በሽብር ተጠርጥረው በማዕከላዊ እስር ላይ የሚገኙት እነ ሀታብሙ አያሌው ልደታ ፍ/ቤት ቀረቡ
**************************************
በማዕከላዊ እስር ቤት ከ115 ቀን እስር በኋላ ዛሬ ክስ ተመሰረተባቸው
****************************
በትላናው ዕለት አራዳ ምድብ ችሎት ይቀርባሉ ተብሎ ቢጠበቅም ሊቀርቡ ያልቻሉት የፓርቲ አመራሮች፣ በድብቅ ትላንትናውኑ ልደታ ፍ/ቤት መቅረባቸውንና ዳኛ ባለመሟላቱ ለዛሬ ጠዋት ተቀጠረው ነበር፡፡ ዛሬ ጠዋት ከታሰሩበት ማዕከላዊ ፍርድ ቤ/ት ፖሊስ አጅቦ ቢያመጣቸውም ከቀኑ በግምት 5፡00 ሰዓት አካባቢ 4ኛ ወንጀል ችሎት ካስገቡዋቸው በኋላ፣ 6፡00 ሰዓት ሲሆን ወደ መኪናቸው በመመለስ ከሰዓት በኋላ በ8፡00 ሰዓት እንደሚቀርቡ ለመጣው ታዳሚ ከችሎት አስተናጋጇ በመገለጹ፣ ከሰዓት በ 8፡00 ሠዓት 4ኛ ወንጀል ችሎት ቀረቡ፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ ችሎት መግባት ይከለከል የነበረ ሲሆን በዛሬው ዕለት ግን ታዳሚው ችሎት እንዲገባ ተፈቀደ፡፡
በችሎቱ የቀረቡት 10 ተከሳሾች ሲሆኑ እነሱም፡-
1ኛ. ተከሳሽ የአ/አ ዩኒቨርስቲ ማስትሬት ተማሪ የሆነው ወጣት ዘላለም ወርቅአገኘሁ
2ኛ. ሃብታሙ አያሌው
3ኛ. ዳንኤል ሺበሺ
4ኛ. አብርሃ ደስታ
5ኛ. የሺዋስ አሰፋ
6ኛ. ዮናታን ወልዴ
7ኛ. አብርሃም ሰለሞን
8ኛ. ሰለሞን ግርማ
9ኛ. ባህሩ ደጉ
10ኛ. ተስፋዬ ተፈሪ ናቸው፡፡
በችሎቱ ላይ 3 ዳኞች የተሰየሙ ሲሆን የመሀል ዳኛው የዘገየነው ዳኞች ባለመሟላታቸው መሆኑን ከገለጹ በኋላ ተከሳሾችን ክሱ እንደደረሳቸው ጠየቁ፡፡ ተከሳሶችም ክሱ እንዳልደረሳቸው መለሱ፡፡ ክሱ የቀረበው ጥቅምት 20 ቀን2007 ዓ.ም መሆኑን ዳኛው ከገለጹ በኋላ ክሱ እንዲታደላቸው አደረጉ፡፡
ከ1ኛ እስከ 5ኛ ያሉት ተከሳሶች አቃቤ ህግ ያቀረበባቸው ክስ ህገመንግስቱንና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ የሚንቀሳቀሰው ራሱን ግንቦት 7 የሚባለው ድርጅት አባል በመሆን ከድርጅቱ አባሎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ አባላት በመመልመል፣ ህጋዊ የፖቲካ ፓርቲን ሽፋን በማድረግ ሕዝቡ በመንግስት ላይ እምነት እንዲያጣ በማድረግ፣ በደቡብ ክልል ግጭት እንዲቀሰቀስ በማድረግ መግለጫ በመስጠት፣ እንዲሁም ትህዴን ከሚባል ድርጅት ጋር በህቡዕ ግንኙነት በመፍጠር የሽብር ተልዕኮ ለመፈጸም በዋና የወንጀል ድርጊት ተካፋይ በመሆን የተከሰሱ ሲሆን ከ6ኛ እስከ 10ኛ ድረስ ያለት ተከሳሾች ክስ ህገመንግስቱንና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ ማህበራዊ ተቋማትን ለማፈራረስ የሽብር ድርጊቱን ለመፈጸም በውጭ ሀገር በተማሩት የማህበራዊ ድህረ ገጽ አጠቃቀም የተለያዩ የፌስ ቡክ አካውንቶችን በመጠቀም ለድርጊቱ መፈጸም ሲሰሩ እንደነበር የአቃቤ ህግ ክስ ያመለክታል፡፡
እንደ ቅደም ተከተሉ ክሳቸው ተነቦ ካለቀ በኋላ ዳኛው ተከሳሾች ጠበቃ ማቆም ትችላላችሁ ወይስ መንግስት ያቁምላችሁ ብለው በጠየቁት መሰረት ከ8ኛው ተከሳሽ በስተቀር ሁሉም ጠበቃ እንደሚያቆሙ ገለጹ፡፡ ነገር ግን እኛ ጠበቃ ብናቆምም ከታሰርንበት ሀምሌ 1 ቀን ጀምሮ ከጠበቆቻችን ጋር መገናኘት አልቻልንም ክቡር ፍ/ቤቱ ልንገናኝ እንድንችል ትዕዛዝ ይስጥልን፣ እስካሁን ከታሰርንበት ማዕከላዊ ወደ ማረሚያ ቤት እንድንሄድ እንዲታዘዝልን በማለት አቶ ሀብታሙ አያሌው ለፍ/ቤቱ ጠይቋል፡፡
አቃቤ ህግ አንቀጽ ጠቅሶ በሽብር የተጠረጠረ የዋስትና መብትን አይፈቅድም ይላል በመሆኑም ተከሳሾች በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ እንደረግ ጠየቀ፡፡
ዳኛውም በዋስትና ላይ ያላችሁን አስተያየት ይዛችሁ ረቡዕ ጥቅምት 26 ከጠዋቱ በ3፡00 ሰዓት መልሳችሁን በጽሑፍ ይዛችሁ ቅረቡ ተከሳሾች በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ይደረግ በማለት ፍርድ ቤቱ አዟል፡፡