Quantcast
Channel: Abugida Ethiopian American Amharic Web Page
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1809

የመንፈስ ታዳጊ ያገኘው በዓሉ ግርማ (በየነ ሞገስ)

$
0
0

ጽሁፌን በእውነተኛ ኑዛዜ ልጀምረው፡፡ ሰሞኑን በመጽሐፍት አዟሪዎች እጅ ‹በዓሉ ግርማ – ሕይወቱና ሥራዎቹ› በሚል ርዕስ የቀረበ መጽሐፍ ተመልክቼ ነበር፡፡ በዓሉን በተመለከተ ብዛት ያላቸውን ጋዜጦች፣ መጽሐፍት፣ መጽሔቶችና የተለያዩ ጹሑፎች የተመለከትኩና ቃለ መጠይቆች የሰማሁ መሆኔን በማመን ‹ምን አዲስ ነገር ይኖራል?› በሚል ጥያቄ በእጄ ሳላስገባ አለፍኳቸው፡፡ የመጽሐፍ ደንበኛዬ የሆነው ባለመደብርም ስልክ ደውሎ ይህንኑ መጽሐፍ እንዳነብ ሲጠይቀኝ የሰጠሁት መልስ እላይ የጠቀስኩትን ይመስል ነበር፡፡ አሱ ግን በቀላሉ አለቀቀኝም ‹የለም! ተሳስተሃል፡፡ መጽሐፉ የተለየ አቀራረብና በብዙ ማስረጃዎች የተደገፉ የታሪክ ሂደቶችን አቅርቧል› አለኝ፡፡ የደንበኛዬን አስተያየት ብዙ ጊዜ ስለማምንበት መጽሐፉን ወስጄ አነበብኩት፡፡ በጣም የተሳሳትኩ መሆኔን የተረዳሁት ገና ማንበብ እንደጀመርኩ ነው፡፡ አንብቤም ከጨረስኩ በኋላ በዚህ መጽሐፍ ላይ ያደረብኝ ስሜትና አድናቆት ለአንባቢያን መግለጽ አስፈላጊ ሆኖ አገኘሁት፡፡

በኢትዮጵያ የድርሰት በተለይም የልብ ወለድ አጻጻፍ ከፍተኛ የሆነ አሻራ ከአሳረፉት ደራሲያን መካከል በዓሉ ግርማ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ‹በዓሉ ግርማ – ሕይወቱና ሥራዎቹ› በሚል ርዕስ በ439 ገጾች የዚህን ተደናቂ ደራሲ የሕይወት ታሪክ ያቀረበልን እንዳለጌታ ከበደ ከውልደቱ እስከ ህልፈቱ ያለውን ታሪክ በጥሩ ገለጻ፣ በጥሩ ቋንቋ፣ በአሳማኝ ማስረጃዎች ያስቃኘናል፡፡

ጸሐፊው የበዓሉን እድገት፣ ትምህርት፣ ሥራ እንዲሁም በሕይወቱ ፍጻሜ አካባቢ የነበረውን ድባብ በሰፊው አቅርቧል፡፡ ለገለጻው የሚረዱ ብዙ መጽሐፍትንና የተለያዩ የታተሙና ያልታተሙ ጹሁፎችን ለትረካው ተዐማኔነት ተጠቅሟል፡፡ በዓሉ ለንባብ ባበቃቸው ስድስት መጽሐፍት በሚስላቸው ገጸ ባህሪያት የሚታወቅበት አሰራሩ የመጽሐፎቹን ባለታሪኮች በሚያውቃቸው ግለሰቦች አምሳያ መቅረጹ ነው፡፡ አልፎ አልፎም የራሱን እምነት፣ ባህሪና ገጠመኞች በልብ ወለድ መልክ በሚያቀርባቸው ባህሪያት የሚያካትታቸው መሆኑም ነው፡፡ እንዳለጌታ በዚህ መጽሐፉ ይህንን እውነታ በማስረጃ እያስደገፈና እያጣቀሰ ይገልጸዋል፡፡

