ሆያሆዬ ሳይደርስ ሆያሆዬ .. ዉሮሸባዬ ሳይከፈት እስክስታ..ካለጊዜ ያውራዶሮ ገደል ማሚቱ ከመሆን አንድም ይሰውረን አንድም ያድነን::ምርቃት የማይደርስበት እርግማን እንደክፋት ላይገን ያደባበት የጊዜ ጀግንነት ለመደረብ የምንራወጥበትን ሰከን ብለን በሰውነት ጀግንነት የምንለካ ያድርገን::ጊዜን በአግባቡ እንደ ወርቅ ለመድመቅ ልንጠቀምበት የሚገባዉን ከአንዱ ይህ እይታውን ያደላዋል::የሚገባው በሚገባው ዘመን ላይ የማይገባው በሚያላዝንበት መደድ ላይ መሆናችንን መዘንጋት የለብንም:: በማንኛውም ደረጃ ላይ ቢሆን በትክክል ጊዜን መጠቀም ልናውቅበት ይገባል፡፡ ከልክ እና ከአቅማችን በላይ ከመጣደፍ ያድነን ፤ ካልሆነ ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ ይራመዳሉ ፡፡ የትክክለኛዋ ቅፅበት ሰላይ ልንሆን ይገባል፡፡ የጊዜን መንፈስ አነፍንፈን ማሸተት ግድ ይለናል፡፡ ወደ ድል የሚወስዱንን መንገዶች በዚያ እናገኛለን፡፡ ጊዜው ካልበሰለ ማፈግፈግን ልናውቅበት ይገባል፡፡ ሲበስል ደግሞ ፈፅሞ ወደኋላ ማለት አይገባም: ወደፊት መገስገስ ነው::ታላቅ ቁምነገር ይህ ነው ጊዜን እና ትግልን እያቀናጁ ወደድል መንጎድ ነው::
ጊዜን በትክክል መጠቀም የሚችል ዝግጅትን ዋና ጉልበቱ ያደርጋል፡፡ ድግሱ ከመድረሱ በፊት የምግብ እህሉን፣ የጌሾ ጥንስስ ስንቁን ማደራጀትና በመልክ መልኩ መሸከፍ፣ መጥኖ መደቆስ፣ መብሰያና መፍያ ጊዜውን በቅጡ ለድግሱ ሰዓት ማብቃትን ከሸማች እስከ አብሳዩ ውል ሊያስገቡት ይጠበቃል፡፡እንኳን ከበሰለ በኋላ እንዲሁም መዘናጋት አይገባንም::ያለመላ ግጭት ጅልነት ነው፡፡ የዝግጅት ጊዜ ወስዶ አስቦ፣ ሁሉን አመቻችቶ ነው ትግል፡፡ አንዴ ከገቡ ደግሞ መስዋዕት መኖሩን ሳይረሱ ምንጊዜም ሳያቋርጡ፣ ሳይማልሉና ሳይታለሉ መቀጠል ግድ ይሆናል፡፡
ዘመን የጊዜ ጥርቅምና የቅራኔና የሥምረት ውጤት ነው፡፡ ስለዚህም እንደታሪክ ክፉውንም ደጉንም ማጣጣሚያውና ያንን የመመርመር፣ ከስህተት የመማር፣ ነገን የመተለም ጉዳይ ነው ጊዜን ማወቅ ማለት መጪውንም ምርጫ በጊዜ ማስላት ነው የምንለው ለዚህ ነው፡፡ ጊዜን ጨበጥክ ማለት ድልን ጨበጥክ ማለት ነው፤ የሚባለው እንዲያው ለወግ አይደለም! ጊዜን እንደመሳሪያ የምንቆጥረው ከዚህ በመነሳት ነው፡፡ ንቃት እና ግንዛቤን በጊዜ እንግዛ ሌሊትን፣ ተስፋንና ንጋትን – ይንገረን፡፡ ይህ ሚጠቅመን በማታ ሩጫ እንዳንጀምር ከነጋ በኋላም እንዳንዘናጋ ነው!