Quantcast
Channel: Abugida Ethiopian American Amharic Web Page
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1809

ዘውግና ብሄራዊ አንድነት እንዴት ይታረቃሉ? በፕሮፌሰር መሳይ ከበደ የመፍትሄ ኣሳብ ላይ ሊነሱ የሚችሉ የሰሉ ጥያቄዎች ገለታው ዘለቀ

$
0
0

ይህን ርእስ የወሰድኩት በቅርቡ ቪዥን ኢትዮጵያ ከኢሳት ቴሌቪዥን ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ “የኢትዮጵያ ዘውጋዊ ክፍፍሎችና የመፍትሄ ኣሳብ” በሚል ርእስ ስር ካቀረቡት መሳጭ ጥናታዊ ጽሁፋቸው ስር ካነሷቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች መሃል ኣንዱን መዝዤ ነው። ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ በዚህ ፕሮግራም ላይ ያቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፋቸው በርግጥ ደረጃውን የጠበቀና በሚገባ የተደራጀ ነው። ፕሮፌሰሩ ፈላስፋም ስለሆኑ ኣሳባቸውን በሚገባ ገልጸዋል። ኣስበውበት ተፈላስፈውበት በመሆኑ ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል። በእንዲህ ዓይነት ስብሰባዎች ላይም እንዲህ ዓይነት ትንተና መኖሩ መልካም ነው። በአሁኑ ሰዓትም አገራችን ኢትዮጵያ ከተወደዱ ምሁራኖቿ የምትሻውና የተራበችው ነገር ምሁራን ተጨንቀው ኣስበው ኣማራጭ መፍትሄዎችን እንዲያመጡላት ነው። በእንዲህ ዓይነት ከፍ ያሉ ጉባዔዎች ላይ የሚቀርብ ጥናታዊ ጽሁፍ ከተራ ንግግር ኣይነት ወጣ ብሎ አማራጭ መፍትሄ የሚጠቁም መሆን ኣለበት። ፕሮፌሰሩ ኣስበውበት ደክመውበት እንደመጡ ስለተሰማኝና ለውይይት የሚጋብዝ በመሆኑ እንደ ዜጋ ኣመስግናቸው ኣመስግናቸው ብሎኛል። ታዲያ ይህንን ስል ኣሳባቸውን የተቀበልኩት እንዳይመስላቸው ደሞ። ባልቀበልስ ምንቸገራቸው እንጂ::

ፕሮፌሰር መሳይ ኣቀራረባቸውንና ያመጡትን ኣሳብ ለመሞገት ያላቸውን የሃሳብ ኣደረጃጀትና ትንተና ብማርበትም በዚህ በዛሬው ጥናታዊ ጽሁፋቸው ውስጥ ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ችግሮች “መፍትሄ” ብለው ባቀረቡት ኣሳብ ዘንድ ብዙ ጥያቄዎችን ኣስነስቶብኛል። ጥያቄ ኣስነስቶብኛል ብቻም ሳይሆን የመፍትሄ ኣሳብ ያሏቸው ኣቅጣጫዎች የኢትዮጵያን ማህበረ ፖለቲካ ችግር ፈጽሞ የሚፈታው ኣይነት መስሎ ኣልታየኝም። እናም ዛሬ ፕሮፈሰር መሳይ ባቀረቡት ኣሳብ ላይ ጥያቄ ላነሳባቸው እነሆ እርሳሴን ኣነሳሁ።

ፕሮፈሰር መሳይ ከበደ ከፍ ሲል እንዳልኩት ፈላስፋ በመሆናቸው ጽንሰ ሃሳቦች ይማርኳቸዋል። እሳቸውም ይህንኑ ብለዋል። ይሄ ደስ ይላል። በመሆኑም ከመግቢያ ላይ ስለ ዘውግ ፖለቲካ ምንነት የተለያዩ ኣስተምህሮቶችን (school of thoughts) በማንሳት ኣሰርድተውናል። በውነት ትምህርት ይሰጣል። priordialism, instrumentalism and constructivism የተባሉ ጽንሰ ሃሳቦችን ተንትነዋል። በዚህ ዙሪያ የፕሮፌሰር መሳይን ትንተና ለማዳመጥ እነሆ ማስፈንጠሪያው::

ወደ ውይይታችን ማእከላዊ ጉዳይ እንግባና በአሁኑ ሰዓት ስልጣን ላይ ያለውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት የሚገልጸው የፍልስፍና መሰረት ማለትም (priordialism) በሚገባ ሊታይ ይገባዋል። priordialism የቋንቋና ባህል ልዩነትን በጣም የሚያጎላና ቡድኖች ዘውገኝነታቸውን አጥብቀው እንዲይዙ የሚጨቀጭቅ ኣስተምህሮ ነው። ምሁራን ከፖለቲካ አንጻር ይህን ትምህርት ሲያነሱ ለሩዋንዳው እልቂት መናጆ አድርገው ይወስዱታል። የብሄር ፖለቲካም ቡድናዊ ልዩነትን የሚያየው priordialism መነጽርን በማድረግ ነው። የብሄር ወይም የዘውግ ፖለቲካ በዘር፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በደም ተፈጥሮ በሚገኝ ትስስር ላይ የሚቆም የፖለቲካ ስርዓት መሆኑን እንረዳለን። ፖለቲካው በነዚህ ተፈጥሯዊ ትስስሮች ላይ የሚቆመው ዘውጋዊ ስሜት በፈጠረው የስሜት ኤነርጂ ላይ ስለሚቋምጥ፣ ስለሚመካበት ነው። ይህ ስሜት ገንኖ የሚታየው ደግሞ በራሱ በቡድኑ ውስጥ ሳይሆን ቡድኑ ከሌሎች ቡድኖች ጋር በሆነ ኣጋጣሚ ሲገናኝና ለሆነ ዓላማ ሲወዳደር ወይም ውድድር ውስጥ ነኝ ብሎ ሲያምን ነው እጅግ ሃይለኛ ሆኖ የሚገለጸው። ይህንን ሃይለኛ ስሜት የዘውግ ፖለቲከኞች ቤታቸውን ሊሰሩበት ሲያስቡ በሃይለኛ ስሜቱ በጣም ይታመናሉ። ለሚፈልጉት ዓላማም ይህ ሃይለኛ ስሜት አድራሽ ከፍተኛ ኤነርጂ እንደሚሆን ስለሚያውቁ የማንነት ፖለቲከኞች ፖለቲካቸውን በዚህ በተፈጥሮ ተሳስሮ ባለ ስብስብ ላይ ያንጻሉ። የዘውግ ፖለቲከኞች priordialist ነን ይበሉ እንጂ በተግባር ግን ዘውግ የፈጠረውን ትስስር ለፖለቲካ ስልጣን መጠቀሚያ ማድረጋቸውን የሚያሳየው እነዚህ ፖለቲከኞች ይህንን ስብስብ ለስልጣን ሩጫ ሲጠቀሙበት ኣንዱ ችግር ዘመናዊ የሆነን የፖለቲካ ኣስተሳሰብንም በኣንድ እጃቸው ለመጎተት እየሞከሩ መሆኑ ነው። የቋንቋና የባህል ትስስር የፈጠረውን ስብስብ ለፖለቲካ ዓላማ የሚጠቀሙበት ወገኖች የፖለቲካቸው ኣጀንዳ ቆመንለታል የሚሉትን ዘውግ ባህላዊ ማንነት መሰረት ያደረገ ኣይደለም። ከዚያ ስብስብ የሚፈልጉት በዋናነት ኤነርጂውን ሲሆን ፕሮግራሞቻቸው በዘመኑ ካሉ ዓለማቀፋዊና ዘውግ ዘለል ከሆኑ የፖለቲካ ኣስተሳሰቦች ጋር የሚሄድ ነው። ለምሳሌ ያህል ኣንድ የኦሮሞ ህዝብ ድርጅት ነኝ የሚል ቡድንን ብንወስድ ይህ ቡድን የኦሮሞን ባህላዊ ቡድን መሰረት ያደረገ የማንነት ጥያቄ ያነሳና ነገር ግን የገዳን ስርዓት መሉበሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ባህሉ ሳይበረዝ ለመቀጠል ኣይደለም የሚጥረው። ወይም ሊመሰርት የፈለገው ስርዓት የገዳ ስርዓት አይደለም። ስልጣን ቢይዝ ኦሮምያን በገዳ ስርዓት ኣይደለም የሚያስተዳድረው። ገዳ ለዴሞክራሲ ማስተማሪያ ኣድርጎ ነገር ግን ከዘመኑ ኣስተሳሰብ ጋር ቀላቅሎ ነው ሊቀጥል የሚፈልገው። ከመነሻው priordialism ኣስተሳሰብ ቢያሳይም ነገር ግን የቡድኑን ባህላዊ ማንነቶች በተሃድሶ ስም ራሱ ሲቀይር ይታያል። ከገዳ የምወስደው ኣለ ይላል ግን ደግሞ ሌላ ኣዲስ ስርዓትም ያሳያል። ዴሞክራሲ የሚባለውን ኣዲስ የኣስተዳደር ጥበብ ይጠቅሳል። ይህ ጥበብ ደግሞ የሁሉም ቡድኖች ባህል ነው በርግጥ። ይህንን ዘውግ ዘለል የኣስተዳደር ጥበብ ይዞ ነው ዘውጌ ፖለቲካ የሚመሰርተው። ይህ ጉዳይ በርግጥ የሚያሳየው ፖለቲካው ምንም እንኳን በባህላዊ ቡድኑ ትስስር ላይ የቆመ ቢሆንም የሚፈጥረው ማንነት ግን ቅልቅል በመሆኑ ሳያስተውል ኣዲስ ማንነትን መፍጠሩ ነው ማለት ነው። ስለዚህ ዘውጋዊ ፖለቲካዊ ማንነት ኣይባልም ማለት ነው። በዘውጉ ማንነት ላይ የቆመ ሳይሆን በኣብዛኛው ዘውግ ዘለል የሆነውን የዴሞክራሲ ባህል በማቀንቀን ላይ የተመሰረት በመሆኑ ዘውጋዊ ፖለቲካዊ ማንነት ሊባል ኣይችልም። ነገር ግን ለሂቃኑ የሚሹትና የሚጓጉለት በርግጥ ያንን ወደ ፈለጉት ኣቅጣጫ ሊወስድ የሚችልን ኤነርጂ በመሆኑ ስለባህሉ መቀየጥ ኣይጨንቃቸውም።

