አንድነት ፓርቲ በተሳካ ሁኔታ ጠቅላላ ጉባኤውን ፈጽሞ በበርካታ ወጣቶች የተገነባውን ካቢኔ ይፋ ካደረገ ጥቂት ሳምንታት አለፉ፡፡ በነዚህ ጥቂት ቀናትም የምንታገልለትን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ለማድረግ ቀን ከሌሊት መስራት ይገባል የሚል እቅድ አንግቦ ደፋ ቀና በማለት ላይ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለን ግን፣ የግል አስተያየት በማለት የኢሳቱ ጋዜጠኛ ፋሲል የኔአለም «የአንድነት ፓርቲ የመጭው ጊዜ ፈተና» በሚል የፃፈዉን ያልታሰበበት ጽሁፍ አነበብኩ፡፡
በቅድሚያ ለጽሁፉ ለምን መልስ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ እንዳገኘሁት መግለጽ ይገባኛል፡፡ ፋሲል ማስተላለፍ የፈለገው «አንድ ጫፍ ብቻ» የረገጠ መልእክት የተዛነፉ ሃሳቦች የተላለፈበት፣ ከግለሰብ ጥላቻ በመነሳት ፓርቲውን ፈተና ውስጥ፣ ያለ በማስመሰልና ዋጋ እየከፈሉ ያሉትን ውድ አባሎቻችንን በግብአትነት በመጠቀም ክፍፍል ለመፍጠር የፈለገ በመሆኑ ነው፡፡ ወይም ፀሀፊው «ሁለት የከረሩ ጫፎች ብቻ ያስፈልጋሉ» ከሚል አይነት አመለካከት ላይ ቆሞ ከመፃፍ የመነጨ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያቴ፣ በአምባገነኑ ስርዓት ተጠፍንገው ከተያዙ የብሮድካስት ሚዲያዎች ውጭ፣ አማራጭ አልባ ለሆነው ህዝብ በአማራጭነት ለቀረበው ኢሳት፣ ካለኝ አክብሮት ነው፡፡ ምክንያቱም ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም የኢሳት ባልደረባ እና ኃላፊነት የያለበት ሰው በመሆኑ፡፡
ፋሲል በጠቅላላ ጉባኤው በከፍተኛ ድምጽ የአንድነት ፓርቲ ፕሬዚደንት ሆነው የተመረጡት ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው ከሪፖተር ጋር ቃለ-ምልልስ ካደረጉት ውስጥ «ከኢህአዴግ ጋር ገንቢ ግንኙነት (Contractive engagement) እንዲኖረን እፈልጋለሁ. . .» የሚለው ለሱ ሃሳብ የሚመቸውን ቆንጥሮ በማውጣት ከልደቱ አያሌው «ሦስተኛ መንገድ» ካለው ወይም «መሀል ላይ መቆም» ብሎ ከተረጎመው ሃሳብ ጋር ለማያያዝ ሞክሯል፡፡ ስህተቱ እዚህ ላይ ይጀምራል፡፡ አንድነት በሊበራል አስተሳሰብ የሚያራምድ በመሆኑ የግለሰቦች መብት በቅድሚያ መረጋገጥ አለበት ብሎ ያምናል፤ በስትራቴጂው እንዳስቀመጠውም የኢህአዴግ አይነት የብሔር (የቡድን) መብትን ማክበር ወይም የዚህ ተቃራኒ የሆነው የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ላይ ብቻ ቆሞ ሌሎችን አለማዳመጥ ዴሞክራሲያዊ አይደለም ይላል፡፡ ሁሉም ባልተሸራረፈ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ያለምንም ጣልቃ ገብነት የመደራጀት መብታቸው መከበር አለት፡፡ ስለዚህ ጥያቄው ጫፍ የመቆም ሳይሆን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የመፍጠር ነው፡፡
ስለዚህ አንድነት እንደ ሊበራል ፓርቲ ከገዢው ፓርቲ ጋር መደራደር ይገባዋል፡፡ መደራደር፣ ሰጥቶ መቀበል እንደነውር መታየት የለበትም ብሎ አስቀምጧል፡፡ ኢ/ር ግዛቸውም በቃለ ምልልሱ ያስቀመጡት ይህንን ነው መደራደር የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ ሥራ ነው፡፡ መደራደር ዘመናዊ አስተሳሰብም ነው፡፡ አሁንም እየታገልን ያለው ያለው ችግራችንን በጠረጴዛ ዙሪያ እንፍታ፣ ሆደ ሰፊ እንሁን፣ ጠርዝ ከያዘና ከፍረጃ ፖለቲካ እንላቀቅ ማለት ነው፡፡ ጋዜጠኛ ፋሲል «መሀል ላይ መቆም» ያለው እንደዚህ አይነቱን ሃሳብ ነው እንጅ ራሱ ፀሀፊው አንድነትም ሆነ አመራሩ ተንበርክኮ እንዳልሆነ፣ እንደ አንድነት ዋጋ የከፈለና እየከፈለ ያለ ፓርቲ እንደሌለ የሚያውቅ ይመስለኛል፡፡
