Quantcast
Channel: Abugida Ethiopian American Amharic Web Page
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1809

ኦባማ፣ ዛሬ የተናገሩትን ለመናገር ኋይትሐውስም ሆነው ይችሉ ነበር –ኤልያስ ገብሩ ጎዳና

$
0
0

ኃይለማርያም፣ የማይጥምዎትን ጥያቄም ሰምቶ በመርሳት ስሌት ማለፍ የቅን ልቦና ማጣት በሽታ ነው! (በቅርቡ ስለተፈቱት ሶስት ጋዜጠኞች እና ሁለት ጦማሪያን የተጠየቁትን መመለስ አልቻሉም)
ፍትሕአወቅ (የኢብኮ ጋዜጠኛ) ሆይ፣ ዓለም ያደመጠውን ጥያቄ ኤዲት አታድርግ! …ነገ ይጥልሃል
———-
ዛሬ ከሰዓት በኋላ በብሔራዊ ቤተመንግሥት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እና የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ንግግር አድርገው ነበር፤ ከንግግራቸው በኋላ ለጥቂት ለተመረጡ (በእኔ አረዳድ ነው፣ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪም በመጡ ጊዜ በሸራተን ሆቴል በተግባር አይተነዋልና) ጋዜጠኞች ዕድል መሰጠቱ አልቀረም፡፡
የሁለቱም መሪዎች ንግግር፣ ብዙዎቻችን እንጠበቅነው ስለ‘ልማት’፣ ‘ዕድገት’፣ ኢንቨስትመንት፣ ሽብርተኝነት …ወዘተ ለዓመታት የሰማነውን መድገም ነበር ብል ይቀለኛል፡፡ የአንዳቸውንም ንግግር (አዲስ ነገር ይኖረዋል በሚል) ጓጉቼ ባለጠብቀውም፤ እስከመጨረሻው አድምጬ ግን ጨርሼዋለሁ፡፡ ልዩነቱ ኃይለማሪያም በማንበብ፣ ኦባማ ደግሞ በቃል በመናገራቸው ነበር – መሞጋገሱም ሳይዘነጋ፡፡
ከንግግራቸው በኋላ ጋዜጠኞች ላቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ያው የተለመዱ ‹‹ገብስ ገብስ ጥያቄዎች ከኢብኮ ጋዜጠኛ ጀመረና ከኤ.ኤፍ.ፒ አንዲት ሴት ጋዜጠኛ ላይ አበቃ፡፡ ይህቺ ሴት ጋዜጠኛ በቅርቡ ከእስር ስለተፈቱት ሶስት ጋዜጠኞች እና ሁለት የዞን 9 ጦማሪያን የመፈታት ትክክለኛ ምክንያት እንዲሁም ሲፒጄን ጠቅሳ ኢትዮጵያ ፕሬስን ከሚያፍኑት ሃገራት መካከል በሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን በማስታወስ፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ነጻነትን ነጻነትን በተመለከተ ‹‹መንግሥትዎ ምን ያስባል›› የሚል ይዘት ያለው ጥያቄ ለሃይለማርያም ሰነዘረችና ለኦማባ ደቡብ ሱዳንን የተመለከተ ጥያቄ አቅርባላቸው ነበር፡፡ ኦማባም ቢሆኑ፣ ዛሬ የተናገሩትን ንግግር እና ምላሽ ለመስጠት ኋይትሐውስም ሆነው ይችሉ ነበር፡፡
ትኩረቴ በሀገራችን ሥላለው የጋዜጠኝነት ሥራ ነውና፣ አቶ ኃይለማርያም የሚሉትን ለመስማት ጠበኩኝ፡፡ እሳቸውም፣ ፕሬስ ለአንድ ሀገር አስፈላጊ መሆኑን ከጠቆሙ በኋላ፤ የሙያ ሥነ-ምግባርን ጠበቆ መስራት እንደሚያሻ ሊመክሩን ቃጣቸው፡፡ አክለውም፣ ከአሸበሪ ቡድኖች ጋር መስራት ወንጀል መሆኑንም አስገነቡ – በአሜሪካም ጭምር በማለት፡፡
