Quantcast
Channel: Abugida Ethiopian American Amharic Web Page
Viewing all 1809 articles
Browse latest View live

አቡጊዳ –የመኢአድ መሪ አቶ አበባዉ ዉህደቱን ላለመፈረም ያቀረቡት ምክንያት በቂ አይደለም ተባለ

$
0
0

የመኢአድ ሊቀመንበር አቶ አበባዉ መሃሪ በደብተራው ፓልቶክ ክፍል ቀርበዉ ባደረጉት ሰፊ ዉይይት፣ በመኢአድ እና በአንድነት መካከል ስላለዉ የዉህደት እንቅስቃሴ ማብራሪያ ሰጥተዋል። «አንድነቶች እኮ ልጆቻችን ናቸው። መኢአድ የነበሩ ናቸው» ያሉት አቶ አበባዉ በመኢአድ እና በአንድነት መካከል የፖለቲካ ፕሮግራም ልዩነቶች እንደሌሉ ተናገረዋል።

«ታዲያ የሁለቱም ፓርቲዎች ምክር ቤቶች ከወሰኑ በኋላ ምንድን ነው ምክንያቱ መኢአድ ለመፈረም ያልቻለው ? » በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ አበባዉ ካቀረቧቸው ምክንያቶች መካከል ሁለቲ ተደጋግመው ተገልጸዋል።

የመጀመሪያ የፓርቲዉን ስምን በተመለከተ እንደሆነ የተናገሩት አቶ አበባዉ «አዲስ ስም ከሚሆን፣ መኢድም፣ አንድነት የሚታወቁ እንደመሆናቸው መኢአድ/አንድነት ይሁን ብለን ነበር፣ እነርሱ ግን በስሙ ንቅናቄ የሚል ቃል ይግባባት ብለዋል» ሲሉ ያልፈረሙበትን አንዱ ምክንያት አስረድተዋል።

«የዉህዱ ፓርቲ መሪዎች ሲመረጡ ፣ መመዘኛ መኖር አለበት» የሚል አቋም መኢአድ እንደያዘ የተናገሩት አቶ አበባዉ፣ በዚህም ጉዳይ አንድነት እንዳልተስማማ ተናግረዋል።

አሁንም የዉህደቱ እንቅስቃሴ እንዳልተቋረጠ የገለጹት አቶ አበባዉ «በሂደት ላይ ነው ያለነው፤ ትግል ነው፤ ተስፋ መቁረጥ የለብንም» ሲሉ በዜናዉ ያዘነዉን የክፍሉ ታዳሚ ለማረጋጋት ሞክረዋል።

የደብተራዉ ክፍል ታዳሚዎች የመኢአድ እና የአንድነት ዉህደት አለመፈጸሙ እንዳሳዘናቸው እየደጋገሙ ገልጸዋል። የቀረቡት ምክንያቶች በጣም ቀላል እና ትንሽ እንደሆኑ የገለጹት አንዳንድ የክፍሉ ታዳሚዎች ፣ አቶ አበባዉ ያልገለጹት ሌላ ምክንያት ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል። በዚህ ጉዳይ ላይም ክፍሉ የአንድነት አመራርን አቅርቦ እንደሚያወያይም አሳዉቋል።

ከመኢአድ ጋር ለዉህደት የሚደረገው ድርድር ከሁለት አመታት በላይ እንደፈጀ ይታወቃል። «ለዚህ ታሪካዊና የሕዝብ ጥያቄ መደናቀፍ ምክንያቱ የመኢአድ ፕሬዘዳንት ሲሆኑ ይህን ሁኔታ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ለሚገኙ ለሁለቱ ፓርቲዎች አባላት፣ ደጋፊዎች፣ በግል ተነሳሽነትና በሀገር ተቆርቋሪነት ስሜት ሁለቱን ፓርቲዎች ለማደራደር ሲደክሙ ለነበሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎችና ለሕዝቡ ጥሩ ዜና ባይሆንም ላለመፈረሙ ኃላፊነቱን የሚወስዱት የመኢአድ አመራሮች በተለይም ፕሬዘዳንቱ መሆናቸውን ማሳወቅ እንወዳለን» ሲል አንድነት ባወጣው መግለጫ የመኢአድ ሊቀመንበርን በዋናነት ተጠያቂ አድርጓል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው የፖለቲካ ተንታኝ፣ የመኢአድ ዉስጣዊ አሰራር ለዉህደቱ መጓተትና አለመሳካት አስተዋጾ እንዳለው ይናገራሉ። የድርጅቱ ላእላይ ምክር ቤት የወሰነዉን ሊቀመንበሩ ከቀለበሱ፣ በመኢአድ ዉስጥ ሊቀመንበሩ ከምክር ቤቱ በላይ ስልጣን እንዲኖራቸው የሚያደርግ አሰራር ሊኖር እንደሚችል ይናገራሉ። በመኢአድ ዉስጥ የመኢአድ የበላይ ጠባቂ የሚባል አቶ ኃይሉ ሻዉል ያሉበት አካል እንዳለ የሚናገሩት እኝህ ተንታኝ፣ ይህ የመኢአድ የበላይ ጠባቂ በሊቀመንበሩ ላይ ግፊት አድርጎም ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን ግምት ገልጸዋል።

«አንድነት ጉልበትና ጊዜ በዚህ ላይ መጨረስ የለበትም። ከመኢአድ ጋር ከሁለት አመታት በላይ ድርድር ተደረገ። ከዚያ በላይ መሄድ አያስፈልግም። መኢአዶች በዉስጣቸው ያለውን ችግር አስተካክለው ከመጡ እጅ ዘርግቶ ይቀበላቸው። አለዚያ ግን እነርሱን ማስታመም መቆም አለበት» ያሉት እኝህ ተንታኝ፣ ፓርቲው በሚሊዮኖች ድምጽ ንቅናቄ፣ በኑሮ ዉድነት ዙሪያ በአዲስ አበባ በሚደረግ የ«እሪታ» ሰልፍ፣ በምርጫ ዘምቻ ላይ እንዲያደርግና በመኢአድ ጉዳይ መጠመድ እንደሌለበት በመግለጽ አስተያየታቸውን ያቀርባሉ።

የአንድነት ፓርቲ መግለጫ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ !


ሲቪል ድርጅቶች –ግርማ ሞገስ

$
0
0

ዴሞክራሲ ስርዓት በመገምባት ላይ በሚገኙ ወይንም የዴሞክራሲ በዳበረባቸው አገሮች ውስጥ እጅግ ብዙ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ተቋሞች ከመንግስት ነጻ ሆነው ይመሰረታሉ። በነፃነት ይንቀሳቀሳሉ። የጋዜጠኞች ማህበሮች፣ የጋዜጠኞች መድረኮች፣ የሰራተኛ ማህበሮች፣ የተማሪ ማህበሮች፣ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች፣ የስነጽሑፍ ማህበሮች፣ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ አሳብ አቀንቃኝ ድርጅቶች፣ የፖለቲካ አሳብ አቀንቃኝ ቡድኖች፣ የህዝብ ጤንነት እና ኑሮ ሁኔታ መሻሻል ተቆርቋሪ ድርጅቶች፣ የመንግስት ግልጽነት ታዛቢ እና አጋላጭ ድርጅቶች እና የመሳሰሉትን ድርጅቶች ማለታችን ነው።

በአንድ አገር የዴሞክራሲ ስርዓት በሃቅ ግንባታ ላይ መሆኑ ወይንም የዴሞክራሲ ስርዓት መዳበሩ የሚለካው እንደነዚህ አይነት በርካታ ድርጅቶችን ዜጎች በነፃ ማቋቋም እና በነፃነት ማንቀሳቀስ መቻላቸው ሲረጋገጥ ነው። የዴሞክራሲ ስርዓት በሚገነባባቸው ወይንም ባደገባቸው አገሮች ውስጥ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በህዝብ የተመረጠ ቢሆንም ህዝቡ የመረጠውን መንግስት የሚቆጣጠረው በእነዚህ ነፃ ድርጅቶቹ ተጠቅሞ ነው። እነዚህ ድርጅቶች በነፃነት መቋቋም እና መንቀሳቀስ ካልቻሉ ዜጎች መንግስታቸውን የሚቆጣጠሩበት መሳሪያ እንዳይኖራቸው ተደርገዋል ማለት ነው። ይህ ደግሞ የሚደረገው አምባገነኖች በሚያስተዳድሩዋቸው አገሮች ብቻ ነው።

ስለዚህ አንድ አገር ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር በማድረግ ላይ መሆኗ ወይንም አለመሆኗ አንደኛው መለኪያም እነዚህ ድርጅቶች ከገዢው ፓርቲ ቁጥጥር ስር ነፃ ሆነው እንደ ልብ ማበብ እና በነፃነት መንቀሳቀስ መቻላቸው ነው።

እነዚህ ድርጅቶች ነፃ ከሆኑ የዲሞክራሲ ኃይል ምንጮች በመሆን ለዴሞክራሲ ሽግግር ከፍተኛ ግልጋሎት ይሰጣሉ። ገዢው ፓርቲ የፖለቲካ ጭፍራዎቹን በእነዚህ ድርጅቶች ላይ በመላክ ለማዳከም ከሞከር ወይንም አመራራቸው ላይ በማስቀመጥ እነዚህን ድርጅቶች በቁጥጥር ስር ካደረገ ግን ድርጅቶቹ ወደ መንግስታዊ ተቋምነት ተቀይረዋል ማለት ነው። ገዢው ፓርቲ የተለያዩ ድንጋጌዎች በማወጅ እነዚህ ድርጅቶች እንዲጠፉ ወይንም እንዲዳከሙ ካደረገም መንግስት ሆን ብሎ ወደ ዴሞክራሲ በሚደረገው ሽግግር ላይ ጦርነት ከፍቷል ማለት ነው።

ይህን የሚያደርግ መንግስት አምባገነን መንግስት እንጂ በምንም አይነት አለም አቀፍ መስፍርት ዴሞክራሲያዊ መንግስት ሊሆን አይችልም። አምባገነን አይደለሁም የሚል ከሆነ ከእነዚህ ተግባሮች መቆጠብ አለበት።

የአንድነት ፓርቲ የወላይታ ዞን ምክር ቤት ስብሰባ በመንግስት ካድሬዎች በሀይል ተደናቀፈ –አንድነት

$
0
0

የአንድነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ እና ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ ዳንኤል ሺበሺ ደህንነታቸው አደጋ ላይ ነው፡፡

የሟቹን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር የአቶ መለስ ዜናዊ ምስል ያለበት ቲሸርት የለበሱ ከ 10 የሚልቁ የመንግስት ካድሬዎች በወላይታ ሶዶ እየተደረገ የነበረውን አንድነት ፓርቲ የወላይታ ዞን ምክርቤት ስብሰባን በሀይል ማደናቀፋቸውን ከስፍራው ለፍኖተ ነጻነት የደረሰው ዘገባ አመለከተ፡፡

ካድሬዎቹ የስብሰባ አዳራሹን በሃይል በመስበር ከተሰብሳቢዎቹ ላይ የተለያዩ ሰነዶችን የቀሙ ሲሆን ብብደባ በመፈፀም ላይ ናቸው፡፡ በስብሰባ አዳራሹሳሽፅ የነበሩት የአንድነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ እና ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ ዳንኤል ሺበሺ ደህንነታቸው አደጋላይ መሆኑን ለፍኖተ ነፃነት ተናግረዋል፡፡

ከ32 የሚበልጡ የአንድነት ፓርቲ የወላይታ ዞን ምክር ቤት አባላትና አመራሮች ንብረቶቻቸው ተቀምቶ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እየተጋዙ ነው፡፡

የአንድነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ እና ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ ዳንኤል ሺበሺ ከፓርቲው የተላኩ መሆኑን የሚያሳየውን ደብዳቤ ጨምሮ መታወቂያቸው ሳይቀር በካድሬዎቹ ተነጥቋል፡፡
10150630_609195442498727_1046966781_n1981763_609195462498725_1372041561_n

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ልሳን የሆነው ፍኖተ-ነጻነት ጋዜጣ በግማሽ ሚሊዮን ብር የራሱን ማተሚያ ማሽን በመግዛት እና በመትከል በቅርብ ቀን ሕትመቱ ለሕዝብ በገበያ ላይ እንድሚውል ተገልጸ፡፡

$
0
0

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ልሳን የሆነው ፍኖተ-ነጻነት ጋዜጣ በግማሽ ሚሊዮን ብር የራሱን ማተሚያ ማሽን በመግዛት እና በመትከል በቅርብ ቀን ሕትመቱ ለሕዝብ በገበያ ላይ እንድሚውል ተገልጸ፡፡
የአንድነት የድርጅት ጉዳይ ሐላፊ የሆኑት አቶ ዳንኤል ተፈራ እንደገለጹት፤ የአንድነት ፓርቲ እና የፍኖተ ነጻነት የኢዲቶሪያል ቦርድ ባለፈው አመት ያሳትማት የነበረችው ጋዜጣ በ2005 ዓ. ም. በጉልበት እንድትዘጋ በመደረጉ እና የመንግስት ጋዜጣ ማተሚያ ቤት የሆነው ብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤትን ጨምሮ በማንኛውም ኢትዮጵያ ውስጥ ባለ የግል ማተሚያ ቤት ጭምር እንዳትታተም ከተደረገ በኋላ ይህንን ችግር በዘላቂነት የፓርቲውን መገናኛ ብዙሃን ለማጠናከር እና ለመምራት ምንድነው የሚያስፈልገው? የሚል ሰፋ ያለ ውይይት በማድረግ የፓርቲውን የማተሚያ ማሽን መትከል በጣም አስፈላጊ፤ አንገብጋቢ እና ወሳኝ ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል።

ይህንኑ ከግንዛቤ በማስገባት የአንድነት ፓርቲ አመራሮች፤ የፍኖተ ነጻነት የኢዲቶሪያል ቦርድ፤ የአንድነት ፓርቲ ደጋፊዎች እና በውጭ አገር የሚገኙ የአንድነት ፓርቲ የድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ይህንን የተቀደሰ ሐሳብ በጋራ በመካፈል እና የሚሰጠውን ጥቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት ከፍተኛ የሆነ ለሶስት ወራት የቆየ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘመቻ በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር በማካሄድ ግማሽ ሚሊዮን ብር አካባቢ መሰብሰቡን ገልጸዋል።

አቶ ዳንኤል በመቀጠልም በአሁኑ ሰአት “ኮርድ” የሚባል የማተሚያ ማሽን በግማሽ ሚሊዮን ብር ግዥ የተፈጸመ ሲሆን፤ ይህ ማሽን በአጠቃላይ ለፓርቲው አገልግሎት እና ፓርቲውን ከሕዝብ ጋር ሊያግናኙ የሚችሉ ጋዜጣ፤ በራሪ ጽሁፎች፤ ፖስተሮች፤ መጽሄት፤ መጽህፍ፤ የመሳስሉትን ሁሉ ማተም የሚችል በመሆኑ ለአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ የፓርቲው ትጥቅ መሆኑን ገልጸው በተለይ አንድነት ለሚያካሂደው የሰላማዊው ትግል ከፍተኛ መሳሪያ መሆኑን እና በተለይ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የታፈነበት አገር ላይ ያለን በመሆናችን ይህ ማሽን ሰራዎቻችንን በበለጠ የሚያቀላጥፈልን እና ሕዝቡ ጋር በቀላሉ ለመደርስ የምንችልበትን አቅም በክፍተኛ ሁኔታ የሚጨምር መሆኑን አስረድተዋል።

አቶ ዳንኤል ተፈራ በመጨረሻም የፍኖተ ነጻነት ማተሚያ ማሽን ተከላ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ተጠናቆ በአምባገነኖች የተዘጋችው ፍኖተ ጋዜጣ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ለሕዝብ የምትቀርብ መሆኑን የገለጹ ሲሆን ለአንድነት አባላት፤ ለአንድነት ደጋፊዎች፤ በውጭ አገር ለሚኖሩ የአንድነት የድጋፍ ሰጭ ድርጅቶች፤ ደጋፊዎች፤ ይህንን ማሽን ለመግዛት በገንዘብ፤ በሐሳብ እና በተለያየ መንገድ አስተዋጻኦ እና እግዛ ያደርጉትን ኢትዮጵያውያኖች በሙሉ በአንድነት ፓርቲ እና በፍኖተ-ነጻነት ኢዲቶሪያል ቦርድ ስም ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።

አቡጊዳ ድህረ ገጽም በዚሁ አጋጣሚ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የምትገኙ ኢትዮጵያውያን በሙሉ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንድሚባለው ሁሉ ይህንን ማሽን ላመግዛት ማንኛውንም እገዛ እና ትብብር ላደርጋችሁ በሙሉ ከፍተኛ ምስጋናችንን እያቀረብን፤ የአንድነት ፓርቲ አመራሮች እና የፍኖተ ነጻነት ኢዲቶሪያል ቦርድ እና ጋዜጠኞች፤ ደጋፊዎች በሙሉ እንኳን ድስ አላችሁ እንላልን!!IMG_0671 (1)IMG_0670 (1)

እነ ዳንኤል ተፈራ ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ተለቀቁ!! ወላይታ ሶዶ ነፃነት አልባዋ የማፊያ ካድሬዎች ከተማ!!

$
0
0

ከወላይታ ዞን የአንድነት ፓርቲ አመራሮች የእስርና እንግልት ማብራሪያ

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራና ድርጅት ጉዳይ ም/ሃላፊ አቶ ዳንኤል ሺበሺ በደቡብ ቀጠና በወላይታ ዞንና በሲዳማ ዞን አዋሳ ከተማ ያሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር የፓርቲውን የትግል ስትራቴጅክ ዕቅዶች ላይ ማብራሪያ፣ ደንብና ፕሮግራም ለመስጠት እንዲሁም የስራ ጉብኝት ለማድረግ በ 12/07/06 ወደ ወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ ተገኝተው ነበር፡፡ በ13/07/06 ደግሞ ከሶዶ ከተማ ስራ አስፈፃሚና ከወረዳ አመራር አባላት ጋር የፓርቲያችንን ደንብ፣ ፕሮግራምና ቀጣይ የስራ አቅጣጫ አስመልክቶ የተሰናዳው ውይይት ላይ ለመታደም ከ32 በላይ አመራሮችም ተገኝተው ነበር፡፡

ቅዳሜ በ 13/07/06 ዓ.ም ከአባላት ጋር ባለው ዕቅድ መሰረት የፓርቲያችንን ህጋዊ ሰነዶችን ለወረዳና ለዞን አመራሮች ለመስጠት፣ ቀጣዩን ሀገራቀፍ ምርጫ አስመልክቶ መረጃ ለመለዋወጥ ምርጫችን የነበረው የፓርቲያችን አባል የሆነውና ወጣ ብሎ ፀጥታ የሰፈነበት ግቢ ነበር፡፡ ይህንን ለማድረግ ህገ መንግስታዊ መብት ነበረን፡፡ የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች የፖለቲካ ደንብና ፕሮግራማቸውን ለዞንና ለወረዳ አመራሮች ለማስጨበጥ ፈቃድ እንደማያስፈልግ ጠንቅቀን እናውቅም ነበር፡፡

በተለይም ሃለማሪያም ደሳለኝ በሞግዚትነት ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ወላይታ ሶዶ ነፃነት አልባ ከተማ እንደሆነች ለማረጋገጥ ችለናል፡፡ ወላይታ በካድሬ ተወጥራለች፡፡ ዝርዝሩን በቀጣይ እንደምናቀርብ ቃል እየገባን ለአሁን በእኛ ላይ የደረሰውን በቅንጭቡ እንደሚከተለው ለኢትዮጵያ ህዝብና ለታሪክ እናቀርባለን፡፡

1. 32 የሚሆኑ አንድነት ፓርቲ የወላይታ ዞን አመራሮች የተሰባሰቡት ከላይ በገለፅነው አላማና ህገ መንግስታዊ መብታችንን ተጠቅመን ቢሆንም ለውይይት ቅድመ ዝግጅት ስናደርግና ውይይቱን ለመጀመር ስንዘጋጅ መታወቂያ የሌላቸው ከ 8-10 የሚሆኑ ጡንቻቸው የፈረጠመ ግለሰቦች እንደ ኮማንዶ ለውይይት የተገናኝበትን የአባላችንን ጊቢ ሰብረው በመግባት የያዝናቸውን የፓርቲ ሰነዶች፣ ሳምሰንግ ጋላክሲ ስልኮችና ያገኙትን ሁሉ ዘርፈው ሂደዋል፤ አመራሮችን ደብድበዋል፡፡
2. እነዚሁ ደብዳቢዎች ታርጋ ቁጥር በሌላቸው ሞተሮች በመታጀብ ፖሊስ ይዘው በመምጣት ፕሮግራማችንን ለማደናቀፍ በሃይልና በጉልበት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወስደውናል፡፡
3. ፖሊስ ጣቢያውም እኛን የደበደቡንንና ንብረታችንን የቀሙንን ሲቢል ለባሽ ካድሬዎች በመልቀቅ የአንድነት ፓርቲ 20 አመራሮችን የወላይታ ሶዶ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ሻለቃ ላሊሼ ኦሌ ቢሯቸው አስገብተው ችግሩን እንደሚቀርፍ አመራር ካነጋገሩንና ቃላችንን ከተቀበሉ በኋላ ሞባይሎቻችንን በመንጠቅ እንድንታሰር አድርገዋል፡፡
4. የእስሩ ሰዓት ከቀኑ 5፡00 ጀምሮ ነው፡፡ እንድ ቀፋፊና አስቀያሚ ማጎሪያ ውስጥ ካስቀመጡን በኋላ ከምሽቱ 2፡00 ላይ ህገወጥ ስብሰባ አድርጋችኋል በማለት ቃል ስጡ የሚል ምዝገባና ህገ ወጥ ስብሰባ እንዳደረግን እንድንመሰክር ለማስገደድ ቢሞክሩም እኛ መብታችንን እንደተጠቀምን እንጂ እነሱ እንደተረጎሙት ህገ ወጥ ስብሰባ እንዳላደረግን ሀቁን ስንነግራቸው እንዲሁም ሀሰትን ከመቀበል መታሰር እንደሚቻል የአንድነት አባላት ቁርጠኛ እንደሆንን ሲያውቁ ግራ ተጋብተው የበላይ አካል እስከሚያረጋግጥላቸው ጠብቀው ከእኩለ ለሊት በኋላ (ከምሽቱ 6፡30) በኋላ በእስር ላይ የቆዩ ከ20 በላይ ከፍተኛ አመራሮች እንዲወጡ ተደርጓል፡፡ ይሄ የሆነው ለመፍታት ታስቦ ሳይሆን ከወረዳ የመጡ አባላት ማደሪያ ቦታ እንዲያጡና ለአደጋ እንዲጋለጡ በማሰብ ነው፡፡
5. ስንታሰር ከተዘረፉ ሞባይሎች ውጭ በፖሊስ ጣቢያ አዛዡ ተይዞ የነበረው የታሳሪዎች ሞባይል ባልታወቀ ነገር ተነክሮ ከአገልግሎት ውጭ ተደርጓል፡፡ ሞባይላችን የተነከረውና ከጥቅም ውጭ የተደረገው በኬሚካል ይሁን በሌላ ነገር አልተረጋገጠም፡፡ የማንኛችንም ሞባይል ግን ከጥቅም ውጭ ሁኗል፡፡ ይሄ የሆነው የፖሊስ አዛዡ አቶ ላሊሼ ቢሮ የታሰረ ሞባይላችን ነው፡፡
ነገ ምን እንደሚገጥመን ማወቅ አይቻልም፡፡ ያረጋገጥነው ነገር ቢኖር ወላይታ ሶዶ ነፃነቷን የተነፈገች፣ በታርጋ አልባ ሞተሮች የምትታመስና ምንም ዋስትናና ህግ የሌለባት ከተማ መሆኗን ነው፡፡ ስለዚህ ነፃነት አልባዋ ወላይታ ነፃ መውጣት አለባት!!!

