Quantcast
Channel: Abugida Ethiopian American Amharic Web Page
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1809

የመረጃ ግብአት…የ”ወሳኙ ማዕበል”ዘመቻ 9ኛ ቀን ውሎ አበይት ክንውኖች በነቢዩ ሲራክ

$
0
0

* በ9ኛ ቀን በሳውዲ መራሹ ” ወሳኙ ማዕበል !” የአየር ማጥቃት ዘመቻ በየመን ሰማይ በተጠኑ ወታደራዊ የሁቲ አማጽያን ይዞታዎች ላይ አየር ድብደባው መቀጠሉን የዘመቻው መምሪያ ቃል አቀባይ ብ.ጀኔራል አህመድ አሲሪ ናቸው ፣ ጀኔራሉ በዚሁ መግለጫች በወደብ ከተማዋ በኤደንም የሁቲ አማጽያ አልበገርላቸው ካለው የአካባቢ ሚኒሽያ ጋር ውጊያ መግጠማቸውን አስረድተዋል

* ከሁቲ አማጽያንን ኤደንን እንዳይቆጣጠሩ በአካባቢው ሚኒሽያ በመሬት ቃታ እየሳበ እንቅስቃቀሴያቸውን ሲያሽመደምደው በሰማይ የህብረቱን ጦር በተጠኑ ኢላማዎች ላይ እንዲያተኩር በማድረግ በሚከወነው ድብደባ አማጽያኑን አቅመ ቢስ አድርጎ እንዳዳከማቸው ቃል አቀባዩ ተናግረዋል

* ቃል አቀባዩ ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ሰርጎ የሚገባባትን በሚዮን ደሴት Meon Island የሚገኙ የባህርና ሃይሉና የእግረኛው ጦር መሳሪያዊች በሳውዲ መራሹ የአየር ድብደባ ኢላማ ገብተው ተደምስሰዋልም ብለዋል

* በአየር ድብደባው ተስፋ የቆረጡና የተዳከሙት የሁቲ አማጽያን በመገናኛ ብዙሃንን ከእውነት የራቁ መረጃዎችን በማሰራጨት ህዝቡን በማሳሳት ላይ ናቸውም ብለዋል ብ.ጀኔራል አህመድ አሲሪ

* በሌላ በኩል እየተካሔደ ስላለው ዘመቻ ማብራሪያ የሰጡት በአሜሪካ የሳውዲ አንባሳደር አድል አልጃብሪ ዘመቻው በጥሩና በመጥፎ መካከል እንጅ በሱኒና በሸአ የእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል ሚካሔድ ጦርነት አለመሆኑን ተናግርዋል። አምባሳደሩ በማከልም የሳውዲ መራሹ አረብ ሃገራት ዋና አላማ በኢራን በሂዝቦላህ የሚመራውን የሁቲ አማጽያን ከስልጣን አስወግዶ ፣ ህጋዊው የፕሬዚ አብድልረቡ መንግስት ወደ ቦታው መመለስ ነው ብለዋል ። አንባሳደሩ የቀድሞው የየመን ፕሬዚ አሊ አብደላህ ሳላህን በሚመለከት ሲናገሩ አሊ አብደላ ሳላህ ከሁቲዎች ጎን መሰለፋቸው የተሳሳተ አካሄድ ነው ሲሉ ነቅፈውታል

በሳውዲ የመን ደንበር ድንበር መገዳደል …
============================

* በሳውዲ የመን ድንበር ባሳለፍነው ረቡዕ አንድ ድንበር ጠባቂ በሳውዲ የመን ድንበር ሁለት የድንበር ጠባቂ መገደላቸው የሚታወስ ሲሆን ትናንት አርብ ተጨማሪ ሁለት ወታደሮች መሞታቸውን ተጠቅሷል ። መረጃውን የድንበር ጦሩ ዳይሬክተር ሌተናል ኮሎኔል አዎል ቢን ኢድ አል በላዊ አረጋግጠውታል