‹‹ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ›› እንዲሉ፣ ነጻ ፕሬስን አዳፍኖ መቃብር ውስጥ በመክተት እኩይ ተግባር ላይ የተሰማራውን መንግሥታቸውን ከደሙ ነጻ በማድረግ፣ ስለጋዜጠኝነት ሥነ-ምግባር እና ስለአቅም ውስኑነት ሲያወሩ ትንሽ እፍረትም አልተሰማቸው፡፡ ባያፍሩም በውስጣቸው ያለውን ዕውነት መካድ አይችሉምና ፈጣሪ በ50 ዓመታቸውም ልቦና ይስጣቸው ብያቸዋለሁ፡፡ (የኢትዮጵያን ፕሬስ በተመለከተ ብዙ ማለት ይቻላል)
በቅርቡ ከእስር ስለተፈቱት ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን አፈታት ለቀረበላቸው ጥያቄ ግን በተረሳ በሚመሰል መልኩ ሳይመልሱ አልፈውታል፡፡ ለነገሩ፣ ለእንደዚህ ዓይነት ጥያቄ፣ ከራሳቸው ጋር ተማክረው ብቻ እንዴት ሊመልሱልን ይችላሉ? ለጋራ የፖለቲካ ውሳኔ በግል መመለስ አይችሉምና!!! ይህቺን ጥያቄ ባለመመለስ ውስጥ ‘ጠቅላዩ’ ሃይሌ፣ ፍርሃትና ብልጠትን ተጠቅመዋል ብዬ አስባለሁ፡፡
ሌላው አስገራሚ ነገር፣ ከመሪዎቹ ንግግር መቋጨት በኋላ ኢብኮ በቀጥታ ስርጭቱ ከብሔራዊ ቤተ-መንግሥት ጋዜጠኞቹን ጠይቆ ማብራሪቸውን ሲያስደምጥ ነበር፡፡ አንዱ ጉዳዩን አብራሪ የነበረው፣ በ‘ትልልቅ’ ስብሰባዎች ላይ የማይታጣው ፍትሕ-አወቅ የሚባለው (ወንድወሰን የአባቱ ስም ይመስለናል) ጋዜጠኛ ነው፡፡ ይህ ጋዜጤኛ፣ ‹‹ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል ፕሬስን የተመለከተ ቀርቦ ነበር›› ካለ በኋላ፣ ኃይለማርያም ስለፕሬስ አስፈላጊነት የጠቀሱትንና የጋዜጠኞችን አቅም ከፍ ለማድረግ ሥልጠና እንደሚያስፈልግ በመጠቆም፣ እነአሜሪካ በዚህ በኩል ድጋፍ እንዲያደርጉ የገለጹትን ክፍል ብቻ ተናግሯል፡፡
ፍትሕአወቅ፣ የኤ.ኤፍ.ፒ ጋዜጠኛ ስለጋዜጠኞች እና ጦማሪዎቹ ያነሳችውን ጥያቄ ድጋሚ ለማንሳት በጭራሽ አልደፈረም፡፡ ዓለም በቀጥታ ስርጭት የሰማውን ጥያቄ ለመደበቅ መሞከር፣ ክብር የማያሰጠውን ‹አድር-ባር›፣ ‹እበላ-ባይ›ና ‹እኖር-ባይ› ማንነት ከመላበስ ውጪ ምን ረብ አለው?!
ፍትሕአወቅ ሆይ፣ ዓለም ያደመጠውን ጥያቄ ኤዲት አታድርግ! ገና በወጣትነት ዕድሜህ መሰል ነገር ከለመደብህና አንዱ የሙያህ መገለጫ ማድረግን ሥራዬ ካልከው አይጠቅምህም፤ ነገ ጠልፎ የሚጥልህ የራስህ መሰል ሥራ ነው፡፡
ሳጠቃልል፣ ብዙሃን ኢትዮጵያች፣ የምንኖርበትን እውነት እያወቅነው ‹ለመንግሥታዊ ዲፕሎማሲ› ተብሎ የሚሸረድደንን የውጭ ሀገር መሪ፣ እውነተኛ ምላሽ የሚያሻን ጥያቄ ሰምቶ፣ በረሳ በሚመስል መልኩ፣ በቅን ልቦና ማጣት ቀመር፣ መልስ የሚነግገን ኢትዮጵዊ ጠ/ሚኒስትርና በቀጥታ ሥርጭት ዓለም ያየውን ጥያቄ ዳግም ላለማንሳት የማይደፍር እበላ-ባይ ጋዜጠኛ የዛሬዋ ኢትዮጵያ አትሻም!!!


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1809

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>