዲስ ግዛት ውስጥ ፈረንሣይ ድምጥማጣቸውን እስክታጠፋቸው ድረስ ለተወሰነ ጊዜ በሼሪዓ ህግ የሚተዳደር እስላማዊ መንግሥት መሥርተው እንደነበሩት የቱዋሬግ አማፅያን የሚመሰሉ ናቸው – ወያኔዎች እንደሶማሊያው አልሻባብ ዓይነትም ናቸው – ነገር ግን መንግሥት ስለያዙ ደፍሮ በአሸባሪነት የፈረጃቸው ዓለም አቀፍ ኃይል ሊገኝ አልቻለም፡፡ ለነገሩ ወያኔዎች ሀገራዊ አጀንዳ ስለሌላቸውና የማንንም ፀረ-ኢትዮጵያ የሆነ አጀንዳ አንከርፍፈው በተባባሪነት ስለሚጓዙ ለዓለም አቀፍ ታዋቂ ኃይሎች እስትራቴጃዊ ጠቀሜታ እስከሰጡ ድረስ በአጋርነት የሚያስጠጋቸውና ሙሉ ድጋፍ የሚሰጣቸው አያጡም(ኢትዮጵያውያንን ለጊዜውም ቢሆን እያስቸገረን ያለው ይህን መሰሉ የወያኔ እስስታዊ ተፈጥሮ ነው)፡፡ እነዚያ የአልቃኢዳ የአፍሪካ ክንፍ የሆኑ አማጽያን በቲምቡክቱ ውስጥ የነበሩ ዕድሜያቸው በሺዎች ዓመታት የሚገመት የታሪክ ቅርሶችን በዶማና አካፋ እንዲሁም በግሬደር በአጭር ጊዜ የሥልጣን ቆይታቸው ውስጥ ድራሻቸውን ማጥፋታቸውን የቅርብ ጊዜ ትዝታ በመሆኑ ከዐይነ ልቦናችን ገና አልተሰወረም፡፡ ወያኔዎችም እያዋዙ በእስከዛሬው የኃይል አገዛዛቸው እጅግ በርካታ የኢትዮጵያ ቅርሶችንና ታሪኮችን አጥፍተዋል – ከሁሉም የሚብስ ጥፋታቸው ግን ከቁሣዊው ይልቅ ሥነ ልቦናዊውና ኅሊናዊ ወመንፈሣዊው አጠቃላይ ውድመት የበለጠ ኪሣራ ያደረሰብንና ለማገገምም ብዙ ጊዜ የሚወስድብን ከባዱ ጥፋት ይመስለኛል፡፡ እነዚህ ናቸው እንግዲህ ጅብ እማያውቁት ሀገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ እንደሚል በምናውቃቸው ምሥኪን ዜጎች መሀል ሆነው ገበሬው የነሱ እንደሆነ የሚሰብኩን፡፡ ለነገሩ ጅብ እንኳን በማያውቁት ሀገር ነበር ተናገረው የተባለውን የተናገረው፡፡ ወያኔዎች ግን ዐይናቸውን በጨው አጥበው እኛው ፊት ሸፍጣቸውንና የሀሰት ቱሪናፋቸውን ካለተቀናቃኝ ለብቻቸው በተቆጣጠሩት ሚዲያቸው ያናፉብናል፡፡
የኢትዮጵያ ገበሬ ኑሮው ምን ይመስላል?
በአሁኑ ወቅት በወያኔ ሥርዓት እንደገበሬው የሚማረር የለም፡፡ የወያኔን የውሸት ፕሮፓጋንዳ ለወያኔና ወያኔያውያን ትተን እውነቱን ብቻ እናውራ ካልን የገበሬው ኑሮም ሆነ የአጠቃላዩ የሀገሪቱ ሕዝብ ሕይወት ያሳዝናል ብቻ ሳይሆን ያስለቅሳል፡፡ እኔ ይህን መልእክት የምጽፍላችሁ ዜጋ በሀገር ቤት የምኖርና አልፎ አልፎ ወደገጠር ለሥራ ጉዳይ ወጣ የምል በዚያም ምክንያት የብዙ አካባቢዎችን ነዋሪዎች ሰቆቃና የዕለት ከለት ውጣ ውረድ የምታዘብ ሰው ነኝ፡፡ ስለዚህም የምለው ነገር በስማ በለው የተገኘ ሳይሆን በራሴም ሕይወት እየደረሰ ያለ እውነተኛ ሰቆቃ መሆኑን ላስታውስ እፈልጋለሁ፡፡ የገበሬው ኑሮ ከእኛ ከከተሜዎቹ የባሰ እንጂ የተሻለ እንዳልሆነ በውነት እመሰክራለሁ፡፡
የአንድ አምባገነን መንግሥት ትልቁ ሕዝብን የመግዣ መሣሪያ ሌላ ሳይሆን በማይምነትና በድንቁርና ሸብቦ በማስፈራራትና በማስራብ አንቀጥቅጦ ወደተናጋሪ እንስሳነት መለወጥ ነው፡፡ ወያኔም እያደረገ ያለው ይህንኑ ነው፡፡ በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ ብትሄዱ ለይስሙላ ትምህርት ቤቶች ይሠሩ እንጂ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ባለመኖሩ መማር ካለመማር የሚለይበትን መሠረታዊ ነጥብ ፈልጋችሁ ልታገኙ አትችሉም፡፡ በመሆኑም ገበሬው ከትምህርት ርቋል፤ የጨለማ አዘቅት ውስጥም ከገባ ቆይቷል፡፡ በማይምነት አለንጋ እየተገረፈ፣ በብጥቅጣቂ እርሻ ላይ በሚዘራት አነስተኛ ሰብል እየተሰቃዬ፣ ከዚያችም ሰብል ላይ ከፍተኛ ግብር እንዲከፍል እየተገደደና ከብቱንና ንብረቱን ሸጦ ግብር እንዲያስገባ እየተጠየቀ የሚገኝ ገበሬ ወያኔን ጣዕረሞት ሲይዘው “በፍቅርና በትግስት ይሸከመዋል” ሳይሆን “የወያኔን ሬሣ ተሸክሞ ወደመቃብሩ ይሸኘዋል” ቢባል ነው ትክክለኛው፡፡ ገበሬው በቀን አንድ ጊዜም የሚቀምሰው በሌለበት ሁኔታ፣ ገበሬው የልጁን ወስፋት የሚሸነግልበት አንዳችም እህልና ጥሪት አልባ በሆነበት ሁኔታ፣ ገበሬው ከገጠር እየፈለሰ ወደከተሞች በመግባት ለወያኔ ሕንጻና ፋብሪካ ግንባታዎች የቀን ሠራተኛ እየሆነ ባለበት ሁኔታ፣ ገበሬው ልጆቹ ወደዐረብ ሀገር እየተሰደዱ ለዐረብ ጀማላ የሠይፍ እራትና የአስገድዶ መድፈር ሲሳይ እየሆኑ ባሉበት ሁኔታ፣ ገበሬው በማዳበሪያ ዕዳ የስንግ ተይዞ ኤሎሄ እያለ በሚገኝበት ሁኔታ፣ ገበሬው በአድሎኣዊ የመሬት ሥሪት ምክንያት መድሎ እየተሠራበት ማለፊያው የውሃ መሬት ለካድሬዎችና ለወያኔዎች እየተሰጠ ጭንጫውና መናኛው መሬት ግን ለድሃ ገበሬ እየተሸነሸነ ባለበት ሁኔታ፣ገበሬው ከማሳውና ከመኖሪያው እየተፈናቀለ መሬቱ በልማት ስም ለወያኔ ከበርቴዎች እየተቃረጠ ባለበት ሁኔታ፣ አህያ የተጫነችውን እንደማትበላ ሁሉ ገበሬውም ያመረተውን ምርት ለዕዳ ክፍያ ሲል ለጠገቡ የወያኔ ‹ልማታዊ ባለሀብቶች› በርካሽ እንዲሸጥና ጨርቁ በላዩ ላይ አልቆ በባዶ እግሩ እየሄደ በእሾህና በእንቅፋት አሣሩን እንዲበላ ተፈርዶበት ባለበት ሁኔታ፣ … በረከት የተናገረውን መስማት በርግጥም ተዓምር እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? በቀደመው ዘመን “እስመ አልቦ ነገር ዘይሰአኖ ለእግዚአብሔር” ነበር ሲባል እምንሰማ፡፡ አሁን ደግሞ “እስመአልቦ ነገር ዘይሰኣኖ ለወያኔ”ብንል እንሳሳት ይሆን? ወያኔ ጥቁሩን ነጭ፣ ነጩን ጥቁር፤ ልቅሶን ሠርግ፣ መርዶን ብሥራት ማድረግ የሚችል ልዩ ምትሃት ያለውና በአፍ ጤፍ የሚቆላ ፍጡር ነው፡፡ ወያኔን ለሚያውቅ የወያኔ ዲስኩርና ፕሮፓጋንዳ ችግር የለውም – በወያኔ ፕሮፓጋንዳ የሚጃጃል ወያኔን የማያውቅ ወይም ማወቅ የማይፈልግ ብቻ ነው፡፡ ‹ብታምኑም ባታምኑም የኢትዮጵያ ሕዝብ ወያኔን ከእግር እስከራሱ ጠንቅቆ ያውቀዋል!›፡፡ እናም በተለይ በአሁኑ ወቅት ወያኔ ማንንም ሊያታልል በማይችልበት ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ሞቶ በሞቶ እርግጠኛ ሆኜ እናገራችኋለሁኝ፡፡
እናም ወያኔ ስለገበሬው የሚያወራውና እኛ ስለገበሬው የምናውኧው፣ ገበሬውም ስለወያኔ የሚለውና ስለራሱም ከራሱ ኑሮ የሚስተዋለው ለዬቅል መሆናቸውን ልብ ማለት ይገባል፡፡ ‹ይሉሽን በሰማሽ ገበያ ባልወጣሽ› ይባላል፡፡ በረከት የሚናገረው ለሌሎች ብቻም ሳይሆን ለራሱም ሀሰት መሆኑን ማንም አያጣውም፡፡ በረከትን በማታው ‹ክብ ጠረጴዛ› አግኝተን “ምነው ወዲ ስምዖን፣ እንደዚያ ያለ ነጭ ውሸት ማናፈስ ደግ ነው እንዴ ? ለመሆኑ አንተስ ታምንበታለህ? ኅሊናስ የሚባል ነገር የለ(ህ)ም እንዴ?” ብንለው መልሱ ቀላል ነው፡፡ “ወንድሜ፣ በፖለቲካ ኅሊና ብሎ ነገር የለም፡፡ ዋናው ማምለጥ ነው፡፡ የምታደርገውን አድርገህ፣ የምትናገረውን ተናግረህ በፊትህ ከተደቀነብህ ችግር ማፈትለክ እንጂ ስለምትናገረው ነገር እውነትነት ከተጨነቅህ ፖለቲካ ውስጥ ቀድሞውን መግባት የለብህም፡፡ በተለይ እንደኛ ዓይነቱን ችግር ለጠላትም አይስጥ ወንድሜ፡፡ የገባንበት አጣብቂኝ በቀላሉ የሚወጡት አይደለም፡፡ መጥኖ መደቆስ አስቀድሞ ነበር ወዳጄ፡፡ በደም ጨቅይተናል፤ በሙስና በክተናል፤ በዘረኝነቱም ረገድ ያጠፋነውን ጥፋትም ቆም ብለው ሲያስተነትኑት የአንጎልን ሚዛን የሚያዛባና የሚያሳብድ ነው፤ ወደትግል ከገባንበት ጊዜ ጀምሮ የገደልነውና ለስደትና ለእሥራት የዳረግነው ዜጋ የኅሊና ዕረፍት እያሳጣ መቆሚያ መቀመጫ ያሳጣናል፤ ለዚህም ነው ብዙዎቻችን ቢሯችን ውስጥ ሣይቀር በብርጭቆ ውስጥ መደበቅን የምንመርጠው፡፡ ሰው ወዶና ፈቅዶ ጉበቱን በመጠጥ ቦጫጭቆ ሞትን በራሱ አይጋብዝም፡፡ ታዲያ አሁን ምን እናድርግ? ነገር የተበላሸው ዱሮ ነው፤ አሁን ሁሉም ነገር ጠርዝ ከለቀቀ በኋላ ከመዋሸትና ከማምታታት ውጪ ምን አማራጭ አለን? አንድ ነገር ሲገቡበት ቀላል ነው፤ ለመውጣት ግን ከባድ ነው፡፡ የኛ ወደዚህ ሥፍራ መምጣትና አንድ ሰው ወደአደንዛዥ ዕፅ ሱስ መግባት ሂደቱ ተመሳሳይ ነው፤ ሁለታችንም እንደዋዛ እንገባለን – እንደዋዛ መውጣት ግን ለሁለታችንም ከባድ ነው፡፡…” አዎ፣ በረከት በዊስኪ ጨዋታው ለሁነኛው ልክ እንደዚህ እንደሚያጫውተው ‘subconscious’-ኡን በርቀት በማንበብ መረዳት ይቻላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ለወደቀም ማዘን ተገቢ ነው፤ ‹ለሚወድቅ› ብላችሁ ልታሻሽሉትም ትችላላችሁ፡፡ እንደኔ ግን ወያኔዎች ሲነሱ ነው የወደቁት፡፡ ሰው ሲወለድ ነው የሞተው እንደምንል መሆኑ ነው፡፡ ወያኔዎችም ክፋትን መሥራት ሲጀምሩ፣ በቂም በቀል የተቃኘ የጥላቻ አገዛዛቸውን በስፋት ሲያጧጡፉ፣ ሀገርን ሲሸጡና ሲለውጡ፣ ምድርን በደም ረግረግ ሲሞሉ፣ አማራን ከትግሬ፣ ትግሬን ከኦሮሞ እዬለዩ አንዱን መጥቀምን ሌላውን መጉዳትን ባህላቸው ሲያደርጉ፣ ዳር ድንበርን እንዳወጣ ለባዕድ ሀገራት ሲቸበችቡ፣ ሀገርን ካለመውጫ በር ዘግተው የሚሊዮኖችን እስትንፋስ ሲዘጉ፣ … ያኔ ነው ወያኔዎች ገና በጧት ሳይወለዱ የሞቱት፡፡ እዚህ ላይ የሞት ዓይነት ብዙ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ እንጂ የአሁኑ እስትንፋሳቸውማ በ“ሥልጣን” ካሳለፉት ጊዜ አንጻር ሲታይ የደቂቃዎች ያህል ጊዜ ብቻ የቀራቸው ጉድጓዳቸው የተማሰ ልጣቸውም የተራሰ ስለመሆኑ ጨረቃና ፀሐያቸውን በማየት ብቻ የምንረዳው ነው – ዘመናቸው አልቋል፡፡ … የኔ አይደለም …የርሱ እንጂ፡፡ የፍርድ ሂደቱና ብያኔው ከታች አይደለም – ከላይ እንጂ፡፡
የኢትዮጵያን ገበሬ ኑሮ በረከት አያውቀውም ማለት ዘበት ነው፡፡ የኢትዮጵያን ገበሬ ወያኔ አያውቀውም ብሎ በዚህ ሰውዬ ንግግር መደመምም ከንቱ ነው፡፡ በገበሬው መቀለድ አምሯቸው እንጂ የሚናገሩት ነገር እውነቱ የተገላቢጦሽ መሆኑን አጥተውት አይደለም፡፡
ስለሆነም በረከት የሚለው ነገር “አይሰማም!” እንላቸዋለን ፡፡ በረከት ልፋ ብሎት ተናገረ የተባለውን ይናገር እንጂ የራሱ ስብሰባ አባላት ሳይቀሩ ሲችሉ በግልጥ ሳይችሉ ደግሞ በውስጣቸው ይስቁበታል፡፡ ለዚያውም ከትከት ብለው ነው እሚስቁበት – እንደጅል በመቁጠር፡፡ እርግጥ ነው – በረከት ጅል አይደለም፡፡ ጅል ለመምሰል የቆረጠው ግን ምርጫ በማጣት ይመስለኛል፡፡ አንድ ሰው ፀሐይ የሞቀውን እውነት ለመሸፈን በመሞከር በግልባጩ ለማውራት ከተገደደ አንድም ያስጨነቀው ነገር አለ ማለት ነው፤ አለበለዚያም የመዋሸት ተፈጥሯዊ ጠባይ አለበት ማለት ነው – ልክ እንደመለስ ዜናዊ፡፡ መለስ ዜናዊ በሣይንስ የተረጋገጠ ላይሆን ይችላል እንጂ በእንግሊዝኛው ‘pathological liar’ የሚባል ዓይነት ግለሰብ እንደነበር መረዳት አይቸግርም፡፡ እርሱ በቲቪ ቀርቦ የሚናገራቸውን ንግግሮችና መሬት ላይ ይታይ የነበረውን እውነት በማስተያየት የዚህን ሰው ውሸት በመናገር የመርካት ጠባይ ወይም የተዛባ ተፈጥሯዊ ባሕርይ በቀላሉ መገንዘብ ይቻል ነበር፡፡ በዚህ መልክ ይህ ተጋቦታዊ ደዌ በትግል አጋርነትና በጥቅም ተጋሪነት ምክንያት ለበረከትም ተርፎ ይሄውና በረከትም አንድም ሰው ላያምነው – አንድም የራሱ ሰው ሳይቀር አምኖ ላይቀበለው – እንዲሁ ድከም ብሎት ሲወሻክት እናደምጠዋለን፡፡ እስከመቼ እየወሻከተ በሰው ስቃይ ሲደሰትና የሰውን ስቃይ ለሚዲያ ፍጆታ ያህል ለከንቱዎች በመሸጥ እንደሚኖር ገና የምናየው ይሆናል፡፡ ወደኅሊናው የሚመለስ አይመስለኝም እንጂ ከተመለሰ ግን የገበሬውም ሆነ የአጠቃላዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ካሉት በታች ከሞቱት በላይ የሆነ የሰቆቃ ሕይወት በሚያሳድርበት የእርግማን መዘዝ እንደይሁዳ ራሱን ሰቅሎ እንደሚገድል አምናለሁ፡፡ ያ ቀን ደግሞ በጣም ቀርቧል፤ ምን አለ በሉኝ እነዚህ ጉዶች የሥራቸውን የሚከፈሉበት ጊዜ በብርሃን ፍጥነት እየገሰገሰ በመምጣት ላይ መሆኑ ይሰማኛል፡፡ ቋቱ ሞልቷል፤ የሚቀረው የሚጠራርጋቸውን ማዕበል የሚያስነሣው የፈጣሪ ፊሽካ ብቻ ነው፡፡
የኃጢኣት ትንሽና ትልቅ ባይኖረውም አንድ ሰው ሰርቆ ቢበላ እርቦት ሊሆን ይችላልና ምንም አይደለም ሊባል ይችላል፤ ቢሳደብ ተናድዶ ሊሆን ይችላል በሚል ይቅርታ ሊደረግለት ቢችል ምንም አይደለም፡፡ ነገር ግን በመንግሥት ሠራሽ ርሀብና በግፈኛ አገዛዝ እያለቀሰ የሚኖርን ገበሬ በሚያስለቅሰው ዘረኛ ሥርዓት ተደስቶና ደልቶት እንደሚኖር በሚያስገርም አነጋገር ሰይጣናዊ ስብከትን በመገናኛ ብዙኃን መልቀቅ ከይቅርታ በላይ ነው፡፡ ብሶቱን ችሎ፣ የሚደርስበትን ግፍና መከራ ተቋቁሞ በሞትና በሕይወት እየተንጠራወዘ በሚኖር ሕዝብ ላይ ይህን የመሰለ ቀልድና ድራማ እየሠሩ መሣለቅ ለዘር የሚተርፍ መራራ ቅጣት ሊያስከትል እንደሚችል በረከትም ሆነ ግብረ አበሮቹ መረዳት አለባቸው፡፡ ይህ መሪር ቀልዳቸው ዛሬና ለነሱ ምንም ላይመስል ይችላል፡፡ ይሁንና እያንዳንዷ የምናደርጋት መጥፎ ነገር ሁሉ ትልቅ ዋጋ ሳታስከፍል እንዲሁ የምትቀር እንዳልሆነች ቀልደኞቹና በኢቲቪ የሚገኙ ሆዳም ወናፎች ሁሉ ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ ዛሬ ገበሬውም ሆነ ከተሜው አንደበቱ ተለጉሟል፤ አይናገርም፤ ሊናገርም አይፈልግም፡፡ ሰሚ ስለሌለውና ፈጣሪው ፊቱን እንዳዞረበት ስለተረዳ ሁሉም በዝምታ ተቀምጧል፡፡ ይህ ማለት ግን ዘመን አይለወጥም፣ ዝም ያለም ሁሉ ደንቆሮና አላዋቂ ነው ማለት አይደለም፡፡ ወያኔ እንዳልነበር ሁሉ የማይኖርበት ጊዜ ሲመጣ ሊከሰት የሚችለውን ትዕይንት አለማየት ነው፡፡ ያኔ እንደዛሬው እዩኝ እዩኝ እንደተባለ ሁሉ ደብቁኝ ደብቁኝ የሚባልበት ጊዜ መድረኩን ይረከባል፡፡ ጥጋብ ደግሞ ወደራብ መንዳቱ ያለና የነበረ ነው፡፡ የጠገበ የሚራብ የማይመስለው የመሆኑ መጥፎ አጋጣሚ ግን አሳዛኝ የታሪክ ግጥምጥሞሽ እንደሆነ እስካሁን አለ – ሲገርም፡፡ አንዱ ከአንዱ ገመና ትምህርት ቢገበይ፣ የሚነሣው ከሚወድቀው ቢማር ግና የችግሮቻችን መንስኤዎች እንደጤዛ በረገፉ፣ እንደጉምም በበነኑ ነበር፡፡ ይህ አለመታደል እስከመቼ እንደሕግ ሆኖ እንደሚበጠብጠን አላውቅም፤ እስኪ የመጨረሻችን ያድርግልን፡፡
በማጠቃለያዬ ማሳሰብ የምፈልገው ነገር አለኝ፡፡ በረከትም ሆንክ ሌላ ጊዜ ሰጠኝ የምትል ባለሥልጣን ሁሉ ካለፈው ታሪክ ተማር፡፡ የሚያሳዝነኝ ነገር አፄዎቹ ከቀደሙት አፄዎች መማር ሳይፈልጉ ቀሩ፤ ቀሩናም ሕዝብን ሲንቁ ሲንቁ ቆይተው በናቁት ሕዝብ እርግማንና አመፅ ምክንያት እንዳልሆኑ ሆኑ – ዘር እንኳን አልወጣላቸውም፡፡ ደርግም ፈጣሪን ሣይቀር ከድቶና አስከድቶ ራሱን የፈጣሪን ያህል በመቁጠር ሕዝብን ሲንቅና ሲያዋርድ ቆይቶ በናቀውና ባዋረደው ሕዝብ እርግማንና ሁለንተናዊ የእምቢታ አመፅ ሰበብ እንደባቢሎን አይሆኑ ሆኖ ተንኮታኮተ – ስንትና ስንት ዘመናዊ ትጥቅ እያለው አንዱም አላዳነውም፤ ይንቃቸው በነበሩ መናኛ የጫካ ወሮበሎች በቀላሉ ተገፍትሮ ወደቀ፡- መጽሐፉ ‹ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም› እንደሚል መዘንጋት አይገባም፡፡ እነዚህኞቹ ፀረ-ኢትዮጵያ ጉጂሌዎችም አይነጋ መስሏቸው የኢትዮጵያ ታሪክ መዝገብና ሕዝቡ ሊሸከሙት ያልተቻላቸው ግፍና በደል በሀገርና በሕዝብ ሠሩ፤ ዋናዎቹ የአገዛዙ ቁንጮዎች በሣምንታት ልዩነት ወደማይቀሩበት የሲዖል ሥፍራቸው ተጓዙ፤ ቀሪዎቹም በመኖርና ባለመኖር አጣብቂኝ ውስጥ ተሰንቅረው ያደርጉትን በማጣት ፈጣሪ ሩህያቸውን ጨርሶ እስኪወስዳት እየተንጠራወዙ ይገኛሉ – ይህን እውነት ማስተሃቀር ፈጽሞውን የሚቻል አይደለም፡፡ ለውስጥ አዋቂዎች ወያኔዎች በሕይወት እንደሌሉ ከገባን ቆይተናል፡፡ በሕይወት ያሉ እንዲመስሉ የሆነው ምናልባት ለበጎ ነው፡፡ እንጂ እንደእውነቱ ወያኔ አከርካሪው የተመታው ዋናውን የሥርዓቱን መሃንዲስ መለስ ዜናዊን ፈጣሪ ባልተጠበቀ ወቅት ገና በ‹ማለዳ ዕድሜ›ው ሲጠራው ነው፡፡ ልብ ከተገኘ “ሁሉም ከእያንዳንዱ፣ እያንዳንዱም ከሁሉም እንዲማር ጊዜ ለመስጠት ተብሎ ነው የወያኔ የማይቀር ኅልፈት አዝጋሚ እንዲሆን የተደረገው” ብሎ ማሰብም ይቻላል – ምንም ነገር ማሰብ በማንም አልተከለከለምና (ወያኔዎች ግን ይህንንም ተፈጥሯዊ መብት ሊነፍጉን ይቃጣቸዋል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖርክ ወያኔን ስለመጣል ወይም በሀገሪቷና በሕዝቡ ላይ የጣሉትን ግፈኛ የአገዛዝ ቀምበር ስለመቃወም “ማሰብ”ም አትችልም – ማሰብህ በዐይነ ውኃህ የፊት-ንባብ ከተደረሰበት በአሸባሪነት ተጠርንፈህ ዘብጥያ ትወርዳለህ)፡፡ ማሰብ በቻልንበት ሃሳብ ውስጥ በጊዜ ሰጪነት የምንጠረጥረውን አካል ደግሞ ለሁላችንም እኩል በሚገባን ቋንቋ አቶ ታሪክ ልንለው እንችላለን፡፡ ታሪክ የሚያዳላ ይመስለናል እንጂ ለማንምና ለምንም በጭራሽ አያዳላም – የራሱ የጊዜ ቀመር እንዳለው ግን ማጤን ተገቢ ነው (እርግጥ ነው – ‹መብሰሉ ለማይቀረው ጭንቅላት እንጨት ይፈጃል› እንደሚባለው አንድ ታሪካዊ ኹነት ተከናውኖ ቀጣዩ ሌላ ኹነት እስኪከናወን የሚኖረው የጊዜ እርዝማኔ በትግስታችንና በሃይማኖታችን ጭምር አሉታዊ ጥላውን ማጥላቱ የማናልፈው የዘመን ቅጣት ይመስላል፤ ማን ነበረች – አዎ፣ ሜሪ አርምዴ – “ፍቅር ያዘኝ ብለሽ አትበይ ደንበር ገተር፤ እኛም አንድ ሰሞን እንደሱ አ’ርጎን ነበር፤› ያለችውን የዘፈን ግጥም አለመዘንጋት የአጽናኝነት ጠቀሜታ አለውና እናስታውሰው፡፡) ዕድሜ ይስጠን ሁሉን እናያለን፡፡ ሌላ ዘፋኝም “እናያለን ገና” ብሏል፡፡ ይህንኑ ዘፈን ልጋብዛችሁና እንለያይ፡፡ ጣሊያኖች ሲለያዩ “አሪቬዴርቺ” ይላሉ – በ“ሰላም ያገናኘን” ለማለት፡፡
ሰበር መርዶ!
