Quantcast
Channel: Abugida Ethiopian American Amharic Web Page
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1809

የኢትዮጵያ መለኮታዊ ዕጣ፡ ይድረስ ለአቤል ጋሼ ከጃፋር ሐሰን

$
0
0

የኢትዮጵያ መለኮታዊ ዕጣ በሚል ርዕስ የተጻፈ ጽሑፍ በአቡጊዳ http://www.abugidainfo.com/amharic/index.php/10541#commentsና http://quatero.net/pdf/queen-azeb-and-ethiopia.pdf በቋጠሮ ድረ-ገፆች ባለፈው የካቲት ወር ለንባብ በቅቷል፡፡ ጽሑፉ በ75 ገፆች የቀረበና በጥልቀት የተዘጋጀ በመሆኑ ለመረዳትና የተሰጠውን ተስፋ ለመጠበቅ ጊዜ የሚፈልግ ነው፡፡ ጸሐፊው አቶ አቤል ጋሼ ላደረገው እንደዚህ ያለ ሰፊ ጥናት ምስጋና ይገባዋል፡፡ በአቡጊዳ ላይ አስተያየት ከሰጡት አራት ሰዎች መካከል ቢያንስ ሁለቱ ስለ ጽሑፉ ጥሩ ብለዋልና በጽሐፉ ላይ የአስተያየት ሰጪዎችንም ተሳትፎ ሳናደንቅ አናልፍም፡፡

የአገራችን ኢትዮጵያ መለኮታዊ እጣ ሁላችንንም የሚያነጋግርና እንድናስብበት የሚገባ ነው፡፡ የምንችለውንም ነገር ሁሉ በምንችለው አቅም ልንሰነዘር ሊያነሳሳን ይገባል፡፡ እኔም በጉዳዩ ላይ በአቶ አቤል ጽሑፍ ላይ ተንተርሼ ጥቂት ነገሮችን ለመናገር ለአቶ አቤልም ጋሼም ገንቢ የሆነ ማሳሰቢያ ለመስጠት የሚከተሉትን ሃሳቦች አስፍሬአለሁ፡፡

የኢትዮጵያ መለኮታዊ ዕጣ – እንደ አቤል ጋሼ

የኢትዮጵያን መለኮታዊ ዕጣ በሰፊው የሚያብራራው ጽሑፍ ብዙ ነገሮችን ያካተተና በተለይም መንፈሳዊ የተደረገ እንዲሁም ጸሐፊው እንዳቀረበው በንግስተ ዓዜብ ፍርድ ላይ የተሽከረከረ ነው፡፡ ንግስተ ዓዜብ በሬጋን ሕንፃ ፍርድ እንደጀመረች መንፈሳዊ የስልጣን ሽግግርም ከቀዳማዊት ዓዜብ ወደ ንግስተ ዓዜብ እንተደላለፈ ያስረዳናል፡፡ እነዚህን ነገሮች ሁሉ በጊዜው የምናያቸው ቢሆንም ነገሮች በጣም ምስጢሮች በመሆናቸው በፊደላት ቀመር ስሌት እየተሰሉ ትርጉማቸው እንደሚፍለቀለቅ ተመልክተናል፡፡

በጣም ግሩም በሆነም መልኩ ከ70ዎቹ ገፆች ጀምሮ ኢትዮጵያ አገራችን ገናና ሆና ሁሉም ዓለም በግዕዝ መንፈስ እንደሚሰማት ተነግሮልናል፡፡ ይሁንልን! ይበጅልን! ያርግልን! አገራችን ትቅደም! ትውጣ! በማለት ሁላችንም ያንን ጊዜ መጠበቅ ይኖርብናል፡፡

የአቤልን ጽሑፍ ቀስ ብሎ የሚያነብ ሰው ግን ብዙ ጥያቄ ይፈጠርበታል፡፡ የአገራችን የኢትዮጵያ ዕጣ እንዲህ ውስብስብና አስቸጋሪ የሆነበት ምክንያት ምንድነው? አገራችን ኢትዮጵያ ከሌላው አገር ሕዝብ የተለየ የቃል ኪዳንና የምስጢር አገር ያረጋት ማስረጃው ምንድነው? አንድ አገር እንደዚህ ዓይነት ውስብስብ የኮድና የምስጢር ቱባዎች ውስጥ የመግባቷ አስፈላጊነትስ በእርግጥ ምኑ ላይ ነው? ወ.ዘ.ተ የሚሉ ጥያቄዎች ይፈጠሩበታል፡፡ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ጽሑፉን በእርጋታ አንብቤ የሚከተሉት ነገሮች አልገባ ስላሉኝ እንደገና እንዲታዩ አንስቻቸው የአገሬን ዕጣ በተመለከተ አጭር ማሳሰቢያ መስጠት ጉጉት አደረብኝ፡፡

