የአንድነት ፓርቲ ያለፈው አመት፣ የሚሊዮኖች ንቅናቄ በሚል መርህ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ሰላማዊ ሰልፎችን እንዳደረገ ይታወሳል። በየክልሉ ጠንካራ የአንድነት መዋቅሮች ተዘርግተዋል። በሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት እንዲሁም በሚሊዮኖች ድምጽ ለመሬት ባለቤትነት እንቅስቃሴዎች፣ ሁለት ጊዜ በደሴ፣ በባህር ዳር፣ በአዲስ አበባና በአዳማ/ናዝሬት፣ አንድ ጊዜ በጊዶሌ/ደራሼ ፣ በአርብ ምንጭ፣ በፍቼ፣ በጎንደር፣ በጂንካና በወላይታ ሶዶ ሰልፎች ተደርገዋል። በተጠሩት ሰልፎች ሕዝቡ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በተሞላበት ሁኔታ ድምጹን አሰምቷል። በባሌ ሮቢ፣ በቁጫ፣ በመቀሌና በአዋሳ ሊደረጉ የታሰቡ ሰልፎች በአገዛዙ አፈና ተጨናግፈዋል። በክረምት ወራት ሰለሚዘንብና ከመኢአድ ጋር የዉህደት እንቅስቃሴ ይደረግ ስለነበረ ዘገየ እንጂ፣ እንደገና በመቀሌና በጂንካ፣ እንዲሁም ለመጀመሪያ ጊዜ በድሬዳዋ፣ በአሶሳ፣ በነቀምቴ ፣ በደብረ ታቦርና በአርማጭሆ ሰልፎች ይደረጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ብዙዎቻችን 2007 ለለዉጥ እያልን መጪዉ አመት የለዉጥ ዘመን እንዲሆን ምኞታችንን ግልጸናል። ለዉጥ ዋጋ ያስከፍላል። ለውጥ እንዲሁ በባዶ አይመጣም። ከሁሉም በላይ ደግሞ መረዳት ያለብን፣ የፓርቲ መሪዎች የራሳቸው አስተዋጾ ቢኖራቸዉም፣ ለዉጥ በራሳቸው ሊያመጡ እንደማይችሉ ነው። እንደዉም መሪዎች ሁሉንም ነገር ለነርሱ ከተዉንላቸው፣ ትግሉን ክፉኛ የሚጎዳ ስህትቶች ሊሰሩም ይችላሉ። “ሆይ ሆይ” ስንላቸው አምባገነን ሆነው ልናገኛቸው እንችላለን። በመሪዎች ተክለ ሰውነት ላይ የተመስረተ ትግልም በርግጥ ያለ ጥርጥር ለውጥ አያመጣም። ድካምና ጊዜ ማጥፋት ነው። ለውጥ የሚመጣው ሕዝቡ የትግሉ ባለቤት ሲሆን ብቻ ነው። ለዉጥ የሚመጣው እንታገላለን የሚሉ ድርጅቶች መሪዎች ፣ ለሚወስኑት ዉሳኔ ተጠያቂ ሲሆኑ ነው።
በአንድ ድርጅት ውስጥ ችግሮች ፣ አለመስማማቶች፣ ግጭቶች ይፈጠራሉ። ግልጽነትና ተጠያቂነት በሚንጸባረቅበት ድርጅት የሚፈጠሩ ችግሮች አይድብሰበሱም። በቀላሉ አባልትና ደጋፊዎች እንዲያውቁት ይደረጋል። ለተወሰነ ጊዜ በአባላት መረብሽና ማዘንም ይከሰታል። ነገር ግን የድርጅቱ ባለቤት፣ አባላትና ደጋፊዎች በመሆናቸው ያዘኑትን ያህል መሪዎችን ተጠያቂ በማድረግ መሪዎች ከስህተቶቻቸው እርማት እንዲያደርጉ በማስገደድድ፣ ካስፈለገም መሪዎችን በመቀየር በድርጅታቸው ዉስጥ ያለውን ችግር ማስተካከል ይችላሉ።
ኮሚሲስታዊና ሚስጥራዊ በሆኑ፣ ወይንም በግለሰቦች ተክለ ስውነት ላይ በተመሰረቱ ድርጅቶች ዉስጥ ችግሮች ሲፈጠሩ ግን፣ ብዙ ጊዜ አባላትና ደጋፊዎች ሳያውቋቸው አመታት ያልፋሉ። ችግሮቹ ዉስጥ ውስጡን እያመረቀዙ፣ የፈነዱ እለት፣ የድርጅት መሪዎቻቸዉን እንደ አምላክ አምነው የተቀመጡ ደጋፊዎች፣ ትልቅ ድንጋጤ ይድርስባቸዋል። ምንም ማድረግ የማይችሉብት ሁኔታ መሆኑንም ሲረዱ ተስፋ ቆርጠው ጥለው ይሄዳሉ።
