Quantcast
Channel: Abugida Ethiopian American Amharic Web Page
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1809

ከኢሕአዴግ ጋራ በአንድነት ለመቆም ….. –ግርማ ካሳ

$
0
0

ላለፉት ሁለት ሳምንታት የኢሕአዴግ መንግስት ላይ ወርደንበታል !!!! ጥሩ ነው ያደረግነው። በተለይም ትላንትና ህዝቡ ተቃዉሞዉን ማሰማቱ በጣም አስደስቶኛል። አርክቶኛል። ሕዝብ ሲናገር መስማት የመሰለ ትልቅ ነገር የለም። ምርጫ 2007 ትላንት የተደረገ ነው የመሰለኝ። በተለየም መሪዎቹ እዚያ ቆመው፣ የሕዝቡን ፉጨትና ጩኸት መስማታቸው ጥሩ ነው። ያለዉን የሕዝቡን ስሜት በአካል መረዳታቸው፣ ምናልባት አይምሯቸው ላይ የሚጭረው ነገር ሊኖር ይችላል።

አፉን ዝም ብሎ የሚከፍተዉ፣ ዱርዬው ሬድዋን ሁሴን፣ወደዚያ ተዉትና፣ ከዶር ቴዎድሮስ አዳኖምና ከአቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ የሰማነው ነገር አለ። እንደ አይሰስ ያሉትን ለመወጋት አንድ እንሆኑ የሚል ጥሪ ነው ያቀረቡት። በተቃዋሚ ጎራው ያሉት፣ በአገር ዉስጥም ከአገር ዉጭም የሚኖሩት ኢትዮጵያዉያን ፣ እንደ አይሰስ እና አልሻባብ ያሉ በአካባቢያችን የሚንቀሳቀሱ ሽብርተኞች ላይ መዝመት እንደሚያስፈልግ ያምናሉ። ለዚያም ግፊት ያደርጋሉ። (እንደዉም እኔ ኢትዮጵያ በሶማሌያ ያላትን እንቅስቃሴ አጠናክራ ከዚያ አካባቢ ሙሉ ለሙሉ አልሻባብን ማጥፋት አለባት የሚል አቋም ነው ያለኝ) ሁላችንም፣ በአገር ጉዳይ ላይ ከኢሕአዴግ ጋር በጋራ ለመቆም፣ አንድ ሆነን ለመሰለፍ እንፈልጋለን። ነገር ግን እነርሱ ፣ ኢሕአዴግች፣ በአደባባይ ተናገሩት እንጂ፣ ፍላጎት አላቸው ወይ ? የሚለው ነው ቁልፉ ጥያቄ !!!!

ከፈለጉ በሥራቸው ያሳዩን። ቢያንስ እነርሱን የማይጎዳ፣ ግን በነርሱና በተቀረው መካከል መቀራረብን የሚያመጣ ፣ በመካከላችን ያለውን እምነት መስርቶ የሚያጠናክር፣ እርምጃዎች ይወሰዱ። አብረን እንስራ እያሉ፣ እኛ ላይ የሚዘምቱ ከሆነ፣ እነርሱን ለመመከትና ከነርሱ ለመሸሽ እንሞክራለን እንጂ እንዴት ከነርሱ ጋር አብረን እንሆናለን ?

የጸረ-ሽብርተኝነት ሕጉ
————————–
የጸረ-ሽብርተኛነት ሕግ አለ። ይሄ ሕግ እዉነተኛ ሽብርተኞች ላይ ያነጣጠረ አይደለም። በመሆኑም ሕጉ ይሻሻል። ሁለት ነገሮች በቶሎ ሊወሰዱ ይችላሉ። እነርሱም ፓርላማው ሽብርተኛ ብሎ ከፈረዳቸው ቡድኖች ዉስጥ ኦብነግ፣ ኦነግን እና ግንቦት ስባትን ሰርዞ፣ አይሰስን መክተት አንዱ ነው።