ይህን ጦማር ጽፌ የጨረስኩት ሌሊት ነው፡፡ ጧት ወደሥራ ልሄድ ስነሳ እንደወትሮው ሁሉ ቤቴ አጠገብ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን ወደዬክፍላቸውን ከማስገባታቸው በፊት ሰንደቁ አጠገብ አሠልፈው ብሔራዊ መዝሙር በቴፕ ከፍተው ሲያጮኹ ሰማሁ፡፡ ይሄኔ ኮምፒውተሬን ከፍቼ ይህችን ሃሳብ በሰበር መርዶነት ለመሰንቀር ወደድኩ፡፡ የሀገር ሞት ከዚህ በላይ የለም፡፡ በጥንት ጊዜ ብሔራዊ መዝሙር ተማሪው ነበር በስሜት ተውጦ በመዘመር ወደክፍሉ የሚገባው፡፡ አሁን ዕድሜ ለወያኔ አዲሱ መዝሙር ሊያውም በመሣሪያ ብቻ የተቀነባበረው በቴፕ ይዘፈንና ወደክፍል ይገባል፡፡ ዛሬ ዛሬ የኢትዮጵያን ብሔራዊ መዝሙርና ባንዴራ የሚያውቅ ትውልድ እየጠፋ ነው፡፡ ራሱ መለስ ዜናዊ (በሕይወት ኖሮ) ይህን መዝሙር ውጣው ቢባል የሚችለው አይመስለኝም፡፡ ሌሎቹ የወያኔ ባለሥልጣናት ቢጠየቁም የሚያውቁት ስለመሆናቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም – ብቸኛ ዘመዳቸው ሆዳቸው በመሆኑ ስለሀገር ምንነት የሚያውቁት ነገር የለም ማለት ይቻላል፡፡ የሚሰቀለው ባንዴራ ደግሞ የተቀዳደደ፣ የነተበ፣ ቀለሙን የለወጠ፣ ከተሰቀለ የማይወርድና ተበጣጥሶ እስኪያልቅ 24 ሰዓት የሚውለበለብ የማን ሀገር ባንዴራ መሆኑም የማይታወቅ ነው፤ የጥንቱን የባንዴራ አሰቃቀልና አወራረድ ሥርዓት የሚያስታውስ ዜጋ የአሁኑን ሲያይ ያለቅሳል፡፡ ከአዲስ አበባ ወጣ በሚል ቦታ ደግሞ የኦሮሚያ ባንዴራና የኦሮሚያ ብሔራዊ መዝሙር በትምህርት ቤቶች እንደዚሁ በቴፕ ሲዘመር ወይም ልጆች በግዴታ አጥንተው እንዲዘምሩት ሲደረግ ታያላችሁ፡፡ ይህችን የነፃነት ምኩራብ የሆነች የታሪክ አምባ ሀገራችንን እንዲህ ባለቤት ያሳጧት የሰይጣን ልጆች ዋጋቸውን ሳያገኙ ከቀሩ በርግጥም ኢትዮጵያ ፈጣሪ የላትም፡፡ አላስችል ብሎኝ አሁን በእግረ መንገድ ትንሽ ለመናገር ፈለግሁ እንጂ ይህ ጉዳይ ብዙ የሚያናግር ነው – የጋራ የሚባለል አንዳችም ነገር እንዳይኖረን ከፍተኛ የጥፋት ሥራዎች በመሠራታቸው አሁንና ለጊዜው ጠፍተናል፤ አለን እንላለን እንጂ በርግጥም በወኔያዎች ደባና ሤራ የአብሮነት ኅልውናችን አደጋ ላይ ወድቋል – ብዙ የትስስር ገመዶች ተበጣጥሰዋል፡- የጋራ ቋንቋ፣ የጋራ መሪ(ዎች)፣ የጋራ የመከላከያ ጦር፣ የጋራ የፖሊስ ሠራዊት፣ የጋራ ድንበር፣ የጋራ ባህል፣ የጋራ ትውፊት፣ የጋራ ሥነቃልና ሥነ ጽሑፍ፣ የጋራ ቤተ መንግሥት፣ የጋራ መንግሥታዊ መዋቅር፣ የጋራ… የጋራ… የጋራ… የምንለው ነገር እንዳይኖረን ተደርገን አንዳችን አንዳችንን የጎሪጥ እንድናይና እንድንፈራራ ተደርገናል፡፡ ሌላው ሁሉ ቀርቶ የጋራ ስብዕና ወይም የሰውነት ደረጃ እንኳን የለንም፤ አንዱ ከሌላው የበለጠ ሰው ነው – ሌላውም ከአንዱ ያነሰ ሰው ነው፡፡ አንዱ የሰው ዘር ከሌላው በተለዬ ምርጥ ነው – ሌላው ደግሞ ውዳቂና ቢገድሉት የበቃ ነፍሱ ከእንስሳት ነፍስም ሳይቀር ያነሰ ዋጋ ያለው ነው – ሩቅ ተመልካቹ ጆርጅ ኦርዌል ጨርሶታል – “All animals are equal, but some are more equal than the others.”፡፡ በዚህ መልክ በፈረጁን ሰዎች ነው እንግዲህ አጥንታችን ድረስ ዘልቆ በሚጠዘጥዝ መሪር ፈረዖናዊ አገዛዝ እየተቀጠቀጥን የምንገኘው፡፡
ያን ደገኛ ኢትዮጵያዊ የአንድነት መንፈስ ለማምጣት እነቴዲ አፍሮን የመሰሉ የቁርጥ ቀን ልጆች ብቻ ሣይሆኑ ሁላችንም የየበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል – ለራሳችንና ለልጆቻችን ስንል፡፡ ከራስ ወዳድነትና ከአህያይቷ የ‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል› ያረጀ ያፈጀ አስተሳሰብም ባፋጣኝ እንውጣ፡፡ አርቀን መመልከትን ባህላችን እናድርግ፡፡ ጎርፉ ሳይደርስብን ራሳችንን በኅሊና ጸጸት አጥበን ለመጪው መልካም ኢትዮጵያዊ ዘመን ዝግጁ ሆነን ለመጠበቅ እንሞክር፡፡ በየድረ ገጹ የሚታዬው ዘረኝነት ላይ የተመሠረተ ወያኔያዊ የዱባ ጥጋብ መሰል ቡራከረዩና ወንዝ የማያሻግር ከፋፋይ ፕሮፓጋንዳ ዘመኑን እያገባደደ በመሆኑ የአንዲት እናት ልጆች ነንና እንሶብር፡፡ ወያኔ የጋተንን ብርብራና መቅመቆ ማርከሻ እንፈልግለት፤ “ስሜት-ወለድ” ማስጠንቀቂያየን እዚህም ላይ ልድገመው – “እዩዩኝ ያለ ደብቁኝ ደብቁኝ ይላል”፡፡
ከቃሊቲና ቂሊንጦ እስር ቤቶች በላይ የሚያንጸባርቁ ከዋክብት ዳዊት ከበደ ወየሳ (አትላንታ)
(ይህ ጽሁፍ የርዕዮት አለሙ የልደት በአል በአዲስ አበባ በተከበረበት ወቅት; ከውጭ አገር ንግግር እንዳደርግ በተጋበዝኩበት ወቅት… የስራ ባልደረቦቼን እስክንድር, ውብሸት እና ርዕዮትን በማሰብ የተዘጋጀ ነው)
ይህ ሳምንት የታላቁ ማርቲን ሉተር ኪንግ የልደት በአል በመላ አሜሪካ የሚከበርበት ነው:: በአሜሪካ ከክርስቶስ ልደት ቀጥሎ ስራ እና ትምህርት ቤት ተዘግቶ ልደቱ የሚከበርለት አንድ ሰው ቢኖር ማርቲን ሉተር ኪንግ ብቻ መሆኑን ልብ ይበሉ:: የማርቲን ሉተር ኪንግ የልደት በአል በሚከበርበት ወቅት በህይወት ዘመኑ ለጥቁር ህዝብ ነጻነት ያደረገው አስተዋፅኦ ይታወሳል:: በህይወት በነበረበት ወቅት ለሰው ልጅ እኩልነት ተሟግቷል; የነጻነት ቀንዲልን ለኩሷል:: ሆኖም እኩልነት እና ነጻነትን ሳያጣጥም በበርሚንግሃም እስር ቤት ተጥሎ ፍዳውን እንዲቆጥር ተፈርዶበት ነበር:: በመጨረሻም የሰውን ልጅ ክብር እና ነጻነት በማይደግፉ ሰዎች ህይወቱ ማለፉ ይታወቃል – መልካም ስራዎቹ ግን አላለፉም::
ዛሬም በአገራችን ስለፍትህ, ስለነጻነት የሰበኩና የደሰኮሩ; የጻፉና የመሰከሩ… ለሃቅ ቆመው፣ ግፍ የተሰራባቸው፣ ከአገር የተሰደዱና የወጡ፤ በግፍ ሰንሰለት ለጨለማ እስር የተዳረጉ ወገኖቻችን ብዙ ናቸው:: እስክንድር፣ ውብሸት፣ ርእዮት፣ አንዷለም እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን በሰብአዊነት መሰረት ላይ ስላነጹ እና ሃሳባቸውን በነጻነት ስለገለጹ መጨረሻቸው እስር እና እንግልት ሆኗል::
እንደ እውነቱ ከሆነ ሃሳብን በነጻነት መግለጽ… ብሎም የህዝብ ልሳን ሆኖ ለህዝብ የቤዛነት ዋጋ መክፈል የሚያስከብር እንጂ የሚያሳስር አልነበረም:: በመሆኑም ለነጻ ፕሬስ መክፈል የሚገባቸውን ዋጋ ከመጠን አሳልፈው የከፈሉት፤ ርዕዮት አለሙ፣ እስክንድር ነጋ እና ውብሸት ታዬ… ሶስቱም ከአገራቸው አልፈው በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና አግኝተዋል:: በአለም አቀፍ ደረጃም በልዩ ልዩ አለም አቀፍ የጋዜጠኞች ማህበራትና ተቅውውማት ለሽልማት ታጭተው አሸናፊ ሆነዋል::
የ’ነዚህ የስራ ባልደረቦቼ ብዕር… ህዝብን ሳይሆን የተወሰኑ ወገኖችን አሸብሮ ሊሆን ይችላል:: እነርዕዮት አለሙ በዚህ አይነት ሰበብ አስባብ በቃሊቲ እና በቂሊንጦ እስር ቤት ታግተው፤ ነጻነታቸውን አጥተውና ህክምና ተነፍገው ይታሰሩ እንጂ፤ ለእውነት የቆሙ ወገኖች ግን ለመልካም ስራቸው ሽልማትን አልነፈጓቸውም::
ማርቲን ሉተር ኪንግ በበርሚንግሃም እስር ቤት ታስሮ ቢማቅቅም የአሜሪካም ሆነ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ አልዘነጋውም:: ቆይቶም ቢሆን የአለም አቀፉ ኖቤል ተሸላሚ እስከመሆን ደርሷል:: ዛሬ በእስር ላይ የሚገኙት የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች የኖቤል ተሸላሚ ባይሆኑም አለም ግን አልረሳቸውም:: ከታሰሩበት የጨለማ ወህኒ ቤት ጀርባ፤ ከብረት ፍርግርግ እና ከግድግዳዎቹ ባሻገር በመቶዎች፣ በሺዎች እና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እነዚህን ጋዜጠኞች በመልካም ስራቸው ያስታውሷቸዋል; ይዘክሯቸዋል:: ስለሆነም የጻድቃን ሞት፤ የሰማዕትነት ጽድቅ ተደርጎ እንደሚቆጠረው ሁሉ… የነ እስክንድር፣ ውብሸትና ርዕዮት እስር፤ ከቶውኑ ዋጋ ቢስ እና ፍሬ አልባ ሊሆን አይችልም::
ኢትዮጵያ ውስጥ በነበርኩበት ወቅት በፕሬስ ጉዳይ ተደጋጋሚ የሆነ እስር ደርሶብኛል:: በ’ነዚህ የእስር እና እንግልት ጊዜያት ግን… ከጨለማው እስር ቤት ማዶ ለምን እንደታሰርኩ የሚረዱ ሺዎች በመኖራቸው ሁልጊዜ እጽናና ነበር:: በተደጋጋሚ እስር ቤት እየመጣ የሚጠይቀኝ እና የዋስ መብቴን አስጠብቆ ከእስር እንድወጣ ያደርገኝ የነበረው ወላጅ አባቴ፤ “የታሰርከው ሰርቀህ ወይም ሌላ ወንጀል ሰርተህ ሳይሆን፤ እውነትን ስለተናገርክ ነው:: ስለዚህ አንገትህን ቀና ልታደርግ እንጂ ልትሸማቀቅ አይገባህም::” የሚል አጽናኝ ቃል ሁሌ ይነግረኝ ነበር:: ዛሬ አባቴ በህይወት የለም:: ቃሉ እና ምክሩ ግን አብሮኝ አለ:: በእስር ላይ ለሚገኙ የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች፤ “አንገታችሁን ቀና አድርጉ!” የሚለውን መልዕክት አጋራቸዋለሁ::
ዛሬ በጋዜጠኞቻችን ላይ የተለያዩ ክሶች ተመስርቶባቸው መታሰራቸው ሳያንስ; ከታሰሩም በኋላ በሃሰት ሊወነጅሏቸው የሚሹ ብዙ ግራ ዘመም ሰዎች መኖራቸውን ታዝበናል:: በአሜሪካ ከፍተኛ የአየር ሽፋን አግኝቶ ዲሞክራቶችን በመሳደብ የሚታወቀው ራሽ ሊምቦ የተባለ ጋዜጠኛ በቅርቡ ኔልሰን ማንዴላ በሞት ሲለዩ… “ብታምኑም ባታምኑም ኔልሰን ማንዴላ አሸባሪ ነበሩ::” ብሎ ሰፊ ሙግት ፈጥሮ ነበር:: ይህ አባባሉ ለኛ እና ለሌሎች አፍሪቃውያን ሊገርመን ይችል ይሆናል:: ነገር ግን የራሳቸው አመዛዛኝ ህሊና ያልፈጠረባቸውና ይህን ሰው በጭፍን የሚከተሉት ሰዎች “አዎ ማንዴላ አሸባሪ ነበሩ” ብለው ቢሉ ሊገርመን አይገባም::
ዛሬም ባገራችን በተመሳሳይ መልኩ የነርዕዮት አለሙን መልካም ስም ጥላሸት ለመቀባት እላይ ታች የሚሉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ… እኛ ግን እንላለን:: “ወንጀል አልሰራችሁምና አንገታችሁን ቀና አድርጉ!” ስማችሁ ከቃሊቲና ከቂሊንጦ እስር ቤቶች በላይ፤ በጠራው ሰማይ ላይ ያንጸባርቃል፤ ቃለ ሃቃቹህ በአየር ናኝቶ… ኢትዮጵያዊያን ባሉበት ሁሉ በመላው አለም ላይ ተሰራጭቷል::
የማርቲን ሉተር ኪንግ ልደት ሲከበር መልካም ስራዎቹ እንደሚወደሱ ሁሉ፤ ዛሬም ሆነ ወደፊት የነርእዮት አለሙ ልደት ሲከበር መልካም ስራዎቻቸው በተደጋጋሚ ይነሳሉ ይዘከራሉ:: ዛሬ ማንዴላን አሸባሪ ብለው የሚከሱ ሰዎች እንደመኖራቸው መጠን; በተመሳሳይ መልኩ ለነርእዮት አለሙ ተመሳሳይ ስም የሰጡና ያሰጡ… ለመስጠት እና ለማሰጠት የሚጥሩ ሰዎች አሉ:: እኛ ግን የተለኮሱ ሻማዎች ይዘን ልደት ስናከብር; የብርሃናችን ጮራ፤ ሌሎች የፈጠሩትን የጨለማ ድባብ ሰንጥቆ… አንዳች ብርሃን እንደሚፈነጥቅላቸው በማመን ነው:: ዛሬ የርዕዮት አለሙን የልደት ቀን ስናከብር፤ ያለፍትህ የታሰሩትን ፍትህ የሚፈልጉትን፤ ነጻነት የተጠሙትን ነፍሶች በማሰብ ጭምር ነው::
መልካም ልደት – ርዕዮት!
አንድነት –እነ አንዷለም አራጌ ነገ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ
አንድነት – እነ አንዷለም አራጌ ነገ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ
ዝርዝር ለማንበብ እዚህ ይጫኑ !
አቡጊዳ –የአንድነት ፓርቲ ወጣት አመራሮች ከኢሳት ጋር ያደረጉት ጠንካራ ቃለ ምልልስ –ክፍል 1
የአንድነት ፓርቲ ወጣት አመራር አባክላት ም/ፕሬዘዳንቱ አቶኢ በላይ በፍቃዱና የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊዉ አቶ ሃብታሙ አያለው ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልሶች ጠንካራ ጥያቄዎች ቀርበዉላቸዋል። ቢሳት የቀረቡት ጥያቄዎች ተመሳሳይነት ያላቸው ከመሆናቸውም በተጨማሪ የአንድነትን ፓርቲ አመራሮችን ተስፋ ለማስቆረጥና ኮርነር ለማድረግ ሆን ተብሎ ተመርጦ የተዘጋጁ ጥያቄዎች እንደሆኑ ብዙዎች እየተናገሩ ነዉ።
ከኢሳት የተነሱ ጥያቄዎች ይዘት ተመሳሳይነት መኖራቸው የኢሳትን ገለልተኝነት የማይንጸባርቁ እንደሆኑ ብዙዎች ቢናገሩም፣ የአመራር አባላቱን በሳል መልስ ሳያደንቁ አላለፉም።
መደመጥ ያለበት አቶ በላይ በፍቃዱና አቶ ሃብታሙ አያሌው፣ ያደረጉትን ክፍል 1 ቃለ ምልልስ ለማዳመጥ እዚህ ይጫኑ !
አቡጊዳ –የአንድነት ፓርቲ ወጣት አመራሮች ከኢሳት ጋር ያደረጉት ጠንካራ ቃለ ምልልስ –ክፍል 2 እና 3
የሚኪያ በሀይሉ የቤተልሔም ት/ቤት የልጅነት አብሮ አደጐች የሀዘን መግላጫና የመፅናኛ መልዕክት
ሚኪያ በሀይሉን በሀዘን ላጣችሁ ሁሉ ፈጣሪ አምላክ መፅናናትን ይላክላችሁ!
በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን! የእግዚያብሔር አብ ቸርነት፤ የድንግል ማሪያም አማላጅነት፤ የልጇ የእየሱስ ክርስቶስ ምህረት፤ የመንፈስ ቅዱስ ፀጋና በረከት፤ የጻድቃን ሰማዕታት ተራዳኢነት እህታችንን በሀዘን ከተነጠቅነው ቤተሰቦች፤ ዘመዶች፤ አብሮአደጐች፤ጐረቤቶች፤ ጓደኞችና የጥበቧ አፍቃሪዎች ጋር ሁሉ ይሁን አሜን! እሱ ሀያሉ አምላክ ልዑል እግዚያብሔር ብርታቱንና መፅናናቱን ለሁላችንም ይስጠን አሜን።
የኛ የሚኪያ አብሮ አደጐች ሀዘን ጥልቅና የመረረ ቢሆንም የውድ ቤተሰቦቿ፡ የቅርብ ዘመዶቿና የቦንቱ ናንሲ ሀዘን ግን ከእኛ በላይ የከበደ መሆኑን ከቅርብና ከሩቅ ሆነን በሚገባ ተረድተናል። በልጅነት ዕድሜ በቤተልሔም ት/ቤት ውስጥ አብረናት ያደግነው የእሷ ዘመን ተማሪዎች ከሀገር ውስጥም ሆነ ከባህር ማዶ ሁነን ውድ እህታችንን በሀዘን ስናስባት ሀዘናችሁ የእኛም ሀዘን መሆኑን በዚህ አጋጣሚ በመግለፅ ጭምር ነው። ሚኪያ
ከእኛና ከብዙዎቻችው ዘንድ በአካል የተለየች ነገር ግን በውስጣችን ህያው ሁና የምትኖር የዘመናችን ዕንቁ ወጣት ነች። እግዚያብሔር
መርጦ የሰጣትን የተፈጥሮ ችሎታ ያልቀበረች፤ ይልቁንም ለበጎ አላማ የተጠቀመችበትና ሀገርንና ህዝብንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስጠራት የሞከረች የሀገርና የህዝብ ወኪልም ነበረች። ብዙ ታአምር መስራት በምትችልበት የለጋነት ዕድሜ በአምላኳ ፈቃድ በመጠራቷ ድንጋጤውና ሀዘኑ ቅስማችንን ቢሰብረውም ትታልን በሄደችው ቅርስና ጥበብ ግን ወደፊት ስንዘክራት እንኖራለን። አብረናት ባደግንባቸው በእነዛ የማይተኩ የልጅነት ዘመናት ውስጥ ያጠራቀምናቸው ትዝታዎች እንዲህ በቀላሉ የሚዘነጉና
ከአዕምሮአችን የሚጠፉ ባለመሆናቸው ምናልባት አንድ ቀን እሷንና ብዙዎቻችንን ያስተሳሰረውን የአብሮ አደጐች ትዝታ የምንተርክበት
አጋጣሚ ወደፊት ይመጣ ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ፈጣሪ አምላክ ነፍሷን ከአብርሃም ከያዕቆብና ከይስሐቅ ጐን ያሳርፍልን። ምህረትን ሰጦ ነፍሷን ይማርልን። እናንተን ውድ ቤተሰቦቿንም ብርታቱን፤ መፅናናቱንና ጥንካሬውን በቶሎ ይላክላችሁ እንላለን።
ከቤተልሔም ት/ቤት የልጅነት ጓደኞቿ
Yebethlehembach1990@yahoo.com
ነፍስ ይማር
ከዚህ በታች ያለውን ግጥም ምትክ ለማናገኝላትና ገና በወጣትነት ዕድሜ ድንገት ለተለየችን ገጣሚና ታዋቂ ድምጻዊ ሚካያ በሀይሉ ሳበረክት ከህጻንነት ዕድሜ ጀምሮ በቤተልሔም ት/ቤት ውስጥ አብረናት ባደግነው የእሷ ዘመን ተማሪዎች ስምና ከእኛ ዕድሜ በላይ እንዲሁም በታች በዛው ት/ቤት ውስጥ በተማሩ ተማሪዎች፤ መምህራኖችና ሰራተኞች ስም ጭምር ነው። የሚኪያ ድንገተኛ ህልፈት በተለይ ከሀገረ ኢትዮጵያ ተለይተው በምዕራቡና በተለያዩ ዓለም ሀገራት ለረጅም ዘመን የሚኖሩትን የቅርብ ቤተሰቦች፤ ዘመዶች፤ አብሮ አደጐችና የጥበቧ አፍቃሪዎች ከማሰደንገጡም በላይ ለረጅም ዘመን በአካል ሳያገኟት በለጋነት ዕድሜ በመለየቷ የተሰማቸውን ከባድ የሀዘን ስሜት በአይነ-ህሊናዬ እንዳስተውለው አድርጐኛል። ህልፈቷን ድንገት በሰማሁበት ወቅትም የተሰማኝ ከፍተኛ የሀዘን ስሜት ከብዙዎቻችሁ ስሜት ጋር ይመሳሰል ይሆናል ብዬ ስለገመትኩ እንደ ፀበል ተረጭቶ የደረሰኝን በጣም ትንሽ የግጥም ስጦታ በመጠቀም የብዙዎቻችንን የሀዘን ስሜት (ከገለፀው በሚል) ከዚህ በታች እንደሚከተለው በግጥም ደረደርኩት ።
ከቅጥርዋ ግቢ ከሚሞቀው ጓዳ
ያቺ ቤተልሔም ኮከብ ወልዳ ወልዳ
እኔን ለምስክር እነሱን ለትንግርት ደባልቃ አሳድጋ የማልከፍለውን ሞት እንደ ብድር አርጋ
በል ክፈል አለቺኝ ሚካዬን በዕዳ።
ምነው እትዬ ቆንጂት ምነው ጋሽ አዲሱ?
በተቀደሰው ቀን መርዶን ማርዳታችሁ በዕለተ ሐሙሱ። ባሕር ማዶ ሆኜ ድምጿን ባየር ሞገድ ስጠብቅ በተስፋ
ቪኦኤ አረዳኝ ሳያስጠነቅቀኝ ገላልጦ በይፋ። መርዶ ሞገድ ሆኖ ባሕር ተሻገረ
ደረት መቶ መቅበር ሳልስት መቀመጥ 40 ማውጣት ቀረ።
ያ የጥበቦቸ ቤት የምርጦቸ መፍጠሪያ
ቴድሮስን የሰጠን ሚኪያን የሰጠን ለሀገር ማስጠሪያ
ምን ብሎ ይሆን ይሆን? ድንገት ሞት ሲነጥቀው ኮከቡን ከጉያ?
አባቷ ወለዱ እናቷ ወለዱ ላገር የምትበቃ ኩሩ ኢትዮጵያዊ
ቅኔውን የምትዘርፍ፤ ወርቁን የምትመዝን፤ሰሙን የምታቀልጥ አማላይ ድምፃዊ ግና ምን አተረፍን?
አስር ሀያ አመት አይኖችሽን ሳናይ አይናችንን ሳታይ ከአንጀት ተነፋፍቆ በሬዲዮ ሞገድ ለዛውም በግላጭ መርዶሽን ጠብቆ
በባይተዋር አገር በባዕዳን ምድር በእንባ ተንሰቅስቆ
ሀዘን ያደማውን የልጅሽን አንጀት እንደ ዝናር ታጥቆ ሰራቂ ድምፅሽን የጥንት ትዝታሽን ዘላለም ሰንቆ
ሚካዬን የሚያክል አብሮአደግ ያገር ልጅ በሀዘን ተነጥቆ እ…ህ….እየተባለ በቁጭት ህይወት ላይ ፀፀትን አጥልቆ ኪሳራ ነው እንጂ ትርፍማ መች ታውቆ!
እንግዲህ ቤተሎች እርማችሁን አውጡ ድፍን ኢትዮጵያዎች እርማችሁን አውጡ የድምጿ አፍቃሪዎች እርማችሁን አውጡ አምላክ የጠራትን ምትክ ላታመጡ። ከዚህ ክፉ ምድር የሱ-ዓለም ተሽሎ የፈጠራት አምላክ ልውሰድሽ ነኝ ብሎ በሰማዪ ገነት አኖራት ጨክኖ።
እንግዲህ ዘምሪ ከነኪሩቤል ጋር ከመላዕክቶች ጋር አውርጂ ምስጋና
ድሮም ስጦታሽ ነው ድምፅ ማንቆርቆሩ ማስረቅረቅ በዜማ። እኛ ግን……….
