Quantcast
Channel: Abugida Ethiopian American Amharic Web Page
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1809

የተሰደዱ እና ባገር ውስጥ በየእስር ቤቱ የታጎሩትን ጋዜጠኞች እና ጸሃፍትን ብዛት ላሰበ ሰው አማርኛ አሁንም የሚጻፍበት ቋንቋ ሆኖ መዝለቁ እሰየው ነው። አሊ ጓንጉል

$
0
0

ደርጉ ሲረገምበት ከሚኖርባቸው ሌሎች ብዙ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ፣ በማንኛውም ስነ-ጽሁፍ ላይ ያደርገው የነበረው ”ሳንሱር” እና፣ ሊሾም ሊሸለም ይገባው የነበረውን በዓሉ ግርማን ያህል ታላቅ ደራሲ መግደሉ ነው። ይኼም ሆኖ ግን፣ በደርጉ ጊዜ ይታተሙ በነበሩ መጽሃፎች ዙሪያ በእነ “መጽሃፈ ሲራቅ”፣ “አቸናፊ ዘደቡብ አዲስ አበባ”፣ ጠንክር ዘካዛንችስ፣ “ዳግላስ ጴጥሮስ” … ወዘተ በመሳሰሉት የብዕር ስሞች ይቀርቡ የነበሩት ስነ-ጽሁፋዊ ትችቶች ብስለት እና የስነ-ጽሁፉን እድገት የምታውቀው ያንዱን ትችት አንብበህ እና “ፖ!” ብለህ አድንቀህ ሳታበቃ አንዱ አዲስ አርታዒ የፊተኛውን ተችቶ ስታነብብ፣ ያን “ፖ!” ያስባለህን ጽሁፍ ታወርደዋለህ፣ እንደገና ይኼኛውን ደግሞ ሌላው ጸሃፊ ሲተች ስታነብ፣ የፊተኛው ተቺ ያላያቸውን አዳዲስ ጉዳዩች ሲያነሳልህ ታደንቃለህ። የደርጉ የሳንሱር ማነቆ እንዳለ ሆኖ፣ ይህ የስነ-ጽሁፍ እድገት መገለጫው ነው።

ዛሬ ዛሬ በሩብ ክ/ዘመን ወደ ኋላ ቀረንና፣ አለማዊ በሚሰኘው ጽሁፍ ዙሪያ ሁሉ ባብዛኛው ሲጽፉ የምናየው ዲያቆናት እና ደብተራዎች ብቻ የሆኑ ይመስላል። በቅርቡ በውቀቱ ስዩም በጻፈው “ከአሜን ባሻገር” መጽሃፍ ላይ ከወጡት አንድ አራት ትችቶች ውስጥ፣ ስሙን መጥቀስ ካልፈለገው አንድ በሳል ጸሃፊ እና ከኔው በስተቀር፣ ሁለቱ በጽሁፋቸው እንደምንረዳው እና በማእረጋቸውም ባደባባይ እንደነገሩን ዲያቆን እና የቤተ-ክህነት ሰዎች ናቸው። ዲያቆን እና ደብተራ አለማዊ ጽሁፍን አይተችም አይባልም። መተቸት የማንኛውም ሰው መብት ነው። የአርታኢነት ስነ-ምግባር እንዲኖር ግን ያስፈልጋል፤ ከተራ ስድብ እና ዘለፋ ያለፈ፣ አስተማሪ እና ሚዛናዊ ሊሆን ይገባዋል። ከቤተ-ክህነት ጋር ግንኙነት ካላቸው ታዋቂ ጸሃፊያን አንዱ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ነው። ሰለሱ ታች ላይ እመለስበታለሁ።

ጥቂት ወራት ቀደም ብሎ “የመቀሌ አማርኛ በአዲስ አበባ” በሚል ርዕስ የወጣውን ጽሁፍ አይቶ ያልገረመው ሰው፤ በተለይም መገናኛ ብዙሃን እና ቋንቋ አካባቢ የሰራ ወይም እየሰራ ያለ ሰው ቢኖር ይገርመኛል። ጽሁፉ የሚያሳየው ነገር ቢኖር፣ ያገሪቱ የትምህርት ስርዐት እየሞተ መሆኑንም ነው። በርካታ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል።