ፕሮፌሰር መሳይ የዚህን ኣስተምህሮ ነቀፌታ ሲጠቅሱ በስሜት ላይ ተመርኩዞ በመሄድ ደም እስከማፋሰስ የሚደርስ ሆኖ ሳለ ነገር ግን ቡድኖች ለምን ይከተሉታል? የሚል ነገር አንስተዋል። ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የዘውግ ፖለቲካን መሰረት መፈተሽ ኣለብን። የብሄር ኢንተርፕሩነርስ ወይም ለሂቃን እንበላቸው ያንን ዘውግ የፈጠረውን የትስስር ስሜት ወደ ፖለቲካል ኤነርጂ ቀይረው ሲሄዱ ዋናው መሰረታቸው ስሜት ነው በሚለው ላይ ስምምነት ኣለ። ዋናው መሰረት ራሽናል ኣሳብ፣ ወይም መርህ ኣይደለም። የዘውገኝነትን ስሜት መጠቀም በመሆኑ ነው በቀላሉ ቡድኑን ማንቀሳቀስ የሚችሉት። በስሜት ላይ ወይም በሰው ልጆች ድክመት ላይ የሚቆም ፖለቲካ በመሆኑ ነው ግድፈቶች ሲፈጸሙ ሰው ኣስተውሎ ሁኔታውን በቶሎ ለመመርመር የማያስችለው። ይሄ ተፈጥሯዊ ነው። በአለፈው ጊዜ ዶክተር ዲባባ በኢሳት ቴሌቪዥን የትምህርት ብልጭታ ፕሮግራም ላይ ጥሩ ኣድርጎ ገልጾታል። የሰው ልጅ ውሱንነት ኣለው። ፍጹም ባለመሆኑ ማለት ነው። ከነዚህ ውሱን መገለጫዎች ኣንዱ ደግሞ ኣንዳንዴ በስሜት ላይ ተመርኩዞ የሚያደርጋቸው ግድፈቶቹ ናቸው። በስነ-ልቡና ሳይንስ ውስጥም ታላቁ የስነ-ልቡና ጠበብት ሲግማን ፍሮይድ እንደሚለው የሰው ልጅ ስብእና የተገነባው ከሶስት ጉዳዮች ነው። እነዚህም ኢድ፣ ኢጎ እና ሱፐር ኢጎ ይባላሉ።

የዘውግ ፖለቲካ የሰው ልጆችን የታችኛውን የስብእና ኣካል የሆነውን ኢድ (id) ነው ሊጠቀምበት የሚሻው። ቅጽበታዊ አካባቢያዊ ርካታዎችን በማጉላት የሚቀሰቅስ ሲሆን ይህ ነገር የቡድን አባላት ስሜት ቢያስነሳ ኣይገርምም። ኣንድ ዘውጌኛ ካድሬ ሱፐርኢጎን ማለትም የሰዎችን ከፍ ያሉ የሞራልና የመርህ ፍላጎትች ተጭኖ የቡድኑን ኣባላት በመቀስቀስ ጥፋት ሊያመጣ ይችላል። ሰው ለምን ይሀን ይከተላል? ፍጹም ስላልሆንና አንዳንዴ በስሜት የምናደርጋቸው ጉዳዮች ስላሉ። ለዚህ ነው ፖለቲካ ሃላፊነት የተሞላበት የቅስቀሳ ስራ እንዲሰራና፣ የሰው ልጆችን ከፍተኛ የመርህ ስብእና በማዳበር ላይ ያተኮረ ፕሮግራም እንዲኖረው የሚያስፈልገው። በ1997 ዓ .ም በሰላም ኣገር የወያኔ መንግስት በቅንጅት መሪዎች በመድረክ በዝረራ ሲሸነፍ ቶሎ ወደ ጓዳው ሮጦ የመዘዘው ሰይፍ “ኢንተርሃሞይ” የሚል ነበር። በመርህ ላይ መወዳደር ሲያቅተው ቶሎ ብሎ ወደ ስሜት ቅስቀሳ የገባው የቆመበት የፍልስፍና መሰረት ይሄው በመሆኑና በክፉ ጊዜ አንድን ቡድን በስሜት በማነሳሳት ስልጣኑን ማቆየት ዋናው መሳሪያ በመሆኑ ነው። ይህ የፖለቲካው ተፈጥሮ ነው። በአለማችን የተደረጉ የዘር ማጥፋት ድርጊቶች በስሜት ላይ በሚነዱ መሪዎች የተደረጉ ቅስቀሳዎች ነበሩ። የኣንድን ተፈጥሮኣዊ ቡድን ማንነት በማራገብና የቡድኑን ኣባላት በከፍተኛ ስሜት ውስጥ በመክተት ይህ ቡድን ለህልውናህ ጸር ነው በሚል ወንጀል ያስፈጸሙ መሪዎች ብዙ ኣሉ። አካባቢያዊ ጥያቄዎችን በማጉላትና ሱፐርኢጎ የተባለውን የሰው ልጆች ስብእና መሰረት በመጫን በብሄራዊ ደረጃ ወይም በማህራዊ ደረጃ ትክክል ነው ኣይደለም የሚለውን ፍርድ የቡድን ኣባላት እንዳያደርጉ በማዋከብና ኢድ እንዲያሸንፍ በማድረግ ወንጀል ያስፈጸሙ ህዝብን ያሳሳቱ ብዙ ፖለቲከኞች ኣሉ። ለምሳሌ ሩዋንዳ ውስጥ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ይፈጽሙ የነበሩትን ግለሰቦች ስናይ ፖለቲከኞች በስሜት እንዲሰክሩ ስላደረጓቸው ነበር። የብሄር ማንነታቸውን በማራገብና የቱትሲ አባላት ለሁቱዎች ፍላጎት ጠላት እንደሆኑ ኣድርጎ በማሳየትና ኣባላት ሱፐር የሆነውን መርህና ሰብዓዊነትን የሚመዝነውን የሰውነት ክፍላቸውን በመጫን የሃይማኖትና የባህል ቆባቸውን ሳይቀር በማስጣልና በማሳበድ ዓለም የማይረሳውን ወንጀል እንዲፈጽሙ ኣድርገዋል። በኢንተርሃሞይ ቅስቀሳ ያበዱት ሰዎች በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ነበሩ። በ 1994 E.C ሩዋንዳ ውስጥ ለመቶ ቀናት በየሰዓቱ ወደ ሶስት መቶ ሰላሳ ኣራት ሰዎች ይታረዱ ነበር። አገር በኢንተር ሃሞይ ኦፐሬሽን ኣብዶ ነበር። ወንጀሉ የተፈጸመው በስሜት ነው:: ኣይገርምም? በስሜት ስምንት መቶ ሺህ የሚሆኑ ዜጎች በመቶ ቀናት ብቻ አልቀዋል። ወንጀሉ ካበቃ በሁዋላ ሰው ሁሉ ወደ ነፍሱ ሲመለስ እየተላቀሰ ይቅርታ…. በስሜት ነው ያደረኩት…ራሴን አላውቅም ነበር…. በማለት ሲጠይቁ ይታያል። ከዓመታት በፊት አንድ ጊዜ በአንድ አለማቀፍ ኮንፈረንስ ላይ አንድ ሩዋንዳዊ ወጣት አግኝቼ ነበር። ትንሽ አወጋኝ። ይህ ወጣት ከአጠቃላይ ቤተሰቡ ለምልክት የተረፈ ነበር። የቱትሲ ጎሳ ኣባል ነው። ወደዚህ ኮንፈረንስም የመጣው ለጉባኤው ምስክር ይሆን ዘንድ ነበር። በጣም ያሳዝናል። ከቤታቸው ድረስ መጥረቢያ ይዘው እየገቡ ጨፍጭፈዋቸዋል። ጨፍጫፊዎቹ በትክክል በፖለቲከኞቹ ፕሮፓጋንዳ ሰክረው ኣብደው ነበር።

ለዚህ ነው በደም፣ ወይ በሃይማኖት ወይም በባህል ትስስር ላይ የቆመ ኣስተዳደራዊ ኣይዲዮሎጂ ኣደገኛ ነገር ኣለው የሚያስብለው። ከኣንድ በላይ ባሉ የቡድን ኣባላት በኣንድ መንግስት ስር ራሳቸውን ካገኙ በሁዋላ የጋራ ኣስተዳደር መስርተው ለመኖር ካማራቸው የመጀመሪያው ርምጃ ፖለቲካቸውን ከዘውግ ነጥቀው ማውጣት ነው። ኣገር ይህን ይጠይቃላ። የጋራ ኣገር መመስረት ካስፈለገ ያ የጋራ ኣገር ወደ ህልውና የሚመጣው ቢቻል ከሁለቱ ቡድኖች ውጭ ባለ የጋራ ማንነት ላይ ሲቆም ነው። ይህ ሲሆን ግን ቡድኖች ኣንድ የሚያደርጉት ነገር ኣለ። ቋንቋና ባህላቸውን ሜዳ ላይ መጣል ሳይሆን ይህንን ባህላቸውን በሌላ የባህል ኣሰተዳደር ለማስተዳደር ቢስማሙ ጥሩ ነው። ኣንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ፈጥረው በሌላ በኩል ደግሞ ባህላዊ ጉዳዮቻቸውንና ቋንቋቸውን በተለየ ኣስተዳደር መምራት ይችላሉ። ፕሮፌሰር መሳይ የግለሰቦች መብት መከበር ብቻውን ዘውግ የሚያነሳውን ጥያቄ አይመልስም ብለዋል። ይህንን እቀበላለሁ። የግለሰብ መብት ተከበረ ማለት የቡድንም መብት ተከበረ ማለት ነው የሚለው ኣሳብ የቡድኖችን መብቶች ለንፋስ ያጋልጣቸዋል። ነገር ግን የቡድን መብት ምንድን ነው? የሚለው ላይ ነው ብዙ ማስብ የሚጠይቀው። ቡድን እንደ ቡድን የሚይዟቸው እንደ ቋንቋና ባህል ወግ ልማዶች ዋናዎቹ ናቸው። እነዚህን መጠበቅ በጣም ኣስፈላጊ ነው። ይህ ማለት ግን ዘውጌኛ ፖለቲካ መቀፍቀፍ ማለት ኣይደለም። የቡድኖችን መብት መጠበቅና የዘውግ ፖለቲከኛ መሆን ለየቅል ናቸውና።

