Quantcast
Channel: Abugida Ethiopian American Amharic Web Page
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1809

የአትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥለሴ ትንግርታዊ ዝቅጠት (አብርሃም አየለ)

$
0
0

በቅርቡ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥለሴ ለቢቢሲ ጋዜጠኛ የሰጠው ቃለ መጠይቅ በዚህም ‹ዲሞክራሲ ለአፍሪካ አያስፈልጋትም! ለአፍሪካ የሚያስፈልጋት መልካም አስተዳደር ነው› ብሎ የተናገረው ‹ድንቅ› አባባል የመገናኛ ብዙሀን መነጋገሪያ ለመሆን መብቃቱ ይታወቃል፡፡ ኃይሌ ሊነግረን ያልቻለው በዲሞክራሲና በመልካም አስተዳደር መካከል ያለውን ተዛምዶና ልዩነት ነው፡፡

‹ትንሽ እውቀት አደገኛ ነው› የሚባል አባባል አለ፡፡ ትንሽ እውቀትም ሳይኖር አዋቂ ነኝ ብሎ በማያውቁት ጉዳይ ላይ መናገር ደግሞ ከአደገኝነት ባለፈ ፈገግ የሚያሰኝበትም ጊዜ አለ፡፡ የኃይሌን የተጠቀሰውን አባባልም ከዚህ አያልፍም፡፡

ከሁሉ በፊት የሚገርመው ኃይሌን ስለ ሩጫ፣ በሩጫም አማካኝነት ስለአገኘው ሀብትና በዚህ ስለሰራቸው ሆቴሎች ስለገነባቸው ህንጻዎች ጋዜጠኛው ቢጠይቀው መልካም በሆነ ነበር፡፡ ‹ከብት ባልዋለበት ኩበት ለቀማ› እንደሚባለው፤ ጋዜጠኛው ይህን የመሰለ ዐብይ ጉዳይ የጠየቀው ማንነቱን ሳያውቅ ቀርቶ ሳይሆን፤ ስለአፍሪካዊያን አመለካከት በዚህ መልኩ በማቅረብ አንባቢዎቹንና አድማጮቹን ፈገግ ለማሰኘት ይሆናል ብሎ መገመት ያስኬዳል፡፡

ከዚህ ጉዳይም አልፎ መንገድ በስሙ ሰይመን ከፍተኛ ቦታ ስለሰጠነው ኃይሌ ብዙ መናገር ይቻላል፡፡ ነገርን ነገር ያነሳዋልና እስቲ አንድ ሁለት የሚሆኑ ጉዳዮችን እናንሳ፡፡

በዓለም እውቅና ያገኙ አትሌቶች፤ በሩጫም ሆነ በኳሱ እንዲሁም በሌላ ያገኙትን ሀብት ወገናቸው የሚራደበትን ተቋማትና ሌላም አስተዋጽኦ ሲያደርጉ በብዛት ሰምተናል፡፡ በዚህም መልካም ምግባራቸው ከልብ ያደነቅናቸውም አሉ፡፡ ለምሳሌ ለመጥቀስ ያህል – አፍሪካዊ የሆነው የአይቮሪኮስቱ ተወላጅ ድሮግባን እንመልከት፡፡ በ38 ዓመት እድሜ ላይ የሚገኘው ይህ ታዋቂ የእግር ኳስ ተጫዋች ድሮግባ በአገሩ ለአገሩ ሕዝብ በሰራቸው አንጸባሪቂ ስራዎቹ ፍቅርና አክብሮትን ከወገኖቹ ለማግኘት ችሏል፡፡ ከአደረጋቸው ተግባራትም መካከል ለአብነት ያህል የሚከተሉት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ለአምስት ዓመታት በዘለቀውና በሁለት ተጻራሪ ቡድኖች መካከል በአገሩ የተደረገውን ደም አፋሳሽ የእርስበርስ ጦርነት ያለውን ተደማጭነት በመጠቀም እንዲቆም አድርጓል፡፡ ለአንድ ድርጅት ለሰራው ማስታወቂያ የተከፈለውን ሶስት ሚልዮን ፓውንድ እንዳለ ወገኑ የሚጠቀምበትን ሆስፒታል አሰርቶበታል፡፡ ለምሳሌ ያህል እነዚህ ተጠቀሱ እንጂ ድሮግባ በለሌች የማኅበራዊ ዘርፎችም እንዲሁ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ የሚገኝ ሰው ነው፡፡ የእኛው ኃይሌና ጓደኞቹ ሆቴል ከመስራት፣ ህንጻ ከመገንባት ባለፈ ይሄ ነው የሚባል ለወገናቸው ያደረጉት ምን አለ? መልሱን ለአንባቢ ልተወው፡፡

