መቼ ነው በሐገራችን ውስጥ እረሃብ የሚጠፋው? ሰርተን፤ በልተን፤ ጠግበን የምንኖረው?
መቼ ነው በተማርነው መሰረት ያለዘመድ ሥራ የምናገኘው?
መቼ ነው ዘረኝነት የሚጠፋው? እኩልነት የሚሰፍነው?
መቼ ነው ዝርፊያው፤ ሙስናውና ብዝበዛው የሚቆመው?
መቼ ነው የሐገሪቷ ሀብት ወደ ውጭ ሀገር የሚሰረቀው? ገንዘቧ የሚራቆተው? የመግዛት አቅሟ የደቀቀው?
መቼ ነው በሐገራችን ኮርተን መኖር የምንችለው?
መቼ ነው በሐገራችን ውስጥ እንደልባችን ሃሳባችንን መግለፅ (በአፍ፤ በፅሁፍ፡ በራዲዮ፤ በቲቪ) የምንችለው? በተነፈስን ጊዜ ሁሉ ግራና ቀኝ የማናየው?
መቼ ነው በሐገራችን ዲሞክራሲን ዕውን የምናደርገው? በነፃ የመወዳደራችን መብት የሚከበረው? በፈልግንበት የፖለቲካ ድርጅት ሥር ለመሥራት የምንችለው? የፈልግነውን ተወዳዳሪ መምረጥ የምንችለው?
መቼ ነው “አምስት ለአንድ” ተደራጅተህ እኔን ብቻ ምረጠኝ የሚለውን የዲሞክራሲ ባላንጣ በፈቃዳችን መገርሰስ የምንችለው? መቼ ነው ድምፃችን በዲሞክራሲ ሕግ እንደ መራጭ ሕዝብ የሚሰማው?
መቼ ነው በሐገራችን ውስጥ በሰላም የምንኖረው? ያለፍርሃት ወጥተን ያለፍርሃት ተመልሰን ወደ ቤታችን የምንገባው?
መቼ ነው በሐገራችን ውስጥ የሕግ የበላይነት የሚከበረው/የሚሰፍነው? መቼ ነው ሕዝብ ያፀደቀው ሕገ መንግሥት የሐገሪቱን ሕዝብ መብት የሚጠብቀው?
እስከመቼ ነው ተምረን እንዳልተማረ፤ የአምባገነኖች ቅጥር በመሆን፤ በዪና አስበዪ የምንሆን? የአምባገነኖች ፖሊሲ አቀንቃኞች፤ ጠበቆች፤ ዳኞች፤ አስተዳዳሪዎችና ወታደሮች የምንሆን?
መቼ ነው ልጆቻችን እናት ኃገራቸውን ለቀው፤ ሞትን መርጠው፤ ወደማያውቁት ህገር መሰደድ የሚያቆሙት? መቼ ነው እንደአያቶቻቸው በኩራት ኃገራቸው/ቀያቸው ውስጥ በኩራት የሚኖሩት? እንደልባቸው ወጥተው እንደልባቸው የሚገቡት?
መቼ? መቼ? መቼ? መቼ? መቼ? መቼ? መቼ? መቼ ነው።
የፖለቲካ እንካ ሰላምታ ያብቃ
ሰሞኑን፤ የአ/አባባን ማስተር ፕላንን በመቃወም በኦሮምያ አካባቢ የተጀመረውን የሕዝብ አመፅና እንቅስቃሴ እንደምክንያት በመጠቀም፤ ብዙ የተቃዋሚ ድርጅቶች እርሰ በርሳቸው መነጋገር መጀመራቸው በጣም የሚያስደስት ነው። ሁላችሁም በአንአድነት፤ ለዲሞክራሲ፤ ለፍትህ፤ ለፍቅርና ለብልፅግና ለመሥራት መነጋግርችሁ ታላቅ ጅማሬ ነው። እግዚአብሔር ይርዳችሁ።
እንግዲህ ከሃምሳ አመት በላይ የተካሄደው “የፖለቲካ እንካ ሰለምታ” ይቁም። ዶ/ር በያን አሶባ በቅርቡ በአዲስ ድምፅ እሬድዮ “ሁሉም የተቃዋሚ ድረጅቶች የጋራ ፕላትፎርምና ስምምነት አድረገን ዲሞክራሲያዊ ትግል ማካሄድ አለብን። …70% የሚሆነው ኢትዮጵያዊ እድሜው በሰላሳ ዓመት ቤት ነው። … የኛ ትውልድ አሁን ይሄን ትብብር ካላደረገና የዲሞክራሲ ትግል ካላካሄደ ጊዜው ያልፍበታል … በጥድፍፊያ እስከዛሬ ያልሰራንውን ሰርተን ለመጪው ትውልድ የማስረከብ ግዴታ አለብን …” ብለዋል። እንደዚህ አይነት የሚያረካ ንግግር ከተቃዋሚዎች አፍ መስማት ትልቅ ነገር ነው። ዛሬ ነገ ሳንል አንድነታችንን እናጠንክር።
እስካሁን የነበረው አካሄዳችን በጣም የሚያስዝን ነበር። ትላንትና በዳይፐር ተጠቅልልለው በቅኝ አገዛዝ ስርዓት ይድሁ የነበሩት የአፍሪካ አገሮች እንኳን፣ እኛ “የፖለቲካ እንካ ሰላምታ” ቁጭ ብለን ስንለዋወጥ፣ በአጭር ግዜያቶች ጥለውን በርረዋል። እኛ ከቅኝ ግዛት እንዲላቀቁ የረዳናቸው ብዙ ሃገሮች ዲሞክራሲን ሲገነቡ እኛ ወደኋላ ተመልሰን በራሳችን ልጆች ተገዚዎች ሆነናል። እኛ ለመሰረትነው የአፍሪካ እግር ኳስ ድርጅት፤ ቋሚ ተመልካቾች ሆነናል። አያችሁ፤ ከአያቶቻችን እንሻላለን እንላለን። እነሱ ግን ከና ከድሮው “የተናቀ ይስረግዛል” ብለው ጨርሰውታል።
አያቶቻችን ባቆዩልን የሺህ ዓመታት ነፃነት ውስጥ፤ እንኳንስ የቴክኖሎጂ እድገት ልናመጣ ይቅርና ጠግበን ለማደርም አልቻልንም። በየሰላሳና በየሃምሳ ዓመታቶች ሕዝባችን በከፋ የረሃብ ሰቆቃ ውስጥ በተደጋጋሚ እየተዘፈቀ የዓለም ለማኞች ሆነን ቀርተናል።
በእንደዚህ አይነት ጉዞዋችን፡ የጎንደር፤ የአክሱምና የላሊበላ ታሪካችን ለዓለም ሕዝቦች “የልብ ወለድ ታሪክ” ሊመስላቸው የሚችልበት ወቅት እሩቅ አይመስልም። ለዚህ ሁሉ ድክመት (ክሽፈት እንዳሉት ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም) በኔ አስተሳሰብ፤ ከአፄ ኃ/ሥላሴ ጀምሮ የነበረው ትውልድ ነው። ከዚያ በፊት የነበረውን ትውልድ ዘመናዊ መንግሥትና ዘመናዊ የትምህርት ስርዓት ካለመኖር ጋር አያይዘን ከተጠያቂነቱ ብናላቅቀው ይሻል የመስለኛል።
እንግዲህ፤ በአፄ ኃ/ሥላሴ ጊዜ የነበረው ትውልድ፤ በየተማሪ ቤቶች ቅጥር ግቢ ውስጥ፤ በቀ ኃ/ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እየተመራ የነደፈውን አብዮታዊ ትግል አጫጭሶ የገዢውን መደብ ለመገርሰስና ተራማጅ የሕዝብ መንግሥት ለመገንባት ታላቅ መስዋእትነት ከፍሏል።
ይሄው አብዮቱን በቀደምተኝነት በዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ ይመራ የነበረው ተማሪ፤ ግቢውን ለቆ ከወጣ በኋላ ግማሹ በከተማ ሆኖ፤ ሌላው ደግሞ ወደሜዳ ወርዶ የአብዮቱን አቅጣጫ በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ሥር እየቀየሰ ታግሏል።
አሁን ኢትዮጵያና ኤርትራ ወስጥ ያሉት የገዢ መደቦችም በዚያን ወቅት ተረግዘው ጭንጋፍ የሆኑ የኢትዮጵያ ተማሪዎች አብዮት ናቸው። በደርግ ጊዜም የሰፊውን ሕዝብ አብዮት ያኮላሹት ከነዚህ ጭንጋፎች ያልተሻሉ ዩኒቨርስቲው የወለዳቸው የአብዮቱ የእንግዴ ልጆች ናቸው። ከ40 ዓመታት በበለጠ የፖለቲካ እንካ ሰላምታ ተፋጥጠው በኤርትራና በኢትዮጵያ ውስጥ ላሉት ጭንጋፎች፡ የዕድሜ ማራዘምያ ዋስትና በሚያስገርም መንገድ እየሰጡ ያሉትም አሁንም ከዚያው ከቀ.ኃ.ሥ ዩኒቨርስቲ የበቀሉት ተራማጅ ተማሪዎች ናቸው። ይሄ “የአፄ ኃ/ሥላሴ እርግማን ይሆን?” ያሰኛል።
ስለዚህ፤ እርግማንም ከሆነ ጠበል እንረጭና፤ ለሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት፤ ፍትህ፤ መብትና ብልፅግና፤ ነገ ዛሬ ሳንል፤ በጋራና በትብብር እንስራ።
ከአብዮቱ አበይት ጥያቄዎች ሁለቱን ለመጥቀስ
መሬት ላራሹ አማሮችን በተመለከተ