* የሳውዲው ንጉስ ሰልማን ቢን አብድልአዚዝ የሟች የድንበር ወታደር ቤተሰቦችን ልዩ የሀዘን መልዕክተኞች በመላክ አጽናንተዋል

ከዘመቻው ድጋፍ እስከ የመንን መልሶ መገንባት ….
================================

* በሳውዲ ታላላቅ ምሁራንና ታላላቅ የሐይማኖት አባቶች በሳውዲ መራሹን የየመን አየር ድብደባ ድጋፋቸውን እየሰጡ ነው

* የመን ከሁቴ አማጽያን ጠርታ የፕሬዚደንት አብድል ረቡ መንሱር ሃዲ መንግስት በሁቲ አማጽያን የተቀማውን ስልጣን ተቀብሎ የመን ስትረጋጋ የባህረ ሰላጤው ባለ ሃብቶች 150 በላይ ፕሮጀክቶችን በመክፈት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የማፍሰስ እቅድ መያዛቸው ተጠቅሷል
( መቸ ይመጣ ይሆን? ብቻ ለዚያ ቀን ያድርሰን …)

በየመን የኢትዮ ይዞታና የ” እውነት ፣ ውሸቱ” እሰጣ ገባ
===================================

* በየመን የኢትዮጵያ ኢንባሲ ጥቃት እንደደረሰበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶር ቴዎድሮስ አድሃኖምና መስሪያ ቤታቸው ከቀናት በፊት ፣ ቀጥሎም የኢትዮጵያ ቴሌቪዠን ቢያስታውቁም የተላለፈው መረጃ አነጋጋሪ ሆኗል። በተባራሪ ጥይት በኢንባሲው የሚገኝን አንድ መኪና ጎማ መታ ተብሎ ጥቀሰት ብሎ ማቅረቡ የተጋነነ መሆኑን ከየመን ሰንአ የደረሱኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ

* በየመን ሰንአ የኢትዮጵያ ኢንባሲ ዲፕሎማቶች ሳይሆኑ የኮሚኒቲ ሰራተኞች ለመመለስ ፍላጎት ያላቸውን ተመላሽ ዜጋዎች በመመዝገብ ላይ መሆናቸው ተጠቅሷል ። የኢንባሲውን መደብደብ ዜና የሰሙት በቦታው ያሉትን የኮሚኒቲ ተወካዮች ሳይቀር በሚኒስትሩ ኢንባሲው ተጠቃ በሚል በቀረበው መረጃ ግራ የተጋቡ እንደነበር የአይን እማኞች ጠቁመዋል

* የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶር ቴዎድሮስ አድሃኖም ” በየመን ሰነአ የኢትዮጵያ ኢንባሲ ጥቃት ደረሰበት!” ያሉትን ሰሞኛ ዝርዝር መረጃ ያልቀረበበት አነጋጋሪ መረጃቸውን ተከትሎ ” ከአውስትራልያ የመጣች ታዳጊ 20 ሚሊዮን… ለገሰች !” እንደተባለችው ታዳጊ ወጣት ስጦታ ገንዘብ ምንጭ ዙሪያ የተደረገውን ያህል ሙግት እሰጣ ገባ የየመኑ ጥቀሰት ባይገንም ” እውነት ፣ ውሸቱ ” ግን ቀጥሏል
( አሜሪካ ቢሆን ይህ ይደምቅ ነበር ያሉኝ አሉ: ) )

* ከቀናት በፊት በኤደን የመን አድርገው ጅቡቲ የገቡት 30 ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገር ቤት መግባታቸው ተጠቁሟል ፣ ” ወደ ሃገር ቤት መግባቱ ለደህንነታችን ያሰጋናል !” ያሉት ግን ወደ ሶስተኛ ሃገር የሚሻገሩበትን መንገድ በመላ አለም የምንገኝ ኢትዮጵያውያን ድምጻቸውን እናሰማላቸው ዘንድ በመማጸን ላይ ናቸው !

እስኪ ቸር ያሰማን !

