Quantcast
Channel: Abugida Ethiopian American Amharic Web Page
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1809

የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቢሻሻልስ? በአያሌው አስረስ

$
0
0

የግብፅ መንግሥታት፣ ደካማ ኢትዮጵያን ለማየት ካላቸው ፍላጎት የተነሳ የኤርትራ ነፃነት ግንባሮችን መልምለው፣ አሠልጥነውና አስታጥቀው በኢትዮጵያ ላይ አዘመቱ፡፡ የኤርትራ ግንባሮች በበኩላቸው ጦርነቱ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንዲዳረስ ለማድረግ የተጠቀሙበት መንገድ የብሔረሰብ ንቅናቄዎችን መፍጠር እንዲሁም ሌሎች የእነሱን አርዓያ ተከትለው እንዲቋቋሙ ማገዝ ነው፡፡ የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተመሠረተውን የፌዴሬሽን ግንኙነት ማፍረሱ በቀጣናው ጦርነት እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሆኗል፡፡ ዘውዳዊውም ሆነ ወታደራዊው መንግሥት በየአካባቢው ለተነሱ የአስተዳደርና የፖለቲካ ጥያቄዎች ተገቢ መልስ አለመስጠታቸው በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎችም ጦርነት እንዲቀሰቀስ አድርጓል፡፡ ትልቋ ሶማልያ በመመሥረት አባዜ መንፈሱ የናወዘው የዚያድ ባሬ መንግሥት አስታጥቆ የላካቸው የውስጥና የውጭ ኃይሎችም በዘመኑ የአገሪቱ ተጨማሪ ራስ ምታቶች ነበሩ፡፡

በመንግሥትና በአማፂያን መካከል ለሠላሳ ዓመታት የተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ግንቦት 1983 ዓ.ም. ሲያበቃ፣ ቀደም ብሎ በየአካባቢው በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩት የየብሔረሰብ ኃይሎች በተለያየ ደረጃ ከነትጥቃቸው ነበሩ፡፡ ከሁሉም ጠንካራ የነበረው ሕወሓት/ኢሕአዴግም ሆነ ሌሎች የነፃነት ንቅናቄዎች ለበርካታ ዓመታት ትግል ያካሂዱ የነበረው ማዕከላዊውን መንግሥት ለመቆጣጠር ሳይሆን ለመገንጠል ነበር፡፡ ደርግ ሲወድቅ ግን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግራ ተጋቡ፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ አንድ ሆኖ መቀጠል ወይም አለመቀጠል ዋናና ወቅታዊ ጥያቄ ሆኖ ቆመ፡፡
የየራሳቸውን መንግሥት ለመመሥረት ሲታገሉ የነበሩት እነዚህ የብሔር ድርጅቶች፣ በታሪክ አጋጣሚ ለኢትዮጵያ ችግሮች መፍትሔ አፈላላጊ ሆነው ተገኙ፡፡ የድርጅቶቹ መሪዎችና አባላት ኢትዮጵያን እንደ አገራቸው ማየት የተሳናቸው፣ የኢትዮጵያን አንድነት መጠበቅ ለአንድ ብሔረሰብ ብቻ ጥቅም የሚያስገኝ ሆኖ የሚሰማቸው የነበሩ ከመሆናቸውም በላይ ለዘመናት በራሳቸውና በተከታዮቻቸው ልብ ውስጥ የዘሩት የማዕከላዊ መንግሥት ጥላቻ የሚይዙት የሚጨብጡት እንዲጠፋባቸው አደረጋቸው፡፡

ማንም ትንሽ አገር መምራት አይፈልግም፡፡ ሕወሓት/ኢሕአዴግም በእጁ የገባችውን ኢትዮጵያ እንደ ፍጥርጥርሽ ብሎ አልተዋትም፡፡ ማዕከላዊውን መንግሥት እንደያዘ ለመቆየት የታየው አማራጭ ኢትዮጵያን በፌዴራል ሥርዓት ማዋቀር ሆነ፡፡ ፌዴራላዊ ሥርዓተ መንግሥት ለኢትዮጵያ ችግር ትክክለኛና ወቅታዊ መፍትሔ መሆኑን ብዙዎች ቢቀበሉትም፣ ኢሕአዴግ የመረጠው ግን በብሔር አሰፋፈር ላይ የተመሠረተውን ፌዴራላዊ ሥርዓት ሆነ፡፡