ነፍስ ይማር፤…. ነፍስ ይማር፤….. ነፍስ ይማር….. ብለናል
ለእናትና አባቷ ለምትክ ልጇ፤ ለስጋዋ ክፋይ መፅናናት ልከናል።
ደረጀ ሙሉጌታ ተፈሪ ከአትላንታ
Yebethlehembach1990@yahoo.com
የእነ አንዱዓለም አራጌ ቀጠሮ ተምታታ፤ ፍርድ ቤቱ ለጥር 30 ቀጥሯቸዋል፤ ሬጅስትራር በበኩሉ ጥር 24 ቀን 2006 ዓ.ም መቅረብ አለባቸው ይላል- ፍኖተ ነጻነት
ፍርድ ቤቱ ለጥር 30 ቀጥሯቸዋል፤ ሬጅስትራር በበኩሉ ጥር 24 ቀን 2006ዓ.ም መቅረብ አለባቸው ይላል
በነአቶ አንዱአለም አሬጌ ስም ያለው የክስ መዝገብን በሚመለከት በፌዴራል ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ከተከሳሽ ጠበቆችና ከቤተሰቦች ጋር ብንቀርብም ፍርድ ቤቱ ቀጠሮው ትላንት ስለ ማለፉ ተናግሯል፡፡ የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው አጀንዳቸው ላይ የያዙት ዛሬ ጥር 16 ቀን 2006 ዓ.ም መሆኑን ቢገልፁም በዳኛ አዳነ ንጉሴ፣ ዓሊ መሐመድ፣ አልመው ወሌ እና ሙስጠፋ አህመድ የተሰየመው ችሎት በበኩሉ የቀጠሮው ቀን ትላንት ማለፉን ተናግረዋል፡፡
ችሎቱ ቀጠሮው ዛሬ እንኳ ቢኆን መዝገቡ እጅግ ሰፊ በመሆኑ ውሳኔው እየተጻፈ በመሆኑ ምክንያት ለጥር 30 ቀን 2006 ዓ.ም እንዲቀርቡ አዟል፡፡
በሌላ በኩል የፍርድ ቤቱ ሬጂስትራር ቀጠሮው ዛሬ መሆኑን አምኖ ነገር ግን ለከሳሽ አቃቤ ህግ መጥርያ ያልተላከ በመሆኑ ለአቃቤ ህግ ድጋሚ ትዕዛዝ ለማፃፍ ጥር 21 ቀን 2006 ዓ.ም ችሎት እንድቀርቡ አዟል፡፡ ከሬጂስትራሩና ከፍርድቤቱ ቀጠሮ የትኛው ትክክል እንደሆነም ለማወቅ አልተቻለም፡፡
በሌላ በኩል አንድነት ፓርቲ ለክትትል ያመቸው ዘንድ የእስክንድር ነጋን የሰበር ሰሚ ይግባኝ ለማጣራት ሙከራ ቢያደርግም በእስክንድር ስም የቀረበ አንዳችም ይግባኝ እንደሌለ ሬጂስትራሩ አረጋግጧል፡፡ ባለቤቱን ጨምሮ ሎሎች አስተያየት ሰጪዎች ግን እስክንድር ያለ ጠበቃ ለመከራከር ይግባኝ ማለቱን አምነዋል፡፡
መንግስት ለአቶ አንዱአለም አያሌው ያቆማቸው ጠበቃና በሽብር ድርጊት ተጠርጥረዋል የተባሉትን ሰዎች ክስ የመሰረተው የመንግስት ዓቃቤ ህግ ከሀገር መሰደዳቸው ይታወሳል፡፡
አቡጊዳ –የአራና አመራር አባላት በሕወሃት ካድሬዎች በአዲግራት ተደበደቡ
ወጣት አብርሃ ደሳትን ጨምሮ በርካታ የአራና አመራር አባላት በሕወሃት ካድሬዎችን በአዲግራት እንደተደበደቡ በስፋት ኡእይተዘገበ ነዉ። አራና፣ አዲግራት በሚያደርጋቸው ስብሰባ ሕዝቡ እንዲሳተፍ በከተማዋ እየተዘዋወሩ ሲቀሰቀሱ ነዉ ተይዘው የተደበደቡት። ከአቶ አብርሃ በተጨማሪ፣ አቶ አሰግዴ ገብረስላሴ፣ አቶ አምዶም ገብረስላሴ ይገኙበታል። የተደበደቡት የአመራር አባላት ፣ ወደ ፖሊስ ተወስደዉ ፣ ለአራት ሰዓታት ታስረዉ፣ ስብሰባዉን እንዲሰርዙ ማስጠንቀቂያ ተሰቷቸው ተመልሰዋል። የደረሰባቸው ድብደባ በጣም የከፋ በመሆኑ አቶ አምዶም እና አስቶ አሰገዴ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።
የአዲግራትን ስብሰባ በተመለከተ፣ ከመደብደቡ በፊት በአብርሃ ደስታ የቀረበዉን ጽሁፍ እንደሚከተለው አቅርበናል ፡
የዓረና-ዓጋመ የእሁድ ስብሰባ – አብርሃ ደስታ
=====================
ዓረና መድረክ ከዓጋመ (ዓዲግራት) ህዝብ ጋር በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ለመወያየት ለእሁድ ጥር 18, 2006 ዓም በዓዲግራት ህዝባዊ አዳራሽ (ከጠዋቱ 2:30 ጀምሮ) ቀጠሮ መያዙ ይታወቃል። ዓረና ፓርቲ ለተሰብሳቢው ህዝብ አማራጭ ፖሊሲው ያስተዋውቃል፣ ፖለቲካዊ ትምህርት ይሰጣል፣ ያደራጃል፣ መረጃ ይለዋወጣል። የዓረና ዋነኛ ዓላማ ህዝብ ከጭቆናና ባርነት ለማላቀቅ ማስተማር ነው።
ህዝብ ካሁኖቹ ጨቋኞች እንዲሁም ለወደፊቱ ሊመጡ ከሚችሉ ጨቋኞች ነፃ እንዲወጣ ለማድረግ ፖለቲካ (ስለ መብትና ነፃነት) እናስተምራለን። ምክንያቱም አንድ ህዝብ (ወይም ብዙ ህዝቦች) ከጭቆና ለማላቀቅ ህዝብ መሳርያ ማስታጠቅ አለብን። የፀረ ጭቆና ሚሳኤል ፖለቲካዊ ትምህርት ነው። የፖለቲካ ትምህርት በመስጠት የህዝብ የፖለቲካ ንቃተህሊናው ከፍ እንዲል ማድረግ ይቻላል። ህዝብ የፖለቲካ ንቃተህሊናው ካዳበረ ለማንም ጨቋኝ ስርዓት አሜን ብሎ አይገዛም። መብቱ ማስከበር ይችላል። ነፃነቱን አሳልፎ አይሰጥም። ስለዚህ ፖለቲካዊ ትምህርት ፀረ ጭቆና ሚሳኤል ነው። ህዝብ ራሱ ከጨቋኞች ነፃ ለማውጣትና ለመከላከል ከፈለገ (አንድ) ፖለቲካ ማወቅ አለበት፣ (ሁለት) መደራጀት አለበት። ወደ ዓዲግራትና ሌሎች አከባቢዎች የምንቀሳቀሰውም ይህንን ፀረ ጭቆና ሚሳኤል ለማስታጠቅና ለማደራጀት ነው።
ህወሓቶች ግን ይህን ዓላማ እንዳይሳካ ጥረት ማድረጋቸው አይቀርም። ምክንያቱም ህዝብ ፀረ ጭቆና ሚሳኤል ከታጠቀ ለህወሓቶች አሜን ብሎ የሚገዛ አይሆንም። መብቱ ይጠይቃል፤ ነፃነቱ ይፈልጋል። ስለዚህ ህወሓቶች ህዝብ ይህንን ፀረ ጭቆና ሚሳኤል እንዲታጠቅ አይፈልጉም። በዚህ መሰረት ህዝብ ዓረና በጠራው የህዝብ ስብሰባ እንዳይሳተፍ የተለያዩ ዕንቅፋቶች መፍጠራቸው አይቀርም። ህዝቡ በስብሰባ እንዳይሳተፍ ማስፈራራታቸው አይቀርም። ምክንያቱም ህወሓቶች የህዝብን ማወቅ ያስፈራቸዋል። ምክንያቱም የህዝብ ማወቅ ለስልጣናቸው ስጋት ነው። ህዝብ አሜን ብሎ የሚገዛ እስካላወቀ ድረስ ብቻ ነው። ስለዚህ የህወሓቶች ስትራተጂ ህዝብ ወደ ስብሰባው እንዳይገባና እንዳያውቅ መከልከል ነው የሚሆነው።
የህወሓቶች ዕንቅፋት ሳይበግረን እንገባበታለን። ምክንያቱም የህዝብን የማሳወቅ ዓላማ አንግበናል። የኛ ዓላማ ህዝብ ስለ ፖለቲካዊ መብቱ ግንዛቤ ኖረት የራሱ ዕድል በራሱ እንዲወስን ማስቻል ነው። ለዚሁ ዓላማ ሟቾች ነን። ህወሓቶችም ለስልጣናቸው ሟቾች ናቸው። የህወሓት ሃይማኖት ስልጣን ነው። ስለዚህ ህወሓት ለስልጣኑ መስዋእት ይከፍላል። ለስልጣኑ ይሞታል። እኛም ለዓላማችን እንሞታለን። ሁለታችን ለተለያየ ዓላማ እንሞታለን፤ እንፎካከራለን። በመጨረሻም ሁላችን ፖለቲከኞች ሞተን የመጨረሻ ድሉ የህዝብ ይሆናል። ህዝብ ያሸንፋል።
እውን ፍቅር ያሸንፋል? ሽመልስ ከተማ
የቴዲ-አፍሮ እና የፕ/ር ኤፍሬም ይስሃቅ የፍቅር ያሸንፋል ጽንሰ-ሀሳቦች ( concepts) ብዙ አይገቡኝም፤ ፍቅር ነክቶኝ ስለማያውቅ ወይም የፍቅር የስበት ሃይል ሳይገባኝ ቀርቶ አይደለም፣ በቤተሰብ ደረጃ ቢሆን ይገባኛል፤ ከቤተሰብ አልፎ ግን ፍቅር እንዴት አድርጎ የአንድን አገር ውስብስብ ችግሮች ሊፈታ እንደሚችል ባስብ ባስብ መልሱ አልታይህ ብሎኛል። ፕ/ር ኤፍሬም ይስሃቅ በአዲስ አድማስ ላይ “የኢትዮጵያ ( ሰላም) መሠረቱ ህዝቡ ነው፡፡ ህዝቡ ባህል አለው፤ መንፈሳዊ ህዝብ ነው፤ ሰው የሚያከብር ነው፡፡ ከመካከላችን ግን አሉ፤ ሃይለኞች፡፡ በተለይ የማኪያቬሊን መጽሐፍ ያነበቡ፣ የማርክሲዝም ትምህርት ተምረው አንጐላቸው ትንሽ የዞረ ጥቂቶች አሉ ” ይላሉ። ፕሮፌሰሩ “ጥቂቶች” የሚሉዋቸው የእርሳቸውን “የፍቅር ፖለቲካ” አስተሳሰብ የማይቀበሉትን ነው፤ እኔም ከእነዚህ ጥቂት ከዞረባቸው ሰዎች መካከል ልመደብ እችላለሁ፣ አካሄዳቸው አይገባኝምና ። ችግሩ ግን እኔ የማኪያቬሌ ወይም የማርክስ ተከታይ አለመሆኔ ነው፣ ቃሊቲ እያለሁ የማርክስን “ዳስ ካፒታል” ለማንበብ ጀምሬ ሳልጨርሰው ወጣሁ፣ የማኪያቬሌን The Prince እና Discouses አይቻቸዋለሁ። ሁለቱም ፈላስፎች የእነ ፕ/ር ኤፍሬምን የ” ፍቅር ” ዜማ እንዳልቀበል ተጽእኖ አላሳደሩብኝም። ፍቅር ለዚህ አለም የህይወት ጣጣ መፍትሄ አለመሆኑን ለመከራከር እነዚህን መጽሀፎች ማንበብ አይጠበቅብንም ። ፍቅር ለወዲያኛው ዓለም ሊሰራ ይችላል፣ ለዚህኛውም ዓለም (ለምድራዊው) ግን አይሰራም ። ( በነገራችን ላይ የማኪያቬሌ ስም ብዙ ጊዜ አሉታዊ ከሆኑ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ሲቀርብ ይገርመኛል፤ የማኪያቬሌን The Prince ያነበበ ሰው ማኪያቬሌን የአምባገነኖች መካሪ አድርጎ ቢወስደው አይገርምም፣ ይሁን እንጅ Discourses ን ያነበበ ሰው ማኪያቬሌ ስልጣንን እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻል ያመላከተ ፣ ለዛሬው የዲሞክራሲ መገለጫ ለሆነው check and balance ጽንሰ ሀሳብ መነሻ የሆነ ሰው መሆኑን ያደንቃል ። )
ወደ ዋናው ነጥባችን እንመለስ፣ አዎ! የፍቅር ያሸንፋል ጽንሰ ሀሳብ የአገራችንን ሁለንተናዊ ችግር አይፈታም!
አንደኛ! በአገራችን በስርዓቶች አማካኝነት ብዙ በደሎች ተፈጽመዋል፣ የሩቁን ትተን፣ ከአስር አመታት በሁዋላ የተፈጸሙትን እንኳ ብናይ በምርጫ 97 200 ሰዎች ተገድለዋል፤ ከዛ በሁዋላ በኦሮምያ፣ ኦጋዴን፣ አማራ፣ አፋር፣ ቤንሻንጉል ወዘተ ቁጥሩ የማይታወቅ ህዝብ ተገድሏል፣ ታስሯል፣ ተሰቃይቷል። በእነዚህ ችግሮች ላይ ሳንነጋገር፣ አጥፊዎች ጥፋታቸውን አምነው ሳይቀጡ ወይም ይቅርታ ሳይጠይቁ ፣ ፍቅር ያሸንፋል በማለት ብቻ ችግራችን አይፈታም፣ በደል የደረሰባቸው ሁሉ ፍትህ ማግኘት አለባቸው። ፍትህም የሚገኘው አንድም አጥፊዎች በነጻ ፍርድ ቤት ጉዳያቸው ታይቶ ተመጣጣኝ ህጋዊ ቅጣት ሲሰጣቸው ( retributive justice) ሌላም አጥፊዎቹ ጥፋታቸውን አምነው በመጸጸት በደል የደረሰባቸውን ሰዎች ይቅርታ ሲጠይቁና ችግሩ ዳግም እንዳይፈጠር መስራት ሲችሉ ነው ( restorative justice) ። ተበዳይም በዳይም በአንድነት ተቻችለው እንዲኖሩ፣ ቢፋቀሩ ባይፋቀሩ የራሳቸው ጉዳይ ነው፣ ለሁለቱም የሚሆን ስርዓት እስከሰፈነ ድረስ በቂ ነው፤ ተኩላዎችንም በጎችንም እንደጠባያቸው አድርጎ የሚያስተዳደርው ስርዓት ደግሞ ዲሞክራሲ ነው፤ ዲሞክራሲ ፍጹም አይደለም፣ ነገር ግን መፋቀር የማይችሉትን ሰዎች ተከባብረው እንዲኖሩ ያደርጋል፤ የሚፋቀሩትንም ሆነ የማይፋቀሩትን ሰዎች በአንድ ላይ ለማኖር ከዲሞክራሲ ውጭ ለሰው ልጆች የተሰጠው ሌላ የተሻለ ስርአት የለም። እናም ቴዲ በመረዋ ድምጹ እንዲሁም ፕ/ር ኤፍሬም በውብ ብእራቸው ስለፍቅር ከሚሰብኩ ስለዲሞክራሲ ምስረታ ቢሰብኩ የችግራችንን ቁልፍ አገኙት እላለሁ።
ቴዲ አፍሮ ፍቅር ካለ ቂምና ቁርሿችን ሁሉ ይፈታል ይለናል፣ እንዲህ ያብራራዋል፦ ” ትልቁ ነጥብ፣ ካለፍንበት ታሪክ ተነስተን ለሚቀጥለው ጊዜ ምን እናድርግ የሚለው ነው፡፡ ያዘንበትን ነገር በይቅርታ ሰርዘን፣ የወደድነውን ነገር ደግሞ አሳድገን ለመጓዝ፣ ትልቁ መድሃኒት ፍቅር ነው፡፡ ይቅር ተባብሎ የቀድሞ ስህተቶችን ለማስተካከልና በህብረት ተጠራርቶ የቀድሞ ትክክለኛ ነገሮችን ለማሳደግ፣ ፍቅር ያስፈልጋል፣ የዘመናችን ፈተናዎች ሳያንሱ፣ የቅርብ ጊዜ የቂም ታሪክንም እየተሸከመን፣ ከዚያም አልፎ የሩቅ ጊዜ የቅሬታ ታሪኩንም እየቆሰቆስን ቂምን የምናወርስ ከሆነ፣ ለማናችንም ሕይወት የማይጠቅም፣ የልጆቻችንንም ተስፋ የሚያጨልም አደጋ እየፈጠርን እናልፋለን፡፡ ቂምን መሻር፣ ቁስልን መፈወስ፤ ከዚያም አልፎ ለሁላችንም የሚበጅና የተስፋ ብርሃንን የሚያደምቅ ነገር መስራት የምንችለው በፍቅር ነው”። የምር ይሄ ታምረኛ ፍቅር ለእኔ አልገባኝም፣ እንዴት እንደሚገኝም አላውቅም፣ እንዴያውም ለእኔ ፍቅር ይመጣል ከተባለም፣ ይቅር ከተባባልን በሁዋላ እንጅ፣ ይቅር ሳንባባል እንዴት ሊመጣ እንደሚችል አይገባኝም፤ ከፈረሱ ጋሪው ቀድሞብኛል፤ ቴዲ እስከ እነ ችግራችን አፍቃሪ መሆን የሚያስችለን መድሃኒቱ ካለው ቢነግረን አይከፋም፣ አልያ ግን ንግግሩ ባዶ ጩኸት ይሆንብኛል። የቴዲ ምርጥ ንግግር የመጨረሻዋ ቃል ” ዲሞክራሲ” በሚል ቢተካ ኖሮ ቴዲን ከምርጥ ተናጋሪዎችና አሳቢዎች ዘንዳ እፈርጀው ነበር። እንግዲህ ይሄ የፍቅር ቋንቋ ለእኔ ስላልገባኝ የቴዲ አድናቂዎች አትፍረዱብኝ፣ ከቻላችሁ አስረዱኝና እኔም ” ወይ ፍቅር” እያልኩ አብሬው ልዘምር።
ሁለተኛ! “የፍቅር ያሸንፋል” ጽንሰ-ሀሳብ በምድራችን ላይ ተግባራዊ ይሆናል ብየ የማላስብበት ተጨማሪ ምክንያቶች አሉኝ። ሰዎች ሁሉ እኩል ናቸው የሚባለው በእግዚአብሄር ፊት እንጅ በሰዎች ፊት (በምድር ላይ) አይደለም፤ ሰዎች በሃብት፣ በእውቅት በክብር ወዘተ ይለያያሉ። አንዱ የብር ማንኪያ ይዞ ይወለዳል፣ ሌላው እንደተወለደ የእናቱ ጡት እንኳን ይደርቅበታል፤ አንዱ የመጽሀፉን ቃል አምኖ ጥሮ ግሮ ለመኖር ይታትርና ባዶ እጁን ይገባል፣ ሌላው ሞጭልፎ በሳምንት ውስጥ አየር ላይ ካልተኛሁ ይላል። ክርስትና “ሰዎች በእግዚአብሄር ፊት እኩል ናቸው” ባይል ኖሮ ሃብታሞችና ድሆች እርስ በርስ የሚያደርጉት መገዳደል ይጨምር ነበር፣ አሁንም ይገዳደላሉ። በብሉይ ኪዳን “ደሃ ድህነቱን ይረሳ ዘንድ ወይን ይጠጣ” ይላል፣ የወይን መግዢያ የሌለው ድሃ ምን ጠጥቶ ድህነቱን እንደሚራሳ ግልጽ ባይሆንም፤ በአዲስ ኪዳን ደግሞ አባባሉ ተሻሽሎ “ሃብታም መንግስተ-ሰማያትን ከሚወርስ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀለዋል” ይላል። ይሄ አባባል ለደሃው ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ነው- ለእነማርክስ የአመጽ ጥሪ ማርከሻ ወርቅ መልእክት። ደሃ፣ ደሃ በመሆኑ መንግስተ ሰማያትን እንደሚወርስ ከተነገረው ደሃ ሆኖ መኖር እንጅ ሌላ ምን ይፈልጋል? ቢሞትም በቀጥታ የሚገባበትን ያውቃል፤ ሀብት አካፍለኝ ብሎ በሃብታሙ ላይስ ለምን ያምጻል? እስልምና በዚህ ጉዳይ ምን እንደሚል አላውቅም።
አንዳንድ ጊዜ ሃይማኖቱን የማይከተሉ ድሆች በሃብታሞች ላይ ማመጻቸው አልቀረም። ለወደፊቱም ያምጻሉ፤ እንደዛ ማድረጋቸውም ስህተት ነው ብየ አላስብም፤ እንዴያውም ለእኔ ስህተቱ ደሃ እስከ ድህነቱ የሞተ ጊዜ ነው፤ ሰርቶ ካላለፈለት አምጾ መብላት አለበት። አለም እኮ ጎደሎ ነች። አንዱ ጠግቦ ሌላው ተርቦ የሚያድርባት፣ አንዱ ሌላውን አሸንፎ የሚኖርባት የፉክክር መድረክ ፤ ተሸናፊው ያዝናል፣ አሸናፊው ይደሰታል። የእነ ቴዲ ” የተፋቀሩ መልዕክት” ሀብታምና ደሃን፣ ተበዳይና በዳይን፣ አሸናፊና ተሸናፊን አፋቅሮ ሊያኖር አይችልም። በክሬን ቢሳቡ እንኳ አይፋቀሩም! ተቃራኒ ሃይሎች ሳይበላሉና ሳይጠፋፉ ፍላጎታቸውም እንደተጠበቀ ሊኖሩ የሚችሉት፣ እንዲፋቀሩ በመምከር ሳይሆን፣ ሁሉንም አስማምቶ የሚያኖር ስርአት ሲዘረጋ ነው፤ ያም ስርአት ከላይ የጠቀስኩት “ዲሞክራሲ” የሚባለው ነው። ምሁራን democracies rarely go to war ይላሉ። እውነታቸውን ነው፣ እስከዛሬ ዲሞክራሲ አገሮች ሲዋጉ አላየንም፣ ተፋቅረዋል ማለት ግን አይደለም፤ ዲሞክራሲ የፍቅር መገለጫ ሳይሆን እሰከነ ቂምና ቁርሾ ተቻችሎ የሚኖርበት ስርዓት ነው።
ሶስተኛ! በአይናችን እንዳየነውና ተጽፎም እንዳነበብነው ተረጋግተው የሚኖሩ አገሮች የመረጋጋት መሰረታቸው ፍቅር ሳይሆን ስርዓት ነው። እኔ የምኖርባትን ሆላንድ ( ኔዘርላንድንስን) ተመልከቱ ፤ መብት እንደልብ የሆነባት ፣ ግብረሰዶማዊው በአደባባይ የሚሳሳምባት፤ ሀሺሻሙም ፍላጎቱን የሚያረካባት ነጻ አገር ናት። እንደፈለግን ብንሆን ማን ከልካይ አለብን የሚሉ ሰዎች ያሉበትን ያክል “ቴሌቪዥን የሃጢያት ስር ነው” ብለው ቤታቸው ውስጥ ቴሌቪዥን የሌላቸው ሰዎችም አሉ፤ በሁለቱም አይነት ሰዎች ቤት ገብቼ ተስተናግጃለሁ። አንዱ ሌላውን አጥብቆ ይጠላል ፣ ነገር ግን ሁለቱም አይጠፋፉም፤ በአንድ ስርዓት ውስጥ ተቻችለው ይኖራሉ። ደቡብ ሆላንድ ካቶሊክ ነው፣ ሰሜኑ ደግሞ ፕሮቴስታንት ፣ ሁለቱም አይዋደዱም፣ ቂምና ቁርሾ አላቸው፣ ሁለቱም ግን ተከባብረው በአንድ ስርዓት ስር ይኖራሉ፤ አሜሪካም ጥቁሩና ነጩ ቂም አለው፣ በአውሮፓ ህብረትም ጀርመንና ፈርንሳይ ብርቱ ቂም አላቸው፤ እንዲህ እያሉ የአገሩን ታሪክ ሁሉ መዳሰስ ይቻላል፤ ዞሮ ዞሮ የምንደርስበት መደምደሚያ ግን ፣ “አገር ተረጋግቶ የሚመራው አንጻራዊ በሆነ መልኩ ለሁሉም በሚሆን ስርአት እንጅ በፍቅር አይደለም የሚለውን ነው።”
አራተኛ ምክንያት! ስለፍቅር የሚሰብኩት የሃይማኖት አባቶች ራሳቸው ሲጣሉ እናያለን ። ወደው እንዳይመስላችሁ ፣ እነሱም የሚኖሩት በዚህ በጎደሎው አለም ውስጥ ስለሆነ ነው። ቀሳውስቱም ሼኹም በዚህ አለም መኖር የሚችሉት አሸናፊ ሆነው ሲገኙ ብቻ መሆኑን ባይረዱትም ያውቁታል፤ ምድራዊ ስልጣን ይፈልጋሉ፣ አልያ ሌላው ቦታቸው ላይ ይወጣና የጨፈልቃቸዋል። ስለፍቅር ቢሰብኩም የሚኖሩት ውድድር ባለበት አለም ነው፤ ውድድር ባለበት አለም ደግሞ ” ፍቅር” ቦታ የለውም። የሃይማኖት አባቶቹ ተቻችሎ የሚያኖር ፍትሃዊ ስርዓት ከላገኙ እነሱም እንደሌላው መባላታቸው አይቀርም። ቴዲ አፍሮ ከሁለቱም የኢትዮጵያ አርቲስቶች ጋር ፍቅር ነው ቢባል የአለምን እውነታ መካድ ነው የሚሆነው። ፕ/ር ኤፍሬምም ከሁሉም ሽማግሌዎች ጋር ፍቅር ናቸው ቢባሉ መዋሸት ነው የሚሆነው። እነሱም ከሁሉም ጋር ፍቅር ነን አይሉም፤ ነገር ግን ቴዲ ከአርቲስቶች ጋር ባይፋቀር እንኳ፣ ተወዳድሮ እንዲኖር የሚያደርገው ፍትሃዊ ስርዓት ያስፈልገዋል።
አምስተኛ! ከፍቅር ያሸንፋል ጀርባ ያለው መልዕክት፣ በተለይ የቴዲ፣ ቅደም ተከተሉን ቢያዛባውም፣ ቁጭ ብላችሁ ተነጋገሩ የሚል ነው። ጥሩ ሃሳብ ነው ሊባል ይችላል፣ ነገር ግን ይህም ቢሆን አልጋ ላይ ተኝቶ እንደማለም ቀላል አይሆንም ። ፖለቲከኞች ቁጭ ብለው የሚነጋገሩት በፍቅር ሳይሆን በሁለት ምክንያቶች ነው። አንዱ፣ አንደኛው ወገን አሸናፊ እየሆነ ሲመጣ እና ሌላኛው ወገን እየተሸነፈ መሆኑ ሲሰማው፣ ሁለተኛው ደግሞ፣ ሁለቱም ሳይሸናነፉ ጉልበታቸውን ሲጨርሱና ሲደክማቸው “እስኪ እርስ በርስ ከምንጠፋፋ እንነጋገርና” ሲሉ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ገዢው ፓርቲ እየተሸነፍኩ ነው ብሎ አያምንም፤ ስለዚህም ተፋቀር ስለተባለ ከልቡ ለድርድር አይቀመጠም፣ ተሸናፊዎችም ጉልበት ሳይኖራቸው የሚያደርጉት ድርድር ዋጋ እንደሌለው ያውቁታልና ከምር አይደራደሩም። በአጭሩ ፍቅር ወደ ድርድር አይወስድም፣ ምናልባት ድርድር ወደ ፍቅር ይወስድ ይሆናል፣ ለመደራደር ደግሞ ስርአት መገንባት አለበት።
አምስተኛ! የፍቅር ያሸንፋል መልዕክት አንዳንዴ አትታገሉ የሚል ድምጸትም አለው። በተለይ ለመብታቸው የሚታገሉ ሰዎችን ፕ/ር ኤፍሬም እንደ ሃይለኛ ወይም በሰከነ- አእምሮ የማይመሩ፣ አድርገው ይቆጠሩዋቸዋል፤ በተዘዋዋሪ መንገድ እንደ በጎች ሆናችሁ አገልግሉ በማለት ስርዓቱ እንዲቀጥልም የሚፈልጉ ይመስላል። ለመብትና ለእኩልነት መታገል እንደ እብደት ካስቆጠረ፣ በእርግጥም ሁላችንም እብዶች ነን፣ ባርነትን እምቢ ብለናልና። ፍቅር ግን ነጻነትን አያወርስም! በነጻ ለመኖር የሚፈልግ ሰው መታገል እንጅ ማፍቀር አይጠበቅበትም።
በቴዲ አፍሮ “የፍቅር ያሸንፋል” መልዕክት ውስጥ አትታገሉ የሚል ድምጸት አለው ባልልም፣ “ፍቅር ፍቅር” የሚለው ስብከት የመታገልን፣ ታግሎ የማሸነፍን ወኔ ይንድብኛል፣ የዚህን ዓለም እውነታ ያፋልስብኛል ። በተደጋጋሚ እንደገለጽኩት በዚህ ዓለም ለመኖር ታግሎ ማሸነፍ ግድ ይላል። በዚህ እና በወዲያኛው አለም መካከል ያለው ልዩነት በምን ይገለጻል ብትሉኝ መልሴ “በትግል ነው” የሚል ነው። በዚህ ዓለም መታገልና ታግሎ መኖር ግዴታና ቅድስ ነው፣ በወዲያኛው ዓለም ደግሞ መታገልና ታግሎ መኖር ግዴታም ቅዱስም አይደለም፣ ማርና ወተት እንደልብ ይፈስበታልና ( ሁለቱንም ለማትወዱ ግን እንጃ! ደግሞም መቼ ሄደህ አየኸው? እንዳትሉኝ)። ለማንኛውም በዚያኛው አለም ትግል የለም፣ ሀብታምና ደሃም የሉም፣ እኔና ቢል ጌት ከአንድ ማዕድ እኩል እንቆርሳለን፣ ስለዚህም ተፋቀሩ የሚለን ሳይኖር እንፋቀራለን። ምንስ የሚጣላን ነገር አለ? በሃብት እንዳንጣላ፣ ሀብት ማፍራት ክልል ነው፣ በሴት እንዳንጣላ ሴት መያዝ ክልል ነው ( ሰማይ ቤት የሚኖረን ጾታም አይታወቅም)፣ ለስልጣን እንዳንጣላ፣ ስልጣን በአንድ አምላክ በሞኖፖል ተይዟል፣ በእግዚአብሄር ላይ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ወይም መፈንቅለ መንግስት እናድርግ ብለን እንዳንነሳ ቀድም ብሎ የሞከረው ሳጥናየልም የተሰጠውን ቅጣት የምናውቀው ነው፤ ታዲያ ለምን አንፋቀር። መማር፣ መውደቅ፣ ማለፍ ምናምን የሚባል ነገር ከሌለ፣ ያለጭንቀት ጧት ተኝተን ማታ ከተነሳን መፋቀርማ ሲያንሰን ነው። እሱን ይጭነቀው እንጅ የእኛማ ስራ ቁጭ ብሎ መቀለብ ነው ( እንዳትወፍሩ ግን ስፖርት መስራት ልመዱ)። ትክክለኛው ፍቅር ያለው ሰማይ ቤት ነው። ቴዲ ወንድሜ፣ ምድር ላይ ትክክለኛውን ፍቅር አገኘዋለሁ ብሎ ባይደክም ይሻለዋል እላለሁ። ምናልባት እሱ አግኝቶት እኔ ሳላገኘሁ ቀርቼም ከሆነ የሚገኝበትን መንገድ ያመላክተኝና ልከተለው።
በመጨረሻም፣ ቴዲ አፍሮ “ፍቅር ያሸንፋል” እያለ ማዜሙን ትቶ “ዲሞክራሲ ያሸንፋል” እያለ ቢያዜም እሱ የሚመኘው መቻቻልና ተከባብሮ መኖር በእሱ እድሜ እውን ይሆናል እላለሁ። ቴዲና አድናቂዎቹ ምን ትሉ ይሆን?
