Quantcast
Channel: Abugida Ethiopian American Amharic Web Page
Viewing all 1809 articles
Browse latest View live

ጥያቄዎቻችን በጆሮ ዳባ ልበስ ሊታለፉ አይገባም፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና ገዢው ፓርቲ ተገደው እንዲሰሙ የማድረግ ህዝባዊ ትግል ይቀጥላል!!

$
0
0

ከ33ቱ የፔቲሽን ፈራሚ ፓርቲዎች ባቀረብነው ጥያቄ ዙሪያ በቀጣይ የጋራ አቋም ላይ የተሰጠ መግለጫ

1.መግቢያ

በአዳማ ከተማ በ2005 ምርጫ የጊዜ ሠሌዳ ላይ ለማወያየት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሰበሰበን ወቅት ከተሣታፊ 66 ፓርቲዎች 41ዱ ከጊዜ ሠሌዳው በፊት የውድድር ሜዳውን መስተካከል በሚመለከቱ አበይት የምርጫ ጉዳዮች ልንወያይ ይገባል ከሚለው ኃሣብ በመነሣት እና በጉዳዩ ለመግፋት ፔቲሽን ፈረምን፡፡ በመቀጠልም በ29/02/05 ዓ.ም 18 ጥያቄዎችን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ /ኢብምቦ/፣ 13 ጥያቄዎችን ደግሞ በ08/04/05 ለክቡር ጠቅላይ ሚ/ር ጽ/ቤት፣ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈጉባኤ ጽ/ቤት አቅርበን ከቦርዱ ጥያቄአችሁ “ውሃ አያነሳም” በሚል ሙሉ በሙሉ ውድቅ መደረጉ በ10/04/05 ዓ.ም በቃል ሲገለጽልን፤ ከጠቅላይ ሚ/ር ጽ/ቤት፣ ከህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈጉባኤ ጽ/ቤት መልስ እየጠበቅን መሆኑን ገልጸን መልስ መጠባበቃችንን ቀጠልን፡፡

ነገር ግን ጥያቄዎቻችን ግልጽና የማያሻሙ ቢሆኑም ምርጫ ቦርድ “ጆሮ ዳባ ልበስ” በሚል ለጥያቄአችን መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ አፀደቅሁ ባለው የጊዜ ሠሌዳ መሠረት በገዢ ፓርቲ አይዞህ ባይነት ወደ ምርጫው አፈፃፀም ገብቷል፡፡

2. በሂደቱ የተገኙ የውሳኔ መነሻ ነጥቦች፤

2.1 ምርጫ ቦርድ ምላሽ የሰጠን የቦርዱ ሰብሳቢ በአዳማ ስብሰባ ላይ፣ የቦርዱ ጽ/ቤት ኃላፊ ደግሞ በ06/03/05 በአዲስ አበባ ቢሮአቸው፣ የጥያቄችንን አግባብነት አምነው የውይይት /ምክክር መድረክ ይዘጋጃል በማለት የሰጡትን መልስ በማጠፍ/ ቃላቸውን በመካድ መሆኑ፤

2.2 ከቦርዱ ምላሽና አካሄድ በመነሣት እኛም የቦርዱን “. . .የገዢው ፓርቲ ወገንተኝነትና ጉዳይ ፈፃሚነት . . .”፣ ምርጫውን ለማስኬድ እየገፋ ያለው “. . .ለኢህአዴ ብቻ በተመቻቸ ሜዳ . . .” መሆኑን፣ የሚሉ አቋሞቻችንን በገለጽንበት ሂደቱ ወደ ተግባር የተሸጋገረ መሆኑ፤

2.3 የቦርዱ ሰብሳቢ በ24/04/05 በኢቲቪ ቀርበው ጥያቄአችንን በማጣጣል . . .” ከ33ቱ ፈራሚዎች 5ቱ የምርጫ ውድድር ምልክት ወስደዋል. . .”፣ “. . . በርካቶች እየመጡ ጥያቄው እኛን አይመለከተንም እያሉን ነው . . .” ከማለት አልፈው “. . .የኮሚቴው አባለት ህጋዊ ውክልና ባይኖራቸውም በሆደ ሰፊነት አነጋግረናቸው ተማምነን ተለያይተናል . . .” ሲሉ ፍፁም የክህደትና የመከፋፈል ሴራ የተሞላ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ እንደ ሰብሳቢው መግለጫ 5ቱም ምልከት ቢወሰዱ እንኳ የ28ቱ ጥያቄ ውድቅ መደረግ ያለበት በጥያቄዎች ይዘት /ፋይዳ ወይስ በጠያቂዎች ቁጥር? በብዛትስ ቢሆን 28 ፓርቲዎች ጥያቄውን ለማቅረብ ትንሽ ቁጥር ነውን? የሚሉትን ጥያቄዎች አኑረን ይህ ምን ያመለክታል ወደሚለው ስንገባ፤

ሀ. ቦርዱ በጋራ ባቀረብናቸው ጥያቄዎች ጭንቅ ውስጥ መግባቱን ሲሆን ለዚህም ምላሹን በጽሁፍ ለመስጠት እንኳ ፈቃደኛ ያለመሆኑ ማሣያ ሲሆን፣ እንዲሁም በትብራችን የተደናገጠውን አይዞህ ባዩን ኢህአዴግ ለመከላከል እየተወራጨ መሆኑን ደግሞ የእነ ወ/ሮ የሺ፣ የአቶ ነጋ እና የፕ/ር መርጋ መግለጫዎች /ምላሾች በግልጽ የሚያሳይ መሆኑን፤

ለ. ለእኛ የአካባቢ ምርጫ በህዝቡ ውስጥ መሠረት ለመጣል ዘልቆ መድረሻ በመሆኑ ትኩረት ሰጥተን እየተንቀሳቀስን መሆናችንን በተደጋጋሚ ብንገልፅም፤ ከተሰጠን ምላሽ የምንረዳው ገዢው ፓርቲ /መንግሥት ጥያቄአችንን ከጥቅም ጋር በማገናኘት የተለየ ትርጉም በመስጠት ለማሳነስ እየጣረ መሆኑን፤

ሐ. እስካሁን ድረስ እንኳን ፔቲሽን ፈራሚዎች 5ቱ፤ ከኢህአዴግና አጋር ፓርቲዎች በቀር ጥያቄአችንን በይፋ /በአደባባይ የተቃውመ ወይም አይመለከተንም ያለ አለመኖሩ፣ ይልቁንም ሁሉም ማለት በሚቻልብት ሁኔታ ለጥያቄው በይፋ ድጋፍ የገለፁበት የጥያቄአችንን ትክለኛነትና ፖለቲካዊ አንደምታ በግልጽ የሚያሳይ መሆኑን፤

መ. ምርጫ ቦርድ በህግ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ነፃ፣ ፍትሀዊ፣ ተአማኒና አሳታፊ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማስፈጸም ገለልተኛ ያለመሆኑን፤ ነፃነቱ ፣ ፍላጎትም ሆነ ተነሣሽነት የሌለው መሆኑን፤

ሠ. በህዝብ ውስጥ ጠንካራ የለውጥ ፍላጎትና ይህንንም በምርጫ ለማምጣት ከፍተኛ ተነሳሽነት ቢታይም መራጩ ዜጋ በሚጭበረበር ወይም ድምፁ በሚነጠቅበት ምርጫ የተሰላቸ /ተሥፋ የቆረጠ/ ቢመስልም ከጉዳዩ አሳሳቢነትና ካለው አገራዊ ፋይዳ አኳያ ጥያቄአችንን በትኩረትና በንቃት እየተከታተለ መሆኑን፤
ረ. በጥያቄአችን የተነሱት ጉዳዮች በምርጫ ባለድርሻ አካላት በአጠቃላ እንዲታወቁ እየተደረገ መሆኑን እንዲሁም የሁሉንም ትኩረት በመሳብ የመወያያ ርዕስ መሆናቸውን፤ ወዘተ
በአጠቃላይ ከስብስቡ የጋራ ጥያቄ አቀራረብ የተገኘው ትምህርትም ሆነ የእስከዛሬው የጋራ አቋም /ጥረት ያሳደረው ተጽዕኖ እንዲሁም ሂደቱ ያስከተለው ፖለቲካዊ አንድምታ ይበል የሚያሰኝ /አበረታች/ ለቀጣይነቱም ለሁላችንም በዓላማና ተግባር እንድንተሳሰር ወቅታዊ አገራዊ ጥሪ የሚያስተላልፍ መሆኑን በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡

3. የጋራ አቋም

ጥያቄአችን ከመነሻው በምርጫ የመሣተፍ /ያለመሣተፍ ጉዳይ አልነበረም፤ ዛሬም አይደለም፡፡ ጥያቄአችን በጥቅሉ በህገ መንግስቱ መሠረት የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ተከብረው በዜጎች ይሁንታ /ድምጽ በሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር የህግ የበላይነት የተከበረበት፤ ትክክለኛ መድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት እንዲቻል ለነፃ፣ ፍትሃዊ፣ ተአማኒ፣ አሳታፊ፣ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የውድድር ሜዳው ይስተካከል ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ገዥው ፓርቲ የምርጫ ፖለቲካውን በቁጥጥሩ ሥር በማዋል ለቀጣይ 40 እና 50 ዓመታት በብቸኝነት አገሪቱን እገዛለሁ ለሚለው ዓላማዊ የኢብምቦን በጉዳይ ፈፃሚነት የሚጠቀምበትን ሥውር (አንዳንድ ጊዜም ግልጽ) እጁን እንዲያነሣ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተሻሻለው የምርጫ ህግ (አዋጅ ቁጥር 532/1999) አንቀጽ 7 በተሰጠው ሥልጣንና ተግባር መሠረት ኃላፊነቱን በገለልተኝነት መወጣቱን እንዲያረጋግጥ፣ በዚህም ነፃና ግልጽ የውይይት /ምክክር መድረክ በመፍጠር በዚህ ወሳኝ አገራዊ ጉዳይ ላይ በምርጫ ህጉ አንቀጽ 7(16) መሠረት እንደ ዋነኛ ባለድርሻ ያወያየን/ እንመካከርበት ነው፡፡

ስለዚህ በጥያቄአችን የተነሱ መሠረታዊ ጉዳዮች ባልተሟሉበት ማለትም ባለንበት ተጨባጭ እውነታ እንደ ፓርቲ ስለውድድር፣ እንደዜጋ ስለ መራጭነት ምዝገባ መነጋገር ለገዢው ፓርቲ የምርጫ ሴራ ይሁንታ መስጠት፣ አልፎም የምርጫ መርሆዎች እንዳይከበሩ በመተባበር በህገ መንግሥቱ መሠረት ዘላቂ የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚደረገውን ሠላማዊ ትግልና ጥረት ወደኋላ መጎተት ነው፡፡ ይህም የለውጥ ፍላጎታችንን፣ የዓላማ አንድነታችንን፣ ጽናታችንንና ቁርጠኝነታችንን በጥያቄ ውስጥ መክተት ነው፡፡

በመሆኑም ጥያቄአችን ባልተመለሰበት ስለምርጫ ተሣትፎ ማሰብ “ተጨፈኑ ላሞኛችሁን” መቀበል ከመሆኑ በተጨማሪ ጥያቄአችንን እነርሱ ወደ ፈለጉት ደረጃ ማውረድ /ማሳነስ ነው፡፡ ስለዚህ በጋራ ይዘን ለተነሳው ጥያቄ ምርጫ ቦርድም ሆነ ገዢው ፓርቲ /መንግሥት እስከዛሬ ጆሮአቸውን ቢደፍኑም ዛሬም ጊዜ እንዳላቸው በማስረዳት ተገደው እንዲሰሙ ለማድረግ ህዝባዊ ንቅናቄ በመፍጠርና ማስተባበር የተባበረና የተቀናጀ ትግላችንን እንቀጥላለን፡፡

ይህ ማለት መቼውንም እኛ ከምርጫው ሂደት ውጪ አይደለንም፤ ማንም ውጪ ሊያደርገን አይችልም፡፡ እንደዋነኛ የምርጫው ባለድርሻ በሂደቱ ላይ ያነሣነው ጥያቄ እስኪመለስ መራጩን ህዝብ ከጎናችን በማድረግ በጥያቄአችን ያነሣናቸው ጉዳዮች መፍትሔ እንዲያገኙ እኛም በተደጋጋሚ እንደገለጽነው ወደ ሥልጣን መሸጋገሪያው ብቸና መንገዳችንን አስከፍተን በተስተካከል የመወዳደሪያ ሜዳ የመጠቀም /በምርጫ የመሣተፍ/ መብታችንን ለማስከበር የሚደረግ ትግል ነው፡፡ ለዚህ ተፈፃሚነት በአጭር ጊዜ በጋራ ማከናወን ያለብን ተግባራት

1.ባሳለፍነው ውሳኔ መሠረት ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መውሰድ፤

2.እየተነጋገርንበት ላለው በትብብር የመሥራት ጉዳይ የተዘጋጀውን የመግባቢያ ሠነድ ረቂቅ በማጠናቀቅ አጽድቆ በሠነዱ መሠረት ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መግባት፤

3.የመግባቢያ ሠነድ ረቂቅ ላይ ከሚደረገው ውይይት ጎን ለጎን ይህንን የጋራ አቋማችንን ለጉዳዩ ዋነኛ ባለቤትና ባለድርሻ አካላት ማሳወቅ፤ በተለይም ከጉዳዩ ተጠቃሚና ቀጥተኛ ባለቤት (መራጩ ህዝብ) ጋር በህዝባዊ የውይይት መድረክ መገናኘትና መወያየት፤ ናቸው፡፡