በዚህ መንገድ የተመሠረተው ፌዴራላዊ መንግሥት፣ “ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከ መገንጠል ያለው መብቱ በማንኛውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው” የሚል ሕገ መንግሥታዊ አንቀጽን (39/1) ደጀን አድርጎ የቆመ በመሆኑ፣ የፌዴራል ሥርዓቱ ቀጣይነት ጥያቄ ውስጥ ወድቋል፡፡

በክልልም ሆነ በፌዴራል መንግሥቱ ሥልጣን ላይ የተቀመጡ ሰዎች፣ ለሥልጣን የሚበቁት በትምህርት፣ በአስተዳደራዊ ብቃት ወይም በሙያ የላቁ ሆነው በመገኘታቸው ሳይሆን፣ በብሔር ተዋጽኦ በመሆኑ ይህ ዕድል ከእጃቸው እንዲያመልጥ አይፈቅዱም፡፡ ስለዚህም በሚያገኙት አጋጣሚ ሁሉ አገር አቀፍ ጉዳዮችን ዝቅ እያደረጉ ክልላዊ ጉዳዮችን በማጉላት ለክልላቸው ያላቸውን ታማኝነትና ተቆርቋሪነት ማሳየት እንደ ግዴታ ቆጥረው ይዘውታል፡፡ በብሔር ብሔረሰቦች ቀንና በብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ወይም በመሳሰሉት ክንውኖች ወቅት፣ በሕዝቦቿ መተባበር እየተገነባች ስላለች አገር ቢናገሩም ሲያደርጉት የሚታየው ግን ተቃራኒውን ነው፡፡ ሕወሓት ስለትግራይ፣ ኦሕዴድ ስለኦሮሚያ፣ ደኢሕዴን ስለደቡብ ኢትዮጵያ፣ ሌሎች ፓርቲዎችም ስለየክልላቸው ሲብሰለሰሉና ሲንሰፈሰፉ ውለው ያድራሉ፡፡

ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ሲነሳ፣ የፌዴራልና የክልል መሪዎች ቀድሞ በሐሳባቸው የሚመጣው የአፄ ምኒልክ የግዛት ማስፋፋት ጦርነት እንዲሁም በዘመቻው የሞቱ ሰዎችና የወደመ ንብረት እየሆነ ነው፡፡ በቅርቡ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ምሥረታን በማሰብ በደኢሕዴን አዘጋጅነት ቀርቦ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ባሰራጨው ፕሮግራም፣ በደቡብ ኢትዮጵያ የአፄ ምኒልክን ሠራዊት ለማዳከም ከተቻለም ለማንበርከክ ሠራዊቱ በፈንጣጣ በሽታ እንዲጠቃና በንብ እንዲነደፍ መደረጉ ተገልጿል፡፡ ይህ እውነት ከሆነ ኢሕአዴግ አፄ ምኒልክን የሚራገመው፣ እሳቸው ምናልባትም በዓለም ታሪክ የመጀመሪያውን የባዮሎጂካል ጦርነት አሸንፈው የመሠረቷትን ኢትዮጵያ እየመራ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ በጣም ያሳዝናል፡፡
ዛሬ በዓለም ላይ የሚገኙት አገሮች የተመሠረቱት ጉልበተኛው ደካማውን እያስገበረው ነው፡፡ በኢትዮጵያም ከአፄ ቴዎድሮስ ጀምሮ እስከ አፄ ምኒልክ ዘመን የተካሄደው የተበታተነች አገርን የመሰብሰብ ዘመቻ ከዚህ የተለየ አልነበረም፡፡ ኢሕአዴግም ወደ ሥልጣን የመጣው በጉልበት እንጂ በድርድር አይደለም፡፡ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፣ የአፄ ምኒልክ ዘመቻ ወንጀል የሚሆንበትን ምክንያት መሪዎቻችን ከአካባቢያዊነት ተላቅቀው ከታሪክ ማስረጃ ጠቅሰው ሊያሳዩን በተገባ ነበር፡፡

ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ ምክንያት የሆነኝ ሒሩት ደበበ የተባሉ ጸሐፊ ጥቅምት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. በወጣው ሪፖርተር ላይ “የሰንደቅ ዓላማ ቀን ክብረ በዓል በብሔራዊ ቀን ቢታጀብስ” በሚል ርዕስ ያቀረቡት ጽሑፍ ነው፡፡ ጸሐፊዋ ጥቅምት 3 ቀን 2007 ዓ.ም. የተከበረው ሰባተኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ቀትረ ቀላል” እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡ ይህም የሆነው ከብሔራዊው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በላይ የክልል ሰንደቅ ዓላማዎች ነግሰው በመታየታቸው እንደሆነ በአማራ ክልል የታዘቡትን አከባበር ማስረጃ አድርገው አቅርበዋል፡፡

በእኔ እምነት በዓሉን ቀትረ ቀላል ያደረገው ከላይ ለማሳየት የሞከርኩት ከጊዜ ወደ ጊዜ ሥር እየሰደደ የመጣው ብሔርተኝነት ነው፡፡ መንግሥት ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀንን እንዲያውጅ የገፋፉትን ነገሮች መመልከታችን፣ በዓሉ ከድርጅት አጀንዳነት እንዳይወጣና የመንግሥት ወዳጆችም ሆነ ተቀናቃኞች ባንድነት እንዳያከብሩት ያደረገበትን ምክንያት ለመረዳት ያግዘናል፡፡ መንግሥት በዓሉን ያወጀው በሕዝቦች መካከል ብሔራዊ አንድነትን የማነጽ ግብ ይዞ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ይህ ዓላማ ፍፁም ትክክል ነው፡፡ ችግሩ ግን ጠዋት ስለተባበረችና አንድ ስለሆነች አገር ተናግረው ከሰዓት በኋላ ስለ መለያየት በሚሰብኩ ክፍሎች እጅ መውደቁ ነው፡፡

ሕወሓትና ኢሕዴን (አሁን ብአዴን) በጦር ሜዳ በቆዩባቸው በርካታ ዓመታት ዓርማም ሰንደቅ ዓላማም አድርገው ሲገለገሉበት የኖሩት የየራሳቸው ድርጅታዊ መለያ ነበራቸው (ይህ መለያ ዛሬ የየክልላቸው መንግሥታት ባንዲራ ሆኗል)፡፡ በየድርጅቶቻቸው ስብሰባ ላይና በፕሮግራሞቻቸው ወቅት የተቀረፁ የቪዲዮ ምስሎች የሚመሰክሩት ይህንኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለብሔራዊው ሰንደቅ ዓላማ ቦታ እንዳልነበራቸው ያመለክታል፡፡ በውጊያ ወቅት በእጃቸው ለሚገባው ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ የነበራቸው አያያዝም የስኳርና የጨው መቋጠሪያ እስከ ማድረግ ድረስ እጅግ ክብረ ነክ እንደነበረ በኢትዮጵያ አብዮታዊ ሠራዊት የተማረኩ አባሎቻቸው ገልጸዋል፡፡ ደርግ ይህን ለፕሮፓጋንዳ ጠቀሜታ ማዋሉም አይዘነጋም፡፡ በኋላም አዲስ አበባን በተቆጣጠሩ ማግስት ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሰንደቅ ዓላማ ጨርቅ ነው በማለት የተናገሩት እሳቸውም ሆነ የሚመሩት መንግሥት ለሰንደቅ ዓላማው አክብሮት እንደሌላቸው እንደ ማረጋገጫ ተቆጠረ፡፡ እነዚህ ሁለት ጉዳዮች ኢሕአዴግንና መንግሥቱን እንደ ቆላ ቁስል ውስጥ ውስጡን ሲበሉት ቆዩ፡፡