ቃላት ካንዱ ቋንቋ ወደ ሌላው የመዋዋስ እና የማልመድ ነገር አዲስ አይደለም። አማርኛ ሆኖ ለምዶ የቀረ በርካታ እንግሊዝኛ ወይም ፈረንሳይኛ ቃላትን (እንደ “ሸሚዝ” የመሳሰሉ) በምሣሌ መጥቀስ ይቻላል። ስረ-መሰረታቸው አንድ ግዕዝ የሆነው አማርኛ እና ትግርኛም ሲወራረሱ እና አንዱ ከሌላው ጋር የመመሳሰላቸው ጉዳይ አያስገርምም። የየቋንቋዎቹን የሰዋሰው ስርዓት ማዛባት ግን ስህተት ነው። አቅሙ ካለ እንኳንስ የፌደራል የስራ ቋንቋ የሆነው አማርኛ፣ ቋንቋዎች ሁሉ በጥናት እና ክትትል እንዲጎለብቱ ማድረግ ተገቢ ነበር። በ“የመቀሌ አማርኛ በአዲስ አበባ” ላይ በግልጽ እንደተዘረዘሩት አይነት ስህተቶች ደግሞ የቋንቋ/ው እውቀት በሌላቸው ሰዎች የሆነም ይመስለኛል።

ሳይቸግር በአማርኛ ውስጥ የትግርኛ ቃላት መሰንቀርም እየታየ ነው፣ ለዚያውም በቋንቋው ላይ በተከታታይ ጽሁፎችን እያቀረቡ ባሉ ሰዎች። ዳንኤል ክብረት የሚጽፋቸውን ጽሁፎች አነባለሁ (አንዳንዶቹን)። አንዳንድ ጊዜ የሚያነሳቸውን ጉዳዮች ያየባቸውን ማዕዘናት እወድለታለሁ። ጥቂት ቀደም ብሎ “አዳቦል” በሚል ርዕስ በለቀቀው ጽሁፍ ውስጥ “መመያየጥ/ምይይጥ” የሚለውን የትግርኛ ቃል በአማርኛ ጽሁፉ ውስጥ ሰንቅሮታል። ይኸው፦

“… ለሰው የሚገባው፣ ግልጽ የሆነና ፍሬ ያለው ነገር ለመና[ገ]ርና ለመጻፍ የቋንቋ ችሎታም ያስፈልጋል። … ሳይሰክን የተቀዳ ቡናና መግለጫ ያጣ ሐሳብ አቅራቢ አንድ ናቸው። … የቋንቋ ችሎታ ማለት ጉዳዩን እስከ ጥግ ድረስ በመናገሪያው ቋንቋ አልቆ ለመናገር መቻል ነው።… ሐሳቡን በራስህ መንገድ ማቅረብ ስለማትችል በአሰልቺ ቃላት (ጃርገን) ትሞላዋለህ። አዳቦልነት … እየበዛ በሄደ ቁጥር የመልዕክት ልውውጡ የተሰበረ፣ አንጆ አንጆ የሚል፣ ችክታ የበዛበት፤ ተግባቦት የሚያጥረውና ሐሳቡ የነጠፈ ይሆናል። ይኼ ደግሞ የዕውቀት ሽግግርን፣ የሐሳብ ምይይጥን፣ የመልእክት ዝውውርን ይጎዳል…”

“ምይይጥ” ህወሃትን ተከትሎ መሃል አገር የገባ የትግርኛ ቃል ነው–ቃሉ እንደ ትግርኛ ቋንቋ ቃል ወትሮም የነበረ ቢሆንም። እኩያ አማርኛው “ውይይት”፣ እንግሊዝኛው ደግሞ “discussion” ይመስለኛል። ዳንኤል የተጠቀመበት አውድ ይህን የትግርኛ ቃል ለመጠቀም የሚያስችልም የሚያስፈልግም አልነበረም። ዳንኤል ቃሉን የተጠቀመበት፣ የሌሎች ሰዎችን ቋንቋ ለመተቸት በጻፈው ጽሁፍ ውስጥ መሆኑ ደግሞ “ምጸት” ያደርገዋል። በጽሁፉ ወስጥ የተበላሸው አማርኛው ብቻ ሳይሆን ትግርኛውም ነው። የቋንቋው የግስ እርባታ ህግም ነው የተበላሸው።

