የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ልሳን የሆነው ፍኖተ-ነጻነት ጋዜጣ በግማሽ ሚሊዮን ብር የራሱን ማተሚያ ማሽን በመግዛት እና በመትከል በቅርብ ቀን ሕትመቱ ለሕዝብ በገበያ ላይ እንድሚውል ተገልጸ፡፡
የአንድነት የድርጅት ጉዳይ ሐላፊ የሆኑት አቶ ዳንኤል ተፈራ እንደገለጹት፤ የአንድነት ፓርቲ እና የፍኖተ ነጻነት የኢዲቶሪያል ቦርድ ባለፈው አመት ያሳትማት የነበረችው ጋዜጣ በ2005 ዓ. ም. በጉልበት እንድትዘጋ በመደረጉ እና የመንግስት ጋዜጣ ማተሚያ ቤት የሆነው ብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤትን ጨምሮ በማንኛውም ኢትዮጵያ ውስጥ ባለ የግል ማተሚያ ቤት ጭምር እንዳትታተም ከተደረገ በኋላ ይህንን ችግር በዘላቂነት የፓርቲውን መገናኛ ብዙሃን ለማጠናከር እና ለመምራት ምንድነው የሚያስፈልገው? የሚል ሰፋ ያለ ውይይት በማድረግ የፓርቲውን የማተሚያ ማሽን መትከል በጣም አስፈላጊ፤ አንገብጋቢ እና ወሳኝ ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል።
ይህንኑ ከግንዛቤ በማስገባት የአንድነት ፓርቲ አመራሮች፤ የፍኖተ ነጻነት የኢዲቶሪያል ቦርድ፤ የአንድነት ፓርቲ ደጋፊዎች እና በውጭ አገር የሚገኙ የአንድነት ፓርቲ የድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ይህንን የተቀደሰ ሐሳብ በጋራ በመካፈል እና የሚሰጠውን ጥቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት ከፍተኛ የሆነ ለሶስት ወራት የቆየ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘመቻ በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር በማካሄድ ግማሽ ሚሊዮን ብር አካባቢ መሰብሰቡን ገልጸዋል።
አቶ ዳንኤል በመቀጠልም በአሁኑ ሰአት “ኮርድ” የሚባል የማተሚያ ማሽን በግማሽ ሚሊዮን ብር ግዥ የተፈጸመ ሲሆን፤ ይህ ማሽን በአጠቃላይ ለፓርቲው አገልግሎት እና ፓርቲውን ከሕዝብ ጋር ሊያግናኙ የሚችሉ ጋዜጣ፤ በራሪ ጽሁፎች፤ ፖስተሮች፤ መጽሄት፤ መጽህፍ፤ የመሳስሉትን ሁሉ ማተም የሚችል በመሆኑ ለአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ የፓርቲው ትጥቅ መሆኑን ገልጸው በተለይ አንድነት ለሚያካሂደው የሰላማዊው ትግል ከፍተኛ መሳሪያ መሆኑን እና በተለይ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የታፈነበት አገር ላይ ያለን በመሆናችን ይህ ማሽን ሰራዎቻችንን በበለጠ የሚያቀላጥፈልን እና ሕዝቡ ጋር በቀላሉ ለመደርስ የምንችልበትን አቅም በክፍተኛ ሁኔታ የሚጨምር መሆኑን አስረድተዋል።
አቶ ዳንኤል ተፈራ በመጨረሻም የፍኖተ ነጻነት ማተሚያ ማሽን ተከላ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ተጠናቆ በአምባገነኖች የተዘጋችው ፍኖተ ጋዜጣ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ለሕዝብ የምትቀርብ መሆኑን የገለጹ ሲሆን ለአንድነት አባላት፤ ለአንድነት ደጋፊዎች፤ በውጭ አገር ለሚኖሩ የአንድነት የድጋፍ ሰጭ ድርጅቶች፤ ደጋፊዎች፤ ይህንን ማሽን ለመግዛት በገንዘብ፤ በሐሳብ እና በተለያየ መንገድ አስተዋጻኦ እና እግዛ ያደርጉትን ኢትዮጵያውያኖች በሙሉ በአንድነት ፓርቲ እና በፍኖተ-ነጻነት ኢዲቶሪያል ቦርድ ስም ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።
አቡጊዳ ድህረ ገጽም በዚሁ አጋጣሚ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የምትገኙ ኢትዮጵያውያን በሙሉ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንድሚባለው ሁሉ ይህንን ማሽን ላመግዛት ማንኛውንም እገዛ እና ትብብር ላደርጋችሁ በሙሉ ከፍተኛ ምስጋናችንን እያቀረብን፤ የአንድነት ፓርቲ አመራሮች እና የፍኖተ ነጻነት ኢዲቶሪያል ቦርድ እና ጋዜጠኞች፤ ደጋፊዎች በሙሉ እንኳን ድስ አላችሁ እንላልን!!