በ1997 ዓ.ም. በተካሄደው ሦስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ከቀደሙት ምርጫዎች በላቀ መጠን መንግሥት ተቀናቃኝ ኃይሎች ሰፊ የሬዲዮና የቴሌቪዥን አየር ሰዓት እንዲያገኙ ፈቀደ፡፡ ተቀናቃኝ ኃይሎች፣ ኢሕአዴግ በያዘው የፖለቲካ አቋም የተነሳ ኢትዮጵያን የባህር በር ማሳጣቱን፣ በብሔር ላይ የተመሠረተ የፌዴራል አስተዳደር ዘርግቶ ብሔርን ከብሔር እያቃቃረ መሆኑን፣ ለብሔራዊው ሰንደቅ ዓላማ አክብሮት እንደሌለው ወዘተ… በመዘርዘር በቴሌቪዥን መስኮት ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለቡ ኢሕአዴግንና የሚመራውን መንግሥት ቁም ስቅላቸውን አሳዩዋቸው፡፡ በዚያ ምርጫ ለደረሰበት ሽንፈት የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ያበረከተውን ድርሻ የተገነዘበው ኢሕአዴግ ስለ ሰንደቅ ዓላማ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለበት አመነ፡፡ ‘እኔም የሰንደቅ ዓላማ ፍቅር አለኝ’ ለማለት በየዓመቱ ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን እንዲከበር አወጀ፡፡ የአዋጁ ዓላማና እየተከበረበት ያለው መንፈስ ግን የሚገናኙ አልሆኑም፡፡ ወ/ሮ ሒሩትም የታዘቡት ይህንኑ ነው፡፡

አበው ርጥብ ሬሳ ደረቅ ያስነሳ ይላሉ፡፡ አቶ በሪሁን ተሻለ የተባሉ ጸሐፊ “የሰንደቅ ዓላማ ቀን የሕዝብ በዓል ነው ወይ?” እና “ዓርማ የሌለው ሰንደቅ ዓላማ ነውሩ ምንድን ነው?” በሚሉ ርዕሶች ሐምሌ 13 እና 26 ቀን 2006 በወጡት የሪፖርተር ዕትሞች ላይ ጽፈው እንዳስነበቡን ይታወሳል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ላይ ለምን ተዘመተ?” በሚል ርዕስ ለእሳቸው በሰጠው መልስም ጉዳዩ አነጋጋሪነቱን እንደያዘ መቆየቱን የሪፖርተር አንባቢዎች እንደሚያስታውሱ አምናለሁ፡፡ ጊዜው ቢዘገይም አጀንዳው የሚያረጅና የሚሞት ባለመሆኑ ዛሬ መልሼ ልቀሰቅሰው ተገድጃለሁ፡፡

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 3.1 “የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሀል ቢጫ ከታች ቀይ ሆኖ በመሀሉ ብሔራዊ ዓርማ ይኖረዋል፡፡ ሦስቱም ቀለማት እኩል ሆነው አግድም ይቀመጣሉ፤” ይላል፡፡ በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ ደግሞ “ከሰንደቅ ዓላማው ላይ የሚቀመጠው ብሔራዊ ዓርማ፣ የኢትዮጵያን ብሔሮች ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦችና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንፀባርቅ ይሆናል” ተብሎ ተደንግጓል፡፡ መንግሥታት በየዘመናቸው መገለጫችን የሚሉትን ዓርማ ስለሚያወጡ ኢሕአዴግ እንዲህ መደንገጉ የተለመደ አሠራር በመሆኑ የሚያስወቅሰው አይደለም፡፡

ወቀሳና ተቃውሞ የሚቀሰቀሰው አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዩ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ፣ በሰማያዊ መደብ ላይ ባለ አምስት ጨረርና ባለ አምስት ጫፍ ኮከቡን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ዓርማ እስካልያዘ ድረስ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ ተደርጎ ሊወሰድ እንደማይችል በአዋጅ ቁጥር 654/2001 በአንቀጽ 16 መደንገጉ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ከፀደቀና በሥራ ላይ ከዋለ ከ14 ዓመታት በኋላ የወጣው ይህ አዋጅ እስከዚያ ጊዜ ድረስ በሥራ ላይ የቆየውንና በሕዝብ እጅ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ክብረ ቢስና ተራ ጨርቅ ያደርገዋል፡፡ የአቶ ዘሪሁን ተሻለም ሆነ የእኔ ተቃውሞ የሚመነጨው ከዚህ ነው፡፡ ተቃውሟችን ፌዴራል መንግሥቱ ለምን ዓርማ ይኖረዋል ሳይሆን ዓርማ የሌለው ሰንደቅ ዓላማ መጠቀም ለምን ሕገ ወጥ ይሆናል ነው፡፡