የአንድነት ፓርቲ የወላይታ ዞን አመራር አባላት ከምሽቱ 9፡00 ሠዓት
ሶዶ ከተማ10150630_609195442498727_1046966781_n1981763_609195462498725_1372041561_n

አቡጊዳ –የአንድነት እና መኢአድ ዉህድ ፓርቲ የመድረክ አባል አይሆንም ተባለ

$
0
0

መኢአድ እና አንድነት መጋቢት 11 ቀን የቅድመ ዉህደት ፊርማ ይፈረማሉ ተብሎ ሲጠበቅ ፣ ከመኢአድ ፕሬዘዳንት አቶ አበባው መሃሪ በተጻፈ ደብዳቤ፣ ላልተወሰነ ጊዜ ፊርማው እንዲዘገይ መደረጉ በስፋት ተዘግቧል። አቶ አበባዉ የቅደመ ዉህደቱን ፊርማ ላለመፈረም ሶስት ያልተፈቱ ነጥቦች የሚሏቸውን ያቀርባሉ። ነጥቦቹም የዉህድ ፓርቲው ስያሜን፣ የመሪዎች መመዘኛን እና አንድነት ከመድረክ ጋር ያለዉን ግንኙነት የሚመለከቱ ናቸው።

አቶ አበባዉ ባቀረቧቸው ነጥቦች ዙሪያ ምላሽ የሰጡት የአንድነት ዋና ጸህፊ አቶ ስዩም መንገሻ ፣ የቀረቡት ነጥቦች ንግግር ተደርጎባቸው ምላሽ የተሰጣቸውና ስምምነት የተደረሰባቸው መሆኑን፣ ወደ 800 ታዳሚዎች በነበሩበት የደብተራዉ ፓላቶክ ክፍል ቀርበው፣ መጋቢት 13 ቀ 2006 ዓ.ም በሰጡት ማብራሪያ አስረድተዋል።

አቶ ስዮም የመድረክና የአንድነት ግንኙነት እንደ ነጥብ መነሳቱ እንዳስገረማቸው ይናገራሉ። «አንድነት እና መኢአድ ሲዋሃዱ አንድነት እንደ ፓርቲ አይኖርም። ይፈርሳል። ምርጫ ቦርድም ከመድረክ ውስጥ ሆነ፣ እንደ ደርጅት ይሰርዘዋል። ዉህዱ ፓርቲ አዲስ ፓርቲ ነው የሚሆነው። መድረክ ዉስጥ መግባት ካስፈለገም እንደ ገና ሀ ተብሎ ለመድረክ ማመልከቻ ገብቶ፣ ለምርጫ ቦርድ አሳዉቆ ነው የሚሆነው» ሲሉ የአንድነት እና የመኢአድ ዉህድ ፓርቲ የመድረክ አባል እንደማይሆን በግልጽ አስቀምጠዋል። «ይሄንንም የመኢአዱ ሊቀመንበር ጠንቀቀው ያወቁታል» ያሉት አቶ ስዩም በዚህ ረገድ ጥያቄ መነሳቱ ግራ የሚያጋባ እንደሆነ ይናገራሉ።

የዉህዱን ፓርቲ የሚመሩ መሪዎች መመዘኛ ሊኖር እንደሚገባ በአቶ አበባዉ የቀረበውን ነጥብ በተመለከተ አቶ ስዩም አንድነት በዚህ ጉዳይ እንደተስማማ ገልጸዋል። የዉህድ ፓርቲዉን ሊቀመንበር እና ምክትል ሊቀመናብርት የሚመርጠዉ ከሁለቱን ድርጅቶች እኩል የተወጣጣ ጠቅላላ ጉባኤ እንደሆነ የገለጹት አቶ ስዩም ፣ «በቅድመ ስምምነት የድርጅቱን መሪዎች አይወሰኑም። የዉህዱን ፓርቲ የሚመሩት ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በጠቅላላ ጉባኤዉ የተመረጡ ናቸው» ሲሉ ስምምነት የተደረስበትን የመሪዎች የመሪዎችን አመራረጥ ሁኔታ አስረድተዋል።

የዉህዱ ፓርቲ ስም ምን ይሁን በሚለው ዙሪያ ስምምነት እንደተደረሰ አቶ ስዩም ይናገራሉ። «እነርሱ መኢአድ/አንድነት የሚል ስም፣ አንዴ ደግሞ የመላዉ ኢትዮጵያ አድነት ፓርቲ (መኢዴፓ) የሚል ስም አቀረቡ። እኛ መኢአድ/አንድነት የሚለው መዋሃዳን አያሳይም በሚል አስልተስማማንም። መኢአፓ የሚለዉን በግማሹ ተቀብለነው «መላው» የሚለው ቃል ወጥቶ «የኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲ» ይሁን አልናቸውም» ያሉ አቶ ስዩም በስሙ ዙሪያ የነበረዉን ዉይይት ይዘረዝራሉ። ሲያክሉም «እና ፓርቲ ከሚባል ትግሉ የሕዝብን ጥያቄ ያዘለና ሕዝባዊ በመሆኑ ፓርቲ ከሚለው ቃል ይልቅ ንቅናቄ የሚል እንዲገባበት ፈለግን። በኋላ ግን ሁለተቻንም ሁለት ሁለት ስሞችን እንድናቀርብ፣ አባላትና ደጋፊዎች ደግሞ ስም እንዲያቀርቡ በመጠየቅ፣ የሁለቱ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ በድምጽ ብልጫ ስሙን ይወስን በሚለው ተስማምተን ጨርሰናል» ሲሉ አቶ ስዩም የዉህዱ ፓርቲ ስም ምን ይሁን የሚለዉም ጉዳይ እልባት የተግኘለት እንደሆነ ይናገራሉ።

በአቶ አበባዉ የቀረቡ ሶስቱም ነጥቦች በስፋት ንግግር የተደረገባቸውና እልባት የተገኝላቸው እንደሆነ የገለጹት አቶ ስዮም፣ ሌሎች ንግግር ያልተደረገባቸው፣ ያልተፈቱ ጉዳዮች ካሉ፣ አንድነት ለመነጋገር ምን ጊዜም ዝግጁ እንደሆነ ገልጸዋል። «ከአሁን በኋላ እኛ የምናደርገው ነገር የለም። በአንድ እጅ አይጨበጨብም። እኛ አልተፈቱም የምንላቸው ነጥቦች አሉ ብለን አናስብም። ከነርሱ ጋር ከሁለት አመታት በላይ ነው የተነጋገርነው። አይ ይሄ ችግር አለ የሚሉት ነገር ካለ ያቅርቡና እንነጋገራለን» ሲሉ በአቶ አበባዉ የቀረቡት ሶስት ነጥቦ ምላሽ ያገኙ እንደመሆናቸው፣ ሌሎች በአቶ አበባዉ ደብዳቤ ያልተካተቱ፣ ከዚህ በፊት ስምምነት አልተደረሰባቸው የሚባሉና በአንድነት ዘንድ ያልታወቁ፣ ነጥቦች ከቀረቡ አንድነት ለመወያየት ሁሉጊዜ ዝግጁ እንደሆነ አስረድተዋል። አቶ ስዩም «ኳሷ መኢአድ ሜዳ ላይ ነዉ ያለቸው» ሲሉ አንድነት ከመኢአድ አዎንታዊ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ የመኢአድን ፋይል ሳጥን ዉስጥ ለጊዜው ከቶ ሌሎች እንቅስቃሴዎች ላይ እንደሚያተኩር አብራርተዋል።

መጋቢት 7 ቀን 2006 ዓ.ም የአንድነት እና የመኢአድ ላእላይ ምክር ቤቶች ዉህደቱ በአንድ ወር ጊዜያት እንዲጠናቀቅ፣ የቅደም ዉህደቱም ስምምነት መጋቢት 11 ቀን እንዲፈረም በሙሉ ድምጽ መወሰናቸው ይታወቃል። አቶ አበባዉ የመኢአድ ላእላይ ምክር ቤት ዉሳኔን ቀልብሰው ፣ በግላቸው ስምምነቱን ላልተወሰን ጊዜ እንዳይፈረም የማድረግ መብት እንደሌላቸው፣ ከመኢአድ አመራር አባላት በኩል የሚነሱ አስተያየቶች እየተሰሙ እንደሆነም ለማረጋገጥ ችለናል። የአዲስ አበባ የመኢአድ ምክር ቤትን ጨምሮ፣ በየክልሉ ያሉ የመኢአድ አስተባባሪዎችና መዋቅሮች ፣ ምክር ቤቱ ወስኖ ስምምነቱ ለምን እንዳልተደረገ እየጠየቁ መሆናቸውንም ለማረጋገጥ ችለናል።

በዚህ ጉዳይ ያነጋገርናቸው የፖለቲካ ተንታኝ የመኢአድ እና የአንድነት የቅድመ ዉህደት ፊርማ ለጊዜው አለመፈረሙ ጊዜያዊ ስቅታ እንጂ እንደ ትልቅ ችግር የሚታይ እንዳልሆነ ይናገራሉ። «በአንድነት ዘንድ በሩ ክፍት ነው። አቶ አበባዉ ባነሷቸው ነጥቦች ዙሪያ ስምምነት ተደርሷል። የመኢአድ አባላትና ደጋፊዎች ፣ ምክር ቤቱም ዉህደቱን ይፈልጉታል። የዉህደቱ ንግግሩ በችኮላ ወይም ለምርጫ ሲባል የተደረገ ሳይሆን ከሁለት አመታት በላይ የፈጀ ነው። የዉህደቱ እንቅስቃሴ 98% ተጠናቋል» ሲሉ ያስረዱት እኝሁ ተንታኝ የቀረው 2% ፣ አቶ አበባው እንዳይፈርሙ ያደረጋቸው ሌላ ምክንያት ካለ፣ ግልጽ በሆነ መንገድ አቅርበው፣ ውይይት በማድረግ ስምምነቱን ማጠናቀቅ እንደሆነ ይናገራሉ።

አቡጊዳ –ሕወሃቶች አሰብን እናስመልሳልን እያሉ ነው !

$
0
0

በሕዝብ ብዛት ቁጥር ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሁለተኛ ከአለም ደግሞ አሥራ አምስተኛ ናት። ወደ ሰማኒያ ሚሊዮን ሕዝብ ሲኖራት፣ ያን ያህል ሕዝብ ኖሯት የባህር በር የሌላት ብቸኛ አገር ናት። ከኢትዮጵያ ቀጥሎ ብዙ ሕዝብ ኖርቷት የባህር በር የሌላት አገር፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ሶስተኛ የሚሆን ሕዝብ ያላት ዩጋንዳ ናት። የቀድሞ ጥቅላ ሚኒስተር አቶ መለስ ዜናዊ፣ በባህር ወደብ ዙሪያ ሲጠየቁ «ለእድገት ይባህር ወደብ የገድ አያስፈልግም። ስዊዘርላንድን ናታም እንዴ ? ያደገች አገር ናት ፤ ግን ወደብ ይላት» ይሉ ነበር። ስዊዘርላን በሕዝብ ብዛት ከአለም ዘጠና አራተኛ ስትሆን ወደ 7 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ ብቻ ነው ያላት።

ሕወሃቶች፣ በአንድ በኩል «ከኤርትራ ጋር ታብራላችሁ» እያሉ ዜጎችን በሽብርተኝነት ተራ ክስ እያሰሩ፣ በሌላ በኩል እራሳቸው የሻእቢያ ጥቅም የሚያስጠብቅ ፖሊሲን አጥብቀው በመያዝ «አሰብ የኤርትራ ናት፤ ኢትዮጵያ የባህር በር አያስፈልጋትም» እያሉ ሲከራከሩ እንደነበረ በስፋት የሚታወቅ ነው።
የአረና ፓርቲ አመራሮች፣ በተለያዩ በትግራይ የሚገኙ ከተሞች በሚያደርጓቸው ዘመቻዎች በሕዝብ ያላቸው ተቀባይነት እየጨመረ መምጣቱን የተረዱት ሕወሃቶች ከዚህ በፎኢት በሚያራምዷቸውና በሕዝብ ዘንድ ተቃዉሞ ባስነሳባቸው ፖሊሶዎቻቸው ላይ ማሻሻያ እንደሚያደርጉ እየተናገሩ መሆናቸው የሚገልጹ መረጃዎች እየቀረቡ ነው።
በዋናናት አሰብ የኢትዮጵያ እንደሆነ በመግልጽ አረና ያቀረባቸው ቅስቀሳዎች በሕዝቡ ከፍተኛ ድጋፍ በማግኘታቸው ሕወሃቶች « እኛም አሰብን እናስመልሳለን» እያሉ ነው። አብርሃ ደስታ በዚህ ጉዳይ ላይ የዘገበዉን ለማንበብ ከታች ያለውን ይመልከቱ!

=============================================================
ህወሓቶች ሰግተዋል “ህወሓት ካልተመረጠ የትግራይ ማንነት ይጠፋል” እያሉ ነው – አብርሃ ደስታ

ህወሓቶች በዓረና እንቅስቃሴና በትግራይ ህዝብ የተቃውሞ መንፈስ በጣም ደንግጠዋል። የዓረና ተከታታይ ህዝባዊ ስብሰባዎችን ተከትሎ ህወሓትም ተከታታይ ህዝባዊ ኮንፈረንስ ለማድረግ ወስኗል፤ ጀምሯልም። የህዝብ ተወካዮች ተብለው የተመረጡ የየአከባቢያቸው ህዝብ እንዲሰበስቡ መመርያ ተሰጥቷል። ይቅርታ የህዝብ ተወካዮች ሳይሆኑ የፓርቲ ተወካዮች መባል አለባቸው፤ ምክንያቱም የተመረጡት በህዝብ ሳይሆን በህወሓት ነው። የሚያገለግሉትም ለህዝብ ሳይሆን ለህወሓት ነው። ምክንያቱም በህዝብ ተመርጠው ተብለው የህዝብ ችግር ከመናገር ይልቅ የህወሓትአጀንዳ ደግፈው የሚያጨበጭቡ ናቸው። እስካሁን የመረጠውን ህዝብ ችግር የተናገረ የህዝብ ተወካይ የህወሓት አባል አላገኘሁም። በህወሓት የፖለቲካ ፍልስፍና የተማእከለ ዴሞክራሲ መሰረት አንድ አባል ከፓርቲው አስተሳሰብ ወጥቶ የፓርቲው ብልሹ አሰራሮች ባደባብይ ወይ በፓርላማ ማጋለጥ አይችልም። ካጋለጠ ከፓርቲው ይባረራል። ለዚህም ነው የህዝብ ተወካዮች ተብለው ፓርላማ ይገቡና የፓርቲው ተወካዮች ሁነው የሚቀሩ።

የህዝብ ወይም የህወሓት ተወካዮች ህዝብ ሲሰበስቡ ፈተና እያጋጠማቸው ነው። የሽረ ተወካይ ህዝቡ ሰድቦ አባሯታል። ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋ በዓድዋ ህዝብ ተሰድባለች። የዓድዋ ህዝብ ለቅዱሳን “እናንተ ቤተሰቦቻቹ ለመርዳት እንጂ መቼ ለህዝብ ደህንነት ሰርታቹ ታውቃላቹ?” የሚል አስተያየት ሰጥቷል። በመቐለም አዲሳለም ባሌማ ህዝብ (ይቅርታ በመቐለ ህዝብ ተብለው የተሰበሰቡ ካድሬዎች ነበሩ) ሰብስቦ እርዱን ማለቱ ታውቋል። የመቐለ ዉሃ በ2007 ዓም ፕሮጀክት ቀርፀን እንፈተዋለን፤ ብቻ እኛን ምረጡ ብሎ ተማፅኗል። የመቐለ ነጋዴዎች ሰብስቦ ችግሮቻቹ ለመፍታት ተዘጋጅተናል ብሎዋል።

አጠቃላይ የህወሓት ስትራተጂ ህዝብን ለመሸወድ ያለመ ሲሆን የሚያጠነጥነውም “ህወሓት ካልተመረጠ የትግራይ ማንነት ይጠፋል” የሚል ነው። “ጠላቶቻችን እየመጡ ናቸው፤ ከህወሓት ጎን ተሰለፉ! ጦርነት ሊከፈትና ልጆቻችሁ አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ” እያሉ ይገኛሉ።

ግን የትግራይ ማንነት በህወሓት ህልውና የተንጠለጠለ አይደለም። እንኳን የህዝብ ማንነት የአንድ ግለሰብ ማንነትም ሊጠፋ አይችልም። ምክንያቱም የህዝብ ማንነት ቀርቶ የአንድ ሰው ማንነት ከጠፋ የሰውየው መብትና ነፃነት ተጥሷል ማለት ነው። መብቱ ወይ ነፃነቱ ከተጣሰ ደግሞ አዲስ የመጣ ስርዓት ልክ እንደ ህወሓት አምባገነናዊ ስርዓት ነው ማለት ነው። የህውሓትን ያህል አምባገነን ስርዓት ከመሰረትን ደግሞ ህወሓት አልተቀየረም ማለት ነው። ህወሓት ካልተቀየረ የፖለቲካ ለውጥ አልመጣም ማለት ነው። የፖለቲካ ለውጥ ካልመጣ ደግሞ ትግላችን ይቀጥላል (ለውጥ እስኪመጣ ድረስ)። ስለዚህ እኛ የምንታገለው ከህወሓት የተሻለ ስርዓት ለመመስረት እንጂ ህወሓትን በሌላ አምባገነን ስርዓት ለመተካት አይደለም። ስለዚህ ላረጋግጥላቹ የምፈልገው ነገር ቢኖር የማንም ህዝብ ወይ ግለሰብ ማንነት ይከበራል እንጂ አይጠፋም።

“ጠላቶቻችን እየመጡ ነው” የሚለው ዉንጀላ ግዜው ያለፈበት ፕሮፓጋንዳ ነው። የህዝብ ጠላት ጨቋኝ ስርዓት ነው። ህዝብ ከጨቋኝ ስርዓት ዉጭ ሌላ ጠላት የለውም። ጨቋኝ ስርዓት የህዝብ ጠላት እስከሆነ ድረስ እንታገለዋለን። ጨቋኝ ስርዓት ምን ግዜም አንቀበልም። ጨቋኝ ስርዓት ስለማንቀበል ነው አሁን ህወሓትን የምንቃወመው። ስለዚህ ዓላማችን የስርዓት ለውጥ ማምጣት እስከሆነ ድረስ ለጨቋኞች ቦታ የለንም፤ ህወሓትም ሌሎችም። እኛ የምንቀበለው ዴሞክራሲያዊ የህዝብ መንግስት ብቻ ነው።

ህወሓቶች በዓረና አጀንዳዎች በመስጋታቸው ምክንያት የዓረና ሐሳቦችን ለመቀበል እየተገደዱ ነው። በቅርቡ በህዝብ ፊት እየቀረቡ የመሬት ይዞታ ጉዳይ በዓረና እየቀረበ ያለውን ሐሳብ እንደሚደግፉ እየገለፁ ነው። (የዓረና ሐሳብ እንደግፋለን እያሉ ሳይሆን የህዝብን ፍላጎት ለማሟላት እንሞክራለን በሚል ነው። የህዝቡ ፍላጎት ደግሞ የዓረና የመሬት ፖሊሲ ነው)። የዓሰብ ወደብም በሰለማዊ መንገድ ለማስመለስ እንሞክራለን በማለት እየተመፃደቁ ነው። ለነጋዴዎችም ግብር እንቀንሳለን በሚል ምክንያት ለመጀንጀን እየሞከሩ ነው።

አሁን ግራ ሲገባቸው ስራ የሌላቸው ወጣቶች ለውትድርና ለመመልመል እየሞከሩ ሲሆን ማንም ወጣት ፍቃደኛ ሊሆን አልቻለም። በወጣቶቹ ዉሳኔ የተደናገጡ ህወሓቶች የጎዳና ተዳዳሪ የነበሩ ህፃናት ልጆች አታለው (ስራ እንሰጣቸዋለን በሚል ምክንያት) ለዉትድርና መመልመላቸው ታውቋል። ለምሳሌ በመቐለ ከተማ የነበሩ ብዙ የጎዳና ተዳዳሪ ህፃናት ተወስደዋል (ማረጋገጥ ይቻላል፤ አሁን በመቐለ ከነበሩ ህፃናት አንድ የቀረ የለም)። ግን አብዛኞቹ ህፃናት ከ16 ዓመት በታች ናቸው። ከ16 ዓመት በታች ህፃናት ለውትድርና የሚመለምል የቸኛ ሕገወጥ መንግስት ኢህአዴግ መሆኑ አይቀርም። ምክንያቱም በማንኛውም ሕግ ከ16 ዓመት በታች ህፃናት ለውትድርና መመልመል ሕጋዊ ሊሆን አይችልም። ጉዳዩ የሚከታተለው ካገኘ በዓለም አቀፍ ሕግ ወንጀል ሊሆን ይችላል።

በዓዲግራት የፈፀሙብንን ድብደባ በጣም አክስሮባቸዋል። የትግራይ ህዝብ ሙሉበሙሉ እንዲጠላቸው ሁነዋል። እናም በጣም ሰግተዋል። በቅርቡ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ሊጀምሩ ይችላሉ። በወታድሩም ቢሆን ህወሓቶች ድጋፍ የላቸውም።

ፓርቲዎች መዋሃድ ያለባቸው በያዙት ፕሮግራም፣ ስትራተጂና የፖለቲካ አቅጣጫ መሰረት ነው። የፕሮግራም፣ ስትራተጂና የፖለቲካ አቅጣጫ ወይም አጠቃላይ ርእዮተ ዓለም ልዩነት ካላቸው ብቻ ነው ተለያይተው መቀጠል ያለባቸው። አሁን ፓርቲዎች እንደተለያዩ ናቸው። የሚያሳዝነው ግን የተለያዩበት (የማይዋሃዱበት) ምክንያት የፕሮግራም፣ ስትራተጂ፣ የፖለቲካ አቅጣጫ ወይም ርእዮተ ዓለም ልዩነት ስላለባቸው አይደለም። የማይዋሃዱበት ምክንያት የፖለቲከኞቹ የባህሪይ ወይ የአመለካከት አለመጣጣም ስላለ ብቻ ነው። ይህንን የፖለቲከኞች ችግር የሚፈታው ህዝብን በማስተማር ነው። ህዝብን አስተምረን በፖለቲከኞቹ ተፅዕኖ እንዲያሳድር እናደርጋለን። እናም ፖለቲከኞቹ ከሰውኛ አመለካከት ወጥተው መርህ መሰረት ያደረገ ፖለቲካ በማራመድ ተመሳሳይ አይዲዮሎጂ የሚያራምዱ ፓርቲዎች እንዲወሃዱ ይሆናል። ተዋህደውም ለህዝብና ሀገር አማራጭ የፖለቲካ አቅጣጫ ይዘው ይቀርባሉ።

የአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት በተፈናቃዩች ተጥለቀለቀ:: –አንድነት

$
0
0

ተፈናቃዩቹ ከጎንደር አካባቢ ተነስተው ከዛሬ 20 ዓመት በፊት ወደ ምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ዳኖ ወረዳ በመውረድ በእርሻ ስራ የተሰማሩ ገበሬዎች ናቸው፡፡ከ1996ዓ.ም ጀምሮ በተለያየ ደረጃ ‹‹ክልላችንን ለቅቃችሁ ውጡ››ሲባሉ ቆይተዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማስፈራሪያው ወደ ግድያ፣ድብደባና ወከባ በማደጉ ለአቤቱታ አካባቢያቸውን ጥለው አዲስ አበባ ለመግባት ተገደዋል፡፡ ከተፈናቃዩቹ መካከል የተወሰኑት ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ካሳ ተ/ብርሃን ጽ/ቤት በማምራት አፈ ጉባኤውን ለማናገር ቢሞክሩም ሊያገኟቸው አልቻሉም፡፡የአፈ ጉባኤው ጸሐፊ ጉዳያችሁ ታይቷል ወደ መጣችሁበት ተመለሱ››ያለቻቸው ቢሆንም ተፈናቃዩቹ ‹‹ብንመለስ ሊገድሉን ስለሚችሉ አንመለስም››የሚል አቋም ይዘዋል፡፡

ከ26 የሚልቁ ሰዎች በአደባባይ ድብደባ ደርሶባቸው እጅና እግራቸው እንደተሰበረ የሚናገሩት ተፈናቃዩቹ‹‹አቶ ጌጡ ክብረት የተባለ ግለሰብ በገበያ ቦታ በገጀራ ተቆራርጦ ህይወቱ ማለፉን በሀዘን ስሜት ተውጠው ይናገራሉ፡፡ በአዲስ አበባ ማረፊያ ባለማግኘታቸው ለችግር መጋለጣቸውን የሚገልጹት ተፈናቃዩቹ ወደ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ጽ/ቤት በመምጣት ‹‹ፍትህ እንድናገኝ ለኢትዩጵያ ህዝብ ሰቆቃችንን አሰሙልን››በማለት ተማጽነዋል፡፡

የአንድነት ፓርቲ ዋና ጸሐፊ አቶ ስዩም መንገሻ ‹‹ህገ መንግስቱ በግልጽ እያንዳንዱ ዜጋ በፈለገው ክልል በመሄድ ንብረት ማፍራት እንደሚችል ቢደነግግም መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ህገ ወጥና አስቸጋሪ ነው››ብለዋል፡፡1526292_10152342593559743_900241474_n


በወላይታ የተፈፀመው መንግስታዊ ውንብድና የስርአቱን ዝቅጠት የሚያሳይ ነው!! ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የተሠጠ መግለጫ

$
0
0

በአገራችን ኢትዮጵያ ሁሉም መብቶች ያለምንም ገደብ የሚከበሩበትን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ላለፉት ዓመታት በርካታ መስዋዕትነቶች ተከፍለዋል፡፡ ዜጎች የመደራጀትና ሀሳባቸውን የመግለጽ ህገ-መንግሥታዊ መብት እንዳላቸው ጧት ማታ በመንግሥት ብዙሀን መገናኛዎች ቢለፈፍም፤ ሁሉም ነገር የይምሰልና የስልጣን እድሜ ማራዘሚያ ስልት እንደሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግልፅ ነው፡፡

ከሕግ በላይ የሆነ አገዛዝ ባለበት አገር በየስፍራውና በየክልሉ የሚገኙ ካድሬዎችና የስርዓቱ ባለሟሎች እራሳቸውን ከህግ በላይ አድርገው ቢቆጥሩ የሚገርም አይደለም፡፡ በዚሁም ምክንያት በገዢው ፓርቲ ተቋማት፣ ኃላፊዎችና ባለስልጣናት የሚፈፀመው ኢ-ሰብአዊና ኢ-ዴሞክራሲያዊ ድርጊቶች እጅግ እየከፋ መጥቷል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት በፓርቲያችን በአንድነት የተሰጣቸውን የተለያዩ ተልዕኮዎችን ለለማስፈፀም ወደ ደቡብ ክልል በተንቀሳቀሱት የአንድነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራና ም/ኃላፊው አቶ ዳንኤል ሽበሺ ላይ እና ከ32 በሚበልጡ የወላይታ ዞን አመራሮች ላይ መጋቢት 13 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም መንግስታዊ ውንብድና ተፈፅሞባቸዋል፡፡ በወላይታ ዞን ፖሊስ አዛዥ ሻለቃ ላሊሼ ኦሌ የሚመሩና የደህንነት ሰዎችን ጨምሮ ከ8-1ዐ የሚሆኑ መንግስታዊ ወሮበሎች የአንድነት ፓርቲ የወላይታ ዞን ምክር ቤት አባላት የተሰበሰቡበትን ግቢ በሀይል ሰብረው በመግባት የፓርቲ ሰነዶችን፣ ሁለት ሳምሰንግ ጋላክሲ ስልኮችን ጨምር በድምሩ ከ2ዐ የሚበልጡ የሞባይል ስልኮችን ዘርፈው ሄደዋል፡፡

ወሮበሎቹ ታርጋ የሌላቸው ሞተር ሳይክሎችን በመጠቀም አመራሮቻችንን ወደ ፖሊስ ጣቢያ አስገድደው ወስደዋል፡፡ ከፓርቲያችን አመራሮቻችን የተነጠቁ ስልኮች በዞኑ ፖሊስ አዛዥ ቢሮ ውስጥ ፈሳሽ ውስጥ በመጨመር ከጥቅም ውጭ በማድረግ ሁለቱ ከፍተኛ አመራሮችና የዞኑን ም/ቤት አመራሮች ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳይኖራቸው አድርገዋል፡፡ አመራሮቹን አፀያፊ በሆነ ማጎሪያ ውስጥ ከቀኑ 5፡00 ሰዓት እስከ ሌሊቱ 6፡30 አስረው ማደሪያ ሊያገኙ በማይችሉበት ሰዓት ለቀዋዋቸዋል፡፡ ይህ አይነቱ ከመንግስታዊ አካል የማይጠበቅ ውንብድና በሚሊዮኖች ድምጽ የመጀመሪያው እንቅስቃሴ ወቅት ሐምሌ 5 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም በዚሁ ዞን ተፈፅሞ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በወቅቱ የጠራነውን ሕዝባዊ ስብሰባ ለማደናቀፍ ታርጋ የሌላቸውን ሞተር ሳይክሎች በመጠቀም በቅስቀሳ ላይ የነበሩ አባላትን በመደብደብና በመዝረፍ እንዲሁም የተከራየነውን አዳራሽ ጥበቃዎች ዘግተው እንዲሄዱ ከመደረጉም ባሻገር ከግለሰብ የተከራየነውን ሞንታርቮ ዘርፈው እስከ ዛሬም አልመለሱም፡፡

ምንም እንኳ የአንድነት ከፍተኛ አመራርና አባላት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መስፈን በሚካሄደው ትግል ውስጥ መንገላታት፣ መደብደብ፣ መታሰርና ሞትም ካለ አይናቸውን ሳይጨፍኑ አፍጠው ለመቀበል ዝግጁ ቢሆኑም ይህን አሳፋሪ ድርጊት በቸልታ የማንመለከተውና አስፈላጊውን ነገሮች አጣርተን ተገቢውን ፖለቲካዊና ሕጋዊ እርምጃ የምንወስድበት ጉዳይ መሆኑን መግለጽ እንወዳለን፡፡

ሕገ መንግሥቱ ላይ የሠፈረውን የመደራጀት መብትና እና በተሻሻለው በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2ዐዐዐ አንቀጽ 46 ንዑስ አንቀጽ‹2› የፖለቲካ ፓርቲዎች የዕለት ከዕለት ተግባሮችን ስር ፤ የሕዝቡን ፖለቲካዊ ግንዛቤ ማዳበር፣ የፓርቲውን ዓላማ ለሕዝቡ ማስረጽ፤ ዜጎች በአገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው መቀስቀስ፣ በሕዝቡና በመንግሥት ተቋማት መካከል ግንኙነት እንዲጠናከር ማድረግ የሚሉ ግልጽ ድንጋጌዎች ሰፍረዋል፡፡ በአንፃሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከገዛ አባሎቻቸው ጋር በማንኛውም ጊዜ መሰብሰብ እንደሚችሉ እየታወቀ በመንግስትና በገዢው ፓርቲ የሚፈፀሙ ሕገ ወጥ ተግባሮች በየእለቱ ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ ሕግ ማክበርም ማስከበርም ያልቻለው ኢህአዴግ ሠላማዊ ትግሉን የሚደፈጥጡ ድርጊቶች ፈፃሚና አስፈፃሚ ካድሬዎች እና ሕገ አስከባሪ የተባለው የወላይታ ዞን ፖሊስ አዛዥ አይነት ግለሰቦችን በማበረታታት ሕጋዊና ሠላማዊ ትግሉን ወደ ጠርዝ እየገፋ ይገኛል፡፡

በዚህ አጋጣሚ ለፓርቲያችን ከፍተኛ አመራሮችና ለወላይታ ዞን የወረዳ አመራሮችና አባላት ያለንን ክብር እየገለፅን፣ በወላይታ ሶዶ በአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮችና የፓርቲያችን የዞኑ ምክር ቤት አባላት ላይ የተፈፀመው መንግስታዊ ውንብድና ስርአቱ የወረደበትን የዝቅጠት ደረጃ አመላካች እንደሆነ ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

ድል የሕዝብ ነው!
መጋቢት 16 ቀን 2ዐዐ6 ዓም
አዲስ አበባUDJ-SEAL

የእሳት ፖለቲካ በኢትዮጵያ (Fire Politics in Ethiopia) –ይሄይስ አእምሮ

$
0
0

በሃይማኖት መሪዎችና አገልጋዮች ዙሪያ ሰሞኑን አንዲት መጣጥፍ ጽፌ ለድረ ገፆች ልኬ ነበር፡፡ ለኅሊናቸው ተገዢ የሆኑ አወጡት – አስነበቡን፤ እግዚአብሔር ይስጣቸው፡፡ ለባህልና ለይሉኝታ ያደሩት እንዲሁም እነሱ በሚፈልጉት ሙዚቃ ብቻ ታንጎና ማሪንጌ መደነስ የሚፈልጉት ወደቅርጫታቸው ከተቱት – ይክተቱት፡፡ ሁሉም የመሰለውን የማድረግ መብት አለውና ያነበበም ያስነበበም፣ ያፈነም ያሳፈነም የኅሊናው ዳኝነት ይፍረደው ከማለት ውጪ በዚህ በውዥንብር ዘመን መወቃቀሱም ሆነ መካሰሱ ፋይዳ የለውም፡፡ ግን ግን የእውነት አምላክ ለሁላችንም እውነተኛውን የልቦናና የኅሊና ሚዛን እንዲሰጠን እጸልያለሁ፡፡ ሁለትና ሁለት ሲደመር አራት ብቻ የሚሆንበት ሃቀኛ ዘመን እንዲመጣልንም እንዲሁ፡፡ በተረፈ የልጆቼ ልጆች “Mother stomach is ranger.” ሲሉ እሰማለሁና በዚያ “ሜጀር” የተቃኘ የቅሬታ ዘፈኔን ጋብዣቸው በገዢዎቻችን አነጋገር ንቅድሚት እላለሁ፤ ሕይወት እንዲህ ናትና፡፡

አንድ የብዕር ወዳጄ ያቺን መጣጥፍ ካነበበ በኋላ በነካ እጄ በዚህች ወያኔያዊ የእሳት ፖለቲካ ላይ ጥቂት ነገር እንድል አሳሰበኝ፡፡ ርዕሲቱንም የሰጠኝ እርሱ ራሱ ነው – Please take the credit dear Mr. Thingummy, wherever you may be.

ሀገራችን ተመልካች ያጣ የሕዝብ ብዛት ብቻ ሣይሆን ጭንቅት የሚያዞሩ እጅግ በርካታ ችግሮች የሚርመሰመሱባት በመሆኗ አንባቢን ላለማስቸገር ወይም ብዙ አንባቢ የለም በሚል ተስፋ መቁረጥ ወይም “አድማጭና የእርምት እርምጃ ወሳጅ ኃላፊነት የሚሰማው ጤናማ ወገን በሌለበት የኳስ አበደች ሀገራዊ ምስቅልቅል ሁኔታ ውስጥ ተነቦስ ምን ፋይዳ ሊያመጣ?” ከሚል ብሶት የተነሣ ሆን ብለን እየተውነው እንጂ መጻፍ የምንፈልግ ዜጎች የምንጽፈበት ጉዳይ በሽበሽ ነው፤ በበኩሌ አድማጭ ቢኖር ሃያ አራት ሰዓት ብጽፍ የማይደክመኝና የሚያጽፍ ጉዳይም ሞልቶ የተረፈ መሆኑን የምገልጸው የሚያፍኑኝን ድረ ገፆች ደስ አይበላቸው በሚል የመከፋት ስሜት ሳይሆን ተናግረን አድማጭ ባለመኖሩ ሳቢያ በእጅጉ የምቆረቆር መሆኔን በሚጠቁም የቁጭት ስሜት ነው፡፡ የወያኔው የዘረኝነት አባዜ ካስከተለብን ተነግሮ የማያልቅ ሰቆቃና የግፍ አስተዳደር ጀምሮ እነሚሚ ስብሃቱን የመሳሰሉ የሥርዓቱ ዘውጋዊ አባላትና እበላ ባይ ሆዳም ደጋፊዎቻቸው ባቋቋሟቸው የሠራተኛ አስቀጣሪ ድርጅቶች አማካይነት የሚካሄደውን ዘመናዊ ባርነት ብንመለከት ጉዳችን በጽሑፍም ሆነ በቃል ተዘርዝሮ የማያልቅ አስገራሚ ፍጡራን ሆነናል – እኛ “ኢትዮጵያውያን”፡፡ ቴዲ አፍሮ “እዚህ ጋ’ም እሳት፣ እዚያ ጋ’ም እሳት፣ እሳት፣ እሳት፣እሳት…” ሲል እንዳቀነቀነው ሀገራችን ወያኔያዊ እቶን ላይ ተጥዳ በየአቅጣጫው እንደባቄላ አሹቅ እየተንገረገበች ናት፡፡ ፖለቲካው እሳት፣ ሃይማኖቱ እሳት፣ ፌዴራሉ እሳት፣ ፖሊሱ እሳት፣ ቀኑና ሣምንቱ እሳት፣ ወሩና ዓመቱ እሳት፣ ኑሮው እሳት፣ ባለሥልጣናቱ እሳት፣ ነጋዴው እሳት፣ ዳኛው እሳት፣ በሽታው እሳት፣ ርሀቡ እሳት፣…፡፡ ሁሉም በእሳት አለንጋ ይጋረፋል፤ ይጠብሳል፤ ይሸነቁጣል፤ የት እንድረስ? የትስ እንግባ? ከነዚህ ከሲዖል ካመለጡ ሽፍቶች የሚታደገን ማን ነው? አምላከ ኢትዮጵያ ወዴት አለ? ኤሎሄ! ኤሎሄ! ኤሎሁም! በዚህ መከራችን ላይ ነው እንግዲህ ወያኔ በሐረርም በአዲስ አበባም እንደዚያች ተዘውትራ እንደሚነገርላትና “እዚህ አካባቢ እሳት ይነሳል ብያለሁ” ብላ ባስጠነቀቀች ማግስት ራሷ እንደምትለኩሰው የደሴዋ ዕብድ ሴት በሹምባሾቹ አማካይነት በሚፈልጋቸው ቦታዎች ላይ እሳት እየለኮሰ፣ እንዳይጠፋም ከልካይ ዘብ እያቆመ በሀገር ሀብትና በሕዝብ ዕንባ እየተዝናና የሚገኘው፡፡ ለማንኛውም አስታዋሼን ላመስግንና በጠቆመኝ ሃሳብ ዙሪያ እንዳመጣብኝ ትንሽ ልብከንከን፡፡ እውነትን ላለማየት ዐይነ ኅሊናቸው የታወረ፣ እውነትን ላለመስማት ዕዝነ ልቦናቸው የተደፈነ፣ አእምሯቸው በፀረ-ለውጥ ቫይረስ ለፈውስ ባስቸገረ ሁኔታ “corrupted” ለሆነ የ“ሚዲያ ሰዎች”ም የቮልቴርን አባባል ባስታውሳቸው ቅር አይለኝም – ቮልቴር እንዲህ አለ አሉ፡- “በምትናገረው ሁሉ ባልስማማም መናገር የምትፈልገውን ጉዳይ በነፃነት መናገር እንድትችል ግን ሕይወቴንም ቢሆን እገብርልሃለሁ!” አይ ኢትዮጵያ! በሁሉም ድሃ፡፡ ግን ተስፋ አለኝ – ትልቅ ተስፋ፡- ወደፊት አንድ ቀን ይህ ሁሉ ድንቁርናችንና ከንቱ ትምክህታችን እንደጤዛ ሲረግፍልን ሰው እንደምንሆን፡፡

በዓለማችን የፖለቲካ ዓይነቶች ብዙ መሆናቸው ከናንተ የተሠወረ አይደለም፡፡ የድንበር ፖለቲካ፣ የውኃ ፖለቲካ፣ የዘር ፖለቲካ፣ የዘውግ ፖለቲካ፣ የውጭ ብድርና ዕርዳታ ፖለቲካ፣ የሀገር ውስጥ የድርቅ ጊዜና የርሀብ ወቅት ዕርዳታ ፖለቲካ፣ የሃይማኖት ፖለቲካ፣ … ዝርዝሩ ብዙና ኪስን ሳይሆን አንጎልን የሚቀድ ነው፡፡ ወያኔ በኢትዮጵያ ላይ ያልሞከረው የፖለቲካ ዓይነት ደግሞ የለም፡፡ እርግጥ ነው ወያኔ ብቻውን አይደለም፡፡ ይህ ቀረሽ የማይባል ሁለንተናዊ ድጋፍ ለወያኔዎች በገፍ እየሰጡ በ17 ዓመታት ውስጥ የሰው ኃይሉን ከሰባት ሰውነት ወደሚሊዮንነት በማሳደግ ፀረ-ኢትዮጵያ አቋማቸውን በተግባር የገለጡት የውጭ ጠላቶቻችንም በዚህ ኢትዮጵያን ወደፖለቲካዊ ቤተ ሙከራነት የመለወጡ ሂደት ውስጥ ያሳዩት ጉልህ ተሳትፎም ለአፍታ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ከዓለም ሕዝቦች መካከል እኛ ኢትዮጵያውያን ላይ ያልተፈተሸ ፖለቲካዊ መርዝ የለም፡፡ ባጭሩ የወያኔ ብቻ ሣይሆን የፈረንጆቹም guinea pig ሆነን የቀረን ብቸኛ መዘባበቻ ዜጎች ብንኖር እኛ ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ እርግጥ ነው እነኢራቅንና አፍጋኒስታንን ብንረሳ አግባብ አይደለም – እኛን እየገረፈን ያለው የኃያላኑ የእሳት ወላፈን እነሱንም እየጠበሰ ነውና፡፡ “አልማሊኪ ቡሽ፣ ካርዛይ ቡሽና መለስ ቡሽ እያሉ ሃቀኛ ሰላም አይኖርም፡፡”

ወያኔ ተግባር ላይ ካዋላቸው ሕዝብን የማሰቃያና ሀገርን የማውደሚያ መንገዶች አንደኛው እሳት ነው፡፡ እንዲህ የምላችሁ ወዳጄ አሁን ስላስታወሰኝ ብቻ እንዳይመስላችሁ፡፡ ከጥንትም በሚገባ አውቀዋለሁ፡፡ ለነገሩ ጨካኝና አምባገነን መንግሥታት ለዓላማቸው ስኬት የማያደርጉት ነገር የለም፡፡ ደርግም በተወሰነ ደረጃ ይህን የእሳት ፖለቲካ ይጠቀምበት እንደነበር በጊዜው ሰምቻለሁ፡፡ ሞኙ ደርግ እሳትን ይጠቀምበት የነበረው ኮንትሮባንድን ከመቆጣጠር አንጻርና በጣም በጥንቃቄ እንደነበር በወቅቱ የነበሩ አሁን ድረስ ያስታውሳሉ፡፡ የወያኔ ግን የተለዬ ነው፡፡

በመሠረቱ ወያኔ ምን እንደሆነ መናገር የዐዋጁን በጆሮ ነው፡፡ ይሁንና ወያኔዎች በተጣባቸው የትውልድ መርገምት ምክንያትም ይሁን በሌላ ከሆዳቸውና ያሻቸውን እንዲሠሩ ከሚጠቅማቸው የጨበጡት ሥልጣን በስተቀር የኢትዮጵያዊነት ስሜት በጭራሽ የሌላቸው፣ እንዲያውም ከያዙት ጥቅምና ሥልጣን ያስወግደናል ብለው የሚፈሩት በቀን ሰመመንና በሌት ቅዠት የሚያባትታቸው የኢትዮጵያዊነት ስሜት በመሆኑ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚልን ዜጋ ሁሉ በየሄደበት እያሳደዱና እየገደሉ በደም ባሕር እየዋኙ የሚኖሩ፣ ጥላቸውንም የማያምኑ የከተማ ወሮበሎች መሆናቸውን እዚህም ላይ በድጋሚ ማስታወሱ በአሰልችነት ሊያስወቅስ አይገባም፡፡ እናም አስታውሱ – ወያኔ የዜጎችን የላብ ውጤት የሆነ ሀብትና ንብረታቸውን ማቃጠል ብቻም ሣይሆን ሕዝብን በሠልፍ ኮልኩሎ እንደሂትለር የኦሽትዊዝ ቻምበር የማይፈልጋቸውን በጋዝ እየለበለበ ቢፈጃቸው የሰይጣናዊ ተፈጥሮው የሞራል ምሰሶ ክፋትና ጥፋት ነውና ደስታን የሚያስገኝለት እንጂ ሰብኣዊነት የሚሰማው ሩህሩህ ፍጡር አይደለም፡፡ ሰብኣዊነትና ወያኔ ዐይንና ናጫ ናቸው፡፡