1ኛ፡ የፊደሎች የቁጥር ዋጋ

ጸሐፊው ለአማርኛ ፊደሎች የቁጥር ዋጋ በድንገት በማዘጋጀት የአንዳንድ ቃላትን የቁጥር ስሌት ለመስጠትና በዚያም ላይ በመመስረት ትርጉምና ትንታኔ አድርጓል፡፡ ነገሩ እውነትነትና ተጨባጭነት ቢኖረው ጥሩ ነበር ነገር ግን እውነትነቱና ተጨባጭ ውጤት የሚያመጣ መሆኑ ጥያቄ ያስነሳል ስለዚህም ይህ የአቶ አቤል አካሄድ በተወሰኑ ነጥቦች ዙሪያ እንደገና ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ምክንያቱም በጣም ኋላ የቀረ የNumerology ጥንቆላ ጉተታ ውስጥ ኢትዮጵያውያን እንዲመለሱ የሚያዘናጋ ነውና፡፡

ከዚህም ባሻገር የጸሐፊው የፈደል ቀመሮች ውስጣዊ ችግሮች አሏቸው፡፡ ችግሮቹን ለማስወገድ ደግሞ ግልፅ የሆነን ማብራሪያ በግርጌ ማስታዎሻ ላይ እንኳን አልተተወልንም፡፡ እኔ እንኳን ከታዘብኩት “ፊደል “”ሸ””ን በተመለከተ ችግር አጋጥሞኛል፡፡

ለመሆኑ ፊደል “ሸ” የት ጠፋች?

በማስታዎሻ 3 ገፅ 8 በፊደል ቀመራህ ውስጥ ሁሉንም የአማርኛ ፊደሎች ተጠቅመህ ነገር ግን ፊደል “ሸ”ን ትተሃታል፡፡ አቶ አቤል ምናልባት እረስተሃት ይሆናል! ወይንም ከ26 ቀመራህ ጋር አልሄድ ብላህ አስወግደሃት ይሆናል! ወይንም እንዲያው መንፈስ እድርገሃት ጠልተሃት ይሆናል! ወይንም የባዕድ ፊደል አድርገሃት ይሆናል! ብቻ የራስህ ምክንያት እንደሚኖርህ ምንም አልጠራጠርም፡፡ በገፅ 48 ላይ ፊደል “ሰ”ን እና “ሸ”ን በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ ቢኖርም ፊደል “ሸ”ን ከፊደል ተራ ቁጥር ውስጥ ማስወጣትህን አልነገርከንም፡፡ አቶ አቤል ይህንን ያደረግህበት ተጨባጭ ምክንያት ካለህ ለሁላችንም ብትገልጥና የፊደሎቻችንንም መንፈሳም ሆነ ስጋዊ ሚስጢር የበለጠ ብታስተምረን ጥሩ ነበር፡፡ ለማንኛውም ፊደል “ሸ”ን በጽሑፍህ ውስጥ ምናልባት አልተጠቀምክባት ይሆናል በማለት “Randomly” አንድ ገፅ ወሰድሁና ፊደሏን መፈለግ ጀምርሁ፣ ለምሳሌም ያህል በወሰድኩት “ራንደም ገፅ” በገፅ 16 ላይ አምስት ጊዜ በሚከተሉት ቃላት ማለትም “ሙሽራው፣ ሙሽራዋ፣ በትንፋሽ፣ ተሻግረን፣ እና ያሻል” በሚሉት ቃላት ውስጥ ትገኛለች፡፡
የራስህም የአባት ስም በ-ጋሼ ውስጥም በቀመራህ ውስጥ ያጎደልካት ፊደል “ሸ” ትገኛለች፣ የራስህንና የአባትህን ስም ፊደላት በአንድ ላይ የቀመር ትንተና ውስጥ ማስገባት ቢያስፈልግህ እንዲያው ምን ልታደርግ ነው? ስምህን በአዋጅ ትቀይር ይሆን ወይንስ ከቀመር ነፃ ማለትም ለ”ሸ” ፊደል ዜሮ ቁጥር ትሰጥ ይሆንን? ወይንስ ሰ ማለት ሸ ነው ልትለን ይሆን? እኔ አላውቅም!!

ይህንን ሁሉ የተናገርኩበት ምክንያት ከፊደል “ቀ” ጀምሮ የሰጠኻቸው የቁጥር ዋጋዎች ሁሉ ስህተቶች በመሆናቸው በዚህ ጽሑፍ ላይ የሰጠኻቸው የቀመር ዋጋዎች ሁሉ የተዛቡ መሆናቸውን እንድትረዳ ነው፡፡ ይህ ማስረጃ ደግሞ ከውጭ የመጣ ሳይሆን በራስህ ጽሑፍ ውስጥ ውስጣዊ የሆነና የመሳሳትህ የራስህ ማስረጃ ነው፡፡ ስለዚህም አንድ ምሳሌን ብቻ በመውሰድ ምን ያህል ተሳስተህ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ (ጽሑፍህን ያነበቡትን ማለቴ ነው) እንዳሳሳትህ “እግዚእ” ለሚለው ቃል የሰጠኸውን ቀመር ድምር እንመልከት፡፡ በዚያው በገፅ 8 ላይ የቀመር ስሌት ምሳሌህ አድርገህ በጥሩ ሁኔታ አስቀምጠኸዋል “360 ዲግሪ፣ ክብ መለኪያ” ብለኸዋል፡፡ እንግዲህ እንዳልከው ቢሆን በጣም ጥሩ ነበር ነገር ግን ፊደል “ሸ”ን የምታስወግድበት ምንም አሳማኝ ማስረጃ ስለሌለህ ወይንም ደግሞ ቢያንስ በአሁኑ ወቅት ስላልሰጠኸን ፊደል “ሸ”ን በተገቢ ቦታዋ ላይ ብናስቀምጥና “እግዚእ”ን ብናሰላው የሚመጣው ውጤት አንተ በገፅ 8 መጨረሻ ላይ ከሰጠኸን የተለየና እንደሚከተለው ነው፡-