መንግሥታት በተለዋወጡ ቁጥር የመንግሥታት ዓርማዎች ይለዋወጣሉ፡፡ በአፄ ቴዎድሮስ ማኅተም ላይ እየተራመደ ያለ አንበሳ እናገኛለን፡፡ አፄ ዮሐንስ አንበሳውን ወስደው ዘውድና መስቀል ጨመሩበት፡፡ በአፄ ምኒልክ፣ በንግሥት ዘውዲቱና በአፄ ኃይለ ሥላሴ የንግሥና ዘመን ደግሞ የአንበሳው ዓርማነት ቀጥሎ ሰንደቅ ዓላማ እንዲይዝ ተደርጓል፡፡ ደርግ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር መንግሥቱን ያወጀው ባለዘውዱን አንበሳ በዓርማነት በያዘው ነጋሪት ጋዜጣ ነው፡፡ በመሀሉ አንድ ዓይን ያለበት የኢትዮጵያ ካርታን ለጥቂት ጊዜ በዓርማነት የተገለገለው ደርግ ለሁለት ጊዜያት የመንግሥቱን ዓርማ ቀይሯል፡፡ የመጨረሻ ዓርማው ጋሻና የአክሱም ሐውልትን ያካተተ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ የሽግግሩን መንግሥት ሲያውጅ የተጠቀመው ምንም ዓርማ የሌለበት ነጋሪት ጋዜጣ ነበር፡፡ በሽግግሩ መንግሥት ጊዜ ድልድይ፣ ሚዛን፣ እርግብ፣ የማሽን ጥርስና የስንዴ ዛላ ያለበት ዓርማ ሲገለገል ቆይቷል፡፡ አሁን እየተጠቀመበት ያለው ከኮሙዩኒስቶች የተቀዳው ባለጨረሩ ኮከብ ሥራ ላይ የዋለው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መፅደቅ ቀን ተከትሎ ነው፡፡

ተወደደም ተጠላ ከነሐሴ 22 ቀን 2001 ዓ.ም. ወዲህ ያለውና ሕጋዊው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ባለአረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይና ሰማያዊ ቀለም ነው፡፡ “ባንዲራችን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ…” በማለት መዘመር ቀርቷል፡፡ ከሕዝብ እምነትና ፍላጐት ውጪ ሰንደቅ ዓላማችን ተለውጧል፡፡

የተወካዮች ምክር ቤት አዋጅ ቁጥር 654/2001 ከመጽደቁ በፊት በጠራው የሕዝብ አስተያየት መሰብሰቢያ መድረክ ላይ ከተሳተፉ ሰዎች አንዱ እንደነበርኩ አስታውሳለሁ፡፡ በዚያን ጊዜ ትክክል አይደለም ብዬ የተቃወምኩት የሰንደቅ ዓላማውንና የዓርማውን በግድ መዋሀድና ዓርማ የሌለበት ሰንደቅ ዓላማ፣ ሰንደቅ ዓላማ አይደለም መባሉን ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር የሆኑት ዶ/ር ተክለሃይማኖት ገብረሥላሴ፣ በጉዳዩ ላይ ሙያዊ አስተያየት ተጠይቀው ሰንደቅ ዓላማውና ዓርማው የግድ መዋሃድ እንደሌለባቸው መናገራቸውንና የሚቀበላቸው ማጣታቸውን ነግረውኛል፡፡ ምክር ቤቱ ይህ አዋጅ ያስከተለውንና የሚያስከትለውን ጉዳት አስቀድሞ ያየው አይመስልም፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ በደስታውም በመከራውም ጊዜ ሰንደቅ ዓላማን የሚጠቀም ሕዝብ ነው፡፡ በትግራይ አንድ ሰው ሲሞት አካባቢው ለሟች ያለውን አክብሮት የሚገልጸው ሰንደቅ ዓላማ ይዞ በመውጣት ነው፡፡ የሚጠየቀው ስንት ሠንጋ ታረደ ተብሎ ሳይሆን፣ ስንት ሰንደቅ ዓላማ ወጣለት ተብሎ ነው፡፡ በገጠርም ሆነ በከተማ አዳራሾች የሚደምቁት በባንዲራ ነው፡፡ ሃያና ሰላሳ ሜትር ርዝመት ያላቸው ሰንደቅ ዓላማዎች በየሕንፃው በሚሰቀሉበት በአሁኑ ጊዜ፣ ከፍተኛው የሰንደቅ ዓላማ መጠን 210 በ420 ሳንቲ ሜትር ነው ብሎ መደንገግ ትክክል ሆኖ አይታየኝም፡፡ ሰንደቅ ዓላማው በብዙዎች እጅ ሊገኝ የቻለበት ምክንያት ደግሞ ሕዝቡ ራሱ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ጨርቆችን በመስፋት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በግሉ መሥራት በመቻሉ ነው፡፡ አሁን በየትኛውም አካባቢ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ በአዋጅ 654/2001 መሠረት ይህን መብትና ዕድሉን ተገፎአል፡፡ ጉዳት አንድ በሉ፡፡

