Quantcast
Channel: Abugida Ethiopian American Amharic Web Page
Viewing all 1809 articles
Browse latest View live

የትግራይና የህወሀት የበላይነት ጥያቄ –ዕውነቱ ውሸቱና ማስፈራሪያው ከፈቃደ ሸዋቀና

$
0
0

ኮሎኔል መንግስቱ ሀይለማሪያም እንድ ጊዜ ኢህድሪ የሚባለውን መንግስታቸውን ካቋቋሙ በኋላ “ዕውን አሁን ደርግ አለ?” ብለው አገሩን በሳቅ ሊፈጁት ነበር። ይዘቱ ያው የሆነ ነገር በቅርጹ ስለተለየ በውጤቱ የተለየ ይሆናል ብለን እንድናመን ፈልገው ነበር መሰለኝ። አሁን ደግሞ የህወሀት መሪዎች ተራ በተራ ካላንዳች ተከራካሪ በሞኖፖል በያዙት ቴሌቪዝን ላይ እየወጡ “ዕውን አሁን የትግራይና የህወሀት የበላይነት ኢትዮጵያ ውስጥ አለ”? የሚል ተጨፈኑልኝ ላሞኛችሁ ዘፈን መሰል ነገር በኦርኬስትራ መልክ እየተቀባበሉ እየደለቁት ነው። (ከብዙ ጥቂቱን እዚህ ይመልከቱ)። ተከራክረው እንደማይረቱ ሰለሚያውቁ ራሳቸው ጎን ለጎን ተኮልኩለው እየተቀባበሉ ይነጋገራሉ እንጂ ሞጋች አያስቀርቡም። ጥያቄ አቅራቢውም መልስ ሰጭውም እነሱ ናቸው። ዲሞክራሲ ማለት ያንድ አቅጣጫ መንገድ ነው ወያኔዎች ቤት። እነሱ ከተናገሩት ዕውነት ነው። አለቀ። ክርክርና ትችት እንደጦር ሲፈሩ ይገርሙኛል። ተቺ ጠቃሚ አስተካካይ ሳይሆን አሸባሪ ነው። ተቃዋሚ ጠላት ነው ብለው ያምናሉ። ይህ ባህሪያቸው እነሱንም ሃገራችንንም አብሮ እያጠፋና ሊያጠፋ የተቃረበ መሆኑ ፈጽሞ የገባቸው አልመሰለኝም።

የመንግስት ባለስልጣን አይዋሽም አይባልም። ውሸቱ ግን ወይ ለከት ወይ የማስመሰል ቅንብር (nuance) እንዲኖረው ይጠበቃል። ውሸት ብዙ አይነት ነው። አንዳንድ ውሸት ያስቃል። ዕውነት ከመሰለ የሚጠቅም ውሸትም አይጠፋም። አንዳንዱ ውሸት ያሳዝን ይሆናል። ውሸት እየዋሹ ሰው የሚያዝናኑ ሰዎችም አውቃለሁ። እንዳንዱ ውሸት ግን የአድማጩን የመገንዘብ ችሎታ (intelligence) የሚሳደብ ይሆንና ያናድዳል። ሰሞኑን የሰማሁት የአቶ ስዩም መስፍንና የሌሎች ህወሀት ባለስልጣኖች አይነቱ ከኋለኛው አይነት የሚመደብ ነው። አቶ ስዩም መስፍን ከዚህ ቀደም በማግስቱ የተጋለጠ አገር ጉድ ያለው ውሸት ሲዋሹ ያየሁዋቸው ሰው ሰለሆኑ ውሸት ካፋቸው እንዴት ወጣ ብዬ የምሞግታቸው ስው አይደሉም። በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የግልግል (arbitration) ውሳኔ ማግስት ባድሜም ሁሉም ነገር ለኛ ተወሰነልን ደስ ይበላችሁ ያሉንንና በማግስቱ ጭልጥ ያለ ውሸት ሆኖ መገኘቱን ያልሰማ ኢትዮጵያዊ አይኖርም። እንደዚያ የቀናት አድሜ የሌለው ውሸት በሚሊዩኖች ፊት ለምን እንደዋሹ እስከዛሬ ይገርመኛል። ያሁኑን የትግራይና የህወሀት የበላይነት በኢትዮጵያ ምድር የለም የሚለውን ሌላ ቆሞ የሚሄድ ውሸት ምን እንደምንለው አላውቅም። ሳይኮሎጂስቶች አንዳንድ ሰዎችን እንዲህ ጸባየ ውሸታም (habitual liar) የሚያደርግ የሚገፋና የሚወተውት በሽታ (Compulsive Obsessive Disorder) የሚባል ህመም አለ የሚሉትን ነገር እንጠርጥር ይሆን?

ለነገሩ አሁን የምንሰማው “እውን የትግራይና የህወሀት የበላይነት አለ?” ዘመቻ የተቀነባበረ (orchestrated) ይመስላል። ባለስልጣናቱ ተራ በተራ እየደጋገሙት ነው። አቶ አባይ ጸሐዬ፣ አቶ ደብረ ጽዮን ፣ አቶ በረከት ስምኦንና ሌሎችም ይህንኑ አይኔን ግምባር ያርገው ከማለት ያልተናነሰ ነገር ሲናገሩ ሰምተናል።
ሁሉም ሹማምንት ባንድ ሀገር ውስጥ ያንድ ብሔረሰብ የበላይነት አለ ሲባል ምን ማለት ነው የሚለውን ጽንሰ ሀሳብ ለመተርጎም ምንም ሙከራ አላደረጉም። እራሴው ልጽደቅባቸውና ከተለያዩ ምንጮች ያገኘሁትን ትርጉም አሳጥሬ ለሁሉም በሚገባና በሚያስማማ መልክ ተርጉሜ ልጀምር። ያንድ ብሄረሰብ ወይም ቡድን የበላይነት ማለት በቡድኑ ወይም በብሔረሰቡ ስም የተሰበሰበው ስብስብ በግልጽና ግልጽ ባልሆነ መንገድ የሌላ ሕዝብ ስብስብን ወይም ስብሰቦችን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ህልውና በበላይነት የሚቆጣጠርበትና ሌሎቹን በመጫን ራሱንና የራሱን ስብስብ ወይም ወገን ለመጥቀምና በበላይነት ለማስቀመጥ የሚሰራበት ስርዓት ነው። (Political domination is an explicit or tacit measures taken which put a group or groups of people under the political, and sometimes, economic control of another group or groups በማለት Emefiena Ezeani የሚባል “In Biafra Africa Died” ና ሌሎችንም መጽሀፍ የጻፈ አፍሪካዊ ምሁር ከሰጠው አጭር ትርጉም ጋር ይቀራረባል)። የህወሀት መሪዎችን ዕምነትና ክህደት የምንመረምረው ከዚህ ቀላልና ብዙ ሰው ከማያጣላ ትርጉም ተነስተን ቢሆን ይሻላል ብዬ ነው ስለትርጉሙ የተጨነኩት።

አቶ ስዩም መስፍን ትግሬ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን 25 ዓመት ሙሉ ደጋግመው በመዋሸት የትግራይና የህወሀት የበላይነት እውነት ያለ እንዲመስል አድርገዋል ፣ “ፕርሴፕሺን” ፈጥረዋል ይላሉ። በሳቸው ቤት ያለው ዕውነታ ሳይሆን ፐርሴፕሺን (ዕውነት የሚመስል ቅዠት) ነው። “ትግራይ እስክትለማ ኢትዮጵያ ትድማ” ብለው ተርተዋል ፣ የትግራይ መሬት በልማት ሊሰምጥ ነው ብለው ተሳልቀዋል ፣ ትግራይ ፋብሪካ በፋብሪካ ሆነች ፣ መንገድ በመንገድ ሆነች ብለው ዋሽተዋል እያሉ ይከሳሉ። ይህን ሲሉ የኢትዮጵያውያንን የመገንዘብ ችሎታ የሰደቡም አልመስላቸውም። አቶ ስዩም ሲሆን የኢትዮጵያ ህዝብ የዘረጉለትን ሥርዓት አፓርታይድ ብሎ ስላልጠራው ባያመሰግኑት እንኳን የፈጠራ ወሬ የሚያወራ ውሸታም ብለው ሊሰድቡት አይገባም ነበር።

እስኪ ዝርዝር ውስጥ ሳንገባ አገር ስለሚያውቃቸው ነገሮች ከብዙ በጥቂቱ እንነጋገርና ይህን ውሽልሽል ውሸት እንየው። በደርግ ጊዜ የነበሩትን የመንግስት እርሻ ተቋማት ንብረት መሳሪያዎች ትራክተሮች መኪኖች ጄኔሬተሮች (ለምሳሌ ያህል ጣና በለስ የነበረውን) ከዚያ በተጨማሪ ያውራ ጎዳና መስሪያ ዶዘር ኤክስካቬተርና ያ ሁሉ ማሽኒነሪ በጠራራ ጸሀይ ከየቦታው እየተጋዘ ይሄድ የነበረው ወደቱርክ ነበር እንዴ አቶ ስዩም? ያንን ባይኑ በብረቱ የሚያይ ሰው ምን እንዲል ትጠብቁ ነበር? የትግራይ መሬት ሊሰምጥ ነው ማለት ብዙ ንብረት ወደዚያ መጋዙን ለመናገር የቀረበ ዘይቤያዊ እነጋገር እንጂ መቼም ተፈጥሮ መሬቱ ይሰምጣል ማለቱ ነው ብለው ሕዝቡን የሚከራከሩት አይመስለኝም። እስቲ ሌላው ሁሉ ይቅርና አቶ ስዩምን እንድ ቀላል ጥያቄ እንጠይቅ። ለመሆኑ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ሁሉ ጉልሕና ዋና የሆነውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት በርስትነት ለብዙ አመታት ይዘው ቁጭ እንዲሉና ዛሬም ከትግሬ እጅ ያልወጣው እንዲሁም አቶ መለስ እስኪሞት ድረስ 21 አመት ሙሉ በያዘው ስልጣን ላይ የተቀመጠው በብሔረሰብና ድርጅታዊ የበላይነታችሁ ነው ወይስ በብሔረሰብ ቁጥራችሁ ተመዝኖ ባገኛችሁት ድምጽ? ነው ወይስ የናንተን ያህል ችሎታ ያለው ሰው ካገር ስለጠፋ? መልሱ ቀላል ነው። ሕወሀትና እናንተ የትግራዩ ልሒቃን ጠያቂና ተቆጣጣሪ የሌለበት የበላይነት ስላላችሁ ነው። የሌሎቹ ብሄረሰብ ድርጅት አባሎችና ድርጅቶች የናንተ የበታች ፓርትነሮች ስለሆኑ አንዳንዶቹም የናንተ ፍጡራን በመሆናቸው ስለሚፈሯችሁ መሆኑን ድፍን አገር ያውቀዋል። እነሱም ይናገራሉ። ከስር ቤታችሁ አውጥታችሁ የፓርቲ መሪ ያደረጋችኋቸው እነ አባዱላና እነኩማ የበላይ ወይም እኩል እንሁን ብለው ይፎካከሩናል ብለው በሳቅ እንዳይገሉን ብቻ። ይህን ገብስ ገብሱን ቀለል ስለሚል እነሳሁ እንጂ በብሔረሰብ ስብጥር ከሐይለስላሴና ከደርግ መንግስት ቀርቶ ከሚኒሊክ መንግስት ጋር ስለማይወዳደረው የሀገሪቱ ሰራዊት አመራር አላነሳሁም። ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነውን ቁልፍ የመከላከያ ሰራዊት ጄኔራሎችና የሰራዊት አዛዦች የትግራይ ብሔረሰብ ተወላጆች የያዙበትን ሁኔታ ምን ብለን እንጥራው? በሌላ ሀገር እንዲህ አይነቱን ስርዓት አፓርታይድ ነው እኮ የሚሉት። ዶክተር ደብረ ጽዮን መካድ ስለከበደውና ብልጥ የሆነ መልስ የሰጠ መስሎት የመከላከያ ተቋሙ ምን ይሰራል ብላችሁ ጠይቁ እንጂ ብሔረሰቡን አትዩ። መታየት ያለበት የሰራዊቱ አመራር ብሔረሰብ ሳይሆን ሚሺኑ ነው። ስራው ደግሞ ያገር ሰላም መጠበቅ ነው የሚል ደረቅ ሳቅ የሚያስቅ ድሪቶ ነገር ነገረን። የሰራዊቱ ተቋማዊ ስራ የሰራዊቱ መሪዎች ትግሬዎች ብቻ ይሁኑ ብሎ ያስገደደ አስመስሎት አረፈ። የድፍረቱ ብዛት ደግሞ ያስተሳሰብ ቀረጻ ስላልሰራን ነው ህዝቡ እንዲህ የሚያስበው ይላል። የህዝቡን ጭንቅላት ማጠብ ነበረብን ማለቱ ነው። የአቶ በረከት ስምዖን ቅብዥር (bizzare) አስተያየት ደግሞ እንዲህ ይነበባል።
“በኢትዮጵያ ውስጥ ፌዴራል የሚባል ህዝብ የለም፤ ክልላዊ ህዝብ ነው ያለው።አማራ በራሱ ክልል ነው ያለው። ኦሮሞ በራሱ ክልል ነው ያለው። ትግራይም በራሱ ክልል ውስጥ ነው ያለው። ትግራይ ልማቱም ውድቀቱም በራሱ ልጆች እጅ ነው ያለው። አማራ ልማቱም ውድቀቱም በራሱ ልጆች እጅ ነው ያለው። ኦሮምያ ልማቱም ውድቀቱም በራሱ ልጆች እጅ ነው ያለው። እያንዳንዱ ክልል ከለማ የራሱ ልጆቹ እየመሩት ነው የሚለማው። እያንዳንዱ ክልል ካለማ ልጆቹ ፌል (fail) ስላደረጉ ነው የማይለማው። ስለዚህ ሌላ ክልልን ሰበብ ማድረግ አይቻልም። አዲስቱን ኢትዮጵያ ባህሪዋ ይህን ነው። ሌላ ክልልን ሰበብ ማድረግ አይቻልም። ሌላ ክልልን ሰበብ ማደረግ የሚመጣው መቼ ነው? እያንዳንዱን ክልል ራሱን የማልማት ተልእኮ ሳይፈፅም ይቀርና ህዝቡን ሊጠይቀው ይጀምራል። የክልል የወረዳ አመራር ‘ለምን አላለማህኝም’ ብሎ ሲጠይቀው ‘እኔ እኮ ሞክሬ ነበር ግን እከሌ አደናቀፈኝ’ የሚል አመራር ሲኖር………”
በአቶ በረከት ሎጂክ ኦሮሚያ ወይም አማራ ክልል ውስጥ የሚኖር ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ እኖራለሁ ማለት አይችልም። ክልላዊ ነዋ። ክልላዊ ሰው እንጂ ኢትዮጵያዊ ሰው የለም። ክልሎቹን ራሳቸውን ነፃ ሀገር አስመሰላቸው። በሱ ቤት የፌዴራል መንግስቱ ውሳኔዎች ክልሉን አይነኩትም። ሕይወቱ ውስጥ አይገቡም። ጉዳያቸውን በጋራ የሚወስን ፓርላማም የላቸውም። ያለው ክልላዊ ሕዝብ ነው። የፌዴራል ህዝብ የለም። ክልሉ ውስጥ የፌደራል መንግስት አይገባም። የጋምቤላን መሬት ነዋሪ እያፈናቀለ ለህንድና ላረብ የሚቸበችበው የፌዴራል መንግስት አይደለም። ባሁኑ ሰዓት በኦሮሚያና ባማራ ግዛቶች ውስጥ ተሰማርቶ ህዝቡን እየፈጀ ያለው ሰራዊት ሁሉ የፌዴራል መንግስቱ አይደለም። በጣም የሚገርም ነው። ሰው ያውም ትልቅ ባለስልጣን ጭልጥ ያለ ውሸት ሲዋሽና ሲቀዣብር ትንሽ እኳን ትዝብት አይፈራም?

ዛሬ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ኢኮኖሚ ሁለት ሶስተኛው ኤፈርት የሚባል ባሰራሩ ከህጋዊነት ይልቅ ወደማፊያ ኦፐሬሺንነት የሚቀርብ የውሸት ኢንዳውመንት የሚቆጣጠረው መሆኑ የታወቀ ነው። ይህ ኩባንያ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኢንቨስትሜንት ውስጥ እንዳይገቡ የሚከለክለው ህግ ተጥሶ በህወሀት ባለቤትነት እየሰራ ያለ ኩባንያ መሆኑ ሚስጥር አይደለም። ይህን ማድረግ ካለበላይነት ይቻላል? ይህ የበላይነት ማረጋገጫ ካልሆነስ የበታችነት ትርጉሙ ምንድን ነው? የኛን ኢንቨስትመንት ያህል በኢትዮጵያ የሚወዳደር የለም ብለው በአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ የነገሩን እኮ አቶ ስብሐት ናቸው። ዋሸተዋል? ኢንዳውመንት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ቢያውቁስ ባያውቁስ ምናባታቸው ያደርጉናል ብላችሁ ያቋቋማችሁት የፓርቲ ኩባንያ ያስተዳደር ቦርዱ ቤተመንግስት ውስጥ እየተሰበሰበ ይሰራ እንደነበር እኮ በኋላ ከመሀላችሁ የወጡት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባሎች መጽሀፋቸው ላይ ጽፈው ነገሩን።

ስልጣን የወጣችሁ ሰሞን ቅድሚያ በጦርነት ለተጎዱ አካባቢዎች የሚል ውሳኔ አሳልፋችሁ ሌላው የኢትዮጵያ ክፍል በዚያ ክፉ ጦርነት ያልተጎዳ ይመስል ለትግራይ ለይታችሁ ትደጉሙ አልነበረም እንዴ! የትግራይ ህዝብ እንደህዝብ ከዚህ ምን ያህሉ እንደተጠቀመ የሚያውቀው እግዜር ነው። ይህ ግን ባደባባይ ካለፍረት ያወጃችሁት አዋጅ ነው። እኔ እንኳን ባቅሜ ባጋጣሚ የማውቀው እኤአ በ1993 ዐመተ ምህረት ላይ ትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ ባጋጣሚ ባገኘሁት መረጃ አንድ ትግራይ ውስጥ ላለ የመምህራን ማሰልጠኛ ተማሪ የቦርዲንግ ወጭ 180 ብር ሲከፈል በሌላው የሀገራችን ክፍል በሙሉ ላሉት 30 ብር መሆኑን ማወቅ ችዬ ነበር። ይህን ምን አይነት እኩልነት እንበለው? ለመሆኑ አሁን ትግራይ ውስጥ የተሰሩትን አልሜዳ ጨርቃጨርቅ መስፍን ኢንጂነሪንግ መሶቦ ሲሚንቶ የኬሚካልና የማዕደን ፋብሪካዎችና ያገልግሎት ተቋሞች በብዙ ሰው መቅጠርም ይሁን በዘመናዊነት የሚወዳደራቸው ፋብሪካ የትኛው ሌላ ክልል ውስጥ ነው ያለው? ከህዝብ ባንክ ለኤፈርት ኢንቨስትመንት የተበደራችሁትን ብድር ከሰረ ብላችሁ ስትሰርዙና የኢትዮጵያ ሕዝብ ባዶ ከረጢት ይዞ እንዲቆም ማድረግ የቻላችሁት የናንተ የበላይነት ስላልነበር ነው? ይህን ለሌላ ለማን ፈቅዳችኋል? የኦሮሚያን ቡና የውጭ ንግድ የሚነግደው የናንተ ኩባንያ አይደለም እንዴ? እስኪ ሀገሪቱን የሚቀልበው ዋናው የሀብት ምንጭ ኦሮሚያና ትግራይ ውስጥ ባለፈው 25 ዓመት የተገነባው ዘመናዊ ፋብሪካ ልዩነት ይወዳደር። መስፍን እንጂኔሪንግስ የገጣጠማችኋቸውን ካሚዎኖች ለመሸጥ ገበያ የምትፈጥሩት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ ገብታችሁ ለገዥ ብድር በማመቻቸት (በማዘዝ ማለት ይቀላል) መሆኑን ያላየንና ያልሰማን መሰላችሁ? በመንግስት በኩል ኮንትራት ሰጭ በኤፈርት በኩል ኮንትራት ተቀባይ ሁናችሁ ኮንትራት በመዋዋል የምትሰበስቡት ገንዘብስ ካለማናለብኝ የበላይነት የሚቻል ነው? በህዝብ መዋጮ ለሚሰራው ያባይ ግድብ ሲሚንቶና ሌላ ዕቃ ካላጨረታ የሚያቀርቡት የናንተ ኩባንዮች አይደሉም? አንድ ነገር ያንድ ብሔር ልሒቃንና ድርጅት ዝርፊያ ነው የሚባለው ምን ሲሆን ነው አቶ ስዩም? ሜቴክ የሚባለው የናንተ ሰዎች በበላይነት የሚመሩት ጉደኛ ድርጅት ጋ ከገባሁ ስላማልወጣ ባላነሳው ይሻላል። ጋምቤላ ክልል ውስጥ በሚካሄደው የመሬት ዝርፊያ ውስጥ ሰባ በመቶ የሚሆኑት ተካፋዮች የትግራይ ተወላጆች ናቸው ማለት የምን ምልክት ነው? ለልሂቃኖቻችሁ ቅርበት (access) የበላይነታችሁን መከታ በማድረግ አመቻችታችኋል ማለት ነው። ሌላ ምን ትርጉም አለው። ርግጥ ነው ይህ ማለት መላው የትግራይ ህዝብ የዚህ ተግባራችሁ ተጠቃሚ ነው ማለት አይደለም። መምህራችሁ ቭላዲሚር ሌኒን ራሱ እንደሚለው እኮ አንድ ሌሎችን የሚጨቁን ብሔር የራሱንም ብሔር አባላት አይምርም። አሁን ተጠቂ እያስመሰላችሁ የትግራይን ህዝብ በመናጆነት ባታሰልፉት ይበልጥ ትጠቅሙታላችሁ። የትግራይ ህዝብም ረጋ ብሎ ሲያስብና ሲገባው ዝም ብሎ የሚከተላችሁ አይመስለኝም። የምናወራው በስልጣን ላይ ያላችሁትና ተባባሪያችሁ ልሒቅ ሆናችሁ ሀገራችን ላይ ስላሰፈናችሁት የበላይነት ነው ፣ ስለህወሀት ስለሚባል የትግሬዎች ድርጅት ሰራሽ የበላይነት። ይህን ዶሮ ጭራ የምታወጣውን ነገር በጥልቅ የተቀበረ ሚስጥር ማስመሰል ለናንተም ለማንም አይበጅም።

በመጀመሪያዎቹ ጥቂት አመታት የህወሀትም የበላይነት ሆነ የሀገሪቱ ጦር ባብዛኛው በትግሬ አዛዦች መመራቱ ብዙ ነውርነት አልነበረውም። በትግሉ ውስጥ የህወሀት ሚናና ተሳትፎ ትልቁ በመሆኑ ይህ አላስገረመንም። አሁን ግን ሩብ ምዕተ ዓመት አለፈው። ይሉኝታ ይዟችሁ ታሻሽሱታላችሁ ብለን ስንጠብቅ አባሳችሁት። ከሚገባ በላይ ትዕግስት ጠየቃችሁኝ ነው የሚለው አሁን ህዝቡ። ይህን በጩኸት የሚወጣ ድምጽ ሰው እንዴት መስማት ያቅተዋል?

አደገኛው የውሸት መደምደሚያ

ውሸቱ ምንም ሶፍስቲኬሽን የሌለበት ሌጣ ውሸት ስለሆነ ከላይ ያነሳሁዋቸው አይነት ጥቂት ዉሸቶችና ጥቂት አገር የሚያውቃቸው ምሳሌዎች ብቻ ጠጥቶ ርቃኑን ማስኬድ ይቻላል። እኔን ያሳሰበኝና ከማሳሰብም አልፎ ያስፈራኝ ባለስልጣናቱ ከዚህ ውሸት ላይ ተንደርድረው የሚሰጡት ትንታኔና ሀላፊነት የጎደለው መደምደሚያቸው ነው። ለዚህ ጽሁፍ ዋነኛ መነሻ የሆነኝም ከዚህ ያገጠጠ ውሸት በኋላ እነ አቶ ስዩም መስፍን የሚሰጡት ትንታኔና ሊከተል ይችላል የሚሉት “የሰይጣን ጆሮ አይስማው” የሚያሰኝና በነሱ ቤት ሕዝብ ማስፈራሪያ ይሆናል ብለው የሚጠቅሱት ዘግናኝ የታሪክ ምስስል (analogy) ነው። አቶ አባይ ጸሐዬ ይህንኑ ውሸት ከተናገረ በኋላ የጠቀሰልን ምሳሌ የሩዋንዳ እልቂት ጉዳይ ነው። እንደሩዋንዳ ልንሆን እንችላለን እያለ ነው የሚያስፈራራን። አቶ ስዩም መስፍን ደግሞ ስለ አይሁዶች ሆሎከስትና የናዚዎች ጭካኔ በሰፊው ነገረን። የመንግስት ቃል አቀባዩ ቢሮ ደግሞ ድረ ገጽ ላይ የሶሪያን የፈራረሱ ከተሞች ፎቶግራፍ እየለጠፈ ያስፈራራናል። ትግሬ ያልሆነውን የኢትዮጵያ ማህበረሰብ በጅምላ የትግሬ የበላይነት አለ ይላል ብለው ከከሰሱ በኋላ ሩዋንዳ የሆነውንና የጀርመን ናዚዎች ያደረሱትን ጥፋት ሊያደርሱ የተዘጋጁ ኢትዮጵያውያን አሉ ነው የሚሉን ባጭሩ። ለዚህ ሰለባ የሚሆነው ደግሞ እነሱ እንደሚሉት የትግራይ ህዝብ ነው። የፈረደበትን የትግራይ ህዝብም አደጋ መጥቶብሀልና ሌሎች ወገኖችህን ፍራ ከሁዋላችን ሆነህ ለመዋጋትም ወይም ሌሎች ወገኖችህን ለመፍጀት ተዘጋጅ ነው የሚሉት። ሊከሱ የፈለጉት ደግሞ አሁን ራሳቸው እየቀጠቀጡት ያለውን የኦሮሞና ያማራ ህዝብ መሆኑ ነገሩን አሳዛኝ ስላቅ ያደርገዋል። ለመሆኑ ዛሬ በኢትዮጵያ ናዚ ናዚ የሚሸተው ማነው?
እነዚህ ሰዎች ለነዚህ ዋና ጥያቄዎች ምን መልስ ይሰጡ ይሆን። ለመሆኑ ዛሬ በኢትዮጵያ የናዚዎቹን የሚመስል ቁመና ላይ ያለው ማነው? ማለትም በኢትዮጵያ ዛሬ እንደ ናዚዎቹ ባለጠማንጃው ባለስልጣኑና ወታደር የሚያዘው ማነው? እየገደላችሁት ያለው ኦሮሞና አማራ ናዚዎቹን ይመስላል ወይስ ስለባዎቹን አይሁዶች? በየክፍለ ሀገሩ የሠራችኋቸው ኦሮሞና አማራ ያጎራችሁባቸው አውችዊትዝን (Auschwitz) የመሳሰሉ የሰው ማሰቃያ ኮንሴንትሬሽን ካምፖች ከማን ሥራ ጋር ይመሳሰላሉ? አማሮችና ኦሮሞ እስረኞቻችሁ የታጎሩባቸውን የብር ሸለቆና የሁርሶ ካምፖችን የመሳሰሉትን ማለቴ ነው። የናዚዎቹ ወይስ ያለቁት አይሁዶች መታጎሪያ ነው የሚመስሉት? ተብለው ቢጠየቁ አቶ ስዩም መስፍን ምን እንደሚሉ አላውቅም። ልጇን ገድሎ እናትዮዋን ልጅሽ ሬሳ ላይ ተቀመጭ ብሎ የሚቀጠቅጠው ነው ናዚ የሚመስለው ወይስ የልጇን ሬሳ ታቅፋ ሰውነቴ እስኪሰባበር ደበደቡኝ የምትለው እናት? መሀል አራዳ አዲስ አበባ ያለው ማዕከላዊ የተባለውን የሰው መጥበሻ የሰቆቃ ማዕከል የትኛው ብሔረሰብ ሰዎች ናቸው የሚያስተዳድሩት? እዚያ ተቁዋም ውስጥ ዋናው የሹሞቹ ቋናቋ ትግሪኛ መሆኑን አገር እንደሚያውቅ እነ አቶ ስዩም መስፍን የሚያውቁም አይመስሉም። ከዚያ የወጡ ሰዎችን አቶ ስዩም ቢጠይቁ ማን ናዚ እንደሚመስልና በቀላሉም መሆን እንደሚችል በቅጡ ይረዱት ነበር። እነ አቶ ስዩም መስፍንና እነደብረጽዮን ለምን እንድ ጊዜ ቃሊቲ ወይም ቂሊንጦ ብቅ አይሉም። የወህኒ ቤቱ ሀላፊዎች ከየትኛው ብሔረሰብ ናቸው? ታሳሪዎቹስ? ይትኛው ብሔረሰብና የፖለቲካ ድርጅት ሰዎች ናቸው ወደ ናዚዎቹ የተግባር ስምሪት የሚቀርቡት? ለመሆኑ ከዚህ የተለየ ያንድ ጎሳ ድርጅት የበላይነትንስ የሚያሳይ ምን ልታመጡ ነው ተብለው ቢጠየቁ ምን ሊሉን ነው?

የትግራይ ህዝብ ላይ የተነጣተረ ጥላቻ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ብሎ ለመደምደም የሚያስችል ያለቀለት መረጃ አላየንም። ዉሱንም ቢሆን አለ ከተባለ ግን ህወሀት ሁሉንም ቦታ ለመቆጣጠር ሲል በፈጠረው ስራ የተፈጠረ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። የፖሊስ ጣቢያው አዛዦች ትግሬዎች፣ የወህኒ ቤቱ አዛዞች ትግሬዎች፣ የግርፊያው መስሪያ ቤት አዛዦች ትግሬዎች ሆነው መታየታቸው የሚፈጥረው መጥፎ ስዕል (Image) አለ። ይህ ኢሜጅ በራሱ ቁጣ (resentment) ቢፈጥር የሚያስገርም አይመስለኝም። እኔ ከሀገር ከወጣሁ ስለቆየሁ ባይኔ ያላየሁት ነገር ግን በተደጋጋሚ ከብዙ ሰዎች የምሰማው ብዙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ከመጠኑ በላይ (Disproportionate) የሆነ የትግራይ ተወላጆች ቁጥር አለ ሲባል እሰማለሁ። ከተለያዩና ከብዙ ሰዎች ስለምሰማው ውሸት ነው ለማለት አልችልም። አየር መንገድ፣ ኢሚግሬሺን መስሪያ ቤት፣ ጉምሩክ ወዘተ ያላቸው ከሌላው የላቀ ቁጥር ሌሎች ብሔረሰቦች ላይ ጥሩ ስሜት እንደማይፈጥር ለማወቅ ብዙ መማር አያስፈልግም። ችግሩን ማስወገድ የፈለገ ሰው ይህንን ማስተካከል ነው። ሕዝቡ እኮ ዛሬ ባመጸባቸው ቦታዎች ሁለተኛ ዜግነት መረረኝ እያለ ነው። ይህን በተግባር እንጂ በውሸት መቀየር አይቻልም። የትግራይ ህዝብ በጅምላ የዚህ መድሎ ተጠቃሚ እንዳልሆነ ከሌሎቹ ብሔረሰቦች ግን ለመንግስት የተሻለ ቀረቤታ (access) አለው ብለው የሚያምኑ ኢትዮጵያውያን አሉ። የወያኔዎቹ ሹሞች የሚክዱት የበላይነት ትርጉምም ይህ ነው። ድህነት በበዛበት ሀገር ውስጥ ባለው የስራ እድል ሽሚያ ያንድ ብሔረሰብ አባላት እድሉን በማግኘት በልጠው ከታዩ ሌላው ከንፈሩን ይነክሳል። ይህ ይህን ያህል ለሁላችንም ሊገባን ይገባል። ሰብዓዊ ስሜት ነው። የህወሀት ሰዎች የአማራ ለማኝ ባማርኛ በመለመኑ ምክንያት የትግሬውን ለማኝ ይጨቁነዋል እያሉ አልነበር ስታሊኒዝምና ማርክሲዝም ሲያስተምሩ የነበሩት። ነገሩ እኮ ለማያውቅሽ ታጠኝ ነው። የዚያ ሁሉ የህወሀት ጸረ አማራ ዘፈንና ስነጽሁፍ መሰርቱስ ይህ አይደል። ግዙፉ ዕውነት ይህ ነው።

በቅርቡ ከትግራይ ማህበረሰቦች ጋር ተደረጉ የተባሉትን ግጭቶች እያጋነኑ ለመጠቀም መሞከር ለዘለቄታው ሀገር የሚጎዳ ነገር ነው። በተለይ በህዝብ መገናኛ ይህን ወሬ የሚነዙት ባለስልጣኖች ሀላፊነት የጎደለው ስራ እየሰሩ መሆኑን ሊያውቁት ይገባል። መኖር የሌለበት ግጭት ለመፍጠር የሚደረግ የከይሲ ሙከራ ነው። ቢያንስ ከአማራ ክልል ባለስልጣኖች የምንሰማው ህዝቡ ቁጣውን የገለጠው ከመንግስት ጋር ሆነው አጠቁኝ ባላቸው በርካታ አማሮችና ጥቂት ትግሬዎች ላይ እንጂ ትግሬዎችን በዘር እየለየ አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ በዘር ተጣልቶ ለመጋደል የሚያስችል የተፈጥሮም የታሪክም መሰረት የለውም። ኢትዮጵያ ውስጥ የሩዋንዳም ሆነ የሌላ ሀገር አይነት የዘር ግጭት የሚመጣው ባለስልጣኖች የራሳቸውን ስልጣን ለመጠበቅና የዘረፉትን ሀብት ለመንከባከብ ሲሉ ሊፈጥሩ በሚችሉት እኩይ ተግባር ምክንያት ብቻ ነው።

ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ የህወሀትና የትግራይ ልሂቃን የበላይነት ያንፈራጠጠበት ሁኔታ አለ። ኢትዮጵያ በታሪኳ እንደዛሬ የተደራጀ ለአፓርታይድ የቀረበ (Instituionalized and systematic) ብሔረሰብ ጭቆና አይታ አታውቅም። ይህ የትም ቦታ ቢሄዱ አግጦ የሚታይ ሊደብቁት የማይቻል እውነት ነው። ይህን በትልልቅ ስልጣን ላይ የተቀመጡት ሰዎች እነ አቶ ሐይለማሪያም ደሳለኝ መሆናቸው አይቀይረውም። በከፍተኛ ስልጣን ላይ ካሉት ሰዎች በቁጥር የሚበልጡት ትግሬ ያልሆኑ ሰዎች ናቸው የሚለው አባባል ዕውነታውን አይቀይረውም። የሀገሪቱ የምር የሀይል ማዕከል የት እንዳለ ትንንሽ ልጆች ሳይቀሩ ያውቁታል። ሰራዊቱን ኢኮኖሚውንና ደህንነቱን ማን እንደሚቆጣጠረውና በሌላው ብሔረሰብ ተወላጅ ጉያ ቁጭ ብለው ሐይለማሪያምን የመሳሰሉትን ሹማምንት የሚቆጣጠሩት እነማን እንደሆኑ አገር ያውቃል። ችግርና ጥፋት የሚያስወግደው ይህንን ነገር እያፍረጠረጡ በመወያየትና በማረም እንጂ በመሸምጠጥ አይደለም።
ህዝባችን በራሱ በመሀሉ ለጠብ የሚሆን እንደሩዋንዳ የሚያጫርስ ምንም ምክንያት የሌለው ድሀ ህዝብ ነው። አብሮ መኖር ያውቅበታል። ዛሬ በየቤተሰባችን ካንድ በላይ ብሔረሰብ ያለን ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች ሚሊዮኖች ነን። ስልጣን ላይ ያላችሁት ሰዎች በተለይ የህወሀት መሪዎች ይህን ለራሳችሁ ስትሉ የፈጠራችሁትን “ርዋንዳ መጣባችሁ ሂትለር መጣባችሁ” ማስፈራሪያ ይዛችሁ ሂዱልን። በሰላም ከተዋችሁን በዝርፊያ ጭምር ያገኛችሁትን ንብረት መርቀን ልንተዋችሁ የምንፈልግ ኢትዮጵያውያን ብዙ ነን። ለሰላማዊ ለውጥ ከተመቻችሁን ይህን እንከፍላለን። ሕዝቡን ልቀቁት። የትግራይ ህዝብንም ልቀቁት። ከወገኖቹ ጋር በሰላም ይኑርበት።
Fekadeshewakena@yahoo.com


ገደብ የሌለው ድንቁርና ! ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

$
0
0

መግቢያ

ካለፈው ህዳር ወር ጀምሮ እስከ ዛሬ ነሃሴ ወር ድረስ በአገራችን ምድር በህዝባችን ላይ አንድን አገር አስተዳድራለሁ ከሚል፣ ከዘጠና ሚሊዮን በላይ የሚቆጠርን ህዝብ ብቻ ሳይሆን፣ የሚቀጥለውንም ተከታታይ ትውልድ ህይወትና ዕድል የሚወስን አገዛዝ በጭፍን የሚያካሂደው ጭፍጨፋ፣ መደብደብና ማሰቃየት፣ እንዲሁም ካለምንም ማስረጃ እስርቤት ውስጥ መክተት አብዛኛዎቻችንን ያንገበግበናል፣ ያስለቅሰናልም። ማንኛውምን ከህዝብ ወገን የሚነሱ ቅሬታዎችን አዳምጦ በሰላም ማስተናገድና መፍታት እንደ መሞከር ይልቅ አገዛዙ ሆን ብሎ የያዘው ህዝብን ማስፈራራት፣ ማንገላታት፣ መግደልና፣ የተቀረውን ደግሞ እስርቤት ውስጥ መወርወር ሆኗል።

