- እነ BBC፣ CNN የተገደሉት ኢትዮጵያዉያን ናቸው ሲሉ ወያኔዎች ማረጋገጫ የለንም አሉ።
- ኢቢሲ የሊቢያውን ጭፍጨፋ የዘገበው እንደተራ ዜና በሶስተኝንት ነው።
አል ጃዚራ ክርስቲያን ኢትዮጵያዊያንን አይሰስ፣ በሊቢያ ኢሰብአዊና ፍጹም ጭካኔ በተሞላበት መልኩ እንዳረዳቸው ዘግቧል። CNN “ISIS operatives have beheaded two groups of prisoners, believed to be Ethiopian Christians, in Libya” ሲል፣ BBC ደግሞ “ISIS releases new ‘killing’ video of Ethiopian Christians” በማለት የተገደሉት ኢትዮጵያዊያን ክርስቲያኖች እንደሆኑ ነው የገለጹት።
የወያኔ ቲቪ (ኢቢሲ) በተገደሉ ወገኖቻችን ዙሪያ አጭር ዘገባ አቅርባለች። ሬድዋን ሁሴን የተባለውን ግለሰብን በመጥቀስ የተገደሉት ኢትዮጵያዉያን ስለመሆናቸው ማረጋገጫ የለም የሚል መልእክት ነው ለኢትዮጵያ ህዝብ የተነገረው። ሕዝቡ “እግዚአ” እንዳይል፣ እንዳይጸልይ፣ ለምን እነዚህ ሰዎች ግድያው የተፈጸመው በኢትዮጵያዉያን ላይ እንደሆነ ለመሸፈን እንደፈልጉ አይገባኝም። እነዚህ ሰዎች በኢትዮጵያዊያን ላይ ምን አይነት ችግር ነው ያላቸው ? በደቡብ አፍሪካም ቢያንስ አለም ሁሉ ያወቀው የሶስት ኢትዮጵያዉያን አስክሬን ወደ አዲስ አበባ ተልኮ ሳለ፣ በደቡብ አፍሪካ የወያኔ አምባሳደር አንድ ሰው ብቻ ነው የሞተው ብሎ ነው መግለጫ ያወጣው። የአፍሪካ አገሮች ሁሉ የዙማ መንግስት ካይ ጠንካራ አቋም ሲወስዱ ፣ እነ ኃይለማሪያ ደሳለኝ ግን የኢትዮጵያ ሳይሆን የደቡብ አፍሪካ መሪ ነበር የመሰሉት።
አሁን ደግሞ እነ BBC ፣ እነ CNN ፣ አል ጃዚራ ..ያሉ ትላልቅ የሜዲያ ተቋማት፣ ኢትዮጵያዊያን ክርስቲያኖች ናቸው የተገደሉት ሲሉ፣ የወያኔ ቴለቭዥኝ፣ በግብጽ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዉስጥ የተኮለኮሉ ካድሬ ሰራተኞችን በመጥቀስ፣ የተገደሉት ኢትዮያዉያን ላይሆኑ እንደሚችሉ ሲነግረን መስማቱ ድጋሚ እንደመታረድ ነው። ለመሆኑ እነ ሬዳውን ሊቢያ ሄደው DNA ሊያጣሩ ነው ?
ሌላው ደግሞ በጣም ያስገረመኝ፣ ያስደነገጠኝና ዉስጤን ያቆሰለው ነገር ቢኖር፣ ዜናው በኢቲቪ/ኢቢሲ የተሰጠው ሽፋን ነው። ሶስተኛ ዜና ሆኖ ነው የቀረበው። አስቡት ሰበር ዜና፣ ብሬኪንግ ኒዉስ ሆኖ ነበር መቅረብ የነበረበት። ግን እንደዝይ አይዴ የቀረበው። ሰዓት ተጠብቆ በሁለት ሰዓት ዜና ነው የተነገረው። መጀመሪያ ስለ ኮሪያ ባለሃብቶች ዘገቡ፣ ከዚያም በአዲስ አበባ ተደረገ ስላሉት የጣና ጉባኤ ዘገቡ፣ በሶስተኛ ደረጃ ነው ከሁለት ደቂቃ በማይበልጥ ስለ ሊቢያው ጭፍጨፋ ደግሞ ትንሽ የተነፈሱት።
ዜናው እንደተሰማ ፕሬዘዳንት ሙላቱ ከኮሪያ መመለስ ነበረባቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቴሌቭዝን ቀርበው ንግግር ማድረግ ነበረበት። ሕዝቡን የሚያረጋጋ መልእክት መተላለፍ ነበረበት። ህዝቡ ጸሎት እንዲያደርግ፣ ባንዲራ ለሳምንት እንዲዘቀዘቅ፣ በሊቢያ ያሉ ወገኖቻችን ከፈለጋችሁ ተመለሱ ሳይሆን፣ ፈልገው እንዲመለሱ ማግባባትና ማሳመን የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልግ ነበር። ሆኖም ከወያኔዎች ፣ ትንሽ ቢሆን ሃዘኔታ፣ ሴንሲቲቪቲ የሚባል ንገር አላየንም። አቦ እነዚህ ሰዎች ሰይጣኖች ናቸው። ይግረማቸው ብለው እንደው “ዜጎቿን ከሽብርና ከአሸባሪዎች ጥቃት ለመታደግ የሚያስችላትን አስፈላጊውይን ዝግጁነት ተግባራዊ በማድረግ የሃገሩቱን ሰላምን መረጋጋት እንዲሁም ልማት በአስተማማኝ ለማረጋገጥ ችላለች” እያሉም ተመጻድቀዉብናል። ምን አለ አሁን እንኳ ስለልማት እያወሩ ባያሰለቹን ?