እነ ግንቦት ሰባት የመንግስት ተቃዋሚዎች እንጂ ሽብርተኞች አይደሉም። እነርሱን ሽብርተኛ ማለት የሽብርተኝነት የጭካኔ መጠን እና ትርጉም ማሳነስ ነው። አሁን አቡበከር አልባግዳዲ፣ አማን አላዛዋህሪ ያሉትና እና እነ ዶር ብርሃኑ ነጋን፣ ጀኔራል ከማል ገልቺ በአንድ መቀመጫ ማስቀመጥ፣ የነ አቡበከርን ግፍ ማሳነስ ነው።

ሁለተኛ ሕግ እንዲሻሻል ፓርላማዉ ወስኖ፣ ሕጉ እስኪሻሻል ድረስ ሕጉ ተግባራዊ እንደማይሆን መግለጽ ወይንም ሰስፔንድ ማድረግ ነው ። በተለይም የሽብርተኝነት ድርጊት የፈጸመና ሊፈጽም ሲል የተያዘ እንጂ መከሰስ ያለበት «ለመፈጸም አሰበ» በሚል ዜጎች መከሰስ የለባቸውም።

ይህ ከሆነ የታሰሩ የሕሊና እስረኞች አብዛኞቹ ይፈታሉ። ከነእስክንደር ነጋ ጀምሮ በቅርብ እስከ ታሰሩት እስከነ ብርሃኑ ድረስ። በኢሕአዴግ እና በተቃዋሚዎች መካከል ያለውን መካረር ይቀንሰዋል።

ብሄራዊ መግባባት
——————–

አገር ቤት ያሉ የተቃዋሚ ድርጅቶች በአደባባይ መዝለፍና ማስፈራራት አቁሞ፣ ከነዚህ ከተቃዋሚዎች ጋር መነጋገር ያስፈልጋል። እነርሱን የሚቃወም ሁሉ የሕዝብ ጠላት አይደለም። በአገር ጉዳይ፣ አንድ እንሁን ካሉ፣ እነርሱን የሚቃወሙትን ፣ አሳምኖና አግባባቶ ከጎን ማሰለፍ ያስፈልጋል።

የለወጥ ፈላጊው፣ እነርሱን እውቅና የነፈጉት ፣ ግን መዋቅሩን ጠብቆ ያለው የአንድነት፣ የሰማያዊ ፓርቲ፣ የትብብር፣ የመድረክ …አመራር አባላት በአገር ጉዳይ ላይ ከኢሕአዴግ ጋር አብሮ ለመስራት ፍላጎት ያላቸው ነው የሚመስለኝ። ኢሕአዴግ እነርሱን እንደ ጠላት ቆጥሮ ሊያጠፋቸው ይፈልጋል እንጂ፣ በቅንነት፣ «እስቲ ያሉንን ችግሮች እንነጋገር» ብሎ በሩን ቢከፍት ለመነጋገር ዝግጁ ናቸው።

ለምሳሌ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ፣ የመድረክ መሪ የሆኑትን ዶር መራራ ጉዲናንና ዶር በየነ ጵጥሮስን፣ የእዉነተኛው አንድነት መሪ የሆኑት አቶ በላይ ፍቃዱን እና አቶ ተክሌ በቀለን ፣ ከትብብር አቶ ግርማ በቀለን፣ ከሰማያዊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ፣ ከኢዴፓ ዶር ጫኔን ቢሯችው አስጠርተው «እስቲ ምን እናደርግ፣ አንድ ሆነን እንድንቀጥል ? » ለማለትና እንደ ወንድማማቾ በቅንንት ለመወያየት ጥያቄ ቢያቀርቡ ፣ እመኑኝ ፣ እነዚህ መሪዎች ለመነጋገር ፍቃደኛ ነው የሚሆኑት። ከድርጅቶቻቸው በላይ የአገርን ጥቅም የሚያስቀድሙ ናቸው። ግን ይሄን ለማድረግ ትልቅ እና በሳል መሆንን ይጠይቃል።