ሁሉም አይነት አክራሪ መስመሮች ይጎዱናል!!! ከብስራት ኢብሳ (ሆላንድ)
የኛ ነገር፡ የተሸነፈ ርእዮተአገርና ገፊ ፖለቲካ፤ ስለመጪው ሶስተኛ ሪፐብሊክ፤ ካለፈው የቀጠለ፤ ሀ በተክለሚካኤል አበበ
ትንሽ ወደኁዋላ፤ እንደ መግቢያ
1.ግንቦት፤ 2003/2011፤ በቶሮንቶ ከተማ፤ ጃዋርና ኦባንግ፤ አሎ አይደሂስና (ሸጋ የአፋር ሰው ነው) አበበ በለው በእንግድነት የተገኙበትን ሕዝባዊ ስብሰባ ተንተርሼ፤ አንድ ወርቅ የሆነ ጽሁፍ ጽፌ ነበር፡፡ ጽሁፉን ያላነበባችሁ ብታነቡት፤ ያነበባችሁትም ብትደግሙት አይቆጫችሁም፡፡ ጽሁፉ ይቀጥላል ብዬ ጊዜ ጠፋና ቀጣዩን ክፍል ሳላቀርብ ቀጠልኩ፡፡ ስለኦባንግ ገጠመኝ ተርኬ፤ ስለጃዋር ጀምሬ ነበር ያቆምኩት፡፡ አሁን መቀጠሉ ወቅታዊ መስሎ ታየኝ፡፡ ከስብሰባው በፊት ይመስለኛል ስለወቅታዊና መሰረታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ ስናወራ፤ ተራው ህዝብ ለገዢ መደቦች ስራ ተጠያቂ ባሆንም፤ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ግን፤ ተራው የአማራ ህዝብ፤ ገዢው መደብ የፈጠረውን ርእዮተአገር በገቢርም በነቢብም ተቀብሎ ኖሮበታል፤ በብዙ ስፍራዎችም ይሄንን ርእዮተ-አገር ተጠቅሞ ሌሎችን ጨቁኖበታልም፤ ብሎ ለማስረዳት ሞከረ፡፡ ምሳሌ ሰጠ፡፡ ነገሩ ከአመታት በፊት የሆነ፤ የተለመደ ሁሉም ወይም ብዙዎቹ ኦሮሞዎች እለት ተእለት የሚጋጥማቸው ቢሆንም፤ ነጥባችንን ለማስረዳት ይጠቅማልና እጠቅሰዋለሁ፡፡ እነሆ አጋጣሚው፡፡
ጃዋር መሀመድ
2.ጃዋር የገጠር ልጅ ነው፤ ከላይ በጠቀስኩት ጽሁፍ ላይ ራሱ እንዳለው፡፡ የዛሬ አስራምናምን አመት፤ ከቤተሰቦቹ ተለይቶ ከተማ ቤት ተከራቶ ትምህረቱን የሚከታተለው ታዳጊው ወጣት፤ ጃዋር ሲራጅ መሀመድ፤ አንድ ቀን አምሽቶ ዝናብ እየደበደበው ይመስለኛል ወደተከራው ቤት ይመጣል፡፡ አከራዩ ደግ አማራ ሴት፤ ለጃዋር ምግብ ሰጥታ፤ እሳት አንድዳ እያሞቀችዉ፤ ከላዩ ላይ ጋቢ ደርባ “ለምን እስኪመሽ ቆየህ አሁን ከመንገድ አንድ ጋላ ቢያገኝህና አንገትህን ቢልሀስ” አለችው፡፡ የዚህን ልጅ ስሜትና ምላሽ ለመረዳት ኦሮሞ መሆን አያስፈልግም፡፡ ራስን በሱ ቦታ ማስቀመጥና ነገሩን የራስን ጎራ ያለስስት በመተቸት ፈቃደኝነት ማሰላሰል እንጂ፡፡
3.ልክ ጅሁርና ጋይንት፤ ቢቸናና አንኮበር እንደምትኖር አንዲት አማራ ኢትዮጵያዊት፤ ይህቺ ሴት ክፋት እንደሌላትና የንግግሩዋን ፖለቲካዊ አንድምታ፤ በዚህ ልጅ ቀጣይ ማንነት ውስጥ የሚኖረውንም ፋይዳ እንደማታውቅ አሳምሮ መገመት ይቻላል፡፡ ይሄንን አጋጣሚ የነገረን ጃዋር ግን የሚለው፤ ይህቺ የዋህ ሴት የኢትዮጵያ ገዢ መደብ አካላት ያሰራጩትንና ለገዢ መሳሪያነት የተጠቀሙበትን የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍልን ዝቅ የማድረግ አመለካከት፤ ሳታውቀው ከነፍሱዋ አዋህዳዋለች ነው፡፡ ስለዚህም፤ በቀጥታ ይሄንን የተወሰነ ብሄርን ዝቅ የማድረግ ባህል በመፍጠርና በመቅረጽ ባትጠየቅም፤ የዚህ ባህል በረከት ተቁዋዳሽ በመሆንና አውቃም ሳታውቅም ይሄንን ባህል እድሜ በመስጠት ተሳታፊ ነች ሲል ተከራከረ፡፡ በላይኛው ጽሁፍ ላይ ሰፈርኩትን የኦባንግን ገጠመኝ ጨምረን ካየነው፤ የጃዋር መከራከሪያ ስሜት ይሰጣል፡፡
ገረሱ ቱፋ፤
4.የላይኛው የጃዋር ገጠመኝ ቀሽም ሊመስል ይችላል፡፡ ከሰደበኝ መልሶ የነገረኝ እንዳልባል እንጂ፤ የገረሱ ቱፋ የከረሩ ምሳሌዎች ደግሞ አሉ፡፡ አንዱን ልጥቀስ፡፡ ኦሮሞው ወዳጄ ገረሱ ቱፋም፤ እንዲሁ ልጅ ሆኖ ሳለ፤ ጾም መሆኑን ረሳና፤ ወተት ጠጣ፡፡ እናቱ ወደንስሀ አባታቸው ላኩት፡፡ ቄሱ ቃል በቃል ምን ብለው እንደመለሱለትና ልቡን እንዳደሙት የነገረኝን በደንብ አላስታውሰውም፡፡ ብቻ፤ “ኤድያ ደግሞ፤ የጋላ ጹዋሚ ብሎ ነገር የለም” ብለው መለሱለት፡፡ “ለጋላ ንስሀ አባት ዲያቆን መች አነሰው” አይነት የሚለውን፤ የተለመደውን ክብረ-ነክ ተረት የሚያጠናክርና የሚያናንቅ መልስ ነው፡፡ በወቅቱ ገረሱ የሱ ጣፋት መስሎት ነበር፡፡ ነፍስ እያወቀ ሲመጣ ግን የሱ ጥፋት ሳይሆን ልክ እንደጃዋር ቀላቢ፤ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ፤ በቄሱ ውስጥ የተተከለውን የሱን ብሄር ዝቅ የሚያደርግ ገዢው መደብ የፈጠረው ንቀትና ጥላቻ ተገለጸለት፡፡ ከአመታት በሁዋላ፤ እነሆ በገረሱ ነፍስ ውስጥ አብሮ የሚኖርና ዘወትር ቄሱ ስለወጡበት ህብረተሰብ ሲያስብና እኛ ጋር ክርክር በገጠመ ቁጥር ትዝ የሚለው መርዝ አጋጣሚ ሆነ፡፡ እንደውም ኢትዮጵያ ስትባል፤ የኚህን ቄስ ጋቢ የደረበች የአማሮች ፈጠራ መስላ ታየችው፡፡
5.ይሄ ሁሉም ሆኖ፤ ጃዋር እንደውም ኢትዮጵያ ኦሮሞነትን የሚያንጸባርቅ ቀለም ከቀባናት፤ አንድ ነን ወይም ልንሆን እንችላለን የሚለውን ሀሳብ ይቀበል ነበር፡፡ የኛን ቄስ ንግግር ፖለቲካዊ አንድምታ ከተደራ በሁዋላ ለቀብር ካልሆነ ቤተክርስቲያን ደርሶ የማያውቀው ገረሱ ግን፤ የኢትዮጵያ አንድነት የሚባል ነገር አገባውም፡፡ አንድ አይደለንም ባይ ነው፡፡ ከሆንም፤ አንድነታችን የጎደፈ አንድነት ሆኖ ነው የሚታየው፡፡
6.ብዙ እላይ ከጠቀስኩዋቸው የከፉ ምሳሌዎችን ማንሳት ይሻላል፡፡ ግን እነዚህ የኦሮሞም ይሁን ሌሎች ብሄርተኞች የሚያነሱዋቸውን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ክሶች በንደዚህ አይነት አጋጣሚዎችና ማስራጀዎች ለማስረዳት መሞከር፤ የክሱን ስፋትና ጥልቀት ማሳነስ ይመስለኛል፡፡ ማውራቱ ነገሩን ያቀለዋል፡፡ ያንን ስሜትና እውነታ መኖር ግን ከሕመም በላይ ነው፡፡ በዚህ አገባብ ውስጥ ነው ያለፉት ሶስት ወራት የነጃዋር ንትርክ የተጀመረው፡፡
7.እነዚህን ምሳሌዎች ያነሳሁዋቸው፤ አንደኛ፤ በዚህ ሰሞን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ዝልዘላችንን ተቆጣጥረውት የቆዩትን ከአኖሎ ሀውልት እስከ በደሌ ኮንሰርት፤ ከምኒሊክ ቅድስና እስከ ጃዋር ትንተና ያሉትን ጉዳዮች ስንመለከት፤ በተወሰነ መልኩ የነዚህን ሰዎች ስሜት ለመረዳት የነዚህን ሰዎች አመለካከት የለወጡ ወይንም ያዳበሩ አጋጣሚዎችን መስማት ራሳችንንና የምንደግፈውን ርእዮተአገረ ለመደገፍ ከመሽቀዳደም ይልቅ የሰዎቹን ክስ በትእግስት ወደማድመጥ ሊወስደን ይችላል በሚል እምነት ነው፡፡ ሁለተኛ፤ የጃዋርና የገረሱ ፖለቲካዊ ማንነት የተወለደውና የተሞረደው ከንደዚህ አይነት ፖለቲካዊና ማሀበራዊ ክስተቶች ነውና እነጃዋር የሚሉትን መስማትም መገምገምም ያለብን በዚህ ማእቀፍ ውስጥ እንደሆነ ለማሳየትና፤ በዚያ አይነት ጉዞ ውስጥ ያደጉና የነቁ ወጣቶች ኢትዮጵዊነት ለምን እንደሚያስጸይፋቸው ሲናገሩ፤ በተስኪያን እንደገባች ውሻ ከማባረር፤ እንደግለሰብም ይሁን እንደተቁዋም፤ እነዚህን ልጆች ጸረ-ኢትዮጵያ አድርገን ከመፈረጃችን በፊት፤ ህመማቸውን ለማድመጥና ለማከም መጣር ይገባል፡፡ ኢህአዴግ ወደቆ እንድትኖር የምንፈልጋት ኢትዮጵያም፤ እነዚህን ህመሞች ለማስታመም የሚችል ህገመንግስታዊ፤ ስነልቡናዊና ፖለቲካዊ ዝግጅት ከሌላት፤ የተቃውሞ ፖለቲካችን በርግጥም የመፍትሄ ሳይሆን፤ የማውገዝ ብቻ ይሆናል፡፡ የዛሬው ጽሁፌ ስለዚህ ፖለቲካዊ ህክምናና ብናደርግ ስለሚበጁን ነገሮች መንገድ ለመጠቆም ነው፡፡ በዚህኛው ክፍል ጠቅላላ ነገሮች ይነሳሉ፡፡ በሚቀጥለው ክፍል ደግሞ መፍትሄዎች ይጠቆማሉ፡፡
መጀመሪያ አፍሪካዊ ወይስ ኢትዮጵያዊ?
8.ባለፈው ሰሞን፤ አልጀዚራ ላይ በቀጥታ ስርጭት ይመስለኛል፤ ጃዋር ፖለቲካዊ አጣብቂኝ ውስጥ የሚከተውን ጥያቄ ተጠየቀ፡፡ “መጀመሪያ ኦሮሞ ነህ፤ ኢትዮጵዊ?” የሚል፡፡ የሚቀጥለው ምሳሌ መቶ በመቶ ላይመሳሰል ይችላል፡፡ የተወሰነ መመሳሰል ግን አለው፡፡ አንድ ሰላሳ አመት ካናዳ ወይም አሜሪካ ውስጥ የኖረ ኢትዮጵያ፤ ወይንም እነዚህ አገር ውስጥ የተወለደ ናይጄሪዊ ይህንን ጥያቄ ቢጠየቅና፤ መጀመሪያ ናይጄሪያዊ ነኝ ብሎ ቢናገር፤ አሜሪካኖችን ወይንም ካናዳዎችን የሚያስቆጣ አይመስለኝም፡፡ ጃዋር ከኢትዮጵ በፊት መጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ ብሎ ሲናገር ግን ብዙዎች አኮረፉ፡፡ ንትርክ ተጀመረ፡፡ የነቁና የበቁ የሚመስሉ የአንድነት አቀንቃኞች ራሱ ተቆጡ፡፡ አሁን በእመብርሀን ይሄ ምኑ ያበሳጫል? በዚህ መደንገጥም መቆጣትም የለብንም፡፡ ማድረግ ካለብን መጠየቅ ብቻ ነው፡፡ ችግሩ፤ እንድንሸመድድ እንጂ፤ እንድንጠይቅ በሚያበረታታ ባህል ውስጥ አላደግንምና፤ ከመጠየቅ ይልቅ፤ ልጁን ወደመዘልዘሉ ዘለልን፡፡
9.አንደኛ፤ ከአገሬ በፊት ብሄሬን ነኝ የሚለው መልስ እንደየአመለካከታችን ትክክል ሊሆን ይችላል፡፡ በርግጥም ሰው ከአገሩ በፊት ብሄሩን ነው፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ መጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ነህ አፍሪካዊ ቢባልና መጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ ቢመልስ፤ ምንም ብዙ ቁጣ የሚቀሰቅስ አይመስለኝም፡፡ ያ ባይሆንም እንኩዋን፤ እንዲህ አይነት ጥያቄዎች አንድ ወጥ የሆነ ሳንሳዊ መልስ ስለሌላቸው፤ ሰዎች አጣብቂኝ ውስጥ በሚያስገባ መልኩ ሲጠየቁ፤ ብዙ ሳያወጡ ሳያወርዱ እንዲህ አይነት መልስ ቢመልሱ፤ ሲሆን ሲሆን መልሳቸውን መቀበል፤ ያለበለዚያም የመልሳቸውን መሰረት ለመረዳት መሞከር እንጂ፤ ግፋ ካለም መልሳቸው ለምን ስህተት እንደሆነ ለመጠቆም መሞከር እንጂ፤ በመልሳቸው ማውገዝ አግባብ አይደለም፡፡ ለጃዋር የተሰጠው ተቃውሞ ደግሞ በብዛት የመጣው የአሜሪካና ካናዳ እንዲሁም የአውሮፓ ፓስፖርታቸውን ተሸክመው መጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ነን ብለው ከሚናገሩ ሰዎች አንደበት መሆኑን ስናይ፤ አንዳንድ ግዜ ሚዛናችን ምን ህል የተዛባ ነው ያሰኛል፡፡
ጃዋር ሚናገረውን ያውቃል፤ ያለውንስ ለምን አለ?
10.በመሰረቱ፤ ይህ ልጅ መቼም ሰው ነውና አንዳንድ ግዜ አግባብ ያልሆነ ነገር ቢያመልጠውም፤ የሚሰራውንም የሚናገረውንም ያውቃል፡፡ ከላይ በጠቀስኩት ጽሁፍ ኦባንግ ሜቶ እንዳለው፤ “በኢትዮጵያዊነታችን ያጣነው ነገር ስላለ ብቻ ኢትዮጵያዊነታችን ይሰረዛል ማለት አይደለም”። ጃዋር፤ ልክ እንደ ኤርትራ እዚያ አካባቢ ኦሮሞ ወይንም ኦሮሚያ የሚባል መንግስት እስካልተመሰረተ ድረስ፤ ቢወድም ባይወድም፤ ጥንትም አሁንም ኢትዮጵያዊ እንደሆነ ያውቀዋል፡፡ ኤርትራ ተፈጥራም እንኩዋን፤ ኤርትራዊነትና ኢትዮጵያዊነት በሁለቱ አገሮች መካከል እንደሚሰመር ድንበር ይቀላል ማለት አይደለም፡፡ ጥምር ዜግነት የሚሉትን ጽንሰሀሳብም ማስታወስ አይጎዳም፡፡ ኢትዮጵያዊ መሆንም ሙሉ በሙሉ የስራችንና የምርጫችን ውጤት ሳይሆን፤ የትውልድና የሕግ ጉዳይ ነው፡፡ ጃዋር እስከቅርብ አመታት ድረስ የኢትዮጵያ ፓስፖርት ይዞ እንደሚዞር እገምታለሁ፡፡ ልጁ እያለ ያለው ግን፤ ህግና አለማቀፍ ፖለቲካ አስገድዶኝ ኢትዮጵዊ ብሆንም፤ ፖለቲካዊ ነፍሴ ኢትዮጵያዊ አይደለም ነው፡፡
11.ነፍስ እንደዜግነት በህግ አትገደድም፡፡ ነፍስ ዜግነቱዋን ወይም ማንነትዋን ትመርጣለች እንጂ፡፡ ነፍሱ ማንነትዋን መረጠች፡፡ የኛ ስራ መሆን ያለበት፤ መናደድ ወይም ማበድ ሳይሆን፤ መጀመሪያ ማብረድ፤ ልክ አሁን እኔ እንደማደርገው፤ ከዚያ መጠየቅ ነው፡፡ ይሄ ልጅ ለምን እንደዚያ አለ፡፡ ኢትዮጵያዊ ነው ብለን፤ በየሬድዮና ቴሌቪዥናችን ስንሰቅለው፤ በየስብሰባና በየመድረካችን ስናቀርበው፤ ድንገት ተነስቶ እንዴት እንዲህ ጉድ አረገን፡፡ ብዙዎቻችን ግን አልጠየቅንም፡፡ ፈረድን እንጂ፡፡ አትፍረድ ይፈረድብሀል የሚል ብሂል ባነገበ ሀይማኖት ክርስትና የተነሳን ሁሉ ፈረድን፡፡
እንደሚመስለኝ፤ እኔ እንደማስበው፤
12.ጃዋር፤ ያንን የቴሌቪዥን ውይይት የሚከታተል ሁለት ትልልቅ ቡድን እንዳለ ያውቃል፡፡ አንደኛው በተለምዶ የአንድነት ሀይል የሚባለው፤ ሁለተኛው የነጻነት ወይንም የኦሮሞ ብሄርተኛ ሀይል፡፡ ሌሎች ሶስተኛም አራተኛም ቡድኖች ኖራሉ፡፡ ያለውን ፖለቲካዊ ራእይ በተደጋጋሚ የፈነጠቀው ጃዋር፤ ዞሮ ዞሮ የአንድነቱ ሀይል በጥርጣሬ እንደሚያየው ወይንም የብሄር ማንነቱን ጨፍልቆ እንጂ እሱ በሚፈልገው መልኩ እንደማይቀበለው በተለያየ አጋጣሚ አስተውሎዋል፡፡ ስለዚህ በሱ ቦታ ላለ፤ ከላይ በአንቀጽ 2፣ 3፣ እና አራት በጠቀስናቸው የእለት ተእለት ፖለቲካዊና ማህበራዊ ክስተቶች ውስጥ ላደገና ለሚኖር ኢትዮጵያዊ፤ እንደዚያ ባለ ፍጥነትን በሚጠይቅ አጣብቂኝ ውስጥ የሚሰጠው መልስ መጻኢ የፖለቲካ እድሉ ላይ እንደሚያጠላበት ያውቃል፡፡ ስለዚህ፤ መጀመሪ ኦሮሞ ነኝ አለ፡፡ በተወሰነ መልኩም ኢትዮጵያዊነት እንደተጫነበት ጠቀሰ፡፡
13.አስቀድመን ጃዋር ላይ የጫንበት ማንነት ወይንም ዜግነትና ለተጠየቀው ጥያቄ እኛ ያዘጋጀልነት መልስ ከሌለ በስተቀር፤ የሚሰማውን ማንነትና ውስጡ የሚቀበለውን ዜግነት የሚያውቀው እሱ እንጂ፤ እኛ አይደለንም፡፡ ስለዚህም በወቅቱ ብሄርን ማስቀደሙ ምክንያታዊ ውሳኔ ነው፡፡ ፖለቲካዊ ብልሀትም ነው፡፡ በርግጥም በሁዋላ የተከተለውን እሱንና አመለካከቱን የማሳደድ ዘመቻና ውግዘት ለተመለከተ፤ የጃዋር መልስ ትክክል ነበር ያሰኛል፡፡ ምክንያቱም እኝ የቀረጽንለት ኢትዮጵያ ለሱ ስሜት መፈናፈኛ የሌላት ሆና ተገኝታለችና፡፡ ጃዋር የቆየ የኢትዮጵያውን ልሂቃን፤ ”የኛ መንገድ ብቸኛውና አማራጭ የሌለው ምርጥ መንገድ ነው፤ ከኛ እውቅናና መንገድ ውጪ የሚጉዋዝ ውጉዝ ይደምሰስ”፤ የሚል ትውልድ ያጫረሰና፤ እነፍቅረስላሴ ወግደረስ ከ20 አመታት እስርም በሁዋላ ያልለወጡት፤ ችኮ ፖለቲካዊ ስነልቡና ሰለባ ነው የሆነው፡፡ እንደውም፤ ለጃዋር፤ እኛ ከቀረጽንለት ኢትዮጵያ ይልቅ፤ ኢህአዴግ የፈተለለት ኢትዮጵያ የተሻለች ብትመስለው አይገርመኝም፡፡
የብሄር ፖለቲካን፤ በከፊል መቀበል ነው፤
14.እነዚህ ወጣቶችም ሆኑ የፖለቲካ ንስሀ አባቶቻቸው፤ በዚህ በአልጀዚራ ላይ የሰማነውን አይነት፤ ኢትዮጵዊነትን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ፤ ለኛ ለመቀበል የሚያስቸግረን ንግግር ሲናገሩ፤ የቆሰለውና እንዲህ ወዳለው ስሜት ውስጥ የሰነቀራቸውን ፖለቲካዊ ሕመም በማከም ፈንታ፤ እንደጠላት የሚፈርጅ አካሄዳችንና ራሳችንን የኢትዮጵያ አንድነት ጋሻዣግሬዎች አድርጎ የመሾም ባህላችንን ነው፤ እነዚህን ሰዎች ወደጽንፈንነት የሚመራቸው፡፡ ያ ደግሞ ለኛም ለኢትዮጵያም አይበጅም፡፡ በዚህ ረገድ ይሄን ያህል አመት በኢህአዴግ መበለጣችን ሁሌም ይገርመኛል፡፡ ምክንያቱም፤ ኢህአዴግ ለነጃዋር፤ የአንድነቱ ሀይል ለመቀበል የሚያዳግተውን፤ ኦሮሚያ የሚባል ክልል/ካርታ፤ ሙሉ ነጻነት ባይኖረውም በራሱ ቁዋንቁዋ የሚተዳደር መንግስት ሰጥቶዋቸዋልና፡፡ ስለዚህ ከአንድነት ሀይሉ ውግዘት ጋር ሲወዳደር ብቻ ሳይሆን፤ ራሱን ችሎም፤ ኢህአዴግ ለብሄር ፖለቲከኞች የሰጠው ፖለቲካዊ ገጸ-በረከት፤ ልብ የሚማርክ ነው፡፡
15.የዚህ የብሄር ፖለቲካ ርእዮተአገር እንደአዲስ በመጣበት ሰዓት ለብዙዎቻችን አዲስና አስደንጋጭ ነበርና ባንቀበለው አይገርመኝም፡፡ እኔና ተስፋዬ ”ጋላው”፤ ስለሺና ወዲ ትግሬው በብሄር ሳይሆን በሰፈር፤ በቁዋንቁዋ ሳይሆን በክፍል፤ በሀይማኖት ሳይሆን፤ በእድሜ ተከፋፍለን ኩዋስ ስንጠልዝ፤ ሴት ስናባርር፤ ጠላ ስንገለብጥ፤ ድግስ ስናሳድድ ነበርና ድንገት የመጣው፤ በርግጥም የብሄር ፖለቲካ አስደንጋጭ ነበር፡፡ ከ22 አመታት ሽንፈት በሁዋላም ግን ራሳችንንና አስተሳሰባችንን አሸናፊ ሆኖ ከወጣው የብሄር ፖለቲካ ጋር ማጣጣም አለመቻላችን ግራ ነው የገባኝ፡፡ ለዚህም ነው፤ የብሄርተኞችን ቁስል በማከክና በማከም ረገድ ኢህአዴግ በልጦናል፡፡ እኛ እንደውም ቁስሉን የምናክም ሳሆን የምናመረቅዝ ሆነናል፡፡
16.ኢህአዴግ ለነሱ አስቦም ይሁን ለራሱ የፖለቲካ ጥቅም፤ የብሄርን ፖለቲካ በሚገባ ተጠቅሞበታል፡፡ 22 አመታት ያለብዙ ፈተና መርቶበታል፡፡ ስለዚህም እነሌንጮ ለታ እነሌንጮ ባቲ እንኩዋን፤ እንደገና ወደሁዋላ የኢህአዴግን አስተዳደር ተቀብለው ለመኖር እያኮቦኮቡ ነው፡፡ ምክንቱም ኢህአዴግ ጠላት ቢሆንም፤ በሌላ በኩል ከተሰለፈው ወደሁዋላ ሊጎትተን ይፈልጋል ብለው ከሚፈሩት የአንድነት ሀይል የተሻለ ጠላት እንደሆነ ያውቁታልና፡፡ ስለዚህ ይሄንን ጎሳን ወይንም ብሄርን መሰረት ያደረገ ፖለቲካዊ መሳሪያ ይዞ፤ ኢህአዴግ ሌላ 20 አመት ቢገዛም አይገርመኝም፡፡
17.እንደፖለቲካዊ ስበስብ፤ ሙሉ በሙሉ የኢህአዴግን የብሄር ፖለቲካ ባንቀበለውም እንኩዋን፤ ኢህአዴግ ክፉ መንግስት እንደሆነ ቢያውቁም፤ በተወሰነ መልኩ በፊት ያልነበረንን መብት አስከብሮልናል ብለው፤ የኢህአዴግን የብሄር ፖለቲካ ተቀብለው ኢህአዴግን በሀይለኛው የሚደግፉትን ቡድኖች የሚማርክ አማራጭ ማቅረብ አልቻልንም፡፡ እንደግንቦት ሰባት ያሉ በንጽጽር የተሸሉና የሰለጠኑ አባላት ያሉበት ድርጅት እንኩዋን፤ ብዙውን እንዲህ ያለውን ፖለቲካዊ ጉዳይ፤ ”ህዝቡ ይወስናል”፤ የሚል የስንፍናና የሽሽት አንቀጽ ሰንቅረው፤ በጎን ሸውደው አልፈውታል፡፡ በዚህ የፖለቲካ ድርጅቶቻችን፤ እንኩዋን የሚያሸንፍ፤ የሚያሰልፍም አማራጭ ርእዮተ-አገር ባልቀየሱበት ሁኔታ ነው፤ ይባስ ብለን፤ በተወሰነ መልኩም ከኛ ጋር ለመስራት የሚጥሩትን ጃዋሮች አመናጭቀን የምንገፋው፡፡ የዚህኛው ገፊ ፖለቲካ መጨረሻ፤ ልጆቹ ልክ እንደ ሌንጮ ለታ ወደጠላት ጎራ እንዲገቡ መገፋፋት ያለበለዚም ሌላ የፈተና ግንባር እንዲፈጥሩ ማበረታታት ነው የሚሆነው፡፡
18.ባንድ በኩል የሌንጮን ወደኢትዮጵያ የመመለስ ውሳኔ፤ ድፍረትና ብልሀት የተሞላበት ውሳኔ ነው ብዬ ባደንቅም፤ በሌላ በኩል ግን የሌንጮ ወደኢትዮጵያ የመመለስ ውሳኔ የአንድነቱን ሀይል ፖለቲካዊ ችኮነትና ውድቀትም ያሳያል፡፡ ሌንጮስ እድሜውም እየገፋ ነውና እንደጎልማሳነት ዘመኑ ብዙ ላያስቸግረን ይችላል፡፡ መጪውን ዘመን የሚዳኙትን፤ እነጃዋር መሀመድን፤ እነገረሱ ቱፋን ግን በትእግስት ልናስተናግዳቸው ሲገባ፤ ሌንጮን መማረክ የተሳነን፤ በኛ ብሶ፤ ደግሞ ይሄንንም ልጅ፤ ጃዋርን ገፋነው፡፡ ከገፋነው በሁዋላ፤ ምንስ ቢል፤ ምንስ ቢያደርግ፤ ምን ይደንቃል፡፡ ከሲያትል እስከ ለንደን፤ ከቶሮንቶ እስከ እስከ ሚኒያፖሊስ ቀድሞም የድርጅት ድክመት ይዞት እንጂ፤ በቁዋፍ የነበረውን የኦሮሞ ብሄርተኛ፤ ለዘብተኛ የነበረውን ሁሉ፤ ኦሮሞ ይቅደም እያለ ሰበሰበው፡፡ እርግጠኛ ነኝ፤ ጃዋር በህልሙም በእውኑም ያላሰበውን ፖለቲካዊ መድረክ ፈጠርንለት፡፡ ገፊ ፖለቲካችን እኛኑ ሳይፈጀን፤ ይሄንን ገፊ የፖለቲካ ቅኝታችንን መለወጥ አለብን፡፡
ሶስት ሀይሎች፤ አንድነት፤ ነጻነት እና ኢህአዴግ
19.እንደሚመስለኝ፤ ይህ ልጅ፤ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ በዋንኛነት፤ ሶስት አገራዊ ሀይሎች የኢትዮጵያን እጣ ፈንታ ለመለወጥ ትግል እንደገጠሙ ገምቶዋል፡፡ አንደኛው አህአዴግና አጋሮቹ፤ ሁለተኛው በተለምዶ የአንድነት ሀይል የሚባለው ቡድን፤ ሶስተኛው ደግሞ የነጻነት ሀይሎች ወይንም የዘውግ ብሄርተኞች የሚባሉት ናቸው፡፡ እንደሚመስለኝ የጃዋር ጠቅላላ ስሌት የሀይል ሚዛኑን ወደኦሮሞ ብሄርተኞች መድፋት ነው፡፡ ኢህአዴግ ኖሮም ይሁን ኢህአዴግ ወድቆ የምትቀጥለው ኢትዮጵያ እጣ ፈንታ አወሳሰን ላይ፤ ቀደም ሲል ኦሮሞ፤ በድምስሱ ደግሞ እስላም ኦሮሞው የአንበሳውን ድርሻ እንዲይዝ ፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በተለምዶ የአንድነት ሀይል እየተባለ የሚጠራው ሀይል በተዘረረበት ወይንም እርስበርሱ በተከፋፈለበትና በአንድነት ለመስራት በየወንዙ እየተማማለ መሀላውን በየጋራው በሚያፈርስበት ሰዓት፤ ሲሆን ሲሆን ኦሮሞውን አንድ አድርጎ፤ አንድም ባይሆን አጠናክሮ መያዝ፤ በቀጣይዋ ኢትዮጵያ ውስጥ የይል ሚዛኑንን ወደነርሱ እንዲሆን ያሰፋዋል ብሎ ያምናል፡፡
20.ስለዚህ ጃዋር መጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ ሲል፤ ይሄንን ኦሮሞን እንደአንድ ሀይል አጠናክሮ መጉዋዝ፤ መጪዋን ኢትዮጵያን ለመቅረጽ ያስችለናል ከሚል ስሌት ተነስቶ ይመስለኛል፡፡ ምክንቱም፤ ይሄ ልጅ ዞሮ ዞሮ፤ አማራ ወይንም አምሀራይዝድ ሌሎች የበዙበት የአንድነቱ ሀይል በቀላሉ እንደማይቀበለው ያውቀዋል፡፡ ትግሉን እንደከዳ፤ ከአማራ ጋር እንዳበረ እየተከሰሰም ቢሆን፤ ይህ ልጅ አምስት ስድስት አመት፤ ከአንድነት ሀይሉ ጋር አብሮ በልቶ ጠጥቶ፤ ተከራክሮና ተደራድሮ አየው፡፡ አንድነት ጭፍለቃ ነው የሆነበት፡፡ መፈናፈኛ አሳጣው፡፡ ስለዚህ፤ ጃዋር ተገኑን፤ ወይም ኮንስቲቲወንሲውን መምረጡ ነው መጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ ያሰኘው፡፡ በሌላ አነጋገር፤ አማሮችና ትግሬዎች እየተፈራረቁ ይህቺን አገር መርተዋል፡፡ አሁን ደግሞ እኛ እንምራ ነው ነገሩ፡፡ በትግሬ ታኮ ወይንም በአማራ ጥላ ስር ሳይሆን፤ በራሳችን መታወቂያ፡፡ አገሪቱን መምራት ካልቻልንም፤ ቢያንስ የራሳችንን እጣ ፈንታ እንወስን ነው፡፡ የኛ ምላሽ ….