በመጽሐፉ ከተዘረዘሩት የጹሁፍ ማስረጃዎች ባሻገር ስድሳ ለሚሆኑ፤ በዓሉን በቅርብም ሆነ በርቀት ለሚያውቁ ግለሰቦች ከ2003 እስከ 2008 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ጊዚያት ቃለ መጠይቅ በማድረግ በታሪኩ ሂደት ላይ ያጋጠሙትን ክፍተት ለመሙላት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ በተለያዩ መዝገብ ቤቶች የሚገኙና አቧራ የተከመረባቸውን መዛግብት አገላብጦ ተመልክቷል፡፡ የእነኚህን የምርምር ጥረቶችና ማስረጃዎች በጥሩ ሁኔታ በመጠቀም የበዓሉ ግርማን የሕይወት ታሪክ የተዋጣለት አድርጓታል፡፡ እንዳለጌታ በዚህ ስራውና በተጠቀመው ስልት በአንድ ግለሰብ ላይ ለሚቀርብ የሕይወት ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል ማለትም ይቻላል፡፡

ስለ በዓሉም ታሪክ ለማወቅ ያሳደረበትን ፍላጎት ሲገልጽም እንዳለጌታ በመቅድሙ እንዲህ ሲል ገልጾታል፤ ‹ንባቤም፣ ልምዴም ፣ ዕድሜዬም ከፍ እያለ ሲመጣ፣ በዓሉ በደራሲነቱ ሰበብ ሕይወቱን ያጣ ሰው እንደሆነ ስረዳ፣ በመንፈስ ከወለዳቸው ልጆቸች መካከል እንደ አንዱ አድርጌ ራሴን ቆጥሬያለሁና እንደማናኛውም ኢትዮጵያዊ፣ የገባበት ጉድጓድ ማወቅ ያሳስበኝ ገባ..› በማለት፡፡

በዓሉ የሕይወት ፍጻሜው እንደሚያሳዝን ሁሉ በለጋ እድሜው ዓለምን ሲቀበል የደረሰበትም እንዲሁ አሳዛኝ ነው፡፡ ስለዚሁ የበዓሉን የህጻንነት ገጠመኝ በአጭሩ እንመልከት፡፡

የበዓሉ ወላጅ አባት ባንያናዊ (ሕንዳዊ) ሲሆን ስሙም ጂምናዳስ ይባላል፡፡ ከአዲስ አበባ ወደ ኤሊባቡር ሄዶ ሱጼ ከተባለች ቦታ በንግድ ስራ መኖር እንደጀመረ የአገሬው ተወላጅ ከሆነች ያደኔ ቲባ ከተባለች ወጣት ጋር ይዋደዳል፡፡ ተጋብተውም በዓሉ ይወለዳል፡፡ አባት በመጽሐፉ እንደተገለጸው በባንያኖች ባህልና ወግ መሰረት አንድ ወንድ ለአንድ ሴት ብቻ ነው፡፡ በአገሩ ያለቸው ሚስቱ ከህንድ ወደ አዲስ አበባ ስተመጣ ጂምናዳስም ሚስቱንና ልጁን ጥሎ ወደ አዲስ አበባ ሄደ፡፡ በዓሉ የ10 ወይንም የ12 ዓመት እድሜ እንደሆነው እናቱ በተመላላሽ ነጋዴዎች አማካኝነት በዓሉ አባቱጋ ላከችው፡፡ በመርካቶ አካባቢ የጨርቃ ጨርቅ ነጋዴ የሆነውን የበዓሉን አባት አደራ የተሰጣቸው ነጋዴዎች ለማግኘት አልተቸገሩም፡፡ ሆኖም ሱቁ ሲደርሱ ጂምናዳስ አልተገኘም፡፡ ሲደርሱ ያገኙት ግርማ የተባለውን የጂምናዳስን ሰራተኛ ነበር፡፡ ነጋዴዎቹ ሳይመሽበቸው ወደ ጉዳያቸው መመለስ ስለነበረባቸው ግርማ ልጁን ተቀብሎ አባቱ እስኪመጣ አቆየው፡፡ ከዚህ በኋላ ያለውን እንዳለ ከመጽሐፉ፤

