አቶ አንዳጋቸውን አሳልፎ የሰጠው የኤርትራ ደህንነት ጽ/ቤት እንደሆነ ኢትዮጵያ ሪቪዉ ዘገባ። ለሁለት ወራት አደረኩት ባለው ምርመራ ፣ በግንቦት ሰባቱ ዋና ጸሃፊና በኤርትራ መንግስት መካከል የነበሩ አንዳንድ ልዩነቶችን ኢትዮጵያ ሪቪው ዘርዝሯል። አቶ አንዳርጋቸው በሻእቢያ ተስፋ ቆርጠው እርዳታ ከግብጽ ለማግኘት ወደ ካይሮ አመርተው እንደነበረ የዘገበው ኢትዮጵያ ሪቪው፣ የአቶ አንዳርጋቸው የካይሮ ጉዞ ሻእቢያን እንዳበሳጨም ገልጿል።
የሻእቢያ ሰለባ ሲሆኑ አቶ አንዳርጋቸው የመጀመሪያቸው እንዳልሆኑ የዘገበው ኢትዮጵያ ሪቪው የትሕዴን ( የትግራት ህዝብ ዴሞክራቲክ ንቅናቄ ) መሪ አቶ ፍስሐ ሃይለማሪያን በስድስት አመታት በፊት እንደተገደሉ፣ የአርበኞች ግንባር መሪ ኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህም የት እንዳሉ እንደማይታወቅ አትቷል።
በጉዳዩ ላይ ግንቦት ሰባት የሰጠው መግለጫ እስከአሁን ባይኖርም፣ ከሳምንት በፊት ዋሺንግተን ዲሲ በተደረገዉ ሕዝባዊ ስብሰባ ፣ የድርጅቱ መሪዎች ከሻእቢያ ጋር ያለው ግንኙነት ቀጣይነት እንዳለው የሚይሳዩ መልሶችን ይመልሱ እንደነበረ በስፋራው የነበሩ ይናገራሉ።
ከአምስት አመታት በፊት አቶ አንዳርጋቸው አስመራ እንደገቡ ኢትዮጵያ ሪቪው ለመጀመሪያ ጊዜ መዘገቡ ይታወቃል። በወቅቱም የድርጅቱ ሊቀመንበር በአዲስ ድምጽ ራዲዮ፣ የኢትዮጵያ ሪቪዉን ዘገባ ለማስተባበል የሞከሩ ቢሆንም፣ ጥቂት ወራት ካለፈ በኋላ፣ አቶ አንዳርጋቸው እራሳቸው፣ በቺካጎ በተደረገ ስብሰባ አስመራ ሄደው እንደነበረ በመገልጽ፣ ኢትዮጵያ ሪቪው ዘግቦት የነበረዉን ዘገባ፣ ትክክል መሆኑን ማረጋገጣቸው ይታወሳል።