Quantcast
Channel: Abugida Ethiopian American Amharic Web Page
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1809

የኢትዮጵያውያኑ በግፍ የፈሰሰ ደም ከወደ እስራኤል ይጣራል፣ ይጮኻል …!! በፍቅር

$
0
0

የምድራችን ግፉአንና ምስኪኖች እንባና ጩኸት፣ ዋይታና ሰቆቃ ምድሪቱን ክፉኛ እየናጣትና እያናወጣት፣ እያስጨነቃት ነው፡፡ በዚህች ክፋት በሰለጠነባት፣ ዓመፃ በነገሠባት ዓለማችን ጆሮን ጭው የሚያደርግ፣ እግዚኦ የአንተ ያለህ! የሚያሰኝ ሌላ ክፉ ወሬን እያየን፣ እየሰማን ነው፡፡ ገና አንዱን ኀዘናችንን በቅጡ ሳንወጣው፣ እንባችን ‹‹የፍትሕ ያለ!›› በሚል በጉንጫን ላይ እየፈሰሰ ባለበት እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ጻድቁ ኢዮብ የኀዘን መርዶን በላይ በላዩ እየሰማን፣ እየተደረበብን ነው፡፡

በምስኪን ሕዝባችን ላይ በደቡብ አፍሪካ፣ በየመን፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በሊቢያ በኾነውና እየኾነ፣ እየደረሰ ባለው ግፍ፣ መከራና ሰቆቃ ተጽናንተን ሳናበቃ፣ እንባችን ገና በጉንጫችን ላይ እያለ ይኸው ከምድረ እስራኤል ደግሞ ወገኖቻችን ደማቸው እንደ ውሻ ደም በቴላቪቭ፣ በአደባባይ እየፈሰሰ መኾኑን ከመገናኛ ብዙኃን እያየን፣ እየሰማን ነው፡፡ ምን ጉድ ነው ይኼ ወገኔ?!

በእርግጥ በዛች የተስፋ ምድር የቤተ-እስራኤላውያኑ አትዮጵያውያን ወገኖቻችን እየደረሰባቸው ያለው ግፍና መከራ ትናንትና የጀመረ አይደለም፡፡ እነዚህ ሰዎች ያችን የተስፋ ምድር ከረገጡ ጊዜ ጀምሮ እምብዛም አልደላቸውም፡፡ ማንነታቸውንና ታሪካቸውን፣ ባህላቸውንና ትውፊታቸውን በተመለከተ የገጠማቸውን ቀውስና ፈታኝ ጉዞ በድል ለመወጣት ዛሬም ብርቱ ትግል፣ ተጋድሎ ላይ ናቸው፡፡

የዘር፣ የታሪክ፣ የሃይማኖት፣ የባህል፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚው ጥያቄ በየፈርጁ እየተነሡና እየተጣሉ እረፍትና ሰላም በናፈቃት በዛች ምድር በየጊዜው የሚታየውና የሚሰማው ኹሉ የምድሪቱን እስትንፋስ የሚገዛ ከመሆን ካለፈም ሰነባብቷል፡፡ ከአይሁዳውያኑ ምድር የሚሰማ ዜና ኹሉ የምድሪቱን ልብ ምት ቀጥ የሚያደርግ እስኪመስል ድረስ ዜናው ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ፣ ከአውሮፓ እስከ ኤዥያ፣ ከቻይና እስከ ሕንድ፣ ከጃፓን እስከ አውስትራሊያ የሚናኝበት ፍጥነቱ አስገራሚም፣ ደናቂም ነው፡፡

የምድር ኹሉ ዓይን ማረፊያና የዓለማችን ፖለቲካዊ ትኩሳት ማዕከል በኾነችው እስራኤል ከሰሞኑን ደግሞ በሌላ መልክና ገጽታ ኢትዮጵያውያኑ ቤተ-እስራኤላውያን ኢሰብአዊ የኾነ ግፍና መድሎ እየደረሰባቸው ነው፡፡ በቴላቪቭ ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ኢትዮጵያውያን ከእስራኤል ፖሊሶች ጋር በመጋጨታቸው የተነሣ ደማቸው እንደ ውሻ ደም በእስራኤል ምድር እንዲፈስ ኾኗል፡፡

