ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የምትገኝ የረዥም ዘመን ታሪክ ያላት ሀገር ናት፡፡ ማለትም ከአለም መፈጠር ጋር አብራ የሚስተካከል ታሪክ ያላት እንጂ በዘመን ቆጥሮ እና ለክቶ የኢትዮጵያን ዘመን መወሰን ይከብዳል፡፡ ለእዚህም ሁለቱም የታሪክ ማስረጃዎች ማለትም ሳይንሳዊው እና የጥንታዊ ፅሑፎች ማስረጃች ናቸው፡፡ ይህቺ በአፍሪካ ነፀነታውን ጠብቀው ለመዳር ከቻሉ ሁለት አንዷ፣ አሁን አለም የሚተዳደርበት አለም አቀፍ ሕጎችን በአለም ዲፕሎማሲ እኩል ተከራክራ በቀድሞው የአለም ማህበርም ሆነ በአሁኑ የተባበሩት መንግስታት ምስረታ ላይ ፊርማዋን ያስቀመጠች በጎሳ ላይ ሳይሆን ኢትዮጵያ በሚል ጥንታዊ ስሟ ነው፡፡
እ.ኤ.አ. አቆጣጠር በ1885 ዓ.ም በበርሊን ጉባኤ የአውሮፓ ሃያላት ሀገሮች አፍሪካን ሲከፋፍሏት ኢትዮጵያ ነፃነቷን ጠብቃለች፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ነፃነታቸውን ሲያገኙ ሰንደቅ አላማቸውን በኢትዮጵያ ቀለሞች በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ላይ የመሰረቱበት ሀገር ነች ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ተምሳሌትነት ዛሬ ድረስ የአፍሪካ፣ የካሪባን እና የእሩቅ ምስራቅ አገሮች ከህሊናቸው አልጠፉም፡፡
የጎሳ ፖለቲካ ለአለማችን አዲስ ክስተት አይደለም፡፡ የአምባገነኖች መሸሸጊያ ጉረዳ ዘረኝነትና የዘር መርዝ መንዛት ነው፡፡ አደልፍ ሂትለር የጦርነት ጥማቱን ለማርካት የጀርመንን ሕዝብ የተለየ አድርጎ ማቅረብ ነበረበት፡፡ እናንተ የጀርመን ህዝቦች የ‹አርያን› ዘሮች› እያለ ይሸነግል ነበር፡፡ ሆኖም ግን ሁኔታዎች ስህተት መሆናቸውን የምንረዳው እና የምንነቃው ከብዙ የሰውልጅ እልቂት በኋላ ነገሩ ዘግንኖን ወደ አእምሯችን ተመልሰን ስንነቃ ነው፡፡
የ1960ዎቹ የኢትዮጵያ ትውልድ የለውጥ እንቅስቃሴ ሃሳቦችን ብልጫ በማድረግ ስለ ርዕዮተ-አለም ብዙም ጠልቆ የሚያውቅን ወታደሩ አጠገቡ ያገኘውን ርዕዮት እንዲጨብጥ አድርጎታል፡፡ በእዚህ እንቅስቃሴ ስር የተንቀሳቀሱ ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል፡፡ የፓርቲዎች አደረጃጀት ስርነቀል ለውጥ ለውጥ የሚያቀነቅኑ እና የማርኪዝም ፍልስፍናን እንደዋነኛ ሰነድ የሚጠቀሙ ነበሩ፡፡ ኢህአፓ፣ መኢሶን፣ ህወሓት፣ ህግሐኤ (ህግድፍ) ለዚህ ዋቢ ናቸው፡፡ ኢህአፓ እና መኢሶን ኢትዮጵያን የሚረዱበትና ለመለወጥ የሚሞክሩበት አግባብ የወደብ ቅራኔና ዋነኛ አንጓ በማድረግ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ህወሓት እና ኦነግ የብሔር ቅራኔውን በማስቀደም የብሐረሰቦች መብት መከበር የችግሩ መፍትሔ መሆኑን ያስቀምጣሉ፡፡ ነገር ግን ኦነግ ኤርትራን ጉዳይ ሙሉ ቅኝ-ግዛት (Classical Colonialism) መሆኑን ገልፆ የኦሮሚያ ጉዳይ ግን የውስጥ /የአቢሲኒያ ቅኝ ግዛት ነጻ ስለማድረግ እንደሚታገል ይገልፃ፡፡ የዚህ አስተዳደር ድባብ ዛሬም ድረስ ከዚህ አካባቢ በተገኙ የተወሰኑ ምሁራን ላይ ያንፃባርቃል፡፡ የብሔረሰብን ጉዳይ በዋነኛነት በተመሳሳይ መልኩ የያዘው