ይቀጥላል፤
ተክለሚካኤል አበበ፤ ጥር፤ 2006/2014፡፡ ተረንቶ፤ ካናዳ፤
ስኬታማ ውድቀት (Successful Failure!) ይሄይስ አእምሮ
ለውድቀት ስኬት “የምሥራች!” ወይም “እንኳን ደስ ያለን!” የማይባል ነገር ሆኖብኝ እንጂ ከነዚህ የደስታ ማብሠሪያ አባባሎች በአንደኛው ጽሑፌን መጀመር ቃጥቶኝ ነበር፡፡ ለማንኛውም ሀገራችን በማንኛውም ዘርፍ በገባችበት ውድቀትና ኪሣራ ምክንያት ልባችሁ ያዘነና ቅስማችሁ የተሰበረ ወገኖቼን “እግዚአብሔር ያጽናችሁ፤ የሀገራችሁን ትንሣኤም ፈጣሪ በአፋጣኝ እውን እንዲያደርግላችሁ የእግዚአብሔርን ልብ ያራራላችሁ” በሚለው የልመና ቃል ፈጣሪን እየተማጸንኩ ወሬየን ልቀጥል፡፡ ትንሽ በንዴት እንድትንጨረጨሩ ፈቃዳችሁ ይሁንልኝ፤ መልካም መንጨርጨር!
ሰሞኑን ለራሴ የጥሞና ጊዜ እንዲኖረኝ ፈለግሁና በንባባዊ አርምሞ ሰነበትኩ፡፡ በግሌ እንደብዙዎች ሰዎች ብዙ ጉድለት አለብኝ፡፡ ከነዚህ አንድኛው በመሸታ ቤቶችና በግል ግንኙነቶች ከጨዋታዎች ከምሰማው፣ ከመገናኛ ብዙኃን ከምከታተለው፣ በትምህርት ምክንያት ካገኘኋቸው አነስተኛ ግንዛቤዎችና ከጥቂት ንባቦች በስተቀር ስለሀገሬ ታሪክ ብዙም ዕውቀት አልነበረኝም፡፡ ይህን ትልቅ ክፍተት በተቻለ መጠን ለማጠጋጋት አንድ ሃሳብ መጣልኝ – ማንበብ፡፡ እርግጥ ነው የጥንታዊቷን ኢትዮጵያን ቀርቶ የትናንቷን አሜሪካን ታሪክም ቢሆን በንባብ ለመረዳት መሞከር አባይን በጭልፋ እንደማለት በመሆኑ ይህን መሰሉን ታላቅ ተግባር በአንድ ሰው ዕድሜ ማከናወን ከባድ ብቻም ሣይሆን ከነአካቴው የሚቻል አይደለም፡፡ ግን ከለዬለት ድንቁርና በተወሰነ ደረጃ መውጣት የሚቻለው ራስን በንባብ ማበልጸግ ሲቻል በመሆኑ ጊዜየ በፈቀደልኝ ጥቂት መጻሕፍትን – ከፊተኞችም ከአሁነኞችም – ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ ለማንበብ ሞከርኩ፡፡ ወደ አሥር ይጠጋሉ፡፡ ከነዚህ ግንዛቤ አስገኚ መጻሕፍት ውስጥ የርዕዮት ዓለሙ “የኢሕአዴግ ቀይ እስክርቢቶ” የሚለው አንዱ ነው፡፡ እመለስበታለሁ፡፡
የአለቃ ተክለኢየሱስ “የኢትዮጵያ ታሪክ” መጽሐፍ ሌላው ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ዶክተር ሥርግው በሚባሉ ምሁር የአርትዖት ሥራ እንደተካሄደበት ተገልጾኣል፡፡ ግሩም እሳት ነው፤ ሲያነብቡት እያቃጠለ፣ እየለበለበና ኢትዮጵያዊነትንም እያስረገመ ተነብቦ ማለቁ አይቀርም ያልቃል፡፡ ከነዚህ መጻሕፍት ውስጥ ሥልጣን የማይወዱ መሆናቸውን በማስረዳት የሕይወት ዘመናቸውን እያገባደዱ የሚገኙት ፕሮፌሰር መስፍን የጻፉት “አገቱኒ”ም በስህተት ለሁለተኛ ጊዜ አንብቤዋለሁ፡፡ “ካረጁ አይበጁ ነው”ና ደግሜ እያነበብኩት መሆኔን እስክረዳ ብዙ ገፆችን ብጓዝም ጊዜና የማንበብ ፍላጎት ሞልቶ እንደተረፈው ሰው ጨረስኩት (በዚች መጽሐፍ ላይም በጨረፍታ ብመለስ ደስ ይለኛል)፡፡ ኢትዮጵያ የማያውቋት ሁሉ ዝናዋን ከሩቅ በመስማት ውዱን ሕይወታቸውን ሣይቀር ሊገብሩላት የፈቀዱ የዓለም ዜጎች እንደነበሩ “ጥቁር አንበሣ” በሚል መጽሐፍ ተጋድሎውን ካነበብኩለት ኩባዊ ሻምበል ልረዳ ችያለሁ፡፡ ይህን “ጉራ” የምቸረችርላችሁ ስለሁለት ምክንያት ነው፤ አንዱ ጉድለትን ለማስተካከል በግድ ወደንባብ መዞር እንደሚገባን በተለይ ለወጣቱ ትውልድ ለመጠቆም ነው፡፡ ሁለተኛውን ረሳሁት፡፡
የተሣካ ውድቀት ውስጥ መግባት እኛ ኢትዮጵያውያን ብርቃችን እንዳልሆነ ያነበብኳቸው መጻሕፍት ሁሉ በኩራት ይመሰክራሉ፡፡ እነዚህም ሆኑ ሌሎች በተለያዩ አጋጣሚዎች የማውቃቸው ታሪኮቻችን የሚነግሩኝ አንድ ነገር ቢኖር እኛ ኢትዮጵያውያን አንድ የሚጎድለን የተፈጥሮ ቅመም መኖሩን ነው፡፡ ይህ የጎደለን ቅመም እጅግ መሠረታዊ ከመሆኑ የተነሣ ፈልገን ካላገኘነውና ካላስተካከልነው ከአሁን በኋላ አምስት ሚሊዮን ዓመታትም በሀገርነትና በሕዝብነት ብንኖር በዬጊዜው ከምንገባባቸው የተሣኩ ውድቀቶች መውጣት ፈጽሞውን አይቻለንም፡፡ ብዙዎቻችን አዘውትረን እንደውዳሤ ማርያም እንደምንደጋግመው ምቀኝነትና የሥልጣን ጥም በደማችንና በመቅኒያችን የመሸጉብን ስለመሆናቸው የቀድሞና የአሁን ታሪካችን ነጸብራቅ የሆኑ እነዚህን መጻሕፍት በማንበብ መረዳት ይቻላል፡፡
አልጋ ለመቀማት ወይም አልጋውን ላለመቀማት ሲል ንጉሥ አባት ልዑል ልጅን በጦርና በጎራዴና ምግብን በመመረዝ ሣይቀር የሚገድልበት፣ ነገሥታት ከሀገራዊ ልማት ይልቅ ለሥልጣናቸው ሲሉ ለብዙ አሠርት ዓመታት በማያቋርጡ ጦርነቶች ራሳቸውንና ሕዝባቸውን የሚማግዱበት፣ ለሥልጣንና ለሹመት ሲባል አንዱ ሌላውን በመርዝና በሰይጣናዊ መተትና ድግምት የሚጨራረሱበት፣ የሥልጣን አራራን ለማስታገስ ሲባል የገዛ ሚስትን ሳይቀር ለከፍተኛ መሪዎች እያቀረቡ በትዳርና በ“ፍቅር” ጡር የሚሠራበት፣ ሃይማኖትን መሣሪያ በማድረግ ሕዝብ ከእውነተኛ የፈጣሪ መንገድ እንዲወጣና የነገሥታት ባሪያ እንዲሆን የሃይማኖት መሪዎችና ነገሥታት የሚመሣጠሩበት፣ በዕብድና ወፈፌ ነገሥታት የደንቆሮ አገዛዝ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በረባ ባልረባው ሚዛን የማይደፋ ምክንያት እጅ እግራቸው እንዲቆረጥና በ“እኔን ያዬህ ተቀጣ” ለመቀጣጫነት የሚዳረጉበት፣… አሣፋሪ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ውጪ በሌላ ሀገር ስለመኖሩ በበኩሌ አላውቅም፡፡ የትናንቱ ድንቁርናችን ተባብሶ ዛሬም በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የምናስተውላቸው የውድቀታችን መንስኤዎች ከጥንቱ የተወረሱ እንደሆኑ መገንዘብ አይከብድም፡፡
ውድቀት ምንድነው? እንዴትስ ይታወቃል?
ብዙ መፈላሰፍ አያስፈልግም፡፡ በአጭሩ ውድቀት ማለት ኢትዮጵያ ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያና ውድቀት በፍቺ ይመሳሰሉ፤ አንዱ ቃል ሲጠራ ሌላው ይታወሳል፡፡ ይህን ለመገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ መምጣትና እየተዟዟሩ መጎብኘት ነው፤ በሁሉም ዘርፍ የተዘፈቅንበትን ኪሣራና ድቀት (Decadence) በአጭር ጊዜ ውስጥ ማየት ይቻላል፡፡ ልብ ማለት ያለብን ነገር ደግሞ ሕንጻና መንገድ የዕድገት ምልክት አለመሆናቸውን ነው፡፡ ኢትዮጵያ እንደዚህ ዘመን በተሣካ ውድቀት ውስጥ የገባችበት ዘመን የለም ማለት ይቻላል፡፡ የጥንት አባትና እናቶቻችን የጀመሩት ውድቀት ግዘፍ ነስቶ በአካል የታየው አሁን ባለንበት ዘመን ላይ ነው፡፡ ከታክ የማንማር፣ ጥፋትን እያሻሻልንና እያዘመንን ለሌላ ጥፋት ዝግጁ የምንሆን ዜጎች ብንኖር እኛ ኢትዮጵያውን ብቻ ነን፡፡ አሁን ያለንበት የውድመት ደረጃም ሲያንሰን ነው፡፡
የማንተዛዘን፣ አንዳችን በአንዳችን መከራ የምንደሰት፣ በአንዳችን መቃብር ላይ ሌላኛችን የሠርግ ዳስ የምንትል እጅግ ክፉዎች ነን፡፡ እውነት ቢነገር ምን ያመጣል? ምንም!!
ብዙ የውድቀት መከሰቻዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ አንዱ የውድቀት ምልክት የአርአያሰብዕ (Iconic Figure(s)) መንጠፍ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በተለይ ወጣቱ ትውልድ “ወደፊት እንደ እገሌ ነው የምሆነው!” ብሎ ከፊት ለፊቱ የሚያስቀምጠው ሰው እየጠፋ ነው፡፡ ዙሪያ ገባውን ብንቃኝ አርአያ የሚሆን ሰው ማግኘት እንቸገራለን፡፡ ይህ ዓይነቱ ድርቀት ዋና ሀገራዊ ኪሣራ ነው፡፡ የነበሩን መልካም ሰዎችና በሥራቸው አንቱ የተባሉ ዜጎች ብዙዎቹ ከመሬት ሥር ውለው ጥርኝ አፈር ሆነዋል፤ በጣት የሚቆጠሩ ቢኖሩም ዘመኑ ለነሱ አርአያነት ምቹ ባለመሆኑና በወቅቱ የወያኔ መንግሥት በጠላትነት ስለሚፈረጁ በሀገር ውስጥና በውጪው ዓለም ተደብቀዋል፡፡ በወቅቱ መንግሥት ትልቅ ዜጋ ማለት የወያኔን ዘረኛ መንግሥት ፖሊሲዎች ተቀብሎ በወንጀልና በኃጢኣት መመላለስን የመረጠ፣ በሰይጣናዊ ተግባራት ተጠምዶና በባዕድ አምልኮት ተጠምቆ ለሥጋው ድሎት ብቻ የቆመ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ በአንጻራዊ አነጋገር የተሻለ በሚባል ኢትዮጵያዊ የአንድነት ዘመን ውስጥ በምርጥ ዜግነት የሚያሳውቁ ማኅበራዊና ምሁራዊ ተግባራትን በአሁኑ የወያኔ ዘመን ማከናወን ለእሥርና ለእንግልት እንዲሁም ለስደት ይዳርጋል፡፡ ሆዳምነትና ዋልጌነት በነገሠበትና የመንግሥት መታወቂያ በሆነበት ዘመን የሀገርና የሕዝብ አለኝታ ሆኖ ብቅ ማለት ሌላው ቀርቶ ባልተፈጸመ ወንጀል – የወያኔ የወንጀል መፈብረኪያ የደኅንነት መሥሪያ ቤት በሚሸርበው የፈጠራ ክስ – ወህኒ ሊያስወርድ ይችላል፡፡ የቴዎድሮስ ካሣሁንን መስዋዕትነት ያስታውሷል፡፡ ወሩ በገባ በ22ኛው ቀን የሞተን ዜጋ ወሩ በገባ በ23ኛው ቀን ከውጪ ሀገር በመጣው ቴዲ ላይ መላከኩ የገጪውና የተገጪው ግንኙነት ምናባዊ እንጂ እውናዊ መሆኑን እንኳንስ ‹ፍርድ ቤቱ›ና ከሳሾቹ እኛም እናውቅ ነበር – ማወቅ በራሱና ብቻውን ዋጋ የለውም እንጂ፡፡ ወያኔ መርዘኛ በቀለኛ ነው፡፡ ወያኔ ከመረዘ ሳያንፈራፍር በቀላሉ አይለቅም፡፡
በአሁኑ ወቅት ምሁር አለን ማለት ያስቸግራል፡፡ አድርባይና እበላ ባይ አስመሳይ ወይም በዘመኑ ቋንቋ ‹ፎርጅድ› ምሁር እንጂ ትክክለኛው ምሁር በመብራት ተፈልጎም አይገኝ፤ አሉ ከሚባሉት ጥቂት ወጣትና አንጋፋ ምሁራንም መካከል በትዕቢትና በትምክህት የማይወጣጠሩ ልሂቅነታቸው ያላሳወራቸው ትሁት የሕዝብ አገልጋዮችን ለማግኘት መቸገራችን አልቀረም – ከወደቁ አይቀር ውድቀቱ ሁለንተናዊ መሆን አለበትና ይህ የኢትዮጵያ ምሁራን መኮፈስ የማይጠበቅ አይደለም፡፡ ሁሉንም ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሃይማኖታዊ ዘርፎች ብናይ አርአያ ሊሆኑን የሚችሉ ድንቅ ዜጎችን ሣይሆን ለሆዳቸው ያደሩ አጋሰስና ግልብ ዜጎችን ነው የምናገኝ – በአብዛኛው፡፡ ሆድ ሰውነትን ሲገዛው ጭንቅላት ይጫጫና ከርስ/ቦርጭ ውስጥ ወርዶ ይወተፋል፡፡ ያኔ ኅሊና ትጠፋና ሆድአደርነት የማያፍሩባት ይልቁንም የሚኮሩባት የወቅቱ ፋሽን ትሆናለች፡፡ ሀቀኝነት እያሳፈረ ቅጥፈትና ዕብለት ያሾማል፤ ያሸልማል፡፡ በከንቱ ካልታበይንና ባለፈ የደግ ዘመን ጥቂት ታሪክ ተጀቡነን በተረት ተረት መኖርን ካልመረጥን በስተቀር ሀገራችን በዚህ አሣፋሪ ሂደት ውስጥ ትገኛለች – በችኮላ የ‹ደርግ ዘመን› ብላችሁ እንዳታነቡብኝ አደራችሁን፡፡ የሚብለጨለጨውን የቻይና ቴክኖሎጂና ሕንጻና መንገድ በዚህ ስሌት አናስገባውም፡፡ መጥፎ ነው ማለት ግን አይደለም፡፡ እነዚህ የሚታዩ ኳሻርኳራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ውጤቶች በተወሰነ ደረጃ በሀገር ምስል ላይ አወንታዊ ሚና ስለሚጫወቱ መልካም ነገሮች ናቸው፡፡ ውድቀታችንን ግን ሊታደጉ ወይም ሊሸፍኑና እንዳልወደቅን ሊመሰክሩ ግን አይችሉም፡፡
ለእውነት ሲል የወያኔን ግፈኛ አገዛዝ በጥናታዊ ጽሑፉ አጋልጦ ሲመረቅ የለበሳትን ጥቁር ገዋን ያስመሰገነ ምሁር እንፈልግ – ካገኘን እሰዬው፡፡ በሚያገኘው ደሞዝ ብቻ እየኖረ ሕዝብን የሚያገለግል ባለሥልጣን እንፈልግ – ካገኘን እሰዬው፡፡ (እዚህ ላይ የአቶ ገብሩ አሥራትን ከሙስና የጸዳ ስብዕና ሳልጠቅስ ማለፍ አልፈልግም፡፡ አንድ ሰው የተለዬ ቆንጆ ምግብ ያምረውና ወደገብሩ ቤት በእንግድነት ይሄዳል – ቀደም ሲል ገብሩ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት በነበረበት ወቅት ነው፡፡ የቀረበለት ምግብ ግን የጠበቀው ሥጋና በአትክልትና ፍራፍሬ የታጀበ የሀብታም ብፌ ሣይሆን ተራ ቀይና አልጫ የሰላሱት ምግብ ይሆናል፡፡ ሰውዬው በግልጽነት “እዚህ ቤት እንዲህ ያለ ምግብ ነው እንዴ እሚዘጋጀው?” ብሎ ይጠይቃል፡፡ ያገኘው መልስ “የምንኖረው መንግሥት በሚከፍለን ደሞዝ ብቻ በመሆኑ ከዚህ የተለዬ ምግብ ማዘጋጀት አንችልም፡፡” የሚል ነበር፡፡ ይህችን እውነት ለመተንፈስ አጋጣሚ እፈልግ ነበር – ዛሬ ተሳካልኝ፡፡) በሚያገኘው ደሞዝ ብቻ እየኖረ የሀገርን ዳር ድንበር የሚያስከብር አንድም ቢሆን የመከላከያ ወይም የፖሊስ ሠራዊት መኮንን ብናገኝ ዕድለኞች ነን፡፡ የፈጣሪና የመንግሥት ሕጎች በሚያዙት መሠረት ነግዶ የሚከብር ቢያንስ አንድ ነጋዴ እንኳን ቢኖረን አሁንም ዕድለኞች በሆን፡፡ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት በቤተ መቅደስ እንደሚያንበለብለው ሁሉ በሕይወቱም ፈጣሪን የሚታዘዝ ቢያንስ አንድ ጳጳስ ቢኖረን ሎጥን ያገኘን ያህል በቆጠርነው ነበር፡፡ ቴዎድሮስ ካሣሁንንና ሻምበል በላይነህን ከመሳሰሉ በጣት የሚቆጠሩ የኪነ ጥበብ ሰዎች በስተቀር ከምንትስ ምንትስ በዘለለ የሕዝብን ብሶትና ችግር በፈጠራ ሥራዎቻቸው የሚያካትቱ የሥነ ጥበብና የኪነ ጥበብ ሰዎች ቢኖሩን መታደል ነበር፡፡ በተሠሩ በጥቂት ቀናት ወይም ወራት ውስጥ የሚፍረከረኩ የመንግሥት ቤቶችንና መንገዶችን የሚገነቡ በሙስና የተበከሉና በዕኩይ ሥነ ምግባር የተዘፈቁ ሀሳዊ መሃንዲሶች ሀገር ምድሩን ባይሞሉት ኖሮ ትምህርት ዋጋውን እንዳላጣ እንረዳ ነበር፡፡ ዘርዝረን በማንጨርሳቸው አጠቃላይ ችግሮች ውስጥ ተነክረናል፡፡ የትምህርት ጥራት አይነሳ፤ ሁሉም ዜሮ እየሆነ ነው፡፡ ለኅሊናቸው የሚታዘዙ ሠራተኞች፣ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ ወታደሮች፣ ባለሥልጣኖች፣ ነጋዴዎች፣ ዘፋኞች፣ ደራሲዎች፣ የሃይማኖት አገልጋዮች፣ዳኞች፣ ጠበቆች፣ ግምበኞች፣ ወዛደሮች፣ …. ጥቂት እንኳን ቢኖሩን ድቀታችን መልክ በኖረው ነበር፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየን የተሣካ ውድቀት ውስጥ የመገኘታችንን የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ይህችን ሀገር እንደገና ገምብቶ ሀገር ለማድረግ ምን ዓይነት ጥረትና ስንትና ስንት ልፋት እንደሚጠይቀን ፈጣ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ ብዙ ነገሮች ብቻ ሣይሆኑ ከሞላ ጎደል ሁሉም ነገሮች ከደንቡና ከሥርዓቱ ወጥተው በቀላሉ የማንወጣው አዘቅት ውስጥ ገብተናል፡፡
አንዳንዶቻችንን ሊያስከፋን ይችል ይሆናል፡፡ ግን እውነት ስለሆነ እዚህ ላይ ሳንጠቅስ ልንዘለው አንችልም፡፡ ወያኔ በሀገራችን ያነገሠው ዘረኝነት ከቃላት የመግለጽ አቅም በላይ ነው፡፡ትግሬን ተጠቃሚ ለማስመሰልና ከሌላው ሕዝብ ጋር ለማቃረን በእግረ መንገድም በእርግጥም የዘረኛውን ሥርዓት የጎሣ ተዋፅዖ በማጉላት በሥርዓቱ እምነት የሚጣልባቸውን ዜጎች ይበልጥ ለመጥቀም ሲባል እየታዬ ባለ የተንሻዋረረ ጎጠኛ አሠራር የማንታዘበው ጉድ የለም፡፡ ይህ እግዚኦ የሚያሰኝ ጉድ በማንም ሀገር በመቼም ዘመን አልታየም፡፡ የደቡብ አፍሪካው አፓርታይድም ይህን ያህል ግፍና በደል በጥቁሮች ላይ የፈጸመ አይመስለኝም፡፡ የኛ ዋና ችግርና ለአሣራችንም ቀጣይነት አስተዋፅዖ እያደረገ ያለው ክስተት የኛ ጨቋኞች በመልክና በቀለምም በባህልና በቋንቋም ከኛው ከተጨቋኞቹ ጋር በመመሳሰላቸው ጠላትን ከወዳጅ በቀላሉ መለየትና ዘረኛውን ከጤናማው ለይተን መተማመንን በመፍጠር ለነጻነት ትግሉ መትጋት አለመቻላችን ነው፡፡ አስቸጋሪ ነው ጓዶች፡፡ አንተን ከመሰለ ሰው ጋር ታግለህ ወደምትፈልገው ድል ለመብቃት ከባድና ጊዜንና ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቅ ነው፡፡ አንዱና ትልቁ ችግር ይህ ስለሆነ እንጂ እነዚህን አረሞች ለመንቀል የማይቻል ሆኖ አይደለም፡፡ ግን ደግነቱ ይህም ያልፋል፡፡ ቆሞ ያለ የሚመስለው ግን ይጠንቀቅ!