ሀ. ፊደል “ሸ” የጎደለችበት ያንተ ስሌት አ = 40፣ ገ = 200፣ ዘ = 80 እና አ = 40፣ በድምሩ 360 ክብ ዲግሪ
ለ. ፊደል “ሸ” በትክክለኛ ቦታዋ ብትቀመጥ የሚሰጠን ስሌት አ = 50፤ ገ = 300፤ ዘ = 90፤ አ = 50 ናቸው በመሆኑም ድምሩ ደግሞ 490 ይመጣል፡፡
እራስህን በጣም ትክክለኛ እንደሆነ ሰው አድርገህ በገፅ 8 ማጠቃለያ ላይ ከሰጠኸው የክብነት ትርጉም ጋር ልዩነቱን ቆም ብለህ እንድታሰላው አሳስብሃለሁ፡፡
በጽሑፍህ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ብዙ ስህተቶች አሉ፤ ሁሉንም ለማሰስ መሄድ ስራ ያስፈታል ስለዚህ እንደገና እንድትሄድበትና በአቡጊዳና በቋጠሮ ድረ-ገፅ ላይ ጽሑፍህን አግኝተው ላነበቡት ኢትዮጵያውያን የማረሚያ ይቅርታ እንድታስተላልፍ በኢትዮጵያዊ የወንድምነት ስሜት እመክርሃለሁኝ፡፡

2ኛ፡ ለፕሮፌሰር መስፍን በጻፍከው ላይ

የሁላችንንም አስተማሪና ምሳሌ ፕሮፌሰር መስፍንን አክብረህ ለማበረታታት መጻፍህ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ጥቂት ነገሮች ከእውነታ ውጭ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጰያን ከሌሎች አገሮች የተለየች የቃል ኪዳን አገር አድርገህ ማስቀመጥህ ትክክል አይደለም፡፡ በሆሴዕ ትንቢት 9.7 ላይ ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ አረዳድህም የተዛባ ነው፡፡ በትንቢተ ሆሴዕ ላይ የተጠቀሰቸው ኢትዮጵያ በጥሩ መልኩ ሳይሆን በጣም በመጥፎ መልኩ ነው፤ ከእስራኤል ልጆች ይልቅ በተሻለና በተወደደ መንገድ ሳይሆን መጥፎ ምሳሌ ሆና ነው፡፡ የትንቢተ ሆሴዕ ጥቅስ ትክክለኛ ትርጉም የሚሆነው እንደሚከተለው ነው፡- አሕዛብ የሆነችው ኢትዮጵያን ተፀይፌ እንደማየው እናንተንም (እስራኤላውያንንም) የቃል ኪዳን ልጆችን በኃጢአታችሁ ምክንያት እንደዚያ ተፀይፌ አያችኋለሁ፣ እፈርድባችኋለሁ የሚል ነው እንጂ ኢትዮጵያ ከእናንተ የተሻለ የተወደደች ናት የሚል ሐሳብ የለውም፡፡ አንተ እንደምትለው ቢሆን ኖሮ ጥሩና ጮቤ የሚያስረግጥ ነበር፣ ነገር ግን አይደለም፡፡
አየህ አቶ አቤል፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ያልሆንነውን ለመሆን እና ያልተነገረልንን ነገር መናገራችን እስከ አሁን አልጠቀመንም ወደ ፊትም አይጠቅመንም፡፡

ለፕሮፌሰሩ በጻፍከው ደብዳቤ ላይ ገፅ 15 ላይ የማያን ካሌንደር የቱባ ምስጢር እንደሆነ የንግስተ አዜብን ፍርድ 42ኛ ዲግሪ ቀመሮችን አስረድተህ የደብረሲናን እና የደብረ ፅዮንን ህጎች በስሌት አስቀምጠኻቸዋል፡፡ ሁሉ ነገር ትክክል አይደለም ያስቀመጥካቸው የብዜት እና የድምር ውጤቶችም እንኳን ትክክልነት ይጎድላቸዋል፡፡ ፕሮፌሰሩን እንደምን እንደገመትካቸው እኔ አሁን መገመት ይከብደኛል፣ እርሳቸው ደብዳቤህን አንብበው ምን ብለው ይሆን?!!!

