አልጄሪያ በ Front de Liberation National (FLN) መሪነት ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ነፃ ውጥታ ከቆየች በሁዋላ በ1990 (እኤአ) ባካሄደችው የመጀመሪያ ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የህዝቡን 67% ድምፅ በማግኘት አሸናፊ የነበረው የእስላማውያኑ ፓርቲ FLS (Front Islamique du Salut) ነበር። የምርጫው ውጤት በይፋ ታውጆ እስከዚያን ጊዜ ድረስ ብቸኛ ገዢ ፓርቲ የነበረው FLN በዝረራ መሸነፉን መላው አለም አውቆት እና አድንቆት sale ግን ውሎ ሳያድር ውጤቱ ተሰርዟል ተባለ።
በነፃ ምርጫ ውጤት ድል ያደረጉት መሪዎች አንድም ቀን ቤተ-መንግስት ደጃፍ ሳይረግጡ በአገሪቱ ጄነራሎች እና በምዕራባውያን ሙሉ ድጋፍ ወደ ወህኒ እንዲወርዱ ተደረገ። በደጋፊነት የተፈረጁ ዜጎች በከሀዲነት ተወንጅለው እንበለ ህግ ሰቆቃ ተፈፀመባቸው። በነፃ ምርጫ አሸንፎ ዕዳ መግባት ይሏል እንደዚያ ነው። አልጄሪያ ከዚያ ወዲህ እንድም ቀን ሰላም አድራ አታውቅም። ያንን እርምጃ በመውሰድ እንቅልፍ እንተኛለን ብለው የገመቱት ምዕራባውያንም ቢሆኑ ያሰቡት አልሆነም። ጦሱ ዛሬ ከአልጄሪያ አልፎ ጎረቤት አገራትን ነካክቶ እነ ቦኮ ሀራምን በናይጄሪያ ፈልፍሏል…
ከሙባረክ ውድቀት ወዲህ ግብፅ የሆነውን ሁላችሁም ታውቃላችሁ። በአብላጫ ህዝብ ድምፅ ያሸነፈው የእስላማውያን ፓርቲ መሪ በጄነራሎች እጅ ከቤተመንግስት ተጎትቶ መውረድ ሳያንሰው የሞት ፍርድ ተበይኖበታል። በተመሳሳይ ወቅት በዚያው ፍርድ ቤት ለብዙ ሰላማዊ ሰልፈኞች ግድያ እና ዓመታት ግፍ ተጠያቂ የሆነው ሙባረክ ነፃ ሆኖ ተገኝቷል – እርምጃው የህዝብ ነፃ ፍላጎት በአደባባይ ለመረገጡ ጉልህ ማሳያ ነው። የአሜሪካንን ጥቅም የሚያረጋግጡት የሙባረክ ጡት ልጆች ጄነራሎቹ እንጂ ህዝብ ፈቅዶ የመረጠው መሪ አይደለም። ዴምክረሲ ወዲህ አሜሪካ ወዲያ…
የአልጄሪያ ሰላማዊ ህጋዊ ምርጫ ሲጨፈለቅ በነበረበት ወቅት የአፍጋኒስታን ሙጃህዲን የሶቭዬትን ወረራ መመከት እንዲችል ልዩ ወታደራዊ ደጋፍ ስጭ ሆና የቀረበችው አሜሪካ ነበረች። እነ ቢንላደን ተገቢ ስልጠና እንዲያገኙ እና ከረቀቀ ፈንጂ እና ሚሳይል ጋር እንዲተዋወቁ አሜሪካ ልባዊ ድጋፍ አድርጋለች። በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር አፍሳ እስላማውያኑን ተዋጊዎች ስታሰለጥን እና ስታስታጥቅ ነገ ድል ተጎናፅፈው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ይዘረጋሉ በሚል ተስፋ አልነበረም – ለዚያም ደንታ አልነበራትም። አካባቢው ከኮሚኒስት ድባብ ነፃ መሆኑን ለማረጋገጥ ሲባል ብቻ የተወሰደ እርምጃ ነበር – እንደተጠበቀው ሁሉ የሶቭዬት ጦር ጓዙን ጠራርጎ ሸሸ – ሙጃህዲን በድል ተጠናቀቀ።
ባንድ ጊዜ እዚህ አልጄሪያ ላይ ፀረ-‘አክራሪ እስላም’ ፣ እዚያ አፍጋኒስታን አፍቃሬ-‘አክራሪ እስላም’ መሆን የአሜሪካ ውጪ ፖሊሲ ምን ጊዜም ከመሰረታዊ ጥቅም ዝንፍ የማይል መሆኑን ማሳያ ነው።