ማናቸውም ሰው በይበልጥም በዓለም አቀፍ መድረክ እውቅናን ያገኘ በሚዘዋወርበት አገር፣ በሚሰራቸውና በሚናገራቸው ሁሉ ሀገሩን በማስከበር፣ የሀገሩን ባህልና እሴት በመጠበቅ በኩል እንደ አምባሳደር ይቆጠራል፡፡ ይህም ምንም እንኳን ይህን አድርጉ ተብሎ የተጻፈ ህግ ባይኖርም እያንዳንዱ ዜጋ ሊከተለው የሚገባ አመለካከት ነው፡፡ እንግዲህ ኃይሌ በሚዘዋወርባቸው ቦታዎች ከውጭ ጋዜጦች ጋር በሚያደርጋቸው ቃለምልልሶች ሀሳቡን በእንግሊዝኛ ለመግለጽ የሚያደርገውን መፍጨርጨር እየተመለከትንም እየሰማንም ነው፡፡ ምናልባት በራሱ ቋንቋ በአስተርጓሚ ቢናገር ሊያስተላልፍ የፈለገውን በሙሉ ስሜት ለመግለጽ በቻለ ነበር፡፡ አሁን አሁንማ በሕዝባዊ ስብሰባዎች በጉርማያሌ ቋንቋ የሚሰነዝረው አስተያየት በእሱና በአድማጩ መካከል አስተርጓሚ ሳይስፈልግ አይቀርም የሚለውን እሳቤ እንድንወስድ አድርጓናል፡፡

ይህን የመሰለው ዝቅተኛ አመለካከት – ‹ትንሽ እውቀት..› በእሱ ላይ ቢቀር መልካም በሆነ፡፡ ከእሱም አልፎ ልጆቹን በአገራቸው ቋንቋ እንዳይናገሩና እውቀቱም እንዳይኖራቸው ‹አማርኛ ካካ፣ ኦሮሚኛ ካካ› በሚለው ጨቅላ አስተሳሰቡ በክሏቸው ይገኛል፡፡ ይህም ያለውን ግንዛቤና አስተሳሰብ ምን ያህል የወረደ መሆኑን ለማሳየት ጥሩ መስተዋት ነው፡፡

በመጨረሻም ከዙሁ አትሌት ጋር በተገናኘ ለአንባቢዎች ለማስተላለፍ የምፈልገው መልክት አለ፡፡ አሉታዊ አመለካከቶች ‹አይቻልም፣ ክልክል ነው› በተንሰራፉበት ህብረተሰባችን ይህን በአዎንታዊ አመለካከት ለመቀይር ከጥቂት አመታት በፊት ጥረት ተደርጓል፡፡ ‹ይቻላል!› የሚለውና በህብረተሱ ዘንድ እንደ መሪ መፈክር የተወሳደው ቃል ተግባራዊ እንዲሆን ያደረገው፤ ብዙዎች እንዳመኑበት አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ሳይሆን፤ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዜዳንት የነበረው አቶ ክቡር ገና መሆኑ እንዲታወቅና ስራውም ለባለቤቱ እንዲሰጥ አስገነዝባለሁ፡፡

Abrehamayele2008@gmail.com


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1809

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>