ስለሆነም መላው የአገራችን ዜጎች እንዲሁም በኢትዮጵያ አሣታፊ የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ የበኩላቸውን ድርሻ የሚያበረክቱ አገራት፣ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ተቋማት ከጎናችን ሆነው ነፃ፣ ፍትሀዊ፣ አሣታፊ፣ ተአማኒና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ ጥያቄዎቻችን ምላሽ ያገኙ ዘንድ ተገቢውን ተጽዕኖ በማድረግ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪያችንን አበክረን እናቀርባለን፡፡

በተባበረ ሰላማዊ ሕዝባዊ ትግል ዲሞክራሲዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ከድርጅታችን ይልቅ ለአገራዊ የህዝብ ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት በትብብር እንሰራለን!!
ጥር 07/2005 ዓ.ም
አዲስ አበባ
በአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት የተሰራጨ


“ለመለስ አለቀስኩ ለምን ቢሉኝ..”ኤሎን ሳምሶን

$
0
0

ፓውል ኩልሆ ” The Alchemist” በሚለው መጽሀፉ እንዲህ ጻፈ ፦

ናርሲስ ተወዳዳሪ የሌለው ቆንጆ ወጣት ነበር አሉ፤ ከ ውበቱ ጋር ፍቅር ስለያዘው በእየለቱ ወደ አንድ ሀይቅ እየሄደ መልኩን በውሀው ነጸብራቅ ሲያይ ይውላል። አንድ ቀን አጎንብሶ ሲመለከት አሸንራተተውና ሀይቁ ውስጥ ገብቶ ሞተ።

በማግስቱ የጫካ ንግስት ውሀ ለመጠጣት ወደ ሀይቁ ወረደች፤ ነገር ግን በፊት የምታውቀው የሀይቁ ውሀ ወደ ጨውነት ተለውጦ ለመጠጣት አስቸጋሪ ሆነ አገኘችው።

የጫካዋ ንግስትም የሀይቋን ንግስት ጠየቀቻት

“ስለምን እንባዎችሽን ታፈሻለሽ ? እንባዎችሽ እኮ ውሀውን ጨው አደረጉብን?”

” ምን ላድርግ ብለሽ ነው ናርሲስ እኮ ሞተ ”

“አንችማ አልቅሽለት ፣ እኔ እሱን ለማደን በየጫካው እዞራለሁ፣ እሱ ደግሞ ካንጂ ጎን ተደፍቶ ቁንጅናውን ሲመለከት ይውላል። ”

” ናርሲሰስ ቆንጆ ነበር እንዴ?” ጠየቀች የሐይቋ ንግስት

” ቆንጆ ነበር ትያለሽ? ስለሱ ውበት ካንች የተሻለ ማን ሊነግረን ይችላል? ካንች አጠገብ አይደለም እንዴ ተንበርክኮ የሚውለው?”

የጫካዋ ንግስት በሀሳብ ተውጣ ለትንሽ ጊዜ ጸጥ አለች።

ቀጠለች ” አየሽ የናርሲሰስን ውበት አንድም ቀን አስተውየው አላውቅም ነበር፣ ነገር ግን እሱ ከጎኔ መጥቶ አንገቱን አዘቅዝቆ ሲመለከተኝ እኔ በእሱ አይኖች ውስጥ የራሴን ውበት መልሼ ስለማየው እደሰት ነበር። ያለቀስኩትም ለዚህ ነው።”

መለስ በተቀበረ በሳልስቱ ኢህአዴግ ደስ ብሎት” ለመለስ ዜናዊ ያነባህ የኢትዮጵያ ህዝብ ልዩ ምስጋና ይገባሀል” የሚል መግለጫ አወጣ።

የኢትዮጵያ ህዝብም እንዲህ ሲል መለሰ ” አይ ኢህአዴግ ያለቀስነው እኮ ለራሳችን ነው። መለስ የውበታችን ማሳያ ነበር ፤ በእሱ ክፋት የኛን ደግነት፣ በእሱ ጥጋብ የኛን ረሀብ፣ በእሱ ውሸት የኛን እውነት፣ በእሱ ጉራ የኛን ትሁትነት፣ በእሱ ስድብ የኛን ጨዋነት እያየን እራሳችንን እያደነቅን እንጽናና ነበር።”

ኤሎን ሳምሶን ( elonsamson@gmail.com)

መንግሥትና ቤተ ክህነቱ፣ የሁለቱ ሲኖዶሶች ሰላማዊ ድርድር፣ የአቡነ መርቆዮስ ጉዳይ፣ የፓትርያሪክ ምርጫና ውዝግቡስ ወዴየት እያመራ ይሆን!? ክፍል ሁለት፣ ምንጭ –ሪፖርተር ጋዜጣ የእሁድ እትም በፍቅር ለይኩን

$
0
0

ባለፈው አስራ አምስት ቀን ጽሑፌ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ አጠር ባለ መልኩ አጠቃላይ የሆነ የቤተ ክርስቲያኒቱን የረጅም ዘመን ታሪክን ተንተርሼ አንድ መጣጥፍ ለማቅረብ ሞክሬ ነበር፡፡ አንዳንድ አንባቢዎቼ የጽሑፌን ጭብጥ ካለመረዳት ይሁን ወይም በሃይማኖት ካባ ሥር ተሸሽገው ፖለቲካዊ አጀንዳቸውን ለማራመድ ከሚፈልጉና አሊያም ስሜታዊነት ካየለበት የሃይማኖት አርበኝነት መንፈስ ተነሳስተው ነው መሰል ‹‹አንተ ከማን ወገን ነህ፣ ሚናህን ለይ…›› የሚል ሰም ለበስ ጥያቄያቸውን በማስቀደም ‹‹ለመሆኑ በአባቶችና በቤተ ክርስቲያኒቱን ታሪክ ዙሪያ እንዲህ ዓይነቱን ጽሑፍ ለማቅረብ ማን መብት ሰጠህ?!›› ዓይነት አስተያየታቸውን ለግሰውኛል፡፡

ይህን ለማለት ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን የእነዚህን ወገኖቼን አስተያየት አከብራለሁ፡፡ በጨዋነትና በቅን መንፈስም ለእነዚህ ወገኖቼ አሳቤን ለማስረዳት ሁሌም ዝግጁ እንደሆንኩ ጭምርም ልገልፅላቸው እወዳለሁ፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ‹‹ይህን ልትናገር ይህን ልትፅፍ አይገባህም›› በማለት የመናገርና የመፃፍ መብቴን ለመገደብ ከሚሞክሩ አምባገነኖች ጋር ግን መቼም ቢሆን ድርድር አይኖረኝም፡፡

ስለዚህም አንድም እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነቴና እንዲሁም ደግሞ እንደ Professional Historian ቤተ ክርስቲያኒቱ ካለፈችባቸው የታሪክ ውጣ ውረዶች በመነሳት የቤተ ክርስቲያኒቱንም ሆነ ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚመሩ አባቶችን መንፈሳዊ ክብርና ልእልና በማይነካ መልኩ መፃፌን እቀጥላለሁ፡፡ እናም ቃል በገባሁት መሠረት ለዛሬ ከባለፈው የሚቀጥለውን ጽሑፌን በዚህ መልኩ አዘጋጅቼዋለሁ፡፡

ከፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ እልፈት በኋላ የተፈጠረው ቤተ ክርስቲያኒቱን ማን ይምራት ጥያቄ፣ በአገር ውስጥና በውጭ ዓለም ባሉት ሲኖዶሶች መካል የተጀመረው ድርድርስ በምን መልኩ ይቀጥል፣ በግፍ ነው ከመንበሬ የተሰደድኩት የሚሉት የአቡነ መርቆርዮስ ጉዳይስ መቋጫው ምን ሊሆን ይችላል… እና ወዘተ በሚሉትና እነዚህ ተከትለው በተነሱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ያለው ሲኖዶስ ተከታይ የሆኑ ስብሰባዎችን ተካሂደዋል፡፡ ተደጋጋሚ የሆኑ መግለጫዎችም ወጥተዋል፣ በቅርቡም በአሜሪካ ዳላስ ለሰላምና ለአንድነት ሲባልም በሁለቱ ሲኖዶሶች ያሉ ተደራዳሪ አባቶች በጋራ ቀድሰዋል፣ በአንድነት ሆነው ማዕድም ቆርሰዋል፡፡

ይህን ያዩና የሰሙ የቤተ ክርስቲያኒቱ ምእመናንም በዚህ አንድነትና ሰላም ተስፋ ጭላንጭል ውስጥ ሆነው በማኅበርና በየግላቸው ለፈጣሪያቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ይኸው የሰላምና የአንድነት መልካም ጅማሬ ፍጹም ሆኖ ይቀጥልም ዘንድ እግዚአብሔር አንድነትና ሰላምን ለቤተ ክርስቲያኒቱ እንዲሰጥ ምህላ፣ ጸሎትና ሱባኤን አድርገዋል፣ አሁንም እያደረጉ ነው፡፡
ይሁን እንጂ አሁን አሁን በቤተ ክርስቲያኒቱ ሰላምና አንድነት ዙሪያ እየታዩና እየተሰሙ ያሉት ነገሮች የብዙዎችን ተስፋ እያደበዘዘ ያለ ነገር እየሆነ ነው፡፡ አንዳንዶች እንደገመቱት የችግሩ ዋንኛ ምክንያትና ተጠያቂ ናቸው በሚል ከተፈረጁት ከአቡነ ጳውሎስ እልፈት በኋላም እንኳን አሁን ያሉ አባቶች ቤተ ክርስቲያኒቱን ወደ መረጋጋትና አንድነት ለማምጣት ዳገት እንደሆነባቸው እየታዘብን ነው፡፡ እንደውም በተቃራኒው የአቡነ ጳውሎስ እልፈት ለዘመናት ሲንከባለል የቆየውን የቤተ ክርስቲያኒቱን መንፈሳዊ ቀውስና አስተዳደራዊ ችግር ከመቼውም በላይ ገሀድ አውጥቶታል ሲሉ አንዳንድ ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡

ለቤተ ክርስቲያኒቱ ለሁለት መከፈልና ለአስተዳደራዊ ቀውሱ ዋንኛ ምክንያት ናቸው የተባሉት አቡነ ጳውሎስ እረፍት በኋላ ግን የተናፈቀው ሰላም፣ እግዚኦ የተባለለት አንድነት በተቃራኒው ለያዥ ለገራዥ ባስቸገረ መልኩ ውሉ እንደ ጠፋ ልቃቂት እየተወሳሰበ መሄዱን በየቀኑ እያየንና እየሰማን ነው፡፡

በቤተ ክርስቲያኒቱ ለገባችበት አጣብቂኝና የነገ ዕጣ ፈንታዋ ዙሪያ ውዝግቡና ክርክሩ አሁንም የበረደ አይመስልም፡፡ ከቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባዎች በፊትና በኋላ ከሚሰጡ ቅድመ ትንታኔዎችና ትችቶች ጀምሮ በየድረ ገጹ፣ በየብሎጉ፣ በጋዜጦችና በመጽሔቶች የቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳይ የመነጋገሪያ ርዕስ እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ በዚህ ሁሉ ጩኸትና እግዚኦታ መካከል ጎልቶ የሚሰማው ድምፅ ግን በቤተ ክርስቲያኒቱና በአባቶች መካከል ሰላምና አንድነት ይወርድ ዘንድ የሚናፍቅና አጥብቆ የሚሻ እንደሆነ ነው ያስተዋልኩት፣ በትክክልም የተረዳሁት፡፡

በአንፃሩ ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለገባችበት ቀውስ ተጠያቂው ማን ነው? በሚል አንዱን አጽድቀው ሌላውን ኮንነው የሚራገሙና ጎራ ለይተው በቃላት ጦርነት የሚሞሻለቁም አልጠፉም፡፡ በዚህ መካከልም መንፈሳዊ ሽታና ለዛ የራቃቸው፣ ዘረኝነትና ወገኝነተኝነት የሚንጸባረቅባቸው መጣጥፎች፣ መግለጫዎችና አስተያየቶችም እየወጡ ነው፡፡

በዘመኑ የብሔር ፖለቲካ አቅላቸውን የሳቱ አንዳንዶች አሁን ደግሞ ተራው የእኛ ብሔር ነው በሚል ያዙን ልቀቁን የሚሉ ሰዎችም በአደባባይ ድምፃቸውን እየሰማን ነው፡፡ በእርግጥም በቤተ ክርስቲያኒቱ ዙሪያ እየታየና እየተሰማ ያለው ነገር ልክ እንደ ካህኑ ዔሊ ዘመን ጆሮን ጭው የሚያደረግ አሰደንጋጭና አስጨናቂ እየሆነ ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ጭራሽ ምንም ዓይነት መንፈሳዊ መዓዛና ለዛ የሌላቸው፣ ደፋሮች፣ ሆዳቸው አምላካቸው ክብራቸው በነውራቸው የሆኑ መንፈሳዊ ካባን የደረቡ የዘመናችን ተኩላዎችም ዓይናቸውን በጨው አጥበው የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀብትና ንብረት መዝረፉን አጥበቀው ተያይዘውታል፡፡ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የቤተ ክህነቱ ሠራተኛ እንደነገሩኝ፡-
ከመቼውም ጊዜ በላይ ሥርዓተ አልበኝነቱ፣ ዘርኝነቱ፣ እኔ ልሾም ባይነቱ፣ መሰሪነቱ፣ አንዱ አንዱን ጠልፎ ለመጣል የሚያደርገው ሸፈጥ፣ ሴረኝነቱ፣ ወገንተኝነቱ፣ የስም ማጥፋቱ ዘመቻ …ወዘተ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ ፈሪሃ እግዚአብሔርና መንፈሳዊነት ከቤተ ክህነቱ ጓዙን ጠቅሎ የተሰደደ ነው የሚመስለው ይላሉ እኚሁ አባት ሐዘንና ትካዜ በተጫነው ድምፅ፡፡

