Quantcast
Channel: Abugida Ethiopian American Amharic Web Page
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1809

ከስብከት ንስሃ ይቅደም! በላይነህ አባተ

$
0
0

ዓይን ስላለን እናነባለን፣ ጆሮ ስላለን እንሰማለን፣ አይምሮና ህሊና ስላለንም እናሰላስላለን፡፡ አይምሮና ህሊናችንን ካልተጠቀምንና ካላሰላሰልን እንሰሳ ወይም ግዑዝ ነን፡፡ እንሰሳ ወይም ግዑዝ ስላልሆን መንግስቱ ኃይለማርያም መጣፍ ጣፈ፤ አነበብን፡፡ ፍቅር-ሰላሴ ወግደረስ መጣፍ ጣፈ፤ አነበነብን፡፡ ፍስሃ ደስታም መጣፍ ጣፈ፤ አገላበጥን፡፡ ፍስሀ ደስታ ይቅርታ የጠየቀበትን ወንጀሉን ዘርዝሮ ሳይናገር የይቅርታ ከረሚላ እንደ ልጅ ስላላሰን አንዳንዶቻችን እንደ ንፍሮ ሙክክ አልን፡፡ የይይቅርታ ከረሚላ መፈብረክ ያቃተው ታምራት ላይኔ በሕዝብና በአገር የሰራውን ግፍ ሳይናዘዝ “ጌታን ተቀበልኩ” ብሎ ስላለቀሰ አብረን ዘመርን፡፡ ከታምራት ጋር ግፍ የሰራውና ከግፍ ግብር ገና ያልተላቀቀው ጻድቃን ገብረ ተንሳይ የጻፈውን ጠልሰም አንጠለጠልን፡፡ ያንጠለጠልነው ጠልሰምም እንደ መተት እዝለ ልቡናችንን አነሁልሎን እንደ ፕሮፌሰር መሳይ “እውነተኛና ግልጽ ትችት፣ ከልብ የመነጨ መፍትሄ አቅራቢ” read this እያልን ምስክርነት እየሰጠን የምንጃጃል በረከትን፡፡

በመጃጃላችንም ወንጀለኞች ሲቀድሱ ተሰጥኦ እንቀበላለን፤ ሲሰብኩም አፋችንን ከፍተን እናዳምጣለን፡፡ ንስሃ ያልገቡ ወንጀለኞች ስብከት ለስጋም ለነፍስም እንደማይበጅ ከታሪካችን፣ ከተሞክሯችንና ከቅዱሳን መጽሐፍት መማር አቃተን፡፡ ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚያስተምሩት ንጉስ ዳዊት የሠራቸው ስህተቶች፣ ክህደቶችና ወንጀሎች ተዘርዝረው አያልቁም፡፡ ዳሩ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ከተጠቃለሉት መጻሕፍት ሁሉ እሚረዝመው የዳዊት መዝሙር ለብዙ ሺ አመታት ተነቧል፤ ዛሬም ይነበባል ወደፊትም ሳይሰለች መነበቡ ይቀጥላል፡፡ መዝሙረ ዳዊት ተነቦ እማይጠገበው ዳዊት ከልባዊ የፀፀት ወንበር ተቀምጦ፤ የፀዳ የንስሃ ጠረጴዛ ተደግፎ እያለቀሰ በእንባው ስለጻፈው ነው፡፡ ዳዊት የፈጸውው ወንጀሉ ተረስቶ እሚወደደው ከንስሃው እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ከዳግም ሐጥያት ራሱን ጠብቆ ስለኖረ ነው፡፡

መዝሙረ ዳዊትን ሳይሆን መዝሙረ ወንጀለኛን የሚዘምሩልን የኢትዮጵያ ሰባኪዎች የተቀመጡት ከፀፀት ወንበርና ከንስሃ ጠረጴዛ ሳይሆን ከተረሸኑ ዜጎች መቃብር ከተጋደመ የክህደትና የውሸት አግዳሚ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊት ወላድ በድባብ ትሂድና እናቶቻቸው መንግስቱ፣ ፍቅረሰላሴ፣ ፍስሃ፣ ታምራት፤ ጻድቃን ወዘተርፈ እያሉ በሰምና በወርቅ ያጌጡ ስሞች አውጥተውላቸው ከይሁዳ የከፋ አስቀያሚ ተግባር ሲፈጽሙ የኖሩትና ካለሐፍረት ዛሬ እንደ ጻድቅ እሚሰብኩን ከሐጥያት መቀመቅ ተዘፍቀው ነው፡፡