በወቅቱ የነበረው ታላቁ ጥያቄ ከመሬት አስተዳደር ጋር የተቆራኘ ነበር። መሬት ለአራሹ ይሰጥ። የመሬቱ ባለቤት ጭሰኛ ሆኖ ሳለ፤ በላዩ ላይ ተመርቶ ለመጣው ሰው ገባሪ ሆኖ ከሚያመርተው ሰብል አንድ ሶስተኛውን ይገብራል።
ለመሆኑ ይህ የመሬት አያያዝ እንዴት እንደነበርና በምን አኳኋን እንደተያዘ በአጭሩ ብንመለከት፡
1ኛ በእርስት መልክ የተያዘ መሬት። ይህ መሬት ከአባት ወይንም ከእናት የተወረሰ፤ ሲወርድ ሲዋረድ በውልደት የተገኘ መሬት ነው።
2ኛ በጉልት የተያዘ መሬት። ይህ መሬት የመንግሥት ሆኖ አራሹ ግብር እየገበረ የሚተዳደርበት መሬት ነው።
3ኛ የማደሪያ መሬት። ይህ መሬት መንግሥት በድሮ ጊዜ ለሰራተኞቹ (ለምሳሌ ወታደሮች) እንደ ደምዎዝ የመደበላቸው መሬት ነበር።
4ኛ ከማደሪያ መሬት የሚመሳሰለው ሌላው የመሬት አያያዝ ደግሞ የርሻ መሬት በመመራት ነበር። በአፄ ኃ/ሥላሴ አገዛዝ ጊዜ ማንኛውም አርሳለሁኝ የሚል ኢትዮጵያዊ ግማሽ ጋሻ የመንግሥት መሬት መመራት ይችል ነበር። የመንግሥት ሰራተኛ ከሆነ ደግሞ ሙሉ ጋሻ መሬት መመራት ይችል ነበር። የመንግሥት መሬት ማለት በመንግሥት ቁጥጥር ስር ያለና በግለሰብ እጅ ያልገባ መሬት ማለት ነው። ነገር ግን ይህንን ሕጋዊ መንገድ በመጠለል ብዙ እራሳቸው አራሽ ያልሆኑ ግለሰቦች ተጠቃሚ ሆነዋል። በብዙ የኢትዮጵያ ክልልሎች ውስጥ እርቆ የሚኖረው ገበሬም፤ በቋንቋም ሆነ በመገናኛ እጥረቶች ምክንያት ሰለመሬት ግብርና አዋጅ ጠንቅቆ ሰለማያወቅ ለመሬት ንጥቂያው በሰፊው ተጋልጧል። አዲስ መጪው ሰው መሬቱ ግብር እንዳልተከፈለበት ካረጋገጠ በኋላ በቀያሽ አስለክቶ ለመሬቱ ግብር በመክፈል፤ በመንግሥት አዋጁ መሰረት ይህን ግማሽ ወይንም ሙሉ ጋሻ መሬት ሕጋዊ ያደርጋል ማለት ነው። በዚህም እረገድ አማራውም ትግሬውም (በትንሹ የሌሎች ብሄረሰብ ተወላጆችም) ተጠቃሚዎች ሆነዋል።
5ኛ የግል መሬት። ይህ መሬት ለገዢው መደብ እንደሹመቱና እንደቅርበቱ ከመንግሥት የተሰጠ መሬት ነው። አገር አቅንተዋል የተባሉትንና፤ ለሐገር ነፃነት ጦር ግንባር የዘመቱትን ይጨምራል። ከዚህም ጨምሮ በገዢው መደብ መሪዎች በዝርፊያ መልክ በአስተዳዳሪነት ሹመት (አገረ ገዢዎች) በየጠቅላይ ግዛቱ የተላኩ የአፄ ኃ/ሥላሴ መሳፍንቶችና ባላባቶች በራሳቸውና በጭፍሮቻቸው ሥም ያጠቃለሉት በሺህ የሚቆጠር ጋሻ መሬት ነው። ለምሳሌ በጨርጨር አካባቢ በአንድ ባለስልጣን ብቻ ከ 900,000 ሄክታር በላይ ተይዞ ነበር (SILESHI WOLDETSADIK, Land Ownership In Hararge Province Imperial Ethiopian College of Agricultural and Mechanical Arts Experiment Station Bulletin No. 47, 1966). ከዚህ ከተያዘው መሬት ውስጥም በመንግሥት ለቀረጥ የተመዘገበው 1.1% ወይንም 9,900 ሄክታር ብቻ ነበር። በጣም ብዙ መሬት እንደያዙ በስፋት የሚነገርላቸው ራስ መስፍን ስለሺ ነበሩ. እነዚህን የመሳሰሉ ትልቅ ባለሃብቶች፤ በትራክተር ማረስ ሲጀምሩ ደግሞ መሬቱ ላይ ሰፍሮ የነበረውን ጭሰኛ እያባረሩ መጡ። በአካባቢው ያለውን የገበሬ መሬትም በገንዘብ ሃይል እየገዙ ሰበሰቡ።
6ኛ መንግሥት ለቤተክርስትያኖች ለመተዳደሪያ የሰጠው መሬት
7ኛ መንግሥት በሰፈራ የሰጠው መሬት። ይህ መሬት በፊት ሰፋሪ ያልነበረበት የመንግሥት መሬት ነው። ይህ ገበሬዎችን ከተጨናነቀ ቦታ በማስነሳት ወደ ሌላ የመንግሥት መሬት የማስፈር ፕሮግራም የተጀመረው 1958 ዓ.ም ጀምሮ ነው። ከ1974 አብዮት በኋላ ደርግ ከ600,000 የሚበልጡ ሰዎችን በተለያዩ ቦታዎች አስፍሮ ነበር። በ1985 ዓ.ም ባወጣውም የመደርተኛነት (Villagization) ፕሮግራም፤ እስከ 1986 ዓ.ም 4.6ሚ የሚሆኑ ሰዎች፤ በ4500 መንደሮች፤ በሸዋ፣ በአርሲና በሐረርጌ አስፍሯል። በዚህ ፕሮግራም በመቀጠልም ፤ 1989 ዓ.ም ከማለቁ በፊት እስከ 13ሚ ሕዝቦች በመንደርተኝነት አስፍሯል(Thomas P. Ofcansky and LaVerle Berry, editors Library of Congress Federal Research Division (1991)።
የመሬት ይዞታ ተጠቃሚዎች ገዢው መደብና ከገዢው መደብ ጋር የተሳሰሩት ናቸው። እነዚህም መውሳፍንቶች፤ አገረገዢዎች፤ ባላባቶች ሹሞችና ወታደሮች ናቸው። አማሮችን፤ ትግሬዎችንና ኦሮሞዎችን በብዛት ያካትታል።
የሆነ ሆኖ፤ ከመሬት ላራሹ ጥያቄ ጋር ተያይዞ፤ የአማራው ሥም ብቻ ተገንጥሎ የሚነሳበት ምክንያት፦
1ኛ የትግሬውም ሆነ ከሌላ ብሄር የመጣው ባለመሬት ሥም ከአማራ ሥም ጋር ስለሚመሳሰል።
2ኛ ትግሬውም ሆነ ከሌላ ብሄር የመጣው ባለመሬት የአማርኛ ቋንቋን በየሄዱበት (በየሰፈሩበት) ስለሚናገሩ፤ በአካባቢው ነውሪ እንደ አማራ ስለሚቆጠሩ ነው።
በብዙ የሚቆጠሩ የትግራይና (ኤርትራንም ጨምሮ) የኦሮሞ ተወላጆች መሬትና ጭሰኞች ነበራቸው። በወረዳና አውራጃ አስተዳድሪነትም የስርዓቱ አካል በመሆን የመሬት ንጥቂያ ተጠቃሚዎች ሆነዋል።
በመጀምሪያ ደረጃ ግን በመሬት አስተዳደር ችግር ወይም “በመሬት ላራሹ ጥያቄ” በጣም የተኮነነው የአማራው ብሔር ብቻ ነበር።ተራው አማራ፣ ግማሽና አንድ ጋሻ መሬት ተመርቶ ከራሱ ብሔር ውጭ በሌላ ክልል የሚኖረው፣ ምን ያህል መሬት ይዞ እንደነበረ የወጣ ቆጠራ (ስታትስቲክስ) የለም።
እንግዲህ ለምን አማራ ብቻ እንደጠላት እንደሚታይ አይታወቅም። ይህንን የመሬት ላራሹ ጥያቄ ከግብ ለማድረስ ትግሉን በቀደምትነት ከጀመሩት የኢትዮጵያ ታጋዮች አንጋፋዎቹ የአማራ ወጣቶች ለመሆናቸው አያጠያይቅም። በአ/አበባ፣ በጎንደር፣ በደ/ማርቆስ፣ በባህርዳር፤ በደሴና በመሳሰሉት አደባባዮች የወደቁት የኢትዮጵያ/የአማራ አርበኞች ቁጥር ስፍር አልነበራቸውም። ታሪክም አይከዳውም።
መሬት ላራሹ ከታወጀበት ከ1975 ዓ.ም ጀምሮ በሌላው ክልል ይኖር የነበረው የአማራ ሕዝብ፣ (በተለይም በገጠሩ) ሙሉ በሙሉ ለመፈናቀሉ ጥርጥር የለውም። የተፈናቀለው የአማራ ገበሬ በኢትዮጵያዊነቱ በሕግ የተመራውንና (ማለትም በፊት ገበሬ ያልሰፈረበት ቦታ የተመራውን) መንግሥት ከሌላ ቦታ አምጥቶ በመንግሥት ባዶ መሬት ላይ ያሰፈረውን አማራ ይጨምራል። የወያኔ ሕገ መንግስት ነሐሴ 15 ቀን 1987 (21 August 1995) ከፀደቀ በኋላ ከሚኖሩበት ኅገር የተፈናቀሉትና የተጨፈጨፉት አማራዎች ቁጥር በትንሹ ከሚሊዮን ይበልጣል።