እንደ ቀደመው ዘመን ፍቅርንና ትህትናን እንደ ሸማ የለበሱ፣ በጸሎት የተጠመዱ፣ የሌተ ተቀን አሳባቸው የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ የሆነ፣ እንደ ንጉሥ ዳዊት ‹የቤትህ ቅንአት በላችኝ› የሚሉ፣ እንደ ነቢዩ ኤልያስ ‹በእውነት ስለ እውነት ቆመው ከበዓል ነቢያት ጋር ፊት ለፊት የሚጋጠሙ መንፈሳዊ አርበኛ የሆኑ አባቶች› በዘመናችን አድራሻቸው የት እንደሆነ ግራ ተጋብተናል ሲሉ ይገልፃሉ፡፡ በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቀውስ ዙሪያ አስተያየታቸውን የለገሱኝ እኚሁ አባት፡፡

ዛሬ ዛሬ የቤተ ክርስቲያኒቱን አባቶችና አገልጋዮች እንዲሁም በሚያስደንቅ ሁኔታ ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ ደግሞ ምእመናን ጭምር ወንድ ሴት ሳይሉ በአትኩሮት እየተከታተሉት ያሉት የቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳዮች የዕለት ተዕለት የመነጋገሪያ አጀንዳ ወደ መሆን እየተሸጋገረ ነው፡፡ ዓላማው ምንም ይሁን ምን ይህ ዓይነቱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳይ እኔም እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነቴ ያገባኛል በሚል መንፈስ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከአፈ-ነቢብ እስከ ምሁር ድረስ ድምፃችን መሰማቱ መልካም እንደሆነ አሳባለሁ፡፡

በአዎንታዊም ሆነ አሉታዊ በሆነ መንገድ በቤተ ክርስቲያኒቱ በዘመናት ጉዞዋ እየተንከባለሉ በመጡ ችግሮቿና ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ እየተንጸባረቁ ያሉ አሳቦች፣ አስተያየቶች፣ ትችቶችና ውይይቶች እስከነ ብርታታቸውም ሆነ ድካማቸው ይበል የሚያሰኙ እንደሆነ በግሌ አጥብቄ አምናለሁ፡፡

ኑሮአቸውን በአሜሪካ ያደረጉት እውቁ የታሪክ ምሁርና Church and State በሚለው ዘመን አይሽሬ (Classic) የምርምር ሥራቸው የቤተ ክርስቲያኒቱንና የቤተ ክህነቱን ለሺህ ዘመናት የዘለቀ ግንኙነትና ትስስር በሚገባ የተነተኑ፣ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ጥንታዊ ገዳማትና ድርሰቶች ዙሪያ ሰፊ ምርምርና ጥናት በማድረግ የሚታወቁት ፕ/ር ታደሰ ታምራት፣ የዛሬው ትውልድ በቤተ ክርስቲያኑ የውስጥና የውጭ ጉዳዮች ላይ እያሳየ ያለውን ተሳትፎ፣ ቁጭትና እኔም ያገባኛል መንፈስ ይበል የሚያሰኝ መሆኑን በአንድ ወቅት ባደረጉት ቃለ መጠይቅ እንዲህ ገልጸውት ነበር፡-

በአሁኑ ዘመን በምእመኑና በወጣቱ በኩል ያለው የቤ/ን ፍቅርና ከበሬታ እጅግ በጣም ተለየና በጣሙን የሚያስደንቅ ነው ይላሉ ፕሮፌሰሩ፡፡ ወጣቱም ሆነ ጎልማሳው ለቤተ ክርስቲያኗ ያለው የባለቤትነት ስሜት በጣም እጠነከረ መምጣቱም ግልፅ ነው፡፡ ፕ/ር ታደሰ እንደሚገልጹት ምእመኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ ወደ ቤ/ን እየጎረፈ ነው፡፡
እንደዚህ ልቡን በሙሉ ከፍቶ ቤተ ክርስቲያኒቱን የመቅረቡን ያህል የኅሊናውን ጭንቀት፣ ሥጋዊና መንፈሳዊ ችግሮቹን ተረድቶ የሚያረጋጋው ጠንካራና ያልተከፋፈለ መንፈሳዊ መሪ ግን የታደለ አይመስልም፤ ሕዝቡ በአስተሳሰቡም ሆነ በአኗኗሩ መልካም አርአያ የሚሆነው አባትን ይሻል፡፡

በእርግጥም ፕ/ር ታደሰ እንዳሉት እኔም እንደምስማማበት በምእመኑ ዘንድ ብዙ ለውጦች እየታዩ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በቤተ ክርስቲያን በኩል ግን ለዚህ ሰፊ ሕዝባዊ አመኔታ የሚያረካ ወይም መልስ የሚሆን፣ ለወጣቱ ከዛሬ አርባ ዓመት በተሻለ የተሟላ መንፈሳዊ እርካታ ሊሰጥ የሚችል መንፈሳዊና በሳል አመራር ድል ነስቶ ለመውጣት የቻለ አይመስልም፡፡ እናም በአጠቃላይ በቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ጉስቁልና እና አስተዳደራዊ ቀውስ ላይ ያሉ ሮሮዎችና ጩኸቶች ዛሬም ተበራክተው ቀጥለዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ አስተያየታቸውን ሲያጠቃልሉም፡- ‹‹ይህን ያህል የምእመናን ቀጥተኛ ተሳትፎ ያለበት፣ የሃይማኖት መሪዎች አመኔታ ያጡበት፣ መሠረታዊ እምነትን ሚያናጋ፣ ሕዝቡን ከቤ/ን የበለጠ ሊያርቅ የሚችል መንፈሳዊ ዝቅጠት፣ የሞራል ውድቀትና እንዲህ ያለ ውዝግብ በቤተ ክርስቲያኒቱ የረጅም ዘመን ታሪክ እንዲህ እንደ አሁኑ ቅጣ ባጣ መልኩ ስለመከሰቱ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡›› ሲሉ በአሁኑ ወቅት ቤ/ቱ የገባችበትን መንፈሳዊ ክስረትና ውድቀት ይገልፃሉ ፕ/ር ታደሰ በቃለ ምልልሳቸው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቤተ ክርስቲያኒቱ የአመራር አካላትና በራሱ በተቋሙ ውስጥ የተፈጠረውን ውዝግብና ውስጣዊ አለመስማማት በረጋ መንፈስ እንደ ጥንቱ የሐዋርያትና የቅዱሳን አበው ዘመን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መሪ በሆነበት ውይይትና ክርክር በቅንነት ተነጋግሮ ‹‹እኛና መንፈስ ቅዱስ እንዲህና እንዲያ ወስነናል›› የሚል ድምፅ መስማት ከናፈቀን በርካታ ዓመታት እየተቆጠሩ ነው፡፡ አባቶቻችን እርስ በርሳቸው የሚነጋገሩበት ቋንቋ የሃይማኖት ሳይሆን የሥልጣን፣ የኃይል፣ የእልህ እንዲያው በአጠቃላይ ፍጹም ዓለማዊ ቋንቋ እየሆነ መጥቷል፡፡
በዚህ ሁሉ ውዝግብ፣ መንፈሳዊ ክስረትና አስተዳደራዊ ቀውስ ያለችው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አሁን ደግሞ እጅግ ወሳኝ በሆነ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች፡፡ ከሁለት አስረተ ዓመታት በፊት ለሁለት የተከፈለቸው ቤተ ክርስቲያን ዳግም አንድነቷን ለማደስና በመካከሏ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ እየጣረች ብትሆንም፤ ይህ ጥረት ግን እምብዛም ሥር ያለውና ፍሬ የሚያፈራ እንዳልሆነ በግልፅ እየታየ ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግና ቀኖና መፍረስ ጉዳይና በዚህም የተነሣ የአቡነ መርቆርዮስ ከመንበራቸው በግፍ መሰደድ ጉዳይ በሁለቱ ሲኖዶሶች በሚገኙት አባቶች መካከል ለሰላማዊ ድርድሩ መቀጠል እንቅፋት ሆኖ መውጣቱ በግልጽ እየታየ ነው፡፡ ከሰሞኑ በሰላሙ ድርድር ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የውጩ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ አቡነ መልከ ጸዴቅ፡-
ከኢትዮጵያው ሲኖዶስ በኩል ‹‹አቡነ መርቆርዮስ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው መምጣት ይችላሉ፤ ነገር ግን ፓትርያርክ መሆን አይችሉም፡፡›› በሚል የወጣው መግለጫ በጭራሽ በእነርሱ ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው ነው ከረር ባለ ቃል የገለጹት፡፡ እንደውም አሉ አቡነ መልከ ጸዴቅ፡-

አቡነ መርቆርዮስ ወደ አገራቸው የመግባት ጉዳይ እንደ ኢትዮጵያዊነታቸው መብታቸው እንጂ ሲኖዶሱ የሚያጸድቅላቸው ጉዳይ አይደለም ሲሉ ሲኖዶሱ መንፈሳዊ ሥልጣኑን ወይም ኃላፊነቱን ምን መሆኑን የዘነጋና ማንኛውም ሰው በአገሩ የመኖር መብት እንዳለው እንኳን ያለየ በሚል ስሜት የሰላ ትችታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

ለሃያ ዓመታት ያህል በፕትርክና መንበር ላይ የተቀመጡት አቡነ ጳውሎስ ሕጋዊ አይደሉም የሚሉት አቡነ መልከ ጸዴቅ በሁለቱ ሲኖዶሶች መካከል የተላለፈው ውግዘት ገና የተነሳ አለመሆኑን መግለፃቸውም ለእኔና ለእንደኔ ዕይነቶቹ ሌላኛው አስደንጋጭ ዜናና ሰላማዊ ድርድሩም ገና በጽንስና በጭንገፋ መካከል ላይ የሚዋልል መሆኑን ያሳየ ሆኖ ነው የተሰማኝ ያደረገ ነው፡፡
ለመሆኑስ የሆነስ ሆነና ‹‹ውጉዝ ከመ አርዮስ›› ተባብለው የተወጋገዙ እነዚህ የሃይማኖት አባቶች የተወጋገዙበት የውግዘት ቃል ሳይነሳ፣ ልዩነቶቻቸውንና የጠባቸውንም ምክንያት በረጋ መንፈስ ተወያይተው ሳይተማመኑና ሳይፈቱ፣ በመካከላቸውም እርቅና ሰላም ሳይወርድ፣ አብረው የቀደሱበትና ማዕድ የቆረሱበት ሁኔታ በግሌ በእጅጉን አስገርሞኛል፡፡

መጽሐፍ እንደሚነግረን እነኚሁ መንፈሳዊ አባቶቻችንም ደጋግመው እንዳስተማሩን ‹‹በመጀመሪያ መባህን በመሰዊያው ላይ ትተህ አስቀድመህ ከወንድምህ ጋር ታረቅ ነው››፡፡ ታዲያ አሁንም ድረስ በመለያየት መንፈስ ውስጥ ያሉ አባቶቻችን በምን ሂሳብ አብረው እንደቀደሱና ማዕድ እንደቆረሱ ምንም ግልፅ አይደለም፡፡ እነርሱም እስካሁን የነገሩን ነገር የለም፡፡

የእስካሁኑ በሁለቱ ሲኖዶሶች ባሉ አባቶች መካከል በነበረው ውይይት ‹‹የስማ በለው›› መሆኑንና በተጨማሪም በአገር ውስጥም ሆነ በውጩ ዓለም ያሉ የየሲኖዶሶቹ አባቶች በእንደዚህ ዓይነቶቹ ወሳኝ አጀንዳዎች ላይ ቢያንስ ቅድመ ስምምነት ላይ ለመድረስ አለመቻላቸው ሰላማዊ ድርድሩ ቀድሞውኑ የይስሙላና ይኸው እንዲህ ሞክረን ነበር ነገር ግን በሚል አንዱ አንዱን ለማሳጣት የሚደረግ ከንቱ ሩጫና ልፋት እንደሆነ ፍንጭ የሚሰጥ ነው ሲሉ በርካታ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ሰዎች ይናገራሉ፡፡
የአቡነ መልከ ጼዴቅም ከኢሳት የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ያደረጉት ቃለ መጠይቅም ይኸንኑ እውነታ የሚያስረግጥ ነው፡፡ ብፁዕነታቸው ሲገልፁም፡- ‹‹ሰላማዊ ድርድሩ ምንም ዓይነት የመቀራረብ ሁኔታ ያልታየበት እንዲሁ የይስሙላና ብዙም ተስፋ የሌለው በማለት ነው፡፡›› በአጭር ቃል የገለጹት፡፡
በቅርቡም ዶ/ር ተክሉ አባተ የተባሉ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ምሁር Ethiopian Orthodox Tewahdo Church at a Crossroads በሚል ርዕስ በተለያዩ ድረ ገጾች ባስነበቡት ጽሑፋቸውም፡-