‹ጂሚናዳስ ዘግይቶ መጣ፡፡ ወደ ሱቅ ሲገባ አንድ ህጻን አየ፡፡ ደነገጠ፡፡ ‹ምንድነው? ማን ነው?› ብሎ ጠየቀ፡፡

ግርማ ወልዴም፣ ከሱጼ የመጡ ነጋዴዎች ስላስተላለፉት የአደራ መልዕክት ነገረው፡፡ መልዕክቱ ግን በጂምናዲስ ላይ ቁጣ አስመጣ፡፡ ‹ምንድነው የምታወራው? የምን ልጅ ነው የምታሳየኝ? እኔ ተቀበልልኝ አልኩህ ወይ? እንዴት እንዲህ አይነት ጥፋት ታጠፋለህ? ምን አይነት ስህተት ውስጥ ነው የምትከተኝ? አለ፣ ተከፋ፣ ተቆጣ፣ ተበሳጨ፣ ተደናገጠ፡፡

ግርማም ‹አንተን ጥበቃ ብዙ ቆዩ፡፡ ጉዳይ አላቸው፡፡ ነጋዴዎቸች ናቸው፡፡ ልጁን ያመጡት እግረመንገዳቸውን ነው፡፡ እንዲጉላሉ አልፈለግሁም፡፡ ተቀበልኳቸው፤ በቃ› ብሎ ይመልሳል – በጂምናዲስ ቁጣ ግራ ተጋብቶ፡፡

ምን አውቀህ ነው የምትቀበላቸው? እኔ ራሴ የት አውቀዋለሁ? የምትላትንስ ሴት (የበዓሉን እናት ለማለት ነው) የት አውቃታለሁ?› ብሎ ጠየቀ አሁንም ሳይረጋጋ፡፡

‹ልጁ አንተን አንተን ስለመሰለኝ ነው› አለ ግርማ ወልዴ፡፡

ጂምናዳስ ፊቱ ቀልቶና ንዴቱ ገንኖ፣ ‹አላውቅልህም፣ ከትዕዛዜ ውጪ ነው የሰራኽው› አለና፣ ትንሹን በዓሉን ፊት ነሳው! ልጁን በማያውቃቸው ሰዎች ፊት፣ በማያውቀው ቋንቋ አመናጨቀው፡፡

በዓሉ አለቀሰ፡፡ የጭቅጭቁ መንስዔ እሱ እንደሆነ ገባው፡፡ ተረበሸ፡፡›

እንግዲህ መረበሽ ብቻ ሳይሆን ድርጊቶች እንደፎተግራፍ ተቀርጸው በአእምሮ በሚቀሩበት በዚህ እድሜ የሚገኘው ህፃኑ በዓሉ አባት አገኛለሁ ብሎ መጥቶ ይህን በመሰለ መስተንግዶ አቀባበል ሲደረግለት ምን ሊሰማው እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ ይህን በመሰለ ሁኔታ ኅብረተሰቡን የሚቀላቀሉ በአብዛኛው – ጨካኝ፣ ክፉ፣ ቂመኛ፣ በቀለኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ በተለያዩ የኅብረተሰብ ሂደቶች የሚታይ ነው፡፡ በዓሉ ግን ይህንን ሆኖ አልተገኘም፡፡ እንዲሁ በሕይወቱ ከተከሰቱት ጉዳዮችና ይህንኑ ሀሳብ ከሚያጠናክሩልን በመጸሐፉ ገጽ 291 ከተገለጸው አንዱን እንመልከት፡፡

በዓሉ ለኅትመት ከአበቃቸውና ተወዳጅ ከነበሩት መጽሐፎቹ መካከል አንዱን ለአንድ አከፋፋይ ሰጠው፡፡ በወቅቱ የማተሚያ ቤት ክፍያ አፍጥጦ ይጠብቀዋል፡፡ መጽሐፉን አከፋፋዩ በጥቂት ጊዚያት ሸጠ፡፡ ግን ለበዓሉ ምንም ክፍያ አልሰጠውም፡፡ እዳ የሚያናጥርበት በዓሉ አከፋፋዩን ለመነው፣ አስለመነው ችግሪ ቢብስበት ክስ መሰረተ፡፡ ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤት ለበዓሉ ፈረደ፡፡ አከፋፋዩ ለመክፈል ካልቻለ በስሙ የሚገኘው ቤት በሀራጅ ተሸጦ እንዲከፈል አዘዘ፡፡ ቤቱን ለመግዛት ፈቃደኛ ከሆኑ የመርካቶ ነጋዴዎች ጋር ሆኖ በዓሉ ወደ ሰውየው ቤት ሄደ፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ያለውን አሁንም ከመጽሐፉ እንውሰድ፤