ለአሁኑ ግን የዘረኝነቱ ዳፋ በሀገርህ ላይ ተቀምጠህ ሀገርህ እስኪናፍቅህ ድረስ፣ በወገንህ መካከል እየኖርክ ወገን እንደሌለህ እስኪሰማህ ድረስ፣ የጋራ እናት ሀገር እያለህ ምንም ዓይነት ዜግነት የሌለህና ባለቤት የሌለለው የመንገድ ላይ ውሻ የሆንክ ያህል እስኪሰማህ ድረስ ውስጥህን ዘልቆ በሚበረብር የሀገርና የወገን ርሀብ ትሰቃያለህ፡፡ ይህም ማለፉ ባይቀርም ለጊዜው ጭንቅላትህን ሊያፈነዳ በሚችል ሥነ ልቦናዊና እንደዬሁኔታውም ኢኮኖሚያዊ ችግር ልትወጠር ትችላለህ – በዚህ ያበዱና ለማበድም የተዘጋጁ እጅግ ብዙ ዜጎች አሉ፡፡ በ“ሰው ሀገር” እየኖርክ መብትህን መጠየቅ እንደማትችል፣ ብትሞክር ደግሞ ቢያንስ እንደሚሳቅብህና እንደሚፌዝብህ ስትረዳ ሀዘንህ ዕጥፍ ድርብ ይሆናል፡፡ ኬንያ ወይም ሆኖሉሉና ፊጂ ብትኖር የማይጓደልብህ ሰብኣዊ መብት የገዛ ሀገሬ በምትላት ኢትዮጵያህ ውስጥ ወደህና ፈቅደህ ባልሆንከው የዘርህ ማንነት ምክንያት ሲዳላብህ ስታይ አለመፈጠርህን ትመርጣለህ፡፡ ይህች ሀገር፣ ሀገር ተብላ ነው እንግዲህ እነሌንጮ ገብተው በ‹ሰላማዊ መንገድ ሊታገሉና ሕዝብን ነጻ ሊያወጡ› እንደሆነ እየተወራ ያለው፡፡ ተስፋ ስትቆርጥ አንድም ትወጣለህ አንድም ትገባለህ ማለት ነው፡፡ እኔ ተስፋ ቆርጬ መውጣት ፈልጌ መውጫ አጥቼ ቀረሁ፡፡ እነሌንጮ ተስፋ ቆርጠው ወጥተው ተስፋ ቆርጠው ሊመለሱ ነው፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ተስፋ ቆርጦ ይወጣና ተስፋን ሰንቆ ይገባል – እንደአውራምባው ዳዊት ከበደ ያለው፡፡ ይሄ ‹ተስፋ› እሚሉት ግን መልኩ ምን ይመስል ይሆን?
ገባ ብለን በተጨባጭ እንየው፡፡ ትግሬዎች አትቀየሙኝ፡፡ እኔም ዋናው ትግሬ ነኝ፡፡ ዘመኑ ሲያልፍ ትግሬያዊ ማንነቴን እገልጣለሁ – ሊያውም አስፈላጊ ከሆነ፡፡ ያ ግን በመሠረቱ ምንም ማለት አይደለም፡፡ ቀዳሚው ሰውነት ነው፤ እናሳንሰው ካልን ደግሞ ኢትዮጵያዊነት፡፡ እነዚህ ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎችም – በነገራችን ላይ – ወደው አይደለም እንዲህ የሆኑት(አማራጭ አጥተው በገቡበት የወንጀል ዓለም የሚደሰቱበት አይመስለኝም)፡፡ ወደ እውነት ቢመጡ ሥልጣኑን እንደሚያጡት ለአእምሯቸው ነግረው ስላሳመኑት ነው – በዚያም ላይ ከጥንት ጀምረው የሠሯቸው ብዙ መጥፎ ተግባራት ስላሉባቸው በነዚያ ላለመጠየቅ ዋናው አብነት ሥልጣንን አጠናክሮ እስከሕይወት ፍጻሜ ወንበርን የፊጥኝ ማለት መሆኑን ያውቃሉ – በዚህ ረገድ እነሱ ስህተት የለባቸውም፤ ችግሩ የኛ የተጨቋኞች ነው – እነሱን በጋራ ትግል ላለመጣል የተዋዋልነው ፊርማ የለሽ ስምምነት ነው እየጠቀማቸው የሚገኘው፡፡ ጥቂቶች(minorities) “ተወዳድረን ሥልጣን መያዝ አንችልም፤ ብቸኛ አማራጫችን ኃይልና ጉልበት ነው” ብለው ካመኑ በየትኛውም ሁኔታ አስቸጋሪ ናቸው – የማይነቃነቁ ዓለቶች ሆነው ለብዙ ጊዜ ሊያስቸግሩ ይችላሉ፤ በሂደት ግን እንደጤዛ መርገፋቸው እንደጉምም መብነናቸው አይቀርም፡፡ እስከዚያው ግን ይሞቷታል አንጂ ሥልጣንን በፈቃዳቸው አይለቁም – “ሰላማዊ ትግል” የሚሉት ቀልድም እነሱ ዘንድ ከጨዋታነት ባለፈ በፍጹም የማይሞከር ነው፡፡ እነዚህን መሰል ጨቋኞች ዓለም የሠራቻቸውን ወንጀሎችና ሸሮች ሁሉ እያከናወኑ በሥልጣናቸውና ሥልጣናቸው በሚሰጣቸው ጥቅም ላይ እንደመዥገር ተጣብቀው ይኖራሉ፡፡ እናም የእነዚህን መዥገሮች ድርጊት ስናገር መጥፎ ድርጊት በደምና በዘር አይተላለፍምና ጤነኞች ትግሬዎች መናደድ አይገባንም፡፡ እውነቱ ባጭሩ እንግዲህ ይህን ይመስላል፡፡
ከትግሬዎች በስተቀር ሌሎች ኢትዮጵያውያን ድርሽ የማይሉባቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ብዙ ናቸው፡፡ ከነዚህ መካከል የደኅንነትና መከላከያን የመሳሰሉ የፀጥታ መሥሪያ ቤቶች፣ ጅምሩክንና ማዕድናት የመሳሰሉ ከፍተኛ ጥቅም አስገኚ ቦታዎች በዋናነት ይገኙበታል፡፡ እነዚህን የመሰሉት ቦታዎች ከትግሬ በስተቀር ለሌሎች ጥብቅ ምሥጢር ናቸው – አጮልቀው እንኳን እንዲያዩዋቸው የማይፈቀድ፡፡ የማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ከፍተኛ አመራር ሙሉ በሙሉ ማለት በሚያስችል ሁኔታ በትግሬዎች የተያዘ ነው – በስም ደግሞ አትመን (ወያኔ በስም የማታለልን ሸር የተካነበት ገና በረሃ ሳለ ነው- “ወርቅነህ በረደድ” ወይም “ደቻሣ ኩምሣ” ቢልህ እውነት አይምሰልህ – የዚህ ተጋዳላይ እውነተኛ ስም “ሐጎስ ግደይ” “ወዲ ዕንቋይ” ሊሆን ይችላል)፡፡ የትኛውንም የመንግሥት መሥሪያ ቤት አመራር ከላይ እስከታች ብንመለከት ሁሉም ትግሬ ነው፡፡ ውሸታም አትበሉኝ፡፡ እንዳልሆንኩ በተገቢ መረጃ አስደግፌ ልናገር ነው፡፡ ለምሳሌ የአንድ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሚኒስትር እንደ ታሪካዊ ‹መጥፎ አጋጣሚ ሆኖ› ትግሬ አይደለም እንበል፡፡ ያ ሰው አማራ ነው እንበልና እንውሰድ – እዚህም ላይ ለሥርዓቱ ዕኩያንና ዕቡያን ትግሬዎች ይህ ክስተት እንደ ‹መጥፎ የታሪክ አጋጣሚ› ተቆጥሮ፡፡ አንተ አማራ ነህ ልበልህና ደስ አለህ አይደል አሁን? አዎ፣ ደስ ይበልህ እንጂ! “ወንድምህ” – ‹ዘርህ› – ተሾሞልህ ያልተደሰትህ መቼ ልትደሰት! ግን አይምሰልህ ወንድሜ፡፡ መሾምና መሻር በችሎታና በብቃት መሆኑን ዘንግተህና አንተም ወያኔ ሆነህ በደምና በአጥንት የምታመልክ ሰው ሆነህ ዘረኝነቱ ወዳንተም ተጋብቶ የኔ የምትለውን ሰው ሥልጣን ላይ ወጥቶ ያየኸው ከመሰለህና በዚያም ከተደሰትህ ተሳስተሃል ብቻ ሣይሆን ለወያኔው ወጥመድ ተመቻችተሃል እንደማለትም ነው፤ ያ ሚኒስትር የተቀመጠው ለስምና ለፖለቲካዊ ታይታ ብቻ ነው – ከግርጌውና ከራስጌው ታኮና ትራስ ሆኖ በዐይን ጥቅሻና በስልክ የሚያንቆራጥጠው ትግሬ አለ – ለዚህ ነው ሁሉም አዛዥ ናዛዥ ትግሬ ነው የምልህ፤ ለዚህ ነው የሀገሪቱ እስትንፋስ መቶ በመቶ በትግሬዎች ቁጥጥር ሥር መሆኑን በድፍረት የማረዳህ ማለትም የማስረዳህ – አንድም ቦታ ሳይቀር ሁሉም በነሱ እይታና ቁጥጥር ውስጥ ነው፤ ያ ቦታ ከመንግሥት ኅልውና ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ይኑረው አይኑረው ለነሱ ምንም ማለት አይደለም፡፡ የቆሻሻ ገንዳም ይሁን መጸዳጃ ቤት ጥበቃ፣ ስፖርት ኮሚሽንም ይሁን የዱር እንስሳት ጥበቃ ብቻ በአለቅነት ወይም በስለላ መልክ የሌሎች ወንድሞቹን እንቅስቃሴ የሚከታተል የሥርዓቱ ታማኝ እስከተቻለ ትግሬ አለዚያም የወያኔነት ሶፍትዌር የተገጠመለት ሌላ ሆድአደር ይመደባል፡፡ ለታይታ ከላይ የሚቀመጥ የሌላ ብሔር “ባለሥልጣን” ግን አሻንጉሊት ጉልቻ እንጂ ከራሱ አእምሮ አንቅቶ የሥልጣን ወንበሩ የሚፈቅድለትን ተግባራት ሊያከናውን የሚያስችል ቅንጣት የማዘዝ ሥልጣን የለውም ለዚህ ለዚህማ ጠቅላይ ሚኒስትርስ ከወላይታ ተሾሞልህ የለም እንዴ? ቲያትሩን እያስታወስኩህ እንጂ አዲስ ነገር እየነገርኩህ እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ የምነግርህን ነገር ደግሞ ለራሴው ተግባራዊ ግንዛቤ ስል ራሴው በየመሥሪያ ቤቱ እየዞርኩ የተረዳሁት ነው፡፡ ያልሄድኩበት ቦታ የለም፡፡ ከብዙ ገጠመኞቼ አንድ ሁለቱን ያህል ብቻ ለአብነት እዚህ ላይ ልንገርህ፡፡ ወደጦር ኃይሎች ሆስፒታል ባለፈው ሰሞን ሄድኩ – አንድ ዘመድ ለማሳከም፡፡ ህክምናው አነስተኛ ቀዶ ህክምና ነበር፡፡ ዘመዴን ለማከም የቀረቡት ዶክተሩም ነርሶቹም ዕቃ አቀራራቢዎቹም አራቱም ትግሬዎች ናቸው፡፡ በዚህ ብቻ አይግረምህ፡፡ የከሰዓት ተቀያሪዎቹም ሦስቱም ትግሬዎች ናቸው፡፡ በሆስፒታሉ ተዘዋወርኩ፡፡ ከጥቂቶች በስተቀር ሁሉም የአስተዳደርና የህክምና ሠራተኞች ትግሬዎች ናቸው – የግቢው ብሔራዊ ቋንቋም ትግርኛ ነው – በዚህስ አልከፋኝም፡፡ ይህ ሁኔታ በአጋጣሚ ነው ከተባለ በትንሹ ሞኝነት ወይንም “አጋጣሚ” የሚለውን ቃል ካለመረዳት የሚመነጭ የዋህነት ነው፡፡ አንድ ወቅት አንድ ወታደራዊ ሰርቪስ መኪና ውስጥ በአጋጣሚ ተገኝቼ እንደታዘብኩት ከነበሩት አሥራ ምናምን ሰዎች ውስጥ ትግርኛ የማይናገረው ሾፌራችን ብቻ ነበር፡፡ እንዴ፣ እውነቱን እንነጋገር ካልንማ ጉዳችን ብዙ እኮ ነው፤ ለምን እንተፋፈራለን? ባይሆን እናውራውና ይውጣልን እንጂ፡፡
ወደ መንግሥት ባንኮችና ኢንሹራንሶች ሄድኩ፤ ወደ አየር መንገድ ሄድኩ፤ ወደ ዩኒቨርስቲዎችም ሄድኩ፡፡ ሁሉም በትግሬ ተጥለቅልቋል፡፡ የከተማዋ ጠረን ከዳር እዳር ወደትግሬነት ተለውጧል – ምናልባትም ‹መቐለ› ላይ ያለህ ሊመስልህ ቢችል አይፈረድብህም፡፡ አነጋገሬ ዘና ያለ እንዲሆን ያደረግሁት ሆን ብዬ ነውና ብዙም አይሰማችሁ፡፡ እናም ብዙ ቦታዎች ሄድኩ – ያው ነው፡፡ ሰዎች “ይህ ዘመን የትግሬዎች ብቻ ሆኗል” የሚሉትን ሃሜት ሊያስተባብልልኝ የሚችል አንዳች ነገር ባገኝ ብዬ ተመኘሁ፡፡ ነገር ግን አልተሳካልኝም፡፡ ትግሬ በአንዳች ምትሃታዊ ነገር እየተባዛ መላዋን የወያኔ ኢትዮጵያ በምልዓት ያዳረሳት ይህል ተሰማኝ – ማዳረሱ ለበጎ ነው ችግሬ የመድሎና የጥፋት ኃይል መሆኑ ላይ ብቻ ነው፤ ሌላውን ሕዝብ ምን በላው እስክትሉ ድረስ በትግሬዎች የመንግሥትን መሥሪያ ቤቶች በበላይነት መቆጣጠር ትገረማላችሁ – ትግሬ ስልህ ደግሞ በአባቱ ወይ በእናቱ ሊሆን ይችላል – እንዲያውም ትግርኛ የማያውቅና የማይናገርም ትግሬ ልታገኝ ትችላለህ – መሃል አገር የተወለደና ያደገ፡፡ “ትንሽ ሥጋ እንደመርፌ ትወጋ” የምትለዋ ብሂል በወያኔ ዘንድ ትልቅ ዋጋ አላት፤ ሌላውን ስለማያምኑ በተለይ ሹመት ላይ የሚያስቀምጡት ሰው ከነሱ ቁጥጥርና አመኔታ የማይወጣ እንዲሆን ይጠነቀቃሉ፡፡ አሁንም አንድ ነገር ግልጥ ላድርግ – ሌሎች ዜጎች በኃላፊነትም ሆነ በተራ ሠራተኛነት አይቀጠሩም ወይም የሉም ማለቴ አይደለም፤ እያልኩ ያለሁት ትርጉም ባለውና ወሳኝ በሆነ ደረጃ ፈላጭ ቆራጮቹ ትግሬዎች ናቸው ነው፡፡ ለምሳሌ በአንድ መሥሪያ ቤት ውስጥ ከመቶ ሠራተኞች መካከል አምስቱ ብቻ ትግሬዎች ቢሆኑ ዘጠና አምስቱ ሠራተኞች የሚሽቆጠቆጡትና የሚያሸረግዱት ለአምስቱ ትግሬዎች ነው – ከመስቀያው ነው – በጌታዋ የተማመነች ፍየል እኮ ቀንዷን በጎች መሃል ነው የምትሰካ፤ በዚህ ዓይነቱ አጋጣሚ ደግሞ እኛ ኢትዮጵያውያን ያለንን የማሸርገድ ብቃትና ለተሹዋሚ የማጎብደድ ተፈጥሯዊ ዝንባሌ መረዳት ይቻላል፡፡ ጊዜ ዘምበል ሲል ደግሞ እንዴት የመሰለ አክሮባት እንደምናሳይ ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡
በበኩሌ በትግሬ ሁሉንም የሥልጣን ቦታዎች መቆጣጠር ብዙም አልከፋም፡፡ የሚያስከፋኝ ባለሥልጣናቱ ቦታውን የሚያገኙት በችሎታና በትምህርት ሳይሆን በዘር ቁርኝት በመሆኑና ያም ሥራን ክፉኛ እያበላሸ በመሆኑ ነው፡፡ አለበለዚያ ሥራውን በሚችሉ የተማሩ ትግሬዎች ሁሉም ቦታ ቢያዝ ግዴለኝም፡፡ አሁን ያለው ችግር ግን አይነሳ፡፡ አንድም ትምህርት የሌለው ምናልባትም የሁለተኛና የአሥረኛ ክፍል ወያኔ ትልቅ ቢሮ ይይዝና የተማረው የሌላ ጎሣ አባል በሥሩ ሆኖ ከኅሊናው ባፈነገጠ አሠራር በዚህ ማይም ወያኔ እየተረገጠ ስታዩ የሥራው መበላሸት ብቻ ሣይሆን ዘረኝነት አንዲትን ሀገር በምን ዓይነት ደረጃ ድራሹዋን እያጠፋት እንደሆነ በመገንዘብ ታዝናላችሁ፡፡ ትግሬ መሆን ብቻውን ለሥልጣንና ለሀብት ካበቃ፣ አማራ መሆን ብቻውን ጉራን ለመቸርቸርና በትምክህት ለመወጠር ካበቃ፣ ጠምባሮ መሆን ብቻውን ለንቀትና ለተዋራጅ ኑሮ ከዳረገ … ሰብኣዊነትና የጋራ ብሄራዊ ማንነት አዲዮስ! በኢትዮጵያ እየታዘብን ያለነው ጉደኛ ትንግርት ዓይነቱ ብዙ ነው፡፡ ባለፉት 23 ዓመታት የጠፋውን ጥፋት ለማረም ስንት ዓመት እንደሚፈጅ ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ በማይማን የተሞላውን በቅርጽ ያለ የሚመስል በይዘት ግን ደብዛው የጠፋውን የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሰው ኃይል አደረጃጀት ለማስተካከል ራሱ ከሩብ ምዕተ ዓመት ያላነሰ ጊዜን መውሰዱ አይቀርም፡፡ የተማረ የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኛ ለማግኘት፣ በሥነ ምግባር የታነጸና የሥራ ተነሳሽነት ያለው ዜጋ ለማፍራት ብዙ ጥረት ይጠይቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት ለእስታቲክሳዊ ፍጆታ ካልሆነ በስተቀር የመንግሥት ሥራ በአግባቡ ይሠራል ማለት አንችልም፡፡ ከሞላ ጎደል ሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሕይወት ያላቸው የሚመስሉት እዚህና እዚያ በለጣጠፏቸው የማይተገበሩ መፈክሮችና “ራዕይ፣ ዓላማ፣ ተልዕኮ፣…” በሚባሉ ትላልቅ የወረቀት ጀንዲዎች ላይ በጉልህ በተቀመጡ የሚያማምሩ ጽሑፎች አማካይነት ብቻ ነው፡፡ በተረፈ የዚህና የዚያ የሥራ ሂደት ባለቤት እየተባለ በሥሩም ዕውቀትና በቂ ሥልጠና የሌለው ሠራተኛ በዘመድና በፖለቲካ አመለካከቱ እየተመደበ አለተጨባጭ ሥራ ስላውደለደለና ሕዝብን በጉቦ ስላስለቀሰ ሀገር ትለማለች ብሎ መጠበቅ የሚቻል አይደለም፡፡ አዲስ የሚቋቋሙት መሥሪያ ቤቶችም በአብዛኛው የሥርዓቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚጠቅሙ የሀገር ሀብት አባባካኝ እንጂ ለሕዝብና ለሀገር ዕድገት የሚውሉ አይደሉም፡፡ ገመናችን ብዙ ነው፡፡
ንግዱን ያየን እንደሆነ አነስተኛና ጥቃቅን ከሚባሉት የሥርዓቱ ዕንባ ጠባቂዎች ጀምሮ የአንበሳውን ድርሻ ይዘው ያሉት ወያኔዎች ናቸው – ከአዲስ አበባ የንግድ ማዕከላትና ሱቆች ውስጥ፣ በአዲስ አበባ አስፋልት ከሚሽከረከሩ ዘመናዊ አውቶሞቢሎች ውስጥ፣ በየምሽቱ ዳንኪራ ከሚረግጡ ዜጎች ውስጥ፣ በየሉካንዳውና በየመጠጥ ቤቱ በጮማና ዊስኪ ከሚቀማጠሉ ‹ኢትዮጵያውያን› ውስጥ ስንቱ መቶኛ ኢ-ትግሬ ሊሆን እንደሚችል ገምቶ መናገሩ ሆድ ሊያስብስ ስለሚችል ሆድ በሆድ ይፍጀው ይቀመጥ፡፡ (እዚህ ላይ ቅድም በኢሳት የተከታተልኩት አንድ ቃለ መጠይቅ ትዝ አለኝ፡- አሥራት አብርሃም የተባለ ሰሜነኛ ከግዛው ጋር ሲነጋገር እንደሰማሁት የኢትዮጵያ ችግር እርሱና መሰል አመለካከተኞች እንደሚሉት የንግሥናው ነገር ከሸዋ ወደ ትግራይ ወይም ከትግራይ ወደሸዋ የመምጣት ጉዳይ አይደለም፡፡ እንደዚያ ያለው ንትርክ ጉንጭ አልፋ የሽፋን ተኩስ ዓይነት ነው፡፡ ዋናው ትግሬ ነገሠ ወይም አማራ ተሻረ የሚለው ሳይሆን የኅልውና ጉዳይ ነው፡፡ ትግሬና አማራ በሥልጣን መፈራረቃቸው እንግዳ ነገር አይደለም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወያኔ ባመጣው የዘር በሽታ መነደፉና በግፍ አገዛዝ ክፉኛ መሰቃየቱ ግን በታሪካችን ታይቶ የማይታወቅ እንግዳ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ችግሩን እስከዚህ አታሳንሱት – አታውርዱት፤ ችግራችን ከነገሥታት ምርጫ ጋር ፈጽሞውን የሚያያዝ አይደለም – ከጭቆና መግረር ጋር እንጂ፡፡ በከፊል አማራ ያልነበረው መንግሥቱ 17 ዓመታትን በገዛ ጊዜ የዘር ችግር እንዳሁኑ በፈጠጠ ሁኔታ አልነበረም፤ ሕዝቡም ‹ኦሮሞ ገዛን፤ የሸዋ አማራ ይሁንልን!› ብሎ አልጮኸም፡፡ አማራው መልካም ገዢ ካገኘ ሥልጣን ቀረብኝ ብሎ አካኪ ዘራፍ የሚል አይመስለኝም – ትግሬም ሆነ ሌላውም ሕዝብ እንዲሁ፡፡ ይቺ ማምታቻ ናት፡፡ እዬዬም ሲዳላ ነው ወገኖቼ፡፡ ጥድቁ ቀርቶብኝ አሉ …)
ትግሬ ሆኖ ፖለቲካን ከጠላ ወደንግዱ መግባትና ለሌሎች በተዘጋጋ ለርሱ ግን በተመቻቸ የጨዋታ ሜዳ “በመነገድ” በአንድ አዳር ሊከብር ይችላል፡፡ ንክኪ ከሆንክ አንድም ሳንካ ሳይገጥምህ የሀብት መንገድህ ሁሉ አልጋ በአልጋ ይሆንልሃል፡፡ ሌላ ከሆንክ ግን ሁሉም ይከረቸምብህና ብቸኛ አማራጭህ ስደትና ድህነት ይሆናል፡፡ አንዲት እህቴ አንድ ንግድ ትጀምራለች፡፡ ሰዎቹ ይመጡባትና እርሷ በወር የተጣራ ሁለት ሺህ ለማታገኝበት ንግድ በዓመት 62 ሺህ ብር ግብር ክፈይ ይሏታል – ወያኔ ጋ ማሰብ ብሎ ነገር የለም፡፡ በግልጽ ሂድ ላይሉህ ይችላሉ – እንድትሄድ ግን ያደርጉሃል፤ ውጣ አይሉህም እንድትወጣ ግን ያስገድዱሃል፡፡ ያቺ ዘመዴ ምን ከምን ታምጣና ትክፈል? ኪሣራዋን ተከናንባ የባሏን እጅ እያየች ተቀምጣለች፡፡ አንተን በእነሱነት ከጠረጠሩህ ምንም ምክንያት ሳያስፈልጋቸው እንዳትኖር ማድረግ ይችላሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ከንግድ ውጪ እያስወጡ ሙልጭ ድሃ ያደረጓቸውን ወገኖቻችንን ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ የምትሠራበት ቤት የመንግሥት ከሆነ ለነሱ አሸወይና ነው – ኪራይና ግብር ይቆልሉብህና ተማርረህ በራስህ ጊዜ ውልቅ ብለህ እንድትወጣ ያደርጉሃል፤ በማግሥቱ በጥንቱ አነስተኛ ኪራይና በዝቅተኛ የፍሬ ግብር ግምት የነሱን ሰው ያስገቡበታል፤ ስንትና ስንት የትግሬዎች ሱቅና ትላልቅ ንግድ ቤት በግልጽ ካለቫት ሲሸጡ እያየህ ባጠገባቸው የምትገኝ ሚጢጢዬ የሌላ ሰው ሱቅ ግን ካለቫት ስትሸጥ ብትገኝ አሣር ሲገጥማት ታያለህ – እነሱን ማንም አይቆጣጠራቸውም፤ በአንዲት ሀገር ውስጥ ብዙ ዓይነት ዜጎችና ሁለት መንግሥታት በግልጽ የሚታዩት ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑን ስትገነዘብ በደረስንበት የዝቅጠት ደረጃ ታርር ትደብናለህ – ግን እውነትም ሰዎች ስንባል ከእንስሳትም የወረድን ምን ያህል ከንቱዎች ነን? የሚሠራውን ግፍ ስትሰማ ይሰቀጥጥሃል፡፡