The two synods come up with preconditions for negotiation and reconciliation, some of which are irrelevant to the noble cause- unity. Mainly because of the extremely rigid and egoistic nature of the preconditions put forward, previous reconciliation efforts ended in fiasco. በማለት በሁለቱ ሲኖዶሶች መካከል የቀጠለው ድርድር ቁልፍ ባልሆኑ ተራ ምክንያቶች የተነሳ ገና ከጠዋቱ እንቅፋት እንደገጠመው ገልጸውታል፡፡

የሆኖ ሆኖ አሁን እንደሚታየውና እንደሚሰማው ሰላማዊ ድርድሩ ተስፋ ያለው አይመስልም፡፡ ‹‹የቤተ ክርስቲያኒቱ የመንፈስ አንድነትና ሰላሙ›› ይቅደም የሚለው ድምፅም ብዙም ሰሚ ያገኘ አይመስልም፡፡ በተጨማሪም ደግሞ ብዙ የተባለለትን ሰላማዊ ድርድር በይበልጥ የሚያወሳስበው ደግሞ የአሜሪካው ሲኖዶስና በዛ ያሉ አባቶች ኢህአዴግን ከሚቃወሙ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ጋር በተደጋጋሚ አጋርነታቸውን የገለጹና እየገለጹ ያሉ የመሆናቸው እውነታ ነው፡፡

ይህ የእነዚሁ በውጭ አገር በስደት የሚገኙ አባቶች ተቃውሞ መነሻ ደግሞ በሃይማኖት ጉዳይ ላይ ግልፅ የሆነ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እንደሆነ ብዙ የተባለለት ነገር ነው፡፡
መንግሥት ቀድሞውኑ በፓትርያክ መርቆርዮስ ጉዳይም ሆነ አሁን ባለው በወቅታዊው የቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጣዊ ጉዳይ ላይ ያራሱን ፍላጎት ላማስፈፀም ትናንት በቀደደው በር ዛሬም ገብቶ ያሻውን ለማድረግ የሚያግደው ኃይል እንደሌለ የሚያሳዩ በርካታ መሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል የሚሉት እነዚሁ ታዛቢዎች፤ ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በቅርቡ ለአቡነ መርቆርዮስ የላኩት ደብዳቤ ከመንግስት በኩል ሳይውል ሳያድር የገጠመው ብርቱ ተቃውሞ በቂ ማሳያ እንደሆነ በተጨባጭ በመጥቀስ ይከራከራሉ፡፡

ይህም ክርክር በድምዳሜው ምንም እንኳን ‹‹መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አልገባም፣ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያኒቱ ለሀገር ሰላምና ልማት ካላት አዎንታዊ ተጽእኖና ጉልህ ተሳትፎ የተነሳ ከመንግስት አሰፈላጊው የሆነ፣ አድልዎ የሌለበት እገዛና ድጋፍ እናደርጋለን›› ቢልም፤ ብዙዎች እንደሚተቹት በዚህ ሰበብ መንግሥት እንደትላትናው ሁሉ ዛሬም በብልጣ ብልጥና መሰሪ አካሄዱ በቤተ ክርስቲያኒቱ የውስጥ ጉዳይና ጓዳ ጎድጓዳ ውስጥ በመግባት እርሱ የወደደውንና የፈቀደውን ሰው ለመሾም በማንአለብኝነት መንገዱን አገባዷል ሲሉ ይደመጣሉ፡፡
በዚህ መንግሥት በቤተ ክርስቲያኒቱ የውስጥ ጉዳይ ላይ ህጋዊ ፓትርያርክ የሆኑትን አቡነ መርቆርዮስን እስከማውረድ ድረስ የተጓዘበትን ድፍረቱንና አጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ የሚያራምደውን ፖለቲካዊ አቋሙንና ውሳኔዎቹን እንዲሁም የኢኮኖሚ ፖሊሲዎቹን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በመተቸት ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በአሜሪካና በምዕራቡ ዓለም የኢህአዴግን መንግሥት በመቃወም በሚካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ በተደጋጋሚ ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ ሲያሰሙ የነበሩና አሁንም እያሰሙ ያሉትን እነዚህን አባቶች መንግሥት በበጎ ዓይኑ ያያቸዋል ብሎ ማሰብ ትልቅ የዋኽነት ነው የሚሆነው፡፡

በአንፃሩም በሃይማኖታችን ጉዳይ ላይ ግልጽ የሆነ ጣልቃ ገብነት አድርጎ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለሁለት እንድትከፈል ምክንያት ሆኗል፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕጋዊ ፓትርያርክ በማጋዝ የቤተ ክርስቲያናችንን ክብርና ህልውና ተዳፍሯል፣ በሀገሪቱ የጎሳ ፖለቲካና ዘረኝነትን በመዝራት ሕዝቡን ከፋፍሏል…ወዘተ በማለት በኢህአዴግ መንግሥት ላይ የተቀየሙና መሠረታዊ የሆነ ተቃውሞ ያላቸው የእነዚህ አባቶች ፖለቲካዊ አቋምም ድርድሩን በይበልጥ የተወሳሰበ እንደሚያደረገው ግልፅ ነው፡፡
በቅርቡ እንኳን በአሜሪካው ሲኖዶስ ያሉ አንድ አባት የኢትዮጵያ መንግሥት ‹‹ሽብረተኛ›› በሚል ከሰየመው ቡድን የጦር አባላት ጋር በአንድነት የተነሱትን ፎቶ በኢህአዴግ መንግሥት በኩል ሊፈጥር የሚችለው አንድምታ ምን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ልብ ይሏል፡፡

የቤተ ክህነቱ ተቋምና መሪዎቹ በአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ከእውነትና ከፍትህ ጋር ከመቆም ይልቅ በየጊዜው አቋማቸውን ከሚለዋውጡ ፖለቲከኞች ጋር መወገናቸው ሌላው እንቆቅልሽና የአገሪቱም ሆነ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሌላ ተጨማሪ ፈተና ሆኖ መውጣቱ ግልፅ ነው፡፡

ልክ እንደ ቅዱስ አትናቴዎስ If the World stand aginst the Truth Atnatewos stands against the World በሚል መንፈሳዊ ድፈረት ለፍትህ እና ለእውነት የሚቆሙ ጽኑ አባቶች በዘመናችን መጥፋታቸው ቤተ ክህነቱና ቤተ መንግሥቱ እርስ በርሳቸው ሊኖራቸው የሚገባውን ኃላፊነትና ድርሻ የተደበላለቀ አድርጎታል፡፡ ከዚህም የተነሣ የቤተ ክህነቱ ተቋሙና ተቋሙን የሚመሩት አባቶች መንፈሳዊ ልእልናቸውን፣ ክብራቸውንና ሥልጣናቸውን በሚገባ መጠቀም ያልቻሉና ለሚሰሩት ቀርቶ ለሚያስቡት እንኳን በተቃራኒው የመንግሥት ቡራኬና ፈቃድ ጠባቂ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡
ብዙዎች የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት፣ ምሁራንና ታዛቢዎች እንደሚናገሩትም፡-

በይበልጥም ቤተ ክርስቲያኒቱን የመንግሥት ጥገኛ የሚያደርጓት የቤተ ክህነቱ መሪዎች ራሳቸው ናቸው ሲሉም ይደመጣሉ፡፡ እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚተቹት ጳጳሳቱ በራሳቸው አይተማመኑም፡፡ እግዚአብሔርን ሳይሆን የሚፈሩት ባለሥልጣናቱን ነው፡፡

ሥልጣንን እንደ ምድራዊ መሳሪያ እንጂ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደሚያገለግሉበት ኃይል አይቆጥሩትም፡፡ ስለዚህ በእነሱ መንፈሳዊ የመሆን ጉድለት የተነሳ እንደ ጎርፍ ከሚያልፉ መሪዎች ጋር ዘላለማዊቷን የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን ለጥፈዋት ለችግር ሲያጋፍጧት ኖረዋል፡፡ ከዚህ የተነሳም መጪውንም ዘመን ፍቺ የሌለው አድርገን እንድንመለከተው አወሳስበውብናል ሲሉ አምርረው ይተቻሉ፡፡

ቤተ ክህነቱ ራሱን ከመንግሥት ጥገኝነት አላቆ ወደ ቀደመ መንፈሳዊ ክብሩ፣ ልእልናውና ሥልጣኑ የሚመለስበትን ፍፁም መንፈሳዊና ቅን ወደሆነው የእውነት መንገድ ለመመለስ ካልወደደ የምንናፍቀው ሰላምና አንድነት ሩቅ ሊሆንብን ይችላል፡፡

ሰላም… ሰላም… አንድነት… አንድነት… በሚል አስቀድሞ ለሰላማዊ ድርድሩ፣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነትና ሰላም ጉዳይ ቅድሚያ ይሰጥ፣ ለፓትርያርክ ምርጫው ይደርስበታል የሚሉ ድምፆች ጎልተው በወጡበት በዚህ ወቅት የሰላሙና የአንድነቱ ጉዳይ ብዙም ተስፋ ሰጪ አይመስልም፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ስለ ቤተ ክርስቲያናችን አንድነት ደጋግመን መናገራችንን፣ ደጋግመን መፃፋችንና ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ሰላምም መዘመራችንን መቼም ቢሆን አናቋረጥም፡፡

 እርሱ በክቡር ደሙ ፈሳሽነት ንጽሕት፣ ቅድስትና ያለ ነቀፋ ለሆነችው ለቤተ ክርስቲያን ልጆች እንሆን ዘንድ ያበቃን፡- እርሱ ክርስቶስ ኢየሱስ ወልደ ዋህድ፣ የማርያም ልጅ ድንቅ፣ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ ሰላም አለቃ፣ የፍቅር አምላክ ነውና!!!
 ቢሆን ቢሆን አባቶቻችን በመጀመሪያ እርስ በርሳቸው ያላቸውን ልዩነት በፍቅር፣ በትህትና እና በቅንነት መንፈስ በመነጋገር ፈትተው በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የመንፈስ አንድነትንና ሰላምን በማስፈን የሰላም ሐዋርያ መሆናቸውን ቢያሳዩን እንዴት በወደድን፡፡
 ከዛም አልፈው አባቶቻችን መንግሥታትን በቅን መንገድ በመምራት፣ ክፉዎችንና ኃያላኑን በመገሰጽ፣ ለፍትህና ለነፃነት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በመጮኽ፣ ከድሆችና ከተገፉ፣ ከፈጣሪ የተሰጣቸውን መብታቸውን ከተገፉፉና ከታፈኑ የምድራችን ምንዱባን ጋር በመቆም የእውነት ጠበቃ መሆናቸውን ቢያሳዩን እንዴት በተደመምንና ደስ ባለን፡፡
 ምናለስ በሁለቱም ሲኖዶሶች ያሉ አባቶች ድህነት ዕጣ ፈንታዋና መለያዋ ለሆነባት ኢትዮጵያችን፣ ራብና ጠኔ ሕዝቦቿን ለሚያጭድባት ምድራችን፣ ለተሻለ ሕይወት በሚል እንደ ጨው ዘር በዓለም ሁሉ ተበትነው ውረደትን ለተከናነቡ የአብራኳ ክፋዮች፣
 የጥላቻና የጽንፈኝነት አባዜ ቁም ስቃዩን ለሚያሳየው የአገራችን የፖለቲካ ሰማይ እንደ ማንዴላ፣ እንደ ማርቲን ሉተር፣ እንደ ጋንዲ የወንድማማች ፍቅርን፣ እርቅንና ሰላምን ደግመው ደጋግመው ቢሰብኩልን በወደድን፡፡

እንዴት ክፉዎችን፣ አመጸኞችን፣ የምድራችንን ኃያላኖችንና አምባገነኖችን ኃይልና ብርታት ባለው በመንፈሳዊ ቃል ያወግዙልናል፣ ያሳፍሩልናል የምንላቸው አባቶቻችን፣ መጽሐፍ እንደሚልም፡- ‹‹በአሕዛብ ላይ በቀልን፣ በሰዎችም መካከል ቅጣትን ያደርጉ ዘንድ፣ ንጉሦቻቸውን/መንግስታትን በሰንሰለት፣ አለቆቻቸውንም በእግር ብረት ያስሩና የተፃፈባቸውን ፍርድ ሁሉ ያደርጉባቸው ዘንድ›› የሚል መንፈሳዊ ሥልጣንና ክብር በምድርና በሰማይ የተሰጣቸው አባቶቻችን እንዲህ እንደ አሁኑ ዘመን ስለ ፍትህ መጮኽ፣ ስለ እውነት ጠበቃ ሆነው መቆም ሲያቅታቸው ምን ለማለት ይቻለን ይሆን?!
በመጨረሻም ወደ ዛሬው ጽሑፌ ማጠቃለያ ርዕሰ ጉዳይ ስመለስም በአቡነ መርቆርዮስና በፓትርያርክ ምርጫ ጥድፊያ ዙሪያ እየተነሱ ባሉ አሳቦችና አስተያየቶች ላይ ጥቂት ነገሮችን በማለት አሳቤን ላጠናቅቅ፡፡