ኣገር ሲመሰርቱ ሁሉን ወዶ ኣይሆንም። ከዚህ በፊት በጻፍኳት ጦማር ላይ እንደገለጽኩት ኣገር መስዋእትነትን ይጠይቃል። ኣገር ግዙፍ ጉዳይ ነው:: ቡድኖች አገር ሊመሰርቱ ወጥተው ደግሞ ሰስተው አይሆንም። የዓለም ኣገራት ሁሉ የቆሙትና ወደ “እኛ ህዝቦች” የተሻገሩት እያዋጡ እያደባለቁ ነው። ኣገር እንዲሁ በሰንካላ ምልክቶችና በሆታ ኣይቆምም። የጠራ ኪዳን ይጠይቃል። ወደ ፕሮፌሰር መሳይ የመፍትሄ ኣሳብ እንመለስና እሳቸው የሚሉት ኢትዮጵያ ውስጥ የዘውግ ፖለቲካ ይጠፋል ማለት ዘበት እንደሆነ ነው። ዘበት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ጎጂ ኣሳብም ነው ይላሉ። ይልቅስ የዘውግ ፖለቲካንና ብሄራዊ ኣንድነትን ኣብሮ የሚያስኬድ ሞደሬት ኣሳብ ያስፈልጋል ይላሉ። ዋናው ጥያቄም እዚህ ጋር ነው እንግዲህ። እንደሚመስለኝ እሳቸው ራሳቸው በጥቂቱ priordialist ናቸው። ይህ ደግሞ ከዘመናዊው ኣስተዳደር ጥበብ ከዴሞክራሲ ጋር አይጋጭም ወይ። ቡድኖች ከስሜት ወጥተው በመርህ ላይ ካልቆሙ በፌደራል ስርዓትም ሆነ በአሃዳዊ ስርዓት ስር መኖር ኣይችሉም። በዘውግ ፖለቲካና በብሄራዊ ፖለቲካ መካከል ሞደሬሽን የለም። ሁለቱም ቁጭ ብለው የሚወያዩ በአይዲዮሎጂ የተጋጩ የፖሊሲ ጉዳይ የሚያፋጫቸው ኣይደሉም። በዴሞክራሲያዊ መንገድ ስልጣን እየተለዋወጡ በህዝብ ድምጽ ኣሸናፊና ተሸናፊ አየሆኑ የሚኖሩ ኣይደሉም። ጽንፍ የወጣ ልዩነቶች ያላቸው ስለሆነ ሃገሪቱን ቀጣይ በሆነ ህይወት ውስጥ እየተፈራረቁ አይመሯትም። ወይም ደግሞ ኣገሪቱ የፖለቲካ መሰረቷን በዘውግ ላይ ኣድርጋ ለጋራ ጉዳይ ፌደራል ላይ እንገናኝ ከሆነ ይህ ኣይነት የፖለቲካ ኣሰላለፍ በኮንፌደሬሽን ኣይነት ስርዓት ካልሆነ በፌደሬሽን ስርዓት የሚቻል ኣይሆንም። በእንዲህ ዓይነት ስርዓት ላይ ኣንድ ዘውግ ሾልኮ ሃይለኛ እንዲሆንና ብሄራዊ ተቋማትን ሃይጃክ ኣድርጎ እንዲኖር በር ይከፍታል። በብሄር ፖለቲካ ጊዜ ኣንድ በብሄር ላይ የቆመ ሃይለኛ ቡድን ሲኖር ደግሞ ያ ቡድን ኣምባገነን ሆኖ ጥቂት መኖር ይቻላል። ይሁን እንጂ ሁሉም የዘውግ ፖለቲከኞች ጥቂት የሃይል መመጣጠን ካላቸው የፖለቲካው መሰረት ራሱ ለመርህ የማይጨነቅ በመሆኑ ኣገሪቱን ወደ ኣለመረጋጋት ከማምራቱም በላይ ወደ እልቂት ሊወስድ የሚችል ነገር ነው። በተለይ በኢኮኖሚ ያልዳበርን መሆናችንን ተከትሎ በብሄራዊ ሃብት ክፍፍል ዙሪያ ችሮች ሲከሰቱ ቶሎ ዘውጋዊ ጥያቄ ሆነው ስለሚመጡ ኣገሪቱን ወደ ኣለመረጋጋት ነው የሚወስድብን። የዘውግ ፖለቲካ ሌላው ትልቅ ችግር ደግሞ የተፈጥሮ ሃብት ክፍፍል ላይ የሚፈጥረው ግዙፍ ችግር ነው። በመሬት አጠቃቀም፣ በማእድናት አጠቃቀምና በመከፋፈል በኩል ችግሮችን ያመጣል። በብሄራዊ ሃብትና በዘውግ ሃብት መካከል ግጭቶችን የሚያስነሳ ሃይል ይኖረዋል። ይበልጥ ፕሮፌሰር መሳይን ለመጠየቅ እንድንችል ኣሳባቸውን በቀጥታ እንመልከት።

ፕሮፈሰር መሳይ የወደፊቷ ኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ያለባት እንድትሆን ኣሁን ያለውን ክልል ማጥፋት ተገቢ ኣይሆንም ይላሉ። የሚሻለው እነዚህን ክልሎች ተቀብለን በዘውጎች መካከል ኣብሮ መስራትን ማበረታታት ነው ይላሉ። በርግጥ የሚነግሩን ኣሁን ስላሉት ሰለነዚህ ዘጠኝ ክልሎች መሆኑ ነው? እነዚህ ዘጠኝ ክልሎች ምንድናቸውና ነው በኣዲሲቱ ኢትዮጵያ የማይነኩት? ማን ፈጠራቸው? ተፈጥሯቸውስ ምን ይመስላል? የሚለውን ማንሳት ተገቢነው። ኢትዮጵያ ስትፈጠር ዘጠኝ ክልል ኣልነበረችም። ኢትዮጵያ ከሰማኒያ በላይ ብሄር ያላት ኣገር ናት። በዘጠኝ የተሸነሸነችው በአቶ መለስ ነው። ኣቶ መለስ ለምን በዘጠኝ እንደከፈሏት የሚያውቅ እስካሁን ኣልተገኘም። ክልሎቹ በዘውግ ላይ የተመሰረቱም እንኳን ኣይደሉም። ኣብዛኛዎቹ ክልሎች ህብረ ብሄራዊ ይዘት ኣላቸው። በተለይ ደቡብን ካየን በዘውግ የማይገናኙ ቡድኖች የሚኖሩበት ከመሆኑም የተነሳ ከሌሎች በተለየ በአሁኑ ሰዓት በዘውግ ላይ የቆመ ፖለቲካ አፍርሷል። ፕሮፌሰር መሳይ የደቡብ ህዝብ የተገላገለውን እንደገና ወደ ዘውግ ፖለቲካ ይመለስ ሊሉ ነው? የደኢህዴን አባላት ማለት(የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) በዚህ ክልል ስር ያሉ ወደ ኣምሳ ስደስት የሚደርሱ ዘውጎች ፖለቲካዊ ዘውጋዊ ማንነታቸውን በመልክዓምድር ላይ ለቆመ ኣዲስ ማንነት መስዋእት ኣድርገውና ተዋህደው ይታያል። በ 1995 ዓ.ም የየብሄሩን የዘውግ ፓርቲዎች ኣፍርሰው ኣንድ ወጥ ክልላዊ ፓርቲ ኣቋቁመናል ነው የሚሉት።

ይህ የሚያሳየው በአሁኑ ሰዓት በህወሃት (ኢህዓዴግ) ስልጣን ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ዘውጎች ኣብዛኛው ዘውግ ፖለቲካዊ ዘውጋዊ ማንነቱን የሰዋበት ሁኔታ ነው ያለው ማለት ነው። ይሄ ከግንዛቤ መግባት ኣለበት። የደቡብ ህዝብ መፈክርም ኣንድነት ሃይል ነው፣ እኛ የደቡብ ህዝቦች ኣንድ ነን የሚል ነው። ምን ኣልባት ወደ ፊት ያንን ለመልክዓ ምድራዊ ትስስር የሰውትን ዘውጋዊ ፖለቲካቸውን ለሰፊዋ ኢትዮጵያ ይሰውታል። ለጊዜው ግን ደቡብ በዘውግ ላይ የቆመ ፖለቲካው ረግቧል። ሌሎች ክልሎችን ለምሳሌ ሃረሪን፣ በንሻንጉልን፣ ጋምቤላን ብንወስድ ህብረ ብሄራዊ ናቸው። ከአንድ በላይ ብሄርን የያዙ ዘውጎች ኣቶ መለስ በሰጧቸው ክልል መሰረት ይኖራሉ። ኣንድ የክልል ህገ መንግስት ይዘው እስካሁን ኣሉ። እነዚህን ክልሎች እንደማይነኩ ኣድርጎ ማቅረቡን ፕሮፈሰር መሳይ እንዴት እንዳዩት ኣላውቅም። ኣንዱ ጉዳይ ይሄ ነው። ወጥ የሆነ ኣሰራር የሌለውና ምን ኣይነት መርህ እንዳለው የማይታወቅ የአቶ መለስን ክልል መንካቱ ትክክል ኣይሆንም ማለት መነሻው ኣልገባኝም። በርግጥ ኣዲሲቱ ኢትዮጵያ ልታስብበትና ልታስተካክለው የሚገባው ዋና ጉዳይ ይህ የክልል ጉዳይ ነው። ስለ ዘውግ ፖለቲካ ሌላው በኢትዮጵያ ሁኔታ መታሰብ ያለበት ነገር ደግሞ ከሁለትና ከሶስት ከዚያም በላይ ዘውጎች ተቀይጦ የተወለደውን ትውልድ ነው። ይህ ትውልድ በቁጥሩ ካሉት ሰማኒያ ሁለት ገደማ ብሄሮች ሰማኒያ የሚሆኑትን ይበልጥ ይመስላል። በግዙፎቹ ብሄሮች ማለትም በኦሮሞና በኣማራ ነው የሚቀደመው። ከትግራይ፣ ከሲዳማ፣ ከአኙዋክ፣ ከደራሼ ወዘተ ብሄሮች ሁሉ በቁጥሩ ይበልጥ ይበልጥ ይመስላል። ነገር ግን ይህ በቁጥሩ በሶስተኛ ደረጃ ኣካባቢ የሚገኝ ሰፊ ኢትዮጵያዊ መሬት የለውም። ክልል የለውም። ይህ ቡድን ኢትዮጵያዊነትን እንደ ብሄር ወስዶ መኖርን እንደሚመርጥ ብዙ ጊዜ ይታያል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በምስለት ባህር ላይ የዋኙና የተመቻቸው የማንም ብሄር መባል የማይፈልጉና ኢትዮጵያዊ ብቻ መባል የሚሹ ብዙ ሰዎች ኣሉ። የነዚህን የፖለቲካ ተሳትፎም ማገናዘብ ጠቃሚ ነው። ደግሞ ይህ ቁጥር ገና ያድጋል። የወደፊቱን ማየት አለብን:: ምን ኣልባትም ከዓመታት በሁዋላ በቁጥሩ ሁሉንም ብሄሮች በልጦ ኣንደኛ ይሆናል። ስለዚህ እነዚህን ተለዋዋጮችም ከግምት ስናስገባ የዘውግ ፖለቲካ በኢትዮጵያ ሜዳ ላይ ሊጥላቸው የሚችላቸው ብዙ ዜጎች እንዳሉና ዘውጋዊ ፖለቲካ ረጅም እድሜ የሌለው እንደሆነ ይታያል።