እነዚህ ከሐጥያት መቀመቅ የወረዱት ግፈኞች የሌሎችን ስህተትና ወንጀል እሚሰብኩን በራሳቸው እጅ፣ በራሳቸው ትእዛዝ ወይም በመዘዙት መዘዝ ምን ያህል ደም እንደፈሰሰ፣ ስንት ዜጎች መቃብራቸውን ቆፍረው እንደተቀበሩ፣ ስንት እናቶች በሐዘንና በድንጋጤ እንደሞቱ፣ ሰንት ልጆች ያላሳዳጊ እንደቀሩ፣ ስንት ወላጆች ያለጧሪ እንደቀሩ፣ ስንቶች አካለ ስንኩላን እንደሆኑ ሳይነግሩን ነው፡፡ እነዚህ ወንጀለኞች የሌሎችን ወንጀል እሚያዜሙልን በእነሱ ጭካኔ ስንቶቾ በርሃብና በሽታ እንዳለቁ፣ ስንቶች ወህኒ እንደማቀቁ፣ ስንቶች እንደተገረፉ፣ ስንቶች እንደተኮላሹ፣ ስንቶች በፈላ ውሀ እንደተቀቀሉ፣ ስንቶች ጥፍራቸውን እንደተነቀሉ፣ ስንቶች ባውሬ እንደተበሉ፣ ስንቶች ያረብ ገረድ እንደሆኑ ሳይነግሩን ነው፡፡ እነዚህ ሐጢያተኞች ሊሰብኩን እሚከጅሉት ያቶ ኤርምያስ ለገሰና ያቶ ገብረመድህን አርአያን ያህል እንኳን ኃጥያታቸውን ሳይናዘዙ ነው፡፡ እነዚህ ዓይነ-አውጣዎች ሊያሳምኑን እሚዳዱት ከሐጥያት መቀመቅ ተዘፍቀው በተበከለ ጣታቸው ኮቢ እያነሱ ነው፡፡ እነዚህ አታላዮች በተበከለ እንጃቸው የሞነጫጨሩትን እንድናነብላቸው እሚመኙት የበደሉትን ሕዝብ ለመካስ ቁርጠኝነት ሳያሳዩና ዳግም ግፍ ላለመፈጸም በሚያመልኩት የገንዘብ ወይም የስልጣን ጣኦት ሳይምሉ ነው፡፡

ሐጥያተኛ ንስሃ ሳይገባ ከሐጥያቱ መቀመቅ ተዘፍቆ እሚሰብከውን ስብከት “እውነተኛ፣ ከልብ የመነጨ” እያሉ መመስከር ምስክርነትን ማርከስ፣ በንስሃ አለማመን፤ እውነትን አለመሻት፣ መጃጃል ወይም ለመጃጃል መሞከር ነው፡፡ እውነትን እንድንሻና እንዳንጃጃል የሚያይ ዓይን፣ የሚሰማ ጆሮ፣ የሚያሰልስል አይምሮና ክፉውን ከደጉ እሚለይ ህሊና አስታጥቆ ፈጥሮናል፡፡ የሚያሰላስል አይምሮና ክፉን ከደጉ እሚለይ ህሊና ያለን ተሰባኪዎች የምንጮኸው ወንጀለኞች እንደ ዳዊት ከስብከት ንስሃን ያስቀድሙ እያል ነው፡፡ ከስብከት ንስሃን እንዲያስቀድሙ ይርዳቸው፡፡ አሜን፡፡

ሐምሌ ሁለት ሺ ስምንት ዓ.ም. abatebelai@yahoo.com)


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1809

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>