አዲስ አበባ ነሐሴ 15 ቀን 1987 (21 August 1995) በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ የወጣው ወያኔ ያፀደቀው ሕገመንግሥት እንዲህ ይላል።
“አንቀጽ 32 – የመዘዋወር መብት
1. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ ሀገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ዜጋ በመረጠው የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከሀገር የመውጣት ነፃነት አለው።”
“አንቀጽ 40 – የንብረት ደንብ
4. የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች መሬት በነፃ የማግኝትና ከመሬታቸው ያለመነቀል መብታቸው የተከበረ ነው። አፈፃፀሙን በተመለከተ ዝርዝር ሕግ ይወጣል።”
“አንቀጽ 9 – የሕገመንግሥት የበላይነት
2. ማንኛውም ዜጋ፤ የመንሥት አካላት፤ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ሌሎች ማህበራት እንዲሁም ባለሥልጣኖቻቸው፤ ሕገ መንግሥቱን የማክበርና ለሕገ መንግሥቱ ተገዢ የመሆን ኃላፊነት አለባቸው።”
እንግዲህ በሌላ የብሔር ክልል (ኢትዮጵያ) ውስጥ፤ በሕገ መንግሥቱ አዋጅ በአንቀጽ 32 ንዑስ 1፤ የመዘዋወርና የመኖር መብቱ የተረጋገጠለት አማራ ሲባረር…
በሕገ መንግሥቱ አዋጅ በአንቀጽ 40 ንዑስ 4፤ የንብረት ደንብ መሰረት፤ ከመንግሥት ካገኘው መሬት አማራ ብቻ የሆነው ሲፈናቀል…
የመንግሥትም አካላትም ሆነ ወይንም ወንጀለኞቹ፤ ሕገ መንግስቱን ተፃራሪ በመሆን የአማራን ሕዝብ ከሚኖርበት ቤቱ በማባረራቸውና በማፈናቀላቸው፤ በሕገ መንግሥቱ አዋጅ አንቀጽ 9 ንዑስ 2 መሰረት ሃላፊነት አለባቸው።
መሬት ላራሹ ከታወጀስ በኋላ በሌላው ክልል ውስጥ (አሁን በከተማዎች ውስጥ ማለት ነው) ስንት አማራዎች ይኖራሉ? እርሻ ውስጥ አሁን እንደሌሉበት የታወቀ ነው (ካሉም ቁጥር ውስጥ የማይገቡ ናቸው)። የሚተዳደሩትስ በምን ዘርፍ ነው? በንግድና በመንግሥት ሥራ ተሰማርተው መሆን አለበት። ኢትዮጵያዊነት እንደከሰል እየከሰመ በመጣበት (የወያኔ መንግሥት)፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በሌላ ክልሎች ውስጥ አማራ ሆኖ የመንግሥት ሥራ ማግኘት ለዘበት ይመስላል። ስለዚህ በብዛት በሌላ የኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የሚኖሩት አማሮች፤ አያትና ቅድም አይቶቻቸው ተወልደው ባደጉበት ክልል እንደሌላ ዜጋ ወደ ዳር ተገለው በየከተማው ሥር ተሸጉጠው ተቀምጠዋል።
ታድያ መሬት ላራሹ ከታወጀ ከ40 ዓመት በላይ ሆኗል። አሁንም ቢሆን እነዚህ እንደ ባዕድ ተቆጥረው መብታቸው የተገፈፈው ኢትዮጵያኖች በአማራ ሥም ግፍ እየተሰራባቸው ነው። ለዚሁም ተጠያቂው ዘረኛው የወያኔ መንግሥት ነው። በብሔር እልቂትና (genocide) አገርን በማጥፋት ወንጀል ተጠያቂ ነው። ይህ እልቂት አሁንም በቅርብ በቤንሻንጉል ክልል ውስጥ አገርሽቶበት ብዙ ሰዎች አልቀዋል።
የብሔሮች ጥያቄ፤ አማሮችን በተመለከተ
በተመሳሳይ ሁኔታ ሌላ የተነሳው የተማሪዎች ጥያቄ ደግሞ “የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ” ነበር። የዚያን ጊዜ፤ ይህን ጥያቄ ለመፍታት በጋራ ቀደምትነት የቆመው ተማሪ ዘረኛነትን የማያወቅ፤ ለቅንና ለእኩልነት የቆመ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙት ብሔር ብሔረሰቦች ነፃነት ሕይወቱን ለመሰዋት የተዘጋጀ ነበረ።
እንደሚታወቀው ሁሉ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ፤ የብሔርን ጥያቄ በፅሁፍ አቅርቦ በቀ. ኃ/ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ወስጥ ያነበበና በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች መፅሔት ላይ በ1969 ያሳተመው ዋለልኝ መኮንን ነበር። ብዙዎቹ ተማሪዎች ከአማራ ከትግሬና (ኤርትራውያንን ጨምሮ) ከኦሮሞ አካባቢ የመጡ ነበሩ። ከነዚህ ለሰፊው ሕዝብ ሕይወታቸውን ለማሳለፍ ከአብዮቱ ግንባር ከተሰለፉት ተማሪዎች መካከል ቤተሰቦቻቸው በገዢው መደብ ውስጥ ትላልቅ ስልጣን ያላቸውም ነበሩ። እንግዲህ እነዚህ የኦሮምያ፤ የአማራ፤ የትግራይ፤ ወዘተ ተማሪዎች ነበሩ በግንባር ቀደምትነት የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦችን ከጭቆና ቀንበር ለማላቀቅ፤ ለሰብአዊ መብቶች፤ ለብሔር ብሔረሰቦች እኩልነትና ነፃነት ደመ ከልብ ሆነው የቀሩት። ዘር ያልነበራቸው፤ ለዘር እኩልነት የቆሙ፤ በየአደባባዩ ለሰፊው ሕዝብ መስዋዕትነት የከፈሉ።
ይህንን ለመጥቀስ የፈለኩት ባሁኑ ግዜ በአንዳንድ አካባቢ፤ የዘር መርዘኛ ፕሮፓጋንዳ እየረጩ፤ ገና ዛሬ ከዕንቅልፋቸው ብንን ብለው ስለ ብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ “ሊቆች” ሆነው (ይህን ሁሉ ችግር የፈጠረው አማራው እንደሆነ በማስመሰል) ጠበብተኝነትን ሲያራምዱ ስላየሁ ነው። እነዚያ በዩኒቨርስቲውና በየከፍተኛው ት/ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ የበቀሉት፤ ዘር ያልነበራቸው፤ የኢትዮጵያ ተማሪ አርበኞች ስም ሲጎድፍ ሳይ ደሜ ይፈላል። ከነዚህ “ልብ ወለድ የፖለቲካ ደራሲዎች” ውስጥ አንዳንዶቹ ደግሞ የአርበኛውን የኢትዮጵያ ተማሪ ታሪክ እንኳን ያላነበቡ፤ የፖለቲካ ጥልቀት የሌላቸው፤ ለራሳቸውም ይሁን ለሀገራቸው ክብር ብለው እውነተኛ ትግልን ያልቀመሱ “የብዕር ነብሮችና የዘረኞች ደወል” ብቻ ናቸው።