ሌላው መታሰብ ያለበት ጉዳይ ደግሞ የዘውግ ፖለቲካና የወያኔ የብሄር ፌደራሊዝም የሚያመጣውን የዴሞክራሲ ችግር (Democratic deficit) ነው። የወያኔ አባላትም ይህንን ነገር ይቀበላሉ። ከክልላቸው ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የፖለቲካ ተሳትፎ የሚገድብ ዴሞክራሲን ለማንሸራሸር የሚያስቸግር መሆኑን ማየት ይቻላል። በአሁኑ ሰዓት በኦሮምያ ብቻ 11 ሚሊዮን ኣማራዎች ይኖራሉ። የሃረሪ ክልል፣ የቤንሻንጉል ክልል፣ የኣፋር ክልል፣ የጋምቤላ ክልል፣ የትግራይ ክልል እና የሶማሌ ክልል ህዝብ ብዛት ተደምሮ በኦሮምያ ውስጥ የሚኖረው አማራ በቁጥር ይበልጣል። ከኦሮምያ ክልል ውጭ በአማራና በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ከብዙ የደቡብ ብሄሮች በቁጥር ይበልጣሉ። በተለያዩ ክልሎች ኢትዮጵያውያን ተበትነው አገሬ ብለው ይኖራሉና የዘውግ ፖለቲካ ኣንዱ ችግር ይህን ግዙፍ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ተሳትፎ ይገድባል ሰፊ Democratic deficit አለው።

ለአብነት የሃረሪን ክልል ስናይ የኢትዮጵያን የፌደረል ስርዓት ውጥንቅጥ በሚገባ ያሳያል። ፕሮፌሰር መሳይ እንደሚያውቁት ሃረሪ የቆዳ ስፋቷ 334 ኪሎ ሜትር ስኩየር ያህል ሲሆን 183,415 የሚሆኑ ወንድና ሴት ኢትዮጵያውያንን ይዛለች። ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በህዝብ ብዛት ታንሳለች። ይህ ክልል ሲዋቀር ለብቻው አንድ ክልል ይሆን ዘንድ የሚቀሰቅስ ምን ነገር እንዳለ አይታወቅም። የሆነ ሆኖ ግን ከሌሎች ክልሎች በጣም በተለየ መንገድ የሚታይ ጉዳይ አለው። ሃረሪ ካሏት ህዝብ መካከል 56.4% ኦሮሞዎች፣ 22.7% አማራዎች፣ 4.3% ጉራጌዎች፣ 1.53 % ትግሬዎች፣ 8.65% ሃረሪዎች፣ 1.26% አርጎባዎች ናቸው:: ይህ ክልል ሲዋቀር ከሃረሪ ከተማ በተጨማሪ አስራ ዘጠኝ ወረዳዎች ከኦሮምያ ተጨምረውበት እንደሆነ በዚህ ዙሪያ ጥናት ያካሄዱ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። የኦሮሞው ቁጥር በአንደኛነት የበዛውና ከአጠቃላዩ የህዝብ ብዛት ከግማሽ በላይ የሆነው እነዚህ ቀበሌዎች ስለተጨመሩ ነው ማለት ነው። የሃረሪ ክልል የተቋቋመው ሀረሪ ባህሏን እንድትጠብቅ ነው እንዳይባል እጅግ ብዙ ኦሮሞዎችን ከኦሮምያ ክልል ኣምጥተው አቀላቅለዋቸዋል። ይህ ሁኔታ ደግሞ ብዙሃን ቡድን ኣነስተኛ በሆነው ህዝብ ላይ ሲጨመር የባህልና ቋንቋ መዋጥን ያመጣል እንጂ ለባህል ቀጥታ እድገት ኣይረዳም። በዚህ ክልል አወቃቀር ጊዜ ምንም ተጠይቅ የማይታይ ብቻም ሳይሆን የሚገርምም ነው። የክልሉ ባለቤት የሆነው 8.65% የሚሆነው ህዝብ ሲሆን 91% በላይ የሆነው ህዝብ የዚህ ክልል ዋና ባለቤት አይደለም:: ፕሮፌሰር መሳይ ይህንን ምን ይሉታል? የሃረሪ ክልል የኢትዮጵያ ፌደራል ስርዓት ውጥንቅጥ ማሳያ ናት። እንዲህ ዓይነት ለዴሞክራሲ መንሸራሸር ኣስቸጋሪ የሆነ ሳይንስ የጎደለው ክልል ያልተነካ ከቶ ምን ሊነካ። የወልቃይት ጠገዴ ጠለምትን ጉዳይ ስናይ የወያኔ ክልል ሲበዛ ችግር ያለበት መሆኑን እናያለንና እንዲህ ዓይነት ክልሎች በሚገባ መስተካከል ኣለባቸው።

ፕሮፈሰር መሳይ በዋናው የመፍትሄ ኣሳብ ባሉት ክፍል ላይ ሲያቀርቡ ኣገሪቱ ዘውጋዊ ፖለቲካንና ብሄራዊ ኣንድነትን ኣቻችላ እንድትኖር ይመክሩና በዘውግና በብሄራዊ ኣንድነት መካከል መጣጣምን የሚያመጣ ነው ካሏቸው ኣሳቦች ውስጥ ኣዲሲቱ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ተቋማትን፣ ብሄራዊ መግለጫዎችንና ምልክቶችን ማጎልበት እንደሚረዳት ይገልጻሉ። ይሄ ኣሳብ በጣም ኣሳባዊ ኣይደለም ወይ? ነው ጥያቄው። የዘውግ ፖለቲካ እውቅና ኣግኝቶ ከተንሰራፋ በሁዋላ የዘውጎች መቀራረብ እንዲኖር መካከለኛነት እንዲመሰረት ይመክራሉ። ለመሆኑ ይህ መካከለኛነት ከየት ይመጣል? ዜጎች ይህን የመካከለኛነት ስሜት ሊያዳብሩ የሚችሉበትን፣ ይህን የመካከለኛነት ባህል ሊያደብሩ የሚችሉበትን ግሩም እርሻ መቼ ኣዘጋጀን? መካከለኛነት እኮ የባህርይ ለውጥ ነው። ይህን ለውጥ የሚያመጣው ደግሞ የፖለቲከኞችን ተክለ ሰውነት መካከለኛ ኣድርጎ የሚቀርጽ የፖለቲካ እምነት ነው። መጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ፣ መጀመሪያ ትግሬ ነኝ፣ መጀመሪያ ኣደሬ ነኝ ወዘተ ከሚል የፖለቲካ ስሜትና ኢትዮጵያዊነትን በስሱ ከሚያሳይ የፖለቲካ እምነት እንዴት የመካከለኛ ኣገልግሎት ሰጩ ካህናትን ለማግኘት እንሞክራለን? በዘውግ ፖለቲካ ስር ያደጉና የዘውግ ፖለቲካ የቀፈቀፋቸው ፖለቲከኞች ኣዲስ ኣበባ ሲገናኙ ደርሶ ድንገት መካከለኛ ሊያደርጋቸው የሚችል ምን መሰረት ይኖራል። በስብሰባ ከዛሬ ጀምሮ መካከለኛ እንሁን እያሉ በማወጅ ይህ የመካከለኛነት ኣገልግሎት ስሜት ኣይዳብርም። በዘውግ ላይ የተመሰረቱ ፖለቲከኞች፣ ዘውጋቻውን ኣጥብቀው ይዘው በሚታገሉበት የፖለቲካ ድባብ ስር የዘውግ ፖለቲካ ልእልና በረበበበት ኣገር ውስጥ በርግጥ ብሄራዊ ተቋማትን ማጎልበት ይቻላል ወይ? የሚል በጣም ሃቀኛ ጥያቄ መነሳት ኣለበት። የፖለቲካው መሰረት ዘውግ ሆኖና ኣካባቢያዊ ማንነቶች ጡንቻቸው በፈረጠመበት ኣገር እነዚህ ብሄራዊ ተቋማት የሚባሉት ለሃይለኛው የዘውግ ፖለቲካ ድርጅት መጠቀሚያ ከመሆን ኣልፈው በራሳቸው በሁለት እግራቸው የሚቆሙበት መሬት ኣያገኙም። እርሻው ኣይመችምና ኣይበቅሉም።

መቼም ክርስቶስ ግሩም ኣስተማሪ ነው። ኣንድ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ሲያስተምር ስለ ዘር ያስተምራቸው ነበርና እንዲህ ኣለ። “እነሆ፥ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀና ወፎች መጥተው በሉት። ሌላውም ብዙ መሬት በሌለበት በጭንጫ ላይ ወደቀና ጥልቅ መሬት ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ ፀሐይም ሲወጣ ጠወለገ፥ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ። ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፥ እሾህም ወጣና አነቀው፥ ፍሬም አልሰጠም። ሌላውም በመልካም መሬት ላይ ወደቀና ወጥቶ አድጎ ፍሬ ሰጠ፥ አንዱም ሠላሳ አንዱም ስድሳ አንዱም መቶ አፈራ።” ይላል። በርግጥም ዘውግን ባስቀደሙና ፖለቲካዊ ማንነታቸውን መስዋእት ለማድረግ በሰሰቱ ቡድኖች እርሻ ላይ ብሄራዊ ተቋማት ይጎለብታሉ ማለት ከንቱ ምኞት ነው። በቡድኑ ጥቅም የሰከረ ፓርቲ ሃይለኛ ሆኖ ስልጣን ሲይዝ እነዚህን ምልክቶች እያጠፋ ብሄራዊ ተቋማቱን ለራሱ መጠቀሚያ እያደረገ ይኖራል። ሁል ጊዜም በእንዲህ ኣይነት ኣስፈሪ ግዛት ውስጥ የሚኖሩ ተቋማት ይሆናሉና ይሄ እንዴት መፍትሄ ኣሳብ ሊሆነን ይችላል? ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ያመጣልናል ወይ? የሚለው ጉዳይ በጣም ትልቅ ጥያቄ ነው።ፖለቲካውን ዘውጌ ኣድርገን ስለብሄራዊ ምልክቶች ትምሀር ቤት ብናስተምር ምንም ጠብ ኣይልም። ብሄራዊ ተቋማትም ይሁኑ ምልክቶች የሚባሉት ሁሉ ጉልበት ኣይኖራቸውም። ይህን የሚያደርገው ወያኔ ብቻ ኣይደለም። ማንም በዘውግ ላይ የቆመ ሃይለኛ ፓርቲ ሲመጣ እነዚህን ምልክቶች መጠቀሚያ ነው የሚያደርጋቸው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ሃገርን የሚያህል ነገር እንዲህ በጣም በቀጠነ ምልክት ለማቆም መሞከሩ ራሱ ለመረጋጋት መፍትሄ ኣይሆንም ብቻ ሳይሆን ኣለመረጋጋትን የሚያመጣ ነው።

