ጠይም ፊትሽ መጥቆሩን፣
ትንፋሽሽ፣ ጥሎሽ መሸሹን፣
የፊትሽ ወዝ ማጠፈፉን
አካል ቁመናሽ መርገፉን
ሰማሁ እናቴ ሰማሁ፣
አይቻል የለ ችያለሁ።
በዝምታ ተውበሽ
በሰው ሸክም ተሞሽረሽ
በኡኡታ …
በዋይታ…
መሸኘትሽን ሰማሁት
አይቻል የለ ቻል አ’ረኩት
የሆንሽውን ሳልጠይቅሽ ሳትነግሪኝ
ጎንሽ ሆኜ ሳላዋይሽ ሳታዋይኝ
ሞተሽ ቀብርሽ ሳልቆምልሽ ከቀረሁኝ
እናቴ ሆይ! ፍረጂልኝ ፍረጂብኝ
ምን ላድረገው? ምን ታረጊኝ?
ስደት ዶጋ አመድ ያድርግህ!
እንደ እናቴ ትንፋሽ ይንሳህ!
ምንስ ብትነፍግ ብታሳጣ
ካገር ወጪ ብታውጣ
የናቴን! የናቴን እንኳን
የመጨረሽ ሽኝቷን
እንዴት! ከዓይኔ ታርቅ
እንዴት! ከእግሬ ትነጥቅ
አዎን! ግድየለም!
ሞት መቼም ለኛ አዲስ አይደለም
ግን! እናትን ያህል ነገር
እንዴት ታሳጣኝ ቀብር?
ምነው እናቴ አንችስ!
ናፍቆትሽን እስክወጣ
ከሄድኩበት እስክመጣ
ዓይንሽ ከዓይኔ እስኪተያይ
ሞትሽን እንደ ተዋናይ
ገትረሽው በራፍሽ ላይ
ምነው? ነበር በጠበቅሽኝ
እስከማይሽ በቆየሽኝ
አንቺስ! ምነው ሀገሬ
ውለታትሽን ደፍሬ
እርግፍ አድርጌሽ ስወጣ
እናቴን ጭምር እንደማጣ
እያወቅሽው እያየሽኝ
በዝምታ ሸኝተሽኝ
ለትዝብትሽ ምነው ጣልሽኝ
የሀገሬ ጥቁር ምድር
ፍረጅልኝ! ይሄን ነገር
ልብ በይው፣ እስቲ ፀሀይ
ከናቴ ጋር ሳንተያይ
ተገናኝተን ሳንወያይ
ሞት ሊነጥል ይችላል ወይ?
አንተ! ጨካኝ ሞት ራስህ
አፈር ግባ! ድብን ያርግህ!
አንድ እናቴን ሰርቀህ ስትሄድ
ያንጠልጥልህ ሞት ከመንገድ
ብቻ ሞትስ ምን ያድርገኝ
ስንት ዘመን ይጠብቀኝ
ምንታደርጊ አንቺ ራስሽ
ልታገኚኝ በጸሎትሽ
ብዙ ለፋሽ ብዙ አነባሽ
መጨረሻ ደክሞሽ አረፍሽ
ይልቅስ እናት ዓለም
ባይጠቅምሽም
ባይጠቅመኝም
ያየሁትን ልንገርሽ ህልም
በሀገራችን፣ በግቢያችን ገብቶ ነፋስ
ህዝብ ሀገሩን ሲያተራምስ
ጉልበት አጥተሽ
አቅም አንሶሽ…
ንፋስ መሀል ስዳክሪ
ድምጽ አውጥተሽ ስትጣሪ
እየሰማሁ እያየሁኝ
ዝም ብዬሽ ትቸሽ ሄድኩኝ
ይሄን አየሁ ይሄውልሽ
ቀደም ብዬ ከመሞትሽ
ህልም…እልም…
ብዬ ብልም
ያንቺ ነገር ህልም አልሆነም
ይሄው! ጠይም ፊትሽ መጥቆሩን
ትንፋሽሽ ጥሎሽ መሸሹን
የፊትሽ ወዝ ማጠፈፉን
አካል ቁመናሽ መርገፉን
ሰማሁ እናቴ ሰማሁ
አይቻል የለ ችያለሁ።
ለናቴና በስደት ዓለም ሆነው እናት አባት ወይም የሚወዱት ዘመድ
በሞት ለተለያቸው ቤተሰቦች ጭምር መታሰቢያ ይሁን