ባለፉት 25 ዓመታት ይህ አገዛዝ ጸባዩን እንዲያሳምር፣ ህብረተሰብአዊ ባህርይ እንዲኖረውና፣ የህዝብን ቅሬታዎችና የሚደርስበትን በደል ሰላማዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ እንዲያስተናግድ ያላደረግነው ጥረት ይህ ነው አይባልም። ከሌሎች ሁለት አገዛዞች ጋር ሲወዳደር ይልቅ ይህንን አገዛዝ በተቻለ መጠን እሹሩሩ በማለት ጸባዩን በማሳመርና ህዝባዊ ባህርይ ኖሮት የህዝብ ቅሬታዎችን በስነስርዓት እንዲያስተናግድ ሁላችንም በመሰለን መንገድ ድምጻችንን አሰምተናል። በአብዛኛዎቻንንም ዘንድ እንደዚህ ዐይነቱን ሰላማዊና የማስተማር መንገድ እንድንከተል ያስገደደን፣ አንድም ስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ በታሪክ አጋጣሚ ሆኖ ከአንድ ብሄረሰብ የተውጣጣ በመሆኑ ትግላችን ወደ ማይሆን መንገድ እንዳይሄድ ለማድረግ ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ ባለፈው 40 ዐመታት ህዝባችን ብዙ ስቃይንና ፈተናን የቀመሰ ስለሆነ ያለው አማራጭ መንገድ ሌላ ሳይሆን በማስተማርና በመቻቻል ላይ የተመሰረተ ሰላማዊ ትግል ከማካሄድ በስተቀር ሌላ አማራጭ ሊኖር አይችልም ብለን በመገንዘባችንም ጭምር ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ከብዙ አገሮችና ከአገራችንም ልምድ እንዳየነውና እንደተማርነው ከጦር ትግል ይልቅ በአርቆ አስተዋይነትና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ትግል ለአንድ ህብረተሰብ ዕድገት አማራጭ የሌለው ዘዴ መሆኑን በመረዳታችን ነው። ከተለያየ አካባቢና ብሄረሰብ የመጣንና የተለያየ ቋንቋ የምንነጋገርም ቢሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ ሁላችንንም የሚያስተሳስሩን ብዙ ነገሮች አሉ። በታሪክ ሂደት ውስጥ እየተዋሃድንና አንድ ሁላችንንም የሚያግባባ ቋንቋ፣ ኋላችንንም የሚያስተሳስረን ባህል፣ የምግብ ዐይነት፣ የአለባበስ ዘዴና ሌሎች ልዩ ልዩ ነገሮች የሁላችንም መግለጫ እየሆኑ የመጡበትን ሁኔታ እንመለከታለን። ስለሆነም የአንድን ህብረተሰብ ህግ ሂደት ካለመረዳት የተነሳ ባለፉት መቶ ዐመታት በተለያዩ አገዛዝ ጭቆናዎችና በደሎች ቢደርሱም ከህብረተሰብ ምስረታና ከሳይንስ አንጻር ልንክደው የማንችለው ሁኔታ ተፈጥሯል። ይኸውም ኢትዮጵያን እንደ አገራችንና እንደ አንድ ወጥ ህብረ-ብሄር፣ ይሁንና ግን ደግሞ የተለያዩ ብሄረሰቦችን ያቀፈች መሆኗን አምነን የተቀበልን ብዙዎቻችን ነን። ይሁንና ግን ይህ ያልተዋጠላቸውና ጊዜን የሚጠባበቁ ኃይሎች አጋጣሚን በመጠቀም እነሱ ከሌሎች ጋር ሲወዳደሩ በታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ መልክ ከፍተኛ ወንጀል እንደደረሰባቸው በማውራትና፣ በወጣቱና በተከታዩ ትውልድ ጭንቅላት ውስጥ በመትከል አንድ ህዝብ መስራት ያለበትን ታሪካዊ ስራ እንዳይሰራ አድርገውታል፤ እያደረጉትም ነው። ተጠራጣሪ በማድረግ በራሱ ላይ ዕምነት እንዳይኖረው እያደረጉ ነው። የህብረተሰብ ህግና ዕድገት አስቸጋሪ ሁኔታ ባለማጤን ወጣቱ የዝቅተኛ ስሜት እንዲኖረው የሚሆነውን የማይሆነውን በማውራት መተባበርና መከባበር እንዳይኖር አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ፈጥረዋል። በዚህም አካሄዳቸው በወንድማማች ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ጥላቻንና አለመተማመንን ፈጥረዋል። ለውጭ ኃይሎች የተገዙና ልዩ ተልዕኮዎች ያላቸው ይመስል ሆን ብለው የያዙት ስራ አንዱን ጎሳ ከሌላው ማጋጨትና ደም እንዲፋሰስ ማድረግ ነው። በሃማኖትና በጎሳዎች መሀከል የባሰውኑ ክፍፍል እንዲኖር በማድረግ ህዝባችን በዘለዓለማዊ ፍጥጫ ውስጥ እንዲኖር የማይሰሩት ሰይጣናዊ ስራ የለም።

ከዚህ ስንነሳ የወያኔ አገዛዝ ስልጣን ላይ ከወጣበት እስከዛሬ ድረስ ኢትዮጵያችንን እንደ አገሩ፣ ህዝባችንን እንደ አካሉና ስልጣን ላይ ያለ ኃይልም በመሆኑ የታሪክና የህዝብ ግዴታ እንዳለበት በፍጹም የተገነዘበ አይመስልም። ተጠሪነቱ እሱን አምነው ለሚከተሉት ጥቂት አጎብዳጆችና ለውጭ ኃይሎች ይመስል ባለፉት ሃያ አምስት ዐመታት በታሪካችንና በህዝባችን ላይ በቀላሉ ሊቀረፍ የማይችል በደል ሰርቷል፤ ዛሬም እየሰራ ነው። ህዝባችንና አገራችንን መሳቂያና መሳለቂያ አድርጓል። እንደ አንድ የገዢ መደብ የአገራችንን ብሄራዊ ነፃነታችንን ከማስከበርና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ አገር ለመገንባት ማንኛውንም ጥረት ከማድረግ ይልቅ ከውስጥ ተዳክማ በውጭ ኃይሎች በቀላሉ እንድትጠቃ ያላደረገው አገርን የማዳከም ስራ የለም። ይህንን አካሄዱን እንዲያርም ያላደርግነው ጥረት ይህ ነው አይባልም። ይሁንና ግን አገዛዙ የባሰውኑ በማምረር አገርን በማዳከምና፣ ህዝብን በመበደልና በማሰቃየት ገፍቶበታል። እንዲያውም ተፋለሙኝ በማለት የራሱን የግል ጦር በመመስረት ከህዝብ ጋር ግብ ግብ ለማድረግ ተዘጋጅቷል። ባለፈው ህዳር ወርና አሁን ደግሞ በያዝነው ነሃሴ ወር የሚታየው የአገዛዙ ድርጊት ይህ አገዛዝ በፍጹም ከስህተቱ ሊማር እንደማይችልና፣ የህዝባችንን ቅሬታ፣ በተለይም የወልቃይትን ጸገዴንና በኦሮሞ ክልል የተከሰተውን ተቃውሞ በአጠቃላይ ጦርነት ለማዳፈን ወይንም ለመደምሰስ የተዘጋጀ መሆኑን ነው። በተጨማሪም በነሃሴ 15 ፣ 2008 አዲስ አበባ ላይ ሊደረግ የታቀደውን የእንቢ በይ የቀይ ካርድ የይዞ መውጣት ሰልፍ አስመልክቶ ጥሪውን ለማክሸፍ ያሰማራው እስከ 120 000 የሚጠጋ ወታደር የሚያረጋግጠው አገዛዙ የቱን ያህል አረመኔያዊ እንደሆነና ወደ ፋሺስታዊ ድርጊት እያመራ መሆኑን ነው። ይህ አካሄዱና ጠቅላላው ዝግጅቱ ያንን አካባቢ ብቻ የሚመለከት ሳይሆን ጠቅላላውን ህዝባችንንና የአገራችንን የወደፊት ዕድልና ዕድገት የሚመለከት ስለሆነ ዝምብለን ልናልፈው የምንችለው ነገር አይደለም። ስለሆነም አገዛዙንና የውጭ ኃይሎች አገራችንን የማዳከምና የመከፋፈል ህልምና ዕቅድ ማክሽፍ አለብን። ለዚህ ደግሞ የግዴታ ከመቼምውም የበለጠ በአንድ ርዕይ ስር በመሰባሰብና ኃይላችንን በማጠናከር የግዴታ የአገራችንን ክብር ማስመለስ አለብን። የአገር መቆራረስና መከፋፈል፣ እንዲያም ሲል በህዝባችን ላይ የሚደርሰውን በደልና ግድያ ዝም ብለን ማየት የለብንም። አገራችንን ከጥፋት የማዳን ታሪካዊና የትውልድ ግዴታ አለብን።

ሰውን ከእንስሳ የሚለየው ምንድነው ?

ለመሆኑ ዝም ብለን ከመኖር በስተቀር በህይወታችን እኛን ከእንስሳ የሚለየን ምንድነው ብለን ጠይቀን እናውቃለን ወይ? የኑሮአችንን ትርጉምና ዓላማ ለመረዳት እየደጋገምን ጥያቄዎች እናነሳለን ወይ? በተለይም ፖለቲካ የሚባለው ነገር ከሰው ህይወት፣ የኑሮው ፍልስፍናና የአኗኗር ዘዴ ተነጥሎ በሚታይበት ዓለም ውስጥና፣ ጥቂት ጉልበተኞች የብዙ ሚሊዮንን ሰዎች ዕድል በአሉታዊም ሆነ በአዎንታዊ መንገድ በሚወስኑበት ዓለም ውስጥ የሰውን ልጅ ትርጉምና ያሉትን ባህርያቶች እያነሳ የሚጠይቅ በፍጹም ያለ አይመስለኝም። ከዚህም በላይ ከአርቆ-አስተዋይነት ይልቅ ስሜታዊነት ሁሉንም ነገር በሚወስንበት ዓለም ውስጥ የሰውን ልጅ ሚናና የህይወቱን ትርጉም እየመላለሱ የሚጠይቅ የለም። የሰው ልጅ ጭንቅላት ብዙ ውስጣዊ ባህርያት ቢኖሩትም፣ ሰው እንደመሆኑ መጠን እነዚህን ውስጣዊ ባህርያት የሚጠቀም በጣም ጥቂቱ ብቻ ነው። ስለሆነም አንዱ ሌላውን ሲንቀውና ሲያንቋሽሸው፣ ካለምንም ምክንያት እንደጠላት አድርጎ ሲቆጥረውና ሲያሳድደው፣ እንዲያም ሲል የሚኖርበት አካባቢ ለእሱ ብቻ የተፈጠረች ይመስል በጉልበቱ በመመካት ሁሉንም ነገር ቀምቶ ወደ ድህነት ዓለም ውስጥ ሲገፈትረው፣ እነዚህና አያሌ ነገሮች የአንዱ ደስታ የሌላው ስቃይ ሆነው እንደ ተፈጥሮአዊ ህግ በሚወሰዱበት ዓለም ውስጥ የሰውን የማሰብ ኃይል ጉዳይ እየመላለስን እንድንጠይቅ እንገደዳለን።

ሁሉም ሰው በእግዚአብሄር አምሳል ነው የተፈጠረው ተብሎ በሚሰበክበት ዓለም ውስጥና፣ ይህም ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ያለውና፣ በየአገሮች ህገ-መንግስት ተቀባይነት አግኝቶ የሰፈረ ቢሆንም፣ ጥቂቶች ጊዜው የኛ ነው ብለው የየአገራቸውን ህዝቦች ዕድል እነሱ በሚረዱበትና በሚፈልጉት መንገድ በሚወስኑበት ዘመን የሰው ልጅ እግዚአብሄር የሰጠውን ልዩ ልዩ ባህርያት እንዳይጠቀም ተገዷል። ከዚህ ስንነሳ ባለፉት አስር ወራት በአገራችን ምድር የተከሰተውና በአገዛዙ ያላግባብና ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ በህዝባችን ላይ የሚፈጸመው የግድያ፣ የአፈና፣ የማሰርና የማሰቃየት ድርጊቶች የግዴታ እነዚህን መሰረታዊ ጥያቄዎች እንድናነሳ እንገደዳለን።
ዛሬ በአገራችን ምድር የተከሰተውን ሁኔታ አብዛኛዎቻችን ከስርዓት መበላሸትና ከዲሞክራሲ እጦት ጋር ነው የምናያይዘው። በመስረቱ ግን ሁኔታውን ጠለቅ ብለን ማየት ያለብን ይመስለኛል። ባለፈው አርባ ዐመታት በአገራችን ምድር የተከሰተውን አስቀያሚ ሁኔታ በዲሞክራሲ እጦት ምክንያት ነው ብለን የምናሳብብ ከሆነ ለተወሳሰበው የአገራችን ችግር በፍጹም መፍትሄ የምናገኝ አይመስለኝም። በእርግጥ ዲሞክራሲያዊ መብቶችና ለህዝባችንም የሚስማማ ስርዓት መፈጠርና መዋቀር ያለባቸው ይመስለኛል። ይህ ጉዳይ እስከዚህም ድረስ የሚያጣላን አይመስለኝም። ጥያቄው ግን ለምንድነው ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዳንገነባ ያልቻልንበት ምክንያት? በተለይም ስልጣን ላይ የተቀመጡ ሰዎችም ሆነ ቡድኖች ለምድንነው ዲሞክራሲን አጥብቀው የሚጠሉት? ለምንድነው የሰው ልጅ ህይወት የቅንጣትም ያህል የማይሰማቸው? ብለን እየደጋገምን መጠየቅ ያለብን ይመስለኛል። በተለይም መንግስትና አገር የጥቂት ግለሰቦችም ሆነ ቡድኖች የግል ሀብት ሆነው በሚቆጠሩበት እንደኛውና በተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ተራ ዲሞክራሲያዊ መብቶች በራሳቸው ትርጉም አይኖራቸውም። ስለሆነም የነገሩን ውስብስበነት ከዲሞክራሲ ባለመኖር ባሻገር ማየት ያለብን ይመስለኛል። ወደ ዋናውም መሰረተ-ሃሳቤ ልግባ።

ሰው ለመሆናችን በሚታየው አካላችን ብቻ የሚወሰን አይደለም። ሰው መሆናችን በአለን አካልና ሁሉንም ነገር አጠቃሎ በያዘው ጭንቅላታችን የሚወሰን ነው። ይህም ማለት የፈለግነውን ያህል ብናምር፣ ብንወፍርና ጉልበትም ቢኖረን፣ እንዲያም ሲል በሀብት የናጠጥንም ብንሆን የማሰብ ኃይላችንን መጠቀም እስካልቻልን ድረስ ከእንስሳም እምብዛም የምንለይ አይደለንም። በመሆኑም፣ ወደድንም ጠላንም፣ ተጠቀምንበትም አልተጠቀምንበትም የሰው ልጅ ልዩ ልዩ ባህርዮች አሉት። እነዚህም፣ አርቆ-ማሰብ፣ ሎጂካሊ ማሰብና አዲስ ነገር መፍጠር፣ ወይም ለሚታዩ ችግሮች መፍትሄ መሰጠት፣ ኮመን ሴንስ፣ ንቃተ-ህሊና(Potentially)፣ ኢንቲዩሽን፣ መሰማት(feeling)፣ ርህሩህነት፣ ማመዛዘን፣ መፍጠር መቻል፣ ኢንተለጀንስ፣ ምህራዊነት(በማንበብና በትምህርት የሚገኝ፟)፣ በጥልቀትና በሰፊው ማሰብ፣ ስነ-ምግባርነትና ግብረ-ገብነት፣ ማህበራዊነትና ህብረተሰብአዊ ኃላፊነት መሰማት… ወዘተ፣ እነዚህ ሁሉ አብረወን የተፈጠሩና በጭንቅላታችን ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ይሁንና ግን እነዚህ በጭንቅላታችን ውስጥ ያሉ ፖቴንሺያሎች ቢሆኑም ሊዳብሩና እያንዳንዱ ግለሰብ ራሱን ተገንዝቦ ህብረተሰብአብዊ ኃላፊነትን ሊቀበልና ህብረተሰቡን ሊለውጥ የሚችለው ጭንቅላቱ በትክክለኛ ዕውቀት ሲኮተኮት ብቻ ነው። ጭንቅላት በመጥፎ ነገሮች ተበርዞ አካባቢውንም ሆነ ጠቅላላውን ህብረተሰብ እንዳይመርዘውና እንዳያናገው ከተፈለገ አገርንና ህብረተሰብን የሚያፈርሱ አዳዲስ ሁኔታዎች በሚፈጠሩበት ጊዜ የእነዚህን ምክንያቶችና አመጣጣቸውን አጥንቶ ለመዋጋት ይቻል ዘንድ አዕምሮ የግዴታ በትክክለኛ ዕውቀት መኮትኮት አለበት። አዕምሮ የረጋ ባለመሆኑና፣ በሚሆኑ በማይሆኑ ነገሮች በመታለል ከትክክለኛውን ፈር ስለሚወጣ በየጊዜው መታደስ አለበት። ለዚህ ነው ሶክራተስ ሰውነታችን ለመንቀሳቀስና ለመስራት ጅምናስቲክ እንደሚያስፈልገው ሁሉ፣ ጭንቅላትም እንደዚሁ ጂምናስቲክ ያስፈልገዋል የሚለው። በተጨማሪም ሶክራተስ እንደሚያስተምረን የሰው ልጅ ህይወት መፈተን አለባት። ራሱን እንዲገነዘብና ህብረተሰብአዊ ኃላፊነትን ለመሸከም እንዲችል የግዴታ ህይወቱ ከአስቸጋሪ ሁኔታ ጋር መለማምድ አለባት። በሌላ ወገን ደግሞ ጭንቅላታችን ብዙ ጥሩ ፖቴንሺያሎች ቢኖሩትም እዚያው በዚያው ጭንቅላታችን አረመኒያዊ ባህርይ፣ ስግብግብበት፣ መቸኮል፣ አርቆ-አለማሰብ፣ ሎጂካል በሆነ መልክ ማሰብ አለመቻል፣ ስሜታዊነት፣ ህብረተሰብአዊ ኃላፊነት አለመሰማት… ወዘተ. በጭንቅላታችን ውስጥ ያሉ እጅግ አደገኛ ባህሪያችንና በየቀኑ የሚፈታተኑን ናቸው። ይህም ማለት ጭንቅላታችን ወይም መንፈሳችን እዚያው በዚያው በቅራኔ የተወጠረና በዘለዓለማዊ ግጭት ውስጥ የሚኖር ነው። በተለይም ከተወሰኑ ሁኔታዎች ጋር እየተለማመድን ካደግን የኑሮአችን ፍልስፍና በሙሉ ጤናማውን የሰው ልጅ ባህርያት የሚቃረን ይሆናል። ፍርደ-ገምድልነትን፣ መግደልን፣ ማሰቃየትን፣ መዋሸትን፣ አገርንና ህብረተሰብን ማዘበራረቅ ወይም ማፍረስ ዋናው የኑሮአችን ፍልስፍና በማድረግ ለሚያድገው ትውልድም እንዲተላለፍ ማድረግ እንችላለን።

ከዚህ ስንነሳ ባለፉት አርባ ዓመታት፣ በተለይም ደግሞ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የተፈጠረውን ኢ-ፍትሃዊ አስተዳደር፣ አገር አፍራሽ ድርጊት፣ እንዲያም ሲል በአንድ ጥቁር ህዝብ መሀከል ስምምነት እንዳይኖር ጎሳን ከጎሳና፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት ጋር እያጋጩ ህዝቡ የኑሮው ፍልስፍና አድርጎ እንዲወስደው ማድረግ ከዚህ የጭንቅላት መከስከስ ወይም ደግሞ ጭንቅላት ውስጥ አሉ የሚባሉት ጥሮዎች ባህርያት ሙሉ በሙሉ መውደም ጋር የተያያዙ ናቸው ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። በዚህም ምክንያት የተነሳ ጭንቅላታችን አዳዲስ ነገሮች የመቀበል ኃይሉ ስለሚዳከም ከሌላ ሰው የመጣ አዲስና ገንቢ አስተሳሰብን ይቃወማል። ያገኘውን ዝና፣ የተጎናጸፈውን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ስታተስ ይቀናቀነኛል በማለት ህብረተሰብአዊ ለውጥ እንዳይመጣና በዚያውም መሰረትም በሳይንስና በቴክኖሎጂ አማካይነት የሰፊው ህዝብ ኑሮ እንዳይሻሻል ያግዳል። በተለይም በአሁኑ ዘመን ውስጣዊ አገዛዞች ከውጭ ኃይሎች ጋር በሺህ ድሮች ተሳስረው በሚገኙበት ዓለም፣ የውስጥ ኃይሎች የውጭውን ኃይል ተገን በማድረግ ከውስጥ መስረታዊ ለውጥ እንዳይመጣ፣ እንዲያም ሲል በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለና የተወሳሰበ ኢኮኖሚ እንዳይገነባ እንቅፋት ይሆናሉ። በዚህ ዐይነቱ የተቆላለፈ ሁኔታና በጥቅም መተሳሰር የተነሳ ጭንቅላት የባሰውኑ እየዛገና ለዕድገት እንቅፋት እየሆነ ይመጣል። ስለሆነም ይህንን አካሄድ የሚቃውም ኃይል ከውስጥ ሲነሳ ህገ-መንግስቱን የሚጻረር የሽበረተኞች አካሄድ ነው በማለት በማስፈራራትና፣ ይባስ ብሎም አንዳንድ ግለሰቦችን ወይም ደግሞ በጅምላ በመግደል ነገሩን ለማብረድ ይሞከራል። ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱ አካሄድ ችግሩን የሚፈታ ሳይሆን የሚያባብስና ህብረተሰብአዊ ፍጥጫውን ልዩ ዕምርታ የሚሰጠው ይሆናል። ይህ ዐይነቱ ችግርን ከመፍታት የባሰውኑ ማባባስ በብዙ ኋላ-ቀር በሚባሉ አገሮች የሚታይ አደገኛ አካሄድ ቢሆንም፣ እንደወያኔ ያለውን አገዛዝ ባህርይና ስልጣን ላይ ቁጥጥ ብሎ ህዝብን ማሰቃየት በተራ የፖለቲካና ከውጭው ኃይል ጋር በመተሳሰር ብቻ የሚገለጽ አይደለም። ሁኔታው በከፍተኛ ደረጃ ከህሊና-ሳይንስ አንፃር መታየት ያለበትና ከዝቅተኛ ስሜት ጋር በመያያዝ፣ በአንድ በኩል በምንም ማስረጃ የማይደገፍ በአንድ ብሄረሰብ ላይ ያተኮረ የቂም በቀል „ፖለቲካ“ ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ ይህንን ሁኔታ በመጠቀም የአንድን ጎሳ የበላይነት(Dominanz) አስፍኖ አንድን ብሄረሰብ ብቻ ሳይሆን ጠቅላላውን ህብረተሰብ ለማዳከምና ለመግዛት የሚካሄድ፣ ግን ደግሞ የመጨረሻ መጨረሻ የሚከሽፍ መጥፎ አካሄድ አድርጎ መረዳትም ያስፈልጋል። በሌላ አነጋገር፣ ባለፉት ሰላሳና አርባ ዐመታት በብዙ አገሮች አምባገነናዊ አገዛዞች የታዩ ቢሆንም አገሮቻችውን ለማዳከመና ለማፈራረስ የተነሱብት ጊዜ አልነበረም።

አብዛኛውን ጊዜ በብዙ የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮች ውስጥ ያለው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶች የሚታዩት አገዛዞቹ ባለማወቅ በተሳሳተ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሚሊታሪ ርዕዮተ-ዓለም ወይም ፖሊሲ ስለሚመሩ ነው። አብዛኛዎች አገዛዞች በዓለም አቀፍ ደረጃ በተዋቀረው የአገዛዝ ሂራርኪ ውስጥ ስለተካተቱና ወደ ታዛዥነት ስለተለወጡ ካለምንም ምሁራዊ ክርክር ሳያውቁ ተግባራዊ የሚያደርጓቸው ፖሊሲዎች ህብረተሰቦቻቸውን እንዲያናጉና ወደ አለመጋዝት እንዲያመሩ ያስገድዷቸዋል። በሌላ ወገን ወያኔ የሚያካሄደው ማንኛውም ፖሊሲ ሆን ብሎና በውጭ ኃይሎች ታግዞ የሚካሄድ በመሆኑ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የተከላቸው መዘዞች፣ ያሰራጫቸው የጥላቻ መርዞች በቀላሉ የሚነቀሉና የተወሳሰበውን የአገራችንን ችግር በቀላል ፎርሙላ መፍታት የማንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል።

ያም ሆነ ይህ፣ በተለይም ፊደል የቆጠረና ዩኒቨርሲቲም ገብቶ ትንሽም ዓመት ቢሆን ይህንንም ሆነ ያንን ትምህርት የተማረ ሰው ድርጊቱ በሙሉ ተንኮልና ጥፋት ከሆነ ይህንን ዐይነቱን ድርጊት ከአዕምሮ ባህርያት ሙሉ በሙሉ ተሟጠው ከመውደማቸው ጋር ማያያዝ ይቻላል። አንድ ሰው ተማረም አልተማረም የተወሰነ የሞራል ኮድ እንዲኖረው ያስፈልጋል። ወደ ትምህርት ቤት የሚኬደው እንዲያው ከተወሰነ ዐመት በኋላ ዲጊሪ አግኝቻለሁ ለማለትና ለመዘባነን ሳይሆን፣ የማሰብ ኃይሉን ለማዳበርና፣ አልተማረም ለሚባለው ዕውቀትን ለማስተላለፍና የኑሮን ትርጉም ተረድቶት ራሱን እንዲለውጥ ለማድረግ ነው። የመማር ትርጉሙ የአንድን ህብረተሰብና የተፈጥሮን ህግ በመረዳት አንድ ህዝብ ታሪካዊ ስራዎችን ይሰራ ዘንድ መንገዱን ማሳየት ነው። በሌላ አነጋገር፣ የመማር ትርጉሙ፣ አገር ማፈራረስ፣ ተንኮል መስራት፣ ስግብግብነት፣ ከሌላው በልጦ ለመገኘት ሲባል አንዱን ማጥፋት፣ በተለይም ስልጣን ጨብጬአለሁ ብሎ በጠብመንጃ ኃይል በመመካት ሰውን እያነጣጠሩ መግደልና የአንድን ቤተሰብ ህይወት እንዳለ እንዲፈራርስ ማድረግ አይደለም። የፈለገው ሰው ቢሆን፣ በተለይም ደግሞ የመንግስትንንም መኪና የጨበጠና አገርን አስተዳድራለሁ የሚል፣ አንድን ሰው ወይም ብዙ ሰዎችን እንደፈለገው የመግደል፣ የማሰቃየትና የማሰር መብት የለውም። እንደፈለግሁት አደርጋለሁ የሚል ሰው በመጀመሪያ ደረጃ ራሱ ሰው መሆኑን የማይረዳ፣ ወይም ደግሞ ራሱ ከማንኛውም ሰው በላይ ነኝ ብሎ የሚገምት ብቻ ነው።

በመሰርቱ የወያኔን ሰዎችን ባህርይ መረዳት የምንችለው በዲሞክራሲ መኖርና አለመኖር አይደለም። ሰውን ማሰቃየታቸው፣ መግደላቸው፣ ጎሳን ከጎሳ ማጋጨታቸው፣ እነሱ እያበጡ እገር እንድትፈራርስ ማድረጋቸው፣ በተለይም ወጣቱን ትውልድ የዕጽ ሱሰኛ አድርጎ የኑሮን ትርጉም እንዳይረዳ ማድረግ፣ ይህ ሁሉ ርኩስ ድርጊት ሊገለጽ የሚችለው ውጥንቅጡ ከወጣው ወይም በስነስስርዓት ካልተዋቀረው ባህርያቸው ጋር የተየያያዘ ሲሆን ብቻ ነው። ወያኔ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታትም ሆነ ከዚያ በፊት የፈጸማቸውን ወንጀሎችና በድሮ የትግል አጋሮቹ በየጊዜው የሚነገርንን ለማወቅ የግዴታ በኖይሮ ባዮሎጂስት ወይም በህሊና ሳይንስ መመረቅ ወይም መሰልጠን አያስፈልግም። ራሱ የምናየው ነገር፣ ህዝባችን የሚኖርበት ኑሮና የሚፈጸምባቸው ወንጀሎች ራሳቸው በቂ ትምህርት ስለሆኑና፣ ይህንንም ከኖርማል ሁኔታ ጋር በማመሳሰል የነዚህን ሰዎች የጭንቅላት ባህርይ ከሞላ ጎደል መረዳት ይቻላል። ብዙ መመራመር አይሰፈልገውም ማለት ነው። ባለፉት ሃያ ዓምስት ዓመታት ስለወያኔ አረመኔያዊነት ብዙ ተጽፏል፤ ብዙም ተነግሯል። ይሁንና ግን የሁላችንም ግምት ቀን እያለፈ በሄደ ቁጥር ማህበራዊ ባህርይ በመወሰድ ከዚህ አረመኔያዊ ባህርያቸው በመላቀቅ ከህብረተሰቡ ጋር ይቀላቀላሉ የሚል ግምት ነበረን። ስለሆነም አጻጻፋችን ከሞላም ጎደል በተቻለ መጠን ፈሩን እንዳይለቅና ትምህርታዊ በመሆን ግንዛቤ ሰጥቶአቸው ርህሩህ ባህርይ ያዳብራሉ የሚል ግምት ነበረን። እነሱ ግን ሆን ብለው የያዙት አንድም ሌላው ሞኝ ነው፣ በቀላሉ ልናታልለው እንችላለን በማለትና ለሆዱ ያደረውን በመግዛት፣በዚያም አማካይነት በህብረተሰብ ውስጥ ሚዛናዊነት ያለው ድርጊትና የሀብት ፈጠራ እንዳይካሄድ በማድረግ፣ በሌላ ወገን ደግሞ አልፎ የሄዳቸውን ይቀናቀነኛል ብለው በማሰብ እንዲጠፋ በማድረግ በፍጹም ሊማሩና ህብረተሰብአዊ ባህርይ ሊቀስሙ የማይችሉ ፍጡሮች እንደሆኑ ነው በየጊዜው ያረጋገጡልን። በተለይም ከነሱ ኢ-ፍህታዊ አገዛዝ የሚመነጨውን ግፍ የሚቃወመውን ሁሉ ትግሬውን ወንድሞቻችንም ሆነ እህቶቻችን፣ እንዲሁም እናቶቻችንና አባቶቻችንን የተቃወመ በማስመሰል ወይንም በነሱ ላይ የተለየ ጥላቻ እንዳለ በማስወራት የዋሁን ህዝብ በማሳሳት እስካሁን ድረስ እያወናበዱ መግዛት ችለዋል። ይሁ ሁሉ የመጥፎ ባህሪያቸው መግለጫ ነው።

አንዳንድ የድሮ ታጋይ ነን የሚሉና ዛሬ ያገሪቱ ሁኔታ ያሳሰባቸው እንደነ ጄኔራል ጻድቃን እንደሚነግሩን ወይም ለማረጋገጥ እንደሚሞክሩት ሳይሆን፣ በተለይም የኋላ ኋላ ቀስ በቀስ የበላይነትን እየተቀዳጁ የመጡት እንደነ መለሰ ዜናውና ስብሃት ነጋ፣ ሌሎችም ዛሬ በስልጣን ላይ ያሉት በሙሉ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሱት አረመኔያዊነታቸውን እያረጋገጡ ነው። በሌላ አነጋገር በዲሞክራሲያዊና በሰብአዊ መርሆች በመመራት ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመፍጠር አይደለም። ስለሆነም የጄኔራል ጻድቃን ድርጅቱን በአነሳሱ ዲሞክራሲያዊና አብዮታዊ አድርጎ ለማቅረብ መሞከሩ ቢያንስ ድርጅቱ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ ከሚያደርገው አረመኔያዊ ድርጊቱ ጋር በፍጹም የሚጣጣም አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ ድርጅቱ ዲሞክራሲያዊ ባህርይ ቢኖረው ኖሮ በትግሉ ዘመን በመሀከላቸው የነበረውን ቅራኔ ወይንም በሃሳብ አለመግባባት ዲሞክራሲያዊ በሆነ መልክ መፍታት መቻል ነበረበት። በተጨማሪም በአንዳድ ግለሰቦች በሴቶች ላይ የሚደረገውን ግፍና ግድያ ወይም ወደ ገደል ውስጥ መውርወር ሲታይ ዝም ብሎ ማለፍ፣ ወይም እንደዚህ ዐይነቱ መጥፎ ድርጊት እንዳይደገም ወንጀሉን በፈጸመው ላይ ቁርጥ ያለ እርምጃ መውሰድ ሲገባ እነ ጄኔራል ጻድቃን ይህንን አጸያፊ ድርጊት ዝም ብለው የሚመለከቱ ነበሩ። ይህም የሚያሳየው የኋላ ኋላ ድርጅቱን በቁጥጥራቸው ውስጥ ያስገቡት እነመለስና ስብሃት ነጋ፣ እንዲሁም ሌሎችም አረመኔዎች እንደነበሩና የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ባህርይ እንዳልተዋሃዳቸው ነው የሚያረጋግጠው። ከዚህም ባሻገር ማንኛውም የዲሞክራሲን መፍክር ይዞ የሚነሳ ግለሰብም ሆነ ድርጅት ማሰብና ማቀድ ያለበት ስትራቴጂያዊ በሆነ መልክ ነው። በሌላ አነጋገር ማሰብ ያለበት ከስልጣን መያዝ ባሻገር ነው። የእነ መለስ ዜናዊና ስብሃት ነጋ እንዲሁም የተቀሩት የዛሬው ቱጃሮች ዕቅድ ማሰብ የሚችለውንና ትንሽም ቢሆን ከእነሱ የተሻለውን በማስወገድ ወደ ስልጣን የሚመጡበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነበር። ይህንን ዐይነቱንና በብዙ መልክ የሚወራውንና ዕውነትም የሆነውን ወንጀላቸውን ሁሉ የተከታተለ፣ የወያኔ ሰዎች አንድ ሰው እንዲኖረው የሚገባውን ከላይ የዘረዘርኳቸውን ጤናማ ባህርዮች በሙሉ አንድ በአንድ እያጡና የምናየው አካላቸው ብቻ የሚንቀሳቀስ ሆኖ የባሰ ስግብግብነትንና አረመኒያዊነትን ከሰውነታቸው ጋር እያዋሃዱ የመጡበትን ሁኔታ እንመለከታለን። በመሆኑም ከነሱ አስተሳሰብና የአኗኗር ስልት ውጭ ያለ በሙሉ ሰው አይመስላቸውም። ማንኛውም ሰው ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንደሚያስፈልገው የተረዱና የሚረዱ አይደሉም። በተለያዩ መልኮች የሚገለጸው ፍቅር ጭንቅላታቸው ውስጥ የሌለ በመሆኑ ለሰው ልጅ ርህራሄ የላቸውም። ኮመን ሴንስና ኢንቲዩሽን ከጭንቅላታቸው በሙሉ ተሟጠው ያለቁ ስለሆነ ስሜት የላቸውም። የሚመስላቸው እነሱ ጠላቴ ነው ብለው የሚገምቱትን በሙሉ እያሰቃዩ የሚኖሩና፣ በዚህም የሚደሰቱ በመሆናቸው፣ ፍልስፍና ካልነው ይህንን የኑሮአቸው ፍልስፍና አድርገውታል። ከዚህ ስንነሳ ዛሬ በአገራችን ምድር አፍጦ አግጦ የሚታየው የተበላሸ ሁኔታ፣ ህዝባችን ለድህነትና ለረሃብ መጋለጥ፣ ይባስ ብሎ በ21ኛው ክፍለ- ዘመን ተስቦና ኮሌራ ተስፋፍተው ብዙ ህዝብ ሲፈጁና ከተማው በሙሉ በቆሻሻ እቃ ሲሞላና፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ ከቆሻሻ መጣያ ቦታ እየፈለገ ሆዱን ለመሙላት ሲታገል ስናይ፣ ይህ ሁሉ ሊገለጽ የሚችለው እንዲያው በመልካም አስተዳደር እጦት ሳይሆን አገሪቱ ሰብአዊነትን ባጡና ሌላው ፍጡር በሙሉ ሰው በማይመስላቸው ሰዎች እንደምትተዳደር ነው። አስተሳሰባቸውና ድርጊታቸው በሙሉ የህብረተሰብንና የተፈጥሮን ህግ የሚፃረርና አንድ ህዝብ በረጋ መንፈስ ታሪክን እንዳይሰራ የሚያግድ እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው።

ተፈጥሮአዊ ወይም ዩኒቨርሳል ህግ ምን ይለናል !

