ከሽህ ጦረኛ አንድ ወረኛ ትጥቅ ያስፈታል! በበርናባስ ገብረማሪያም
በዝግ ችሎት ይሁን/ አይሁን በሚል ከርክር ያስነሳው እና በሚዲያ የምስክሮች ቃል እንዳይዘብ የተከለከለው የእነሀብታሙ፣ አብርሃ …የፍርድ ቤት ዘገባ
የሺዋስ አሰፋ ከተቀመጠበት አልነሳም አለ
‹‹ምስክሬ ላይ ዛቻ እና ድብደባ ስለተፈጸመ ምስክርነቱ በዝግ ችሎት ይሁን›› አቃቤ ሕግ
‹‹በማስረጃ ባልተረጋገጠ አቤቱታ ችሎት በዝግ ሊታይ አይገባም›› የተከሳሽ ጠበቆች
‹‹ሞት የሚያስቀጣ ክስ ቀርቦብን ጉዳያችን በአደባባይ መታየት አለበት፤ እናንተ ብቻ አይደላችሁም ፈራጆች…›› ዳንኤል ሺበሺ
‹‹ምስክርነቱ በዝግ ችሎት የሚታይ ከሆነ ዛሬውኑ የምትፈርዱብንን ተቀብለን ለመመለስ ዝግጁ ነን›› ሀብታሙ አያሌው
‹‹የአቃቤ ህግን አቤቱታ በማስረጃ ያልተደገፈ በመሆኑ አልተቀበልነውም፤ የምስክሮች ስምና ቃል ግን በሚዲያ እንዳይዘገብ ወስነናል›› ችሎቱ
————-
ዛሬ፣ ዛሬ ሰኔ 01 ቀን 2007 ዓ.ም በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት በእነዘላለም ወርቅአፈራሁ የክስ መዝገብ የተከከሱ 10 ሰዎች ጉዳይ ታይቶ ነበር፡፡ መዝገቡ የተቀጠረው አቃቤ ህግን ምስክሮች ለማድመጥ እና የአቃቤ ህግን ባቀረባቸው ተጨማሪ አቤቱታዎች ላይ ውሳኔ ለመስጠት መሆኑን ከችሎቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ተከሰሾች በቀደም ተከተል ስማቸው እየተጠራ ሲቆሙ የሺዋስ አሰፋ ከመቀመጫው አልነሳም ብሎ ነበር፡፡ የቀኝ ዳኛው ተነስ ቢለውም የሺዋስ በሀሳቡ ጸንቶ አልተነሳም፡፡
አቃቤ ህግ ካስመዘገባቸው 15 ምስክሮች መካከል 12ቱን ዛሬ ማቅረብ የቻለ ቢሆንም ‹‹በአንደኛ ምስክር ላይ ዛቻ እና ድብደባ ስለተፈጸመ፣ እንዲሁም የሁሉንም ምስርክሮች ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ምስክርነቱ በዝግ ችሎት ይደረግልን›› ሲሉ አቶ ብርሃኑ ወንድማገኝ አቤቱታቸውን አሰምተው ነበር፡፡ ተከሰሾች 3 ጠበቆች የነበሯቸው በመሆኑ ከ1ኛ-5ኛ ተራ ቁጥር ድረስ የተከሳሾች ጠበቃ የሆኑት አቶ ተማም አባቡልጉ የአቃቤ ሕግን አቤቱታ እንዲህ በማለት ተቃውመዋል፡-
‹‹ችሎት አስተማሪ በመሆኑ በግልጽ ይታይ ዘንድ መርህ ነው፡፡ ችሎት ዝግ የሚሆነው በተለየ መንገድ ነው፡፡ በሕገ-መንግሥቱ ይህንን በተመለከተ ተደንግጓል፡፡ የችሎት ዝግ መሆን ሊፈቀድ ቢችል እንኳን በማስረጃ ተረጋግጦ መሆን ይኖርበታል፡፡ አቃቤ ሕግ ያቀረበው አቤቱታ በማስረጃ ዘርዝሮ የት፣ መቼ፣ እንዴት የሚለውን አላቀረበም፡፡ ችሎት በአቤቱታ ብቻ አይዘጋም፡፡ በማስረጃ ባልተረጋጋጠበት ሁኔታ ፍርድ ቤቱ ሊፈቅድ አይገባምና የአቃቤ ህግ አቤቱታ ውድቅ ይደረግልን፡፡››
የተቀሩት ሁለት ጠበቆችም በተመሳሳይ መልኩ የአቃቤ ህግን አቤቱታ ተቃውመዋል፡፡
የቀድሞ አንድነት አመራር የነበረው አቶ ዳንኤል ሺበሺም እጁን በማውጣት እንደምንም ካስፈቀደ በኋላ፤ ‹‹ሞት የሚያስቀጣ ክስ ቀርቦብን ጉዳያችን በዝግ መታየት የለበትም፡፡ በአደባባይ ሊታይ ይገባል፤ እናንተ ብቻ አይደላችሁም ፈራጆች፤ ሁሉም ይፍረድ፡፡ ሁሉም ይፈርዳል›› ብሏል፡፡
አቶ ሀብታሙ አያሌውም እንዲናገር ጠበቃ ተማም ለዳኞቹ ተናግረው ሀብታሙ ‹‹አቃቤ ህግ ክስ ሲመሰርትብን በዝርዝር የምስክርችን ስም አልገለጸም፡፡ እኛ ዋስትና ተከልልለን በእስር ላይ ነው የምንገኘው፡፡ ምስክሮችን ልናውቅ የምንችልበት ዕድል ዝግ ነበር፡፡ ዛሬ ገና ነው በከፊል ምስክሮችን እዚህ ያየናቸው፡፡ አቃቤ ህግ ‹ምስክሮቼ ዛቻ ደረሰባቸው፣ ተደበደቡ› ካለ ሊጠየቅ የሚገባው እሱ ነው፡፡ ማነው በጀርባ ያለው? እኛ ከእስር ቤት ሆነን እንዴት ብለን ልናስፈራራ እንችላለን? ይሄ ከአየር ላይ የመጣ ፍረጃ ሲሆን የተፈጸመ ነገር ካለ በግልጽ ይታይ፡፡ የተባለው ነገር በማስረጃ ቀርቦ እንጂ በግምት ሊሆን አይገባም፡፡ ፍርድ ቤቱ ‹በዝግ ችሎት ሂደቱ ይታይ› ብሎ የሚወስን ከሆነ ዛሬውኑ የምትፈርዱብንን ተቀብለን ለመመለስ ዝግጁ ነን፡፡ አቃቤ ህግም ሆነ እናንተ የግፍ እስረኞች መሆናችንን ታውቃላችሁ ብለን እናስባለን፡፡›› ሲል ተናግሯል፡፡
ሶስቱም ዳኞች ‹‹የአቃቤ ህግን አቤቱታና በተከሳሾች በኩል የቀረበውን አስተያየት በጽ/ቤት ተመካክረን ተመልሰን እንወስናል›› ብለው ከችሎት ወጥተው ከ30 ደቂቃ በኋላ በመመለስ ጉዳዩን መመርመራቸውን የቀኝ ዳኛው ገልጸው፤ ችሎት በዝግ የሚታይበትን ሁኔታ በህገ-መንግሥቱና በሌሎች ህጎች ላይ የተደነገጉትን ፍሬ ነገሮች በመዘርዘር ‹‹የአቃቤ ህግን አቤቱታ በማስረጃ ያልተደገፈ በመሆኑ አልተቀበልነውም፤ የምስክሮች ስምና ቃል ግን በህተመት እና በኤሌክትሮኒኪስ ሚዲያ እንዳይዘገብ ወስነናል›› የሚል መልስ ከሰጡ በኋላ ምስክሮችን ወደማድመጥ ሂደት ገብተዋል፡፡ የቃቤ ህግን ምስክሮች የማድመጥ ሂደት እስከፊታችን ሐሙስ ሰኔ 04 ቀን 2007 ዓ.ም ዕለት ድረስ እንደሚዘልቅ ዳኞች ተናግረዋል፡፡
ግልጽ ደብዳቤ ለጥላሁን ገሰሰ ቤተሰቦች ንዋይ ደመረ
ከሁሉም በማስቀደም የከበረ ሰላምታዬ በያላችሁበት ይድረሳችሁ። በዋነኛነት ይህንን ደብዳቤ ልጽፍ ያነሳሳኝ ሰሞኑን በአንድ በጥላሁን ገሰሰ ስም የሚነግድ “መስፍን” በዙ የተባለ ተራና ስብእና የጎደለው አጭበርባሪ ግልሰብ ታማኝ በየነ ለምን ክብርና ሽልማት አገኘ በሚል በአደባባይ “ታማኝ በየነ ገዳይ እና ከፋፋይ” ነው ከማለት አልፎ ግለሰቡ በጥላሁን ገሰሰ ስም (Tilahun Gesesse TV / TGTV) በሚለቀው እውር ድንብሩ በወጣ ቪዲዮ ወያኔን አወድሶ ለአገራቸው መልካም የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያንን ስም ለማጠልሸት ጥረት ሲያደርግ በተደጋጋሚ በማየቴ ነው።
እንደሚታወቀው ታላቁ የሙዚቃ ንጉስ ጥላሁን ገሰሰ በኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክ ውስጥ ልዩ ስፍራ ይዞ የሚገኘው ጊዜ በማይሽራቸው የጥበብ ስራዎቹ ብቻ ሳይሆን ለአገሩና ለህዝቡ በነበረው ጥልቅና ልባዊ ፍቅር እንደ ነበር ጭምር ማንም የሚያውቀው ሃቅ ነው። ጥላሁን ከፍቅር ባሻገር፣ በርካታ ግዙፍ መልእክት ያላቸው ዘፈኖችን እንዲሁም ልብ ውስጥ በልዩ ተሰጥኦው ጣእም ባላቸው ዜማዎቹ ዘልቆ በመግባት የአገርና የህዝብ ፍቅርን እና አንድነትን አስርጿል ብል ፈጽሞ ማጋነን እንደማይሆንብኝ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፉ ስራዎቹ ይመሰክራሉ። ስለዚህም ነው እኔም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የጥላሁንም ይሁን የቤተሰቡ ስም ያለ አግባቡ በተራ ሁኔታ በየመንገዱ ሲነሳ እና ጭቃ ሲቀባ ማየት የሚከነክነኝ።
ምንም እንኳን ጥላሁን በአካል ቢያልፍም ከኢትዮጵያ ህዝብ ፍቅርና ክብርን የተጎናጸፈባቸው በርካታ ስራዎቹን ትቶልን ስላለፈ የዚህን ታላቅ ኢትዮጵያዊ መልካም ስም፣ ታሪክና ቅርስ መጠበቅ የሁላችንም ድርሻ ቢሆንም በተለይ እናንተ የቅርብ ቤተሰቦቹ ከፍተኛ ሃላፊነት እንዳለባችሁ እውን ነው። ይህንን ደብዳቤ ልጽፍላችሁም ያነሳሳኝን ጉዳይ ሳቀርብ እናንተም ሆናችሁ የጥላሁን ገሰሰ ክብርና ስም ያለአግባቡ እንዳይነሳ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥታችሁ መፍትሄ እንደምታፈላልጉለት በመተማመን ነው።
የጥላሁን ገሰሰ ባለቤት የነበሩት የወ/ሮ ሮማን በዙ ወንድም እንደሆነ በየአጋጣሚው የሚያውጀው “መስፍን በዙ”የተባለው ይህ ግለሰብ ይህን ታላቅ ኢትዮጵያዊ በተለያዩ መንገዶች ለማስታወስና ለመዘከር ሲነሳ ከጥላሁን ክብር፣ ዝናና ደረጃ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ስራ ማቅረብ እንደሚጠበቅበት የአደባባይ ሚስጢር ነው። ይሁንና ባለፍት ጥቂት አመታት “መስፍን በዙ” Tilahun Gessese TV / TGTV በሚል ስም እራሱ ደንቁሮ ሌሎችን ለማደናቆር መጣጣሩ ብቻ ሳይሆ የጥላሁንን ገሰሰን ስም በየአደባባዩ ማቆሸሹ አስተዛዛቢ ሆኗል።
ይሄው ግለሰብ ጥላሁን ገሰሰን በቪዲዮ ስርጭት ለመዘከር መንቀሳቀሱ መልካም ቢሆንም ከጥላሁን ስብእና፣ እምነት፣ ስምና ክብር ጋር ሙሉ በሙሉ በሚጻረር መልኩ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ አስከፊ ግፍ፣ ወንጀልና ዘረፋ ከሚፈጽሙት አንባገነኖች ለሚወረወርለት ዳረጎት ህሊናውን ሽጦ አሳፋሪ ስራ በጥላሁን ገሰሰ ስም በመስራት ላይ መሆኑን ለማወቅ ግዜ የሚፈጅ ጉዳይ አይደለም። በእርግጥ ግለሰቡ እንኳን በሌላው ኢትዮጵያዊ ወያኔዎቹም የሚቀልዱበትና የሚሳለቁበት ስለሆነ በህይወቱ ክብደት ያለው ቁምነገር ተናግሮ ፋይዳ ያለው ለውጥ ያመጣል ብሎ ማንም እደማይጠብቅ ግልጽ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ግለሰቡ የሚታወቀው በኪሳራ (bankruptcy) ህይወቱን መምራት የተሳነው በተቀጠረበትም ይሁን በተገኘበት ሁሉ እንደክፉ ውሻ የሚባረር የተጠላና ተራ ሰው በመሆኑ ለእርሱ በቀጥታ መልስ መስጠት እራስን ማዋረድ ነው የሚል እምነት አለኝ።
“ውሸት ለመናገር አትሻም ምላሴ” እያለ ጥላሁንን እያዘፈነ በውሸት እና በማደናገር ላይ ያተኮረ አሳፋሪና ከንቱ ስራ እንዴት ጥላሁንን ሊዘክር እንደሚችል ትልቅ እንቆቅልሽ ነው። ሆድ ለመሙላት ሲባል በህዝባችን ላይ ተዘርዝሮ የማያልቅ ወንጀል ዘውትር የሚፈጽሙ አንባገነኖችን አወድሶ የሚኖር ሰው ስለ እውነት በአደባባይ ቆሞ ሲዘፍን እና ሲያዘፍን ማየት አስቂኝም አሳዛኝም ጉዳይ ነው።
ለእውነት የቆመ ማንም ሰው ጥላሁን ከአጼ ሃይለስላሴ ዘመን ጀምሮ እስከ ህልፈተ ህይወቱ የአገሩን ህዝብ ጉስቁልና፣ እረሃብ፣ ፍትህ መነፈግና የነጻነት እጦት በሚችለው አጋጣሚ ሁሉ አጉልቶ ለማሳየት ሲያደርግ የነበረውን ጥረት ሊዘነጋ አይችልም። ለእውነት የቆመ ሰው ከሆዱ ይልቅ ለህሊናው ይገዛል። ለእውነት የቆመ ሰው የህዝቡ ህመም ይሰማዋል፣ ግፍ፣ ሰቆቃው፣ ግድያ፣ ስደትና ጉስቁልናው ሁሉ ያመዋል። ለእውነት የቆመ ሰው ወገኖቹ በሃሰት እየተወነጀሉ በየአደባባዩ ሲገደሉ በየእስር ቤቱ ከቤተሰቦቻቸው እና ልጆቻቸው ተለይተው ሲሰቃዩ አላየሁም አልሰማሁም ብሎ ዘወትር ይህን ሁሉ ወንጀል የሚፈጽሙ ዘረኞችና ፋሺስቶችን ሲያወድስ የሃሰት እድገት፣ ፍትህና ሰላም ሲዘክር ግዜውን አያጠፋም። ለእውነት የቆመ ሰው ህሊናውን እንደሸቀጥ ለሳንቲምና ለፍርፋሪ አደባባይ አውጥቶ አይቸረችርም። ለእውነት የቆመ ሰው አላዋቂነቱን እንደ እውቀት ይዞ አደባባይ እየወጣ አስምስሎ አይኖርም። ታዲያ ይሄ ግለሰብ የሚሰራው እርካሽ ስራ እየታወቀ ጥላሁን ገሰሰን አክብሮ ሊያስከብረው የተነሳው ምን ቁም ነገር ይዞ ነው? መልሱን ለእናንተ እተወዋለሁ።
ለታማኝ በየነ መከበርና መሸለም አዲስ ነገር አይደለም። ታማኝ ለምን በወገኖቹ ዘንድ እንደሚከበር የታወቀ ጉዳይ ስለሆነ ድምጽ አልባ ለሆነ ህዝብ ድምጽ የሆነ ሰው በመሆኑ ለእውነት፣ ለፍትህ፣ ለመብትና ለነጻነት ለሚደረገው መራራ ትግል ያበረከተውን አስተዋጽኦ መዘርዘር ለቀባሪው አረዱት ስለሆነ መዘርዘር አያስፈልገኝም። ይሁንና እርካሹና በውሸትና በማጭበርበር የገለማው ግለሰብ መሰሎቼን አስተባብሬ “ታማኝን የተቃወምኩት ገዳይና ከፋፋይ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን በጥላሁን ገሰሰ ላይ ከፍተኛ ክህደት በመፈጸሙ ነው” ብሏል። ይህ እርካሽ ክስ ማንን እንመን አያስብልም። መስፍን በዙ የህይወት አቅጣጫ የጠፋበት፣ ከቻይና ሳይቀር በህገወጥ ድርጊቱ የተባረረ መልካም ስብእናና ጤንነት የጎደለው ለእውነት ሳይሆን ለርካሽ ፍርፋሪ የሚሯሯጥ አጭበርብሮ እና ውሸትን ቸርችሮ ከርሱን የሚሞላ ግለሰብ ስለሆነ የእርሱን ከንቱ ክስ ወደ ጎን ተወት አድርገን የተከበረችው የጥላሁን ገሰሰ ልጅ ወ/ሮ ንፁህ ብር ጥላሁን ስለ ታማኝ በየነ በአደባባይ የተናገረችውን ወደሁዋላ መለስ ብለን እናስታውስ።
የዛሬ አራት አመት በዋሺንግተን ዲሲ ለታማኝ ልዩ የክብር ስነስርአት ተዘጋጅቶ ነበር። በዛ የክብር ስነስርአት የሰውን ሁሉ ቀልብ የሳበ ንግግር ከማረግ በላይ አባቷ ከአገሯ ስትወጣ የሰጣትን ቀለበት ለማስታወሻነት ጥላሁን እንደ ልጁ ለሚያየው ለታማኝ በእንባ ታጅባ ማስረከቧ በቪዲዮ ተቀርጾ በአለም ዙሪያ የታየ ሃቅ ነው። ወ/ሮ ንፁህ ብር ጥላሁን ልጄ ነው የሚለውን ታምኝ ያደረገውን ውለታ በጥቂቱ ከዘረዘረች በሁዋላ እንዲ ነበር ያለቸው፣
“ሌላ የማደርገው ነገር የለም። ግን በአባትነቱ ከአገር ስወጣ ጥላሁንዬ ኤርፖርት ላይ መጨረሻ ጠርቶ ከእጁ አውልቆ የጣቱን ወርቅ ሰጥቶኛል። ይሄን የሰጠኝን ስጦታ እኔ ደግሞ ታማኝን እጅግ አድርጌ ስለምወደው ታማኝ ጥላሁንዬ ባይወልደውም የእርሱ ልጅ መሆኑን አረጋግጦለት የሄደውን ይሄን ስጦታ ለእርሱ አሳልፌ እሰጣለሁ።”
ይሁንና መስፍን በዙ የተባለው ይሄ ርካሽ ግለሰብ የቅናት መሆኑ ግልጽ በሆነ መልኩ ሶስት በርካሽ እና ተራ ክስ የተሞላ ቪዲዮ ሰርቶ በማሰራጨት የታማኝን ስም ለማጥፋት ሙከራ አድርጓል። የሚያሳዝነው ደግሞ ይሄንኑ የቪዲዮ ቆሻሻ የዛሬ ሶስት አመት ገደማ የለቀቀው በጥላሁን ገሰሰ ስም (Tilahun Gesesse TV / TG TV) ብሎ በሰየመው የወያኔ መጠቀሚያ የቪድዮ ቆሻሻ አሸንዳ መሆኑ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ለኮሚዩኒቲ አገልግሎት በነጻ ለማህበረሰብ ጥቅም እንዲውል በተቋቋመው የሜሪላንድ ሞጎሜሪ ኮሚዩኒቲ ሜድያ በኩልም አሰራጭቷል። በእርግጥ የኮምዩንቲው ድክመት እንጂ በኢትዮጵያውያን ስም እንዲህ አይነት የረከሰና ተራ ፕሮፓጋንዳ ሊሰርሰራጭ አይገባም ነበር።
ሌላው ከሰሞኑ ያሰራጨው ቪዲዮ የቀድሞው አንባገነን መለስ ዘናዊን እንደጣኦት ያመልኩ የነበሩ የህወሃት ጀሌዎችና አጋፋሪዎቻቸው በአለም መሪዎች ፊት ጣኦታችንን አዋረድክ በሚል ስሜት በጋዜጠኛ አበበ ገላው ላይ በተቀነባበረ መልኩ ከፍተኛ የሆነ ዛቻ፣ የስም ማጥፋት እና አደገኛ ቅስቀሳ ላይ ተጠምደው እንደነበር የማይዘነጋ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ቢያንስ የተወሰነኑትን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ እንቅስቃሴ ለማድረግና የራሱንም ሆነ የቤተሰቡን ደህንነት ለማስጠበቅ ብዙም ባይሆን ገንዘብ መሰባሰቡ መስፍን በዙ እንዳለው አዲስ ግኝት ሳይሆን በይፋ የተከናወነ የአደባባይ ሚስጥር ነው።
በዚህ በሰለጠነው አለም ማንም ሰው ህጋዊ እርምጃ ሲወስድ በሚስጥር ሳይሆን በአደባባይ ነው። እኔ በቀላሉ ማረጋገጥ የቻልኩት ሀቅ አበበ ገላው የህገ ወጡ ቅስቀሳ መሪ ተዋናይ የሆኑትን የአይጋውን ኢሳይስ አባይና ነዋሪነቱ በአትላንታ የሆነ ተባባሪው ላይ በካሊፎርንያ ሳንታ ክላራ እና በአትላንታ ደክላብ ካውንቲ ፍርድ ቤቶች ክስ መስርቶ ‘ንደነበር ማንም በቀላሉ ሊያጣራው የሚችለው ሃቅ ነው። በተጨማሪም ተቀመጭነቱ አትላንታ የሆነው ጠበቃ ዲክሰን ጄምስ [Georgia Bar No. 003989] አበበን የወከለው ሌላውን ወጪ ሳይጨምር በሰአት 250 ዶላር (ያውም በቅናሽ) እየተከፈለው እንደነበር ጠይቆ መረዳት ይቻል ነበር። መስፍን በዙ አላማው ስም ማጥፋት ስለሆነ ብቻ ፈጽሞ በማይመለከተው ጉዳይ የማያውቀውን ዲስኩር ሲያሰማ ታዝበናል።
በአሁኑ ግዜ ክሱም የተቅዋረጠው እንደውም በቂ ገንዘብ ባለመሰባሰቡ እንደሆነ እኔ በበኩሌ የማውቀው ሃቅ ነው። አላዋቂ ሳሚ እንዲሉ አንባገነኑ መለስ አልደነገጠም ታንክ ተደግፎ መጻሃፍ ያነብ ነበር FBI የግድያ ሴራ አላከሸፍኩም አለ ምናም በማለት ለዘባረቀው ከሃቅ የራቀ ዲስኩር እውነቱ ስለሚናገር ማንም መልስ ሊሰጠው አይገባም ብዬ አምናለሁ። ይሁንና በሃሰት የተከሰሰ ግለሰብ ካለ ታዲያ ለምን ወደ ፍርድ ቤት ጎራ ብሎ ባልፈጸምኩት ወንጀል ስሜ ጠፋ ብሎ አይከስም፣ FBIስ ቢሆን ብስሙ ሐሰት ሲሰራጭ እንዴት ዝም አለ። ይሁንና መስፍን በዙ በጥላሁን ገሰሰ ስም እነዚህ ጉዳዮች ውስጥ ምን ያገባዋል። በጥላሁን ስም ከመዘባረቅ ለምን በራሱ ስም አይዘባርቅም። መሰረታዊውን እውነታም ቢሆን የጉዳዩ ባለቤት የሆነው ጉሽ አበራም በአደባባይ ለመካድ አልደፈረም።
እነዚህን ጉዳዮች ከብዙው በጥቂቱ ያነሳሁት ግለሰቡ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘንድ በተከበረውና በታላቁ የሙዚቃ ንጉስ በጥላሁን ገሰሰ ስም ተራ እና እርካሽ ፕሮፓጋንዳ እንዳይሰራጭ እንድታደርጉ በትህትና ለመጠየቅ እወዳለሁ። ይሄንን መስፍን በዙ የተባለ ማፈሪያ ግለሰብም ቢያንስ እህቱ ወ/ሮ ሮማን በዙ ለርሳቸውና ለመላው ቤተሰቡ በጥላሁን ገሰሰ ስም መነገድ እና እርካሽ እና አስተዛዛቢ ስራ ከመስራት እንዲቆጠብ እንደሚያደርጉ እተማመናለሁ። ሁሉም በራሱ ስም ይነግድ።
ቸር ይግጠመን!