አሁንም ለፕሮፌሰሩ በጻፍከው ላይ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ፍርድና ገለጣህ ሁሉ ከእውነታ የራቀና ውስብስብ ነው፡፡ ለአንድ ፕሮፌሰር በሚጻፍ ጽሑፍ ውስጥ የማስረጃ ምንጭ መጥቀስ አስፈላጊ ይመስለኛል ነገር ግን ለሰጠኻቸው ዘገባዎች ማስረጃም አልሰጠህም ምናልባት ከሰማይ መጣልኝ ልትል ይሆን?! አይቀርም፡፡
የፕሮፌሰር መስፍን ምሳሌነት ሁላችንንም የሚያኮራና የሚያበረታታ ነው፣ ነገር ግን ያልሆኑትን ነዎት በማለት ያልሆነ ስም ልንሰጣቸው አይገባም ስለዚህም ለእርሳቸው የመጽሐፍ ቅዱሱን የስምዖንን ቦታ መስጠትህ ትክክልም ተገቢም አይደለም፡፡

3ኛ፡ 9/11 ላይ ያለህ ግንዛቤ

ነገሮችን በመንፈሳዊ አይን ለመመልከት መሞከርህ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ግን አጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ስህተቶች አሉበት፡፡ ከነዚህም ውስጥ ለ9/11 የሰጠኸው የ”ኮዳ”ዊ ትንታኔ ነው፡፡ በገፅ 20 ላይ 9/11 ኮድ ነው ብለኸዋል፡፡ የራዕይም ፍፃሜ እንደሆነ ለመጥቀስ ሞክረሃል በአንቱታ ያሽሞነሞንከው የአሸባሪውን የዖሳማ ቢን-ላደንን ሞትና የሬሳው ወደ ባህር መጣል የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍፃሜ ለማድረግ ራዕይ 20ን ጠቅሰህ ሞክረሃል፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ይገርማሉ በየምክንያቱ ጥቅስ እየተመረጠ የተለጠፈባቸው ባዶ ጥረቶች ናቸውና፡፡

በዚህ በሦስቱ ስር ነቀል መንፈሳዊ ክስተቶች ገለጣህ ውስጥ 9/11 የሚለውን ኮድህን ለማረጋገጥ የኢትዮጵያን ታሪክ አዛብተሃል፡፡ ለምሳሌም ያህል የቀዳማዊ ኃይለስላሴን ከዙፋን መውረድም ከ9/11 ጋር አያይዘኸዋል (በጣም በተደጋጋሚ)፡፡ ምን ለማለት ፈልገህ እንደሆነ ከአጠቃላይ ጽሑፍህ ውስጥ ግልፅ ነው፡፡ አንዳንዶች የግል ሃሳባቸውን ለማራመድ ታሪክ እንደሚረግጡ ሁሉ “የተማረ” ነው የምንልህ መጽሐፍም ይህንንም ጽሑፍ የጻፍከው አንተም ይህንን ማድረግህ ይገርማል፡፡ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ከስልጣን የወረዱት እኮ መስከረም 2 ቀን 1967 ነበር፡፡ ማለትም 10/11 ሊባል ይችላል እንጂ 9/11 አይደለም፡፡ ስለዚህ ከ9/11 ጋር ምን ያገናኘዋል? እኔ እንደሚመስለኝ ጽሑፍህ ለኢትዮጵያውያን የተጻፈ ነው እንጂ ለሌሎች አይመስልም፣ ታዲያ ቢያንስ ይህንን የሚያስታውስ ኢትዮጵያዊ ወይንም አንባቢ ይኖራል ብለህ እንዴት አልገመትክም? ወይንስ የኢትዮጵያን ሕዝብ መናቅህ ነውን?
አየህ የምንጽፈውን ሁሉ አለ-እውቀት ወይንም አለማስተዋል የሚቀበሉን እንዳሉ ሁሉ ጥያቄ የሚፈጥርባቸውም ሰዎች እንዳሉ ማሰብ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ይህን ሐሳብ ስሰነዝርልህ በልጅነቴ ያነብብኩት የክቡር ከበደ ሚካኤልንና በፍፁም የማልረሳውን አንድ የግጥም ስንኝ ላስታውስህ (ባልሳሳት በክቡር ከበደ ሚካኤል የተገጠመ ይመስለኛል)፡፡
“ዋ አስተማሪ ያለበት አባዜ
የተማሪ ጎበዝ የገጠመው ጊዜ”

አሁን የገጠመህ ጎበዝ ተማሪ ነው ማለቴ አይደለም፡፡ ነገር ግን በእውነት ለአገራቸው የሚቆረቆሩ ሆኖም ግን ከነባራዊ ሁኔታ ጋር በእውነት መነፅር ነገሮችን በመመዘን የሚያዩ በዚህም መሰረት የሚንቀሳቀሱ ሰዎች እንዳሉ እንድታውቅ፡፡ ጽሑፎችም ለእንደነዚህ ዓይነት ሰዎች እጅ የሚደርስበት ሁኔታና አጋጣሚ እንዳለ እንድታውቅ ብቻ ነው፡፡
በመሆኑም በገፅ 31 – 32 ላይ የፍርድ ዘመን መሆኑን ለማወቅ ከቀመር ጋርና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ጋር አገናኝተህ የሰጠኻቸው ነጥቦች በተለይ በገፅ 32 ላይ በሀ፣ በለ፣ ወ.ዘ.ተ ቅድም ተከተል የሰፈሩት ከዚህ በፊት የተሰሩት ስህተቶች ፍሬ ቢስ ክለሳዎች ናቸው፡፡ ምዕራፍ አራት 9/11 ላይ ያቀረብከውም ይህንኑ ነው፡፡ እንዲያውም በገፅ 35 ላይ የሆኑት ነገሮች ሁሉ የሳይኮሎጂስቱን የ“የንግን”ን ንግግር ጠቅሰህ ግጥምጥሞሽ ሳይሆኑ ምስጢራዊ ክንውኖች ናቸው ብለሀናል፡፡ ነገር ግን ከ9/11 የኮድ ትንታኔህ ጋር እንድናገናዝበው የሰጠኸን የኃይለስላሴ መውረድ ጋር ማመሳሰልህ የምትናገረው ወይንም “ፅንሰ ሐሳብህ” ማስረጃ ቢስና ሆነ ተብሎ በተጠመዘዘ ታሪክ ማስረጃ ላይ የተመሰረተና ለማንም የማይጠቅም አድርጎታል፡፡

