በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነው እና ሰላማዊ ትግል 101 በሚል ስያሜ የሚጠራው አዲስ መጽሐፍ በኢትዮጵያ ገበያ ላይ ውሏል። ሰላማዊ ትግል 101 የተዘጋጀው በሰላማዊ ትግል የኢትዮጵያን ህዝብ የመንግስት እና የአገሩ ባለቤት በማድረግ ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲ መውሰድ የሚሹ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በተለይም ወጣቱ ኢትዮጵያዊ የሆነ ትምህርታዊ የመወያያ መጽሐፍ እንዲኖረው ታቅዶ ነው። ስለዚህ ሰላማዊ ትግል 101 በአቀራረቡም ሆነ በይዘቱ የውጭ አገር ቅጅ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ነው።
ሰላማዊ ትግል 101 ከአልበርት አነስታይን ሰላማዊ ትግል ምርምር ተቋም ዘመናዊ ስራዎች ውስጥ ጠቃሚዎቹን አቅልሎ አቅርቧል። መጽሐፉ የመንግስት ስልጣን ባለቤት ህዝብ ነው የሚለው አባባል መሰረቱ የፖለቲካ ኃይል ምንጮች ባለቤትነቱ መሆኑን፣ የፖለቲካ ኃይል ድጋፍ ምሶሶዎች ሚና ምን እንደሆነ፣ የሲቪክ ድርጅቶች ሚና፣ ሴቶች ለሰላማዊ ትግል ያላቸው ተፈጥሮዋዊ ቅርበት፣ የሰላማዊ ትግል መፈጸሚያ መሳሪያዎች እነማን እንደሆኑ፣ ሰላማዊ ትግል ህዝብን እንዴት የራሱ ነፃ አውጭ እንደሚያደርገው እና የመሳሰሉትን የሰላም ትግል መሰረታዊ ጽንሰ አሳቦች አቅልሎ ይተነትናል።
መጽሐፉ ስለ ሰላማዊ ትግል እድገት ታሪክ ይተርካል። ይህን ሲያደርግ ግን ከክርስቶስ ልደት ቀደም ብሎ ጀምሮ የሰው ልጅ በየክፍለ ዘመኑ በፍልስፍና እና በንድፈ አሳብ ደረጃ ካደረገው እድገት ጎን ለጎን የየዘመኑን ታሪካችንን በትይዩ በማመላከት አንባቢን ንፅፅራዊ ግንዛቤ ለማስጨበጥም ይሞክራል።
በኃይል የሚፈጸመው የመንግስት ሽግግር ባህላችን መለወጥ እንዳለበት ለማስረዳት ሰላማዊ ትግል 101 ከአክሱም ዘመን አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ በተደረጉ የመንግስት ሽግግሮች የሆነውን፣ የተደረገውን እና የተፈጸመውን አሳዛኝ ታሪካችንን በአጭሩ ይተርካል። ሰላማዊ ትግል 101 ዴሞክራሲ በዳበረበት በምዕራቡ አለም እና አምባገነኖች በሚገዟቸው አገሮች ስለሚደረገው ምርጫ ልዩነት ዘርዘር አድርጎ አቅርቧል። የአሜሪካን፣ የግብጽን፣ የሰርቢያንና የዝምባቡዌን ሰላማዊ ትግልና ምርጫ ልምዶችም በየምዕራፉ ተንትኗል። ከኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ ለ80 አመታት ያህል በኢትዮጵያ የተደረጉትን ምርጫዎችም ይገመግማል ሰላማዊ ትግል 101።
ሰላማዊ ትግል 101 መጽሐፍ 232 ገጾች አሉት። ከፍ ብለው ከተጠቀሱት ቁም ነገሮች በተጨማሪ ብዙ ጠቃሚ ነገሮችን ይዞ በኢትዮጵያ ገበያ ላይ ቀርቧል። በቅርቡ ደግሞ በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓ እና በአውስትራሊያ ገበያዎች ይቀርባል። መልካም ንባብ። መልካም ውይይት።
↧
አዲስ ዜና –ሰላማዊ ትግል 101 መጽሐፍ በግርማ ሞገስ
↧