ነቢዩ ሲራክ
መጋቢት 26 ቀን 2007 ዓም

( Cartoon / From Arabbews newspaper)

—- Nebiyu Sirak wrote —-

የመረጃ ግብአት …
ዘመቻ “ወሳኙ ማዕበል ” በ8ኛው ቀን ክንውኖች …
እና በየመን ሁከትና የኢትዮጵያውያን ይዞታ !
===========================

> ” ኤደን በሁቲዎች እጅ አልወደቀችም! ” የሳውዲ መራሹ ዘመቻ ቃል አቀባይ
> ” በየመን ሰንአ የኢትዮጵያ ኢንባሲ ተደብድቧል፣ 2000 ተመዝግበው 30 ጅቡቲ ገብተዋል ” ዶር ቴዎድሮስ አድሃኖም
> በስደተኞች መጠለያ የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር የመግባት ፍላጎት አላሳዩም፣ የድረሱልኝ ጥሪ እያሰሙ ነው፣ በፖለቲካ የሸሹት የምህረት ጥሪ ይደረግላቸውም እየተባለ ነው

8ኛው ቀን የዘመቻ ክንውን መግለጫ …
========================
ኤደን በሁቲ አማጽያን ስር መሆኗን አልጀዚራና የተለያዩ የአረብ መገናኛ ብዙሀን የጠቆሙ ቢሆንም ትናንት ማምሻውን በሪያድ የአየር ኃይል የጦር ሰፈር ሆነው ለጋዜጠኞች ስለ 8ኛው ቀን የዘመቻ ክንውን መግለጫ የሰጡት የዘመቻው ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጀኔራል አህመድ አሲሪ ኤደንን ለመያዝ ውጊያው እንደቀጠለ መሆኑን ያስረዱ ሲሆን ኤደን ሙሉ በመሉ በሁቲዎች ቁጥጥር ስር አለመውደቋን አስታውቀዋል።።

በ8ኛው ቀን የአየር ጥቃት ዘመቻ መግለጫ የሰጡት ብርጋዴር ጀኔራል አህመድ አሲሪ በኤደን አካባቢ እግረኛ ጦር ጀምሯል ወይ ? ተብለው ተጠይቀው ፣ እግረኛ ጦር አለጀመሩን አስረግጠው ተናግረዋል ። በዚሁ መግለጫቸውም በኤደን ዙሪያ ስለተደረገውና እየተደረገ ስላለው የዘመቻው ክንውን ሲያስረዱ በዋናነት በምድርና በባህር የሁቲ አማጽያን ስንቅና ትጥቅ አቅርቦት እንዳያገኙ መንገዶችን የመዘጋጋት ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል። ከዚህ ባከፈ የእግረኛ ጦር ዘመቻ አለመጀመሩን ቃል አቀባዩ አስረድተዋል ።

“ከወሳኙ ማዕበል” የአየር ጥቃቱን አፋፍሞ በቀጠለበት ሁኔታ በየመን የድንበር ከተማ በደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ በምትገኘው አሲር ክልል በሚያዋስን ድንበር ግጭት መቀስቀሱ ተጠቁሟል። ባልታወቁ ታጣቂዎች በተከፈተ ተኩስም ሰልማን አልመልኪ የተባሉ አንድ የበታች ሹም የድንበር ጠባቂ ወታደር መገደላቸውንና 10 ያህል መቁሰላቸውን የሀገር ውስጥ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ሜጀር ጀኔራል መንሱር አልቱርኪ አስታውቀዋል ። የአየር ጥቃት ከተጀመረ ወዲህ በድንበር ይህን አይነት ክስተት ሲታይ የመጀመሪያው ሲሆን በተባለው ግጭት የሞቱት የድንበር ጠባቂ የቀብር ስነስርአትም ትናንት ሀሙስ በአብሃ ከተማ ተከናውኗል !