የስደቱን መከራ ወደ ምፍትሔ መፈለጊያ እድልነት መቀየር ይቻላል? የመነሻ ሀሳቦች (ፈቃደ ሸዋቀና)
ማስታወሻ ፥ (የዚህን ጽሁፍ መሰረታዊ ይዘት በቅርቡ በተካሔደው ኢሳት ባዘጋጀው ጉባዔ ላይ አቅርቤው ነበር። የኢትዮጵያን ሁኔታዎች አዘውትሮ እንደሚከታተል ኢትዮጵያዊ በሀገራችን የሰፈነው ዘግናኝ ድህነት የፈጠረውን አሳዛኝና አዋራጅ ስደትና ወደፊትም መፍትሔ ካልተበጀ ሊፈጥር የሚችለውን ችግር ገምቼ የባሰ ድህነት ውስጥም ሳንዘፈቅ ችግሩን ምን ብናደርግ ነው መቋቋም የሚቻለው በሚለው ጥያቄ ላይ ሳሰላስል የመጣልኝ ሀሳብ ነው። የሰጠሁት የመፍትሄ ሃሳብ በጉባዔው ላይ ትንሽ አቧራ አስነስቶ ነበር። አንዳንዶችም የየዋህ ሀሳብ አድርገው ወስደውታል። እኔ ችግር ማውራትና ማማረር የሰለቸኝ ሰው ነኝ። ብሶት በባዶ ከማውራት ብዬ የመሰለኝንና ብዙ ዋጋ ሳያስከፍል የችግራችን መፍትሄ ይሆናል ያልኩትን ሀሳብ ነው አቅርቤ ውይይት መቀስቀስ የሞከርኩት። የሌሎችን ሀሳብ ማየትና መከራከር እፈልጋለሁ። ሀሳቤን በተሻለ ሀሳብ ለመለወጥ ዝግጁ ነኝ። የማነሳው ሀሳብ ስራ ላይ የሚውል አለመምሰሉ ይገባኛል። ሙከራዬ የመፍትሄውን ሀሳብ ከማርቀቅ ይልቅ ማዋቀር ላይ ይበልጥ ያተኮረ ነው። የተሟላ ለመሆን ብዙ ውይይት ይጠይቃል። ሀሳቡ ስራ ላይ የሚውለው ተገቢውን በቂ አቅም ገንብቶ በገዥው ሀይል ላይ ተጽዕኖ በመፍጠር እንጂ በልምምጥና ለቅንነት አቤት በማለት ብቻ አይደለም። በዚህ ሀሳቤ ላይ ሊሞግቱኝ የፈለጉ ሰዎች የኔን ሀሳብ ማንጓጠጥ ብቻ ሳይሆን ይህ የኔ ሀሳብ በምን ቢተካ የተሻለ እንደሚሆን የማስረዳት እዳ እንዳለባቸው ሊያውቁ ይገባል። ያን ጊዜ ነው ክርክራችን ትርጉም የሚኖረው።)
መግቢያ፥
ችግሩን አጉልቶ ያሳየን መታረድ ላይ መድረሳችን እንደሆነ እንጂ በስደት የሚደርስብንን ውርደትና ሰቆቃ መመዝገብ ከጀመርን ከርመናል። በየአረብ አገሩ እህት ወንድሞቻችን የሚደርስባቸው መከራ ፣ ወገኖቻችን ስደት ሀገር ከመግባታቸው በፊት መንገድ ላይ ስለሚደርሰው አልቂትና ስቃይ መስማት ከጀመርን ቆይተናል። ሀዘናችን ውስጣችን ድረስ የተሰማንን ያህል በሁላችንም ጭንቅላት ውስጥ የሚጉላሉት ጥያቄዎች አልተመለሱልንም። ይህ ሰቆቃ የመጨረሻው ለመሆኑ ምን ዋስትና አለ? ነገ የባሰ የሚሰቀጥጠን ነገር እንደማይመጣስ በምን ማረጋገጥ ይቻላል? ለምንድነው ከመከራ የማይማር ህዝብ የሆነው? በአለም ዙሪያ ያሉ ማህበረሰቦች አንድ ችግር ደህና አድርጎ ከደቆሳቸው በኋላ ሁለተኛ እንዳይደግማቸው ችግሩን መማሪያ አድርገው መፍትሔ ሲያበጁለት እናያለን። እኛ ተመሳሳይ ችግር እየደጋገመ ሲመታን ዝም ብለን የምንቀጥለው ለምንድነው? ችጋር ህዝባችንን በየጊዜው እየተመላለሰ የቀጠቀጠው ከመጀመሪያው እልቂት መማር ስለተሳነን አይደል? ለመሆኑ ሰደት በተስቦ (epidemic) ደረጃ በሀገራችን እንዲሰፍን ያደረገው መሰረታዊ መንስዔ ምንድነው? መፍትሔውስ? በኔ እምነት ብርቱ ህዝብነታችን የሚለካው ለነዚህ ጥያቄዎች የሚያዋጣ መልስ ፈልገን ስናገኝ ነው። ብዙ ህዝቦች መጥፎ አጋጣሚን ወደ ዘላቂ ችግር መፍቻ ዕድል (opportunity) ይቀይሩታል። እኛ ብዙ ተመሳሳይ ነገር እያጋጠመን አበላሽተነዋል። ይህንንም በቅርቡ የደረሰብንን ውርደትና ሀዘን ባናበለሸው ጥሩ ነው። ኢትዮጵያ በርሀብተኛነት ከደረሰባት የገጽታ ብልሽት ባልተናነሰ በስደተኛ ህዝብ ሀገርነትም ገጽታዋ ክፉኛ እየተበላሸ ነው።
ባለንበት ዘመን ስደት በብዙ ሀገሮች አዲስ ነገር አይደለም። የብዙ ሀገር ሰዎች ወደሌላ ሀገር ይሰደዳሉ። የስደቱ ዓይነትና መጠን ግን በጅጉ ይለያያል። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴዎድሮስ አድሀኖም በቅርቡ ባንድ ክርክር ላይ የኛውን ችግር ለማቅለል በሚመስል መንገድ ስደት አሜሪካኖችም ይሰደዳሉ ሲሉ ሰምቻለሁ። የሰዎችን ከሀገር ሀገር መጓዝና መኖር ሁሉ ስደት በሚል ስም በመጥራት አንድ ለማድረግ መሞከር አሜሪካኖች እንደሚሉት አፕልና ኦሬንጅ ማደባለቅ ነው። ስደት ሁሉ አንድ አይነት አይደለም። ቢያንስ የብዙ ሀገሮች ስደተኞች እንደኛው ሀገር ሞትና ህይወት ሀምሳ/ሀምሳ ሰጥተው የሚጓዙበትና የሚዋረዱበት አይነት አይደለም። የኛ ስደት በመጠንም በዓይነትም ብዙ ተወዳዳሪ የሌለው በጅጉ አደገኛና አዋራጅ ነው። ከሳውዲ አረቢያ ዜጎቻችን በዚያ ቁጥርና ጊዜ ውስጥ የተባረሩበት ሁኔታ በአለም ላይ ተወዳደሪ የሌለው ሬኮርድ ነው። የኛ ሀገር ስደት ስር የሰደደ የክፉ ችግር ምልክት ነው። “ስደት በሁሉም ሀገር አለ” በሚል መሸንገያ ራሳችንን ማታለል አንችልም። ከዚህ ቀደም ጋለፕ (Gallup) የተባለ የህዝብ አስተያየት ተመራማሪና አጥኚ ተቋም በኢትዮጵያ መሰደድ የሚፈልገው ወጣት 46% እንደሚሆን ነግሮን ነበር። ለዝርዘሩ (ይህን ይመልከቱ)። ከሀገራችን ወጣት እኩሌታው ያህል ስደትን የሚመኝ መሆኑን ስናይ ሀገሪቱ ላይ እንድ ትልቅ ህመም እንዳለ አለመገንዘብ ሞኝኘት ነው። ከላይ እንዳልኩት የኛ ስደት በወረርሽኝ (epidemic) ደረጃ ላይ ያለ ነው። የሚሰደደው ሁሉም አይነት ሰው ነው። የተማረ ፣ ያልተማረ ፣ ባለስልጣንና ስልጣን የሌለው ሁሉ የሰደዳል። ከሰው ጋር ሀገሪቱ በጥረት የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ ሁሉ ከሀገር ሲወጣም እያየን ነው። እኤአ ከ2000 እስክ 2009 ባለው ጊዜ ውስጥ 11.7 ቢሊዮን ዶላር ሀገር ጥሎ መውጣቱ ተነግሮናል (ይህን ይመልከቱ)። ይህ ለኛ አይነት ድህነት ለሚፈነጭበት ሀገር ቀላል ኪሳራ አይደለም። ይህ ሀገር ውስጥ ያለ ሁሉ ወደ ውጭ ይበልጥ ሲያይ የሚመጣ ነገር ነው። አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የፈረንጅ ስም የወጣላቸውን ሆቴሎች ፣ የቁርስ ቤቶች ፣ መዋዕለ ህጻናትና ሌሎች ተቋሞችን ልብ ብሎ ላየ ከተማዋ ራሷ እዚያው ሆና የተሰደደች ትመስላለች ። የስኬት (Success) መለኪያችን ራሳችንን ትተን ውጭ ሀገር መምሰል ሲጀምር ነው ስደት ባህል መሆኑን የምንረዳው። ይህ ፈጽሞ የጤነኛ ሀገርነት ምልክት አይደለም። የመዘዘኛ መጭ ጊዜ ጠቋሚ እንጂ።
በኔ እምነት አደገኛ ሰደትንና ሀገራችንን ያንፈራጠጠባትን ባለብዙ ፈርጅ ችግር ማሰወገድ የሚቻለው በስፋት የሚተባበር መንግስትና ህዝብ መፍጠር የሚቻልበት ሁኔታ ሲኖር ፣ ሐገሪቱ ለዜጎቿ የምታጓጓ (Attractive) ሀገር ስትሆንና የተረጋጋ ህይወትም ሊኖርባት የምትችል ሀገር ካደረግናት ብቻ ነው። የሃሳቤ ማጠንጠኛ ይህ ነው። ያንድ ሀገር ሰዎች የፖለቲካና የሀሳብ ልዩነትን ሁሉ የጠላትነት ግንኙነት እያደረግን እስከወሰድን ድረስ መከራችን የሚያባራበት ጊዜ አይኖርም። በተለይ የሀገሪቱ ልሂቃን የህዝቡና የሀገር ጥቅም ላይ የማንስማማ ከሆነ የፈረሰ ሀገር ላይ ለመኖር እንደወሰንን ይቆጠራል። የማይስማሙ ሰዎች አጥፊና ጠፊ ሳይሆኑ የሚኖሩበት ስርዓት ካልገነባን የሀገሪቱ ችግር ፈች ሁሉ ስደተኛ ወይም አመጸኛ ነው የሚሆነው። ባለንበት ዘመን ወጣትና የተማረ የሰው ሀይል ለስደት እየገበሩ ፣ በዜግነቱ የማይተማመንና የማይመካ ዜጋ እያበራከቱ ሀገር እገነባለሁ ህዝብ ከድህነት አወጣለሁ ማለት ደግሞ ከንቱ ወሬ ነው። ይህ ብቻም አይደለም። ማንኛውም ችግር አድጎ አድጎ የመጨረሻ የመገንፈል ደረጃ ላይ ይደርሳል። ያን ጊዜ ደግሞ መፍትሔ ለማግኘት በጣም ይመሻል። ከመሸ በኋላ ችግር ሊፈቱ የሞከሩ ሀገሮች የደረሰባቸውን ደግሞ አይተናል።
ከማርክሳዊ አስተሳሰብ ጋር የወሰድነውና ያልለቀቀን የፖለቲካ “መስመር” የሚባል ግንዛቤና በዚያ መስመር ላይ ያልተሰለፈ ሁሉ እንደ ጠላት ወይም አንድ ቀን ሊያጠቃን እያደባ እንደተቀመጠ ጠላት አደርጎ የመቁጠር ፖለቲካ ኋላ ቀርና መቆም ያለበት ነው። ትንሽና ብዙ ጉዳት የማያስከትሉ ተቃውሞ ያሰሙና ትችት የሰነዘሩ ሰዎችን ሁሉ ማሰር ማዋከብና መጉዳት የሚመጣው በዚህ ብልሹ አስተሳሰብ ምክንያት ነው። ችግራችንን ለመቋቋም ከልብ ከወሰንን የማንስማማ ሰዎች ሆነንም እዚች አገር ላይ ሳንጠፋፋ አብረን ለመኖር ፈቃደኞች መሆን ይኖርብናል።
አሁን ይታያል የሚባለው መንግስትም የሚመካበት የኢኮኖሚ እድገት ብዙሃኑን ተጠቃሚ ማድረግ ቀርቶ ተስፋ እንኳን መፍጠር አልቻለም። የምንሰደድበት ቁጥርና አይነት የሚመሰክረው ይህንን ነው። አልጀዚራ ድረ ገጽ ላይ በቅርቡ ይህን የታዘበ ጽሁፍ አይቼ ነበር። እንዲህ ይላል – “If Ethiopia is so vibrant, why are young people leaving? “ኢትዮጵያ በጥሩ ሁኔታ እየለማች ከሆነ ወጣቶቿ ለምን የሰደዳሉ? ዝርዝሩንና የሰጠውን መልስ (እዚህ ይመልከቱት)። ያሁኑ የኢኮኖሚ ዕድገት መጠንና ፍጥነት የሚባለውን ያህል ይሁንም አይሁን ካለብን ችግር ጋር የሚመጣጠን ካለመሆኑም በላይ ቀጣይ (sustainable) መሆኑ አጠራጣሪ ነው። አሁንም በብዙ መንገድ በርዳታ ከመኖር ያልተላቀቅን ሀገር ነን። ይህ ርዳታም ቀጣይ መሆኑ አጠራጣሪ ነው። ሀገሪቱ ላይ በስፋት የሚካሄዱት እንደ መንገድና ህንጻ ኮንስትራክሽን ያሉት ኢንቨስትሜንቶች በራሳቸው ሌላ ሀብት ፈጣሪ (wealth creator) አይደሉም። ሀብት ፈጣሪ ኢንዱስትሪ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚያዋጣው ድርሻ ገና 12% አካባቢ ነው። ማዕድን ማውጣትና ጥሬ ሀብትን ወደ ሸቀጥነት የሚለውጡ ኢንቨስትሜንቶች በችግራችን መጠን እያደጉ አይደለም። አሁን እየተመዘገበ ነው የሚባለው እድገት ፍጥነቱም ብዛቱም በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ወለል ላይ ከመሆናችን ጋር እየተለካ እንጂ የምናፈራው ሀብት ብዙ ስለሆነ አይደለም። እንደ ኢትዮጵያ ያለ ድሀ አገር በ 10% አድጎ የሚያገኘው ሀብት ትንሽ የዳበሩ ሀገሮች በ 1% እደገት የሚያገኙት ሀብት መጠን አጠገብ በሩቁ እንኳን የሚጠጋ አይደለም። የእድገት አሀዝ እየጠቀሱ ራስንም ሌሎችንም ረጅም ጊዜ ማታለል አይቻልም። በያመቱ ብዙ ተማሪዎች ከኮሌጅ ማስመረቅን እንደ ጥሩ ነገር ማውራት ይቻላል። ጥሩ ነገርም ነው። ምሩቃኑ ራሳቸውንም ሀገርንም የሚጠቅም ስራ ካልሰሩ የወጣባቸው ገንዘብ ሁሉ የሀገር ኪሳራ ነው። በዚህ ቁጥር መኩራራት ከግርጌው የተሸነቆረን በርሜል ውሀ ለመሙላት ስንት ጣሳ ውሀ እንደተጠቀምን ከመቁጠር አይለይም። ስደትን ማቆሚያው ዋና ዘዴ ሰዎችን በበቂ የሚያኖር ስራ መፍጠር ነው። ባለሞያዎች እንደሚነግሩን ባለንበት እንኳን ለመሄድ በየዓመቱ ከሁለት ሚሊዮን ተኩል ያላነሱ ስራዎች ሀገሪቱ ውስጥ መፈጠር አለባቸው። ባጭር አነጋገር ብዙ የሀገሪቱ ሶሺዎ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ሁኔታዎች ዙሪያቸው አያምርም።
የስደታችን መሰረታዊ መንስዔዎች ምንድን ናቸው?
መፍትሔ ፍለጋ ላይ ብዙ ጊዜ የምንሳሳተው የችግሩን መንስዔ አንድ ብቸኛ ምክንያት ላይ ልንደፈድፈው ስንሞክር የመስለኛል። ብዙ ይህን ጥያቄ የማነሳላቸው ወንድም እህቶች የችግሩ ምክንያት መንግስታችን የሚከተለው አካሄድና ፖሊሲ ነው ይላሉ። በኔ እምነት ይህ ከችግሩ አንዱ ምናልባትም ዋነኛው ቢሆን እንጂ ሁሉም አይመስለኝም። የስደት ችግራችን ባለብዙ ምክንያት (multivariate) ይመስለኛል። ችግሩን የምንረዳውም የምንቀይረውም ክፍት አእምሮ ይዞ በመመርመርና እንደማህበረሰብ ውስጣችን የተዋቀሩ የኑሮ ዘይቤዎችን በመረዳት ነው።
ስለስደት ስንነጋገር ስለየትኛው አይነት ስደት እንደምንነጋገር መለየት ይኖርብናል። ስደት አለም አቀፍ ጉዳይ ከሆነ ስለቆየ ሙሉ ለሙሉ ማስቆም አይቻልም። እንዲቆም የምንፈልገው በወረርሽኝ (Epidemic) ደረጃ ያለውንና ዛሬ በኛ ሀገር ያለውን አይነት አደገኛውንና አዋራጁን ብቻ ነው። ሀገሪቱ በድህነቷ ለፍታ ያፈራችውንና ለወደፊቱ በዓለም ተወዳዳሪ ሊያደርጋት የሚችለውን የተማረ የሰው ሀይል እንዳይሰደድ ማድረግም ለዕድል የማይተው ነገር ነው።
ለስደት “ገፊ” ና “ሳቢ” ምክንያቶች (Push and Pull factors) አሉት። ችግሩን የምናገኘው እነዚህን ገፊና ሳቢ የስደት ምክንያቶቻችና ሁለቱ በኢትዮጵያ ያላቸውን መስተጋብር ጠንቅቀን ስናውቅ ነው። ይህ ጠለቅ ባለ ጥናት ብቻ ሊተነተን የሚችል ነው። እኔ እዚህ የምሰጠው አስተያየት ለመነሻ የሚሆን ግርድፍ ዕይት ብቻ ነው።
በግርድፉ የሚከተሉት ነገሮች ከኛ ሀገር ጋር የተያያዙ ዋና የስደት ምክንያቶች ተብለው ይቆጠራሉ።
1. አሀዛዊ መለኪያ አስቀምጠን መመጠን ባንችልም ትልቁ የሀገራችን ገፊ የስደት ምክንያት ድህነት ነው። ድህነትም ከተስፋ ጋር ካለ በራሱ ገፊ ምክንያት ላይሆን ይችላል። ሰዎች ቀያቸውን ትተው የሚሰደዱት ተስፋ ሲቆርጡ ነው። ነገ የተሻለ ቀን የሚመጣ ከመሰላቸው ላይሰደዱ ይችላሉ ማለት ነው። በኛ ሀገር ለብዙሃኑ በተለይ ለወጣቶች የተስፋ ጭላንጭል የማይታይበት የድህነት ጨለማ ነግሷል። ስራ አጥነት በተለይ በወጣቶች ዘንድ ትልቁ የስደት ምክንያት መሆኑን ብዙዎቻችን እናውቃለን። ለአመታት ተምረው ስራ ያጡ ወጣቶች ስራ ማጣት ብቻ ሳይሆን ምንም ሰርተው ያልፍልናል ብለው መገመት ሲያቅታቸው ስደቱ የሚያመጣውን አደጋ ሁሉ ለመቀበል ተዘጋጅተው የሚገቡበት ብዙ ናቸው። ሞትና ህይወትን አማራጭ አስቀምጠው የሚሰደዱት ወገኖቻችን በሀገራቸው ፍጹም ተስፋ የቆረጡት ናቸው። በቅርቡ በሊቢያ ለአሰቃቂ አደጋ የተዳረጉት ውንድሞቻችንና እሁን በሞትና ህይወት መሀል የሚገኙት ሊቢያና የመን ያሉት ስደተኞች ብዙዎቹ እነዚህ ይመስሉኛል።
2. የህግ የበላይነት ባልሰፈነበትና ህግ መከታ ይሆነኛል ብሎ የማይተማመን የፖለቲካ ተቃዋሚም ሆነ ከመንግስት የተለየ አስተያየት ስላለኝ በመንግስት እጠቃለሁ ብሎ የሚፈራ ሰው አንዱ ዋና ምርጫው ስደት ነው። ህግ ሊያስጥለኝ ይችላል ብለው ባለመተማመን ብቻ ሀገርም ህዝብም ባልጎዱበት ምክንያት የተሰደዱ ብዙ ኢትዮጵያውያን እናውቃለን።
3. አንዳንድ ወጣቶች ምንም ብንማር እንኳን መንግስት የሚያካሂደውን ለፖለቲካ ታማኞቹ ቅድሚያ የመስጠት መድሎ ማለፍ አስቸጋሪ ነው እያሉ ሲናገሩ በተደጋጋሚ ይሰማል። መጠኑን ባላውቀውም እንዲህ አይነት አሰራር ለብዙ ወጣቶች ተስፋ መቁረጥ ምክንያት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። እንዲህ አይነት መድሎ የሀገር ባለቤትነት ስሜትን ያጠፋል። እንደኛ ሀገር መንግስት ዋናው ስራ ቀጣሪ በሆነበትና የግል ከፍለ ኢኮኖሚ ድርሻ በጣም ዝቅተኛ በሆነበት ሀገር ደግሞ ይህ ከባድ ገፊ የስደት ምክንያት ነው።
4. ሀገራችን በብሄረሰቦች ክልል መከፋፈሏና ከሱ ጋር ተያይዞ የዳበረው ክልሉ ያካባቢው ቋንቋ ተናጋሪ ብቻ ነው የሚለው አስተሳሰብ ዜጎች ሀገራቸው ውስጥ እንደልባቸው ተዘዋውረው የተሻለ ህይወት ለመፈለግ አይበረታቱም። እንደምንሰማው እንዱ ሌላ ክልል ሲገባ ብዙ የዜግነት መብቶቹን ሁሉ ማጣት ብቻ ሳይሆን ባዕድ ነኝ የሚል ፍርሀትና ሀብት አፍርቶ ተረጋግቶ መኖር የማይቻል ስለሚመስለው ከዚህ ሁሉ ከሀገር ወጥቼ እድሌን ልሞክር ወደሚል አስተሳሰብ ይገፋፋል።
5. በሀገራችን ብዙውን ሰው በሚያስተዳድረው የሚታረስ መሬት ላይ በየጊዜው በሚጨምረው የህዝብ ቁጥር ምክንያት ያንድ ሰው ይዞታ እያነሰ በመሄድ ላይ ይገኛል። ይህም ብዙ የገጠር ነዋሪዎች ወደ ተጣበበው ከተማና ከዚያም አልፈው ወደ ውጭ መሰደድን እንዲመርጡ አድርጓቸዋል። በዚህ ላይ የመሬት ይዞታ ባለቤትነት ርግጠኝነት ስለሌለ ብዙ ገበሬዎች የመሬቱ ይዞታ ቢያንስም ምርታማ ለማድረግ እንዲበረቱ አያደፋፍራቸውም።
6. ሌላው ገፊ ምክንያት ባካባቢ እርስ በርስ ግጭት ወይም ከመንግስት ጋር በሚደረግ የታጠቀ ግጭት በሚደርስ ህይወትና ንብረት ውድመት የአካባቢ ለመኖሪያ አለመመቸት ወይም አደገኛነት የሚከሰተው ነው። ኦጋዴን አካባቢ ያለው ይህ ይመስለኛል።
7. የመንግስት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ሌላ ምክንያቶች መሆናቸውንም እንሰማለን። ለምሳሌ ከጋምቤላ አካባቢ መንግስት በተከተላቸው መሬት አፈናቃይ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ምክንያት ያካባቢው ነዋሪዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውንና ወደ ጎረቤት ሀገር መሰደዳቸውንም እንሰማለን።
8. ብዙ ሰዎች ለወደፊቱ ረጅም ዘመን ሀገሪቱ አስተማማኝ መሰረት ላይ ነች ብለው አያምኑም። ነገ አለመረጋጋትና ችግር ሊመጣ ይችላል ብለው የሚፈሩ ሀብታሞች ሳይቀሩ ልጆቻቸውን ስደት ይልካሉ። ልጆቻቸው የሌላ ሀገር ዜግነት እንዲያገኙ ሚስቶቻቸውን ሌላ ሀገር እንዲወልዱ ያደርጋሉ። ገንዘባቸውንም ወደ ውጭ ያሸሻሉ። ይህ ስልጣን ላይ ያሉ ሰዎችንም የሚጨምር የስደት ዓይነት እንደሆነ በሰፊው ይነገራል።
9. በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ባንጻራዊ ደረጃ ያገኙት የተሻለ ኑሮና ሀብት ለብዙዎች ላልተሰደዱ ወገኖች በሞዴልነት ያገለግላል። ውጭ ሀገር በመኖር ባገኙት ዕድል ወዳጅ ዘመድ ሲረዱ የሚታዩ ወጣቶች ለብዙ ችግሩ ላልባሰባቸው ወጣቶች ሁሉ ሳይቀር አርዓያ የመሆን ባህሪ እንዳላቸው ይገመታል። ይህ የስደት “ሳቢ” ምክንያት ካልነው ውስጥ የሚመደብ ነው።
10. ብዙ ወጣቶች በደፈናው ፈረንጅ ሀገር ተሰዶ መኖር የላቀ ስብዕና የሚጨምርላቸው ይመስላቸዋል። ምዕራብ ሀገር ተሰዶ መኖርን እንደ ህይወት ስኬት ይመለከቱታል። ሀገር ቤት ቢያንስ ጀማሪ የንግድ ተቋም ለማስጀመር የሚችል ወጭ እያወጡ የሚሰደዱ አሉ። የነዚህ የስደት ምክንያት ችግር የፈጠረው ነው ማለት አይቻልም።
በኔ አተያይ እነዚህ ከላይ ያነሳኋቸው ምክንያቶች በተናጠል ወይም ተደራርበው የስደት ችግራችንን መጠንና አደገኝነት ያገዘፉት ይመስለኛል።
የችግሩ የመፍትሄ መጀመሪያ ሀገሪቱ ውስጥ ፖለቲካዊ ዕርቅና መረጋጋት ማስፈን ነው
ከላይ እንዳነሳሁት ብዙዎቹ የመፍትሔ መንገዶች ቁርጠኛ የፖለቲካ ፈቃደኝነትና ውሳኔ የሚጠይቁ ናቸው። በተለይ የሰላምና ዕርቅ መንገድ ከራስ በላይ ለሀገራዊ ጥቅም ቅድሚያ መስጠትን ይጠይቃል። ዕርቅ የሚያጓጓና የሚፈለግ እንዲሆን የፖለቲካ ተቀናቃኝና ታራቂ ወገኖች የሚያገኙት ጥቅምም መኖሩን ማረጋገጥ ያሻል። ከሁሉ በላይ ደግሞ የሰላምና ዕርቅን አካሄድ መከተል አደገኛ ከሆነ የሀይል መፍትሄ አካሄድ ሊመጣ የሚችለውን አደጋ ማስቀረት መሆኑ ሊገባን ይገባል። በህዝባዊና የታጠቀ አመጽ ከሚመጣ ለውጥ በተለይ ገዥዎች ሁሉንም ነገር ነው የሚያጡት። ስልጡኑና አውሬያዊ ያልሆነው መንገድ ስልጣን ላይ ያሉትም ተቃዋሚዎቹም ያልለመዱትን ትብብር ለመፍጠር ማግባቢያ (Incentive) የሚሆን ለሁሉም ወገን እንዲኖር ማድረግ ይመስለኛል። ለመንግስትም ለህዝብም እንድ ቀን ብዙ ሂሳብ የሚያስከፍለውን አስገዳጅ መፍትሄ በግድ ከመቀበል የተወሰኑ ነገሮችን እጥቶ ዋናውን ነገር ማስቀረት በጅጉ ይመረጣል። የሰሜን አፍሪካና እንዳንድ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገሮች መሪዎችና ልሂቃን ይህን በጊዜ ባለማድረጋቸው ነው ራሳቸውንም ሀገራቸውንም ቀውስ ላይ የጣሉት።
እዚህ እንደ መፍትሔ የማቀርበው ሀሳብ የየዋህ ሀሳብ ሊመስል ይችላል። ራስ ወዳድነትን ፣ ስልጣን ወዳድነትንና ለስልጣን መግደልንና መሞትን ማየት የለመደ ህብረተሰብ ውስጥ ይህ ሀሳብ የዋህነት መምሰሉ አያስገርምም። ችግሩን እንደ ህልውና ችግር አድርጎ ለሚመለከትና ሁሉም ወገን አሸናፊ የሚሆንበትን መንገድ ጠቁሞ መፍትሔ ማበጀት የዋህነት አይደለም። የዋሆቹ ችግሩ የማይደርስ መስሏቸው ራሳቸውን የሚያታልሉት ናቸው። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሀይሎች አሁን ባሉበት መንገድ ከቀጠሉ ችግሩ እየባሰ መሄዱ የሚቀር አይመስለኝም። በመሸናነፍና መንግስትን በሀይል በመለወጥ ችግሩ የሚሻሻል ከሆነም መጀመሪያ ተባብሶና ብዙ ቀውስ ፈጥሮ ነው የሚሆነው። ከሁላችንም ወገን በተለይ መንግስት ከሚመራው ኢሕአዴግ በኩል ችግሩን ለመፍታት የሚበጅ የፖለቲካ ፈቃደኝነት ከሌለ ሁላችንም አደገኛ ጥግ ውስጥ ነን።
መንግስት ስልጣን ላይ ያለው ኢህአዴግ ቢያንስ ስልጣኔን በሐይል ለመቀናቀን በቂ አቅም ያለው የፖለቲካ ድርጅትም ሆነ ስብስብ በሌለበት ሁኔታ ወደ እርቅና ሰላም ድርድር ውስጥ መግባት አያስፈልገኝም ብሎ ሊያስብ እንደሚችል መገመት አያደግትም። እስካሁንም የቀረቡ የሰላምና ዕርቅ ጥያቄዎችን ያልተቀበለው አቀበላለሁ ሲልም በኔ መንገድ ብቻ የሚለው በዚህ ምክንያት ይመስለኛል። የመጀመሪያ የሰላምና ዕርቅ ሙከራ ከተደረገባቸው አመታት ይልቅ አሁን ጥያቄውን ትልቅ ቦታ የሚሰጡት የተለዩ ሁኔታዎች የተፈጠሩ ይመስለኛል። ዛሬ ገዥው ሀይል ሊፈራቸውም የሚገባ ሁኔታዎች ይበልጥ ይታያሉ። ከዚህ አካሄድ ብዙ እንደሚጠቀም የሚያሳዩት ምልክቶችም ብዙ ናቸው። የሰላምና ዕርቅ መንገድ በታሪክ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ተግባር ከመሆን በዘለለ በሀይል ከስልጣን ከመውረድ ጋር ተያይዞ ከሚመጣው እስከ ልጆችና የልጅ ልጆች ድረስ ከሚጎዳ ነገርም ይታደጋል። መንግስትን የሚመሩና የሚደግፉ ሁሉ የሚከተሉትን ልብ ሊሉ ይገባል።
1. አሁን ያለው የድህነትና የሩሮ ውድነት ሁኔታ እየተባባሰ እንደሚሄድ የሚያመለክቱ ጠቋሚዎች በብዛት አሉ። ኢኮኖሚው አሁን ያለበት አቅጣጫ የሚያሳየው ይህንን ነው። የሚቆጣ ህዝብ ብዛት በአይነትም በቁጥርም እየጨመረ መሄዱ አይቀርም። ይህ ቁጣ በማንኛውም ማህበረሰብ ውስጥ እንደምናየው ዓይነት ሀገር ለመናጥና መንግስት ለማናወጥ የሚችል ሀይል (critical mass) አንድ ወቅት ላይ ማፍራቱ አይቀርም። የዛሬው ዝምታ ያቺ ወሳኝ ምዕረፍ መድረሻዋን እየጠበቀች መሆኑን ብቻ ነው ሊነግረን የሚችለው። ይህን ሰፊ የህዝብ መነሳሳት በጉልበት ለማቆም ከባድ ይሆናል። ቢሞከርም ትርፉ ታሪክ ይቅር የማይለው ጥፋት ማድረስ ብቻ ነው።
2. ዘመኑ የኢንፎርሜሽን ዘመን ነው። ህዝቡን ለማነሳሳትና ለማደራጀት እያንዳንዱ ቤት ሊገባ የሚችል ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክ መሳሪያ በብዛት አለ። የሳትላይት ቴሌቪዥኖች ሬዲዮዎችና የኢንተርኔት መስመሮች ህዝብ መቀስቀሻም ማደራጃም መሆናቸው የማይቀር ነው። እነዚህ ነገሮች ህዝቡን ከማነሳሳት አልፈው ጉልበት ሊፈጥሩለት (Empower ሊያደርጉት) ሁሉ ይችላሉ።
3. ገዥው ፓርቲ አሁን በፍጥነት እያደገ ነው በሚባለው ኢኮኖሚ ህዝቡን አማልላለሁ ብሎ አስቦም ከሆነ እንደማይቻል ካሁኑ እየታየ መሆኑ ግልጽ ነው። አንደኛ ነገር የኢኮኖሚ እድገት ፍጥነትና መጠን አንድ አይነት ነገር አይደለም። ስለዕድገት ብዙ እየተወራ ቢሆንም የኢኮኖሚውን እድገት ውጤት ባብዛኛው ህዝብ የቤት ውስጥ ኑሮ ላይ ሊንጸባረቅ አለመቻሉ የሚፈጥረው የምሬት ስሜት እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው። ሐገሪቱ ላይ ለውጥ እንዳለ ቢመለከትም ብዙው ራሱን የጥቂት በዪዎች ተመልካች አድርጎ ነው የሚቆጥረው። ይህ ዛሬ እያየነው ያለና በፕሮፓጋንዳና የህዝብ ግንኙነት ስራ ሊለወጥ የማይችል ነው።
4. በሀገራችን ሙስናና ንቅዘት በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ ላይ መሆኑን ብዙ ሰዎች የሚመሰክሩት ነው። በቅርቡ እንድ ወዳጄ የመንግስት ግብር በሰአቱ ለማስገባት ግለሰቦች ጉቦ አስከመስጠት መድረሳቸውን አጫውቶኛል። ይህ ከመንግስት አሰራር ቅልጥፍና ተፈጥሮአዊ ጉድለት (ineficiency) ጋር ተያይዞ በህዝቡ ውስጥ ምሬት እየፈጠረ በመሄድ ላይ መሆኑን ልብ ይሏል። የህዝቡ ማጉረምረም ጮክ ብሎ አልተሰማ ከሆነ በፍርሀት ምክንያት እንጂ ችግር ስለሌለ አለመሆኑን ማወቅ ብልህነት ነው።