ጋዜጠኛ ፋሲል በተሳሳተ ዕይታ የኢ/ር ግዛቸውን ንግግር ቆንጥሮ «ፍርሃት ነው» ለማለት ይሞክራል፡፡ በውጭ ሀገር እየኖሩ መታገል፣ ትግሉን መደገፍ እንደሚችል አምናለሁ፡፡ ለፋሲል ግን አንድ ጥያቄ መጠየቅ እፈልጋለሁ፡፡ የሚፈራ ሰው መቀመጫው የት ነው? እንደሚመስለኝ ወይ የኢኮኖሚ ጥያቄ ካልሆነ በስተቀር ፀሀፊው ከሀገር የወጣው ሀገሩን ስለሚጠላ ሳይሆን ሥርዓቱን ስለፈራ ነው፡፡ ሥርዓቱን ፈርቶ በተሰደደ ሰውና ከሥርዓቱ ጋር ፊት ለፊት ግብግብ እየፈጠረ ያለ ሰው መካከል ትልቅ የሞራል ልዩነት አለ፡፡ ስለዚህ ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም ፍርሃትን የተረጎመበት መንገድ ድንጋዩ ተመልሶ ወደ እርሱ እንዲያርፍ የሚያደርግ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ከሀገር ወጥቶ ትግሉን መደገፍ ትክክል ቢሆንም ፖለቲካውን ለመምራት መሞከርም ሌላ ትልቅ ስህተት ይሆናል፡፡ እንዲህ ሲባል እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት የአቅማችንን እያደረግን ያለን ሰዎች መተቸት የለብንም ብዬ አላምንም፡፡ በመሳደበና በመተቸት መካከል ግን ትልቅ ልዩነት እንዳለ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
ሌላው ማንሳት የምፈልገው ጋዜጠኛ ፋሲል የአንዱዓለምንና ናትናኤልን ስም በመጥቀስ ጫፍ ላይ የቆመ ሃሳብ የሚያራምዱ አድርጎ መግለፁም ስህተት ነው፡፡ አንዱዓለምም ሆነ ናትናኤል ፋሲል የጠቀሰውን አይነት ሃሳብ የሚያራምዱ አይደሉም፡፡ ሆነውም አያውቁም፡፡ በተለይም የአንዱዓለምን ሃሳብ ለመረዳት መጽሀፉን ማንበብ ተገቢ ነው፡፡ ወጣቱ ፖለቲከኛ በሆደ ሠፊነት «ኧረ የመቻቻል ያለህ፣ ኧረ የድርድር ያለህ፣ ኧረ የመደማመጥ ያለህ . . .» በማለት አንድ ጫፍ ላይ ቆሞ ማክረር እንደማይጠቅም ገልጿል፡፡ ለአዲሱ አመራርም እውቅናና ድጋፍ ሰጥቷል፣ ደስተኛም ነው፡፡ ይሄን የምለው አንዱዓለም ለገና በዓል በአካል አግኝቼ ሃሳቡን የማዳመጥ እድል ስለገጠመኝ ነው፡፡
በመጨረሻ ግን ስለ ኢሳት ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡ ኢሳት ለኢትዮጵያውያን በአማራጭነት ብቅ ያለ ትልቅ ሚዲያ ነው፡፡ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ያለውን አበርክትቷል ማድነቅ እፈልጋለሁ፡፡ እኔም በተለያየ ጊዜ በዚሁ ሚዲያ ላይ የተለያዩ ሃሳቦችን ሰጥቼ አውቃለሁ ወደ ፊትም እድሉን ባገኘሁ ቁጥር እሰጣለሁ፡፡ የተለያዩ አማራጭ ሃሳቦችን በተደራጀ ነፃ ሚዲያ ማግኘት የተራበው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳያዝን የኢሳት ጋዜጠኞችን የኢዲቶሪያል ቦርድ አባላት በእጅጉ ሊያስቡበት ይገባል፡፡ ማንኛውም ሚዲያ ከአድሎ አሠራር ነፃ መሆን አለበት፡፡ በዚህ ሚዲያ ላይ የሚሰሩ ጋዜጠኞቹ ግን የግል አመለካከታቸውንና እምነታቸውን በማስቀደም አንድን ድርጅት ለማጥቃት የሚሄዱበትን መንገድ መፈተሽ ጠቃሚ ነው፡፡ ጋዜጠኛ ፋሲል በአንድነትና አመራሩ ላይ የሰነዘረው የተዛባ አስተሳሰብ በሚል አስተያየት ስም የቀረበ ቢሆንም ግለሰብ አንድ ትልቅ ፓርቲ ላይ ሲጽፍ መውሰድ የሚገባውን ጥንቃቄ አላደረገም፡፡ ስለዚህ ብዙ ተሳሳተ፡፡ ለማንኛውም ሁሌም ከጥላቻ የሚነሳ ሃሳብ ለህዝብም አይጠቅምም፡፡ አበቃሁ፡፡