በመንግሥት ቀጥተኛ በሆነ ጣልቃ ገብነት በግፍ የተሰደዱት አቡነ መርቆርዮስ መመለስ አለባቸው እስከሚሉና አይ እሳቸውማ መንጋውን በትነው የቤተ ክርስቲያኒቱን መከራና ሰቆቃ እዚሁ ከመንፈሳዊ ልጆቻቸው ጋር ሆነው መሸከም ተስኗቸው ከእናት ምድራቸው ገዳማት ይልቅ አሜሪካን መርጠው ጥለውን ሄደው የለ ታዲያ ምን ሲሉ በተኗቸው ወደሄዱት መንጋዎች ተመልሰው ለመምጣት ይችላሉ እስከሚሉት ድረስ በአቡነ መርቆርዮስ ዙሪያ የተለያዩ እሳቤዎች አሁንም ድረስ እየተንሸራሸሩ ነው፡፡

በአንፃሩ ደግሞ ‹‹አቡነ መርቆርዮስ ወደ አገራቸው መምጣት ይችላሉ፤ ፓትርያሪክ ለመሆን ግን አይችሉም፡፡›› በሚል በቅርቡ ከኢትዮጵያው ሲኖዶስ የወጣው መግለጫ ቢያንስ ለጊዜውም ቢሆን በእርሳቸው ዳግም ወደ ፓትርያርክነት መመለስ ጉዳይ ላይ ያለው አቋም አሉታዊ መሆኑን ግልፅ አድረጓል፡፡

ደግነቱ በዚህ ሁሉ ጩኸትና ውዝግብ ውስጥ እንደ መርግ በሆነ ዝምታ ውስጥ ያሉት እኚሁ አባት ድምፃቸው አለመሰማቱና ምን እያሰቡ እንዳለም አለመታወቁ አንዳንዶቹ ሁሉንም ነገር ትተው በፍፁም አርምሞ ውስጥ ናቸው ያሉት ወደሚል ድምዳሜ እንዲደርሱ እያደረጋቸው ነው፡፡

በበኩሌ በመሠረቱ አቡነ መርቆርዮስ ወደ መንበራቸው ይመለሱ ወይስ አይመለሱ፣ ከተመለሱስ ሥልጣናቸውና ኃላፊነታቸው ምን ድረስ ሊሆን ይገባዋል፣ አሊያም ደግሞ አምስተኛ ፓትርያርክ ብለን እንደገና ወደኋላ ተመልሰን አራት አንልም ስድስተኛ እንጂ የሚል ምንም መንፈሳዊ አመክንዮትና ሽታ የሌለበት ቅድመ ሁኔታዎችና ሙግቶች መቼም ቢሆን የሰላሙንና የአንድነቱን መንፈስ ጎዳና ሊያጨልሙት አይገባቸውም ባይ ነኝ፡፡

እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ሁኔታዎች አባቶችን ሊነጋግሩባቸው የሚገባ ከሆነም በሁለተኝነት መነሳት ያለበት ጉዳይ ነው የሚመስለኝ፡፡ ከሁሉ አስቀድመን መነጋገር፣ መወያየት ካለብን ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ፍቅር፣ ሰላምና አንድነት ጉዳይ ነው መሆን ያለበት ነው የሚመስለኝ፡፡

መሠረታዊውና አንገብጋቢ የሆነውም ጥያቄ ይኸው ነው፡፡ አንድነትና ሰላም ይሻለናል ወይስ እንደ ትናንቱ በመለያየትና በመወጋገዝ የጀመርነውን ጉዞ መቀጠል፡፡ እኛ ግን ለቤተ ክርስቲያኒቱ ህልውና ፍፁም የሆነው የፍቅሩ፣ የሰላሙና የአንድነቱ መንገድ ሁሌም ቢሆን መልካም መሆኑን በቃል ከመናገር በተግባርም ከማሳየት እንዳንዘነጋና እንዳንደናቀፍ የአባቶቻችንን አምላክ እንማጸናለን፡፡

በቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች ፊት የቀረበው ይህ አማራጭም አባቶቻችንን በእግዚአብሔር፣ በታሪክና በትውልድ ፊት ወይ የሚያስመሰግናቸው አሊያም ደግሞ ሲያስወቅሳቸው የሚሆን ውሳኔ ሊሆን ይችላል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች የሆኑ አባቶቻችን የፍቅርን፣ የእርቅን፣ የሰላምንና የአንድነትን መንገድ ይመርጡ ዘንድ ከአርያም የሆነ መንፈሳዊ ወኔና ቆራጥነት ከአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ዘንድ እንዲሆንላቸው ከልብ በመመኘት ልሰናበት፡፡
ሰላም! ሻሎም!

« ፍቅረኛሞቹ» አዜብና ብርሃነ (ከኢየሩሳሌም አርአያ)

$
0
0

አዜብ መስፍንን ከሱዳን አምጥቶ ሕወሓትን እንዲቀላቀሉ ያደረገ ነው። የፍቅር ግንኙነትም ነበራቸው። ይህ ሰው ብርሃነ ኪዳነማርያም (በቅፅል ስሙ ብርሃነ-ማረት) ነው። አዜብና ብርሃነ ድርጅቱን ሲቀላቀሉ የተቀበሏቸው አቶ አስገደ ገ/ስላሴ (አሁን የአረና አባል) ነበሩ። ጥቂት የበላይ አመራሮች በሁለቱ የፍቅር ግንኙነት ዙሪያ መከሩ። ከዛም የብርሃነና የአዜብ ግንኙነት እንዲቋረጥ በማድረግ ከለያዩዋቸው በኋላ ከመለስ ዜናዊ ጋር አዜብ እንዲጠቃለሉ ሆነ። (በነገራችን ላይ አንዳንድ ወገኖች አዜብና ሟቹ ክንፈ ገ/መድህን በጫካ ግንኙነት እንደነበራቸው ተደርጎ የሚነገረው ከእውነት የራቀ እንደሆነ የቅርብ ታማኝ ምንጮች ይገልፃሉ፤)
ወደ ዋናው ርዕሰ ጉዳይ እናምራ፥ በሕወሓት ውስጥ አድፍጠው መሰሪ ተግባር ከሚፈፅሙት አንዱ ነው ተብሎ በፓርቲው ወገኖች የሚፈረጀው ብርሃነ ኪ/ማርያም (ብርሃነ-ማረት) ማንነትና አደገኛ አካሄድ ምን እንደሚመስል ከላይ የተገለፀውን መንደርደሪያ ያስቀደሙ ታማኝ ምንጮች ተከታዩን ይላሉ።

ፓርቲው ወደ ስልጣን ሲመጣ አቶ ብርሃነ የተመደበው በመቀሌ ማዘጋጃ ሃላፊ ተደርጎ ነበር፤ መንግስት የከተማውን አስፋልት መንገድ ለማሰራት እንዲውል የመደበውን አምስት ሚሊዮን ብር « ቅርጥፍ» ያደርጋል። በወቅቱ የክልሉ ፕ/ት የነበሩት ገብሩ አስራት በወሰዱት እርምጃ ብርሃነ እንዲባረር ሲደረግ፥ ሁለት ግብረ-አበሮች የተባሉ ደግሞ ይታሰራሉ። የተባረረው ብርሃነ አዲስ አበባ ይመጣል። አዜብን ለማግኘት ብዙ ጥረት ካደረገ በኋላ ተሳካለት። ከዚያም አዜብ የቀድሞ « ፍቅረኛቸው»ን ለመታደግ ሲሉ ብርሃነ በሲቪል ሰርቪስ ኰሌጅ እንዲገባ ያደርጋሉ። ለረጅም አመት ድምፁን አጥፍቶ በኰሌጁ ቆየ። የኢትዮ- ኤርትራን ጦርነት ተከትሎ ለብርሃነ «ጥሩ» አጋጣሚ ፈጠረለት። ከቤተ መንግስት የማይጠፋ ሆነ፤ ከመለስ ጋር ቀን-ከሌሊት ምስጢራዊ ምክክሩ ቀጠለ። ታማኝና ቀኝ እጅ መሆኑን ለማሳየት በተግባር ተንቀሳቀሰ።

በ1993ዓ.ም ፓርቲው ለሁለት ከመሰንጠቁና ይፋ ከመውጣቱ በፊት « ጥንስሱን » ያውቁ የነበሩት አቶ መለስና ብርሃነ ነበሩ። ብርሃነ ታህሳስ 1993ዓ.ም ከፍተኛ ባጀት ተመድቦለት ወደ አሜሪካ መጣ፤ በወቅቱ በፓርቲው ውስጥ ገና ክፍፍል አልተፈጠረም፤ በተባራሪዋቹም በኩል የታወቀ ነገር አልነበረም። ብርሃነ በአሜሪካ ፥ ላስቬጋስ፡ ቴክሳስ፡ቦስተን፡ አትላንታ፡ ሲያትል…ከተሞች እየተዘዋወረ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ቅስቀሳ በማካሔድ በሕወሓት መከፋፈል መፈጠሩን በይፋ ለድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች ገለፀ። ጎን ለጎን ሰዎችን በመመልመል ከአቶ መለስ ጎን እንዲቆሙ አደረገ። በኢምባሲ የተመደቡትን ሳይቀር እያስፈራራና እየዛተ ድጋፍ እንዲሰጡ አዘዘ። በቅስቀሳው ላይ የሚባረሩትን፡ የሚታሰሩትን አመራሮች በስም እየጠቀሰና በስድብ እያብጠለጠለ ነበር ቅስቀሳውን ያካሂድ የነበረው። በተለይ የገብሩ አስራትን ስም በማንቑዋሸሽ… ዘመቻ አካሂዶዋል።« ግዳጁን » በአግባቡ በመፈፀሙ…የፓርቲው ማ/ኰሚቴ አባል ተደርጎ የተመረጠው ወዲያው ነበር።

በሙልጌታ አለምሰገድ ይመራ የነበረውንና በፓርቲው መሰንጠቅ ማግስት የተቋቋመው የፌደራል ደህንነት ቢሮን ከጀርባ እንዲመሩ ከተመደቡት አንዱ የሆነው ብርሃነ፥ ተግባሩን ሲጀምር..የአፈናና ስቃይ ሰለባ ያደረጋቸው ከፓርቲው የተወገዱ አመራሮች – ጠባቂዎችን ነበር። የገብሩ አስራትን ጠባቂዎች (ታጋይ የነበሩ) ጨምሮ በጅምላ እንዲታሰሩ አደረገ። ግርማይ (ማንጁስ) ከተባለ የፌዴራል ፖሊስ ኮማንደር ጋር በቅንጅት ሆነው ጠባቂዎቹን በደም እስኪታጠቡ አሰቃዩዋቸው፤ እነ ገ/መስቀል የተባሉ የቀድሞ ታጋዮች እጅና እግራቸው በብረት ሰንሰለት ታስሮ ከተሰቃዩ በኋላ ወደ ትግራይ ተወስደው..በአደገኛ ቦዘኔነት ክስ እንዲመሰረትባቸው አደረጉ። በስቃይ ብዛት ገ/መድህን የተባለ ህይወቱ አለፈ። ለረጅም ወራት ታስረው ከተፈቱ በኋላ በመቀሌና ማይጨው የቁም እስረኛ ተደረጉ። ምንም ስራ መስራት አይችሉም፤ ወደየትም ስፍራ መንቀሳቀስና ሌላ አካባቢ መሄድ አይችሉም፤..ይህ ሁሉ በብርሃነ የተፈፀመ ነበር።

በሌላ በኩል ደግሞ የዚህን ሰው አደገኛና መሰሪ አካሔድና ተግባሩን ከማንም በተሻለ ጠንቅቀው የሚያውቁና የእርሱ ወጥመድ «ሰለባ» የሆኑ የቀድሞ የፓርቲው አመራር አባላት ምንም ትንፍሽ አለማለታቸውና አለማጋለጣቸው አስገራሚ ነው። ምክንያቱም እነዚህ አካላት በአገር ውስጥ እንዴት እንደታፈኑ ብቻ ሳይሆን ..በዚህ ሰው እንዴት እንደተሰቃዩ ያውቁታል፤ ያስታውሱታል…ሲሉ ምንጮቹ ትዝብታቸውን ሳይጠቁሙ አላለፉም።..

በውጭ አገራት የሚኖሩ የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች ማንነትና የሚያራምዱት አቋም በተመለከተ መረጃ አለው። በተመሳሳይ በተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና አባላት እንዲሁም ደጋፊዎች ዙሪያ መረጃ ማነፍነፍ የየዕለት ተግባሩ ነው። በተለያዩ አገራት የሚመደቡ አምባሳደራት በዚህ ሰው ጥብቅ ክትትል ይካሄድባቸዋል። ሲፈልግ አምባሰደራቱን በስድብ እያብጠለጠለ ያስፈራራል። አንዳንዶች ደግሞ የፈጣሪያቸው ያክል « ጠብ እርግፍ » እያሉ ይሰግዱለታል። በአውሮፓና አሜሪካ ሲዘዋወር በአስር ሺዎች የሚቆጠር ዩሮና ዶላር ተመድቦለት ነው የሚንቀሳቀሰው።..( በነገራችን ላይ አሜሪካ-ዲሲ የከተሙ የብርሃነ ጋሻ ጃግሬዎች አሉ፤ አንዳንዶቹ በፖለቲካ አሳበው ጥገኝነት የጠየቁ ናቸው። ግን ስራቸው ፓርቲውን በምስጢር ማገልገል፡ በየጊዜው ኢትዮጲያውያንን እየሰለሉ ለብርሃነ መረጃ ማቀበል ነው፤ የአሜሪካ ዜግነት ወስደው ይህን እየሰሩ የሚገኙትን በተመለከተ በቀጣይ እመለስበታለው፤ ማንነታቸው ይጋለጣል።)…
.አደገኛው የፓርቲው ሰላይ ብርሃነ ከወራቶች በፊት በአሜሪካ በተከሰተው ሁኔታ ውስጥ ነበር፤ ይኸውም አቶ መለስ በተገኙበት ስብሰባ ላይ ጋዜጠኛ አበበ ገላው ጠ/ሚ/ሩን ሲቃወም …ብርሃነ በአዳራሹ ነበር። ከተቀመጠበት ተስፈንጥሮ በመነሳት ለጠ/ሚ/ሩ አጃቢዎች ትዕዛዝ ይሰጥ ነበር። ..

