Some people want it to happen
Some wish it to happen
Others made it happen
(Michael Jordan)
ከውነቶች ጀርባ የተደበቁ ውሸቶች ፣ ከነኚያ ውሸቶች ጀርባ የተደበቁ ውነቶችን እያቀላቀሉ መናዘዝ ለፅድቅ አያበቃም። እንደ ቡቱቶ ጨርቅ ያንንም ያንንም ደራርቶ ፣ ጠቃቅሞ ሀተታ በማርቀቅ ‘ጋዜጠኛ’ በሚል ማዕረግ የግል ጥላቻን በድረ-ገፅ ላይ ማሰራጨት አሳፋሪ እና ቀላልነት ነው።
ጋዜጣ እና ጋዜጠኛው ምን ያገናኛቸዋል – ወሬ እና ወሬ አቀባዩ እንዴት ይዛመዳሉ? ለመሆኑ በምን መስፈርት ነው አንድ ሰው ጋዜጠኛ በሚል ‘ማዕረግ’ የሚጠራው ፤ ጋዜጠኛ የሚለውስ ሙያ እንደ ፊታውራሪ ፣ እንደ ዶክተር ፣ እንደ ኢንጅነር ከስም ጋር ተዳብሎ መጠሪያ ሊሆን ይችላል ወይ? ወያኔ አዲስ አበባ በገባ ማግስት ያሻችሁን ፃፉ ተብሏል በሚል ከተማይቱን እንደ ሱናሚ ያጥለቀለቀው ጋዜጣ እንደ ጎርፍ አገብስብሶ ወደ ወሬ አቀባይነት ያመጣቸው ሁሉ ጋዜጠኞች ነበሩ? ሙያው የሚጠይቀውን ስነምግባር እና ብቃት ሳይማሩ እንዲያው ከጎዳና ላይ ተነስቶ ጋዜጠኛ መባልስ ተገቢ ነው? መዘዙ እሰከ ዛሬ የተከተለን ይመስላል።
ውነትም አዲስ ዘመን ላይ ነን!!
አንድ ሰው ወሬ አቀባይ የሚሆነው በተለያዩ ምክንያቶች ነው – በተፈጥሮ የተጎናፀፈውን ዝንባሌ አዳብሮ ወደ ሙያው የሚቀላቀል እንደመኖሩ ሁሉ የእንጀራ ነገር ሆኖበት ብዕር ሲደነቁል የሚኖር ብዙ ነው። አንድ ጠባብ አላማ አንግቦ (ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ) ወሬ ማቀበል የሚጀምር ሰው ነገሮችን ሁሉ እሱ በግሉ ከሚከተለው የፖለቲካ መስመር አኳያ እያመጣጠነ ለመተንተን ይገደዳል። ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ የሚሉት ነገር ይከተላል… ግለሰብ ላይ ያተኮረ ሀተታ ልፅፍ አልተነሳሁም – ይህን ለመፃፍ ያነሳሳኝ ሀተታ ግን የግለሰብ ስለሆነ ተዛማጅ ጉዳዮች አብረው መነሳታቸው አልቀረም።
እናማ ሰሞኑን የተናፈሱ ወሬዎችን ስንፈትሽ የግንቦት 7 መሪ ወደ ትግሉ ሜዳ ገቡ የሚል ባድናቆት የታጀበ ወሬ ቀዳሚውን ስፍራ ይዞ እናገኛለን። ከወሬው በስተጀርባ ትንተና ብጤ እዚህም እዚያም ተሰጥቷል – እኔን በሚመለከት የግንቦት 7 መሪ ትግሉ አካባቢ መጓዛቸው ለምን እንደ ዜና እንደቀረበ (ያውም ሰበር ዜና) አልገባኝም። እስከዚያ ድረስ ሲታገሉ እንዳልነበር ሁሉ። ለኔ ዜና የሚሆነው እሳቸው ከታጋዩ ሰራዊት ጋር ሆነው ያከናወኑት አዲስ ነገር ካለ ብቻ ነው። ትግሉንማ ጠንስሰው ፣ አስማምተው ካንድ እርከን ላይ አድርሰውታል – እና ‘ተቀላቀሉ’ የሚለው ወሬ አስፈላጊነቱ አይታየኝም።