እነዚህ ወገኖች ጥቁር በመሆናቸው የተነሣ የዘር መድሎ ሲደረግባቸው፣ ለሕክምና በሚል ሰበብ የተቀዳ ደማቸውን ተጸይፈውት በመሬት ላይ ተደፍቶ ከአፈር ሲቀላቀልና ሲላቁጥ፣ በቅርቡም ቤተ እስራኤላውያኑ ሴቶች እንዳይወልዱ ዘራቸው እንዲመክን የተደረገበትን ሴራ፣ ኢሰብአዊና ጸያፍ የኾነውን አሰቃቂ ዜና ከዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ሲቀባበሉት እየተሳቀቅንና እያዘንን ሰምተናል፡፡

ግና የእኛ የኢትዮጵያውያን መከራችን፣ ዋይታችን፣ ሰቆቃችን ማባሪያ፣ ማቆሚያ የሌለው የመሰለው ለምን ይኾን?! እንዲህ በሔድንበት ምድር ኹሉ ክብር የሌለን፣ የተዋረድን፣ ያየን ኹሉ ፊቱን የሚያጠቁርብን፣ ግንባሩን የሚከሰክስብን፣ በረገጥናት ምድር ኹሉ እንደ ቃየል የጨካኞች የበቀል ሰይፍ የሚከተለን፣ የሚያሳደድደን፣ ጦርና ጎራዴ የሚመዘዝብን የኾነበት ምክንያቱ ምን ይኾን?! እንዲህ በላያችን ላይ ሰማይ ናስ፣ ምድሪቱም ብረት የኾነችብን ምክንያቱ ምንድን ነው፣ እኛ ምን ሕዝቦች ነን?!

ይህን ጥያቄ፣ ይህን ለዘመናት እንቆቅልሽ የሆነ በኢትዮጵያችን ላይ የተጣበቀብንን መከራ፣ ውርደትና ግፍ በተመለከተ ሃይማኖተኛውም፣ ፖለቲከኛውም፣ የተማረውም ያልተማረውም ኹላችንም በአንድነት ይህን ጥያቄ መጠየቅ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ግፋችን እንዲህ የበዛው፣ ተንከራታችና መፃተኛ የኾነው፣ እንባችን ማቆሚያ ያጣው፣ ተነሣን ስንል የምንወድቅበት፣ አሁንስ ነጋልን ስንል የሚጨልምበት፣ ተስፋችንና ብሩህ ነጋችን እንዲህ የራቀበትን ምክንያቱን ለማወቅ ራሳችንን መጠየቅ፣ አሁንም መጠየቅ!!

በምድረ እስራኤል በወገኖቻችን ላይ ወደደረሰባቸው ግፍ ጉዳይ ስንመለስም ከኹለቱ አገራትና ሕዝቦች ከታሪክና ከሃይማኖት አንጻር አንዳንድ እውነታዎችን ማነሳት ግድ ይለናል፡፡ በአንድ ወቅት አሁን በሕይወት የሌሉት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚ/ር የነበሩትና በቅጽል ስማቸው ‹‹ሻሮን ዘቡል ዶዘር›› በሚል የሚታወቁት ኤለን ሻሮን፣ አገራቸውን ሲጎበኙ ለነበሩት ለቀድሞው ጠቅላይ ሚ/ር ለአቶ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያውያንና እስራኤላውያንን በተመለከተ እንዲህ ብለዋቸው ነበር፡፡ ‹‹የኹለቱ አገራትና ሕዝቦች ሺ ዘመናትን ያስቆጠረው ግንኙነታቸው ጥልቅ የኾነ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ መሠረት ያለው ነው፡፡››