“… የቋንቋ ችሎታ ማለት ጉዳዩን እስከ ጥግ ድረስ በመናገሪያው ቋንቋ አልቆ ለመናገር መቻል…” እንደሆነ የሚነግረን ዳንኤል ክብረት፣ ቁልጭ ያለውን እና ምንም አይነት ማብራሪያም ሆነ ፍቺ የማያስፈልገውን የአማርኛውን “ውይይት” በትግርኛው “ምይይጥ” ተክቶ መጠቀም እና “አሰልቺ ቃላት” የሚለውን ሃረግ፣ በእንግሊዝኛው (ለዚያውም ጨርሶ በማይመስለው) “ጃርገን” መፍታት/ማብራራቱም ራሱ ስህተት ነው የሚመስለው። ምክንያቱም አንዱ ሌላውን ሊተካ አይችልም።

… ዳንኤል ‹‹የጠቅል አሽከር›› በሚል ርዕስ በለቀቀው በሌላ ጽሁፉም ውስጥ “አነዋወር” የሚለውን ቃል የ“ኑሮ” የግስ እርባታ አንዱ አድርጎ ነው የተጠቀመበት።
“… በርግጥ ያንን ሕዝብ አንድ ሕዝብ የሚያደርጉት የጋራ ባሕል፣ ቋንቋ፣ እምነት፣ የአነዋወር ዘይቤ ይኖረዋል። … በትውልድ የዚያ ማኅበረሰብ አባል ከመሆኑ በቀር በቋንቋ፣ በእምነት፣ በባሕል ወይም በአነዋወር ዘይቤ የማይመሳሰል ሰውም አለ።…”
“አነዋወር” የሚለው ቃል በዚህ ዓ.ነገር አውድ ውስጥ “አኗኗር” ለማለት ካልሆነ ሌላ ምን ለማለት ሊሆን እንደሚችል አይገባኝም።
“አነዋወር” የ“ነውር” እርባታ ይመስለኛል ሊሆን የሚችለው። [ሸፍጥ › ሸፍጠኛ › አሸፋፈጥ] ሲል እንደሚረባው ሁሉ፤ [ነውር› ነውረኛ› አነዋወር] “ ቢባል ያስኬድ ይመስለኛል። ስለዚህ “አነዋወር” ካለቦታው የገባ ይመስላል–“አነዋወር” በግዕዝ ወይም በመጽሃፍ ቅዱስ ቋንቋ/ፍቺ “አኗኗር” ማለት ነው ካልተባለ በስተቀር። ብቻ… የመጽሃፍ ቅዱስ ስነ-ጽሁፍ እንደ አብዛኛው ያገሬ ሰው ሳይገለጥልኝ እንዳልሞት።

በተረፈ ዳንኤል ክብረት የ“የበጎ ሰው ሽልማት” ድርጅት መስራች መሆኑን በቅርቡ ባንዱ ጽሁፍ ውስጥ ያየሁ ይመስለኛል። ስለ ራሳችን እርስ በርሳችን ስለ-አለመተማመናችን፣ …ወዘተ በርካታ ጸለምተኛ የሆኑ ነገሮቻችን ብቻ ጎልተው በሚወሩበት እና በሚነገሩበት በዚህ በኛ ማህበረሰብ ውስጥ እንዲህ በጎ ስራ የሰሩ ሰዎችን እየመረጡ ማቅረብ እና መሸለም፣ ተተኪው ትውልድም እንዲማርበት የሚያደርግ ነውና ዳንኤል ክብረትን በመልካም ስራው እጅግ አከብረዋለሁ– አገር እንዲያድግ እና እንዲለማ ምኞት እና ፍላጎት ያለው ሁሉ ይህ የዳንኤል ጅምር እንዲቀጥል የበኩሉን እንዲያደርግ አበረታታለሁ–አንዳንድ “በበጎ ሰውነት” በተመረጡት ሰዎች ላይ ቅሬታ ቢኖረኝም።

በጥቅሉ የቋንቋው እንዲህ እየሞተ መምጣት የትም/ስርዓቱ ሞት መገለጫም ነው። ፍትህ እና ነጻነት በሌለበት ማህበረስብ ውስጥ የትምህርት ስርዓቱ ሁልጊዜም በነጻ ውድድር በችሎታቸው እየተራቀቁ እና እየመጠቁ ሊወጡ የሚችሉ ሰዎችን ወደ ኋላ እያስቀረ እና አንገት እያስደፋ፣ አድርባይ እና ለጥቅም ያደሩ ስዎችን እያቀና እና እያግበሰበሰ ይጓዛል።