ወያኔዎች እንደገቡ ሰሞን የምንሰማቸው ብዙ የእሳት አደጋዎች ነበሩ፡፡ እነዚያ እሳቶች እንደሰሞነኞቹ የሕዝብን አንጡራ ሀብትና ገንዘብ ለማቃጠል የታለሙ ሣይሆኑ ጫካና ደን የማያውቁት መደዴዎቹ ወያኔዎች ደቡብ ኢትዮጵያንም እንደሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ለማራቆት የታቀዱ ደኖችን የማቃጠል ወያኔያዊ የክተት ዘመቻዎች ነበሩ፡፡ በርካታ የደቡብና የኦሮሞ ብሔር መኖሪያ አካባቢዎች በነዚያ ወያኔ በቀሰቀሳቸው የሰደድ እሳቶች ተቃጥለዋል – አንጀታቸው ለተፈጥሮም የሚጨክን አረመኔዎች ናቸው፡፡ በምክንያትነት ሲቀርብ የነበረው ግን የኦነግን ሸማቂዎች ከምንጫቸው ለማድረቅና መደበቂያ ቦታ ለማሳጣት የሚል ነበር፡፡ ትግራይ ውስጥ ወያኔን ሊደብቅ የሚችል ዋሻ ካልሆነ በስተቀር ደንና ጫካ እንዳልነበረ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን ጫካ ቢኖር ኖሮ ወያኔን ለማጥፋት በሚል ሰበብ የደርግ መንግሥት ነዳጅ በቦቴ መኪናዎች ጫካ ውስጥ እየደፋ በአብሪ ጥይትም በአሻጋሪ እየለኮሰ ሀገር ለማቃጠል የሚያበቃው የሞራል ድቀት ውስጥ እንዳልነበረ ያንጀቴን እመሰክራለሁ – ሰው ካልሞተ ሚስትም ካልተፈታች ወይ ካልሞተች አይመሰገኑም ወንድማለም፡፡ ደርግ ዜጎችንና ሀገርን በእሳት አይቀጣም፤ ደርግ ኢትዮጵያዊ ጨካኝ እንጂ እንደወያኔ ወፍዘራሽ የባንዳ ውላጅ አልነበረም፡፡ እሳት ባለጌ ነው፡፡ እሳት እጅግ መጥፎ ነው፡፡ ምሕረትን አያውቅም፡፡ እንኳንስ ዜጋህን ጠላትህንም ቢሆን በአግባቡ ውጋው እንጂ፣ በአግባቡ ቅጣው እንጂ ኢ-ሰብኣዊ በሆነ ሁኔታ በእሳት አትገርፈውም፡፡ እነሂትለርና ሙሶሊኒ እንኳንስ ዜጎቻቸውን ጠላቶቻቸውንም ቢሆን በሰደድ እሳት አልቀጡም፤ በእሳት መቅጣት የጀግና ሙያ ሳይሆን የፈሪ ዱላ ነው፡፡ ወያኔ ግን ከየትኛው የጀሃነብ ሰማይ እንደወረደብን አይታወቅም ይሄውና ጫካና ደንን ከማቃጠል አልፎ የምሥኪን ዜጎችን ቤትና ንብረት እንዳሻው በሚያዛቸው ኅሊናቢስ ጀሌዎቹ እያቃጠለ ይገኛል፡፡ ወያኔ እኮ በእሳትም ብቻ ሳይሆን እንደተራ ተንኮለኛ ዜጋ ምግብንና መጠጥን በመመረዝና የታወቀ ጠንቋይ ቤት ድረስም በመሄድ የሚጠላቸውን የሚያስወግድ ጉደኛ ፍጡር ነው፡፡ ኪሮስ አለማየሁ እንዴት ሞተ? አለማየሁ አቶምሳስ? በውነት ቆሻሾች ናቸው፡፡ ምን አድርገን ይሆን ፈጣሪ እነዚህ ለቅጣት የሰጠን ግን? እስኪ ወደዬኅሊና ጓዳችን እንግባና ራሳችንን በቅጡ እንመርምር፡፡

በዚያን ሰሞን ሐረር ውስጥ የተቃጠለው መንደር የዚሁ የወያኔን ዜጎችን በእሳት የመቅጣት የእሳት ፖለቲካ ያሳያል፡፡ የኢትዮጵያን ገንዘብ ለራሱ ፖለቲካ በመጠቀም ዜጎችን በአነስተኛና ቀጫጭን የሚባል አዲስ ፈሊጥ እያደራጀ አንዱን ርሃብተኛ ሌላውን ጥጋበኛ እያደረገ እናያለን፡፡ በጥቃቅን የማይደራጅን በጠላትነት በመፈረጅ በገቡበት እየገባ ያሳድዳቸዋል፡፡ ከወያኔ የተለዬ ነጋዴ ኑሮውና ግብሩ እሳት ሆነው እንዲያቃጥሉትና ከሀገር እንዲጠፋ ወይም በርሀብ አለንጋ ተገርፎ እንዲሞት ሲደረግ ወያኔን የተጠጋ ሆድ አደር ግን እምብርቱ እስኪገለበጥ እየበላና እየጠጣ ተንደላቅቆ ይኖራል፡፡ እንዲህ እንዲኖርም በመዥገሮች የተወረረችው እናት ሀገር በወያኔዎቹ አማካይነት ለአንዱ የእንጀራ እናት ለሌላው ደግሞ የእውነት እናት ሆና ለሆዳም ጥገኞቹ ሁሉንም ነገር እያመቻቸችላቸው ትገኛለች፡፡ ለምሳሌ በወያኔ ማኅበር ያልተደራጀ ዜጋ ሁለት በሁለት ለሆነች የንግድ ቤት ከገቢው ጋር ፈጽሞ የማይመጣጠን እጅግ ከፍተኛ ኪራይና ግብር እንዲከፍል ሲገደድ (ሂድ አትበለው እንዲሄድ ግን አድርገው በሚሉት ፈሊጣቸው) ለሆዳሞቹ ግን ካስፈለገ ካለኪራይና ካለአንዳች ግብር በሕዝብ ገንዘብ እንደፈለጉ ይሆናሉ፡፡ ባንኮች ሳይቀሩ ለነሱ የግል ጥገቶች ናቸው፡፡ የሀገር ስሜት ዛሬ ያልጠፋ ታዲያ መቼ ይጥፋ?
ይህ መሰሉና ሌላው ግፍ ሁሉ አልበቃ ብሎ ነው እንግዲህ የእሳቱ ፖለቲካ በሀገር ደረጃ እየተፋፋመ የሚገኘው፡፡ እንደሰማነው በሐረር ከአንዴም ሁለት ጊዜ ቃጠሎ ተነስቶ በብዙ ሚሊዮን የሚገመት ብርና ሀብትና ንብረት ወድሟል፡፡ ይህ የሆነው በወያኔው ፈቃድና ይሁንታ መሆኑን የምንረዳበት መንገድ ደግሞ እሳቱን ለማጥፋት ጥረት ሲደረግ አስቀድሞ የተዘጋጀው የወያኔ ጦር እሳቱን ከብቦ አላሰቀርብም ማለቱና የእሳት አደጋ ሠራተኞችም እሳቱ የሚፈለገውን ጥፋት ካገባደደ በኋላ ሥራቸውን እንዲሠሩ መፈቀዱ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ግፍ ከኢትዮጵያ ውጪ የሚደረግ አይመስለኝም፤ እንዲያውም አይደረግም፡፡ ምክንያቱም የሀገር ዜግነቱን የካደና ሀገር እየቸረቸረ የሚሸጥ የሀገር መሪ ከኢትዮጵያ ውጪ በየትም ሥፍራ ይኖራል ብዬ አላምንምና፡፡
የሐረሩ እሳት መንስኤው ወያኔ ሆኖ ዓላማው ደግሞ ቦታውን ለወያኔያዊ ባለሀብቶች ለመስጠትና በእግረ መንገድም ተቀናቃኝ ኢ-ወያኔያዊ ባለሀብቶችን ለማክሰም ነው – ይህን እውነት ለማወቅ ጠንቋይ መቀለብ አያስፈልግም፡፡ በጣም ግልጽ ነው፡፡ መንታ ዓላማ ያነገበ ቃጠሎ ነበር ማለት ነው፡፡ አንደኛውና ዋነኛው በሥርዓቱ የማይፈለጉ ዜጎችን ማደኽት – ሁለተኛው በነሱ ቦታ ደግሞ ለሥርዓቱ ዕድሜ ቀን ከሌት ተንበርክከው ሰይጣንን የሚለምኑ ፍቁራን አባላትንና ደጋፊዎችን ማቋቋም፤ በቃ፡፡ በጨው ደንደስ በርበሬ ተወደስ ይባላል፡፡ በኢትዮጵያ መሬት፣ በኢትዮጵያውያን ሀብትና ንብረት ፀረ-ኢትዮጵያ የሆኑ የመንግሥትን ሞሰብ ገልባጮችና ደጋፊዎቻቸው ይገባበዙበታል፤ ይጠቃቀሙበታል፡፡ እንግዴ ልጅ ሀገር ሻጭ ማዕዱን ሲጫወትበት ልጅ ከበይ ተመልካችነትም ወርዶ የሥቃይ ሰለባ ሆኗል፡፡ እየተራቡ በሀገር መኖርም ክልክል ሆኖ ለሞትና ለስደት መዳረግ ዕጣችን እንዲሆን ተፈርዶብናል፡፡ ይህን ቅሚያና ዘረፋ፣ ይህን የግፎች ሁሉ የበላይ የሆነ ግፍ በእሳት አማካይነት እውን ለማድረግ ደግሞ የኢትዮጵያን መለዮ ለባሽ ይጠቀማሉ -በዓይነቱ ልዩ የሆነ የታሪክ ምፀት ማለት ይህ ነው፡፡ ዋ እኔን! ይህች ቀን ልታልፍ እምቢልታው ሲነፋ እነዚህ ጉግማንጉጎች ምን ይውጣቸው ይሆን?
አዲስ አበባም ውስጥ በትንሹ ሁለት ያህል ቃጠሎዎች በነዚህ ሁለት ቀናት ውስጥ ተከስተዋል፡፡ አንደኛው የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሲሆን ሌላኛው በአንድ ግለሰብ ቤት የደረሰና የሦስት ሰዎችን ሕይወት የጠየቀ ቃጠሎ ነው፡፡ ያሳዝናል፡፡ ነፍሳቸውን ይማር፡፡ የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤቱ ግን ያጠያይቃል፡፡ እርግጥ ነው – ቃጠሎው ተፈጥሯዊ ሊሆን ይችላል፡፡ እንደማንኛውም አደጋ ሆን ተብሎ ሳይሆን ድንገት ሊነሳ የመቻሉ ዕድል እንዳለ ሆኖ ከወያኔ ባሕርይ ተነስተን ስንገምት መነሾው ፖለቲካዊ አንድምታም ሊኖረው እንደሚችል ብንጠረጥር “ጠርጣሪዎች(skeptics)” ተብለን ልንታማ አይገባም፡፡ እንዲያውም ስንትና ስንት ጥበቃ የሚደረግለት ትልቅ ድርጅት በቀላሉ ለእሳት ይዳረጋል ብሎ ከማሰብ አለማሰብ ይሻላል ብለን ብንከራከር የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም ከድንገቴ አደጋነት ይልቅ የወያኔው ተንኮል እንደሚኖርበት መገመት አይከብድም፡፡ ወያኔ ለምን ብርሃንና ሰላምን ያቃጥላል? ምን ያገኛል? ከመገመት ባለፈ እውነተኛውን ነገር ማወቅ ሊከብድ ይችላል፤ መገመት ደግሞ ለማንም የማይከለከል የሁሉም መብት ነው፡፡

ከሁሉም በፊት ግን አንድ አጠቃላይ እውነት መኖሩን እንመን፡፡ ያም እውነት ወያኔ ቢቻል ቢቻል ኢትዮጵያ እንዳለች ብትቃጠል ወይም እንጦርጦስ ብትወርድ ደስ ይለዋል እንጂ የማይከፋ መሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ስሟ ሲነሳ የሚዘገንናቸውና ጠበል በመጠመቅ ያለ ሰው ላይ እንደተከሰተ ሰይጣን የሚያንዘረዝራቸው እነበረከትንና ሣሞራን የመሳሰሉ መፃጉዕ ዜጎች የሚገኙበት መንግሥታዊ መዋቅር የኢትዮጵያ ታሪክ የሚዘከርበትና አእምሯዊ ቅርስ የሚቀመጥበት ማዕከል ቢቃጠል አይደሰትም ብሎ ማሰብ የዋህነት ይመስለኛል፡፡ በዕንቆቅልሽ ሀገር ውስጥ ልንጠብቅ የማይገባንን ነገር ብንጠብቅ ብልህነት እንጂ ትዝብት ውስጥ ሊያስገባን የሚችል ሞኝነት አይደለም፡፡

በመሆኑም ወያኔ ይህን የእሳት ፖለቲካውን በመጠቀም ዜጎችን ራቁታቸውን ማስቀረቱንና ወደበረንዳ ሕይወት መለወጡን እንዲያቆም፣ የዘመናት ቅርሳችንን እያቃጠለ ታሪክ አልባ ሆነን እንድንቀር ማድረጉን እንዲገታና እስከተቻለ ደግሞ ነፃነታችንን እውን ለማድረግ የምንችልበትን የጋራ ሥልት መቀየስ እንድንችል የጋራ ጥረት እንድናደርግ ጥሪየን አቀርባለሁ፡፡ ሰላም፡፡

የአዲስ አበባው የእሪታ ቀን ተቆረጠ –የአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቅ ክፍል የፓርቲውን ደብዳቤ ተቀብሏል፤ –ፍኖተ ነጻነት

$
0
0

የአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቅ ክፍል የፓርቲውን ደብዳቤ ተቀብሏል

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የአዲስ አበባ ምክር ቤት የከተማይቱ መሰረታዊ ችግሮች እየተባባሱ ከመምጣት ውጪ ለውጥ ማሳየት ባለመቻላቸው ለዚህ ተጠያቂ መሆን ያለበትን የከተማይቱን አስተዳደርና ገዢውን ፓርቲ የሚቃወም ‹‹የእሪታ ቀን››በሚል መሪ ቃል መጋቢት 28/2006 ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚደርግ አስታውቋል፡፡

በዛሬው እለት የፓርቲው ተወካዩች ለአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቅ ክፍል ስለ ሰልፉ የሚገልጽ ደብዳቤ በማስገባት ተመልሰዋል፡፡ሰላማዊ ሰልፉ በተያዘለት ቀነ ገደብ የፓርቲው ጽ/ቤት ከሚገኝበት ቀበና በመነሳት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ፊት ለፊት እንደሚጠናቀቅ የአዲስ አበባ አንድነት ህዝብ ግኑኝነት አቶ ያሬድ አማረ አስታውቀዋል፡፡AA-001

አቡጊዳ –የሕገ መንግስቱ መሰረት የሆነው ቻርተር በኤርትራዊዉ በረከተ ሃብተ ስላሴ በሚመራ ኮሚሽን እንደዘጋጀ ተገለጸ

$
0
0

ኢሕአዴግ አዲስ አበባ ሲገባ፣ በጎሳ የተደራጁ ድርጅቶችን በማሰባሰብ ፣ በ1991 በተደረገው የአዲስ አበባ ኮንፈራንስ ፣ የሽግግር መንግስት ቻርተር ተብሎ የሚታወቀዉን ሰነድ እንዲጸድቅ ማስደረጉ ይታወቃል።

ቻርተሩ አሁን ያለውን በጎሳ ላይ የተመሰረተ ዘረኛ ፌዴራል አወቃቀር ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲገበር ያደረገ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ በየትኛው አገር የሌለ፣ ጸረ-ኢትዮጵያዊ የብሄረሰቦች የመገንጠልን መብትን በሕግ ለመጀመሪያ ጊዜ የደነገገም እንደሆነ ይታወቃል።

ዶር ነጋሶ ጊዳዳ አባል የነበሩበት የሕገ መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን፣ በቻርተሩ የተቀመጠዉን ፌዴራል አወቃቀርና የመገንጠል መብትን እንዳለ ሕገ መንስግቱ ዉስጥ እንዲካተት በማድረግ ፣ ቻርተሩ «ሕገ መንግስት» የሚል ሽፋን ተሰጥቶት፣ ኢዴሞክራሲያዊና ኢፍትሃዊ በሆነ መንገድ የአገሪቷ ሕግ እንዲሆን መደረጉም የሚረሳ አይደለም።

በኋላ እንደ ሕግ መንግስት የተወሰደው ይሄ ቻርተር፣ በአዲስ አበባ ኮንፍራንስ በኢትዮጵያዉያኖች እንደጸደቀ ቢነገርም፣ በተሰነይ/ ኤርትራ ፣ በአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ፣ አቶ መለስ ዜናዊና አቶ ሌንጮ ለታ በተቋቋመው እና ኤርትራዊዉ ዶር በረከት ሃብተስላሴ በሚመሩት ግብረ ኃይል አስቀድሞ የተዘጋጀ እንደሆነ፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት የነበሩት ዶር ነጋሶ ጊዳዳ ይናገራሉ።

ዶር ነጋሶ በቅርቡ ዘሃበሻ ላይ ለአንባቢያን ባቀረቡት ጽሁፍ ፣ «There is also evidence that a task force including Bereket Habte Sellasie was established by Isayas, Meles and Lencho to draft the Charter and agreed upon between Meles and Lencho at Tesenai/Eritrea.” ሲሉ ነበር የነበረዉን ሁኔታ ለማስረዳት የሞከሩት።

የዶር ነጋሶን ጽሁፍ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ !

!

የውህደቱ ቁማርተኞች –አስራት አብርሃ

$
0
0

የሀገራችን የተቃውሞ ፖለቲካ ወደ አንድ ጠንካራ የለውጥ አማራጭነት እንዲሰባሰብ እና ገዥውን ፓርቲ የሚገዳደር ወሳኝ ኃይል ሆኖ እንዲወጣ ማስቻል የብዙ ቀናት አሳቢ ኢትዮጵያውያን ፍላጎት እንደሆነ ይሰማኛል። እኔም ራሴን ይህ ዓላማ ከፍፃሜ እንዲደርስ ከሚፈልጉ ወገኖች ውስጥ እንደ አንዱ በማድረግ እቆጥረዋለሁ። ውህደት እንዲኖር መፈለግ አንድ ነገር ሆኖ፤ ማን ከማን ጋር ነው የሚወሃደው? የውህደት መስፈርቱን ምን መሆን ይኖርበታል? የሚለውንም አብሮ ማየቱ የሚገባ ይሆናል።

ከርዕዮተ ዓለም አንፃር በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በዋነኝነት ሶስት ዓይነት አሰላለፍ ነው ያለው። አንደኛው “ወግ አጥባቂ” ወይም “ቀኝ አክራሪው” ኃይል እየተባለ የሚጠራው ነው። በዚህ ጎራ የሚመደቡት ኃይሎች ላይ ላዩ ሲታዩ፣ በርዕዮተ ዓለም የግለሰብ ነፃነት መሰረት የሚያደርገውን ሊበራል ዴሞክራሲ የሚከተሉ ይመስላሉ፤ በተጨባጭ ካላቸው አመለካከት፤ ከሚያራምዱት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ አንጻር ሲታዩ ደግሞ፤ የተወሰነ አከባቢ ወይም የህብረተሰብ ክፍልን በማዕከልነት የሚወክሉ፤ ከዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ባሻገርም ኢህአዴግ በሚከተለው የብሄር ተኮር ፖለቲካ ምክንያት አጥተነዋል የሚሉቱን የበላይነት የማስመለስ አጀንዳ ያላቸው ናቸው።

የእነዚህ ኃይሎች አካሄድ ያለፈው ስርዓት በምንም ዓይነት መልኩ ተመልሶ እንዲመጣ ከማይፈልጉ ኃይሎች ጋር በተቃራኒ እንዲቆሙ ስለሚያደርጋቸው ባሉት ፖለቲካዊ አስላለፎች መካከል ውህደት እንዳይኖር እንቅፋት የሚሆን ነው። ይሄ ጎራ አንዱን ጥግ ወይም ጫፍ ይዞ የሚሄድ፤ በደንብ የተደራጀ፤ ከሌሎች አሰላለፎች አንፃር ድርብ፣ ድርብርብ የሆነ ግብ እና ዓላማ ያለው በመሆኑ ጎልቶ የሚሰማና የሚታይ ነው። በመሆኑም የፖለቲካ ጨዋታው ሜዳ ጥቂቶች ብቻ የሚጫወቱበትና ሌላውን የዳር ተመልካች እንዲሆን የሚያደርግ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር፤ በተለያዩ ልሂቃን መካከል መተማመን እንዳይኖር በማድረግ በእኩል የድርሻውን የሚያበረከት ነው።

ሁለተኛው አሰላለፍ ከላይ በአንደኛው ከተገለፀው ጎራ በተቃራኒው ያለ እና ከርዕዮተ ዓለም አንፃር ሲታይም ግልፅ ባለ ሁኔታ ማስቀመጥ የሚያስቸግር፤ በዋነኝነት ክልላዊ ብሄርተኝነት ጎልቶ የሚንፀባረቅበት፤ ከፖለቲካዊ ግብ አንፃር ደግሞ የራሳቸውን አከባቢ ያለምንም ጣልቃ ገብነት ከማስተዳደር ጀምሮ በፌደራል መንግስት ውስጥም ተገቢውን ውክልና እንዲኖራው የሚፈልጉ፤ እንዲሁም አሁን ካለው ፌደራል መንግስት በመገንጠል የራሳቸውን ነፃ ሀገር ለመመስረት የሚታገሉ ቡድኖች በአንድ ላይ የሚያጠቃልል ነው። በዚህ ጎራ የተሰለፉ ኃይሎች በሚያራምዱት ፖለቲካዊ አመለካከት ምክንያት “የተነሱት ኢትዮጵያን ሊበታትኑ ነው” የሚለውን የሌላኛው ወገን ውንጀላ ስለሚያጋልጣቸው እና ስለሚያስጠረጥራቸው አብሮ መስራትና በጋራ መታገል እንዳይቻል ምክንያት መሆናቸው አልቀረም።

እውነትም የአንዳንዶቹ እንቅስቃሴ ሲታይ ኢትዮጵያን ሊበታተን የሚችል አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ለመረዳት ጥልቅ ምርምር የሚያስፈልገው አይደለም። ከሁሉም በላይ ደግሞ እነዚህ ኃይሎች ወደ አንድ ህብረ ብሄራዊ የሆነ ኃይል ለማምጣት እና ከሌላው ጋር ማዋሃድ በጣም አስቸጋሪ ነው። አንዳንዶቹ “ከሌላው ጋር ከተዋሃድን በሌሎች እንዋጣለን” ይላሉ፤ የዚህ ዓይነት ስጋት ካላቸው ፓርቲዎች ውስጥ የአንዳንዶቹ ስጋት ውሀ የሚቋጥር አይደለም። ለምሳሌ የኦሮሞ ፓርቲዎች “በሌሎች እንዋጣለን” ሲሉ በእውነቱ ልብ ለሚል ሰው ራሳቸውን በራሳቸዉ የሚሰድቡ ነው የሚመስሉት፤ ወይም ደግሞ ሰፊውን የኦሮሞ ህዝብ አይወክሉም ማለት ነው። የተወሰኑ ደግሞ “ከሌሎች ጋር ከተዋሃድን የተመሰረትንበትን የብሄር ወይም የክልል ዓላማችንን ማስፈፀም አንችልም” የሚል ምክንያት የሚያቀርቡ ናቸው። እነዚህ ኃይሎች ከሌሎች ጋር ጥምረት ወይም ግንባር በመፍጠር የፌደራሉን መንግስት መመስረት የሚፈልጉ፤ አሁን በስራ ላይ ያለውን ህገ መንግስትም ሆነ አስተዳደራዊ አከላለል ላይ ብዙም ቅሬታ የሌላቸው፤ ብዙውን ጊዜ ከገዥው ፓርቲ ጋር ያላቸው ልዩነት የአፈፃፀምና የአተገባበር የሆነ፤ ወይም በኢህአዴግ የተሰጠው “የብሄር መብት በቂ አይደለም” የሚሉ ናቸው። እነዚህ ኃይሎች ጥቂት ይሁን እንጂ በዚህ አሰላለፋቸው እንዲገፉበት የሚያደርግ ከውጭም፣ ከሀገር ውስጥም ፅንፈኛ የሆኑ ደጋፊዎች ያላቸው ናቸው።