ህወሓት ስለጎሳ ጉዳይ አብዝቶ የማንሳቱን ያክል ኦነግ ስለጎሳ ሲያነሳ ደግሞ አይጥመውም፡፡ ምክንያቱም ጉዳዩ የስልጣን ሹም እና ጎዳን ሁሉም የሚጠቀመው ለስልጣን መወጣጫ ስልት በመሆኑ ነው፡፡ በሌላ በኩል በወታደሩ የተመሰረተው ኢሰፓ (ኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ) ሌላው መሰረቱን ግራ ዘመም ፍፁም ፈላጭ ቆራጭ ቢሆንም በጎሳ አስተሳሰቦች ውስጥ ያልጠነከረ ይልቁንም ለሀገራዊ እድገትና ማንነት የሚሰጠው ልዩ ትኩረት ከቀኝ ዘመኖች የተወሰደ መሆኑ ነው፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያ በ1967 ዓ.ም ከነበረችበት ሁኔታ በብዙ የተለዩ አዲስ ክስተቶች አሉባት፡፡ የኢትዮጵያ ፓለቲካዊ፣ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ሁኔታዎች ብቻ ሳይሆኑ አንድ ትውልድ አልፎ አዲስ ትውልድ ተተክቷል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ከ30 ሚሊዮን በ3 እጥፍ ወደ 90 ሚሊዮን ተተኩሷል፣ የባሕር በር ተዘግቷል፡፡ ወጥ ነበረው የመንግስት ስሪት በጎሳና ቋንቋ ላይ በተመሰረተ አስተዳደር ተቀይሯል፡፡ ከተሞች በመጠን ሰፍተዋል፡፡ በከተማ የሚኖረው ሕዝብ ከገጠሩ ጋር ሲነጻጸር ግን በእነኝህ ሁሉ ከሶስት አስርተ ዓመታት በአለም ከ90 በመቶ ወደ 85 (83) በመቶ ነው ዝቅ ያለው፡፡
የሕዝቡ የኑሮ ደረጃ እ.ኤ.አ. በ1970ዎቹ ነጻነታቸውን ከተቀዳጁት የአፍሪካ ጥቁር ሕዝቦች እንደ ናይጄሪያ እና ጋና ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ የሚባል ከእጅ ወደ አፍ ነው፡፡ 1983ን ተከትሎ ‹‹የብሔር ብሔረሰብ መብት›› የመፍትሔው ማዕከል ነው ተብሎ ብዙ ተነግሮለታል፡፡ ሆኖም ግን ያለፉት 25 አመታት ያሳዩን ከ25 ዓመታት በፊት የነበረውን ሳይንሳዊ ትንተና ነው፡፡ የጎሳ ፖለቲካና ፌዴራሊዝም የግጭትና የብጥብጥ ምንጭ መሆኑን ይህ ጎሳ ተኮር ግራ ዙሪያ አስተሳሰብ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ታሪክና ባህላዊ/እሴታዊ ማንነቶች ከፍተኛ ንቀት ያለው ከመሆኑም በላይ ለእነኝ እሴቶች ዋጋ የሚሰጡትን ሁሉ እና አስተሳሰብ ተባባሪ የነበሩትን ሁሉ ከማግለል ጀምሮ በተለያዩ ዘዴዎች ማፈን፣ ማሳደድና መጨቆን እንደ ዋና ስልት ያመለክተዋል፡፡
በዘመነ ኢህአዴግ/ወያኔ ደግሞ የውስጥ ቁርሾው በደርግ ዘመን ከነበረው የሕዝብ ስልጣን ለህዝብ የማስረከብ ጥያቄን የመመለስ ሙግት ብቻ ሳይሆን ‹‹መንግስታዊ የጎሳ ፖለቲካ›› በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ማህበራዊ፣ ፖለቲካ እና ምጣኔ ሀብታዊ ግንኙነት ላይ አደገኛ ጥላ አጠላ፡፡ የጎሳ ግጭቱ ከሌሎች የመሬት ግጭት አልፎ እስከ መንደር የከብቶች መሰማሪያ ሜዳ ድረስ ኢትዮጵያውያንን አጋጨ፡፡ ይህ ስርዓት በተለየ ቁጭ ብሎ ህዝብን ለህዝብ ጋር ለማጋጨት የሚሰሩ የደህንነት ሰዎች ያሉት መሆኑ ኢታዮጳ ምን አይነት አደገኛ ሁኔታ ላይ መሆኗን ያሳያል፡፡