አንድ አማራ፤ አንድ ኦሮሞ ወይንም አንድ ትግሬ የዛሬ ሀምሳ ዓመት ሰደበኝ ወይንም አንቋሸሸኝ ብሎ አንድ ብሔረሰብን በጠቅላላ መወንጀል ትልቅ ሥህተት ነው። በየብሔረሰቡ ስንት መረን የወጣ ባለጌ ሰው አለ? በኢትዮጵያ ውስጥ ከባለሞያዎች እኩል የተሰደበ ሰው ነበር እንዴ? በየብሔረሰቡ ሸክላ ሰሪው “ፉጋ”፤ ብረት ሰሪው “ቀጥቃጭ”፤ እንጨት ሰሪው “አናጢ” እየተባለ ይሰደብ አልነበረም? ይሄ ለምን መጣ? ከትምህርት ማነስ ነው። ስንቱ ነው ኢዚህ ሰሜን አሜሪካን እንኳን መጥቶ አፍሪካ አሜሪካዎችን “እነዚህ ጥቁሮች” የሚለው (ይህን ከፍተኛ ትምህርት ያለው ሰው ሲናገር ሰምቻለሁ) አንዳንዱ ደግሞ “እነዚህ ባሪያዎች” ይላል። አዳንድ ጊዜ ከቀለም ትምህርት ደግሞ ኮመንሴንስ ያለው ሰው ይሻላል። አንዳንዱ ሲናገር ጭቃ ነው። እንደዚህ አይነቱን ጭቃ ከየአህጉሩ ለቅሞ ማውጣት አይቻልም። ዘወትር የሚወልዳቸው ቤት አይጠፋምና።
ስለዚህ፤ እኛ ከተማርን፡ ሕዝባችንን ካስተማርን (መጥፎ መጥፎውን ሳይሆን ጥሩ ጥሩውን ነገር) በፊት የነበረው መጥፎ ቋንቋ በጥሩ ቋንቋ ይቀየራል። ዛሬ አንድ ዘረኛ “ኒገር” ብሎ ቢሰድበኝ፤ አለቃዬ ደግሞ በቀለሜ የተነሳ ተፅዕኖ ቢያደርግብኝ፤ መብቴን ለማስከበር በህግ እጠይቀዋለሁኝ እንጂ የነጭን ዘር በጠቅላላ አልኮንንም። በጭፍንና በደምፍላት መራመድ አደገኛ ነው።
ስለዚህ ሐገራችን ውስጥም ይሄንንው የሕዝብ ህልውና የሚያስከብር የሕግ የበላይነት ያስፈልጋል። የሕግ የበላይነት እንዲነግስ በትብብር ከሰራን፤ መከባበር፤ መፈቃቀር፤ መረዳዳትና አንድነት ሳይወዱ በግድ ይዛመዱናል። የዘረኝነት ሰንሰለት ይሰበራል።ሰሞኑን በአዲስ ድምፅ ራዲዮ ዶ/ር አረጋዊ “ላለፈው ቤት ክረምት አይሰራለትም” ብለዋል። ያለፈውን፤ ጊዜ የጣለውን ስርዕት እያነሳን ወርቃማ ጊዜያችንን በከንቱ ከማጥፋት፤ እስቲ መጀመሪያ የየራሳችንን አቋም በደምብ ገምግመን ትልቋን ኢትዮጵያ ለመገንባት አብረን እንነሳ። ትብብራችንን ዛሬ እንጀምር። ማንኛውም ቅራኔ በንግግርና በመደማመጥ ይፈታል።
የገዢው መደብች ከብሔር ጋር ያላቸው አሰላለፍ ምን የመስላል?
የባላባቱ የገዢ መደብ
ኢትጵያን በዚያ ወቅት የሚያስተዳድረው የገዢ መደብ፤ በብዛት የተውጣጣው ከኦሮሞ፤ ከአማራና ከትግሬ ብሔረሰቦች ነበር። የዚህ የገዢ መደብ ያገዛዝ ስርዓት ባላባታዊ (ፊውዳላዊ) ነበር። ይህ ባላባቲዊ አገዛዝ፤ ለብዙ ዓመታት የሁሉም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ብሔረሰቦች የአገዛዝ ስርዓት ሆኖ ቆይቷል። ወላሞ በወላሞ ባላባቶች፤ ከፋ በከፋ ባላባቶች፤ ኦሮሞ በኦሮሞ ባላባቶች፤ ከምባታ በከምባታ ባላባቶች፤ አማራ በአማራ ባላባቶች፤ ትግሬም በትግሬ ባላባቶች ተገዝተዋል። ወ.ዘ.ተ።
በባላባታዊ አገዛዝ ሥር የሁሉም ብሔረሰብ ጎሳዎች ተገዢዎች ነበሩ። በዚህ አገዛዝ መሰረት፤ አነስተኛ ሕዝብና ግዛት ያላቸው ባላባቶች፤ መብታቸውንና ጥቅማቸውን ለማስከበር ሲሉ ለትላልቆቹ ባላባቶች ይገብራሉ (በገቢያቸው መጠን እንደቀረጥ ማለት ነው)። ትላልቆቹ ባላባቶች በተራቸው ደግሞ፤ ግዛታቸውን ለማስስፋፋትና ሃይላቸውን ለማጠናከር በጊዜው ላሉ ሃይለኛና ገናና ባላባት ይገብራሉ። ጊዜ ሲሳካላቸው ደግሞ እነሱም ያስገብራሉ።
በየብሔሩ ወስጥ ያለው ባላባትዊ ሽኩቻ በዚህ መልከ ገፅታው እንደ አይነት ባህሪ የነበረው ነበር። አንድ ብሔር ሌላውን ብሄር ሊያንበረክክ የቻለውም በሃይል ነበር። አማራውም፤ ኦሮሞውም፤ ክርስትያኑም፤ እስላሙም ይህንን የመሰለ ባህርይ አሳይቷል።
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አንድ ብሔረ ወጥ የሆነ የባላባት (የመሳፍንት) ሥርዓት ኢትዮጵያን መርቶ አያውቅም፤ ከሌላ በመቀላቀል እንጂ። አፄ ተዎድሮስ እንኳን ቢሆኑ፡ ምንም እንኳን የመሳፍንት ዘር ባይኖራቸውም (አላቸው የሚል ሰው ቢኖርም)፤ ጎንደርን፤ ትግሬን፤ ውሎንና ሸዋን በማስገበር ነው ኢትዮጵያን አንድነት ጠቅልልለው ለመግዛት የቻሉት።
በዚያን ወቅት ኢትዮጵያን ለመግዛት “ሃይልና ሃይማኖት” ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ይህንን ሃይል ለማግኘት ባላባቱ በጥቅም የመደጋገፍንና በጋብቻ የመተሳሰርን ዘዴዎች ለብዙ ዓመታት ተጫውቷል። ለዚህም የአፄ በዕደ ማርያም ሚስት የነበረችውን ንግሥት ዕሌኒንና (1450-1500) በየጁ መሳፍንቶች ግዜም (1670-1845; በነራስ ዐሊ፣ ራስ አሊጋዝ፣ ራስ ጉግሳ፤ ወዘተ) በጣም ጎልቶ የታየውን በጋብቻ የተገመደ ሀይል መጥቀስ ይረዳል። ንግሥት ዕሌኒ፤ ገራድ መሐመድ የተባለው የደዋሮ ገዢ ልጅ ነበረች። አፄ በዕደ ማርያም በ1470 ዓ.ም ሲሞቱ ልጆቻቸው (አፄ እስክንድር፤ ያዕቆብና ልብነ ድንግል) ለአቅመ አዳም ስላልደረሱ ንግሥት ዕሌኒ እስዋ እራሷ እንደራሴ በመሆን ለብዙ ዓመታት እንደንግሥት ገዝታለች። በዙርያው ካሉ የስላም ገዥዎች ጋር የቤተሰብ ግንኙነት ስለነበራት ሁለቱንም ክፍሎች በማስማማትና በማስተባበር ጠቅማለች።
ስለዚህ የገዢው መደብ (የባላባታዊ የአገዛዝ ስርዕት) ከራሱ ብሔርና ሀይማኖት ውጭ ይቅርና፤ በራሱ ብሔርና ሀይማኖት ውስጥ ካሉትም ባላባቶችና መሳፍንቶች ጋር፤ ጥቅሙን ለማስከበር በጋብቻ ተሳስሯል። ሰፊውን ሕዝብ ለብዙ አመታት በጭቆና የገዛው በየራሱ ብሔር ውስጥ ያለው ባላባት እንጂ ከሌላ ብሔር የመጣ ባላባት አይደለም። በጦርነት ቢሸነፍም ተሸናፊው ባላባት (በዚያው ክልል ያለው) ለአሸናፊው (ከሌላ ክልል ወይንም ከዚያው ክልል ለመጣው) ይገብር እንጂ ተራው ሕዝብ ግን ሁልጊዜ የሚገብረው ጊዜ ለሾመው ባላባት ነበር።
የደርግ የገዢ መደብ
በደርግም ጊዜ፣ የገዢው መደብ አማራ ነው እየተባለ (የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች የፕሮፖጋንዳ ጨወታ ሆኖ ቆይቷል) ይወራ ነበር። እውነተኛው ሀቅ ግን ደርግ ዘር አልነበረውም። ቢኖረውም እንኳን አገሪቱን ይመሩ ከነበሩት ሃይሎች ውስጥ 60% የሚያክሉት የኦሮምያ ተወላጆች ነበሩ ይባላል (አንዳንዶቹ በእናት ወይ በአባት፣ እንደ ኮሎኔል መንግስቱ)። ይህ እንግዲህ በቁጥር ጥናት መረጃ (እስታትስቲክስ) የተረጋገጠ አይደለም ።
የሆነ ሆኖ፤ ቀደም ብሎ እንደተገለፀው፤ መሬት ተወርሷል። በሌላው የኢትዮጵያ ክልል የሚኖረው አማራ ተፈናቅሏል። ግማሹሁም ተቃጥሏል። ሌላውም ከየገደሉ ተወርውሮ ተሰባብሯል። በራሱም ሆነ በሌላ ክልሉ ውስጥ የሚኖረውም አማራ፡ የአብዮቱን መፈክር በልጆቹ ክንድ አስይዞ፤ የትግሉ ግንባር ቀደም በመሆን መስዋእት ከመክፈል በስተቀር ያገኘው ፋይዳ የለም። ታድያ የአማራ ሥም ከደርግ የገዢ መደብ ጋር ምን አገናኘው?
