መምህራኑ በዛሬው ዕለት በመቀሌ ከተማ የተለያዩ አዳራሾች ተሰብስበው በ3 አጀንዳዎች ላይ እንደሚወያዩ የተገለጸላቸው ሲሆን አጀንዳዎቹም፡-
1 . ስለተሃድሶ መስመራችንና የኢትዮጵያ ህዳሴ
2 . ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችንና ፈተናው
3 . የትምህርት ጥራትና ማነቆዎቹ
የሚሉ ሲሆን ስብሰባው የሚቀጥለው ለ 7 ቀን እንደሆነና ቅዳሜና እሁድንም እንደሚጨምር ከመድረኩ መሪዎች ተገለጸላቸው፡፡ መምህራኑም ” እኛ ቅዳሜና እሁድ መሰብሰብ አንፈልግም ማረፍ አለብን:: በተጨማሪም እናንተ እየዞራችሁ ስትሰበስቡ አበል እንደምትወስዱት እኛም አበል ያስፈልገናል:: አበል አለው ወይ? ” የሚል ጥያቄ መምህራኖቹ አንስተዋል፡፡
ከመድረኩ መሪዎች አቶ ወልዳይ አሰፋ የመቀሌ ዞን ፀጥታ ኃላፊ እና አቶ ተካላይ የአዲሃውፂ ክፍለከተማ አስተዳደር የተሰጣቸው ምላሽ ” እኛ ወንድሞቻችን በረሃ ወጥተው ለሰላምና ዲሞክራሲ ብለው ታግለው ህይወታቸውን ሰውተዋል:: እናንተ ግን ለአንድ ሳምንት ለሚቆይ ስልጠና አበል ትጠይቃላችሁ ? እኛ አስተማሪዎችን፣ የፍትህ አካላት፣ አነስተኛና ጥቃቅን እና ሌሎችንም እንሰበስባለን:: ስብሰባው አገር አቀፍ ነው:: ለዚህ ሁሉ አበል ሰጥተን እንዴት እንችላለን ? ዓላማችን አንድ ነው :: ለምንድን ነው አበል የምትጠይቁት ? ” በማለት ሊያሳምኑ ሞከሩ ::
“ነገር ግን መምህራኑ “እኛ ጋ ሲደርስ ነው በጀት የሚያጥራችሁ ? እናንተ ግን በሀገሪቱ ሀብት እንደፈለጋችሁ ትጠቀማላችሁ ” በማለት የተቃወመ ሲሆን “ነገ መምጣት አለባችሁ” በሚል ኃይለቃል ከመድረኩ ቢገለጽም ስልጠናው ባለመስማማት ተበትኖዋል ሲል የመቀሌ የዜና ምንጫችን ለፍኖተ ነፃነት ዝግጅት ክፍል ገልጾዋል፡፡