ታላቁ የሮማውያን የመንግስት ፈላስፋ ሴናካ የሚባለው ታላቅ መሪ እንደሚለን፣ ማንኛውም ህብረተሰብአዊ ችግሮችና ፖላቲካዊ ፍጥጫዎች የሚከሰቱት የተፈጥሮን ህግ ባለመረዳት ነው ። የተፈጥሮን ህግ ለመረዳት የማይችል ሰው ደግሞ የግዴታ የአንድን ህበረተሰብ ጤናማና ሚዛናዊ አካሄድን ያዘበራርቃል። የዕድገትና የሰላም ጠንቅ ይሆናል። አንድ ህብረተሰብ ዕውነተኛ ስልጣኔን እንዳይጎናጸፍ ልዩ ልዩ መሰናክሎችን በመፍጠር አንድ ህዝብ ፍዳውን እያየ እንዲኖር ያደርጋል።

ቀደመ ብዬ ለማሳየት እንደሞከርኩት የሰው ልጅ ከማሰብ ኃይል ጋር የተፈጠረ ነው። የማሰብ ኃይሉ በተለያየ መልክ የሚገለጽ ሲሆን፣ ይህንን በተለያየ መልክ የሚገለጸውን ግን ደግሞ በአንድ አጠቃላይ ውስጣዊ ኃይል የሚገዛውን ሎጂካዊ አስተሳሰብ በመጠቀም የማሰብ ኃይሉን በማዳበር ተፈጥሮን በመለወጥና በማሻሻል መኖሪያ ያደርጋታል። የማሰብ ኃይሉን በመጠቀም የተዘበራረቀውን ሁኔታ በምሁራዊ ኃይል መልክና ስርዓት በመስጠት በአንድ በኩል በሰዎች መሀከል የሚኖረው ግኑኝነት ሚዛናዊነት እንዲኖረው ያደርጋል፣ በሌላ ወገን ደግሞ የተፈጥሮን ህግ በመረዳት በተፈጥሮና በሱ መህከል ሊኖር የሚገባውን መደጋገፍ በመገንዘብ በተፈጥሮ ላይ ብዙም አደጋ ከማድረስ ይቆጠባል። ተፈጥሮን የበለጠ ቅርጽ እየሰጠና እየተንከባከበ ወደ ምድራዊ ገነትነት ይለውጣታል። በዚህ ብቻ ሳይቆጠብ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠርና በማዳበር ስራውን ያቃልላል፤ እንዲያም ሲል በተወሰነ ሰዓት የበለጠ ምርትን ማምረት ይችላል። ይህ ዐይነቱ የማሰብ ኃይል ከዘርና ከቀለም ባሻገር ለሰው ልጅ ሁሉ የተሰጠ ጸጋና ከሰው ልጅ ጋር አብሮ የሚፈጠር ነው። ይሁንና ግን እያንዳንዱ ሰውና ህብረተሰብ ይህንን ተፈጥሮአዊ ጸጋ ለመጠቀም እንዳይችል የሚያግዱት የተወሳሰቡ ህብረተሰብአዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ግኑኝነቶች በየአገሮች ውስጥ አሉ። በአለንበት በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ደግሞ የአንድ ህዝብ የማሰብና የመፍጠር፣ ወይም ደግሞ ያለማሰብና ያለመፍጠር ኃይል ከውጭው ዓለም ጋር ባለን ግኑኝነት የሚወሰን ነው። የየአገሮች ባህሎች፣ ኢኮኖሚዊ ግኑኝነቶና ፖለቲካዊ አወቃቀሮች በጎሎባል ካፒታሊዝም ውስጣዊ ኃይል ስለሚወሰኑ፣ አንድን አገር በተስተካከለና በሳይንሳዊ ዘዴ ለመገንባት እጅግ አስቸጋረ እየሆነ የመጣንበትን ሁኔታ እንመለከታለን። በሌላ አነጋገር በብዙ መልክ የሚገለጸው ግሎባል ካፒታሊዝም የሃሳብ ጥራትን ከማምጣትና የማሰብ ኃይልን ከማዳበር ይልቅ እያዘበራረቀውና የሰውን ልጅ ወደ አልባሌ ተግባርና ወደ አረመኔያዊነት ድርጊት እየመራው እንደሆነ በምድር ላይ የሚታየውን ለተከታተለና ራሱን ለጠየቀ በቀላሉ መልስ ሊያገኝ ይችላል። በተለይም ደግሞ እንደኛ ባለው ምሁራዊ ኃይል እጅግ ደካማ በሆነበት አገርና፣ ሎጂካዊና የተወሳሰበ አስተሳሰብ ቦታ በሌላቸው አገሮች ውስጥ በተወሳሰበ መልክ ከውጭ የሚመጣውን አገርንና ህብረተሰብን አፍራሽ አስተሳሰብ ለመዋጋት እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል። ከዚህም በላይ የዓለም ማህበረሰብ ሁሉ በአንድ ፎርሙላ መመራት አለባቸው እየተባለ በሚሰበክበት ዓለም ውስጥ ውሸትን ከዕውነት፣ የሰይጣኑንመንገድ ከመንፈሳዊው ለመለየት በጣም ያዳግታል።

ከዚህ ስንነሳ የዩኒቨርሳል ህግ ወይም ተፈጥሮአዊ የማሰብ ኃይል ፈሩን ሊለቅ የሚችልበትን ሁኔታ ጠጋ ብለን እንመልከት። ለአንድ ሰው የማሰብ ኃይል መዳከም እንዲያም ሲል በአልባሌ ነገሮች መወጠርና ወደ ጨካኝነት ማምራት ብዙ ምክንያቶችን መስጠት ይቻላል። በተፈጥሮ ውስጥ ከአፈጣጠር ጋር የሚከሰተውን የማሰብ ኃይል ድክመትና በየአገሮች ውስጥ ያለውን የባህል ሁኔታ ወደ ጎን ትተን፣ ሌሎች የንቃተ-ህሊናችንን እንዲያም ሲል የማሰብ ኃይላችንን መዳከም የሚወስኑ ነገሮች ላይ እናተኩር። በመጀመሪያ ደረጃ በተለይም በዘመኑ በብዙ አገሮች የታዩትንና እንደትዝታ የሚወሩትን የጭካኔ እርምጃዎችና የግፍ አስተዳደሮች ለተመለከተ አረመኔያዊነት በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተስፋፋ የመጣውና መንግስታትም የበለጠ ጨቋኝ መሆን የቻሉት ከንቃተ-ህሊናቸው ጋር ሊስተካከል ከማይችል ቲክኖሎጂ፣ የጦር መሳሪያዎችና ቢሮክራሲያዊ አስተዳደሮች ጋር በመተዋወቃቸው ነው። በሌላ አነጋገር በካፒታሊዝም መስፋፋት በየአገሩ እየተንጠባጠበ የገባው ዘመናዊነት በተለይም በከፍተኛ የህብረተሰብ ሂራርኪ ውስጥ የሚገኘውን የሀብረተሰብ ክፍል አረመኔያዊ፣ ሀብት አውዳሚና አገር አፍራሽ እያደረገው እንደመጣ መገንዘብ እንችላለን። ይህም ማለት ዘመናዊነት ጭንቅላትን ብሩህ ከማድረግና ልብንም ርህሩህ አድርጎ ህብረተሰብአዊ ኃላፊነት እንዲሰማ ከማድረግ ይልቅ፣ አንዱ ሌላውን የሚንቅበትና፣ ራሱ ጥሩ ኑሮ እየኖረ ሌላው ደግሞ ተጨማደደና የተዝረከረከ ኑሮ እንዲኖር የሚያደርግበትን ሁኔታ እንመለከታለን። ይህ ዐይነቱ በብዙ አገሮች የሚታየው የጭቆናና ግፍ አስተዳደር በየአገሮች ውስጥ ያለው ህዝብ የማሰብ ኃይሉን እንዳያዳብር አፍኖ በመያዝ ለድህነት ዋናው ምክንያት ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ ፓለቲካዊ ንቃተ-ህሊና፣(Political Consciousness ) ህብረተሰብአዊ ንቃተ-ህሊና፣(Soical Consciousness) አካባቢን የመንከባከብ ንቃተ-ህሊና፣(Ecological Consciousness) ባህላዊ ንቃተ-ህሊና፣(Cultural Consciousness) ታሪካዊ ንቃተ-ህሊና፣(Historical Consciousness)… ወዘተ. እነዚህን የመሳሰሉት ለአንድ ህብረተሰb እንደ ማህበረሰብ ተስማምቶ እንዲኖር የሚያደርጉትና ታሪካዊ ነገሮችን እንዲሰራ የሚያስችሉት በብዙ መልክ የሚገለጹ ዕውቀቶች እንዳይዳብሩና የህብረተሰብ ኖርሞች ሆነው ማንኛውም ዜጋ እንዲከተላቸው ማድረግ አልተቻለም። በዚህም ምክንያት የተነሳ ውንብድና፣ ሸፍጠኝነት፣ በስነ-ስርዓት አለመስራት፣ ፕሪንሲፕል-አልባ መሆን፣ ለዚህም ለዚያም ነገር መስገብገብ፣ አለሁ አለሁ ማለት፣ ስንትና ስንት ወንጀል እየሰሩ አልሰራሁም ማለት፣ ወይም የሰራሁት አንድ ነገር አሳስቶኝ ነው ማለት ህብረተሰባዊ ኖርሞች በመሆን የአንድን ህብረተሰብ የተወላገደ ጉዞ ደንጋጊ መሆን በቁ። ይህ ዐይነቱ ባህርይ በብዙ ያለደጉ አገሮች፣ በተለይም ደግሞ በኛ አገር ጎልቶ የታያና የሚታይ በብዙ መቶ ሺህ ለሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት መጥፋትና ለተፈጥሮ ሀብት መውደም ምክንያት የሆነ ነው። ዛሬ በአገራን ውስጥ ያለውንም አረመኔያዊ አገዛዝ ከዚህ ዐይነቱ ሁኔታ ጋር ማያያዝ ይቻላል። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ባልተስተካከለ የኢኮኖሚ ዕድገትና ከታች ወደ ላይ በጥናት ባልተደራጀ መንግስታዊ አወቃቀር በመጠናከር አንድ ህብረተሰብ ፈሩን እንዲለቅ ሊደረግ ቻለ።
ከዚህ ስንነሳ በመሰረቱ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ህዝብ ንቃተ-ህሊና መዳበር ሊወሰንና ህዝቡም ያለውን ተፈጥሮአዊ ፖቴንሺያል ሊጠቀምና፣ ጤናማና የሚተሳሰብ ማህብረሰብ ሊገነባ የሚችለው መንግስታዊ አወቃቀርና የፖለቲካው ሁኔታ መልክ ሲይዙ ብቻ ነው። የአሳ መግማት የሚጀምረው ከጭንቅላቱ ነው እንደሚሉት አነጋገር፣ ንቃታ-ህሊናው እጅግ ደካማ የሆነ ወይም ተሟጦ ያለቀ፣ ዓላማው አንድን ማህብረሰብ መገንባትና ህብረተሰብአዊ ስምምነት ሳይሆን ስግብግብነትን የሚያስቀድም፣ በውጭ ኃይል ተማምኖ ከውስጥ የሚነሱ ብሶቶችን ለማፈን እችላለሁ ብሎ የሚገምት ኃይል በታሪክ አጋጣሚ ስልጣንን በሚጨብጥበት ጊዜ አስተሳሰቡና ድርጊቱ ሁሉ ህብረተሰቡን መረበሽ ይሆናል። የአንድ ህዝብ አስተሳሰብ በመፍጠር ላይና የራስን ኑሮ በማሻሻል እንዳያተኩር የሆነ ያልሆነ ተንኮል በማውጠንጠን የሰፊው ህዝብ ጭንቅላት በአልባሌ ነገሮች እንዲጠመድ ያደርጋል። ኑሮው ጭንቀትና ሀዘን ብቻ እንዲህን በማድረግ የራሱን የግዛት ዘመን ለማርዘም የሆነ ያልሆነውን በህግ መልክ ተግባራዊ በማድረግ በአጠቀላይ ሲታይ አንድ ህብረተሰብ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሊዳረስ የሚችል ብሄራዊ ሀብት(National Wealth) እንዳይዳብር ያደርጋል። ይህንን ዐይነቱን አንድን ህብረተሰብ ማወላገድ በአገዛዙ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ኢንስቲቱሽኖችና ሽብርተኝነትን የሚፈለፍሉና በተለያየ መልክ የሚዶግሙ የካፒታሊስት አገር የስለላ ድርጅቶችም ዋና ተግባር ነው። በዚህ መልክ በተሰበጣጠረ ግኑኝነት የተነሳ አንድ ህዝብና አንድ አገር ልኡልናቸውን ያጣሉ። በዘለዓለማዊ ትርምስ ውስጥ እንዲኖሩ ይገደዳሉ። ድህነት፣ ተደጋጋሚ ረሀብ፣ በአጠቃላይ ሲታይ አንድ ህዝብ ለህይወቱ የሚያስፈልጉት መሰረታዊ ነገሮች እንዳይሟሉ ማድረግ የተፈጥሮ ህግ ሆነው ስለሚወሰዱ ጠቅላላው ህዝብ በልመናና በመጽዋት እንዲኖር ይገዳድል። በዚህ መልክ የአንድ ህዝብ የመፍጠር ኃይል ይዳፈናል። ንቃት-ህሊናውን ለማዳበር አቅም አይኖረውም። በተመጣጠኑ ምግቦች ዕጥረት በግልጽ የምናየው ሰውነቱ ብቻ ሳይሆን የማሰብ ኃይሉም ይዳከማል።

ለዚህ ዐይነቱ ለብዙዎቻቸን በግልጽ ከማይታየን የተሳሰረና ጭንቅላታችንን አፍኖ ከያዘን ሁኔታ መውጣት የሚቻለው ጠቅላላው ህዝብ የመንፈስ ነፃነት ሲያገኝና፣ እንደልብም መንቀሳቀስ ሲችል ብቻ ነው። በሌላ አነጋገር የማሰብ ኃይሉን ማዳበር ሲችልና ራሱን ሲያገኝ ብቻ ነው። አንድ ህዝብ የማሰብ ኃይሉን ሲያዳብርና በሁሉም አቅጣጫ በተወሳሰበ መልክ ማሰብ ሲችል ለማንኛውም ጭግር መልስ ማግኘት ይችላል። አዳዲስ ችግር ፈቹ ቴክኖሎጂዎችን ያፈልቃል። ይህ ማለት ምን ማለት ምን ማለት ነው ? ዛሬ በዓለም ላይ የምናያቸውና የምንጠቀምባቸው ቴክኖሎጂዎችና ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የምንሽከረከርባቸው መመላለሺያዎች ከሰማይ ዱብ በለው የወረዱ ሳይሆን በሰው የማሰብ ኃይል የተፈጠሩ ናቸው። በተፈጥሮ ውስጥ ብዙ ተፈጥሮአዊ ነገሮች ቢገኙም እነዚህን አውጥተን በኃይል (Energy)አማካይነት ወደ መጠቀሚያነት መለወጥ የምንችለው በማሰብ ኃይላችን ብቻ ነው። ኃይል በተፈጥሮ ውስጥ ያለ ቢሆንም እሱን አባዝተን ለመሳሪያ መስሪያ መጠቀም የምንችለው እንደዚሁ በማሰብ ኃይላችን ነው። በሌላ ወገን ግን ይህንን የዩኒቨራሳል ህግ ያልተረዳና ለመጠቀም የማይችል አገዛዝም ሆነ ህዝብ እጣው ድህነትና ረሃብ፣ እንዲሁም ኑሮው መዘበራረቅ ይሆናል። እንደ አገራችን ባለ ሁኔታ የአገዛዙ የፖለቲካ ዘይቤ ተንኮል መጠንሰስ በሆነበትና፣ ስልጣን ላይ ለመቆየት ሲባል ብቻ አንዱን ጎሳ ከሌላው ጎሳ ጋር ማጣላት፣ ወይም አንዱን ሃማኖት ከሌላው ጋራ በማጋጨት በከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ አማካይነት ለዘለዓለም ስልጣን ላይ ለመቆየት መሞከር በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ያለን ውስጣዊ ኃይልና የተፈጥሮን ሀብት ያወድማል። በዚህም ምክንያት የተነሳ ጠቅላላው ህበረተሰብ በአልባሌ ነገሮች ስለሚጠመድና ምክንያቱን ሳያውቀው ርስ በርሱ ስለሚነታረክ ተፈጥሮ የሰጠውን ውስጣዊ የማሰብ ኃይሉን እንዳይጠቀምበት ይገደዳል። ይህ ዐይነቱ አካሄድ ኃይል ማወደሚያ ህግ (The Law of Energy Destruction) ይባላል። በሌላ አነጋገር ጠቅላላው የማሰብ ኃይል ህብረተሰብንና የተፈጥሮን ሀብት በማውደም ላይ የሚያተኩር ስለሚሆን ህብረተሰብአዊ ሀብት(National Wealth)እንዳይፈጠር መንገዱን ሁሉ ይዘጋል። አንድ ህዝብ የሰለጠነ ኑሮ እንዳይኖር ያግዳል። ይህ ዐይነቱ የኃይል ውድመት የሰውን የማሰብ ኃይል ድክመት የሚመለከት እንጂ በተፈጥሮ ውስጥ ያለን ኃይል አይደለም። በፊዚክስ ህግ ኃይል(Energy) ሊፈጠርና ሊወድም አይችልም። ተፈጥሮአዊ ኃይል ከአንድ ሁኔታ ወደ ሌላ ሁኔታ የሚለወጥ ብቻ ነው። ይሁንና ግን ኃይልን በስነ፟-ስርዓት ካለመጠቀም የተነሳ መባከን ይፈጠራል። በሌላ አነጋገር እንደዚሁ በተፈጥሮ ውስጥ ያለን ኃይልና ከአንድ ሁኔታ ወደሌላው የሚለወጠውን ኃይሉ ሳይቀንስ ለመጠቀም ከተፈለገ የግዴታ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች መፈጠር አለባቸው። ይህ ዞሮ ዞሮ የሰውን ልጅ የማሰብ ኃይል ሁኔታ ይጠይቃል። በአጠቃላይ ሲታይ ለሰው ልጅ ዕድገትና በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ስምምነትና ሰላም መኖር የዩኒቨርሳል ህግ ወሳኝ ሲሆን፣ የዩኒቨርሳል ህግን መረዳት ደግሞ በተለይም የማንኛውም ለፖለቲካ ስልጣን እታገላለሁ የሚል ግዴታ ነው። ይህንን ህግ ሳይረዳ ስልጣን ላይ የሚወጣ የግዴታ ህብረተሰቡን አንድገና ለአንድ ሺህ ዐመት በጨለማ ዓለም ውስጥ እንዲኖር ያደርገዋል።

ወደ ሁለተኛው፣ በሰውና በተፈጥሮ መሀከል ሊኖር የሚገባውን ግኑኝነትና መደጋገፍም መረዳት የምንችለው የማሰብ ኃይልን ከፍተኛ ቦታ ስንሰጠው ነው። የሰው ልጅ ተፈጥሮን ይፈልጋታል እንጂ ተፈጥሮ ሰውን አትፈልገውም። ብዙም ሳናስብ(Intutively) የሰው ፍጡርም ሆነ እንስሳ ሁሉንም ነገር ሊያገኙ የሚችሉት ከተፈጥሮ ነው። ለመተንፈስ አየር፣ ለመጠጣትና ለመታጠብም ሆነ ለመቀቀያ ውሃ፣ አፍርን ለማብቀያ ብቻ ሳይሆን ወደ ማሺንነት የምንለውጣቸው ጥሬ- ሀብቶች በሙሉ ከተፈጥሮ ውስጥ የሚገኙ የሰው ልጅ ሳይፈጥራቸው በጸጋ የተሰጡ ናቸው። እነዚህን ግን በስነ-ስርዓት እያወጡና በተፈጥሮ ላይ ሚዛናዊንት እንዳይጓደል መጠቀም የሚቻለው የማሰብ ኃይላችንን ስንጠቀም ብቻ ነው። እንዲያው በጭፍንና በጉልበት እየተመካን በተፈጥሮ ላይ ዘመቻ ብናደርግ ተፈጥሮ ራሷ አንድ ቀን የቂም በቀሏን ትወጣለች። በሌላ አነጋገር ዝም ብለን ዛፍን የምናወድም ከሆነ የግዴታ ለዝናብ እጦት ወይም አለመዝነብ አመቺ ሁኔታ እንፈጥራለን። በተጨማሪም አንድ ቀን ኃይለኛ ዝናብ በሚዘንብበት ጊዜ መሬቱ በዛፍ መቆረጥ በመራቆቱ የተነሳ የመሬቱ ፍሬያማ አካል በጎርፍ በመጠራረግ እንደገና ዘር ዘርቶ ለማብቀል የማይቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል። ከዚህም ባሻገር በየቦታው ለጊዜው ሀብት ለማካበትና በአንድ ጊዜ ቱጃር ሆኖ ለመገኘት ሲባል ከዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር በመስማማትና በመፈራረም በሳይንስ ያልተጠና የማዕድን አወጣጥ በተፈጥሮና በሰው ህይወት ላይ ከፍተኛ አደጋ ያስከትላል። በዚህም ምክንያት የተነሳ አንድ አካባቢ ስለሚመረዝ ቦታዎች ከብት የማይረባባቸው፣ ሰው የማይኖርባቸውና ምንም ነገር የማይበቅልባቸው ይሆናሉ።

ይህ ብቻ ሳይሆን አንድ አገዛዝ በዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው በሚባለው እየተመከረና እየታገዘ ከተፈጥሮና ከህብረተሰብ ህግ ጋር የማይጣጣም የኢኮኖሚ ፖሊሲ አውጥቶ ተግባራዊ የሚያደርግ ከሆነ የግዴታ የሰው የማሰብ ኃይል እንዲዘበራረቅ ያደርጋል። ውስጣዊ ኃይሉ ወደ አንድ አቅጣጫ እንዲያተኩር በማድረግ የመፍጠር ኃይሉ እንዲሟጠጥ ያደርጋል። በዚህም ምክንያት የተነሳ በተፈጥሮ ውስጥ ያለን ሀብት በማሰብ ኃይሉ እየታገዘ ህብረተሰብአዊ ሀብት እንዳይፈጠር ያደርጋል። በአገራችን ምድር ለሃያ አምስት ዐመታት ያህል ተግባራዊ መሆን የጀመረውና በገበያ ኢኮኖሚ ስም የሚካሄደው ፖሊሲ ዋና ዓላማው ህብረተሰብን ማዘበራረቅ ብቻ ሳይሆን፣ እያንዳንዱ ዜጋ የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ ተረድቶ ቆንጆ ቆንጆ ነገሮች እንዳይሰራ የተወጠነ የኢምፔሪያሊስቶች ሴራ ነው። ሁሉ ነገር በገበያ ኢኮኖሚ ዙሪያ አካባቢ የሚሽከረከር ከሆነ የሰው ጭንቅላት ገንዘብ በማግኝት ይጠመዳል። ጠቅላላው የኑሮው ፍልስፍና ገንዘብ ወደ ማግኘት ስለሚለወጥ አብዛኛው ህዝብ ተፈጥሮ የሰጠውን በልዩ ልዩ መልክ የሚገለጽውን የማሰብ ኃይሉን እንዲያጣ ይገደዳል። በመሆነም ከሰብአዊነት ይልቅ አረመኔያዊነት በመስፋፋት አንድ ህዝብ ወደ መበላላት ያመራል። በተለይም ደግሞ እንደዚህ ዐይነት ናላው የዞረ አገዛዝ ስልጣን ላይ ሆኖ የሱም መስገብገብና ድርጊቱ እንደምሳሌ በሚወሰድበት አገር አንድ ህዝብ አቅጣጫውን እንዲስት ይገደዳል። ግብረ-ገብነትና ስነ-ምግባር የህብረተሰቡ መለኪያዎች መሆናቸው ቀርቶ ሀብት ማካበትና በማቴሪያል መሸብረቅ መለኪያዎች ይሆናሉ።

ከዚህ ስንነሳ በወያኔ አገዛዝ በአገራችን ምድር ተግባራዊ የሆኑት የኢኮኖሚም ሆነ የጎሳ ፖለቲካዎች በሙሉ ከፍተኛ የሆነ የሀብት ውድመት እንዲፈጠር ነው ያደረጉት። እያንዳንዱ ዜጋ የማሰብ ኃይሉን በመጠቀም ርስ በርሱ የተሳሰረ ግን ደግሞ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተደገፈ ህብረተሰብአዊ ሀብትና፣ ርስ በርሱ የሚደጋገፍና የሚከባበር ህብረተሰብ እንዳይፈጠርና እንዳይገነባ ነው ያደረገው። በተለይም የብሄረሰብ መብት የሚባለውና በክልል ደረጃ የተዋቀረው የከፋፍለህ ግዛ „ፖለቲካ“ ዋና ዓላማው ይህንን በተለያዩ ጎሳዎች መሀከል ሊኖር የሚችለውን የዕውቀትና የሃሳብ መለዋወጥ፣ እንዲያም ሲል የካፒታልና የሰው ኃይል እንቅስቃሴ እንዳይኖር ያገደ ነው። በመሆኑም ጠቅላላው ህዝብ አንድ ላይ ሆ ብሎ በመነሳት ብሄራዊ ምወይም አገር-አቀፍ በሚባሉ ተግባሮች ላይ እንዳይሰማራ ያገደው እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው። ከተማዎችን እንዳይገነባ፣ በየክልሉ የሰራ ክፍፍል በማዳበር ሰፋ ያለ ገበያ እንዳይገነባ፣ በአጠቃላይ ሲታይ ጠቅላላው ህዝብ እዚያው ቀጭጮ እንዲቀር የሚያደርግ ፖሊሲ ነው ባለፉት ሃያ አምስት ዐመታት ተግባራዊ የሆኑት። በዚህ ዐይነቱ የክልልና የማሰብ ኃይልን የማወደም ዕቅድና ተግባር የወዳጅ አገሮች የሚባሉት እንደ እንግሊዝና አሜሪካ እንዲሁም ሌሎች የምዕራብ አገሮች ተሳትፈውበታል። አገዛዙን በመሳሪያም ሆነ በገንዘብና በተለያዩ የተንኮል ዘዴዎች በማሰልጠንና በመደጎም ጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ በራሱ ተነሳሽነትና ዕውቀት አንድ ጤናማና ሚዛናዊ ያለው ህብረተሰብ እንዳይመሰረትና እንዳይገነባ አድርገውታል። በርዳታ ስም በመግባትና በመሰግሰግ አቅመ-ቢስ አድርገውታል። በዚያው መጠንም አገሪቱ ወደ አስረሽ ምቺው ተለውጣለች። ሰፊውን ህዝብ ቡና አምራች፣ አበባ ተካይ፣ የሸንኮራ አገዳ አብቃይና ስኳር አምራች በማድረግ ለምዕራቡ ዓለም የጥሬ-ሀብት አቀራቢ አድርገውታል። ባጭሩ የባሪያ ስራ እንዲሰራና ዘለዓለሙኑ እንደ ነፃና ኩሩ ዜጋ ሆኖ ራሱን አውቆ እንዳይኖር አግደውታል። ስለሆነም በአገራችን ምድር ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ ሀብት ሊወድም የቻለውና ህዝባችንም የማሰብ ኃይሉን ተጠቅሞ ቆንጆ አገር እንዳይገነባ የተደረገው በዚህ ዐይነቱ የእከክልኝ ልከክልህ፣ በውስጥና በውጭ ኃይሎች መሀከል በተፈጠረው መተሳሰርና መተጋገዝ ነው። ከዚህም አንፃር ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ስልጣንን የተቆናጠጠው የወያኔው አገዛዝ የውጭ ቅምጥ ነው ማለት ይቻላል። ጠቅላላውን የኢትዮጵያን ህዝብም ሆነ የትግሬን ብሄረሰብ የሚወክል አይደለም። በከፍተኛ ደረጃ የተፈጥሮ ሀብትና የሰውን ልጅ የማሰብ ኃይል ያወደመና፣ አካሄዱና ተግባራዊ ያደረጋቸው ፖሊሲዎች በሙሉ ዩኒቨርሳል የሆነውን የሰውና የተፈጥሮ፣ እንዲሁም የህብረተሰብን ህግ የሚጻረሩ እጅግ አደገኛ ድርጊቶች ናቸው ማለት ይቻላል። በ1930ዎቹ ዓመታት የጀርመን ናዚዎች ተግባራዊ ካደረጉት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር እንኳን የቅንጣትም ያህል የሚወዳደር አይደለም። እጅግ በጠባብ ስሜት በመወጠር የሶስት ሺህ ዐመት ታሪካዊ ቅርስ እንዲወደም ያደረገና፣ በተለያዩ መልኮች የሚገለጹ አጸያፊ ድርጊቶች እንዲስፋፉና፣ የአብዛኛው ህዝብ የኑሮ ፍልስፍና እንዲሆን ያደረገ ተፈጥሮአዊ ህግን የሚጻረር ነው። በህብረተሰብአችን ውስጥ የጨአት መቃም መስፋፋት፣ የሴተኛ አዳሪዎች ቤት መስፋፋትና በዝሙት ዓለም ውስጥ መዋኘት፣ የአገሪቱ ሀብት ሊሸከም የማይችለውን ውድ ውድ መጠጦችና አሸብራቂ ዕቃዎች እያመጡ ሀብት ማውደምና ታዳጊውን ትውልድ እንዲባልግ ማድረግ… ወዘተ. እነዚህ ሁሉ የአንድን ህብረተሰብ ጤናማና ሚዛናዊ አገነባብ የሚጻረሩ ናቸው። አንድ ህብረተሰብ ተከታታይነት(Sustainable) እንዳይኖረው የሚያደርጉ ናቸው። የህብረተሰቡ ኑሮ የተዘበራረቀ እንዲሆን በማድረግ ለበሽታ የሚዳርጉት ናቸው። ኃይሉን የሚሟጥጡ ናቸው።

ይሁንና ግን ህዝባችን ብዙ ግፍ እየደረሰበት፣ በምድር ላይ የሚታየው እጅግ የሚዘገንና ህዝባችንም የባሰውኑ በድህነት ዓለም ውስጥ በተወረወረበትና በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ በረሀብ አለንጋ በሚገረፍበት አገር ውስጥ አገዛዙና ካድሬዎቹ፣ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ኩሙኒቲው የሚባሉት የአምባገነኖች የጀርባ አጥንት የሚነግሩን በአገራችን ምድር ተዓምር እየተሰራ መሆኑን ነው። ህዝባችንና አገራችን በታሪካችን ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የኢኮኖሚ ዕድገትና ብልጽግና እያዩ ናቸው ነው ብለው የሚነግሩን። ህዝባችን የሚኖረው በአሸበረቁ ቤቶች፣ በጋርተን በተከበቡ ከተማዎች፣ መንደሮችና ከተማዎች በልዩ ዐይነት የትራንስፖርቴሽን መገናኛዎች በመገናኝት ህዝባችን በምድር ላይ የገነት ኑሮን እየኖረ ነው እያሉ ለማሳመን የሚሞክሩት። ምንም ስለኢኮኖሚ ዕድገትና ስለ አገር ግንባታ ምንነት የማይረዱና፣ አንድስ ህብረተሰብ በምን መልክ መደራጀትና መገንባት እንዳለበት ለመገንዘብ የማይፈልጉ እዚህ አውሮፓና አሜሪካ የሚኖሩ የአገዛዙ አቀንቃኞች የሚሉንም ይህንን ነው። አገሪቱ ሌሎች አደጉ የሚባሉ አገሮች ደረጃ ለመድረስ የቀራት ትንሽ ጊዜ ነው እያሉን ነው። ይህንን ዐይነቱን ነገሮችን እየገለበጡ ማየት ከድንቁርናና ከጭንቅላት መዛግ ጋር ማያያዝና ማገናኘት ይቻላል። የግሪክ ፈላስፎች የሚሉት አንድ ግሩም አባባል አለ። ይኸውም ጭንቅላት ከታወረ ዐይን ማየት አይችልም የሚለው ፍልስፍናዊ አባባል ነው። በሌላ አነጋገር ጭንቅላቱ ሰብአዊ በሆነ ትምህርት ያልተዋቀረ ስለሰው ልጅና ስለተፈጥሮ ምንነት ሊረዳ አይችልም። የኑሮ ፍልስፍና ስሌለውም ኑሮው ሁሉ ገንዘብ ከማግኝት የሚያልፍ አይደለም። ስለዚህም ከእንደዚህ ዐይነቱ ጭንቅላታቸው ከታወሩ ሰዎችና ስለ ሰውልጅ ምንነት ከማይረዱ ኢትዮያውያን ምንም የምንጠብቀው ነገር በፍጹም ሊኖር አይችልም። ይህንን ካልኩኝ በኋላ ወደ ተጨባጩ ሁኔታ ልምጣ።

ወያኔ ያልገባውና ሊገባው የማይችለው ነገር !

እስካሁን ድረስ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለብዙዎቻችን እንቆቅልሽ የሆነብን ነገር እንዴት አድርጎ የጠቅላላው ኢትዮጵያ የስልጣኔ ምንጭ ከሆነ አካባቢ ብቅ ያሉ ግለሰቦችም ሆነ ቡድኖች በተቀረው ህዝብ ላይ ሳይሆን በራሳቸውም ታሪክና ስልጣኔ ላይ እንደሚዘምቱ ነው። ሁላችንም አምነን የተቀበልነው ነገር ከአክሱም በፊትም ሆነ ከአክሱም ጀምሮ የነበሩት አገዛዞች ለዛሪዪቱ ኢትዮጵያ የስልጣኔ ምንጮች እንደሆኑ ነው። ወያኔዎች ግን ይህንን በመካድና የራሳቸውን ልዩ ዓለም በመፍጠር የተቀረይቱን ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን እያራቆቷትና ምስቅልቅሏን እያሳጧት ነው። ጠቅላላው ህዝብ የበደላቸው ይመስል ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበር በህዝባችንና በአገራችን ላይ ሁለ-ገብ ጦርነት አውጀውብናል። ራሳቸው በልዩ ደሴት ይኖሩ ይመስልና፣ በራሳቸው ጥረት ብቻ ታላቋን ትግራይ ይገነቡ ይመስል ከፍተኛ ዝርፊያ እያደረጉ ነው። የታሪክ ወንጀል እየሰሩ ነው።

ከዚህ ስንነሳ ወደ ሰሜኑ የውልቃይት ጽጌ ሁኔታ ስንመጣ እጅግ የሚያሳዝንም የሚያስቅም ሁኔታ እንመለከታለን። በመጀመሪያ ደረጃ ያ አካባቢ የወልቃይቶች እንደሆነ ራሳቸው አንዳንድ የትግሬ ምሁራንና የገዢው መደብ አባል የነበሩ አረጋግጠውታል። የትግሬ ክፍለ-ሀገር አካል ነው ብሎ ማውራት የተረት ተረት እንደማውራት ይቆጠራል። በሌላ ወገን ግን ወልቃይትና ጸገዴ ብቻ ሳይሆኑ፣ ጤናማ አስተሳሰብ ያለው ጠቅላላው አገራችን በዚያች ምድር የሚኖር ህዝብ ወይም የተለያዩ ብሄረሰቦች ሀብትና አገርም ነች። በተለይም ስለ ስልጣኔና ስለዕድገት፣ እንዲሁም ስለህብረተሰብና ስለ ህብረ-ብሄር ምስረታ፣ እንዲያም ሲል በአንድ ባንዲራ ስር ስለሚተዳደር ህዝብ የሚያወራ ይህ የኔ መሬት ነው፣ ያ ያንተ ነው ብሎ አንዱ ኢትዮጵያዊ በሌላው ላይ ሊዘምትበት አይችልም። በሌላ አነጋገር ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በጠቅላላው ኢትዮጵያ ምድር በመንቀሳቀስ ህጋዊ በሆነ መልክ፣ የአካባቢውን ህዝብ ሳይጋፋ፣ ሊሰራ፣ መሬት ሊከራይና እዚያው በመቀመጥ ቤት ሰርቶ ሀብት ሊያፈራ ይችላል። ፋብሪካዎች በማቋቋምና የስራ መስኮችም በመክፈት ማህበራዊና ህብረተሰብአዊ ግዴታውን ሊወጣ ይችላል። ይህ ጤናማ አካሄድ ለማንኛውም በአንድ አገር ውስጥ ለሚኖር ህዝብ ለዕድገቱ እጅግ አስፈላጊ ነው። ይህ የኔ ክልል ነው አትድረሰብኝ ቢል በራሱ ላይ ነው የሚፈርደው። የዕውቀትና የሀብት መንሸራሸር እንዳይኖር ነው የሚያደርገው። አካባቢው እንዳይለማና ቀሰ በቀስም ህብረተሰብአዊ መተሳሰርና መደጋገፍ እንዳይኖር ነው የሚያደርገው። በአጭሩ የዕድገትና የስልጣኔ ዕንቅፋት በመሆን አንድ ህዝብ ለዝንተ-ዓለሙ በጨለማ ዓለም ውስጥ እንዲኖር ያደርጋል። ከዚህ ስንነሳ በወልቃይት-ጸገዴና በትግሬ ብሄረሰብ መሀከል የረጅም ዐመታት መተሳሰር ያለና፣ በተለይም ከትግሬ እየመጡ እዚያው እየሰሩና ሀብት እያፈሩ መኖር የተለመደ ነገር ነው። ነግሩ መበላሽት የጀመረው ወያኔዎች ትግል ሲጀምሩና ታላቋን ትግሬ እንመሰርታልን ብለው ወደ ድል ካመሩና አዲስ አበባ ላይ ቁጥጥ ማለት ከጀመሩ ወዲህ ነው።

ይህንን ህልማቸውን ዕውን ለማድረግ ስልጣን ከመያዛቸው በፊትም በኋላ ሆነ በወልቃይት ጸገዴ ኗሪ ሰዎች ላይ አሰቃቂ ድርጊቶችን ፈጽመውባቸዋል። የህዝቡ ቁጥር እንዲቀንስ እንደ ቢልጌት ከመሳሰሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጥቁር ህዝብ ቁጥር እንዲቀንስ እጅግ አደገኛ ስራ ከሚሰሩ ከናጠጡ ሀብታሞች ጋር በመመሰጣጠር የአማራው ህዝብ ቁጥር እንዲቀንስ የስትሬላይዜሽን ፕሮግራም ተግባራዊ አድርገዋል። ብዙ ጥናቶችም እንደሚያመለክቱት ወያኔ ስልጣን ከያዘ በኋላ የአማራ ብሄረሰብ ቁጥር ወደ አራት ሚሊዮን ያህል ቀንሷል። ብዙ ለአቅመ አዳም የደረሱ ሴቶች የወር አበባቸውን እንዳያዩና እንዳያረግዙ ተደርገዋል። በተለይም በወንዶች ላይ አስቃቂ ግፍ ተፈጽሞባቸዋል። በጠራራ ጸሀይ የተገደሉት ዘመዶቻቸው ሬሳቸውን ለማንሳት ሲሯሯጡ የለም አሞራ ይብላው በመባል ተከልክለው የሰው ልጅ የአሞራና የጅብ እራት ተደርጓል። ይህ አጉል የጥላቻ ዘመቻ ሳይሆን በግልጽ የተካሄደ ነው። ይህ ድርጊት ፋሺስታዊ ድርጊት ነው። ሌላ ሊባል አይችልም።

ያም ሆነ ይህ፣ ይህ የወያኔ እጅግ አስቃቂ ድርጊትና ታላቋን ትግሬን የመገንባት ህልም ምንድነው የሚያረጋግጠው? በአጭሩ ይህ ድርጊታቸው የሚያረጋግጠው ድንቁርናቸውን ነው። የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ ያልተረዱ መሆናቸውን ነው። በመጀመሪያ ደረጃ፣ አዲስ አበባ ተቀምጦ የኢትዮጵያን ህዝብ ወክላለሁ ብሎ ወደ ውጭ ዕውቂያን ያገኘ አገዛዝ አንድን አካባቢ በመሸንሸን ወይም ቆርጦ በመውሰድ የትግሬ አካል ለማድረግ መሞከር ከማሰብ ኃይል ጉድለት የሚመነጭ እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ በታሪክ ውስጥ አንድ ወጥ የሆነ ብሄረሰብ ስልጣኔንና ዕድገትን ያመጣበትና የመነጠቀበት ሁኔታ በታሪክ ውስጥ ታይቶ አይታወቅም። የስልጣኔን ታሪክ በደንብ ለተከታተለ አገሮች ሊያድጉና የአንድ አገር ህዝብም የመፍጠር ችሎታው ሊዳብር የሚችለው፣ አንደኛው ከሌላው ህዝብ ወይም ብሄረሰብ ጋር ሲጋቡ፣ ሲቀላቀሉና የሃሳብና የባህል ልውውጥ ሲያደርጉ ብቻ ነው። ከማዕከለኛው ምስራቅ አገሮች፣ ሶሪያ፣ ኢራክና ሌሎች የአካባቢው አገሮች ከሁለትና ከሶስት ሺህ ዘመናት በፊት ከተለያዩ አካባቢ የፈለሱ ህዝቦችን በማስተናገድ ነው በዘመኑ ስልጣኔያቸውን የተገናጸፉት። የግብጽ ስልጣኔ የኋላ ኋላ ዕምርታን ሊያገኝ የቻለው በታላቁ አሌክሳንደርና፣ ከሌላ አካባቢ በመጡ ፈላስፎችና ምሁራን አማካይነት ነው። በስድስተኛውና በአምስተኛው ክፍለ-ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት አዮን በምትባለው ደሴት የግሪኩ ስልጣኔ ሲያብብ ከግብጽና ከህንድ በመጡ ዕውቀቶች፣ ነጋዴዎችና የዕደ-ጥበብ ሰዎች አማካይነት ነው። በአውሮፓ ምድር ውስጥም ከአስራአራተኛው ክፈለ-ዘመን ጀምሮ ቀስ በቀስ ስልጣኔ ዕምርታን ማግኘት የቻለው ከተለያዩ አካባቢዎች በመጡ ህዝቦች አማካይነት እዚያ ሲጋቡና ዕውቀታቸውን ሲያዳብሩ ነው። ጀርመንም ወደ ኋላ በቀረችበት በ18ኛውና በ19ኛው ክፍለ-ዘመን የፕረሽያ ነገስታት ወይም ሞናርኪዎች ከሆላንድና ከፈረንሳይ በሃይማኖት ሰበብ የተባረሩ አዋቂዎችን በማስተናገድና ቴክኖሎጂውን ውስጣዊ በማድረግ ነው ከሌሎች እርምጃዎች ጋር ተደምሮ ጀርመን በአንድና በሁለት ትውልድ ለማደግ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ ኢኮኖሚ መገንባት የቻለችው። ሆላንድ ራሷ በ17ኛው ክፍለ-ዘመን፣ እንግሊዝ ደግሞ እንደዚሁ በ18ኛው ክፍለ-ዘመን ከወጭ ዕውቀታቸውን ይዘው በመጡና እዚያው ኗሪ በሆኑ ይሁዲዎችና ሌላ ዘሮች አማካይነት ነው የኢንዱስትሪ አብዮት ባለቤት ለመሆን የበቁት። ዛሬ አሜሪካን ኃያል መንግስት ሆኖ ብቅ ማለት የቻለው ከተለያዩ አገሮች የመጡ ህዝቦችን በማስተናገድ ነው። ይህ ዐይነቱ ህብብረተሰብአዊ ዕድገት በተፈጥሮ ውስጥ ይታያል። ሞኖ ካልቸርድ የሆኑ ሰብሎች በቀላሉ ለተባይ ይጋለጣሉ። ሌላ የሚከላካለቸው የሰብልና የአትክልት ዐይነት ከወደመ የማደግና የመዳበር ኃይላቸው የመነመነ ነው። ለጊዜው በማዳበሪያ ኃይል ምርታማ ቢሆኑም ከጊዜ ብዛት በኋላ ምርታማነታቸው በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ ነው የሚመጣው። በቀላሉ ለተባይም ይጋለጣሉ። በሌላ አነጋገር መቀላቀልና መደጋገፍ የተፈጥሮ ህግና ለዕድገትም በጣም አመቺ ነው። በዚያውም መጠን ውስጣዊ ጥንካሬን ያገኛሉ።

