ነገ መስከረም 22 ቀን በ”ሽብርተኛ” ክስ የተከሰሱት አራቱ ወጣት ፖለቲከኞች፣ ሃብታሙ አያለዉና ዳንኤል ሺበሺ ከአንድነት፣ የሺዋስ አሰፋ ከሰማያዊ እና አብርሃ ደስታ ከአረና ፣ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ። ወጣቶቹ ምንም አይነት ክስ እሰከአሁን ያልተመሰረተባቸው ሲሆን፣ ከሐምሌ አንድ ቀን ጀመሮ በማእከላዊ እሥር ቤት ነው የሚገኙት።
እስረኞቹ ለምን እንደታሰሩ አያውቁም። ክስ ሳይመሰረትባቸው ነው ለ86 ቀናት የታሰሩት። ፖሊስ መረጃ ገና አሰብስቤ አልጨረስኩም ስላለ ብቻ።
ያ ብቻ አይደለም፣ በሕገ መንግስቱ የተደነገገው በጠበቃዎቻቸው የመጎብኘት መብታቸው ሙሉ ለሙሉ ተረግጧል። ነገ ፍርድ ቤት በሚቀርቡበት ጊዜ ከጠበቃቸው ጋር ሳይነጋገሩና ሳይማከሩ ነው። ተመልከቱ እንግዲህ የኢሕአዴግን ሕግ ….!!!
ይሄ ሁሉ ፍርደ ገምድልነት፣ ኢሕአዴግ አሁን ያለበትን የዘቀጠ የአስተሳሰብ ደረጃ ከማመላከቱም በተጨማሪ፣ ሕግ በአገራችን ኢትዮጵያ ቦታ እንደሌለው የሚያሳይ ነው። ኢሕአዴግ ዉስጥ ጥሩ ልብ ያላቸው ወገኖች ሊኖሩ እንደሚችሉ ቢታወቅም፣ በአሁኑ ጊዜ ኢሕአዴግን እያሽከረከሩት ያሉት አክራሪ ኃይሎች መሆናቸውን አገር ህዝቡ እያወቀ ነው። አገዛዙ እየሄደበት ያለው ፍጹም አምባገነናዊና ደርጋዊ አካሄድ፣ እየፈጸማችው ያለውም ግፎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ፕለቲካውን እያካረረ፣ አገሪቷን ወደ ከፋ ደረጃ እየወሰዳት ነው።
አንዳንዶቻችን የታሰሩ ወጣት ፖለቲከኞች ነገ ሊፈቱ እንደሚችሉ ተስፋ ልናደርግ እንችላለን። ነገር ግን ገዢዎች መልካምና የቀናዉን ነገር የማድረግ ፍላጎት ያላቸው አይመስለኝም። ከዚህ በፊት ያሰሯቸውን ሰዎች፣ በብርቱካን ሚደቅሳን ሚደቅሳና በቅንጅት መሪዎች እንድደረጉት፣ አሰቃይተው፣ ቶርቸር አድርገው፣ አዋርደው፣ ይቅርታ አስጠይቀውና በቴለቭዥን አናዘው ይፈታሉ ፣ ወይም እንደ ፕሮፌሠር አስራት ሊሞቱ ሲሉ ይለቃሉ እንጂ፣ በምንም አይነት ሁኔታ እስረኖችን አይፈቱም። ባህሪያቸው አይደለም። ርህራሄ፣ ምህራት፣ ፍቅር፣ ወንድማማችነት አያውቁም። ጨካኞና ቂመኞች ናቸው።
ምናልባት እኛ የማናውቀው፣ በኢሕአዴግ ዉስጥ በተደረገ ውስጣዊ ትግል ፣ ሞደሬቶች አይለው አክራሪዎች እያደረጉት ያለዉን ማስቆም ከቻሉ፣ እስረኞች የሚፈቱበትት ሁኔታ አለ። ግን እድሉ በጣም የመነመነ መሰለኝ።
እስረኞቹ፣ ወይም ሌላ ቀጠሮ ተጠይቆባብቸው፣ የፈጠራ ክስ ተምስርቶባቸው፣ ዋስትና ተነፍገው እንደታሰሩ ይቀጥላሉ የሚል አስተያየት ነው ያለኝ ። የነገ ሰው ይበለንና የሚሆነውን ነገ እናያለን።