5. በብዙ መረጃና አንዳንድ ጊዜም በምናበ እይታ (perception) ደረጃ ሀገሪቱን ያንድ ብሄረሰብ ልሂቅ መጠቀሚያ ሆናለች ሲባል የምንሰማው ያደባባይ ሀሜት አንድምታውም መዘዙም ቀላል አይደለም። በየማህበራዊ መገናኛ ብዙሃኑ የጥላቻ የመጠቃትና ይቁጭት አስተያየት ሲሰነዘር መስማት የተለመደ ሆኗል። ይህንን ጥላቻ መጥፎ ነገር ነው በማለት ብቻ ወይም ይህ አመለካከት ያላቸውን ሰዎች በማናናቅ እንዲቆም ማድረግ አይቻልም። ይህን የሚሉት ደግሞ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ አለማቀፍ ተደማጭነት ያላቸው ተቋሞች ሁሉ ናቸው። ፍሪደም ሀውስ የተባለው ተቋም ለምሳሌ በዘንድሮው ሪፖርቱ እንዲህ ይላል። “The government tends to favor Tigrayan ethnic interests in economic and political matters, and the EPRDF is dominated by the Tigrayan People’s Liberation Front”. ለዝርዝሩ (ይህን ይመልከቱ)። ዘ ኢኮኖሚስት የሚባለው ታዋቂ መጽሄትም በቅርብ ጊዜ እትሙ እንዲህ ብሎ ነበር። “.. ethnic Tigrayans, of whom Meles was one, still control the army, security services, telecoms and foreign affairs”. (ይህን ይመልከቱ)። በእንደኛ አይነት ሀገሮች እንዲህ አይነት አስተሳሰብ የሚያመጣውን መዘዝ አይተናል። ይህን ሁላችንም በተለይ የመንግስት ስልጣን የሚያክልን ነገር የያዙ ሰዎች ሊፈሩና ሊጨነቁ ይገባል።
6. ብዙ ጠቋሚዎች እንደሚያመለክቱት በሀገራችን የመንግስት ፍራቻና ጥላቻ እየጨመረ ነው። የህግ አስተዳደር (Rule of law) ላይ ብዙ ሰው ተስፋ እየቆረጠ ነው። የመከፋቱ ደረጃ የሰላማዊም ይሁን የሀይል አማራጭ ለመረጡ የፖለቲክ ሀይሎች ትልቅ ድጋፍ መሰብሰቢያ መሳሪያ ሆኖ ማገልገሉ የማይቀር ነው። ጋዜጠኞችን በማሰር ከአፍሪካ አንደኛ ሆናችኋል ሲባልና በእስር ላይ ባሉ ዜጎች ላይ ይፈጸማል እየተባለ ስለምንሰማው ስቃይ (ቶርቸር) ሲሰሙ የመንግስት ባለስልጣኖች ብዙ የጥፋት ርቀት እንደተጓዙ የተገነዘቡ አይመስሉም። በዚህ ዓመት (2015) የወጣው የፍሪደም ሀውስ ሪፖርት ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉ 49 ያፍሪካ ሀገሮች በሰብዓዊ መብት ይዞታዋና በሲቪል ነጻነት 43ኛ ሆና ተመዝግባለች። አለማቀፍ መህበረሰብም ይህን ስዕል እያየ ትዕግስት እያጣ በመሄድ ላይ ያለ ይመስላል። ይህ አስተያየት የኢትዮጵያን መንግስት ገላጭ አስተያየት (narative) እየሆነ በመሄድ ላይ ይገኛል።
7. በየጎረቤት ሀገሩ ያሉ ችግሩን በሀይል እንፈታለን ብለው የተነሱ ሀይሎች በቀላሉ ድጋፍ ሊፈጥርላቸው የሚችል ምሬትና ሊደግፋቸው ወይም ሊቀላቀላቸው የሚፈልግ ህዝብ በተለይ ወጣት በብዛት መኖሩን መንግስት እንደ አደጋ ሊያየው ይገባል። ሞትና ህይወት እኩል ዕድል ባለበት ሁኔታ ውስጥ ስደትን የሚመርጥ ወጣት መንግስትን ተዋግቼ አውርጄ የተሻለ ቀን አመጣለሁ ብሎ እንዲያምን ከተደረገ አይኑን ሳያሽ ሊገባበት ይችላል። ከ 30 ዓመት ዕድሜ በታች ያለው ወጣት ከሀገሪቱ ሕዝብ 70 በመቶ መሆኑን ደሞ ልብ ይሏል። ጥያቄው በዚህ ፍልሚያ ማን ያሸንፋል የሚል አይደለም። ይልቁን በግጭት መጠመድ በራሱ የሚያስከትለውን ድቀት ነው አብዝቶ ማጤን።
8. ኢሕአዴግ ስልጣን ላይ ሩብ ምዕተ ዓመት ቆይቷል። ይህ ረጅም የስልጣን ዘመን ነው። አሁን ያሉት ባለስልጣኖች የሰሯትን ስራ ሁሉ ከቀድሞ ገዥዎች ጋር እያወዳደሩ ለመመጻደቅ የሚመች አይደለም። አብዛኛው አሁን በኢትዮጵያ የሚኖረው ህዝብ የደርግን ዘመን እንኩዋን በቅጡ አያውቅም። የኢሕአዴግ አካሔድ አስቀድሞ የሚታወቅ (predictable) ሆኗል። ካሁን በኋላ እያደገ ሳይሆን እየደከመና እየተሰለቸ ለውጥና አዲስ ነገር ለመሞከር የሚፈልገው ህዝብ ቁጥር እየጨመረ መሄዱ አይቀርም። ፍጹም ነጻ የሆነ ምርጫ በኢትዮጵያ ዛሬ ቢካሄድ ኢህአዴግ ማሸነፍ የሚችልበት ሁኔታ የለም።
ሰሞኑን የተካሄደው አይነት ፍጹም አሳፋሪና አግላይ (Exclusionary) ምርጫ ለጊዜው ለገዥው ፓርቲ ጊዜያዊ የቁጥጥር ጉልበት ያሳይ እንደሆን እንጂ የህዝብን ዘላቂ ፈቃደኝነት የሚያሳይ አይደለም። የምርጫው አሰራርና ውጤቱ በተለይ አንድ ላምስት የሚባለው ቀፋፊ አሰራር ከመካከለኛው ዘመን የባሪያ ፍንገላ ዘዴዎች ብዙም አይለይም። የዘንድሮ ምርጫ በተለይ ውጤቱ የጠቀመው ካለ ይህን መንግስት በሀይል ከማስወገድ ውጭ አማራጭ የለም ለሚሉ ሀይሎች ነው። በዚህ የምርጫ ውጤት ብዙ ነገር ያጣ ካለ አሸነፍኩ ያለን ገዥ ፓርቲ እንጂ ሌላ ማንም አይደለም። ሌላው ቀርቶ ወዳጅና ለጋሽ ተባባሪ ሀገሮች አፍንጫቸውን ይዘው እንኳን ለመቀበል እያንገዳገዳቸው መሆኑን እያየን ነው።
በነዚህና በሌሎችም ብዙ ምክንያቶች ገዥው ፓርቲ አስካሁን የያዝኩት መንገድ የጎላ ማሻሻያ ሳላደርግ ካለእክልና አደጋ መቀጠል እችላለሁ ብሎ ካሰበ ራሱንም የሚጎዳ ትልቅ ስህተት ነው የሚሰራው። በተለይ መሪዎቹ ለልጅ የልጅ ልጆቻቸው የሚተርፍ ችግር ነው ትተው የሚሄዱት። በመሆኑም በሰላምና ዕርቅ መንገድ ብዙ ነገሮችን የሚያተርፍ ካለ በስልጣን ላይ ያሉት ናቸው። ከላይ ባነሳኋቸው ምክንያቶች እንዴውም ገዥው የፖለቲካ ሀይል ለዕርቅና ዕርቅ ለሚፈጥራቸው ሪፎርሞች ከተቃዋሚዎቹ ያልተናነሰ ፍላጎት ሊኖረው ይገባል። ፖለቲካዊ አቅማቸው ምን ያህል እንደሆነ ባይታወቅም ቢያንስ ይህን ለማሰብ የሚችሉ ሰዎች ኢህአዴግ ውስጥ የሉም ለማለት ይከብዳል።
ስላምና ዕርቅን የሚፈጥሩ ሁኔታዎችን መፍጠር
የችግሩ መፍቻ ማስተር ቁልፍ ያለው በሀገሪቱ ጉዳይ ላይ ወሳኝ ሀይል በመያዙ ምክንያት መንግስትን የሚመራው የፖለቲካ ሀይል ህወሀት/ኢህአዴግ ጋ ነው። እስካሁን ያለው አግላይ ፖለቲካ የሀገሪቱን አቅም አሰባስቦ ዘላቂ የኢኮኖሚ ለውጥ ለማምጣት አልረዳም። ይዋል ይደር እንጂ ሰፊ አለመረጋጋትም መፈጠሩም አይቀርም። በውጭም ሀገር ውስጥም ያለው የኢትዮጵያውያን ሀብት በገፍ ተሰብስቦ ሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ችግር ለመመከቻ የሚውልበትን አስቸኳይ መንገድ መፈለግ ትልቁ የመንግስት ስራ ሊሆን ይገባል። ይህ ማለት ሀገሪቱን ከባዕዳን ይልቅ ለራሷ ተወላጆች የምታጓጓ (attractive) ማድረግ ያስፈልጋል ማለት ነው። መንግስትም ተቃዋሚም ህዝብም ይህንን ችግር እንደ አስቸኳይ ጊዜ (emergency) ችግር አድርገን መቁጥርም ይኖርብናል። ቀጠሮ ከሰጠነው በጥፋቱ ላይ መቀጠልን የመስማማት ያህል አደረግነው ማለት ነው። ለዚህ የሚከተሉት ዋና ዋና እምነቶችና ርምጃዎች ጠቃሚ ይመስሉኛል።
1. የኢሕአዴግ መንግስት በተለያየ መንገድ ተጣልቶ የወነጀላቸውንና ከሀገር የወጡትን የፖለቲካ መሪዎችና ድርጅቶች እንዲሁም ባንድ ምክንያት ወይም በሌላ መንግስት ይተናኮለኛል ብለው ለሚያስቡ ግለሰቦች ሁሉ አጠቃላይ ምህረት (Comprehansive Amnesty) ማወጅ ይኖርበታል። ይህ በሀገር ውስጥ የታሰሩ የፖለቲካ አስረኞችን ጋዜጠኞችንና የሀይማኖት መሪዎችን መፍታትን ይጨምራል። ይህ ውሳኔ የዜግነትን ወይም የኢትዮጵያ ተወላጅነትን ስሜት የሚያነሳሳ ይሆናል። በሁላችንም ዘንድ የይቅር ባይነት ስሜትንም ይፈጥራል። መንግስት ይህን ሲያደርግ የተሸናፊነት ሳይሆን የትልቅነት ስሜት ሊሰማው ይገባል። ይህን እንዴውም ለችግር መፍቻው እንደወሰደው ተቃዋሚዎቹን መገዳደሪያ ርምጃ አድርጎ ሊቆጥረው ይገባል።
2. ከላይ ባንደኛ ተራ ቁጥር ከተጠቀሰው ውሳኔ ጎን ከፖለቲካ ድርጀቶች ጋር ተገቢ የሆነ የፖለቲካ ድባብ (Environment) ለመፍጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይትና ድርድር መጀመር ያስፈልጋል። ድርድሩ ሁሉን አቀፍ (Comprehansive) ሆኖ ሁሉንም ወገን አሸናፊ የሚያደርግና የህዝቡና የሀገር ጥቅምን መሰረት ያደረገ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል።
3. ማህበረሰቦች የሚጠነክሩትና መንግስትና ጉልበተኞችን የሚቆጣጠሩት የሲቢል ማህበረሰቦች ሲያብቡና ሲበዙ ነው። መንግስት የሲቪል ማህበራትን ደብዛ እንዲያጠፋ አድርጎ ያወጀውን አዋጅ ማንሳት ይኖርበታል። ይህ ለብዙ በጎ ስራዎችና ለዜግነት ክብር ማበብ በር ይከፍታል።
4. የድርድሩ ሂደትና ውጤት ዋስትና እንዲኖረው ከሀገር ሽማግሌዎች በተጨማሪ ወዳጅና ለጋሽ መንግስታትና ተቋሞች ድርድሩን እንዲያግዙ እንዲታዘቡና እንዲዳኙም ማድረግ ይጠቅማል።
5. በብዙ ምክንያት በተለይም ብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ ጋር በተያያዘ አይን ለአይን መተያየት የማይችሉ የፖለቲካ ሀይሎች ውይይት መጀመርና የሀገሪቱን ዋና የድህነት ችግር ለመፍታት ልዩነታቸውን ማቀራረብ ይኖርባቸዋል። ይህን ችግር ልንፈታ ስንነሳ ድህነት የሚያሰቃያቸውና ተስፋ ያስቆረጣቸው ወገኖቻችን አንድ ጉድጓድ ውስጥ እንዳሉ ቆጥረን መሆን ይኖርበታል። ሁሉም ነገር ላይ ባንስማማ ምንም አይደለም። ቀሪውን ችግር ለወደፊቱ በውይይት በህግና በህዝብ ፍርድ ለመፍታት መወስን ነው ትልቁ ነገር።
6. ሀገሪቱን የሚመሩት የፖለቲካ ሰዎችና ቡድኖች (ህወሀት/ኢህአዴግ) እንደማንኛውም ሰው የራሳቸው ህልውና ሰጋትና ፍርሀት እንዳላቸው ሁላችንም ልንገነዘብ ይገባል። ስልጣን ላይ ያሉት ሰዎች ተቃዋሚዎቼ ያጠፉኛል ብለው ካሰቡ አካሄዳቸው መዘዝ ያለው መሆኑን እያወቁ እንኳን እስከመጨረሻ ለመከላከል ቆርጠው እንደሚቀመጡ ልንገነዘብ ይገባል። ትልቁም ስራ ከዚህ ስጋት እንዲላቀቁ ማድረግ ስለሆነ ከፍተኛ የቅንነት ስራ መስራት ያስፈልጋል። ተቃዋሚ ሀይሎች ሀገሪቱን የሚመራውን የፖለቲካ ሀይል ሙሉ ለሙሉ መወገድ አለበት የሚል አቋማቸውን ትተው በራሳቸውም ላይ ይሁን በህዝብ ላይ ተፈጽመዋል የሚሏቸውን የመንግስትና ግለሰብ መሪዎች ጥፋቶች ይቅርታ ለማድረግ መዘጋጀትና በስምምነት በሚወሰን ጊዜ ውስጥ ስልጣን በምርጫና በምርጫ ብቻ የሚያዝበት መንገድ ላይ ዋስትና ያለው ድርድር ለማድረግና ለመስማማት ፈቃደኛ መሆን ይኖርባቸዋል።
7. በሁሉም ወገን ያሉ ጥፋቶችን በይቅርታ ለመፍታት ቆርጦ ሁሉም የሚተማመንበት ኮሚሺን አጣርቶ በሚወስናቸው የጥፋት ዝርዝሮች ላይ ተወያይቶ ጥፋቶችን ከመቀበልና (Acknowledgement) መማሪያ ከማድረግ ባለፈ በማንም እንዳይደረግ አስቀድሞ መወሰን ይጠቅማል። ከሌሎች ልምድ ሲጠቅም አይተናል። በደል ደረሰብን የሚሉና ፍርድ የሚጠይቁ ዜጎች ሲኖሩም ጉዳታቸውን ግለሰቦች ሳይሆኑ መንግስት የሚክስበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይቻላል።
8. በተቃዋሚዎች በኩል አሁን በስልጣን ላይ ያሉ ግለሰቦች ያፈሩትን ሀብትና ጥሪት ካለምንም ጥያቄ እንዲጠቀሙበትና ለቤተሰባቸውም እንዲያወርሱት ዋስትና በሚሰጥ ሁኔታ ማረጋገጥ ትልቅ ወደ እርቅ መንገድ መሳቢያ ዘዴ አድርጎ መውሰድ ያስፈልጋል።
9. ከዚህ ጎን ለጎን በውጭም በሀገርም ያሉ ኢትዮጵያውያን እንዳመቻቸው በግልና በህብረት በኢንቨስትመንት ስራ ላይ የሚሰማሩበት ሁኔታ እንዲመቻች ማድረግና መጋበዝ ማበረታቻም መስጠት ያስፈልጋል። በርካታ ሰራተኛ ለመቅጠር ለቻሉ የኢንቨስትመንት ተቋማት የታክስና ሌላም ማበረታቻ የሚሰጥ ፖሊሲ ማዘጋጀት ያስፈልጋል። በዚህ ጊዜ ሁላችንም ከስደት ወደሀገራችን መመለስና ስራ መስራት እንመርጣለን። ራሱን ጠቅሞ ወገንን እንደመጥቀም የሚያስደስት ምንም ነገር የለም። ከዚያ በላይ ደግሞ ከህግ በላይ የሚፈራ ነገር በሌለበት ሀገር መኖርን የሚጠላ የለም።
10. ከላይ በተነሱትና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ መግባባት ከተፈጠረ በኋላ ፍጹም ነጻ የሆነ ምርጫ የሚከናወንበትን ጊዜና ሁኔታ አመቻችቶ ባለማቀፍ ታዛቢዎች ፊት ማንም ወገን የማይገለልበት ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማድረግ ውጤቱንም በጸጋ ለመቀበል መወሰን ያስፈልጋል።
ከላይ ካነሳኋቸው ውጭ ብዙ ዝርዝር አከራካሪ ጉዳዮችና ችግሮች መኖራቸው ይገባኛል። እነዚህን ያነሳሁት ይዕርቁ መንፈስ ውቅር ምን መምሰል እንዳለበት ለማሳየት ያህል ነው። የተጠቀሱት የመፍትሄ ሃሳቦች ከመንግስት ቅን ምላሽ የሚያገኙት ቀደም ሲል እንዳነሳሁት በቅንነት ወይም በበጎ ፈቃደኝነት ብቻ አይደለም። የፖለቲካ ተቃዋሚዎች መንግስት ላይ ከፍተኛ ግፊት የሚፈጥር ትግል ማድረግና ያቀረቡለትን የመግባቢያ ሀሳብ እንዲቀበል ከማስገደድ ያልተናነሰ ተጽዕኖ መፍጠር አለባቸው። ተቃዋሚዎች ልዩነታቸውን አጥብበው ባንድ ላይ መሰለፍ ቢችሉ ትልቅ የተጽዕኖ ሀይል ይፈጥራሉ። ለዚህ የሚሆን መሰረታዊ የመስማሚያ ሀሳብ ማፍለቅ አንድ ትልቅ ጊዜ የማይሰጠው ስራ አድርገው ሊያዩት የሚገባ ይመስለኛል። እንዴውም ከቀዳሚዎቹ ነገሮች እንዱና ዋነኛው በተቃውሞው ጎራ የተሰለፉ የፖለቲካ ሀይሎች ያግድሞሽ ትግል ከማድረግ ወጥተው በእንድ ላይ የመሰለፋቸው ጉዳይ ነው።
ማጠቃለያ፥
ሁሉም ወገን አሸናፊ ሆኖ ፣ ሰላምና እርቅ ሰፍኖ ካለፈው ይልቅ መጭው ጊዜ ወሳኝነት ላይ ያተኮረ አመለካከት እንዲዳብር ማድረግ የችግራችን አይነተኛ መፍትሄ ነው። እንደ ሀገራችን ልማድ ይዋል ይደር እንጂ መንግስትን በሰፊ የህዝብ አመጽ ማስወገድ ይቻላል። ኪሳራው ግን ቀላል እይሆንም። ብዙ ህይወትና ንብረት ያስከፍላል። የኢትዮጵያን ድህነት ልብ ብሎ ለሚያይ ሰው የመጀመሪያው ምርጫው አብዮት ሊሆን አይችልም። በዚህ መንገድ ዛሬ ካሉብን የድህነት ችግሮች ለመላቀቃችንም ሆነ የሚቀጥለው ስርዓት ዴሞክራሲያዊ ስለመሆኑ ዋስትናም እናገኝም። በሰላምና ዕርቁ መንገድ ከሄድን ካለብዙ ኪሳራ ሁላችንም በተለይ መጭው ትውልድ የምንፈልገውን አገኘን ማለት ነው። የሰላምና ዕርቅ መንገድ ብዙ ለመቀበል የሚያስቸግሩ ይቅር መባባሎችንና ምህረተኛነትን ይጠይቃል። ይህ እንዳንድ ጊዜ ፍትሐዊም ላይሆን ይችላል። ይህንም ለተሻለ መጭ ጊዜ ስንል እንደምንከፍለው ሂሳብ ልንቆጥረው ይገባል።
እዚህ የሰጠሁት ሀሳብ በግብር እንዲውል ሰፋ ያለ ደጋፊ ህዝብ (Constituency) ያስፈልገዋል። የተባበረና በመንግስት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ መፍጠር የሚችል የተቃውሞ ሀይልም አስፈላጊ ነው። ሌላው አስፈላጊ ነገር ከፖለቲካ ፉክክር ውጭ ያሉ ተደማጭነት ያላቸው ሽማግሌዎች በበቂ ማግኘትና በመንግስትና በተቃዋሚዎች መሀል እንደልብ እየተመላለሱ ድልድይ እንዲሆኑ መፍቀድ ነው። ሁላችንም ሀገራችን የበደልናት አንድ ትልቅ ነገር ተደማጭነትና የሞራል የበላይነት ያላቸው ሽማግሌዎች (Statesmen) እንዳይኖራት ማድረጋችን ነው። ከኔ ጋር ካልሆንክ ጠላቴ ነህ የሚለው የአርባ ዐመት ፖለቲካችን ይህን በነገስታቱ ዘመን በመጠኑም ቢሆን የነበረንን የባህል ቅርስ አጥፍቶብናል። ነገር ግን አሁንም ብዙ ጥሩ ሽማግሌዎች ሊወጣቸው የሚችል ቅን ሰዎች የምናጣ አይመስለኝም። እዚህ ካነሳሁት የመነሻ ሀሳብ የበለጠ ሀሳብ ያላቸው ሰዎች እንዳሉም አውቃለሁ። ይህ በግርደፉ የሰነዘርኩት ሀሳብ ይበልጥ ተዘርዝሮ ሊዳብር ይችላል። በሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ ተዋናይ የሆኑ ሀይሎች ሁሉ ውረድ እንውረድ ከሚል ዛቻ ወጥተን ዘመናዊ ሰዎችና ሀገሮች እንደሚያደርጉት አጥፊ ጉዳት ለሌለው መፍትሔ ከተዘጋጀን ከዚህ ከገባንበት ውርደት መውጣት ብቻ ሳይሆን ሀገራችን ለራሷ ቀርቶ ለብዙ እንድትተርፍ ማድረግ እንችላለን። ኢትዮጵያም ህዝብ ጥያቄ ባነሳ ቁጥር ጠመንጃና ታንክ የማይጎተትበትን ዘመናዊውን ስልጡን ዓለም ተቀላቀለች ማለት ነው። መንግስትም በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ የሀይለኞች ንብረት ከመሆን ተላቆ የዜጎች ማገልገያ ሆነ ማለት ነው። ያን ጊዜም በገፍ መሰደድና መዋረድ ይቀርና የተሰደድነውም ወደሀገራችን ተመልሰን የየአቅማችንን ማዋጣት እንጀምራለን።
Fekadeshewakena@yahoo.com
የእንስሣት አብዮት የመጽሃፍ ትርጉም መስፍን ማሞ
በስደተኛ ማህበረሰቦች ውስጥ የባህል ግጭት ጭንቀት፤ ድብርት እና እራስን የማጥፋት አደጋ ውይይት በአዲስ ግርማ ፋውንዴሽን
በእነዘላለም ወርቅአገኘሁ ክስ መዝገብ ስር የሚገኙት ተከሳሾች ለብይን ተቀጠሩ
በሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸው የሚገኙትና ጉዳያቸው እየታየ የሚገኘው እነዘላለም ወርቅአገኘሁ ከረፋዱ 4፡30 ላይ ልደት በሚገኘው 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀረቡ፡፡
ችሎቱ ዛሬ ተሰይሞ የነበረው በተከሳሾቹ ላይ አቃቤ ህግ ባቀረበው የሰነድና የሰው ማስረጃ ላይ ብይን ለመስጠት እንደሆነ ያወሱት የመሃል ዳኛው ሸለመ በቀለ፣ አቃቤ ህግ ለአራተኛ ጊዜ ተጨማሪ ማስረጃዎችን እንዳቀረብ ጊዜ ይሰጠኝ በሚል ያቀረበው ጥያቄ ችሎቱ ያልተቀበለው በመሆኑ ውድቅ መደረጉን ገልፀዋል። ከ1ኛ እስከ 6ኛ ያሉት ተከሳሾች እንዲሁም የ9ኛ ተከሳሽ ጠበቃ የሆኑት አቶ ተማም አባቡልጉ ለፍርድ ቤቱ የማመለክተው ነገር አለኝ በማለት ደምበኞቻቸው ላይ የቀረቡ ማስረጃዎች የተገኙት ከህግ አግባብ ውጪ መሆናቸውንና ደምበኞቻቸው ከተያዙ በኋላ የቀረቡ መሆኑንና ይህም የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀፅ 146 የተላለፈ መሆኑን ገልፀው አቃቤ ህግ ያቀረበው የሰነድ ማስረጃም ሆነ የሰው ምስክር ከክሱ ጋር ያልተያዘዘ መሆኑን ተረጋግጧል በማለት ሀሳባቸውን አጠቃለዋል። አቃቤ ህግ በበኩሉ ጠበቃ ተማም አባቡልጉ የሰነድ ማስረጃዎቹም ሆነ የሰው ምስክሮቻችን ውድቅ ሊሆኑ ይገባል ሲሉ ተጨባጭ ማስረጃ እንዳላቀረቡ ገልፆ ያቀረባቸው የሰነድ ማስረጃዎችም ሆነ የሰው ምስክሮች ተቀባይነት ያላቸው መሆኑን አስረድቷል። አያይዞም የቀረቡት ‹‹የሰነድ ማስረጃም ሆነ የሰው ምስክሮች የቀረበውን ክስ ያስረዳሉ አያስረዱም የሚለው ፍርድ ቤቱ የሚመዝነው መሆኑን ገልፆ፣ ፍርድ ቤቱ የጠበቃ ተማም አባቡልጉን መቃወሚያ ወድቅ እንዲያደርገውና በተሰሙት የሰው ምስክሮችና በቀረቡት የሰነድ ማስረጃዎች ተገቢውን ብይን እንዲሰጠን እናመለክታለን›› በማለት ሀሳቡን አጠቃሏል፡፡
ፍርድ ቤቱ የዛሬው ችሎት ውሎ ከመቅረፀ ድምፅ ተገልብጠው ከመዝገቡ ጋር እንዲያያዝ በማመልከት ብይን ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ለሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም ሰጥቷል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ አርበኞች ግንቦት ሰባትን ለመቀላቀል በማሰብ የሚል ክስ የተመሰረተበት የአንድነት አባል የነበረው መሳይ ትኩ፣ በተመሳሳይ ሰአት ፍርድ ቤት ቀርቦ የነበረ ሲሆን ክስ መቃወሚያ ካለው ከጠበቃው ጋር በመሆን ሰኔ 26 ቀን 2007 ዓ.ም ይዞ እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በተመሳሳይ ዜና በዘላለም ወርቅ አገኘሁ የክስ መዝገብ ስር የሚገኙት የቀድሞ የአረና ፓርቲ አመራር አቶ አብርሃ ደስታ፣ የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ ም/ድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ሺበሺና የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል አፈጉባኤ የነበረው አቶ የሺዋስ አሰፋ ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ዞን ሶስት እንደተዘዋወሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡
እጹብ ድንቅ ሃሳብ ፤ ሆኖም ጋሪዉን ከፈረሱ ማስቀደም አይሆንም? በፈቃደ ሸዋቀና የፖለቲካ እርቅ ሃሳብ ላይ አስተያየት ሰለሞን ገ/ስላሴ
ትግሌንም አደራ በተለይ ለኔ ትውልድ ሳሙኤል አወቀ!! በጎንቻው
የሳሙኤል አወቀ መገደል የነፃነት ትግሉን አያስቆመውም !!የሰማያዊ ድጋፍ በሰሜን አሜሪካ
“ለማንኛውም የምከፍለው ዋጋ ለለሃገሬና ለነፃነት ነው፡፡ በአካል ብታሰርም ህሊናዬ አይታሰርም፡፡ ከገደሉኝም ትግሌን አደራ!!! አገራችን የወያኔ ዘረኞች ብቻ መፈንጫ መሆን የለባትም! ትግላችን የነፃነት፤ ጉዞአችን ጎርባጣ፤ መድረሻችን ነፃነት፤ ታሪካችን ዘላለማዊ ነው፡፡” ሳሙኤል አወቀ ፊስቡክ ገፅ ላይ የተገኘ ሰኔ 8/2ዐዐ7 ዓ.ም፡፡
ምስራቅ ጎጃም ግንደ ወይን 1978 ዓ/ም ተወልዶ – በህግ የዲፕሎማ እና ዲግሪውን ሰርቷል፡፡ ሣሙኤል አወቀ የሠማያዊ ፓርቲ መስራች አባልና ከዚያም በፊት እንደ ሌሎች ጓደኞቹ ከቅንጅት ጀምሮ በአንድነት ፓርቲ ውስጥ ሲታገል የቆየ ጠንካራ ኢትዮጵያዊ ነበር፡፡ ሣሙኤል በሙያው የህግ ባለሙያና በጥብቅና ስራ በግል እየሠራ ጎን ለጎን ደግሞ ለአገሩ ከነበረው ፅኑ ፍቅር የተነሣ በሠላማዊ ትግል በማመን ገና በልጅነቱ ትግሉን ተቀላቅሎ በግፍ እስከተገደለ ድረሥ በንቁ የፖለቲካ አመራር ሲታገል ቆይቷል፡፡ ሣሙኤል የሠማያዊ ፓርቲ ከተመሠረተ ጀምሮ በከፍተኛ ኃላፊነት በንቃትና በተደራጀ መልኩ በተወከለበት ቀጠና በምስራቅ ጎጃም ዞን ሲያደራጅና ሲያስተባብር ነበር፡፡
ሳሙኤል አወቀ በአካባቢው ዘንድ የተከበረ እና ምስጉን ወጣት ነበር፡፡ በቅርቡም በተደረገው ሃገራዊ ምርጫ ፓርቲውን ወክሎ የዞኑ የተወካዬች ም/ቤት ጠንካራ ተወዳዳሪ እንደነበር አስመስክሯል፡፡ ሣሙኤል በምሰራቅ ጎጃም አካባቢ እታች አርሦ አደሩ መንደር በመዝለቅ በንቃት ሲያደራጅና ሲያስተባብር የነበረ በየአካባቢው ይደርስ የነበረውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ አስተዳደራዊ ጭቆናና በደል እየተከታተለ ለሕዝብ መረጃ ሲያቀብል እንደነበረ! በተለይም በፓርቲው ልሣን በነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላይ አምደኛ በመሆን ተከታታይ መረጃዎችን ሲያቀብል የነበረ ጠንካራ የማይበገር ታጋይ እንደነበር ተገንዝበናል፡፡
በትናትናው ዕለት ማለትም ሰኔ 8 ቀን 2ዐዐ7 ዓ.ም የወያኔ ኢህአዴግ የፀጥታ ሃይሎች ከምሽቱ አንድ ሰዓት ተኩል አካባቢ ከሚኖርበት ቤት አጠገብ ደ/ማርቆስ ከተማ ውስጥ እጅግ አሠቃቂ ድብደባ ተፈጽሞበት በግፍ ለተገደለው የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አባል ሣሙኤል አወቀ አለም ሃዘናችን ፅኑ፣ መራርና ፈጽሞ ለአፍታም ያህል የማይረሳ የዘመናችን የነፃነት ትግል አርዓያ ዋና ተምሣሌት፣ እንዲሁም ለኢትዮጵያችን እንደቀደሙት ጀግኖች እንደነ አቡነ ጴጥሮስ የታሪክ ባለአደራ የወቅቱ የትግል ጥሪ ፈር ቀዳጅ ጀግናችን ነው፡፡ ለሣሙኤል አወቀ ቤተሰቦች እግዚአብሔር እንዲያፅናናቸው እየተመኘን ዛሬ ሣሙኤል በአካል ከትግል አጋሮቹ ጋር ባይኖርም የሥራው ተምሣሌት ግን ለነፃነት ትግሉ ጉዞ ህያው ሥንቅ ሆኖ ይቀጥላል፡፡
ሣሙኤልን በጥቅም ሣይደለል በኃይል በማስፈራራት ወይም በአካሉ ላይ ድብደባ በመፈጸም ትግሉን ለማስቆም ያልቻሉት የወያኔ ኢህአዴግ ቅልብ ወንጀለኞች በአካሉ ላይ ያደረሱት ጉዳት አልበቃ ብሏቸው በትናትናው ዕለት በስለት ፊቱንና አካሉን በመቆራረጥ ማንነቱን መለየት እስከማይቻል ድረስ በጭካኔ ገድለው ጥለውታል፡፡ ይህ ዓይነቱ የመንግስታዊ አሸባሪነት የመጀመሪያ ሣይሆን በተደጋጋሚ የታዬና አገዛዙ ጠንካራ ተቃዋሚ አመራሮችን በተመሣሣይ ጥቃት ሲያደርስ እንደቆየ ሕዝቡ ያውቃል፡፡ በኢትዮጵያ ተንሠራፍቶ ያለው ኢሰብአዊ አምባገነን ዘረኛ መንግስት በሕዝቡ ላይ በተለይም በተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና በነፃው ኘሬስ አባላት ላይ ከፍተኛ በደሎች ማለትም እስራት፣ ድብደባ፣ግድያና ሁለገብ የሆነ የስነ ልቦና፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሃይማኖታዊ ወንጀል እየፈጸመ ይገኛል፡፡ የሣሙኤል አወቀ የግፍ ግድያ ከላይ እነደተጠቀሰው አገዛዙ ሕዝቡን የሚያጠቃበት መለያ ባህረው አንድ አካል መሆኑን አስረጅ ሊሆን የሚችልና አገዛዙ ምን ያህል በጥላቻ እንደተጠመደና እጅግ አሣሣቢ ደረጀ ላይ መድረሱን ያሣያል፡፡ የወንድማችን የሣሙኤል የግፍ አገዳደል አልበቃ ብሏቸው የአገዛዙ ቅልብ ነፍሰ ገዳዬች በሣሙኤል ቀብር ላይ የተገኙትን ሌሎች አመራር አባላት ከቀብሩ ስነስርዓት ሲመለሱ አግተው አስረዋቸዋል፡፡
ውድ የኢትየጵያ ሕዝብ ሆይ፦
ይህ አይነቱ እጅግ ዘግናኝ በደል ሃዘናችንንና ቁጭታችንን ያባብሰዋል እንጅ ለነፃነት የተጀመረውን መራር ትግል ለአፍታም አያስቆመውም፡፡ በአገርቤትም በውጭም የምንኖር የሠላማዊ ትግል ደጋፊዎችና አራማጆች እንዲሁም መላው አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የአገዛዙን ሰይጣናዊ ስራ በአንድ ድምፅ ማውገዝና መቃወም ይገባናል፡፡ ዛሬ በሣሙኤል ሞት ልባችን እንደቆሰለ ነገ በሌሎች ሣሙኤሎች ተመሣሣይ ግፍ እንዳይፈጸም ሁላችንም በአንድ ላይ እንነሣ! አገዛዙን በጋራ ታግለን ማስወገድ ይኖርብናል፡፡
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!