ከዚህ ስንነሳ የወያኔ የአማራን ዘር እያጠፉ የራስን ግዛት ለማስፋፋትና ለማበጥ መሞክር በፍጹም ወደ ዕድገት የሚያመራው አይደለም። ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት የትግሬ ብሄረሰብ ከሌላው ህዝብ ጋር ሲጋባና ሲቀላቀል ብቻ ነው ጤናማ ዕድገትን ሊጎናጸፈ የሚችለው። የወያኔዎች ትልቁ ችግር ከውጭ ኢንዱስትሪ እያንጋጉ በመትከል ዕውነተኛ ዕድገትን የሚጎናጸፉ መስሏቸዋል። በታሪክ ውስጥ እንደተረጋገጠው የቴክኖሎጂ ምጥቀትና በኢንዱስትሪ ማደግ ኢቮሉሺናዊ አካሄዶች ናቸው። በምዕራብ አውሮፓ ውስጥ ከሞላ ጎደል ጤናማና የተስተካከለ ዕድገት ሊመጣ የቻለው የኢንዱስትሪ ዕድገት ከታች ወደ ላይ (Organic Grwoth) በመጓዙ ነው። በሌላ አነጋገር በመጀመሪያ የሚያማምሩ ከተማዎችን በመገንባት፣ ለህዝብ መኖሪያ ቦታዎችን በመስራት፣ የገበያ አዳራሾችንና ሌሎች ህዝቡን ሊሰበስቡና የፈጠራ ችሎታውን ሊያዳብሩ የሚችሉ ነገሮች በመስራት ነው።በመጀመሪያ ደረጃ በዕደ-ጥበብ አማካይነትና(Industrialiazation before Industrialization) በንግድ መዳበር የሀብት ክምችትን በማዳበር ነው ወደ ኢንዱስትሪ አብዮት መሸጋገር የቻሉት። በዚህም ምክንያት የተነሳና በከፍተኛ ደረጃ የህዝብና፣(Social Mobility) የሀብት(Capital) እንቅስቃሴ አማካይነት በቀላሉ ማደግና መበልጸግ ችለዋል። ይኸኛው ነው ጤናማው የካፒታሊዝም ዕድገት። በአንፃሩ ይኸኛውን ጤናማውን የዕድገት ጉዞ ያልተከተሉ እንደ ብራዚል፣ ሜክሲኮና ብዞዎች የአፍሪካ አገሮች ውስጥ መዘበራረቅ የሚታየውና ስርዓት ማጣትና የሀብት መባከን ሊፈጠር የቻለው ተፈጥሮአዊ የሚመስለውን የህብረተሰብ አገነባብና የኢኮኖሚ ዕድገት አካሄድ ባለመከተላቸው ነው። በሌላ አነጋገር በአንድ ወጥ ብሄረሰብና ከላይ ወደ ታች በሚጫን የኢንዱስትሪ ተከላና ጋጋታ ሚዛናዊ ዕድገት ሊመጣ አይችልም። የህዝቡም የመፍጠር ኃይል ውስን ስለሚሆን ቲክኖሎጂያዊ ምጥቀት ሊታይ አይችልም።

ስለሆነም አንድን ህዝብ እየጨረሱና መሬትን እየቆረሱ በመውሰድ ታላቋን የትግሬን ሬፑብሊክ እንመሰርታለን፣ ጠንካራ ኢኮኖሚ እንገነባለን፣ በዚህም አማካይነት የተቀረውን የኢትዮጵያ ክፍል የጥሬ-ሀብት አምራችና ላኪ በማድረግ አቀጭጨን እናስቀረዋለን የሚለው ህልም በፍጹም የሚሰራ አይደለም። ከዚህ ባሻጋር የአንድ አገር ዕድገት በኢንዱስትሪ መንጋጋት ብቻ የሚገለጽ አይደለም። የአንድ ህዝብ ዕድገት ሁለንታዊ ነው። በሚያማምሩ ከተማዎችና መንደሮች የሚገለጽ ነው። በቲያትርና በሙዚቃ እንዲሁም በሙዚየሞች የሚታይ ነው። በጋርደኖችና በተለያዩ የመገናኛ ማመላለሻዎች የሚገለጽ ነው። እንደዚህ ዐይነቱ በልዩ ልዩ መልክ የሚገለጸው ስልጣኔ ከአንድ ብሄረ-ሰብ በተውጣጣና ከሌላው ጋር ባልተቀላቀለ በፍጹም ተግባራዊ ሊሆን የሚችል አይደለም። ከዚህ ይልቅ ወደድንም ጠላንም ብዙ ብሄረሰቦችን የሚያሰተናግደውና፣ በተለያዩ ነገሮች የሚገለጸው፣ ግን ደግሞ የተሳሰረው የተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ጥሩና አገር ወዳድ መንግስት ካገኘ ከሃያ እስከ ሃምሳ ዐመት ባለ ጊዜ ውስጥ የተስተካከለ ዕድገትን ሊያመጣ ይችላል። የኦሮሞው፣ የጉራጌው፣ የጎሙ-ጎፋው፣ የወላይታው፣ የከፍቼው፣ የአማራውና የሌሎችም ጤናማ አስተሳሰብ ወደ ዕድገት አቅጣጫ እንዲመጣ ከታቀደና ከተጠና ባጭር ጊዜ ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሁለ-ገብ ዕድገት ሊታይ ይችላል። ይሁንና እነዚህ የተቀሩት የኢትዮጵያ ግዛቶች ለማደግና በአጭር ጊዜ ውስጥ ዕምርታን ለማግኘት ከምዕራብ አውሮፓ የካፒታሊስት አገሮች ቴክኖሎጂን መስረቅና መኮረጅ አለባቸው። ብዙ ነገሮች የተፈጠሩ ስለሆነ ከእንግዲህ ወዲያ ብዙም አዲስ ነገር መፍጠር አንችልም። ጥያቄው ከውጭ የሚመጣውን ቴክኖሎጂ እንዴት አድርገን ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር ማገናኘትና ህዝቡ የራሱ በማድረግ ሊያሻሽላቸው ይችላል? በሚለው ላይ ነው በየጊዜው ምርምር መደረግ ያለበት።

ያም ሆነ ይህ የወያኔዎች ሀብትን መዝረፍና ህዝብን እያፈናቀሉ ለማበጥና ለማደግ፣ እንዲያም ሲል ሌላውን ለመዋጥና አቀጭጮ ለማስቀረጥ መሞክር ገደብ የሌለው ድንቁርና ነው። ሳይንሳዊ አካሄድ አይደለም። የራሱን የትግሬ ህዝብ የሚያቀጭጨውና ዘለዓለሙኑ እየፈራና እየተባ እንዲኖር የሚያደርገው ነው። በራሱ ላይ እንዳይተማመን የሚያደርገው ነው። በሌላ ወገን ደግሞ ተሰርቶ ባልተገኘ ሀብት በመዘባነን ሌላውን የሚንቁበት ሁኔታ ይፈጠራል። ይሁንና ግን በዚህ አካሄዳቸው ወያኔዎች የተቀረውን የዋሁን የትግሬ ብሄረሰብ እየጠቀሙት እየመሰላቸው የመጨረሻ መጨረሻ እርቃኑን እንዲቀር እያደረጉት ነው። ይህ አስተሳሰባቸውና አካሄዳቸው እንዲሁም ኢ-ሰብአዊ ድርጊታቸው በተገለጸላቸውና የበላይነት ስሜት በማይሰማቸው የትግሬ ምሁራን መቆም ያለበት ጉዳይ ነው። ይህ የወያኔዎች አካሄድ በተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ፣ በተለይም በአማራው ላይ ብቻ ያነጣጠረ ሳይሆን በጠቅላላው በጥቁር ህዝብና ስልጣኔው ላይ ያነጣጠረ እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው። ስለሆነም እንደዚህ ዐይነቱ የአንድን ብሄረ-ሰብ የበላይነት ለማጎልመስ የታቀደ ህልም በእንጭጩ መቀጨት አለበት። የዕድገትና የስልጣኔ ፀር ነው። ጠቅላላው ህዝብ እየተሸማቀቀ እንዲኖር የሚያደረገው ነው። ስለሆነም ወያኔ የግዴታ ዲሞክራሲያዊ በሆነና በሰለጠነ አገዛዝ መተካት አለበት።

ኢ-ሳይንሳዊ የፖለቲካ አካሄድ !

በአገራችን የፖለቲካ ትዕይንት ታሪክ ውስጥ ቢያንስ አብዮቱ ከፈነዳበት ጊዜ ጀምሮ ስለ ፖለቲካ ስልት ያለን ግንዛቤ ሳይንሳዊ ያልሆነና ፍልስፍናዊ መሰረት የሌለው ነው። ፖለቲካ የሚባለው ህብረተሰብን የሚያረጋጋ፣ አርቆ-አሳቢ አድርጎን በማሰብ ኃይላችን እንድንፈጥር፣ አስተሳሰባችንን በማሾል የህብረተሰባችንን ሁኔታና በፖለቲካው መስክ የሚታየውን የተጣመመ አካሄድ በተወሳሰበ መልክ በመተንተን እንድንረዳውና መፍትሄም እንድንሻ የሚያደርገን ሳይሆን፣ የስልጣን መወጣጫና የራስን ጥቅም ማሳደጃ ሆኖ ነው የተገነዘብነውና ይህንንም እንደስልት የተጠቅምንበት። ከዚህም በላይ ፖለቲካ ህብረተሰብአዊ ፕሮጀክትን ለማካሄድ የሚጠቅም መሳሪያና፣ በህብረተሰብ ውስጥ የሚከሰቱ ቅራኔዎችን በሳይንስ እየተነተኑ መፍቻ መስጫ መሳሪያ እንዳልሆነ ነው ሁላችንም እንድነረዳው የተደረገው። በዚህም ምክንያት የተነሳ ፖለቲካ የሚባለው በስሜታዊነት የታመቀ፣ የራሳቸው አጀንዳ ያላቸው ግለሰቦች እነሱን የሚመስል ስልጣንን ብቻ የሚመኝ አድርባይ እየፈለጉ በቡድን የሚደራጁበትና፣ አንዱን በማራቅ ሌላውን በማስጠጋት አንድን አገርና መንግስትን የግላቸው ሀብት አድርገው በመቁጠር በነሱ የተወላገደ አስተሳሰብ የማይስማማውን ሁሉ የሚወነጅሉበትና የሚያርቁበት መሳሪያ ሆኖ ነው የተወሰደው። ይህ ዐይነቱ የፖለቲካ አመለካከት ግንዛቤ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ በየካቲቱ አብዮት ዘመን እንደታየው የዲሞክራሲንና የማርክሲዝምን አርማ አንግቦ ዲሞክራሲ ያለገደብ እያለ የሚጮኸው ሁሉ ጠብመንጃ አንስቶ ወንድሙን የሚገድልበትና የሚያሳድድበት መሳሪያ ለመሆን በቃ። ፖለቲካ ሳይንስና ህይወት ያለው፣ ህዝብን የሚያቀራርብና ለስራ የሚያዘጋጅና ህብረተሰቡንም በየረድፉ አደራጅቶ ታሪክን ለመስራት የሚጠቅም መሳሪያና በየጊዜው እየተሻሻለ በየወቅቱ የሚከሰቱ ችግሮችን መፍቻ ዘዴ ከመሆን ይልቅ አንድን አገር ወደ ጦርነት አውድማነት መለወጫ መሳሪያ ሆነ። አብዮቱ ተቀለበሰ ከተባለና የብዙ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ህይወት ከጠፋ ከሰለሳ ዐመታት በኋላም አሁንም ቢሆን የፖለቲካ ግንዛቢያችን ይህንን ያህልም የተለወጠ አይመስለኝም። ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ምሁራዊነትን ያካተተ፣ የአንድን የህብረተሰብ ታሪክ በደንብ ያገናዘበና የዕድገቱንም ውጣ ወረድነት በደንብ ለመተርጎም የሚያስችል፣ ፍልስፋናዊና ሳይንሳዊ ዕውቀትን ምርኩዝ ያደረገ ለመሆኑ ብዙዎቻችን ጭንቅላት ውስጥ በፍጹም የለም። ከዚህም በላይ ለፖለቲካ እታገላለሁ የሚል ግለሰብም ሆነ ቡድን የግዴታ መንፈሳዊ ነፃነትን መቀዳጀትና፣ ከማንኛውም ለአንድ ህብረተሰብ ዕድገት ጠንቅ ከሆኑ ዕቡይ ተግባሮች መላቀቅን እንደሚጠይቅ እስከዚህም ድረስ ግልጽ አይደለም። በመሰረቱ ዕውነተኛ የፖለቲካ ሰው ስነ-ምግባራዊና ግብረ-ገባዊ ነው። ለአንድ ቡድን ወይም ብሄረሰብ ያደላ ሳይሆን ግዴታውና ኃላፊነቱን የአንድን ህዝብና የአገርን ደህንነት መጠበቅ ነው። ታሪክን ለመሰራት የሚችልና ለዚህም ለሰፊው ህዝብና ለተከታዮቹ ብቃት ያለው አመራር የሚሰጥ መሆን አለበት። ወደ አገራችን ስንመጣ እነዚህ መሰረተ-ሃስቦች በፍጹም የተጤኑና ከሰውነት ጋር የተዋሃዱ አይደሉም።

የዚህ ሁሉ ችግር ምንድነው ? በህብረተሰብአችን ታሪክ ውስጥ የህዝብን ችግር ስልጣን በመያዝ አማካይነት እንፈታለን ተብሎ ትግል ሲጀመር ከመጀመሪያውኑ ከታች ወደ ላይ መጠናት ያለባቸውን ነገሮች፣ ማለትም ፍልስፍና፣ ሳይንስና የቲዎሪ ዘዴዎች ላይ ለመረባረብ ገቱና ዘዴው የለንም። እነዚህም ነገሮች እንደ ቅድመ-ሁኔታዎች መወሰድ ያለባቸውና በጭንቅላትም ውስጥ መቋጠር እንዳለባቸው ግንዛቤ የሚያደርግ የለም። ከዚህም በላይ ተነጻጻሪ ጥናት(Comparative studies) በሚባለው በህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ የተለያዩ ህብረተሰቦችን ለማወዳደር የሚያስችል የቲዎሪና የኢምፔሪካል ጥናት ላይ ትኩረት ለመስጠት አለመፈላገችን ከመጀመሪያውኑ ለፖለቲካ የሚደረገውን ትግል የተኮላሸ አድርጎታል። እንዲዚህ ዐይነቱ የተቻኮለና መሰረት የሌለው የፖለቲካ ትግል ዘዴ የግዴታ የሸፍጠኝነትን ስልት ለሚያስቀድሙ በሩን ይከፍትላቸዋል። ከመጀመሪያውኑ ሰፋና ጠለቅ ያለ ዲሞክራሲያዊ ውይይት ስለሚዳፈን፣ የፖለቲካ ድርጅትን ለመመስረት የሚታገሉ ግለሰቦች የግዴታ ለማዳመጥና ለመደማመጥ ለማይፈልግ ካድሬያዊ ፖለቲካ መንገዱን ሁሉ ያመቻቻሉ። በዚህም ምክንያት የተነሳ ታሪክ መስሪያና የስልጣኔ መንገድ ቀዳጅ የሆነው በሳይንስ ላይ የተመሰረተው ፖለቲካ ወደ ቡድናዊነትና መፋጠጫ መድረክ በመለወጥ፣ በርዕዮተ-ዓለም ዙሪያ የሚደረግና የሚካሄድ ትግል ያስመስለዋል። በመሰረቱ ግን ያለፈውን ሃምሳ ዐመት ያህል የሚጠጋውን የፖለቲካ ትግል ታሪካችንን ለተመለከተ ፊዩዳላዊና ጠባብ አስተሳሰብን ያዘለ ነው። በርዕይ ደረጃ አንድን ህብረተሰብ ለመገንባትና መረጋጋት እንዲፈጠር የሚያስችለው ይኸኛው የፖለቲካ አመለካከት ነው በሚለው ላይ አይደለም ትግሉና ክርክሩ ያተኮረውና ይካሄድ የነበረው። እኔ እስከማውቀው ድረስ የግራ ፖለቲካንም ሆነ፣ ባለፉት ሃያ አምስት ዐመታት በሊበራል ርዕዮተ-ዓለምና በነጻ ገበያ ስም የተካሄደውን ትግል ስመለከት ትግሉ በቲዎሪ፣ በሳይንስና በፍልስፍና ላይ ያተኮረና የተመረኮዘ አይደለም። በመሆኑም ይሁ ሁኔታ የግዴታ አድማሳችንን በማጥበብ በድፍረትና በራስ በመተማመን በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ትግል ማካሄድ እንዳንችል አድርጎናል። ያለፈውን አስርና አስራአምስት ዐመት የፖለቲካ ትግላችንን ስንመለከት በዚህ ዐይነቱ አካሄዳችን ብዙም ስለ ስልጣኔም ሆነ ስለህብረተሰብ ግንባታ ለማይነግሩንና ለመተንተን ለማይችሉ ግለሰቦች በሩ ተከፍቷል። ከፖለቲካዊ ክርክርና ውይይት ይልቅ የራሳቸውን የበላይነት ለማስፈን ለሚፈልጉ ግለሰቦች አመቺ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል። በተለይም የግንቦት ሰባቱ ምርጫ ውጤት ሊከሽፍና ህዝባችንም አስራአንድ ዐመት ያህል የግፍ ጽዋን እንዲቀምስና እንዲሰቃይ የተደረገው ይኸኛውን በግለሰቦች ዙሪያ የሚካሄደውን የትግል ፈሊጥ በመከተላችን ነው።

ከዚህ መጠን ብሎ ስለቀረበው ስለፖለቲካ ያለን ግንዛቤ ስንነሳ የወያኔን የተጣመመ ፖለቲካ አካሄድና ህዝብን ማከረባበቻ መሳሪያ አድርጎ መቁጠር መገንዘቡ ከባድ አይሆንም። ወያኔ የትግሬዎች ድርጅት ስለሆነ ነው ይህንን ዐይነቱን የማከረባበት ፖለቲካ ሊያካሂድ የቻለው ከሚለው ቀላል አስተሳሰብ መነሳቱና መደምደሚያ ላይ መድረሱ ለችግራችን መፍትሄ ሊሆን አይችልም። ይህ ዐይነቱ አካሄድ የራሳችንን ድክመት ከመሸፈኑም ባሻገር የአገራችንና የህብረተሰብአችንን አወቃቀርና፣ እንዲሁም የፖለቲካ ባህል እንዳንረዳው ያግደናል። በሌላ ወገን ደግሞ የድርጅቱን ታሪክ ለተመለከተና፣ የኋላ ኋላ ወደ ማፊያነት መለወጥ የግዴታ የመጣበትን ብሄረሰብ ተገን እንዲያደርገው አድርግታል። ይሁንና ግን እስከተወሰነ ደረጃ ድረሰም ቢሆን የህብረተሰብ መሰረቱን(Social Base) ለማስፋት እንደጣረና፣ በተለይም ተጨቆኑ የሚባሉትንና ለሆዳቸው ያደሩትን በመሰብሰብና በጥቅም በመግዛት የተወሰነ ሌጂቲሜሲ ለማግኘት እንደቻለ የማይታበል ሀቅ ነው። ይህ ባይሆን ኑሮ ሃያ አምስት ዓመት ያህል ስልጣን ላይ ለመቆየት ባልቻለ ነበር። ከዚህም በላይ ኢትዮጵያን ለማዳከምና አቅመ-ቢስ አድርጎ ለማቆየት የሚፈልጉ ኢምፔሪያሊስት ኃይሎችን ተገን በማድረግ ዓለምአቀፋዊ ዕውቅናን በማግኘት እነሱ የሚፈልጉትን ፕሮጀክት እንዲሰራላቸው ዕድል አገኙ። ወደ ሶሻል መሰረቱ ስንመጣ ወያኔ ሁለት አካሄድን የመረጠ ይመስላል። በአንድ በኩል ከዚህም ሆነ ከዚያኛው ብሄረሰብ የተውጣጡ ግለሰቦችንና፣ በአብዮቱ ዘመን የዚኸኛው ወይም ያዚያኛው የፖለቲካ ድርጅት አባል የነበሩ ግለሰቦችን ሲያቅፍ፣ በሌላ ወገን ደግሞ በማፊያ ስራ የተሰማራና በተለይም በራሳቸው ጥረት በማደግ ላይ የሚገኙ ግለሶቦችን በማስፈራራት፣ ውዝፍ ቀረጥ አልከፈላችሁም በማለት ወደ እስር ቤት ውስጥ መክተትና ሀብታቸውን መንጠቅ፣ አንዳንዶችን ደግሞ በመግደልና ይህንን የፖለቲካ ስልቱ በማድረግ እስካሁን ድረስ ቆይቷል። ይህንን ዐይነቱን ማፊያዊ ፖለቲካውን የሚከተለው ያልተማሩና ያለተገለጸላቸውን ትግሬዎችን በመጠቀም ነው።

የውጭውን ዓለም ድጋፍ ለማግኘት ሲል ደግሞ አውቆም ሆነ ሳያውቅ ድህነትን ፈልፋይ የሆነውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን በቀመበልና ተግባራዊ በማድረግ ዕውነተኛ የሊበራል የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አራማጅ ሆኖ ቀረበ። በዚህም ምክንያት የተነሳ እስካሁን ድረሰ ቢያንስ ወደ 40 $ ቢሊዮን የሚቆጠር ዕርዳታ በማግኘትና ራሱን በማደለብ ስልጣኑን ለማጠናከር ቻለ። ከዚህ ስንነሳ በአንዳንድ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ተንታኞች ወያኔ ብቻውን እንደቆመና ካለውጭ ዕርዳታ እዚህ ለመድረስ እንደቻለ የሚሰጠው ትንታኔ ኢ-ሳይንሳዊ ብቻ ሳይሆን በጣም አደገኛም ነው። የውጭ ኃይሎች ለአንድ ደካማ አገር ዕርዳታ የሚሰጡት በእርግጥም የዚያ አገር መንግስት እነሱ የሚፈልጉትን ፖለቲካ፣ በተለይም ደግሞ የትርምስና የጦር ፖለቲካ እስካካሄደ ድረስ ብቻ ነው። የውጭ ኃይሎች በተለይም እንደ አሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የመሳሰሉት የአገራችንን በሳይንስና በቴክኖሎጂ ዳብሮ የተረጋጋና የተከበረች አገር እንዲገነባ አይፈልጉም። በራሱ የሚተማመን አገር ወዳድ ዜጋና ባህሉን ዕምርታ እየሰጠ የሚጓዝ ትውልድ የነሱ ጠላት እንደመሆኑ መጠን እንደዚህ ዐይነቱ ትውልድ ስልጣን ላይ እንዲመጣ በፍጹም አይፈልጉም። በመሆኑም አሁንም በአንዳንድ ኢትዮጵያውያን የሚቀርበው „እሮሮ አሜሪካ ጊዜው ሳያመልጥህ ቶሎ ብለህ የህዝባችን ወዳጅ ሁን“ የሚለው አቤቱታ እጅግ አደገኛና ትጥቅ አስፈቺ ነው። ህዝባችን የዲሞክራሲንና የነጻነት እንዲያም ሲል የስልጣኔን ብርሃን እንዳያይ ከመጀመሪያውኑ በሩን እንደመዝጋት የሚያስቆጥር አደገና አካሄድና ትጥቅ አስፈቺ ነው። አደገኛ የሆነ በፖዘቲቭ ሳይንስ ላይ የተመሰረተ የድህነቱንና የጨለማውን ዘመን የሚያራዝም ነው። ከዚህም በላይ የአገራችን የሶስት ሺህ ዐመት ታሪክና በተደጋጋሚ ሊወሩ የመጡ የውጭ ኃይሎችን በጀግና ልጆቿ አማካይነት መክታ የመለሰችውን አገርና የጀግና ልጆቿን ታሪክ እንደማንቋሸሽ ይቆጠራል። ለኢትዮጵያ ህዝብ ያዘኑ ይመስል በየጊዜው እንደዚህ ዐይነት የእሮሮ ድምጽ ማሰማትና ደብዳቤ መጻፍ ከዓለም ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ የተለያዩ የአሜሪካ አገዛዞች በታሪካቸው ውስጥ ዕውነተኛ ሰብአዊነትን ያሳዩበትና እሴትም(Values) አላቸው የሚያስብላቸው ታሪክ የላቸውም። የዛሬይቱ አሜሪካ ታላቅ ሆኖ ብቅ ማለት የቻለው በመጀመሪያ ደረጃ 17 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢንዲያኖችን ከጨፈጨፈ በኋላ ነው። ከዚያም በኋላ ጥቁር አሜሪካንን በፕላንቴሼን ኢኮኖሚ ላይ በማሰማራትና በመበዝበዝ ነው የካፒታል ክምችትን በማዳበር በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረት ዕድገትን ለመጎናጸፍ የቻለው። እስከ 1960ዎቹ አጋማሽ ድረስ ጥቁር አሜሪካውያን እንደ ነጩ በዕኩልነት የማይታዩ አልነበሩም። ይህ ሁኔታ በመሰረቱ አሁንም ቢሆን ስር ሰዶ ያለ ነው። ብዙ ጥቁር አሜሪካውያን ተነጥለው የሚኖሩና ከነጩ ጋር ሲወዳደር ኮሌጅና ዩኒቨርሲቲዎች ገብቶ የመማር ዕድላቸው በጣም የመነመነ ነው። በተጨማሪም ባልተመጣጠነ የምግብ ዐይነትና በድህነት የተነሳ በብዛት በተለያዩ የስልጣኔ በሽታዎች በሚባሉት የሚሰቃየው ጥቁር አሜሪካዊ ነው። ከዚህ ስንነሳ የአሜሪካንን አገዛዝ እሴት(Values) ያለው አገዛዝ አድርጎ ማቅረብ የጥቁርን ህዝብ መስደብ ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ ደረጃ ታሪክንም ማጣመም ነው።

ሌላው ቢቀር ቢያንስ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ያለውን ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ ሁኔታ በምንመረምርበት ጊዜ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በምንም ዐይነት ዲሞክራሲና ብልጽግናን በሶሰተኛው ዓለም አገሮች፣ በተለይም በአፍሪቃ፣ በላቲንና እንዲሁም በማዕከለኛው አሜሪካ እንዲሰፍንና፣ እነዚህ አገሮች ራሳቸውን እንዲችሉ ያደረገበት ጊዜ የለም። በእነዚህ አገሮች ውስጥ ሁሉ የተካሄዱት የመንግስት ግልበጣዎችና በኮሙኒዝም ስም እየተሳበበ ለዲሞክራሲና ለዕድገት የታጋሉ ግለሰቦች እንዲታረዱ፣ ወደ እስርቤት እንዲወረወሩና እንዲሰቃዩ፣ የተረፈው ደግሞ ወደ ውጭ አገር እንዲሰደድ የተደረገው በአሜሪካን ኢምፔረያሊዝም ዕውቅ ፖሊሲና ድጋፍ ነው። እስካሁን ድረስም አብዛዎቹ የላቲንና የማዕከለኛው አሜሪካ አገሮች በብዙ ሺህ ድሮች በተሳሰሩ ችግሮች የሚሰቃዩት ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በተዘረጋው አገሮችን ከማዳከም የሚሊታሪ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ የአሜሪካን ስትራቴጂ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ አሜሪካና የተቀሩት የምዕራብ አውሮፓ አገሮች እነሱ ብቻ በተቀረው የዓለም ህዝብ ላይ የበላይነትን ይዘው ለመቆየት ሲሉ በሊበራሊዝምና በነጻ ገበያ ስም በአገሮች ላይ ጭነት በማድረግ፣ አልቀበለም ያሏቸውን ደግሞ ተቃዋሚ የሚሏቸውን ቡድኖችንና ግለሰቦችን በገንዘብ፣ በሃሳብና በጦር መሳሪያ በመደገፍ በአንድ አገር ውስጥ በወንድማማቾች መሀከል ጦርነት እንዲካሄድና ደም እንዲፈስ ያደርጋሉ። ዋናው ስትራቲጄያቸውም በተለይም ጥንታዊ የታሪክ አገሮችን፣ እንደ ኢራክ ሊቢያና ሶሪያ የመሳሰሉትን አዳክሞና አገሮችን በጎሳ ነጣጥሎ ትናንሽ አገሮች እንዲፈጠሩ ማድረግ ነው። ከዚህም በላይ በዩጎዝላቢያ ላይ የተካሄደው ጣልቃ ገብነትና በኋላም የይጎዝላቢያ መበታተን፣ በቅርቡ ደግሞ ዩክሬይንና የተቀሩትን የባልቲክ አገሮችን አሳቦና ተገን አድርጎ ራሺያን መክበብና ወደ ጦርነት ውስጥ እንድትገባ ማድረግ ዋናው የአሜሪካን፣ የእንግሊዝና የተቀረው የምዕራብ አውሮፓ አደገኛ ፖለቲካ ነው። በመሆኑም አሜሪካን ለኢትዮጵያውያን የተለየ ሊሆን አይችልም። ብዙ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡትና ካለብዙ ጭንቀትም መገንዘብ እንሚቻለው እስከየካቲቱ አብዮት ድረስና፣ በኋላም አሜሪካ ኢትዮጵያ እንድትዳከምና ቀጭጫ እንድትቀር ያላደረገው ሙከራ ይህ ነው አይባልም። ኢትዮጵያችንም በትናንሽ አገሮች እንድትሰነጣጠቅ የማያደርገው ጥረት ይህ ነው አይባልም። በአሜሪካ አማካይነት ነው „ኢትዮጵያ ዘመናዊነትን ለመጎናጸፍ የቻለችው፣ እኛም የስኮላርሺፕ ዕድል ለማግኘት የቻልነው“ የሚለው አባባል ዘመናዊነት(modernization)ማለት ምን ማለት እንደሆነ ካለመገንዘብ የተነሳ የሚነፍስ አደገኛና አሳሳች አባባል ነው። ዘመናዊነት በሚለው ዙሪያ የተደረገውን ሰፊ የቲዎሪ ትንተናና ኢምፔሪካል ምርምር ለተመለከተ ከ1945 ዓመት በኋላ በአገራችንም ሆነ በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች የተካሄደው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዝብርቅርቅነትን ያመጣና አዲስ ህብረተስብአዊ ግኑኝነትን የፈጠረ ነው። ይህንን ዐይነቱን ዘመናዊነት ለመረዳት ደግሞ፣ በቀላሉ የኛንና የብዙ የሶስተኛውን ዓለም አገሮች ከካፒታሊስት አገሮችና፣ በኋላ ደግሞ ከጃፓንና ከደቡብ ኮሪያ ጋር በማወዳደር ውስጣዊ ድክመቱን መረዳት ይችላል። ይህንን በሚመለከት አሁን ለንባብ ባወጣሁት አዲስ መጽሐፌ ላይ በሰፊው ስላተትኩ መጽሐፉን መመልከቱ ከሞላ ጎደል ጥሩ ግንዛቤ ሊሰጠን ይችላል። በዚያው መጠንም አገራችንና የተቀሩት የአፍሪቃ አገሮች መከተል ያለባቸውን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲ መረዳት ይቻላል።

ያም ሆነ ይህ ይህንን ትተን ወደ ውስጡ ፖለቲካ ስንመጣ አንድ አገዛዝ ለረጅም ጊዜ ስልጣን ላይ ለመቆየት ከፈለገ በህብረተሰቡ ውስጥ አሉ የሚባሉትን ቅራኔዎች በማባባስና አርቲፎሻል ነገሮችን በመፍጠር ለዘለዓለም ስልጣን ላይ ለመቆየት አይችልም። የግዴታ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ከተፈለገ በምድር ላይ የሚታዩትን ችግሮች፣ ማለትም ድህነትንና ረሃብን፣ በመሰረቱ መሰረታዊ ፍላጎቶች(Basic Needs) በመባል የሚታወቁትን ለመፍታት መቻል አለበት። በዚህ ብቻ ሳይረካ አገሩ የተረጋጋች እንድትሆንና፣ ዘላቂነት ያለው ስላም እንዲስፍን ከፈለገ ሰፋ ያለ የስልጣኔ ፕሮጀክት መዘርጋት አለበት። በዚህ መልክና በሚፈጠረው ህብረተሰብአዊ መተሳሰርና ጥንካሬ አንድ አገዛዝ ህዝባዊ ተቀባዊነትን በማግኘት እንደ አለኝታ ይታያል። የብልጣ ብልጡ ወያኔ ተልዕኮውና ህልሙ ግን ይህ አይደለም። አገሪቱን በሁሉም አቅጣጫ ማዳከምና ከውስጥ ህብረተሰብአዊ ቅራኔዎች እንዲፋፋሙ በማድረግ እራሱን አጎልምሶ ታላቋን ትግሬ መገንባት ነው። ሞኙ ህዝባችን ይህንን እጅግ አደገኛና የጥቁር ህዝብ ጠላት የሆነውን ፕሮጀክቱን ዝም ብሎ መመልከት አለበት። ይህንን ዐይነቱን የህዝብ ጠላት የሆነውን አደገኛና በቀላሉ ሊቀረፍ የማይችለውን ተግባር ወያኔዎችና ግብረ አበሮቻቸው ፖለቲካ ይሉናል።

በመሰረቱ ይህ ዐይነቱ የፖለቲካ ግንዛቤና አካሄድ አንዳንድ የድሮ ድርጅቱ አባል ከሆኑት እንደሚሰማው ከሆነ፣ ድርጅቱ አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ በመሆኑ ነው ይህንን የፖለቲካ አካሄድ እንዲመርጥ የተገደገደው የሚለው አመለካከት ኢ-ሳይንሳዊ አቀራረብ ነው። ሁለቱንም መሰረተ- ሃሳቦች ነጣጥለን በምንተነትንበት ጊዜ ሁሉቱም ፅንሰ-ሃሳቦች የሚሰጡን የተለያየ ትርጉም አለ። በመጀመሪያ ደረጃ አብዮት የሚባለው ጽንሰ-ሃሳብ ጤናማ አስተሳሰብ ያለውና ስር-ነቀል እርምጃን የሚያካትት ነው። በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ በአንድ አገዛዝ የሚገለጽና ተግባራዊ የሚሆን ለዕድገት ጠንቅ የሆነ ህብረተሰብአዊና ፓለቲካዊ ግኑኝነት ባለበት ጊዜ የጥገና ለውጥ የማይቻል ከሆነ የግዴታ አብዮታዊ እርምጃ የሚያስፈልግበት ጊዜ አለ። ይህ ዐይነቱ አብዮት የግዴታ ከማርክሲዝም ጋር መያያዝ የለበትም። ማርክሲዝም እንደፍልስፍናና የፓለቲካ መመሪያ ሆኖ ከመፈጠሩ ወይንም ብቁ ከማለቱ በፊት ከሁለትና ከሶስት መቶ ዓመታት በፊት የከበርቴው አብዮት ተካሂዷል። በዚህም መሰረት ነው የፊዩዳሉ ስርዓት ሊገረሰስና ለከበርቴያዊ፣ እንዲያም ሲል ለኢንዱስትሪ አብዮት መሰረት መጣል የተጀመረው። በሌላ ወገን ደግሞ በኢንዱስትሪ አብዮት የተነሳ ህብረተሰብአዊ መመሰቃቀል ሲመጣና ድህነት ሲከሰት፣ እንዲሁም የአካባቢ መቆሸሽ ህዝቡን መኖሪያ ሲያሳጣው ማርክስና ተከታዮቹ ብቻ ሳይሆኑ ሮማንቲኮች የሚባሉ ምሁሮችም ለህብረተሰብአዊ ለውጥ ታግለዋል። ትግላቸው ግን ደም መፋሰስን የሚጋብዝ ሳይሆን በሰብአዊነት መርሆች ላይ የተመረኮዘ እንደነበር በበቂው ተመዝግቧል። ዲሞክራሲ የሚባለው ጽንሰ-ሃሳብ ደግሞ የማያሻማ ትርጉም አለው። ሌላ ትርጉም ካልተሰጠው በሰተቀር ህዝብን የሚያካትትና የህዝብን ጥያቄ መመለሻ መሳሪያ ነው። በሌላ አነጋገር ለጥቂት ኤሊት ነን ባዮች የሚሰጥ ጽንሰ-ሃሳብና መሳሪያ አይደለም። በአገራችን ካልሆነ በስተቀር በታሪክ ውስጥ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚባል ነገር የለም። ይሁንና ግን በብዙ የቀድሞ ሶሻሊስት አገሮች በማዕከል ደረጃ ያልተፍታታ ዲሞክራሲያዊ ሴንትራሊዝም የሚሉት አነጋገር ነበር። ይህ ዐይነቱ ዲሞክራሲያዊ ሴንትራሊዝም አገራችን ውስጥ አለ ከሚባለው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም። በጊዜው የዲሞክራሲ ሴንትራሊዝም ሰፍኖባቸዋል በሚባሉት የቀድሞ የሶሻሊስት አገሮች ውስጥ የነበረውን የህዝቡን ኑሮ ስንመለከት አብዛኛው ህዝብ ስራ የነበረውና በህይወቱም እርግጠኝነት የሚሰማው ነበር። ድህነት የሚባል ነገር አይታወቅም ነበር። በውጭ ፖለቲካቸውም እንደኛው እንደ ዛሬው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ተቀጢያዎች አልነበሩም። ከሞላ ጎደል ራሳቸውን የቻሉ ነበሩ። የተጨባጩ ሶሻሊዝም(Real Socialism) ችግር ቀስ በቀስ እያለ ስርዓቱን ለማደስ ወይም ጥገናዊ ለውጥ ለመውሰድ አለመቻሉ ነው። ሁሉም ነገር በማዕከል ደረጃና ዕቅድ ይካሄድ ስለነበር ለግለሰብ ፈጠራ አመቺ ሁኔታን ሊያዘጋጅ አልቻለም። ከፖለቲካ ኢኮኖሚ ህግ አንጻር የማርክስን ዳስ ካፒታል ላነበበ፣ የኢኮኖሚ ዕድገቱ አካሄድ ቀስ በቀስ እያለ ከዝቅተኛ ወደ ከፈተኛ ደረጃ የሚሸጋገርን የኢኮኖሚ አካሄድ የተከተለ አይደለም። ሌላው የሶሻሊዝም ድክመት ልክ እንደካፒታሊስት አገሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀብትን በመዝረፍ የተገነባና ሌሎች አገሮችን የጥሬ-ሀብት አምራቾች አድርጎ ለማስቀረት የቻለ ባለመሆኑ የመጨረሻ መጨረሻ ስርዓቱ ሊከሽፍ ችሏል። ይህ ማለት ግን አንዱ አገር ሌላውን ካልበዘበዘ ሊያድግ አይችልም ማለቴ አይደለም። ተጨባጩን የካፒታሊዝምን ዓለምአቀፋዊ የሀብት ክምችትና የብዝበዛ ዘዴ ለማሳየት ብቻ ነው። ይሁንና ግን በጊዜው የሶሻሊዝም ርዕዮተ-ዓለም መስፋፋትና ተግባራዊም መሆን ከካፒታሊዝም ውስጣዊ ቅራኔ ጋር የተያያዘና የአንደኛውና የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወጤት ነው ማለት ይቻላል። በጊዜው ግዴታዊ አካሄድ ነበር። በመሆኑም ሶሻሊዝም ወደ ናሺናሊዝምነት በመለወጥ ሶቭየትህብረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከእርሻ (Agrarian) ኢኮኖሚ በኢንዱስትሪ ላይ ወደ ተመሰረተ ኢኮኖሚ መሸጋገር ችላለች። ኃያል መንግስትም ለመሆን በቅታ ነበር። በጦርነት የፈራረሰውን ከተማዎቿን እንደገና መልሳ ለመገንባት ችላለች። ይህንን ሁሉ ያደረገችው በራሷ ጥረትና እንደ አሜሪካ ዕውቀትንና ሀብትን ከሌሎች አገሮች በመውሰድ አይደለም። ከዚህ ስንነሳ ስለ አብዮታዊ ዲሞክራሲና በቀድሞ የሶሻሊስት አገሮች የነበረውን ስርዓት መለያየት አለብን። እንዲያው በጥላቻ ላይ ተመርኩዘን የምናደርገው ዘመቻ በሰፊው እንዳናስብ ብቻ ሳይሆን፣ አማራጭ መንገዶችንንም እንዳንፈልግ ከመጀመሪያውኑ መንገዱን ይዘጋብናል።