በመሰረቱ የትጥቅ ትግል ለመምራት የተሰለፉ ጀግኖች እርምጃቸውን ለማቀለጠፍ ሲሉ በመረጡት ጊዜ እና ቦታ መገኘት አዲስ ነገር አልመሰለኝም። እነ ኦሊቨር ታምቦ ፣ እምቤኪ የዛሬው ሙጋቤ ወይንም ሟቹ ሳሞራ ማሼል የትጥቅ ትግላቸውን የመሩት በመላው አለም ነፃነት ወዳድ ህዝብ መካከል በመመላለስ ነበር። አብዛኛውን ጊዜም ያሳልፉ የነበረው ትትቅ ትግሉን የሚያግዝ ዲፖሎማሲያዊ እና ማቴሪያል ድጋፍ ፍለጋ በውጭው አለም መሆኑን ማስታወሱ ይጠቅማል። የፍልስጤም ነፃነት መሪ ያሲር አራፋት ፓለስታይን ምድር የገቡት ጥንካሬ ባስገኘው ከብዙ ዘመን ቆራጥ ትግል እና ድርድር በሁዋላ እንደ ነበረም ማስታወሱ መልካም ነው። እናም የግንቦት 7 መሪ ትግሉን ለማቀላጠፍ ሲል በመረጠው ጊዜና ቦታ ቢገኝ አማራጩ የድርጅቱ አመራር ብቻ ይሆናል። ‘ትግሉን ተቀላቀሉ’ የሚለው አባባል ግን ስህተት ይመስለኛል። ዶ/ር ብርሀኑ በዚህ ብሔራዊ የነፃነት ትግል የተነሳ በቤተሰቡ ፣ በግል ንብረቱ እና ደጋፊዎቹ ላይ ጠላት ያደረሰውን ጉዳት አለማስተዋልም ይመስለኛል። ማን መርቶ ለዚህ አብቅቶት ነው ዛሬ ‘ተቀላቀሉ’ የሚባለው? ነገ ሌላ ቦታ በሌላ ጠቃሚ የትግል ግዳጅ ላይ ቢታዩስ ከትግሉ ራቁ ሊባል ነው?
ተናግረው አናጋሪ ስለሆኑት ፎቶዎች ትንሽ ለማለት የጀመርኩት ረቂቅ ወደ ሌላ ይዞኝ ጭልጥ አለ – አዎ ፎቶዎቹ ይናገራሉ – ያናግራሉም ፣ ያስቀባጥራሉ። ልጅ ሆኜ አንድ ቄስ ነበሩ። አጋንንት በማስለቀቅ ዝነኛ ናቸው። ፎቶዋቸው እንዳንድ ብር ይሸጥ ነበር። አጋንንት ሰፍሮበታል የተባለ ሰው የቄሱን ፎቶ ሲያይ መቀባጠር መለፍለፍ ይጀምራል። ታዲያ አሁንም የትጥቅ ትግሉን ጀማምሬው ነበር የሚለን ወሬ አቀባይ ሰሞኑን ያየነውን የተቀላቀሉ ወሬ ፎቶ ላይ የምታዩት አገሌ ነው… ጥግ የቆመው ፣ መሀል የተገተረው.. እያለ የቋጠረውን ሁሉ ዘረገፈው።
የትጥቅ ትግሉን መተቸት አንድ ነገር ነው ፣ ተገቢም ይሆናል። ያን ማድረግ ሙያዊ ብቃት እና ስነ-ምግባር ይጠይቃል – ባንድ አጋጣሚ ያገኙትን የግለሰቦች ማንነት እየዘረዘሩ መቀባጠር ግን የጤና አይደለም። ፎቶ አይቶ መለፍለፍ የነበረ ቢሆንም – ይኸኛውን የተጠናወተው ግን የበረታ ነገር ነው።