ባለኝ መረጃ መሠረት በውድ ትምህርት ቤቶች ከሚማሩ ተማሪዎች መካከል ከ95 በመቶ በላይ የነሱ ልጆች ናቸው፤ ሌላው መንደር ያውደለድላል ወይም እንደሚፈጭ ጥሬ ጎዳና ላይ ተሰጥቶ ይውላል፡፡ የመንግሥት ት/ቤት ተብዬዎቹ ውሎ መግቢያ እንጂ ትክክለኛው የመማር -ማስተማር ሂደት የሚካሄድባቸው አይደሉም፡፡ በየቦታው የሚገነቡ ሕንጻዎችና የንግድ ተቋማት የነሱው እንደሆኑ ሁሉም ይናገራል፡፡ ከነሱ ውጪ ሌላው ነግዶም ሆነ ሠርቶ መብላት እንዳይችል በህግ የተገደበ ይመስላል፡፡ ለነገሩ ህግ የሚባል ነገር የለም፤ ሀገሪቱ በኳስ አበደች ዓይነት ጰራቅሊጦሳዊ ያልተለመደ የጉሽ ጠላ ስካር ውስጥ ትገኛለች፡፡ ለምሳሌ አትቀደም እንጂ ሰው ቢገድልህ ተከታትሎ በደለኛን ወደህግ የሚያቀርብ አካል ለማግኘት ትቸገራለህ፤ በኪነ ጥበቡ ይነጋል፤ ይመሻልም፡፡ የሙስናው ነገርም የጉድ ነው፡፡ በፖለቲካ አይሁን እንጂ ወንጀለኛን ወይም በሕግ ሥር የሚገኝን ሰው ለማስፈታት ጉቦ ከከፈልክ ባደረበት ወይም በዋለበት ማረፊያ ቤት አይውልም ወይም አያድርም ፡፡ ከሚነዳው የሕዝብ ትራንስፖርት መኪና አንድ ሰው በር ከፍቶ ዘልሎ ሲወርድ በመሞቱ ምክንያት የተከሰሰ አንድ ሾፌር ፍርድ ቤት በነጻ ካሰናበተው በኋላ ፖሊሶች አሥረው 17 ሺህ ብር ገደማ በሚስቱ በኩል አስመጥተው እንደተከፋፈሉ የሰማሁት በቅርቡ ነው፡፡ ሀገርህ ያለች ትመስላለች እንጂ በቁሟ ሞታልሃለች፡፡ ህግ ወደ ተራ ነገርነት ተለውጦ የምንተዳደረው በጉልበትና በሙስና ብቻ ሆኗል፡፡ በደሞዝ መተዳደር ስለማይቻልና ስለቀረም በሙስና የማይሠራ ነገር የለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን እንኳን ብትሄድ ጥሩ የመቃብር ቦታ ለማግኘት፣ ረጂም የጸሎት ፍትሀት ለማግኘት፣ የሰበካ ጉባኤ አገልግሎት ለማግኘት፣ የልደት ሠርቲፊኬት ለማግኘት፣ አገልጋይ ከሆንክ ደህና ገቢ ወዳለው ደብር ለመዛወር፣ የድቁና ወይም የቅስና ማዕረግ ለማግኘት፣ በጠያፍ ድርጊት የክህነት ሥልጣንን ላለማጣት፣በቄሰ ገበዝነት ጥሩ ቦታ ለመሾም/ለመመደብ… ካለጉቦ አይሞከርም፡፡ ውድቀት ከዚህ በላይ ካለ እኔ አላውቅም፡፡ ሥርዓቱ የሞሰነ (የጠፋ) ስለሆነ የዚህ ሁሉ ጥፋት እስፖንሰሩ ወያኔ ነው፡፡ (በአንዲት ጨዋታ ለምን ፈገግ አላሰኛችሁም – አንድ ሦስት የሚሆኑ ሙስሊም ጓደኛሞች ሶላት ላይ ናቸው፡፡ አንድ በቅርባቸው የነበረ ሌላ ሙስሊም ሣንቲሞችን በብዛት ከኪሱ ያወጣና እየሰገዱ እንዳሉ ሆጨጭ አድርጎ አጠገባቸው ይበትናል፡፡ በተንቃጨለው የሣንቲም ድምፅ ሰጋጆቹ ከስግደቱ ተናጥበው ወደተንቃጨለበት ሥፍራ ሁሉም በአንዴ በደመ ነፍስ ዘወር ይላሉ፡፡ ያኔ ያ ተንኮለኛ ሰውዬ “ይህንን ዱኣ እንኳን አላህ እኔም አልቀበለውም” አላቸው ይባላል፡፡ ለምን ትዝ አለኝ ግን?አዎ፣ ልብንና ኩላሊትን የሚመረምር የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሞኝ የሚመስለን የሃይማኖት ሰዎች እጅግ ብዙ ነን፡፡ እርሱንና የርሱን እየረሳን ወደ ዓለም ብንጠፋና ከወንበዴዎች ጋር ብንወግን የወንበዴዎቹን የመጨረሻ ዕጣ እንጋራለን፡፡)
ትግሬዎች ተሳስተዋል፤ “የትኞቹ ትግሬዎች? “ በሚል ፀጉር አንሰንጥቅ፡፡ ኩይሃ ወይም እንደርታ ገጠር ውስጥ በላቡ አፈር እየገፋ የሚኖር ገበሬ መቼም ተሳስተሃል ልል አልችልም፡፡ ስለዚህ የተሳሳቱት ትግሬዎች ሕወሓትን አምልከውና አምነው ኢትዮጵያን ለማውደም ታጥቀው የተነሱትን እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህኞቹ ትግሬዎች ይህን ያህል ገሃድ የወጣ ዘረኝነት ውስጥ መግባት አልነበረባቸውም፡፡ መሪዎች ሊሳሳቱ ይችላሉ፡፡ ተራዎቹ ዜጎች ግን ከትዝብት በሚያልፍ እስከዚህ ደረጃ ጭልጥ ብለው ወርደው በተሳሳቱ መሪዎች የጥፋት ጎዳና መትመም አይጠበቅባቸውም ነበር፡፡ ምክንያቱም “ነገ” የሚባል ጦሰኛ ቃል አለ፡፡ የትናንትን ታሪክ ማንበብ ያሰኘኝ – ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት – ዛሬን ከትናንትና ትናንትንም ከዛሬና ከነገ ጋር በማስተያየት መጪው ጊዜ ምን ሊሆን እንደሚችል በመገመት ለመተንበይ ነው፡፡ እንደዚያም ይቻላል፡፡ እናም እተነብያለሁ – ነገ ለትግሬዎች ክፉ ቀን ይሆናል፡፡ አሁን ላይ ሆኜ እንደሚታየኝ የእኔን መሰል ደጋግ ትግሬዎች ሸክም ከባድ ነው፡፡ በትግሬነቴ ብዙ መሥራት የሚገባኝ አሁንና ለወደፊትም ብዙ የሥራ ጫና እንዳለብኝ ይሰማኛል፡፡ በወንድሞቼና በእህቶቼ ተላላነት ምክንያት እየሆነ ባለው ነገር ሁሉ አዝናለሁ፤ ማዘን ብቻውን ግን የታሪክን ቅጣት እንደማያስቀር እረዳለሁ፡፡ እናም በትግሬነቴ ሸክሜ ብዙና የሚያጎብጥም መሆኑን የምገነዘበው ከዚህ አኳያ ነው፡፡ ዶክተር ኃይሉ አርአያ፣ አብርሃ በላይ፣ ኤልያስ ክፍሌ፣ አብረሃም ደስታ፣ አስገደ ገ/ሥላሴ፣ ፀጋዬ ገብረ መድኅን፣ ጌታቸው ረዳ(የኢትዮሰማይ ድረገጽ አዘጋጅ)፣ … እና ሌሎችም ጥቂት የማይባሉ ብርቅዬ ትግሬዎች እየደከሙ ያሉት ሦስተኛውን ዐይናቸውን ፈጣሪ ስለከፈተላቸውና የነገን የፈጣሪና የታሪክ ፍርድ ከወዲሁ በማወቃቸው እንጂ እንደትግሬነታቸው ቢሆን ውጪ ያሉት ወደሲዖሊቱ ኢትዮጵያ በመግባት ቢፈልጉ ሚኒስትር ቢፈልጉ የናጠጠ ነጋዴ ሆነው በደናቁርት ወንድሞቻችን አገዛዝ ሥር ሥጋቸውን በምቾት ሊያኖሩ በቻሉ ነበር፡፡ ግን ግን “ከሰው መርጦ ለሹመት፣ ከእንጨት መርጦ ለታቦት” እንዲሉ ነውና እነዚህ በሁለት እሳት ውስጥ ሆነው እየተለበለቡ የሚገኙ ትግሬ ወገኖቻችን ሁሉንም እንዳመጣጡ እንዲቋቋሙ ፈጣሪ ትግስቱንና ችሎታውን ሰጥቷቸው ኢትዮጵያ የሁሉም ዜጎቿ እኩል ሀገር እንድትሆን እየተደረገ ባለው ሁለንተናዊ ትግል የበኩላቸውንና አቅማቸው የፈቀደላቸውን ያህል በመታገል ላይ ይገኛሉ፡፡ እግዚአብሔር ከነሱም ጋር ይሁን፡፡
የወደፊቱ ጊዜ ከአማራነት ስሜት፣ ከትግሬነት ስሜት፣ ከኦሮሞነት ስሜት፣ … በጥቅሉ ከጎጠኝነት ስሜት በአፋጣኝ መውጣት የሚጠበቅብንና የምንገደድበትም ጊዜ ነው፡፡ በተመሳሳይ የቂሎች ዘፈን ነጋሪት እየደለቅን በከንቱ የምንጠፋፋበት ዘመን ማብቂያው ላይ የደረሰ ይመስለኛል፡፡ ለዚህ አስከፊ አደጋ ያጋለጡን ብዙ ታሪካዊ አጋጣሚዎች መኖራቸው እውነት ቢሆንም የአሁኑ ትውልድ ከአንጋፋዎቹ ንዝህላልነት ብዙ የሚማርና የራሱን መፃኢ ዕድል የተቃና እንዲሆን ጥረት የሚያደርግ ይመስለኛል፡፡ በተቆፈረለት ጉድጓድ እየገባ ለማለቅ የቆረጠው ትውልድ በሂደት ለአዲሱ ትውልድ ሥፍራውን እየለቀቀ ይሄድና ወደመላው ዓለም የተበተነው ሥልጡኑ ኢትዮጵያዊ በአዲስ የአብሮነት ስሜት አዲሲቷን ኢትዮጵያ ገንብቶ እያንገሸገሸው ካለው የስደት ኑሮ ሊገላገል የወሰነ ይመስለኛል፡፡ አሮጌው ትውልድ ከነተንኮሉና ከነከፋፋይ ቅራቅንቦው ወደታሪክ መዝገብነት የሚከተት ይመስለኛል፡፡ በዘር መሳሳብና በአንድ ቅጽበት የናጠጠ ከበር የሚኮንት ጊዜ ተወግዶ በወዝና በላብ ተሠርቶ የሚከበርባት ኢትዮጵያ ልትፈጠር ዳርዳርታው የተጀመረ ይመስለኛል፡፡ (የአንድ ባለሥልጣን የዘመድ ልጅ አሠራ ሁለተኛ ክፍል እምቢዬው ይለዋል፡፡ በአንዲት ቀጭን ደብዳ ከሞሰበ ስሚንቶ በዱቤ ስሚንቶ እንዲወስድ ይደረጋል፡፡ ወዲያውኑ ያን ስሚንቶ ሸጦ ከወጪ ቀሪ 4 ነጥብ ምናምን ሚሊዮን ብር በከፈተው የባንክ አካውን ውስጥ ዘጭ ይልለታል – በድንጋጤ አለመሞቱ እሱው ሆኖ ነው – በአሁኑ ሰዓት ቢጠሩት የማይሰማ የልጅ ቱጃር ነው፤ እሱን መሰሎች ደግሞ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አሉ፡፡ እኔ ብሆን በደስታ ብዛት ሞቻለሁ፡፡ እኛ እንዲህ ነን፡፡ ወያኔ እንዲህ ነው፡፡ በአንድ ሌሊት ወገኑን ማክበርና በአንድ ሌሊት ተመሳሳይ ደግሞ የሚጠላውን ወደ አሰቃቂ ድህነት በማውረድ ማማቀቅ የሚችል ሕወሓት ብቻ ነው፡፡)
የሸዋ አማራ ለቀብራራው ጎንደሬ እንደባሪያ የሚቆጠርበት ዘመን ነበር፤ አማራነት እንደ ልዩ ትምክህት እየተቆጠረ በባዶው የሚኮፈሱበት፣ ከባዶ እግር ሳይወጡና ትከሻ ላይ ያለቀን መርዶፋና አቡጄዲ ሳይቀይሩ እንዲሁ በከንቱ በዘር የትውልድ ሐረግ የሚኩራሩበት ዘመን ነበር፡፡ በአማራነት ሥራ መያዝ ወይም አለመያዝ፣ በትግሬነት ሥራ መያዝ ወይም አለመያዝ፣ በኦሮሞነት ሥራ መያዝ ወይም መልቀቅ የገሃዱ እውነታ አሳዛኝ ነፀብራቅ ነበር፤ አሁንም በባሰ ደረጃ እንደቀጠለ ነው፡፡ ደረጃው ይለያይ እንጂ የአሁን ጥፋቶች አሁን አልተጀመሩም ቢባል ማጋነን አይደለም፡፡ እውነትን እንዳለ መቀበል የንስሃ መጀመሪያና የፅድቅ መንገድ ስንቅ ነው፡፡ የነበሩን ችግሮች ናቸው ግዘፍ ነስተው ኅልውናችንን እስከመፈታተን የደረሱት፡፡ ወያኔ የጀመረው ጥፋት የለም፤ ግን አራቀቀና ጫፍ አደረሳቸው፡፡ ስህተትን ወርሶ በዐዋጅ ማፅደቅና የመንግሥት መለያ ማድረግ የወያኔ ተፈጥሮ ሆነ እንጂ ቀድሞም ስህተቶች ነበሩብን፤ አልነበሩብንም ማለት ሞኝነት ይመስለኛል፡፡ የአሁኑ ትውልድ ግን ከራሱ ታሪክና ከየሚሰደድበት ሕዝብ ብዙ እየተማረ የወደፊት ሕይወቱን አስተካክሎ በዘልማድ ሳታጣ ያጣች የምትባለዋን ሀገሩን በቁጭትና በእልህ በጋራ ለመገንባትና በፍቅርና በመተሳሰብ ለመኖር የሚረባረብ ይመስለኛል – ነገ፡፡ ምን እስክንሆን እንጠብቃለን? በዓለም ፊት ከዕቃነት ከመቆጠር የበለጠ ምን ሊደርስብን ይችላል? ከአሁን ዘመን በበለጠ ብሔራዊ ክብራችን የተዋረደበት ዘመን የለም፡፡ እናም ሁሉም ነገር እንደሚፀነስና እንደሚወለድም፣ እንደሚያድግና አርጅቶም እንደሚሞት በወያኔ አድጎና ጎምርቶ ለአካለ መጠን የደረሰው የብሔራዊ ክብራችን ውድቀትና የጋራ ማንነታችን መደብዘዝ አሁን በማርጀቱ የማይቀርለትን ሞት እየሞተና በአንጻሩ የወደቀው ክብራችን ትንሣኤውን የሚቀዳጅበት ብሩኅ ዘመን እየመጣ ይመስለኛል፡፡ ብዙ እውን ሊሆኑ የሚችሉ የሚመስሉኝ ነገሮች እየታዩኝ ስለሆነ ወያኔዎች በተስፋ መቁረጥ አትውቀሱኝ፡፡ በል በል የሚለኝ አንዳች ነገር ስላለ ነው እንጂ እናንተን ለማስቀየም ፈልጌ አይደለም፡፡
ወደነማን እናንጋጥ? መሲሆቻችን እነማን ናቸው? ወጣቱ ምን ከነማን ይማር?
እመለስባቸዋለሁ ወዳልኳቸው ሁለት ነገሮች ልመለስ፡፡ ሰው በጠፋበት ዘመን አንዲት ሴት ልጅ ከርቸሌ ውስጥ ተገኘች፡፡ ይህች ልጅ ርዕዮት ዓለሙ ናት፡፡ አንድ የዐረብ ሀገር ተረት ባማርኛ ላስታውሳችሁ፡፡ “እከክ የሰጠ ጥፍር አይነሳም፡፡” ተፈጥሮም እግዜርም አንድ ተመሳሳይ ሕግ ያላቸው ይመስላል፡፡ በጨለማ ውስጥ ብርሃን እንዲጸነስ ያደርጋሉ፤ በብርሃንም ውስጥ ጨለማ፡፡ እነዚህ ነገሮች እየተፈራረቁ የሕይወትን ምንነት በአሉታዊና በአወንታዊ መልኮች ጎልተው እንዲታዩ ያደርጋሉ – አንዴ ይነጋል፤ አንዴ ይጨልማል፡፡ ምናልባት ባይነጋና ባይጨልም ኖሮ ማን ያውቃል ሕይወት ትርጉም አልባ ልትሆን ትችል ነበር፡፡ ስለዚህም ይመስላል እልም ባለ የተስፋ መቁረጥ ዘመን ውስጥ ተስፋን የሚያጭሩ ጥቂት ዜጎች ከወደቀው ትውልድ ውስጥ ብቅ የሚሉት፡፡ ስለዚህም ይመስላል ቆመናል የሚሉት በወደቁበት ሰዓት ከታናናሾች መካከል ታላላቆች የሚነሱትና የአርአያነትን መቅረዝ ከፍ አድርገው ይዘው እንደመጥምቁ ዮሐንስ በምድረ በዳ የነጻነትን ፋና የሚያበሩት፡፡ ስለዚህም ይመስላል ብዙዎች ወድቀው እንደዓሣማ የገማ ጭቃ ውስጥ ሲርመጠመጡ ጥቂቶች የኅሊናቸውን ጥሪ ተቀብለው በአካላዊ ስቃይ ለሚገኝ መንፈሣዊ ሃሴት የሚተጉትና ታሪካቸውን በወርቃማ ቀለም የሚጽፉት፡፡ ሕይወት ታላቅ ዩኒቨርስቲ ናት፤ ብዙ አየን – እያየንም ነው፡፡
ርዕዮት እግዚአብሔርና አላህ የሰጡን የኢትዮጵያ ዕንቁ ልጅ ናት፡፡ ርዕዮት በችግራችን ጊዜ ፈጣሪ የሰጠን እንስት ኤፍሬም ናት – “ኤፍሬም” ማለት “በመከራዬ ጊዜ የሰጠኸኝ ልጅ” ማለት ነው ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ ርዕዮት ብዙ ያነበበች መሆንዋን ከመጽሐፏ መረዳት ይቻላል፡፡ መስዋዕትነት ከማወቅ ጋር ሲሆን የሠመረ ይሆናል፡፡ ማወቅ ብዙ ትናንሽ ግን አዘናጊ የሆኑ ዓለማዊ ነገሮችን እንድንንቅ፣ ታጋሽና አስተዋይ እንድንሆን፣ ከሚጠፋና ከሚጠወልግ ዝናና የዓለም ሀብት ይልቅ ለማይሞት የሀገርና የወገን ክብር እንድንተጋ… ያደርገናል፡፡ ይህን በርዕዮት፣ በእነእስክንድር ነጋና አንዱዓለም አራጌ አማካይነት እያየነው ነው፡፡ ብዙዎች ሊሸከሙት የከበዳቸውን ቀምበር እነሱ ተሸከሙት፡፡ የኛ ክርስቶሶች እነሱ ናቸው፡፡ የኛ ቤዛዎች እነሱ ናቸው፤ ብዙዎች ሲከዱን እነሱ ከጎናችን ሆነው ስለኛ የኛን መስቀል ተሸከሙ፡፡ ልደቱ አያሌውን የመሰለ ከሃዲ በወጣበት ማኅጸን እስክንድር ወጣበት፡፡ ሙሉጌታ አሥራተ ካሣ በወጣበት ማኅጸን አንዷለም አራገጌ ወጣበት፡፡ ገነት ዘውዴ በወጣችበት ማኅጸን ርዕዮት ዓለሙ ወጣችበት፡፡ ለጊዜው ማለት የምንችለው እንዲህ ብቻ ነው – ሌላ ምን ማድረግ እንችላለን? ምንም፡፡ እውነተኛ የሕዝብ ድምፅ የሚከበርበት ጊዜ ሲመጣ ግን በተለይ ይሁዳዎች ተገቢ ፍርዳቸውን እንዲያገኙ በፍትህ አደባባይ በግልጽ እንጮሃለን፡፡
ባነበብኩት የ204 ገጽ ስብስብ ሥራዎቿ ውስጥ ይህች ወጣት ሴት ጋዜጠኛና ለዜጎች መብት ተሟጋች ያልዳሰሰችው ማኅበራዊ ችግር የለም፡፡ ከይዘቶቹ በመነሣት ነው ልጂቱ ብዙ ያነበበች መሆንዋን የተገነዘብኩት፡፡ ለስኬታማው ውድቀታችን እንደ አንድ ማሳያ ይሆነኛል ብዬ ካሰብኩት ውስጥ የአንድ ዘምቦለል ኢትዮጵያዊን ታሪክ ከርዕዮት መጽሐፍ ጠቅሼ መናገር እፈልጋለሁ፡፡
“… በዘመናችን ከሚገኙ ታዋቂ ሰዎቻችን መካከል አንዱ የሆኑት አንጋፋው የማሰታወቂያ ባለሙያ አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ በአንድ ወቅት ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ ይታወሰናል፡፡ በቃለ ምልልሳቸው ሴትና መኪናን ቶሎ ካልቀያየሩት ባሕርይው እንደሚበላሽ ሊያስረዱን የሞከሩት አቶ ውብሸት ሁሌም ለብሰው ከሚታዩት ካባ ጋር አብረው የጠቀስነውን ብቃት (የሕዝብ ሰው የመሆንን ብቃት ማለቷ ነው) አለመጎናጸፋቸውን እንረዳለን፡፡” (ገጽ 177)
ርዕዮት የጻፈችበት ርዕሰ ጉዳይ እንስታዊነት (ፌሚኒዝም) በኢትዮጵያ ያለበትን ችግር ነው፡፡ የጠቀሰችው ሰውዬ ታዋቂና ዝነኛ ነው – አርአያ ሊሆን ይገባው የነበረ ነገር ግን እንደኔ አመለካከት ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን ገደል የከተተ ብኩን ዜጋ ነው – መፍረድ ቀላል ነው መቼም፡፡
ታዋቂነት ዕዳ ነው፡፡ ብዙ መዘዝ አለበት፡፡ አንድ ሰው ታዋቂ ከሚሆን ይልቅ የማይታወቅ ቢሆን ይሻለዋል፡፡ ከታዋቂነት ጋር የሚመጡ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ውሎውና አዳሩ ሁልጊዜ በክትትል ውስጥ ነው – እሱ ተኝቶ የማይተኙለት ሰዎች አሉ፤ በበጎም በክፉም፡፡ ታዋቂ ሰው በባህርይው እንደ መላእክት የሆነ ያህል ወይም እንዲሆን የሚጠበቅበት መሆኑን የሚያመላክቱ ሁኔታዎች ሞልተዋል፡፡ ለአንዳንድ የዋህ ታዛቢ ታዋቂ ሰው የማይጠጣና የማይሰክር፣ የማይቆጣና የማይሳደብ፣ ከእንትን የራቀ ድንግላዊ፣ የማይዋሽና የማይቀጥፍ፣ … በጥቅሉ ፍጹም ሰው አድርጎ የማየት አዝማሚያ አለ፡፡ ግን ስህተት ነው፡፡ ሰዎች እንደመሆናቸው ሰው የሚሆነውን ይሆናሉ፤ ሰው የሚያደርገውን ያደርጋሉ፤ ሰው የሚኖረውም ይኖራቸዋል፡፡ ልዩነቱ ግን በነሱ ጎልተው እንዲወጡ የማንጠብቃቸው ብዙ ነገሮች መኖራቸው ነው፡፡ እነሱም መጠንቀቅ የሚገቧቸው እኛም ከነሱ የምንጠብቃቸው በአነስተኛው ማሟላት የሚገቧቸውን ሥነ ምግባራት ማሟላት ሲያቅታቸው ካስቀመጥናቸው ከፍ ያለ ቦታ አውርደን እንፈጠፍጣቸዋለን – እንደውብሸት፡፡ ለኔ ውብሸት ማለት አርአያ ሊሆን የማይችል እንዲሁ ተራና ቅሌታም ሽማግሌ ነው፤ ዕድሜውም ሆነ ያሳለፈው ተሞክሮ ያላስተማረው ከነማሙሽነቱ የሸበተ የእንጨት ሽበት ነው፤ ካባውን የሚያወልቅልኝ ሰው ስንት ጊዜ ፈልጌ አጣሁ፡፡ በባህል ማፌዝ ነው ሰውዬው የተያያዘው፡፡ ካባውን እንዲያወልቅ ብትነግሩልኝ ውለታ አለብኝ፡፡ ከ15 እና ከ16 ዓመት … ነውር ነው!