ይህ ሃሳብህ ደግሞ እንደገናም ተደጋግሞ ቀርቧል አሁንም እንደገና ላስታውስህ በገፅ 39 ላይ ስለ ኃይለስሳሌ መንግስት በኢትዮጵያ ከጥቅምት 1924 – ጥቅምት 1966 በፈረንጆች ደግሞ 9/11/31 – 9/11/73 አድርገህ አቅርበኸዋል ይህም ደግሞ በተደጋጋሚ እስከ መጨረሻው ጽሑፍህ ቀርቧል፡፡ አቶ አቤል ስለምን እንዲህ አደረግህ? በተሳሳተ መንገድ የጠቀስካት “የንግስተ አዜብ ፍርድ ፅንሰ ሐሳብህን” ለማስረዳት መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ በአገሪቱ ውስጥና በዓለም ያለው እውነታ፤ እንዲሁም የንግስተ ዓዜብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አገላለጥ እና ትርጓሜ አንተ ከምትለውና ደጋግመህ ካቀረብከው ንግርት ጋር በፍፁም አብሮ አይሄድም፡፡

3ኛ፡ መንፈስ መንፈስ መንፈስ … …

ኢትዮጵያን የወጋ የአውሬው መንፈስ በሚለው ምዕራፍ 6 ውስጥ፣ መንፈሱ ማነው? የሚለው ጥያቄ ከቀረበ በኋላ የተሰጠው የቀመርና የትንታኔ አካሄድ በፍፁም አላማረኝም፡፡ በአቶ አቤል ጽሐፉ ውስጥ ሁሉ ነገር መንፈስ ሆኖ ቀርቧል ቋንቋም እንኳን ሳይቀር መንፈስ ተብሏል፡፡ በገፅ 46 ላይ ከአርባ በላይ የተለያዩ መንፈሶች ተጠቅሰዋል፡፡ የኦርቶዶክስ፣ የፕሮቴስታንት፣ የአማራው፣ የደቡብ ሕዝብ፣ የኦሮሞው፣ የቅንጅት፣ የምዕራባውያን፣ ለማንኛውም ሁሉ ነገር መንፈስ የሚል ስም ተሰጥቶታል፡፡ ይህ ሁሉን ነገር መንፈስ ነው (ማለትም የአውሬው መንፈስ ነው ማለት) በገፅ 46 ላይ አላቆመም ይቀጥላል በሌሎችም ምዕራፎች ሁሉ፡፡

በአቶ አቤል ጋሼ መሰረት እነዚህ ሁሉ ኢትዮጵያን የሚወጉ የአውሬው መንፈሶች ናቸው፡፡ በቀመራውም መሰረት ሲሰሉ “666” ይመጣሉ በጣም ይገርማል!!! ፖለቲካው ፓርቲ፣ ሃይማኖቱም ቋንቋውም ሁሉ መንፈስ ከሆነ የሰው ልጅ ድርሻ ታዲያ የቱ ላይ ነው የሚገኘው? ሁሉንም ነገር የአውሬ መንፈስ እና ተዋጊ ነው በማለት ተወጊውንና ተዋጊውን እንዴት ልንለየው እንችላለን? እውነተኛው መንፈስ የሚሆነውስ ለመሆኑ የቱ ነው፣ የቤተክርስትያን ሰውስ ቤተክርስትያንን እንደ አውሬ መንፈስ እንዴት ሊቆጥራት ይችላል?

ከዚህም በላይ የሚያስገርመውና የአቶ አቤልን ፅንሰ ሐሳቦች መጥፎ በሆነ ጥያቄ ውስጥ ከሚጥሉት ነገሮች ውስጥ ከገፅ 53 አስከ ገፅ 55 በፊደል ተራ “ለ” ውስጥ ስለ ስልክ መንፈስ የተሰጠው መግለጫ ነው፡፡ አቶ አቤል ስልክና በስልክ መጠቀም የመንፈስ ስራ ነው ይላል፡፡ ይህንንም መንፈስ በስልክ የሚስለከለክና በገጠርም በከተማም የሚሰራ በማለት አስቀምጦታል፡፡ ይህንን በኮድና በቀመራህ፣ ትክክል ባልሆነው ስሌትም ከወከለው በኋላ፣ ስልክ አውሬው የሚሰራበት የኮድ ጥበብ ነው ብሎታል፡፡ ለዚህም ሐሳቡ ምንም አሳማኝ ማስረጃ አልሰጠንም፡፡ ምንም አይደለም አሁን ባለንበት የቴክኖሎጂ ደረጃ ሕዝቡ ግንኙነትን እንዲያደርግ “ከሰይጣኑ መንፈስ” ስልክ ሌላ ሕዝቡ ሊጠቀምበት የሚችልበትን ሌላ አማራጭንም አላቀረበልንም ታዲያ ይሄ ሁሉ የአቶ አቤል “ፅንሰ ሐሳብ” ምን ይባላል?