ውሎ አድሮ ግን አፍጋኒስታን ከመላው አለም ለተሰባሰቡ አዳዲስ የሙጃህዲን ተዋጊ ምልምሎች መካ ሆነች። ታሊባን አፍጋኒስታንን ብቻ ሳይሆን በሁሉም እስልምና ተከታይ አገሮች እና አልፎ መላው አለም በሙጃህዲን አመራር መዳፍ ስር መግባት እንዳለበት ተደፋፈሩ። ቢንላደን አፍጋኒስታን ላይ ከተመ – እናም የሴፕቴምበር 11 ጥቃት እቅድ እና አፈፃፀም የተነደፈባት ምድር ሆና ተገኘች – መጃህዲኖቹ ለስልጣን ከበቁ በሁዋላም ሆነ ከተባረሩ ወዲህ የነበረው እንዳለነበር ሆኖ ይኸው እስከ ዛሬ አካባቢው እንደታመሰ ነው። አሜሪካ መባነኗ ቀጥሏል…
በድህረ-ታሊባን ካቡል በሞግዚትነት የተቀመጠው መንግስት ደግሞ የርእሰ ከተማዋን ፀጥታ እንኳን በወጉ ማስከበር ያልበቃ ፣ በሙስና እጅግ አድርጎ የተዘፈቀ ፣ የጎሳ አለቆች የሚራኮቱባት ግን ምርጫ በያምስት ዓመቱ የሚጠራ – ‘ዴሞክራሲያዊ’ መንግስት ነው። ዛሬ ድርድር ተደርጎ ነፃ ምርጫ ቢፈቀድና ታሊባን ወደ ውድድር ቢገባ አላንዳች ጥርጣሬ እንደሚያሸንፍ ይታወቃል – ይህን ውነታ እነኝህም እነኛም… ሁሉም ወገኖች ጠንቅቀው ያውቃሉ – ደግነቱ ምርጫ እንጂ ነፃ ምርጫ የለም – አወይ ዲሞክረሲ!!
እናም የአሜሪካንን ጥቅም ተጠብቆ እንዲቆይ ከተፈለገ ሁሉን አሳታፊ ነፃ ዴሞክረሲያዊ ምርጫ አፍጋኒስታን ምድር ላይ ማድረግ የማይታሰብ ነው። ጉዳዩ ይህ ከሆነ ዘንዳ ታሊባን ምን ቀረው? በሰላማዊ መንገድ ስልጣን መያዝ ከተከለከልክ ሌላው መንገድ አመፅ ብቻ ነው… ትርምሱ ቀጥሏል።
አሁን ደግሞ የኛይቱን አገር በወፍ በረር እንቃኝ – በምርጫ 97 ወቅት ምዕራባውያን ታዛቢዎች የመሰከሩለት የቅንጅት ድል በወያኔ መጭበርበሩ ሳያንስ መሪዎቹ ወህኒ ወርደው ፍዳ እንዲቀበሉ ተደርጓል። ይህ ሲሆን ምዕራባውያን ዝርዝሩን ጠንቅቀው ያውቃሉ – የህዘብ ፍላጎት ምን እንደሆነ ግልፅ ነበር። ወያኔ በፈፀመው እመቃ የደረሰውን እልቂት እና ሰብአዊ መብት ጥሰት በአሀዝ ጭምር መዝግበው ሰነዳቸው ውስጥ አስቀምጠውታል – ዴሞክራሲያዊ ነፃ ምርጫ የሚባል ነገር በዚያች ምድር በወያኔ ፈቃድ የማይታሰብ መሆኑንም ተረድተዋል። አልጄሪያ ፣ ቺሌ ፣ ኮንጎ (ሉሙምባ) እና ግብፅ ላይ እንዳደረጉት ካምባገነኖቹ ጎን መቆማቸውን ፈጥነው አቋማቸውን ይፋ አላንፀባረቁም – ስልት የታከለበት የማዘናጊያ አዞ እምባ ማፍሰሳቸውም አልቀረም። ውሎ አድሮ ግን ከወያኔ ሌላ ታማኝ ሎሌ በዚያች ምድር እንደማያገኙ እንደተረዱ ሁሉ ዴሞክራሲያዊ በዚያች ምድር እንዲዳፈን ተገቢውን ድጋፍ ሰጥተዋል – አሁንም እየሰጡ መሆኑን ለማየት የኦባማን ጉብኝት ብቻ መጥቀሱ በቂ ነው።
በጥሞና ብናየው በዴሞክረሲያዊ እና ሰላማዊ ምርጫ ለስልጣን መብቃት ከንቱ መሆኑን የሚመሰክሩ ታሪካዊ ውነቶች እየተደጋገሙ ነው – ከዚህ የተነሳ ይመስላል ብቸኛው መንገድ ዘገር መነቅነቅ መሆኑን የሚመሰክሩ ፍልሚያዎች እየተጋጋሙ ነው።
በቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን የምዕራቡ ዓለም ወዳጅ ለመሆን ሶቪየት ህብረትን ወይንም ቻይናን ማውገዝ ብቻ ይበቃ ነበር። ቀይ አደጋ በቀላ አረር ይመከታል በሚል እነ ኮሎኔል ሞቡቱ ሴሴኮ በህዝብ ሙሉ ፍላጎት ስልጣን ላይ የወጣውን ወጣት መሪ ሉሙምባን ለሲአይኤ ቢላ ዳርገው እነሱ የዋይት ሐውስ ኮክቴል እንግዶች የሆኑበት ዘመን…። እነ ፒኖቼ የኮምኒስት አደጋን ከአሜሪካ ክፍለ ዓለም ለመፋቅ በሚል ሰበብ ህዝብ አደባበይ ተሰልፎ የመረጠውን መንግስት በታንክ ገልብጠው የፈጁትን ፈጅተው አሜሪካንን ከስጋት የታደጉበት ወረታ…።