ኢሕአፓና መኢሶን ከአማራ የገዢ መደብ ጋር ነው እንዴ የታገሉት? መኢሶን (በኃይሌ ፊዳ መሪነት) ያጠናከረውና የገነባው የደርግን እንጂ የአማራ የገዢ መደብን ነበር? አሁንም ይሄው መከረኛው የአማራ ሥም፣ በልብ ወለድ ፖለቲከኞች፣ ከአፈር ጋር እንደታሸ ነው። ስለዚህ የገዢው መደብ ከዚህ ብሔር ነው የመጣው ለማለት አይቻልም። ደርግ የተለየ እንክብካቤና ጥቅም ለአንድ ብሔር ብቻ ሲሰጥ አልታየምና። የአማራ ብሔር፤ እንደሌሎቹ የኢትዮጵያ ብሔሮች (እንዲያውም ከሌሎቹ በላይ) የተጨቆነ ነበር።
የወያኔ የገዢ መደብ
የወያኔ የገዢ መደብ ደግሞ ከሁሉም በግልፅ የተለየ ነው። የገዢው ቡድን መቶ ፕርሰንት ከትግራይ ብሔር ነው። በፓርላማ ውስጥ፤ ከዚህ የገዢ ቡድን ጎን የተቀመጡት የሌላ ብሔር ተወካዮች የገዢውን ቡድን በዓለም ዓቀፍ ሕብረተሰብ ፊት ኅጋዊ ለማስመሰል ብቻ የተቀመጡ ተዋናዮች ናቸው። ጠቅላላው የሀገሪቱ መመሪያዎችና ደንቦች ይህንን የገዢ መደብ በስልጣን ኮርቻ ላይ ለማቆየት የተነደፉ ናቸው። ከነዚህም በዋነኝነት የሚቀመጠው መመሪያ “ብሔር ብሔረሰቦችን በዘር ከፋፍሎ፤ እርስ በርስ እያናከሱ” የመግዛት ፖሊሲ ነው።
በገዢው የወያኔ መደብ ውስጥ ሥርዐቱን ተቆጣጥሮ ዓላማውን ለማራመድ የተሰማራው (የተቀጠረው ወይም በጥቅም ላይ ያለው) ሕዝብ ምን ያህል ነው? 10 ሺህ? 50 ሺህ? ወይም 100 ሺህ? (ይሄ ማለት እንግዲህ ከ6.1ሚ የትግራይ ሕዝቦች ውስጥ 0.16%፣ 0.41% ወይም 1.64% ማለት ነው)። እንግዲህ ወያኔ የአምባገነን ክንዱን በቀረው 99ሚ ሕዝብ ላይ ጭኖ በአፈሙዝ የሚመራው ከ1% ባነሱት የትግራይ ተወላጅ ወበዴዎችና ቅጥረኞች እንጂ በመላ የትግራይ ሕዝብ ድጋፍ አይደለም። ይህ በደንብ መታወቅ አለበት። አራት ነጥብ።
የገዢው መደብ በትግሬ ጠበብተኝነት (ዘረኛ) የሚመራ አምባገነናዊ መንግሥት ነው። ስለዚህ ሰፊው የትግራይ፣ የአማራም፣ የኦሮምያ፣ የሱማሌም፤ ወዘተ ሕዝብ ለመቶ ዓመታት እንደተጨቆነው ሁሉ፤ አሁንም የገዢው መደብ ጭዳ ሆኖ ቀርቷል። ለዚህ ነው ወያኔ የትግራይን ሕዝብ በጭራሽ አይወክልም የምለው።
የገዢው መደብ ወያኔ ግን በለመደው የዘረኝነት አንደበቱ የትግራይን ሕዝብ ከጎኑ ለማሰለፍ “እኔ ከወረድኩኝ አለቀልህ”፤ “ለዘለዓለም ተበዳይ ሆነህ ትቀራለህ”፤ “ይሄ የትግራይ ሕዝብ ፓርቲ ነው”፤ “በሜዳ ያመጣንውን ድል ከማንም አንጋራም፤ የትግራይ ሕዝብ ድል ነው” እያለ መሸንገሉን አላቆመም። ለትግራይ ሕዝብ ግን የወያኔ መንግሥት “ታላቅ የታሪክ ጠባሳ” ነው። በትግራይ ሕዝብ ሥም የሚነግድ፤ የትግራይ ሕዝብን ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር የሚያቃቅር፤ ኢትዮጵያ የምትባለውን ሀገር ለመገነጣጠል የጥላቻ መርዝ እየበጠበጠና እያሻማ የሚገኝ አደገኛ የገንዘብ ቅጥር ነፍሰ ገዳይ ነው።
ወያኔ ዘርን በዘር ላይ ለማስነሳት ያጧጧፈው ፕሮፓጋዳና የወለዳቸው ውጤቶች
በአማራ ላይ ጥላቻ መጀመሪያ የቀሰቀሰው ጣልያን ነው። “ከፋፍለህ ግዛው” የሚለውን የቅኝ ግዛት መርሆውን እውን ለማድረግ ከሰማይ ላይ ወረቀት እያበተነ “አማራ ጠላትህ ነው። አትተባበረው። አባርረው። ግደለው” እያለ በየከተማውና በየባላገሩ ይበትን ነበር። የተባበረውን ሁሉ ሾሟል። ከተሾሙት ውስጥም “ባንዳው” የመለስ ዜናዊ አባት ይገኙበታል።
ወያኔ በአማራ ላይ የተነጣጠረ የዘር ጥላቻ ፕሮፓጋንዳውን የጀመረው ገና ሜዳ በነበረበት ወቅት “አማራ የትግራይ ሕዝብ ጠላት ነው” እያለ እንደነበር አቶ ገ/መድህን አርዓአያ በማያወለውል ማስረጃ ገልፀውታል (ኢሳት ቲቪ)። ይህ እንግዲህ ከጣልያን የተወሰደ ግልባጭ ፕሮፓጋንዳ ነው።
ይህ የዘር ጥላቻ ፕሮፓጋንዳ የሚሰበከው ለትግራይና ለኦሮምያ ሕዝብ ነው። ወያኔ የትግራይ ሐዝብ እንዲያቅፈው የኦሮሞ ሕዝብ ደግሞ እንዲደግፈው ይፈልጋል። በትግራይ ሕዝብ ድጋፍ ብቻ ኢትዮጵያን ለመግዛት አይችልምና።
ኦሮሞና አማራ ትላልቅ ብሄሮች ናቸው። እነሱ በአንድነት ከቆሙ፤ ወያኔ አለቀለት ማለት ነው። የወያኔ መረዎች የኦሮምያ መሪዎችን በቀላሉ ሸንግለው አንጃ እንደሚፈጥሩ እርግጠኞች ነበሩ፤ የታወቀ ንቀት ስለነበራቸው። ስለዚህ አንጃ ፈጥረው ኦሮሞና አማራን ደም ማቃባቱ ትልቁ የወያኔ እስትራቴጂ ነው።
ለዚህ ነው ወያኔ እሱ እራሱ በአዋጅ ያወጣው ሕገ መንግሥት ባላንጣ ሆኖ፤ የአማራው ሕዝብ ሲባረር፤ ሲፈናቀል፤ ገደል ውስጥ ሲወረወር፤ ሲቃጠልና ሲጨፈጭፍ አይኑን ጨፍኖ፤ ጆሮውን ደፍኖ ቁጭ ያለው።
አቶ ጅዋር መሃመድ ደግሞ (ከእንጀራ አባቱ ከሊቀ መኳስ መለስ ዜናዊ የተማረውን ቲወሪ እንዳለች ገልብጦ) “መጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ፤ ኢትዮጵያን በሰከንደሪ ደረጃ ነው የማያት” ይለናል። “ኢትዮጵያን ከመቀበሌ በፊት የኦሮሞን አቅምና ጡንቻ መጨመር ያስፈልጋል” እያለ ይፎክራል። ጡንቻው ማንን ለምስፈራራት እንደሆነ የሚያውቀው እሱ ብቻ ነው። ይህ አባባል ግልፅ የሆነ፤ ዘርን ከዘር ለማጋጨት የተጠነሰሰ “የዘረኝነት ፕሮፓጋንዳና ሴራ” ነው።
አቶ ጅዋር መሃመድ በሲ.ቢ.ኤስ ተጠይቆ ከሰጣቸው መልሶች መካከል አንዱ እንዲህ ይላል። “በመቶ የሚቆጠሩ የኦሮሞ ወጣቶች በየቀኑ በሊቢያ በኩል አውሮፓ እየገቡ ነው። እነሱን እየተቀበልን በፍጥነት ተደራጅተው ወደ ትምህርትና ወደ ሥራ መስክ እንዲገቡ ጥረት እያደረግን ነው”። ሌሎቹንስ የኢትዮጵያ ወጣቶች ማነው የሚረዳቸው? አማራውም፤ ትግሬውም፤ ሲዳማውም፤ ሀድያውም፤ ወላሞውም የየራሱን ብሔር ከፈለገ ይርዳ ማለት ነው? እነዚህ የኢትዮጵያ ልጆች በአውሮፓም ሆን በአሜሪካ የሚታወቁት በብሔር ስማቸው ነው ወይስ በኢትዮጵያዊነታቸው ነው? ሐገርህ ማነው አቶ ጅዋር? ከዚህ የበለጠ ጎስኝነትና ብሔረሰብኝት አለ? ይህ አስተሳሰብ ብቻ አቶ ጅዋር መሐመድን እንደኢትዮጵያ ጠላት ሊያስቆጥረው ይገባል።