ከፓርቲው ሊቀመንበር ህልፈት በኋላ፥ ብርሃነ የፓርቲው የጀርባ « አጥንት » በመሆን ማሽከርከሩን ተያይዞታል። በተጨማሪ ከአሁኑ ጠ/ሚ/ር ጀርባ አድፍጦ የመሪነት ሚና መጫወቱን ቀጥሎበታል። በሌላም በኩል ሽማግሌው ስብሃት ነጋ በየመድረኩ የሚፈነጩት ያለምክንያት አይደለም፤ ይህን ሰው ይዘውና ተማምነው ነው። ምስጢሩ ደግሞ ሁለቱ ማለትም ብርሃነና ስብሃት በጋብቻ የተሳሰሩ በመሆናቸው ነው። በተጨማሪ የፌዴራል ደህንነት በፀጋይ በርሔ ነው የሚመራው ይባል እንጂ ከፍተኛ ሚና የሚጫወተው ብርሃነ ነው። ሁለቱም ከስብሃት ጋር በጋብቻ የተሳሰሩ ናቸው። …ሽማግሌው ስብሃት በአዜብ ዙሪያ « መፈንቅለ ኤፈርት » ደግሰው « ጥንስሱን » ተግባራዊ ለማድረግ ሩጫቸውን ገፍተውበታል። ..ብርሃነ በቀድሞ « ፍቅረኛው » ላይ የሽማግሌውን የሴራ በትር ያሳርፋል?…በቀጣይ የሚታይ ይሆናል፤..ብለዋል ምንጮች።

በሚቀጥለው መጣጥፍ.. በ40 ሚሊዮን ብር ህንፃ ስለተገነባለት የአዜብ ውሽማ…የምንለው ይኖራል፤

መነገር ያለበት ቁጥር አራት ከበልጅግ ዓሊ

$
0
0

ጉዳዩ – እሁድ ጃንዋሪ 13 ጠዋት ጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ በምገኝበት ወቅት ነው የተከሰተው። የዜጎቻችንን ቁጥር ስለበዛ (አበሻ የሚለውን ቃል መጠቀም ስለሚደብረኝ) ምን ይሆን ምክንያቱ ብዬ አካባቢውን እየቃኘሁ ፓስፖርቴን አሳይቼ ወደ ውስጥ ገባሁ። ሰሌዳው ላይ የጀርመን አየር መንገድ የሆነው ሉፍታንዛ ወደ አዲስ አበባ ጉዞ እንዳለውና መግቢያውም በበር ቁጥር 22 እንደሆነ ይገልፃል። በተጠቀሰው በር በኩል ሳልፍ በርከት ያሉ ተሳፋሪዎች ተመለከትኩ። አንድ አውሮፕላን ይህን ሁሉ ሰው ይዞ ይጓዛል? ራሴን በራሴ ጠየቅሁ። መልሱ ብዙም ሰላላስጨነቀኝ ወደ ፊት ቀጠልኩ። እዚህ አካባቢ የተመለከትኩት የዜጎቻችን ኮተት ማብዛት ፈገግ እያስደረገኝ ወደ ፊት ገሰገስኩ። የፍራንክፈርት አውሮፕላን ማረፊያ ለንደንን አያክል እንጂ ትልቅ ነው። በተለይ ኮተት ለተሸከመ ሰው አድካሚ የውስጥ ለውስጥ ጉዞ ይጠብቀዋል።

ለንደን የሚጓዘው አውሮፕላን መግቢያው በር ቁጥር 47 ላይ ስለነበረ ጉዞዬን ቀጠልኩ። በመንገድ ላይ ተጨማሪ ዜጎቻችን ነበሩ። አንዳንዶቹ የያዙትን ኮተት መጎተት አቅቷቸው እረፍት ለመውሰድ ኮተታቸውን ከራሳቸው ላይ አራግፈው ቆመዋል። ከተጓዦቹ ማህል አንዷ እንዲውም በጣም ገርማኛለች። ከፍ ያለ ታኮ ጫማ ተጫምታለች። ቦርሳ አንግታለች፣ ላፕ ቶፕ ተደግሟል፣ አነስ ያለ ቦርሳ ይጎተታል፣ ከውስጥ የተገዛ ውስኪ በከረጢት ተደርጎ ተይዟል። ልብ ብሎ ለተመለከታት ቤት የምትለቅ ትመስላለች። ይህ ዓይነት ሸክም በብዙው ተሳፋሪ ላይ የሚታይ ነው።

ሁሉንም መርዳት ሰለማይቻል ጉዞዬን ቀጠልኩ። በመንገድ አንደ ጠና ያሉ ሴት አገኘሁና መርዳት አለብኝ ብዬ ተጠጋሁ። በትግሪኛ አነጋገሩኝ። እንደማልችል ገልጽኩላቸው። አማራ ነህ አሉኝ። ዘር መቁጠር ሰለማይጥመኝ ዝም አልኩ። ዘር መቁጠር ብጀምርም ማንነቴን ለመግለጽ እስከ ሰባት ቤት ድረስ መዘዘር አለብኝ። ሸክሙ ሲቀላቸው አፋቸውን ቀለለው መሰለኝ ጥያቄውን ያዥጎደጉት ጀመር። እኔ ደግሞ ሸክሙ ስለበዛ ለመልሱ ቦታም አልሰጠሁት።

- አዲስ አበባ ነው እንዴ የምትሄደው ?
- አይደለም። እርስዎ አዲስ አበባ ነው የሚሄዱት?
- አዎ።
- ከሆነ ቦታ ተሳስተዋል። በር ቁጥር 22 ነው’ኮ መግቢያው።
- እሱ ሉፍታንዛ ነው። የእኛ አውሮፕላን 48 ቁጥር ላይ ነው።
- አሁን ግራ ገባኝ ወደ አስመራ የሚሄድ ሌላ አውሮፕላን ያለ መሰለኝ። <<የኛ>> ማለት ምን ማለት እንደሆነ አልገባኝም።

ወደ መሳፈሪያው በር ላይ ስደርስ ነገሩ ግልጽ እየሆነልኝ መጣ። አዲሱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 787(Boeing 787 Dreamliner) ፊቱን ወደ መስታወቱ አዙሮ ቆሟል። ከውጭ ሲያዩት ደስ ይላል። ወደ ሃገሬ ምድር የቀረብኩ መሰለኝ። እቃውን አስረክቤ ሴትየዋን በሉ በሰላም ይግቡ አልኩና ተለያየሁ።

በነገራችን ላይ ስለ ኢትዮጵያ አየር መንገድ የጀርመን ቅርንጫፍ ሳነሳ አንድ የማይረሳኝ ነገር አለ። የፍራንክፈርት ባቡር ጣቢያ የሚገኘው መሃል ከተማው አካባቢ ነው። ከባቡር ጣቢያው ፊት ለፊት የታወቀው ካይዘር (Kaiserstraße)በመባል የሚታወቀው ሴተኛ አዳሪዎች የሚገኙበት መንገድ ነው። ከዚህ መንገድ ጎን ደግሞ ሙንሽነር መንገድ የሚባል አለ። በሁለቱ መንገዶች መሃል አንድ ሕንጻ አለ። ድሮ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቢሮ የነበረው በዚህ ሕንፃ ላይ ነው። በሕንጻው ላይ በትልቁ Ethiopian የሚል ተጽፎ ነበር። እሱን ባየን ቁጥር ዜጎች የሃገራችን ስም በፍራንክፈርት እምብርት ላይ በመለጠፉ እንደሰት ነበር። አየር መንገዱ በደከመ ዘመን እንኳን ይህንን ቢሮ ይዞት ከርሟል። አሁን ግን በወያኔ ዘመን ይህ ጽሁፍ ከቦታው ወርዷል። የአየር መንገዱም ሥራ ለወያኔ ደጋፊዎች ተበታትኗል። ቢሮውን ተለቋል ። ያ እንደ ትልቅ የምንኮራበትም ጽሁፍ አሁን የለም። እዚያ ሕንጻ ላይ መለጠፉ ትልቅ አየር መንገዱን ማስታወቂያ ስለነበር ገርሞኛል። ( ፎቶው የተጠቀሰው ሕንጻ ነው)

ወደ ቦታዬ ለመሄድ እየተዘጋጀሁ ዞር ከማለቴ ፍራንክፈርት አውቀው የነበረ ሰው አሁን የአየር መንገዱ ቢሮ ከፈረሰ በኋላ ሥራውን ተረክቦ ይራወጣል። በእሱ እድገት እየተገረምኩ መንገደኛውን አንድ በአንድ መመለክት ጀመርኩ። ወደ አዲስ አበባ የሚጓዝ ሰው ከውጭ እንጂ ከውስጥ አጋጥሞኝ ስለማያውቅ ብዙ የሚያሰገርም አዳዲስ ክስተቶች በዜጎቻችን ላይ ተመልክቻለሁ።

ከሁሉ በፊት የተረዳሁት የሴት ዜጎቻችንን ፀጉር ረጅም መሆኑን ነበር። አንድም ቀምቀሞ ላገኝ አልቻልኩም። ሹርባም የለም። ኢትዮጵያውያን ሴቶች የጸጉር ቀለማቸው ምን ዓይነት ነው? ተብሎ ቢጠየቅ መልሱ ሊከብድ ይቻላል። ብሎንድ፣ ቢጫ፣ ነጭ፣ ቀይ ፣ ጥቁር በየዓይነቱ ጸጉር ተሰክቶል። ግሩም ማማር!መሽቀርቀር እንዲህ ነው። የሚገርመው ሁሉም ሴቶች አንድ አይነት የአንገት ሰበቃ ይዘዋል። ፈረንጆች ጸጉራቸውን ንፋስ አምጥቶ ፊታቸው ላይ ሲጥልባቸው ጸጉሩን ለመመለስ እንደሚደርጉት ዓይነት። የኛዎቹ ግን ጸጉር ወደ ፊት ቢመጣም ባይመጣም አንገት መስበቅ እንደ ልምድ አድርገውታል። እንደ ሥልጣኔ! እንደ ፈረንጅነት!

ጸጉሩን ተወት አድርጌ ወደ ታች ስመለከት የአለባበሱን ጉዳይ መናገር ያቅታል። ጉዞ ጀምሮ፣ ታኮ ጫማ አድርጎ መደናቀፉ የሚገርም ነው። የዝነጣው ዓይነት ግማሾቹ ከአውሮፕላን ሲወርዱ ሙሽራ የሚሆኑ ይመስላሉ። ማጥናቴን ቀጥዬ የእጅ ጥፍር ላይ ስደርስ ግን ግራ የሚያጋባ ነው። ሁሉም አዲስ ጥፍር አስክተዋል። ረጅም ለምንም ሥራ የማይመች። ያ ጥፍር ደግሞ ዜጎች ለለመድነው ምግብ ተስማሚ አይደለም። እንጀራን በሹካ ካልሞከርነው በቀር። ችግር የለም ለካ ክትፎ በቀንድ ማንኪያ መሆኑን ረስቼው ነው። ጥፍሩን ከማስነቀል እንጀራም በፈሳሽ መልክ ቢዘጋጅ ምን ነበረበት። ለቅምጥል ሲያንስ ነው።

ወደ ወንዶቹ ስዞር ደግሞ ጥቁር የቆዳ ጃኬት የታደለ ይመስላል። <<የተከበሩ>> ኢንቨስተሮቻችን መዳፈር አይሁንብኝ እንጂ የእጃቸው ስልክ አስሬ ነው የሚጮኸው። ዶላር ስንት ሆነ? ኢሮስ? መኪናው ደረሰ ወይ? ጠዋት ነው የምደርሰው መኪና ይጠብቀኝ? መኪናውን ለምን ሸጣችሁት ? አሁን በምን ልጠቀም ነው? ኮንቴነሮችን እስቶር አስገቧቸው! እኔ ስመጣ ነው የሚከፈቱት! ሆቴል ያዝልኝ! ። ጨኸት በጩኸት! ንግግሩ ለኛ ይሁን ለሌላው አይገባኝም። ግን ሁሉም እየጨኸ በሞባይል ያወራል። እድሜ አዲስ ጀርመን ለገባው የስልክ ካርድ – ላይካ። ስልክ እንደሆነ ረክሷል። ብዙዎቹ መነጽራቸው ወደ ላይ ወደራሳቸው ገፋ ተደርጓል። እዚህ እንደሁ ክረምት ነው ፀሐይ የለም። ምን አልባት ለአዲስ አበባ ይሆን ? ይሁን መቼስ።