እነዚህ ከላይ ያሉትን ፍፁም ተፃራሪ የሚመስሉትን ሁለት ጎራዎች ለማዋሀድ ማሰብ ከባድ ነው። ነገር ግን ፍፅም የሚቻል አይደለም ለማለት የሚስችል መሰረታዊ የሆነ ምክንያት አለ ብዬ አላስብም። እኔ በበኩሌ እነዚህን ኃይሎች በጋራ ሊስማሙበት የሚችል ፖለቲካዊ አጀንዳ በመቅረፅ፣ እርስ በእርሳቸው መተማመን የሚችሉበትን ሁኔታ በመፍጠር አንድ ላይ ተዋህደው አስተማማኝ የሆነ የፖለቲካ አማራጭ ሊያመጡ ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ። ይህን አቋሜንም በተገኘ አጋጣሚ ሆሉ ከማንፀባረቅ ተቆጥቤ አላውቅም። በዚህ አቋሜ ደስተኛ ያለሆነ አንዱ አፍቃሬ ህወሀት “አይጥና ድመት የሚተባበሩበት አጋጣሚዎች አሉ” በማለት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ፖለቲካዊ አሰላለፎች ለማዋሀድ ማሰብን ድመትን ከአይጥ ጋር የማስማማት ያህል ፈፅሞ የማይቻል አድርጎ አቅርቦታል።

እንደ እኔ እምነት ከሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተገቢ የሆነ የተሳካ ውህደት ማድረግ ያልቻሉበት ስረ ምክንያት በፓርቲዎቹ መካከል ባለው ያለመተማመን፤ የስልጣን ጥመኝነት እና የተወሰነ አካባቢን ብቻ የሚወክል ድብቅ ፖለቲካዊ አጀንዳ መኖር ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ የፖለቲካ መሪዎች ራዕይ ማጣት ነው። ከማንኛውም ተፅዕኖ ውጪ ሆነ ለሚያየው ሰው ኢትዮጵያውያን ሁሉ ወደ አንድ ኃይል ተሰባስበው እንዳይታገሉ የሚያድርግ መሰረታዊ የሆነ ችግር የለም። በዋነኛነት ውህደት ይቻላል ሲባል ከዚሁ መሰረታዊ እምነት በመነሳት ነው።

በአንድ ላይ ለመስራትና በአንድ ላይ ለመኖር ሰው በመሆናችን ብቻ በራሱ በቂ ምከንያት ነው። ለምሳሌ የአሜሪካ የጥቁሮች የነፃነት አባት የሚባለው ማርቲን ሉተር ኪንግ “I have Dream” በሚለው ታሪካዊ ንግግሩ “አንድ ቀን ጥቁሮችና ነጮች ሁለቱም እኩልነት በአንድ ላይ በአንድ ሀገር እንደ አንድ ህዝብ ሆነው የሚኖርበት ቀን እንደሚመጣ ህልም አለኝ” ያለው ከዚሁ የሰው ልጆች ሰብአዊ አንድነት በመነሳት ነው። ያን ህልሙ እርሱ በህይውት ኖሮ ባያየውም፤ እኛ በዘመናችን እውነት ሆኖ ተመልክተናል። ዛሬ አሜሪካውያን ነጭ እና ጥቁር ሳይሉ ለሁሉም የምትስማማ ሀገር ለመፍጠር መሰረታዊውን ጥያቄ መልሰው ጨርሰዋል። የዛሬ ሀምሳ ዓመት ፍፁም ሊታሰብ የማይችል የነበረውን በጥቁር ፕሬዝዳንት የመመራት ጉዳይ፣ ዛሬ ጥቁሩን መሪያቸው አድርገው በመምረጥ በሰላም አብረው እየኖሩ ነው፤ ከዚህ አንጻር ለሌላውም ጥሩ ምሳሌ ሆነዋል።

እንደዚሁም ታላቁ አፍሪካዊ የነፃነት አባት ኔልሰን ማንዴላ “ነጮች ከሀገራችን ይውጡ!” የሚለውን ፅንፍ የያዘ አቋም በማስቀረት “ጥቁሮችም ሆነ ነጮች በሰላምና በፍቅር አብረን መኖር እንችላለን፤ ደብብ አፍሪካ ለሁላችንም ትበቃናለች።” የሚለውን ሀሳብ በማቀንቀን ድል አድርጓል። ለሁሉም ደቡብ አፍሪካውያን የነፃነት ጮራ፣ ሰላምና ነፃነት አስገኝቷል። በዚህም ተደናቂነትን፣ እንዲሁም ምሳሌ የመሆንን ክብር ተጎናጽፎበታል። በዚህ እምነቱም ምክንያት በክብር ኖሮ በክብር አልፏል። ይህ ትልቅ የነፃነት ሰው፤ በሰው ልጆችን መሀል መሰረታዊ የሚባል ልዩነት እንደሌለ በመገንዘብ “ሰው ሁሉ አንድ ነው፤ ማንኛውም ሰው እኩል በሰውነቱ ታውቆ፣ በአንድ ላይ በፍቅር፣ በመከባበር እና በመቻቻል ሊኖር ይችላል” ከሚል ትክክለኛ ፍልስፍና ስለተነሳ ስኬቱ ታላቅ ሆኗል።

በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያን ሰው ከመሆን ባሻገር፤ ከሌላው ሀገር ህዝብ የሚለየን ብዙ ነገር አለ፤ ይብዛም ይነስም በአንድ ሀገር ለረጅም ጊዜ አብረን የኖርን፣ የጋራ የሆኑ ብዙ ነገሮች ያሉን፣ ክፉ እና ደጉን አብረን ያሳለፍን፣ የተዋለድንና የጋራ በሆነ ማንነት ያደግን ህዝቦች ነን። ይህ ሁሉ ታሳቢ ሲደረግ ኢትዮጵያውያን ከቋንቋ እና ከዘር በላይ ከፍ ባለ ሀገራዊ ማንነት ለማሰብ፤ ለመዋሀድ፣ አብረን ለመስራት እና የጋራ የሆነ ፖለቲካዊ አጀንዳ ለማራመድ የሚከለክለን ነገር የለም። ሌላው ቢቀር እንኳ በአንድ ላይ ለመኖር የሚያስችል፣ በደቡብ አፍሪካ ከሚኖሩት ነጮች እና ጥቁሮች በላይ የሆነ ምክንያት አለን።

ስለዚህ በእኛ ሀገር በተለያዩ ፖለቲካዊ ኃይሎች መካከል ያለውን ልዩነት የአይጥ እና የድመት ያህል መሰረታዊ እና ተፈጥሯዊ አስመስሎ ማቅረብ ትክክል አይደለም። ልዩነቱ የአይጥ እና የድመት ያህል፤ የጠፊ እና የአጥፊ ዓይነት ከሆነ አብሮ መጓዝም፣ መዋሀድም የሚታሰብ አይደለም ማለት ነው። ምክንያቱም መሰረታዊ የሆነ የተፈጥሮ ልዩነት ካላቸው ልዩነቱን ማስታረቅ የማይቻል ይሆናል። አይጥ እና ድመት በምንም ተአምር ተስማመተው፤ አብረው ሊኖሩ የሚችሉ ነገር አይደሉም። እኔ እስከማውቀው ድረስ አይጥና ድመት ተቃቅፈው አንድ ላይ በፍቅር መኖር እንደሚችሉ ተስለው ያየሁት በጀሆባ ምስክሮች (Jehovah’s Witness) መፅሔት ላይ ነው።

በእኔ እምነት በሀገራችን ህዝቦች መሀል መሰረታዊ የሆነ ልዩነት የለም። በሀገራችን ያለው መሰረታዊ ችግር በልሂቃኑ መካከል ያለውን ያለመተማመን፣ የስልጣን ጥመኝነት፣ ጠባብነት፣ ጥላቻ እና ቂም በቀል ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ዛሬ ላይ ለሚታው ፖለቲካዊ ውጥንቅጥ ለዘመናት ተንሰራፍቶ የኖረውን የፊውዳሊዝም እና የባለአባታዊ ስርዓተ ማህበር የፈጠረው የአስተሳሰብ ሰንካላነት ውጤት ነው።

ሶስተኛው ፖለቲካዊ አሰላፍ ከላይ ያሉትን ሁለቱንም ጫፎች በማስቀረት ወይም በማስታረቅ ለዘብተኛ የሆነ አቋም የሚያራምዱ የተካተቱበት ነው። የእድል ጉዳይ ሆኖ በዚህ ጎራ የሚመደቡ ኃይሎች አንድም በአግባቡ የተደራጁ አይደሉም፤ አንድም የተደራጁትም ነጥረው ለመውጣት አልቻሉም። ለዚህ እንደምክንያት ሊሆን የሚችለው ከላይ በተገለፁት ሁለት ፅንፍ አሰላለፎች በእኩል ስለሚመቱ ነው። በእኔ እይታ መካከለኛ አቋም ከሚያራምዱት ፓርቲዎች መካከል አንድነት ፓርቲ አንዱ ይመስለኛል። ነገር ግን አንድነት በዚህ መስመር ለመጓዝ ብዙ ዋጋ እንዲከፍል ተደርጓል። በወግ አጥባቂዎቹ በእኩል ለዘብተኛ እና ሁሉንም አቃፊ የሆነ ፕሮግራም ያለው በመሆኑ፤ እንዲሁም ብሄር (ክልል) ተኮር ከሆኑ ፓርቲዎች ጋር አብሮ በመስራቱ ምክንያት በማድረግ ወደዚያኛው ጥግ፣ ወደ ግራ ዘምም ጎራ እንደተቀላቀለ አድርገው ዘመቻ ያካሄዱበታል። በሌላ በእኩል ደግሞ በብሄር የተደራጁ ኃይሎች የአማራ ብሄር ወይም የከተሜ ድርጅት አድርገው በመሳል ሁለቱን ጫፎች ለማቀራረብ በሚያደርገው ሙከራ ላይ ውሀ ይቸልሱበታል።

በእውነቱ፣ በዚህ ሰዓት የሚፈለገው የእነዚህን ሁለት ጫፍ የሆኑ ኃይሎችን ልዩነቶችና ስጋቶች የሚያስወግድ መካከለኛ የሆነ መንገድ የያዘ፤ ሁሉም ኃይሎች ሊያሰባስብ የሚችል አስታራቂ አቋም ያለው ፖለቲካዊ ኃይል ነው። በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ መድረክ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች ተዋህደው ወደዚህ ደረጃ ይሸጋገራሉ የሚል ተስፋ ነበር። ነገር ግን በመሪነት ደረጃ ባሉ ልሂቃን ምክንያት ሊሳካ አልቻለም። ይሄ በቀላሉ እንደማይሳካ ግልፅ እየሆነ ሲመጣ በመድረክ አባል ፓርቲዎች መካከል የተጀመረውን ውህደት በማጠናከር ዓረና ከአንድነት እና ከደቡብ ህብረት ጋር እንዲዋሀድ ስራ ተጀምሯል። ይሄ ነው እንግዲህ ድመትን ከአይጥ ጋር እንደማዋሃድ ተደርጎ በህወሀት ሰዎች ዘንድ እየተተቸ ያለው። የአረና እና የአንድነት ውህደት መድረክ ከተመሰረተ ጀምሮ ሲታሰብ የነበረ ቢሆንም፤ በተለያዩ ምክንያቶች ሊሳካ አልቻለም። ከአንድነት ጋር ውህደት እንዲኖር የምፈልግበት ዋናው ምክንያት አንድነት በሀገራችን ካሉት የተቃውሞ ኃይሎች ጋር ሲነፃፀር በፕሮግራም እና በተወሰነ መልኩ በአመለካከት ደረጃ ለዘብተኛ የሚባል አቋም ያለው ፓርቲ ሆኖ ስለሚሰማኝ ነው።

ነገር ግን ዓረና የውህደት ጥያቄ ባቀረበት ማግስት አንድነት ከመኢአድ ጋር አስቸኳይ የውህደት እንቅስቃሴ መጀመሩ፤ በዓረና በእኩል ደግሞ ከአንድነት ይልቅ ከደቡብ ህብረት ጋር ውህደት እንዲኖር የሚፈልጉ ወገኖች መኖር፤ በዚህ ሀገር ያለውን የእንተባበር እንቅስቃሴ የልብ እንዳልሆነ አንዱ ማሳያ ነው።

አንድነት ከመኢአድ ጋር ለመዋሀድ መፈለጉ በራሱ ችግር የለውም፤ ነገር ግን በማን ፕሮግራም ነው የሚዋሃደው? የሚለው ጉዳይ ወሳኙ ነገር። አሁን ያለው የአንድነት ፕሮግራም የግለስብና የቡድን መብቶችን ባገናዘበ ሁኔታ የተዋቀረ፤ በብዙ መልኩም ተራማጅ የሚባል ዓይነት ነው። መኢአድ በዚህ ፕሮግራም የሚዋሃድ ከሆነ ጥሩ ለውጥ ይሆናል። ቀጥሎ ከዓረናም ሆነ ከደቡብ ህብረት ጋር ሊኖር የሚችለውን ውህድት እንዲሳካ መንገድ የሚጠርግ ይሆናል። አንድነት ወደኋላ ተመልሶ በመኢአድ ፕሮግራም የሚዋሀድ ከሆነ ግን የተመደውን አሰላለፍ ከማጠናከር የዘለለ አዲስ ዓይነት የኃይል አሰላለፍ የሚያመጣ አይሆንም። መኢአድ በብሄር ወይም በክልል የተደራጁ ኃይሎች ላይ ያለው አመለካከት እጅግ የተዛባ፤ ወግ አጥባቂ እና ነባራዊውን እውነት ያላገናዘበ የሚባል ዓይነት ነው። ከዚህ አንፃር ካየነው ለአንድነት የብሄርንና የጎሳን ልዩነት በቅጡ ከማያውቅ ወይም ሊያውቅ ከማይፈልግ ፓርቲ ጋር መዋሀዱ የሚፈይድለት ነገር ያለ አይመስለኝም።

ዓረናም ቢሆን ከደቡብ ህብረት ጋር የሚያደርገው ውህደት ሀገራዊ ፓርቲ የመሆን ፍላጎቱ እውን ከማድረጉ ውጪ ያን ያህል ትርጉም ያለው ውህደት ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ሰሜንና ደቡብ ላይ ቆመው እንዋሃድ ቢሉ፤ ሁለት ፍቅረኞሞች በአጥር ተንጠራርተው ለመሳሳም የሚያደርጉትን ሙከራ ያህል አስቸጋሪ ይሆናል። ምክንያቱም መሀሉን ለማገናኘት ረጅም ጊዜ እና ብርቱ ጥረት የሚጠይቅ በመሆኑ ነው።

የሰማያዊ ፓርቲ ቁጥር 5 ነገረ- ኢትዮጵያ ጋዜጣ ርእስ አንቀጽ –ለለውጡ ዝግጅት ያስፈልጋል!

$
0
0

ለለውጡ ዝግጅት ያስፈልጋል! እንዲህም ተብሏል ለውጥን ማዘግየት ይቻል እንደሆን እንጂ ገድቦ ማስቀረት እንደማይቻል ከትርክት አልፎ በተግባር የታየ ሀቅ ነው፡፡ በተለይ ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴን አፍኖ መዝለቅ የማያዛልቅ ሙከራ እንደሆነ በተለያየ ጊዜ በተለያዩ ሀገራት ታይቷል፡፡ በዓለም ላይ የማይለወጥ ነገር አለ ከተባለ ራሱ ለውጥ ነው የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት ጆን ኦፍ ኬኔዲ ‹‹እነዚያ ሰላማዊ ለውጥን የማይቻል ለማድረግ የሚሞክሩ ሁሉ ሀይል ያመዘነበት አብዮትን የማይቀር ያደርጉታል›› እንዲሉ ለውጥን ለመገደብ መሞከር በራሱ ከዚያም በላይ የሆነ ታላቅ አብዮትን ይጠራል፡፡

በሀገራችን ለበርካታ ጊዜያት ይህ ሀቅ በእውን ተከስቷል፡፡ 40 አመታትን ወደኋላ ብንጓዝ እንኳ የ1966ቱ አብዮት ያለበቂ ዝግጁነት የተካሄደ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ በወቅቱ የኑሮ ውድነት፣ ብዝበዛ እንዲሁም ቅጥ ያጣ በስልጣን መባለግ የነበረ ቢሆንም፣ የአጼው ስርዓት የህዝብን ሰቆቃና ቅያሜ፤ የዓለምንና የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ከምንም ባለመቁጠሩ የተቀጣጠለውን ህዝባዊ አብዮት፣ በአግባቡ መርቶ ፍሬያማ ለማድረግ የሚያስችል ስራ ባለመሰራቱ አሁን ድረስ ለዘለቀው የፖለቲካችን ብልሹነትም ሆነ ለስርዓቱ አሳዛኝ መጨረሻ ጉልህ አሉታዊ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡

ህዝባዊ አብዮት መቼ ሊቀሰቀስ እንደሚችል በእርግጠኝነት ለማወቅ ቢከብድም በአንዲት ሀገር ያለው ነባራዊ ሁኔታን በመመልከት ግን የለውጡን ነጋሪት ማዳመጥ ይቻላል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በተለያዩ ሀገራት የተነሱትን አብዮቶች ስናይ፣ ማናቸውም በአምባገነን የአገዛዝ ስርዓት ስር የሚገኝ ህዝብ ነጻነቱን በህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ለማወጅ ወደ ኋላ እንደማይል ነው፡፡ በቱኒዝያ፣ ግብጽ፣ ሊቢያና በሌሎችም ሀገራት የተስተናገደውን ህዝባዊ አብዮት ለአብነት ማንሳት ይቻላል፡፡

ሰሞኑን ደግሞ መሰል አብዮት ከወደ ዩክሬን ተስተናግዷል፡፡ የዚህ ሁሉ አብዮት መንስኤ በየሀገራቱ ሰፍኖ የቆየው አምባገንነት ነው፡፡ ወደ ሐገራችን ሁኔታ ስንመለስም ከ1966ቱ ጊዜ በባሰ የኑሮ ውድነት፣ የሐይማኖት ጣልቃገብነት፣ ኢ-ፍትሐዊነት፣ የመሰረታዊ አገልግሎት መጓደልና ሌሎችም ችግሮች ተደራርበው የህዝብን ጫንቃ አጉብጠውት ይገኛሉ፡፡

ይህን በሀገራችን የተንሰራፋውን ጭቆናና የኑሮ ውድነት ስናይ የህዝባዊ አብዮትን መምጣት እንድንገምት ያደርገናል፡፡ እንዲህ አይነቱ ሲጠራቀም በቆየ የህዝብ ብሶት ምክንያት ሊነሳ የሚችልን የህዝብ የለውጥ እንቅስቃሴ ደግሞ ማስቀረት አይቻልም፡፡

ትንታጉ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ደጋግሞ ይለው እንደነበረው ዳግም አብዮቱ በኢትዮጵያ መከሰቱ አይቀርም፡፡ ይህን ለውጥም የሚያስቀረው ኃይል አይኖርም፤ ያለው ብቸኛ አማራጭ (በተለይ በመንግስት በኩል) የሚመጣውን ለውጥ በአግባቡ ማስተናገድ ወይም ‹ማኔጅ› ማድረግ ነው፡፡

በእርግጥም ለውጡ ካለው የሀገሪቱ ሁኔታ አኳያ ሲታይ መከሰቱ የማይቀር ነው፡፡ ስለሆነም አሁን ላይ ለሚመጣው ህዝባዊ እንቅስቃሴና ለሚከተለው ለውጥ መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ የተከሰተውን ህዝባዊ አብዮት በአግባቡ አለመምራትና አለማስተናገዳችን ያስከተለብንን አሉታዊ ተጽዕኖ የዛሬ 40 ዓመት አይተናል፡፡ አሁን ከዚያ ድክመታችን ትምህርት ቀስመን የቀረበ የሚመስለውን የለውጥ ትግል መምራትና ማስተናገድ እንዳለብን እሙን ነው፡፡

በህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ሁለት ዋና ዋና አካላት ይበልጡን ከፊት የሚገኙ ይሆናል፡፡ አንደኛው መንግስት ሲሆን ሌላኛው በተቃውሞ ጎራ ያለውና የትግል አቀጣጣዩን ክንፍ (ነጻ ማህበራት ሊሆኑ ይችላሉ) የሚያካትተው አካል ነው፡፡ መንግስት ቢችል ለውጡን የማደናቀፍ ስራን ለመስራት መሞከሩ አይቀርም፡፡ ከዚህም አልፎ ጭራሹን የህዝብን እንቅስቃሴ ለመጨፍለቅ ሊሞክር ይችላል፡፡ ይህም እርምጃ እጅጉን አደገኛና ክቡር ህይወትን ሊቀጥፍ የሚችል እስከመሆን ይደርስ ይሆናል፡፡ እንዲህ አይነቱ እርምጃ የሚመጣው ለለውጡ ካለመዘጋጀት ስለሚሆን በመንግስት በኩል ከአሁኑ ዝግጅት ማድረግ እንዳለበት ነገረ-ኢትዮጵያ ማሳሰብ ትወዳለች፡፡

ይህን በማድረግም መንግስት ቢያንስ ለውጡን ‹ማኔጅ› በማድረግ ኃላፊነቱን መወጣት ይቻለዋል፡፡በሌላ በኩል ደግሞ የለውጡን እንቅስቃሴ በአግባቡ መርቶ ተፈላጊውን ውጤት ማምጣት ለማስቻል በተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድና በነጻ ማህበራት በኩል በቂ ዝግጅት ማድረግን እንደሚጠይቃቸው ማስገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ምንም ያህል ከስርዓቱ ወገን ለውጥን ለማስተናገድ ያለመፈለግና ያለመዘጋጀት ቢታይም እንኳ ህዝብ የተነሳለትን ዓላማ ማስቀረት እንደማይቻል ተገንዝበው፣ ለውጡን በተደራጀና በአንድነት መንፈስ ለመምራት የፓርቲዎችና የማህበራት ሚና የጎላ መሆኑ ለአፍታም መዘንጋት የለበትም፡፡ ስለሆነም እነዚህ አካላት ጥቃቅን ልዩነቶች ሊኖራቸው ቢችል እንኳ በእንዲህ አይነት ወቅት ትብብራቸውን ማጠናከርና ለጋራ የህዝብ ጥቅም መቆም ይኖርባቸዋል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ሊመጣ የሚችለው ለውጥ እውን ከሆነ ማግስት ሌላ ችግር እንዳይከሰት ህዝብ አመኔታ የሚጥልበትና በቀጣይ የመሪነት ሚናን ለመወጣት ጠንካራ ፓርቲ ሆኖ መውጣት ግድ ይላል! ለዚህም ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል!

negere_ethiopia_032614
ሙሉዉን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ !

አቡጊዳ –አትላንታ እና ዴንቨር የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን በአዋሳና በደሴ የሚደረጉትን የሚሊየም እንቅስቅሴ ስፖንሰር እንደሚያደርጉ ተገልጸ

$
0
0

በአትላንታ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን በአዋሳ፣ በደንቬር የሚኖሩ ደግሞ በደሴ ለሚደረጉት የሚሊዮኖች ድምጽ ለመሬት ባለቤትነትና ለፍትህ እንቅስቃሴዎች የሚያስፈልግትን ወጭዎች ሙሉ ለሙሉ እንደሚሸፍኑ ማረጋገጣቸውን ፣ የሰሜን አሜሪካ የአንድነት ድጋፍ ማህበራት፣ ሸንጎን እና የሽግግር ምክር ቤቱን ያሳተፈው የሚሊዮኖች ድምጽ የዳያስፖራ ግብረ ኃይል ገለጸ።

የመጀመሪያዉን የአዲስ አበባ እንቅስቃሴን ላስ ቬጋሶች፣ በድረደዋ ከተማ የሚደረገዉን የደብተራዉ ፓልቶክ ክፍል ፣ የቁጫ ከተማ ደግሞ የቃሌ ፓልቶክ ክፍል ስፕንሰር እንዳደረጉ መዘገቡ ይታወሳል።

በአትላንታና እና ዴንቨር ስፕንሰርሺፕ ዙሪያ ከግብረ ኃይሉ የደረሱንን ዘገባዎች ለማንበብ ከታች ይጫኑ

አትላንታ እና ሃዋሳ

ደሴና ደንቨር


ወያኔ ኢህአዲግ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም የቆመ መንግስት አይደለም :: (ገዛኸኝ አበበ ከኖርዌይ)

$
0
0

ወያኔ ኢህአዲግ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም የቆመ መንግስት አይደለም :: ሀገር ማለት የተለያዩ ብሄሮች ፣ የተለያዪ ጓሳዎች እና የተለያዩ ሃይማኖቶች ያሎቸው ሰዎች መኖሪያ ናት :: እኛም ሀገራችን ብለን የምንጠራት ሀገራችን ኢትዮጵያ አኩሪ ታሪክ ያላት የተለያዩ ህዝቦች መኖሪያ ሀገር ስትሆን ሕዝቦቾም ለዘመናት በፍቅር፣ በመተሳሳብ ፣ በመከባባር እና በመተባባር አብሮ ሲኖር የነበሩ ህዝቦች እንደነበሩ ከታሪክ መረዳድ እንችላላን::ይችን ሀገራችንን ኢትዮጵያን በተለያዩ ጊዜና ዘመናትም የተለያዩ መንግስታቶች ለዘመናት በመፈራረቅ መርተዋታል

መንግስታቶችም የኢትዮጵያን አንድነት እና ሎአላዊነትን ጠብቀው ህዝቡም ኢትዮጵያዊነቱን ጠብቆ እና አስከብሮ እንዲኖር የበኩላቸውን አስተዋጹ አብርክተው አልፈዋል:: ጀግኖች አባቶቻችንም የኢትዮጵያ ሕዝብም ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያ አንድነት ሲሉ ደማቸውን አፍስሰዋል፣ አጥንታቸውን ከስክሰዋል ፣ ህይወታቸውንም መሰዋት አድርገው አሳልፈው ሰተዋል :: ምክንያቱም ኢትዮጵያውነት ኩራት ኢትዮጵያውነት ፍቅር ኢትዮጵያውነት አንድነት መሆኑን ከመሪያቸው ተምረውታልና:: በአሁን ሰአት በስልጣን ላይ ያለው እና የኢትዮጵያን ሕዝብ እየመራው ነው የሚለው የኢህአዴግ ወያኔ መንግስት ወደ ስልጣን ብቅ ካለበት ቀን ጀምሮ ሀገርን በመሸጥ ፣ በመገንጠል እና ሕዝብንም በዘር፣በብሔር፣ በጓሳ እና በቋንቋ በመከፋፈል ኢትዮጵያዊነትን የማጥፋት ርኩስ ተግባሩን እየገፋ ባለበት በእነዚህ አስርት አመታት ውስጥ ግን ኢትዮጵያውነት ኩራት መሆኑ ቀርቶ ውርደድ፣ ስደት መከራ እና ስቃይ መሆኑ እየጨመረ መጥቶል::

በእነዚህ አመታቶች ኢትዮጵያውነት የሀገር ስሜትና ወኔ ከህዝብ ዘንድ የጠፋበት እና ሕዝቡም እንደ ዜጋ መኖር በማይችልበት ሁኔታ ውስጥ ይገኛል ::በእነዚህ አመታቶች ውስጥ ለሕዝቡና ለኢትዮጲያዊነት ግድ በሌለው በዚህ ሰይጣናዊ እና አረመናዊ አገዛዝ ስር ብዙዎች ታስረዋል፣ ተገለዋል፣ ወላጆች እንዳይወልዱ መካን ተደርገዋል ሕዝቦች ቄያቸውን መሬታቸውንና ሀብት ንብረታቸውን በግፍ ተነጥቀው ለስደት እና ለመከራ ተዳርገዋል፣እናቶች ልጆቻቸው በግፍ ተገሎባቸዋል ይህ ነው የማይባል ብዙ ብዙ ግፍ በሕዝብ ላይ ተፈጽሞል :: ከእለት ወደ እለትም ሕዝባችን በሀገሩ ላይ መኖር በማይችልበት አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል::

ከሰሞኑ እንኮን እንዳየነው የወያኔ ስርአት ባመጠው በዘር እና በጎሳ ፖለቲካ ችግር ምክንያት ድብድባ እና ስቃይ ደርሶባቸው ከምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ዳኖ ወረዳ የተፈናቀሉ ገበሬዎች አዲስ አበባ ገቡ የሚለወን ዜና ከድህረ ገጹች ላይ ባነበብኩኝ ጊዜ ውስጤ ምን ያክል በሀዘን እንደተሞላ ልነግራቸው አልችልም እነዚህ ወገኖቻችን አዲስ አበባ በመግባት በአካባቢው የደረሰባቸውን ችግር በጊዜው ሀገሪቷን እያስተዳደርኩኝ ነው ለሚለው ለወያኔ ባለስልጣኖች ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት በመጎዝ ቢያስታውቁም በተገቢው መንገድ አቤቱታቸው ሊሰማ ባለመቻሉ እ ነዚህ ተፈናቃዩቹ “ብንመለስ ሊገድሉን ይችላሉ” በማለት ወደ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ጽ/ቤት በመሂድ ‹‹ፍትህ እንድናገኝ ለኢትዩጵያ ህዝብ ሰቆቃችንን አሰሙልን››በማለት የተማጽኖ ድምጻቸውን ሲያሰሙ ተመለክተናል፡፡

ዛሬ በየቤቱ በዚህ ጨቋኝ ስርዓት የማይማረር የለም:: የሕዝብም የመኖር ሁኔታ ጥያቄ ውስጥ ነው :: የወያኔ ኢህአዲግ መንግስት ለሕዝብ ምንም የጠቀመው ነገር የለም:: ይልቁንስ በሀገር ሀብት እና ንብረት በማን አለብኝነት እንደፈለጋቸው ሲፈነጥዙ ኖረዋል አሁንም እየኖሩ ይገኛሉ:: መንግስታት ሀገርን ሊያስተዳድሩ እና ሊመሩ ወደ ስልጣን ሲመጡ የሀገርን ሉአላዊነትን እና የሕዝብን ጥቅም ለማስከበር ነበር በተቃራኔው ግን እንደ አለመታደል ሆኖ ሀገራችን ኢትዮጵያ ሕዝቦቿም ለዚህ ባለመታደል መብታቸውን እና ነጻነታቸውን ለመስከበር እንደ ሰው መኖር በሚችሉበት ሁኔታ በነጻነት ለመኖር በመፈለግ በየቀኑ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሕዝቦች ሀገራቸውን በመልቀቅ ወደተለያዩ ሀገሮች ለስደት ይዳረጋሉ :: በብዛት ወደየ ሃረብ ሀገሩ የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ዜጎቻችን ለተለያየ እንግልት መከራ እና ስቃይ እንዲሁም ለሞት የሚዳረጉ ሲሆን በየቀኑ የብዙዎቹ ህይወት እንደዋዛ ያልፋል::

ነገር ግን ሕዝባችን በየቦታው እና በየአረብ ሀገሩ አሰቃቂ ድብደባ ግፍ እና ግድያ ሲፈጸምበት ሀገርን እየመራው ነው ሕዝብንም እያስተዳደርኩኝ ነው የሚለው የወያኔ ኢህአዴግ መንግስት አንድም ቀን የዚህ ሕዝብ መከራ እና ችግር ግርፋት ሰቃይ እና ሞቱ ግድ ሲለው እና ለሕዝቡ አለኝታነቱ ሲቆም አይተን አናውቅም::ስለዚህ የኢህአዲግ መንግስት ለኢትዮጵያም ለኢትትዮጵያ ሕዝብም እስከ አሁንም ምንም የጠቀመው ነገር የለም አሁንም ወደፊትም አይጠቅምም ::ስለዚህ ማንኛችንም ኢትዮጵያኖች ከወያኔ መንግስት ምንም ነገር ልንጠብቅ አይገባም ባይ ነኝ ነገር ግን መብታችንን እና ጥቅማችንን የሚያስከብርልንን መንግስት ለመፍጠር በመነሳት ለወያኔ ኢህአዲግ መንግስት ግን ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውነትን ሊወክል እንደማይችል ልንነግረው ይገባል ባይ ነኝ:: ለሀገር እና ለሕዝብ ጥቅም ቆሚያለው የሚል መንግስት የሀገርን ሉአላዊነት ሲያስከብር የሕዝብን ደህንነት እና ጥቅም ሲያስከብር ብቻ ነው እንደ መንግስት በሕዝብ ዘንድ ሊታይ የሚችለው በማለት ጹሁፌን ላጠቃል::

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!

ያልታሰረው ማን ነው?? ከአንተነህ መርዕድ

$
0
0

ሰሞኑን አንድ ኢትዮጵያዊ በቶሮንቶ የህሊና እስረኞችን ለመዘከር በግሉ አዳራሽ ተከራይቶ የአንዱዓለም አራጌን “ያልተሄደበት መንገድ” የሚለውን መጽሃፍ ለሽያጭ በአቀረበበት ቦታ ተገኝቼ ነበር። በዚህ አዳራሽ አንዱዓለምን፣ እስክንድርን፣ ርዕዮትን …ወዘተ ለመዘክር ብለው የተሰባሰቡ ሰዎች ብዛት ስመለከት “በእውነቱ እስረኞች እኛ ነን ወይስ እነ ዓንዱአለም?” የሚል ጥያቄ ጫረብኝ። አገርን ያህል ትልቅ ነገር ከራሳችን የፖለቲካና የግል ጠባብ ፍላጎት ዙርያ ቀንበበን ልንከተው ስንቸገርና አልሆንልን ሲል ደግሞ እርስ በርሳችን ስንጎነታተል አሁን አለንበት የመከራ ዘመን እንድንቆይ በራሳችን የፈረድን መሆኑ ግልጽ ይሆናል።

ትንሹን ህይወታቸውንና ጠባቡን የግል ፍላጎታቸውን በትልቁ ለሚያይዋት ኢትዮጵያ የሰውትን ወንድሞቻችንን ልናስታውስ በሚደረግ እንቅስቃሴ ሁሉ ብዙዎቻችን በተረባረብንና የነሱን ከባድ መስዋዕት በትንሽ በትንሹ በተጋራናቸው ነበር። እውነቱ ግን ያ አይደለም። ለብዙዎች የእንቅስቃሴያችን ማዕከል ሁሉ “እኔ” ስለሆነ ከዚያ የተለየን ማውገዝ፣ ማደናቀፍ፣ አለመተባበር…ተግባራችን የሆነ ይመስላል።
አንዱዓለም እንዳለው ከዚህ በፊት ያልተሄደበትን የመቻቻልና የመከባበር መንገድ መጀመር የጊዜው ጠቃሚ እርምጃ ነው። ይህ ሁኔታ መጽሃፍ ቅዱስ ላይ የዮሃንስ ወንጌል ምዕራፍ 8 ቁጥር3 እስከ 11 “ጻፎችና ፈሪሳውያንም በምንዝር የተያዘች ሴት ወደ እርሱ አመጡ በመካከልም እርስዋን አቁመው መምህር ሆይ ይች ሴት ስታመነዝር ተገኝታ ተያዘች። ሙሴ እንደነዚህ ያሉትን እንዲወገሩ በህግ አዘዘን። አንተስ ስለእሷ ምን ትላለህ? አሉት።….ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በደንጋይ ይውገራት አላቸው።…እነሱ ይህንን ሲሰሙ ህሊናቸው ወቀሳቸውና ከሽማግሌዎች ጀምረው እስከ ኋለኞች አንድ አንድ እያሉ ወጡ” ይላል። ከኛም መካከል ህሊናው የሚወቅሰው ካለ ከተሳሳተ ድርጊቱ መቆጠብ አለበት። በዚሁ መጽሃፍ ቅዱስ የሉቃስ ወንጌል ላይም “በወንድምህ ዐይን ያለውን ጉድፍ ስለምን ታያለህ፤ በራስህ ዐይን ግን ያለውን ምሰሶ ለምን አትመለከትም?” ሲል ይደግመዋል። እያንዳንዳችን የምንከተለው መንገድ ትክክል ሊመስለን ይችላል። የሌሎችን ሆነ የእኛን ትክክለኝነት የሚዳኘው ተግባራችንና ጊዜ ነው። እስከዚያው ግን መከባበርና መተባበርን የመሰለ ትልቅ ነገር የለም።

ፖለቲከኞች፣ የሃይማኖት ሰዎች ሆነ ተራው ግለሰብ የራሳቸውን ሳይሆን በሌሎች ሰዎች ስህተት ላይ ብቻ ማተኮር ሲጀምሩ የውድቀታቸው መነሻ ይሆናል። ማንም ሰው ሲሠራ ሊሳሳት ይችላል። መጥፎው ነገር ከስህተት አለመማር ነው። ስህተቱን በጸጋ የሚቀበልና የሚያርም ትልቅ ነው። በእስልምና እምነትም ሃዲስ ላይ (በትክክል መጥቀስ ባልችል ይቅርታ ይደረግልኝ) እንዲህ ይላል “የማያውቅ ሆኖ የማያውቅ መሆኑን ማወቅ የማይፈልግ ቂል ስለሆነ ሽሸው። የማያውቅ ሆኖ አለማወቁን የሚያውቅ ከሆነ ልጅ ነውና አስተምረው። የሚያውቅ ሆኖ አዋቂ መሆኑን የማያውቅ ከሆነ ቀስቅሰው፤ ተኝቷልና። አዋቂ ሆኖ አዋቂነቱን የሚያውቅ ከሆነ ጥበበኛ ነውና ተከተለው” የብዙዎቻችን ባህሪ ባንዱ ሁሉ የሚካተት ነውና ቦታችንን ማወቅና እርምጃችንን ማስተካከል የተገባ ነው። ስለሆነም የታሰሩ ወንድምና እህቶቻችን የተሸከሙት እዳ ከግላችንና ከቡድናችን ፍላጎት በላይ አገራዊ ስለሆነ ከመጎነታተል፣ ከመከፋፈል ወጥተን አገራዊ ስፋት ባለው አላማ ዙርያ በጋራ መቆም ይኖርብናል።
ወደ ተነሳሁበት ርዕስ ልመለስና “ኢትዮጵያ የብሄረሰቦች እስር ቤት ናት” የሚለው ለትናንቶቹና ለዛሬዎቹ ጠባቦች መንደርደርያ ማዕከላዊ ሃሳብ ቢሆንም ደጋግመው እንደሚናገሩት ይህንን ብሂል በሃቅ ለብሄር ብሄረሰብ ነፃነት አልተጠቀሙበትም። ያ ቢሆን ምንኛ በታደልን። ድርጊታቸው ግን ተቃራኒ በመሆኑ ኢትዮጵያን ወደ ገሃነምነት ቀይረዋታል።

በአምደጽዮን፣ በፋሲለደስ፣ በቴዎድሮስ፣ በዮሃንስ፣በምኒልክ፣ በሃይለስላሴ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ማበብ ነበረበት ብሎ የሚያስብ አእምሮ ቅንነት አለው ብለን አንጠብቅም። እነዚህ ነገስታት ግዛታቸውን ለማስፋት፣ በስልጣናቸው ላይ ለመቆየት ባደረጉት እንቅስቃሴ ጭካኔ የተሞላበትን መንገድ መሄዳቸው ግልጽ ነው። በዴሞክራሲያዊ ስርዓት እናስተዳድራለን ብለውም አያውቁምና የሚጠብቅም አልነበረም። ዳኝነታቸው ርህራሄና ፈሪሃ እግዜብሄር ያለበት እንዲሆን ሁሌ ባያከብሩትም ይናገራሉ፤ ህዝቡም ይጠብቃል።

ዛሬ በትናንት ታሪክ ታስረን፣ ለዚያ የከፋ ድርጊት ከመካከላችን ተጠያቂ ፍለጋ ስንኳትንና አጽም ለማውጣት መቃብር ስንቆፍር የሁላችን መቀበርያ አዳዲስ መቃብር እየተዘጋጀልን መሆኑን ዘንግተናል። በተለይም በዴሞክራሲ ስም እየማሉ የገዙን ሁለቱ ስርዓቶች ማለትም ደርግና ወያኔ ካለፉት ነገሥታት በባሰና በዘገነነ ሁኔታ ጨካኞች ናቸው። አገሪቱንም ወደ ሙሉ እስር ቤትነት የቀየሯት እነዚህ አምባገነኖች ያለፉትን አገዛዞች በኮነኑበት አንደበት የራሳቸውን ትልቅነት ከመስበክ ወደ ኋላ አላሉም። በነዚህ አገዛዞች “ኢትዮጵያ የዜጎች ሁሉ እስር ቤት ናት” የሚለው ከፀሃይ የደመቀ ዕውነት ነው።
ይህን ዓለም ያወቀውን እውነት በመካድ የትናንቶቹ አምባገነኖች መንግስቱ ኃይለማርያምና ፍቅረስላሴ ወግደረስ የነሱ አገዛዝ ፍትህ የሰፈነበት፣ ዴሞክራሲ የሞላበት የሚያስመስል ስንክሳራቸውን አሳትመው እንደጲላጦስ እጃቸውን ሊታጠቡ ይዳዳቸዋል። ፍቅረስላሴ “እኛና አብዮቱ”ባለው መጽሃፉ ቢያንስ ለታሪክና ለህዝብ ክብር ትንሽ የቅንንነት ጥፍጣፊ እንኳ ጨምሮበት ‘ሰርተን ያለፍነው ስህተት ይህ ነበር፣መጪው ትውልድ ከእኛ ስህተት ተምሮ መልካም አገር መገንባት አለበት’ የሚል እውነት በመጠኑም ይዞ ይቀርባል ተብሎ ሲጠበቅ ለብቻቸው ያዝዟቸው በነበሩት ሠርቶ አደር ጋዜጣ፣አዲስ ዘመን፣ የዛሬይቱ፣ ሄራልድ፣ ሬድዮና ቴሌቪዥን ላይ ሲያደነቁሩን የኖሩትን ፕሮፓጋንዳ ሃያ ሶስት ዓመታት ሲያመነዥከው ቆይቶ ለህትመት ሲያበቃ የህዝቡንም የማስታወስ ችሎታ መናቁን አሳይቷል። ፍቅረስላሴ በእስር ባሳለፈው ሃያ ዓመታት ወደ ኋላ በትዝታ መለስ ብሎ የሄዱበትን መንገድ ሁሉ በመቃኘት ወደ እውነቱ ቀርቦ መገኘት ሲገባው ሲታሰር ተኝቶ ሲፈታ የነቃ ይመስል። የኢትዮጵያ ህዝብ ቀድሞ ያለፈበትን የመከራ ዘመን ሆነ አሁን እየደረሰ ያለበትን ጭቆና ዳግም እንዳይመለሱ በመታገል ላይ እያለ ፍቅረስላሴ ባንኖ በመንቃት ድሮ የጻፈውም ሜሟር እንዳለ ይዘምርልናል። “በማይጨው ጊዜ የደነቆረ ስለማይጨው ሲተርክ ይኖራል” እንዲሉ ስልጣን ሲለቁ እንደደነቆረና ከዚያ ወዲህ የኢትዮጵያ ህዝብ በምን አስተሳሰብ ላይ እንዳለ ለመገንዘብ ያልታደለ መሆኑ እንድናውቅ ያደርጋል።

ፍቅረስላሴ አሁን ድረስ የሚያመልክበትና በፍርሃት የሚያሸረግድለት መንግስቱ ኃይለማርያም ብቸኛ አላማው የሆነውን የስልጣን ጥማቱን ለማርካት የህዝቡን ለጋ ወጣቶች ብቻ ሳይሆን በእድሜና በልምድ መከበር የሚኖርባቸውን አዛውንት ኢትዮጵያውያንን፣ ጓደኞቹን ሳይቀር ተራ በተራ ሲያርዳቸው ቆሞ ሲንቀጠቀጥ፣ ማረጃ ሰይፍ ሲያቀብል እንዳልነበረ የነሱን የፍጅት ዘመን ከወያኔ ጋር እያነጻጸርን እንድንናፍቀው በተዘዋዋሪ ሊነግረን ይሞክራል።

የኢትዮጵያን ጠላቶች በየፈፋው ያርበደበዱት እነጄኔራል ታሪኩ ላይኔ፣አማን አንዶም፣ አምሃ ደስታ፣ ፋንታ በላይ ….ወዘት ዛሬ ተርፈው የተንሸዋረረ ታሪክ ሊነግሩ እንዳሉት በፍርሃት አልራዱም። አምባገነኑን አምባገነን ነህ እያሉ ነው የሞቱት። ታሪካቸውን ራሳቸው ባይናገሩም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ያውቀዋል። ሲያከብራቸውም ይኖራል። እነሱንና አገሪቱ የገደሉት የታሪክ ዝቃጮች ስለሥራቸው ምን ቀለም ቢቀባቡ ማንነታቸውን ሊደብቁ አይችሉም።

ለመሆኑ የአስራ ሰባት ዓመቱ የ“እኛና አብዮቱ” ውጤት ምን እንዳስገኘ ፍቅረስላሴ ይዘረዝረዋል? ህዝቡንና አገሪቱን ቀፍዶ አስሮ ለወያኔና ለሻዕብያ ያስረከበው ማን ነው? “ወርቅ ሲያነጥፉለት ፋንድያ የሚመርጥ” ብሎ መንግስቱ ሃይለማርያም የሰደበውን ህዝብ አንተም በተጠያቂነት ታቀርበው ይሆን?