“ኢትዮጵያ የምትባለውን ሐገር እኛ ላይ እንደጫና ነው ያስቀመጡብን። የራሳችንን የብሔር መታወቂያና (አይዴንቲቲ) ቋንቋ እንድናወግዝ (ዴናውንስ እንድናደርግ) እንገደዳለን። ካላወገዝን ደግሞ እንታሰራለን” ይላል። “ይሄ ባባቴም ባያቴም ጊዜ ተደርጓል” ይላል። አቶ ጅዋር! በአያትህ ጊዜ ባልኖር፤ በአባትህ ግዜ አንተ ያልደረስክበትን (ያላየህውን) ብዙ የኦሮሞ ክልልሎች ተዘዋውሬ አይቻለሁኝ። ኦሮሞ በመሆኑ ብቻ፤ የኦሮሞ ቋንቋ በመናገሩ ብቻ! ይታሰራል የምትለውን ግርድፍ ውሸት ከየት እንዳመጣህውም አላውቅ። በዚያን ጊዜ እኮ ስንት በሥማቸውና በብሔራቸው የኮሩ የኦሮሞ ጄኔራሎች፤ ሚኒስቴሮች፤ መሳፍንቶችና ባላባቶች ነበሩ። ይሄ እኮ የኦሮሞን ሕዝብ መሳደብ ነው። እንደዚህ እየተሳደብክ እንዴት ያሁኑን ሃላፊነት ሰጡህ? ከየት ጉድጓድ ወስጥ ነው ብቅ ያልከው አቶ ጅዋር? የየትኛው የአረብ ሐገር ቅጥረኛ ነህ? ማነው ደሞዝህን እየከፈለ፤ አልጃዚራ ላይ መድረክ እየሰጠ (ካታር?) “ኢትዮጵያን ገነጣጥልልን” ያለህ? ወያኔም የዚህ ደመወዝ ከፋይ ይሆን?
ገና የስልጣን ኮርቻ ላይ ሳንቀመጥ፣ በጎሳ የተመሰረተ አደረጃጀትና አወቃቀር በውጭ አገር ሆነን ከጀመርን፣ ሃገር ቤት ሥልጣን ይዘን ብንገባ እንዴት ልንሆን ነው? “አሁን ደግሞ የኛ ተራ ነው። አርፈህ ተቀመጥ” ነው?
አቶ ጅዋር! አትሳሳት። በዘር የበላይነት የተመሰረተ አገዛዝ በኢትዮጵያ ውስጥ ከአሁን ወዲያ ጨርሶ ቦታ አይኖርም። ሰፊው ሕዝብ ሞኝ አይደለም። አንድ ጊዜ በጥፊ ተመቷል። ለሁለተኛ ጊዜ ግን አይመታም።
የባላገሩ ጥያቄና የብሔሮች አንድነት ውጤት
አበው ሲተርቱ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” ይላሉ። ትብብራችንና አንድነታችን፤ እድገታችንና ኩራታችን ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ጨዋ ነው። በባህሉና በልምዱ ተፋቅሮና ተጋግዞ መኖር እንደሚችል ያስመሰከረ ሕዝብ ነው።
እድሉን አንግኝቼ፣ ሌሎች የአፍሪካ ሃገሮች እንዳደረኩት፤ ወደ ብዙ የኢትዮጵያ ከተሞችና ገጠሮች ሄጃለሁኝ። የብዙ ቀን መንገድ በበቅሎ፣ በፈረስና በመኪና ተጉዣለሁኝ። ተራ ኢትዮጵያዊ ነኝ። የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ባህሎችና ሃይማኖቶች አጋጥመውኛል። ግን በየደረስኩበት ሁሉ ለእንግዳ የሚሰጠው ክብር ተለይቶኝ አያውቅም። ይሄ ነው እንግዲህ እኔ የማውቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጨዋነት።
የባላገሩና የከተሜው ጥያቄ
ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ አንገብጋቢ ጥያቄ ምንድነው? የከተሜው/የገበሬው ጥያቄ ምንድነው? እስቲ ከምትኖሩበት ቪላ ቤት ወይም አፓርትመንት ወደ በረንዳ ወጣ ብላችሁ በሚመች ወንበር ላይ ተመቻችታችሁ ተቀመጡ። ከዚያም ወደ ውድ አገራችሁ ኢትዮጵያ ውስጠ ኅሊናችሁን ልካችሁ ባንድ ክፍል ከተማ ቤት ወስጥ ከአራትና አምስት ልጆቻቸው ጋር የሚኖሩትን ወላጆች፤ በገጠር ደግሞ ወደ ባላገር ወረድ ብላችሁ ያችን ጭስ ያፈናትን ጎጆ ከታች ተመልከቷት።
እስቲ መጀመሪያ ኦሮምያ፤ ከምባታ፤ ወላይታ፤ ሱማሌ፤ አፋር፤ ትግሬ፤ ጉራጌ፤ አማራ ውስጥ ውዳለችዋ ትንሿ የኢትዮጵያ ጎጆ ቤት እናምራ።
ምን ይታያችኋል? ጭስ ያቀለመውን የሣር ኮፍያ ደፍታ፤ ለሺህ ዓመታት ጠብቃ ያቆየችውን የጭቃ ቤት ንድፍ ጥበብ ከርሻው በስተጥግ ሆና እያስመረቀች፤ የገበሬው ኩራትና ዞሮ መግቢያ ሆና ተቀምጣለች። ወደ ጓዳዋ ገባ ስትሉ ደግሞ፤ ባንድ በኩል የቤት እቃዎች፤ በሌላ በኩል ደግሞ የዕንግዳ መቀበያና የመኝታ ሥፍራ አቅፋ፤ መሃል የቆመውን ምሰሶ ተደግፋ ቆማለች።
ጤናይስጥልኝ የገበሬው ጎጆ። እስቲ ምን ትፈልጊያለሽ? ምን ጎደለሽ ብላችሁ ጠይቋት? ስለ እግዚአብሔር ብላችሁ፤ ምነው በርሽ ተጣመመ? የማገርሽ ምርጊት ምነው ተበላ? ለምን የሳር ኮፍያሽ በጭስ ቀለመ? ለምን ክፍልሽ እበት እበት ይሸታል ሪፍረሽነር እናምጣልሽ እንዴ? እስቶቩና ፍሪጁ የት ነው የተቀመጠው? ብላችሁ እንዳትጠይቋት። “አይ ልጆቼ ትናንትና ፈረንጅ ሀገር ብትሄዱ በአጭር ግዜ ውስጥ ያሳደገች እናታችሁን ኑሮ እረሳችሁ?” በማለት ልቧ እንዳይሰበር።
ለጠየቃችኋት ጥያቄዎች እንዲህ በማለት ትናገራለች። እናት ከልጆቿ አትደብቅምና።
1ኛ ከቀን እቀን ጦም ማደሩ ገደለኝ። አምናና ዘንድሮ ዝናም ጠፍቷል። እንዴት ልሁን? መሬቱም እንደድሮው ካለ ማዳበሪያ አያፈራም። እሱን ለመግዛት ደግሞ አቅም የለኝም።
2ኛ ከቅድም አያት ወደ አያት፤ ከአያት ወደ አባት፡ እያለ የሚዋራረሰው መሬት ቁራጭ እየሆነ መጥቷል። በዚህች ኩርማን በምታክል መሬት እንኳን ቤተሰብን ይዞ ለአንድ ለራስም መኖር አይቻልም። መቼ ነው ኢንደስትሪው ተስፋፍቶ ልጆቻችን ሰርተው መብላት የሚችሉት? ምንድነው የናንተ የልጆቻችን እቅድ? አለበለዚያማ ሀገሩ በሙሉ ለማኝ መሆኑ አይደል? ትላለች
3ኛ ልጆቼን የት ላስተምር? ት/ቤት ያለው ከቀን ጉዞ በኋላ ነው። እናንተ እንኳን በፈረንጅ ሀገር ልጆቻችሁን ባውቶሞቢል እያንቀባረራችሁ ታስተምሩ የለ? ምነው እኔን እናታችሁን እረሳችሁኝ?