በእርግጥ በሃይማኖትና በታሪክ፣ በባህልና በትውፊት የተሳሰረ፣ ዘመናትን የተሻገረ በጋራ የሚጋሩት ማንነትና ታሪክ ባላቸው በኢትዮጵያና በእስራኤላውያን መካከል ይህ መኾኑ አሳፋሪም፣ እጅግም አሳዛኝ ነው፡፡ እስራኤላውያን ለነጻነታቸው ብርቱ የኾነ መሥዋዕትነትን ከከፈለው፣ የፈርኦን የልጅ ልጅ ከመባልና ከግብጽ ቤተ መንግሥት ድሎትና ደስታ ይልቅ ግፉአንን ምስኪን ከኾኑ ሕዝቦቹ ጋር መከራን መቀበል ከመረጠው ከነጻ አውጪያቸው ከትሑቱ ነቢያቸው፣ ከሙሴ ጀምሮ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የታሪካቸው፣ የማንነታቸው ማዕከልና ማጠንጠኛ ነበር፣ ነውም ብል እምብዛም ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡

አይሁዳውያኑ ለነጻነታቸው ባደረጉት ለአርባ ዓመት በዘለቀው የበረኻ ጉዞአቸው ኢትዮጵያዊቱን ያገባው ነጻ አውጪው ሙሴ፣ በሚስቱ አማካኝነት የኢትዮጵያዊነት ክቡር ማንነትን ተካፍሏል፡፡ ከፈጣሪ ዘንድ የተቸረውን የኢትዮጵያዊነት የነጻነት ክቡር መንፈስ፣ ግዙፍ ታሪክ፣ ገናና ሥልጣኔና ሕያው ቅርስ ሙሴን ልቡን በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ማንነት ውስጥ እንዲሸፍት እንዳደረገውም ጥርጥር የለውም፡፡

እናም የአይሁዳዊው ሙሴና የኢትዮጵያዊቱ ጋብቻ መሠረቱ የወረት ፍቅርና ዘርን የመተካት ዓላማን ብቻ ያነገበ አልነበረም፡፡ ጋብቻው ከሥጋዊነት ባለፈ ጥልቅ የኾነ መንፈሳዊ መሠረትና ትርጓሜ ያለው ነበር ማለትም ይቻላል፡፡ ይህን አሁን ለመተንተን የምሞክረው አይሆንም፡፡ ግና በወቅቱ ይህ የሙሴ ጋብቻ ብርቱ የኾነ ቁጣን አስነሥቶ ነበር፡፡ ከእኛ ዘርና ሃይማኖት ውጭ ጋብቻ ምን ሲባል ይታሰባል በሚሉት በወንድሙ አሮንና በእህቱ ማርያም በኩል ሙሴ የበረታ ተግሣጽና ቁጣ ነበር የገጠመው፡፡

ከወገናችን ውጭ የተደረገ ጋብቻ ነው በሚል ተነሣውን ግብዞቹን የዘር፣ የማንነት ጥያቄ መሠረት አልባ፣ እርባና ቢስና ውድቅ ያደረገ ምላሽ ከሰማይ አምላክ ዘንድ ተሰጣቸው፡፡ በእነዚህ በሙሴ ተቃዋሚዎች ላይ ከአምላካቸው ያሕዌ ዘንድ የመጣው ቁጣ በለምጽ እንዲነዱ አደረጋቸው፡፡ ይህን አይሁዳውያኑን ግብዝነት ከንቱ ያደረገ ሌላም እውነታ በታሪካቸው ኾኗል፡፡ እስቲ በአጭሩ እንየው፡፡