ያም ሆነ ይህ ወደ ወያኔው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ስንመጣ በምንም ዐይነት ለውጥን ሊያመጣ የቻለና የሚያስችል አይደለም። ለስርዓት ለውጥም የሚያመች አይደለም። የዚህ ዐይነቱ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ፍልስፍና፣ ሳይንስና ቲዎሪ ምን እንደሚመስል የሚታወቅ ነገር የለም። በመሰረቱ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የፍልስፍና መሰረቱ ማርክሲዝምና የሶሻሊዝም ቲዎሪ መሆን ነበረባቸው። የወያኔ አገዛዝ ግን ከማርክሲዝም ጋር የተሰናበተው በመጀመሪያ ደረጃ ጫካ ውሰጥ ሆኖ ሰው መግደል ሲጀምር ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ስልጣን ከጨበጠ በኋላ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረ ወዲህ ነው። ስለሆነም ይህ የተምታታ ፖሊሲው ለዘመናዊ ፊዩዳሊዝም መንገዱን የከፈተና፣ በዓለም አቀፍ ደራጃ ደግሞ የባሰውኑ ቀጭጨን እንድንቀር የሚያደርገን የስራ-ክፍፍል ውስጥ ነው የከተተን። አዲስ ዐይነት የሴንተር-ፔሪፌሪ(Center-Peripheri) ግኑኝነት ተግባራዊ ያደረገ „አብዮታዊ ዲሞክራሲ“ ነው ተግባራዊ የሆነው። ስለሆነም የስትራክቸራል አድጀስትሜንትን ፕሮግራም ወይም የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲን የተቀበለና ተግባራዊ የሚያደርግ አገዛዝ ለመሰረታዊ ወይም ለአብዮታዊ ለውጥ ዝግጁ አይደለም። እንደሚታወቀው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዋና ዓላማው በየአገሮች ውስጥ አዲስ ዐይነት የሶሻልና የፖለቲካ ግኑኝነት(Social and Political Relationship) በመፍጠር አገዛዞችን በዓለም አቀፍ የአገዛዝ ሂራርኪ ውስጥ በማካተት ህዝቦችን ማሸትና ማድኸየት ነው። ለዚህ ደግሞ ናኦሚ ክላይን(Naomi Klein) The Shock Doctrine በሚለው ግሩም መጽሀፏ ውስጥ እንዳሳየቸው የገበያ ኢኮኖሚ ብለው በሚጠሩት የሞኔተሪ ፖሊሲ የጠቅላላውን ህዝብ ጭንቅላት ሙሉ በሙሉ ማጠብ ነው። በሌላ አነጋገር፣ በዚህ ዐይነቱ የሾክ ዶክትሪን ቲዎሪ አማካይነት የአንድ አገር ህዝብ ጭንቅላት ከድሮ አስተሳሰቡ እንዲላቀቅ መደረግ አለበት። ጭንቅላቱ ተበጥብጦ ሲጣራ የዚያን ጊዜ የገበያ ኢኮኖሚን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ ይጀምራል። ሙያው ሁሉ ገንዘብን ማሳደድ ይሆናል። ናኦሚ ክላይን የብዙ አገሮችን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሁኔታ ኢምፔሪካል በሆነ ዘዴ ከመረመረች በኋላ የደረሰችበት ውጤት ይህ ዐይነቱ ሾክ ዶክትሪን በብዙ አገሮች ኢኮኖሚያዊ ብልጽግናንና የማህበራዊ ሁኔታን መሻሻል ሳይሆን ያመጣው፣ በከፍተኛ ደረጃ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ድቀትን ነው ያስከተለው። ለዚህም ነው አጥፊው ካፒታሊዝም(Disaster Capitalism) ብላ የጠራችው። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አምባገነናዊ አገዛዝን በማጠናከር ሁኔታው እየተበላሸ ሲሄድ ደግሞ ወደ ፋሺስታዊ ስርዓት እንዲሸጋገር ማድረግ ነው። ለዚህ ደግሞ በአገዛዙና በህብረተሰቡ ውስጥ ያለው በጣም ዝቅተኛ የፖለቲካ ንቃተ-ህሊና በጣም አመቺ ነው። ስለሆነም ሴኪዩሪቲውን በአዲስ መልክ ማደራጀትና ማጠናከር፣ ልዩ አፋኛና አነጣጥሮ የሚተኩስ ቡድን ልክ ናዚዎች ያደራጁት ዐይነት ኤስ ኤስ(SS) የሚመስል ፋሺሽታዊ የጦር ኃይል በማደራጀት የተዘረጋውን ስርዓት ይቀናቀኑኛል የሚላቸውን ሁሉ እያነጣጠሩ መግደል ነው።

የመሰለውን አነጣጥሮ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን የሚገድለውን ፋሺስታዊ አጋዚ የሚባለውን የጦር ኃይል ሲአይኤ(C.I.A) ሲያሰለጥነው፣ የፌዴራል ፖሊስ የሚባለውን አስፈሪ ኃይል ደግሞ እንግሊዝ ናት ያስታጠቅችውና ያሰለጠነችው። በተጨማሪም ኢትዮጵያ የሲአይኤ መመላለሻ ቤት ስትሆን፣ በውጭ ጉዳይ ምኒስቴርና በጸጥታ ኃይል ውስጥ እንግሊዞችና ሌሎች የምዕራብ አውሮፓ ሰዎች ተስግስገውበታል። ከዚህ በላይ የሃይማኖት ሰባኪዎችና የዕርዳታ ሰጪዎች በመምሰል በአገሪቱ ውስጥ በመሰማራት የአማራው ብሄረሰብ ዝቅ አድርጎህ ይመለከትሃል በማለት ህዝባችን ርስ በርሱ እንዲበላላና የማያልቅ ጦርነት ውስጥ እንዲገባ የጥላቻ መርዛቸውን እየረጩ ነው። እንግዲህ እነዚህ የወዳጅ አገሮች የሚባሉት ናቸው የወያኔ የጀርባ አጥንት በመሆን ህዝባችን ርስ በርሱ እንዲተላለቅና አገራችንም በዘለዓለም ትርምስ ውስጥ እንድትኖር የሚያደርጉት። ይህ ዐይነቱ የፍርሃትና የጦርነት ፖለቲካ ደግሞ በአሜሪካን አገርም በግልጽ የሚታይ ነው። ፖሊሱን ወደ ወታደርነት በመቀየርና አነጣጥሮ የሚተኩስ ጠብመንጃ ይዞ እንዲዘዋወር በማድረግ፣ አደጋ ሊያደርሱብኝ ነው የሚላቸውን ለጋ ወጣቶች ሁሉ ሳይቀር ምክንያት እየፈለገ እያነጣጠረ እንዲተኩስ ፈቃድ ተስጥቶታል። ስለሆነም ህዝቡ በፍርሃት ዓለም ውስጥ እንዲኖር ተገዷል። በዚህ መልክ በ1960ዎችና በ1970ዎቹ ዓ.ም በላቲን አሜሪካንና በሴንትራል አሜሪካ አገሮች ፋሺስታዊ አገዛዞች በመስፋፋት በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ምሁራንና የዋህ ህዝቦችን ገድለዋል፣ የተቀረውን ደግሞ በየስርቤቱ ጥለዋል። ይህ ዐይነቱ የመንግስታት መኪናዎች አደረጃጀት ዘዴ ፣ በአንድ በኩል በየአገሮች ውስጥ የተፈጠረውን ልዩ ዐይነት ህብረተሰብአዊ ግኑኝነት መጠበቅ ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ አገዛዞችን ፍጥጫ ውስጥ በመክተት በጎረቤት አገሮች መሀከል ጦርነት ለመቀስቀስና ህዝብን ለመጨረስ ነው። በዚህ መልክ የየአገሩ መንግስታት በመፈራራት የማያቋርጥ ወይም በቀላሉ መፍትሄ የማይገኝለት ጦርነት ውስጥ ይገባሉ። በዚያው መጠንም እነዚህ አገሮች በኢንዱስትሪ አገሮች የሚሰሩት የጦር መሳሪያዎች ማራገፊያ ወይም ገበያ ይሆናሉ። ይህ የካፒታሊዝም ውስጣዊ ህግ ነው። ካፒታሊዝምና ጦርነት የተያያዙ ናቸውና።

ከዚህ ዐይነቱ የእከክልኝ ልከክልህ ፖለቲካና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተዘረጋውን የአገዛዝ ሂራርኪ ስንረዳ ነው የወያኔንም የውስጥ ፖለቲካ መገንዘብ የምንችለው። ይህንን የተወሳሰበና በሺህ ድሮች ተሳስሮ ለስልጣኔና ለዕውነተኛ ዲሞክራሲ እንቅፋት የሆነውን ስርዓትና ከውጭ ኃይሎች ጋር ያለውን መተሳሰር ካልተረዳን ስለ እኩልነትና ስለ ዲሞክራሲ ማውራት በፍጹም አንችልም። ስለዚህም የነገሮችን መተሳሰር መመልከት አለብን። ከዚህ ስንነሳ ካለፉት አስራአንድ ወራት ጀምሮ፣ በተለይም ካለፉት አራት ሳምንታት ጀምሮ ወያኔ በህዝባችን ላይ የሚያደርሰው ግድያና ማሰቃየት ከበስተጀርባው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም አለበት። በተለይም ደግሞ የጎሳው ፖለቲካ ስላልሰራና በሃይማኖት መተላለቅም ስላልተከሰተ የምዕራቡ ዓለም በጣም ተደናግጧል። አገራችንን የመበታተኑና በዘለዓለማዊ ጦርነት ውስጥ ዘፍቃ እንድትቀር የታሰበውና የታቀደው ስትራቴጂ ስላልሰራ አገዛዙ አነጣጥሮ በመተኮስ እርምጃው እንዲገፋበት የአረንጓዴ መብራት ተስጥቶታል። ስለዚህም ነው እስከዛሬ ድረስ እንደዚያ በአገራችን ምድር ብዙ ደም እየፈሰሰ የምዕራቡ ሚዲያ ምንም ነገር የማይጽፈውና የማያሰማው። ሁኔታው እንደሶሪያ እስኪሆን ድረስ ነው እነ አሜሪካና የተቀረው የምዕራቡ ዓለም የሚጠባበቁት። በመሆኑም ከብዙ የዋህና ተማርን ከሚሉ ኢትዮጵያውያን የሚቀርበው እሮሮና የይድረሱልን ጩኸት ቦታና ትርጉም የለውም። ይህ ዐይነቱ የይድረሱልኝ እሮሮና ከአሜሪካን ሆኖ ተጠባባቂ መንግስት መመስረት አለብን እያሉ መጮህ ህይወቱን በተሰዋውና በየቀኑ በሚሰዋው ህዝባችን ላይ እንደማላገጥ ይቆጠራል። ከዚህ ዐይነቱ ጭንቅት ለመውጣት የግዴታ በራሳችንና በህዝባችን ላይ መተማመን አለብን። ራሳችንንም ነፃ ማውጣት የምንችለውና ጠንካራ አገር መገንባት የምንችለው በአሜሪካን በመታገዝ ሳይሆን በራሳችን ጥረት ብቻ ነው።

በሌላ ወገን ግን ወያኔ አሁንም የሚከተለው የግድያና የአፈና ፖለቲካው ውድቀቱን የሚያፋጥነው ነው። በተለይም በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የጎንደርና የጎጃም ህዝብ ቆርጦ መነሳቱ በጣም ያስደነገጠው ወያኔ በጠቅላይ ምኒስተርነቱ አማካይነት ይህ ዐይነቱን ከጭቆናና ከዘረፋ ለመውጣት የሚደረገውን የጦር እንቅስቃሴ ከውጭ ወረራ ጋር ለማያያዝ ነው የሞክረው። በአቶ ኃይለማርያም አባባል፣ የኢትዮጵያን ሀብት ለመዝረፍ ጠላት በየጊዜው ወረራ እንዳደረገባትና፣ አሁንም እንዳልተኛ ነግረውናል። አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ግን የሚነግሩን የተገላቢጦሹን ነው። በብዙ መቶ የሚቆጠር ጋሻ መሬት ለውጭ ከበርቴዎች በመሰረቱ ዘራፊዎች አከራይቶ የአገር ሀብት እንዲበዘበዝና ተራው ገበሬ ከመሬቱ እንዲፈናቀል፣ እምቢ ያለውን ደግሞ የሚገድለው ወያኔ ነው። የጎንደር፣ የጎጃም፣ የኦሮሞና የጋምቤላ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚታገሉት በመሬታችን ላይ ከአበባ ይልቅ ለምግብ የሚሆን እህል እንትከልበት፤ ከመሬታችን አታፈናቅሉን እያሉ ነው። በተጨማሪም አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ስለ ዕድገት ያላቸው አስተሳሰብ የተጣመመ ነው። አንድ ሰው መዋያው ያማረ ቤተ-መንግስትና ጋርተን ውስጥ የሚዘዋወርና የሚበላውም ምግብ የተለየ ከሆነ ስለሌላው ማሰብ አይችልም። ስለዚህም አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝና የካቢኔት ሹማምንቶቻቸውን የምንመክረው ሌላው የአገሪቱ ክፍሎች ጋ ሳይሄዱ እዚያው አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ መርካቶ ቢዘዋወሩና አንድ ሁለት ቀን እዚያ ቢያድሩ ስለ ዕድገት ያላቸውን አስተሳሰብ ሊለውጡ ይችሉ ይሆናል። የምንመክራቸውም ሼራተን በመሄድና በመመገብ ሳይሆን፣ ወይም የተወሰነ አካባቢ በመዘዋወር ሳይሆን ስለ ዕድገት መናገር የሚቻለው በየቦታው በእግር በመዘዋወር የህዝባችንን አኗኗር ሁኔታ በመቃኘት ነው። እንደምናየው አብዛኛው ህዝባችን እንደ አይጥ እየተሽሎከለከ በቆርቆርና በተሰባበረ የእንጨት ቤት ውስጥ የሚኖር ነው። ከዚህም በላይ አገሪቱ የቆሻሻ መጣያ የሆነችና ወደፊት በቀላሉ ይህንን ሪሳይክል ለማድረግ የማይቻልበት ሁነታ ተፈጥሯል። ይህ የሚያሳየን ምንድነው ፟? አንድ አገዛዝ የተፈጥሮን ህግ ሳይረዳ በራሱ ስሜትና በማፊያ መልክ በተደራጀው የዓለም-አቀፍ ኮሙኒቲ በሚባለው የወጣና የሚደገፍ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ካደረገ የአንድን አገር የሰውና የተፈጥሮን ሀብት ያወድማል። አዳዲስ ቲክኖሎጂዎችን ሊፈጥር አይችልም። በዚህም የተነሳ ከህዝብ ቁጥር ማደግ ጋር የሚያያዝ ምርታማነትን ሊታይ አይችልም፤ ዕውነተኛ ህብረተሰብአዊ ሀብትም አይፈጠርም። ዛሬ በአገራችን ምድር ያለውን የኢኮኖሚ ሁኔታ አስመልክቶ አንደ የገዢው መደብ አቀንቃኝ የሆነች ከአውስትራሊያ ለሚተላለፈው የአማርኛ ፕሮግራም አዘጋጅ ለቀረበላት ቃለ-መጠይቅ የሰጠችው መልስ የሚያስቅ ነው። የህዝቡ ጥያቄ(Demand) ስለአደገ ነው የኢኮኖሚ ችግር የሚታየው የሚለው ግራ የሚያጋባ ነው። በመሰረቱ በአለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በአገራችን ምድር አገሪቱን ሊያዳርስ የሚችል በመንግስትና በኢንስቲቱሽን የተደገፈ ብሄራዊ ሀብትን ሊፈጥር የሚችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ አልተካሄደም። የስኳርና የኮካኮላ እንዲሁም የቢራ ፋብሪካ በየቦታው በመትከልና በማምረት የአንድን ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎት ማሟላት አይቻልም። በሁለተኛ ደረጃ፣ አንደ ከአገዛዙ ጋር የተቆራኘ እንደ ኢፈርት የመሳሰለ ድርጅትና አላሙዲ የሚባል ተልዕኮው ምን እንደሆነ የማይታወቅና ስለ ኢኪኖሚ ህግ መሰረታዊ ዕውቀት የሌለው ሰው ሁሉንም ነገር በሚቆጣጠሩበት አገር ውስጥ ስለ ዕውነተኛ ዕድገትና ሰለ ህዝብ ጥያቄ ማደግ ማውራት በፍጹም አይቻልም። በሶስተኛ ደረጃ፣ የግል ባለሀብቶች በየቦታው እየተንቀሳቀሱ ኢንቬስት እንዳያደርጉ መዓት እንቅፋቶች በተደቀነበት አገር ውስጥ የስራ መስክ መክፈትና የተለያዩ የምርት ዐይነቶችን ማምረት አይቻልም። ይህም ማለት በአንድ አገር ውስጥ መንግስት ብቻውን የአንድን ህዝብ ፍላጎት ሊያሟላ አይችልም። ቴክኖሎጂያዊ ምጥቀትና ሰፋ ያለ የመዋዕለ-ነዋይ እንቅስቃሴ ሊታይ የሚችለው ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ ያለ የግለሰቦች ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ሲኖር ብቻ ነው። በሌላ ወገን ግን መንግስትና ድርጅቱ ማፊያዊ በሆነ መልክ የሚንቀሳቀሱትን ግለሰቦች ምክንያት እየፈጠሩ ገበያውን ለቀው እንዲወጡ ያደርጓቸዋል። አንዳንዶች ደግሞ በወያኔ የማፊያ ሰዎች ይገደላሉ። ታዲያ በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ እንዲት አድርጎ ኢኮኖሚውን ማሳደግና በየጊዜው እያደገ የሚሄደውን የህዝብ ግላጎትና ጥያቄ ማሟላት ይቻላል ?

ያም ሆነ ይህ በየቦታው መፋፋም የጀመረውን ሰላማዊና ራስን ወደ መከላከል የተለወጠውን የህዝብ እንቅስቃሴ ወያኔ ለመፍታት የሚፈልገው የባሰዉኑ በጠብመንጃ ኃይል ብቻ ነው። በየጊዜው አረመኔያዊነቱን እያረጋገጠና ህፃናትንና እናቶችን ሳይቀር በጠራራ ፀሀይ በመግደል እንቅስቃሴዉን የሚገታ መስሎታል። በዚህ መልክ የሚያካሄደው የጭፍን ፖለቲካው የባሰውኑ ኃይሉን እየበታተነበትና፣ ለትግሬዎች ወንድሞቻችንና እህቶቻችን፣ እንዲሁም እናቶቻችንና አባቶቻችን አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እየከተታቸው መጥቷል። በተለይም ቶሎ ብለው አገዛዙን ማግለል የማይችሉና ሰፊው ወንድማቸው ጎን ቆመው ለዲሞክራሲና ለነፃነት ለመታገል የማይችሉ ከሆነ በተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ እንዲጠሉ ይደረጋሉ። ስለዚህም በአስቸኳይ ከሰፊው ህዝብ ጎን መቆማቸውን ማሳወቅ አለባቸው። የወያኔ አገርን የመበታተንና ኢትዮጵያን አዳክሞ ታላቋን ትግሬ የመገንባት ህልምና ፕሮጀክት ያከተመለት መሆኑን ማንኛውም ወጣት እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ትግሬዎች መረዳት አለባችው። አንድ ህዝብ ታሪክ ሊሰራ የሚችለው በመነጣጠልና በመናቆር ሳይሆን፣ በመሰባሰብና፣ ኃይሉን በማጠንከርና አንዱ ከሌላው በመማር የተረዳዳና ለጋራ ዓላማ የተነሳሳ እንደሆነ ብቻ ነው። በመሆኑም የፖለቲካን ሰፊና ገንቢ ትርጉም መረዳት የጊዜው አንገብጋቢ መሰረተ-ሃሳብ ይሆናል። ለአዲሲቱና ለዲምክራሲያዊቱ ኢትዮጵያ መገንባት የሁላችንንም ተሳትፎ ስለሚጠይቅ፣ ይህንን ከፋፋይና ህብረተሰቡን አዳክሞ የውጭ ኃይሎች ተገዢ የሚያደርገንን አገዛዝ በጋራ ትግል መጣል አለብን። ወያኔ የራሱ ጦር አልበቃ ብሎት ከውጭ ጦር በማስመጣት በህዝባችን ላይ መዝመቱ ማንኛውንም የፖለቲካ ውይይት መንገድ ዘግቶታል። ይህ አገዛዝ ስልጣን ወይም ሞት ብሎ ቆርጦ የተነሳ ስለሆነና፣ በዚህም የሚገፋበት በመሆኑ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ይህን አገዛዝ ይቅርታ እንዲጠይቅና ወደ ህዝብ እንዲመለስ የሚያደርገው ጥሪ እጅግ አሳሳችና አደገኛ ነው። ይህ ዐይነቱ አቀራረብ በአንደ በኩል በአገዛዙና በኢምፔሪያሊስት ኃይሎች የተቀነባበረብንን ልዩ ሴራ በቅጡ ካለመገንዘብ የሚሰነዘር ኢ-ፖለቲካዊ አባባል ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ የህዝባችንን ዕውነተኛ የነፃነትና የስልጣኔ ጥም ለመረዳት ካለመቻል የሚቀርብ አስፈላጊ ያልሆነ ጩኸት ነው።

ከኛ የሚጠበቀው !

እኛ እዚህም ሆነ እዚያ ሆነን ጩኸታችንን የምናሰማ ኢትዮጵያውያን በአገራችን ምድር ሰላም፣ መረጋጋት፣ ዲሞክራሲና ነፃነት እንዲሁም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ብልጽግና እንዲመጣ ከፈለግን ከሁለት ነገሮች አንዱን መምረጥ ያለብን ይመስለኛል። ለብዙዎቻቸን እስካሁን ግልጽ ያልሆነና ከጥንት ጀምሮ ፈላስፋዎችን ሲያከራከር የነበረው ሁለት የዕድገት ፈለገ አለ። አንደኛው እነሶክረተስና ፕላቶን የፈጠሩትና የመንፈስን የበላይነት ያስቀደመው መንገድ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ በሚታዩና በሚጨበጡ ነገሮች ላይ ያተኮረው ዕውቀትን የመፍጠሩ ጉዳይ ነው። ይህ ዐይነቱ አካሄድ በተለይም ከአስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በአንድ በኩል በነላይብኒዝ የሚወከለውና የእነ ፕላቶንን ፍልስፍና መሰረት ያደረገው የስልጣኔ መንገድ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በእንግሊዞች ኤምፕሪሲስቶች የሚሰተጋባው ከሶፊስቶች የተወሰደው ዕውቀትን የማፍለቅ ዘዴ ወይም ፖዚቲቭ ሳይንስ በመባል የሚታወቀውና፣ አንድን ተቀባይነት ያገኘን ስርዓትና አገዛዝ፣ እንዲሁም ከዚህ የፈለቁትን መመሪያዎች ሳይመረምሩ እንዳለ መቀበል ነው በሚለው መሀከል የተካሄደውን የጦፈ ክርክር ነው። በጊዜው እነላይብኒዝ ይከራከሩና ተከታዮቻቸውን ያስጠነቅቁ የነበረው ማንኛውም አገር የእንግሊዝ ፈላስፋዎችን መንገድ የምትከተልና፣ ፖሊሲዎች በሙሉ በዚህ መሰረት የሚወጡ ከሆነ መጪው የዓለም ህዝብ ዘለዓለሙኑ በጦርነትና በድህነት ውስጥ ዘፍቆ ፍዳውን እንደሚያይ ነው። ይህ አመለካከት በኋላ በመጡት በእነ ካንትና ሺለር፣ በኋላም በእነ ሄገል በመስፋፋት፣ የአንድ አገር ዕድገት የግዴታ በአርቆ አስተዋይነትና በከፍተኛ ንቃተ-ህሊና(Self-Consciousness) ላይ መመርኮዝ እንዳለበትና፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከሌሎች ህብረተሰብአዊና ማህበራዊ እንዲሁም ባህላዊ ዕድገት ተነጥሎ መታየት እንደሌለበት አስተምረዋል። በእነሱ አመለካከት አንድ ነገር ከሌላው ጋር የተያያዘ ስለሆነ፣ በአንድ አካባቢ የሚሰራ ስህተት የግዴታ በሌላው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል። በሌላ አነጋገር አንድ አገዛዝና አገር የተሳሰተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚከተሉ ከሆነ የመጨረሻ መጨረሻ ጠቅላላዉን ሁኔታ ያዘበራርቃሉ። የአገራችንን ሁኔታ ለሚመለከተው ይህንን መረዳቱ ከባድ አይሆንም። ለዚህ ነው በአገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለም-አቀፍ ደረጃ ሚዛናዊነት እየጠፋና ጥቂቶች እየደለቡና፣ ሲጠግቡ ደግሞ ወደ ጦርነት የሚያዘነብሉት። ይህንን ለማመልከት ሲል ነው ውድ ወንድማችን ዳዊት አለማየሁ „ሚዛንሽ ተዛባ አንቺ ዓለም“ እያለ ግሩም በሆነ መልክ የሚዘፍነው። ስለዚህ ይህ ሙዚቃና ታች ከዚህ ጽሁፍ ጋር የተያያዙት የድህረ-ገጽ አድራሻዎች ብዙ መልዕክቶችን ያስተላልፉልናል። የዓለምን የመዘበራረቅ ሂደት በትንሹም ቢሆን ጠጋ ብለን እንመልከት።

በተለይም ከአስራስምንተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የእንግሊዙ መንገድ ባሸናፊነት ከወጣ ጀምሮ ቀስ በቀስ ብዙ አገሮች ሳያውቁት ይህንን መንገድ በመከተል የየአገሮቻቸው፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሚሊታሪ ፖሊሲ መመሪያ በማድረግ ህዝብን መቆጣጠሪያ ዘዴ አደረጉት። በጊዜው የእንግሊዝ ኤምፕሪሲስቶች የሰብአዊነት አመለካከት ያላቸውን አዋቂዎችን ካሸነፉ በኋላ ነፃ ገበያና ነፃ ንግድ የሚለውን በማወጅ፣ በዚያው መጠንም እንዴት አድርገው ዓለምን ለመቆጣጠር የሚችሉበትን ዘዴዎች ቀሰ በቀስ ተግባራዊ ማድረግ ጀመሩ። ይህ አካሄድ የመጀመሪያው የተጣመመው የግሎባላይዜሽን መሰረት ነው። ከዚህ በመነሳት ነው ቀሰ በቀስ የቅኝ-አገዛዝ ፖሊሲ አገሮችን የማዳከም ስትራቴጂ የተቀየሰውና ተግባራዊም የሆነው። በውጥኑ መሰረት አብዛኛዎች የአፍሪቃ አገሮች የጥሬ-ሀብት አምራችና አቅራቢ በመሆን እዚያው ቀጭጨው መቅረት አለባቸው። እንደ ህብረተሰብና እንደ አገር በሁሉም አቅጣጫ ማደግና መበልጸግ የለባቸውም። በተለይም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በአሸናፊነት ከወጣ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ይህ መንገድ የበለጠውን በመርቀቅና እየተወሳሰበ በመምጣት የብዙ አገሮች መመሪያ ሆነ። ብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች በዘመናዊነት ስም ዕውነተኛ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ሳያደርጉ፣ በዚያው መጠንም የየመንግስት መኪናዎቻቸውን በአሜሪካ የጦር አደረጃጀት ስልት ማዘጋጀት ተገደዱ። ጠቅላላው የሲቪል ቢሮክራሲው በሙሉ በዚህ ዐይነቱ የፖዘቲቭ ሳይንስ መመሪያ በመሰልጠኑ በዓለምአቀፍ ደረጃ በተዘረጋው የሚሊታሪ-ኢንዱስትሪ ኮምፕሌክስ ውስጥ በመዋሃድ በየአገሮች ውስጥ ሚዛናዊነት ያለውና ከተፈጥሮና ከህዝብ ፍላጎት ጋር እየተመጣጠነ የሚሄድ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዳይሆን አገደው። በተለይም እ.አ በ1944 ዓ.ም እነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና(IMF) የዓለም ባንክ(World Bank) ከተቋቋሙ ጀምሮ ዋናው ተግባራቸው በተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት በየአገሮች ውስጥ የተዛባ ዕድገት የሚመስል ነገር ማምጣትና፣ በዚያውም መጠንም ድህነትን መፈልፈል ነው። ይህ ዐይነቱ የፖሊሲ አወቃቀር በየጊዜው ስሙን በመለዋወጥና በየአገሮች ውስጥ ተግባራዊ በመሆን የብዙ አገሮች ኢኮኖሚዎችና ማህበረሰቦች እንዲዘበራረቁ ሆኑ። ቀስ በቀስም ማህበራዊ ቀውሱ ጥልቀት በማግኘት፣ እ.አ ከ1989 ዓ.ም በኋላ የተፈጠረውን አዲስ ክስተት ተገንና ሽፋን በማድረግ የየአገዛዞች ዋናው ተግባር አሸባሪዎችን መዋጋት ነው በሚል የአብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮች መንግስታት ዋናው ተግባር ወደ ጦርነት በማድላት የመንግስታቶቻቸውን መኪና የባሰውኑ ሚሊታራይዝ በማድረግና የየአገሮቻቸውን ሀብት በመምጠጥ በፍጥጫ ዓለም ውስጥ እንዲወድቁ ተገደዱ። በአስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን እነላይብኒዝና፣ የኋላ ኋላም ተከታዮቻቸው ሌሎች የጀርመን ፈላስፎች ያሰጠነቀቁት የነበረው ሁኔታ ዕውን በመሆን፣ ይህ ዐይነቱ መንግስታዊ አወቃቀርና ከዚህ የሚወጣው ፖሊሲ ለአንደኛውና ለሁለተኛው ዓለም ጦርነት ምክንያት ሆነ። የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ፍጻሜ ካገኘና አሜሪካንም የበላይነትን ከተቀዳጀ በኋላ ጦርነት ወደ ሶስተኛው ዓለም አገሮች በመሸጋገር ብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች በጦርነት ዓለም ውስጥ እንዲዘፍቁ ተገደዱ። ከቬትናም እስከ አንጎላና ሞዛምቢክ ድረስ በ60ኛውና በሰባኛው ዓ.ም ይካሄዱ የነበሩት ጦርነቶችና ለብዙ መቶ ሺህ ህዝቦች ማለቅ ምክንያት የሆኑት ዋናው ቀስቃሺዎች አሜሪካንና ተካታዮቻቸው ናቸው። እነዚህ በወንድማማቾች የተካሄዱት ጦርነቶች በሙሉ በመሰረቱ የውክልና ጦርነቶች(Proxy War) ናቸው። ዛሬ ወያኔ በአገራችን ምድር ላይ የሚያካሄደው ጦርነት የውክልና ጦርነት ነው። ካለበቂ ምክንያት በወንድማማቾች መሀከል የሚካሄድ ጦርነት ነው። እነ ሻቢያም ነፃ ወጣን እስካሉ ድረስ ጀምሮ ያካሂዱ የነበረው ጦርነት በውጭ ኃይሎች የታገዘና በማቴሪያልና በገንዘብ የሚደገፍ ለብዙ መቶ ሺህ ኢትዮጵያውያን-ኤርትራውያን እልቂት ምክንያት የሆነ ጦርነት ነው። የኦሮሞ ነፃ አውጭ ነኝ የሚባለው ድርጅትና ራሳቸውም የግራ ኃይሎች ነን ይሉ የነበሩት ሳያውቁት ያካሂዱ የነበረው ጦርነት በመሰረቱ የውክልና ጦርነት ነበር። ኃይልን የሚበታትን፣ ሀብትን የሚጨርስና የድህነቱን ዘመን የሚያረዝመው ነው። በመሰረቱ በአንድ አገር ውስጥ በአንድ ህዝብ መሀከል በብሄረሰብና በርዕዮተ-ዓለም ስም አሳቦ ወይም ስልጣን ላይ ለመውጣት በማለት የማያስፈልግ ጦርነት ማካሄድ ይቅርታ የማይደረግለት ነው። የታሪክ ወንጀል እንደመስራት ይቆጠራል። ግሎባላይዜሽንና ነፃ ገበያ አማራጭ የሌላቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ናቸው ተብለው መሰበክ ከተጀመሩበት ከ90ዎቹ ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአንድ በኩል የዎል ስትሪት(Wall Street) ተዋንያንና በዓለም አቀፍ ኢንስቲቱሽኖች ውስጥ ሲሰሩ የነበሩና እንደሎሚ ልጣች ተመጥጠው ያለቁ ኤክስፐርቶችን እየላኩብን በቀጥታ የኢኮኖሚ ጦርነት አውጀውብናል። በተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ደሃ ሆነን እንድንቀር ለማንም የማይታይና ማንም ሊረዳው የማይችል የረቀቀ ጦርነት አውጀውብናል። ከዚህም በላይ አሸባሪዎች የሚባሉትን በየቦታው እንድ አሸን እንዲፈልቁ በማድረግ ጦርነት አውጀውብናል፤ ለአለመረጋጋት ምክንያት ሆነዋል። ይሁንና የአሸባሪዎች ዋናው አማካሪ፣ መሳሪያ አቀባይና ገንዘብ አቅራቢዎች ደግሞ የአሜሪካን የስለላ ድርጅትና በዘይት ዶላር የናጠጡ የአረብ አገሮች ናቸው። አልሻባብ የሲአይኤና የወያኔ ውልድ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ በአሸባሪነት ስም የሚካሄዱት ግድያዎች በሙሉ ከዘጠና በመቶ በላይ በስለላ ድርጅቶች የሚካሄዱ ናቸው። ለዚህ ደግሞ እንደ ሃርፕ የመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀምና የወጣቱን ጭንቅላት በማዞር ነው።

ይህ ማለት ማለት ነው? እኛ የዛሬውን አገዛዝ የምንታገልና ነፃነት እንዲመጣ የምንፈልግ ኃይሎች ሁሉ ከሁለት አንደኛውን መንገድ መምረጥ አለብን። ከመንፈሳዊውና ከሰይጣኑ መንገድ። በዝህቦች መሀከል ስምምነት እንዲመጣ፣ እያንዳንዱ ዜጋም የማሰብ ችሎታውን በማዳበር አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠር የሰለጠነች አገር እንዲገነባ ከተፈለገ የግዴታ የመንፈሳዊዉን መንገድ መምረጥ አለብን። ወጣቱ ቄስ ዳነኤል እንደሚያስተምረን ወደ ገነት ለመግባት ከፈልግህ የሰይጣኑን መንገድ መምረጥ የለብህም። የግዴታ ቅዱሳዊውንና የገነቱን መንገድ ስትመርጥ ብቻ ነው ወደ ገነት መግባት የምትችለው። በዩኒቨርሳል ህግ ወይም በተፈጥሮ ህግም መሰረት ዋናና ተቀዳሚው ተግባር የአስተሳሰብ አንድነት(Unity of Thought) ማዳበር ነው። የአስተሳሰብ አንድነትና ጥራት ሲኖር የስልጣኔው መንገድ ብሩህ ይሆናል። የአስተሳሰብ ጥራት ሲኖረን እርስ በራሳችን መናቆሩን እንተወዋለን። ሁለተኛው የዩኒቨርሳል ህግ መመሪያ በተናጠል አንድ ግብ መድረስ አይቻልም። በአንድ ጣት ምንም መስራት አይቻልም። በሁለት ጣቶች እርሳስ ማንሳት ይቻላል። በአምስት ጣቶችና በሁለት እጆች ብዙ ነገሮች መስራት ይቻላል። ብዙ ሰዎች ስንሆን ደግሞ ተራራንም ማንቀሳቀስ እንችላለን። ስለሆነም አንድ ጠንካራና ስላም እንዲሁም ብልጽግና የሚሰፍንባት አገር ለመገንባት ከፈለግን የግዴታ ኃይላችንን መስብሰብ አለብን። ሁሉም ታጋይ ነኝ እያለ በየቦታው ለመታየት የሚፈልግ ከሆነና፣ እዚህና እዚያ የፖለቲካ ፓርቲ የሚሉትን ፈሊጥ የሚመሰርት ከሆነ አንድ ጠንካራ አገር መገንባትና ሰላምን ማምጣት በፍጹም አይቻልም። ሶስተኛውና እጅግ አስፈልጊው የዩኒቭርሳል ህግ የግዴታ በራስና በራስ ህዝብ መተማመንን ይፈልጋል። ለዚህ ደግሞ የመንፈስ ነፃነት እንዲሰማ ያስፈልጋል። ከዚህ ስንነሳ የውጭ ተጠሪ የሆነና በውጭ ኃይል የሚተማመን ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል አገዛዝ በምንም ዐይነት ዕውነተኛ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ስልጣኔና ዕድገትን አያመጣም። በአራተኛ ደረጃ፣ ሌላው የዩኒቨርስ ህግ አንዱ ለሌላው ማሰብና ርስ ብርስ መረዳዳት አለበት። በተለይም መጦሪያ የሌላቸውንና በየቦታው የወደቁትን ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን፣ እንዲሁም እናቶቻችንና አባቶቻችንን መደገፍ ካልቻልንና መጠለያ ካልሰጠናቸው ስለ አገርና ዕድገት ማውራት በፍጹም አንችልም። በአምስተኛ ደረጃ፣ ሌላው የዩኒቨርስ ህግ የሚለን በአንድ አገር ውስጥ የተለያየ ብሄረሰብና አስተሳሰብ፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ የምግብ ዐይነቶችና ባህሎች መኖራቸው ተፈጥሮአዊ ናቸው። ተፈጥሮ ራሷ በልዩ ልዩ ነገሮች የምትገለጽ ነች። ሰውነታችንም ራሱ እዚያው በዚያው አንድም ብዙም ነው። ስለዚህም በአገራችን የተለያዩ ብሄረሰቦች መኖራቸው የውበታችን መግለጫዎች ናቸው እንጂ የመጠላላትና የመቀናናት ምክንያት ሊሆኑ አይገባቸውም። ጥያቄው እንዲዚህ ዐይነቱን ነገሮች በምን ዐይነት ፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲ ልንፈታቸው እንችላለን በሚለው ላይ ነው መነጋገር ያለብን። ስለሆነም ሁሉም ህዝብ ከዘርና ከሃይማኖት ባሻገር መረዳዳት አለብን። በመረዳዳትና በመከባበር ብቻ ነው ጤናማና ተከታታይነት ያለው አገር መገንባት የምንችለው።
የለም እኛ በአሜሪካን ትምህርት ነው የሰለጠን ነው፣ የአሜሪካን እሴትም ትክክለኛው ነው ብለን ይህንን የሙጥኝ ብለን የምንይዝ ከሆነ ያለመረጋጋቱንና የፀረ-ስልጣኔውን መንገድ መረጥን ማለት ነው። የሰይጣኑንና የመበታተኑን መንገድ ፈለግን ማለት ነው። ከዚህ ስንነሳ ወያኔን ለማስወገድ የሚደረገው ትግል ከዚህ ዐይነቱ የአስተሳሰብ ክልል ውጭ ሊታይ አይችልም። በሌላ አነጋገር በአገራችን ምድር ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ከተፈለገ፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የዚያች አገር ዜጋ መሆኑን እንዲረዳና ሙሉ ነፃነቱን እንዲቀዳጅ ከተፈለገ ነገሩ ወያኔን በማስወገድ ብቻ የሚያቆም መሆን የለበትም። በኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ በአጭሩ በአገር ግንባታና በሚሊታሪ ፍልስፍና ዙሪያ የምናካሄደው የጦፈለት ክርክር ወደ ፊት ይጠብቀናል። ዛሬ በሰሜንም ሆነ በደቡብ ከወያኔ ጋር የሚጋፈጠውና የነፃነት ያለህ እያለ የሚጮኸው ህዝባችን የሃሳብ ጥራትን ይጠብቃል። ከወያኔ ከተላቀቀ በኋላ በአስቸኳይ ጊዜያዊ ችግሩን እየቀረፍንለት ሰፊውን የአገር ግንባታ ተግባራዊ እንድናደርግ ከኛ ይጠብቃል። የመጨረሻ መጨረሻ ዕውነተኛ ነፃነቱ በተጨባጭ ነገሮችም የሚመነዘር መሆን አለበት። አዳዲስ ከተማዎችንና መንደሮችን መገንባት፣ ሀብትንና የሰው ኃይልን ለማንቀሳቀስ በየቦታው ኢንስቲቱሽኖችን ማቋቋም፣ በህዝብ ዘንድ ያለን ገንዘብ ለማንቀሳቀስና ምርታማ በሆነ ነገር ላይ ለማዋል የባንኩን ስይስተም በአዲስ መልክ ማደራጀት፣ የምግብን ችግር ለመቅረፍና በምግብ ራሳችንን ለመቻል የመሬትን ጉዳይ በአዲስ መልክ ለመፍታት መቻል፣ በተለይም ልዩ ልዩ የሰብልና የእህል ዐይነቶች ሊዘሩና ሊበቅሉ የሚችሉበትን ሁኔታ ማጥናትና በአስቸኳይ ተግባራዊ ማድረግ፣ በንጹህ ውሃ እጦት ለሚሰቃየው ህዝባችን በአካባቢውና ከረጅም ጊዜ አንጻር ደግሞ ቤት ውስጥ የመጠጥ፣ የመቀቀያና የማጠቢያ ውሃ የሚያገኝበትን ዘዴ ማጥናት፣ በተለይም የቤትን አሰራር በአዲስ መልክ በመቀየስ በማዕከለኛው ዘመን ይኖር ይመስል ለሚሰቃየው ህዝባችን አዲስ የአኗኗር ስልትን እንዲለምድ… ወዘተ. በነዚህና በአያሌ የአገር ግንባታ ነገሮች ላይ መረባረብ አለብን። ይህንን የህዝባችንን ህልምና ፍላጎት ዕውን ማድረግ የምንችለው ዓለምንና እያንዳንዱን አገር ከሚያጠፋው የሰይጣን ርዕዮተ-ዓለም የተላቀቅን እንደሆን ብቻ ነው። ለዚህ የተቀደሰ ተግባር ቀን ሌሊት መስራት አለብን። ብርታቱንና ጽናቱን ይሰጠን ዘንድ ራሳችንን በራሳችን ማግኘት አለብን። ሁሉም ነገር በጭንቅላታችን ውስጥ ስላለ ህዝባችን የተመኘውን ስለምና ዕድገት ተግባራዊ ለማድረግ ምንም የሚቸግረን ነገር የለም።ሁሉም ነገር አለን፣ ነገር ግን እንዳናስብና እንዳንሰራ ታግደናል !!
ፈቃዱ በቀለ
fekadubekele@gmx.de

http://www.ethiopia.org/index.php?lang=en

የኛ ነገር፤ ትግሬን መነጠል፤ ሐሳዊ-ኢትዮጵያዊነት ነው፤ ተክለሚካኤል አበበ፤

$
0
0

1- ሰሞኑን በሰጠሁት በትግሬነት ላይ የሚሰነዘረው ውግዘት ትክክል አይደለም የሚል አስተያየት ላይ፤ የተለያዩ ሀሳቦች ተሰንዝረዋል፡፡ የሚነሳው የተዛባ አመለካከት ከገመትኩት በላይ አሳሳቢና፤ የመልስ ዘረኝነት ወይም ጥላቻ፤ ፈረንጆች reverse racism የሚሉት ነገር የተጸናወተው ይመስላል፡፡ የብዙዎቹ ትችት አሁን ያለው የኢትዮጵያ መንግስት የትግሬዎች መንግስት ስለሆነ፤ መንግስት ለሚፈጽመው ጥፋት ትግሬዎች ሁሉ ተጠያቂ ናቸው የሚል ድምጸት አለው፡፡ ብዙዎቹ ተቺዎች፤ ትግሬዎች ሕወሀት ካልሆኑ ያረጋግጡልን የሚል ፈተና ያቀርባሉ፡፡ ነጻ መሆናቸውን ካላረጋገጡ በስተቀር፤ ትግሬዎች ሁሉ ወንጀለኞች ናቸው አይነት ነገር፡፡ ይሄ፤ አለም የተቀበለውን፤ እኛም በአገራችን እንዲሰፍን የምንመኘውን የነጻነት መርህ የሚጻረር፤ ከምንም በላይ ደግሞ ጸረ-ኢትዮጵያዊ የሆነ አቋም ነው፡፡