እግዚአብሔር የሣሙኤልን ነፍስ በገነት ያኑርልን!
ሳሙኤል እንደ እስጢፋኖስ በበላይነህ አባተ
በደሙ ተፃፈ፤ከጥበበ ሣሙኤል ፈረንጅ
በጭካኔ ጥበብ ተንኮል የተካኑ፤
ስብዕናን ያጡ ለውነት የመከኑ፤
በሐሰት ተጠምቀው በውሸት የፀደቁ፤
በሌላው መከራ ሳቁ ተሳለቁ::
ሊጥሉት ሞክረው አልወድቅም ቢላቸው፤
ቀጥቅጠው ገደሉት በፈሪ ዱላቸው።
በድቅድቅ ጨለማ ተስፋ በታጣበት፤
የነፃነት ትግል በደበዘዘበት፤
ሣሙኤል አወቀ እንደሻማ በርቷል፤
ለወገኑ ክብር በሕይወቱ ከፍሏል።
ፈለጉን ተከተል አደራ ብሎሃል፤
ደሙ ከአጥናፍ አጥናፍ ይጣራል ይጮሃል፤
እምቢ በል ወገኔ ተነሣ ይልሃል፤
ፀጥ ያለው ነጎድጓድ፤ የታመቀው ቁጣ፤
የዝምታው መብረቅ፤ ገንፈሎ እንዲወጣ፤
አብረህ ተነሳ፤ ይቅር ማመንታቱ፤
ስዓቱ አሁን ነው ህዳሴ አብዮቱ።
የግፍ ጽዋ ሞልቶ ፈልቶ ሲገነፍል፤
እንዳላየህ አይተህ፤ አልፈህ ዝም ስትል፤
ታሪክ ይጠይቃል የት ነበርክ ይልሃል።
ግፉዓን ሲጮሁ፤ ፍትሕን ተጠምተው፤
አንደበት የሆኑ ድምጽ ለሌላቸው፤
እንደነ ሣሙኤል ደፍረው የጀገኑ፤
በጨቅላ ዕድሜያቸው እንደጉም ሲተኑ፤
እንዴት ያስችለናል ሰምቶ ዝም ማለቱ፤
በወንበዴ መንግስት ሲቀጩ ሲሞቱ።
ሣሙኤል በደሙ ታሪኩን ጽፎታል፤
የነፃነት ቀንዲል አሻራውን ትቷል፡
የጀግናው መሰዋት እንዳይቀር በክንቱ፤
ይብቃ ብለህ ተነስ የዝግታ ሞቱ
ይብቃ ብለህ ተነስ ውርደቱ ስደቱ።
በጨካኞች በትር ሕይወቱ ላለፈው፤ ለወጣት ሣሙኤል መታስብያ ትሁንልኝ።
የነካ ነካ ፖለቲካ ያመረርክ እንደሆን ምረር እንደ ቅል፣ ዱባነህ ተብለህ እንዳትቀቀል፤ ታደለ መኩሪያ
በሕብረተሰባች ውስጥ ንዝህላልነት ወይም ዳተኛነት ጎልቶ ይታያል፤ ራሱን፣ ትውልዱን ፣ሀገሩን ጭምር፣ለዘለቄታው ለሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ ያለው ተሣትፎ የቀዘቀዘ ነው። መንስዔውን ለመግለጽ በተረጋገጠ እውነት ላይ የተመሠረተ ማስረጃ የለኝም። ሆኖም በጋራም ሆነ በተናጠል ለሚመራበት፣ የፖለቲካ ሥርዐት በአሉታም ሆነ በአዎንታ ፍላጎቱን በነፃነት መግልጽ አይችልም፤ ላለፉት ሁለተ አሥርት ዓመታት በቁርጥኝነት ራሱን ገልፆ ለራሴም ለሀገሬም ይጠቅማሉ በሎ ያመነበትን ይዞ የቀጠለበት ሁኔታ ጎልቶ አልታየም፤ የታየው በአምስት ዓመት አንዴ ለሚደረገው የውሸት ምርጫ የነካ ነካ ፖለቲካ መጫወት ነው። ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶች በተለያዩ ወቅቶች ይቀርባሉ፤ በሥልጣን ላይ ያለው መንገሥት በኃይል በአንድ ዘር ስም ሀገሪቷን ተቆጣጥሯል ይላሉ፤ ተቃዋሚዎቹም አይተባበሩም፣ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት እርስ በእርሰ በመናኮር በማለት ይገልፃሉ፤
እኔ የተለየ አስተያየት አልኝ፤ በሕብረተሰባችን ውስጥ ንዝህላልነት ገዝፎል ፣ በማንኛው መስክ የምንሰራውን ሥራ አውኳል፣ የነካ የነካው ፖለቲካም የዚያ አካል ነው፤ አንደኛ፣ ለሚገጥሙን ችገሮች በግልም ሆነ በጋራ ከመቋቋም ይልቅ ራሳችንን አግለን ላለማድረጋችን በሌላው ላይ አላከን፣ ለራሳችን ግን ይቅርታ ሰናደርግ በራሳችን ላይ የጭቆናውን ሸምቀቆ ማጥበቃችንን እንዘነጋለን፤ ሁለተኛ፣ ችግሮች ሲገጥሙን ራሳችንን መቆጣጠር አቅቶን ስሜታዊ መሆናችንና ችግሩን እንዳለ ተቀብለን ለመፍትሔ ከመጣር ይልቅ አሉታዊ ኃይል እናዳብራለን፤ ሦስተኛው፣ ችግሩን መጋፈጥ ከተጀመረ በኋላ አቅማችንን በመራድና በመፍራት እናባክነዋለን፤ ሆኖም ሶስተኛው እላይ ከተገለጹት ሁለቱ የተሻለ ቢሆንም ከታሰበው ግብ አያደርስም። አራተኛው፣የሚገጥሙንን ተግዳራት ለመጋፈጥ የአእምሮ ዝግጅት አድርገን ፣ አደርገዋለሁ በሚል አዎንታዊ ኃይል ራሳችንን አሣምነን በደስታ በግልም ሆነ በጋራ ለነፃነታችን ከቆምን ጊዜ ይውሰድ እንጂ ችግሮቻችንን እናስወግዳቸዋለን። በወያኔ እስር ቤት የሚማቀቅት ጋዜጠኞች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣የፖለቲካ ተጠሪዎች ያንን ስዕብና ስላላችው በዚያ ሰቆቃ ውስጥ ሆነው በሀገርም በውጭ ላለነው ከእስር ቤት በጹፋችው ያስተምሩናልን።
ችግሮቻችንን ከመጋፈጥ ይልቅ ጥቃቅን ምክንያቶችን ማቅረቡ የትም አያደርሰንም፤ ለምሳሌ ወያኔን እኛ ኢትዮጵያውያን እንጠለዋለን፤ የበአዳን አገሮች ይወዱታል፤ የሀገር ሠራዊት የሚያከራያቸው አሜሪካኖች፤ የሀገሪቱን የተፈጥሮ ሐብት ያለገደብ እንዲዘርፉ፣ ርካሽ፣ ሸቀጣቸውን ሕዝቡ ላይ እንዲያራግፉ የፈቀደላቸው ቻይናዎች ፤ ወሰን ቆርሶ የሰጣቸው ሱዳኖች፣ ሀገሬውን አፈናቅሎ መሬት ያከራያችው ሕንዶች፤ እንደ ባሪያ ፈንጋይ ቡቃቅላ ሴት ኢትዮጵያውያንን የሚያቀርባላችው የአርብ አገሮች ይወዱታል፤ ስለጥላቻ ትንሽ ልበል፤ ከክርስቶስ ልደት ከ3ሺ ዓመት በፊት የሥልጣኔ ጮራ በፈነጠቀባቸው፣ ሞሶፖታሚያና ግብፅ አሣማ በጣም የተጠላ ዕንሰሳ፣ ከምድረ ገጽ እንዲጠፋ የተወሰነበት ነበር፤ በሀገራችም የዕስልምና ሃይማኖት ተከታዩ አምርሮ ይጠለዋል፤ የእርሱ ዝርያ በሆነው በከርከሮ ከማለ ለእርቅ አይቀርብም፤ በኦሮሞኛ ‘ፎን ከርከሮ’ የከርከሮ ሥጋ ከተባለ ትልቅ ማህላ ነው። በኦርቶዶክ ዕምነት ተከታዩም የአሣማ ሥጋ አይበላም። በዚህ ዘመን ከቻይና እሰከ አሜሪካ ከቁርስ እሰከ እራት ሕዝቡ የሚመገበው አሣማ ነው።ከክርስቶሰ ልደት ከ3ሺ ዘመን በፊት እንዲጠፋ የተፈረደበት አሣማ በምግብነቱ ተወዶ ዓለም ይመገበዋል። እኛ ዛሬ ወያኔን ብንጠላውም ከቻይና እሰከ አሜሪካ ተወዳጅነት አለው፤ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በነዚህ አገሮች ለምን እንደተወደደ በአጭር አረፍተ ነገር አሰቀምጦታል፤ ‘‘የውጭ ምንዛሬ ለማግኝት የቡና እግር አንቆጥርም ፤ የወታደር እግር እንቆጥራለን፤’’ በኦሮመኛ እንዲህ ይተረታል፤ ‘’ ሃሬ ኪራ ገልቱ ኪራ ዱቱ ጭራ’’ የክራይ አህያ ከገባች ኪራዬ ከሞተችም ጭራዋ ይባላል፤ ሱማሌያ ውስጥ ተገለው ሬሣቸው ስለተጎተቱት ኢትዮጵያውያን በተቃዋሚዎች ለአቶ መለስ ዜናዊ ጥያቄ ሲቀርብለት፣’ ለማወቅ አይገባችሁም’ ነበር መልሱ።
ባጠቃላይ የፖለቲካ አካሄዳችን የነካ ነካ ፖለቲካ የሆነበት ምክንያት ወያኔን በውል ያለመረዳትና ሁለት ልብ መሆን ነው፤ ከግንቦቱ ምርጫ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ርዕዮት ዓለሙ ከአለችበት እስር ቤት ‘ነቄ ነን’ በሚለው መጣጣፏ ‘ገማሽ እርግዝና የለም፣’ እንቁርጥ የሚል ዕድምታ አለው።
ወያኔ በሙሉ ልቡ የሚያጠነጥነው አማራ ብሎ ከፈጠረው የጎሣ ፓለቲካ ዙሪያ ነው፤ በ1968 ዓ ም በደደቢት በነደፈው መረሃ-ግብር ውስጥ አማራው በትግራይ ሕዝብ ላይ ያደረሰውን በደል እንዲህ አሰቀምጦታል፤የታሪክ ሥርቆት ተካሂዶብናል፣ ማንነታችንን በግድ እንድንቀይር ተደርናል፣ በመንግሥት መመሪያ እንድንቆርቁዝ ተወስኖብናል፣ ለስደት ለሴተኛ አዳሪነት ተጋልጠናል የሚሉ ሮሮዎች ናቸው፡፡እነዚህ ሮሮዎች የቀረቡት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሆነ፣ መርምሮ መፍትሄ በሰጠ ነበር።ሮሮውን አቅራቢው ወያኔ በሥልጣን ከሃያ ዓመት በላይ ቆይቶም ለሮሮው መብትሔ አላገኘም፤ አሁንም ‘ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ’ ነው። ይህ ለእኔ ዕንቆቅልሽ ሆኖብኛል፣ ለእናንተስ አልሆነባችሁም? ይህንን መሰል ደረቅ ርዕዮተ ዓለም ከሚያካሄድ ቡድን ጋር የሚደረግ የፖለቲካ ፊልማ በነካ ነካ ፖለቲካ ከታቀደው ግብ አይደረስም፤ ለሃያ ዓመት የታየው ያ ነው። ከመነሻው ቡዱኑ በግብተኝነት ተነሣስቶ ትግራይን ከኢትዮጵያ እገነጥላለሁ ያለ ነው። እንደህ ከሆነ አጣብቅኝ ውስጥ ከገባው ወያኔ ጋር በምርጫም ሆነ በድርድር መሠረታዊ ነገር ላየ መድረስ ይከብዳል። ስለመንደሩ ራዕይ መረሃ-ግብር ነድፎ ከሚቀሳቀስ ቡድን ጋር ተቀምጦ ሰለ ትልቋ ሀገር ችግር መፍትሔ ማግኘት እንዴት ይቻላል? በጥናት በተረጋገጠ እውነት ላይ መሠረት አድረጎ የተነሣ ቡድን አይደለም፤ እፍረቱንና ድክመቱን ከጠመንጃ ጀርባ ከልሎ፣ ከክርሰ መቃብሩ የሚወርድበትን ቀን የሚጠብቅ ነው። ቆምኩለት ለሚለው የትግራይ ሕዝብ ከአድማስ ባሻገር የሚያሳየው ተስፋና መልካም ራዕይ የለውም፤ ያመጣው በሌሎቹ ወገኖቹ መጠላትን ነው፤ ለዋሆቹ፣ ለሥልጣን ጥመኞቹ፣ ለሰው ንብረት ቋማጮቹ፣ ለሀገርና ለወገን ግድ የለሾችና ተስፈኞች፣ የወያኔ መንግሥት እንቁጣጣሽን የፈጠረላቸው ሊመስላቸው ይችላል፣ ሆኖም ግን በሰከን አእምሮ ለሚያየው የትግራይ ሕዝብ ከቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያለያይ እንጅ ሮሮውን የሚመልስ አይደለም፤ የጥላቻን መርዝ የሚረጭ ነው።
ይህን መሰል መረዝን የሚረጭን መረሐ -ግበር ነድፎ ሀገርን የሚያስተዳድርን ቡድን በነካ ነካ ፖለቲካ ወይም ትግል አስወግዳለሁ ማለት እራስን ማታለል ነው፤ የያንዳንዱን ዜጋ እንደ አቅሙ ተሣትፎን ይጠይቃል፤ ሀገርን ከጥፋት ማዳን በሁሉም ትከሻ ላይ ያረፈ ሸክም መሆኑ ሊሰማን ይገባል፣ ለድረጅቶችና ለግለሰቦች ትቶ የራስን ነጻነት አሰቀምቶ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ወርደትን ለራስ መምረጥ ነው፤ ለቤተሰብም ለትውልድም ማፈሪያ፤ የሰው ልጅ ከገነት ወይም ከጀነት የፈጣሪውን ተዕዛዝ ባለማክበር ወደምድር ሲጣል፣ከነሙሉ ነጻነቱ ጋር መሆኑን ቅዱስ ቁራንም ሆነ መጽሐፍ ቅዱስን ጠቅሰው የሃይማኖት አባቶች ይሰብካሉ፤ ሕዝብ ክርስቲያኑም ሆነ ዕስላሙ ዓምላኩ ያልነፈገውን ነፃነቱን በራሱ መሰል ሰው መብቱን አስቀምቶ መኖሩ በራሱ ኃጢያት ነው፤ የሃይማኖቶቹ ሰባኪዎቹ ሆኑ ተከታዮቹ ሙናፍቂያን ካልሆኑ በስተቀር አይቀበሉትም፤ እውነተኛው ሃይማኖት ለራስ ነፃነትና ለሌሎች መብት መከበር በእውነት መቆምን መሠረት ያደረገ መሆኑ ይታወቃል። በሌላ አንፃር ስናየው፣ አንድ ሰው በግልም ሆነ በጋራ ለራሱ ሙሉ ነፃነት ለማስከበር የሚያስከፈለውን ዋጋ ካልከፈለ ዘውትር ተዋርዶ ይኖራል፤ ሀገርም ብትሆን የያንዳንዱ ዜጋ ስዕብና የተከበረበት ምድር መሆን አለባት። ስለሆነም በነፃነት መኖርን ማንም ሊሰጠን ወይም ሊነሣን አይችልም፤ ከፈጣሪያችን የተሰጠን ጸጋ ነው ብለን የማመኑን ኃይል በአእምሮአችን እንፍጠር!
ታደለ መኩሪያ
tadele@shaw.ca
የሰላም ትግሉ በኢትዮጵያ (ክፍል ፩) አንዱዓለም ተፈራ –የእስከመቼ አዘጋጅ
ኢትዮጵያዊያን፤ ተከታታይ አምባገነን መሪዎችን ከነአገልጋዮቻቸው ለማስወገድና የሕዝቡን የሥልጣን ባለቤትነት ለማረጋገጥ የምናደርገው ትግል፤ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ ነው። በ ፲፱፻፷፮ ዓመተ ምህረት ሕዝቡ የተነሳባቸው የመብትና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄዎች አሁንም አልተመለሱም። ይኼው ሃምሳ ዓመት አለፈው። ይባስ ብሎ ሕዝቡን የመንግሥት አገልጋይ አድርጎ የሚጠቀም ጠባብ አምባገነን ገዢ፤ በሀገራችን ነግሷል። ይኼን መንግሥት ለማስወገድ የሚደረገው ትግል ማዕከል የለውም። በሀገር ቤት ከፍተኛውን መስዋዕትነት እየከፈሉ የሚንቀሳቀሱት የሰላማዊ ታጋዮች እና ከሀገር ውጪ ያሉ ታገዮች፤ በመካከላቸው የትግል ቅንጅት የለም። በሀገር ቤት ያሉት የሚያደርጉት ትግል፤ ምስጋና ለወራሪው የትግሬዎች ነፃ አውጪ አምባገነን መንግሥት ምስጋና ይግባውና፤ መልክ እየያዘ ነው። የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ የአንድነት ፓርቲና የሰማያዊ ፓርቲ ታጋዮች ወደ አንድ መሰባሰባቸው፤ የትግሉን ማዕከል ለማበጀት የማዕዘን ድንጋዩን ጥሏል።
ሰላማዊ ትግል ካለው መንግሥት ዓይን የተሰወረ ተግባር የለውም። ለአቸናፊንቱ ያለው እምነት የተመረኮዘው፤ የጨበጠው እውነትና ያነገተው የሕዝብ እዮታ ነው። እውነት ምን ጊዜም አቸናፊ ሆኖ ይወጣል። የሕዝብ እዮታ ደግሞ፤ ይዘገይ እንደሆን እንጂ፤ አቸናፊ ሆኖ መውጣቱ አያጠራጥርም። ምንም እንኳ የገዥው ክፍል፤ በዕለት በዕለት በሥር በሥሩ እየተከታተለ ሰላማዊ ታጋዮችን ሊያመክን ቢሞክርም፤ ምንጫቸው የገዥው በደል የደረሰበት ሕዝብ ነውና አይደርቅም። እኒህ በሰላም ለመታገል ቆርጠው የተነሱ ታጋዮቻችን የሚያደርጉትን ትግል፤ እነሱም ሆነ ከነሱ ውጪ ያለነው ሌሎች ታጋዮችና ሰላማዊው ሰው፤ ስለሚያደርጉት ሆነ ማድረግ ስላለባቸው እንቅስቃሴ ያለን ግንዛቤ፤ አንድ አይደለም። የሰላማዊ ትግልን ምንነት፣ ጠቃሚ ግንዛቤና ዝርዝር መርኅ፤ ከመጽሐፍትና ከድረገፆች ማግኘት ይቻላል። ያ መሠረታዊና ለመነሻው መረጃ ነው። እናም እንደ ማንኛውም ኅብረተሰባዊ ክስተት ሁሉ፤ በሚተገበርበት ቦታ፤ ያካባቢውን ተጨባጭ እውነታና የትግል ተመክሮ ከዝርዝር ውስጥ አስገብቶ፤ ያካባቢው የተለዬ ሁኔታ አስተካክሎት፤ ለሂደቱና ስኬቱ ዋነኛ የሆኑ ወሳኝ ሁኔታዎችን በትክክል ካልተረዳን፤ ድፍኑ የሰላማዊ ትግል ግንዛቤ፤ ተንሳፋፊ ነው። ከዚህ በመነሳት፤ በኢትዮጵያ የሰላማዊ ትግልን ግንዛቤ በግልጽ በመተንተን፤ ሰላማዊ ትግሉ እንዴት ነው? የሚለውን መልሼ፤ አንድ ተመሳሳይ ግንዛቤ ላይ እንድንደርስ፤ በዚህ ጽሑፍ አሳያለሁ።
በሀገራችን በኢትዮጵያ፤ ሰላማዊ ትግል፤ በሀገራችን ያለውን ሕግና ስነ-ሥርዓት በትክክል አምነውበት፤ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን ሁኔታዎች መሟላትና መኖር ተቀብሎ፤ መንግሥታዊ ሥልጣኑን በምርጫ ተወዳድሮ በማቸነፍ፤ ገዥውን ፓርቲ ለመተካትና ያለውን ሥርዓት ለማስቀጠል የሚደረግ የፖለቲካ እንቅስቃሴ አይደለም። ሰላማዊ ትግል የተወዳዳሪ ወይም የተፎካካሪ ፓርቲዎች መንገድ አይደለም። የተፎካካሪ ወይም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች፤ ያለውን ሥርዓት ትክክለኛነት ከጥያቄ ውስጥ አይስገቡም። ከገዥው ክፍል ያላቸው ልዩነት፤ ውስንና የአስተዳዳር ዘይቤ ላይ ያተኮረ ነው። ሰላማዊ ትግል፤ መሠረታዊ የሆነ ሀገራዊ የአስተዳዳር ፍልስፍናና ተግባር፤ ከዚህም ተነስቶ የአስተዳዳር መመሪያውን አፈጻጸሙ ላይ ልዩነት ያቀርባል። ሰላማዊ ታጋዮች፤ የፖለቲካ ምኅዳሩ መጥበብ ብቻ ሳይሆን፤ ተዘግቷል ብለው ያምናሉ። ሰላማዊ ትግሉ፤ ገዥውን ክፍል ለማስወገድ የሚደረግ ንቅናቄ ነው። ለመተካት የሚደረግ ሩጫ አይደለም።
ሰላማዊ ትግሉ፤ ሁለት ተፃራሪ የሆኑ ተግባራት ባንድ ላይ የሚከናወኑበት ሂደት ነው። የመጀመሪያው እንደ ፖለቲካ አካል ለመንቀሳቀስ፤ የሀገሪቱ ሕግና ደንብ በሚያዘው መሠረት፤ ተመዝግበው ሕጋዊ የሆነ እንቅስቃሴያቸውን ማካሄድ ነው። ይህ፤ የማይወዱትን ግዴታ እንዲቀበሉ ያስገድዳቸዋል። እናም መከተል ያለባቸው መንገድና ማድረግ ያለባቸው ግዴታ አለ። እንደ የፖለቲካ አካል በምርጫ ቦርዱ መመዝገብ፣ ተወዳዳሪዎችን ማዘጋጀትና ማቅረብ፣ መወዳደር የመሳሰሉት ናቸው።
ሁለተኛውና የሕልውናቸው መሠረታዊ ዓምድ፤ ሰላማዊ ከሚለው ማንነታቸውን ገላጭ ቃል ቀጥሎ ያለው ትግሉ ነው። ይህ እምቢተኝነታቸው ነው። ይህ ነው ትግሉ። ሕዝቡ ዕለት በዕለት በየቦታው የሚደርስበትን በደል አብረው ተካፋይ ስለሆኑ፤ ተበዳዩን ወገን በማሰለፍ፤ በእምቢተኝነት ለአቤቱታ ይነሳሉ። መልስ እንደማያገኙ ግልጽ ነው። ሆኖም ግን፤ በሂደቱ፤ እያንዳንዱን የሕዝብ በደል፤ ሀገራዊ መልክና ይዘት በመሥጠት፤ ሕዝቡን ለእምቢተኝነት ይቀሰቅሱበታል። የበደሎችን ተዛማጅነት ያሳዩበታል። የመወዳደር ግዴታቸውንና በዚህ አጋጣሚ የሚፈጠሩ መድረኮችን፤ ለዚሁ ተግባር ያውሏቸዋል። ተወዳድረው ለማቸነፍ ሳይሆን፤ የውድድሩን ሂደት ሕዝቡን ለመድረሻና ለመቀስቀሻ ይጠቀሙበታል። አምባገነኑን ገዥ ክፍል ለማጋለጫ ይጥእቀሙበታል። መወዳደራቸው የመጀመሪያውን ግዴታቸውን ሲያሟላላቸው፤ ተወዳድረው የማቸነፍ በሩ እንደተዘጋ ያውቃሉና፤ ሂደቱን ለመቀስቀሻ ሲጠቀሙበት፤ ሁለቱንም ግዴታዎቻቸውን አሟሉ ማለት ነው።
ይህ ነው በተወዳዳሪ ድርጅቶችና በሰላማዊ ታጋዮች መካከል ያለው አንዱ ልዩነት። በመሠረታዊ ማንነታቸው ላይ ያለው ሌላው ወሳኝ ልዩነት፤ ተወዳዳሪ ድርጅቶች ከአንድ በላይ ሊሆኑ ይችላሉ። ሰላማዊ ትግሉን የሚያራምዱ ታጋዮች ግን፤ አንድ እና አንድ ድርጅት ብቻ ነው የሚኖራቸው። ካንድ ከበዙ የሰላማዊ ትግሉን ሂደት አበላሽተውታል። ለምን?