ከአሕዛብ ወገን የኾነችው ሞዓባዊቷ ሩት አይሁዳዊት ምራቷን ኦርፋን ሕዝብሽ ሕዝቤ፣ አምላካችሁ አምላኬ ይኾናል፡፡ እኔና አንቺን ሞት እንኳን ቢሆን አይለየንም በሚል የበረታ እምነት፣ ጽኑ ፍቅርና ተስፋ በኢየሱስ ክርስቶስ ዘር ግንድ ውስጥ የገባች ብቸኛዋ ሴት ለመኾን በቅታለች፡፡ እናም እውነታው ሲከፈት፣ ሐቁ ሲገለጽ ጥያቄው አይሁዳዊ የመኾን፣ የዘር ወይም የማንነት ጉዳይ አልነበርም፡፡ ይልቁንም ሞት እንኳን የማይረታው ፍቅር፣ የጸና እምነት፣ ብርቱ ትዕግሥት፣ ዘላለማዊና ሰማያዊ ተስፋ እንጂ!! ሙሉ ታሪኩ በመጽሐፈ ሩት ውስጥ በዝርዝር ተጽፎ ይገኛል፡፡

በሙሴና በልጆቹ ደም ውስጥ የሠረጸው የኢትዮጵያዊነት ነጻነት፣ ውበትና ጥበብ እዛ ጋር ብቻ አልቆመም፡፡ በዝና በሰማችው ጥበቡና ማስተዋሉ በጥበብ ፍቅር የወደቀችው ኢትዮጵያዊቷ ንግሥተ ሳባ ጥበብን ፍለጋ አገሯንና ሕዝቦቿን ጥላ ተሰዳ ነበር፡፡ ይህን በጆሮ የሰማችውን የንጉሥ ሰለሞንን ጥበብ በዓይኗ አይታ ለማረጋገጥ ከብዙ ጓዝና ስጦታ ገር ወደ እስራኤል ምድር የተጓዘችው ሳባ ‹‹ባየችውና በሰማችው ነገር ነፈስ አልቀረላትም፡፡›› ነበር ይለናል ቅዱስ መጽሐፍ፡፡

ይህች የጥበብ ምርኮኛ፣ በጥበብ ፍቅር የተነደፈች ኢትዮጵያዊት ንግሥት በዛ በሰለሞን ጥበብና ማስተዋል ውስጥ አሻግራ ያየቸው፣ በሩቅ የተሳለመችው፣ ሐዋርያው ቅዱስ ጳወሎስ ለቆላስያስ ክርስቲያኖች በጻፈው መልእከቱ አስረግጦ እንደተናገረው፣

‹‹የእግዚአብሔርን ምሥጢር፣ የተሰወረ የጥበብና የእውቀት መዝገብ የኾነውን››፡- የዳዊትን ልጅ፣ የቅድስት ድንግል ማርያምን ልጅ፣ የሕያው እግዚአብሔርን ልጅ፣ የሰው ልጅ ተብሎ የተጠራውን ኢየሰሱ ክርስቶስ ነበር፡፡ በመዋዕለ ሥጋዌውም ኢየሱስ እንዲህ ሲል ተናገረ፡፡ ‹‹… ንግሥተ ዓዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰለሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፤ እነሆም ከሰለሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ፡፡ (ማቴ. ፲፪፣፵፪)

በንግሥተ ሳባ ውስጥ በሩቅ ቆመን፣ በሩቅ ኾነን የተሳለምነውን፣ የናፈቅነውና ተስፋ ያደረግነውን የእግዚአብሔርን ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን በኋለኛው ዘመን ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ በወንጌላዊው ፊሊጶስ አማካኝነት በጥምቀት ተቀበልነው፡፡ ያች በጥበብ ፍቅር የወደቀች ኢትዮጵያና ሕዝቧም በኢየሩሳሌም ሊሰግድና መሥዋዕት ሊያቀረብ በኼደው በጃንደረባው፣ የዘላለም ኪዳን ተስፋ በኾነው በኢየሱስ ክርስቶስ ናፍቆቷ ፍጻሜውን አገኘ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሀ ሀበ እግዚአብሔር!›› እንዲል፡፡ ንጉሥ ዳዊት፡፡

