በዛሬው እለት በቦስተን በተደረገው “የሕሊና እስረኛ አንዱአለም አራጌ የውደሳ እና የምስጋና ቀን” በርካታ ኢትዮጵያውያኖች በተገኙበት በደማቅ እና እጅግ በተሳካ ሁኔታ ተክናውኗል። በዚሁ ዝግጀት ላይ የሕሊና እስረኛ አንዱአለም አራጌ የሕይወት ታሪክ እና በኢትዮጵያ ውስጥ የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመፍጠር በሚደረገው የሰላማዊ ትግል ያደረገውን አስተዋጻኦ በተመለከተ የተዘጋጀ ዶክመንተሪ ፊልም የቀርበ ሲሆን፤ በወጣት ማሙሽ እና በወ/ሮ ደብረወርቅ የተዘጋጁ ጽሁፍ እና ግጥም ተደምጠዋል። በመቀጠልም ከአዲስ አበባ የወቅቱ አንድነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት አቶ ሐብታሙ አያሌው በቀጥታ በስልክ ለተሳታፊዎቹ አንዱአለምን በተመለከተ እና የወቅቱን የአንድነት ፓርቲ እንቅሰቃሴ ላይ ሰፋ ያለ ገለጻ አድርገው፤ ከተሳታፊዎች ጋር አጠር ያለ የጥያቄና መልስ ዝግጅት አድርገዋል።
በተጨማሪም የአንዱአለም አራጌ “ያልተኬደበት መንገድ” በሚል ርዕስ በእስር ቤት የጻፈው እና በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው መጽሀፍ በቦስተን አካባቢ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በይፋ ተመረቆ በገበያ ላይ የዋለ ሲሆን፤ በዝግጅቱ የተካፈሉ ታዳሚዎች በሙሉ የፈርሙበት መጽሀፍ ለጨረታ ቀርቦ በክፍተኛ ዋጋ የተሸጠ ሲሆን የጨርታው አሸናፊ መጽሀፉ የተሳታፊዎችን ፊርማ የያዘ በመሆኑ፤ የትግል አጋርነታችንን ለመግለጽ በቦስተን ሕዝብ ስም ለአቶ አንዱአለም አራጌ በስጦታ እንዲላክ ለአስተባብሪው ኮሚቴ አበርከትዋል።
በመጨረሻም የቦስተን ነዋሪዎች በኢትዮጵያ ውስጥ እየተደረገ ያለውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ ለማስወገድ እና የሰው ልጅ መብት እንዲከበር እንዲሁም ሁሉም ኢትዮጵያውያን በመከባበር የሚኖሩባት ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው የሰላማዊ ትግል የአንድ ፓርቲ ወይም ግለሰብ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚመለከት መሆኑን በመግለጽ እና እኛም “ከሚሊዮኖች አንዱ ነን” በማለት ዛሬ የተሰበስብነው የሕሊና እስረኛ አንዱአለም አራጌን በማወደስ በመሆኑ፤ ቦስተን የአንዱአለም አራጌ ትወልድ አካባቢ በሆነው የደብረታቦር ከተማ ሊካሄድ የታቀደውን “የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት” ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ስፖንሰር ለማድረግ በሙሉ ድምጽ ውሳኔያቸውን አስተላፈዋል!!