ከጥቂት ዓመታት በፊት ይህ ወሬ አቀባይ አስመራ ደርሼ መጣሁ ብሎ በየራዲዮ ሾው እና ህዝባዊ ስብሰባ ላይ እየቀረበ የትጥቅ ትግሉ በዚህ በዚያ ወጥቶ ወርዶ እያለ አዱኛ ሲያሰባስብ እንደነበር እናስታውሳለን። እኔ የመሰለኝ ያጠናቀረውን የሚዘግብ ፣ እንደ ወሬ አቀባይ የታዘበውን ለታዳሚው የሚያካፍል መስሎኝ ነበር። ለመሆኑ እንደ ጋዜጠኛ ሙያ ተጠያቂነት ያለበት ስራ ለመስራት የቆመ ሰው ከሆነ ትናንት አስመራ ሄዶ እሱ የፈፀመውን እርባና ቢስ ነገር በየትኛው ዳኛ እናስጠይቅ? አሳዛኙ ጉዳይ ትናንት በዚያ መልኩ ሲያዘረከርክ የቆየው ተረስቶ ዛሬ ለሌላ ዝባዝንኬ ይዞልን ብቅ ማለቱ ነው።
በትግሉ ሜዳ የተሰማሩ ግለሰቦችን ስም ወይንም የስራ ድርሻ በዝርዝር ለማወቅ የሚጓጓ ካለ ያው ጠላት ብቻ ነው። የስለላ መረቡን ያጠናከረው ወያኔ ለዚህ የሚያንስ አይመስለኝም – ታዲያ የወያኔን ስራ እዚህ ሆኖ ከመሻማት አንደኛውን ጠቅልሎ እንደ (ዳዊት ከበደ) ወያኔ ጉያ መቀላቀሉ አይሻልህም? ፎቶ አይተህ ይህን ያህል የምትበረግግ ፣ ስዕል ስታይ የቋጠርከው የሚፈታብህ ከሆነ ማን ለንዳንተ አይነቱ ቀዳዳ ጆሮውን ይሰጣል?
የቄሱ ነገር – ታዲያ እኛ የማውቃቸው ቄስ ፣ አጋንንት የሰፈረበት ሰው ፎቶአቸውን ብቻ አይቶ ሲወራጭ ከታየና ዘመድ አዝማድ ካለው እሳቸው ዘንድ ያመጣዋል። እሳቸውም ጠበል ረጭተው መስቀል አሳልመው
“… ልቀቅ ፣ ለቀህ ወደ መቀመቁ ውረድ…” እያሉ በግዝት አጋንንቱን አዋክበው ከልክፍት ይገላግሉታል…
የወሬ አቀባዩን ነገር እያጤንኩ ሳለ… እንዲህ አይነቱን ተራ ወሬ ለማርቀቅ የሚገፋፋ ስሜት ምን እንደሆነ ለማጤን ትንሽ ሙከራ አድርጌ ነበር – እውቁ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ማይክል ጆርደን ባንድ ወቅት የተናገረው ቁምነገር ትውስ አለኝ – በመግቢያዬ ላይ እንዳስቀምጥኩት ሁሉ በውርስ ትርጉሙ ሀተታዬን ደመድማለሁ –
አንዳንድ ሰዎች እንዲፈፀም ይፈልጋሉ ፣ አንዳዶች ደግሞ እንዲፈፀም ይመኛሉ ሌሎች ግን ይፈፅሙታል!!
Some people want it to happen
Some wish it to happen
Others made it happen
(የትርጉሙ ችሎታዬ አቅም ያንሰዋል – )
ዛሬ ከምንገኝበት ወሳኝ ትግል አንፃር ስተረጉመው ደግሞ – “አንዳንዶች ነፃነት ለመጎናፀፍ ይፈልጋሉ ፣ አንዳንዶች በነፃነት ለመኖር ይመኛሉ ፣ ሌሎች ግን ነፃነትን ለመጎናፀፍ በቆራጥነት ይታገላሉ” አልኩ።
የፈለጉም ፣ የተመኙም ብፁአን ናቸው የሚፈፅሙት ግን ፃድቃን ናቸው!!
ልቀቅ… ወደ መቀመቁ… ወደ ወያኔ ሰፈር ውረድ!!