2- ትናንትናና ዛሬ ሕወሀት/ኢህአዴግ፤ ነጋሪት ጎስሞ፤ አዋጅ ነግሮ፤ የኢትዮጵያን ችግር ሁሉ የፈጠረ አማራ ነው ሲል፤ ያንን ስንቃወም የኖርን ሁላ፤ አሁን ደግሞ መልሰን የኢትዮጵያ ችግር ሁሉ ፈጣሪ ትግሬ ነው ስንስል፤ ለሕወሀት/ኢህአዴግ የአመታት ዘመቻ እጅ ብቻ ሳይሆን፤ እግርም እየሰጠን ይመስላል፡፡ እነሆ ከ25 አመታት በኋላ፤ አያቶቻቸውና አባቶቻቸው፤ ኢትዮጵያን ከውስጥም ከውጭም ጠላት ለመከላከል፤ በኢትዮያዊነት ኩራት የሞቱ ጎንደሮች፤ ጎዣሞች፤ ሸዋዎች፤ ዛሬ የአማራ ምንትሴ፤ የአማራ ቅብርጥሴ ብለው ሲደራጁ ማየት እንዴት ያስፈራል፡፡ ያ ብቻም አይደለም፤ ትናንት ሕወሀቶች አማራን ጠላት ባደረገ ርእዮተ-አገር አሳብረው አራት ኪሎ ገብተዋልና፤ እኛም እነዚህን ዘረኞች የምናሸንፈው፤ ትግሬዎችን ሁሉ ጭራቅ አድርገን በመሳል ነው የሚው ቅኝት ነው ሌላው ትልቅ ስህተት፡፡ በዚህ አቋሜ፤ ከወዳጆቼ ጋር መጋጨቴ አልቀረም፡፡ ግን፤ ሀሳብን በነጻነት ከመግለጽ አንጻር፤ ወዳጄቼ ከኢህአዴግ እንደማያንሱ ስለማውቅ፤ የመሰለኝን ልጻፍ፡፡

3- አሁን ያለው መንግስት የትግሬዎች መንግስት ነው የሚለውን ዜማ ይዘው የሚከራከሩት ሰዎች የሚነሱት፤ አንደኛ የትግራይ ህዝብ ከስርአቱ ተጠቃሚ ስለሆነ ስርአቱን ይደግፋል ከሚል ግምት ነው፡፡ ይሄንን ለማስረዳት፤ አንዳንዶቹ ቦሌና 22 ላይ የተደረደሩትን ፎቆች ይቆጥራሉ፤ ይሄ የጀነራል ሰዓረ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ የጀኔራል ገብረዮሀንስ፡፡ ይሄ ደግሞ የአርከበ እቁባይ፡፡ ይቀጥላል፡፡ የግለሰቦች ሀብት በምን ስሌት የህዝብ እንደሚሆን አይረዳንም፡፡ በርግጥ፤ ባለፉት 25 አመታት በንጽጽር፤ ከሌሎች ክልሎች በተሻለ በትግራይ የተነገቡትን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ተቋማት፤ እንዲሁም የትግሬዎችን በማእከላዊ መንግስት ውስጥ ያላቸውን የተዛባ ድርሻም ጠቅሰው የሚከራከሩ አሉ፡፡ ሁለተኛው የሚነሱት፤ ይሄንን በሌሎች ኢትዮጵያዊያን ላይ የሚደርሰውን ግፍ፤ ትግሬ ጠንቅቆ ያውቃል ከሚል ግምት ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ በሙሉ፤ ወይም ባብዛኛው፤ የህወሀትን መንግስት አውቆ፤ ተጠቃሚ ከሆነም፤ ተጠቃሚነቱ በሌሎች ኪሳራ የመጣ እንደሆነ ተረድቶ፤ ሕወሀትን ይደግፋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ያንን ሀሳብ የሚያራምዱ ሰዎች፤ ግምት እንጂ፤ አሳማኝ ማስረጃ አያቀርቡም፡፡

4- ቁሳዊ ሀብትና ንብረት፤ የባህል የበላይነትም እንደማስረጃ ከተቆጠረ፤ በተለይ ከኢህአዴግ በፊት በነበሩት ዘመናት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የአማራውን ያህል ሀብት ያከማቸ ብሄር የለምና ይሄኛው ክስ ከአማሮች ባይመጣ ይመረጣል፡፡ በርግጥ አማራው ባለፉት 25 አመታት ክፉኛ ተመቷል፡፡ አንዳንዶች፤ በተለይም የትግሬ ልሂቃን፤ እነስዬ አብርሀ፤ ሕወሀት በአማራው ላይ የፈጠነውን ደባ ለማሳነስ፤ በኢህአዴግ አገዛዝ ዘመን፤ ኦሮምኛ የእስርቤት ቋንቋ እስኪመስል ድረስ፤ ኦሮሞው ተጠቃ ይላሉ እንጂ፤ ባሳለፍነው 25 አመታት እንደአማራው የተጠቃ ብሄር የለም፡፡ ግን ደግሞ፤ ባብዛኛው በቀደሙት አመታት፤ በፊታውራሪነት ኢትዮጵያን የቃኘው ብሄር አማራው ስለሆነ፤ አማራው በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብት የበላይነት፤ እንዲህ በ25 አመታት አይደለም በ250 አመታትም የሚናድ አይደለም፡፡ እንደውም ሳስበው ሳስበው፤ የህወሀት ትልቁ የ25 አመታት ፈታና፤ እነሱ ራሳቸው የጠሉትን አማራ እየሆኑ መምጣታቸው ይመስለኛል፡፡ ሕወሀት፤ ጭራቅ አድርጎ የሳለውን አማራና የአማርኛ ባህል ማሸነፍ አቅቶት፤ እንደውም እለት እለት እንደጠላት በሚቆጥረው ባህል እየተሸነፈ መምጣቱ መሰለኝ ብጥብጥ ያደረገው፡፡ ይሄንን ወደፊት አስረዳለሁ፡፡ ለዛሬ ግን በትግራይ ህዝብ ላይ ስለሚቀርበው ጎዶሎና የነቂስ ክስ ስህተት ማስረዳት ልቀጥል፡፡

5- ብዙ ሰዎች የላይኛውን ትግሬ ነገሰብን፤ በዚህም የንግስና ሂደት፤ የትግራይ ህዝብ እንደደጋፊም፤ እንደአጃቢም፤ እንደባለቤትም ሆኖ፤ ከሕወሀት ጎን ቆሟል የሚል ሀሳብ ለማስረዳት በዋንኛነት እንደማስረጃ የሚጠቀሙት፤ ሁለት ነገሮችን ነው፡፡ አንደኛው፤ የህወሀት መሪዎች፤ እነሳሞራ የኑስ እነአባይ ጸሀዬ እነስብሀት ነጋ እነስዩም መስፍን፤ ብድግ ብለው የትግራይ ህዝብና ሕወሀት አንድ ነው፤ ማንም አይለያያቸውም ሲሉ፤ የትግራይ ህዝብ አላስተባበለም፡፡ ስለዚህ ዝምታ የመቀበል ያህል ይቆጠራል ነገር ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፤ የሌሎች አካባቢዎች ህዝቦች ለመንግስት ያላቸውን ተቃውሞ በተለያየ መንገድ ሲያሰሙ፤ የትግራይ ህዝብ ግን ተቃውሞ አድርጎ አያውቅም የሚል ነው፡፡ ሁለቱም መከራከሪያዎች፤ አንዳንዶቻችን በጥላቻ አጥቅሰን ካልዋጥናቸው በቀር፤ ወይንም ገሚሶቻችን አገርቤት በሚፈጸመው ግድያ ደማችን ተንተክትኮ፤ አዝነን፤ በንዴት መንፈስ ካልተቀበልናቸው በስተቀር፤ ውሀ አይቋጥሩም፡፡

6- የትግራይ ህዝብ፤ በርግጥም ሕወሀትን ወይንም አሁን ያለውን መንግስት ደግፎ ከሆነ፤ ፈረንጆች የምክንያታዊ ሰው መስፈሪያ (the reasonable person standard) በሚሉት ሚዛን ሲለካ፤ የትግራይ ህዝብ ደግ ነው ያደረገው፡፡ የትግራይ ህዝብ ህወሀትን ለመደገፍ የሚያበቃ፤ ማንም ምክንያታዊ ሰው የሚቀበለው፤ በቂ ምክንያት አለው፡፡ ቢያንስ ከማህጸናቸው የወጡ ልጆች፤ አንድን፤ ሀያል የተባለን ሰራዊትና ስርአት አሸንፈው፤ በማእከላዊ መንግስት ውስጥ ጉልህ ሚና ሲጫወቱ ማየት ማንንም ያኮራል፡፡ ስለዚህ የትግራይ ህዝብ በልጆቹ ቢኮራ፤ ህወሀትን ቢደግፍ ብዙም አያሰደንቅም፡፡ አያስቆጣምም፡፡ ትናንት ጦርነት ይካሄድበት የነበረ ምድረ፤ በተወሰነ መልኩ፤ ከጦርነት ተላቆ፤ ከብቶች በሰላም የሚግጡበት፤ ሰዎችም በሰላም ወደስራ የሚሰማሩበት፤ ልጆች የሚማሩበት፤ የስራ እድሎችና የንግድ እንቀስቃሴዎች የሚሟሟቁበት ሁኔታ ሲፈጠር፤ ቀድሞ ከነበረው ጦርነት ጋር በማስተያየትም ይሁን በራሱ፤ ያንን ሰላማዊ ህይወት የሰጠን ህወሀት ነው ብለው ቢያምኑና ቢደግፉት ሊያስከስሳቸው አይገባም፡፡

7- ሕዝብ ባይወቀስም፤ የትግራይ ህዝብ ግን መወቀስ ካለበት ሊያስወቅሰው የሚገባው፤ ሕወሀት በሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወገኖቹ ላይ የሚሰራውን ሸፍጥና ተንኮል ያወቀና የተባበረ እንደሁ ነው፡፡ ከላይ እንዳልኩት፤ የትግራይ ህዝብለ ራሱም የጭቆና ሰለባ በመሆኑ እንጂ፤ በሌሎች ወገኖቹ ላይ የሚደርሰውን ግፍ አውቆ ሕወሀትን አይደግፍም፡፡ በዚህ የትግራይ ህዝብ በሙሉ ሕወሀትን አውቆና ነቅቶ ይደግፋል በሚለው የአስተሳሰብ መንገድ ከተጓዝን፤ እድለኞች ሆነን፤ እንደብርሀኑ ነጋ ሸዋ፤ እንደኤፍሬም ማዴቦ ሌላ ቦታ፤ እንደኔ ቦረና ካልተወለድን በስተቀር፤ ሁላችንም ከዚህ ክስ አንተርፈም፡፡ ሁላችንም፤ ትግራይ ተወልደን አድገን ቢሆን፤ እስከተወሰነ ደረጃ ሕወሀትን ከመደገፍ ወደኋላ አንልም፡፡ ነአምን ዘለቀ፤ አልማዝ መኮ፤ ኡስታዝ አቡበከር፤ አበበ ገላው፤ ሲሳይ አጌና፤ ተክሌ የሻው፤ ብርሀኑ ነጋ፤ ሌንጮ ለታ፤ ጃዋር መሀመድ፤ ታማኝ በየነ፤ ወይም እኔም ራሴ ትግራይ ብንወለድ ሕወሀትን የመደገፍ እድላችን በጣም ሰፊ ነው፡፡ እኔ እንኳን ዘወትርም የተቃራኒን ጎራ ክርክር ማየት ደስ ስለሚለኝ፤ ቀንደኛ የህወሀት ደጋፊ ላልሆን እችላለሁ፡፡ የሆነ ሆኖ ግን፤ ዛሬ መፈክር ይዘው ትግሬ ይውደም የሚሉ ሁሉ፤ ትግራይ ተወልደው ቢያድጉ አክራሪ ትግሬዎች ነበር የሚሆኑት፡፡

8- ብዙ ታዋቂ አክራሪ ኢትዮጵያዊያን አሉ፡፡ ብዙ አክራሪ ኦሮሞዎችም አሉ፡፡ ብዙ አክራሪ አማሮችም እተፈጠሩ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ትግራይ ተወልደው ቢያድጉ፤ አክራሪ ትግሬዎች ነበር የሚሆኑት፡፡ የትግራይ ህዝብ ሁሉ ወያኔን ይደግፋል የሚለው መከራከሪያ ካሳመነን፤ እንግዲያውስ ማናችንም ትግራይ ብንወለድ እንደትግራይ ህዝብ ነው የምናደርገው፤ ወያኔንን እንደግፋለን፡፡ ስለዚህ፤ እስክናጣራ፤ ትግሬ ሁሉ ወያኔ ነው የምንል ሰዎች፤ ስለትግሬዎች ስንናገር፤ ስለራሳችንም እየተናገርን ነው፡፡ እስኪጣራ፤ አማራ ሁሉ፤ ትምክህተኛ ነው፡፡ እስኪጣራ፤ ኦሮሞ ሁሉ ጠባብ ነው፡፡ እስኪጣራ፤ እስላም ሁሉ ሽበርትኛ ነው አይነት ነገር፡፡ ያ ትክክል አይደለም፡፡ ገደል የሚከት አስተሳሰብ ነው፡፡

9- የትግራይ ህዝብ ግን አውቆና ነቅቶ ሕወሀትን ይደግፋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ወይንም ሕወሀት በሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች (ወይ ጉድ፤ ሕዝቦች ማለት ለመድኩ እኔ ራሴ)፤ በተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የሚፈጸመውን ግፍና ጭቆና አውቆ፤ ወይም የተወሰነ አብላጫ ተጠቃሚነት ካገኘም፤ ያ ተጠቃሚነት የመጣው በሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጭቆናና በደል እንደሆነ ቢረዳ፤ አቅምና እውቀት አንሶት ካልሆን በስተቀር፤ የትግራይ ሕዝብ ከህወሀት ጎን ይሰለፋል ብዬ አልገምትም፡፡ ከደገፈም ሌላ ምርጫ ስላልተሰጠው ይመስለኛል፡፡ ልብ በሉ፤ የትግራይ ህዝብ ላይ የተለቀቀው የ43 ምናምን አመታት ፕሮፓጋንዳ አለ፡፡ ጥርነፋውስ፡፡ የትግራይ ህዝብ ከተቀረው ኢትዮጵያ ህዝብ በፊት ነው አስቀድሞ የተጠረነፈው፡፡ ሌላ እንዳይሰማ፤ ሌላ እንዳያውቅ ተደርጎ የታፈነና የተቀፈደደ ህዝብ ነው፡፡

10- ገብሩ አስራት እንደጻፈው፤ ብዙዎች ሕወሀትን ጠንቅቀው በሚያውቁ ሰዎች እንደተነገው፤ ሕወሀቶች በትግላቸውም ይሁን በአገዛዛቸው ዘመን፤ እንዴት አድርገው ከነሱ አመለካከት የተለየ አመለካከት ያላቸውን ትግሬዎች ሁሉ አጥፍተው እዚህ እንደደረሱ ገልጧል፡፡ በነገብሩ ላይ የደረሰው፤ የሕወሀትን አንድ ወጥ አመለካከት ለመቅረጽ የሚሄድበትን ርቀት የሚያሳይ ነው፡፡ ከነሱ የተለየውን ከማሰር፤ ከማሰቃየት፤ ከማደህየት፤ ከማግለል፤ ካስፈለገም ከመግደል ጭምር አይመለሱም፡፡ ሕወሀት የተቀረውን ኢትዮጵያ የሚያስተዳድርበትን መንግድ በደንብ ከተመለከትንም፤ ያ በሌሎች ክልሎች ያየነው፤ ሕወሀት እንዴት አድርጎ ትግራይን አፍኖ እንደሚስተዳድር ይነግረናል፡፡ ስለዚህ ይሄንን የታፈነ ህዝብ፤ በማያውቀውና በሌለበት፤ እንዴት ከተቀረው ህዝብ አይቆምም፤ ወይም ዝም ያለው ደግፎ ነው ብሎ መውቀስ ተገቢ አይደለም፡፡

11- እንደህዝብ፤ ጭቁን የትግራይ ህዝብ ከተቀረው ምስኪን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚለየው ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ አንዲት የትግራይ እናት፤ ልክ አንድ የኦሮሞ እናት፤ ወይም አንድ የአማራ እናት ወይም አንድ የጉራጌ እናት ያላት ደግነት አላት፡፡ የትግራም አባት እንደዚያው፡፡ ይሄንን መርሳትና፤ የተወሰኑ ትግሬዎች፤ ከተወሰኑ አማራዎችና ኦሮሞዎች ጋር ተባብረው ለሚሰሩት ወንጅል፤ የትግራይን ህዝብ ብቻ ወይንም ትግሬን በነቂስ መወንጀል ጤናማ ክስ አይደለም፡፡ ይሄ ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብም አይደለም፡፡ የአማራ ህዝብ በስሙ ግፍ ከተሰራ፤ ግፍ ሰሪዎቹ እንጂ አማራው እንደማይጠየቀው ሁሉ፤ የትግራይ ህዝብም እንደዚያ በስሙ ለሚሰራ ግፍ ተጠያቂ ሊሆን አይችልም፡፡ መቼም ዛሬ አማራውንም፤ ኮንሶውንም፤ ኦሮሞውንም የሚገድሉት ጥይቶች ትግርኛ ይናራሉ ካላልን በስተቀር፤ አማራና ኦሮሞ፤ ወይም ጋምቤላና ሶማሌ ሰው ላለመግደሉ ማስረጃ የለንም፡፡ ስለዚህ፤ ይሄ ትግሬ ላይ ያነጣጠር ክስ በደንብ ይፈተሸ፡፡ በብሄር መጠየቅ ከመጣ፤ በአማራው ላይ የሚቀርበው ክስ ይገዝፋልና፡፡

12- ትግሬን ብቻ ነጥሎ የሚከስ አካሄድ፤ ጸረ-ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ በዘመናት ሂደት የተገመደ ኢትዮዊነታችን የምንለውን ነገር ባዶ ያስቀረዋል፡፡ አለበለዚያ የምንለው ኢትዮጵያዊነት ጎዶሎና ሰንካላ ነው፡፡ በውስጡ ዘረኝነት የተበረዘበት ወይንም ሀሳዊ ኢትዮጵያዊነትን ነው የምናራምደው ማለት ነው፡፡ ሰው በተገደለ ቁጥር ብድግ ብለን አንዱን ብሄር ተጠቂ አንዱን ብሄር ተጠያቂ የምናደርግበት ማንነት መሆን የለበትም፤ ኢትዮጵያዊነት፡፡ ኢትዮጵያዊነት፤ ከዚያ ይሰፋል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከዚያ ይጠልቃል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ትንሽ ትግሬነት፤ ትንሽ አማራነት፤ ትንሽ ኦሮሞነት፤ ትንሽ ትንሽ ከየብሄሩ የተወጣጣ፤ ክፋትም ልማትም ያለበት ስሪት ነው፡፡ ባለፈው እንደጻፍኩት፤ ስልጣኔን ተጋርተን፤ ሰይጣንነትን ግን ላንድ ብሄር ብቻ የምንጭን ከሆነ፤ ያ ጸረ-ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡

13- ኢትዮጵያዊነት ገና ያላለቀ ሂደት ነው፡፡ ሲጀመር ሲቋረጥ፤ ሲጀመር፤ ሲቋረጥ፤ አንዱ ሲጀምር ሌላው ሲያፈርስ፤ አሁን ደግሞ ኢህአዴግ የጀመረው ኢትዮጵያዊነት እነሆ እዚህ አደረሰን፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ፤ የአርከበ እቁባይ ሚና ይበዛ እንደሆን እነጂ፤ የሙክታር ከድርም አስተዋጽኦ አለበት፡፡ የጌታቸው አሰፋ ወንጀል ይገዝፍ እንደሆን እንጂ፤ የኩማ ደመቅሳ አድርባይነትም አለበት፡፡ እነአባይ ጸሀዬን ወንጅሎ፤ እነአባዱላ ገመዳን፤ እነገዱ አንዳርጋቸውን መተው ስህተት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ችግሮች፤ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡ ይሄ የጳውሎስ ነው፤ ይሄ የአጵሎስ አልልም፡፡ ስለዚህ የትግራይ ህዝብን ወይም ትግሬዎችን የጥቃት ዒላማ ያደረገ ፕሮፓጋንዳ መቆም አለበት፡፡

14- ይልቅስ፤ እንደሀሳብ፤ ትግሬዎችን ወይም የትግራይ ህዝብን፤ የጥቃት ዒላማ ሳይሆን፤ የንቃት ማእከል ያደረገ ፕሮፓጋንዳ ያስፈልጋል፡፡ አሁን አሁን ሳስበው፤ ኢሳት ከኦሮምኛ ይልቅ፤ ትግርኛ ፕሮግራም ቢጀምር የተሻለ ነበር፡፡ መጀመርም አለበት፡፡ ሕወሀት የጋተውን ለማስተፋት፤ ሕወሀት የሞላውን ለማጉደል፤ ሕወሀት ያሳሳተውን ለማስተካከል፤ ሕወሀት የጋረደውን ለመቅደድ ያለመ ፕሮፔጋንዳ ያስፈልጋል፡፡ ትግሬዎችን የሚያገልና የሚስደነግጥ ሳይሆን፤ ትግሬዎችን የሚያቅፍና የችግሩም የመፍትሄውም አካል ያደረገ ፕሮፔጋንዳ ነው የሚያስፈልገን፡፡ ጎበዝ፤ በሱ ላይ እንስራ፡፡ አሁን እየተከሄደበት ያለው የፕሮፓጋንዳ ስልት ግን፤ ከኢትዮጵያ ይልቅ፤ ለኢህአዴግ ያደላ ስልት ነው፡፡ ምክንያም፤ አንድም ጭፍንና የመንጋ ባህርይን የሚያበረታታ ነው፤ አንድም ትግሬዎችን ሁሉ በፍራቻ ከኢህአዴግ ጉያ የሚያስገባ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ፤ ትናንት በብሄራችን ተጠቃን ብለው እሪ ሲሉ በነበሩ አማሮች ሲቀጣጠል፤ አያምርም፡፡ ይሄ መታረም አለበት፡፡ ያበለዚያ፤ በ2009 እኔም ትግሬ ነኝ ብዬ አውጃለሁ፡፡ ለነገሩ፤ ኢትዮጵያዊ ብሄር የለውም፡፡ ብሄሬ በኢትዮጵያዊነት እሳት ቀልጧልና፡፡

ተክለሚካኤል አበበ፤ ቶሮንቶ፤ ካናዳ፤ መስከረም፤ 2009

ተራራም ይሰረቃል? የራስ ዳሽኑ ፖለቲካ ክንፉ አሰፋ

$
0
0

ራስ ዳሸን ተራራ ከትግራይ “ክልል” ካርታ የመውጣቱ አሲዮ ቤሌማ በብሄራዊ ቴሌቪዥን ሲነገር፤ “ደፍረውናል! ንቀውናል! ብታምኑም ባታምኑም በቁም ሞተናል!” የሚለው የኮሎኔል መንግስቱ ንግግር በጆሮዬ ላይ አቃጨለ። ድፍረቱ እና ንቀቱ እንዳለ ሆኖ፣ በቁም የሞቱት ግን እኛ ሳንሆን እነሱ መሆናቸውን የሚያበስር የዜና እወጃ ነበር።

ነገሩ እንጂ ሁሉም የተለመደ ነገር ነው። ውሃ ይጠፋል፣ መብራት ይጠፋል፣ ስልክ ይጠፋል፣ ገንዘብ ይጠፋል፣ ኮንዶሚንየም ህንጻም ይጠፋል። ይህ በህወሃት ፖለቲካ ጥርሳቸውን ላልነቀሉትም አዲስ ነገር አይደለም። ዘረፋም ለነሱ አዲስ አይደለም። መንግስት ሆነው ከተቀመጡ በኋላ እንኳን 10 ቶን ቡና ሰርቀዋል፣ የመብራት ጀነሬተሮች ሰርቀዋል፣ ከብሄራዊ ባንክ ወርቅ ሰርቀዋል… የህዝብን ድምጽም በተደጋጋሚ ሰርቀዋል። ተራራ ተሰርቆ ሲመለስ ግን የመጀመርያው ነው።

ከኢትዮጵያ አንደኛ፣ ከአፍሪካ ደግሞ በከፍታ 4ኛው ተራራ ነው ራስ ዳሸን። ከሰሜን ጎንደር ከየዳ ወረዳ ተሰርቆ ለ25 አመታት ሙሉ ትግራይ ክልል ገብቶ ነበር። ወንጀሉ ወደ ትግራይ “ክልል” መግባቱ ብቻ አይደለም። አንድ ትውልድ እና በስነ-ምድር ሳይንስ በውሸት ታሪክ እንዲታነጽ መደረጉ እንጂ!

በነገራችን ላይ በመላው ሃገሪቱ መስከረም 2 ላይ መጀመር የነበረበት ትምህርት እስካሁን አልተጀመረም። ምክንያቱም ግልጽ ነው። ተማሪዎች እየተካሀደ ያለውን አመጽ መጨረሻው ደረጃ ያደርሱታል በሚል ስጋት ነው። በሁለተኛው አለም ጦርነት ግዜ እንኳን ትምህርት አልተቋረጠም ነበር። ሂትለር ትምህርት እንዳይቋረጥ አዝዞ ነበር። ጦርነት እየተካሄደም፣ ትውልድ እንዳይጠፋ ውስጥ ለውስጥ ትምህርት ይሰጥ ነበር። የኛዎቹ ጉዶች ግን ለአራት ወይንም አምስት ሰዎች ስልጣን ጥማት ሲባል “ትምህርት ገደል ይግባ” ያሉ ይመስላል።

ለመሆኑ ማን ነው ወንጀለኛው? መምህሩ፣ ህዝቡ ወይንስ ስርዓቱ? በመማርያ ካሪኩለም ውስጥ ራስ ዳሽንን ትግራይ ካርታ ውስጥ አስገብተው፣ መጽሃፍም አሳትመው ሲያበቁ ፣ የንግድ ድርጅቶቻቸውን ዳሽን ባንክ፣ ዳሽን ቢራ… እያሉ የሰየሙት የ”አማራው” ተወካዮች ከዶሮ ያልታሻለ ጭንቅላት ይዘው፣ ስብእናቸውን እና ማንነታቸውን ጥለው ፓርላማ የተባለው ጉረኖ ውስጥ ተሰግስገዋል።

አንድ ትውልድን በዘረኝነት መርዝ ብቻ ሳይሆን በዚህ አይነት ውሸት ክመረዙ በኋላ ይቅርታ መጠየቁ ምን ይበጃል? በፈተና ግዜ ራስ ዳሽን ተራራ የሚገኘው በሰመን ጎንደር ነው ብለው የወደቁትስ የአእምሮ ካሳ ሊከፈላቸው ነው? የህወሃት ሰዎች አፍ እንጂ ጆሮ ስለሌላቸው ጥያቄዎችወች እንጂ አንድም መልስ አናገኝም።

ለመጀመርያ ግዜ ከህወሃት አንደበት ይቅርታ የሚል ነገር ሰማን ልበል? አንድ የፖለቲካ ተንታኝ በአንድ ወቅት ሲናገር የበታችነት ስለሚሰማቸው ይቅርታን ከሌላው ይሿታል እንጂ ፈጽሞ አይሏትም እንዳለ ትዝ ይለኛል። ይህ አንደኛው መጨረሻውን ጠቋሚ መሆኑ ነው። በመጨረሻም እንዲህ ይሆናል። የፖለቲካ እስረኞች ይፈታሉ። ይቅርታ ማለት ይጀምራሉ። አጠር ያለች ረጅም የአብዮት ትንታኔ!

ይህ ይቅርታ ከመባሉ ሳምንታት በፊት፣ ሰላሳ ሚሊዮን አማራን ማጥፋት የሚችል ሃይል እንዳላቸው ደብረጽዮን በፌስ ቡክ ገጻቸው ጽፈውልናል። “አባ በጠጡ አቃቢቱን…” እንዲሉ ይህንን የደብረጽዮን ጽሁፍ ሃይለማርያም ተቀብለው ሲያበቁ በመገናኛ ብዙሃን ቀርበው አንቦርቅቀውታል። “አብዮታዊ ሰራዊቱ ሕዝቡን እንዲገድል ትእዛዝ ሰጥቻለሁ!” ያሉ መሰለኝ። ለማመን እስኪከብድ ሂትለራዊ ቀረርቶ እና ፉከራም ሳይቀር አሰምተውናል። እነ አቦይ ስብሃት ታዲያ ጥጋቸውን ይዘው፣ በጨበጡት ብርጭቆ ሰንጥቀው እየመነጠሩዋቸው “ደፋር!” ሳይሏቸው አልቀረም። “ስልብ፣ በጌታው ብልት ይፎክራል!” ይላሉ አበው።

ሕዝብን ለመጨረስ ትዕዛዝ አስተላልፈናል ያሉበት አንደበታቸው ገና ሳይዘጋ ከጎንደር የሰረቅነውን ተራራ መልሰናል። ይህንን ተራራ ትግራይ ላይ አኑረነው ስለነበር ይቅርታ! ብለው መናገራቸው ጨዋታ የመቀየር ስልት መሆኑ ነው። ሕዝብ ቀድሟቸው ባይሄድ ኖሮ ሊሸውዱት ይሞክሩ ነበር። የተለመደ ነጠላ ዜማ፣ በተመሳሳይ ግጥም – በተመሳሳይ ዜማ ይዘው መከሰታቸው ግን ከእንሰሳ እንኳን ያልተሻሉ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው። ህዝቡን የሚያዩበት መነጽር አሁንም አልቀየሩትም።

ራስ ዳሽንን ከይቅርታ ጋር ለባለበቱ መልሰናል ብለዋል። ከዚህ ቀደምም የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ተገቢ ነው ብለውናል። የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ተገቢ መሆኑን የባነኑት የአማራ ሕዝብ ሲነሳ መሆኑ ግን የፖለቲካ ጨዋታውን ቀልድ አስመስሎታል። በዚህ አላበቁም ለፈሰሰው የወገናችን ደም ካሳ እንደሚከፍሉም ተናግረዋል። የሰው ልጅን ህይወት እንደ እቃ ቆጥረው ሲያበቁ በገዛ ራሱ ገንዘብ ሊክሱት ቃል መግባታቸው የባሰ ያሳምማል። የህይወት ካሳ አለ እንዴ? ለመሆኑ የአንድ ሰው ነብስ ስንት ያወጣል?

የራስ ዳሽን መመለስ ኢትዮጵያ አሁን የገባችበትን ችግር አይፈታውም። የሕወሃትን ማንነትን ግን የበለጠ ይፋ አድርጎታል።

“ማኔ፣ ቴቄል፣ ፋሬስ”፡- ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ./መንግሥት ሆይ በሚዛን ተመዝነህ ቀለህ እየተገኘህ ነውና እንግዲህ እንጠይቅህ …ተጠየቅ …?! በተረፈ ወርቁ

$
0
0

ይህን “ማኔ፣ ቴቄል፣ ፋሬስ” የሚለውን ኃይለ ቃል የምናገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ በትንቢተ ዳንኤል መጽሐፍ ክፍል ውስጥ ነው፡፡ የዚህ ጽሕፈት ምክንያትና ትርጓሜ ታሪክ በአጭሩ እንዲህ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆኑት እስራኤላውያን በኃጢአታቸው፣ በክፋታቸውና በዓመፃቸው የተነሳ እግዚአብሔር ተቆጥቷቸው፣ አዝኖባቸው ነበር፡፡ እናም አምላካቸው ጠላቶቻቸውን፣ ወደረኞቻቸውን በላያቸው ላይ አሥነስቶባቸው በጦርነት ድል ኾነው፣ ውርደትንና ሃፍረትን ተከናንበው፣ ከምድራቸው፣ ከአባቶቻቸው ርስት ተነቅለው በባዕድ ምድር ምርኮኛ፣ ግዞተኛና ተንከራታች ሕዝብ ሆነው ነበር፡፡

በግዞት፣ በባዕድ ምድር ከእናት ምድሩ ከኢየሩሳሌም ርቆ፣ በስደት ሀገር ባቢሎን በአሕዛብ ምድር የነበረው የእግዚአብሔር ሰው ነቢዩ ዳንኤል – የአንቺ የይሁዳ ምድር፣ የአባቶቼ ርስት “ኢየሩሳሌም ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ፣ ምላሴም ከትናጋዬ ጋር ይጣበቅ …!” በሚል ሰቀቀንና ናፍቆት፣ የኀዘን እንጉርጉሮ፣ የወገኖቹን ኃጢአት በደላቸውን፤ ፍዳ ሐበሳቸውን ተሸክሞ፣ የሕዝቡን ውርደታቸውንና ሥቃያቸውን፣ መከራና ሰቆቃቸውን፣ ዋይታና ጩኸታቸውን … የአባቶቻቸው አምላክ ያህዌ ከሰማይ በቃ ይልና ወደ ምድራቸው፣ ወደ አባቶቻቸው ርስት ይመልሳቸው ዘንድ በጸሎቱ፣ በእንባው ስለ ሕዝቡ የተማፀነ፣ አብዝቶ የቃተተ፣ የተሟገተ ብርቱ ነቢይ ነበር፡፡ መጽሐፍ እንዲህ እንዲል፡-

“በከለዳውያን መንግሥት ላይ በንገሠ … በአሕሻዊሮስ ልጅ በዳርዮስ በመጀመሪያ ዓመት እኔ ዳንኤል የኢየሩሳሌም መፍረስ የሚፈጸምበትን ሰባውን ዓመት፣ እግዚአብሔር በቃሉ ለነቢዩ ለኤርምያስ የተናገረውን የዓመቱን ቁጥር በመጽሐፍ አስተዋልሁ፡፡ ማቅ ለብሼ በአመድም ላይ ሆኜ ስጾም፣ ለሕዝቤና ለሀገሬ እጸልይና እለምን ዘንድ ፊቴን ወደ ጌታ አምላክ አቀናሁ፡፡” ዳን. ፱፣፩-፲፱፡፡

ታዲያ ይህ የሀገሩና የሕዝቡ መጥፋት አብዝቶ የሚገደው፣ ሕዝብህ በባዕድ ምድር ያለ መሪና እረኛ የትም ተበትኖ፣ ባዝኖ አይቅር … አቤቱ እባክህ ሕዝብህን አስብ፣ ርስትህንም ባርክ – እያለ ማቅ ለብሶ ትቢያ ነስንሶ፣ በአመድ ላይ ተቀምጦ እግዚአብሔር አምላክ ሕዝቡንና ምድሩን በምሕረትና በቸርነት ይጎበኝ ዘንድ የመከራ እንጀራን እየበላ ሱባኤ የገባ፣ በእንባና በጸሎት ወደ ፈጣሪው ስለ ሕዝቡ አጥብቆ የጸለየ፣ የማለደና የቃተተ ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው ነበር ነቢዩ ዳንኤል፡፡ (እዚህች ጋር እግረ መንገዳችንን አንድ ትዝብት አከል ጥያቄ እናንሳ እስቲ … እንደው በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ክቡር የሰው ልጅ በየአደባባዩ በጥይት እየተመታ፣ ደሙ በግፍ ሲፈስ- ምድሪቱ አኬል ዳማ ሆና የኢትዮጵያ እናቶች የፍርድ ያለህ እያሉ እንባቸውን ወደ ሰማይ ሰማያት ሲረጩ፣ ዋይታና ጩኸት በየአቅጣጫው ሲሰማ- ሕዝብም:-
“እነርሱ አዲስ አበባ – ተነጋገሩና፣
ካርታውን ድንበሩን – ጨርሰው ላኩና፣
ወንድምህን ጠላት ነው – ብለው መከሩና፣
ወንድምየው ሞተ – እግዜሩም ተናቀ፣
ና! ውረድ አንተ አምላክ – ወገን ተላለቀ፡፡”

እያለ የኀዘን እንጉርጉሮውን ሲያሰማና ሙሾውን ሲያወርድ የየትኛው የሃይማኖት ተቋም የሃይማኖት አባቶችና መሪዎች ናቸው እንደ ነቢዩ ዳንኤል ማቅ ለብሰው ትቢያ ነስንሰው ስለ ሕዝብና ስለ አገር ጥፋት ከሕዝባቸው ጋር ሱባዔ የገቡት …?! የትኛዎቹ የሃይማኖት አባቶች ናቸው- መንግሥትን ገሥጸው፣ ሕዝብን በፍቅር ቀርበው አረጋግተው፣ የዕርቀ ሰላም ሥራ የሠሩት … እንደውም አንዳንዶቹ ከሰሞኑን እንደታዘብነው በቲቪ ቀርበው፣ በመንግሥት ሳምባ የሚተነፍሱ “ልማታዊ የሃይማኖት መሪዎች” መሆናቸውን በደንብ አስረገጡልን እንጂ … የሃይማኖት መሪዎቻችንን የአዲስ ዓመት የመልካም ምኞት መግለጫዎችን ያስታውሷል፤ ያስተውሏል፡፡)