ከሁሉ የገረመኝ አብረው የሚሄዱት ፈረንጆች ናቸው። ቱታ ለብሰው፣ አሮጌ የቴንስ ጫማ ተጫምተው ዘና ብለው ለመንገድ ተዘጋጅተዋል። ጥፍርም አላስተከሉ፣ አዲስ ልብስ አልገዙ፣ በታኮ ጫማም አልተደናቀፉ። ዜጎቻችን የሰባቱን ሰዓት ጉዞ የለበሱት፣ የተቀቡት፣ እንዳይበላሽ ሲጨነቁ ፈረንጆቹ በሰላም ሊደርሱ ነው። እንዲውም አንዱ ከላይ የሃገራችን መስቀል የተጠለፈበት ሸሚዝ ነው ያደረገው። ወይ እንደ ፈረንጅ መሆን።

ከተጓዦቹ ማህል አንዳንዶቹን በዓባይ ግድብ ቦንድ ሽያጭ ወቅት ፍራንክፈርት (Nordweststadt saalbau) በተደረገ ወቅት እየተንደረደሩ ሲገቡ በውጭ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ነበርንና ሰልፈኛው ሆዳም ሆዳም ብሎ ሲሰድባቸው አይቻቻዋለሁ። እነርሱም ሰላዩኝ ይህንን ካነበቡ ማንን ማለቴ እንደሆን ይገባቸዋል።

ወደ አውሮፕላኑ ሲገቡ የተለያየ ሁኔታ መገንዘብ ቻልኩ። አንዱ የባለቤትነት፣ ሌላው ደግሞ የእንግድነት። ቀደም ፣ ቀደም ብለው በድፍረት የሚሄዱ አሉበት፣ እንደ እንግዳ እየተሽኮረመሙ የሚገቡ አሉበት፣ እንደ እውነተኛ ነጋዴ የሚዝናኑ አሉበት፣ አስመሳይ ኢንቬስተሮችም አሉበት፣ ለመዘነጥ የሚሄዱ አሉበት፣ እውነተኛ የሃገር የቤተሰብ ፍቅር አንገብግቦት የሚሄድ አለበት፣። ሁሉም ድብልቅልቅ ያለ ነው። ስንቱ ይሆን ሱሱን ለማርካት የሚሄደው? ዋናው ጥያቄዬ እሱ ነበር።

ባለፈው ሳምንት በድረ ገፆች እየተዘዋወርኩ ሳነብ <<አዲስ አበባ በህገወጥ ልማዶችና የወሲብ ድርጊቶች እየተናጠች ነው !!! >> በሚል እርዕስ ያነበብኩት ትዝ አለኝ። እንዲህ ይላል፡ -

ግብረሰዶም ከሚገመተው በላይ በከፍተኛ መጠን እየተስፋፋ ነውአብዛኞቹ የከተማዋ ማሳጅ ቤቶች የወሲብ ንግድ እንደሚያጧጡፉ ታውቋል። ከ3600 በላይ ህገወጥ ልማዶችና የወሲብ ድርጊቶች የሚፈፀምባቸው ቤቶች አሉ። ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ፖሊሶችና ነጋዴዎች የአነቃቂ እፆች ተጠቃሚ ናቸው።በእርቃን ጭፈራ ቤቶች ደጃፍ ከሚቆሙ መኪኖች አብዛኛዎቹ የመንግስትና የንግድ ታርጋ የለጠፉ ናቸው። በአዲስ አበባ ህገወጥ ተግባራት የሚከናወኑባቸው ቤቶች በከፍተኛ መጠን እየጨመሩ ምጣታቸውንና ከተማዋ አደጋ ላይ እንደሆነች ሰሞኑን ይፋ የተደረገ ጥናት አረጋገጠ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በትናንትናው ዕለት ይፋ የተደረገው ጥናት “መጤ ባህሎችና ልማዳዊ ድርጊቶች በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በተለይም በወጣቶችና ሴቶች ላይ እያስከተሉት ያለው አሉታዊ ተጽእኖ” በሚል ርዕስ የተካሄደ ሲሆን ከ3600 በላይ ህገወጥ የወሲብ ድርጊት የሚፈፀምባቸው ቤቶች እንዳሉ ጠቁሟል፡፡

ይህ ሁሉ አስከፊ ድርጊት ወደ ሃገሪቱ እንዴት እንደተዛመተ መገመት ይቻላል። ጥናቱም <<መጤ ባህሎችና ልማዳዊ ድርጊቶች>> በሚል አስቀምጧቸዋል። አንዳንድ ዜጎቻችንን ከውጭ እየያዙ የሚገቡትን አንዳንድ መጥፎ ተግባራት በአላቸው ገንዘብ በመጠቀም በእርካሽ አገር ውስጥ ስሜታቸውን አርክተው ግን ወጣቱን ትውልድ ወደ ውጭ እናወጣኻለን በሚል አበላሹት። ፈረንጆቹም ቢሆኑ ከእንደዚህ ዓይነት ተግባር የጸዱ አይደሉም። ወያኔ ደግሞ እንዲዚህ ዓይነት ብኩን ዜጎች መብዛታቸው ያስደስተዋል እንጂ አያስከፋውም። ሊያምጽ የሚችለውን ወጣት በሱስ ማደነዝ ቀዳሚ ተግባሩ ነውና።

እነዚህ ሁሉ ሲመለሱ ደግሞ የሃገሪቷን ሁኔታ በተለያ መነጽር መመለከታቸው አይቀርም። ለመዘነጥ የሄደው ፣ስለዘናጩ ብዛት ይነግረናል፣ ነጋዴው ስለነጋዴው የተሳካ ኑሮ፣ ኢንቨስተሩም እንዲዚሁ። የዛችን ሃገር ፣ የዛን ሕዝቡ ሰቆቃ ለማየት ያልፈለገ አያየውምና ተንጋግተው እንደሄዱ፣ ተንጋግተው ይመለሳሉ። ይህ መንጋ እውነቱን እንዳያይ፣ አዲሱ ጸጉሩ ፣ አዲሱ ጥፍሩ ፣ አዲሱ እሱነቱ የጥንቱን ማንነቱ ይሸፍንበታል። ችግር ከሃገሪቱ ጠፍቷል ብሎ ይቀደዳል። የተቃዋሚዎችን ስህተት እያጎላ ይሰብካል። ይህ በወያኔ የተሰጠው ሃገርን የማጥፋት ፍቃድ እንዳይቀርበት በሚያምበት ሁሉ ይሳላል።

ይህ ዝርክርክ፣ ግትልትል ዜጋ ትንሽ አፍ እላፊ ከተናገረና የወያኔን ማንነት ካጋለጠ ይህ ኑ እንታያይ የዝንጣ ኑሮ ሊቀርበት ሰለሆነ እንደ ዘመኑ ቋንቋ ጎመን በጤና! እያለ እየዘፈነ ይኖራል። ከዛም አልፎ የግድብ ቦንድ ገዥ፣ ለመለስ ሞት በየኤምባሲው ደረት መቺ ቢሆን አይደንቅም። ወያኔም ይህ ሽቅቅርቅር የዲያስፖራ ቡድን የተቃዋሚውን ትግል ለማዳከም መርዙን ለመርጨት ይጠቀምበታል።

ወገን እስከመቼ ነው እንደዚህ የምንኖረው?

እነርሱ ከገቡ በኋላ የእኔም ተራ ደረሰና ወደ አውሮፕላናችን ገብተን የለንደን ጉዞ ። እና የስደት ኑሮ ቀጠለ ! አውሮፕላኑ ውስጥ በእውቀቱ ስዩምን አስታወስኩ። ቆዳ ጃኬትና መነጽር አጥቶ ይሆን? የሃገር ልብስ ለብሶ ለንደን ውስጥ ለኦለምፒክ የተጋበዘ ጊዜ በየስብሰባው የሚሄደው። በሚቀጥለው ሳገኘው እስቲ እጠይቀዋለሁ።

ሰለዛች ሃገር የሚያስብ ሁሉ በሰላም ይክረም!

ፍራንክፈርት
ጃንዋሪ 13/2013

Beljig.ali@gmail.com

በዜጎቻችን ላይ የሚፈጸመው ኢሰባዊ ድርጊት ይቁም!! በሰሜን አሜሪካና በአውሮጳ የአረና መድረክ ደጋፊዎች የጋራ መግለጫ

የጥፋት ራእይ፤የክህደት ሌጋሲ፤

የትግራይ ሌጆች ስሙኝ በናታችሁ በኤልን ሳምሶን


የሙት መንፈስ በዋልያ በክፍሉ ሁሴን

$
0
0

ይበል ይበል እንደማለት
ተመናምኖ ከነበረበት
ማንሰራራቱን በማየት
የዋልያውን መቦረቅ
ለአገሩ ስም ለማምጣት

እነሱ እቴ ምን በወጣቸው
ይልቅ አስቀናቸው
እንደወያኔዊ ልማዳቸው
እናም ተነሱ የሙት መንፈስ ሊጭኑበት
ሊያደርጉት ሽባ ሊያሽመደምዱት
እንዳያስጠራ ኢትዮጲያን
እንዳያስተባብር ሕዝቡን

ግን ይሳካል?
ዋልያ ሸብረክ ይላል?
የሙት መንፈስ ይቀበላል?
ደግሞስ ይረሳል?
ሙት ይዞ እንደሚሞት
ያውም ዘረኛ የሙት ሙት መንፈስ
እጅግ ርቆ መቀበር ያለበት ርኩስ

ካምፓላ ጃንዋሪ 25, 2013
Email;kiflukam@yahoo.com

ልማታዊው ኪስ አውላቂ ክንፉ አሰፋ

$
0
0

ማስታወሻ፡ ባለፉት ጊዚያት በጫጫርኳቸው አጫጭር ጽሁፎቼ፤ ገንቢ ትችቶች ለላካችሁልኝ አንባብያን ሁሉ ምስጋናዬ የላቀ ነው። በአንጻሩ አፍራሽ ትችቶች በስማችሁ ጽፋችሁ የላካችሁልኝ ወገኖችንም አደንቃለሁ። ነገር ግን በብእር ስም ራሳችሁን በመደበቅ፤ ነውር እና አሳፋሪ የሆነ የፈጠራ ስራ ለምትሰሩ ደግሞ፡ ልቦና ይስጣችሁ ከማለት ውጭ የምለው የለም። ሰውን ዘልፎ ለመጻፍ እንቅልፋቸውን የሚያጡ ሰዎችን ፈረንጆቹ ‘ባለ ትንሽ ጭንቅላቶች’ ይሏቸዋል። ችግሩ ከአስተዳደግ ጉድለት፣ ከአስተሳሰብ ድህነት እና በራስ ካለመተማመን የሚመጣ የስነልቦና በሽታ ነው።

የ ‘ህዳሴው ቦንድ’ ግዢ ግርግር ሞቅ ብሎ በነበረበት ሰሞን ይነገር የነበረ አነድ ቀልድ አለ። የ‘ማረሚያ’ ቤት ፖሊሶች እና ታጋዮች 500 ብር በሰረቀ ሌባ ላይ ውይይት ያደርሉ። ተከሳሹ ብሩን ያላግባብ ይስረቅ እንጂ በገንዘቡ የህዳሴውን ቦንድ መግዛቱ ነው ጉዳዩን ለውይይት የዳረገው። ይህ ሌባ መታሰር የለበትም የሚሉት ታጋዮች፡ ለፖሊሶቹ ያቀረቡት መከራከሪያ ነጥብ ልማታዊ ሃሳብ ነበር። እንዲህ ነበር ያሉት፡ ‘ይህ ልማታዊ ኪስ አውላቂ ነው። እንዲያውም እንደዚህ አይነቶቹን ሌቦች የበለጠ እንዲሰሩ ማበረታታት ነው ያለብን።…’ ሁሉም በዚህ ሃሳብ ተስማሙና ሌባውን በያዘው ልማታዊ ተግባር የበለጠ እንዲሰራበት መክረው ለቀቁት።

ይህ እነግዲህ ቀልድ ነው። ቀልድ ደግሞ በመጠኑም ቢሆን የእውነታ ነጸብራቅ እነጂ ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ክስተት አይደለም። ‘ልማታዊ’ የሚለው ቃል ትርጉሙ ተዛብቶ ምን ያህል እየተቀለደበት መሆኑን ከዚህ ቀልድ ግንዛቤ እንወስዳለን። በዚህ ላይ ወደሗላ እመለስበታለሁ።

ቀልዱን በቀልድ እንለፈውና አንድ ምሽት በኢ.ቲ.ቪ. ያየሁትን እውነታ ላውጋችሁ። ኢ.ቲ.ቪ. በሚያዘጋጀው የትምህርት ቤቶች ጥያቄና መልስ ውድድር ላይ ‘ቦንድ ማለት ምን ማለት ነው?’ የሚል የ500 ብር ጥያቄ ቀርቦ ነበር። ከተወዳዳሪዎቹ አንዱ መልስ ሰጠ። እነዲህ ሲል፣ “ቦንድ ማለት፡ መንግስት በህዝብ እጅ ያለውን ጥሬ ገንዘብ ለአንድ አላማ ወደ ባንክ እንዲገባ ለማድረግ የሚጠቀመበት ዘዴ ነው።”