‹ገዥዎች ቋምጠዋል፤ በሐራጁ ለመሳተፍ ሁሉም አቆብቁቧል፤ እና ግቢውን ተዘዋውረው ጉብኝተው ሲጨርሱ ወደ ቤቱ ተገባ፡፡ ባለብዙ ክፍል ነው፤ ሰውየው ቀን በቀናለነት የገዛው፡፡ በዓሉ አንድ ክፍል ሲገባ የሰውየው ልጆች አሉ፣ ልጆቹ ቁርሳቸውን እየበሉ ነው፡፡ አራት ናቸው፣ ላይ በላይ የተወለዱ፡፡ በዓሉ የተከሳሹን ልጆች አየ፣ እየበሉ ያሉትን ምግብ ደረጃ መዘነ፡፡ እነሱን ለማስተናገድ እየኳተነች ያለች እናታቸውን አየ፡፡ ልቡ ውስጥ ሀዘን ገባ፣ ወዲያው ወደ ሐራጅ ተሳታፊዎቹና ተጫራቾች አምርቶ ‹ይቅርታ አድርጉልኝ፣ ስላጉላላኋችሁ ይቅርታ እጠይቃለሁ፣ ይህ ቤት ተሸጦ በፍርድ ቤት እንዲከፈለኝ የታዘዘውን ነገር ትቼዋለሁ፣ እነዚህ ለእህል ያላነሱ ለትምህርት ያልደረሱ ልጆች ላይ መጨከን አልሆንልህ አለኝ፡፡ ሰውየው በራሱ ድክመት ልጆቹን ዕዳ ላይ ከትቶ ያሳነሳቸው ሳይበቃ፣ እኔም ተባባሪ ሆኜ በማይመለከታቸው ነገር እንዲቀጡ አልፈርድም፡፡ ትቼዋለሁ፤ የማተሚያ ቤት ዕዳዬንም እኔው ራሴ እከፍላለሁ፡፡› ብሎ ሃያ አምስት ሺህ ብሩን ይቅር ብሎት ወጣ›፡፡ ይህ የሆነው በ1970ዎቹ አካባቢ ሲሆን ገንዘቡ በወቅቱ ምን አይነት ዋጋ እንዳለው መገመት አያስችግርም፡፡

በዓሉ ግርማ እንዲህ አይነት ሰው ነበር፡፡ በጽሁፉ ብቻ ሳይሆን ይህን በመሰለው ሰባዓዊነቱ የሚታወስ፡፡

ለበዓሉ ህልፈተ ሕይወት ወሳኝ፣ ትዕዛዝ አስፈጻሚና ፈጻሚ የሆኑት የወቅቱ ኃላፊዎች ተግባራዊ ሂደታቸው በመጽሐፉ ተገልጾል፡፡ የመጽሐፉ አቅራቢ ራሱን የበዓሉ የመንፈስ ልጅ በማድረግ ፍጻሜውን ለማወቅ ያደረገው ጥረት እውነተኛ የመንፈስ ልጅነቱንም አስመስክሮበታል፡፡ በበዓሉ አሳዛኝ ህልፈት ምክንያት የሰቆቃው ገፈት ቀማሾች ባለቤቱ፣ ልጆቹና የቅርብ ዘመዶቹ ሲሆኑ፤ ለሀገራችን የስነ ጽሁፍ ሂደትና እድገት ብዙ ሊያበረክት የሚችለውን ይህንን ድንቅ ጸሐፊ ማጣትም ሀዘንና ቁጭቱ የብዙዎቻችን እንዳደረገው አምናለሁ፡፡

beyenemoges@yahoo.com


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1809

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>