ጽሑፍህን ያነበበ ሰው ሁሉ የሚመስለውና የሚገምተው ነገር ውስብስብ እና ግራ በተጋባ ጽሑፍና ፍልስፍና አማካኝነት ሕዝቡን ከዘመናዊው ቴክኖሎጂ ለማራቅ እንደምትመኝ፡፡ ከዚህም ባሻገር አንተና መሰሎችህ ብቻ አዋቂዎች ሚስጢር የተገለጠላቸው እየተባላችሁ ሕዝቡ ለእናንተ አይነት ሰዎች በጭፍን እንዲገዛ እንደምትታገሉ አስመስሎታል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በየትኛው የዓለም ክፍል ውስጥ እንዳለህ በውኑ አላውቅም፣ ነገር ግን የድረ-ገፅ የቴሌቪዥን እንዲሁም የኮምፒውተርና የኢ-ሜል ተጠቃሚ እንደሆንክ ተረድቻለሁ፡፡ ስለዚህም እነዚህን ብዙዎቹን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሳትወነጅል በገጠርም በከተማም የቀረበውን ስልክና ሰዎች በቀላሉ የሚገናኙበትን መንገድ መንቀፍህና ከሰይጣን መንፈስ ጋር ማገናኘትህ ይገርማል፡፡ የአንተ አካሄድ ቢያንስ ከ100 ዓመት በፊት ከኖሩትና ሬዴዮና ስልክ የሰይጣን ነው በማለት ይከራከሩ ከነበሩት ጥንታዊ የሮማን ካቶሊክ ቄሶች ጋር ያስፈርጅሃል፡፡ ጊዜውን አውቃለሁ፣ የጊዜው ምስጢር በተለይም የኢትዮጵያ ትንሳኤ ተገልጦልኛል ከሚል አንድ ሰው ይሄንን አንጠብቅም ትክክልም አይደለም፡፡

4ኛየሃሰት ፍልስፍናዎችና ትምህርቶች የጋራ ምልክቶች

ከጥንት ጀምሮ በዓለማችን ላይ የተነሱ የሐሰት ፍልስፍናና ትምህርቶች ሁሉ በቀላሉ የሚታወቁበት የጋራ መለያ ምልከት ትተውልናል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ምስጢራዊነትና ውስብስብነት ይገኙበታል፡፡ ለጋራ አገራችን ኢትዮጵያ እንደገና መነሳት አቶ አቤል ስላለህ ምኞት ማንም ሰው ሊያደንቅህ ይገባል፡፡ ነገር ግን ሃሳብህ ሁሉ በ”ቱባ ምስጢር” እንዲሁም በተወሳሰበ ከዚህም በላይ ማስረጃ በሌላቸው ቁልፎች ውስጥ የተቆላለፈ ነው፡፡

የአዜብ ምስጢር፣ የዲግሪ ቀመር፣ የሁለቱ በኩሮች ያልካቸው አሟሟት ሚስጢር እና የአዜብ መንፈሳዊ ግዛት መጀመር፣ የፖለቲካ ድርጅቶችን ሁሉ መንፈስ አድርጎ መቁጠር፡፡ አንዱ ቦታ ላይ ያመሰገንከውን ሌላ ቦታ ላይ መዘርጠጥ፤ ለምሳሌ የቀዳማዊ ኃይለስላሴን የይሁዳ ነገድ መሆን አባባል መንቀፍና የእርሳቸውን መውረድ ደግሞ “ኢካቦድ” ማለት፡፡ እነዚህ ሁሉ ውስብስብና ያላስፈላጊ ነገሮች ናቸው፡፡ የሚመስለው “በሕልም” ውስጥ እንደመኖር ብቻ ሳይሆን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ በመንፈሳዊ ትርጉም ምስጢር ውስጥ በጣም መራቅና ሌሎችንም በሕልም ዓለም ውስጥ እንዲኖሩ ማድረግ ነው፡፡