ሰላማዊ ትግል፤ ያለው የገዢ ቡድን መወገድ አለበት ብሎ የተነሳ ሕዝብ፤ የሚወስደው የፖለቲካ እርምጃ ነው። በዚህ እምነት ዙሪያ የሚሰባሰቡ፤ ውስን በሆነ የመታገያ ዕሴቶች የተባበሩና ከዚያ ውጪ፤ የተለያዬ አመለካከት ያላቸው ናቸው። በአሁኗ ኢትዮጵያ የሚደረገው ሰላማዊ ትግል፤ አስራ ሁለት መሠረታዊ የትግል ዕሴቶችን ያቅፋል።
፩ኛ. ያለው አስተዳደር፤ ጠባብ፣ ወገንተኛና አምባገነን ነው።
፪ኛ. በሀገራችን ሕዝቡ ዴሞክራሲያዊ መብቱ ተረግጧል።
፫ኛ. የገዥው ክፍል እውነተኛ የሕዝብ ተወካይ አይደለም።
፬ኛ. ይህ ሥርዓት ሲወገድ፤ የሚከተለው ሥርዓት፤ ዴሞክራሲያዊና ኢትዮጵያዊ ይሆናል።
፭ኛ. ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረገው ትግል፤ በሽግግር መንግሥት ሂደት ሥር ያልፋል።
፮ኛ. በዚህ የሽግግር ወቅት፤ የሀገራችን የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ይረቀቃልና ይጸድቃል።
፯ኛ. በዚህ የሽግግር ወቅትና በሕገ-መንግሥቱ፤ የግለሰብ ዴሞክራሲያ መብቶች ይከበራሉ።
፰ኛ. በዚህ የሽግግር ወቅትና በሕገ መንግሥቱ፤ በሀገራችን የሕግ የበላይነት ይሰፍናል።
፱ኛ. በሕገ-መንግሥቱ፤ እያንዳንዳችን በኢትዮጵያዊነታችን ብቻ የምንሳተፍበት የፖለቲካ ምኅዳር ይዘረጋል።
፲ኛ. በዚህ የሽግግር ወቅትና በሕገ-መንግሥቱ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ይጠበቃል።
፲፩ኛ. በዚህ የሽግግር ወቅትና በሕገ-መንግሥቱ፣ የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ይከበራል፤ ሀገሪቱ ለኢትዮጵያዊያን ትሆናለች።
፲፪ኛ. በዚህ የሽግግር ወቅት፤ ለዴሞክራሲ ሥርዓት መሠረታዊ የሆኑ ተቋማት ይቋቋማሉ።
የሚሉት ናቸው።
በነዚህ ዙሪያ የሚሰባሰቡት የፓርቲ አባልት አይደሉም። በነዚህ የትግል ዕሴቶች ዙሪያ የሚሰባሰቡት፤ መላ የተበደሉና ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያዊያን ናቸው። ከነዚህ የትግል ዕሴቶች ሌላ ይዞ ሊንቀሳቀስ የሚችል፤ የገዥውን ክፍል ለውጥ የሚሻ አይኖርም። ሌላ አጀንዳ ያለው ካለ፤ የትጋዩ ክፍል አካልም ወገንም አይደለም። ይህ ወደ ሽግግር መንግሥት የሚወስደው ጎዳና፤ አንድ ነው። ከዚያ በኋላ የሚከተለው እንዲህ ነው።
ታጋዩ ክፍል፤ ሕዝቡ የትግሉ ባለቤት፣ መሪና የድሉ ባለቤት መሆኑን አምኖ ይቀበላል። ስለዚህ የሕዝቡ ድርሻ የሆነውን፤ በሽግግሩ ጊዜና ከሽግግሩ በኋላ፤ ሕዝቡ የሚወስነው ይሆናል። ከዚያ በፊት ለሚደረገው ትግል፤ ታጋዩን በሙሉ በአንድነት ማሰባሰብና፤ ትግሉ በአምባገነኑ ወገንተኛ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርና በሕዝቡ መካከል ብቻ መሆኑን ተረድተን፤ አንድ ትግል አንድ ኢትዮጵያዊ ራዕይ ይዘን የምንፋለምበት መሆን አለበት።
ሰላማዊ ትግሉ በኢትዮጵያ የአሁን ተጨባጭ የፖለቲካ ሀቅና ከትጥቅ ትግል ተለይቶ የተሻለ አማራጭ የሚሆንበትን ምክንያትና ሌሎች ትንታናዎቼን በሚቀጥሉት ክፍሎች አቀርባለሁ።
አለም አቀፍ ድጋፍ የተቸረው “ልማታዊ” አንባገነናዊነት በኢትዮጵያ ከያሬድ ኃይለማርያም
‘የአፍሪቃ ድሃ ባይጠግብም እንኳ ቀምሶ ካደረ ይበቃዋል’ አይነት ንቀት የተሞላው የምዕራቡ አለም ምልከታ ከመቼውም ጊዜ በከፋ መልኩ አፍጦና አግጦ እየታየ ነው፡፡ በርሃባችንና በእርስ በእርስ መናቆራችን ለዘመናት ሲነግዱበትም ሲማረሩበትም ቆይተዋል፡፡ ዛሬ ዛሬ የመጫወቻው ካርድ ተቀይሮ ለአፍሪቃ አንባገነኖች አንድ ቃል ተለጥፎላቸው ካሳላፍነው ታሪክ ምናልባትም በከፋ መልኩ ጉዟችንን ቀጥለናል፤ የኋሊት ይሁን ወደፊት እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን የምዕራቡ አለም “ልማታዊ” በሚል ካባ የተከናነበውን የለየለት አንባገነናዊነት ሙሉ ድጋፋቸውን እየሰጡ ለመሆኑ የኦባማን የኢትዮጵያ ጉዞ ጨምሮ በርካታ ምልክቶችን እያየን ነው፡፡ ከምርጫው በፊትም ሆነ ከተጠናቀቀ በኋላ የአውሮፓ ኅብረትና የአሜሪካን መንግስት ያሳዩትም ድጋፍ የእዚሁ መገለጫ ነው፡፡ በአፋኝ አገዛዝ ውስጥ ላለ ሕዝብ ዲሞክራሲን፣ ሰብአዊ መብቶችን፣ ፍትሕን እና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚደረግ ድጋፍ ለተራበ ሕዝብ ስንዴና ዘይትን እንደመርዳት ቀላል አይደለም፡፡ እህል ተርፏቸው ወደ ባሕር የሚጨምሩ አገሮች የተራበ ሲያገኙ የተረፋቸውን መወርወራቸው አንድም እርዳታ በመስጠትና ለጋሽ በመሆን የሚገኝው የመንፈስ እርካታና በዋነኝነት ደግሞ የተጠኑ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትርፎችም አሉት፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ላለፉት አስርት አመታት በርካታ የአፍሪቃ አገራት፤ የኛዋ አገር ደግሞ በግናባር ቀደምነትነት የዚህ የእህልና የገንዘብ ድጎማ ተጠቃሚ ሆና ቆይታለች፡፡ በዚህ የቁስ እርዳታ ማን እንዳተረፈ በጥልቅ መመርመር የግድ ይላል፡፡ በእርግጠኝነት ግን መናገር የሚቻለው አገርንና ሕዝብን ለውርደት የዳረገና ክፉ የታሪክ ጠባሳም መሆኑን ነው፡፡ ዘንድሮ ስንዴና ዘይት የሚላክለት ድሃ ሕዝብ ያለችውን ቅሪት እየሸጠ በርሃና ባሕር አቋርጦ በራሱ ጥረት “ምና አደከማችሁ እኔ እዛው እምጣለሁ” ብሎ ለጋሾቹ ደጃፍ ደርሷል፡፡ ለዚህም በየአመቱ ከኢትዮጰያ፣ ከኤርትራ፣ ከሱዳን እና ከሱማሌ የሚሰደደው ሕዝብ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ የምዕራቡ አለም እርዳታውን በመርከብ ከማጓጓዝ ሳይድን አልቀረም፡፡ ስንዴ የሚጭኑ መርከቦች ሽብርን ለመዋጋት በሚል ሽፋን የጦር መሳሪያ በማጓጓዝ ስራ የተጠመዱ ይመስለኛል፡፡
ዛሬ ላይ የቻይና ቢዝነስ ተኮር ወረራ ያስደነበራቸው የምዕራቡ አለም አገራት የአፍሪቃን አንባገነኖች ከነ ወንጀሎቻቸውና ስንክሳራቸው ተቀበለው አብረው ለመዝለቅ የተገደዱበትና መለማመጥ የጀመሩበት ሁኔታ ነው የሚታየው፡፡ “ልማት” እና “ደህንነት” (security) ብቸኛዎቹ የምዕራቡና የአፍሪቃ አንባገነኖች የመወያያና የመደራደሪያ አጀንዳዎች ሆነዋል፡፡ ሰብአዊ መብቶች፣ ዲሞክራሲንና የሕግ የበላይነትን በዋነኝነት ያነሱ የነበሩት አውሮፓዊያን ሳይቀሩ እነዚህን አጀንዳዎች ወደጎን የገፉዋቸው መሆኑን በግልጽ እየታየ ነው፡፡ ለዚህም በኢትዮጵያ የ2007 ምርጫ ዙሪያ ያሳዩት የዳር ተመልካችነት ሚና እና ከምርጫውም በኋላ የሰጡዋቸው መግለጫዎች በግልጽ እንደሚያሳዩት ሁሉን ነገር ወደ ጎን ተትው “ሰላም” በሚለው አጀንዳ ላይ ብቻ ያተኮሩ ናቸው፡፡ ምርጫው በሰላማዊ መንገድ በመጠናቀቁ የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ ከ”ልማታዊው” አንባገነናዊ ሥርዓት ጋር ያላቸውን ጥብቁ ቁርኝት አድሰው እንደሚቀጥሉ በግልጽ የሚያሳየውን የአጋርነት መግለጫቸውን አንብበናል፡፡
በአገዛዝ ሥርዓቱና በአለም አቀፉ ማኅበረሰብ መካከል፤ የአፍሪቃ ኅብረቱንም ጨምሮ በኢትዮጵያ ምርጫ ላይ ቀደም ብሎ የተደረሰበት አንድ አይነት ስምምነት እንዳለ የሚያሳየው የምርጫ ቦርድና ገዢውን ቡድን ጨምሮ ሁሉም መፈክራቸው “ምርጫዉ ሰላማዊ በሆነ መልኩ ተጠናቋል” የሚል ነበር:: ይህ መሪ መፈክር ተደጋግሞ በሁሉም ሚዲያዎችም እነቪኦኤን ጨምሮ እስክንደነቁር ድረስ ሲነገርን ቆይቷል፡፡ ይህ ሆን ተብሎ ቅድመ ሥራ የተሰራበት ነገር ስለመሆኑ ምንም አያጠራጥርም፡፡ አንደኛ ሰላም ባለበት አገር ልክ ምርጫውን ተከትሎ አንዳች የመተላለቅ ዳመና እንዳንጃበበ ተደርጎ የተሰራው ዘገባ ሁሉ ሕዝቡ ስጋት ውስጥ እንዲገባና እንዲሸበር አድርጎታል፡፡ ይህ ተንኮል ያልገባውና ቀላል ግምት የማይሰጠው ሕዝብም ሊመጣ ይችላል ከተባለው አደጋ እንኳን ወያኔ አንዳች ኃይል ያለው ሰይጣንም ቢያስጥለው አይጠላም፡፡ ይህም ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ነገር ነው፡፡ የሌለን ነገር እንዳለ አድርጎ ፈጥሮ ሕዝብን ማስጨነቅና ማስሸበር የተፈለገበት ዋነኛ አላማም የገዢውን ኃይል ብቸኛ የሰላም አስከባሪ አካል አድርጎ ሕዝብ እንዲያየውና ወያኔ ከሌለ ያልቅልናል የሚል ስጋት በብዙዎች ዘንድ እንዲፈጠር አድርጓል:: ይህ ደግሞ ከአመታት በፊት ቀድሞ የተወሰነና የምዕራቡንም አለም ቅቡልነት ያገኘውን የገዢውን ቡድን በስልጣን የመቆየት እቅድና ሕዝብ ባይዋጥለትም ሳያንገራግር እንዲቀበል ለማደረግ ቀላሉና ብቸኛው መንገድ ነበር፡፡ ስለሆነም “ነጻና ፍትሐዊነት” በምንም መልኩ የዚህ ምርጫ መሪ መፈክር አልነበሩም፡፡ ወያኔም ይህን ለማሟላት ዝግጁ አይደለም፡፡ ስለዚህ ምርጫውን ተከትሎ አንዳች የመተላለቅ አደጋ እንዳንጃበበ አድርጎ የማቅረቡ ፋይዳ ለወያኔም ሆነ ለምዕራቡ አለም ብቸኛው የማደናገሪያ ካርድና የመውጫ ቀዳዳ ነበር፡፡
ድምጽ በሚሰጥበት ዕለት እንኳን በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት፣ ዕጩዎችና ደጋፊዎቻቸው ሲጉላሉ፣ ሲደበደቡ፣ ሲታሰሩና አልፎም በአንዳንድ ቦታዎች ሲገደሉ የበርካታ ሚዲያዎች፣ የአፍሪቃ ሕብረት ታዛቢዎችና አለም አቀፍ ሚዲያዎች ሳይቀሩ አንድ አይነት ነጠላ ዜማ ነበር የሚያዜሙት፤ “የምርጫው ሂደት ሰላማዊ ነው፡፡ … በሰላምም ተጠናቋል፣ ወዘተ…”፡፡ ይህ ከላይ እንዳልኩት አንድም የአገዛዝ ሥርአቱን ብቃትና ጥንካሬ ለማጉላት ያለው ብቸኛ መንገድ ስለሆነ በሌላ መልኩም ቀድሞ የተዶለተበትንና አለም አቀፍ ቅቡልነት ያገኘውን በምርጫ ስም የአንባገነን ሥርዓቱን የአገዛዝ ዘመን የማደስ ስልት ለመሸፈን የተደረገ የትብብር ዘመቻ ነው፡፡
ምርጫ የዜጎች ዲሞክራሲያዊ መብቶችና ነጻነቶች ከሚረጋገጡባቸው መንገዶቹ አንዱ ነው፡፡ ልማት ደግሞ የአንድ አገር ሕዝብ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መበቶች በተሟላ መልኩ እንዲረጋገጡ የሚያስችል ሌላው መንገድ ነው፡፡ ልማትና ዲሞክራሲ ተጣጥመው በሚሄዱበት ስፍራ ሁሉ ማህበራዊ ፍትሕም ይሰፍናል፣ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላምም ይኖራል፡፡ ለዚህም ነው በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ ውስጥ በሁለት ማዕቀፍ የተቀመጡት መብትና ነጻነቶች፤ የሲቪልና የፖለቲካ እንዲሁም የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የባሕላዊ መበቶች ሳይነጣጠሉ መተርጎምና መከብር እንዳለባቸው የተደነገገው:: ይሁንና ለድሃ አገራት ስንዴና ዘይት እየረዳ ስለ ሰብአዊ መብቶችና ነጻነቶች መከበር ካንገት በላይም ቢሆን ይሟገት የነበረው የምዕራቡ አለም ‘ድሃ በል’ በሆነው የገበያ መርህና በግሎባላይዜሽን ስም የዝርፊያ ጋሪውን አስቀድሞ ዜማውን በመቀየር ከ”ልማታዊ” አንባገነኖች ጋር ተስማምቶ የእጃዙር ቅኝ ግዛት መረቡን አፍሪቃ ላይ ጥሏል፡፡ እኛንም ከገዢዎቻችሁ የተራረፈውን ቀምሳችሁ ማደር ከቻላችሁ ዲሞክራሲንና ሰብአዊ መብቶችን ቀስ ብላችሁ በመቶ አመት ሂደት ትቀዳጃላችሁና ተረጋጉ እያሉን ነው፡፡ ለጊዜው አለማችን እኛው በፈጠርናቸው ሽብርተኞች ተወጥራለችና እጃቸው ከመውደቋ በፊት እነሱን ለማጥፋት እንተባበር እያሉን ነው፡፡ እንግዲህ የሚበጀንን እንምረጥ::
በቸር እንሰንብት!
ያሬድ ኃይለማርያም
ከገዥው ወገን የምንለይበት፤ አንዱዓለም ተፈራ –የእስከመቼ አዘገጅ
እኔ ከያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የበለጠ ለትግሬዎች ጥብቅና እቆማለሁ፣ እኔ ከያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የበለጠ ለኦሮሞዎች ጥብቅና እቆማለሁ፣ እኔ ከያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የበለጠ ለአማራዎች ጥብቅና እቆማለሁ፣ እኔ ከያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የበለጠ ለሶማሌዎች ጥብቅና እቆማለሁ፣ እኔ ከያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የበለጠ ለአፋሮች ጥብቅና እቆማለሁ፣ እኔ ከያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የበለጠ ለኦጋዴኖች ጥብቅና እቆማለሁ፣ እኔ ከያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የበለጠ ለአኙዋኮች ጥብቅና እቆማለሁ፣ እኔ ከያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የበለጠ ለሲዳማዎች ጥብቅና እቆማለሁ፤ የሚል ግለሰብም ሆነ ድርጅት፤ ከያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ይልቅ ከአምባገነኑ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ጋር የበለጠ የጋራ የሆኑ መቀራረቢያ ጉዳዮች ስላሉት፤ ሰፈሩን ወደዚያ ቢያቀና ይቀለዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአምባገነኑ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ጋር መሠረታዊ ልዩነቱ፤ እያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን፤ “እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ። በሀገሬ በኢትዮጵያ የማደርገው ማንኛውም የፖለቲካ ተሳትፎ፤ በኢትዮጵያዊነቴ ብቻ ነው። በኢትዮጵያዊነቴ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ባልተለዬ ሁኔታ፤ እኩል በፖለቲካ ምኅዳሩ፤ የግለሰብ ዴሞክራሲያዊ መብቴ ተከብሮልኝ፤ በማንኛውም የሀገሬ ክልል፤ የመኖር፣ ሀብት የማፍራት፣ በአካባቢውና በሀገር አቀፍ የፖለቲካ ሂደት ተሳትፎ የማድረግ ሙሉ መብት አለኝ።” ስንል፤ አምባገነኑ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ደግሞ፤ “የለም ኢትዮጵያ የትግሬዎች፣ የአማራዎች፣ የኦሮሞዎች፣ የደቡቦች፣ የሶማሌዎች፣ የአፋሮች፣ የአኝዋኮች ነች። ግለሰብ ኢትዮጵያዊ የሚባል የለም። እናም የፖለቲካ ተሳትፎ የሚደረገው በነዚህ ክልሎች ዙሪያ እንጂ፤ በኢትዮጵያዊነት አይደለም።” የሚለው ነው።
ከዚህ በመነሳት፤ አምባገነኑ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት፤ አስተዳደሩን በዚህ ላይ ተከለ። በሂደቱም የተለያዩ ለየብቻቸው የተካተቱ ክልሎችን መሠረተ። አያንዳንዱ የዚህ ገዢ ቡድን ተቀጥላ ጥገኛ የክልል የፖለቲካ ድርጅት፤ የራሱን የክልሉ ተወላጆች ብቻ በክልሉ ለመክተትና ለማስተዳደር ሙሉ መብት አገኘ። እናም በገዥው ቡድን ፈቃድና ፍላጎት፤ ሌሎችን ከክልሉ ማባረር፣ ሀብታቸውን መዝረፍ፣ መግደል፣ አይቀሬ ሆነ። በተግባርም ተፈጸመ። ሀገራችንን ፍጹም ወደማትመለስበት አዘቅት ለመክተት፤ ይኼው ገዥ ቡድን ተሯሯጠ። ተከትለው የሚሄዱት የሕዝቡን ድምጽ ማፈን፣ ሀገሪቱን እስር ቤት ማድረግ፣ አንገቱን ሰብሮ የማይገዛውን ማሰር፣ ማባረርና መግደል፤ ተዥጎደጎዱ። ለዚህ ተቃውሞ፤ ኢትዮጵያዊያን የተለያዩ ድርጅቶችን መሥርተው በመታገል ላይ ናቸው። እንግዲህ በዚህ ትግል፤ ሁለት ሰፈሮች ብቻ በገሃድ አሉ። አንደኛው የሕዝቡ ሰፈር ነው። ሌላው የአምባገነኑ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ሰፈር ነው። የግለሰብ ሆነ የድርጅት ጉዳይ እዚህ ቦታ የለውም። የግለሰብ እምነት ወይንም የድርጅት መርኀ-ግብር፤ ከሁለቱ መርጠን ባንዱ ሰፈር እንድንሰለፍ ያደርገናል። የሰልፉ መለያ ደግሞ፤ የፖለቲካ ፍልሰፍናችን እና ከዚህ የሚመነጨውና በተግባር ለማዋል የምንፈልገው የአስተዳደር መመሪያ ነው።
ይህ ነው የአሁኑ የሀገራችን የኢትዮጵያ የፖለቲካ እውነታ። ይሄን በጁ ያልጨበጠ ማንኛውም ሂደት፤ መዳረሻው ተመልሶ ያው ነው። የድርጅት መሪዎችም ሆኑ ታጋይ ግለሰብ ኢትዮጵያዊያን፤ መሠረታዊ የሆነውን የልዩነት ነጥብ በማንገት፤ ትግሉን መልክ ሠጥተን መሄድ አለብን። አማራ ነኝና ከሌሎች የበለጠ ለአማራዎች እኔ ነኝ ተቆርቋሪ፣ ለኦሮሞዎችም፣ ለትግሬዎችም፣ ለሶማሌዎችም፣ ለአፋሮችም፣ ለአኙዎኮችም፣ ለሲዳማዎችም እኔ ነኝ ተቆርቋሪ የሚለው አባባል፤ የኢትዮጵያዊነት ጠላት ነው። እንደ ኢትዮጵያዊ ካላሰብን፤ ኢትዮጵያዊነት በውስጣችን የለም። እንደ ኢትዮጵያዊ ካልታገልን፤ ኢትዮጵያ የለችም። በሀገራችን፤ ለኢትዮጵያዊያን ሉዓላዊነት፣ ለሀገራችን ዳር ደንበር መከበር፣ ለያንዳንዳችን ዴሞክራሲያዊ መብት የምንታገለው በኢትዮጵያዊነታችን ነው። አንዳችን ከሌላችን ጎን የምንሰለፈው፣ የያንዳንዳችን ጉዳይ የሌላችን በመሆኑ ነው። አለዚያ፣ አንተም ለራስህ እኔም ለራሴ ከሆነ፤ ትግሉ ለኢትዮጵያዊያንና ለኢትዮጵያ ሳይሆን፤ በየኪሳችን ለያዝነው ዘውድ ነው። መነሻችን ይሄ ከሆነ፤ መድረሻችን ኢትዮጵያ ናት።
ይሄን እንድጽፍ ያስገደደኝ፤ ስለሰላማዊ ትግል የመጀመሪያውን ክፍል ባቀረብኩበት ወቅት፤ ከሌሎች የተላኩልኝ አፀፋዎች ነው። የገዥውን ስም ለምን “ትግሬዎች” ትላለህ የሚለው በተደጋጋሚ የቀረበልኝ ቢሆንም፤ ባሁኑ ሰዓት ቁንጮው ላይ ደረሰ።
እናም ይሄን ጻፍኩ። እኔ ራሳቸውን እንዲጠሩበት በመረጡት ስም ነው የጠራኋቸው። ለኔ ካላይ እንደገለጽኩት የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ነው። ኢትዮጵያ አንድ ናት። ኢትዮጵያ የኢትዮጵያዊያን ናት። በትግራይ ያሉት ኢትዮጵያዊያን፤ ትግሬዎች ይባላሉ። በአፋር ያሉት ኢትዮጵያዊያን አፋሮች ይባላሉ። ታዲያ ትግሬዎችን ነፃ አወጣለሁ ብሎ የተነሳ ግንባር፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ነኝ ሲል፤ ሌላ ምን ብዬ ልጠራው ነው። የትግራይ ሕዝብ፣ የአማራ ሕዝብ፣ የኦሮሞ ሕዝብ ካልኩማ፤ ሰፈሬ ከገዥው አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር አይሆንም ወይ? ለኔ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ የትግራይ ሕዝብ፣ የአማራ ሕዝብ፣ የኦሮሞ ሕዝብ፣ የሶማሌ ሕዝብ፣ የሲዳማ ሕዝብ፣ የአኝዋክ ሕዝብ፣ የቤንሻንጉል ሕዝብ፣ የወላይታ ሕዝብ የለም። እናም፤ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ብዬ አልጽፍም። ለምን ይሄን ጽፍክ የሚለኝ ካለ፤ ሄዶ ስም ያወጣውን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ይጠይቅ።
በሀገራችን ያለው ትግል፤ ሀገርን ከአምባገነን ፀረ-ኢትዮጵያ የሆነ ጠላታችን አንጻር፤ ልዩነታችን በግልጽ ወጥቶ፣ ተሰላፊዎች ባደባባይ ታውቀን የቆምንለት እንጂ፤ አንዳችን ሌላችንን የምንለማመጥበት ጉዳይ አይደለም። ትግሉ የመላ ሕዝቡ እንጂ፤ የዚህ ወይንም የዚያ ወገን የግል ጉዳይ አይደለም። ታጋዩን የሕዝብ ወገን ወደ አንድ ማሰባሰቡ የትግሉ የመጀመሪያ ግዴታ ነው። በርግጥ መተባበር የዲፕሎማቲክ ሥራ እንጂ፤ አንተም ባፈተተህ የሚባልበት ሂደት አይደለም። በቅርቡ የተለያዩ ታጋይ ድርጅቶች ቢያንስ ተገናኝተው ለመነጋገር ይችሉ እደሆነ በማሰብ፤ ጥረት አድርጌ ነበር። ይሰበሰቡና መፍትሔ ያቀርቡልናል የሚል ብዥታ አልነበረኝም። ነገር ግን፤ በሂደቱ ሁላችን ሀገራችን ያለችበትን አደጋ በመመልከትና ቅድሚያ ለሀገር ብለን፤ በድርጅት ያሉትም ሆነ ግለሰብ ታጋዮች፤ የመሰባሰቡን ሂደት ያቀላጥፉታል ብዬ ነበር። አልተሳካም። ትግሉ ከገዥው አምባገነን ጋር የምንፋለምበትን ጉዳይ በቅርብ በልብ አንግተን፤ የጠራና ፀሐይ የሞቀውን ልዩነታችንን ባደባባይ አንግተን የተነሳንበት ግብግብ ነው። ይሄን ላስደስት፤ ያንን ላቆላምጥ የሚባልበት አይደለም። በተለይ በሥልጣን ላይ ያለን መንግሥት ለመለወጥ የሚደረግ ትግል፤ የጠራ አመለካከት ከሌለው፤ ትግሉ ውጤታማ አይሆንም። ጠላት ማነው፣ የምንታገለው ለምንድን ነው? ግባችን ምንድን ነው? መመለስ ያለባቸው ጥያቄዎች ናቸው። በዚህ ትግል፤ ጠርተው የሚወጡ ጽንሰ-ሃሳቦች አሉ። እኒህ የትግሉን ሂደት ይተረጉሙታል። ግንዛቤን ያዳብራሉ። በሥልጣን ላይ ያለውን ገዢ ቡድን ማንነቱን ለመግለጽ የምንጠቀምበት ስም፤ ራሱን ግልጽ አድርጎ የሚጠራበትና የሚጠራበት መሆኑ፤ በትግሉ ላይ ትልቅ አስተዋፅዖ አለው። የምናየው የትግል አሰላለፍ ትርጉሙ የሚመነጨው፤ ከግንዛቤያችን ላይ በመቆም ነው።
በአንድ በኩል ጠላታችን የሚታወቀው ራሱ ነኝ ብሎ ባወጣው ስም እንጂ፤ እኛ በምናወጣለት ስም አይደለም። በሌላ በኩል ደግሞ በመካከላችን እብሪተኛን እብሪተኛ ማለት ካልቻልን፤ ታጋዮች ሳንሆን ወሬኞች ነን። ከሁሉም በላይ የሀገሬ ጉዳይ ብሎ ያልተነሳ ታጋይ፤ የሕዝቡ ወገን ሊሆንም ሆነ ታግሎ የሕዝቡን ድል ሊያስገኝ አይችልም። ቢሳካለት ገዥውን መተካት ነው ሩጫው።
የበረሃው ጂኒ ፣ የባህሩ ጋኔል በልጅግ ዓሊ
ብቻውን ሆኖ ከጥግ ቆሞ ይቆዝማል። ጸጉሩን እየፈተለ ይናደዳል . . . ብቻውን ያልጎመጉማል። ትንሽ ቆይቶ ያለቅሳል። ለጉድ! ያነባዋል። ሰው እንዳለ እንደሌለ አካባቢውን ይቃኛል። ገና ወደዚህ አካባቢ እንደመጣ ሲብስበት በሰው ፊት ያለቅስ ነበር። አሁን አሁን ግን ሲያለቅስ ሰው ሲያየው አይወድም። መጀመሪያ አካባቢ ጎረቤቶቹ ሲያለቅስ ሲመለከቱ ያጽናኑት ነበር። በኋላ ግን ቀውሷል ብለው ደመደሙ። እንዲያው በደፈናው ግማሾቹ ፍቅር ይዞት ነው ሲሉ፣ ሌሎቹ ደግሞ የሳሃራ በረሃ ጋኔል አግኝቶት ነው. . . ወይም የባሕር ጂኒ ተጠናውታው ይሆናል ማለት ጀመሩ። በየሄደበት ሁሉም እብድ ነው፣ ቀውሷል ብለው ደምድመዋል። ስለሚናገረው ነገር ግን ማንም ልብ ብሎ ያስተዋለውም፣ የጠየቀውም የለም። እሱም መናገር አይወድም። በእርግጥም ስለሱ የሚያውቅ ማንም የለም።
ብቸኝነቱን ሲያስብ፣ የውስጥ ሃዘኑ የአዕምሮውን ጣሪያ ሲነካበት ከቤት ተነስቶ ውልቅ ይላል። ባቡር ይሳፈርና ወደ ፍራንክፈርት ይሄዳል። መሄጃ እንደሌለው የሚያውቀው ግን ፍራንክፈርት ሲደርስ ነው። ለምን ከቤቱ እንደወጣ ግራ ይገባዋል። ባቡር ጣቢያ ከሚገኘው ማክዶናልድስ ይገባና ቁጭ ይላል። እዛም ሆኖ በሃሳብ እንደገና ይወረሳል። ወዲያው ደግሞ እንባው ድቅን ይላል። የጸጋዬ ገብረ መድህንን ወንድ ልጅ ተደብቆ ነው የሚለቅሰው የሚለውን ግጥም በቃሉ ይወጣዋል።
ከወዳጅ ከዘመድ ርቆ፣
አንጀቱን በአንጀቱ ታጥቆ፣
ተሸሽጎ ተገልሎ ተሸማቆ ተሸምቆ፣
ከቤተሰብ ተደብቆ፣
መሽቶ የማታ ማታ ነው፣ ሌት ነው የወንድ ልጅ እንባው ።
እውነት ነው! ወንድ ልጅ በቀን አያለቅስም ብሎ ራሱን ያሳምናል።
በእንባ የጠበቡ ዓይኖቹን እየደጋገመ ጠረግ ጠረግ ያደርጋቸዋል። ጭንቅላቱ ግን በሃሳብ እንደተወጠረ ነው። እዬ! ዬ! ብሎ . . . አልቅሶ ቢወጣለት ምንኛ በወደደ ነበር። አካባቢውን ዞር ዞር ብሎ ይቃኛል። የሚያውቀው ሰው የለም። ማልቀስ እችላለሁ። ማን እንዳይታዘበኝ? ከማን ነው የምደበቀው? እዚህ አበሻ የለም . . .ቀውስ የሚለኝ የለም . . . እያለ ራሱን በራሱ በሚጽናኑ ቃላት ማባበል ይጀምራል። ብቻው ሲያለቅስ አበሾች አይተው ቀውሷል እንዳይሉት መፍራቱን ግን አልተወም።
ቁጭ ባለበት በሃሳብ ይነጉዳል። እንቅልፍ እንደያዘው ሰው በመሃል እንደገና ከሃሳቡ ይባንናል። በቀስታ ድምጽ ማዕበል፣ ማዕበል ፣ ማዕበል ይላል። አጠገቡ ያሉት ሰዎች ቋንቁው ባይገባቸውም በትዝብት ይመለከቱታል፤ በመቀጠልም ጮክ ብሎ እጄን ያዢኝ ፣ እጄን ያዢኝ ፣ እጄን ያዢኝ እያለ ይጮኻል። ሁሉም ሰው ወደ እሱ ይመለከታል፣ እሱ ግን ሰው እንደሚመለከተው ከቶ አያስተውልም። ለምን ለቀቅሽኝ ፣ ለምን?. . . ለምን ለቀቅሽኝ ብሎ ይጮኻል። ከዚያም ወዲያው ፈቱን የእንባ ዘለላ ያርሰዋል። ያለቅሳል ፣ ይንሰቀሰቃል. . . በጉንጩ ላይ ከሚፈሰው ይልቅ ደረቱን ሰንጥቆ ወደ ውስጥ የሚገባው እንባ ይብሳል ።
ጥቂት ቆይቶ ራሱን የጸጋዬን ግጥም ውስጥ ለመደበቅ ይሞክራል። እሱም አልመች ሲለው ግጥሙን እያሰላሰለ ማን ነው . . . ወንድ ልጅ ተደብቆ ነው የሚያለቅሰው፣ የሚንሰቀሰቀው ያለው? . . . ስህተት ነው ፀጋዬ! ወንድ ልጅ የሚያነባው አደባባይ ላይ ነው እንጂ! . . . ፀጋዬ ተሳስተሃል! ግጥምህን አርመው! ባንተ ዘመን ይሆናል በምሽት ተደብቆ የሚያለቅስው፣ በእኛ ዘመን ግን ተቀይሯል። በእኛ ዘመን ወንድ ልጅ ሲደላው ብቻ ነው ተደብቆ በምሽት የሚያነባው፣ እንደዚህ ቀይረነዋል፣ አንተም ቀይረዋ!