“ንግባዕኬ ኀበ ጥንተ ነገር” እንዲሉ አባቶቻችን ሊቃውንት፣ ወደ ቀደመ ጉዳያችን እንመለስ፡፡ ነቢዩ ዳንኤል ከሕዝቡ ጋር በግዞት በነበረበት ባቢሎን ምድር በአንድ ወቅት ንጉሡ በቤተ መንግሥቱ ታላቅ ግብዣ ላይ መኳንንቱን፣ ታላላቅ ሹማምንቱን፣ ባለሟሎቹንና እቁባቶችን ሰብስቦ እግዚአብሔርን ያሳዘነ ፀያፍና የማይገባ ነገርን ያደርግ ጀመረ፡፡ የዚህን ጊዜ የሰው እጅ ጣቶች በንጉሡ እልፍኝ ግድግዳ ላይ እንዲህ ጻፈች:- “ማኔ፣ ቴቄል፣ ፋሬስ”፤ ንጉሡ ይህን ጽሑፍ ባየ ጊዜ በድንጋጤ ተመታ- ፊቱ ተለወጠበት፣ የወገቡ ጅማት ተፈታ፣ ጉልበቱ ከዳው፣ ብርክ ያዘው፡፡

አንዳንች ክፉ ድንጋጤ የወረደበት ንጉሥ ብልጣሶር የዚህን ጽሑፍ ምስጢር ይፈቱ ዘንድም በአስቸኳይ የከለዳውያንን ጠቢባን ሁሉ ወደ እልፍኙ አስጠራ፡፡ ግና የባቢሎን ጠቢባን የዛን ጽሑፍ ምስጢር፣ ፍቺ ለንጉሡ ሊፈቱለት አልተቻላቸውም ነበር፡፡ የዚህን ጊዜ ነበር የእግዚአብሔር ሰው የሆነውን የዳንኤልን ማስተዋልና ጥበብ ጠንቅቃ የምታውቀው የንጉሡ የብልጣሶር ሚስት ወደ እልፍኙ ዘልቃ፣ ወደ ባለቤቷ ጆሮ ተጠግታ በባቢሎን ምድር ከዳንኤል ውጭ የዚህን ጽሕፈት ምስጢር የሚፈታ ማንም ሌላ ሰው እንደሌለ ሹክ አለችው፡፡ “የሴት ብልሃቱን የጉንዳን ጉልበቱን፤ የሴት ምክር የእሾህ አጥር፡፡” እንዲሉ አበው ንጉሥ ብልጣሶር በሚስቱ ደገኛ የምክር ቃል አማካኝነት የእግዚአብሔር ሰው ዳንኤል ወደ ንጉሡ እልፍኝ በክብር ተጠርቶ ገባ፡፡

ዳንኤልም በዙፋኑ ላይ በመኳንንቱ፣ በሹማምንቱና በእቁባቶቹ ተከቦ በድንጋጤ ግራ ተጋብቶ የተቀመጠውን ንጉሥ ብልጣሶርን እንዲህ አለው፤ “ንጉሥ ሆይ እግዚአብሔር አምላክ ለአባትህ ለናቡከደነፆር ሰፊ መንግሥትንና ግዛትን፣ ክብርንና ግርማን ሰጠው፡፡ እርሱ ግን ልቡ በታበየ፣ በኩራትም ያደርግ ዘንድ መንፈሱ በጠነከረ ጊዜ ከመንግሥቱ ዙፋን ተዋረደ፣ ክብሩም ተለየው፡፡ ከሰው ተለይቶም ተሰደደ፣ ልቡም እንደ አውሬ ልብ ሆነ፣ መኖሪያውም ከምድረ በዳ አህዮች ጋር ነበረ፤ እንደ በሬ ሣር በላ፣ አካሉም በሰማይ ጠል ረሰረሰ፡፡ አንተም ይህን ሁሉ ስታውቅ በአባትህ የክፋት፣ የዓመፃ፣ የትዕቢት መንገድ ሄደሃልና ውርደትህና የዓመፅ ደመወዝህ እነሆ በፊትህ አለ …፡፡

ይህ ጽሕፈትም ስለ ክፉ ሥራህና ስለ መንግሥትህ አሳዛኝ ፍጻሜ እንዲህ ተጽፎአል፡፡ የጽሑፉ ፍቺም እንዲህ ይተረጎማል፡፡ ንጉሥ ሆይ ሺህ ዓመት ንገሥ … በረከትህ ለአንተ ይሁን፣ ለእኔ ያልከውን ሽልማትህንና ክብርህንም ለሌላ ሰው አድርገው፤ የነገሩ፣ የጽሕፈቱ ፍቺ ግን ይህ ነው፤ “ማኔ ማለት፥ እግዚአብሔር መንግሥትህን ቈጠረው ፈጸመውም ማለት ነው፤ ቴቄል ማለት፥ በሚዛን ተመዘንህ፥ ቀልለህም ተገኘህ ማለት ነው፡፡” በማለት የእግዚአብሔር ሰው የሆነው ዳንኤል ለባቢሎን ንጉሥ ለብልጣሶር አሳዛኝ የሆነውን የእርሱንና የመንግሥቱን ፍጻሜውን እንዲህ አረዳው፡፡
“እግዚአብሔር ሲቆጣ በትርን አይቆርጥም፣
ያደርገዋል እንጂ ለወሬ እንዳይጥም፡፡”

እንዲሉ አበው – የንጉሥ ብልጣሶር መንግሥት ፍፃሜው ያማረ አልሆነምና፣ በዛው ሌሊት በጠላቶቹ ተይዞ፣ በግፍ ተገደለ። መንግሥቱና ግዛቱም ለሁለት ተከፍሎ ለሜዶንና ለፋርስ ነገሥታት ተላልፎ ተሰጠበት፡፡ ታሪኩን በዚሁ ልግታውና ወደ ዋናው የዚህ መጣጥፌ ጭብጥ ልለፍ፡፡
ዛሬም ኢሕአዴግ/መንግሥት የቆመበት የታሪክ ጫፍና መስቀለኛ መንገድ ይህን ከላይ ያነሣሁትን ታሪክ የሚያጎላ መስሎ ቢሰማኝ ይህን አሳዛኝ ታሪክ እና “ማኔ፣ ቴቄል፣ ፋሬስ” የሚለውን የመጽሐፍ ኃይለ-ቃል የዛሬው መጣጥፌ አርዕስትና መግቢያ፣ መንደርደሪያ ይሆነኝ ዘንድ መረጥኩት፡፡ ሮማዊው የሕግ ሰው፣ ፈላስፋና የታሪክ ሊቅ የሆነው ሲስሮ፣ “ከታሪክ ለመማር የማይወዱ ሁሉ ታሪክን ለመድገም የተፈረደባቸው ናቸው፡፡” እንዲል፤ ከዘውዱና ከወታደራዊው የደርግ ሥርዓት አሳዛኝ ውድቀት ለመማር የፈለገ የማይመስለው ኢሕአዴግም ሌላ የጥፋት፣ የውርደት ታሪክ በራሱና በአገሪቱ ላይ ለመድገም በተጠንቀቅ የቆመ፣ የተፈረደበት ነው የሚመስለው፡፡

ዛሬ አርፍዶም ቢሆን ኢሕአዴግ/መንግሥት በመልካም አስተዳደር እጦት፣ የሕዝብ አገልጋይነት ቅን መንፈስ መራቆት ድርቅ ክፉኛ ተመትቼ እየተንገላታሁ ነው፣ ሙሰኝነት የሥርዓቱ/የመንግሥቴ አደጋ ሆኖ ከፊት ለፊቴ እንደ ዘንዶ ሊውጠኝ አፉን ከፍቶብኛል፣ የባለ ሥልጣናቶቼ ኪራይ ሰብሳቢነት ዓይን ያወጣ ሌብነት/የጠራራ ፀሐይ ዝርፊያ በአፍጢሜ ሊደፋኝ ደርሷል፣ የመበስበስና ዝቅጠት አደጋው ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍቶብኛል፣ ትምክህተኝነትና ጠባብነት እንደ አብሾ አናታቸው ላይ የወጣባቸው መንገዴን ሁሉ በእሾህ አጥረውና ዳጥና ጨለማ አድርገውት ግራ አጋብተውኛል፤

እስከ አንገቴ ያጠለቀኝ የሕዝብ የፍትሕ ያለ ጥያቄና ብሶት፣ ዋይታና ሮሮ ጎርፍ ሆኖ ጠራርጎኝ ከመወሰዴ በፊትም “በጥልቀት መታደስ/መለወጥ” አለብኝ በሚል ከጓዳ እስከ እልፍኝ ድረስ ተጠራርቶ በየክልሉ አፈርሳታ ተቀምጧል፤ እንግዲህ ወዶም ይሁን ተገዶ በሚዛን ላይ የወጣው ኢሕአዴግ ወይ ተመዝኖ ያልፋል አሊያም ደግሞ እንደ ገለባ ቀሎና ተቃሎ – “ማኔ፣ ቴቄል፣ ፋሬስ” ተብሎ በእግዚአብሔር ፍርድ – እንደ ትቢያ ተራግፎ፣ በሕዝብ ቁጣ ነፋስ ተገፍቶ በታሪክ ማህፀን ውስጥ ተጠቅልሎ አልፎ በጸጸት በነበር እናወሳው ይሆናል፡፡ መቼም ኢሕአዴግ መንግሥተ-ሥላሴ አይደለምና ለዘላለም አይኖርም፤ ሊኖርም አይችልም፡፡ ሀገርና ሕዝብ ግን ሁሌም ይኖራሉ፡፡ ኢሕአዴግ/መንግሥት ሆይ እንግዲህ የታሪክ እውነታው ይኼና ይኼው ብቻ ነው፡፡

ከዚህ የታሪክ እውነታ ባሻገር ግን … እስቲ በዚህ የጭንቅ፣ የጣር ቀን ወዶም ይሁን ፈቅዶ፣ አሊያም ባጋጠመው ተግዳሮት፣ ብርቱ ፈተና ማጣፊያው አጥሮት ሳይወድ በግድ ራሴን እገመግማለሁ፣ በጥልቀት አያለሁ፣ እፈትሻለሁ ብሎ ወደ ሚዛን ላይ ተገፍቶ የወጣውን የትናንትናውን የበረሃ ፋኖ የዛሬውን የኢሕአዴግ መንግሥት ታሪኩን፣ ገድሉን ከዛሬው የትግሉ ፍሬ ጋር እያነፃፀርን በጥቂቱ፣ በጣም በጥቂቱ እናየው፣ እንፈትሸው ዘንድ ወደድኹ፡፡

ያን ወርቃማ የወጣትነት አንዳንዶቹም ገና አፍላ የልጅነት ዘመናቸውን ምንም ነገር ሳይጓጓቸው – የእናት፣ የአባት፣ የቤተሰብ፣ የወዳጅ ዘመድ … ናፍቆትና ትዝታ ወደ ኋላ ሳይጎትታቸው ከሞቀ ቤታቸው፣ ከእናቶቻቸው ጉያና ነገ የተሻለ ኑሮንና ሕይወትን ከሚያመቻችላቸው ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ወጥተውና ርቀው ወርቃማ የወጣትነት ዘመናቸውን ለበረሃ የገበሩ- የበረሃው እዋይና ንዳድ … ፈጽሞ ሳይበግራቸው፣ ረሃቡና ጥሙን ታግሰው፣ አንጀታቸውን በዝናር መቀነት ጥብቅ አድርገው አስረው፣ ከጠኔ ጋር ታግለው፣ አንጀታቸው በረሃብ የተነሳ ክፉኛ ታጥፎ፣ በውሃ ጥም ጉሮሮአቸው እየተሰነጠቀ … የልጅነት ወዛቸው በፀሐይ ሐሩር ገርጥቶ፣ የወጣትነት ውበታቸው እንዲያ ከስሎና እንደ ምድጃ ጠቁሮ፣ ከሰውነት ተራ ወጥተው ብርቱ ሥቃይን ያሳለፉ እኒያ የትናንትናው የድሃው ገበሬ ልጆች፣ የጭቁኑን ወገናቸውን ተስፋውን፣ የነገ ሕልሙን ተሸክመው ረጅሙን ተራራ በጽናት የወጡ፣ ተራራን ያንቀጠቀጡ፣ ተራራን ያናወጡ ትውልዶች፣ ከእሳት የወጡ ትንታጎች፣ ፋኖዎች፤

ከላይ ሳያቋርጡ የእሳት አሎሎን ከሚያዘንቡ የጦር ጀቶችና አውሮፕላኖች፣ በምድር ላንቃቸውን ከፍተው ሳያባሩ የሞት መቅሰፍትን ከሚተፉ ከባድ የጦር መሣሪያዎች ፊት አንዳንች ፍርሃት ሳይበግራቸው፣ በታላቅ ጀግንነትና ወኔ ሞትን፣ ፍርሃትን ተቋቋመው ስለ ፍትሕ የተሟገቱ፤ በሞት ጣር ሸለቆ፣ አስፈሪ የጨለማ ፅልመት ውስጥ አልፈው፤ ከደሃው፣ ከጭቁኑ ገበሬ ጋር የበላውን በልተው፣ ረሃቡን ተርበው፣ ጥማቱን ተጠምተው፣ የመኝታ መደቡን ተጋርተው፣ በማጀቱና በጎታው ውስጥ ውለውና አድረው፣ ሀገርን ያህል – ኢትዮጵያን ያህል ትልቅ ምስጢር በልባቸው ቋጥረው – በምድር ልብ፣ በዋሻና በሸለቆ ውስጥ ለሕዝብ፣ ስለ ሕዝብ ከሕዝብ ጋር በአንድነት ቁመው፣ መክረውና ዘክረው፤

… አዎን እነዛ ፋኖ ብላቴናዎች፣ ታላላቅ ነን በሚሉት ዘንድ እጅግ የተናቁ፣ በብዙዎች ዘንድ አንዳንች ክብርና ሥፍራ የተነፈጋቸው፣ አብዝተው ስድብንና ንቀትን የጠገቡ ታናናሽ የሕዝብ ልጆች ባልፀና ጉልበታቸው፣ ባልጠነከረ ጫንቃቸው … ግን ደግሞ ከብረት በጠነከረ ወኔያቸው፣ ተራራን ባፈለሰ ፅናታቸው እንደ መርግ የከበደውን ያን ሁሉ የመከራ ውርጅብኝ ተሸክመውና ታግሰው፣ ስለ ጭቁኑ ወገናቸው ያላቸው ታላቅ ፍቅርና መቆርቆር – ኃይልና ጉልበት ሆኗቸው የሕዝባቸውን ቀራኒዮ በጽናት፣ በትዕግሥት የወጡ ባለ ድሎች፤ ባለ ገድሎች፡፡ ለፍትሕና ለዲሞክራሲ፣ ለነፃነት፣ ለሰው ልጆች መብትና እኩልነት ሲሉ በየበረሃው የወደቁ የታጋይ ጓዶቻቸውን የደም ቃል ኪዳንና የወገናቸውን ፅኑ፣ ታላቅ አደራ በልባቸው ጽላት ተሸክመው ረጅሙን ተራራ የወጡ የሕዝብ ባለ አደራዎች፤
ስለ ፍትሕ፣ ስለ ጭቁኖች መብትና እኩልነት፣ ስለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት … ገና ከማለዳው ‹‹ዱር ቤቴ›› ብለው ፋኖነትን ምርጫ ያደረጉና አብዝተው ስለ ጭቁኑ ወገናቸው የጮኹ፣ የቃተቱ … ላባቸውን፣ ደማቸውንና እንባቸውን በአንድነት ቀላቅለው ሳይሰስቱ ለሕዝባቸው ጥቅም የገበሩ- የድሃው ገበሬ የአብራኩ ክፋዮች፣ በእሳት የተፈተኑ፤ ታሪካቸውን፣ ገድላቸውን በደም የጻፉ፣ የሕዝብ ልጆች ትናንትና ነበሩን፣ ዛሬም አሉን …፡፡ ታሪካችንን ስንመረምር ድኅነትንና ኋላ ቀርነትን ለማጥፋት፣ ፍትሕና ዲሞክራሲን ለማስፈን በሚል ዓላማ ስር በየአቅጣጫው ተሰልፎ ከፍተኛ የሕይወት መሥዋዕትነትን የከፈለው የተማሪው፣ የገበሬው፣ የሀገሪቱ ምሁራንና ሕዝብ ቁጥር የትየለሌ ነው፡፡

ይህ መሥዋዕትነትና ታላቅ ገድል፣ ይህን አኩሪ ታሪክ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ኢትዮጵያ ጫፍ ያሉ ሕዝቦች ስለ ነፃነትና ፍትሕ፣ ስለ ሰው ልጆች እኩልነት፣ መብትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መስፈን ላባቸውንና ደማቸውን የገበሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በጋራ የሚጋሩት የሕዝብ ልጆች ሁሉ ታሪክና ገድል ነው እንጂ ከአንዳንድ የኢሕአዴግ አንጋፋ ታጋዮች ዘንድ በነጋ ጠባ እንደምንሰማው ሌላውን በጠላትነትና በፀረ ሕዝብነት ፈርጀው ብቻቸውን የሚኩራሩበት የእነርሱና የእነርሱ የብቻው የሆነ ታሪክ ወይም ገድል እንዳይደለ፣ እንዳልሆነም በቅን መንፈስ ለዛሬዎቹ ልባቸው በኩራት ለታበየባቸው የኢሕአዴግ ታጋዮችና ሹማምንት ልንነግራቸው እንወዳለን፣ እንደፍራለንም፡፡

የቀድሞው የሕወሓት አንጋፋ ታጋይ ሜ/ጄ አበበ ተ/ሃይማኖት/ጆቤ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ እንዳሉት፣ “ከ25 ዓመት በፊት በተገኘው የትጥቅ ትግል ድል አድራጊነት ታሪክ አልያም መንፈስ እየተኩራሩና እየተኮፈሱ መኖር አይቻልም። አንዳንድ ወገኖች፣ የትግሉ ድል ሕዝቦች በጋራ ያመጡት መሆኑን ክደው (የትግራይ ሕዝብ ከፍተኛ መሥዋዕትነት የከፈለ መሆኑ ሳይዘነጋ) ‘እኛ ያመጣንላችሁ ነጻነት ነው፤’ በማለት ሲኮፈሱ …” በማለት ያነሡት መከራከሪያ፣ የወቀሳ ሐሳብ ከላይ ያነሣሁትን ሐሳቤን የሚያጠናክርልኝ ይመስለኛል፡፡ ይህን የታሪክ እውነታ ከፍ ስናደርገው፣ ስናልቀው ደግሞ፡-

ለሦስት ሺህ ዘመናት የሚልቅ የሥርዓተ መንግሥት/State Formation የረጅም ዘመናት ታሪክ ያላትንና በበርካታ ፖለቲካዊ፣ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበረሰባዊ … ወዘተ- ውስብስብ የታሪክ ሂደቶችና ለውጦች ውስጥ ያለፈችን ታላቅ አገር- ኢሕአዴግ ዛሬ ደርሶ ትናንትና እንዳልነበረችና ዛሬ በእርሱ ትግልና ተጋድሎ ሕያው የሆነች ነገም ኢሕአዴግ ከሌለ ዕጣ ፈንታዋ የሚከፋ ሞቷም ሆነ ትንሣኤዋ በእርሱ እጅ ብቻ እንዳለ በመቁጠር – የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ “አልፋና ኦሜጋ” እርሱና እርሱ ብቻ እንደሆነ የማሰብ አባዜ፣ ታሪክን የመቀራምትና የመጠቅለል ሩጫ፣ ከልክ ያለፈ ኩራት/over dose pride ፈጽሞ ጤነኛ አካሄድ አይመስለኝም፡፡

ይህ ሕዝብ/ኢትዮጵያውያን እኮ የረጅም ዘመናት የነፃነት ተጋድሎ አኩሪ ታሪክ ያለውና ይህ ታሪኩ፣ ባህሉና ቅርሱ – ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ፣ ከአውሮፓ እስከ መካከለኛው ምሥራቅ፣ ጃማይካና ካሪቢያ ድረስ ተሻግሮ እልፍ የነፃነት ፋኖዎችን መንፈስና ወኔ የቀሰቀሰ፣ በጥቁር ሕዝቦች ላይ የተጫነን የቅኝ ግዛትን አስከፊ የጭቆና ቀምበርን የሰበረና የነፃነት ቀንዲልን የለኮሰ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ከጉራዕና ጉንደት እስከ መተማ፣ ከደባርቅ እስከ መቅደላ፣ ከዶጋሊ፣ አምባላጌ፣ መቀሌና ዐድዋ እስከ ማይጨው … ወዘተ ለነጻነታቸው፣ ለሉዓላዊነታቸው ያደረጉት ተጋድሎ- ለአፍሪካ አሜሪካውያኖቹ የጥቁሮች መብት ታጋዮች ለእነ ማርከስ ጋርቬይ፣ ማልኮሜክስ፣ ለዶ/ር ማርቲን ሉተር ለፓን አፍሪካኒስቶቹ – ለኬንያው የነጻነት አባት ጆሜ ኬንያታ፣ ለጋናው ለዶ/ር ክዋሜ ንኩርማ፣ ለደቡብ አፍሪካው የነጻነት፣ የፀረ አፓርታይድ ታጋይና አርበኛ ለኔልሰን ሮሂላላ ማንዴላ … ወዘተ የወኔ ስንቅ የኾነ፣ የአፍሪካና የመላው ጥቁር ሕዝቦች ኩራት የኾነ የአኩሪ ታሪክ ባለቤት ታላቅ ሕዝብ መሆኑን- ኢሕአዴግ/መንግሥት ፈጽሞ፤ ፈጽሞ ሊዘነጋ አይገባውም፡፡ ይቀጥላል፡፡
ሰላም!!

ህወሓት/ኢህአዴግ ከስልጣን ይውረድ የሽግግር መንግስት ይቋቋም ከትግራይ ተወላጆች የተሰጠ መግለጫ

የኦህዴዱ መሪ ወርቅነህ ገበየሁ ትግሬ ነው፤ ምስጢሩ እነሆ…ክንፉ አሰፋ

$
0
0

ከምርጫው ጥቂት አስቀድሞ የወርቅነህ ገበየሁ አያት ስም ገብረኪዳን ነበር። የቀድሞ ወዳጄ ወርቅነህ የአያቱን ስም ከገብረ-ኪዳን ወደ ኩምሳ ለመቀየር የወሰደበት ግዜ እና ምክንያቱ አላስደነቀኝም። ይህንን የዘር ፖለቲካ ጨዋታ ጠንቅቆ የሚያውቀው ዶ/ር መረራ ጉዲናም የተቃዋሚ እጩ ተመራጭ ነበር። ጉዳዩን ጠንቅቆ ያውቀዋል። በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ ፖለቲካ ሳይንስ ፋካልቲ ስንማር ሁለታችንንም በአንድ ክፍል አስተምሮናል። የወርቅነህ ትክክለኛ አያት ስም ያለበት ሰነድም በእጁ አለ። ግን ጉዳዩን አላጋለጠውም። ምናልባት የሙያው ስነ-ምግባር ይህንን ለማድረግ አይፈቅድ ይሆናል።

ወርቅነህ ገበየሁ ሻሸመኔ ነው ተወልዶ ያደገው። እዚያ መኖሩ ደግሞ ኦሮምኛን አቀላጥፎ እንዲናገር ረድቶታል። ዘር መቁጠር ጸያፍ ቢሆንም ይህ ግን ታወቅ ያለበት ጉዳይ ነውና ርቅነህ ገበየሁ ወላጆች ኦሮሞዎች አይደሉም። ከትግራዩ አቶ ገበየሁ ገብራኪዳን ይወለዳል።

ወርቅነህ ገበየሁ ውሎውም ቢሆን ከጆሌ ኦሮሞ ጋር አይደለም። ከነ ጌታቸው ረዳ፣ ከትግራይ ተወላጆች ጋር በብዛት ያዘወትራል። ለዚህም ምክንያት አለው። ይህ ሰው አሁን የኦሮሞውን ድርጀት እንዲመራ መመረጡ አንደኛው ምክንያት ነው። በህወሃት የፖለቲካ ጨዋታ ምክትል ሆነው የሚቀመጡት በዘር መስፈርት ተለክተው አልያም ታማኝ አገልጋይ ሲሆኑ ብቻ ነው። ዋናውን ስራ የሚሰሩትም በምክትል ስም ያሉት ናቸው። ከስር ሆነው ዋናዎቹን እንደ ሮቦት ያንቀሳቅሷቸዋል። ጠ/ሚ ሃይለማርያም ደሳለኝ እና ምክትሉ ደብረጽዮንን ያስተውሏል!

ለመሆኑ ወርቅነህ ገበየሁ ማን ነው? ለምንስ ታስሮ ተፈታ? የወንጀል እስረኛ የነበረ ይህ ሰው እንዴትስ በጥቂት ጊዜ እዚህ ደረጃ ላይ ሊደርስ ቻለ? ከዚህ ቀደም በማስታወሻዬ ላይ ያሰፈርኩዋትን ቁም ነገር ላካፍላችሁ። መልካም ንባብ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጭር ብሏል። ኢህአዴግ ወደ አዲስ አበባ ሲጠጋ፤ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ደግሞ ለወታደራዊ ስልጠና ወደ ብላቴ ማሰልጠኛ ካምፕ ገብተው የተኩስ ልምምድ በማድረግ ላይ ነበሩ። በግንቦት ወር ኢህአዴግ ከተማውን ከተቆጣጠረ በኋላ፤ ተማሪዎች እንደወትሮው ጥቁር ጋዋናቸውን ለብሰው፤ የአበባ እቅፍ አልተበረከተላቸውም – 1983 ዓ.ም.።

ከወራት በኋላ በዩኒቨርስቲው አካባቢ ይመላለሱ የነበሩ ተማሪዎች ተስፋ የሚያስቆርጥ ዜና ሰሙ። አዲሱ የሽግግር መንግስት እንደከዚህ ቀደሙ ተማሪዎችን በየመስሪያ ቤቱ የማይመድብ መሆኑ ተገለጸ። ከዜናው ጋር የብዙ ተማሪዎች እና ቤተሰቦቻቸው ተስፋ አብሮ ጨለመ። በተለይ በወቅቱ በፖለቲካ ሳይንስ ለተመረቅነው ተማሪዎች፤ ምንም ክፍት የስራ ቦታ እንደሌለ በግልፅ ተነገረን።

በዚህ አይነት ያለ ስራ ብዙ ቆየን። በወቅቱ በፖለቲካ ሳይንስ ከተመረቅነው መካከል በከፍተኛ ነጥብ የተመረቀው ወርቅነህ ገበየሁ ጭምር ምንም አይነት የስራ እድል ለማግኘት አልቻለም።

ህወሃት ካመጣብን የዘር ፖለቲካ በፊት በትምህርት ቤትም ሆነ በዩኒቨርሲቲ ከቶውንም የትውልድ ዘራችንን ተጠያይቀን አናውቅም። ማን ምን እንደሆነ፣ ለማወቅ ፍላጎቱም አልነበረንም። የኋላ ኋላ ግን ነገሮች እየተቀየሩ መጡ። በጓደኛሞች መካከል የሚፈጠር ጥርጣሬና፣ የዘር ግንድ ማጥናቱ ኢህአዴግ በኢትዮጵያ እንደተስቦ ያመጣብን በሽታ ነበር እና የቅርብ ወዳጅን ማወቁ የግድ ሆነብን። ወርቅነህ ገበየሁም የሻሸመኔ ልጅ ከመሆኑ ባሻገር፤ ከትግራይ ሰው መሆኑን ያወቅነው ከዩኒቨርስቲ ከወጣን በኋላ ነበር። በወቅቱ ነበረው የሽግግር መንግስት ባወጣው የዘር መስፈርት መሰረት፤ ወርቅነህ በትግራይነትና በደቡብ ህዝብነት መካከል የቆመ፤ ምርጥ የትግራይ ልጅ አለመሆኑ፤ በዚህም ምክንያት ሊያገኝ ይችል የነበረው ጥቅማ ጥቅም በመቅረቱ የጓደኛችን ጉዳይ ያሳዝን ነበር።

ከብዙ ጊዜ አንዴ ስንገናኝ፤ አንዳንድ ጓደኞቻችን ፀጉራቸው አድጎ፤ ንፅህናቸው ተጓድሎ፤ ከስተውና ተኮሳምነው ይታዩ ነበር። ከነዚያ ከሰውነት ውጪ ከሆኑት ተማሪዎች መካከል አንዱ ወርቅነህ ገበየሁ ይጠቀሳል።

የ1980ዎች አጋማሽ የፕሬስ ነጻነት የታወጀበት ወቅት በመሆኑ በርካታ መጽሄቶችና ጋዜጦች በገበያ ላይ ይውሉ ነበር። ሞገድ ጋዜጣም በወቅቱ ከነበሩት ከመጀመሪያዎቹ የነጻ ፕሬስ ጋዜጦች ረድፍ ላይ ይሰለፋል። ወርቅነህ ገበየሁም በነበረው አቋም ምክንያት የሞገድ ጋዜጣ ተባባሪ አዘጋጅ ሆኖ የመስራት እድሉን አገኘ። ወርቅነህ የጋዜጣው አዘጋጅ እንደመሆኑ መጠን በእለት ተለት የጋዜጣው ህትመት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም። ሆኖም ሳምንታዊ ደሞዙን ለመቀበል ወደ ቢሮ ሲመጣ በወጡት ዜናዎችና ጽሁፎች ላይ አልፎ አልፎ እንነጋገራለን። አንዳንዴም በጣም ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎችን ስናገኝ፤ ከማንም በፊት ከወርቅነህ ጋር በመመካከር መስራታችንን ቀጠልን።

አንድ ቀን የሃሙስ እትማችንን የውስጥ ገጽ ስራዎች አጠናቀን በፊት ለፊት ሊቀርቡ የሚገቡ ዜናዎችን እየመረጥን ሳለ፤ ስልክ ተደወለ። ግርማቸው ነበር።

“ሰላም ግርማቸው? ምን ዜና አለ?”
“ብቻህን ነህ?”
“አዎ”
“ጥብቅ የሆነ ሚስጥር ነው። ተጠንቀቅ።”
“ምንም ችግር የለም፤ ንገረኝ።” አልኩና እስክሪብቶና ወረቀት አዘጋጀሁ።
ግርማቸው ጉዳዩን ሙሉ ለሙሉ በስልክ ሊነግረኝ የፈራ ይመስላል። ፈራ ተባ እያለ፤ “ከውጭ አገር ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የኢህአፓ አባላት ናቸው…”
“እና ምን ሆኑ?”
ግርማቸው አሁንም በስጋት ስሜት፤ “ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው። ለማንኛውም ለምን አንገናኝም?” አለኝ።
“ፖስት ራንዴቩ እንገናኝ?” ስለው ከጭንቀቱ የገላገልኩት ያህል፤ “አዎ እዚያ እንገናኝ።”

ረቡዕ ቀን ረፋዱ ላይ ፖስት ራንዴቩ ወደ ግርማቸው ጋ ስሄድ ብቻዬን አልነበርኩም። ወርቅነህ ገበየሁ አብሮኝ ነበር። በቀጠሮው ቦታ በሰዓቱ ተገናኘን።

ግርማቸውን ፖስት ራንዴቩ ስናገኘው ዘና ብሎ ያጫውተን ጀመር። “እንግዲህ ሰዎቹ የኢህአፓ አባላት ናቸው። ጉዳያቸው በሚስጥር መያዝ አለበት። ወደ አገር ቤት የመጡት ልዩ ሚሽን ተሰጥቷቸው ነው። ጉዳዩን ስትገናኙ በዝርዝር ትነጋገራላችሁ።” አለንና ስለሰዎቹ ማንነት አንዳንድ ተጨማሪ ነገሮችን ሲገልጽልን እስክሪብቶና ወረቀት አውጥቼ መጻፍ ጀመርኩ።

“በምታገኛቸው ጊዜ ይህንን የሚስጥር ኮድ መናገር አለብህ” አለና የድብቅ ስማቸውን ነገረኝ።

“የድብቅ መጠሪያ ስማቸው ‘ቤሬክ’ ይባላል” ሲለኝ ወረቀት ላይ ይህንኑ አሰፈርኩት። ወርቅነህም እስክሪብቶውን ከኪሱ አውጣ።

“በዚህ ስልክ ደውሉና የእኔን ስም ጥሩላቸው። ለጋዜጣችሁ በርካታ መረጀዎችን ሊሰጡዋችሁ ይችላሉ።’ አለን ግርማቸው።

ስልክ ቁጥራቸውን እየነገረን ወረቀት ላይ መጻፍ ስጀምር፤ ወርቅነህም ስልክ ቁጥሩን በእጁ መዳፍ ላይ ሲጽፍ አይቼ ሁኔታው አስገርመኝ። ነገር ግን በይሉኝታ ዝም አልኩት።

በወቅቱ በርካታ ጋዜጦች የፈሉበት ጊዜ በመሆኑ፤ ወርቅነህ ይህንን ዜና ከሞገድ ጋዜጣ ውጪ ለሚታተሙ ፕሬሶች አሳልፎ ሊሰጥ ነው በሚል ጥርጣሬ ብቻ ድርጊቱ አስገረመኝ። ከአንድ የትምህርት ቤት ጓደኛ፣ ከዛ በላይ ላስብ አልችልም። ልጠይቀውም አሰብኩና ጠይቆ ከመቀያየም ዝም ማለቱን መረጥኩ። በወቅቱ በውስጤ ቅሬታ አሳደረብኝ።

በሚቀጥለው ቀን… ግርማቸው በሰጠኝ ስልክ በተደጋጋሚ ብደውል እነ ቤሬክን ላገኛቸው አልቻልኩም። ቀን ላይ፣ በምሽት እና በሌሊት፣ ስልኩን መቀጥቀት ያዝኩ። ስልኩ ይጠራል። የሚመልስ ግን አልነበረም።

ከቀናት በኋላ ግርማቸውን ለመፈለግ ዘወትር ወደምንገናኝበት ወደ ፖስት ራንዴቩ ለብቻዬ አመራሁ። ሌሎች ጓደኞቼ እንደወትሮው ክብ ሰርተው ይጫወታሉ። ግርማቸው ግን አልነበረም።

“ግርማቸውስ?” አልኳቸው ወድያው እንደተቀላቀልኩ። ሞቅ ያለ ጨዋታቸውን እንዳቋረጥኳው ይሰማኛል።

“ሰላምታ አይቀድምም?” አለ አንዱ፣ ከፊቴ የሚነበበውን የደንጋጤ ስሜት በማስተዋል።

“ቀን ላይ ተደዋውለን ነበር። በሆነ ጉዳይ ትንሽ ተረብሿል። ለማንኛውም ዛሬ እንደምንገናኝ ነግሮኝ ነበር።” ሲል ሌላኛው መለሰ።

ግርማቸው አረፋፍዶ ብቅ አለ። ፊቱ ላይ አንዳች የብስጭት ስሜት ይነበባል። በውስጡ የታመቀውን ንዴት ያወጣው ገና ወንበሩ ላይ ሳይቀመጥ ነበር።

“ሰዎቹን አሳሰራችኋቸው አይደል?” ሲል ፍጹም ሃዘን በተሞላበት አንደበት ጠየቀ፣ ወደ እኔ እየተመለከተ።

“ወርቅነህ!” አልኩ ሳላስበው በመጮህ።

በመካከላችን ለአፍታ ጸጥታ ሰፈነ። ለተልካሻ ነገር የጠረጠርኩት ሰው ከጀርባዬ ሆኖ ከባድ ወንጀል እየሰራ ኖሯል!