ከዚህ ጋር አብሮ የሚሄደው ሌላው ነገር በገፅ 28-30 የቀረቡት የንግስተ አዜብ ሰማያዊ ምስጢራት ናቸው፡፡ ሰንጠረዥ 1 ውስጥ ያቀረብካቸው ነገሮች በአብዛኛው ትክክል አይደሉም፡፡ የ42 ዘመን አቆጣጠር ስሌትህ ትክክል አይደለም ለዚህም የሰጠኸን ማስረጃ ወይንም በሂሳብ የማጠጋጋት ህግ እንኳን እንድንቀበለው ያደረከው ሙከራ የለም፡፡ ይህንንም እንኳን የኢትጵያን ሕዝብ ማገናዘብ እንደማይችል አድርገህ መናቅህ በማለት አንድ ሰው እንዲያስብ ያደርጉታል፡፡ ለምሳሌ በ42 ዘመን ቀመር ስር፡

a.September 11 – May 2, 2011 የሚለው እንዴት 42 ወር እንደሚመጣ ግልፅ አይደለም፡፡ (9) ዘጠኝ ወርን 42 ወር ብለን እንድንወስድ ፈልገህ ይሆን ይህንንም አልነገርከንም፡ እንደዚህ አድርጋችሁ ለጊዜው ውሰዱ አላልከንም፡፡

b.1/1/24 – 1/1/1966 የቀዳማዊ ኃይለስላሴን አነጋገስ ስሌት 42 ዓመት እንደሚመጣ ልታሳየን ሞክረሃል፡፡ ቢሆን ጥሩ ነበር ነገር ግን የሚመጣው 43 ዓመት ነው ምክንያቱም ጥቅምት 23 1923 ነግሶ ብለህ አስቀምጠኸዋልና፡፡ ስለምን የታሪክን ቀናትና ዘመናት መለዋወጥ አስፈለገ?

c.ገፅ 29 የኢካቦድ ዘመን ከ1966 -2008 ድረስ ይሆናል ብለሃል፣ ይህ ዘመን በቀደመው ሰንጠረዥ ላይ ካጥላላሃው የይሁዳ አንበሳ ገዢ መንፈስ የሚለየውና “ኢካቦድ” ያሰኘው ነገር ምንድነው? ግልፅ አይደለም፡፡ በሌላው ቦታ ላይ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን በተደጋጋሚ ለኢካቦድ ፍፃሜህ የሌለውን ስም “መንግስቱ ኃይለማርያም ደሳለኝ” በማለት ለማቅረብ ሞክረሃል፡፡ ግን ለምን ግን ለምን?

d.ቀጥሎም ከግንቦት 20 (በኢትዮጵያ) እስከ ግንቦት 18 (የፈረንጆች) የሚል ሃሳብ ቀርቦ 42 = 21 (ቤተክህነት + 21 ቤተመንግስት) የሚል ቀመር ተቀምጧል፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? በየትኛው ዓመተ ምህረት ነው? ዓመተ ምህረቱ ስላልተጠቀሰ 42 ቀን ሳይሆን የሚመጣው የአስር ቀናት ጉድለት ነው፡፡ (በሂሳብ ስሌት -10 መሆኑ ነው)፡፡

e.በገፅ 30 ላይ ወዳለው ስንመጣ 42 ቁጥር እንዲመጣ የተሰጡት ብዜቶች ከዋቢ ሰንጠረዡ ጋር በፍፁም አሳማኞች አይደሉም፡፡

f.በመጨረሻም የኢየሱስ የዘር ሐረግ 42 ዲግሪ ከDan Brown የቅዠት ሰይጣናዊ መጽሐፍ ጋር እንዴት እንደሚዛመድም ግልፅ አይደለም፡፡ አንድ አማኝ እንደሆነ እራሱን ከሚቆጥርና መጽሐፍ ቅዱስን ከሚጠቅስ ሰው የዳን ብራዎንን ስም እና የማያን ቆጠራ እንደማገናዘቢያ መስማትም አሳፋሪ ነው፡፡
እነዚህ ሁሉ ውስብስቦች እና የጠቀስካቸው የማያ ቀመር 26000 እና የዳን ብራዎን ሐሳቦች ለጻፍከው ጽሑፍ ትልቅ ጥያቄዎችን አሳድረውበታል፡፡ ለመሆኑ እንደዚህ ዓይነት አጠያያቂ ውስብስብ ነገር ውስጥ ለመግባት ስለምን አስፈለገ?

ይህ አሁን አንተ የያዝከው ዓይነት አካሄድና ኮዳዊና ቀመራዊ ትንተና በዘመናት የተነሱ የሐሰት ፍልስፍናና ትምህርት አራማጆች ባህርይ ነበር አሁንም ነው፡፡ ነገር ግን ጥንትም አሁንም ሰዎች ይጃጃሉበታል እንጂ የሰጠው ምንም ጠቀሜታ በታሪክ ውስጥ የለም፡፡ ቀላል ማስረጃ ልስጥህ በአይሁድ እምነት ውስጥ ልክ እንደ አንተ ያለ ቀመራና ኮድ የሚያምኑ ብዙዎች ተነስተው ነበር፤ ኮዳቸውም ቀመራቸውም ተረት ሆኖ ነው የቀረው እነርሱም ተከታዮቻቸውም የሉም፡፡ ስለዚህም አንተን የመሰለ የተማረ ሰው እንዲህ ዓይነት ውስብስብ ምስጢራዊና የማይሰራ ኮድ ውስጥ ከምትገባና በማይሆን እንዲሁም በሌለ በማይሰራም ነገር ከምትጨነቅ ጊዜህንም ከምታቃጥል ይልቅ ግልፅ ወደ ሆነው ነገር እንድትመጣ እመክርሃለሁ፡፡

