ይሄንን ፎቶ ሳይ ያስታወሰኝ ለመጀመሪያ ጊዜ የማዕከላዊን ሲኦል ጊቢ የረገጥኩበትን ቀን ነው። በዛን ቀን በጠዋቱ አራዳ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ብዙዎች ተገኝተናል። ዕለቱም ዞን9ኞችና ጋዜጠኞቹ የማዕከላዊ ሲኦል ቤትን የምርመራ ጊዜያቸውን ጨርሰው ክስ የሚመሰረትባቸው ቀን ነው። ምን ብለው ይከሷቸዋል ወይስ የሚከሱበት ምክንያት ስለሌላቸው ይለቁዋቸው ይሁን? የሚለው ጥያቄ በአእምሮዬ እየተመላለሰ ነበር።
በዛንው ቀን እንዲሁ አንድነት ፓርቲ በእነሀብታሙ አያሌውና ዳንኤል ሺበሺ የማዕከላዊውን የፀረ- ሽብር ግብረ ኋይል የምርመራ ክፍል ኋላፊ የሆነውን ኮማንደር ተክላይን በ24 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት አላቀረባቸውም ሲል ከሶት በዕለቱም ፍርድ ቤቱ ይዞዋቸው እንዲቀርብ አዞት ስለነበር እነሱም ያሉበትን ሁኔታ ለማየት አብዛኞቻችን( ሁላችንም ያላልኩት ከእኛ ያልተናነሰ በመጭረሻ እንዳየነው የደህንነት ሰዎች በመሀከላችን ተሰግስገው ስለነበር ነው በወቅቱ) ከፍተኛ ጉጉት አድሮብናል።
ኮማንደር ተክላይም እጁን ኪሱ ከቶ ከስንት ሰዓት ጥበቃ በኋላ ብቻውን ተከሰተ አቅርባቸው ያለው ፍርድ ቤትም አለማቅረቡ ትክክል እንደሆነ የሚያስከስሰው ጉዳይም እንደሌለ ፈርዶ ጀግኖቻችንን የማየት ጉጉታችንን ቆረጠው።
በዚህ ተበሳጭተን ከፍርድ ቤቱ ወጥተን የተለያየ ግሩፕ ሰርተን ስለነበረው ነገር እንዲሁም ዞን9ኞችን ከሰዓትም ቢሆን ያቀርቡዋቸዋል ብለን እዛው ለመጠበቅ በምንነጋገርበት ወቅት ከፍርድ ቤቱ የወጣች አንዲት ፒካፕ መጥታ ከፊት ለፊታችን ገጭ እንዳለች ከየት እንደመጡ ያላወቅናቸው ደህንነቶች ከበውን ከመሃል 6 ልጆችን ለቅመውን የተደበቀውን ቦንብ ታወጣለህ እያሉ ፒካፗ ላይ እያዋከቡ ይጭኑን ጀመር።
እየወሰዱንም እንዳለ ክሳችንን እዛው ፈጠሩልን ክሳችንም የነበረው ከተደበቀው ቦንብ ተቀይሮ ወደ ኮማንደር ተክላይን ልትጠልፉት ለማገት እንደተዘጋጃችሁ መረጃው እንዳላቸው እየነገሩንና እያስፈራሩን ማዕከላዊ ሲኦል ግቢ ደረስን ወደ ምርመራ ክፍል እንዳስገቡን ከፊት ለፊታችን ያላሰብነው ነገር ተፈጠረ። እነኛ ስንጠብቃቸው የነበሩ ወጣቶቹ ልጆች ከፊታችን ተሰልፈው በአንዲት ባስ ሊጫኑ መጡ እነሱም እንደተመለከቱን ምን ተፈጠረ፥ ምን ሆናችሁ በሚል በእጅ ለመግባባት መልዕክት መቀያየር ያዝን የነበርንባት ክፍልም ጠባብ ስለነበረች እየተገፋፋም ከነሱ ጋር ሰላም ለመባባል ስንሞክር በሁኔታው የተበሳጩት ደህንነቶች ጋር አርፋችሁ ተቀመጡ በሚል ግብግብና እሰጣ ገባ ውስጥ ገባን ማነው ጀግኖቹን አስከ ግርማ ሞገሳቸው አይቶ የሚቀመጠው ባይሆን ይፎክራል እንጂ። በጣም ደስ ብሎን ስለነበር እነሱን በማግኘታችን እርስ በእርስ የነበረን የአይዞን ባይነት ቃላት ሳንለዋወጥ በምልክት ልውውጦች መግባባታችን ሀሴትን የሚፈጥር የጋራ የትግል አጋርነትን የሚያበስር በ20 እርምጃዎች መሀል የተፈጠረ አሁን በህሊናዬ ሳስበው የሚታየኝ ስዕል የሚያምር በምርጥ ዳይሬክተር የተሰራ የማይም ትወና የሚመስል መስተጋብር ነበረው። ደህንነቶቹ በኢትዮጵያ ምድር እንደሚፈሩ ሁሉ ረስተነው ነበር።
ይሄን ደስተኝ ፍቅርን የሚረጭ ሩህሩህነትን የሚለግስ ፈገግታን ብርታትን የሚያወርስ የፊትና የእጅ እንቅስቃሴ ጣቶቻቸውን እየሳሙ ያሳዩን የነበረው የእንወዳችኋለን መልዕክቶቻቸው የማይነጥፈውን ለብዙዎቻችን የሚተርፈውን ከፊታቸው ላይ የሚነበበውን ለሰው ልጅ ያላቸውን ጥልቅ ክብርና ፍቅራቸውን የተመለከትኩበት ሁሌም ከህሊናዬ እንዳይጠፋ ሆኖ የታተመውን የወዳጅነት የፍቅር ልግስናቸውን። ያኔ ነበር ከማሂና ከኤዶም ፥ ከበፍቄና ናቲ፥ ከአቤላና ዞላ፥ ከአጥኔክስና ተስፍሽ እንዲሁም ከአስሚቲ ከትውልዴ ባለራዕዮች የተመለከትኩት።