ዶ/ር ወንድወሰን ተሾመ በቪየና ዩኒቨርሲቲ የአንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል ተመራማሪ እ.ኤ.አ አቆጣጠር በ2008 ዓ.ም በዓለም አቀፍ ሰአቂ ሳይንስ የምርምር መጽሔት ላይ የኢትዮጵያ የኢህአዴግ/ህወሃት የጎሳ ፖለቲካ በሚገልጽ የወጡት የጥናት ፅሑፍ ላይ ‹‹የጎሳ ፌዴራሊዝም የህወሃት›› ከፋፍለ ግዛ ፖሊሲ ሲሆን የተዋቀረበት ዋናው ምክንያትም ስርዓቱ የራሱን ስልጣን ለማስጠበቅ ነው፡፡ ሁኔታው ግን አገሪቱን እንዳትከፋፍል ያሰጋል ይላል፡፡ ‹‹ የመንግስታዊ የጎሳ ፖለቲካ›› መሰረት ያደረገውን የፌዴራል ስርዓት በትክክለና የመሬት አቀማመጥ እና የሕዝቦች ታሪካ አሰፋፈር መሰረት ያደረገ የፌደራል ስርዓት መቀየር መሆኑ እየታወቀ ኢህአዴግ/ወያኔ የተጋጩትን የጎሳ አባላት መዳኘትን እንደትልቅ ግብ እየቆጠረ በዜና እወጃው ላይ በስሌት ብቻ ማውራቱ አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡
የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች ትልቅ ግብ ቆመንለታል ያሉት ጎሳ አይደለም፡፡ ቆመንለታል ያሉት ሕዝብ አጥንቱን ከስክሶ ለስልጣን እስኪያበቃቸው ድረስ የአዞ እንባ ያነቡለታል፡፡ ስልጣን ላይ ሲወጡ ግን ስልጣናቸውን ማደላደል ብቻ ቀዳሚ ስራቸው ይሆናል፡፡ የጎሳ ፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ ደግሞ ዛሬም ሆነ ነገ እንቅፋት ይሆኑኛል የሚለው ‹‹ደንቃራ›› ከፊቱ ይታዩታል፡፡ እርሱም በረጅም ዘመናት የተገነባው ያለፈው እና አሁን በህዝብ ልብ ውስጥ ያለው ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ ይህ ኢትዮጵያነት ደግሞ ባለፈ ማንነት ታሪክ፣ ባሕልና እምነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ስለዚህ ዛሬ ሰበብ አስባብ ፈልጌ ያለፈ ማንነትን የሚጎዱ ናቸው ያላቸውን የህዝብ ግጭቶችን፣ በነበሩበት ጊዜ ጀግና ያሰብሉ የነበሩ በ21ኛው ክ/ዘመን ግን ክፉ ተግባራትና ፈጽመው የሌሉ ታሪኮችን በመፍጠር የኢትዮጵያዊነት መሰረቶች እንዲናዱ ይሞክራል፡፡
ለምሳሌ የብሔር ብሔረሰቦች ጉዳይና ፌዴራሊዝም አስተዳደሮች በጽነሰ ሀሳብ ደረጃ ባልተፈጠሩበት ዘመን ላይም አልታወጁም ነበር? የሚመስል ‹ውኃ ቀጠነ›› ንግግር ኢትዮጵያዊነትን ይሳደባል፣ ያናንቃል፣ ይልቁን ፌዴራሊዝም በአለው ሳይታወቅ እነ አባጅፋር የራሳቸውን ግዛት በራሳቸው ያስተዳድሩ እንደነበር ግን በጋራ ከማእከላዊ መንግስት ጋር በማያገናኛቸው ጉዳይ ላይ አብረው ይሰሩ እንደነበር አያስተውልም፡፡ ታዲያ አሁን ባለንበት ዘመን በእነዚህ አስተሳሰቦች ሺዎች ተገድለዋል፡፡ ሌሎች አያሌ ሺዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ከእዚህ ሲዘል ደግሞ ማስረጃ ለሌለው ተረት ሁሉ ሃውልት ይሰራ ባይ ነው፡፡ የእዚህ አስተሳሰብ አራማጆች ዋና ግባቸው ‹‹እኛ ስልጣን ላይ ከሌለን እና የምንፈልገውን ካልፈጸምን ጭር አይልም›› ባዮች ናቸው፡፡ ለእነዚህ እኩይ ተግባራት የሚተባበራቸው ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይል ጋር ለመተባበር ዝግጁ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊነት አንድነትና፣ ሕብረት ሲጠናከር ይደነግጣሉ፡፡ ምክንቱ ደግሞ የእነሱ አስተሳሰብ በጠንካራ ኢትዮጵያዊነት አስተዳደብ ፊት ሞገስ እንደሌለውና እነርሱንም ወደ ስልታን ኮርቻ ላይ እንደማያፈናጥጣቸው ይረዳሉና፡፡