የነ ቤሬክ መሰወር በውስጤ ጥርጣሬ፣ ፍርሃት እና ቅያሜ ፈጥሮብኝ ኖሮ ወርቅነህን እርቀው ጀመር፣ ከዛ ስልክ ከተቀበልንበት እለት በኋላም አልተገናኘንም። ከሞገድ ጋዜጣም ቀስ በቀስ እየራቀ መጣ።

አንድ ቀን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ የሃይድሮ ፖለቲክስ ምሁር የሆኑትን ዶ/ር ያቆብ አርሳኖ ስለአባይ ጉዳይ ቃለመጠይቅ ለማድረግ ሄጄ ወርቅነህን ከሩቅ አየሁት። ከዚያ ደግሞ ተሰወረ።

ስራዬን ጨርሼም ከዩኒቨርሲቲው ግቢ ለመውጣት ስሯሯጥ ከኋላዬ አንድ ሰው ያዘኝ።

እኔን ያላየኝ መስሎኝ ነበር። ከእነማን ጋር እንደምንገናኝና ምን እንደምሰራ በአይነ ቁራኛው ይከታተለኝ ኖሯል ወርቅነህ።

“ለምንድነው የምትሸሸኝ?” አለኝ፣ እንደመቆጣት እያደረገው።

ትንሽ እንደመደንገጥ ብዬ ስለነበር ለሰኮንዶች ጸጥ ካልኩ በኋላ “አንተስ ለምንድ ነው የምትከታተለኝ?” አልኩት በቁጣ።

“እውነቱን እንድነግርህ ነው የምትፈልገው?… ተረጋጋ እና አድምጠኝ፣ ሁሉንም ጉዳይ እነግርሃለው።” አለኝ መልሶ ረጋ ባለ አንደበት። ቁጣዬን ለማብረድ ሲል ያደረገው ይመስላል። በድንጋጤ የተነሳ የምናገረውም ጠፋብኝ እና ጸጥ ብዬ ከአንደበቱ የሚወጡትን ቃለት መተባበቅ ጀመርኩ።

“በደህንነት መስሪያ ቤት ውስጥ ተቀጥሬ እየሰራሁ ነው።” ሲለኝ ያልጠበኩትን ሚስጥር ድንገት ስለነገረኝ ሁኔታው አስደነገጠኝ።
“በደህንነት ውስጥ በመስራቴ ደግሞ እናንተን ከስንት አደጋ ጠብቅያችኋለሁ። በአጭሩ ‘I am protecting you’ ስለዚህ አትሽሸኝ።” አለኝ። ከእግር ጥፍሬ እስከራስ ጸጉሬ አንዳች ነገር ወረረኝ። ልቤ በፍጥነት ሲመታ፣ ደምስሮቼ ሲገታተሩ ተሰማኝ።

“እና ሰዎቹን…” መናገር አልቻልኩም።
“የምን ሰዎች?”
“እነቤሬክን ያሳፈንካቸው?” አልኩትና መልስ ሳልጠብቅ እዛው የቆመበት ጥዬው ሄድኩ።

***
ከወራት በኋላ ወርቅነህ የደህንነት ሃላፊ ሆኖ ሻሸመኔ ስራ መጀመሩን ሰማሁ። ይህንን ዜና ሰምተን ብዙ ሳንቆይ “ወርቅነህ በጦር መሳሪያ ሽያጭ ተያዘ” ተብሎ ወደ እስር ቤት ተወረወረ።

ከሰባት ወራት በኋላ ወርቅነህ ገበየሁ ከእስራት መፈታቱን ሰማሁ። ከእስራት ሲፈታ ግን የምናውቀው የወርቅነህ ገበየሁ የዘር ሃረግ ተቀይሮ፤ የ‘ኦሮሞ’ ብሄር ተወላጅ ተብሎ፤ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ከፍተኛ አመራር ሆኖ፤ ሹመት አግኝቶ የኢህአዴግን ካምፕ በግላጭ ተቀላቀለ… ወጣት ወርቅነህ ገበየሁ።

የእድሜ፣ የትምህርት ደረጃ፣ የስራ ልምድ፣ በተለይ በፖሊስ ሰራዊት ስራ የሚጠይቀው የስራው ስነ-ስርዓት እና በሙያው ስነምግባር ላልተካነ ግለሰብ ያንን ትልቅ ስፍራ እንዲመራ ነው፤ አቶ መለስ ዜናዊ ሹመት የሰጡት።

አንዳንዴ ወርቅነህ ገበየሁ በቴሌቭዥን ሲቀርብ የድሮውን መልካም ሆነ ክፉ ነገር እያሰብኩ፤ “ወይ ጊዜ” ማለቴ አልቀረም። ወርቅነህ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካ ሳይንስ በባችለር ዲግሪ በጥሩ ውጤት የተመረቀ ወጣት ስለሆነ ከሌሎቹ ፊደል ካልቆጠሩ የህወሃት ባለስልጣናት የተሻለ ነው። ሆኖም በማናቸውም ጊዜ የግል ፋይላቸው ታይቶ ወደ እስር ቤት ሊወረወሩ ከሚችሉት፤ በ“ቀይ መስመር” ከቆሙት ባለስልጣኖች አንደኛው መሆኑ እርግጥ ነው። ግና ለጌቶቹ ታማኝ መሆኑን በዘሩ ብቻ ሳይሆን በስራውም አረጋግጦላቸዋል። ዛሬ ኦህዴድን የሚመራው የኦሮሞ ተወላጅ ሳይሆን የኦሮሞ ተናጋሪ ትግሬ እንዲሆን የተፈለገበት ዋነኛው ምክንያት ትክክለኝስዎቹ የኦሮሞ ተወላጆች ላይ ህወሃት እምነት ስላጣ ይመስላል።

የኢትዮጵያ መሰረታዊ ችግር፤ የበሔራዊ አጀንዳ እጦት ነው። (ክፍል አንድ) በጥበበ ሣሙኤል ፈረንጅ።

$
0
0

ኢትዮጵያ ውስጥ የሕዝብ አመጽ ሲነሳ ይህ የመጀመርያው አይደለም። በተደጋጋሚ የተነሱ ሕዝባዊ ቁጣዎች፤ በስርዓቱ ጨካኝ እርምጃ፤ ቢዳፈኑም ሁሌም ውስጥ ለውስጥ እየተንቦገበጉና፤ እየተብላሉ፤ ጊዜና አጋጣሚ ጠብቀው መነሳታቸው አልቀረም። ዛሬም በኦሮምያ፤ በአማራና፤ በቆንሶ የምናየው ይህንኑ ነው። ሕዝቡ በሶቱን በአደባባይ ይገልጻል ውጭ ያለው የሃገር ተቆርቋሪው ዜጋ፤ የወገኖቹን ችግር ከአድማስ እስከድማስ ያስተጋባል። ምንም ህሊና በሌላቸው ግለሰቦችና፤ የወሮበላ ቡድን የሚመራው አገዛዝም፤ ለሁሉ ነገር መልሱ እስራት፤ ድብደባና፤ ግድያ በመሆኑ፤ ሕዝቡን ማሰቃየትና፤ የሃገሪቱን ብርቅዬ ዜጎች ሕይወት መቅጠፉን ቀጥሎበታል። ተው የሚለው ያጣው ይህ ግፈኛ አገዛዝ፤ ላለፉት 25 ዓመታት፤ ይህን የግፍ አገዛዙን ሊቀጥል የቻለው፤ በጥንካሬው ሳይሆን፤ በተቃዋሚው ደካማነት መሆኑ በተደጋጋሚ ቢነገርም፤ መልዕክቱ አድማጭ ያገኘ አይመስልም። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፤ ከአመታት በፊት “ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ” የሚለው መልእክታቸው ዛሬም ወቅታዊና ያልታሰበበት ጥያቄ ነው።

ደግመን ደጋግመን የምናየው ነገር፤ ሃገራችን ያጣቸው፤ በበቂ ሁኔታ ተደራጅቶ፤ ብሔራዊ አጀንዳ ቀርፆ ትግሉን አቅጣጫ የሚያሲዝ የፖለቲካ ሃይል ነው። በጊዜያዊ አጀንዳ፤ በግዚያዊ “ድል” የሰው ሃይልና ገንዘብ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ፤ የብርቅዬ ወጣቶች ሕይወት ሲጠፋ እያየን ነው። በየጥጉ ጮዋሂው በዝቶ፤ አድማጭ ለመጥፋቱ፤ የማህበራዊ ሚድያዎች ምስክር ናቸው። ላለፉት 42 ዓመታት፤ ወያኔ በሃገራችን የተከለውን የመርዝ ችግኝ ለመንቀል ከፍተኛ ትግል ቢደረግና ከፍተኛ መስዋዕትነት ቢከፈልም፤ የትግሬ ብሔርተኝነት፤ የአማራ ብሔርተኝነት፤ የኦሮሞ ብሔረተኝነት፤ ወዘተ፤ ከሁሉም በላይ ደግም ጽንፈኛ አመለካከቶች እያደጉና እያበቡ ሲመጡ አየን እንጂ፤ መስዋዕትነቱ የምንፈልገውን ፍሬ እያፈራ አይደለም። ከዚህም አልፎ በኢትዮጵያዊነት ስም፤ ዘረኝነት በአደባባይ ሲደሰኮር፤ “እረ ተው የሚለው ሰው ቁጥርም” ማነሱን የምንመስክርበት አደገኛ ወቅት ላይ ደረስናል።

የ1966 (በኢትዮጵያ አቆጣጠር) የፈነዳው አብዮት፤ አስተባባሪና መሪ ድርጅት በመጣቱ፤ ወታደራዊ መንግስት፤ ስልጣኑን ዘርፎ ለ17 ዓመታት ሲያስረን፤ ሲደበድበን፤ ሲያሳድደንና ሲገድለን ኖረ። በስንት ውድ ኢትዮጵያውያን ሕይወት መስዋእትነት፤ ፋሽስታዊው ደርግነ በማስወገድ የተገኘው ሕዝባዊ ድልም፤ ብሔራዊ አጀንዳና፤ ኢትዮጵያዊ ራእያ ባጡ ጥቂት ወሮበሎች ተነጥቆ፤ ላለፉት 25 ዓመታት ስንታሰር፤ ስንደበደብ፤ ስንሳደድና፤ ስንገደል ኖረናል፤ አሁንም እየሞትን ነው። ይህ ከታሪክ ባለመማራችን የከፈልነው ከፍተኛ ዋጋ ነው። ዛሬም ትምህርት አልወሰድንም፤ ዛሬም ብሔራዊ አጀንዳ ቀርጾ ሕዝቡን ከዳር እስከዳር የሚያነቃንቅ ሃይል አጥተን፤ በምናያቸው “የአካባቢ ሕዝባዊ አመጾች” እና ንቅናቄዎች እየተኩራራን፤ ‘ወያኔ ሊወድቅ ነው አለቀለት’ እያልን በውሸት እራሳችንን እናሞክሻለን። በእኛው ስህተት ትግሉ ረጅምና መራራ ሆንዋል። ወያኔ ጠንካራ ሆኖ አያውቅም፤ ፈተናችን ጠንካራ ተፎካካሪ አለማግኘቱ ነው። ወደ ኋላ ተመልሼ፤ በተለይ ተቃዋሚው ስለተጎናጸፋቸው ድሎች፤ ስለፈተናውና ስለችግሮቹ ብናገር፤ ስድስት መጽሐፍት ይወጣዋል። ዛሬ ካለው ነገር ልነሳና፤ እየተጓዝን ያለንበትን አቅጣጫ፤ እንዲሁም ስር ነቀል ለውጥ ከፈለግን ምን ማድረግ እንዳለብን ያለችኝን ላካፍል።

ከብዙ አቅጣጫ የሚነሳው ጥያቄ፤ በተለይ የትግራይ ሕዝብ ለምን ዝም አለ የሚል ነው። ለጥያቄው መልስ የሚሰጡት ጥያቄውን ያነሱት ሰዎች በመሆናቸው፤ ለእነሱ ምቹ የሆነው መልስ፤ የትግራይ ሕዝብ “የማይነሳው”፤ ከአገዛዙ ተጠቃሚ ስለሆነ ነው የሚል ነው። ከዚህ ድምዳሜ በመነሳት፤ ይህንኑ አመለካከታቸውን፤ የተቀረው ሕዝብ ላይ ለመጫን፤ ባገኙት አጋጣሚና፤ በተለይም በየማህበራዊ ድህረ ገጾች ላይ ይለጥፋሉ። ሌላው ቀርቶ “በጋዜጠኝነት ሙያቸው አንቱ ተባልን” ብለው የሚገምቱ ግለሰቦች ሳይቀሩ፤ ሳሞራ “ትግሬና ወያኔ አንድ ነው” ብሏልና ከፈለጉ ትግራይን ይዘው ይሂዱ በሚል አሳሳች አመለካከት፤ ወያኔ ወደሚፈልገው አቅጣጫ እንድንሄድ ግፊት ሲያደርጉ፤ ‘ተው እንዲህ አይደለም’ የሚላቸው እንኳን አላየሁም። “ትግሬ ዝም አለ” እያሉ ሳንባቸው እስኪድክም የሚጮሁ ዜጎች ግን፤ አዲስ አበባ ለምን ዝም አለ፤ ወላይታ፤ ጉራጌ፤ሽዋ፤ ወሎ፤ ወዘተ ለምን ዝም አለ ሲሉ አንሰማቸውም። ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንደገለጽኩት፤ የትግራይ ሕዝብ፤ ይህንን ስርአት ለመጣል፤ ከሌላው ሕዝብ የተለየ ምንም ሃላፊነት የለበትም። ወያኔ ለሚፈጽመው በደልና ግፍ ተጠያቂው የወያኔ አመራር፤ አባላቱና ደጋፊዎቹ ናቸው። ሳሞራ “ትግሬና ወያኔ አንድ ነው” ብሏል፤ ስለዚህ ሳሞራ ልክ ነው የሚሉን ሰዎች፤ ብአዴን የአማራን ሕዝብ እወክላለሁ ስላለ፤ ብአዴን የአማራን ሕዝብ ይወክላል ብለው ያምናሉ ወይ ብለን ለመጠየቅም እንገደዳለን። አቶ ተክለሚካኤል አበበ የተባሉ ጽሃፍ “የኛ ነገር፤ ትግሬን መነጠል፤ ሐሳዊ-ኢትዮጵያዊነት ነው” በሚል ርዕስ ባስነበቡት ጽሁፋቸው “ትናንትናና ዛሬ ሕወሀት/ኢህአዴግ፤ ነጋሪት ጎስሞ፤ አዋጅ ነግሮ፤ የኢትዮጵያን ችግር ሁሉ የፈጠረ አማራ ነው ሲል፤ ያንን ስንቃወም የኖርን ሁላ፤ አሁን ደግሞ መልሰን የኢትዮጵያ ችግር ሁሉ ፈጣሪ ትግሬ ነው ስንል፤ ለሕወሀት/ኢህአዴግ የአመታት ዘመቻ እጅ ብቻ ሳይሆን፤ እግርም እየሰጠን ይመስላል፡፡” ያሉት፤ ለሁላችንም የሕሊና ደውል ሊሆን ይገባዋል።

ለምን ይህ ወይም ያኛው ብሔር/ብሔረሰብ አልተነሳም ከማለታችን በፊት፤ በኦሮምያና በአማራ ክልል የተነሱት ንቅናቄዎች ጥያቄያቸው ምንድ ነው ብለን መጠየቅ ያለብን ይመስለኛል። በአማራ ክልል፤ በወልቃይትና ጠገዴ ማንነት ጥያቄ ዙርያ ንቅናቄ ከመንሳቱ በፊት፤ በኦሮምያ አካባቢ የአዲስ አበባን መስፋፋት አስመልክቶ በተነሳው ተቃውሞ የተጀመረው ንቅናቄ ላይ፤ በዙዎቸ “በተቃዋሚው ጎራ የተሰለፍ ሃይሎች” ጥያቄውን ሲያጣጥሉና “ጠባብነት” ነው፤ የአዲስ አበባ መስፋፋት ምን ችግር አለው ሲሉ አንብበናል፤ ሰምተናል። በ2016 መጀመርያዊች ላይ በአማራ ክልል ንቅናቄው ሲነሳና እያደገ ሲመጣ ነው፤ በኦሮምያና በአማራ ክልል ያለው ንቅናቄ እንደ “የጋራ ትግል” እየተቆጠረ የመጣው። ዛሬ በኮንሶ ያለውንም ንቅናቄ ስናይ፤ ንቅናቄው የተነሳው ከኮንሶ መሬት ጋር በተያያዘ ነው። ይህም በመሆኑም ነው፤ ከነዚህ ከሶስት ክልሎች ውጭ፤ በተቀሩት የኢትዮጵያ ክልሎች ሕዝባዊ ንቅናቄ የማናየው። ብዙዎች፤ በተለይ “ወያኔ አለቀለት” በሚል ስሜት ውስጥ ያሉ ሰዎች ያልጠየቁት እና ያላዩት ነገር፤ የወልቃይትና ጠገዴ ጥያቄ ቢመለስ፤ የትግሉ አቅጣጫ ምን ይሆናል? የኦሮምያ ክልል ጥያቄስ ቢመለስ ትግሉ ወዴት ሊሄድ ይችላል? የሚለውን ነው። ነውጡ በመነሳቱ ብቻ እርካታ አግኝተው፤ ሊመለሱ የሚገባቸውን ጥያቄዎች የዘነጉ በዙዊች ናቸው። ለመሆኑ፤ የወያኔ ጥንካሬውና ድክመቱ ምንድነው? የተቃዋሚውስ ድክመትና ጥንካሬ ምንድነው? ወታደሩ፤ ፖሊሱ፤ አጠቃላይ የፀጥታው መዋቅር በወያኔ ቁጥጥር ስር ሆኖ፤የተቃዋሚው ጎራ፤ ሕዝቡን ከጥግ እስከጥግ ሳያስተባብር፤ ስር ነቀል ለውጥ ሊመጣ ይችላል ወይ? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ ካለ፤ መልሱን እስካሁን ያስነበቡን ስዎች ያሉ አይመስለኝም።

ወያኔና ሻዕብያ፤ ከዚያድ ባሬ ከወሰዱት ተመክሮ፤ “አማራ” ላይ ያነጣጠረ ትግል አድርገው ነው “ስኬታማ የሆኑት” እኛም ትግሉን በፀረ “ትግራይ” ላይ ካደረግን “ስኬታማ” እንሆናለን የሚል አመለካከት ካለ፤ ትግሉ፤ ሕዝቡ ወደ ሚፈልገው ትክክለኛ አቅጣጫና፤ የምንፈልገውን ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ስርዓት ለመግንባት ወደሚያስችል መንገድ የሚሄድ አይመስለኝም። ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚደረገውን ትግል ያህል፤ ብሔራው አጀንዳውን “ፀረ ትግራይ” ለማድረግ በትጋት የሚሰሩ ጽንፈኞች ለመኖራቸው ሶሻል ሚድያው በግልጽ ያሳብቃል። “ትግራይ ሁሉ ቆዳው ሲፋቅ ወያኔ ነው” የሚለው ደካማና አደገኛ አመለካከት፤ መለስ ዜናዊ ባንድ ወቅት “የኦሕዴድ አባል ሁሉ ቆዳው ቢፋቅ ኦነግ ነው” ከሚለው እኩይና ደካማ አስተሳሰብ የተለየ አይደለም። ማንም ሕዝብ፤ የትግራይን ሕዝብ ጨምሮ፤ሌላው ሕዝብ ሲጎዳ ደስተኛ ይሆናል ብሎ ማሰብ ሕሊናችን በጠባብነት እንዲዳክር መፍቀድ ነው። ትግሬ ሁሉ አመለካከቱ አንድ ነው ካልን፤ አማራ ሁሉ ኦሮሞ ሁሉ ወዘተ አመለካከቱ አንድ ነው ብለን እናምናለን ማለት ነው፤ ይህን ከተቀበልን ደግሞ ስለነዚሀ ብሔሮችም የሚባለውን መጥፎ ነገር ሁሉ እንቀበላለን ማለት ነው። ይህን ካመንን ደግሞ፤ ‘ነጭ ሁሉ አዋቂና ብልህ ነው፤ ጥቁር ሁሉ ደንቆሮና ወንጀለኛ ነው” የሚለውንም መላ ምት የምንቀበል ልንሆን ነው ማለት ነው። የሰው ልጅ “በዘሩ ያስባል” የሚል አመለካከት የለኝም። በነገሬ ላይ “የትግራይን ሕዝብ” በሌላው ሕዝብ ለማሰጠላትና፤ “እኛና እነሱ” የሚለውን ጎራ ለማስፋፋት፤ የወያኔ አባላት የሚሰሩበት ስትራተጂ ነው። የትግራይ ክልል ተጠቅሟል ወይስ አልተጠቀመም የሚለው ጉንጭ አልፋ ክርክር ከመሆን አያልፍም። በዚህ ጉዳይ ላይ አቶ ፈቃድ ሽዋ ቀና በቅርቡ “የትግራይና የህወሀት የበላይነት ጥያቄ – ዕውነቱ ውሸቱና ማስፈራሪያው” በሚል ርዕስ ባሰነበበን ጽሁፍ በሚገባ ገልጾታል። የትግራይ ክልል ተጠቃሚ ሆንዋል፤ ፋብሪካዎች መከፈታቸው፤ የአግልግሎት ሰጭ እንዱስትሪዎች መስፋፋታቸው፤ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች፤ የዘመናዊ እርሻ መስፋፋት፤ እነዚህ ሁሉ ለትግራይ ክልል የስራ እድል ፈጥረዋል። እነ ኤፈርት፤ እና ትልማ፤ የትግራይን ክልል ለመጥቀም እየሰሩ ነው፤ እነዚህ ድርጅቶች፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ከማንኛውም የንግድ ተቋማት በበለጠ፤ ከባንኮች ገንዘብ የማግኘት እድል አግኝተዋል፤ ያለቀረጥ እቃ ከውጭ ያስገባሉ፤ ተገቢውን ቫትም ሆነ የገቢ ታክስ አይከፍሉም፤ ይሁ ሁሉ ለትግራይ ክልል ትልቅ ጥቅም ነው። የትግራይ ክልል አልተጠቀመም ብዬም አልከራከርም። ግን የትግራይ ሕዝብ ለዚህ ተጠያቂ ነው ወይ? ፋብሪካ ሲከፈት አትክፈቱ ማለት አለበት? መንገድ ሲሰራ አትስሩ ማለት አለበት? ይህንን እያንዳንዱ ሰው ይመልሰው። የትግራይ ክልል ተጠቀመ ማለት፤ ትግሬ ሁሉ ተጠቀመ ማለት እንዳልሆን ይሰመርልኝ፤ ይህ ቢሆን ኖሮ፤ አዲስ አበባ በትግራይ ችግረኞች ተጥለቅልቆ ባላየን ነበር። ይህ ቢሆን ኖሮ መቀሌ “አፓርታይድ” ተብሎ የተሰየመ መንደር ባላስተናገደች።

ቀጣዩ ጥያቄ የትግራይ ክልል ከሌላው ክልል በተሻለ መልኩ ነጻነት አለው ወይ? ሕዝቡስ በሰላም ወጥቶ የመግባት እድሉ ከሌላው ክልል የተሻለ ነው ወይ? የሚል ነው። በእኔ እምነት ለዚህ መልሱ የተሻለ አይደለም የሚል ነው። እንደውም የትግራይ ክልል ከሌላው በበለጠ መብቱ የተረገጠና፤ ነፃነቱን የተነፈገ ለመሆኑ ብዙ መረጃዎች አሉ። ሌላው ቀርቶ ትግራይ ውስጥ የግል ጋዜጦች እንኳን አይገቡም። በትግራይ ውስጥ ምንም ዓይነት ተቃዋሚ እንዲንቀሳቀስ አይፈቀድለትም። በግንቦት 1991 (አውሮፓ አቆጣጠር) ወያኔ በትረ መንግስቱን ሲጨብጥ፤ ሃገር ውስጥ “በሕጋዊ መንገድ” ለመንቀሳቀስ ከገቡት ድርጅቶች መካከል፤ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ህብረት (ኢዲህ) አንዱ ነበር። ለዑል መንገሻ በትግራይ ሕዝብ የተወደዱና የተከበሩ በመሆናቸው፤ ትግራይ ክልል በዙ ደጋፊ አፍርተው ነበር፤ ይህ ያሰደነገጠው ወያኔ በርካታ የኢዲህን አባላት በማሰር፤ በማፈን፤ ንብረት በማቃጠል፤ የድርጅቱን ደብዛ ከትግራይ እንዲጠፋ አድርጓል። በርካታ ሕብረ ብሔር ድርጅቶች ትግራይ ውስጥ ለመንቀሳቀስ ባደረጉት ሙከራ፤ በስርዓቱ ያጋጠማቸውን ችግር በተደጋጋሚ መግለጫ አውጥተውበታል። ዛሬም አረና ትግራይ የተባለው ድርጅት ምን አይነት ማነቆ ውስጥ እንዳለ የምንሰማውና የምናየው ነው። ትግሬዎች ወያኔ ላይ ስላላቸው ተቃውሞ ሲነሳ፤ የማይነሳው፤ የትግራይ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትሕዴን) ስለሚባለው ድርጅት ነው። ይህ ድርጅት ከግንቦት ሰባት ጋር ግንባር ፈጥሮ ወያኔን እየታገለ እንደሆነ በቻ ሳይሆን፤ ወያኔን በትጥቅ ትግል ከሚፋለሙት በብዛትም በትጥቅም የበለጠ መሆኑን በተደጋጋሚ ተገልጽዋል፤ ታድያ የእነዚህ የትግሬ ታጋዮች መስዋእትነት አይቆጠርም? ሞላ አስገዶም የተባለው የድርጅቱ መሪ ለወያኔ እጁን ሲሰጥ፤ “ዘር ከልጓም ይስባል” ተብሎ ሲተች፤ በእኔ እምነት፤ ከሞላ የበለጠ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ ጉዳት ያደረሰውና አሁንም በማደርሰ ላይ ያለው ሰለሞን ተካልኝ የተባለ ሙዚቀኛ፤ በዘር ልጓሙ እንዴት አልተመዘነም? ዛሬ ወያኔን የሚደግፍ ሁሉ ትግሬ ብቻ ነው ካልን፤ እነ አባዱላ፤ እነ ተፈራ ዋልዋ፤ እነ ሙክታር፤ ወዘተ በምን የዘር ሂሳብ ነው የሚሰሉት?

በእኔ እምነት ትልቁ ችግር ብሔራዊ አጀንዳ አለመኖሩና ሕዝቡን በብሔራዊ አጀንዳ ስር እንዲነሳ አለማድረጉ ነው። ከጥቂት ጊዜያት በፊት፤ የአዲስ አበባን ህንጻ ያንቀጠቀጠው የሙስሊሙ ማህበረሰብ የት ገባ? ተገቢ ጥያቄ ይመስለኛል። ችግራችን፤ አፈንጫችን ሲመታ ዓይናችን አለማልቀሱ ብቻ ሳይሆን፤ ልባችን አለመድማቱም ጭምር ነው። ከ 1993 እሰክ 1996 (አውሮፓ አቆጣጠር) በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ ሬድዮ ላይ እሰራ በነበረበት ጊዜ፤ በዋሽንግተን አካባቢ የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ አባላትን የማነጋገር እድል አጋጥሞኝ ነበር። በወቅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የስብአዊ መብት ጥሰት የነበረበት ወቅት ነበር፤ እነዚህን መሪዎች በዚህ ጉዳይ ላይ አቋም እንዲወስዱ ስንጠይቅ፤ የሚነግሩን ገለልተኛ እንደሆኑ ነበር። እንዳውም አንዳንዶቹ፤ ከወያኔ ጋር በቁርኝት ይሰሩ ነበር። የሙስሊሙ ማህበረሰብ እንደ አንድ ማህበረሰብ የተነቃነቀው፤ ወያኔ በቀጥታ በሙስሊሙ ሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ በመግባት በፈጸመው ወንጀል ነው። ይህን የማነሳው ጣት ለመጠቆም አይደለም፤ ዛሬም ተመሳሳይ ነገር ስለማይ ነው። አንዱ ሲነካ ሌላው እንዲነሳ፤ የአንዱ ጉዳት የእኔም ጉዳት ነው እንድንል፤ የሚያስተባብር ሃይል የለንም። በግንቦት 1997 የአዲስ አበባ ነጋዴዎች አድማ አድርገው በነበረበት ጊዜ (በወቅቱ አዲስ አበባ ነበርኩ)፤ እኔና ጓደኞቼ ባለታክሲዎቹም እንዲያድሙ ለማስተባበር ስንሞከር፤ የሰጡን መልስ፤ “እኛ ስናድም ማን አገዘን?” የሚል ነበር። ያኔ የነበረው “የብሔራዊ አጀንዳ እጦት” ዛሬም ድረስ መቀጠሉ፤ ‘ለዚህ ተግባር ብቃት ያላቸው የተቃዋሞ መሪዎች አሉ ወይ’ ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል። ትልቁ ችግር፤ የአማራው ጥቃት፤ የኦሮሞ ጥቃት፤ የክርስቲያኑ መጠቃት፤ የሙስሊሙ መጠቃት ሆኖ እንዲሰማን የሰራነው ስራ የለም። ሁሉም “ለየእራሱ” ነው የሚጮኸው። የኦሮም ብሔራዊ ኮንግረስና ሰማያዊ ፓርቲ አብረን መስራት ጀምረን ካሉ ወራቶች አልፈዋል። ዛሬ ግን መግለጫ ከመስጠት ባሻገር የፈየዱት ነገር ምን እንደሆነ ለእኔ ግልጽ አይደለም። ውጭ የምንገኘውም፤ ያለውን ሕዝባዊ ንቅናቄ ብሔራዊ መልክ እንዲይዝ፤ ሃገር ውስጥ ያሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን በሃሳብም ይሁን በገንዘብ ለማገዝ በቂ እርዳታ እያደረግን አይደለም። እንዲተባበሩም ለማድረግ፤ መጀመርያ እኛ እራሳችን እዚህ መተባበር አለብን። እዚህም ቢሆን ላለፉት 25 ዓመታት በዲፕሎማሲው በኩል ምንም ስራ አልሰራንም ማለት ይቻላል። ያለንን የፖለቲካ ካፒታል ልንመነዝረውና ጥቅም ላይ ልናውለው አልቻልንም። ብዙ ጊዜ ችግራችን፤ ከሃገር ፍቅር የበለጠ፤ የድርጅትና የቡድን ፍቅር ማየሉ ይመስለኛል። ዛሬም “ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ” ማለት ግድ ይላል። በተሰባበረ አጀንዳ ወጣቱ አይለቅ፤ ብሔራዊ አጀንዳ ሊኖረን ይገባል፤ ዘረኝነት ከየትም አቅጣጫ ይምጣ ሊወገዝ ይገባል። “ጥሩ አማራ የሞተ አማራ ብቻ ነው” የሚለው የመከነ ወያኔያዊ አስተሳሰብ አደገኛና በታኝ ነው ብለን ካመንን “ጥሩ ትግሬ የሞተ ትግሬ ብቻ ነው” የሚለውን የመከነና የደከመ አስተሳሰብ ባንድ ድምጽ ልናወግዝ ይገባል። እንዲህ ዓይነት የተሳሳቱና ከፋፋይ አስተሳሰቦች፤ ትግሉ በሔራዊ አቅጣጫ እንዳይዝ የሚያደርጉና፤ ሃገራችንን ከፍተኛ አደጋ ላይ የሚጥል ነው። በዙ ጊዜያችንን የምናባክነው፤ ሃገር ውስጥ ያለውን ሕዝባዊ ንቅናቄ በማራገብ ነው። አስትዋጾአችን ከዚህ የተሻለ መሆን አለበት፤ ትግሉ ብሔራዊ አቅጣጫ እንዲይዝ፤ ብሔራዊ አጀንዳና እስትራቴጂ ለመቀየስ መስራት ይኖርብናል። አለዚያ፤ ልክ እንደ 2005 ምርጫና ነውጥ፤ ወያኔ ትግሉን ለጊዜውም ቢሆን ሊያዳፍነው ይችላል። ይህ ሁላችንንም እንቅልፍ ሊነሳ የሚገባ ነገር ነው። በቅርቡ በወያኔ፤ ጎንደር ውስጥ የታፈነችው ወጣት እንዳለችው፤ “እነሱ ሃገር ለማጥፋት ሌት ተቀን እየሰሩ፤ እኛ ሃገር ለማዳን ሌት ተቀን መስራት እንዴት ያቅተናል?”


“እናቱ ገበያ የሄደችበትም እንዲሁም የሞተችበትም እኩል ያለቅሳል” አሉ፤ የሰሞኑ ጩኸቴን ቀሙኝ አሳፋሪ ዜማ ከተጋሩ ማሕበርሰብ

$
0
0

አገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ እንደዚህ አይነት አሳፋሪ አምባገነናዊ መንግስት እና ሕብረተሰብ በዮዲት ጉዲትም ይሁን በፋሺሽት ኢጣልያ ጊዜ አጋጥሟት አያውቅም።

ዘረኛው የወያኔ መንግስት ስልጣን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 25 ዓመታት አገርን በማፈራረስ፤ ሕዝቦችን በዘር ከፋፍሎ፤ የአገሪቷን ዋና ዋና የስልጣን ቦታዎች ማለትም የፖለቲካ፤ የመከላከያ፤ የደህነነትን እና ቁልፍ ቁልፍ የሆኑ የኢኮኖሚ አውታሮችን በመቆጣጠር ታይቶ የማይታወቅ የሰብአዊና እና የዲሞክራሲ ጥሰት በማደረግ በወገኖቻችን ላይ እየፈጸመ ያለው ግፍና በደል ይህ ነው አይባልም።

ዛሬ ደግሞ በአገሪቷ ውስጥ በቀጥታ በሚደርገው የኢኮኖሚ ዘረፋ እና የገንዘብ ማሸሽ ተዋናይ የሆኑ በአካባቢያችን የሚገኙ ቀንደኛ የትግራይ ተወላጅ ተብዬዎች ሰሞኑን “ከአማራ ክልል ለተፈናቀሉ የተጋሩ ሕብርተሰብ” መልእክት አዲስ ከተቋቋመው ኮሚቴ በማለት በማሳቹሴትስ ስቴት ለሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች፤ ከአማራ ክልል ለተፈናቀሉ የተጋሩ ሕብረተሰብ ገንዘብ ለማሰባሰብ እና አጋርነታችንን ለማሳየት በሚል በፊታችን ኦክቶበር 2, 2016 በ2፡00 PM በቦስተን ኮመን ሆቴል በሚል የተላለፈ ጥሪ ተመልክተናል። ለመሆኑ በእርግጥ ከአማራ ክልል የተፈናቀለ የትግራይ ብሔረሰብ አለ? ይሄ በከተማችን ያሉ የገዥው ፓርቲ የወንጀልና የጥቅም ተካፋይ የሆኑ ጭፍን ደጋፊዎች እያወቁት ለፖለቲካ ጥቅም ሲባል በተለይም የአማራውን ሕዝብ በጅምላ በአይሮፕላን ለመጨፍጨፍ እንዲያመቻቸው የራሳቸውን ሰዎች ማውጣታቸው የታወቀ ሀቅ ሆኖ እያለ “ከአማራ ክልል የተጋሩ ብሔረሰብ ተፈናቀለ” የሚባለው በሬ ወለደ አይነት፤ እንዳው ጩኸቴን ቀሙኝ አሳፋሪ ዜማ የወያነው አፋኝ ቡድን ሴራ መሆኑ ግልጽ ነው።

እውነት ለወገናቸው አሳቢ ከሆኑ በቅርብ ቀን በወገኖቻችን ላይ ለደረሰው ግፍ እና በደል አጋርነታችንን እና ወገንተኝነታችንን እንደ ማንኛውም ዜጋ፤ ኢትዮጵያውያኖች በመሰባሰብ “ለወገን ጥሪ ከወገን ምላሽ” በማለት በተዘጋጀው ዝግጅት ላይ የት ነበሩ? የገንዘብ ማሰባሰብ እርዳታ የሚያስፈልገው እርግጥ በሐሰት ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል የሕውሃት ካድሬዎች ለሰሩት ድራማ? ወይስ በእርግጥ በአጋዚ ጦር በሰላማዊ መንገድ መብትን ሲጠየቁ በጥይት ግንባር ግንባራቸውን እይተመቱ ለዘላለም ላሸለቡ፤ ልጆቻቸው ደርሰውልን ይጦሩናል ሲሉ ልጆቻቸውን ለተነጠቁት ደካማ አሮጊት እናቶች? መልሱን ለሕሊና ፍርድ እንተወዋለን፤

ለመሆኑ በአካባቢያችን ይህንን የንቀት እና የፌዝ ድራማቸውን በማሕበረሰቡ ላይ ሊሰሩ ያቀዱት እውን በአገራችን ያለውን እውነታ አጥተውት? ወይስ በጭፍን ጥላቻ እና በንጹሃን ኢትዮያውያን ደም ሰክረው ነውን?

እውነት በውጭ አገር የሚኖሩት የትግራይ ተወላጅ ኢትዮያጵውያኖች በአገራቸው ላይ የሚካሄደውን እውነታ ማለትም ህውሃት ስልጣን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ ያለውን በደል አያወቁም ኖሯልን?

•የኦሮሞ ሕዝብ መብቱን በመጠየቁ እንደበደል ተቆጥሮ እስር ቤቱን ከማጣበቡ አልፎ፤ በቅርብ ደሞ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በሺህ የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎችን ደም ከማፍሰሱም በላይ በዓለም ላይ የማይደረግ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ እናትን የልጇ ሬሳ ላይ እንድትቀመጥ አደርጎ ማሰቃይቱን።

•የአማራ ተወላጆች ላለፉት 25 አመታት ከኖሩበት ንብረታቸውን እየተነጠቁ ሲፈናቀሉ፤ በቅርብ ደግሞ መብታቸውን ሰለጠየቁ በአልሞ ተኳሾች በለጋ እድሜያቸው ሲረግፉ እና አሮጊት እናት በድሃ አቅሟ አሳድጋ ልጄ ደርሰልኝ ስትል እና የወላድ መካን መሆኗን።

•የጋምቤላ ተወላጆች በግፈኛው የወያኔ መንግስት ታጣቂዎች በአንድ ቀን ጀምበር ብቻ ከ400 በላይ ንጹሃን ዜጎች በግፍ ሲገደሉ፤ መሬታቸውን በኢንቨስተመንት ስም ተነጥቀው በግፍ ሲፈናቀሉ።

•በኦጋዴን በሺህ የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎች በጅምላ በግፍ ሲጨፈጨፉ።

•በ2005 ዓ. ም. ወያኔ በአደባባይ በምርጫ ሲሸነፍ አይን ያወጣ ማጭበረበር በማደርጉ ተቃውሞ የወጡ ንጹሃን ዜጎች በጠራራ ጸሃይ በጥይት ሲገደሉ።

•በአለማችን በዚህ ክፍለ ዘመን እጅግ አሰቃቂ፤ በቂሊንጦ እና በተለያዩ እስር ቤቶች የታሰሩትን የሕሊና እስረኞችን ጨፍጭፎ ሲያበቃ በሞቱ እስረኞች ላይ እሳት ሲነድ።

•ዜጎች በማናቸውም ጊዜ በክረምቱ ወቅት ሳይቀር ቤቶቻቸው በላያቸው ላይ እየፈረሰ ለሊዝ ጨረታ ለብር ማግበስባሻ ወደ ሜዳ ሲጣሉ።

•የወደብ ባለቤት የነበረችውን ታላቅ ሀገር ወደብ አልባ ማድረጋቸውን።

•ላለፉት 25 ዓመታት ዜጎች በጎሳ፣ በዘር፣ በኃይማኖት፣ በፖለቲካ እየተለያዩ በጎሪጥ አንዲተያዩ እና እንዲናቆሩ መደርጉን።

ኧረ ስንቱ? ሆድ ይፍጀው

በአጠቃላይ በታሪክ ጭቆናን እና ግፍን ለዘላለም ተሸክሞ የሚኖር ህዝብ ስለሌለ ጭቆናው ሞልቶ በመፍሰሱ በአብዛኛው ሀገሪቱ ክፍል ህዝባዊ እምቢተኝነት ተነስቷል፡፡ ይህንን እምቢተኝነት ለማፈን ስርዓቱ እንደተለመደው የጭካኔ እርምጃዎች እየወሰደ፤ ደም እያፈሰሰ፤ የንጹሃንን ነፍስ እየቀጠፈ ቢሆንም ሕዝቡ ነጻነቱን ለማስመለስ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ አገር በቁርጠኘነት በመታገል ይህንን አሳፋሪ እና የበሰበሰ ግፈኛ ስርዓት ለግብዓተ ቀብሩ አቃርበውታል። በመሆኑም እኛ በቦስተን አካባቢ የምንገኝ ኢትዮጲያዊያን የሚከተሉትን ጥሪዎች ለማስተላለፍ እንወዳለን።

በውጭ አገር በተለይ በቦስተን አካባቢ ለምትገኙ የትግራይ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን የቀረበ ጥሪ

በውጭ አገር በተለይ በከተማችን የምትኖሩ የትግራይ ተወላጅ ኢትዮጵያውያኖች ከላይ ያለውን እውነታ በመገንዘብ በወገኖቻችን ላይ በሚደርስ ግፍና መከራ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ተስምቷችሁ ይህንን ግፈኛ አገዛዝ በማጋለጥ እና ስርዓቱ የትግራይን ሕዝብ እንደማይወክል የማስገንዘብ ሐላፊነት በእናንተ ላይ የተጣለ መሆኑን በመገንዘብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር በጋራ እንድትቆሙ ይህንን ታሪካዊ ጥሪ እናደርጋለን።

በቦስተን እና አካባቢዋ ለምትገኙ ኢትዮጵያውያኖች የቀረበ ጥሪ

በወገናችን ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ እና በደል በሚገባ እየተከታተላችሁ መሆኑን እናውቃለን፤ በመሆኑም ጊዜው የትብብር፤ አገርን የማዳን እና የሕዝባችንን እልቂት የመታደግ የሞራል ሐላፊነት ስላለብን፦

1.ሕዝባችንን፤ አገራችንን ፤ ባህላችንን እና ማንነታችንን እየገደለ ካለው ግፈኛ የሕውሃት አገዛዝ ደጋፊ የሆኑ ባለማወቅ በዘር እና በጥቅም እየደገፉ ያሉትን ጓደኞቻችሁን የወቅቱን የአገራችንን ሁኔታ በማስረዳት ከሕዝባቸው ጎን እንዲቆሙ ጥሪ ማድረግ።

2.ከአገር ቤት የሚመጡ ከገዥው ፓርቲ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሸቀጦችን አለመግዛት፤ በኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ሌሎችም የገዥው ፓርቲ ጋር ግነኙነት ያላቸውን የንግድ ተቋማት ላይ ማዕቀብ ማድረግ።

3.ወደፊት በሚደረጉ አገራዊ ውይይቶች ላይ በመገኘት ወገናችሁን ከእልቂት አገራችሁን ከአደጋ ለማዳን በሚደርጉ ተሳትፎ ላይ በንቃት እንድትሳተፉ።

4.የሕውሃት አገዛዝን፤ ግድያና የአገር ማፈረስ ሴራ የሚደግፉ እና የሚተባበሩ አካላትን በማውገዝ በተለይም በግልጽ የሚታውቁ በሕውሃት ካድሬዎች የሚመራ ቤተ ክርስቲያን፣ በቅርቡም በዚህ ግፈኛ መንግስት ለተገደሉ ንጹሃን ዜጎች ጸሎት/ፍትሃት እንኳን እንዳይደረግ ባደረጉ ቤተ ክርስቲያናት መሳተፍ በወገኖቻችን ደም ላይ ማፌዝ በመሆኑ ማንኛውንም አገልግሎት ባለመሳተፍ ከወገናችሁ ጎን እንድትቆሙ።

5. በዚህ ግፈኛ ስርዓት የኢኮኖሚ ዝርፊያ እና የአገሪቷን ገንዘብ እና ሐብት በማሸሽ፤ ንጹሃን ሕዝቦችን ከሚገድል መንግስት ጋር ከሚያብሩ እና በተለይ ይሄን የወገን ጥሪ ንቀው የወገናችንን ስቃይ ከሚያራዝሙ ወገኖች ጋር ምንም አይነት የማህበራዊ ግንኙነት ባለማድረግ የሕዝብ ወገንተኛነታችሁን እንድታስመሰከሩ በአክብሮት ጥሪ እናደርጋለን።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!
የቦስተን እና አካባቢዋ ኢትዮጵያውያን!!

Viewing all 1809 articles
Browse latest View live


<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>