ምርጫዉ ይራዘም- ወቅቱ የምርጫ ወቅት አይደለም
———————————————————

ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ምርጫ ይደረጋል። ይህ ምርጫ ለአገር ሰላምና መረጋጋት ሲባል ቢራዘም ጥሩ ነው። የምርጫው ሂደት በጣም ተበላሽቷል። ምርጫው ተዓማኒነት ከወዲሁ አጥቷል። በዚህም ምርጫ ኢሕአዴግ አሸነፍኩ ብሎ ቢወጣ የሚያገኘው ምንም የፖለቲካ ትርፍም ሆነ ሌጂቲማሲ አይኖርም። አብይና ጠንካራ የሚባለውን ድርጅት፣ አንድነትና፣ አግዶ፣ እንደ ሰማያዊ ያሉ የበርካታ ድርጅቶች ተወዳዳሪዎችን ሰርዞ፣ ብዙ ተወዳዳሪዎችን አስሮ፣ ሜዲያውን አፍኖ የተደረገ ምርጫ የእቃ እቃ ጨዋታ ነው። አንዱ ምክንያት ይሄ ነው።

ሁለተኛዉና ዋናው ምክንያት ደግሞ፣ ምርጫዉ ሳይሆን በአሁኑ ጊዜ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ በዉጭ አደጋ ላይ ያሉ ወገኖቻችን ጉዳይ መሆኑ ነው። ሁላችንም አቶ ኃይለማሪያም እንዳሉት መረባረብ አለብን። በመሆኑም በዚህ ሁኔታ ዉስጥ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ አይቻልም። ምርጫው ዲስትራክት ሊያደርገን አይገባም። በብዙ አገሮች ብሄራው አንገብጋቢ ጉዳዮች ሲኖር ምርጫዎች የተራዘሙበት ሁኔታ አለ።

በመሆኑም አሁን ያለው አገዛዝ ለሁለት አመት ቀጥሎ፣ መስተካከል ያለባቸው ተስተካክለው (የዴሞክራሲ ተቋማትን ገለልተኛ የማድረግ ሁኔታ) ፣ ከሁለት አመት በኋላ በመልካም ሁኔታ ምርጫዉን ማድረግ ይሻላል።

እንግዲህ ከላይ እንዳልኩት፣ ኳሷ ያላችው ኢሕአዴግ አመራሮች ደጃፍ ላይ ናት። አገሪቷ ብዙ ችግሮች አላት። የግድ ኢትዮጵያዉያን መሰባሰብ አለብን። ኢትዮጵያዉያን እንዲሰባሰቡ በር መክፈት የሚችሉት ደግሞ ፣ እነርሱ ናቸው።

ያንን ማድረግ ካልቻሉ ግን፣ ማንም ሳይቀሰቅሰው ትላንትና ከትላንትና ወዲህ ተቃዋሞ ያሰማው ህዝብ እንደገና ሳያስቡት ምን ሊያደረግ እንደሚችል መገመት አለባቸው። ሊቢያ፣ ሶሪያ ከቁጥጥር ዉጭ የሆኑት ሲጀመር ጋዳፊና አሳድ ግትር በመሆናቸው ነው። በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ምሬትና ቁስል አለና፣ እርሱን ማከሙ ላይ ቢበረቱ ይሻላል። ከላይ ያስቀመጥኩት ሐሳቦች የሕዝቡን ቁስል ሊፈዉሱ የሚችሉ፣ በብሄራዊ መግባባት ላይ ያተኮሩ ጠቃሚ ሐሳቦች ናቸው።የሚቋወሟቸውን መፍራትና መጠራጠር የለባቸዉም። ሕዝቡ ከጅምሩ ፀቡ ከድርጊቶቻቸው እንጂ ከነርሱ ጋር አልነበረም። ምነው ደርግ ሲወድቅ በሩን ከፍቶ አይደለም እንዴ ሕዝቡ ያስገባችው ?

እንግዲህ አራት ኪሎ ያሉ አይኖቻቸው ይከፈት ዘንድ፣ በዚያ አካባቢ ያለውን የክፋት፣ የጭካኔና የእልህ መንፈስ ይመታ ዘንድ እጸልያለሁ። የእግዚአብሄር መንፈስ ተናግሯችው፣ ቀና ሆነው፣ ፊታቸው ወደ እግዚአብሄር መልሰው፣ ራሳቸውን ቢያዋርዱ አገር ምንኛ በተባረከች ነበር !!!
ከኢሕአዴግ ጋራ በአንድነት ለመቆም ….. – ግርማ ካሳ


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1809

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>