የኔ በአዲስ የአዲስ ማስተር ፕላን ዙሪያ ያሉ የኦሮሚያ ክልል ገጠር መሬቶች ማከተቱ በራ ችግር አይደለም፡፡ እንደውም ፕላኑ ኦሮሚያ አልፎ ሌሎች ከተማችንም ቢያካትት እሰየው ነው፡፡ ከተማ ቢያድግ መልካም ነው፡፡ ከተማ ሲያድግም በዙሪያው ይሰፋል፡፡ ይህ ባህርያዊ ነው፡፡ ግን ችግር አለ፡፡ በኢህአዴግ ዘመን እየተስተዋለ ያለው የከተሞች ማስፋፊያ ስትራቴጂ አፈጻጸም መሬት ወደ ከተማ ሲገባ በዙ የሚኖሩ አርሶ አደሮች ለፈቃዳቸው ከቄያቸው ይፈናቀላሉ፣ በቂ ካሳ (ክፍያ) ቢያሰጣቸውም፡፡ በዚህ መሰረት አርሶ አደሮች ተቃውሞ ሊያሰሙ ይችላሉ፡፡
ሌላው ምክንት ደግሞ ከላይ እንዳየነው የብሔር ፖለቲካችን ነው፡፡ ይሄ መሬት የኦሮሚያ ነው፡፡ ነፍጠኞች እንዳይወስዱባቹ ተጠንቀቁ እያለ ጥላቻ ሲሰብክ ከርሞ አሁን የኦሮሞ ተወላጆች ‹‹የኦሮሚያ መሬት የኛ ነው፡፡ ለማንም አሳልፈን አንሰጥም! ሲሉት ጊዜ ለምን ኃይል እርምጃ መወሰድ መረጠ? ኢህአዴግ ራሱ የዘራውን ነው እያጨደ ነው፡፡ ለማንኛውም ሁኔታው መረጋጋት አለበት፡፡ ኢህአዴግም በጉዳዩ ላይ ራሱን የሚፈትሽበት ይሆናል፡፡
በአንድ በተወሰነ ርዕዮተ አለም ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አስተዳደርም ሆነ በሰፈርተኛነት ላይ የተመሰረተ የአንድ ሰሞን ግርግርታ ከኩፍኝ በሽታ ጋር በትክክል ይመሳሰላሉ፡፡ ኩፉኝ የአንድ ሰሞን በሽታ ነች፡፡ ካልታከመች አደገኛ ነች፡፡
ከታከመች ግን የትም አትደርስም፡፡ በዘመነ ደርግ ስለሶሻሊዝም ስህተት ለአንድ የቀበሌ ጥበቃ መናገር እስከሞት የሚያደርስ ፍርድ ሊያሰጥ ይችላል፡፡ በወቅቱ ጉዳዩ ስለመግደሉ ‹‹ትክክለኛት›› እርግጠኛ ነበር፡፡ ከአመታት በኋላ
‹‹ኩፍኝ›› አልፎ ሲመለከተው ግን ስህተቱ ይታየዋል፡፡ የጎጥ ስሜትና መሰረቱ እርሱን ያደረገው የፖለቲካ ዘውግም ይሄው ነው፡፡ እነዚህ በተለያዩ የጎሳ ድርጅቶች ስም የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች አላማቸውን ለማስፈጸም የሚሞክሩትና የሚተባበሩት በአፈሙዝ ነው፡፡
ይህ ማለት በሌላ አገላለጽ መጨውም የፖለቲካ መድረክ የሚስተናገደው በአፈሙዝ ስልጣን ላይ የሚመጣ የሚደመጥበት ነው ማለት ነው፡፡ አሁን ለሰላማዊ የስልጣን ሽግግር አልታደልንም ማለት ነው፡፡ የሀገራዊ ኢትዮጵያዊነት ስሜት ግን ጥብቅ የሆነ ማህበራዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ትስስር ያለው ነው፡፡ ዘለቄታዊውን የጋራ ቤታችንን ኢትዮጵያን እንጂ ጎሳዊ ስሜት ይዞ መሄድ አያዋጣም፡፡ ስልጣን ከሆነ በኢትዮጵያዊ እውነተኛ ስሜት መነጋገር
አንድ ነገር ነው፡፡ በወጡበት ጎጥ ስም እየማሉ ወጣቶች እና ሕፃናት ላይ እንዲሁም የሌላ ጎሳን በጥላቻ ዘይት እየቀቡ ሕዝብ ማፋጀት ግን ለጊዜው የተሳካ ቢመስልም ውሎ አድሮ የህሊና ቁስል ይሆናል፡፡ አበቃው፡፡ ሀገሬ ኢትዮጵያ የሰላም አየር የሚነፈስባት፣ ትሆን ዘንድ ተመኘሁ፡፡