አዎ ኢህአፓዎች፣ መኢሶኖች፣ወዝሊጎች፣ ማልሬዶች፣ ሻዕብያዎች፣ ወያኔዎች፣ ኦነጎች…..በዚች አገር ውድቀት አውቀውም ሆነ ሳያውቁ አስተዋጾ ማድረጋቸውን ለማወቅ ህዝቡ የፍቅረስላሴንና የጓደኞቹን ምስክርነት የሚፈልግ አይደለም። ምንም እንኳ ይህ ነበር የኛ ድርሻ ለማለት ድፍረቱን ባያገኙትም ህዝብና ታሪክ የሁሉንም አስተዋፆ አይረሳውም።

ቀበሌዎችን፣ የጦር ካምፖችን፣ መኖርያ ቤቶችን፣ ትምህርት ቤቶችን ሁሉ ወደ እስር ቤትነት የቀየረ፣ ወላጆች የልጆቻቸውን አስከሬን ለመቀበል የተገደሉበትን ጥይት ዋጋ ያስከፈለ፣ አልቅሰው እርም እንዳያወጡ የከለከለ፣ አዛውንቱን ኃይለስላሴን ያለፍርድ ገድሎ መቃብራቸው ላይ መፀዳጃ ቤት የሰራ…ወዘተ ይህን ሁሉ ያደረገ የደርግ ስርዓትና መሪዎቹ የሌሎችን ያነሰ ስህተት የሃጢያታቸው መጠራረጊያ ፎጣ ሊያደርጓቸው የሚያስችል የሞራል ብቃት የላቸውም።

የመሬት አዋጅን እንደትልቅ ድል ደጋግሞ ማንሳቱም የሚገርም ነው። ብዙ ኢትዮጵያውያን የተዋደቁለ የመሬት ጥያቄ በደርግ ሆነ በወያኔ አልተመለሰም። አዋጁ መሬትን ከመሬት ከበርቴዎች ነጥቆ ገበሬውንና መሬቱን የአምባገነኖች ንብረት ነው ያደረገው። ወያኔዎችም ካባታቸው ደርግ ደህና አድርገው ተምረዋልና ኢትዮጵያዊ የመሬት ባለቤት የሚሆነው “በኢህአዴግ ሬሳ ላይ ነው” ሲል መለስ ዜናዊ ደምድሞታል።

ከገበሬው የወጣን ነን የሚሉት የደርግ አባላት ሆኑ ለገበሬው ቆሜያለሁ የሚሉት ወያኔዎች በካድሬዎቻቸው አማካይነት ንብረቱና ራሱን ገበሬውን የራሳቸው የግል እቃ፣ በቤቱም ውስጥ እስረኛ አድርገውታል። በህብረት እንዲያርስ የተገደደውና በችጋር የተጠበሰው የአርሲ ገበሬ “በናንተ ህብረት እርሻ ያተረፍነው በርሃብና በተባይ ማለቅን ነው” ብለው ብልቃት ሙሉ ቅማል ለደርግ ባለስልጣን ማሳየታቸውን በወቅቱ በቦታው የነበርነው ጋዜጠኞች ተመልክተናል። ይህን እውነት በአብዛኛው አገሪቱ ለሥራ በተዘዋወርሁባቸው ወቅት ባይኔ አይቻለሁ።

ደርግ የጀመረውን የአፈና መንገድ ወያኔዎች በረቀቀና በሰላ መልኩ ተጠቅመውበታል። የመሰረት ደንጋዩን ያስቀመጡላቸው ግን እነፍቅረስላሴ ናቸው። ወያኔ አገርን በመበተን ከደርግ የከፋ ቢሆንም የደርግን ዘመን የሚናፍቁ ካሉ የዚያ ስርዓት ተዋናዮችና ተጠቃሚዎች የነበሩ ብቻ ናቸው። የኢትዮጵያ ህዝብ ከሁለቱም አምባገነኖች የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ይገባዋል።

ወደ ተነሳሁበት የእስር ጉዳይ ልመለስና በደርግ ሆነ በወያኔ መታሰርን በተደጋጋሚ ቀምሼዋለሁ። ለምን ታሰርሁ ብዬ አልቆጭም። ከህዝቡ መከራ የተጋራሁበት እውነተኛ የህይወቴ ምዕራፍ ስለነበር ባሰብሁት ቁጥር መጠነኛ የመንፈስ እርካታ ይሰማኛል። ሁለቱም ስርዓቶች በጣም ፈሪዎች ስለሆኑ በጣም ጨካኞች ናቸው። የተማሩትንና ለስልጣን ተቀናቃኝ ይሆናሉ ያሉትን ማሰርና በግፍ መግደላቸው እንዳለ ሆኖ በሁለቱም ስርዓቶች የሰባና የሰማንያ ዓመት በጤና የደከሙ ከፊሎችም ዐይናቸው የታወሩ አዛውንቶች ያለፍርድ እስር ቤት ቀስ እያሉ በሞት ሲያሸልቡ አይቻለሁ። መደገፍያ ከዘራቸውን ማንሳት የማይችሉትን አዛውንትና ክፉና ደግ የማያውቁ ህፃናትን የስርዓታቸው ተቀናቃኝ አድርገው የሚባንኑ አምባገነኖች ናቸው ሁለቱም።

ያ ሁሉ መጨፍጨፍ፣ ያ ሁሉ እስር የደርግን ስርዓት ከመፈራረስ፣ መንግስቱን ከመፈርጠጥ፣ ጓደኞቹን እነፍቅረስላሴንና ለገሰን እንደበግ ከመጎተት አላዳናቸውም። የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ወያኔዎች ግድያውን፣ እስሩን ካስተማራቸው ከደርግ በባሰ ሰልጥነው ውድቀቱንም እየወረሱት ነው። የተፈጥሮአቸው እድገት ጣርያ (ክላይማክስ)ላይ ደርሰው ቁልቁለቱን ጀምረዋል። የገነቡት ሁሉ እየተናደ እንዳይቀብራቸው ራስን የማዳን ጥድፊያ ላይ ተጠምደዋል። ይህ መንፈራገጥ ግን የበለጠ ሚዛናቸውን እያሳታቸው ቁልቁል ይወረውራቸዋል። ሲወድቁ በሚያደርጉት መንፈራገጥ ብዙ ጉዳት ማድረሳቸው ግን የተጠበቀ ነው። የወያኔ የአጥቂነት ጊዜ አልፎበት አሁን በመከላከል ላይ ተጠምዷል። ጅኒው ከጠርሙሱ ወጥቷልና መልሶ የመክተት አስማት የሚሠራ አልሆነም።

ታላቁ ሩስያዊ ደራሲ፣ የታሪክ ምሁርና የሶብየትን አምባገነንነት አጥብቆ ይተች የነበረው አሌክሳንደር ኢሳየቪች ሶልዝሄንጺን የሩሲያውያንን መከራ ለዓለም በሚገባ ካሳወቀባቸው በርካታ ሥራዎቹ ዘ ጉላግ አርፒላጎ የዘረዘራቸውን ስናነብ ደርግና ወያኔዎች ያንን እያነበቡ የፈጸሙ ይመስለናል። በአንደኛው ጽሁፉ “እኛ በሚሊዪን የንምቆጠር ሩስያውያን ሴቶችና ወንዶች ከቀን ቀን፣ ከዓመት ዓመት ራሳችንን ደፍተን ወደ እስር የምንጎተትበት ምክንያት ይህ ነው። የማስጠንቀቂያ ደወል አናጮህም። በጎዳናዎች ተቃውሟችንን አናሰማም። እንዲያውም በተቃራኒው በጎዳና ላይ በጓደኞቻችን ፊት ስንነዳ እኛ ግዞተኞች ምንም እንዳልተፈጸመብን ፊታችንን ቅጭም አድርገን አንገታችንን ደፍተን፤ እነሱ የነገ ግዞተኞችም እኛን እንዳያዩ ዐይናቸውን መሬት ላይ ተክለው እንተላለፋለን። ህዝባችን ይህንን ድርጊት ሂደቱን ሳያዛባ ተግባራዊ ማድረጉን ተክኖበታል። በብዙ ማሰቃየት የታጀበው ምርመራ ሲጠናቀቅ እኛ ትንንሾቹ አሳዎች መረባቸው ውስጥ ዋኝተን እንገባላቸዋለን። …ባህሩን የሞላን ጥሩ አሳዎች፤ የአጥማጆቻችንን መንጠቆ ጉሮሮአችን ውስጥ ለማስገባት የምንሽቀዳደም፤ እኛን በመጎተት እንዳይደክሙ ወደ ላይ ቀዝፈን የምንቀርብላቸው…..” እያለ ለአምባገነኖች የመከራ ማገዶነት ምንም ሳይንፈራገጡ ወደ ማረጃው፣ ወደ እስሩ የሚሽቀዳደሙ ሩሲያውያንን የሸነቆጠበት አነጋገር እኔንም እንዳለንጋ መንፈሴን ይተለትለዋል።

በአሁኑ ሰዓት በመደበኛ እስር ቤቶች፣ በጦር ካምፖችና በድብቅ እስር ቤቶች የሚማቅቀውን ኢትዮጵያዊ ቁጥር ማወቅ ይከብዳል። በደፈናው እኛና ዓለም የሚያውቃቸው ደፋርና ለዴሞክራሲ ስርዓት ማበብ ከፍተኛ መስዋዕት በመክፈል ላይ ያሉትን አንዱዓለም አራጌ፣ እስክንድር ነጋ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ ውብሸት ታዬ፣ በቀለ ገርባ፣ አቡበከርና ጓደኞቹ ……እያልን ብንዘረዝር ቁጥራቸው የትየለሌ ነው።
እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው በአካል የተገደቡ እስረኞች ናቸው ብንልም በመንፈስ ልዕልና ያላቸው ንፁሃን ናቸው። በእኔ አስተያየት እነሱ ሳይሆኑ እኛ ቀሪው ኢትዮጵያውያን ነን እስረኞች እላለሁ። እስክንድር፣ አቡበከር፣ ውብሸት፣ ርዕዮትና አንዱዓለም በአካል ከታሰሩበት ወህኒ ዘልቀው በመንፈስ ነጻ መሆናቸውን አሳውቀውናል። ያሉበትን መከራ እንደ ኢምንት በመቁጠር የምንከፍለው ቀላል ነው እያሉ ምንም ለመክፈል ያልተዘጋጀነውን፣ ከዳር ቆመን በፍርሃት የምንርደውን ህሊናችን እንዲሞግተን በመተው ባለ እዳ አድርገውናል።

ርዕዮት፡ “በኢትዮጵያ ፍትህ ማጣትና ጭቆና የተንሰራፋ በመሆኑ ለህይወቴ አዳጋ ይኑረውም አይኑረው ለእውነት እቆማለሁ” ብላለች። ይብላኝ ለእኔና ለእናንተ ዳር ለቆምነው።
አንዱዓለም፡ “ያልተሄደበት መንገድ” በሚል ርዕስ ከእስር ቤት ጠባብ ክፍል በጻፈው መጽሃፉ “እስር የስቃይ ብቻ ቢሆንም ከነፃነትና ከዴሞክራሲ እጦት አይከብድምና በጸጋ መቀመል ነበረብኝ” ሲል የአካል ስቃይን ፈርተን ህሊናችንን ለአሰርነው አማራጩን ይነግረናል። ከዚያም አልፎ “ይህ ሁሉ የመከራ ሸክም የማን ነው? የታሳሪ ፖለቲከኞች ብቻ ወይስ የነፃነት ናፋቂ ኢትዮጵያውያን ሁሉ?” በማለት የፍትህና የነፃነት ናፍቆታችን አፋዊ በመሆኑ ህሊናችን እንዲወቅሰን ጥያቄውን ወረወረልን።

እስክንድር፡ ሰሞኑል ለልጁ (ርዕሱ ለልጁ ይሁን እንጂ መልዕክቱ ለእኛ ነው) ከእስር ቤት በፃፈው ደብዳቤ “በጣም ናፍቄሃለሁ። እናትህንም ጭምር። ስቃዩ አካላዊ ስቃይ ብቻ ነው የሚሆነው። የቤተሰባችን ስቃይ ለረጂም ጊዜ መከራ ከተሸከመው ህዝባችን ተስፋ ጋር የተቆራኘ ነው።ከዚህ የበለጠ ክብርም የለም።ስቃዩን ሁሉ በመቋቋም፣ የሚቻለውን ሁሉ ርቀት በመሄድ፣ማንኛውንም አቀበት በመውጣት፣የትኛውንም ባህር በማቋረጥ ነፃነት ላይ በመድረስ ጉዞአችንን ማጠናቀቅ አለብን። ከዚህ ያነሰ ትግል ህሊናን ማደህየት (ባዶ ማስቀረት)ነው” ሲል ጽናቱንና የምንሄድበትን እርቀት አመልክቶን “አምባገነንነት ፍርሃት የነገሠበት በመሆኑ መንግስታዊ ሽብር፣ እስራትና ማሰቃየት ዋነኛ ተግባሩ ነው። በዚህ መንገድ ግን ሁሉንም ህዝብ ማንበርከክ አይቻልም። ነገር ግን የተወሰኑ ሰዎችን የጥቃት ኢላማ በማድረግ ብዙውን ሰው በፍርሃት ማደንዘዝ ይችላሉ። በጥቁር ዓለም ጥንታዊ የመሆናችን የጋራ ኩራት ይህንን አስማት ለመጨረሻ ጊዜ እንድንሰብረው ያስገድደናል” ሲል በነሱ መታሰርና መሰቃየት ሩቅ ሆነን በፍርሃት ተሸብበን የታሰርነውን ሊፈታን ይታገላል።

ሌሎችም እስረኞች ደጋግመው በተለያዬ መልክ ያስተላለፉልን መልዕክት ይሄው ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ህዝብ በአጠቃላይ እስረኛ መሆኑ ቢታወቅም ውጭ ያለነው እንኳ በፍርሃት፣ በራስ ወዳድነት፣ በክፍፍል፣ በመከነና የትም ባላደረሰን የትናንት አስተሳሰብና ከዚያም አልፎ በስሜታዊነት እስረኛ ነን። አንዱዓለም፣ እስክንድርና ሌሎችም የሚሉን ‘አሳሪ ሳይኖራችሁ ራሳችሁን ያሰራችሁ ራሳችሁን ነፃ አውጡና ትልቅ አገራዊ ዓላማ ይዘን አገር ነፃ እናውጣ’ ነው የሚሉን።

የጽሁፌ ማጠቃለያው ሁላችንም እስረኞች ነን።በመጀመርያ ራሳችንን ነፃ እናውጣ። ከዚያ የታሰሩ ወንድሞቻችንን፣ እህቶቻችንንና አገራችንን ነፃ ማውጣት እንችላለን።
ግለሰብ ሆኖ በህሊናው፣ ድርጅት ሆኖ በአሰራሩ ነፃነት ከሌለው ለነፃነት ቆሜያለሁ ማለት ከአፋዊነት አይዘልም። እስከ አሁንም የሆነውና ያየነው ይህንኑ ነው። ራሳችን ለራሳችን የነፈግነውን ነፃነት ከአምባገነኖች በልመና አናገኝም።

ኢትዮጵያን እግዚአብሄር ይባርክ!
ጸሃፊውን በamerid2000@gmail.com ማግኘት ይቻላል

የነጻነት ደዉል በአዲስ አበባ፣ በአዋሳ እና በደሴ ተደዉሏል! –የሚሊዮኖች ድምጽ

$
0
0

የአንድነት ፓርቲ ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ የሚንቀሳቀስ ድርጅት ነው። በኢትዮጵያ የፌዴራልም ሆነ የክልል ባለስልጣናት የተለያዩ ሕጎችን ደንቦች ሊያወጡ ይችላሉ። ነገር ግን ሕገ መንግስቱ የሕጎች ሁሉ የበላይ ነው። በሕገ መንግስቱ የተቀመጡ መሰረታዊ የሕግ አንቀጾችን ማንኛዉም አካል ሊሽረው ወይንም ሊቀለብሰው አይችልም።

የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት አንቀጽ 30 ዜጎች ነፍጥ ሳይዙ የመሰባሰብ፣ ሕዝባዊ ሰላምዊ ሰልፎች የማድረግ፣ ፔትሽኖችን የማሰባሰብ ሙሉ መብት እንዳላቸው ይደነግጋል።

“Everyone shall have the freedom, in association with others, to peaceably assemble without arms, engage in public demonstration and the right to petition. Appropriate procedure may be enacted to ensure that public meetings and demonstrations do not disrupt public activities, or that such meetings and demonstrations do not violate public morals, peace and democratic rights.”

በአዲስ አበባ፣ በደሴና በአዋሳ ሰላማዊ ሰልፎች ይደረጋሉ። በሰልፉ የጥበቃ ኃይላት ያሰማሩ ዘንድ ለባለስልጣናት አስፈላጊዉ የማሳወቅ ደብዳቤ ተልኳል። በታሰበው ቀንና ቦታ ሌሎች እንቅስቃሴዎች ካሉና በቂ የጥበቃ ኃይል ማሰማራት ባለስልጣናት ካልቻሉ፣ ቀኑ እንዲራዘም ወይንም የሰልፉ ቦታ እንዲቀየር ሊጠይቁ ይችላሉ። ከዚያ ዉጭ ሰልፎችን የመፈቀድም ሆነ የመከልከል መብት ባለስልጣናት የላቸውም። ይሄ መታወቅ አለበት። ከከለከሉ ወይንም መፍቀድ አለብን ካሉ፣ በቀጥታ የአገሪቷን ሕግ ያፈርሳሉ ማለት ነው። ሕገ ወጥ የሚሆኑት እነርሱ ናቸው ማለት ነው።

ሰልፍ ማድረግ አመጽ አይደለም። የአንድነት ፓርቲ፣ ሰማያዊ ላለፉት በርካታ ወራት የተለያዩ ሰልፎች አደርገዋል። በሰዉም ሆነ በንብረት ላይ አንድም ጉዳት አልደረሰም። ከፖሊሶች ጋር ምንም አይነት ግብግብ አልተፈጠረም። አንዲት ጠጠር አልተወረወረችም። ኢሕአዴጎች ይሄን ልብ ብለው ፣ እነርሱ ሌላው ሕግ ማክበር አለበት እንደሚሉት፣ ሕግን ማክበሩ ያዋጣቸዋል።

እንግዲህ ሁላችንም እንዘጋጅ፤ ዉስጥ ውስጡን ማጉረምረም ይብቃናል። እርስ በርስ ማንሾካሾክ ይበቃናል። ከሚሊዮኖች ጋር ሆነ ድምጻችንን በድፍረት፣ በአደባባይ እናሰማ። ፈርተን እና ተስፋ ቆርጠን በመደበቃችን፣ በመሸሻችንና ዝምታን በመምረጣችን፣ በሙስናና በመልካም አስተዳደር እጦት የተዘፈቁት ገዢዎቻችን ገዢዎቻ የደገፍናቸው እየመሰላቸው ነው። እንነሳ፣ እንቀሳቀስ። ሕገ መንግስቱ ይፈቅድልናል። ኢትዮጵያዊ የዜግነት ግዴታ አለብን።

እኛ ጥይት አንተኩስም ! ጠጠር እንወረወርም! ጥላቻን አንዘምርም። ክርስቲያን፣ ሙስሊም፣ ኦሮሞ፣ ትግሬም ፣አማራ፣ በብሄረሰቡ መታወቅ የማይፈልገው ቅልቅሉ..…ሁላችንም በዘር፣ በኃይማኖት ሳንከፋፈል፣ ሚሊዮኖች ሆነን ድምጻችንን እናሰማለን። በርግጠኝነት የሚሊዮኖችን ጥያቄ ሊንቅ የሚችል ማንም ኃይል አይኖርም።

እንግዲህ የነጻነት ደዉል በአዲስ አበባ፣ በአዋሳ እና በደሴ ተደዉሏል። ጥሪ ቀርቧል። ትኩረቱ ወደነዚህ ከተሞች !!!!!

በላስ ቬጋስ፣ በአትላንታ እና ዴንቨር የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን እነዚህ ሶስት ከተሞችን ስፖንሰር በማድረግ ድጋፋቸውን በመግለጻቸዉ ሊመሰገኑ ይገባል። ሌሎቻችንም ተደራጅተን ሶሊዳሪቲ በማሳየት የሚሊዮኖች አንዱ እንሁን !

እንበርታ ፣ እንጎብዝ ! ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !993754_546619252089680_666940779_n

የክህደት ኣቀበት አብረሃ ደስታ

$
0
0

እውነቱን ለመናገር በኢትዮጵያ ፖለቲካ ምክንያት እንደሰሞኑን በግኜ የማውቅ ኣይመስለኝም። ኣቤት ክህደታችን! እንዴት ተክነንበታልሳ ወገኖች! ረጋ ብላችሁ በጥሞና ኣንድታነቡኝ ብርታቱን ይስጣችሁ፥

1• በዛሬይቱ ኢትዮጵያችን ነባራዊ ሁኔታ ብሄር ማለት ምን ማለት እንደሆነ በትክክል የሚነግራችሁ ሰው ኣታገኙም። የብሄር ፖለቲካ ኣቀንቃኞቹ ራሳቸው የሚግባቡበት ወጥ የሆነ የብሄር ትርጉም እንኳን የላቸውም። ብሄር ለኣንዳንዱ በቋንቋ ነው የሚገለፀው፤ ለሌላው በዘርና ትውልድ ሃረግ ነው የሚገለፀው፤ ደግሞ ለሌላው በጂኦግራፊ ነው የሚገለፀው፤ የምርጫ ጉዳይ እንጂ ሌላ ምንም መስፈርት ኣይጠይቅም የሚሉም ኣሉ። ከየትም ይወለድ የትም፤ ማንኛውንም ቋንቋ ይናግር፤ የትም ይኑር ብሄሩ «የመረጠው» የህይወት ዘይቤ ነው የሚሉ የብሄር ፖለቲካ ኣራማጆችም ኣሉ። (ወደ ዝርዝሩ ኣልገባም፤ ጊዜና ቦታ ይፈልጋልና፤ ሆኖም በትርጉም ደረጃ እንኳን እንደማይግባቡ ኣስምረንበት እንለፍ።)

2• በብሄር ትርጉም የማይግባባ ፖለቲከኛ የብሄር ፖለቲካ ሲያራምድ ማየት በጣም የሚደንቅ ምፀት ነው። የብሄርን ትርጉም በቅጡ ሳናውቅ፤ ምናባዊ ብሄሮች ፈጠረን ስም ሰጠናቸው። ትግራይ፡ ኦሮሞ፡ ኣማራ፡ ሶማሌ፡ •••።

እስቲ ቆም እንበል እዚች ጋ። 30 ሰኮንድ።

ትግራይ የሚባል ብሄር በዛሬይቱ ኢትዮጵያችን ውስጥ ኣለ? ኣማራ የሚባል ብሄር ኣለ? ኦሮሞ የሚባል ብሄር ኣለ? •••? እስኪ ረጋ ብለን እናስበው ትግራዋይ የምንለው ማንን ነው? ኣማራ የምንለው ማንን ነው? ኦሮሞ የምንለው ማንን ነው?