ይህን መሰል የእንጨት ሽበት በሞላባት ሀገራችን ውስጥ ነው እንግዲህ እነቴዲ አፍሮ ስለጨዋ ባህላችን እየዘመሩ እነውብሸት እያፈራረሱት የሚገኙትን ባህላችንን እየጠገኑ የሚገኙት፡፡ እግዚአብሔር የነዚህን ደጋግ ዜጎች ጸሎት ምህላቸውን ይቀበል ዘንድ፣ ምድራችንን ዳግም የጨዋዎች መፍለቂያ ያደርግልንም ዘንድ እንለምነው፡፡
ወደፕሮፌሰር መጽሐፍ ስመጣ፡-
በዩንቨርስቲ ኮሌጅ የክፍል ኃላፊ የሆንኩት በመከራ ሰው ጠፍቶ ነው፤ ገፋፍቶ የክፍል ኃላፊ እንድሆን ያደረገኝ ዠቪ ያቬትዝ የሚባል እሥራኤላዊ ዲን ነበረ፤ ወደ አገሩ ለዕረፍት ሲሄድ ተጠባባቂ ሆኜ በሱ ቦታ እንድሠራም አግባባኝ፤ … (ገጽ 8)
የዩንቨርስቲው ሠላሳኛ ዓመት ሲከበር የአገልግሎት ሽልማት ስለሚሰጠኝ በበዓሉ እንድገኝ ፕሬዝደንቱ [ዶክተር]ዱሪ መሀመድ ነግሮኝ ነበር፡፡ በዩንቨርስቲ ኮሌጅ አንዲት ኤሊ አለችና እስዋ ትቀድመኛለች፤ ለስዋ ስጣት፤ አልመጣም፤ ስሜን አትጥራ ብዬው ነበር፡፡ ግን ባልነበርሁበት ስሜ ተጠራ፡፡ የደርግ አሥረኛ ዓመት ሲከበርም ልሻን እንደሚሰጠኝ ሰምቼ የጥሪ ካርዱ ላይ ባለ ስልክ ደውዬ እንደማልገኝ አስታውቄ ቀረሁ፤ በሌለሁበት አሁንም ስሜ ተጠራ፤ በጃንሆይ ዘመንም ወደ ፅሕፈት ሚኒስቴር ሄጄ ልሻን እንድቀበል ተነግሮኝ አልሄድኩም፡፡ … (ገጽ 13)
ፕሮፌሰር በነዚህ አባባላቸው ምን ማለት እንደፈለጉ ባውቅ ደስ ባለኝ፡፡ በመሠረቱ ሥልጣንን መውደድና መጥላት ግለሰባዊ ጉዳይ ነው፡፡ አያጣላም፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሰው ሥልጣንን ቢጠላ ሀገርን የሚመራት ሰው እንደማናገኝ መረዳት ይገባል፡፡ ስለዚህም ሥልጣንን መጥላት ወይም ከሥልጣን መሸሽ ሁልጊዜ የጤናማነት ምልክት እንደሆነ ተደርጎ መወሰድ ያለበት አይመስለኝም፡፡ መተኮር ያለበት ሥልጣንን በአግባብ የመጠቀም ጉዳይ ላይ ነው፡፡ ሥልጣንና ሽልማትን መጥላትን ለመግለጥ የሚከድበት መንገድ ደግሞ የጨዋነትን ፈር የተከተለ ሊሆን ይገባዋል፡፡ አንድ ሰው አደረገው ተብሎ ለሚታመን መልካም ተግባር እንሸልምህ ሲሉት ለዔሊዋ ስጧት ብሎ ማጣጣል ከሞራል አንጻር ምን ሊባል እንደሚችል በበኩሌ ይጨንቀኛል፤ ለዚህም ነው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ይህን ክፍል ሳነብ የሚገባኝ ነገር አጥቼ ወይም እንዲገባኝ የማልፈልገው ሊገባኝ ፈልጎ ሲፈታተነኝ ያን ጠልቼ በሃሳብ የናወዝኩት፡፡ ሰውን እንደመረዳት ያለ አስቸጋሪ ነገር የለም፤ ማለት በፈለገው ማለት ያልፈለገውን ወይም ማለት ባልፈለገው ማለት የፈለገውን ለመገንዘብ እንደመቃጣት የሚከብድ ነገርም የለም፡፡ በዚህ የፕሮፌሰር የሥልጣን አልወድም ገለጻ የገባኝ ነገር ሣይገባኝ ቢቀር እንደሚሻለኝ ተመኘሁ፡፡
በመሠረቱ ሹመትን ጠልቶ ዋና ትኩረቱ ከሹመት ጋር ስለሚያያዘው ፖለቲካ ማውራት አይቻልም፤ ሹመት በዓለም ብቻም ሳይሆን በገዳማትም አለ፡፡ ሀገርን ለማቅናትም ሹመት የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ እውነተኛና ለሕዝብ በቀናነት የሚሠራበት ሹመት ሊጠላ አይገባም፡፡ በሌላም አነጋገር ሹመትንና ሥልጣንን አምርሮ መጥላት ባለሥልጣናትንና ሹሞችንም አብሮ እንደመጥላት ያህል ሊያስቆጥር ይችላል፡፡ ሥልጣንን በመጥላትና በማስጠላትም ተጨባጭ ቁም ነገር መሥራት የሚቻል አይመስለኝም፤ ዓላማው ግልጽ አይደለምም፡፡ ሥልጣንን የሚጠላ ሰው ደግሞ ስለሥልጣንና ስለፖለቲካ የሚናገረው ነገር ላይ የተወሰነ ጥላ ማሳረፉ አይቀርም፡፡ ያልተዛባና ፍትሃዊ አስተያየት ስለመስጠቱም አጠራጣሪ ነው፡፡ ቀድሞውን አወንታዊ እይታ የለውም ተብሎ ስለሚገመት ነጻና ገለልተኛ አስተያየት ይሰጣል ተብሎ አይገመትም፡፡ …
ላጠቃልል ነው፡፡ የሕዝብ ሰው መሆን ከፍ ሲል እንደጠቆምኩት ከባድ ነው፡፡ ሰውን ማክበር ያስፈልጋል፡፡ ትሁት መሆን ይገባል፡፡ ከአፈንጋጭ ስብዕና ለመራቅ ዘወትር መጠንቀቅ ያስፈልጋል፤ በዚህች ምድር የሚያኮራና እንድንታበይ ሊያደርገን የሚችል አንድም ነገር የለም፡፡ ሁሉም አላፊና ጠፊ ነው፤ ሀብትን ብል ይበላዋል፤ ዕውቀትን ‹ምሥጥ› ያነክተዋል፤ የዝናን ወርቃማ ቀለም ዘመን ያደበዝዘዋል፤ መልክና ውበት የዕድሜ ሽብሽባት ያጠወልገዋል፡፡ ምን ቀረን? ምንም! አንድ በትምህርትም ሆነ በሌላ ነገር ዕውቅናና ስመጥርነትን ያገኘ ሰው ከግል ሕይወቱ ሥምረት ጀምሮ ለሌሎች አርአያ ለመሆን መትጋት ይጠበቅበታል፡፡ ትዳርን ማክበር፣ ሃይማኖታዊ ትዕዛዛትን በተቻለው መጠን ማክበር፣ ሥነ ልሣናዊ የመግባባት ደረጃዎችን መለየትና በአግባቡ መጠቀምን መልመድ (ለምሳሌ አንተ እና አንቱ የሚባሉ አጠቃቀሞችን፣ የማዕረግ ስሞችን እንደዬሁኔታው መገልገልን ማወቅ …)፣ በወገን ችግር ጊዜ ቀድሞ መድረስንና ከልብ ለመርዳት መሞከር፣ ከምንም ዓይነት ዕብሪታዊና ትዕቢታዊ የአነጋገር ሥልት መለየት … ይጠበቅበታል፡፡ የተገነባ ስም እንደሚናድም መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ብዙ አብነቶችን መጥቀስ ቢቻልም አላሙዲን ብቻ ይበቃናል፡፡ (ሰው ባጣንበት ዘመን ሰው የሆኑን እነቴዲ አፍሮና ታማኝ በየነ የሰይጣናዊ የልብ እብጠት ሰለባዎች እንዳይሆኑብንና እንዳይሰናከሉብን በበኩሌ እጸልያለሁ፤ ሁላችንም እነዚህን ወገኖች እንዲያበዛልን በአቋማቸው እንዲያጸናልንም እንጸልይላቸው፡፡ የሰው ዐይን ድንጋይ ይሰብራልና ከዐይን ያውጣልን፡፡ ሰው አልበረክትልን ብሎ ተቸግረናልና ይህን ሾተላይ ፈጣሪ እንዲያነሳልን ወደላይ እንማጠን፡፡)
እንዲያው ግን ሌላውን ነገር ሁሉ ልርሳውና አርአያ የሚሆን ሰው ጌታ በኪነ ጥበቡ አስተካክሎ ይስጠን – ከየዘርፉ፡፡ ደግሞም ይችላል፡፡ ከቁጣ የራቀ፣ ከትዕቢት የተቆራረጠ፣ ከትምክህት የተፋታ፣ ከጥበብ የተጋባ፣ አስተዋይነትና ትህትና ሞልቶ የተረፈው፣ ቅን አሳቢና ለሀገር ለወገን ተቆርቋሪ የሆነ የሕዝብ ሰው ይስጠን፡፡ ሁሉን ነገር ማድረግ የማይገደው የኢትዮጵያ አምላክ እኛንም ባሕርያችንን ገርቶ እንደገና ይፍጠረንና እርስ በርስ የምንተሳሰብ፣ ደገኞችና አስተዋዮች ያድርገን፡፡ ለዘመናት ከሚጨፍርብንና እግር ከወርች በማሰር ኮድኩዶ ከያዘን የምቀኝነት አባዜ ነጻ የወጣን እንሆን ዘንድም ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፤ አሜን በሉ፡፡ ኧረ አቅላቀችንን ይመልስልን ወገኖች! ተበታትነን ቀረን እኮ፡፡ ብዙ ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራልና በነገር እንዳላሰለቻችሁ ነገሬን ሳላንዛዛ ባጭሩ እዚህ ላይ ልቋጭ፡፡
ህወሓት/ኢህአዴግ የትግራይ ህዝብ አማራጭ ሀሳብ እንዳያገኝ እያካሄደ ያለውን አፈና አጥብቀን እንቃወማለን!!! ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ(አንድነት) የተሰጠ መግለጫ
ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ(አንድነት) የተሰጠ መግለጫ፤
ፓርቲያችን አንድነት በአፅንኦት እንደሚያምነው የትግራይ ህዝብ እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የዴሞክራሲ ዕጦት ሰለባ ነው፡፡ ስርዓቱ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክልል እንደሚያደርገው በትግራይም ሰብዓዊ መብት ይረግጣል፣ ፍትህ ይደፈጥጣል፣ በካድሬዎች ይደበደባል፣ ይንገላታል፣ እንዲሰደድ ይደረጋል፡፡ ስርዓቱና በስርዓቱ ውስጥ የደላቸው ሹማምንት በስሙ ከመነገድ በዘለለ ዋጋ የተከፈለበትን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ዘርግቶ ተጠቃሚ ማድረግ አልቻለም፡፡ ህወሓት/ኢህአደግ ክልሉን እንደዋና ካምፕ በማየት በአፈና ውስጥ እንዲኖር አድርጎታል፡፡ የትግራይ ህዝብ የነፃ ፕሬስ ውጤቶችን እንዳያገኝ፤ አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንዳያዳምጥ የተፈረደበት ሕዝብ ነው ማለት ማጋነን አይደለም፡፡ ይሄ እውነትም ሕወሓት/ኢህአዴግ በተለያየ ጊዜ በህዝቡ ላይ በፈፀማቸው ኢ-ዴሞክራሲያዊና ኢ-ፍትሃዊ ድርጊቶች የታየ ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው አምባገነኑ ህወሓት/ኢህአዴግ አረና ባለፈው ሳምንት በትግራይ ክልል አዲግራት ከተማ ሊያደርግ የነበረው ሕዝባዊ ስብሰባ ልክ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ታፍኖበታል፣ አባላቱ ተደብድበዋል እንዲሁም ታስረዋል፡፡ ይሄ የሆነበት ምክንያት የትግራይ ህዝብ አማራጭ እንዳያገኝና በጉልበት የህወሓት አንጡራ ሀብት ብቻ ሁኖ እንዲያገለግል ከመፈለግ ነው፡፡ ከዚህ በፊትም ፓርቲያችን በመቀሌ ከተማ ሊያደርግ የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ በከፍተኛ አፈናና እስር እንዲያስተጓጉል መደረጉ የቅርብ ግዜ ትዝታ ነው፡፡ አንድነት ፓርቲ የትግራይ ህዝብ አማራጭ ሓሳብ የማዳመጥ፣ የሚጠቅመውን የመምረጥና የመቃወም ሕገ-መንግስታዊ መብቱ የተጠበቀ መሆኑን በፅኑ ያምናል፡፡ ስለዚህ አማራጭ ሓሳብ በሚያቀርቡ ፓርቲዎች ላይ ህወሓት/ኢህአዴግ እየወሰደ ያለውን ኢ-ዴሞክራሲያዊ ርምጃና አፈና በጥብቅ እንቃወማለን፡፡ አንድነት የአረና ፓርቲ የሚያደርገውን ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ተከትሎ ህወሓት/ኢህአደግ ለማደናቀፍ የሚያደርገውን ህገወጥ ዘመቻ እንዲያቆም እየጠየቀ አሁንም ተቃዋሚዎችን ‹‹ከጠላቶቻችን ጋር የሚተባበሩ›› በማለት የትግራይን ህዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ለመነጠል የሚካሄደውን ዘረኝነት የተሞላበት ከፋፋይ ርምጃ ለአገራችን እጅግ አደገኛ እንደሆነ አምኖ እንደ ሌላው ህዝብ ሁሉ ለነፃነቱ መከበር የሚያደርገውን ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥልና ሰላማዊ ትግሉን በመደገፍ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እውን እንዲሆን የከበረ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ ዘላለማዊ ክብር ለኢትዮጵያ!!! አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ጥር 19 ቀን 2006ዓ.ም አዲስ አበባ
በቦረና በተነሳ የጎሳ ግጭት ከ8 በላይ ሰዎች ህይወታቸው ሲያጡ በርካቶች የደረሱበት አልታወቀም፤ ፍኖተ ነጻነት
በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን መልካ ሶዳ ወረዳ ኩሮ ነጌሌ ቀበሌ በቦረና እና በጉጂ ኦሮሞ ጎሳዎች መካከል በተነሳ ግጭት ከ8 በላይ ሰዎች ህይወታቸው ማጣታቸውን የፍኖት ነፃነት ምንጮች አስታወቁ፡፡ የመከላከያ ሰራዊቱ ምንም አይነት የማረጋጋት እርምጃ አለመውሰዱ ጉዳቱን እንዳባባሰውም የአካባቢው ነዋሪዎች ገልፀዋል፡፡
የአካባቢው የፍኖተ ነፃነት ምንጮች እንዳስታወቁት ለጊዜው መነሻው ባልታወቀ ምክንያት ጥር 17 ቀን 2006 ዓ.ም በተነሳ የሁለቱ የኦሮሞ ጎሳዎች ግጭት ከስምንት በላይ ሚሆኑ ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ በርካታ ሰዎች የገቡበት አልታወቀም፡፡
የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ወደ አካባቢው በመደወል ባደረገው ማጣራት በአካባቢው በስፋት ሚንቀሳቀሰው የመከላከያ ሰራዊት አንዳችም የማረጋጋት እርምጃ ባለመውሰዱ በግጭቱ የደረሰው ጉዳት መባባሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግጭቱ የቆመ ቢመስልም ሁለቱም ጎሳዎች ከግጭቱ አካባቢ ንብረቶቻቸውን በማሸሽ ለሌላ ጦርነት መዘጋጀታቸውን ከአካባቢው ነዋሪዎች ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ጨምረው ለፍኖተ ነፃነት እንደገለፁት “ባለፉት 22 አመታት በየጊዜው በአካባቢው ያለው የግጭት መጠን የመጨመር አቅጣጫ ማሳየቱ መንግስት የሚከተለው ፖሊሲ ውጤት ነው” የሚሉት የአካባቢው ነዋሪዎች “የሀገሪቱ የመከላለያ ሰራዊት አንድም ጊዜ የማስታረቅም ሆነ ግጭቱን የማርገብ እርምጃ አለመውሰዱ አስገራሚ ነው፡፡”
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አካባቢው ወደ ግጭት ቀጠናነት እየተለወጠ በመምጣቱ በጉጂና በቦረና ኦሮሞዎች፣ በጉጂ ኦሮሞና በቡርጂ፣ በኮንሶ ና በቦረና፣በጉጂና በአማሮ እንዲሁም በአካባቢው ባሉ ሌሎች ብሄሮች መካከል በየጊዜው ግጭቶች እየተከሰቱ በሰው ህይወት፣ በአካልና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ እንደሚገኝም ይታወቃል፡፡
ስለግጭቱ መንግስት የሚለውን ለማካተት ጥረት ቢደረግም የዞኑ አስተዳደር ስልክ ባለመስራቱ ጥረቱ አልተሳካም፡፡
ቃላትን ማባከን! በልጅግ ዓሊ
በጀርመን ውስጥ እንደ አውሮፓውያን አቆጠጠር 1971 ጀምሮ የዓመቱ ምርጥ ቃል ይመረጣል። ይህ በየዓመቱ የሚደረገው ምርጫ አዲስ የተፈጠሩ አባባሎች ወይም ቃላቶች አሮጌም ቢሆኑ በአለፈው ዓመት ውስጥ የአጠቃቀማቸው ሁኔታ ታይቶ የሚካሄድ ብሂል ነው። ለአሸናፊነት የሚበቃው ቃል በሕብረተሰቡ ውስጥ ተቀባይነት ያገኘው ይሆናል። ምርጫው በኮሚቴ ዳኝነት ተሳታፊዎቹን ቃላቶች አወዳድሮ ከፍተኛ ድምጽ ያገኘውን አሸናፊ ያደርጋል።
በዚህ ውድድር ማንም ሰው ሊያሸንፍ ይገባዋል የሚለውን ቃል መጠቆም ይችላል። በዚህ ዓመት የተመረጠው ቃል አሸናፊ የሆነው ከተጠቆሙት ከ2400 ቃላቶች ውስጥ ከፍተኛውን ድምጽ አግኝቶ ነው። ከተጠቆሙት 2400 ቃላቶች ውስጥ 10 ቃላት በዳኞች ይመርጡና ለሕዝብ ለድምጽ ይቀርባሉ ። ከዛም ሕዝብ ድምጽ ይሰጥበትና አሸናፊው ይወሰናል። ጀርመኖች በተለይ ከሥነ ጽሁፍ ጋር ግንኙነት
ያላቸው ቃላትን ያከብራሉ። በዓመቱ ውስጥ የዓመቱ ቃል ብቻ አይደለም የሚመረጠው። ሌሎችም ለምሳሌ የወጣቶች የዓመቱ ቃል፣ የሽማግሌዎች የዓመቱ ቃል ወዘተ . . .የሚባሉ የተለያዩ ምርጫዎች አሉ.።
በ2013 የጀርመን የዓመቱ ቃል ሆኖ ያሸነፈው “GROKO“( grossen Koalition) ሆኗል። ይህ ቃል ከሁለት ቃላት የተፈጠረ ነው። grossen – ትልቅ . . . . Koalition – ጥምረት ማለት ነው። አንድ ላይ ሲሆን ትልቁ ጥምረት ማለት ነው። ቃሉ የተመረጠው ጀርመኖች በዚህ ዓመት ምርጫ አካሂደው በዚህ ምርጫ ሁለቱ ትልልቅ ፓርቲዎች ማለትም ሶሻል ዲሞክራቱም (SPD) ሆነ ወግ አጥባቂው (CDU) ሃገሪቱን ብቻቸውን ለመምራት የሚያስችል ድምጽ ባለማግኘታቸው ጥምረት መፍጠር ስለነበረባቸው ነው። ጥምረቱን ለመፍጠር ብዙ ወራት የወሰደ ድርድር አድርገዋል። በዚህ ድርድር ወቅት ጋዜጠኞች አጭር ቃል ፈጥረው ነበር ይህን ቃል “GROKO“ የሚል ስያሜ ሰጥተው ነበር። ይህ ቃል ነው የዚህ ዓመት አሸናፊ የሆነው።
በእኛም ሃገር ይህንን መጀመር ያስፈልግ ይሆናል። በተለይ በዚህ ዓመት በወያኔ በታሰሩት የሃይማኖት መሪዎች ምክንያት የተፈጠሩ ቃላቶች አሉ።“ አል ሃብሽነ“Al Habash” ወይም ዋሃቢነት “Wahhabism” “ድምጻችን ይሰማ“ ለውድድር ሊቀርቡ ይችላሉ። ከሳውዲ ስለተመለሱት ስደተኞቻችንም በተመለከተ “የመጀመሪያው ሒጂራ“ የሚል ቃል ነበር። ቴዎድሮስ አፍሮ አለ የተባለው “ቅዱስ ጦርነትም“ ለውድድር መቅረብ ይችላል። ከዛው ተያይዞ “ጡት ቋራጭ“ የሚለውም የነ ጃዋር ክስ ሊወዳደር ይችላል። ለነ ጃዋር የወጣውም “ሜንጨኞች“ የሚለው መጠሪያ ድጋፍ ሊያገኝ ይችላል። በሃገሪቱ የታወቁ ድረ ገጸች ይህንን ቢያዘጋጁና ድምጽ ቢያሰጡበት ጥሩ ይሆን ነበር።
ከዚሁ ከጀርመን ሳንወጣ ለውድድር አይቅረቡ እንጂ በኢትዮጵያውያን አዳዲስ የአማርኛ ቃላትም ተፈጥረዋል። እነዚህ ቃላት ቢወዳደሩ ሊያሸንፉ ይችላሉ። ከሁሉም ያስደነቀኝና ሊያሸንፍ ይችላል ብዬ የማምነው ቲታኒክ (Titanic) የሚለው መጠሪያ ነው። ይህ መጠሪያ የተሰጣቸው በሰሃራ በረሃ አድርገው፣ ሜዲትራንያን አቋርጠው፤ ላፓዱሳ ላይ ባሕር ላይ ሳይሰምጡ አውሮፓ የደረሱ ዜጎቻችንን ነው። ይህ ስም አትላንቲክ ውስጥ የሰመጠችውን ታላቋን መርከብ ቲታኒክ (Titanic) በማስታወስ ነው። አንድ ሰው በሳሃራ አቋርጦ አውሮፓ የደረሰ ከሆነ እሱ “ቲታኒክ” ነው ይባላል። በዚሁም ብዙ ዜጎቻችን ከአደጋ ተርፈው አውሮፓ ገብተዋል። “ቲታኒኮች” ብዙ የሚተረክ ታሪክ አላቸው። በዚህ ዓመት የጀርመንን የአማርኛ ቋንቋ በአንድ ቃል ከፍ አድርገውታል።
በጀርመን አዲስ ቃላቶች እየተፈጠሩ ቢሆንም በሌሎች አገሮች ደግሞ ያሉትን ቃላት መጠቀም እንዳይቻል አዲስ ሕግ ለማውጣት ሙከራ እየተደረገ ነው። እስራኤል ውስጥ “ናዚ” የሚለውን ቃል አላግባብ መጠቀም እንዲከለከል በእስራኤል ፓርላማ(knesset)እቅንስቃሴ ተጀምሮ የመጀመሪውን ክፍል አልፏል። እስራኤሎች በተለምዶ ፖሊስም ይሁን ወታደር ወይም ባለስልጣን ሥልጣኑን በመጠቀም ከተጋፋቸው ይህ ሰው “ናዚ” ነው ይላሉ።
http://www.haaretz.com/news/national/1.569281
ይህ ሕግ ከጸደቀ ብዙ ሕይወት ያለቀበትን የናዚ ድርጊት በተራ ቃል አለቦታው ወይም አላግባብ መጠቀም ይከለከላል ማለት ነው። ቃላትን በሕግ መከልከል ጥቅሙ የጎላ ላይሆን ይችላል። ከመናገር ነጻነት ጋርም የሚያያዝ ይሆናል። እያንዳንዳችን ከምንጠቀምበት ቃል ጋር የተያያዙ አስከፊ ነገሮችን ማሰብና የቃሉን ጥቅም ማልከስከስና የተፈጸመውን ግፍ እንደማቅለል እንዳይቆጠር መጣር ይኖርብናል። “ናዚ” የሚለው ቃል ከዘር ማጥፋት ጋር የተያያዘ ነውና። በትራፊክ ጥፋት የቀጣንን ፖሊስ ሁሉ “ናዚ” ነው ማለት የናዚን ትርጉም ዝቅ ያደርገዋል። ተራ ጠብቅ ብሎ ሥነ ሥርዓት ያስጠበቀውንም “ናዚ“ ማለት ቃሉን ትርጉም ያሳጣዋል ነው የእስራኤሎቹ እምነት።
ወደ ሃገራቸን ስንመጣ ደግሞ ብዙ ቃላትን አለ ቦታቸውና አላግባብ መጠቀም እየለመደብን መጥቷል። በመንግሥት ሥልጣን ላይ የተቀመጠው ወያኔ ቃላትን አላግባብ በመጠቀም የተጨበጨበለት ነው ብንል ስህተት አይሆንም። የምዕራብያውያንን ድጋፍ በመሻትም ሆነ የፖለቲካ ጥቅምን በሚመለከት ከብዕር በስተቀር ምንም የሌለውን ጋዜጠኛ “ ሽብርተኛ“ ወይም “ፀረ ሰላም“ ብሎ ወያኔ ሲፈርጅ የትርጉም ስህተት መስሎ የሚታየን አንጠፋም። በአሁኑ ወቅት በመንግሥት የሕዝብ መገናኛ መንገዶችና(እንደ ኢቲቪ ዓይነታቸው) ደጋፊዎቻቸው “አክራሪ“ የሚባሉት በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉት የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የወጣላቸው ከእነርሱ ጋር ግንኙነት እንደሌላው የሚታወቅ ነው። ሰላማዊ ሰዎችን “ሽብርተኛ“ ወይም “አክራሪዎች“ ብሎ መጥራት እውነተኞቹ አሸባሪዎች በሕዝብ ላይ የሚያደርሱትንና ወይም ያደረሱትን ጉዳት ማሳነስ ይሆናል።
በተቃዋሚ በኩልም ቃላቶች ይባክናሉ። የዓባይን መገደብ የደገፈን ወይም አባቱን ለመጠየቅ ወደ ሃገሩ ጎራ ያለውን ሁሉ “ወያኔ“ ማለት የወያኔነትን ትርጉም ዝቅ ማድረግ ይመስለኛል። ናዚነት ለእስራኤሎች ትርጉም እንደሚሰጥ ወያኔነት ለእኛም የሚሰጠን ዘግናኝ ትርጉም አለው። ስለዚህ ያለፈ ያገደመውን ስላልደገፈን ብቻ ተነስተን “ወያኔ“ ማለት የወያኔን ግፍ በጣም ማቅለል ይሆናል። ለነገሩ የአርሶ አደሮች ንቅናቄ የነበረውንና የተከበረውን “ወያኔ“ የሚለውን ስም ያልከሰከሰው ራሱ ወያኔ ነው። የሕዝብን ንቅናቄ የነበረው መጠሪያ ለአንድ ዘረኛ ድርጅት መጠሪያ ሲያደርግ ነው ነገሩ የተበላሸው። ዛሬ በወያኔ መጥፎ ተግባር ምክንያት “ወያኔ“ የሚለው ቃል የትግል መጠሪያ ሳይሆን ዘረኛ፣ ጠባብ ፣ ከፋፋይ ፣ ግፈኛ የሚል ትርጉም ይዟል።
በሌላ በኩል ደግሞ በድርጅት ውስጥ ዴሞክራሲ የጠየቀውን ሁሉም አንጃ ማለት ስህተት ነው። በተለይ እንደ ሃገራችን አቆጣጠር 1969-70 ዓ.ም በኢሕአፓ ውስጥ በነብርሃነ መስቀልና ጌታቸው ማሩ ደጋፊ አንጀኞች የተፈጸመውን ግፍ ማቅለል ይመስለኛል። ይህ በአሁኑ ወቅት የምንሰማው የአንጃነት አፈራረጅ በእነ ብርሃነ መስቀልና ጌታቸው ማሩ ደጋፊዎች የደረሰውን ጥፋት የሚያልከሰክስና በዚያም ወቅት ሕይወታቸውን ያጡትን ዜጎች ደመ ከልብ የሚያደርግ ሆኖ ነው የታየኝ። ፓሊስ ሲቀጣን ናዚ ማለት የቃሉን ክብደት ካቀለለው በድርጅት ውስጥ በተነሳ የሃሳብ ልዩነት የተለየንን ወይም የተቃወመንን ሁሉ አንጃ ስንልም የአንጀኞችን በደል ተራ እናደርገዋለን።
ቃላትን ትርጉም እንዲኖራቸው ስናደርግ ከግል ጥቅም አንጻር ወይም ከወቅታዊ የፖለቲካ እሰጥ አገባ ብቻ ሳይሆን እንደ ጀርመኖች ከሀገርና ከሕዝብ ጥቅምና ጉዳት አኳያ እየመዘንን ቢሆን ነው ከበሬታ የሚኖረን። በዚህ ውድድር ጀርመን ውስጥ በስልጣን ያለውን መንግሥት የሚያጋልጡ ቃላት የማሸነፍ እድላቸው ትልቅ ነው። ጋዜጠኛውን “ሽብርተኛ“፣ የዓባይ ግድብን የደገፈውን “ወያኔ“፣ ከእኛ ጋር የሃሳብ ልዩነት ያለውን “አንጃ“ ብሎ ከመሬት ተነስቶ ደፍሮ መናገር ወይም መጻፍ የራስን ማንነት የሚያጋልጥ ነው። ይህ ደግሞ ወዳጅንም ሳይሆን ጠላትን እያበዛ የሚሄድ አሰራር ነው የሚሆነው። በሕዝብ ታማኝነትንም ያሳጣል። ሲበዛ ደግሞ ቀበሮ መጣብኝ ብሎ ሲያታልል እንደቆየው እረኛ፣ የእውነቱ ቀበሮ ሲመጣ ጩኸቱ እንደ ማታለል ነው የሚቆጠረው።
ቃላትን በሕግ መከልከል ልዩነት ያመጣል ብዬ አላምንም። በሕግ መገደብን ከተቃወምን ደግሞ ራሳችንን በተፈጥሮ ሕግ ማስተዳደር ይኖርብናል። ስንት ዜጎች ያለቁበትን ጉዳይና ስያሜ ወደ ጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም መተርጎም ኢሰብአዊነት ነው የሚሆነው። በተለይ የምንወነጅለው ግለሰብ ነጻ ከሆነ በግለሰቡ ላይ የሰራነው ወንጀል ትልቅ ነው።እንደ ወያኔ ራስ ከሳሽ፣ ራስ ፈራጅ እስከ አልሆንን ድረስ በነጻ መድረክ መረጃ አቅርቡ ብንባል ማጣፊያው ሊያጥረን ይችላል። ማንም የሚጠይቀን የለም ብሎ ያልሆነውን መለደፍ ደግሞ የዝቅተኝነታችን ምልክት ነው የሚሆነው። መድረክ አገኘሁ ብለን ደግሞ የጠላነውን ሁሉ “አንጃ“ ብሎ መጻፍ ወይም በሰፈር ጠብ “ወያኔ“ ብሎ መሳደብ ትዝብት ላይ ይጥላል።
በሁሉ የሚገርመው እኛ በውጭ ሃገር ተቀምጠን፣ ወያኔ የማይደርስብን መሆኑን አረጋግጠን፣ አገር ውስጥ የሚችሉትን የሚያደርጉትን “ቡከን“ ብለን ብንሳደብ ማን ነው የሚሰማን? ይህንን ዓይነት ሁኔታ ቃላትን ከማባከን በላይ ፋይዳ ሊኖረው አይችልም። “ቡከን“ ብለን ስንተች ሌሎች የፈሩትን እኛ ሰርተን ካላሳየን ባዶነታችን ነው ጎልቶ የሚታየው። ስድባችንም የአህያ ፈስ ነው የሚሆነው። አይሸትም አይገማም። ማንም ለአህያ ፈስ አፍንጫውን የሚይዝም አይኖርም።
በደርግ አስራ ሰባት የግፍ አገዛዝ ውስጥ የተፈጠሩ የማውገዣ ቃላት ብዛታቸውን ማስታወስ ያዳግታል። ግን ሁሉም መፍትሄ አላመጡም። ዛሬም ወያኔ የማያወጣው ስም የለም ግን ቃላት ማባከን እንጂ የሚያመጣው ትርፍ የለም። ከስድቡ ባሻገር አልፈን “ወያኔም“ ሆነ “አንጃ“ “ቡከን“ ሆነ “ሽብርተኛ“ ብለን የምንፈርጃቸው ሰዎች እውን እንደምንላቸው ናቸው ወይ? ካልሆኑ ደግሞ ችግራቸውን አጥንተን ችግሩን ለመፍታት ስንጥር ነው መፍትሄ የምናገኘው። “ጸረ ሰላም“ “ሽብርተኛ“ ብሎ ተቃዋሚዎችን መፈረጅ ችግሩን አይፈታም፣ የውስጥ ዴሞክራሲን የጠየቀውን ሁሉ አንጃ ብሎ መለደፍ ድርጅትን ዴሞክራሲዊ አያደርግም። ሙከራችን ቃላትን ማባከን እንዳይሆን ከመፈረጃችን በፊት ማሰብ መቅደም አለበት።
ሰለ ሃገራችን ሰላም የሚያስቡ ሁሉ በሰላም ይክረሙ!
በልጅግ ዓሊ
23.01.14 ፍራንክፈርት
Beljig.ali@gmail.com