በሰላማዊ መንገድ ፣ በህዝብ ምርጫ ስልጣን መያዝ የዴሞክረሲ ምሰሶ ነው የሚሉን ምዕራባውያን በተደጋጋሚ ያንን መርህ የሚጥስ ተግባር በመፈፀማቸው የተነሳ የነርሱም ሆነ የዴሞክረሲ ስብከታቸው ታማኒነት ተመናምኗል።
ዴሞክረሲን በአረቡ አለም ሰርፃለሁ በሚል ሰበብ ኢራቅ የዘመተው የአሜሪካ ሰራዊት የቀድሞ ወዳጁን ሳዳም ሁሴንን ገመድ ላይ አንጠልጥሎ ቢሸሽም በዚያች አገር ዘላቂ ህልውና ላይ ብሎም በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ዘንድ ያልተጠበቀ ስጋት የደቀነ ቀውስ አስከትሎ መቅረቱን ይኸው እየታዘብን ነው። አሜሪካ ወራሪ እንጂ የዴሞክረሲ ስርአት አዋላጅ አለመሆኗን እነ አቡጋሬብ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አስተጋብተዋል። በቁሙ ለውርደት የተዳረገው የአረብ ዘር ለበቀል ቆርጦ የተነሳ መሆኑን የሚያመለክቱ የቦምብ ፍንዳታዎች ፣ ጭካኔ የተመላበቸው ግድያዎች እየበረከቱ ነው። አይሲስ የተሰኘው አክራሪ የእስልምና ድርጅት ዛሬ የደረሰበትን ያጤኗል።
አይሲስ የወጣቱን ብሔራዊ ስሜት ለማነሳሳት እና ከጎኑ እንዲሰለፍ ለማድረግ ብዙ አልተቸገረም። እንደሚታወቀው በተዋጊነት የተሰለፉ ወጣት ወንዶች እና ሴቶች ከምዕራቡ አለም ድሎት ጭምር በፈቃዳቸው እየፈለሱ የሚሄዱ ናቸው – የግዴታ ምልመላ የለም። ለዚህ ያበቃቸው የሃይማኖት ሰበካ ብቻ ነውን(?) ብሎ መጠየቅ የፈለገ ምዕራባዊ አገር ያለ አይመስልም። አሸባሪነት ወንጀል መሆኑን ከመግለፅ ባሻገር የህዝብ ፍላጎት የተረገጠባቸውን አጋጣሚዎች መዘዝ ያጤነው የለም።
ሶቭዬት ዛሬ የለችም ፣ ቻይና ግን እግሯንም ጥፍሯንም አስረዝማ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የዜግነት ክብር በተጠሙ አገሮች ሁሉ ዋግምቷን ተክላለች። ዋግምቱን ለመንቀል ዴሞክረሲ ዋስትና ሊሰጥ አልቻለም! በመሰረቱ ቻይና ስለ ዴሞክረሲ እና ሰብአዊ መብት መረጋገጥ ደንታ የላትም። ስለዚያም የምተደሰኩረው ነገር የለም – ዴሞክረሲ ገሀድ በተጨፈለቀባቸው አገሮች ቀድማ በመድረስ እንደ ወያኔ ካሉ አፋኝ ገዢዎች ጋር ለመሻረክ ግን የሚቀድማት የለም። አለማችን እንዲህ ውጥንቅጡ በወጣ ትርምስ ውስጥ ትገኛለች። ግርግር ለሌቦች ፣ ለሰብአዊ መብት አፋኞች ፣ ለጎጠኞች ተመችቷል።
ብዙ የዋህ ዜጎች የማይጠብቁት እነ አሜሪካ በዚህ ትርምስ ውስጥ የመሳተፋቸው ነገር ነው። ህዝብ በነፃ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መተዳደር ይሻል – እስልምና እና ዴሞክረሲ ተጣጥመው መሄድ ይችላሉ። ድህነት እና ዴሞክረሲ ተጣጥመው መሄድ ይችላሉ። ዴሞክረሲ የህግ በላይነት ማለት መሆኑን ካሰመርንበት በህግ አግባብ ስልጣን የያዘን ሀይል ጨፍልቆ የይስሙላ ምርጫ እያደረጉ ስልጣን ላይ መቆየት ከወንጀሎች ሁሉ የከፋ ህዝብን ወደ አልተፈለገ አማራጭ የሚገፋ ጦስ ነው።
በነፃ ዴምክራሲያዊ ምርጫ በመረጡት መሪ መተዳደር ያልተፈቀደላቸው ህዝቦች የሚቀራቸው አማራጭ ምን እንደሆነ ለመተንበይ የፖለቲካ ጠቢብ መሆን አይጠይቅም።