*የኢትዮጵያ ኢንባሲ መደብደብና
አሳሳቢው የኢትዮጵያውያን ይዞታ…
======================

በየመን ሰንአ የኢትዮጵየ ኢንባሲ ባሳለፍናቸው ቀናት በጦርነቱ የድብደባ ጥቃት የተፈጸመበት መሆኑን የኢፊድሬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶር ቴዎድሮስ አድሃኖም ባሰራጩት መረጃ አስታውቀዋል። በተፈጸመው ድብደባ የተጎዳ ሰው የለም ከማለት ውጭ በጦር መሳሪያ ተደበደበ ስላሉት ኢንባሲ የጉዳት መጠን የሰጡት ዝርዝር ማብራሪያ ግን የለም ።

በየመንን ሁከት ተከትሎ በኢትዮጵያ ኢንባሲ በኩል ወደ ሀገር ለመመለስ የተመዘገቡት 2000 ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሩ ከተመዘገቡት መካከል 30 ያህል በጦርነት ከምትናጠው ከኤደን ተነስተው ጅቡቲ መግባታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መረጃ ያስረዳል። በየመን እያደር የጦርነቱ መባባስ ስደተኞችን የመመለስ ስራውን እንዳወሳሰበው የጠቆሙት ዶር ቴዎድሮስ በሚቀጥሉት ቀናት የተመዘገቡትን ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር የመመለሱ ስራ በተቻለው መጠን እንደሚደረግ አስረድተዋል። በመጨረሻም ባስተላለፉት መረጃ የብዙ ሀገር ዲፕለማቶች የመን ሰንአን ለቀው ሲወጡ ” ከዜጎቻችን በፊት አንወጣም !” ብለው እስካሁን የመን አሉ ላሏቸው የኢትዮጵያ ኢንባሲ ዲፕሎማቶች ምስጋና አቅርበዋል ።

በሌላ በኩል በስደተኞች መጠለያ የሚገኙት ከ5000 ስደተኞች ጨምሮ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ በየመን በኩል ወደ ሳወዲ ለመግባት አስበው በተለያዩ የየመን ክልሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ አዳዳቢ እንደሆነ ቀጥሏል። ወደ ሶስተኛ ሀገር እንጅ በኑሮው ውድነትና በፖለቲካው አለመረጋጋት ተማረው በ UNHCR የስደተኛ ማረጋገጫ የተሰጣቸው ግን ወደ መጡባት ሀገራቸው ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ፍላጎት እንደሌላቸው እየተናገሩ ነው። እኒሁ በጭንቅ ላይ ሆነው ወደ ሀገር የመግባቱ ነገር እንደ ተሻለ አማራጭ የማያዩት ወገኖች አማራጩ ጥሏቸው ከየመን የወጣው በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን UNHCR ወደ ሶስተኛ ሀገር ያሸጋግራቸው ዘንድ የተለያዩ አለም አቀፍ ድርጅቶችን እንዲማጸኑላቸው በተለያዩ አለማት ላሉ ኢትዮጵያውያን የድረሱልኝ ጥሪ እያሰሙ ነው!

በየመን ሁከቱ እያየለ ከሄደና የሳውዲ መራሹ የ10 አረብ ሀገራት የምድር ጦር እግረኛ ማዝመት ከጀመረ ያለውን አማራጭ መጠቀም ባልፈለጉ ኢትዮጵያውያን ላይ የከፋ አደጋ እንዳያጋጥማቸው ስጋት ተደቅኖባቸዋል ። በተለያየ ምክንያት ፖለቲካውን ሸሽት ሀገር ለቀው አሁን አደጋ ላይ ሲወድቁ ወደ ሃገራቸው እንዳይመለሱ የእስራት ፍርዱን የፈሩ ዜጎች ቁጥር ከፍ ያለ መሆኑ ይነገራል። ይህን መሰሉን ችግር ማቅለል ይቻል ዘንድ የኢትዮጵያ መንግስት ከችግሩ ቀጠና ወደ ሃገር ለሚመለሱ ማናቸውም ስደተኞች የምህረት ጥሪ ያቀርብ ዘንድ በዚሁ ዙሪያ ያነጋገርኳቸው ወገኖች ያስረዳሉ !

ቸር ያሰማን !

ነቢዩ ሲራክ
መጋቢት 25 ቀን 2007 ዓም


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1809

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>