ኣንዱ የፕሮፌሰር መሳይ የመፍትሄ ኣሳብ ችግር ይሄ ነው። አገርን የሚያህል ግዙፍ ማንነት በጣም በቀጠነ ምልክት ሊያቆሙ ይፈልጋሉ። ብሄራዊ ተቋማትንና ምልክቶችን መገለጫዎችን በዘውግ ፖለቲካ መሃል ኣብቦ ማየት ይፈልጋሉ። ዘውግ መኖሩ በራሱ ኣይደለም ችግሩ። ዘውጎችማ ይኑሩ። ጥንካሬና ውበት ይሆናሉ። ዘውግን ማጥፋት ሳይሆን ነገር ግን ዘውጎች ተሰባስበው መኖር ሲሹ ኣንድ የጋራ ኣዲስ ማንነት መፍጠር ኣለባቸው:: ይህ ማንነት ማንንም ሳይጨፈልቅ መሆን ኣለበት። ቡድኖች የጠሉት ነገር ብሄራዊ ማንነት ሲፈጠር ቡድኖችን እየጨፈለቀና በኣንዱ ቡድን ኣምሳል ሌላው እየተቀረጸ መሆኑን ነው። ይህንን ማስተካከል በርግጥ ያስፈልጋል። ሁለት የተለያዩ ባህል ያላቸው ቡድኖች ኣንድ የጋራ ቤት መስራት ካማራቸው ኣንድ ሌላ ሶስተኛ ባህል ኣምጥተው ያ ሶስተኛ ባህል ሁለቱንም ቡድኖች ሊያያይዛቸው ይችላል። ይህ ሶስተኛ ባህል ደግሞ ዴሞክራሲ ሊሆን ይችላል። ይህ ባህል የሁሉ የጋራ ከሆነ ፖለቲካዊ ማንነታቸውን በኣንድ ድንኳን ስር ለማድረግ እንዴት ይሳናቸዋል።

ሁለተኛው የፕሮፌሰሩ ኣሳብ ደግሞ የዘውግ ፖለቲካና ብሄራዊ ኣንድነት ሳይቃረኑ ይኖሩ ዘንድ ፕሬዚደንታዊ ኣስተዳደር የመከከለኛነት ኣገልግሎት በመሰጠት ሊያገለግል ይችላል ይላሉ። ፕሬዚዳንታዊ ሲሆን በቡድኖች ምርጫ የሚመጣው ፕሬዚደንት የብሄራዊ ኣንድነት መገለጫ ምልክት ሆኖ ይኖራል ማለት ነው። ይሄም ጥያቄ ኣለበት። በዘውግ ፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ ያደገ ፕሬዚዳንት ልንመርጥ ነው ማለት ነው። ይህን ፖለቲካዊ ስብእና የያዘን ሰው የቱንም ያህል ህግ ቢኖር በህግ የበላይነት ላይ ጥያቄ ያስነሳል። ዋናው ተፈላጊው ነገር ህጉ ብቻ ሳይሆን የባህሪ ለውጥ ነው። የሚፈለገው የዳበረ ጸባይ (character)ና ፖለቲካዊ ስብእና ነው። በፕሬዚደንቱ ህይወት ውስጥ ከውስጥ የሚመነጭ የሃገር ፍቅር ስሜት ነው እንጂ መለኪያው ጥሩ ህግ ኣውጥቶ ኣንድ ዘረኛ ቢመጣ ያው ህጉን መጫወቻ ነው የሚያደርገው። የህወሃት ሰዎች ይሄውና ጥሩ ህግ እያሳዩ ኣይደል የሚጫወቱብን። ኣድልዎ የሚፈጽሙት የፖለቲካ ስብእናቸው ኣካባቢ ችግር ስላለ ነው። ከውስጥ የሆነ የባህሪ ለውጥ ነው የሚያስፈልገን። ይህ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ዋናው ችግር ኣገሪቱ በከፍተኛ የዘውግ ፖለቲካ ስር ባለችበት ሰዓት የምርጫ ጉዳይ በሚገባ መጠናት ኣለበት። በዘውግ ጊዜ ብሄራዊ ምርጫ ሁል ጊዜ ለማንነት ድምጽ (identity vote) በከፍተኛ ሁኔታ ይጋለጣል። ከራሱ ከፕሬዚዳንቱ የፖለቲካ መሰረትና ስብዕና በተጨማሪ ዜጎችንም በማንነት ድምጽ ውስጥ ወስዶ የሚዘፍቅ የፖለቲካ ከባቢ በሚኖርበት ኣገር ውስጥ ገለልተኛና የሁሉ ኣባት የሚሆን ፕሬዚዳንት መፈለግ ላም ካልዋለበት ሜዳ ኩበት ለቀማ መውጣት ኣይሆንብንም ወይ ነው ጥያቄው። ሰፊው ፖለቲካዊ ስልጣን በዘውገኞች ተይዞ ኣንድ ፕሬዚዳንት ብንመርጥስ ይሄን ያህል ምን ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ፓርላማውም ይሰራ ዘንድ ከማንነት ፖለቲካ መጽዳት ኣለበት። ምን ኣልባት ኣገሪቱ በኮንፌደሬሽን ኣይነት ኣስተዳደር ስር ከተዳደረች ትክክል ነው። ፕሮፈሰር ያነሷቸው ምልክቶች ሊሰሩ ይችላሉ። ነገር ግን በፌደራል ስርዓትና በኣሃዳዊ ስርዓት ውስጥ እነዚህ ያነሷቸው ምልክቶች በተግባር ኣሜኬላ ያለባቸው በመሆኑ ሊሰሩ የማይችሉ ናቸውና ለዚያች ኣገር መፍትሄ ይሆናል ወይ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ሌላው የዘውግ ፖለቲካ እንዳይነካ የሚፈልጉትን ፕሮፌሰር መሳይን መጠየቅ ያለብን ነገር የቀመር ጉዳይን ነው። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በቁጥራቸው እጅግ የሚራራቁ ብሄሮች የሚኖሩባት ኣገር ናት። እነዚህ ዘውጎች ከፍተኛ የሆነውን ስልጣን በምን ቀመር ሊከፋፈሉት ነው? በህዝብ ብዛት ከሆነ በቁጥራቸው የሚያንሱትን ቡድኖች ተስፋ የሚያስቆርጥ ከመሆኑ የተነሳ ወደ መገንጠል ሊወስዳቸው ይችላል። በከፍተኛ ቁጥር ኣካባቢ ያሉትም ፉክክር መግባታቸው አይቀርም። አንዱ የሚገጥመን ትልቅ ችግር ይሄ ነው። የጠራ ቀመር እናጣለን። ይህ ደግሞ ውሎ ሲያድር አለመረጋጋትን ያመጣል።

ከሁሉ በላይ ግን ፕሮፌሰር መሳይ ከበደን ወደዚህ ኣሳብ ምን ኣመጣቸው? የሚለውን ነገር ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል። እንደሚመስለኝ ፖለቲካዊ ዘውገኝነትን በኢትዮጵያ ከሚገባው በላይ ኣጉልተው ያዩት ይመስላሉ። በጣም ስር የሰደደና ወደፊትም ጨርሶ የማንላቀቀው ኣድረገው ከማሰብ የመጣ ይመስላል። አለም ሁሉ ከዘውግ ፖለቲካ እየተላቀቀ ወደ ዴሞክራሲ ኣድጎ ሳለ ኢትዮጵያ ከዘውግ ፖለቲካ እስከ ሃቹ መውጣት እንደማትችል ኣድርገው ለምን ያስባሉ? ኢትዮጵያን ለምን ከዓለም ያወጧታል? ከዘውግ ወደ ዴሞክራሲ ወደ መርህ ፖለቲካ ማደግ እኮ የሰው ልጆች የእድገት ውጤት ነው። የመማር ውጤት ነው። ስለዚህ ይህን የፕሮፈሰሩን ኣሳብ እቃወማለሁ። መሬቱ ላይ ያለው እውነት ከፕሮፈሰር መሳይ የተለየ ነው የሚመስለኝ። ከፍ ሲል እንዳልኩት ብዙው የኢትዮጵያ ቡድን የደቡብ ህዝብ የዘውግ ፖለቲካ የለውም። በኣሁኑ ዘውግ በጣም ገነነ በተባለበት ዘመን እንኳን ማለቴ ነው። ሌላው ጉዳይ ደግሞ ዘውጌኛ ፖለቲካ በኢትዮጵያ መሰረተ ቢስ መሆኑን ለፕሮፌሰር መሳይ መግለጽ እወዳለሁ። በሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ የተጠላ ነው።ሰፊ ህዝባዊ መሰረት የለውም ማለቴ ነው። ኣንዱ ይሄ ነው። ሌላው ጉዳይ ግን ፕሮፌሰር ኣልማርያም ያሉት ጉዳይ ነው። ፕሮፌሰር ኣልማርያም በዚሁ ስብሰባ ወቅት ኣሜሪካውያን ከመላው ኣለም ተሰባስበው “እኛ ህዝቦች….” ማለት ከቻሉ እኛ ኢትዮጵያውያን ተስኖናል ብሎ ማሰቡ ትክክል ኣይደለም። የዘውግ ፖለቲካ በኢትዮጵያ በጥቂት ኤሊቶች የተጫነብን እንጂ የመረጥነው ኣድርጎ መቅረብ የለበትም። ሌላው መሰረታዊ ጉዳይ ደግሞ የዘውግ ፖለቲካ ስንል በኢትዮጵያ ምን ማለት ነው? ተብሎ መተንተን ኣለበት። በኢትዮጵያ ውስጥ ወገን ለይ ብሎ ብቅ ያለው ፖለቲካ ሃይማኖት ኣይደለም። የቋንቋና የባህል ቡድነኝነት ነው።ይህ ልዩነት ደግሞ ከዘር ልዩነት በታች ነው። ባህላዊ ቡድኖች የፖለቲካ ስልጣን ኣምሯቸዋል። ምንም እንኳን ብዙሃኑን ባይወክሉም። እነዚህ ቡድኖች ስልጣን በሃይል ያማራቸው ደግሞ እዚያው ክልላቸውን በማስተዳደር ላይ ኣይደለም እውነቱን ለመናገር። ዋናው ልባቸው የቋመጠው የፌደራል መንግስቱን መቆጣጠር ነው። ለምን ከተባለ በዴሞክራሲና በፍትህ ላይ ተረማምዶም ቢሆን የቡድናቸውን ህልውና ለማስጠበቅና እድገትን ለማምጣት ጥሩ ስትረተጂክ ቦታ መስሎ ስለሚታያቸው ነው። በተለይ ኢኮኖሚክ ኣድቫንቴጆችን ለመውሰድ ስትራተጂክ ቦታ ነው ብለው ያስባሉ። ህወሃት የዘውግን ፌደራሊዝም ለኢኮኖሚክ ኣድቫንቴጅ ነው እየተጠቀመብት ያለው። ስለዚህ ነው ብሄራዊ ተቋማት ሁል ጊዜ በኣደጋ ከባቢ ውስጥ እንዲኖሩ እንዲኮስሱ የሚያደርጋቸው። ወደ ኢትዮጵያ የዘውግ ፖለቲካ ጉዳይ እንመለስና እንግዲህ ዘውግ ስንል በኣማርኛ ወገን ማለት ነው። የምን ወገንተኛ ስንል ደግሞ የባህልና ቋንቋ ኣርበኞች እንደማለት ነው። መቼም የኢትዮጵያ ቡድኖች በሰው ልጆች ከፍተኛ የሆነ የዘር ልዩነት ውስጥ ኣይገቡም። ሁሉም ጥቁር፣ ምስራቅ ኣፍሪቃውያን ናቸውና። ሊያነሱ የሚችሉት ልዩነት በቋንቋ ማህበረሰብ ወገንተኝነት ላይ የተመረኮዘ ነው ማለት ነው። ታዲያ እንዲህ ኣይነቱ ልዩነት በራሱ የማይለወጥ የማይነቃነቅ ማንነት ነው ወይ ወደሚል ጥያቄ እንመጣለን። ዛሬ ደቡብ ኣፍሪካ ውስጥ ነጭ፣ ጥቁር፣ ከለር ሁሉም በአንድ የፖለቲካ ድንኳን ውስጥ ገብተው ስለ ዴሞክራሲ ሲያወሩ እኛ ኢትዮጵያውያን ይህቺን የባህልና የቋንቋ ልዩነታችንን ኣጉልተን ዘውጌኛ ፖለቲከኞች ስንሆን ዓለም ምን ይላል?

