ጀግናችንን ፍቱልን!! ይህ በፎቶው ላይ የምትመለከቱት የነፃነት ታጋይ የቀድሞው አንድነት ፓርቲ መስራች አባል፣ የወረዳ 2/14 ሰብሳቢ እንዲሁም የብሄራዊ ምክር ቤት አባል ነው:: ለሰው ልጆች ያለውን አክብሮት እና ፍቅር የትግል አጋሮቹ እንዲሁም የስራ ባልደረቦቹ እና እውቀቱን ሳይሰስት የሚለግሳቸው ተማሪዎቹ ምስክርነት የሚሰጡለት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ::ናትናኤል መኮንን ይባላል::
በቅርብ የምናውቀው ጓደኞቹ ሆድዬ በሚል ቅፅል ስም እንጠራዋለን። ለሰው ልጆች ሰላም እና ፍትህ ሲታገል የማፍያ ቡድን ስብስብ የሆነው የወያኔ መንግስት በሀሰት ክስ ወንጅሎ የ18 አመት እስራት በመፍረድ ወህኒ የወረወረው፣ ባለትዳርና የልጅ አባት የሆነው የፅናት ተምሳሌቱ ማንም የሚያወቀው፣ ይህ ትንታግ ፖለቲከኛ እንዲፈታም ጮኸን ድምፃችንን እናሰማለን።
ናትናኤል የሰላም ደቀ መዝሙር እንጂ አሸባሪ አይደለም። አሳሪዎቹ ካንጋሮው ፍርድ ቤት ባቀረቡት ጊዜ ይህንን ታሪካዊ ንግግር አድርጎ ነበር። እኔም ቀንጨብ አደረኩላችሁ፡
“ክቡር ፍ/ቤት፡- እኔ እንኳን ሰውን ያህል ክቡር ፍጡር ስለመግደል ላሴርና ፣ የህዝብ ሀብት፣ የሆኑትን መሰረተ ልማቶች ስለማውደም ላቅድ ቀርቶ አፈናን፣ ጭቆናንና ግፍን በሰላማዊ መንገድ ከመታገልና ከመቃወም ውጭ የገዥውን ፓርቲ አባላትና አመራሮች እንኳን በጥላቻ ዓይን ተመልክቼ አላውቅም፡፡ ወደፊትም አልመለከታቸውም፡፡ ነገር ግን በፅናት አምርሬ እታገላቸዋለሁ፡፡ አፈናቸውን እንዲያቆሙ ከቁልቁለት ጉዟቸው እንዲመለሱ።
ክቡር ፍ/ቤት፡- ሽብር የእኔ መገለጫ አይደለም፡፡ አገዛዙ እንዳለው እኔ ባለስልጣናትን ለመግደልና የህዝብ ሀብት የሆኑትን መሰረተ ልማቶች ለማውደም ያሴርኩ፣ ያቀድኩና በሽብር የተፈረጀ ድርጅት አባል ያልሆንኩና ከኢትዮጵያ ጋር በጦርነት ሁኔታ ላይ ካለው የሻዕቢያ መንግስት ጋርም የተባበርኩ ሳልሆን በሰላማዊ መንገድ የሚታገለው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ መስራችና የም/ቤት አባል ለአንድነት አላማዎች ተፈፃሚነት በቁርጠኝነት የምታገል፣ እንኳን ከሻዕቢያ ጋር ልተባበር፡- ከሻዕቢያ ጋር በመተባበር ሀገሬን የባህር በር ያሳጣትን ወያኔን የምታገል ለሀገር አንድነትና ክብር የምታገል፣ ሀገር ወዳድ ዜጋ ነኝ።
ክቡር ፍ/ቤት፡- አሁን በአገዛዙ እየተወሰዱ ያሉት የእስር እርምጃዎች ዋነኛ ምክንያት ሽብር ስለተሞከረ፣ ወይም ስለታቀደ፣ ወይም ደግሞ የሻዕቢያ ተላላኪ ስለተገኘ ሳይሆን ዜጐች ህገ-መንግስታዊ መብታቸውን በመጠቀም የሚያቀርቧቸውን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎች ማዳፈን ነው፡፡ እስሩ ባለ ሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ባለች ሀገራችን “ለምን ራበን፣ ለምን ኑሮ ተወደደ” ትላላችሁ ነው፡፡ ለምን የነፃነት ጥያቄ ታነሳላችሁ ነው፡፡ የእስሩ ምክንያት ለምን እኔ የምላችሁን ብቻ አትቀበሉም ነው፡፡ ለምን የለውጥ ጥያቄ ታነሳላችሁ ነው፡፡ የእሥሩ ምክንያት በአረብ አገራት የለውጥና የነፃነት ንፋስ ወደ አቶ መለስ አገዛዝም እንዳይመጣ የተወሰደ የመከላከል እርምጃ ነው።