Quantcast
Channel: Abugida Ethiopian American Amharic Web Page
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1809

መነበብ ያለበት መጽሓፍ “ፍፁም ነው እምነቴ” ግርማይ ተስፋጊዮርጊስ

$
0
0

ይህ በአቶ ነሲቡ ስብሃት የተፃፈ መጽሓፍ በደርግ ዘመን በኢትዮጵያ በነበረው አረመኔያዊ ሥርዓትና ሥርዓቱን ሲታገል በነበረው ኢሕአፓ የተመራው ቆራጥ ትውልድ መካከል የተካሄደው መራራ ትንቅንቅን በዝርዝር መረጃዎች አስደግፎ ያቀርባል።

ስለሆነም፤ በዛን ጊዜ የነበረውን የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ማለት፣ በአንድ በኩል ላገርቷ አንድነት፣ ለህዝቧ ነፃነት፣ ፍትሕና እኩልነት ለመታገል ቆርጦ የተነሣ ትውልድ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የህዝቡን ትግል አጨናግፎ የራሱ ፍላጎት በህዝቡ ላይ በሓይል ለመጫን የተነሣ የጦር መሣርያ የያዘ ወታደራዊ ኃይልና እሱን በመደገፍ ለመጠቀም በሞከሩ ቡድኖች መካከል የነበረውን ፍልሚያ ቊልጭ አድርጎ ያሳያል። ይህ መጽሐፍ አያይዞም ጊዜው ምን ያህል ጭካኔ የተፈፀመበት ወቅት እንደነበረ በዝርዝር ይገልፃል።

ደራሲዉ ያ ወቅት ባንድ በኩል ለሀገሩና ለህዝቡ ፍቅር ሕይወቱን ለመሰዋት ቆርጦ የተነሣው ትውልድ የነበረበት ጊዜ መሆኑን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሰውን በማሰቃየትና ደምን በማፍሰስ የሚደሰቱ በእውነት ኢትዮጵያ ያፈራቻቸው ናቸው ወይ የሚያሰኝ ወንጀለኛ ወገኖች የኖሩበት ጊዜ እንደነበረ ያሳያል።

የደራሲው ድንቅ ኣገላለጽና ስእላዊ አቀራረብ ሲታይ የደርግ ዘመን የኢትዮጵያን ታሪክ በተንቀሳቃሽ ፊልም ተቀርጾ የሚታይ ይመስላል።

የአቶ ነሲቡ መጽሐፍ የሚያተኵረው ጸሐፊው ራሱ በሚያውቀውና በኖረበት አከባቢ (ከፍተኛ 15) በተፈፀመው ታሪክ ላይ ነው። ያቀረበው ፈሬ ነገር ግን በዛን ጊዜ በመላው ኢትዮጵያ የነበረ ሁኔታን የሚያንፀባርቅ እውነታ ነው ቢባል ስሕተት አይሆንም። ያም ሆነ ይህ ሌሎችም እንደ አቶ ነሲቡ በየነበሩባቸው ቀበሌዎችና ሌሎች አከባቢዎች (ክፍለ-ሃገሮች፣ ወረዳዎች ወዘተ.) የነበሩ ቀጥተኛና ትክክለኛ መረጃ ያላቸው ሰዎች የሚያውቁዋቸው ፍጻሜዎችን ቢጽፉ የዛ ዘመን ታሪክ ተጠቃልሎ ሲነበብ ፤ቀጣዩ ትውልድን የተሟላ ግንዛቤ ሊያስጨብጥ ይችላል።

አንዳንድ ብሔርተኛ ድርጅቶች በፈፀሙት ስሕተት ወይም ጥፋት ምክንያት በጊዜአችን የኢትዮጵያን አንድነት በሚመለከት የተከሰቱትን አደጋዎች ከሁሉም ብሔረሰቦች በተውጣጡ አገር ወዳዶች ተቋቊሞ ላገርቷ አንድነት፣ ለህዝቧ እኩልነት፣ መብትና ፍትሕ የታገለው ኢሕአፓን ተጠያቂ ለማድረግ የሚሞክሩ ወገኖች መሠረተ-ቢስነትም ያስረዳል።

ደራሲዉ “ፍፁም ነው እምነቴ” የሚል የ“ያትውልድ” መፈክር ይዞ የታገለው በእውነትም ፅኑ እምነቱ ስለነበረ መሆኑን አሁንም ትግሉን በቆራጥነት እየቀጠለ በመሆኑ እያስመሰከረ ይገኛል፣ የሚያውቀውን ደግሞ በዝርዝር ጽፎ አቅርቦልናል። ስለዚህ አቶ ነሲቡ ለዚህ ድንቅ ታሪክና አቀራረብ መመስገንም አለበት እላለሁ። ሆኖም በዛን ጊዜ የተካሄዱ ስንትና ስንት ያልተካተቱ እውነታዎች መኖራቸው ግልፅ ስለሆነ ሌሎችም በዛን ጊዜ የተፈፀሙ ሁኔታዎችን በሚመለከት የሚያወቁትን እንድጽፉ ማበረታታት ያስፈልጋል።

በዚሁ መጽሓፍ የተገለጹ ተጨባጭ እውነታዎች በ60ዎቹ በጨረሻና በ70ዎቹ መጀመርያ ዓመታት በኢትዮጵያ የተፈፀሙ አዎንታዊና አሉታዊ ተግባሮች፣ የወቀቱ የኢትዮጵያ ታሪክ ስለሆኑ ላሁኑንም ሆነ ለመጪው ትውልድ እጅግ ጠቃሚ ናቸውና ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲያነበው አደራ እላለሁ። መነበብ ያለበት ደግሞ የተፈፀሙ ጥፋቶችን ለመበቀል ሳይሆን እያንዳንዱ አንባቢ ስህተቶችና ጥፋቶች እንዳይደገሙ አስተዋጽኦ ለማድረግና ኢትዮጵያ የሁሉም ዜጋ መብት የሚከበርባት አገር እንዲትሆን የተቻላቸውን ለማበርከት መሆን አለበት።

ግርማይ ተስፋጊዮርጊስ (4/02/2007)


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1809

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>