ጣሩ ሲበዛበት ግፍ መከራው፣
በቀን በጠራራ ፀሐይ አደባባይ ሕዝብ ፊት ነው፣
ወንድ ልጅ የሚያለቅሰው፣ የሚንሰቀሰቀው።
ማንነቱ የተደፈረበት፣
እሱነቱን ያጣበት፣
ብሶቱን የሚገልጽበት፣
ቁጭቱን የሚያሳይበት፣
ብቸኝነቱን የሚወጣበት።
ቀን ነው የሚያነባው፣
ሰው ፊት ነው የሚያለቅሰው፣
አደባባይ ነው ስቅስቅ የሚለው፣
ሕዝበ አዳም፣ የሃበሻ ዘር ብሶቱን እንዲያይለት ፣
አይቶም እንዲያላግጥበት . . . ።
ፀጋዬ ግጥምህን ቀይረው። . . . ይላል።
ወዲያው ቀና ብሎ ላፍታ ሰውን ሁሉ ከገላመጠ በኋላ፣ የአዳም ልጅ ሁላ አላግጥ . . . እኔን እያየህ ተዝናና ብሎ ከማክዶናልድ ይወጣል። ነገር ግን፣ ውጭ ወጥቶ የሚሄድበትን አያውቀውም። መሃል መንገድ ላይ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ቆሞ፣ እንደገና ለራሱ ብቻ በሚገባው ቋንቋ ማልጎምጎም ይቀጥላል፡፡
ከዚያም ፈጠን ፈጠን እያለ በርካታ እርምጃዎች ይራመዳል ። ወዲያውም ዘው ብሎ አንዱ አበሻ ቡና ቤት ይገባል። እዚያም ላፍታ አይቆይም። ይወጣል። እንደገና ሌላው ጋ ይገባል። ከዚያም ይወጣል። ከረንቦላ መጫወቻ ቤት ይሄዳል። . . . እዚያም እንደደረሰ፣ ተጫዋቾቹንና የከረንቡላ መጫወቻወን ጠረንጴዛና ኳሶች ትኩር ብሎ ቆሞ ያስተውላል።
ይኽ ትዕይንት ለሱ የዕለት ተዕለት ኑሮው ነው።
ከእነዚህ ቀናት በአንዱ ግን፣ እንዲህ ሆነ። …. በዚው በለመደው ቤት የከንቡላ ጨዋታ እያስዋለ ሳለ፣ ድንገት ሳይታሰብ . . . “ማዕበል ! ማዕበል ! እጄን አትልቀቂ ! . . . ጀልባውን ይዤዋለሁ እጄን አትልቀቂ ! ሲል አንቧረቀ። በአንድ እጁ ጀልባውን፣ በሌላኛው እሷን እንደሚጎትት ያህል ሰውነቱ ተወጣጠረ። ጮኸ ! ተጣራ ! ከረንቦላ ቤቱ ላፍታም ቢሆን በጸጥታ ተሞላ። ሁላችንም በአንክሮ ወደ እሱ ተመለከትን። በአዕምሮው አንድ ነገር እንዳስታወሰ ዓይኖቹ ፈጠጡ። እንባው በፊቱ ላይ ቦይ ቀዶ ቁልቁል መንዠቅዠቅ ጀመረ። . . . በከረንቦላው ጠረቤዛ ላይ ያሉትን ድንጋዮች በታተናቸው። ጨዋታውን ተረበሸ። ተጫዋቾቹ ጮኹበት። “ይህንን ቀውስ አስወጡት” ብሎ አንዱ ጮኸ ። ባለቤቶቹ “ውጣ! እንግዳ አትረብሽ” ብለው ገፍትረው አስወጡት።
የእሱን እግር ተከትሎ፣ በከረንቦላ ቤቱ ውስጥ የጦፈ ክርክር ተነሳ። “ይህንን ሰውዬ መምህር ግርማ ቢያገኙት ያድኑታል” አለ አንዱ። “እባክህ ተወን! በዓለም የታወቀው የጀርመን ሃኪም ያላዳነውን እንዴት ነው መምህር ግርማ የሚያድኑት?” አለ ሌላኛው። ክርክሩ ከእሱ አለፈና ወደ መምህር ግርማ ሥራና ተዓምር ተቀየረ። አንዱ የእሳቸው አድናቂ ሌላው ደግሞ ጽኑ ተቃዋሚ ሆነው ይከራከሩ ጀመር።
እኔንም በውል የማላውቀው ስሜት ገፍትሮ ከውስጥ አስወጣኝ። ተከተልኩት። እንደተለመደው ለማጽናናት ሞከርኩ። “ፀሐፊ ነኝ ትል የለም እንዴ?” ሳላስበው ጠየቀኝ። መልሱን ሳይጠብቅ ቀጠለ። “እስቲ ጻፈውና እንይህ? እስቲ ንገርልን ምን እንደደረሰብን ? አቦ ጀግና ሁና ! እውነቱን ጻፈዋ ? ቀውሷል እያሉ ከየአበሻው ቡና ቤት ከሚያባርሩኝ የደረሰብኝን ንገራቸው። ሳሃራን አየሁት. . . ባህሩን አየሁት ብለኸኝ የለም እንዴ ? ጻፈዋ እናንብበው ? ወይስ ሰሃራ ድረስ የሄድከው የአሸዋውን ማማር፣ የቴምሩን ጣእም፣ የፀሃዩን ግለት፣ የሙቀቱን ትእይንት ለማያውቁት ልታሳውቅ ነበር? ወይንስ ዕረፍት አምሮህ ነው ? …. ጉድ እኮ ነው! የኛ ስቃይ ለእናንተ መዝናኛ መሆኑ አይገርምህም ! ” በማለት ሳላስበው በጥያቄ ላይ ጥያቄ እአደራረበ ጠየቀኝ።
“ለመሆኑ ኩፍራን ታውቀዋለህ ? ከሱዳን ተነስተን እስከ ሊቢያ ኩፍራ ድረስ ምን ያህል የሰው ልጅ ስቃይና መከራ እንዳለ ታውቃለህ ? ሳሃራን አቋርጠህ ሰዎች የሚኖሩበት ቦታ ስትደርስ የሚሰማህን ታውቃለህ ? አንተ አታውቅም ! መች ይህን ጉድ ቀመስክና ! አንተ ኤር ኮንድሽን ባለው መኪና ውስጥ ተቀምጠህ አይደል እንዴ ሳሃራን የጎበኘኸው ? እሱንም እንኳ ቢሆን ጻፍና አስረዳቸው. . . መቀወስ ይነሰኝ እንዴ ? ቀውስ ነው እያሉ የሚያሽሟጥጡኝን በውል አስረዳቸው እንጂ ? ዳሩ አንተ ብትጽፈው መች አንብበውት፤ ለእሱ መች ጊዜ አላቸውና፤ አንዳንዶቹም ማንበብ አይችሉም። መታወቂያቸው ላይ ያለውን ስማቸውን እንኳ በውል አያውቁትም እኮ ! . . . እኔ ግን ቀውስ አይደለሁም። እነርሱ ናቸው አውቆ አበዶች። ሙሉ ቀን ድንጋይ ሲያፋትጉ የሚውሉ፣ ቤት ሞልተው በባዶ ሁካታ ሲንጫጩ የሚውሉ፣ ጫት እንደ ከብት እያመነዥኩ በቅዠት ምናብ የሚደሰኩሩ፣ በቁማር ፍቅር ሲነዱ ለሚያድሩ፣ የቡና ቅራሪ ሲጋቱ የሚውሉ፣ እነርሱ ናቸው እንጅ ቀውሶች። …. ህ’ ህ ! …. የህሊና ሚዛናቸው የተዛባ፣ አዙሮ የሚያይ አንገት የሌላቸው፣ የመጡበትን የረሱ፣ የሚሄዱበት ካርታ የጠፋባቸው።” መድረሻቸው ከከንቱ የሆነ ። “ሰው መሳይ በሸንጎ ማለት እነሱ ናቸው።”
“ደግሞ ንገራቸው. . . በሳር ውስጥ ተሸሸጎ፣ ታፍኖ፣ ከኩርፋ ትራቫሎስ ድረስ ያለውን መከራ። ስለ ባሕሩም፣ ስለ ጀልባውም ንገራቸው ለእነዚህ አረመኔዎች። እኔን ቀውሷል እያሉ ከየቡና ቤቱ የሚያባርሩኝን ። ቀውስ ነው በላቸው። በፍቅር ነው ያበደው ይሉ የለም? አዎ በፍቅር ነው የቀወሰው በላቸው። ስለ ፍቅር ምን ያውቃሉ? በሃሳብ የሚገለሙቱ፣ በሥራ ቦዝነው ከረንቦላ የሚጫወቱ፣ ጫት እያመነዠኩ በከንቱ ፍልስፍና ለሚሟገቱ፣ የመንፈስ ድኩማኖች፣ ሲመሽ አንቡላ እየጋፉ በየጎዳናው ለሚጣለዙ ግብዞች፣ አስረግጠህ ንገራቸው። እኔ ሰው ወድጄ ስለሰው ነው ያበድኩት . . . እነርሱ ግን የራሳቸውን ጠልተው ሰለ ሆዳቸው አብደዋል። አዎ አሁን በእኔና በእነሱ መካከል ልዩነት አለ። ይኸውም እኔ ሰው ወድጄ ስለፍቅር እራሴን ሰጥቻለሁ፣ እነሱ ደግሞ ሞራል አጥተው ለሱስ ስብዕናቸውን ጥለዋል።”
“አይገርምም! ለሴት ፍቅር እንዴት ታለቅሳለህ ብሎ ጠየቀኝ እኮ አንዱ። እንዴት አላለቅስም? አለቅሳለሁ እንጂ! ሱዳን ነበር የተዋወቅነው። እዚያ ነው ያፈቀራት በላቸው።”
ሻይ የምትሸጥበት ቦታ ነው የተዋወቅነው። ገንዘብ አልነበረኝም። ርቦኝ ነበር ። ምንም ሳልፈራ መራቤን ነገርኳት። ዳቦና ሻይ ሰጠችኝ። እንደ እናቴም እንደ እህቴም ታየችኝ። ደግነትዋ እንድቀርባት አደረገኝ። በልቼ ስጨርስ ሲርብህ ሁል ጊዜ ና አለችኝ። እኔም ከእሷ አካባቢ መጥፋትን አልደፈርኩም። ስቀርባት ወደድኳት ። ስቀርባት ወደደችኝ ። ተዋደድን። እኔ ገንዘብ አልነበረኝም። ከውጭ ይልኩልኛል ብዬ የተማመንኳቸው ወንድሞቼና እህቶቼን በቃላቸው አላገኘኋቸውም። ታሪኬን ነገርኳት። አዘነችልኝና እኔ አለሁልህ አለችኝ። ገንዘብ ሠርተን አውሮፓ እንደርሳለን አይዞህ አለችኝ። ከወንድሞቼና ከእህቶቼ ያጣሁትን የሰው እምነት እንደገና የሰጠችኝን ካላፈቀርኩ ማንን ላፍቅር?”
“ንገራቸው ለእነዚህ ብኩኖች! ሻይ ሽጣ ነበር ወደ ሊቢያ የምንሄድበትን የከፈለችው። ያንን ሁሉ መከራ አልፈን አብረን ነበር ሊቢያ የደረስነው። ካንተ አልለይም ብላ አብራኝ የተሰቃየችው። ሳጣ ያጣችው፣ ሳገኝ የተደሰተችው፣ የፍቅር ማጀቴ ነበረች እኮ ። አንድ ለእኔ የተፈጠረች፣ ውብ ቆንጆ፣ ደግ ለሰው አዛኝ፣ ጠይቅ ድፍን ሱዳንን፣ ጠይቅ ድፍን ሊብያን፣ ማን እንደነበረች ይነግሩሃል። . . . እርጉዝ እኮ ነበረች፣ የመጀመሪያው ልጄ እናት፣ አውሮፓ እናሳድጋለን ስንል ነው እኮ ጥላኝ የሄደችው፣ እንዴት አላብድ? እንዴት አልቀውስ፣ እንዴት አላለቅስ፣ ለእሷ ያልታበደ ለሌላ ለማን ይታበድ?”
“እነዚህ ስለ ፍቅር ምን ያውቃሉ? እነዚህ ከልጃቸው አፍ ቀምተው ለቁማር የሚገብሩ እብዶች እኔን እንዴት ቀውስ ይሉኛል? እነሱ አሉ አይደሉም እንዴ ጨርቃቸውን ያልጣሉ በቁም ሙቶች። ይህንን ቀውስ አስወጡት ሲሉ በጫት አፋቸው ሲለፈልፉ አያፍሩም እኮ።”
ነገሩን ለማወቅ ቸኩዬ “. . .ታዲያ ለምን ተጣላችሁ? የትነች ያለችው? እናስታርቃችሁ እንጂ. . .?” ብዬ ጠየቅኩት። ዓይኑን ፈጠጥ አድርጎ አይቶኝ ። ቀጠለ።
“እኔ ጠቤ እንደነሱ ከሰው አይደለም። እኔ ጠቤ ከተፈጥሮ ነው። ከበረሃው ነው በልልኝ፣ ከማዕበሉ ጋር ነው በልልኝ። ያንን የሳሃራን በረሃ አቋርጠን ሊቢያ ስንደርስ ደስታችን ብዙ ነበር ። መለያያችን መድረሱን መች አስብንና። ሁለት ወር ሊቢያ ውስጥ ተደብቀን ኖርን። በተለይ እሷ ራሱዋን ደባብቃ አስቀያሚ ለመምሰል ትጥር ነበር። የእሷን ቁንጅና ያዩ ሊቢያኖች እሷንም እንደማይለቋት እኔንም እንደማይለቁኝ አውቀን ነበር። ለነገሩ ሁላችንም ተደብቀን አልነበረም የምንኖረው? እዛ ነበር እርጉዝ መሆኗን የነገረችኝ ። የመደንገጥም፣ የመደሰትም፣ የማዘንም ስሜት ተሰማኝ። እንደ ምንም ገንዘቡ ተከፍሎ፣ ጀልባው ተዘጋጀና ጉዞ ጀመርን። የሊቢያን የባሀር ክልል ስንወጣ ጀልባው ላይ ችግር እንዳለ ተረዳን። ከአንድ ወገን ያሉ ሰዎች በተፈጠረው ግርግር ወደ እኛ አካባቢ መጡ ። ጀልበዋ ተገለበጠች። ብዙዎቹ ሰመጡ። እኔ እጇን እንደያዝኳት እሷም እጄን እንደያዘችኝ ነበር ጀልባው መስጠም የጀመረው። በአንድ እጄ እሷን በሌላው ጀልባውን እንደያዝኩ፣ እሷ ደግሞ በአንድ እጇ እኔን በአንድ እጇ ባዶውን ጀርካን እንደያዘች ነበር። ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ሳይታሰብ ማዕበል ተነሳ። ይህንን ጊዜ ስትጸልይ ነበር። ፈጣሪ ላልተወለደው ልጃችን ብለህ ማረን፣ ማዕበሉን አቁምልን እያለች ነበር የምትጸልየው፣ ማርያምን ነበር የምትማጸነው።”
“በአንድ እጄ እሷን በአንድ እጄ ጀልባውን ይዤ ነበር ማዕበሉን ለመቋቋም የታገልኩት። በከፍታ የተነሳው ማዕበል ውሃውን ፊታችን ላይ ስለረጨን አፈነን። እጄን ለቀቀችው። ለመያዝ ሞከርኩ አልቻልኩም። እሷም ታገለች። ስሜን እየጠራች ጮኸች። ከአጠገቤ ድምጿ ራቀኝ። ድምጿ በአራቱም ማዕዘን ይሰማኝ ጀመር። ወዴት ልሂድ? ዋና አልችል። እዚህ ነኝ ብዬ መለስኩ። አበድኩ፣ በዚያ ጨለማ ምን ላድርግ፣ አበድኩ፣ ጮኩ፣ ምን ልሁን? ሌሊቱን ሁሉ ተጣራሁ፣ ድምጿ እየራቀ መጣ። እንዲሁ እንዳበድኩ ምሽቱ እየነጋ መጣ። ጠዋት ላይ የለችም፣ ትልቅ መርከብ መጥቶ እኛን አዳነን፣ ጀሪካኑን በሩቅ አየሁት። ፈለኳት ነገር ግን ላገኛት አልቻልኩም፣ የለችም። ከዚያ ቀን ጀምሮ መንፈሴ ታወከ፣ ህሊናየ ተነካ፣ ሰላሜና ፍቅሬ አብሮ በማእበል ዳግም ላይመለስ ተወሰደ፣ እኔም የሰውና የመንፈስ ደሃ ሆንኩ። አበድኩ፣ ቀወሰኩ። ንገራቸው ለምን እንደቀወስኩ። መቼም አይሰሙህም። ቁማር ተበልቶ አበደ ብትላቸው ነበር የሚሰሙህ!”
“ለእነዚህ ሃይማኖት ለሌላቸው ግብዞች። ለእሷ ያላበድኩ ለማን ልበድ?. . . ለማን ልቀውስ? እንደነርሱ ለቁማር፣ ለጫት፣ ለዝሙት . . . ? ጂኒ ባሕር ላይ መታው አይደል የሚሉህ? አዎ! የባህር ነውጥ ጭካኔና የሰው ፍቅር ማዕበል፣ የሳህራ በረሃ አባዜና የሰው ልጅ ውዴታውና ውለታው ነው እሱን ያቀወሰው በላቸው። እንደ እናንተ በየመሸታ ቤቱ ከበርቻቻና ጫት ቁማርና አደንዛዥ ዕጽ አይደለም እኔን ያሳበደኝ ብሏል በላቸው። መቼም ስለደነዘዙ አይሰሙህም እንጅ፣ ንገራቸው። ሰው ለሰው እንደ ተፈጠረና እንደሚኖር ሁሉ፣ ሰው ለሰው እንደሚሞትም ይወቁ።”
ካለኝ በሁዋላ፣ ጥሎኝ እያለቀሰ ሄደ። እያነባ፣ እየጮኸ፣ እያጉተመተመ፣ ሄደ . . . የባህሩ ጂኒ፣ የባሕሩ ጋኔል ነው ፍቅሬን የወሰዳት እያለ ሄደ። ቀን ከሌሊት አነባለሁ፣ አለቀስሳለሁ፣ ለእንባና ለሃዘን ቀጠሮ የለውም ጸጋዬ አንተም አልተረዳኸውም እያለ ፈጠን ፈጠን እያለ ሄደ።
መከራ ሲመጣ አይነግርም አዋጅ ፡
ሲገሰግስ አድሮ ሌት ይደርሳል እንጅ
እንዲሉ፣ ጸጋዬ ተሳስተሃል፣ እኔ ዛሬም ነገም አነባለሁ፣ ዓይኔ እስከሚከዳኝ አነባለሁ። የሰው ልጅ አሳር ፍፃሜ እስከሚያገኝ፣ ፍቅር፣ ደግነት ልግስናና ርህራሄ ሚዛን እስከሚደፋ፣ ፣ የሰውልጅ ሃብቱ ሰው መሆኑ እስኪታወቅ ድረስ ዛሬም ነገም አነሆ አለቅሳለሁ.፣ማዕበሉ ፀጥ እስከሚል አነባለሁ . . እያለ እያጉተመተመ፣ ከዓይኔ ራቀ።
ተፈጸመ
(ግንቦት፡ 2015 ዓ.ም)
Beljig.ali@gmail.com
• በፍራንክፈርት ከተማ የሊቢያንና የደቡብ አፍሪካን ሰማዕታት ለማስታወስ በተዘጋጀው የሐገር ፍቅር ሥነ ጥበብ ዝግጅት ላይ የቀረበ በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ልብ ወለድ።
በምርጫው ውጤት ሊተላለፉ የተፈለገው መልእክት ምንድን ነው?። ዳዊት ዳባ
ምርጫው ወያኔ በሚፈልገው እንደውም ባቀደው መንገድ አጠናቋል። “እረጭ ያለ ምርጫ”። እስከቅርብ ጊዜ እንዲደርሰን የተደረገው መረጃ ምርጫውን በመቶ ፐርሰንት ማሸነፋቸውን ነበር። አሁን ለይቶለታል። በመቶ ፐርሰንት ማሸነፋቸውን ብቻ ሳይሆን በተወሰኑት ምርጫ ጣቢያዎች ላይ አገኘንም የሚሉት ድምጽም በተመሳሳይ መቶ ፐርሰንት እንደሆነም ነው። ሌብነቱ እንዳለ ሆኖ ምርጫውን ከዚህ በተሻለና በሚመስል መንገድ ከውኖ በመንግስትነት ለመቀጠል መሞከሩን የሚያውቁት ነበር። አልፈለጉትም እንጂ መቶ ከመቶ ከሚለው በተጓዳኝ አሁንም እንደ አንድ አማራጭ አይተውት ነበር ብሎ በእርግጠኛነት መናገር ይቻላል። የሩቆቹ ነጮቹ አለቆቻችንም የተሻለ ብለው የመከሩት ይህንኑ እንደነበረም እየሰማን ነው። ታዲያ ለምን? መቶ በመቶውን ምርጫቸው አደረጉት።
አንደኛው ምክንያት ነገሮችን ከተለመደው በጣም ባፈነገጠ መንገድ ማድረጉን ደጋግመው ተጠቅመውበት ፍቱን የሆነ መላ ሆኖ ስላገኙት ነው። አሁንም ይህው መላ ህዝብን ተስፋ በማስቆረጥ ተገዥነቱን ለማስቀጠል የጠቅማል ብለው ስላሰቡ ነው። ሁለት በአገር ውስጥ የሚደረገውን በይበልጥም ሰላማዊ የሆነውን ትግል ማከርከርያ ለመምታት ነው።
መታወቅ ያለበት ተገዥነትም ሆነ ገዥነት የጭንቅላት ጨዋታ አለበት። ትክክል ናቸው አይደሉም የሚለውን እናቆየውና ለሀይሉ እራሱን ፍፁም በሆነ ሁናቴ ያስገዛው አገሬው ነው ብለው ሰዎቻችን ያምናሉ። ይሄን ምርጫ ያከናወኑበት ጠቅላላ ሁናቴ ይህ እምነታቸው ምን ያህል ስር የሰደደና ለውሳኔያቸውና ለድርጊቶቻቸው ሁሉ መሰረት መሆኑን ነው የሚያሳየን። በዚህ 24 አመት ውስጥ ተመሳሳይነት ያላቸውን ድፍረትና ንቀት ያለባቸውን ተግባራቶች ብንዘረዝር ከአንድ ሚሊዬን ምክንያቶች ውስጥ የዚህ ምርጫ ውጤት አንዱ ብቻ ሆኖ ነው የምናገኘው። ስልሳ ጀነራሎች ካንድ ዘር ሶሙ ስንል ሌላ ስልሳ ጀነራሎች አሁንም ከራሳቸው ዘር ሾመዋል። ተገዥ አድረገንዋል የሚለው እሳቦት ለውሳኔ ዋንኛ መሰረት እስከሆነ ተገዥ እንደሆንን እንድንቀጥል ጉልበታቸውን አግዝፈው ማሳየት ደግሞ አለባቸው። መቼም ልናሸንፋቸው የማይቻለን እንደሆነም ደጋግመው ሊያስታውሱን ግድ ይላል። በተጓዳኝ ደግሞ የትኛውንም አይነት የኛመገዳደር ኮስሶ እንዲታይ ማድረግ ደግሞ አለባቸው። አይቀጡ ቅጣት የሚያስቀጣም ተደርጎ እንዲወስድም ይፈለጋል። ለማንኛውም ይህ ሁሉ አዲስ አይደለም ሗላ ቀር ተብሎ የተተው ነው እንጂ ድሮ በባርያ ስረአት ዘመን ባርያ ለማሳደር ሲጠቀሙበት የነበረ ነው።
መቶ በመቶ አይነት እርምጃ በዋናነት ተገዝቶልናል ብለው ከሚያስቡት ህዝብ በላይም ማማ የሆናቸው ክፍል እንደተሸከመ እንዲቀጥል በእጅጉ አስፈላጊ ስለሆነም ነው። ጦሩ፤ካድሬው፤ የፓርላማ ምናምንቴው፤ አንድ ለአምስት የተደራጀው፤ አጋር በሚል በየዘሩ ያሰባሰቡት…። ፈቅደው ተጠቃሚ አደረጉት እንጂ ያው ተገዥቸው አድርገው ነው የሚያዩት።
ይህ ሰው ያንድ አውራጃ አስተዳዳሪ ነው። ባለቤቱን ቀድሞ ውጪ ልኳል። አሁን ላይ እፎይታ ሊሰማው አልቻለም። በዚህ ምርጫ ሰበብ ስራ በዝቶበት ጭንቅም ላይ ነው የሰነበተው። ከነልጆቹ ከቤቱ ለቆ በመሳርያ የሚጠበቅ ቦታ ከቶ ነበር። ልጆቹን በመሳራያ እያስጠበቀ ትምህርት ቤት ማመላለስ ድረስ ፈርቷል። በደወለ ቁጥር እነዚህን ልጆች ከዚህ በቶሎ ማውጣት እንዴት አቃተሽ። የዚህ አገር ሁኔታ አይታመንም። አስፈሪ ነው። አንድ እራሴን ሁኔታዎች ሲብሱ ወደጎረቤት አገር በቶሎ መሻገር እችል ነበር። እነዚህ ልጆች ግን ምን አድረጌ። ሲያለቃቅስ ነው የከረመው።
ስርአቱ ውስጥ የዚህ ግለሰብ አይነት እጅግ በዙ ናቸው። የዚህ አይነቶቹ በእርግጥም መቶ ከመቶ ካልሆነ ባነሰ ውጤት በጭራሽ አይፀኑም። ዋናው ነገር ቁንጮዎቹ እዚህ ድረስ ያሳስባቸዋል። ያስባሉም። ልብ ልንለው የሚገባ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ትንሽ ለቀቅ አድርገው ቢሆን ዘንድሮ እኛም የተዘረፍነው ድምፅ ጨምረንም ነፃነታችንን መጠየቃችን አይቀርም ነበር። በመቶ በርሰንት
እንዳሸነፉን ሲነግሩን ደነገጥን። መቶ በመቶው በዚህ አኳያም እንደሚጠቅም አስበውበታል ማለት ይቻላል። በተጨማሪም በሰላማዊው ትግል ውስጥ ድርሻ እያደረጉ ካሉ ዜጎች ውስጥ የተገኘውን ያህል ተስፋ ቆርጠው አብዛኞቻችንን የሚመስሉ ከተገኙም የሚለው አለበት።
Graham Peebles አሳምሮ ገልፆታል።
The recent election was an insult to the people of Ethiopia, who are being intimidated, abused and suppressed by a brutal, arrogant regime that talks the democratic talk, but acts in violation of all democratic ideals.