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መለኮታዊ እጣ እንደ አቶ አቤል ጋሼ ከሆነ በኮድ የተቆላለፈ በቀላሉ የማይፈታ የሕልም ዓለም፣ ውስብስብ መቼም እንደሚሆን የማይታዋቅ ግራ የተጋባ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ግን እንዲህ ዓይነት እጣ የለንም ሊኖረንም አይችልም፡፡

እውነተኛው የኢትዮጵያ መለኮታዊ ዕጣ፡ ለአገሪቱ የሚጠቅመው ማጠቃለያ፡፡

በዓለም ውስጥ በአገራችንም እየሆኑ ያሉት ነገሮችን ለመረዳት ምንም ኮድና ምስጢር ውስጥ መግባት አያስፈልግም፡፡ ኢትዮጵያንም ከሌሎች አገሮች የተለየ አድርገን ልንቆጥራት የሚያስችለን ምክንያትም ማስረጃም የለንም፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን እንደማንኛውም የሰው ዘር በምድር ላይ ለመኖር መብትና እድል ከፈጣሪ ተሰጥቶናል፡፡ በእርግጥ የተጋፈጡብን መከራዎችና ችግሮች ቀላሎች አይደሉም፡፡ እነዚህ ችግሮቻችን ግን ምስጢሮችም በኮድ የተቆለፉም አይደሉም፡፡ እነዚህን ለመፍታትም ብዙ መራቀቅና መፈላሰፍም ውስጥ መግባት አያስፈልገንም፡፡ ያልሆንነውን መሆንና ሁኔታዎችን በጥልቅ መንፈሳዊ ኮድ ለመፍታት ጥረት በማድረግ ስራ መፍታትም ጊዜ ማቃጠልም የለብንም፡፡
ችግራችን ግልፅና የየትኛውም አገር ዓይነት ችግር ነው፡-
ጥሩ አስተዳደር አልነበረንም – አሁንም የለንም፡፡ መፍትሔው ጥሩ አስተዳደር ለመመስረት አብሮና ተባብተሮ መነሳት ብቻ ነው፡፡

ጥሩ የስራ ሰዎች አልነበርንም – አሁንም አይደለንም፡፡ መፍትሔው ጠንክሮ ለመስራት መነሳትና ጠንካራ ሰራተኞች እንድንሆን መወሰን መማርና ማስተማር በተግባርም ማሳየት ነው፡፡
ገዢዎቻችን የሚሰጡትን ጠቃሚ መመሪያዎች በጥላቻ በመሞላት ወይንም በትዕቢት አልተቀበልንም – አሁንም አንቀበልም፡፡ እንዲያውም የሌለ መንፈሳዊ ትርጉም በመስጠት ዓመፅን እና ስራ መፍታትን እናበረታታለን ለምሳሌ በአቶ አቤል ጽሑፍ ውስጥ food security ለማምጣት የሚደረገው ጥረት የተተረጎመው በባባቢሎን ግንብ የጥፋት ጥረት ነው፡፡ ይህም በጽሑፉ ውስጥ ከመጀመሪያው ገፅ ጀምሮ ግልፅ ነው፡፡ በሌላ መልኩ አቶ አቤል ለፕሮፌሰር በጻፈው በገፅ 13 ላይ መልካችን “የረሃብ መልክ” ነው በማለት ገልፆታል፡፡ ታዲያ የምግብ ዋስትና ጥረት ስለምን ይነቀፋል? ገዢዎች የሚሰጡት ወይንም የሚያወጡት ፖሊሲ ከፊሉ መጥፎ ሊሆን እንደሚችል ጥሩም የሆነ ይኖረዋል፡፡ የኛ ስራ ጥሩውን ደግፈን መጥፎው እንዲወገድ መታገል መሆን አይገባውምን?

ለመልካም ነገር ትብብር እናሳይ መጥፎውን ለማስወገድ ደግሞ አብረን በግልፅነትና በእውነት እንቁም፡፡
የሚጠቀመን ነገር ውስብስብ እና ተጨባጭ ባልሆነ የሕልም ዓለም ውስጥ መኖር ሳይሆን በተገለጠውና በቀላል ሁላችንንም በሚጠቅመው ግልፅነት አብረን ተከባብረንና ተፋቅረን በትጋት መስራት ነው፡፡

የምዕራባውያኑ ዕድገት የመጣው በስራ ነው፣ ቻይኖች አሁን የደረሱበት ደረጃ የደረሱት በትጋት በመስራት ነው፡፡ ጃፓን እንደምን ሰለጠነች የሚለውን መጽሐፍ ከሠላሳ ዓመታት በፊት ያስነበቡን ኢትዮጵያውያን ይነግሩን የነበረው ጃፓን የሰለጠነችው በስራ እንደነበር ነው፡፡ የእኛም አገር መለኮታዊ ዕጣ በመስራት ማደግ፣ በመስራት ማደግና መሻሻል ብቻ ነው ሌላው ግን ቅዠትና የቀን ሕልም ብቻ ነው፡፡

ቸር ይግጠመን
ጃፋር ሐሰን


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1809

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>