እናቶች አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ዶቃዎችን በልጆቻቸው ፀጉር ላይ በማስገባት ወይም የአንገት ጌጥ በማድረግ ለልጆቻቸው ስለሰንደቅ ዓላማና ስለአገር ፍቅር ለማስተማር የነበራቸውን ዕድል አዋጁ እንዲያጡት አድርጓል፤ ለምን ቢባል አሁን ሰማያዊ ቀለም የተጨመረ ሲሆን ባለ ሰማያዊ ቀለም ዶቃ ደግሞ ከተቀሩት ቀለማት ጋር አብሮ ቢደረደር ሰንደቅ ዓላማውን በትክክል አያስገኝም፡፡ ሰማያዊው ቀለም ባመጣው በዚህ ጦስ የተነሳ አባቶች የነጠላቸውንና የጋቢያቸውን፣ እናቶች ደግሞ የኩታቸውንና የቀሚሳቸውን ጥለት አረንጓዴ ቢጫና ቀይ በማድረግ በአገራቸው ሰንደቅ ዓላማ የመዋባቸው ዕድል እንደ ጉም ተኖ ጠፍቷል፡፡ ዛሬ በየከተማው በወጣቶች ልብሶችና የመዋቢያ ቁሳቁሶች ላይ የሚስተዋለው የሦስቱ ቀለማት ኅብር ዋጋ የለሽ ሆኗል፡፡ በየአደባባዩና በየቤተ እምነቱ የምናያቸው አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ጥብጣቦች ምንም ዋጋና ክብር የሌላቸው ተራ ጨርቆች ሆነዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስና የአትሌቲክስ ቡድኖች ማልያም ቢሆን ትርጉም አጥቷል፡፡ ጉዳት ሁለት፡፡
ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ልዩ ልዩ የጦር ክፍሎች የክፍለ ጦሩን ዓርማ በብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ላይ ያትሙ ዘንድ ይፈቀድ ነበር፡፡ አሁን ሰንደቅ ዓላማው በአዋጅ አንድ ወጥ በመደረጉ ጦሩ ይህ ዕድል እንዳያገኘው ተደርጓል፡፡ ሌላው ቀርቶ የመቶ፣ የሃምሳና የአሥር ብር ኖቶች በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለሞች እንዲዋቡ የተደረጉት ሰንደቅ ዓላማውን መሠረት አድርገው በመሆኑ ይህም ትርጉም አልባ ሆኗል፡፡ ጉዳት ሦስት፡፡

ለማጠቃለል መንግሥት፣ መንግሥታዊ ሰነዶችን ለማረጋገጥ የሚጠቀምበት ዓርማ የሚያስፈልገው እንደመሆኑ መጠን ይህን በሕገ መንግሥቱ መደንገጉ እምብዛም ለመቀበል አዳጋች አይሆንብኝም፡፡ ችግሩ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ላይ ዓርማው በግድ እንዲቀመጥ መደረጉ ነው፡፡ ሰንደቅ ዓላማ የገዢው ፓርቲ ወይም መንግሥት ሳይሆን የጠቅላላው ሕዝብ ሀብት ነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከሰንደቅ ዓላማው፣ ሰንደቅ ዓላማውን ከሕዝብ የለያየው አዋጅ 654/2001 መሻሻል በተለይም አንቀጽ 16 መሰረዝ አለበት፡፡ የተወካዮች ምክር ቤትም በሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ላይ ለምን ተቃውሞ በዛ ማለቱን ትቶ ይህን አዋጅ መለስ ብሎ እንዲያየው ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ ቸር ወሬ ያሰማን፡፡

ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው ayalewnegadras2005@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1809