ከዚህ እውነታ ጋር መታረቅ፣ ዛሬም ከዚህ እውነታ ጋር መቆም ያቃታቸው ‹‹የእፉኝት ልጆች›› ግን ዛሬም ዘር መዘው፣ አጥንት ቆጥረው፣ የቆዳ ቀለም ለይተው ደም እያፈሰሱ ነው፡፡ የአብርሃም ልጆች ነን ይላሉ፤ ግና የአብርሃምን ሥራ ለመሥራት ፈጽመው አይወዱም፣ አይፈቅዱምም፡፡ እናም ዛሬም አባቶቻቸው እንዳደረጉት ኹሉ ደምን በግፍ ያፈሳሉ፡፡ ‹‹በምድርህ ላይ በሚኖሩ ስደተኞችና መፃተኞች ግፍን አታድርግ፣ አንተም በአሕዛብ ምድር መፃተኛና ስደተኛ የኾንከብትን ጊዜ አስብ፡፤›› የሚለውን የአምላካቸውን ማስጠንቀቂያና ማሳሰቢያ ረስተውታል፣ ዘንግተውታል፡፡

እነዚህ አይሁዳውያን ሕዝቦች ለዘመናት እንደ ጨው ዘር በተበተኑበት ዓለም ኹሉ መጠጊያና መድረሻ የተነፈጋቸው፣ በምድር ዙርያ ኹሉ ተበትነው፣ ፍዳቸውን ሲያዩ የነበሩ፣ መከራና ግፍ የጸናባቸው ሕዝቦች፣ በቁማቸው ቆዳቸው እየተገፈፈ፣ ሰውነታቸው ስብ እየቀለጠ ለሳሙና መስሪያነት የዋለ፣ በሂትለር ትእዛዝ ስድስት ሚሊዮን ሕዝባቸው በግፍ ያለቁባት እስራኤል ዛሬ ያን የትናንትና ታሪካቸውን ዘንግተው በምድራቸው መፃተኛ በኾኑ ሕዝቦች ላይ እንዲህ ዓይነቱን ግፍ መፈጸማቸው ወዮው ያሰኛል፡፡

እስቲ መቼም ሰሚ አገኝንም አላገኘንም አንድ ነገር እናድርግ፡፡ በአገራችንም ኾነ በዓለም ዙርያ ኹሉ በሕዝባችን ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍና በደል ይቆም ዘንድ ድምፃችንን ከፍ አድርገን እናሰማ፡፡ የአንድ ነጭ ሞት ዜና ከጫፍ እስከ ጫፍ በሚናኝነበትና ቁጣ በሚቀሰቅስባት፣ ፍትሕ በጎደላት በዚህች በምንኖርባት ዓለም አፍሪካዊ፣ ኢትዮጵያዊ ወይም ጥቁር በገፍ በሚታረድባት ዓለም፣ የጥቁር ዘር ነፍስን ባለቤትና ጠያቂ የሌላት አድርጎ መቁጠር የግፍ ግፍ፣ ኢሰብአዊነትና ወደር አልባ የኾነ ጭካኔ ነውና ኹላችንም ድምፃችንን እናሰማ፡፡

መቼም በነጩም ኾነ በጥቁር ወንድሞቻችን ደም ስር ውስጥ የሚፈሰው ደም ያው ቀይ መኾኑን ይዘነጉታል ብልን አናስብም፡፡ በዘረኝነት ክፉ መርዝ ፈጽሞ የነተበ፣ ብኩን የኾነ ግብዝ ማንነታቸው ወደ ፍቅር፣ ወደ እውነት፣ ወደ ፍትሕ መንገድ ይመለስ ዘንድ ለእነዚህ ወገኖች እንጸልይላቸኋለን፣ እንመኝላችኋለንም፡፡ እስከዛው ግን ፍቅርን፣ ሰላምን፣ እውነትንና ፍትሕን በተጠማች ምድር የወገኖቻችን፣ የግፉአንና የምስኪኖች እንባና ደም እስኪታበስ ድረስ ለፍቅር፣ ለሰላም፣ ለእውነትና ለፍትሕ እንባችን ምድሪቱን አልፎ ሰማዩን እስኪያናውጥ ድረስ መጮኻችንን አናቋርጥም፡፡
ሰላም! ሻሎም!


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1809

Trending Articles