“ጥያቄው በትክክል ተመልሷል!” የሚል መልስ ነበር ህዘብ ከጠያቂ ጋዜጠኛው ይጠብቅ የነበረው። ጠያቂው ግን ተወዳዳሪው ትክክል እንዳልመለሰ ተናግሮ፡ ጥያቄውን ተመልካቾች እንዲመልሱለት ጋበዘ። አነዱ ‘ልማታዊ’ ተመልካች ከመሃል ተነስቶ “ትክክል” የተባለለትን መልስ ሰጠ። መልሱ ይህ ነበር፣ “ቦንድ ማለት ወለዱ ከግብር ነጻ የሆነ የቁጠባ ዘዴ ነው። ”

በዚህ ልማታዊ ጋዜጠኛ የተሳሳተ የቦንድ ትርጉም ተወዳዳሪ ተማሪው ብቻ ሳይሆን፤ የቴሌቭዥኑ ታዳሚዎችና ተመልካቾችም በሙሉ ቀልጠዋል። ይህ ጥያቄ በትምህርት ቤት ፈተና ላይ ቢመጣ ተመሳሳይ ‘ልማታዊ’ መልስ ያልሰጡ ተማሪዎች አያልፉም ማለት ነው።

በአጭር አነጋገር ቦንድ ማለት፤ ህዝቡ እንዲቆጥብ ታስቦ ሳይሆን መንግስት የገንዘብ እጥረት ሲኖርበት ከህዘብ ላይ በብድር መልክ የሚሰበስበው ገንዘብ ማለት ነው። ቦንድ መሸጥ አዲስ ነገርም አይደለም። የምእራቡ አለም መንግስታትም በአንደኛው እና በሁለተኛው የአለም ጦርነቶች ወቅት የገንዘብ እጥረታቸውን ለመሸፈን ለሕዝብ ቦንድ ይሸጡ ነበር። ዩናይትድ ስቴትስ ለሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት ገንዘብ ስላስፈለገ፤ ፕሬዚዳንት ሩዝቬልት የተጠቀሙት ዘዴ ‘የነጻነት ቦንድ’ ያሉትን ኩፖን በመሸጥ ነበር። ጀርመን፣ እንግሊዝና ካናዳም በተሳካለት የጦር ቦንድ ሽያጭ የሚጠቀሱ ሃገሮች ናቸው።

ወደ ዋናው ነጥብ ስንገባ ልማታዊ መንግስት የሚለው ጽንሰ-ሃሳብ የመነጨው በ20ኛው ክፍለዘመን መገባደጃ አካባቢ ከነበሩ የምስራቅ ኤሽያ ሃገሮች ነው። እነዚህ በወቅቱ እጀግ ደካማ የሚባሉ የኤሽያ ሀገሮች፡ በመንግስት የሚመራ የማክሮ ኢኮኖሚ እቀድ በማውጣት የሃገራቸውን ኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ስልጣን አጥብቀው በመያዝ ወደ ምጣኔ ሃብት እድገት ያመሩ ናቸው።

ልማታዊ ነን የሚሉ እነዚህ መንግስታት የብዙሃን ፓረቲ ዲሞክራሲን፣ የፕሬስ ነጻነትንና የመሳሰሉ መብቶቸን በመጠኑም ቢሆን ያፈኑ ቢሆኑም ‘ልማት ከሰብአዊ መብት ይቀድማል!’ ከሚሉት ከኛዎቹ ገዚዎች ፍጹም የተለዩ ናቸው። ልማታዊ መንግስታት ከህዝባቸው ጋር ሆድና ጀረባ በመሆን ከህዝባቸው ጋር ጦርነት ሲገጥሙ አላየንም። እነዚህ ሃገሮች ትኩረታቸውን በሙሉ በኢኮኖሚ እድገት ላይ በማድረግ ህዝባቸው በምግብ ራሱን እንዲችል ከማድርግ አልፈው የአብላጫው ህዝብ የኑሮ ሁኔታ በእጀጉ እንዲሻሻል ረድተዋል።

ዛሬ የደቡብ ምስራቅ እሺያ ሀገሮች እና የቻይና ዜጎች የፖለቲካ ተሳትፏቸው እጅግ ዝቅተኛ ይሁን እነጂ የኑሮ ደረጃቸው በእጅጉ ተሻሽሎ እናያለን። በአንጻሩ በልማታዊው የኢህአዴግ ስርአት በግልጽ የማይታይ የሁለት አሃዝ እድገት መጠን ከማውራት ያላለፈ እድግት ባሻገር የህዝቡ የኑሮ ደረጃ ሲብስ እንጂ ሲሻሻል አይታይም። በልማታዊ መንግስት ስም 80 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዘብ ከነጻነቱም፣ ከኑሮውም ሳይሆን አሁንም በባሰ የኑሮ ጉስቁልና ውስጥ ይገኛል።

በቅርብ ከኢትዮጵያ የመጣ አንድ ሰው፡ የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ ከአንድ የእግር ኳስ ስታዲየም ጋር በማስመሰል ይገልጸዋል። በአንድ የእግር ኳስ ስታዲየም ውስጥ ያሉ ሰዎች በሶስት ምድቦች ይከፈላሉ፤ ተጫዋቾች፣ አጫዋቾች እና ተመልካቾች። የኢትዮጵያም ህዝብ እንደዚሁ በሶስት ምድብ ይከፈላል። ባለስልጣናቱ አጫዋቾች፣ አጫፋሪዎቹ (ለባለስልጣናቱ አየር ባየር ቢዝነስ የሚሰሩት) ተጫዋቾች – ሲሆኑ ህዝቡ ደግሞ የዚህ ጨዋታ ተመልካች ሆኗል።

ሕዝቡ የሃገር ሃብት ነው። ህዝብን ሳያሳትፉ ስለ እድገት ማውራት ከቶውንም የሚቻል አይሆንም። በተለይ ደግሞ ዲያስፖራውን። የምስራቅ ኤሸያ እድገት ሚስጥር ዲያስፖራው መጠነ ሰፊ ገንዘብ እና እውቀትቱን ይዞ በሃገሩ መስራት መቻሉ ነበር።

ህወሃቶች እንደሚሉት ‘ቶክሲክ’ (መርዘኛ) ዲያስፖራ እያሉ የሃገር ሀብት የሆነውን የዲያስፖራ ሃይል ቢሳደቡ ኖሮ እስያውያን እዚህ ደረጃ ባልደረሱ ነበር። በተማረ የሰው ሃይል፣ በቴክኖሎጂ እና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ውስጥ ሆኖ ዲያስፖራውን በጅምላ ጠላት ማድረግ ከእብደት ውጭ ሌላ ትርጉም አይሰጠውም። የኢትዮጵያ ዲያስፖራ የሰራው ወንጀል ቢኖር ‘ሰብአዊ መብት በሃገሪቱ ይከበር!’ ብሎ መጮሁ ብቻ ነው።

በአንድ ሃገር ኢኮኖሚ ላይ የዲያስፖራውን ሚና ለማሳየት ምሳሌ ሊሆነን የሚችለው የሲንጋፖር የእድገት ታሪክ ነው። ሲንጋፖር ከታላቋ ብሪታንያ ቅኝ ግዛት ነጻ በወጣች ማግስት ህዝቧ በድህነት ውስጥ ነበር። ሲንጋፖር አንዳች የተፈጥሮ ሃብት የሌላት ፍጹም ድሃ የሆነች ደሴት ነበረች። ከዚህ ድህነቷ ለመላቀቅ የነበራት አማራጭ የተማረ የሰው ሃይሏን መጠቀም ብቻ ነበር። አንድ የሲነጋፖር ዜጋ እነዲህ ብሎ ነበር ያጫወተኝ።

‘ሲንጋፖር በተፈጥሮ ሃብት ያልታደለች የትናንሸ ደሴቶች ክምችት ነች። ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነጻ እንደወጣች የመጠጥ ውሃ እንኳን አልነበራትም። በወቅቱ የተረፈን ጭንቅላታችን ብቻ ነበር – የተማረ የዲያስፖራ ሃይል። ከባዶ በመነሳት ሲንጋፖር አሁን ያለችበት ደረጃ እንድትደርስ ያደረጉት እውቅት እና ቴክኖሎጂ ይዘው የመጡ የዲያስፖራ ምሁራን ናቸው።’

‘የሲነጋፖር ምሁራን ከጎረቤት ሃገር ከማሌዢያ የሚፈሰውን ቆሻሻ ውሃ በቱቦ አማካይነት ወደ ሃገሪቱ እንዲገባ ካደረጉ በሗላ፡ ውሃውን እያጣሩ ለማሌዥያ መልሰው መሸጥ ጀመሩ።…’

የእውቀት ኢኮኖሚን የያዘ የዲያስፖራ ሃይልዋን ያልናቀችው ሲንጋፖር ዛሬ የኢንዱስተሪ ሃገር ናት። አንባገነንነቱ እና ሙስናው እነደተጠበቀ ሆኖ፡ ይህቺ ደሴት የበርካታ ሀገሮች የእድገት ምሳሌ (ሞዴል) ለመሆንም በቅታለች።

የኤርትራው ኢሳያስ አፈወረቂ እንኳን፤ በትረ ስልጣናቸውን የጨበጡ ሰሞን ‘ኤርትራን የአፍሪካ ሲንጋፖር እናደርጋታለን።’ ብለው ነበር። ይልቁንም ከ21 አመታት በሗላ ኢሳያስ አፈወርቂ ኤርትራን ሲን ጋፖር ሳይሆን ‘ሲንግል ኤንድ ፑር’ አደረጓት እያሉ ተቺዎች ይቀልዱባቸዋል። የኢትዮጵያም የእድገት ማነቆ ምስጢሩ በስብአዊ መብት አፈናው ሳቢያ ለተማረ የሰው ሃይል እና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ቦታ ካለመስጠቱ ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ልማታዊ መንግስት ነን ይበሉ እነጂ፤ የልማታዊነት ትርጉሙ እንኳን የገባቸው አይመስልም። አሁን የተያዘው የኮብል ሰቶን ልማትን እንመልከት። የኮበልስቶን ስራን ሊሰራ የሚችል ያልሰለጠነ የሰው ሃይል በገፍ ባለበት ሃገር፤ በባችለር እና በማስተርስ ዲግሪ ከዩኒቨርሲቲ የሚመረቅ ዜጋ ሁሉ ድንጋይ መፍለጥ፣ መጥረብ እና መዘርጋት እንዲሰራ መደረጉ ለብዙዎች እንግዳ ነገር ነው። የተማረ እና የሰለጠነ የሰው ሃይልን በጉልበት ስራ የሚያሰማራ ልማታዊ መንግስት በኢትዮጵያ ብቻ ነው የታየው። አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝም በመገናኛ ብዙሃን ቀርበው በባችለር እና በማስተርስ ዲግሪ ከዩኒቨርሲቲ ለሚመረቁ ተማሪዎች የኮብል ሰቶን ስራ አዋጭ ስራ መሆኑን ሲናገሩ ተደምጠዋል። አዋጪ ስራ መሆን አንድ ነገር ነው። የሃገር እድገት ደግሞ ሌላ። የሚያሳዝነው አማራጭ ያጡ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን የዚህ የተሳሳተ ልማታዊ አስተሳሰብ ሰለባ መሆናቸው ብቻ ነው።

የህንጻ እን የከተማ መንገድ ግንባታ የከተማን ውበት ሊያሳምር ይችል ይሆናል። በህንጻ ግንባታ ከተማ ልትቀየር ትችልም ይሆናል። ይህ ግን ከሃገር እድገትና ከዜጎች የኑሮ መለወጥ ጋር ፈጽሞ ሊገናኝ አይችልም። ምሁራኑ ድንጋይ ሲፈልጡ፣ ሲጠርቡ እና ሲያነጥፉ፡ የነሱን የሙያ ቦታ ያልተማሩ ካድሬዎች እነዲይዙት ማድረግ። ሃገር በዚህ አይነት ሂደት ታድጋለች የሚል የልማታዊ መንግስት ፍልስፍና የለም። ይህ እንዲያውም በልማት ስም የሚሰራ መንግስታዊ ወንጀል ነው። ኪስ አውልቆ ቦንድ ከመግዛት የማይተናነስ ወነጀል።

የጀግና ልጅ ጀግና እንጂ የእሳት ልጅ አመድ አይሆንም ከበላይ ገሰሰ

ታደሰ በዛብህ የመርካቶው አይጥ ክፍል ሁለት በልጅግ ዓሊ

ጂሃዳዊ እርምጃን በኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠሩት ሲጋለጡ ዳኛቸው ቢያድግልኝ

የማለዳ ወግ . . . የ”ጃሃዳዊ ሐረካት”ዘጋቢ ፊልም መዘዝ ! ለማየት የጓጓነው ዘጋቢ ፊልም . . . ነቢዩ ሲራክ -ከሳውዲ አረቢያ

የህወሓት/ኢህአዴግን አሸባሪ አገዛዝ በጋራ እንታገል (ሸንጎ)


የነብይ ያለህ የጎንቻው

ኢሕ አድግ ከመቻቻል ይልቅ መጃጃልን መረጠ ከትዝብት አድማሱ

ለቅሶ ሳቅ –ሳቅ ለቅሶ አሥራደው (ከፈረንሳይ)

የካቲት 1966 39ኛ ዓመት መታሰቢያና እና ያ ትውልድ ተቋም

የዕምነትና የታሪክ በዓቶቻችን አይደፈሩ!

Viewing all 1809 articles
Browse latest View live


<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>