እንግዲህ ወገኖቼ፣ አስቡት ኢትዮጵያውያንን ከሽብር ጠብቀናል እያሉ ነው የሚመጻደቁት። እንኳን ወገኖቻችን ከሽብር ሊጠብቁ፣ እንኳን ወገኖቻችን ሊሰበስቡ፣ እንኳን ወገኖቻችን ለማዳን ሊተጉ፣ ወገኖቻችን ፓስፖርት ሲፈለግ፣ የተለያዩ ሰርቪስ ሲሹ እነርሱን የሚያንገላቱ ናቸው። በአገር ቤት ደግሞ ሰላማዊ ዜጎችን ሽብርተኛ እያሉ የሚያሸብሩ ወንበዴዎች ናቸው።
ኢትዮጵያዊያን ከአገር የሚሰደዱት በነርሱ አገዛዝ ምክንያት ነው። ኢትዮጵያ ለነርሱና ለዘመዶቻቸው፣ ለጥቂቶች ገነት፣ ለአብዛኛው ህዝብ ግን የምድር ሲኦል በመሆኗ ነው። በስደት ያሉትም ወደ አገራቸው መመለስ የማይፈልጉት፣ ኢትዮጵያ ምን እንደሚጠበቃቸው ስለሚያወቁ ነው። ሕግ የለም። አቤት የሚባልበት ቦታ የለም። ፍርድ ቤት የለም። የብር የመግዛት አቅም ላይ ወጧቷል። ያልታወቀበት ረሃብ፣ ዉስጥ ዉስጡን በጠኔ ሰዉን እየገደለ ነው። ወያኔ ካልተኮነ ሥራ ማግኘት የለም። ኢትዮጵያዉያን በአገራቸው ባሪያና የተጨቆኑ ስለሆኑ፣ የዚህ ዘር፣ የዚያ ዘር እየተባሉ በአገራቸው ስለሚፈናቀሉ፣ የተሻለ ነገር ካገኘን ብለው ነው አገር ጥለው የሚሄዱት። በደቡብ አፍሪካም በሊቢያም ለተፈጠረው፣ በዋናነት፣ ኢትዮጵያውያን በገፍ ከአገር እንዲወጡ የሚያስገድድ ፖለቲካን የሚያራምደው የወያኔ ስርዓት ነው።
እንግዲህ በዚህ ሳምንት የተፈጠሩት፣ ልብን የሚሰብሩ፣ ምናልባትም ለብዙ ሳምንታት በሐዘን አንገታችንን የሚያስደፉ ክስተቶች ወደፊት እንዳይከሰቱ ማሰብና መጸለይ አለብን። አሜሪካኖች አልካይዳ አይርፕላኖች ጠልፎ በአንድ ቀን በጥቂትን ደቂቃዎች ዉስጥ ከሶስት ሺህ በላይ ሰው ሲጨፈጭጭፍባቸው፣ አዘኑ። ግን እዚያ ላይ አላቆመም። ዴሞክራት፣ ሬፓብሊከን ሳይባባሉ እንደ ሕዝብ የአሜሪካን ጠላቶችን ለመፋለም ተነሱ። እኛም እነዚህ ትላልቅ ሐዘኖች ዉስጣችንን ቢሰብሩትም፣ እንደ ሕዝብ ሊያሰባስቡን ይገባል። እንደትሰበርን፣ እንዳዘንን መቅረት የለብንም። አገራችን ዉስጥም እንገደላለን። እንታሰራን። እንደበደባለን። በዉጭ አገርም እንገደላለን። አገር ቤት ያለውን ድህነት፣ በሽታ፣ ሽብር፣ ጭቆናና ግፍ ለመሸሽ ስደት መፍትሄ የማይሆንበት ጊዜ እየመጣ ነው። በመሆኑም ሁላችንም አገራችንን ለስደትና ለመከራ እየዳረገ ያለዉን ዘረኛ ስርዓት እንዲለወጥ ከመቼዉም ጊዜ በላይ መትጋት አለብን። አገር እያለን የምንዋረድበት ምንም ምክንያት የለም።
ከሁሉም በለይ ደግሞ እንደ ህዝብ ንሰሐ እንግባ። እግዚ እንበል። የተጠላን እንታረቅ። በጥንቆላና በመሳሰሉት የተጠመድን ወደ እግዚብሄር ፊታችንን እንመልስ። እግዚአብሄር ከፍርሃት፣ ከራስ ወዳድነት፣ ከጥላቻ፣ ከዘረኝነት፣ ከሙስና ፣ ከጭካኔ ነጻ ወጥተን እንደ ህዝብ እጅ ለእጅ የምንያያዝ፣ አንዳችን ለአንዳችን የምናስብ፣ አንዳችን ሲያመን ሌሎቻችንም የሚያመን፣ የወደቀን ረግጠን የምናልፍ ሳይሆን የወደቀን የምናነሳ ህዝብ ያድርገን !!!!!
አንዳንድ የወያኔ ካድሬዎች ሊከራከሩ የሚሞክሩ አሉ። ከላይ የጻፍኩት ፈጥሬ ሳይሆን ትክክለኛ እንደሆነ ያወቁ ዘንድ የኢቢሲ/ኢቲቪ ሊንክ ከታች አስቀምጫለሁ። ለማወዳደር ይቻል ዘንድ እነ BBC ፣ እነ CNN የዘገቡትን እንዲሁ፡
http://www.ethiopian.tv/ethiopian-news-sunday-april-19-2015/
http://www.bbc.com/news/world-middle-east-32373166
http://www.cnn.com/2015/04/19/africa/libya-isis-executions-ethiopian-christians/