የአንድነት ባህል መሪዎችን ተጠያቂ የማድረግ ባህል ነው። የአንድነት ፓርቲ ዉስጥ ያሉ ጥንካሬዎችንም ሆነ ድክመቶችን አባላትና ደጋፊዎች ያውቃሉ። የተደበቀ ነገር ያለ አይመስለኝኝም። ላለፉት አምስት ሳምንታት በሊቀመንበሩ አመራር ዙሪያ ብዙ ዉይይቶች እየተደረጉ ነው። ይህ ዉይይት ጠቃሚና አስፈላጊ ቢሆንም፣ ፓርቲዉ ባለው አሰራሩ፣ ከአባላትና ደጋፊዎች የሚሰጡ አስተያየቶችን ከግምት በማስገባት፣ መሪዎቹን እስከመቀየር ድረስ በመሄድ ችግሮቹን መፍትት ይችላል የሚል አስተያየት አለኝ። ሊቀመንበሩም ሆነ የሥራ አስፈጻሚው አካል ለብሄራዊ ምክር ቤቱ ተጠያቂ ናቸው። የፕሬዘዳንቱን ዉሳኔን ምክር ቤቱ ሊያሻሽለውም ሆነ ሊሽረው ይችላል። በመሆኑምም በ2007 የአንድነት ፓርቲ ከ2006 በበለጠ ሁኔታ፣ ስህተቶቹን አርሞ፣ ሚሊዮኖችን የሚያንቀሳቅስ ጠንካራ ድርጅት ሆኖ ይወጣል የሚል ተስፋ አለኝ።
ይኽው ስራው በትንሹም ቢሆን በአዲሱ አመት ተጀምሯል። ከአንድነት አመራሮች፣ ስምምነትን አንድነትን፣ መቻቻልን ፣ ብስለትን፣ ለስልጣን አለመጓጓትን ተላብሰው፣ በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ ሕዝቡን ለመብቱን ለነጻነቱን እንዲነሳ ያንቀሳቅሱታል ብለን እየጠበቅን ባለንበት ሁኔታ፣ አባላት እራሳቸውን በራሳቸው እያነሳሱ ትግሉን ለማቀጣጠል ተነስተዋል።
በአዲስ አበባ የአንድነት ምክር ቤት፣ የወጣቶች ኮሚቴ፣ ለመስክረም 11 ቀን የተጠራ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ አዘጋጅተዋል። የታሰበው በአራት ኪሎ ወይንም ስድስት ኪሎ ቢሆንም፣ አስተዳደሩ በነዚህ ቦታዎች ፣ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ፣ ዝግጅቱ እንዲደረግ እውቅና ባለመስጠቱ፣ ሕዝባዊዉ እንቅስቃሴ በሌላ አማራጭ ሆኖ በቀረበ ቦታ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
እዚህ ላይ የምናየው አባላትንና ደጋፊዎች ተደራጅተው፣ አመራሩ በቀዘቀዘበት ጊዜ ትግሉን ሲያቀጣጥሉና አንድነት የመሪዎች ብቻ ሳይሆን የአባላቱና የደጋፊዎቹ እንደሆነም በግልፅና በገሃድ ሲያሳዩን ነው።
በማንኛዉም ሁኔታ፣ ሕዝቡ ብሶቱን የሚገልጽበትና ለመብቱ የሚጮህበት መድረክ የሚያዘጋጁና የሚያስተባብሩ አካላት ሊደገፉና ሊበረታቱ ይገባል። ከነዚህ አካላት መካከል ፣ የአዲስ አበባ አንድነት ወጣቶች ኮሚቴ አንዱ ነው። በነገራችን ላይ፣ እነዚህ ወጣቶች፣ ሕዝቡ በአደባባይ ወጥቶ፣ ሻማ በማብራት ድምጹን እንዲያሰማ ለማድረግ፣ ከአስተዳደሩ ጋር እያደረጉት ላለው ትንቅንቅ አድናቆቴን እገልጻለሁ።
ከእገር ቤትና ከአገር ዉጭ ያለን፣ የአንድነት አባላትና ደጋፊዎች፣ እንዲሁም ለዉጥ የምንፈልግ፣ ዲሞክራሲን የተጠማን በሚሊዮኖች የምንቆጠር ኢትዮጵያዊያን ሁሉ፣ ከነዚህ ቆራጥ ወጣቶች ጎን መቆም ይጠበቅብናል። ሥራ ካልተሰራና የአመራር ጉድለት ሲኖር በመቃወም መሻሻል እንዲኖር ግፊት ማድረግ እንደሚያስፈልገው ሁሉ፣ ሥራ ሲሰራ ደግሞ አብረን መተባበር፣ በቀጥታ የሥራው አካል በመሆን፣ አሊያም ድጋፍ በመስጠት ሶሊዳሪቲ ማሳየት ያስፈልጋል።
ለዉጥ በወሬ አይመጣም። ለዉጥ መግለጫ በማውጣት አይመጣም። ለዉጥ በጋዜጣዊ መግለጫዎች ጋጋታ፣ ወይንም በራዲዮና በቴሌቭዥን ቃለ መጠይቅ በማድረግ አይመጣም። ለዉጥ በምኞት አይመጣም። ለውጥ የሚመጣው በትግል፣ በስራ፣ በትብብር፣ በቁርጠኝነትና እያንዳንዱ ዜጋ የድርሻውዉን ለማበርከት በሚነሳበት ጊዜ ነው። ለውጥ የሚመጣዉ ትግሉን ከቢሮ ወደ ሜዳ የሚወስዱ ወገኖች ሲበዙና ሲበረታቱ ነው።