የመድረክ አመራር አባል ዶር በየነ ጴጥሮስ ፣ ከአዲስ አድማሷ ጋዜጠኛ ኤልሳቤጥ እቁባይ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ አስተያየት ሰጥተዋል። በተለይም በመድረክ ዉስጥ ስላሉት ችግሮች የተጠየቁት ዶር በየነ፣ ከአንድነት ፓርቲ ጋር ከተፈጠረው ችግር ዉጭ ሌላ ምንም ችግር መድረክ ዉስጥ እንደሌለ ገልጸዋል። በአረና ትግራይ ዉስጥ፣ ታዋቂው ታጋይ አቶ አስገዴን ጨምሮ ከአረና በለቀቁ አባላት ዙሪያ ምላሽ የሰጡት ዶር በየነ፣ አረና በድርጅቱ ደንብ መሰረት በአባላቶቹ ላይ አስፈላጊውን እርምጃ በመዉሰዱ የአረና ጉዳይ ችግር እንደሌለው ተናግረዋል።
« አንድነት ፣ ከመኢአድ ጋር የውህደት ሂደት ላይ ነው፡፡ ይህ ከመድረክ ጋር ካለው ግንኙነት አንፃር እንዴት ይታያል? » ተብለው ለተጠየቁት ዶር በየነ፣ መኢአድን ቁም ነገር የሌለውና የትእቢተኛና የትምህክተኛ ቡድን እንደሆነ በመግለጽ የአንድነት ፓርቲ ከዚህ ቁም ነገር ከሌለው ቡድን ጋር እዋሃዳለሁ ማለቱ ከመድረክ ጋር ያለዉን ግንኙነት እንዳበቃ አድርገው እንደሚያዩት ዶር በየነ ገልጸዋል።
«ይሄ ፈጽሞ የማይጣጣም ነገር ነው፡፡ የ“አንድነት” የእገዳ ጊዜ አልፏል፤ ነገር ግን አንድነት በዚህ መሀል ማሟላት ያለበትን ማሟላት እንዳልቻለ ተግባሩ ያሳያል፡፡ ልዋሀድ የሚለው አካል መኢአድ፣ ወደ መድረኩ ገብቶ እንዲጣመር በጠየቅነው ወቅት፣ “በኢትዮጵያዊነት ላይ ያላችሁን አቋም በፅሁፍ ግለፁልን” የሚል የትምክህትና የትእቢት ደብዳቤ የፃፈ ቡድን ነው፡፡ ያ አካል ከመድረክ ጋር አብሮ ሊሄድ አይችልም፡፡ ለእኛ የኢትዮጵያዊነት ሰጪና ከልካይነት፣ የትምክህት አስተሳሰብ ያለው ነውረኛ ደብዳቤ የሰጠ ድርጅት ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ቁምነገር ከሌለው ቡድን ጋር ጊዜያችንን አናባክንም ብለን ትተነዋል፡፡ በእኔ ግምገማ፣ አንድነት ከመኢአድ ጋር እዋሃዳለሁ ማለቱ፣ ከመድረክ ጋር ያለው ግንኙነት እንዳበቃ ነው የሚያሳየው፡፡ መድረክን ከሚኮንን ወገን ጋር መዋሃድ ማለት ምን ማለት ነው? መድረክን መኮነን ማለት ነው፡» የሚል ምላሽ ነበር ዶር በየነ የሰጡት።