ከማንነቶች መካከል የለውጥ ህግ የሚሰራበት ኣንዱ ማንነት ባህል ነው። ባህልና ቋንቋ የሚያድግ የሚሞት የሚለውጥ ነገር ነው። የብዓዴን፣ የኦህዴድ፣ የደኢህድን፣ የህወሃት ኣባላት ተሰብሰበው ሲነጋገሩ ሶስቱም ሱፍ ለብሰው ነው የሚታዩት። በኣለማቀፉና በእርስ በርሱ የባህል ልውውጥና ውህደት ባህር ላይ ይዋኛሉ። ባህል በሁለት ኣቅጣጫ ያደጋል። ኣንደኛው በራሱ የለውጥ ኣቅጣጫ ያድጋል። ትውልድ ኣልፎ ትውልድ ሲተካ ባህሉን እያሻሻለው ይሄዳል። ይለወጣል። ሁለተኛው ደግሞ ኣብሮ ከሚኖራቸው ቡድኖች ጋር እየተዋሃደ ሳያውቀው ኣዳዲስ ባህሎችን እያሳደገ ይሄዳል። በመሆኑም ባህል የማይናወጥ የፖለቲካ የማእዘን ራስ ማድረጉ ሩቅ ኣለማየት ያስመስላል የሚሉ ወገኖች ኣሉ።

ዋናው ጉዳይ ለፕሮፌሰር መሳይ የሚቀርበው ጥያቄ ግን ወገንተኛ ፖለቲካ በብዙህ ኣገር ውስጥ ሳይንሳዊ ካለመሆኑ የተነሳ ኣገሮች ሁሉ ከዘውጋዊነት ወደ መርህ እያደጉ ወደ ዴሞክራሲ እያደጉ በሚመጡበት ሰዓት ኢትዮጵያ ዋና የፖለቲካ መሰረቷን ዘውግ ኣድርጋ ብሄራዊ ኣንድነቷን በምልክት እንድትኖር ለምን ትመከራለች ነው። ለምን የተገላቢጦሽ ኣይሆንም። ዘውጋዊ ማንነቷን ከፖለቲካ ኣላቃ ባህላዊ ማንነቷን ደግሞ በተደራጃ ምልክት ለምን ኣታደርገውም ነው። ባህላዊ ማንነቶችን ለምን በቀጥታ ባህል ኣይረከብምና ኣሁን የመጣውን ኣዲሱን የኣስተዳደር ዘየ ደግሞ ቶሎ ብለን ለሁላችን ኣድረገን ኣብረን ኣንኖርም። ሃረሪ ውስጥ ላእላይ ምክር ቤቱ የሃረሪን ባህል ጠባቂ ነው ይባላል። የፖለቲካ ውክልና ያለው፣ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ኣርበኛ ባህልን ለመጠበቅ ይሞክራል። ይሄ የሚያሳየው ፖለቲካው ራሱ ባህላዊ ፖለቲካ መሆኑን ነው። ይሄ ተለውጦ የባህል ኣርበኞች ቤት ለብቻው ቢበጅና ባህልና ፖለቲካ ቢሊያይ ጥሩ ነው። ልክ ሃይማኖትና ፖለቲካ የተለያዩ ናቸው እንደምንለው ባህልን ለብቻው ማስተዳደር ብንችል ቡድኖችን ከባህል ኣንጻር እንዳይዋጡ ማድረግና ሁሉም በባህሉ እንዲኮራ ማድረግ እንችላለን። በሌላ በኩል ደግሞ የምንፈጥረው የጋራ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት አድልዎ እንዳይኖረው የፍትህ ኣካሉን በጥሩ መሰረት ላይ ማቆም ይቻላል። ብሄራዊ ተቋማት በለሰለሰ እርሻ ላይ ስለሚዘሩ ዴሞክራሲያዊ ባህርያትን እያፈሩ ያድጋሉ። ከውጭው ኣለም ጋርም ሳንቸገር መኖር እንችላለን።

የፕሮፌሰር መሳይ ዓላማ ዘውግንና ብሄራዊ አንድነትን ማስታረቅ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ዘውግ (በኢትዮጵያ ሁኔታ) ና ብሄራዊ ኣንድነት መቼ ይጣላሉ። ኣይጣሉም እኮ። ባለፈው በጻፍኳት ጦማር ላይ የጠቀስኩትን እንደገና ኣሁንም መግለጽ እፈልጋለሁ። ቡድኖች በተፈጥሯቸው ላይ ኣይነቃቀፉም። ያንተ የልብስ ባህል ኣያምርም የእኔ ያምራል፣ ያንተ ቋንቋ ኣይጥምም የኔ መልካም ነው፣ ያንተ ምግብ ወዲያ የኔ ይጣፍጣል ወዘተ በሚል ኣይጋጩም። ይህ ልዩነታቸው ኣያጣላቸውም። ቡድኖችን ወደ ግጭት የሚወስደው ይህንን ጥበባቸውን ይዞ የፖለቲካ መጫወቻ የሚያደርግ ኣካል ሲፈጠር ያ ኣካል የሚቀሰቅሰው ኣስተዳደራዊ ችሎታን ወይም ጥበብን ከተፈጥሮ ጋር ስለሚያያይዘው ብርታትም ሆነ ድክመት የቡድኑን ስሜት ቶሎ የሚኮረኩርና የሚያነቃ ይሆናል። ከዚህ ክብ ውስጥ የወጣ ኣንድ ሰው በሚያደርገው መልካም ስራ ቡድኑ ይረካል። ያጋንናል። ድክመቶች ሲታዩ ደግሞ ይደብቃል። ያፍራል። በኣንጻራዊ ያሉት ቡድኖች የዚያን ሰው ድክመት ኣጠቃለው የቡድኑ ኣድርገው ያዩታል የሚል እምነት ያድርበታል። የተፈጥሮ ድክመት ኣድርገው ሌሎች ያስባሉ ብሎ ያስባል። እናም በዚህ ዙሪያ በሚደረጉ ክርክሮች ዙሪያ ሃፍረቱን ኣውልቆ ጥሎ ኣምክህኖትን ወዲያ ጥሎ ሞራልንና መርህን እየረመረመ ያ ጥፋተኛ ትክክል ነው ብሎ ይከራከራል። ከፍ ሲል እንዳልነው መሰረቱ ስሜት በመሆኑና ለሱፐር ኢጎ ቦታ ስለማይሰጥ መርህ በአደባባይ ይጣሳል። ይህ ነው ወደ ግጭት የሚያመራው። በመሆኑም በኢትዮጵያ ውስጥ ዘውግን ከብሄራዊ ኣንድነት ጋር ኣሳልጦ ለማስኬድ ፖለቲካን አውጥቶ በዴሞክራሲ ባህል ኣንጾ ያንን ሶስተኛ ባህል ኣድርጎና የጋራ ኣድርጎ በኣንድ የፖለቲካ ጥላ ስር መኖር ነው ትልቁ መፍትሄ።

ሌላ ቁም ነገር ላንሳ። የኢትዮጵያን የቡድኖች ጥያቄ በሚገባ መግለጽ የተቻለ ኣይመስለኝም። በሃገራችን የቡድን ጥያቄ የለም ማለት ጥሩ ኣይደለም። በሚገባ ኣለ። በኢኮኖሚ ህይወቱ ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ተመሳሳይ ኑሮ ነው የሚኖረው። የሰሜን ገበሬ ከደቡቡ ከምእራቡ ከምስራቁ ጋር ያው ነው። ከተሞች ኣካባቢ ሚዛናዊ ያልሆነ የሃብት ክምችት ይኖራል። ስለ ሰማኒያ በመቶው የኢትዮጵያ ህዝብ ስናወራ ግን ኣንድ ኣይነት የኢኮኖሚ ህይወትን ይኖራል። የደቡቡ ገበሬ በሰሜኑ ህይወት ኣልቀናም። የኦሮሞው ገበሬ በሲዳማው ኣልቀናም። ኢትዮጵያ ውስጥ ቡድን ከቡድን አልተጎዳዳም። በኢትዮጵያ ሁኔታ በቡድን ሊገለጽ የሚችል ችግር ካለ ከባህልና ቋንቋ ኣያያዛችን ጋር የተገናኘ ነው። በርግጥ ይህንን ችግር ለመፍታት ኣንዳንዴ የፖለቲካ ስልጣንን መሳሪያ ለማድረግ ይሞከራል። ይሁን እንጂ ችግሩ በግልጽ ባህላዊ ነው። ባለፈው ጊዜ አቶ ሌንጮ ባቲ ጥሩ ነገር ተናግረዋል። እኛ ኦሮሞዎች የሚሰማን ነገር ኣለ። ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ስትሉ እኛን ያካተታችሁን ኣይመስለንም ኣይነት ተናግረዋል ። ይሄን መረዳት ለወደፊቷ ኢትዮጵያ ኣስፈላጊ ነው። በመሆኑም የሚታየው ችግር የባህል መዋጥ ችግር ነው። ኣንድ ባህል ሌሎቹን በከፍተኛ ሁኔታ ውጦ ይታያል። ይህንን ጥያቄ አቅልሎ የምግብ የልብስ የምናምን ጥያቄ ነው ማለት ጥሩ ኣይደለም። የቡድኖች ጥበብ ማንነትን የሚገልጽ በመሆኑ ጥንቃቄ ይሻል። ጥያቄያቸውን ዜጎች በተለያየ መንገድ ሊገልጹት ይሞክሩ ይሆናል እንጂ ኣንዱ ችግር የባህላዊ ማንነት መዋጥ ነው። ኣንድ ጊዜ ደቡብ ሄጄ የሆነውን ላውጋችሁ።