4ኛ መብራቱን እንኳን ተውት የከተማውንም ሰምተናል። ሃኪም ቤት እኮ በአካባቢው ጨርሶ የለም፤ ሴቶቹ በምጥ ምክንያት እያለቁ ነው። ሃኪም በቅርብ ቢኖር ይድኑ ነበር። እንዴ አስክናልቅ ድረስ ነው እንዴ እናንተ የምትጠብቁት?
5ኛ አካባቢው ያለው ወንዝ በጣም እሩቅ ነው። ወንዙ ትንሽ ስለሆነ ውሃው ደግሞ ለመጠጥ አይሆንም። ሰው በወስፋትና በትል በሽታ እያለቀ ነው። እንዲያው የጉድጓድ ውሃ የምናገኘው መቼ ነው? እንዲያው የናንተን ቅዘን አጥበን አሳድገን በውሃ ጥም እስክንሞት ትጠብቃላችሁ?
እንዳያችሁት፤ አንገብጋቢው የጎጆዋ ጥያቄ ከመገንጠል ጋር አይያያዝም። ተገነጠለችም፤ አልተገነጠለችም “ይህ የሕልውና ጥያቄዋ ቀጠሮ አይሰጣትም” ነገ ተነገወዲያ ሳይባል መመለስ አለበት።
ከዚህ ከገጠር ጉብኝት በኋላ ደግሞ ወደከተማ ተመለስ። በየጎዳናውና በየመንደሩ ሰው እንደሰርዲን ታጭቋል። የመኪና መንገዱ በተሽከርካሪዎች ተጨናንቋል። ዋናውን መንገድ ለቀህ፤ ቀጭን የግር መንገዷን ተከትለህ ቁልቁል ስትወርድ፤ ከአንድ ትልቅ ቤት ጀርባ ተለጥፋ የተቀመጠች የአንድ ክፍል ቆርቆሮ ቤት ትደርሳለህ። አንኳኩተህ ግባ።
እንደገባህ በስተቀኝህ በኩል ሁለት አነስተኛ አልጋዎች በሰያፍ ተገጣጥመው ተንጋለዋል። ከፊታቸው አግዳሚ ወንበሮች ተኮልኩለዋል። በግራ በኩል ደግሞ ዳርና ዳሩ የሚታይ በመጋረጃ የተከለለ ተለቅ ያለ አልጋ ይታያል። ከአልጋው በስታግርጌ ግድግዳውን ተደግፎ ትልቅ የኮመዲኖ ሳጥን አንጋጦ ቆሟል።
ሰላምታ ከተለዋውጥክ በኋላ፡ “ምንድነው ችግርህ? ብሶትህ? ምን ቢደረግልህ መልካም ይመስልሃል ብለህ ትጠይቀዋለህ።
“አይ ወንድሜ እሱስ ምኑ ቅጡ” ብሎ ይጀምራል።
1ኛ ከቀን ወደ ቀን የልጆቻችንና የራሳችንን ሆድ እንኳን ለመሸፈን እየከበደን መጥቷል። የምግብ ዋጋ ቀን ከቀን ወደ ላይ እየናረ ነው። የዛሬ ዓመት በቀን ሶስቴ በሽሮውም፤ በጎመኑም አድርገን እንበላ ነበር። ስጋውንማ በአመት በዓል እንኳን ለመቅመስም አልቻልንም። በዚህ ዓመት ደግሞ ቁርሱንም አቁመናል። የሚመጣውን ዓመት እንግዲህ እግዜር ይወቅ።
2ኛ የቤቱም ኪራይ ከኑሮ ወድነት ጋር አብሮ እያደገ ሄዷል። ደሞዜ ከምግብና ከቤት ኪራይ አያልፍም። ለኮንዶምንየም ካመለከትን ዓመታት አልፈዋል። ዕጣው ግን ሊደርሰን አልቻለም። ቤቶቹ ለራሳቸው የወያኔ ዘመዶችና ካድሬዎች ነው የሚከፋፈለው። ለኛ እንግዲህ ከመቶ አንድ ይደርሰን ይሆናል። እጣውም እንኳን በአሁኑ ጊዜ ቢደርሰን እንዴት አድርገን የመጀመርያ ክፍያውን እንደምንከፍል አናውቅም።
3ኛ ሥራ የለም። ባለቤቴ በሂሳብ ሥራ የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ ናት። እንኳን በትምህርቷ የሚሆን ሥራ ይቅርና ማንኛውንም ሥራ ቢሆን እስካሁን አላገኘችም። ሥራ ለማግኘት ካድሬ መሆን ወይንም የመንግስት ዝምድናን ይጠይቃል። አሁንማ ሁሉም ሥራ ለማግኘት ብሎ ካድሬ ስለሆነ እሱም አልተገኘም። ለዚህ ነው ወጣቱ ተምሮም ሥራ በማጣቱ በነፍሱ ቆርጦ ሀገሩን ትቶ በገፍ ወደውጭ ሐገር የሚሰደደው።
4ኛ ልጆቼ ተራቁተዋል። በምን አቅሜ ላልብሳቸው? ጓደኞቻቸው ጥሩ ጥሩ ለብሰው ሲያዩ ይሳቀቃሉ። በስልጣን ዝርፊያና በሙስና ስለከበሩ፤ እንደዚያ የሚለብሱት የባለጊዜዎቹ የወያኔዎችና የካድሬዎቻቸው ልጆች ናቸው። እነሱ ለአንድ ምሳ የሚያጠፉት እኔ በወር ከማገኘው ደምወዝ በላይ ነው።
5ኛ ልጆቼ ቢታመሙ፤ እኔና ባለቤቴ ብንታመም ሞተን መቅረታችን ነው። መታከምያ እንኳን ገንዘብ በእጃችን የለም።
6ኛ የትራስፖርት ችግሩ ይሄ ነው ብዬ ለመንገር ቃላቶች ያጥሩኛል። ጧት ስሄድ ቀደም ብዬ ከቤት ብወጣም ከሰው ብዛት የተነሳ ከአንድ ሰዓት ያላንሰ ተሰልፌ ተራ መጠበቅ አለብኝ። ስመለስማ እንዲያውም ከጧቱ ይብሳል፤ እጥፍ ሰዓት ነው የሚወስድብኝ። ምን ብዬ ልንገርህ ወንድሜ! እያለቅን ነው። ዋና ዋናውን ነገርኩህ እንጂ መከራችን ብዙ ነው። እናንተም ትረዱናላችሁ፤ ለችግራችን መፍትሄ ይዛችሁ ትመጡ የሆናል ብለን ስንጠብቅ ዓመታት አለፉ። ተዳክመናል በቶሎ ካልደረሳችሁልን ማለቃችን ነው ብሎ ለተጠየቀው ጥያቄዎች መልስ የሰጣል።
እስኪ አሁን ይህን ሁሉ ከሰማህ/ሽ በኋል ከሰሜን አሜሪካ ወደ ኃገር ቤት የላከውን/ሺውን ውስጠ ኅሊና መለስ አድረገህ/ሽ እውን አለም ትገባለህ/ቢያልሽ ማለት ነው።
ታዲያ የህዝቡ አንገብጋቢ ጥያቄ ምንድነው?