የአርባ ሁለት የአ.አ.ዩ. ፕሮፌሰሮች ባንድ ጊዜ በመለስ ዜናዊ ትዕዛዝ ከስራ መባረር (ምሁራኑ ባሁኑ ጊዜ በየምዕራብ አገሩ ተበትነው፣ በየከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ውስጥ ከፍተኛ መምህራን ሆነው እየሰሩ ነው) በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በቋንቋው ላይ ያሳደረው ጫና ቀላል አይደለም። በነጻነት እና ፍትህ ማጣት አገራቸውን ጥለው የተሰደዱ እና አገር ቤት ውስጥ በየእስር ቤቱ የታጎሩትን ጋዜጠኞች (እስክንድር ነጋ፣ እና ሌሎቹም) እና ጸሃፍትን ብዛት፣ ላሰበ ሰው አማርኛ አሁንም የሚጻፍበት ቋንቋ ሆኖ መዝለቁ እሰየው ነው።

አማርኛ እየወረደበት ያለው መቀመቅ አስፈሪ ነው። አሁን በዚያ የአረቦች አመጽ ሰሞን፣ በጀርመን ድምጽ ሬድዬ “አረብ ስፕሪንግ” የሚለውን እንግሊዝኛ “የአረብ ጸደይ” በሚል ተተርጉሞ ሲነበብ ሰምቻለሁ። በ“Arab spring” ውስጥ ያለው “spring” የሚለው ቃል፣ አመጹ ከቱኒዚያ ተነስቶ እና ባንዴ ተስፈንጥሮ ሌሎቹን የአረብ አገሮች እንዴት እንዳዳረሰ የአመጹን በፍጥነት ወደሌሎቹ አገሮች የ“መስፈንጠሩን” ሂደት የሚገልጽ ነው፤ እንጂ ከወቅት ገላጩ “spring” (ጸደይ) ጋር የሚያመሳስለውም ሆነ የሚያገናኘው ነገር የለም። የአሜሪካ ድምጽም ይኸኑ በቅርቡ ሲደግም ሰምቻለሁ ልበል?

የትርጉም ነገር ከተነሳ አይቀር በ1996 ዓ.ም “ሳባ” በሚል ርዕስ የታተመውን የ“እንግሊዝኛ-ትግርኛ-አማርኛ” መዝገበ ቃላት (ለምሳሌ “abyss”ን “ገደል” ብሎ ተርጉሞታል) ያነበበ ሰው፣ ድሮ ድሮ በ1950ዎቹ የታተመውን “ያለ-አስተማሪ” መዝገበ ቃላት፣ እንደ አቡነ ተክለሃይማኖት ባንድ እግሩ ቆሞ ሃያ አራት ሰዓት ሙሉ ያጨበጭብለት ይመስለኛል። በ“አረብ ስፕሪንግ=አረብ ጸደይ” ትርጉም አኳያ ሲታይ ደግሞ ለ“ሳባ” መዝገበ ቃላት ልናጨበጭብ ይገባል።

የጀርመን ድምጽ ሬድዮ፤ አንዳንዴ አማርኛ የሚቸግረው ጣቢያ ነው። እያንዳንዱ ቋንቋ የራሱ የሆነ የአነባበብ ስልት (ለምሳሌ ፍስሠት፣ “ፋታ” [pause?]፣ ድምጸት [tone?] ወዘተ …) አለው። የአንዳንድ ቀኑ አነባበብ የተለመደው የአማርኛ ቋንቋ ድምጸት የለውም። ፋታ በሚያስፈልገው ቦታ ላይ (ለምሳሌ የአንድ ዓ.ነገር ማሰሪያ/ማለቂያ) ላይ ፋታ-ቢስ ሆኖ ወደ ሌላው ዓ. ነገር ፈስሦ ይወርዳል፣ አንዳንዴ ደግሞ ፋታ በማያስፈልገው ቦታ ላይ (ለምሳሌ “አበበ በሶ…..[ረጅም ፋታ ይሆንና] … በላ”) አይነት አነባበብ የተለመደ ነው የሚመስለው። አንባቢው መቸስ ከአገር ከወጣ በጣም ቆይቶ ኖሮ፣ አማርኛ ቸግሮት ነው … አይባል ነገር፣ አማርኛው የጠራ ነው፣ ማለትም “አክሰንት” የለውም። የኖረበት የባህር ማዶ አገር ቋንቋ አነባበብ ተጽእኖ አሳድሮበት ሊሆን ይችል ይሆን? እላለሁ–አንዳንዴ … እንዲያው ሳስበው ግን ራስን ላለመሆን ከራስ ጋር በሚደረግ ግብ ግብ፣ ወይም ሌላውን ለመምሰል፣ የተከሰተ ይመስለኛል። እንዴ..? አንዳንዴ’ኮ ስረ መሰረቱ ያልታወቀ ዜማ የሚያዜም እንጂ ዜና የሚያነብ አይመስልም።