ቦታው ቡርጂ ነው። ቡርጂ የምትገኘው ወደ ኬንያ ጠረፍ ኣካባቢ ሲሆን በኣማሮ፣ በጉጂ፣ በኮንሶ ብሄሮች ተከባለች። ብሄረሰቡ በቁጥር ብዙ የሚባል ኣይደለም። በኣሁኑ ኣደረጃጀት በልዩ ወረዳ የተከለለ ኣካባቢ ነው። ዋና ከተማዋ ሶያማ ትባላለች። እዛች ትንሽየ ከተማ ውስጥ ጥቂት የምግብ ቤቶች ኣሉ። ታዲያ ከእለታት ኣንድ ቀን ወደ ኣንዲቱ ምግብ ቤት ኣመራሁና ለምሳ ተሰየምኩ። ታዛዣ መጣች….
“ምን ላምጣ?”
“ኩርኩፋ” ትንሽ ላስፈግጋት ብየ እንጂ ምንም ምርምር ኣስቤ ኣልነበረም::
“ኩርኩፋ?”
“ኣዎ ትኩሱን ቶሎ በይ”
ሳቀች። አየደገመች ሳቀች። እኔም ኣላማየ ደክሟት ከሆነ ነቃ እንድትልና ዘና ባላ ከባቢ ተስተናግጄ እንድሄድ ዘና ብየ በለቼ እንድሄድ ነበርና ዓላማየ ግቡን መታ ማለት ነው። ስለዚህ ወደ እውነተኛው ፍላጎቴ ተመለስኩና ኮስተር ብየ ያንኑ ጥብሴን ኣዘዝኩ። ኣመጣችልኝና ምግቡን ቁጭ እያደረገች።
“የምርህን ነው ግን?” ኣለችኝ።
“ምኑን?”
“ኩርኩፋ ኣላልከኝም። ከፈለክ ኣለ እሰጥሃለሁ::” ኣለችኝ።
ያዘዝኩት ምግብ ስላለና በውነት ማስቸገርም ስለመሰለኝ ግዴለም ሌላ ጊዜ…… ብየ ኣመስግኘ ንግግራችን ተቋጨና ለቀልድ ብየ ያመጣሁት ነገር የእለቱ ኣስተማሪ መሪ ኣሳብ ሆነና ሲያናውዘኝ ዋለ። በዚያች ከተማ ውስጥ ኣንድም የኩርኩፋ ምግብ ቤት የለም። የእንጀራና ወጥ ምግብ ቤት ብቻ ነው ያለው። ይህ የሆነው ደግሞ የሰሜን ሰዎች ስለሚበዙ ኣይደለም። ብዙ የሉም። ለራሳቸው ለቡርጂዎች የተዘጋጀ ምግብ ቤት ነው። በዚያ ማህበረሰብ ኣይምሮ ውስጥ ምግብ ቤት ሲባል እንጀራ በወጥ ብቻ ነው። የሰሜን ባህል ውጧቸዋል። ጨርሶ ባይምሯቸው የራሳቸው ምግብ ለገበያ የሚውል ኣድርገው እንዳያስቡ ኣድርጓቸዋል ማለት ነው የሚል ከአቅሜ በላይ የሆነ ጥያቄ መጣና ትንሽ ኣንገላጀጀኝ። የቡርጂዎች ባህል እንኳን ወደ ብሄራዊ ከተማዎች ቀርቶ በቡርጂዎች ከተማ ሶያማ ውስጥ ገበያ ላይ ኣልወጣም ። ኩርኩፋ በነገራችን ላይ በጣም የወደድኩት ምግብ ነበር። ይህ ለእኔ ያስተማረኝ የኢትዮጵያ የባህል ፍስሰት ፈጽሞ ሊስተካከል ይገባዋል። መስተካከሉ ደግሞ ለሁላችን ጠቃሚ ነው። ኣገራችን የባህል ቫራይቲ እንዲኖራት ከመርዳቱም በላይ ለምግብ ዋስትናና ከድህነት ለመውጣት ለምናደርገው ጥረት ትልቅ ጥቅም ኣለው። ገበያ ያደራል:: ከሁሉ በላይ ግን ቡድኖችን ኣንዳንዴ የሚያነጫንጫቸውን ሚስጥር መረዳት ኣለብን። ጥያቄው በፖለቲካ በኩል መልስ የሚያገኝ እየመሰላቸው ወደዚያ ይሮጣሉ እንጂ ከሚገባው በላይ የተጫናቸው ባህል ኣለ። በብሄር ዘለል ግንኙነት ጊዜ ሊያነጫንጫቸው ቢችል እውነት ኣለው። ኦሮሞ ነኝ ማለት የኦሮሞ ጥበቦችና ቋንቋ ሁሉ ባለቤት ነኝ ማለት ነው። እነዚህ ጥበቦች ገበያ ላይ ውለው ቢያይ ኮራ ብሎ ይናገራል። አዲስ ኣበባ ከተማ ውስጥ የኦሮምኛ ቋንቋ ኣካዳሚዎች ቢያይ ደስ ይለዋል። ከገበያ ተከልተው በሌላ ባህል ተውጦ ሲያይ እኔ ጥበብ የለኝም ወይ የሚል የችሎታ ጥያቄ በነፍሱ ሊያነሳ ይችላል። ሙሉ ቀን ራሴን ኦሮሞ ኣድርጌ እዚህ የምኖርበት ኣገር ሆኘ ኣስቤ ኣውቃለሁ። በትክክል የባህላዊ ማንነት ጥያቄ ሊያነሳ ይገባዋል። ታዲያ ይህንን የባህል መዋጥ ጥያቄ የሚፈጥረውን ስሜት ከተረዳን ማስተካከያውም ኣይከብድም። ወደ ፖለቲካ መሮጥና ፖለቲካን ለኢኮኖሚና ለባህል ማጉያ መሳሪያ ኣድርጎ ማሰብ ሙስና ኣለበት። ፖለቲካን የሁሉ መፍትሄ ሰጪ ኣድርጎ ማሰቡ ትክክል ኣይደለም። ማህበራዊ ችግሮቻችንን ማህበራዊ በሆነ መንገድ መፍታት ይሻላል። የባህል ጥያቄ የሚመለሰው ባህላዊ ኣስተዳደርን በተጠናከረና በተደራጀ ሁኔታ ስናዋቅረው ነው። ይሄ ነው የሃገሪቱን የማንነት ጥያቄ የሚፈታው። የእኩነትን ጥያቄ የሚፈታው።

ይህን ለማደረግ ደግሞ ባህላዊ ኣስተዳደሩ በስርዓት መደራጀት ኣለበት። ኦሮሞ የገዳ ተወካዮቹን ይዞ፣ ኮንሶ ንጉሱን ይዞ ሌላው መሪውን የገደለውም እንዲሁ የማስመለስ ስራ ሰርቶ ወይም የቋንቋና የባህሉን ማህበረሰብ ተወካይ ሾሞ የባህል ኣርበኞች ቤት ማቋቋም ጥሩ ነው። ይህ የባህል ኣርበኞች ቤት ደግሞ በሆነ ኪዳን ሊያዝ ይገባዋል። ቡድኖች ባህላቸውን ለኢትዮጵያዊነት ሰውተው መልሰው የሚንከባከቡበትን ኪዳን ከገቡ የኢትዮጵያን ቡድኖች ባህል ሁሉ ሁልም ኢትዮጵያዊ ይደሰታል ደግሞም ይጠብቃል። እነዚህ ቡድኖች በኣንድ ሃገር ጥላ ስር ይኖራሉና ኣንድ ከፍ ያለ ኪዳን መጀመሪያ መግባት ኣለባቸው። ኪዳን ህገ መንግስት ሳይሆን ከዚያ በላይ የሚውል ከፍ ያለ ኪዳን ማለቴ ነው። የባህል ኣስተዳደሩ የራሱ ኣሰራር ኖሮት ባህልን እየጠበቀ፣ የእርቅና የሰላም ስራዎችን እየሰራ መኖር ይችላል። ባህል ኣስተዳዳሪ ሲኖረው የተዋጠው ባህል ከገባበት ኣዘቅት እንዲወጣ በማድረግ የእኩልነት ስሜትን በኣደባባይ ያሳያል። ሌላው ኣስተዳደር ደግሞ ፖለቲካዊ ሲሆን ቡድኖች ሁሉ በያሉበት ተወያይተው ለመስዋእት ተዘጋጅተው የሚፈጥሩት ማንነት ነው። ኢኮኖሚያቸውንና ፖለቲካዊ ህይወታቸውን ኣተኩሮ የሚሰራ ስርዓት ፈጥረው ይህ ስርዓት ህይወታቸውን ወደ ተሻለ ኣቅጣጫ ይመራል። ብሄርን፣ ዘውግን ተገን ኣድርጎ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማእከላዊ ሃይል ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት ሁሉ ሙስና ኣድርገው ኣውግዘው በህጋቸው ከልክለው ቢኖሩ ችግሮች ሁሉ በሂደት እየተፈቱ ይመጣሉ። ኣንድነት በጣም ኣይቀጥንም። ፕሮፈሰር መሳይ ባሉዋቸው ምልክቶች ላይ የሚቆም ሳይሆን በተደላደለ መሰረት ላይ የቆመ ብቻውን መቆም የሚችል ኣካል ያለው ማንነት መፍጠር ይችላሉ። ከፍ ሲል እንዳልኩት የኣንዳንድ ቡድን ኣባላት የቡድንን ስሜት በመጠቀም የኢኮኖሚና የማእከላዊ ስልጣን ፍላጎት ካለ ይህ ስሜት በራሱ ፍትሃዊ ኣለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ ሙስና ነው። በአንጻሩ ባህላዊ ማንነትን መንከባከብና ማንነቴ ተጎዳብኝ ራሴ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊ ኣይሸተኝም ማለት ግን ፍትሃዊ ጥያቄ ነው።