የከተማዋም አንድ ክፍል የቆርቆሮ ቤት ሆነች የገጠሯ ጎጆ፤ መሰረታዊው ጥያቄያቸው “የሕልውና” ጥያቄ ነው። ይህ የሕልውና ጉዳይ ቀጠሮ የማይሰጥ አንገብጋቢ ጥያቄ ነው። የሚውል የሚያድር አይደለም።
የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝብ መገንጠል አይደለም አንገብጋቢ ጥያቄው። ይሄ እንደረቀቀ ቲወሪ “በልብ ወለድ ፖለቲከኞች” መፅሀፍ ወስጥ፤ ከነማርክስና ከነሌኒን ተግልብጦ በመጀመሪያ ገፅ ላይ የተፃፈ መፈክር ነው። የሌላ ሀገር ሰዎች ከራሳቸው የኢኮኖሚና የማህበራዊ ኑሮ አቋሞችና ስርዐአቶች ጋር በማያያዝ ያካሄዱትን አብዮት በካርቦን ከመገልበጥ፤ የራሳችን የምንለው፤ ከራሳችን የኢኮኖሚና የማህበርዊ ኑሮ ጋር የሚጣጣም ወቅታዊ መፍትሄ ማምጣት አለብን።
አማራም ተነስቶ ዛሬ ለመገንጠል ይችላል። ኦሮምያም እንደዚሁ። ትግራይም እንደዚሁ። ወዘተ። ከዛስ በኋላ? ኦሮምያ ከተገነጠለች የትኛው ክፍል ነው ሥልጣን የሚይዘው? ክርስቲያኑ? እስላሙ? ነቀምቴው? አርሲው? አምቦው? ቦረናው? የትኛው የፖለቲካ ድርጅት? በኦሮሚያ ውስጥ የሚኖሩት ጎሳዎችስ እንዴት ሊሆኑ ነው። ሕዝቡ ከፈለገ ደግሞ ትንሹም ብሄር መገንጠል ይችላል። ትልቅ ብሔር ለሆነ ለኦሮሚያ ክልል ግን ከመገንጠል ጥቅሙ፤ ጉዳቱ ይብሳል። ትልቅ ብሔር እንደመሆኑ መጠን በአንድነት ግንባር ውስጥ ትልቅ ድርሻ በመውሰድ ብዙ ለሐገር የሚጠቅሙ ሚናዎች መጫወት ይችላል።
ችግሩን የሚያባብሰው ተማርኩኝ ያለው “የልብ ወለድ ፕሮፖጋንዳ” ፀሃፊው ነው። ኦሮሞን እንገንጥል። ትግሬን እንገንጥል። ሲዳማን እንገንጥል። ወዘተ ይለናል። እንዴት ነው የምንገነጣጠለው? አንተስ/አንቺስ የምትገነጠለው/የምትገነጠዪው? እስቲ እንዴት እንደምትገነጠል፤ ክልልህ ውስጥ ካሉት የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር እንዴት መተባበር እንድምትችል፤ ምን አይነት መግሥት እንደምትመሰርት፤ የመገንጠልህ ጥቅምና ጉዳቱ፤ መገንጠል የሚያመጣው የኢኮኖሚ ጥቅምና ጫና፤ ከጎረቤቶችህ ጋር ያለህ ግንኙነት፤ ወዘተ. ወዘተ… በድንብ ተጠንቷል? የባእድ ቲዎሪ ከመፍተልና ወያኔ ያቀበለህን የዘረኝነት ልቃቂት ከማጠንጠን ይልቅ ወረድ ብለህ መሰረትህን እወቅ። ማንንነትህን እወቅ።
እንግዲህ መገነጣጠል ከተጀመረ ማለቂያ ላይኖረው ነው። በማንኛውም ክልል ውስጥ አደጋው ይሄ ነው። ሌኒንን እንዳንጠይቀው ሞቶብናል። የራሳችን ሌኒን “መለስ ዜናዊ” ደግሞ እሱኑው ስለዚሁ ጉዳይ ለመጠየቅ በድንገት ሄዶ በትሮትስኪ ሰዎች ተጠልፎ ግምገማ እየተደረገበት ነው ይባላል።
የሰፊው ሕዝብና የሐገራችን ጎጆ ወቅታዊ ጥያቄ መገንጠል አይደለም።
እኩልነት። መብት። ነፃነት። ፍትህ። ይህን ለማስከበር ደግሞ አንድነት። የሁሉም ጭቁን ሕዝቦች ጥያቄና ፍላጎት አንድ አይነት ነው።
በትብብር ሆኖ ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት ምን ያስፈልጋል ለሚለው ጥያቄ የራሴን አስተያየት እንሚቀጥለው አቀርባለሁ።
1. እስካሁን የነበረውን የፖለቲካ እንካ ሰለምታ ጨርሶ ማቆም።
2. በአንድ የጠርጴዝያ ዙርያ ተቀምጦ የሁሉንም ድርጅቶችና ግለሰቦች አስተያየትና ሃሳቦች በዝርዝር መፃፍ (ማስቀመጥ)።
3. የቀረቡት ሃሳቦች ላይ፤ በታላቅ ትዕግሥትና በመደማመጥ፡ ተነጋግሮ፤ እያንዳዱን ነጥብ በጥሞና አኝኮና አብላልቶ፤ በየአንገብጋቢ መልካቸው ቅደም ተከተል ማስያዝ።
4. ጊዜያዊ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ (ከየድርጅቱ) መምረጥ። የዚህ ኮሚቴ አባሎች በብቃታቸው፤ በልምምዳቸውና በብስለታቸው ብቻ የሚመረጡ መሆን አለባቸው።
5. ለዚህ ጊዜያዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፤ የወከላቸው የፖለቲካም፤ የሲቪክናም ሆነ የሀይማኖት ድርጅት ሁሉ የማያወላውል ድጋፍ በመስጠት ከኋላቸው መሰለፍ አለባቸው።
6. በጊዜያዊው ኮሚቴው ሥር የሚሰራ የድርጅቱ አፈቀላጤ (የሚድያ አቋም) ማቋቋም።
7. ጊዜያዊው የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው፤ በወከሉት ድረጅቶችና በራሱ ሚድያ በኩል ዲያስፖራውን በማስተባበር የሰውና የማቴርያል አቅም ለመገንባት፤ ሌት ተቀን ሳይሉ በአስቸኳይ በሥራ ላይ እንዲሰማሩ ማድረግ።
8. ጊዜያዊው የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው፤ በወከሉት ድርጅቶች እየተረዳ ሀገር ውስጥ ካሉ የፖለቲካ፤ የሲቪክና የሃይማኖት ድርጅቶች ጋር ጠንካራ ግንኙነቶችን መፍጠርና መተባበር።
9. በጊዜያዊ ሥራ አስፈፃሚው ኮሚቴ ስር ሆኖ የሚካተት፤ ከአሜሪካና ከአውሮፓ መንግሥታት ጋር የሚያግባቡ (lobby) ግለሰቦችን የሚመራና የሚከታተል፤ በፖለቲካና ፐብሊክ ሪሌሽን ጥሩ ልምምድና ችሎታ ያለው ቡድን ተቋቁሞ አግባቢዎቹን (lobby group) ከፍትኛ ክትትል እዲያደርግ (ይህ የሎቢ ግሩፕ እንደ አንገብጋቢ ጥያቄ መታየት ይኖርበታል)። ከትግሉ ክፍል አንደኛው ትልቁ ምዕራፍ ነውና።
10. እነዚህ የተባበሩት የፖለቲካ፤ የሲቪክና የሃይማኖት ድርጅቶች ሀገር ውስጥ በመዝለቅ ሕዝብን በመቀስቀስ ሥራ ላይ በመሰማራት ታላቅ ግፊት ማድረግ መቻል አለባቸው (በሰላማዊ ሰልፍ፤ በሥራ ማቆም አድማ፤ የገጠር መንገዶችን በመዝጋት፤ የመሳሰሉትን በማድረግ …)
11. ከላይ የተገለፀው ግፊት ወያኔን በጠረጴዛ ዙርያ ለማምጣትም ሆነ በሕዝብ አመፅ ለማንበርከክ የጠቅማል።
12. ጊዜያዊው የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በየጊዜው ስብሰባ በመጥራት፤ በትብብሩ ውስጥ ላሉት ድርጅቶች ሥራው ያለበትን ደረጃ በተመለከተ ማብራርያ መስጠት። ለሕዝብም በሚድያው በኩል ተከታታይ ገለፃዎች መስጠት (to foster transparency).
13. ወ.ዘ.ተ…..
Dayano65@outlook.com