በደንብ የማውቃትን ትግራይን እንደኣብነት ብንወስድ፤ የራያ ገበሬ ከሽረ/እንዳስላሴ ገበሬ በጣም በትንሹ ከሚቀራረብ ቋንቋቸው ውጪ በባህል፡ በዘር ሃረጋቸውና በታሪካቸው የማይገናኙ ፍፁም የተለያየ የየራሳቸው ኣመጣጥ ያላቸው ማህበረሰቦች ናቸው። ቋንቋውም ቢሆን ከሁለቱም ኣካባቢ ራንደምሊ ኣንዳንድ ገበሬዎችን ወስደን በ”ትግርኛ” ቋንቋቸው እንዲወያዩ ቢደረግ ምናልባትም ከግማሽ በላይ ላይግባቡ ይችላሉ። በብሄርተኞች ኣይን ግን ኣንድ ናቸው፤ ትግራዋይ። እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን ‘ኣንድ ናቸው’ ወይም ‘ትግራዋይ ናቸው’ መባላቸው ኣይደለም ችግሩ፤ ይህ ‘ኣንድነታቸው/ትግራዋይነታቸው’ ከሌላው የሚለያቸው “ልዩ ማነንታቸው/Identity” ነው መባሉ ነው ዋንኛ ችግሩ።

ኣማራውም በዚህ መልኩ ነው ኣማራ የተባለው። ኦሮሞውም በዚህ መልኩ ነው ኦሮሞ የተባለው። በራያና በሽረ ገበሬዎች ያለው ልዩነት እንዳለ ሆኖ “ኣንድ/ትግራዋይ ናቸው” ከተባለ፤ በወሎና በጎጃም ገበሬዎች ያለው ልዩነት እንዳለ ሆኖ “ኣንድ/ኣማራ” ናቸው ከተባለ፤ በሃረር በባሌና በወለጋ ገበሬዎች መሃከል ያለው ልዩነት እንዳለ ሆኖ “ኣንድ/ኦሮሞ” ናቸው ከተባለ፤ ••• ወዘተ፤ በትግራዋይ፡ ኦሮሞ፡ ኣማራና ሌሎቹም “ብሄሮች” ያለው ልዩነት እንዳለ ሆኖ “ኣንድ ብሄር/ ብሄረ-ኢትዮጵያዊ” የማይባሉበት ምክንያት ምንድን ነው??! የብሄር ፖለቲከኛው/ዋ መልስ ኣለህ/ሽ?

3• ከላይ ያነሳሁት ጥያቄ ሎጂካሊ ትክክል ሆኖ፤ ለብዙዎቻችን ስሜት የሚሰጥ እንዳልሆነ ኣስባለሁ። ምክንያቱም ለ23 ዓመታት የብሄር ፖለቲካ ተግተነዋልና፤ ትግራዋይ፡ ኣማራና ኦሮሞ የሚባሉ ብሄሮች እንደ «ነባራዊ እውነታ» ተቀብለናቸዋል። ከታች ያስቀመጥኩት የኣንድ ምሁር ንግግር እንደሚያሳየን፤ ብሄሩን በብሄር ደረጃ ብቻ ሳይሆን በካርታም ደረጃ ጭንቅላታችን ውስጥ ኣሰፍረነዋል። ትግራዋይ ማለት በትግራይ ክልል ያለ ኗሪ በሙሉ እንደሆነ ነው የሌላው ክልል ሰው የሚረዳው። በክልሉ ውስጥ በራሳቸው ማንነት ለመታወቅ የሚንገታገቱት ብቻ ናቸው ትግራዋይ ማለት እነሱን እንደማያካትት የሚያውቁት፤ በርግጥ በተቀዣበረ ስሜት ውስጥ ሆነን እኛም ያካባቢው ሰዎች በትግራዋይ ስም እየተደፈጠጡ ያሉ የራሳቸው የ”ብሄር” መለያ ያላቸው ማህበረሰቦች እንዳሉ እናውቃለን። ነገር ግን ፖለቲካዊም ይሁን ማህበራዊ ኣስተሳሰባችን የተቃኘው ትግራይ ኣንድ ናት በሚል ነው። ( “ትምክህተኞች ከኣንድ ፋብሪካ በወጣ ሳሙና ይመስሉናል” ተባሎ በኣንድ ወቅት ይሰራጭ የነበረ ፕሮፓጋንዳ፤ ከፕሮፓጋንዳነቱ ኣልፎ በፖሊሲ ደረጃ በክልሉ ውስጥ ያሉትን በሙሉ በመደፍጠጥ ኣንድ ለማድረግ እየተሞከረ ያ.ሁ.ነ.ያ. )

4. ታድያ በዚህ በተቀዣበረ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ብሄርተኝነትን ኣለቅጥ ለጥጠን እያቀነቀንን ህዝባችን መሃል እየፈጠርን ያለነውን ሁኔታ ሙልጭ ኣድርጎ መካድ ሁሉ ይቃጣናል። ዛሬ ከላይ በተጠቀሰው መልኩ የቀረበልንን የብሄር ትርጉምና ፖለቲካ ተቀብለን፤ ልዩነታችንን እያሰፋን የምንኖረው ሁላችንም ነን። እያንዳንዳችን ኣስተሳሰባችን ሁሉ በዘር ተቃኝቷል ማለት ይቻላል። “diversified” የሆንን ህዝብ እንደሆመሆናችን መጠን ድሮም እኛና እነሱ የሚል ክፍተት የነበረን ቢሆንም፤ ኣሁን ግን ክፍተቱ ህገመንግስታዊ ይዘትንና ድንበርን ተላብሷል፤ politicized ሆኗል።

ድህነት፡ ስራ ኣጥነት፡ የፍትህ እጦት፡ ዝርፊያና በስልጣን መባለግ ባንሰራፋባት ምድር፤ ኣቅመ ቢሱ ህዝብ ብሶቱን የሚወጣበት ብቸኛ መንገድ “scapegoating” ነው። ለዚህ ደግሞ ምቹ ሁኔታ የዘር ፖለቲካችን ፈጥሮልናል። ኣንዱ ፀሃፊ እንዳለው ‘The people may have felt greater anger but no institutions existed … Their rage exploded from time to time but could not be sustained. Discontent was often directed against ´rival ethnic group´ rather than at the government; and the government was happy to leave his people fighting among themselves.’

5. ትላንት ባህርዳር ያየነው ሁኔታ ወዳጄ Tamrat Tam Rat በትክክል እንዳስቀመጠው “[It] is only the tip of the Iceberg”። በኣንድ ወቅት (ኣፈሩን ድንጋይ ያርግለትና!) ኣቶ መለስ በኢቲቪ ለህዝብ ‘የፕላዝማ ሌክቸር ‘ ሲያደርግ እንዲህ ብሎን ነበር፥ “በፌዴራሊዝም ስርዓት ክልሎች (ለኔ ብሄሮች ከሚለው ቃል ጋር synonymous ነው) መዋቀራቸው፤ የብሄር እኩለነት ከማረጋገጥ ኣልፎ የኢኮኖሚ ፖለቲካና ማህበረሰባዊ ፉክክር በክልሎች መካከል እንዲኖር በር ይከፍታል፤ ጤናማ ፉክክር ደግሞ ለልማት ኣስፈላጊ ግብኣት ነው”። ለ23 ዓመት ከሰርቶ ማሳያነት ያልዘለለው የፌደራሊዝም መዋቅር፡ ለጤናማ ፉክክር የሚያስፈልጉት ምቹ ሁኔታዎችን ሳያዘጋጁለትና የታሪክ ጠባሳ እየፈቀፈቁ ማፎካከር የመጨረሻው ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ትላንት በባህርዳር ከታየው ክስተት መገመት ይቻላል።

6. ታድያ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፤ በክህደትና ቅጥፈት የተሞላ ምክንያት ሲደረደርልን ስናይ ያሳዝናልም ያበግናልም። ጩኸቴን ቀሙኝ እንደሚባለው ኣገራዊ ብሂል፤ ዘረኝነትን ህገመንግስታዊ ኣድርገዉ ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ ሌት ከቀን እየሰሩበት፤ ዘረኝነትን ኣወግዛለሁ እያሉ ቀድመውን ይጮኻሉ ጣታቸውን የሚቀስሩት በዘረኛ ኣመለካከት በክለው ያሳደጉት ትውልድ ላይ ሆነ።

ልብ ብላችሁ ከሆነ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብሄርተኝነትን ለማራገብ ባህርዳር ብዙ ነገር ተስርቶባታል። በከተማዋ የተከሰተው የባለፈው ኣመት ቃጠሎ፡ በኣደባባይ በተኩስ እሩምታ የተፈጁት ዜጎች፡ ኣማርኛ ተናጋሪ ዜጎች ከሌሎች ክልሎች መፈናቀላቸው፤ ዘንድሮም በክልሉ ኣመራር መሰደባቸው፤ ከሞረሽ ንቅናቄና የኢሳት ኣራጋቢነት ጋር ተደማምሮ በባህርዳር ይቅርና በሌላም ቦታ የኣማራ ብሄርተኝነትን ኣለቅጥ ኣራግቧል። የተከሰተው ነገር ቢያሳዝንም፤ ክስተቱ የሚገርም ኣይደለም፤ ሰው የዘራውን ነው የሚያጭደውና።

7. ኣንዳንድ ወገኖች ከቅንነት የመነጨ ሊሆን በሚችል መልኩ ጉዳዩን እግር ኳስ ከፈጠረው ስፖርታዊ ስሜታዊነት ጋር ኣያይዘውታል። እንደዚህ ዓይነት መግለጫ ለጊዜው ሁኔታዎችን ለማርገብ ኣስፈላጊ ቢሆንም ማዘናግያ እንዳይሆን ግን እሰጋለሁ። ዛሬ የክልል ቡድኖች ይቅርና የእግር ኳስ ክለቦች ሳይቀር የብሄር ቅርፅ ተላብሰዋል። እስኪ እውነቱን እንነጋገርና ትግርኛ ተናጋሪ ያልሆነ “ደደቢትን” የሚደግፍ ኣለ?? በቅርብ ጊዜ እዚህ ፌስቡክ ላይ ያየሁት ስሜት እንኳን “ደደቢት” የብሄር ፖለቲካ ማዳመቂያ ሲሆን ነበር። ማንዴላ ደቡብ ኣፍሪካውያንን ለማስተሳሰር የተጠቀመበት ቁልፍ ስፖርት እግር ኳስ ነበር። የኛ ኣለመታደል ደግሞ የብሄር ፖለቲካችንን የምናራግብባቸው በብሄር የሚጠሩና የታጠሩ ቡድኖችን እንቀፈቅፋለን።

እኔን እስከሚገባኝ ድረስ ኣብዛኛውን ጊዜ የእግር ኳስ ደጋፊ በስፖርታዊ ስሜት የሚጋጨው የቆየ ቁርሾ ሲኖረው ነው። ኣንድ የፌስቡክ ወዳጃችን በተሳሳተ ግንዛቤ ሊያንፀባርቅ እንደሞከረው፤ የኣርጀንቲናና የኢንግላንድ ብሄራዊ ቡድን ገና ሜዳ ሳይገቡ ብጥብጥ የሚጀምሩት በታሪካዊ ጠባሳቸው ምክንያት እንጂ ጊዜያዊ የስፖርት ስሜት የፈጠረው ሆኖ ኣይደለም። ትላንት የተመለከትነው ክስተትም የዘረኛ ፖሊሲያችን ውጤት መሆኑን ኣሌ የማይባል ነው። እንኳን ጎነታትለውኝ እንዲሁ ኣልቅሽ ኣልቕሽ ይለኛል እንዳለችው ኣንዷ ወዳጄ፤ ሰዎችን ፍፁም irrational የሚያደርግ የስፖርት ስሜት ተጨምሮበት ይቅርና እንዲሁም ዘረኛ ፖሊሲያችንና ስርዓት ዓልባው መንግስታችን እርስ በእርስ የሚያፋጁን ናቸው። ይህን መካድ ኣያስፈልግም፤ የሚያስፈልገው ዓይናችን እያየ ወደ ጥፋት ሳናመራ በፊት ቆም ብሎ ማሰብ ነው። ኣለበለዚያ ይህን የክህደት ኣቀበት የምንወጣው ኣይሆንም።

የምታምኑበትን ዛሬ ምረጡ፤ እኔና ቤቴ ግን ብሄረ-ኢትዮጵያን መርጠናል!
ዘረኝነትንና HIV/AIDSን በጋራ እንከላከል! Abraha Desta

ጎሠኛነትና ሽብርተኛነት (ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም)

$
0
0

March 29, 2014
የጎሠኛነት አጭር ትርጉም ዓለምን በራሱ ጠባብ ኢምንትነት የሚለካ ሰው ነው፤ ለኪው መለኪያው ነው፤ መለኪያውም ለኪው ነው፤ ጎሠኛነት የዘረኛነት የባሕርይ ልጅ ነው፤ ዘረኛነትም ሆነ ጎሠኛነት መሠረታቸው ድንቁርና ነው፤ የድንቁርናው ዓይነተኛ መገለጫ ‹‹ንጹሕ›› የሚለው ቃል ነው፤ ለዚህ ዋና ምስክር አድርጌ የማቀርበው አዶልፍ ሂትለርን ነው፤ ስለ‹‹አርያን ዘር›› ማንነትና ‹‹ንጹሕነት›› የሂትለር Mien Kampf የሚለውን መጽሐፍ ነው፤

የሰው ልጆች ባህል የሚባለው ሁሉ፣ ዛሬ የምናየው የሥነ ጥበብ፣ የሳይንስና የሳይንስ ጥበብ (ቴክኖሎጂ) ውጤት ሁሉ የአርያን ዘር የፈጠራ ውጤቶች ናቸው፤ … ‹ሰው› የሚባለውም እሱ ብቻ ነው።
የሂትለር ዘረኛነት የሰውን ልጅ ሁሉ ጉድጓድ ውስጥ ከተተው፤ አርያኑን ከንጹሕ የሰው ዘርነት ወደብቸኛ የሰው ዘርነት አሸጋገረው፤ ይህ ንጹሕ ድንቁርና ነው፤ የጎሠኞችም መነሻና መድረሻ፣ መንገዱም ይኸው ነው፤ በቅርቡ በፌስቡክ ላይ የታየው የቋንቋ ንጽሕና ክርክር የዚሁ የዘረኛነትና የጎሠኛነት ድንቁርና ቅጥያ ነው፤ ስለቋንቋዎች ባሕርይ ምንም ዓይነት እውቀት ሳይኖረው ቋንቋውን በማንገሥ እሱ ራሱ የነገሠ እየመሰለው ይደሰታል፤ ዓባይን ያላየ ምንጭ ያመሰግናል እንደሚባለው፤ ሙት ቋንቋ ካልሆነ በቀር ቋንቋ እንደሰው ልጅ ይጋባል፤ ይዋለዳል፤ ይለወጣል፤ በ1944 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ አገር ለማየት ከአዲስ አበባ የወጣሁት በጣልያን ትሬንታ ኳትሮ (34) ከባድ የዕቃ መጫኛ መኪና ላይ ተጭኜ ነው፤ ደብረ ማርቆስ ስገባ የሚናገሩት አይገባኝም ነበር፤ እኔ ከለመድሁት የሸዋ አማርኛ ጋር በጣም የተራራቀ ነበር፤ ወሎም ሄጄ አንደዚያው ነበር፤ ዛሬ ከስድሳ ዓመታት በኋላ ሌላ ነው፤ ዘረኛነትም ሆነ ጎሠኛነት የእውቀት፣ የመሻሻልና የእድገት ጸር ነው፤ ቆሞ-ቀር ነው፤ የአእምሮው እይታ አጠገቡ ካለው ወንዝና ጉብታ አያልፍም፤ ራሱ በፈጠረው ግርዶሽ መተናፈሻውንና መንቀሳቀሻውን ያጠበበ ነው፤ ተንጋሎ የተፋ ለራሱ ከፋ!

ዘረኛነትና ጎሠኛነት ከስጋትና ከፍርሃት የመነጨ ነው፤ አልጋው ፍርሃት፣ ትራሱ ስጋት ስለሆነ ጭንቀቱ እያባነነው እንቅልፍ አይወስደውም፤ ሲያቃዠው ያድራል፤ ለየት ያለና ትንሽም ሻል ያለ ነገር ሲያይ ሆን ብሎ እሱን ለማኮሰስ ወይም ለማሳነስ የመጣበት እየመሰለው ይደነግጣል፤ ስለዚህም ከሱ የተሻለውን በማጥፋት እሱ ወደትልቅነት የሚሸጋገር ይመስለዋል፤ ስለዚህም ዘረኛነትና ጎሠኛነት የሽብርተኛነት ምንጭ አንዱና ዋናው ምክንያት ከሱ የተለየውን ለማጥፋት ያለው ዝንባሌ ነው፤ ዘረኛነትና ጎሠኛነት ልብን በጥላቻ ያቆሽሻል፤ አእምሮን በክፋት እየመረዘ ያደነዝዛል፤ ሰውነትን ወደርኩስ መንፈስነት ይለውጣል፤ በባነነና በቃዠ ቁጥር የሚታየው ማታለል፣ ማጥፋት፣ ማፍረስ፣ ማዋረድ፣ ማጎሳቆልና ማደህየት ብቻ ነው፤ ለዘረኛና ለጎሠኛ እድገት ማለት የሌሎች መቀጨጭና መሞት ነው፤ ማደህየት፣ ማሰቃየት፣ ማቀጨጭና መግደል፣ ንብረትንም ማውደም የሽብርተኛነት መገለጫው ነው፤ የሽብርተኛነት ማለትም የዘረኛና የጎሠኛ የደነዘዘ አንጎል ጥፋትን እንደልማት፣ መቀጨጭን እንደእድገት ይመለከታል።

የዘረኛና የጎሠኛ ሽብርተኛነት የሚፈጥረው የደነዘዘ አንጎል ራስንም አይምርም፤ ለራሱ ልጆችና ቤተ-ዘመዶች አያስብም፤ በዙሪያው ያለውን ከሱ የተለየ ዓለም በሙሉ ወደአንጠርጦስ ሲከታቸው የሱም ወገኖች አብረው አንጦርጦስ ቢወርዱ ግድ የለውም! አይጸጽተውም! የተረፉት በሙታኑ መቃብር ላይ አሸብርቀው ሕያዋን መስለው ይታያሉ፤ እነሱ ባያዩትም የቆሙበት መቃብር ጠርንፎ ይዟቸዋል፤ ሕያዋኑና ሙታኑ ተቆራኝተዋል፤ ሙታኑ በተፈጥሮ ሕግ ይበሰብሳሉ፤ ሕያዋን የሚመስሉት በገዛ ሥራቸው ይበሰብሳሉ።

ዘረኛም ሆነ ጎሠኛ ሂሳቡ ምንጊዜም ጅምላ ነው፤ የዘረኛነትም ሆነ የጎሠኛነት የደነዘዘ አንጎል የሚያየው ጅምላ ነው፤ የጥፋቱ ሁሉ መሠረት የሚሆነውም ጅምላውን ደፍጥጦ አንድ አድርጎ ማየቱ ነው፤ ስለዚህም ጥፋቱ ጅምላ ነው፤ የሽብርተኛነት ሂሳብም ጅምላ ነው፤ ዘረኛም ሆነ ጎሠኛ ወይም ሽብርተኛ ራሱንም የሚያየው የጅምላ አካል አድርጎ እንጂ ራሱን የቻለ ነጻ ሰው አድርጎ አይደለም፤ ብቻውን አይደለም፤ ራሱን የሚያየው በጅምላ ከሌሎች መሰሎቹ ከሚላቸው ጋር ነው፤ ከአሱና ከመሰሎቹ የተለዩ ግለሰቦችንም ሲያይ በነጠላ ሳይሆን በጅምላ ነው፤ ለዚህ ምክንያት አለው፤ ራሱን በጅምላ የሚያየው ምሽጉ ውስጥ ሆኖ ከፍርሃት ነጻ ለመሆን ነው፤ ከእሱ የተለዩትንም በጅምላ የሚያየው ሁሉም ኢላማ ስለሆኑ ነው፤ ይህንን ሁነት በትክክል ለመገንዘብ አንድ ሀ ና ለ የሚባሉ ጎሣዎች አሉ እንበል፤ እነዚህ ጎሣዎች ውስጥ ሁ፣ ሂ፣ ሃ፣ ሄ፣ ህ፣ ሆ የሚባሉ አባሎች አሉ፤ ደግሞም ሉ፣ ሊ፣ ላ፣ ሌ፣ ል፣ ሎ የሚባሉ አባሎች አሉ፤ በትክክል ማሰብ የሚችል ሰው ሁሉ በአንዴ እንደሚገነዘበው ሉ የአንዳቸውንም የሌሎቹን የለ ጎሣ አባሎች ተግባር ሊፈጽም አይችልም፤ ሌሎቹም ሉ ን ሊሆኑ አይችሉም፤ የዘረኛና የጎሠኛ መሠረታዊ ድንቁርና እነዚህን ልዩነቶች ማየት ሳይችል በ‹ሀ› በ‹ለ› መሀከል ያለው ልዩነት በጣም ጎልቶ ይታየዋል፤ የድንቁርናውም፣ የጥላቸው፣ የፍርሃቱም፣ የክፋቱም፣ የተንኮሉም፣ የሽብርተኛነቱም መነሻ ይኸው ራሱን ማሰብ እንደሚችል ሰው ያለዘር ወይም ያለጎሣ ምርኩዝ መቆም የማይችል ዝልፍልፍ ደካማ መሆኑ ነው።

በድንቁርናው ከዝልፍልፍነትና ከደካማነት ያወጣኛል ብሎ የመረጠው መንገድ የጎሣ ምሽጉ ውስጥ ገብቶ በ‹ሀ›ና በ‹ለ› መሀከል ያለውን ልዩነት መስበክ ነው፤ በ‹ሀ› ውስጥ ያለ ጎሠኛ በ‹ሁ›ና በ‹ሂ› መሀከል ያለው ልዩነት፣ በ‹ለ› ውስጥ ላለ ጎሠኛም በ‹ሉ›ና በ‹ሊ› መሀከል ያለው ልየነት አይታየውም፤ ስለዚህም ድንቁርናው ከጥላቻውና ከክፋቱ ጋር እየተጋገዘ ወደቀላሉ የጅምላ ውሳኔ ይመራዋል፤ የሽብርተኛነትም ዋናው የድንቁርና ዘዴ ጥፋት በጅምላ ነው።

በዘረኞችና በጎሠኞች አመለካከት አንድም አህጉር ውስጥ የተለያዩ ሰዎች አይኖሩም ነበር፤ የትም ቦታ ቢሆን ሰዎች እንደሰዎች እየተገናኙ እየተፋቀሩ አይጋቡምና አይዋለዱም ነበር፤ በደቡብ አፍሪካ የነጮች ዘረኛ አገዛዝ ‹የክልሶች ክልል› አይፈጠርም ነበር፤ የሰው ልጅ ሰው ሲሆን የሚያደርገው ያስደንቃል፤ በአንድ የአውሮፓ አገር አንድ ወያኔን እንደክፉ በሽታ የሚጠላ ሰው አውቃለሁ፤ ሚስቱ ወያኔ ነች! በአፍሪካ አዳራሽ ይሠራ የነበረ አንድ ግብጻዊ አውቃለሁ፤ ሚስቱ የአሜሪካን ይሁዲ ነበረች! እስክንድር ነጋ ሚስቱ ትግሬ ነች፤ ርእዮት ዓለሙ ጓደኛዋ ትግሬ ነው፤ የሰው ልጅ ሰውነቱን የሚያሳየው ለራሱ አስቦ፣ ከጅምላው ወጣ ብሎ ለብቻው ሲቆም ነው፤ ስለዚህም ለሽብርተኛነት ተፈላጊ የሆነው ነገር ሁሉ ድንቁርናም ሆነ ጥላቻና ክፋት ከጅምላ አመለካከት ጋር ርእዮትና እስክንድር የለባቸውም ብሎ በእርግጠኛነት ለመናገር ይቻላል፤ ስለከሳሾቹ ሳይታለም የተፈታ ነው፤ እነሱው ይናገሩታል፤ ደፍረው የማይናገሩት አሸባሪነታቸውን ብቻ ነው።

Viewing all 1809 articles
Browse latest View live


<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>