“ፈላጭ ቆራጭ አንባገነን ሆናችሁ ያለምህረት ስትቀጠቅጡ የኖራችሁትን ህዝብ ምርጫ ተደርጎ እኛን መረጠን ማለት ስድብ ነው። እናውቃችሗለን ስለዲሞክራሲ ትቀደዳላችሁ ነግር ግን አንዳቸውን የዲሞክራሲ እሴቶች እንኳ ማክበር የተሳናችሁ ደናቁርቶች ናችሁ።”
{ይሄ አሸነፍን ለዛውም በመቶ ፐርሰንት የሚለው ለይልቃል ወይ ለሰማያዊ፤ ለመድረክ ወይ ለመራራ ነው ካልን በትልቁ እራሳችንን እየሸነገልን ነው። ትግሉም ካኛ ጋር ነው። መልክቱም ለኛ ለዜጎች ነው።}
ሁለተኛው በአገር ውስጥ የሚደረገውን ሰላማዊውን ትግል ለማድቀቅ ከተቻለም እስከመጨረሻው ለማጥፋት ነው። ስርአቱ ድርጅቶችን እስከነብሳቸው እየበላ ነው። ብዙ ሺ ሰላማዊ ታጋዬች እስር ቤት ነው ያሉት።። በስቅላት መግደል ሁሉ ጀምረዋል። ባአጠቃላይ ሰላማዊ ትግሉን ብቻ ሳይሆን እውነተኛ ታጋዬችን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማጥፋት ቆርጠው የተነሱ ነው የሚመስለው። ለነገሩ በቅጥቀጣ የሚጠፋ ቢሆን ኖር ድሮ ይጠፋ ነበር። ስለዚህም በተጓዳኝ አይሰራም ብለን እንድናምን ማድረግ አለባቸው። ይህንን ነው ያደረጉት። የሚቀጥለውን የምርጫ ድራማ ካሁኑ የመስራትም ጉዳይ አለበት። ሰይብል ነው ያሉት ሰርተውታል ማለት ይቻላል።
ሰላማዊውን ትግል በተመለከተ ደግሞ ግማሹን ስራ በርትተን ለረጅም አመታት እኛም ስንሰራበት ነው የከረምነው። ስለዚህም በቀላሉ ተፈጻሚ ሊሆን የሚችል ሆኖ ታይቷቸዋል። የድርሻችንን ማድረጉን ዛሬም ቀጥለናል። አጉልተን አገር ውስጥ የሚደረገው ሰላማዊ ትግል አይሰራም፤ አያስፈልግም ማለት የጀመርነው ከምርጫ 97 ማግስት ነው። ይህው ላለፈው አስራ አንድ አመት አካባቢ እየተለዋወጥን ሰርተንበታል። አንዱ ቡድን ሲደክመው ወይ መሳሳቱን አውቆ ሲተወው ሌላው እየተቀበለ እስካሁን ቀጥሏል። ዛሬ የጉጀሌው የኛም ጥረት ተደምሮ ሰላማዊ ትግል አያስፈልግም የሚለው የብዙዎች እምነት ነው። እንደውም ሰላማዊ ትግል አይሰራም የሚለው ይዘቱን ቀይሮ መታገል አያስፈልግም ወደሚለው አድጓል። እግዚአብሔር እንዳመጣቸው እሱ አንድ ነገር ያድርግ ብቻ አይደለም በተፈጥሮ በሂደት ታመውና አርጅተው ይሞታሉ የሚባሉ አነጋገሮች መስማት የተለመደ ሆኗል።
የተዘራው ነው የሚታጨደው።
ደቡብ ኦሞ ደራሼ ውስጥ በጊዶሌ አውራጃ መምረጥ የሚችለው የህዝብ ቁጥር 11773 ለለምመረጥ የተመዘገበው 646 ነው። ንብን የመረጠ 431፤ ጃንጥላን 171፤ ሌላ ሰምቼው የማላውቅ ድርጅትን 44 ህዝብ ነው የመረጠው። በሌሎች ምርጫ ጣብያዎች ውጤት ቢገለጽ ከጊዶሌው ብዙም ልዩነት የሚታይበት አይመስለኝም። ምን አልባት በኦሮሚያ ክልል በተወሰነ ደረጃ ልዩነት ሊኖረው ይችላል።የምርጫው እለት በቀጥታ ስርጭት በፌስ ቡክ፤ በሳይቶች በመወያያ መድርኮች ስለምርጫው አፈፃፀም ይተላለፉ የነበሩ የቀጥታ ምስክርነቶችን ስሰበስብ ነበር። ባብዛኛው ምርጫ ጣቢያ የምርጫ ካርድ የወሰዱና ሊመርጡ የወጡት አንድ ላምስት የተደራጁ ደጋፊዎች መሆናቸውን የሚያሳይ መረጃ ነበር በብዛት የሚመጣው።
ይህ ስኬት ከተባለ መቼስ ማል ጎደኒ ብቻ ነው ማለት የሚቻለው። ይሄ ቁጥር ግን የሚያስፈራ ነው። መጀመርያም ቢሆን የሀይሉ አማራጭ ውጤታማ የሚሆነው በሰላማዊው ትግል መቃብር ላይ ነው የሚለው በጥንቆላ ይሆናል እንጂ እስራተጃዊ ሆነ ፖለቲካዊ ፋይዳው ተሰልቶ የተደረሰበት አይደለም። ይህ ተስፋ መቁረጥን እንጂ ተሳትፎ በመንፈግ የማሳጣት ትግልም አይደለም። ሲጀመር ካገዛዙ ባህሪ አኳያ የማሳጣቱ ትግል በዋናነት ፋይዳው እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ በሁሉም ወገን ስምምነቱ አለ። ከባድ ያደረገው ይህንን አይነት አቋም እንድንወስድ ያደረጉን ገፊ ምክንይቶች የተሳሳቱ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ዘርፈ ብዙ የሆኑ ተጓዳኝ ጉዳዬችን አካቶ የተያዘ አቋም ባለመሆኑ ነው። መስሎን ነው እንጂ የጎዳነው ባጠቃላይ ትግሉን ነው። በዋናነት በሀይል የሚደረገውን ትግል። ንቁ ድርሻ ምርጫውላይና ሰላማዊው ትግሉ ላይ ከነበራቸው ዜጎች ነው የመሳርያውን ትግል እየተቀላቀሉ ያሉት። ሰላማዊ ትግሉን ዜጎች በሚሊዬኖች ጉዳዬ ብለው ይዘውትና ተሳትፈውበት ቢሆን ኖር ትግሉ ወደ ህዘባዊ እንቢተኛነት የማደግም የተሻለ እድል ነበረው። እረጭ ያለ ምርጫ ሲያቅዱ እረጭ ማድረግ ነው መዳኒቱ ትግል አይደለም።
ስለተጠያቂነት ከሆነ ምርጫ ያልነው ተጠያቂነትን በዋናነት መውሰድ ግድ ይልብናል። ምርጫውን እንደ መብቱም እንደ አንድ ትግልም መወስድና ተሳትፎ ማድረግ ይገባቸው የነበሩ ዜጎች በዚህ ደረጃ በማነሳቸው። የነበሩ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ አስገብቶም ቢታይ ልንሰራቸው ይገቡ የነበሩ ነገር ግን ያልሰራናቸው ስራዎች ብዙ መሆናቸውን አጋላጭ ነው። ተጠያቂነቱ በተዋረድ ይቀጥላል። ህዘብም ቢሆን በማኩረፍ ሆነ ተስፋ በመቁረጥ ጠብ የሚል መብት የለም። ቀላል የሆነው የዚህ አይነት ትግል ላይ እንኳ ድርሻ ለማድረግ አቅማችን የተሟጠጠ ዜጎች እዩት የሰራነውን።
“If there is no struggle, there is no progress. Those who profess to favor freedom, and yet depreciate agitation, are men who want crops without plowing up the ground. They want rain without thunder and lightning. They want the ocean without the awful roar of its many waters. This struggle may be a moral one; or it may be a physical one; or it may be both moral and physical; but it must be a struggle. Power concedes nothing without a demand.It never did and it never will.”
― Frederick Douglass
“ትግል ከሌለ የሚሻሽልና የሚለወጥ ነግር የለም። ነጻነትን አብዝተው እያሹ ምንም አይነት አስተዋፆ ለማድረግ ተነሳሽነት የሌላቸው ሰዎች ሳያርሱ አዘመራን ማጨድ የሚጎመጁ አይነት ናቸው። ነጎድጓድና መብረቅ የሌለበትን ዝናብ ያልማሉ። ማእበል የሌለበትንም ውቂያኖስ እንዲሁ። ተገደው ካልሆነ ገዥዎች ፈቅደው የሚሰጡት ጠብታ ነፃነት የለም። አይኖርምም። መገደዱ አለባቸው። ማስገደዱ በሀይል ይሆናል ወይም ተሽሎ በመገኘት። ወይም በሁለቱም። የግድ ግን መታገል አለብን።”
ለነጻነት ለሚደረገው ትግል ወገንተኛ የሆኑ የበዙት መገናኛዎች ምርጫውን በሚመለከት ለጥፋቱ ድርሻቸው ከፍ ያለ ነው። ሀላፊነት አለመወጣት ብቻ ሳይሆን አፍራሽ ሚናቸው የጎላ ነበር ባይ ነኝ። ይህንን ለማሳየት አስቤው የነበረው በትንሹ ከምርጫው ሶስት ወር በፈት ጀምሮ በጣም ካነሰም አንድ ወር ውስጥ ሽፋን የተሰጣቸውንና የተሰራባቸውን ቁምነገሮችን ሁሉ በዝርዝር በሰንጠረዥ ማስቀመጥ ነበር። አንገብጋቢነቱ፤ አንድምታው፤ ህዘብ እንዲወስደው የተፈለገው የጠራው መልእክት። ቃላት ምርጫው። ሆን ብሎ ማንኳሰስ ነበር አልነበረም?። ተስፋ አስቆራጭ ነበር አበረታች?። ምርጫው ውስን በሆነ የጊዜ ሰሌዳ የሚካሄድ ነው። አጥኖትና ቀዳሚነት አግኝቷል አላገኘም?። በምርጫ ቅስቀሳው የነበረ ድርሻ ካለ። የመሳሰሉት ወሳኝ ጥያቄዎች በማንስት መገናኛው የነበረውን አስተዋፆ ማሳየት ነበር። በዚህ እሳቦት ሳዳምጠው ሳገላብጠው ስቦረብረው ስለነበር ተልቅ የሆነ የጥፋት ድርሻ እንደነበራቸው ግልጽ ብሎ ማየት ችያለው። ክሴን ከዚህ በላይ ላመረው እችል ነበር። ቢቸግር ነው እንጂ ይህም በራሱ ዱላ ማቀበል ነው። ልተወው።
አገር ውስጥ የሚደረገውን ትግል እንደግፋለን የሚሉ ድርጅቶችና ድጋፍ ማህበራትም ሀላፊነታቸውን ባግባቡ አልተወጡም። መሽኮርመም ይታይባቸው ነበር። ለታሪክ መዝገብ ቤት የሚቀመጥ አቋም መግለጫ ከመጻፍ የዘለለ አልነበረም አስተዋፆቸው። ይህን ያህል የሰው ድርቀት አለ ወይ ነው የሚያሰኘው። የተያዘውን አቋም እንኳ በካሜራ ፊት መናገር ታቡ ነበር። የፖለቲካ ትግል መናገርን አብዝቶ ይፈልጋል።
እንደዚሁ ተጠያቂነቱ ይቀጥላል አብያተ እምነቶች ህዝብን ወደአምላክ መመለሱ አንድ ነገር ነው። የግድ የተራበና ነጻነት የሌለው ባርያ መሆን ግን የለበትም። ይህ ክፉ ስራ ነው። አምላክም አይደሰትበትም። ስርአቱን አያገለገላችሁ ያላችሁ ዜጎች በይበልጥም ቀለም የቀመሳችሁ ሁሉ መቶ ፐርሰንት ህዘብ አሸነፍኩህ እንዲባል አድርጋችሗል። ይህ ንቀት ነው። ይህ በህዝብ ላይ ማላገጥ ነው። ለዚህ ድርሻችሁ የጎላ ነውና የደረስንበትን ደረጃ እስቲ ቆም ብላችሁ እዩት።
ወያኔ እንዳቀደው ምርጫው እረጭ ያለ እንዲሆን እገዛ ያደረጉ ሌሎች አስተሳሰቦች።
- ትግል መሆኑ ቀርቶ ምርጫ ስለተባለ ብቻ ፍታዊ ምርጫ ይደረግና ድምጽ ተሰጥቶ፤ ጠብ ሳይል ድምጽ ተቆጥሮ አብላጫ ድምጽ ያገኛ ስልጣን መያዝ አለበት። ይህ ካልሆነ ምን ያደርጋል። የሚገርመው ይህንን የምንጠብቀው ዛሬም ከወያኔ ነው።
- የሚገለውም የገደለውም ምርጫ ጫወታ ውስጥ ስለምትገቡ ነው። ይህ ሲታገሉ የሞቱትንና የታሰሩትን ተጎጂ አድርጎ ማየትና ነገ የሚገደሉትን አስገዳይ አሳሳሪ አድርጎ መፈረጅ ድረስ ይሄዳል። ይሄ ፍርደ ገምድል መሆን ብቻ አይደለም ጭካኔም ነው።
- በምርጫው የታሰተፉ እውነተኛ ተቃዋሚዎች የመጨረሻ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል እንዴትም እንደሚመጣ ምንም ብዥታ በጭራሽ አልነበራቸውም። አይደለም ለራሳቸው ለህዘብ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ አስረግጠው ሲናገሩት በጥረታቸውም ሲገልፁት የነበረ ነው። ይህ በሆነበት እያወቁ ለምን ተሳተፉ የሚለውን ጥያቄ ቆም ብሎ ለሰከንድ እንኳ ለማሰብ አለመፈልግ። በቃ ለስልጣን ነው ብሎ መደምደም።
- ትግል የሚያካሂዱበትን ነባረዊ ሁኔታ በጭራሽ ግምት ውስጥ አለማስገባት። ፍቃድ ጠይቀው የሚሰለፉት ፈሪዎች ስለሆኑ ነው። ትግሉን ከሰላማዊ ወደ ህዝባዊ እንቢታ ያላሳደጉት እየተቻለ ስለሚፈሩ ነው። በመንግስት ታውቀው በግላጭ እየሰሩ መሆኑ እየታወቀ በሚስጥር የማይደራጁት እየቻሉ ነግር ግን ጥቅሙ ስላልታያቸው ነው። አቅምና ጉልበታቸውን ግምት ውስጥ ሳያስገቡ በዛ ላይ ድርሻም እገዛም በሌለበት ውጤትና ተግባር አብዝቶ መጠየቅ። ሲጀመር ታጋዬች ለህዘብ ወይስ ህዘብ ለታጋዬች ነው ጉልበት መሆን የሚገባቸው። በሁለቱም አቅጣጫ ያስኬዳል ብንል እንኳ እስከ ድክመቶቻቸው እነሱ መራራ መሰዋትነት እየከፈሉ ትግሉን ቀጥለዋል። እኛስ?።
አገር ቤት ያሉ ሰላማዊ ታጋዬች ምርኩዝ የያዘ የተቀዳደደ ድሮቶ የለበሰ ባዶ እግሩን የሚሄድ ሽማግሌ ቢሆን እንኳ በርታትና ጉልበት ሆነነው፤ አፅድተን ሱፍ አልብሰነው አሸናፊ ማድረግ መናቃችን ግድ ይለዋል። ፍቱንም ነው።
የሰላም ትግሉ በኢትዮጵያ (ክፍል ፪) አንዱዓለም ተፈራ
በክፍል አንድ፤ የሰላማዊ ትግሉ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ምን እንደሆነ ገልጫለሁ። በዚሁ ላይ፤ የሰላማዊ ትግሉ ከተወዳዳሪ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ጋር ያለውን ልዩነት አሳይቻለሁ። በተጨማሪ ደግሞ፤ የሰላማዊ ትግሉ የሚካሄደው በአንድ የሕዝባዊ ንቅናቄ ድርጅት ሥር ብቻ መሆኑንና፤ አማራጭና ተለዋጭ እንደሌለው አስምሬበታለሁ። በሂደቱ መሰባሰቢያ የሆኑትን ሀገር አቀፍ የትግል ዕሴቶች አስቀምጫለሁ። በዚህ ክፍል ሁለት ደግሞ፤ ስለተሳሳተው የሰላማዊ ትግሉ ግንዛቤያችን አስረዳለሁ። ባጠቃላይ፤ የሰላም ትግሉ ከትጥቅ ትግሉ አኳያ ለምን እንደሚመረጥ በግልጽ አሰፍራለሁ። በማጉላትም በአሁኑ ሰዓት፤ የሰላማዊ ትግሉ አማራጭ የሌለው ብቸኛ የትግል መንገዳችን መሆን እንዳለበት አመላክታለሁ።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ስለሚካሄደው ሰላማዊ ትግሉ ያለን ግንዛቤ ጉድለት አለው። አንዳንዶቻችን፤ ገዥው አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ስለሚያስር፣ ስለሚገድል፣ ከሀገር ስለሚያሳድድ የሰላማዊ ትግሉ አይሠራም እንላለን። ሌሎቻችን ደግሞ፣ በምንም መንገድ፤ ገዥው አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ወዶ ሥልጣኑን ስለማይለቅ፤ በምርጫ መሳተፉ ዋጋ የለውም፤ ስለዚህ የትጥቅ ትግሉ ብቻ ነው የሚያዋጣ፤ በማለት ሰላማዊ ትግሉን እናዋድቃለን። ይህ በመሠረቱ በሀገራችን ያለውን አስከፊ የፖለቲካ ሁኔታ ከመመልከትና ይህ የገዥ ቡድን ላንዴም ለሁሌም እንዲወገድ ከመፈለግ የተነሳ መሆኑ ግልጽ ነው። ችግሩ ግን ፍላጎት የታሪክን ሞተር አያሽከረክርም። ተጨባጩ የሀገራችን እውነታና ያንን ለመለወጥ በቦታው የዋለው ተግባር፤ ሂደቱን ይነዳዋል።
ትግሉ በአምባገነኑ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርና በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ነው። ትግሉ ሀቅ ነው። ትግሉ አንድ ነው። በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን በኢትዮጵያ ካለው ሰላማዊ ትግል ባሻገር ያለውን በማካሄድ ላይ ያሉት፤ አንድም የዚህ ወይንም የዚያ አካባቢ ነፃ አውጪ ግንባር ናቸው፤ አለያም ይህ ወይንም ያ ድርጅት ነው። የኢትዮጵያን ሕዝብ አሰባስቦ በአንድ ያሰለፈ ሕዝባዊ ድርጅትም ሆነ ጦር የለም። ስለዚህ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድ ወገን፤ የገዥው አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት በሌላ ወገን የተሰለፈበት ትግል አልተያዘም። እናም ይህ እስካልሆነ ደረስ፤ ትግሉ የሕዝቡ አይደለም ማለት ነው። በርግጥ ሁሉም ድርጅቶች የሕዝብ ነን ማለታችውና ለሕዝብ ነው የምንታገልው ማለታቸው አይቀርም። ከሆነ ለምን በአንድ አይሰባሰቡም? ይህ የሕዝቡ የነፃነት ትግል የማይሆነው፤ የሚታገሉት ለራሳቸው ጠባብ የግል የድርጅታቸው ዓላማና ግብ ስለሆነ ነው። በራሳቸው ጠባቡ የድርጅት ፍላጎትና በሕዝቡ ፍላጎት መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። አለያማ ሁሉም የሕዝቡን ፍላጎት እንከተላለን ካሉ፤ በአንድ ይሆኑ ነበር። እንግዲህ በዚህ ጠባብ የድርጅት መነፅር ሁሉንም ነገር ስለሚመለከቱ፤ የድርጅቶች መፍትሔ ከዚሁ ይመነጫል።
የነሱን ድርጅት የበላይ አድርጎ የማያስቀምጥ ሂደት ሁሉ፤ “ትክክል” አይደለም። ለዚህ ነው ሰላማዊ ትግሉን የሚኮንኑት። በትክክለኛ መንገድ መኮነንም ተገቢ ይሆናል። ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ መኮነን ግን ተገቢ አይደለም። ሰላማዊ ትግሉ፤ ገዥውን ክፍል ለማስወገድ የሚደረግ ንቅናቄ እንጂ፤ ገዥውን ለመተካት የሚደረግ ሩጫ አይደለም። ሰላማዊ ትግሉ፤ ያለው የገዢ ቡድን መወገድ አለበት ብሎ የተነሳ ሕዝብ፤ የሚወስደው የፖለቲካ እርምጃ ነው። ማንኛውም የትግሉ እንቅስቃሴ፤ በመሳተፍ ተወዳድሮ ለማቸነፍ ሳይሆን፤ የውድድሩን መድረክ፤ ሕዝቡን ለመድረሻና ለመቀስቀሻ ለመጠቀም ነው። ሰላማዊ ትግል ሽርሽር አይደለም። መስዋዕትነት ይከፈልበታል። የኛ ታጋዮች እየከፈሉበት ነው። ሳሙዔል አወቀ ከፍተኛውን መስዋዕት ከፍሏል። ሌሎች ቀድመዉታል፤ ሌሎችም ይከተሉታል። ለዚህ ነው ይህ ገዥ አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት መወገድ ያለበት። እና “ምርጫ ተወዳደረን እንድንጥለው ካልፈቀደልን፤ ሰላማዊ ትግሉ አበቃለት!” ማለት፤ ሰላማዊ ትግልን አለማወቅ ሳይሆን፤ ሆን ብሎ ማደናገር ነው። ሰላማዊ ትግል፤ በምርጫ ለማቸነፍ የሚደረግ እንቅስቃሴ ይደለም። በምንም መንገድ በምርጫ የሚቸነፍና ወዶ ሥልጣኑን የሚለቅ አምባገነን ጠላት የለም።
እኔ የሰላማዊ ትግሉን የምቀበለው፤ ፍጹማዊ ከሆነ ከትጥቅ ትግሉ ይበልጣል ከሚል ውሳኔ ተነስቼ አይደለም። በምንም መንገድ ትጥቅ ትግልን አልኮንንም። በአሁኑ የኢትዮጵያ የትግል አሰላለፍ፤ የቅንጣት ታክል ማመነታታት ሳይኖረኝ፤ የሰላማዊ ትግሉ ያላማራጭ ብቸኛ መንገዳችን መሆን አለበት እላለሁ። ለምን? አሁን አንድ የሆነ የትግል ማዕከል የለንም። እያንዳንዱ ድርጅት፤ ለድርጅቱ ግብ የሚታገልበት ሀቅ ነው ያለው። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ለግሉ ታግሎ ሥልጣን ጨብጧል። የያንዳንዱ ድርጅት ትግል፤ ያንን ለመተካት ነው። ውጪሰው ኢትዮጵያዊ ታጋዮች ደግሞ፤ አንድነት ከመመስረት ይልቅ፤ በመከፋፈልና እርስ በርስ በመነካከስ፤ ቁጥራቸው የበዙ ድርጅቶችን መሥርተን፤ በሕዝቡ ትግልና ድል ላይ ልናደርግ የምንችለው አስተዋፅዖ አመንምነነዋል። ዋናውን ጉዳይ ትተን በጠባብ ዕይታችን ታፍነን፤ ሩቅ ማየት አቅቶን ዓይናችን ስለጨፈን፤ የትግሉ ባቡር ጓዙን ጠቅልሎ ጥሎን እየሄደ ነው። እርስ በርስ መነኳኮሩ ጥሞናል። ከዕለት ዕለት መበጣጠስና መቀናነሱ አልቆረቆረንም።
አሁንም ባለንበት ስናዘግም፤ ትግሉ እኛን ታግሎናል። ይልቁንም ከኛ ተከትለው የትግሉን ችቦ የሚያበሩት ታጋዮች፤ መልሰው መላልሰው እንደኛው በተለመዱት፤ ሀገር ወይስ ድርጅት፣ የሰላማዊ ትግል ወይስ የትጥቅ ትግል፣ ከውጭ መደራጀት ወይስ በሀገር ቤት መንቀሳቀስ፣ ከኤርትራ መነሳት ወይስ ኤርትራን በጠላትነት የትግሉ አካል ማድረግ፣ በየግል ድርጅቶች መታገል ወይስ የትግል ማዕከል መፍጠር፤ በሚሉ አንድ ቦታ ላይ በማይደመደሙ ንትርኮች እንዳይጠመዱ ያሰጋል። ከዚህ ወጥተውና የእስከዛሬውን ትግል መርምረው፤ ትምህርት በመውሰድ፤ የአንድነት ትግል የሚያደርጉበትን ሁኔታ ማስተካከል አለብን። ይኼን የማቀርበው፤ በትግሉ ሳይሆን፤ አሁን በውጭ ባለነው ታጋዮች ያለኝ እምነት እየመነመነ በመሆኑ ነው።
ሰላማዊ ትግል፤ ለሚታገሉለት ሕዝብና ሀገር፤ ለኢትዮጵያዊያንና ለኢትዮጵያ፤ የመጨረሻ ከፍተኛውን ቦታ በመሥጠት፤ ከግለሰብ የኔነት ጋር የተያያዙትን በሙሉ፤ የግል ጥቅም ሆነ የድርጅት ግብ ወደ ኋላ ገፍቶ፤ ቅድሚያ ለወገንና ለሀገር የሚሠጡበት ትግል ነው። ትግሉ፤ ገዥውን ወገንተኛ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር አምባገነን መንግሥትን ድል ማድረግ ብቻ ሳይሆን፤ የሚከተለውን ሥርዓት ወሳኝ የሆነ ነው። ትግላችን ከፍተኛ ጥንካሬን ይጠይቃል። ትግላችን ወሰን የለሽ ትዕግስትን ይጠይቃል። ሞትን መናቅን ይጠይቃል። ይህ ሰላማዊ ትግል፤ የሕዝቡ ትግል ነው። ሰላማዊ ትግል፤ ታጋዮች በሕዝቡ መካከል ተገኝተው፣ የአካባቢው አካል ሆነው፣ የአካባቢው ብሶት የራሳቸው ብሶት ሆኖ፣ ከተባሰው ጎን ተሰልፈው፣ ከፍተኛውን መስዋዕትነት እየከፈሉ የሚያካሂዱት ትግል ነው። የድርጅቶች ትግል አይደለም። ሰላማዊ ትግሉ በሕዝቡ የሚደረግ ነው። ሰላማዊ ትግሉ ሁሉን አስተባባሪ ነው። የማንም የግል ድርጅት ንቅናቄ አይደለም። ሰላማዊ ትግሉ ደጋፊው ብዙ ነው። ሰላማዊ ትግል የተወሰነ አባልነትን ብቻ ያነገበ የአንድ ክፍል ጥረት አይደለም። ሰላማዊ ትግሉ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪሰው ኢትዮጵያዊያን ዘንዳ ድጋፍና ተቀባይነትን ይሻል። በዚህ ዓይን ስንመለከተው ነው፤ የኛን አስተዋፅዖ ትርጉም የምናበጅለት።
የትጥቅ ትግሉ ተገቢ ቦታና ጊዜ አለው። አሁን ባለንበት ሀቅ፤ አንድ ማዕከል በሌለበት ሁኔታ፤ እያንዳንዱ ድርጅት ለራሱ መርኀ-ግብርና ግብ በቢታገልበት እውነታ፤ የታጠቀው ጦር የድርጅቶች መሣሪያ በሆነበት ጊዜ፤ የትጥቅ ትግሉ በጣም አደገኛ ነው። ሀገራችንን ወደ መበጣጠስ ያመራታል። በተለይም አብዛኛዎቹ የታጠቁት የነፃ አውጪ ግንባሮች መሆናቸው፤ አደጋዉን ያበዛዋል። እናም የሰላማዊ ትግሉ በጥረታችን አንድ ማዕከል አበጅቶ፤ ትግሉን እንድንቀጥልና ለድሉ እንድናበረክት ይጠራናል። ለሰላማዊ ትግሉ ቆርጠን እንነሳ። በሂደት አንድ ማዕከል ሲፈጠር፤ ሂደቱ ራሱ የሚያስከትለውን አዲስ ክስተት ከዚህ ሆኖ መገመት ከባድ ነው። በወቅቱ ግን ሂደቱን ተከትሎ እምነታችን መቀየር እንዳለበት ጥርጥር የለኝም።