አንድ ሌላ ነገር ከግንዛቤ መግባት ያለበት ይመስላል። እንደ ኢትዮጵያ ባለ ብዙ ዘውግ ባለበት ኣገር ፖለቲካው ዘውጌኛ ሲሆን የዘውግ ኣባላት በተለይም በፖለቲካ የበላይነት ያለው የቡድኑ ኣባላት ሲበዛ ትጉ ይሆኑ ይሆናል። ሲበዛ ምስጢር ጠባቂዎች፣ ሲበዛ ጠርጣሮች፣ ሲበዛ ስጉዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ይህን ስነልቦና ከየት ኣመጡት? ብንል ቡድናዊ ህይወታቸው ኣንጻራዊ ፍክክር ውስጥ ገብቷል ብለው ስላመኑ ነው። አሁን የሚታየው ኣንጻራዊ የስሜት ጉልበታቸው ምን ኣልባትም ኣንድ ከቡድናቸው መሃል የበቀለ የሆነ ቡድን ማእከላዊ ስልጣኑን ይቆጣጠርና ከዚያ በሁዋላ የነብር ጅራት ጨብጫለሁና አግዙኝ ይላል። ከለቀቅኩት ሌላው ቡድን ይመጣና ስልጣን ላይ ሆኖ ወገኖቹን ሲጠቅም ነበር ብሎ ሁላችንን ስለሚፈጅ ኣያይዙኝ ብሎ በሚስጥር በቋንቋቸው ሹክ ይላል። ከፍ ሲል እንዳልነው የዘውግ ፖለቲካ ስሜታዊ በመሆኑ ቀላል የማይባል ደጋፊ ሊያገኝና ጅራት የመወጠሩን ስራ ሊያግዙ የሚነሱ ሰዎችን ሊያገኝ ይችላል። ጅራቱን የያዘው ዋና ቡድን ኤነርጂ ለመጨመር ሲል “የኔ” ያላቸውን ቡድን ኣባላት ከሌሎቹ እንዲጋጩ ያደርጋል። ፕሮፓጋንዳዎች እየነዛ በሚገባ ይጠቀምባቸዋል። አልፎ ኣልፎም ትንሽ ጣል የሚያደርግላቸውም ጥቅማጥቅም የውሎ አበል ይኖራል። ይህንን የዘውግ ፖለቲካ ስነልቡና ማጤንም ተገቢ ነው። የመስኩ ተመራማሪዎች እንደሚናገሩት በዘውግ ኣገዛዝ ጊዜ ወደ ስልጣን የመጣው ቡድን በቁጥሩ በጣም ኣነስተኛ ከሆነና ከጠቅላላው የሃገሪቱ ህዝብ ከሃያ በመቶ በታች ከሆነ ኣገዛዙ በጣም በጭካኔ ላይ ይመሰረታል ይላሉ። ኣሳማኝ ነው። ስጋት ስለሚኖርባቸው ኣንዴ የነብር ጅራት ጨብጠናልና ኣይነት ኑሮ ስለሚሆን ነው የሚጨክኑት። የሶርያን ጉዳይ ስናይ ኣሳድ ወደ 10 በመቶ ከሚሆነው አለዊትስ ብሄር ኣባላት የወጣ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የራሱን ክብ በመስራት ስልጣን ላይ ያለ ሰው ነው። ጭካኔውን አለም ያወቀው ነው። እዚህ ላይ ማብራራት ኣያስፈልግም።

እነዚህ ገዢውን ክፍል ለማኖር በትጋትና በከፍተኛ ምስጢር የሚያገለግሉ ዘውጎች ቢገነጠሉና ራሳቸውን ሜዳ ላይ ለብቻው ቢያገኙት ደግሞ ይህ ትጋት፣ ስጋትና፣ ምስጢረኛነት ይጠፋል። በስቴት ጉዳይ መከፋፈል ይመጣል:: ምን ኣልባትም ኣሁን ማይክሮ ልዮነት የሆኑ ልዩነቶች ተነስተው መከፋፈል ሊመጣ ይችላል።

በብሄር ፖለቲካ ጊዜ ስልጣን ላይ ያለው ዘውግ እንዲህ ሲተጋ ሌሎች ቡድኖች ተገቢውን ቦታና ጥቅም ኣላገኘንም ያሉ ደግሞ በወቅቱ ስልጣን ላይ ያለውን የራሳቸውን ቡድን ተወካይ ኣያምኑትም። ያፍሩበታል። ኣይተጉም። ችላ ይላሉ ማለት ነው። በዘውግ ላይ የሚቆም ፖለቲካ ትልቁ ችግር እንዲህ ቡድኖችን ሁሉ ግራ ማጋባቱና የመርህን ቆብ ማስጣሉ ነው። ከዘውግ ፖለቲካ መሃል ሞደሬሽን መጠበቅ ተላላነት ነው። ኣገርን የሚያህል ግዙፍ ጉዳይ በእንዲህ ዓይነት ጨዋታ ውስጥ መክተት ኣደጋ ይኖረዋል። ለዚህ ነው በባህላዊ ወገንተኛነት ላይ መሰረቱን የጣለ ፖለቲካ እርስ በርስ ከማናቆር ይልቅ ወደ ልማትና ዘመናዊ ኣስተሳሰብ ኣይመራንም የሚያሰኘን ለዚህም ነው። ባህላዊ ፖለቲካ እንኳን በብዙህ ሃገር ይቅርና ለሆሞጂኒየስ ኣገሮችም ኣይጠቅምም። ሆሞጂኒየስ የሆኑ ኣገሮችም ቢሆኑ ፖለቲካቸውን ማራገብ ያለባቸው በሃይማኖታቸው ወይ በባህላቸው ሳይሆን በመርህ በዴሞክራሲ ዙሪያ ቢሆን ነው የተሻለ ስብእና ያለው ዜጋ ማፍራት የሚችሉት። ባህልንና ቋንቋን ከሚገባው በላይ ማረገብና የፖለቲካ ዋና መሰረት ማድረግ ሆሞጂኒየስ የሆኑ ኣገሮችን ምን ኣልባትም ከውጭ ሃገር ዜጎች ጋር የመኖር ክህሎታቸውን ሊጎዳ ብሎም ዚኖፎቢያም ሊያመጣ ይችላል። ቶለራንስ የምንለውን ሊጎዳባቸው ይችላል። መልቲ ካልቸራሊዝምን ይጎዳል። ስለዚህ የማንነት ፖለቲካ ለሆሞጂኒየስ ሃገራትም እንኳን ኣይመከርም።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት ኢትዮጵያን ዘላለማዊ ለማድረግ የዘውግ ፖለቲካ ፈጽሞ አይጠቅመንም። በዘውግ ፖለቲካና በብሄራዊ ፖለቲካ መካከል ደግሞ መሃል መንገድ የለም። ምን አልባት ፖለቲካችንን ከዘውግ ነጥቀን ካወጣን በሁዋላ ፌደራሊዝሙ በቋንቋ ኮሙዩኒቲ ይዘርጋ የሚል ኣሳብ ይመጣ ይሆናል። ይሄኛው ቢያንስ ትንሽ ይሻላል። ይሁን እንጂ አገሪቱ ከዚህም የተሻለ የፌደራል ስርዓት መዘርጋት ትችላለች። ከፍ ሲል እንዳልኩት ኢትዮጵያ ዘውጎችን የሚንከባከብ አንድ ባህላዊ ኣስተዳደር የሚያሻት ሲሆን ይህ ኣስተዳደር የራሱ የሆኑ ፌደሬሽኖችን ሊመሰርት ይችላል። ይህ ፌደሬሽን በመሬት ላይ የማይነበብ ፌደሬሽን ቢሆንና በሌላ በኩል ለኢኮኖሚ እድገትና ለአሰራር ኣመቺነት ያለው ሳይንሳዊ የፌደራል ስርዓት ቢፈጠር ኣገሪቱ ንጹህ ዴሞክራሲን እየተደሰተች በሌላ ብኩል ባህሏን እየተደሰተች መኖር ትችላለች። ፕሮፌሰር መሳይ እንዳሉት ምርጫዋን ደግሞ ፕሬዚደንታዊ ብታደርገው እጅግ ጥሩ ይሆናል። ከዚህ በፊት ከዘውግ ፖለቲካ ጋር በተያያዘ የመጣውን ክፍተት በመዝጋትና ኣንድነትን በማሳደግ በኩል ጉልህ ሚና ይኖረዋል። ይህ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ግን በዘውግ ፖለቲካ ስር ሳይሆን ፖለቲካው ከዘውግ ወጥቶ በንጹህ ኣይዲዮሎጂ ላይ ተመስርቶ ቢሆን ነው የሚሻለን።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት ኢትዮጵያን ዘላለማዊ ለማድረግ የዘውግ ፖለቲካ ፈጽሞ አይጠቅመንም። በዘውግ ፖለቲካና በብሄራዊ ፖለቲካ መካከል ደግሞ መሃል መንገድ የለም። ምን አልባት ፖለቲካችንን ከዘውግ ነጥቀን ካወጣን በሁዋላ ፌደራሊዝሙ በቋንቋ ኮሙዩኒቲ ይዘርጋ የሚል ኣሳብ ይመጣ ይሆናል። ይሄኛው ቢያንስ ይሻላል። ይሁን እንጂ አገሪቱ ከዚህም የተሻለ የፌደራል ስርዓት መዘርጋት ትችላለች። ከፍ ሲል እንዳልኩት ኢትዮጵያ ዘውጎችን የሚንከባከብ አንድ ባህላዊ ኣስተዳደር የሚያሻት ሲሆን ይህ ኣስተዳደር የራሱ የሆኑ ፌደሬሽኖችን ሊመሰርት ይችላል። ፕሮፌሰር መሳይ እንዳሉት ምርጫዋን ደግሞ ፕሬዚደንታዊ ብታደርገው እጅግ ጥሩ ይሆናል። ከዚህ በፊት ከዘውግ ፖለቲካ ጋር በተያያዘ የመጣውን ክፍተት በመዝጋትና ኣንድነትን በማሳደግ በኩል ጉልህ ሚና ይኖረዋል። ይህ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ግን በዘውግ ፖለቲካ ስር ሳይሆን ፖለቲካው ከዘውግ ወጥቶ በንጹህ ኣይዲዮሎጂ ላይ ተመስርቶ ቢሆን ነው የሚሻለን። እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ።

አስተያየት ካለ ኣድራሻየ እነሆ
geletawzeleke@gmail.com


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1809

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>