እያንዳንዱ አንባቢ የራሱ የሆነ “ስታይል” (ዘዬ?) ይዞ መውጣት ይችላል፣ የቋንቋውን አነባበብ ህግ እና ደንብ መስዋዕት እስከማድረግ መድረስ ግን የለበትም። ድምጽ ለማሳመር መሟሟት ያለበት ድምጻዊ (አቀንቃኝ/ዘፋኝ)፤ የሚጫወተውን ገፀ-ባህሪ ለመምሰል መሟሟት ያለበት ደግሞ የድምጽ ተራኪ ነው። የድምጽ ጋዜጠኛ እና አንባቢ ደግሞ እንደወረደ የቋንቋውን አነባበብ ህግ እና ደንብ ተከትሎ … በተፈጥሮ ያለን ድምጽ ዝም ብሎ ማፍሰስ ነው። ለምሳሌ በኢሳቱ “ሁሌ አዲስ” ዝግጅቱ መግቢያ ላይ አንባቢው የሚያወጣው ዜማዊ ድምጽ፣ የራሱ እና እንዳለ እየወረደ ያለ ድምጽ አይመስልም። ይህ አንባቢ ራሱ ሳይዘጋጅ “እንደወረደ” እንብቦ ራሱን ቀድቶ ቢያዳምጥ፣ የራሱን ድምጽ እና በኢሳቱ የ‘ሁሌ አዲስ’ ፕሮግራም መግቢያ ላይ የሚያቀርበውን በየተራ ቢያዳምጠው፣ ልዩነቱን ራሱ መታዘብ የሚችል ይመስለኛል።

አላግባብ አንድን ቃል “መጎተት” ለምሳሌ “ዘወትር” የሚለውን ቃል “ዘ—–ወትር” በሚል አነባበብ መጎተት ወይም ከ“ዘ” ፊደል በኋላ አላግባብ ረጅም pause “ፋታ”?) ማስገባት ባላስፈለገም ነበር። በዚህ አጋጣሚ፣ የኢሳቱ ብሩክ ይባስ፣ በድምጹ ጥራት እና በአነባበብ ፍሰት፣ አይኑን ከሚያነበው ወረቀት ላይ አንስቶ ወደ ተመልካቹ ወይም ካሜራው የሚመልስበት ጊዜ መገጥጠም፣ ኢሳት ካሉት በርካታ ግሩም አንባቢዎች ውስጥ አንዱ ነው። ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌናም ሌላው ግሩም አንባቢ እና አቀናባሪ ጋዜጠኛም ነው። የሚያወያያቸው ስዎች ከአጀንዳው ሲወጡ ወደ ጉዳዩ የሚመልስበት የጋዜጠኝነት ጥበቡ ግሩም ነው። ሰሞኑን ማንበብ የጀመረችው የኦሮምኛ ዜና አንባቢ ደግሞ፣ የተፈጥሮ ድምጿ ጥራት ጥሩ እና ዝነኛ አንባቢ እንደሚያደርጋት መገመት ይቻላል።

በሚቀጥለው ጽሁፌ፣ ከኢሳት እስከ ኢቲቪ፣ ከአዲስ አድማስ እስከ ሪፖርተር እና ሬዲዬ ፋና … ወዘተ፤ እንደ ተስቦ በሽታ በሚዛመት መልኩ እየተለመደ ያለውን የአማርኛ ሰዋሰው ግድፈት በተመለከተ ሌላ ጽሁፍ ይዤ ለመቅረብ እሞክራለሁ።

ቸር ይግጠመን።
አሊ ጓንጉል


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1809

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>