eske.meche@yahoo.com http://nigatu.wordpress.com
የ“ኢህኣዴግ” ግምገማና ፍሬው በገለታው ዘለቀ
በድርጅት ከዚያም ከፍ ብሎ በመንግስት ደረጃና በሃገር ደረጃ ግምገማ ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ ሁሉ ያምናል። የኣንድ ድርጅት ብቃትም በግምገማው ችሎታና ጥራት ሊለካ ይችላል።የኣንድ ሃገር የፖለቲካ መረጋጋት በፖለቲካ ለሂቆቹ የጠራ የሃገር የምናብ ስእልና ብስለት ሊለካም ይችላል። የፖለቲካ ቤቶች ሲኮለኮሉ፣ ፖሊሲዎች ሲቀረጹ ከፍ ያለ ግምገማን ይጠይቃል። ሃገሪቱ ያለፈችበትን የህይወት ጎዳና፣ የገጠማትን ችግር መንስዔና ውጤቶች በሰፊው መገምገም ለሚመሰረቱ የፖለቲካ ድርጅቶች መሰረትና ለሚቀረጹ ፖሊሲዎች ጥራት ወሳኝ ነው። እንግዲህ በሃገራችን ኢትዮጵያ ግምገማ በሰፊው የተወራለት ጉዳይ የሆነው በዚህ መንግስት ጊዜ ነው። ህወሃት በጫካ ኑሮው ጊዜ የነበረው ማህበራዊ ህይወትና የትግሉም ባህርይ የየቀን ውሎውን እየገመገመ እንዲሄድ የሚያስገድድ ሁኔታ ውስጥ ስለከተተው በግለሰቦች ድክመትና ጥንካሬ ዙሪያ ሲገማገም ነው ያደገው። የግምገማው ዓይነት ኣውጫጭኝ ኣይነት ግምገማ ተፈጥሮ ያለው ነው። በመርህ ደረጃ ግምገማ መኖሩ በራሱ ጥሩ ሆኖ ሳለ የግምገማውን ባህርይና ያመጣውን ፍሬ ማየት ግን ኣለብን።
ህወሃት “ኢሃዴግ” ስልጣን ከያዘ በሁዋላ የመጣው ይህ ግምገማ ከድርጅት ኣልፎ ታች በየመስሪያ ቤቱ እንዲሁም ገበሬው ድረስ ወርዶ እንደነበር ይታወሳል። ባህሪው ለየት ያለ በመሆኑና ያልተለመደ በመሆኑ ኣስተማሪዎችን፣ የህክምና ባለሙያዎችን፣ የግብርና ባለሙያዎችን ወዘተ ግራ ኣጋብቶ ነበር። ግራ ያጋባበት ምክንያት በሃሳብ ደረጃ መጥፎ ስለሚባል ኣይመስለኝም። ችግር ያመጣው ኣውጫጭኝ ኣይነት በመሆኑና ከሲስተምና ከፖሊሲ ይልቅ በግለሰቦች ባህርያትና ክህሎት ብቃት ላይ ያተኮረ በመሆኑ እንዲሁም የግምገማው መስፈርት የጠራ ባለመሆኑ የግለሰቦችን ግላዊ ህይወት ሳይቀር ኣደባባይ በማውጣቱ መዘበራረቅን ኣምጥቶ ነበር።
“ኢሃዴግ” ግምገማ ሲል በጣም የሚብከነከነው በኣክተሮቹ ፣ በሲስተሙ ተዋንያን ላይ በመሆኑ የግለሰቦቹን ድክመትና ጥንካሬ በኣደባባይ ኣውጥቶ መወያየት ኣንድን የስራ ሃላፊ ወይም ባለሙያ ያለውን ጠንካራ ጎንና ደካማ ጎን ኣብጠርጥሮ በገበያ ላይ ማውጣት ነው ትልቁ ግምገማ። የሰውን ልጅ ይለውጠዋል የሚል እምነት ኖሮት እንደሆነ ኣላውቅም። የግምገማው ስነ ልቦና ትንሽ ለየት ይላል።ግለሰቦች ባህርያቸውን በጥልቀት ይገመገማሉ። በተለይ በፖለቲካ ድርጅቶች ኣካባቢ የሚበሉበትን የሚጠጡበትን ቤት ሁሉ እያነሱ ማብጠልጠል ሁሉም በየማስታወሻው በኣንድ ኣባል ላይ የያዘውን እያወጣ ድክመት ነው ያለውን በጉባዔ ፊት ለዚያ ሰው መግለጥ ዋና ተግባር ነው።ህወሃት በግለሰቦች በተለይም በታችኛው ኣካል ኣካባቢ ግምገማውን ያብዛ እንጂ እንደ ድርጅት እንደ ሲስተም ሲበዛ ሚስጥረኛና ግልጽነት የጎደለው ድርጅት ነው።
“የኢህ ኣዴግ” ኣይነቱ ግምገማ በሌሎች ኣገሮች ከሚደረጉ ግምገማዎች ሁሉ የሚለይ ይመስላል። በግምገማ ክህሎትን፣ ባህርይን ለማረቅ የሚሞክር ኣካሄድ ይመስላል። የድርጅት ኣባላት ሲናገሩ በኣንድ ሰው ዙሪያ ሁለት ቀን ድረስ የሚፈጅ ግምገማ የሚደረግበት ጊዜ ኣለ። ውሳኔ ያንስሃል፣ ትፈራለህ፣ ታዳላለህ፣ ከእከሊት ጋር ትወጣለህ፣ ብስለትና እድገት ኣይታይብህም፣ ሙስና ውስጥ ገብተሃል፣ ከእከሌ ጋር ያለህ ቅርበት በዝቱዋል፣ ከእከሌ ጋር ለምን ተኳረፍክ፣ ትኮራለህ፣ ኣድርባይ ነህ፣ ወዘተ ወዘተ…. እየተባለ የሚገመገም ብዙ ሰው ኣለ። ኣባላት ሁሉ እየተነሱ ግለሰቡን ቁጭ ኣርገው ያብጠለጥላሉ። ሂስህን ዋጥ፣ ኣልውጥም… ዋጥ፣ ኣልውጥም… ብዙ ሰዓት ይፈጅና ተገምጋሚው “ውጫለሁ” ካለ ይታለፍና ሌላው በተራው ደግሞ እንዲሁ ይብጠለጠላል። ኣንዳንዴም ኣባላት በሆነ ነገር ያናደዳቸውን ሰው ለማጥቃት ሲያስቡ በዚያ ሰው ዙሪያ ሲሰልሉ፣ ድክመት የተባሉትን ሲያሰባስቡ ይቆዩና በግምገማው ሰዓት ኣንጀታቸውን የሚያርሱበት መድረክ እንደሆነም ይነገራል። በኣጠቃላይ እምነቱ ግን የሰዎችን ድክመት በተለይ በኣደባባይ በማውጣትና በመግለጥ የሰው ልጅ ይማራል፣ ምን ኣልባትም በግል በሱፐርቪዥን ከሚድረገው ግምገማ ይልቅ በኣደባባይ በቡድን ፊት መጋለጡ ለባህርይ ለውጥ የተሻለ ነው የሚል ነገር ይመስላል። ኣጠቃላይ ሂደቱ ባህርይንና ክህሎትን ለመቅረጽ ነው ብለን በቅንነት እንውሰድና በተግባር ግን በተለይ በሃገር መሪዎች ኣካባቢ ሰፋ ባለው በሃገር ደረጃ በርግጥ ይህ ኣካሄድ የሚፈለገውን ለውጥ ያመጣል ወይ? ህወሃት “ኢህዓዴግ” በዚህ የግምገማ ስልቱ የተሻሉ መሪዎችን ኣፈራልን ወይ? ኣገራችን መሪዎችን ኣገኘች ወይ? ግልጽነትና ተጠያቂነት እያደገ ሙስና ቀነሰ ወይ? ኣድረን ወደ ዴሞክራሲ ተመነደግን ወይ? የሚለውን መገምገም ተገቢ ነው። ግምገማ ቀላል ነገር ኣይደለም። ፍርድ ነው። ለዚህ ደግሞ ከፍ ያለ ተመልካችነትን የሙያ ቅርበትን ይጠይቃል። “ኢህኣዴግ” ግምገማ የሚለው እርስ በርስ ከተሞሸላለቁ በሁዋላ ሂስ በመዋጥና ባለመዋጥ የሚቋጭ ነው ። ከዚህ በላይ ግን የግምገማው ውጤት ከፍትህ ጋር ጥብቅ ቁርኝት የሌለው ተገንጥሎ የወጣ ነው። ለማናቸውም ግን ግምገማው ጥሩ ነው ጥሩ ኣይደለም ከሚለው በላይ ለዛሬው ጽሁፍፌ መነሻ የሆነኝ ምን ትርፍ ኣገኘን? የሚለው ጉዳይ ነው ::
ከፍ ሲል እንዳልኩት “ኢህኣዴግ” ከተፈጠረ ጀምሮ ከዚያም በፊት በህወሃት ጊዜ ግምገማ በተለይም በግለሰቦች ላይ ያነጣጠረ ግምገማ የሚካሄድ ሲሆን በርግጥ ከዚህ ፍሬ ኣግኝተን መሪዎችን ኣፈራን ወይ? መሪዎቹ ክህሎት ጨመሩ ወይ? ትህትናና ዴሞክራሲ፣ የህግ የበላይነት በመሪዎቹ ኣካባቢ እያደገ መጣ ወይ? ብለን ኣጥብቀን መጠየቅ ኣለብን። ኣቶ ኣባዱላ ገመዳ ላለፉት ሰላሳ በላይ ኣመታት የሰላ ግምገማ ተካሂዶባቸው ኣሁን ክህሎት ጨምረዋል ወይ? ። “ኣዎ!” ከተባለ ከሰላሳ ዓመት በፊት ምን ዓይነት ሰው ነበሩ ማለት ነው? ብለን እንደመማለን። ለኣርባ ኣመት ገደማ የተገመገሙት እነ ኣባይ ጸሃየ፣ እነ ሳሞራ፣ እነ ስዩም ወዘተ በዓርባ ዓመት ግምገማ ውስጥ ኣልፈው ለምን የተሻለ ስብእና ኣላዳበሩም? እነ ኣዲሱ ለገሰና እነ ስብሃት ነጋ ሌሎች መሪዎች በዚህ ግምገማ ተወቅረው…. ተወቅረው …..ተወቅረው….. ምን ወጣቸው? እንዴውም በተግባር የምናየው ህግን ሲጥሱ፣ ኣድረው ጭካኔ ሲያሳድጉ፣ ዴሞክራሲ እንዳያድግ ሲያደርጉ ነው። ይህን ስናይ የዚህ “የኢሃዴግ” ግምገማ ጉዳይ የሆነ ችግር ያለበት መሆኑን እንረዳለን። በዚህ ዙሪያ ነው ኣንዲት ትንሽ ኣስተያየት ለማቀበል የፈለኩት። ቅን የሆኑ “የኢሃዴግ” ኣባላትም ይሰሙኛል ብየ ኣምኜ ነው።
በሃሳብ ደረጃ እንዲህ ኣይነቱ ግምገማ ጥሩ ቢመስልም የሳተው ትልቁ ነገር ግን ሊፈጥር ያሰበው ስብእና መያዣ ኣቁማዳ ተበጅቶለት ኣናይም። የግምገማው ሂደት “ኢሃዴግን” ራሱን እንደ ድርጅት በሲስተምና በፖሊሲ ደረጃ ኣብጠርጥሮ ከመገምገም ይልቅ በኣክተሮቹ፣ በግለሰቦቹ የግል ባህርይና ክህሎት ላይ በማተኮሩ የሰላሳ ኣመቱ ግምገማ ፍሬ ኣላመጣም። ኣንዳንዶቹን እንዴውም በደንብ ኣድርጎ ያደነዘዛቸው ይመስላል። ግምገማን ከመልመዳቸው የተነሳ “ሂሴን ውጪያለሁ” ምንትሴ…… እያሉ ማለፉን መርጠው ለውጥ ሳይመጣ ቀርቶኣል። ኣንዳንዶቹም የሰው ሃጢያት ሲዘረዘር ደስ እያላቸው የግምገማ ጊዜ ሱስ የሆነባቸው ይህን ጊዜም የሚደሰቱበትም እንዳሉ ይሰማል። “የኢሃዴግ” ግምገማ ውጤታማ እንዳይሆን ያደረገው በግምገማ መድረኩ ለማጠብ የሞከረውን ኣባላቶቹን ኣጣጥቦ ኣመድ ላይ መጎለቱ ነው።። ለምሳሌ ኣንድ የፖሊስ ተጠሪ ለህገ መንግስቱ ታዛዥ ኣይደለህም ወዘተ….. ተብሎ ቢገመገምና ሂሱን ውጦ ከመድረክ ቢመለስ ነገ የት ነው የሚገባው? መቼ ፖሊስ ራሱ ነጻ ተቋም ሆኖ ተፈጠረ? የብር ዋጋው ሲወርድ (devaluate ሲደረግ) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ሃላፊ ሳያውቅ በሚወሰንበት ኣገር እንዴት ሆኖ ነው ይህ የባንክ ሃላፊ ውሳኔ ያንስሃል፣ ኣቅም ያንስሃል፣ ወዘተ እየተባለ ሊገመገም የሚችለው? በነጻነት መፍረድ በማይቻልበት ኣገር እንዴት ሆኖ ነው ኣንድ ዳኛ በሙያው የሚገመገመው? ዋናው ችግር ይህ ተቋም ነጻ ኣለመሆኑ ሲሆን ግለሰቡን ገምግመው ኣብጠልጥለው ሂሱን ኣስውጠው ቢልኩት ነገ ሄዶ የሚቀመጠው ኣመድ ላይ ነው። ለዚህ ነው ግምገማው ሲስተሙን ራሱን ጨክኖ የሚፈትሽ ባለመሆኑ የግለሰቦች ኣውጫጭኝ ሆኖ የሰላሳና የኣርባ ዓመት ፍሬው ባዶ የሆነው።
“ኢሃዴግ” ባለፉት ኣመታት ከግለሰቦች ኣውጫጭኝ ይልቅ ሲስተምን የሚያይ “የኢሃዴግን” ተፈጥሮና ፖሊሲዎቹን በሚገባ የሚገመግም ቢሆን ኣገሪቱ ወደ ተሻለ ዴሞክራሲና ልማት ታድግ ነበር። “ኢሃዴግ” ጨክኖ ራሱን እንደ ሲስተም እያየ ምርጫ ቦርድን ነጻ ኣድርገን ፈጥረናል ወይ? ወታደሩ ነጻ ነው ወይ? ፍርድ ቤት ውስጥ ጣልቃ ኣንገባም ወይ? ባንኮችና ኣጠቃላይ የሃገሪቱ ተቋማት በነጻነት ይሰራሉ ወይ? ህወሃት “በኢሃዴግ” ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ ምን ኣደረገው? ይህ ትክክል ኣይደለም! የብሄር ፖለቲካ የመጨረሻ ግብ ኣለው ወይ? እኛ ራሳችን ተሰባስበንበታል የምንለው “ኢሃዴግ” በርግጥ በዚህ ዓለም በህይወት ኣለ ወይ? በኢትዮጵያዊነት ጽንሰ ሃሳብና “በኢሃዴግ” ተፈጥሮ መካከል ያለው ዝምድናና መስተጋብር ምን ይመስላል? የቱን ያህል ጥብቅ ነው? ኣብዮታዊ ዴሞክራሲ ምንድነው? በህገ መንግስቱና በኣብዮታዊ ዴሞክራሲ መካከል ምን ዝምድና ኣለ? የብሄር ፖለቲካና የዴሞክራሲ መርሆዎች ኣብረው ይሄዳሉ ወይ? ህወሃት ለዖህዴድ ምኑ ነው? ወዘተ… ደግሞም ግምገማ በጣም በበዛበት ዘመን በሃገራችን የነበረ ጉቦ እንዴት ወደ ሙስና ያድጋል? እጅግ ብዙ ጥያቄ ለማኝ የሆኑ ጉዳዮች ስላሉ እነዚህ በሚገባ ቢገመግሙ የተሻለ ቤት መስራት ይቻል ነበር። ማህበራዊ ሃብትን የሚንከባከብ የህብረተሰቡን ኢነርጂ የማይቃረን ስርዓትና ፖሊሲ ከተፈጠረ በዚያ ውስጥ የሚኖረው ግምገማ የተሻለ ፍሬ ባመጣ። በመከላከያ ኣካባቢ በኢኮኖሚው ኣካባቢ የህወሃት የበላይነት መታየት የለበትም፣ ኣንድ ግለሰብ ሰረቀ ተብሎ ለሁለት ቀን የሚገመገም ከሆነ የህወሃት ድርጅታዊ ሙስና ለምን በሰፊው ኣይገመገምም? የመሳሰሉትን ስናይ የዚህ መንግስት ትልቅ ችግር ግምገማው ሲስተሙን ጨክኖ የሚገመግም ኣለመሆኑ፣ የሚፈራ በመሆኑ ነው። ሲስተምን ችላ ብሎ ሙስና በተጠናወተው ሲስተም ውስጥ ጥሩ መሪዎችን ለማውጣት መሞከር ኣይቻልም። ታጥቦ ጭቃ ነው የሚሆነው።በድርጅት ህይወት ውስጥ መጀመሪያ መታየት ያለበት ቤቱ ንጹህ ተደርጎ መሰራቱን ነው። ቤቱ ካልጸዳ በውስጡ ያሉት ኣይጸዱም:: ዝም ብለን ብንቀጥል ደግሞ እጥበቱ ድብኝት ኣጠባ ነው የሚሆነው።
በሃገራችን ኣጠቃላይ የፖለቲካ ቅርጽ ኣካባቢ ይህ ችግር ይታየኛል። ሃገራችንን ኢትዮጵያን ተፈጥሮዋንና ማንነቱዋን በሚገባ መረዳት፣ ያለፈችበትን ህይወት በሚገባ መገምገም ችግሮቹን ኣንጥሮ ማውጣት የቀረን ይመስለኛል። ለዚህም ነው ዛሬ ኣንዱ የብሄር ጥያቄ ኣንዱ የግለሰብ እያለ በሁለት ውጥረት ውስጥ የወደቀችው። ችግርን በሚገባ ኣለመለየትና ኣለመገምገም ወደፊት ለምንሰራው የፖለቲካ ቤትም ሆነ ፖሊሲ ተጽእኖው ከባድ ነው። በመሆኑም “የኢሃዴግ” ኣባላት ጨክነው “ኢሃዴግን” ተፈጥሮውን የህወሃትን ግዝፈት የተቋማትን ነጻነት ኣብጠርጥረው ቢገመግሙ ነበር የምንለወጠው። ይህ ግን ኣልሆነም። ህወሃት በግምገማ ስም የበታቾቹን እያመሰ የሃገሪቱን ሃብት ሲቦጠቡጥ ነው የሚታየው። “ኢሃዴግ” በግለሰቦች ኣካባቢ ግምገማ ጊዜ ያለውን ጭካኔ በሲስተም ላይ ማሳየት ኣይፈልግም። እንዴውም ግምገማን የማይፈልገውን ሰው ለመቅጫም ጥሩ መሳሪያ ኣድርጎ በሚገባ ሲጠቀምበት ይታያል።
“ኢሃዴግ” ቁጭ ብሎ ግምገማውን ራሱን መገምገም ነበረበት። ኣርባ ኣመት የተገመገሙትን ሰዎች እያየ ለምን ወደ ፍጹምነት የተጠጋ ስብእና ኣላዳበራችሁም ብቻ ሳይሆን እንዴት በዚያ ግምገማ ውስጥ ኣልፋችሁ ክፋትንና ተንኮልን ትጨምራላችሁ? ብሎ መጠየቅ ካልቻለ እሴት ኣልጨመረም። ነጻ ያልሆኑት ኣቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ውሳኔ ላይ ደካማ ነዎት፣ ይህን ጉዳይ በሚገባ ኣልተወጡም ሊባሉ ኣይችሉም። ከዚህ ይልቅ “የኢሃዴግ” ኣባላት ቆራጥ ቢሆኑ ጠቅላይ ሚንስትሩ ሃይል የላቸውም! እንደ ቃል ኣቀባይ ኣይነት ነው ስራቸው በሚል የህወሃትን ጣልቃ ገብነትና እጅ ኣዙር ኣገዛዝ መገምገም ፍሬ ያመጣ ነበር። ለኚህ ሰው የፈጀው ሰፊ የግምገማ ሰዓት ድራማ ከመሆን የሚያልፈው ተገምግመው ሲያበቁ ነጻ በሆነ የሃላፊነት ወንበር ላይ የሚቀመጡ ሲሆን ነበር። የቡድን ኣመራርን መቃወሜ ኣይደለም። ይሁን እንጂ በቡድን ኣመራር ስም የህወሃት ፈቃድ ብቻ በሚፈጸምበት ኣገር የኣቶ ሃይለማርያም ድርሻ ከቃል ኣቀባይነት ያለፈ ስራ ስለማይሆን ይህን ደፍሮ የሚሰብር ጠንካራ ግምገማ ያስፈልጋል።
በግምገማ ጊዜ ስለ ሙስና ተነስቶ ሰዎች ይወቀሳሉ። ኦዲተሮች ግን በነጻነት ኣይሰሩም። ኣንዳንዱ በሙስና የሚገመገመው ኦዲት በማይደረግ መስሪያ ቤት ነው። ኦዲት ተደርጎ የኦዲት ሪፖርቱ በማይታወቅበት መስሪያ ቤት የሚሰሩ ኣንዳንድ ግለሰቦችን በግምገማ ላይ ማንሳቱ ምን ኣልባትም በሙስና ስም ለማጥቃት ካልሆነ ፍሬ የሌለው መሆኑ ይታወቃል። ሳይንሳዊ ይሁን ስንልም በኣሰራርና ስራንና ሰራተኛን በማገናኘት ሊስተካከሉ የሚችሉትን በቡድን ኣውጫጭኝና ሂስህን ዋጥ ኣልውጥም ሊስተካከል ኣይችልም።
ከዚህ በፊት ኣንድ የብዓዴን ኣባል ኣናግሬ ኣውቃለሁ። ይህ ሰው በድርጅቱ ውስጥ ስልጣን ያለው ነው። እንዴውም የድርጅት ጉዳይ ሆኖ ነበር። እንዴት ነው እናንተ ብዓዴኖች ህወሃትን ኣታሙትም ወይ ? ብየ ጠየኩት:: በደንብ ነው ውጭ ውጭውን የምንንሾካሸከው ብሎኛል። ኦህዴድም እንደዚሁ ነው። ይህ የሚያሳየው በጣም በተበላሸ ሲስተም ውስጥ ነው ግለሰቦች እየተብጠለጠሉ ያሉት። ይህ ደግሞ ለድርጅቱም ለሃገርም ለውጥ ኣያመጣም።
ኣንዳንዱ ሰው ደግሞ የሚወቀሰው ከተፈጥሮው ክህሎት ጋር በተያያዘ ነው። ውሳኔ ያንስሃል ሲባል ይህ ሰው ወስን…. ወስን…. ወስን…… ስለተባለ ኣይደለም የሚወስነው።ውሳኔ በኣብዛኛው መረጃን ከመረዳትና ከመገምገም ጋር ነው የሚያያዘው።በተለይ በከፍተኛ ስልጣን ላይ ያለ ሰው ውሳኔ የሚያጥረው ብዙ ጊዜ የሚመጡ መረጃዎችን የመተንተንና በኣእምሮ የመሳል ኣቅም ሲያጥረው ይመስለኛል:: ባለስልጣን ሆኘ ባላየውም። የውሳኔና ኣመራር ችሎታ በትምህርትና ከተፈጥሮም ጋር ከተያያዘ ተሰጥዖ ጋር ሊሄድ ይችላል። በስብሰባ ኣባላት ስለጮሁበት ኣይደለም። በዚህ መልኩ የመሻሻል እድል ጠባብ ነው የሚሆነው። ኣንዳንዱ ሰው ትላልቅ ፒክቸሮችን በኣይምሮው የማየትና የመደመም(a strong impression) ብሎም ውሳኔ የመስጠት ተሰጦ ላይኖረው ይችላል። ፖሊሲ ውሳኔ ነው። ሚሊዮን ህዝቦችን ተጽእኖ ሊያደርግ የሚችልን ፖሊሲ ሲያመጡ ወስነው ነውና ለዚህ ምናብ ኣስፈላጊ ነው። በሌላ በኩል ቴክኒካል የሆኑ ጉዳዮችን የመፈጸም ኣቅምና ፍላጎት ያላቸው ለዚህ ስራ ስሜታቸው የሚነቃቃ ሰዎች ደግሞ ኣሉ። በመሆኑም ስራና ሰራተኛን ማገናኘት የሚፈታውን ችግር “ኢሃደግ” ከየቦታው ታዛዞቹን ይሰበስብና የማይገባ ቦታ እየሰጠ እንደገና ደግሞ ኣቅም ኣነሰህ እያለ ይገመግማቸዋል። ስራና ሰራተኛን ማገናኘት በራሱ የሚፈታቸውን ጉዳዮች ችላ ማለት ኣገራዊ ኪሳራው ሰፊ ነው።
በየደረጃው ያሉ ባለስልጣናት መረጃዎችን የሚያዩበት መጠነ ርእይ ይለያያል። የታችኛው ኣካል በተወሰነ ኣጥር ውስጥ የሚያይ ሲሆን ወደ ላይ ከፍ ያሉ ባለስልጣናት ደግሞ በሰፊ ስኮፕ ያዩታል። ከፖሊሲና ከማህበራዊ ተጽእኖ (Impact) ጋር ስለሚያዩት የሚደመሙት በዚህ ሰፋ ባለ ተጽእኖና በዚያ ተጽእኖ ውጤት ላይ ነው። ለዚህ የሚመጥኑ ሰዎችን በየደረጃው ማስቀመጥ የተሻለ ሲሆን በፖለቲካ ታማኝነት ብቻ ኣንዱን የቴክኒክ ሰው ሚንስትር ማድረጉ ኣገሪቱን በጣም ጎዳት። ከግምገማ ይልቅ በትምህርት ሊበለጽጉ የሚችሉትን መለየት፣ ግምገማውን ሳይንሳዊ ማድረግ ግለሰቦችን ብቻ ሳይሆን በተለይ ሲስተምን የማጽዳት ስራ መስራት ጠቃሚ ነበር። ስኮፕ የሌላቸውን ሰፋ ኣድርገው ማየት የማይችሉትን ኣጉሮ ኣጉሮ ምንም ለውጥ ማምጣት ኣይቻልም። በተበላሸ ፖሊሲ ስር የቱንም ያህል የግለሰብ ግምገማ ብናካሂድ ኣንለወጥም።ኢትዮጵያ ትታየናለች ወይ? የጥንት ኣባቶች ድካም ይታየናል ወይ? ስለ ሃገሪቱ ማንነት ስናስብ የጠራ ስእል ኣለን ወይ? እያልን የሚሾመው ቢሾም ይሻል ነበር። ኣንድ የጎዳና ተዳዳሪ ህጻን ሲለምን እኔ ተራው ሰውና ኣንድ ከፍተኛ ስልጣን ያለው ሰው ብናገኝና ብናናግር የሁለታችን ምናብና መደመም መለያየት ኣለበት። እኔ ካለኝ ኣካፍየ ካልሆነ ኣዝኘ እሄዳለሁ። ያ ባለስልጣን ግን ከፍ ካሉ ሃገራዊ ጉዳዮች ጋር ኣገናኝቶ ኣገራዊ ተጽእኖ ሊፈጥር የሚችል ስእል ሊያይ ይገባል። በዚያ ጎዳና ተዳዳሪ ህጻን ምላሽ ፖሊሲን እስከማስቀየር በሚደርስ ሃይል ይህ ባለስልጣን ሊመሰጥበት ሊመታበት ይገባዋል። ስኮፕ እንዲህ ነው። ኢትዮጵያንም ኣጠቃላይ ኣካሉዋን በሚገባ የማየትና የመረዳት ብቃትን ይጠይቃል። ከዚህ ውጭ በኣካባቢያችን ያለችውን ችግር ኣይተን በዚያችው ዙሪያ የፖለቲካ ድርጅት መስርተን ለዚያች ችግር መፍትሄ ለማምጣት ብቻ የምንሞት ከሆነ ኢትዮጵያን ለመምራት ኣንመጥንም። መሪዎቻችን ባደጉበት ኣካባቢ ያዩትን ችግር በሰፊ ምናብ ካላዩት በብሄር ፖለቲካና በኢትዮጵያዊነት መካከል ውጥረት ውስጥ ገብተው ራእይ ኣጥተው ሊኖሩ ይችላሉ። ምናብ ለመሪዎቻችን በጣም ወሳኝ ነገር ነው። ታላቁ መሪ ኔልሰን ማንዴላ ኣንዱ ትልቁ ችሎታቸው ደቡብ ኣፍሪካን በይቅርታ መሰረት ላይ ቆማ በጠራ ምናብ ማየት መቻላቸው ነው። በጣም ግትር ከሆነ የፍትህ ኣስተሳሰብ ኣውጥቶ በዚህ ከፍታ ላይ ያስቀመጣቸው ምናባቸው ነው። ኢትዮጵያ ውስጥም እንዲህ ዓይነት መሪዎችን እንሻለን።
ትልቅ ችግር ያመጣው “ኢሃዴግ” እንደ ድርጅት ራሱን ኣለማየቱ ብቻ ሳይሆን ይህ ኣካል ስልጣን ላይ በመሆኑ ተጽእኖው ኣገራዊ ይዘት እንዲኖረው በማድረጉ ኣሁን ላለንበት ውስብስብ ችግሮች ቀንደኛ ምክንያት ሆነ። የተቋማትን ነጻነት ለመገምገም ወይም የፓርቲውን ጣልቃ ገብነት ለመገምገም ባለሞሞከሩ ዛሬ ምርጫ ቦርድ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ገለልተኛ ኣልሆነም። ዛሬ “ኢሃዴግ”በኣምስተኛው ዙር “ምርጫ” በኦሮሚያ፣ በኣዲስ ኣበባ፣ በትግራይ፣ በኣማራ በደቡብ መቶ በመቶ ማሸነፉን ሲሰሙ “ኢሃዴጎች” ዴሞክራሲ ኣደገ ነው የሚሉት? ያ “ግምገማ” በርግጥ ሃቀኛ ከሆነ የዚህ ድርጅት ኣባላት እምቢኝ ማለት ነበረባቸው።ይህቺን ጽሁፍ ስጭር የቅርቡን የምርጫ ውጤት ሲሰሙ ኣንዳንዶቹ “የኢሕዓዴግ” ኣባላት ምን ይሉ ይሆን? ብየ ኣስቢያለሁ። እውነተኛ ለኣገር ኣሳቢ የሆነ ፓርቲ ውስጥ ነው ያለሁት የሚል ለኣገር ኣሳቢ የሆነ “የኢህዓዴግ” ኣባል በግምገማ ወጥሮ መጠየቅ ኣዲስ ምርጫ መካሄድ ኣለበት ኣለያ ሞቼ እገኛለሁ ማለት ነበረበት፣ ኣልነበረበትም?:: በዴሞክራሲ የሚያምኑ ከሆነ ፣ ከዴሞክራሲ መገለጫዎች መካከል ኣንዱና ዋነኛው ምርጫ ሲሆን ውጥንቅጡ በወጣና ተዓማኒነት በጎደለው ምርጫ መቶ በመቶ ኣሸነፍኩ ሲለኝ በርግጥ ለዚህ መሞት ኣለብኝ።መቶ በመቶ ኣሸነፍኩ ብሎ “ኢሃዴግ” ሲያውጅ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ የሆነ የዚህ ፓርቲ ኣባል ድግሱን ኣይበላም። ኣይበላም ብቻ ሳይሆን ይህ ታሪክ እንዲገለበጥ ኣጥብቆ ይሰራል። ኣለያ ቢሞት ይሻለዋል። ኣሁንም ቢሆን ሃቀኛ የሆኑ የኢህዓዴግ ኣባላት ለለውጥ መታገል ኣለባቸው። በስማቸው የሚነግዱትን ጥቂት የበላይ ኣካላት በመፍራት ዝም ማለት የለባቸውም። ለለውጥ ለተሻለ ስርዓት በቻሉት ኣቅም መታገል ኣለባቸው። ህዝባዊ እምቢተኝነት ሲነሳ ከህዝብ ጎን በመቆም ትግሉን ማፋጠን ይጠበቅባቸዋል። ፖሊሶች፣ ዳኞች፣ የባንክ ሰራተኞች፣ ወታደሮች፣ በኣየር ሃይል ኣካባቢ የሚታየውን ኣይነት ትግል ማፋፋም ኣለባቸው። ይህን በማድረጋቸው ከህሊና ፍርድ ነጻ መሆን ብቻ ሳይሆን ከለውጥ ባሻገር ኢትዮጵያ ትኮራባቸዋለች።
እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!
geletawzeleke@gmail.com